Saturday, 2 April 2016

ጾም

 ጾም ፡--በቁሙ ሲተረጐም መተው፥ መከልከል ማለት ነው።ይኸውም ከጥሉላት ማለትም ቅባትነት ካላቸው ሥጋ ነክ ምግቦች መከልከልን ያመለክታል።ቅዱስ ዳዊት፡-“ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ፤ሥጋዬም ቅባት በማጣት ከሳ።” በማለት የተናገረው የሚያመለክተው ይኸንኑ ነው።መዝ፡፻፰፥፳፬።፤ ነቢዩ ዳንኤልም፡--“በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ።ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፥ሥጋና የወይን ጠጅም በአፌ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት /ቅባት/ አልተቀባሁም።”ብሏል።ዳን፡፲፥፪-፫። ነቢዩ ዳንኤልና ሠለስቱ ደቂቅ (አናንያ፣ አዛርያ፣ ሚሳኤል) ፥ በባቢሎን ምርኰ በነበሩበት ዘመን ይህንን ሥርዓተ ጾም በመጠበቅ ጸጋ እግዚአብሔርን አግኝተውበታል፥ከመከራም ተሰውረውበታል።“ዳንኤልም ከንጉሡ ማዕድ እንዳይበላ ፥ ከሚጠጣውም ጠጅ እንዳይጠጣ በልቡ ጨከነ፤እንዳያበላውም የጃንደረቦ ችን አለቃ ለመነው።እግዚአብሔርም በጃንደረቦቹ አለቃ ፊት ለዳንኤል ሞገስንና ምሕረትን ሰጠው። የጃንደረቦ ቹም አለቃ  ዳንኤልን ፡-መብሉንና መጠጡን ያዘዘላችሁን ጌታዬን እፈራለሁ፤በዕድሜ እንደ እናንተ ከአሉ ብላቴኖች ይልቅ ፊታችሁ ከስቶ ያየ እንደ ሆነ ከንጉሡ ዘንድ በራሴ ታስፈርዱ ብኛላችሁ አለው።ዳንኤልም……እኛን አገልጋዮችህን ዐሥር ቀን ያህል ፈትነን፤ የምንበላውንም ጥራጥሬ፥ የምንጠጣውንም ውኃ ይስጡን፤ከዚያም በኋላ የእኛን ሰውነትና ከንጉሡ ማዕድ የሚበሉትን የብላቴኖችን ሰውነት ተመልከት፤እንደ አየኸውም ሁሉ ከአገልጋዮችህ ጋር የወደድኸውን አድርግ አለው።”ይላል። ከዐሥር ቀን በኋላ ሥጋና ጠጅ ከተመገቡት ይልቅ አምረው ወፍረው የተገኙት ጾመኞቹ ብላቴኖች ናቸው።እግዚአብሔርም በትምህርትና በጥበብ ሁሉ ዕውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፤ዳንኤልም በራእይና ሕልምን በመተርጐም ሁሉ አስተዋይ ነበረ። ከሦስት ዓመታት ጾምና ጸሎት በኋላም በንጉሡ ፊት በቀረቡ ጊዜ  ከሁሉም በልጠው ተገኝተዋል።ዳን፡፩፥፩-፳፬1።ስለዚህ እነርሱን አብነት አድርገን፥ እነርሱ ያገኙትን ጸጋና በረከት ለማግኘት፥ እንደ እነርሱ ያለ ጾም ለመጾም፥የጨከነ ቁርጥ ኅሊና ያስፈልገናል።


        የጾም ነገር ሲነገር ሁልጊዜ እንደ አዲስ የሚጠየቀው፡-“ዓሣ ይበላል፥ ወይስ አይበላም?”የሚለው ነው።ጥያቄውን በጥያቄ ለመመለስም፡-“ዓሣ፡-ጐመን፣ ድንችና ሽንኩርት ነው? ወይስ ሥጋ?”ብለን እንጠይቃለን።ከዚህ በኋላ የምንመለከ ተው “ፍትሐ ነገሥት”የሚባለውን የሥርዓት መጽሐፍ ነው።በአንቀጽ አሥራ ስምንት በትርጓሜው ላይ፡-“ደም የሚወጣበት የእንስሳ ሥጋ አይበላባቸውም፤ከእንስሳት የሚገኝ ወተት፣ ቅቤ፣ አይብ፣እንቁላልም አይበላባቸውም፤ከእንስሳት ወገን ያይደለ እንበለ (ያለ) ዘር የሚባዛ ዓሣም አይበላባቸውም።”ይላል።ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በቃልም በመጽሐፍም እንዳስተማሩት “ኢትብልዑ ሥጋ ዘእንበለ ዓሣ፧”የሚለው ንባብ የሚተረጐመው “ዓሣ እንኳ ሳይቀር ሥጋን ሁሉ አትብሉ፤”ተብሎ እንጂ “ከዓሣ በስተቀር ሥጋን ሁሉ አትብሉ፤” ተብሎ አይደለም።                                                    
  ሊቀ መዘምራን ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ የተባሉ የቤተክርስቲያን ሊቅ፥የዛሬ ፴፱ ዓመት፥በ፲፱፻፷፱ ዓ.ም. አሥመራ ከተማ ባሳተሙት፥“መርሐ ጽድቅ ባህለ ሃይማኖት፤” በተባለ መጽሐፋቸው ላይ፥ተጠራጣሪዎች የሚያነሡትን ጥያቄዎች ለቅመው በማውጣት ለሁሉም መልስ ሰጥተዋል።በዚህ ዘመን ተሻጋሪ በሆነ መጽሐፋቸው ነገረ ዓሣንም በገጽ፳፱ ላይ እንደሚከተለው መልስ ሰጥተውበታል።“የቤተክርስቲያን ሊቃውንት የዓሣ ሥጋ በጾም ይበላል፥ ወይስ አይበላም?በማለት እርስ በርሳቸው ይከራከራሉ። ምክንያታቸውም ፡-ዓሣዎች የሚራቡትና የሚባዙት በደመና ነው እንጂ በሩካቤ ዘር አይደለም፤ስለሆነም የዓሣ ሥጋ እንደ ንብ ማርና እንደ እንጨት ፍሬ ስለሚታይ በጾም ጊዜ ቢበላ ምንም አይደለም፥በሚል ነው።ሌሎቹ ደግሞ፡-ዓሣ እንደማንኛውም እንስሳ ደም የሚወጣው ሥጋ ስለሆነ በጾም ሊበላ አይገባም፥ ይላሉ። የዘመኑ ሊቃውንተ ዓለምም (ሳይንቲስቶች) ዓሣዎች በሩካቤ ዘር እንደሚራቡና እንደሚባዙ በምርምር ስለደረሱበት፥ዓሣ ቀጥ ያለ ሥጋ እንጂ የምን ማር ነው? ባዮች ናቸው። የኢትዮጵያ ሊቃውንት፡- የዓሣ ሥጋ ይበላል፥ አይበላም፤ እያሉ ሲከራከሩ የሚለዋ ወጡት መልስ፥ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት፡-በፍትሐ ነገሥት አንቀጸ ጾም፥ ክፍል ፲፰ ላይ “ኢትብልዑ ሥጋ በመ ዋዕለ አጽዋም ዘእንበለ ዓሣ፤” ባለው መሠረት ነው።ይህ ዘእንበለ የተባለው አገባብ ወይም መስተዋድድ በሁለት መልክ ስለሚተረጎም እንደየስሜታቸውና እንደየአተረጓጐማቸው ተለያይተዋል። ምክንያቱም፡- “ይበላል፤”የሚሉት ክፍሎች፡-“ዘእንበለን፥ያለ ዓሣ፣ከዓሣ በስተቀር፤” ብለው ሲተረጉሙት፥ አይበላም የሚሉት ወገኖች ግን፡-“ዓሣ ሳይቀር፤” ብለው ተርጉመውታል። እነዚህም፡-“ወአልቦ ዘአትረፈ ሊተ ንዋይየ ዘእንበለ ብእሲትየ፤ ሚስቴ ሳትቀር ዘረፉኝ፤……ኢትንሥኡ ወርቀ ወብሩረ ዘእንበለ በትር፤ በትር ሳይቀር ወርቅንና ብርን አትያዙ፤” የሚለውን ማስረጃ አድርገው ይጠቅሳሉ። ጦቢ፡፩፥፳፣ ማር፡፮፥፰። ሊቃውንቱ እንደዚህ ሲጠቃቀሱ፥ሠለስቱ ምዕት ደግሞ “ተገዓዝክሙ በጾም አድልዉ ለጾም፤በጾም ምክንያት ብትከራከሩ ለጾም አድሉ፤”ብለዋል።ስለሆነም መቼም ቢሆን በጾም ምክንያት ክርክር ቢነሣ፥ቅዱሳን አባቶቻችን አንዳስተማሩን ለጾም ማድላት ይገባል። ሠለስቱ ደቂቅና ዳንኤል በጾማቸው ጊዜ ከሥጋ ብቻ ሳይሆን ከደረቅ እንጀራ እንኳ ተከልክለዋልና። ከዚህም ሌላ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመነ ፕትርክና፥ የዓሣ ሥጋ ጾም መሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኖአል።  
                            ሀ፡-ጾም የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነው፤  
ጾም፡-ለሰው ልጅ የተሠራ የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ሕግ ነው። እግዚአብሔር፡- የእርሱ ፈጣሪነትና የአዳም ፍጡርነት፥ የእርሱ ገዢነትና የአዳም ተገዢነት ይታወቅ ዘንድ፥“ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤(ጹም)፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ትሞታለህና።(በሥጋህ ወደ መቃብር፥ በነፍስህ ደግሞ ወደ ሲኦል ትወርዳለህና።)” ብሎታል። ዘፍ፡፪፥፲፯። አዳምና ሔዋን እግዚአብሔር የሠራላቸውን ጾም በመሻራቸው፡- ከማዕረጋቸው ተዋርደው፥ ከሥልጣናቸው ተሽረው፥ የሞት ሞት ተፈርዶባቸው ከገነት ተባርረዋል። ዘፍ፡፫፥፳፪-፳፬። እግዚአብሔር ቃል በቃል ፥በነቢያትም እያደረ ትእዛዘ ጾምን የሰጠበት ጊዜ ብዙ ነው። ለምሳሌ፡-ንጉሡን ኢዮርብአምን እንዲገሥጽ ከይሁዳ ወደ ቤቴል የላከውን አረጋዊ ሰው፡-“በዚህም ስፍራ እንጀራም አትብላ፤ ውኃም አትጠጣ፤ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ።”ብሎታል። እርሱ ግን ጾምን ከጀመረ በኋላ በሐሰተኛ ነቢይ ተታልሎ ወደ መብላትና መጠጣት በመመለሱ እግዚአብሔር ገሥጾታል።በመጨረሻም የታዘዘ አንበሳ ሰብሮ ገድሎታል። ፩ኛ፡ነገ፡፲፫፥፩-፳፬። በነቢያት እያደረ ሲናገር ደግሞ፡-“ጾምን ቀድሱ፤ ምህላንም ዐውጁ፤ ሽማግሌዎች ንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤ ወደ እግዚአብሔርም በአንድነት ጩኹ።” ኢዩ፡፩፥፲፬። “አሁንስ፥ይላል፤ አምላካችሁ እግዚአ ብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ፥ ቁጣው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና፥ ወደ እርሱ ተመለሱ።” ኢዩ፡፪፥፲፪-፲፫።እግዚአብሔር ጾምን ያዘዘ ብቻ ሳይሆን በተዋህዶ ሰው በሆነበት ዘመን፥ (በመዋዕለ ሥጋዌው)፥ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾሟል።እከብር አይል ክቡር፥ እጸድቅ አይል ጻድቅ  ሲሆን በገዳመ ቆሮንቶስ የጾመው ለእኛ ምሳሌ ለመሆን ነው። ማቴ፬፥፪።                                  
                       ለ፡-ጾም የቅዱሳን ኑሮ (ሕይወት)ነው፤
     ቅዱሳን  ከእግዚአብሔር ጋር የኖሩት በጾም እና በጸሎት ተወስነው ነው። ልዩ ጸሎት ለማድረግ፥ልዩ ልመና ለማቅረብ ሲፈልጉ ጾም ይይዛሉ፥ ሱባዔ ይገባሉ። እግዚአብሔርም ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው የጾሙትን ጾም ተመልክቶ፥ የጸለዩትን ጸሎት ሰምቶ መልስ ይሰጣቸው ነበር። ነቢዩ ዳንኤል የሦስቱን ሳምንት ጾም በፈጸመ ጊዜ፥ በሚያስፈራ ግርማ የተገለጠለት የእግዚአብሔር መልአክ፥“ዳንኤል ሆይ፥ አትፍራ፤ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ካደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቶአል፥ እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ።”ያለው ለዚህ ነው። ዳን፡፲፥.፩-፲፪።የነቢያት አለቃ ሙሴም በደብረ ሲና፥ በእሳትና በደመና ውስጥ ሆኖ ከጠራው ከእግዚአብሔር ጋር እየ ተነጋገረ፥ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት በቆየበት ወቅት፥ ከእህል ከውኃ ምንም አልቀመሰም ነበር።“እግዚአ ብሔርም ሙሴን በእነዚህ ቃላቶች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ አለው።በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ እንጀራም አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። በጽላቶቹም ላይ አሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ።”ይላል። ዘጸ፡፴፬፥፳፰። ከዚህም፡- የጾም ወቅት፥ ሙሉ በሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር የምንሆንበት ጊዜ እንደሆነ እናስተውላለን። ነቢዩ ኤልያስ ደግሞ የእግዚአብሔር መልአክ ከመገበው በኋላ፥ ምንም ሳይበላና ሳይጠጣ፥ እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ፥ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ያለድካም ተጉዟል። ምክንያቱም ጾም በሰው ላይ ኃይል መንፈሳዊን ይሳድራልና ነው።1ኛ፡ነገ፡፲፱፥፩-፰። በአዲስ ኪዳንም ቅዱሳን ሐዋርያት እርሱን አብነት አድርገው እንደሚጾሙ ጌታ በተናገረላቸው መሠረት በጾም በጸሎት ተወስነው አገልግለውታል። “ሚዜዎች (ሐዋርያት)፥ ሙሽራው(ኢየሱስ ክርስቶስ) ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ (የማዳን ሥራውን ፈጽሞ የሚያርግበት ጊዜ አለ)፥ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ።” ይላል። ማቴ፡፱፥፲፬-፲፮። ቅዱሳን ሐዋርያት ጾመ ኢየሱስን አብነት፥ ትምህርቱን ደግሞ መመሪያ በማድረግ ጾምን የሥራ መጀመሪያ፥ ከመንፈስ ቅዱስም ጸጋን መቀበያ አድርገው ታል።“ እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ፥ መንፈስ ቅዱስ፡- በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ። በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ (ከሾሟቸው)በኋላ አሰናበቱአቸው።” ይላል።የሐዋ፲፫፥፩-፫።ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም እጅግ አብዝቶ ይጾም እንደነበረ በቆሮንቶስ መልእክቱ ላይ መናገሩ የሚያመለክተው ይኸንኑ ነው። ፪ኛ፡ቆሮ፡፲፩፥፳፯።ክርስቲያኖች ሃይማኖት ይዘን፥ ምግባር ሠርተን ከተገኘን በሰማይ የምንኖረው እንደ መላእክት ነው።“በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ፧”ይላልና። ማቴ፡፳፪፥፴። ስለዚህ ላይ የሚጠብቀንን ኑሮ እያሰብን፥ ገና በምድር እያለን እንደ መላእክት መኖርን እንጀምራለን። በመሆኑም ጾም፥ ጸሎት፥ስግደት፥መዝሙር፥ ቅዳሴና ማኅሌት፥ ቅዱሳን መላእክትን የምንመስልበት ጸጋ መሆኑን በማስተዋል በእነዚህ ጸንተን እንኖራለን።ቅዱስ ጳውሎስ ፡-“ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም፥ በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና።” ያለው ለዚህ ነው። ዕብ፡፲፫፥፱። በተጨማሪም፡- “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና። እንደዚህ አድርጎ ለክርስቶስ የሚገዛ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛልና፥ በሰውም ዘንድ የተመሰገነ ነው።”የሚል አለ። ሮሜ፡፲፬፥፲፯-፲፰።  
ሐ፡-ጾም ሰይጣንን የምናሸንፍበት መሣሪያ ነው፤  
ጌታችን በገዳመ ቆሮንቶስ በጾመ ጊዜ፥ በፈቃዱ በሰይጣን ተፈትኖአል። በስስት፥ በፍቅረ ንዋይና በትዕቢት የፈተነውን ሰይጣን፡- በትእግሥት፥ በጸሊአ ንዋይና በትኅትና ድል አድርጐታል።እነዚህ ሥጋ ለባሽ ሁሉ የሚፈተንባቸው ሦስቱ ዋና ዋና ኃጢአቶች ናቸው። ማቴ፡፬፥፩-፲፩። በመሆኑም በእነዚህ የሚፈትነንን ጥንተ ጠላታችንን ሰይጣንን ድል የምናደርገው በጾም መሆኑን እርሱ መንገዱን አሳይቶናል። በመዋዕለ ሥጋዌው ደቀመዛሙርቱ፡- በሽተኛውን ለምን መፈወስ እንዳቃታቸው በጠየቁት ጊዜ፡- “ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህንን ተራራ፡- ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም። ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጾም በቀር አይወጣም።” ብሏቸዋል። ማቴ፡፲፯፥፲፬-፳፩። ከዚህም ጋር ሰይጣን አዳምንና ሔዋንን የጣላቸው፥ ከርስታቸው ከገነት የነቀላቸው ፥ ከእግዚአብሔር የለያቸው፥ በመብል ምክንያት እንደሆነ መርሳት አይገባም።
                                መ፡-ጾም ከታዘዘ መቅሠፍት ያድናል፤  
      ከመቶ ሃያ ሺህ በላይ የሆኑ የነነዌ ሰዎች፥ እግዚአብሔር ተቆጥቶባቸው፥ መቅሠፍት ታዝዞባቸው ነበር። እንደ ሰዶምና ገሞራም እሳትና ዲን ሊዘንብባቸው፥ እሳቱ እንደ ክረምት ደመና ተንጠልጥሎ ነበር። ነገር ግን የነቢዩን የዮናስን የንስሐ ስብከት ሰምተው፥  ከንጉሡ ጀምሮ ሁሉም ሕዝብ አመድ ላይ ተኝተው፥ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በመጾማቸው ከመቅ ሠፍት ድነዋል። ይህንን ጾም የቤት እንስሳትም በረት ተዘግቶባቸው ጾመውታል። ጡት የሚጠቡ ሕጻናትም ጾመውታል። ዮና፡ምዕ፡፩-ምዕ፡፬። በቤተክርስቲያናችንም ሕጻናት ከሰባት ዓመታቸው ጀምሮ እንዲጾሙ ሥርዓት ተሠርቶአል። በመሆኑም ከዚህ ተምረን “እንዴት አድርገው ጾሙን ይችሉታል?” የሚለውን ጥርጥር ልናስወግድ ይገባል። ምክንያቱም እንኳን የሰባት ዓመት ሕጻናት፥ የአርባና የሰማንያ ቀን ሕጻናት እንኳ ለሦስት መዓልትና ለሦስት ሌሊት ጡት ተከልክለው ጹመውታልና። በምክንያት የማይጾሙ ወላጆች ደግሞ ከነነዌ እንስሳት እና ሕጻናት አንሰው አንዳይገኙ፥ ክርስትናው ካለ፥ ወደ ጾምና ጸሎት መመለስ ይኖርባቸዋል።  
         አርጤክስስ የተባለው ንጉሥ፥ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሃያ ሀገሮች ላይ በነገሠበት ዘመን፡- በሐማ ተንኰል፥ በአይሁድ ላይ፥ በተገኙበት ሥፍራ እንዲገደሉ የሞት ዓዋጅ ታውጆባቸው ነበር። ነገር ግን ይኸንን የሰሙ አይሁድ፥ ከላይ እስከ ታች ሁሉም፥ ማቅ ለብሰው፥ አመድ ላይ ተኝተው በመጾማቸው ከመከራው ተሰውረዋል። “የንጉሡም ትእዛዝና አዋጅ በደረሰበት አገር ሁሉ በአይሁድ ላይ ታላቅ ኀዘንና ጾም ልቅሶና ዋይታም ሆነ፥ ብዙዎች ማቅና አመድ አነጠፉ።” ይላል። አስ፡፬፥፫።በዚያን ዘመን አይሁዳዊቷ አስቴር በቁንጅናዋ ለንጉሥ ሚስትነት ተመርጣ በቤተመንግሥት  ትኖር ነበር።አጐቷ መርዶክዮስም፡-“አንቺ በንጉሥ ቤት ስለሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ይልቅ እድናለሁ ብለሽ በልብሽ አታስቢ። በዚህ ጊዜ ቸል ብትዪ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፥ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?”ብሎ ላከባት። እርሷም፡- “ሄደህ በሱሳ ያሉትን አይሁድ ሰብስብ፥ ለእኔም ጹሙ፥ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት አትብሉም፥አትጠጡም፥ እኔና ደንገጡሮቼ ደግሞ እንዲሁ እንጾማለን፤ ምንም ያለ ሕግ ቢሆን ወደ ንጉሡ እገባለሁ፥ ብጠፋም እጠፋለሁ።” ብላ መልሳ ላከችበት። መርዶክዮስም አደረገው። የቀድሞው የሞት ዓዋጅም ወደ ሕይወት ተለወጠ። ዛሬም የታዘዝናቸውን አጽዋማት ሁሉ በእምነት የምንጾም ከሆነ እንኳን ከታሰበው ከተሰነዘረውም እንድናለን። በሥልጣን ወንበር ላይ የተቀመጡ ሹማምንትም በሀገር በወገን ላይ መዓት ሲወርድ እያዩ ዝም እንዳይሉ፥ መርዶክዮስ ለአስቴር ከላከው መልእክት እና ከአስቴር ተግባር መማር አለባቸው። ዛሬ ተመችቷቸው ነገ በእግዚአብሔር ቁጣ ከሚጠፉ፥ ቢጠፉም፣ ቢድኑም ከወገናቸው ጋር ይሻላቸዋል። ደግሞም አይጠፉም፤ ምክንያቱም ለአስቴር ሞገስን የሰጠ አምላክ ለእነርሱም ይሰጣቸዋል፥ አስቴርንም አይሁድንም ያዳነ አምላክ ያድናቸዋል።  
ሠ፡-ጾም ከራስ አልፎ ለልጆችም ለሀገርም ይጠቅማል፤  
         በመጽሐፈ እዝራ እንደተጻፈው፡-ነቢዩ ዳንኤል በጾም ራሱን በእግዚአብሔር ፊት  እንዳዋረደ፥ የእስራኤልም ልጆች በጾም ራሳቸውን በአምላካቸው ፊት በማዋረዳቸው፥ ለልጆቻቸውና ለሀገራቸው የለመኑት ልመና ሁሉ ደርሶላቸዋል።“ስለዚህም ነገር ጾምን፥ወደ እግዚአብሔርም ለመንን፥እርሱም ተለመነን።”ይላል። ዕዝ፡፰፥፳፩-፳፫። ነህምያም በምርኰ እያለ የኢየሩሳሌምን ጥፋት በሰማ ጊዜ ማቅ ለብሶ፥ አመድ ላይ ተኝቶ፥ ጾመ፣ ጸለየ።“ይህንም ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ፥ አያሌ ቀንም አዝን ነበር፤ በሰማይም አምላክ ፊት እጾምና እጸልይ ነበር።” ይላል። ነህ፡፩፥፬። ከዚህ በኋላ ጠላት ያፈረሳትን ሀገሩን ለመሥራት ቆርጦ ተነሣ። ብዙዎች ተስፋ ሊያስቆርጡት ሞክረው ነበር። እርሱ ግን፡- “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፤ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፥ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም እድል ፈንታና መብት መታሰቢያም የላችሁም አላቸው።”ነህ፡፪፥፳። ዙሪያቸውን ያሉ ጠላቶቻቸውም ቀን ከሌሊት እየተዋጉ ብዙ ተፈታትነዋቸው ነበር። እነ ነህምያ ግን በአንድ በኩል እየተዋጉ በሌላ በኩል ሀገራቸውን እንደገና ሠሯት። ነህ፡፯፥፩። በሰባተኛው ወር በሃያ አራተኛውም ቀን የእስራኤል ልጆች ጾመው፥ ማቅም ለብሰው፥ በላያቸውም ትቢያ ነስንሰው ተከማቹ። ኃጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን ኃጢአት ተናዘዙ። ለእግዚአብሔርም ሰገዱ። ነህ፡፱፥፩-፬። በመሆኑም እነርሱን አብነት አድርገን የምንጾማቸው አጽዋማት ሁሉ ለኑሯችን፥ ለትዳራችን፥ ለልጆቻችንና ለሀገራችን፡- ሰላምን፣ፍቅርንና አንድነትን፥ በረከትንና ረድኤትን ያሰጡናል።                                                          
       ረ፡-ጾምን በመጾማችን የሚጐድልብን፥ባለመጾማችን ደግሞ የምናተርፈው የለም፤  
               አብዝቶ ከመጾም ጋር መልካሙን ገድል የተጋደለ፥ መንፈሳዊ ሩጫውን የጨረሰ፥ ሃይማኖቱን የጠበቀ፥የጽድቅ አክሊ ልም የተሰጠው ሐዋርያ፥ ቅዱስ ጳውሎስ፡-“መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጐድልብንም፥ ብንበላም ምንም አይተርፈንም።”ብሏል።፩ኛ፡ቆሮ፡፰-፰።“ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ሁሉ ግን አይጠቅምም።ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም። መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፥ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል።” በማለት የተናገረበት ጊዜም አለ። ፩ኛ፡ቆሮ፡፮፥፲፪። ሐዋርያው፡- “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤” ያለበት ምክንያት አለው። ይኸውም የሰው ልጅ ከነጻ ፈቃድ ጋር፥ ማለትም ከሙሉ ነጻነት ጋር መፈጠሩን ለማመልከት ነው። የሰው ልጅ ጽድቅን ልሥራ ቢል፥ ኃጢአትንም ልሥራ ቢል ሙሉ ነጻነት አለው። እግዚአብሔር የጽድቅን ዋጋ፥ የኃጢአትን ፍዳ ከመንገር ባለፈ አስገድዶ የሚገዛ አምላክ አይደለምና። አዳምን፡- “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታው ቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ትሞታለህና።” አለው እንጂ አላስገደደውም። ዘፍ፡፪፥፲፮-፲፯።  
ሰ፡-“ወደ አፍ የሚገባ አያረክስም፤”  
ጻፎችና ፈሪሳውያን ወደ ኢየሱስ ቀርበው፡-“ደቀመዛሙርትህ ስለምን የሽማግሎችን ወግ ይተላለፋሉ? እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን አይታጠቡምና።” ባሉት ጊዜ ፥“እናንተስ ስለ ወጋችሁ  የእግዚአብሔርን ትእዛዝ  ስለ ምን ትተላለፋላችሁ?” ብሏቸዋል። ምክንያቱም አይሁድ ስለ ወጋቸው እንጂ ስለ እግዚአብሔር ትእዛዝ እምብዛም እይጨነቁም ነበርና ነው። ሕዝቡንም ጠርቶ፡- “ስሙ፥ አስተውሉም፤ ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፥ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው።” አላቸው። ይህ ትምህርት ከጾም ጋር የተገናኘ ወይም በጾም ምክንያት የተነገረ ሳይሆን ምሳሌያዊ ትምህርት ነው። በመሆኑም ቅዱስ ጴጥሮስ፡- “ምሳሌውን ተርጉምልን፤”ብሎታል። ጌታም “ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ አልፎ ወደ እዳሪ እንዲጣል አትመለከቱምን? ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውን የሚያረክሰው ያ ነው። ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው እንጂ ባልታጠበ እጅ መብላትስ ሰውን አያረክሰውም።” በማለት ተርጉሞላቸዋል። ማቴ፡፲፭፥፩-፳።ምሥጢራዊ መልእክቱም፡-“የሰው ልጅ ከልቡ አመንጭቶ ክፉ በመናገሩ ይረክሳል እንጂ፥ በሐሰት የተነገረበትን ክፉ ነገር በመስማቱ አይረክስም፤ ምግብ በአፍ ገብቶ በሌላ በኩል ቆሻሻ ሆኖ እንደሚወጣ ፥በአንድ ጆሮ የሰማችሁትን ክፉ ነገር እንደ ቆሻሻ በሌለኛው ጆሮ አውጥታችሁ ጣሉት፤”ማለት ነው። አይሁድ ጌታን ያረከሱ  መስሏቸው አያሌ ክፉ ነገር ይናገሩበት ነበር፥ በዚህም እነርሱ ይረክሳሉ እንጂ እርሱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ቅዱስ ነው። ዋናው ነገር፡- የጾማቸውን ዋጋ ለቅዱሳን ነቢያት የሰጠ፥ በተዋህዶ ሰው ሆኖ የጾመ፥ “በዚያን ጊዜ ይጾማሉ፤” ብሎ ስለ ጾመ ሐዋርያት የተናገረ፥ “በጾምና በጸሎት እንጂ ሰይጣን እንዲሁ አይለቅም፧”ያለ፥ወደ አፍ የሚገባ አያረክስም፤”የሚለውንም የተናገረ፥ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።የእግዚአብሔር ቸርነት፣የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፧አሜን።by kesis dejene sh.
>+"+ እንኩዋን ለጻድቁ አባታችን "ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት" ዓመታዊ በዓለ-ፅንሰት በሰላም አደረሳችሁ +"+
+*" ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ "*+
=>ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ዐይን ናቸው:: ጻድቁን መንካት የቤተ ክርስቲያንን ዐይኗን መጠንቆል ነው::
+ተክለ ሃይማኖት እንደ ሊቃውንት ሊቅ: እንደ ሐዋርያት ሰባኬ ወንጌል: እንደ ሰማዕታት ብዙ ግፍ የተቀበሉ: እንደ ጻድቃን ትሩፋት የበዛላቸው: እንደ ደናግል ንጽሕናን ያዘወተሩ: እንደ ባሕታውያን ግኁስ: እንደ መላዕክትም ባለ ክንፍ አባት ነበሩ:: ለዚሕ ነው ተክለ ሃይማኖትን የኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ዐይኔ የምትላቸው::
*ልደት*
=>መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ: ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው:: እርሱ በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::
+በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል: ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በሁዋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል::
+ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የጸነሱት መጋቢት 24 ቀን በ1206 ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታሕሳስ24 ቀን በ1207 ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::
*ዕድገት*
=>የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል:: ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት: ሐዲሳትን) ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁናም ከወቅቱ ዻዻስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል::
*" መጠራት "*
=>አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑ በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ::
+የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:: "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን:: ከዚህ በሁዋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በሁዋላ ሰዓትን አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::
*" አገልግሎት "*
=>ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዻዻሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ:: ያን ጊዜ ኢትዮዽያ 2 መልክ ነበራት::
+1ኛ ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::
+2ኛው ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር::
+ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን (ጠንቁዋዮችን) አጥፍተዋል::
*" ገዳማዊ ሕይወት "*
=>ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮዽያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል:: እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ3 ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል::
+እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለ12 ዓመታት: በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለ7 ዓመታት: በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለ7 ዓመታት: በአጠቃላይ ለ26 ዓመታት አገልግለዋል::
+በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በሁዋላም ወደ ምድረ ሽዋ (ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ22 ዓመታት ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም 6 ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል::
*ስድስት ክንፍ*
=>ኢትዮዽያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮዽያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::
+የወቅቱ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በሁዋላ ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር::
+ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:-
-በቤተ መቅደስ ብስራቱን
-በቤተ ልሔም ልደቱን
-በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
-በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
-በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::
+የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ::
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ ተክልየን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው::
+በዚያም:-
*የብርሃን ዐይን ተቀብለው
*6 ክንፍ አብቅለው
*የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
*ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
*ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
*ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
*"ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::
*ተአምራት*
=>የተክልየ ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው::
*ሙት አንስተዋል
*ድውያንን ፈውሰዋል
*አጋንንትን አሳደዋል
*እሳትን ጨብጠዋል
*በክንፍ በረዋል
*ደመናን ዙፋን አድርገዋል::
+ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕጻናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና::
*ዕረፍት*
=>ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው መከራን በብዙ ተቀብለው: እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው: በተወለዱ በ99 ዓመት: ከ8 ወር: ከ1 ቀናቸው ነሐሴ 24 ቀን በ1306 ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: 10 ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::
=>አምላከ ቅዱሳን ከጻድቁ አባታችን በረከትን ይክፈለን::
=>መጋቢት 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት (ጽንሰቱ)
2.ቅዱሳን እግዚእ ኃረያና ጸጋ ዘአብ
3.ቅዱስ አባ መቃርስ ሊቀ ዻዻሳት
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ አጋቢጦስ ጻድቅ
2.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
3.ቅዱስ ሙሴ ፀሊም
4.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
5.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
6."24ቱ" ካኅናተ ሰማይ
=>+"+ በረከት በጻድቅ ሰው ራስ ላይ ነው:: የኀጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል:: የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው:: የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል:: +"+ (ምሳሌ 10:6)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

ደብረ ዘይት

ደብረ ዘይት- አምስትኛው ሳምንት
ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ማለት ነው፡፡ቦታው ከኢየሩሳሌም በስተምስራቅ የሚገኝ የወይራ ዛፍ የበዛበት ተራራ ሲሆን ስሙም ከወይራ ዛፉ:-ደብረ ዘይት (የወይራ ዛፍ ተራራ) በመሰኘት ተገኝቷል። በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ደብረ ዘይት በዓል ሆኖ የሚከበርበት ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረዘይት ተራራ ላይ ሳለ ለቅዱሳን ደቀመዛሙርቱ ስለ ዓለም ፍጻሜ እና ስለ ዳግም ምጽአቱ ስላስተማራቸዉ በጌታችን ትምህርት መሰረት ነገረ ምጽአቱን (የመምጣቱን ነገር) እንድናስታዉስ ወይም እያሰብን እንድንዘጋጅ ለማድረግ ነዉ።
ጌታችን “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያዉቅ የለም” ማቴ. 24፡36 ብሏል። ይህን ማለቱም በየዘመኑ የሚነሱ ክርስቲያኖች ሩቅ ነዉ ብለዉ እንዳይዘናጉ ጊዜዉ ሲቀርብ የሚነሱት ደግሞ ደረሰብን ብለዉም እንዳይሸበሩ/እንዳይታወኩ ለመጠበቅ ነዉ። ከላይ እንደጠቀስነው ጌታችን በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸዉ ወደ እርሱ ቀርበዉ “የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድር ነዉ? አሉት።” ማቴ. 24፡3 እርሱም በስፋትና በጥልቀት ስለ ዓለም መጨረሻና ስለ ዳግም ምጽአቱ ምልክቶች አስተማራቸዉ። ከነዚህምዋና ዋና የሆኑትን ምልክቶች ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታቸዋለን።
1. የምጥ ጣር መጀመሪያዎች ይታያሉ
ምጥ ሲመጣ አስቀድሞ የምጡ መጀመሪያ ሕመም (ጣር) እንዳለ ሁሉ የዓለምም ፍጻሜ በጣር ነዉ የሚጀምረዉ። ይህንንም ጌታችን በግልጽ አስረድቶናል፦ ጦርና የጦር ወሬ መሰማት፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግስትም በመንግስት ላይ መነሳት፣ ርሃብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ መታየት ለዓለም ፍጻሜ የምጥ ጣር መጀመሪያዎች ናቸዉ። እነዚህ ነገሮች በሁሉም ቦታ በአንድ ጊዜ ላይከሰቱ ይችላሉ፤ ነገር ግን በልዩ ልዩ ቦታዎች ለብዙ ዘመናት ታይተዋል፤ እየታዩም ናቸዉ።
2. ስለ ስሜ በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ስሜ (የክርስቶስ ተከታዮች/ ክርስቲያኖች በመሆናችሁ) በዓለም ዘንድ ትጠላላችሁ ብሎናል። ዓለም ክፉ ስለሚሠራ የጥሩ ነገር ተቃራኒ ሆኖ ለብዙ ዘመናት ቆይቷል። ጌታችን “ብርሃንም ወደ ዓለም ስለመጣ ሰዎችም ሥራቸዉ ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ፍርዱ ይህ ነዉ። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፣ሥራዉም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እዉነትን የሚያደርግ ግን ሥራዉ በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።” ዮሐ. 3፡19-21 እንዳለንበክፉ ሥራ ዉስጥ ያለዉ ይህ ዓለም በጎ ሥራ የሚሠሩትን የክርስቶስን ተከታዮች ይጠላል። ጨለማ ብርሃንን ብርሃንም ጨለማን እንደሚጠላ፤ይህ ዓለም እኛን እንዲጠላን፣እኛ ክርስቲያኖች ደግሞ ይህንን ዓለም ልንጠላው ይገባል።
አሁን ባለንበት ዘመን ክርስትና እየተጠላ፣ እየተናቀ ነዉ ያለዉ። “ባደጉት” ዓለማት ባዶ አብያተ መቅደሶች ቀርተዉ እነሆ እንመለከታቸዋለን፤ ትዉልዱ በዓለም ስሜትና በሥጋ ፈቃድ ብቻ እየሄደ ነዉ።ክርስቲያን ነን በሚሉትም አውሮፓውያን ዘንድ የአንገት በላይ (የማስመሰል) ክርስትና እንጂ እንደ ቅዱስ ቃሉ የሚጓዝ አማኝ ማግኘት አይቻልም። እዉነተኞች አይወደዱም፤ ይገፋሉ፤ ይናቃሉ። ሁኔታዉ የዘመኑ ፍጻሜ እጅግ እየቀረበ መምጣቱን በእርግጥ ያስረዳል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህም በላይ፦ ስለ ስሜ ለመከራ አሳልፈዉ ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችሁማል ብሏል። ክርስቲያን በመሆናቸዉ ብቻ ማንንም ሳይበድሉ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ በልዩ ልዩ ሀገራት ክርስቲያኖች ሰማእትነትን እስከ አሁን ድረስ እየተቀበሉ ነው፡፡ቅዱስ ጳዉሎስ “ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ” ሮሜ 8፤36 እንዳለዉ። ይህ በቅዱሱ በክርስቶስ ስም መጠላትና መከራ መቀበል ከዓለም የሚጠበቅ የፍጻሜዉ ዘመን ምልክት መሆኑን አዉቀን መዘጋጀትና ከሐዋርያዉ ጋር “በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።” ሮሜ 8፤37 እያልን በእምነታችን ጸንተን መጋደል ይገባናል።
የክርስቲያኖች ቁጥር እያነሰ መምጣት፣ የአብያተ ክርስቲያናት መዘጋት፣ ሰዉ ሰዉ የሚያሰኘዉን ክብርና ሞገስ ትቶ በግብሩ እንስሳትን ሲመስል፦ የቅድስና ሕይወት ሲጠላና ሲናቅ፤ በአንጻሩ ደግሞ የሰዉ ልጅ ለረከሰዉ ለዚህ ዓለም ምኞትና ፈቃድ ሲገዛ ስናይ የዚህ ዓለም ፍጻሜ ጊዜዉ እየደረሰ መሆኑን አዉቀን፤ ኖኅ በብዙ ኃጢአተኞች መካከል ቢኖርም ራሱን በቅድስና ጠብቆ እንደኖረ (ዘፍ.6-8)፤ ሎጥም እንዲሁ በብዙ ኃጢአተኞች መካከል ሲኖር በነርሱ ኃጢአት እንዳልተባበረ (ዘፍ. 19) ከዚህ ዓለም ክፉ ሥራ ተለይተን ራሳችንን በቅድስና በመጠበቅ እንጋደል።ዓለሙ ስለ እምነታችን ቢጠላንም እኛም ስለ ክፉ ሥራዉ ንቀነው መኖር የግድ መሆኑን እንወቅ እንጂ ስለ እምነት፣ ስለ ቅድስናም ከዓለም በጎ ነገር አንጠብቅ። በተለያዩ ሁኔታዎች የሚደርሱብንን ፈተናዎች ሁሉ በትዕግስት እንቀበላቸዉ እንጂ በማማረር አንዘን፤ ምክንያቱም ስለ ስሜ በዓለም ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ ተብለናልና።
3. የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰዉ ስፍራ ይቆማል
ዓለም እራሱን በማርከስ ብቻ ሳይወሰን በፍጻሜ ዘመን በተቀደሰዉ ስፍራ እንኳን ሳይቀር የጥፋትን ርኩሰት ያቆማል። የተቀደሰዉ ስፍራ የተባለዉ በተቀደሰ ሃይማኖት የሚኖሩትን ሀገራት፣ ሕዝቦች የሚመለከት ነዉ። እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉትን ሀገራት ዲያብሎስ በመልእክተኞቹ ላይ አድሮ በብዙ ርኩሰት ተፈታትኗቸዋል፤ እየተፈታተናቸውም ነው። የየሀገራቱን እምነትና ታሪክ ለማጥፋት ጥሯል፤ ብዙዉንም የቅድስና ሥርዓት በርዞአል፤ የቻለዉንም ከነጭራሹ አጥፍቶታል። አሁን እንኳ አምልኮተ እግዚአብሔር በሚፈጸምባቸዉ ቅዱሳት መካናትና ገዳማት ሳይቀር በልዩ ልዩ ምክንያት የጥፋት ርኩሰት አዉጇል። ይህም የፍጻሜ ዘመኑ አንዱ ምልክት ስለሆነ አንባቢዉ ያስተዉል እንደተባለ የዘመኑን መፍጠን የጊዜዉን መድረስ በመረዳት መዘጋጀት ይገባናል።4. ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሳሉ
ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት በየዘመኑ ተነስተዉ እዉነተኛይቱን ቤተ ክርስቲያን ታግለዋታል፤ ሊያጠፏት ባይችሉም እንኳን ብዙ ልጆቿን ነጥቀዉ አጥፍተዋቸዋል። የነዚህን ሐሰተኞች ሠራተኞች አመጣጥ ከባድ የሚያደርገዉ በተኣምራትና በድንቅ ምልክቶች መምጣታቸዉ ነዉ። ጌታችን እንደተናገረ “ቢቻላቸዉስ የተመረጡትን እንኳን እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ።” ስለዚህ በምትሐታዊ ምልክቶቻቸዉ የብዙ የዋሐንን ልብ በማታለል ከተቀደሰ እምነታቸዉ እያስኮበለሉ አጥፍተዋቸዋል፤ በማጥፋትም ላይ ይገኛሉ። ስለዚህም ሐዋርያዉ ቅ/ዮሐንስ “ወዳጆች ሆይ፦ መንፈስን ሁሉ አትመኑ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነዉ እንደሆነ መርምሩ “ 1ዮሐ. 4፡ 1-3 አለን። ቅዱስ ጳዉሎስም “የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸዉን እየለወጡ ዉሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞ ሠራተኞች ናቸዉ። ይህም ድንቅ አይደለም ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለዉጣልና።” 2ቆሮ. 11፡13-15 ብሏል። ሐዋርያት ሁሉ በየመልእክቶቻቸዉ ከሐሰተኞች አስተማሪዎች እንድንጠበቅ ደጋግመዉ አሳስበዋል። ብዙ ሰዉ ግን በየዋሕነት ስለሚጓዝ የነዚህ ተኩላዎች ሰለባ ሆኗል።
ጊዜዉ ክፉ ነዉና የሐሰተኞች ነቢያት መረብ ጠልፎ ወደ ሐሰተኞች ክርስቶሶች እንዳይወስደን በጥንቃቄ መጓዝ ይጠበቅብናል። ሐዋርያዉ ቅዱስ ይሁዳም በመልእክቱ ቁ .3 “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።“ ሲል እንደመከረን በተቀደሰ እምነታችን እስከመጨረሻ ለመጽናት እንጋደል።
5. የሰዉ ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ይመጣል
ክቡር ዳዊት በትንቢት “እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ፤ ወአምላክነሂ ኢያረምም። እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል፤ አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም።” መዝ. 49፡3 እንዳለ ጌታችን በብዙ ክብርና በብዙ ኃይል ከሰማይ መላእክት ጋር ግልጥ ሆኖ ይመጣል። በዚያን ጊዜ ከመጀመሪያዉ ሰዉ ከአዳም ጀምሮ እስከ መጨረሻዉ ሰዉ ድረስ ሁላችንም በሕይወተ ሥጋ በነበርንበት ጊዜያችን የሠራነዉን ሥራ ይዘን በፊቱ እንቀርባለን (2ቆሮ. 5፡10)። ጌታችንም በጎ የሠሩትን ቅዱሳን በቀኙ፤ ክፉ የሠሩትን ኃጥአንን በግራዉ ያቆማቸዉና ፍርዱን ያስተላልፋል(ማቴ. 25፡31 እስከ ፍጻሜ)።
በዚህ ዓለም ፈቃድ የተጓዙ ኃጥአን ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጉስቁልና ይጣላሉ። በዚህ ዓለም ክፉ ሥራ መንፈሳቸዉን እያስጨነቁ በእምነትና በቅድስና የኖሩ ጻድቃን ደግሞ በደስታ እየዘመሩ ወደማታልፈዉ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ይገባሉ።
ከዚያ በኋላ ሐዘን የለም፤ ሀብታምና ድሃ የለም፤ኃይለኛና ደካማ የለም፤ በማያልቅ ደስታ ለዘላለም እንደ ቅዱሳን መላእክት ሕያው ሆኖ መኖር እንጂ።
ያን ጊዜ የእኛ እጣ በየት ይሆን?
በቀኙ ለመቆም እንዲያበቃን ዛሬ እንጋደል። የቅዱሳን ሐዋርያት መልእክት ፦
“ወደ እግዚአብሔር መንግስት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል…” ሐዋ. 14፡22 እንዲሁም፦
“ጻድቅ በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመጸኛዉና ኃጢአተኛዉ ወዴት ይታይ ዘንድ አለዉ?” 1ጴጥ.4፡18 የሚል ነዉ!
እንግዲህ እጅግ ባጭሩ የደብረ ዘይትን በዓል የምናከብረዉ እነዚህን እንድናስታዉስና “ድልዋኒክሙ ንበሩ:- ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” በተባልነው መሰረት ንስሐ ገብተን፤ ሥጋወ ደሙን ተቀብለን፤መልካም ፍሬ አፍርተን ሁልጊዜም የተዘጋጀን ሆነን እንድንጠብቅ ነው።
በቀኙ ለመቆም እንዲያበቃን የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን የርኅርኂተ ኅሊና የድንግል ማርያም አማላጅነት፣የቅዱሳን ሁሉ ረድኤት አይለየን፤ አሜን።
--------------------ምንጭ፦ተዋህዶ ሃይማኖታችን

ደብረ ዘይት አትም ኢሜይል
መጋቢት 24 ቀን 2008 ዓ.ም.
በአባ ዘሚካኤል ደሬሳ
የዓለሙ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድ ነው?/ማቴ. 24፣3/
በዓቢይ ጾም ውስጥ ካሉት ሳምንታት ደብረ ዘይት 5ኛው ሳምንት ላይ ይውላል፡፡ ደብረ ዘይት ትርጉሙ የወይራ ዛፍ ተራራ ማለት ሲሆን፣ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም በሚገኘው በደብረ ዘይት ተራራ ቅዱሳን ሐዋርያት የዓለሙ ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድነው?/ማቴ. 24፣3/ ብለው ጠይቀውት እርሱም የማይቀረውን የዓለም ፍጻሜና አስቀድመው የሚፈጸሙ ምልክቶችን አስረድቷቸዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ በደብረ ዘይት ሳምንት ታስበዋለች፤ ለምእመናኑም ከዘመኑ ሁኔታ አንጻር በመጻሕፍት የተጠቀሱትን የትንቢት ምልክቶቹን ከተግባራዊ የዓለም ክንዋኔዎች አንጻር በማገናዘብ ታስተምራለች፡፡ በመሆኑም በቤተ ክርስቲያናችን በደብረ ዘይት ሳምንት ምጽአትን አስመልክቶ የሚነገሩ ምስጢራት እጅግ ሰፊ ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጽሑፍ በመጠኑ የምናየው ከቅዱሳት መጻሕፍት አንጻር በዓለም እየተከሰቱ ካሉ ወቅታዊ ምልክቶች ጋር በማገናዘብ ይሆናል፡፡

የሰው ልጅ ከሥነ ፍጥረት መነሻ ጀምሮ ስለ ራሱ መጨረሻና ስለ ዓለም ፍጻሜ ምንነት ማወቅን እንደሚሻ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል፡፡ ከነዚህም በተለይ ቤተ ክርስቲያን በደብረ ዘይት ዕለት የምታስተምረው፤ ቅዱሳን ሐዋርያት የዓለሙ ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድነው?/ማቴ. 24፥3/€™ በማለት የጠየቁት ጥያቄ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ከመለሰላቸው ዋናውና ቀዳሚው የምጽአቱ ምልክት የሐሳዊ መሲሕ መምጣት ነው፡፡ ሐሳዊ መሲሕ ማለት በቀጥታ ትርጉሙ ሐሰተኛ የሆነ በስሙ ማለትም በኢየሱስ፣ በክርስቶስ፣ በአምላክ ስም የሚመጣ የክርስቶስ ተቃዋሚ ማለት ነው፡፡ ትርጉሙን አስፍተን ስናየው፣ ደግሞ ከሃይማኖት ጋር ተያያዥ የሆኑና ያልሆኑ በዓለም እየተካሄዱ ያሉ ሐሰተኛ ጉዳዮችንና የጥፋት መንገዶችን ያጠቃልላል፡፡ የሐሳዊ መሲሕ የጥፋት ሥራዎች ሳያውቁም ሆነ በተለይ ሆን ብለው በዓለማውያንና በክፉ መናፍስት ተከታዮች እየተፈለሰፉ በሚከሰቱ ሁኔታዎች የሚካሄዱ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር የተገኙ የሃይማኖት የሥነ ተፈጥሮ የጋብቻና የመሳሰሉ ድንበሮች ማፍለስን ዓላማ ያደረጉ፤ እንዲሁም መንፈሳዊ ባሕል፣ ሰብአዊ ክብርና የዕድሜ፣ የቅደም ተከተል ትስስርና ክብር እንዲጠፋ የሚሠሩ ሁሉ ከሐሳዊ መሲሕ መደብና ከዓለም ፍጻሜ ምልክት አንጻር የሚታዩ ናቸው፡፡ በዝርዝር ለማየት የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት፣
1.የሃይማኖት ድንበርን ማፍለስ፡-
€አባቶችህ ያኖሩትን /የሠሩትን/ የቀድሞውን የድንበር ምልክት አትፍልስ ምሳ.22፥28፣ 23፥10 አፈጻጸሙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ማንነት እንዳያውቁ ከማድረግ ይጀምራል፡፡ ከዚህም አንዱ ሐሳዊ መሲሕ በእግዚአብሔር ስም በተለያየ ሁኔታና መንገድ መገለጥ ነው፡፡ €እስመ ብዙኀን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ፤ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ብዙ ሰዎች በኔ ስም ይነሣሉና€ /ማቴ. 24፣5/፡፡ ይህም እንደ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትና የቅዱሳን ሐዋርያት ስብከት መሠረት፣ ከክርስቶስ ወደ ሰማይ ማረግ በኋላ የሚመጣ፣ ክርስቶስን የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ ነው ብሎ የማይሰብክ ሁሉ፤ ሌላ አምላክን የሚሰብክ ሁሉ መደቡ ከሐሳዊ መሲሕ ትምህርት ይመደባል፡፡ በመሆኑም ከዚህ በፊት ያለፉ፣ አምላክ ነን ብለው የተነሡ እንደ ቴዎዳስ ዘግብጽና ይሁዳ ዘገሊላ /ሐዋ. ሥራ. 5፣36-37/ የመሰሉ ሁሉ ከዚያም በኋላ በየጊዜው የተነሡና በዚህም ወቅት የዋሁን ሕዝብ €ኢየሱስ ነኝ፣ ኢየሱስ በኛ ዘንድ አለ€ እያሉ የሚያጭበረብሩ ሁሉ ሐሳውያነ መሲሖች ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ክርስቶስን ከአብ የሚያሳንሱ፣ €ሎቱ ስብሐት ነቢይ ነው ብለው የሚያምኑ፣ በመናፍስት አሠራር የሚጠነቁሉ፣ በማቴሪያሊስት /ቁሳውያን/ ወይም በኢቮሉሽን /በዝግመተ ለውጥ/ ትምህርት አምነው አምላክ የለም የሚሉ ሁሉ፣ ወዘተ የሐሳዊው መሲሕ አካላት ናቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ”ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንደሚመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።” /1ዮሐ. 4፣3/ በማለት ይመሰክርባቸዋል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አሁንም በመልእክቱ €ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን።€ /1ዮሐ. 2፥18/ ይለናል፡፡ ከዚህ የምንረዳው የክርስቶስ ተቃዋሚ መምጣት የምጽአት ጊዜው መቃረብ ምልክት መሆኑን የማያሻማ ሀሳብ ያደርገዋል፡፡ በተጨማሪም የምጽአትን መቅረብ የሚያመለክቱ፣ ስለ ሐሳዊው መሲሕ እና ከርሱ ጋር ተያያዥ ስለሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ተዛማጅ የሆኑትን የሚከተሉትን ትንቢቶች እንመልከት፣

ሀ.”የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፥ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው። ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፥ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ። አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።€ /ራእ. ዮሐ. 13፥16-18/ የሚለው የቅዱስ ዮሐንስ ራእይን ሊፈታ ከሚችልበት ትርጉም አንዲት ቅንጣት ብቻ ከዘመኑ አንጻር ብናይ የሚናገር የአውሬው ምስል€™ ማለትም ለሱ ያልተገዙትን ወይም ቁጥሩን ያልያዙትን የሚናገርባቸው፤ ምልክቱን ያልተቀበሉትን ሊገዙና ሊሸጡ እንዳይችሉ ያደርጋል ማለት መኖር፣ መሥራት፣ መሸጥ፣ መለወጥ ወዘተ የሚያግዳቸው ሲል አሁን ባለን ወቅታዊ የዚህ ዓለም አኗኗር አንጻር ሲታይ ተመሳሳይ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ መታወቂያ ወረቀት፣ ፓስፖርት፣ ቪዛ፣ የመኖሪያ ፈቃድ ወዘተ በዓለም አጠቃላይ አሠራር እና ባንድ ሰው የመኖር ማንነት ሚና ላይ ተጽእኖ የሚያደርጉ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ መታወቂያ ወረቀቶች የሌሉት ሰው ካለበት የትም መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ከዚህም በላይ ጉዳዩን ስናሰፋው በሰለጠኑት ዓለማት አሠራር የእያንዳንዱ ሰው የጣት አሻራ ኮምፒውተራይዝድ በሆነ መንገድ የተደራጀ በመሆኑ፣ እዚያ አደረጃጀት ውስጥ ካልተካተተ በቀር እዚያ ሀገር ሊኖር፣ ሊዘዋወር፣ ሊሠራ፣ ሊነግድ ወዘተ አይችልም፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ እዚህ የኮምፒውተር ድር አደረጃጀት ውስጥ ያለ ሰው የትም ዓለም ቢሄድ በጣቱ አሻራ ይታውቃል፡፡ በትንቢቱ” አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።” የሚለው ይህን የሚያደራጀው ጉዳዩን የሚያስተሳስረው ሌላ አካል ሳይሆን ሰው መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት የሚለው ቁጥር የሰው ልጅ የጅማት ቁጥር ነውና፡፡

ለ.ሌላው የምጽአት መቃረብ ምልክት የሐሳዊው መሲሕ ዘመቻን አውቀው በድፍረት፣ ላላወቁት በረቀቀ መንገድ እግዚአብሔርን ያመለኩ አስመስሎ የእግዚአብሔርን ስም፣ እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን፣ ቅዱሳንን፣ ባጠቃላይ በሰማይ የሚያድሩትን መስደብ ነው፡፡ እነዚህም ተግባራት በተለያዩ ዘመናት ሲፈጸሙ የቆዩ ናቸው ዛሬም ተጠናክረው እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ሩቅ ሳንሔድ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችንን እየተፈታተነ ያለው የተሐድሶ ሤራ ዋናው ተቃውሞው የወልድን አምላክነት፣ የድንግል ማርያምን ክብርና አማላጅነት፣ የታቦትንና የመስቀልን ክብር፣ የቅዱሳንን ክብርና አማላጅነት ነው፡፡ በመሆኑም ተሐድሶ በሥራው የአውሬው መንፈስ አራማጅና መንገድ ጠራጊ መሆኑን ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እንዲህ በማለት ያረጋግጥልናል፡፡ ”ለዘንዶውም ሰገዱለት፥ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም፡- አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት። ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፥ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው። እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ። ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፥ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል።€ /ራእ. ዮሐ. 13፣4.8/ እንዲል፡፡

ሐ.ሌላው በዓለም ላይ የሚታየው በሰዎች ዘንድ ክብር፣ ዝናና ታዋቂነትን ለማግኘት ሲባል ራስን ከፍ ማድረግና እንደ አማልክት መቁጠር ከሐሳዊው መሲሕ ያስመድባል፡፡ ከዚህ በተመሳሳይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንደገለጸው የሰናዖር ሰዎችን ኀጢአት ስናሰተውል የተነሡበት ዋናው ነጥብ €™ስማችንን እናስጠራ የሚለው ነበር፡፡ ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው አሉ።€ /ዘፍ. 11፥4/ ነው የሚለን፣ በዚህ እኩይ አሳብ ምክንያት እግዚአብሔር ቋንቋቸውን ደባለቀባቸው፡፡ የሰናዖር ሰዎች ያሰቡትና የተመኙት ትውልዱ እግዚአብሔርን ማድነቅ ትቶ፣ ለዘለዓለም ስማቸውን ሲጠራቸው፣ ሲያደንቃቸው መኖርን ነበር፡፡ ዛሬም ብዙዎቹ ይህንን የሰናዖርን ኀጢአትና የጥፋት ጉዞ እንደ ዓላማ ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

2.የሥነ ተፈጥሮ ሕግ ድንበር መጣስ አንዱ የጊዜው መቃረብ ምልክት ነው፡፡

እግዚአብሔር የፈጠረው ፍጥረት ፍጹም በመሆኑ፣ ይህ ቀረህ፣ ይህ ይጨመርልህ የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት፣ ሰው ለተለያየ ጥቅም በሚል ሰበብ ዝርያቸው የተለያዩ የሆኑትን ፍጥረታት ማዳቀልንና ማደበላለቅን ተያይዞታል፡፡እንስሳትና ተክሎችን ለማባዛት የማያደርገው ጥረትና የማዳቀል ዘዴ የለም፡፡ በተቃራኒውም የሰውን ቁጥር ለመቀነስ የማያደርገው ሩጫ የለም፡፡ በመሆኑም ውጤቱ የሰውን ቁጥር ለመቀነስ ሲባል በሚደረጉ ሕክምናዎች ሰዎች ለተለያዩ በሽታዎች ተዳርገዋል፡፡ በሚደረገውም ማበረታታት በሠለጠኑት ዓለም ብዙዎቹ የግብረ ሰዶም ፈጻሚና አስፈጻሚ ሆነዋል፡፡ ይህ አሠራር አምላክ የሠራውን የፍጥረት ሕግ በማጣጣል ሰው ላሻሽል ወደሚል ያዘነበለ በመሆኑ የሰውን ልጅ ቅጥ ያጣ ድፍረት ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ግን ሥነ ፍጥረቱን እንዲያደባልቁበት አይፈልግም፡፡ እግዚአብሔር ለሊቀ ነቢያት ሙሴ ሥርዓቴን ጠብቁ። እንስሳህ ከሌላ ዓይነት ጋር አይደባለቅ፤ በእርሻህም ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ€ /ዘሌ. 19፣ 19፤/ ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በላያቸው ነው።€ /ዘሌ 20፣ 13/ በማለት ያሰተምረናል፡፡

3.በጋብቻ ላይ የሚደረግ ርኩሰትን ስንመለከትም በየትኛውም ዓለም የፍርድ ቤቶች ትልቁ ሥራ ማፋታት ሆኗል፡፡

ምክንያቱም ተጋቢዎች ባንድ ላይ እንዳይኖሩ አውሬው /አስማንድዮስ/ የጋብቻ ጠላት በመሆን ስለነገሠ ፈተናውን መቋቋም አልቻሉምና ነው፡፡ ስለዚህ አስማንድዮስ ከዛ ይልቅ ግብረ ሰዶምን እያበረታታ በአንዳንድ ሀገሮች እንደሚታየው ወንድ ከወንድ፣ ሴት ከሴት ጋር እያቆራኘ በቤተ ክርስቲያኖቻቸው€ ጋብቻ እስከ መፈጸም አድርሷቸዋል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፣ ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵሰት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው፤ አሜን። ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ዓመፃ ሁሉ፥ ግፍ፥ መመኘት፥ ክፋት ሞላባቸው፤ ቅናትን፥ ነፍስ መግደልን፥ ክርክርን፥ ተንኰልን፥ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፤ የሚያሾከሹኩ፥ ሐሜተኞች፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚያንገላቱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክህተኞች፥ ክፋትን የሚፈላለጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት ያጡ ናቸው፤ እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋር ይስማማሉ እንጂ አድራጊዎች ብቻ አይደሉም።€ /ሮሜ.1፥24-ፍጻሜ

4.መንፈሳዊ ባሕል፣ የክህነት ክብር፣ ሰብአዊ ክብርና የዕድሜ፣ የቅደም ተከተል ትስስርና ክብር እንዲጠፋ የሚሠሩ፣ በሚለው ዙሪያ ስንመለከት በቀላሉ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ያለውን ማየት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡

ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁል ጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና። ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም።€ / 2ጢሞ. 3፥1.7/ በማለት በመጨረሻው ዘመን የሚነሡ ሰዎችን ፀባይን ይነግረናል፡፡ ይህንን ትምህርተ ጥቅስ ለማገናዘብ እግዚአብሔርን የማያምነውን ሕዝብ ትተን፣ አሁን በዓለም ሁሉ ካለው የቤተ ክርስቲያንዋ አማኞች ብቻ አንጻር በመጠኑ እንይ ደግሞ፤

ሀ.መንፈሳዊ ባህል ማፍረስን ስንመለከት፣ የሁሉንም ባይሆን፣ የአንዳንዶቹ አማኞች ሰዎች ጸባይ ቅዱስ ጳውሎስ €ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል የሚያሰኝ ሕይወት የያዙ እንደሆነ ያስረግጥልናል፡፡ እንደ አማኝ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ፣ ነገር ግን መንፈሳዊ አምልኮ የማይፈጽሙና የራሳቸውን አሳብ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊጭኑ የሚፈልጉትን ነው የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል ያላቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቤት መታዘዝ፣ መከባበርና ሰላም የነገሠበት መሆን ነው ያለበት፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ቦታ እንደሚስተዋለው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙዎቹ በመንፈሳዊው ባሕል የጠነከሩ እንዳሉ ሁሉ አንዳንዶቹ ሥራ ፈቶች ሆነው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፖለቲካ፣ ዘረኝነት፣ አሉባልታ፣ ወዘተ በማምጣት ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩአት ይታያል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በተመሳሳይ አይሁድ ቀንተው በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረጉትን አንዳንዶቹ ተረድተው ከሚያመልኩም ከግሪክ ሰዎች ብዙ ከከበሩትም ሴቶች ጥቂቶች ያይደሉ፥ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ። አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ ሕዝብንም ሰብስበው ከተማውን አወኩ፥€ /የሐዋ. ሥራ 17፣ 5/ በማለት እንደገለጸው ያሉ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና።€ ይላቸዋል፡፡

ለ.የክህነት ክብርን ማፍረስ በተመለከተ፣ ቅ. ጳውሎስ €ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም።€ እንዳለው ሁሉ ካህናት ነን ከሚሉት ጀምሮ እስከ ምእመናን ድረስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ሰጥቷቸው በአንብሮተ እድ እየተሾሙ ሲወርድ መጥቶ ለኛ የደረሰውን ታላቁን የድኅነት መፈጸሚያ ክህነት እንደ ኢያኔስና ኢያንበሬስ ዛሬ በብዙዎች ተንቆና ተዋርዶ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ከሚፈጸሙ ስህተቶች ጥቂቶቹን ቀጥለን እንመለከት፣
ቅዱስ ማቴዎስ በዚያን ዘመን ብዙዎች ይሰናከላሉ፣ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፣ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ€ /ማቴ. 24፣10/ እንዳለው ሁሉ፤ ለዘመናት በአንድነት የኖረችውን ቤተ ክርስቲያን ከዓመጻም ብዛት የተነሣ የብዙዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች እንዲል፣ በዚህ ዘመን በድፍረት አስተዳደሩዋን በመከፋፈል ”ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት” እንዲሁ አሳድጋ፣ አስተምራ፣ ክህነት የሰጠቻቸውን እናታቸውን ቤተ ክርስቲያን እስከ ማውገዝ የድፍረት ኀጢአት የተደረሰበት ዘመን ነው፡፡ በመወጋገዙ ሂደት ያለው ጉዳትን ማን አስተዋለው? እግዚአብሔር ይማረን እንጂ እንደ ሰውኛው ከሆነ፣ በጭካኔ፣ ውስጥ ያለው ውጪውን፣ ውጭ ያለው ደጋግሞ ውስጥ ያለውን አውግዞት አንዲት ነፍስ ወደ እግዚአብሔር እንዳትደርስ ተቆላልፎ ቁጭ ብሏል፡፡ ነገር ግን ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሙሴን ቢቃወሙትም ሙሴ ክህነቱ ከእግዚአብሔር በመሆኑ የእግዚአብሔር ክብር በርሱ ላይ ተገልጦ እግዚአብሔርን የተቃወሙት በደላቸው እንደ ተገለጠ ሁሉ፣ ዘለዓለማዊዋ ቤተ ክርስቲያን ክህነታዊ ክብርዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ክቡር ነው፡፡ ”ሁሉ ለንጹሖች ንጹሕ ነው፤ ለርኵሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም የለም፥ ነገር ግን አእምሮአቸውም ሕሊናቸውም ረክሶአል። እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፥ ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ የማይበቁ ስለ ሆኑ፥ በሥራቸው ይክዱታል።€ / ቲቶ. 1፥15/ እንዳለ፡፡

€ሰለስቱ ምእት በኒቂያ ጉባኤ €™ያለ ኢጲስ ቆጶስ ፈቃድ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተ ከክህነቱ ይሻር€™ ብለው ደንግገዋል፡፡ ነገር ግን በተለይ በውጭ አገር እየተለመደ የመጣው ጉዳይ የትኛውንም ኤጲስቆጶስ ሳያስፈቅድ አንድ ካህን፣ ከዚያም አልፎ በሚገርም ሁኔታ ዲያቆን ወይም ምእመን ከፈለገ ቦርድ አቋቋምኩ እያለ ቤተ ክርስቲያን አስተምራ አጥምቃ ያሳደገችውን ምእመን ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን በማውጣት እንደ ማንኛውም ድርጅት ቤተ ክርስቲያን ከፈትኩ የሚባልበት የድፍረት ኀጢአት በጠራራ ፀሐይ ከሚፈጸምበት ዘመን ደርሰናል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ዓይነት ለተቋቋሙ ሁሉ የሚገለገሉበት ታቦት ከየት መጣ? ሜሮን ከየት ተገኘ? የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የላቸውም፡፡ €ብዙዎች ይስታሉ” እንደተባለ በድፈረትና በስሕተት መሠረት ላይ የስሕተትና የድፍረትን ግድግዳ ማቆም፣ የስሕተትና የድፍረት ጣሪያንም ማዋቀር እንደ ሕጋዊ ሥራ ከተቆጠረ ሰነባበተ፡፡

የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰው ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል /ማቴ 24፣15/ በየአጥቢያው የሚሰማውን ክፉ ወሬ ስናስተውል የዚህ ትንቢት ተፈጻሚነት እንዳገኘ ያረጋግጥልናል፡፡ የተሐድሶ ሴራ፣ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጠሩት ጭቅጭቆች፣ በመነኮሳትና በካህናት የሚነሱ ሐሜቶች፣ ሙሰኝነት፣ ዘረኝነት ምን ይነግሩናል? በውጭ አገር በየቦታው አቋቋምን የሚሉት ሰበካ ጉባኤ ሳይሆን ራስ ገዝ የቦርዶቹ አስተዳደር ግፍ ደግሞ በሚገርም ሁኔታ የሚያገለግለው ካህንን የሚያዩት እንደ እግዚአብሔር ካህን ሳይሆን ከአንድ ቅጥር ሠራተኛቸው በታች ነው፡፡ ስለ አስተዳደሩ እንዲያውቅ አይፈልጉም፣ እነሱ ያዘዙትን ብቻ ይሰብካል/ ይናገራል፣ ካህኑም ሲፈልጉ የሚያኖሩት ሲፈልጉ የሚያባርሩት ሆኗል፡፡ ይህን አሠራር ለዘመናት ቤተ ክርስቲያን ከኖረችበት አንጻር ስናየው እጅግ የራቀና አስጸያፊ የሚባል ነው፡፡ ጌታችን ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተው በሥልጣነ ክህነት እንድትተዳደር ሲሆን ይህኛው በተቃራኒ የቆመ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ምእመኑን አስተምራ አጥምቃ አሳድጋ እንደገና በተንኮለኞች ሤራ ልጆቹዋን ቀስጠው በስዋ ላይ እንዲያምጹ ማድረግ የጥፋት ርኩሰት መሆኑን ስንቱ ተረድቶት ይሆን? ቅዱስ ጳውሎስ ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢሆን፥ በትዕቢት ተነፍቶአል አንዳችም አያውቅም፥ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፤ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም ክፉ ዐሳብም እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ፥ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ። /1 ጢሞ.6፥3-5/ እንዳለ፡፡

ሐ.ሰብአዊ ክብርና የዕድሜ፣ የቅደም ተከተል ትስስርና ክብር እንዲጠፋ የሚሠሩ ለሚለው ሌላ ብዙ ከማለት ይልቅ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ €ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ” በማለት የዘረዘረው ለርእሰ ጉዳዩ ተስማሚና በቂ ነው፡፡/1ጢሞ.3፥1-3/

ባጠቃላይም የምጽአት ምልክቶች የሚያሳዩት ሁኔታዎች ከመንፈሳዊው እስከ ዓለማዊው፣ ከተማረው እስከ መሀይሙ፣ ከትልቅ እስከ ትንሽ፣ ያላገባው፣ ያገባው፣ መነኩሴው ሳይቀር ሁሉም ሁሉም ባንድ ላይ ከቅድስና ርቀት፣ ከጥፋት ርኩሰት፣ ከመከራ ሕይወት፣ ተቋዳሽ መሆናቸውን ነው የሚያሳየው፡፡ ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍት ተባብረው እንደመሰከሩልን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድንገት ይመጣል አይዘገይም፡፡ ቅዱስ ዳዊት €ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል። አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይቃጠላል፥ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ።€ /መዝ.49፥2-3/ ብሎ እንደተናገረው፡፡

ከላይ እንደተዘረዘረው የሰው ልጆች ሁል ጊዜ ከመንፈሳውያን እስከ ዓለማውያን ድረስ በተጠመዱበት የዓለማዊ ሥራ እንደ ተወጠሩ ነው ያሉት፡፡ ከዚህም በኋላ የበለጠ በሥጋ ሥራ እየተወጠሩ ይሄዳሉ እንጂ መንፈሳዊ ወደ ሆነው የተጋድሎ ሕይወት የሚያዘነብል ይኖራል ለማለት ያስቸግራል፡፡ እንዲያውም በዐመጽ እየበረታ እስከ መቅደስ ድፍረቱን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይገልጸዋል፤ ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ፥ አይደርስምና። እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አዋጅ እየነገረ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እስኪቀመጥ ድረስ፥ አምላክ ከተባለው ሁሉ፥ ሰዎችም ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው ተቃዋሚ እርሱ ነው።€ /2ተሰ.2፥3-4/ ይለናል፡፡ ነገር ግን ክርስቲያኖች ነን የምንል ሁሉ የጥፋት ትንቢቱ እኛ ላይ እንዳይፈጸም አሁኑኑ ሳናመነታ ንስሐ መግባትና በትንቢት ከተገለጡት ርኩሰቶች ጨክነን መራቅ ይገባናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡

ደብረ ዘይት /የዐቢይ ጾም ሳምንታት/ አትም ኢሜይል
ድጓ
እንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ወይቤሎሙ ለአርዳኢሁ ዑቁኬ ኢያስሕቱክሙ ወንበሩ ድልዋኒክሙ፡፡ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ ወዘአዝለፈ ትእግስቱ ውእቱ ይድኅን፡፡ ወአመምጽአቱሰ ለወልደ እጓለመሕያው ይትከወስ ኵሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር፡፡ አሜሃ ይበክዩ ኵሎሙ ኃጥአነ ምድር ወይወርድ እግዚእነ እምሰማ ዲበምድር በትእዛዙ ወበቃሉ ወበአዕላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእምኀበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬ ሕይወት ውእቱ እግዚአ ለሰንበት፡፡

ትርጉም፡-
ጌታን በደብረ ዘይት ተራራ ተቀምጦ ሳለ ለዳመዛሙርቱ ማንም እንዳያስታችሁ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፣ እስከመጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል፡፡ የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማያትና የምድር ኃይላት ሁሉ ይናወጣሉ፡፡ ያን ጊዜ በምድር ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ ያለቅሳሉ፡፡ ጌታችንም እንደተናገረና እንዳዘዘ ከእርሱ ዘንድ በሆነ በመለከት ድምጽ በቅዱሳን መላእክት ታጅቦ ከሰማይ ወደ ምድር ይመጣል፡፡ አብ እርሱ የሕይወት መገኛ ነውና ያን ጊዜ በኃጢአት ከመሞት ይራራልን፡፡

ምስባክ፡- መዝ.49፤3
እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽእ፣ ወአምላክነሂ ኢያረምም፣ እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፣ ወዐውደሃ ዐውሎ ብዙኀ፡፡

ትርጉም፡-
አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፣ እሳት በፊቱ ይቃጠላል፣ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ፡፡

ምንባባት፡-
1ኛ ተሰ. 4፣13-18
ወንድሞቻችን ሆይ ስለሞቱ ሰዎች ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች እንዳታዝኑ ልታውቁ እንወዳለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ እንደተነሣ ካመንን እንዲሁ እግዚአብሔር ሙታንን በኢየሱስ ያስነሣቸዋል፣ ከእርሱም ጋር ያመጣቸዋል፡፡ ይህንም በእግዚአብሔር ቃል እንነግራችኋለን፣ ጌታችን በሚመጣ ጊዜ ሕያዋን ሆነን የምንቀር እኛ የሞቱትን አንቀድማቸውም፡፡ ጌታችን ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምጽ፣ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና በክርስቶስም የሞቱ ሙታን አስቀድመው ይነሣሉ፡፡ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው ጌታችንን በአየር እንቀበለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፡፡ ከዚያም ወዲያ ለዘለዓለሙ ከጌታችን ጋር እንኖራለን፡፡ ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ፡፡

2ኛ ጼጥሮስ 3፣7-15
አሁንም ሰማይና ምድር በዚያ ቃል ለእሳት ተዘጋጅተዋል፣ ኃጥአን ሰዎች እስኪሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀንም ተጠብቀዋል፡፡ ነገር ግን ወንድሞቻችን ሆይ ይህን አትርሱ፣ በእግዚአብሔር ቀን አንዲት ቀን አንድ ሺሕ ዓመት፣ ሺሕ ዓመትም እንደ አንድ ቀን ነውና፡፡ እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል አያስቀርም ይቀራል ብለው የሚናገሩ አሉና፣ ነገር ግን ስለ እነርሱ ያታገሣል፣ ማንም ይጠፋ ዘንድ አይሻምና ንስሐ ይገቡ ዘንድ ለሰው ሁሉ ዕድሜን ይሰጣል እንጂ፡፡ ሰማያት የሚነዋወጡባትና የሚያልፉባት ቀድሞ የነበረው ፍጥረት ሁሉ በእሳት ነበልባል የሚቃጠልባት፣ ምድርና በእርስዋ ላይ ያለው ፍጥረት ሁሉ የሚቃጠልባት የእግዚአብሔር ቀን ግን እንደ ሌባ ድንገት ትመጣለች፡፡ ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ በተቀደሰች አካሔድና በመልካም አምልኮ ለመኖር ፍጠኑ፡፡ . . .

የሐዋርያት ሥራ
ሐዋ. 24፣1-22
እነርሱም ለጻድቃንና ለኃጥአን የሙታን ትንሳኤ ይሆን ዘንድ እንደሚጠብቁ ለእኔም እንዲሁ በእግዚአብሔር ዘንድ ተስፋ አለኝ፡፡ እንዲሁ እኔም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ የማታወላውል ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እጋደላለሁ፡፡ . . .

ወንጌል፡-
ማቴ.24፣1-36
ጌታችን ኢየሱስም ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሔደ፣ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው የቤተ መቅደሱን የሕንፃ አሠራር አሳዩት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፡- ይህን ሁሉ ታዩታላችሁን? እውነት እላችኋለሁ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም፡፡ በደብረ ዘይትም ተቀምጦ ሳለ ደቀመዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀረቡና እንዲህ አሉት፡- ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለሙ ፍጻሜስ ምልከቱ ምንድነው? ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው የሚያስታችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፣ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዘዎችንም ያስታሉ፡፡ ጦርነትን የጦርነትንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፣ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠንቀቁ፣ አትደንግጡ ነገር ግን ፍጻሜው ገና ነው፡፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ፣ በየሀገሩም ረኃብ፣ ቸነፈርም፣ የምድር መናወጥም ይሆናል፡፡ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው፡፡ ያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣ ይገድሏችኋልም ስለ ስሜም በሰው ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፡፡ ያን ጊዜም ብዙዎች ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፡፡ . . .

ቅዳሴ፡-
ያዕቆብ ዘሥሩግ/አትናቴዎስ 

ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ማቴ.24፡44 አትም ኢሜይል
መጋቢት 23 ቀን 2008ዓ.ም
ዲ/ን ተመስገን ዘገየ
ይህ ቃል ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ለደቀመዛሙርቱ ስለ ዳግመኛ ምጽአቱና ስለ ዓለም ፍጻሜ ምልክቶች ሲጠይቁት የተናገረው ኃይለ ቃል ነው፡፡ ወእንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ቀርቡ ኀቤሁ አርዳኢሁ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እሱ ቀረቡና እንዲህ አሉት፤ ንግረነ ማእዜ ይከውን ዝንቱ ወምንትኑ ተአምሪሁ ለምጽአትከ፣ ንገረን ይህ መቼ ይሆናል የዓለም ፍጻሜ ምልክቱስ ምንድን ነው?አሉት፡፡

ደብረ ዘይት ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻግሮ የሚገኝ ታላቅ ተራራ ነው፡፡ 800 ሜትር ያህል ከባሕር ጠለል በላይ ከፍታ አለው፡፡ ቤተፋጌና ቢታንያም ከግርጌው የሚገኙ መንደሮች ናቸው፡፡ ደብረ ዘይት ስያሜውም የተሰጠው በላዩ ከሚበቅሉት (ተራራውን ከሸፈኑት) የወይራ ዛፎች የተነሳ ነው፡፡ ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ዛፍ የመላበት (በብዛት የሚገኝበት) ተራራ ማለት ነውና፡፡

የደብረ ዘይት ተራራ ብዙ ታሪካዊ ክስተቶችን ያስተናገደ ተራራ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመንም ዳዊት ከአቤሴሎም በሸሸ ጊዜ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት እንደወጣ በ2ኛ ሳሙ 5 ዳዊትም ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ወጣ€ ይላል፡፡ ይህ ተራራ በሕዝቅኤል ትንቢት ስብሐተ እግዚአብሔር እንደሚያርፍበት ተነግሮአል፡፡ የእግዚአብሔር ክብርም ከከተማይቱ መካከል ተነሥቶ በከተማይቱ ምሥራቅ በኩል በአለው ተራራ ላይ ቆመ፡፡ ት.ሕ11፤23

ዘሩባቤል ከሠራው ቤተ መቅደስ ዐደባባይ ደብረ ዘይት 75 ሜትር ገደማ ከፍ ብሎ ይገኛል፡፡ ቤተ ፋጌና ቢታንያም የሚባሉት ታሪካውያን ቦታዎች ከደብረ ዘይት ግርጌ ይገኛሉ፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሆሳዕና ዕለት ከደብረ ዘይት ወደ ኢየሩሳሌም እንደገባ በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 11፡1 ላይ €œወአልጺቆሙ ኢየሩሳሌም ኀበ ቤተ ፋጌ ወቢታንያ በኀበ በደብረ ዘይት ፈነወ ክልኤተ እምአርዳኢሁ ፤ወደ ኢየሩሳሌም ከደብረ ዘይት አጠገብ ወደ አሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ ከደቀ መዘሙርቱ ሁለቱን ላከ€ ይላል፡፡ አይሁድም ጌታን የያዙት በደብረ ዘይት ተራራ ግርጌ በምትገኘው ጌቴሴማኒ ነው፡፡

አንቢቦሙ ወሰቢሖሙ ወጽኡ ወሖሩ ውስተ ደብረ ዘይት ወእምዝ ይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ኵልክሙ ትክሕዱኒ በዛቲ ሌሊት፣ መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ አላቸው፡፡ (ማቴ. 26፡30)

ጌታችንም ሲያስተምር ውሎ ማታ ሔዶ የሚያድረው በደብረዘይት ተራራ ውስጥ ባለችው ኤሌዎን ዋሻ ውስጥ ነበር፡፡ በዕለተ ሆሳዕናም ከኢየሩሳሌም ሲወጡ የገባውም ወደ ደብረ ዘይት ነው፡፡ ማር 11፤1 በዚህ ዓለም የፈጸመውን አገልግሎት ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ሰማይ ያረገውም በደብረ ዘይት ተራራ ነው፡፡ ወደፊትም ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል ተብሎ የተነገረው ትንቢት ላይ መገለጫው ደብረ ዘይት እንደሆነች ተገልጿል፡፡ እነሆ እግዚአብሔር ቀን ይመጣል ብዝበዛሽንም በውስጥ ይከፍላሉ፡፡ አሕዛብም ሁሉ ኢየሩሳሌምን ይወጉአት ዘንድ እሰበስባለሁ ከተማይቱም ትያዛለች፡፡ (ት. ዘካ. 14፤1)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ምጽአቱ (ዳግም ምጽአቱ በደብረ ዘይት ተራራ) ላይ በሰፊው አስተምሯል፡፡በቤተመቅደስ ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስና እንድርያስም ለብቻ ጠየቁት፡፡ እንዲህም አሉት ንገረን ይህ መቼ ይሆናል(ማር 13፤3፣ ማቴ 24፤1-51) ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አቡነ ዘበሰማያት የሚለውን ጸሎት ያስተማረውም በደብረ ዘይት ተራራ ነው፡፡

ከ62 ሀገሮች በላይ ልሳን(ቋንቋ) በሞዛይክ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ ግእዝ ነው፡፡ በመሆኑም 5ኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት የክርስቶስ ነገረ ምጽአት የሚዘመርበት የሚሰበክበት ዕለት ስለሆነ በደብረ ዘይት ተሰይሟል፡፡ ሰያሚውም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ በዕለቱ የሚነበበው የወንጌል ክፍልም ማቴ 24፤1-36 ነው፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቅደስ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት በሄደበት ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ አጠገቡ ቀርበው ዘሩባቤል ያሳነፀውን የመቅደስ ግንቦች እያሳዩት ቀረቡ፡፡

አማን እብለክሙ ኢይትኀደግ ዝየ እብን ዲበ እብን ዘኢይትነሠት፣ እውነት እላችኋለሁ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የኢየሩሳሌምን መፍረስና ዳግም መምጣትን አስፍቶ አምልቶ ከነምልክቱ ለደቀ መዛሙርቱ አስተማራቸው፡፡ ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆንባቸው በሰማያዊ ንጉሥ ፊት ያለ ምክንያት ለፍርድ እንዲቆሙ የእግዚአብሔር ሕገ መንግሥት ወንጌል በአህዛብ ቤት ሳይቀር ለሁሉም ይሰበካል፡፡ በዚህ ጊዜ መጨረሻው እየቀረበ ይመጣል፡፡ (ማቴ.24፤14) በማለት በስፋት አስተምሮአቸዋል፡፡€ እምበለስ አእምሩ አምሳሊሁ፣ ነገሩን በበለስ እወቁ፡፡

የበለስ ቅጠል መለምለም ማለት የጠፋችው እስራኤል መንግሥት መመሥረት የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት 11ኛ ምልክት ነው፡፡ ማቴ 24፤32

ከዚህ በኋላ በማናውቀው ጊዜና ሰዓት እግዚአብሔር ወልድ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት (በአካላዊ መጠን) ከቅዱሳን መላእክት ጋር በደመና ይመጣል፡፡ ናሁ ይመጽእ በደመና ሰማይ ወትሬእዮ ኩላ ዐይን ወእልክቱሂ እለ ወግእዎ ይበክዩ በእንቲአሁ ኩሎሙ አሕዛበ ምድር እወ አማን፣ እነሆ በሰማይ ደመና ይመጣል ዐይን ሁሉ ታየዋለች የወጉትም ሁሉ ያለቅሳሉ የምድር ወገኖች ሁሉ የኀዘን ድምፅ ያሰማሉ፡፡ አሕዛብ ሁሉ ስለ እርሱ ያለቅሳሉ፡፡ (ራእይ 1፤7)

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዳግም ምጽአቱ በተናገረበት አንቀጹ ቅዱሳን ሐዋርያትን ካስጠነቀቀበት ዐቢይ ኃይለ ቃል መካከል ስለ ሐሰተኞች መምህራን መምጣት ነበር፡፡እስመ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ ወያስሕትዎሙ ለብዙኃን የሚያስታችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ በማለት (በማቴ 24፤5) አስጠንቅቋል፡፡

ክርስቲያኖች አሁንም በ21ኛው መቶ ክ/ዘመን የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኩላዎች ከሆኑት ከሐሰተኞች መምህራን ተጠበቁ፡፡ ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማል? በማለት እውነተኛ የወንጌል መምህራንን በመምሰል ብዙዎችን እንደሚያሳስቱ ጌታችን አስተምሮናል (ማቴ 7፤15) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በሮሜ 16፤17 ነገር ግን ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትና ማሰናከያ የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምንቹሃለሁ፡፡ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግር ተንኰል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉና ይላል፡፡

የእስክንድርያው ሊቀጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ እንደተናገረ እኛስ ያለማወላወል የደጋግ አባቶችን ሃይማኖት እንይዛለን€ (ሃይማኖተ አበው) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመጀመሪያውን እምነታችን እስከመጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና፡፡ (ዕብ 3፤14) ይላል፡፡ ስለዚህ በጊዜው ያለ ጊዜውም መጽናት ይገባል (2ኛ ጢሞ4.2)

የዓለም መጨረሻውና የኢየሱስ ክርስቶስ መምጫ ምልክቶች በማቴ 24፤1 በስፋት ተዘርዝረዋል፡፡

ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ታላላቅ ምጽአቶች እንዳሉት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሥዕዋት ኃጢአት ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጧል አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ ያድናቸውም ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታዩላቸዋል (ዕብ 9፤26-28 ) በማለት ተናግሮአል፡፡

የመጀመሪያው ምጽአቱ ሥጋ በመልበስ ለሰው መሥዋዕት ሁኖ ሊያድን ለካሳ በፍጹም ትሕትና የእኛን ውርደት ተቀብሎ በበረት በመወለድ በሥጋ ማርያም መጣ፡፡ በሚሞት በሚሰደድ በሚዳከም ፤በሚበረታ፤ በሚራብ፤ በሚጠማ ፤ በሚዝል በሚወድቅ ባሕርየ ሰብእ (የሰው ባሕርይ) እንደ አንድ ኃጥእ ሞት፣ እስኪፈረድበት ድረስ ራሱን ዝቅ አድርጐ መጣ፡፡

ወንጌለ መንግሥቱን ሊሰብክልን ከሞት ወደ ሕይወት ሊያሸጋግረን በሥጋ ማርያም መጣ፡፡ ከአይሁድ ስድብን ታገሠ ኃጥአንን በሽተኞችን ሊያድን በምድር ላይ ተመላለሰ፡፡ ስለ እኛ ተገረፈ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ ያውም መራራ ለሆነ የመሰቀልሞት ታዘዘ፡፡ ሞቶ በሦስተኛው ቀን ተነሣ ወደ ሰማይም በዐርባኛው ቀን ዐረገ በየማነ አብ ተቀመጠ፡፡ይህ ነው የመጀመሪያው ምጽአቱ መከራን ለመቀበል እኛን ለማዳንና ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር ለመግለጥ ነው፡፡

ዳግማዊ ምጽአቱ፡- በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት በፍጹም ጌትነት በኃጥአን (የመጀመሪያ ምጽአቱን) ባልተቀበሉት ላይ ሊፈርድ ዐይን ሁሉ እየተመለከተው በገሃድ ይመጣል፡፡ እግዚአብሔርስ ገሀደ ይመጽእ ወአምላክነሂ ኢያረምም እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፣ እግዚአብሔር ግልጥ ሁኖ ይመጣል ዝምም አይልም እሳት በፊቱ ይነዳል (መዝ 49፡3)

መጥቶም ዝም አይልም (ኤሌ ለክሙ ጸሐፍት ወፈሪሳውያን መደልዋን፤ ግብዞች ጸሐፍት ፈሪሳውያን ወዮላቸሁ) እያለ ይወቅሳል ወንጌልንም ያስተምራል፡፡ ጻድቃንን እናንተ የአባቴ ብሩካን ወደ እኔ ኑ ብሎ ይጠራል ኃጥአንንም እናንተ ርጉማን ሑሩ እምኔየ፤ ከእኔ ወግዱ ብሎ ያሰናብታቸዋል፡፡ በፊቱ እሳት ይነዳል ማለት ጻድቃን የሚድኑበት ሕይወት ኃጥአን የሚጠፉበት መዓት በባህርዩ አለ ማለት ነው፡፡ ክርስቲያኖች ሆይ! የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሁለተኛ መገለጥ ለእኛስ ለምን ይሆን? ለዘለዓለማዊ ሕይወት ወይስ ለዘለዓለም ሞት?

ጌታችን በደብረ ዘይት ያስተማራቸው ትምህርቶች በመሠረታዊነት በ3 ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡

1.ምልክት (በዚያ ዘመን እንዲህ ይሆናል እያለ በፍጻሜ ዘመን የሚከሰቱትን ድርጊቶች

2.ትእዛዝ (በዚያ ዘመን ከጥፋት እንድን ዘንድ የሰጠን አምላካዊ ትእዛዝ ነው፡፡ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ እያለ ፡፡

3.ማስጠንቀቂያ በፍጻሜ ዘመን እንዲህ ሁናችሁ የተገኛችሁ ወዬላችሁ እያለ የተናገራቸው ናቸው፡፡ ለዚህም ምሳሌ ለእርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው የሚለው እርጉዝ ማለት የኃጢአት ዐሳብ የጸነሱት ሲሆኑ የሚያጠቡ ያላቸው ኃጢአትን ጸንሰው በንግግር የወለዱትን ነው፡፡

በይሁዳ ያሉት ወደተራሮች ይሽሹ (ማቴ 24፤16) በዚህ ቃል መሠረት በይሁዳ በዓለም ያሉ ወደ ተራራ ይሽሹ ተብሏል፡፡ በሃይማኖት ጸንተው ምግባር ትሩፋት እየሠሩ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ወደ ተራራ ይሽሹ ነው፡፡

ተራራ ምንድን ነው?
1.ተራራ የተባለው ረድኤተ እግዚአብሔር ነው፡፡ ተራሮች በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደሆኑ ከዛሬ ጀምሮ ለዘለዓለም እግዚአብሔር በሕዝቡ ዙሪያ ነውመዝ. 124፤2 ይላል በዚህ ቃል የእግዚአብሔር ረድኤት በተራራ ተመስሎ ቀርቧል፡፡ ምክንያቱም ተራራ እንደሚከልል እግዚአብሔርም በረድኤቱ ይከልላልና፡፡ ስለዚህ ወደ ተራራ ሽሹ ማለት ረድኤተ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጉ ማለት ነው፡፡

2.ተራራ የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ ድንግል ማርያም የጽዮን ተራራ ትባላለች €œአንሰ ተሠየምኩ ንጉሠ በላዕሌሆሙ፣ በጽዮን በደብረ መቅደሱ ፤እኔ ግን በእነርሱ ላይ ንጉሥ ሆኜ ተሾምሁ በተቀደሰው ተራራ ላይ በጽዮን ላይ€ መዝ.2፤6 ስለዚህ ትውልድ ድንግል ማርያምን ዓምባ መጠጊያ ያደርግ ማለት ነው፡፡

3.ተራራ የተባሉት ቅዱሳን አባቶቻችን ናቸው፡፡ መዝ.86፤1 መሠረታቲሃ ውስተ አድባረ ቅዱሳን ፤መሠረቶቿ በቅዱሱ ተራሮች ናቸው€ ስለዚህ ወደ ተራራ ሽሹ ማለት ወደ ቅዱሳን አባቶቻችን ቅረቡ በአማላጅነት ሥልጣናቸው አምናችሁ ተማጸኗቸው ሲል ነው፡፡

በሰገነት ያለውም በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ ይላል (ማቴ 24፤17) ሰገነት ከፍ ያለ ቦታ ነው፡፡ በዚህ ቃል በሠገነት የተመሠለ በምግባር በሃይማኖት የበረታ የወጣትነት ዘመን አልፎ ከማዕከላዊነት የደረሰ ማለት ሲሆን በዝቅታ የተመሠለ ደግሞ በኃጢአት ምክንያት የሚመጣ የነፍስ ተዋርዶ ነው፡፡

ዴማስና ይሁዳ በሰገነት ነበሩ በኋላ ግን በዝቅታ ሥፍራ ተገኙ፡፡ መዋል በማይገባቸው ቦታ ውለው ተገኙ፡፡ በክርስትና ከፍ ከፍ ብለው በመንፈሳዊነት መጽናት አቃታቸው፡፡ እኛስ ከየትኛው ስፍራ እንሆን?

በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላ አይመለስ (ማቴ 24፤18 ) በእርሻ የተመሰለ የመነነ ወይም በምንኩስና ሕይወት ያለ ማለት ነው፡፡ በእርሻ ያለ አይመለስ ማለት በምነና በምንኩስና ያለ ይህንን ሕይወት የጀመረ አይመለስ፡፡ ስለዚህ ስደታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ተግታችሁ ጸልዩ አለ (ማቴ 24፤20) ክረምት የፍሬ የአጨዳ ሳይሆን የሥራ የመዝሪያ ወቅት ነው፡፡ ሰንበትም የዕረፍት ቀን ናት በሰንበት ሥጋዊ ሥራ አይሠራም፡፡ አንድም በክረምት ቅጠል ካልሆነ ፍሬ አይገኝም እናንተም ሃይማኖት ይዛችሁ ምግባር ከሌላችሁ ዋጋ የላችሁም ማለቱ ነው፡፡

ሽሽት የተባለ ዕለተ ምጽአት ሲሆን በሽሽት የተመሰለው ሞት ድንገት እንደሚመጣ ዕለተ ምጽአትም በድንገት ስለሚሆን ነው፡፡ ትርጉሙ ንስሓችሁን ሳትጨርሱ የንስሐ ፍሬ ሳታፈሩ በድንገት ዕለተ ምጽአት እንዳይደርስባችሁ ጸልዩ የሚል ይሆናል፡፡ ክርስቲያን በዚህ ዓለም ሲኖር €œድልዋኒክሙ ንበሩ ፤ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ማቴ 24፤24 በተባለው አማናዊ ቃል መሠረት ራሱን በንስሓ አዘጋጅቶ የጌታውን መምጣት ሊጠብቅ ይገባዋል፡፡

Thursday, 31 March 2016

EOTC TV - የሰንበት ት/ቤቶች ትኩረት ለሕፃናት - ክፍል ፪

EOTC TV - የሰንበት ት/ቤቶች ትኩረት ለሕፃናት - ክፍል ፪

‹ሀገር ማለት ሰው ነው›፤ እስኪ ሙት በለኝ!

‹ሀገር ማለት ሰው ነው›፤ እስኪ ሙት በለኝ!


                        D/n ዳንኤል ክብረት

ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገርሙኝ ዘፈኖች አንዱ ‹ሀገር ማለት ሰው ነው› የሚለው ነው፡፡ እሥራኤላዊና ጂፕሲ ይህንን ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን? እላለሁ፡፡ አይሁድ በመላው ዓለም ለ1900 ዓመታት ያህል ተበትነው ሲኖሩ በየአካባቢው ሰው ነበራቸው፤ያውም እንደ ብረት የጠነከረ ማበረሰብ፤ ሀገር ግን አልነበራቸውም፡፡ ሀገር ማለት ሰው ከሆነ አይሁድ ሀገር ፍለጋ ከሺ ዓመታት በላይ መኳተን አልነበረባቸውም፡፡ በአውሮፓ የሚኖሩት ጂፕሲዎች የታወቀ ማኅበረሰብ አላቸው፡፡ ነገር ግን ሀገር የላቸውም፡፡ ሀገር ማለት ሰው ቢሆን ኖሮ ጂፕሲ የሚባል ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ጂፕሲ የሚባል ሀገርም ይኖር ነበር፡፡ ግን የለም፡፡
በአሜሪካ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ‹በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን› የምትባል ሀገር ግን የለቺም፡፡ 1.3 ሚሊዮን የሚደረሱ ግሪኮች በአሜሪካ ይኖራሉ፡፡ ‹የአሜሪካ ግሪኮች› የምትባል ሀገር ግን የለችም፡፡ ‹ግሪክ ሲሠራ አሜሪካ ይኖራል፣ ሲያረጅ ግሪክ ይጦራል› የተባለው ሀገር ሰው ብቻ ስላልሆነ ነው፡፡ 
ሰዎች ተሰብስበው ሀገር ሊመሠርቱ አይችሉም፡፡ በየሀገሩ የተሰበሰቡ ማኅበረሰቦች ‹ኮሙኒቲ› ይባላሉ እንጂ ሀገር አይባሉም፡፡ ሀገር ሀገር ለመሆንና ለመባል ከሰው በተጨማሪ የምትፈልገው ብዙ ነገር አላትና፡፡ ሀገርን ሀገር ለማስባል መሬትም ያስፈልጋል፤ መሬት ሳይኖርህ ሰው ስለሰበሰብክ ብቻ ሀገር ልትሆን አትችልም፡፡ ያውም የእኔ የምትለው፣ የምትሞትለትና የምትለፋለት ታሪካዊ መሬት ያስፈልግሃል፡፡ አይሁድ በ1930 አካባቢ በኡጋንዳ ኡዋሲን ጊሹ (Uasin Gishu County) በተባለ ቦታ እንዲሠፍሩና ሀገር እንዲኖራቸው ታስቦ ነበር፡፡ እንደ ቴዎዶር ኸርዝል ያሉ ታላላቅ የጽዮናዊነት መሪዎችም ለጊዜውም ቢሆን  ተስማምተውበት ነበር፡፡ ብዙኀኑ አይሁድ ግን ‹ሀገር ማለት የሆነ መሬት አይደለም፡፡ ታሪካዊ መሬት ነው› ብለው ተቃወሙትሀገር ማለት የሆነ መሬት ብቻ ቢሆን ለአይሁድ ከዛሬዋ እሥራኤል ይልቅ በአየር ንብረትና በተፈጥሮ ማዕድን፣ ብሎም በአቀማመጥ ኡጋንዳ ትሻላቸው ነበር፡፡ 

ባድሜ ለምትባል ከጦርነቱ በፊት ብዙው ሕዝብ ሰምቷት ለማያውቅ መሬት የተደረገውን ጦርነት የረሳ ሰው ነው ‹ሀገር ማለት ሰው ነው› የሚል፡፡ ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ለባድሜ የተደረገው ጦርነት ለማን የተደረገ ነው ሊባል ነው፡፡ በሄግ ፍርድ ቤት የነበረው ክርክርስ የመሬት ክርክር እንጂ የሰው ክርክር ነበር እንዴ?
ሀገር ማለት ሰው ቢሆን ኖሮ ሰው ስለ ሀገሩ ሲያነሣ ወንዙን፣ ተራራውን፣ ሸለቆውን፣ ሜዳውን፣ ጫካውን እያነሣ ለምን ይዘፍን ነበር ፡፡
‹ያገሬ ተራራ ወንዛ ወንዙ ለምለም
እማማ ኢትዮጵያ ኑሪ ለዘላለም› ለምን ይል ነበረ፡፡
ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ይሄ የኔ ክልል፣ ጎጥና መንደር ነው የሚለው ክርክር ከየት ይመጣ ነበር? ሀገር ማለት ሰው ከሆነ የተለየና የታወቀ የሀገር ድንበርና ካርታ ለምን ያስፈልግ ነበረ? ሰውማ የትም ነው የሚኖረው፡፡ ካርታ አያሻውም፡፡ ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ለምን የአብዛኞቹ ሀገሮች ብሔራዊ መዝሙር ስለ መሬቱና ስለ ድንበሩ ያወራል? ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ለሰው ፓስፖርትና ቪዛ ለም ያስፈልገዋል? ሰው ያለበት ቦታ ሁሉ ሀገሬ ስለሆነ ለምን እንደፈለግኩ ወጥቼ አልገባም? አንድ ሰው ወደ አንድ ሀገር ገባ የሚባለው ወደ መሬቱ ሲገባ እንጂ የሀገሩን ሰው ሲያገኝ ነው እንዴ? ምናልባትም ከአንታርክቲካ በቀር ቪዛ መጠየቅ ያለበት ሀገር አልነበረም፡፡ እርሱ ሰው የለበትምና ‹ሀገር ማለት ሰው ነው› የሚለው አይመለከተውም፡፡ ሀገር ማለት ሰው ከሆነ በሰማይ የሚሄድ አውሮፕላን ‹የአየር ክልሌን ጣሰ› ብሎ መሟገት ምን የሚሉት ሞኝነት ነው? ሰውን አልጣሰ፣ የጣሰው አየር ነው፡፡
ደግሞም አገር ማለት መሬት ብቻ አይደለም፡፡ ያማ ቢሆን ኖሮ አንታርክቲካ ሀገር ይሆን ነበር፡፡ ያማ ቢሆን ኖሮ በዓለም ላይ የሚገኙ ወደ ሃምሳ የሚጠጉ ሰው አልባ ደሴቶች(nonecumene)‹ሀገር› ተብለው በተባበሩት መንግሥታት ይመዘገቡ ነበር፡፡ ሀገር ማለት መሬት ቢሆን ኖሮ መሬት ያለው ሁሉ ሀገር ይኖረው ነበር፡፡ የአሜሪካ ሕንዶች፣ የአውስትራልያ አቦርጅኖች፣ ከጥንት ጀምሮ የሚኖሩበት መሬት አላቸው፡፡ የራሳቸው የሆነ ሀገር ግን የላቸውም፡፡ ደቡብ ሱዳናውያን የራሳቸው የሆነ የሚኖሩበት መሬት ነበራቸው፤ ሀገር ለመሆን ግን መዋጋት ነበረባቸው፡፡ ደቡብ ሱዳኖችን ያን ሁሉ ዘመን ያዋጋቸው የመሬት ጥያቄ ሳይሆን የሀገርነት ጥያቄ ነው፡፡ የራሳቸው ፖለቲካዊ መሬት አግኝተው እንኳን ሀገር ለመሆን ገና እየተሠሩ ነው፡፡ ፍልስጤማውያን ይብዛም ይነስ የሚኖሩበት መሬት አላቸው፡፡ አገር ግን የላቸውም፡፡
አገር ከዚህ ሁሉ በላይ ነው፡፡ ሰው፣ ሰው የኖረበትና ታሪክ የሠራበት መሬት፣ ማኅበረሰብ ከማኅበረሰብ፣ ሰው ከሰው፣ ሰው ከማኅበረሰብ፣ ሰው ከመሬት፣ ሰው ከአራዊት፣ ሰው ከተፈጥሮ፣ ሰው ከወራሪ ጋር የነበረው ትግል፣ ውጊያና ወዳጅነት፤ የተረተው ተረት፣ ያወጋው ወግ፣ የፈጠረው አፈ ታሪክ፣ ያከማቸው ትዝታ፣ ሰው ለመሬቱ፣ ለወገኑና ለእምነቱ የከፈለው መሥዋዕትነት፤ የዘፈነው ዘፈን፣ ያቅራራው ቀረርቶ፣ የፎከረው ፉከራ፤ ያገኘው ድልና የተሸከመው ሽንፈት፤ ያደረሰው በደልና የደረሰበት በደል ይሄ ሁሉ ነው ሀገር፡፡
መገለጫው ቅርስ፣ መዋሐጃው ባህል፣ መታያው ልብስና መዋቢያው ጌጣጌጥ፣ መገናኛው ቋንቋ፣ መዝናኛው ጭፈራ፤ ማስተማሪያው ተረት፣ መክበሪያው ዓመት ባል፣ መጠበቢያው ምግብ፣ መቆዘሚያው እንጉርጉሮ፣ መተከዣው ልቅሶ፣ መተኪያው ልደት፣ ማሳረጊያው ቀብር፤ መገምገሚያው ምግባር፣ ማነወሪያው ነውር፤ መኩሪያ ጀግንነቱ፣ ማፈሪያ ገመናው፤ መደበቂያ ቤቱ፣ መመረሪያ ጫካው፤ ይሄ ሁሉ ነው ሀገር፡፡ ታሽቶ ተገርኝቶ ያመጣው አንድነት፣ ተጣልቶ ተባልቶ ያመጣው ልዩነት፣ እንደ ዘሐ ዘጊ የተጠላለፈው፣ እንደ እግር ሠንሠለት የተቆላለፈው፣ ሲፈተል፣ ሲገመድ፤ ሲባዘት፣ ሲዳውር፤ ሲከካ፣ ሲሰለቅ፤ ሲጣላ፣ ሲታረቅ፤  ሲያውቅና ሲማይም፤ ሲሠለጥንና ሲደኸይ፤ ሲሰፋና ሲጠብ፤ የኖረውና የኖረበት፣ የኖረለትም ነው ሀገር፡፡
ሀገር ትዝታ ነው፡፡ የትም ቦታ ስትሄድ ጠምዶ የሚያመጣህ፡፡ ምንም ሥጋ ብትቆርጥ ከብቱ ትዝ ይልሃል፤ ምንም ቢች ዳር ብትዝናና ወንዙ ትዝ ይልሃል፤ ምን በሽቱ ብትታጠን አፈሩ ይሸትሃል፤ ምን በሥጋጃ ላይ ብትሄድ ጉዝጓዙ ይመጣብሃል፡፡ በኮምፒውተር እየሠራህ ያቦካኸው ጭቃ ይናፍቅሃል፤ በጄት እየበረርክ አህያና በቅሎው ያምርሃል፤ ማንሐተን ተቀምጠህ ሰባተኛ፣ ሎንደን ተቀምጠህ ቂርቆስ፣ ኖርዌይ ሆነህ ጅግጅጋ፣ ካናዳ ሆነህ ሐረር ይወዘውዝሃል፡፡ ሀገር ማለት ትዝታ ነው፡፡
ሀገር ማለት ከምትገልጠው ብታስበው፣ ከምትኖርበት ብትሞትበት፤ ከምትስቅለት ብታለቅስለት የምትመርጥለት ነገር ነው፤ ሀገር ማለት ትተህው ብትሄድ ትቶህ የማይሄድ፣ በራቅከው ቁጥር ልብህ ውስጥ የሚቀር፣ ባወቅከው ቁጥር የምትንገበገብለት፤ በተረዳኸው ቁጥር የምትሳሳለት፣ አንተን እርሱ ውስጥ እንደምታገኘው ሁሉ እርሱንም አንተ ውስጥ የምታገኘው፤ የተሠራህበት ውሑድ፤ የተቀረጽክበት ማንነት ነው ሀገር፡፡
ሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ዘመድ የሌለው ሰው ወደ ሀገሩ ለመምጣት ባልናፈቀ ነበር፡፡ ሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ዘመዶቹ ሁሉ ከእርሱ ጋር ውጭ የሚኖሩለት ሰው ‹ሀገሬን ሀገሬን› እያለ መከራ ባላየ ነበር፡፡ ሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ሰዎች በየዘመናቱ የበደሉት ሰው ሀገሬ በደለችኝ ባለ ነበር፡፡ ሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ሰው ስለ ሀገሩ ሲያስብ ተራራውና ወንዙ፣ አዕዋፉና አራዊቱ፣ ማሳውና ቀየው ለምን ትዝ ይለው ነበር፡፡ በሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ያሸነፈ አትሌት፣ ድል ያደረገ ኳስ ተጨዋች ባንዴራው ሲሰቀል ለምን ያለቅስ ነበር?
‹አዙረሀ አዙረህ ሀገሬ መልሰኝ
በሹም ታዘዘ አፈር አታልብሰኝ› ብሎ ለምን ያንጎራጉር ነበር፡፡ ዐጽሙ በአፈሩ እንዲያርፍ ለምን ይናዘዝ ነበር፡፡ ለምን ሙሾውን፣ የሠርግ ዘፈኑን፣ ወጉን ማዕረጉን ይፈልገው ነበር፡፡
ሀገር በአርምሞ እንጂ በንግግር፣ በተግባር እንጂ በዝርዝር ሊናገሩለት የማይቻል ነገር ነው፡፡ ውጥንቅጥ ሰበዞች የሰፉት ሞሰብ፣ዓይነተ ብዙ  ድርና ማጎች የሸመኑት ጋቢ፣ ልዩ ልዩ ቅመሞች የሠሩት ወጥ፣ ብዙ ገባሮች የፈጠሩት ዓባይ፣ ብዙ ትውልዶች የከመሩት ተራራ፣ ከአራቱ አቅጣጫ ተሰብስቦ በአንድ ወፍጮ የተፈጨ እህል፣ ከየአበባው ተቀስሞ በአንድ ቀፎ የተሠራ ማር፣  ከየእህሉ ወጥቶ በአንድ ማድጋ የተጠመቀ ጠላ፣ ከየ እንጨቱ ተለቅሞ በአንድ ጽንሐ የታጠነ ዕጣን ነው ሀገር፡፡
ሀገር ማለት ሰው ነው? እስኪ ሙት በለኝ

Wednesday, 30 March 2016

መጻጒዕ (ዮሐ. ፭፥፲፫)

መጻጒዕ (ዮሐ. ፭፥፲፫)

በዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ
መጋቢት 18 ቀን 2008 ዓ.ም
የነፍሳችንን ማሠሪያ እንዲፈታና ዓለሙን ከተያዘት የኃጢአት በሽታ እንዲያድን ለቤዛነት፤ እንዲሁም የመልካምና የበጎ ምግባራት ሁሉ አብነት ሆኖ በሥራና በቃል እንዲያስተምር ወዳለንባት ምድር በሥጋ ቅድስት ድንግል ማርያም ወረደ ተወለደ:: ቤተክርስቲያናችን በአራተኛው የቢይ ጾም ሳምንት እግዚአ ለሰንበት ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ"ቤተሳይዳ" የፈጸመውን ተአምራት መጻጒዕ ብላ ሰይማ ስበዋለች። በዕለቱም በዮሐንስ ወንጌል አምስተኛው ምዕራፍ የተቀመጠው ታሪክ በልዩ ልዩ ኅብረ ምሥጢር ተገናዝቦ በሊቃውንቱ ይነገራል።
መጻጒዕ ለ፴፰ ዓመት በአልጋው ላይ ሆኖ ምሕረትን ሲጠባበቅባት የኖረባት ስፍራን "ቤተ ሳይዳ"ትባላለች።በቅዱስ መጽሐፍ የሥፍራዎችን ስያሜ ስንመረምር በይሁዳና በገሊላ ለሚገኙ ሁለት የተለያዩ ግዛቶች በተመሳሳይ አገባብ "ቤተ ሳይዳ" የሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸው እናገኛለን:: በሁለቱ አውራጃዎች (ይሁዳና ገሊላ) ሥር "ቤተ ሳይዳ" በሚል የተጠቀሱት ሥፍራዎች በትርጉም ፊደላቱ ያለአገባብ መሰደር ከወለዱት የሞክሼነት ስህተት (Metathetical Corruption) የተገኘ ክፍተት እንጂ ቦታዎቹስ በጥንታዊቷ የእስራኤል ግዛት ከመገኘታቸው ውጪ ምንም የሚያገናኛቸው መልክአ ምድራዊ ኩነት የለም "ጲላጦስ ጰንጤናዊ መልአከ ይሁዳ ወሄሮድስ ንጉሠ ገሊላ" (ሉቃ· ፫፥፩) እንዲል የግዛቶቹ አገረ ገዢዎችም እንዲሁ ለየቅል ነበሩ:: አገባቡን አካቶ ለመረዳት እንዲያመች የሁለቱንም መካናት ከተማና መንደር ለይቶ ማወቁ ተገቢ ነው::
 በይሁዳ ግዛት ከሚገኙና እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ገቢረ ተአምራቱን ከፈጸመባቸው ሥፍራዎች ፦ ቤተሳይዳ(Bethesda) ፣ ቢታኒያ ፣ ቤተልሔም ፣ ቤተፋጌ ፣ ኢያሪኮ ፣ ጌቴሰማኒ ፣ ሊቶስጥሮስ(ገታ) ፣ ኤማሁስ፣ ቀራንዮ(ጎልጎታ) ፣ ኢየሩሳሌም እና የደብረዘይት ተራራ የሚጠቀሱ ሲሆን፤
 በገሊላ አውራጃ ደግሞ ፦ ቤተሳይዳ(Bethsaida) ፣ ሄኖን ፣ ቃና፣ ቅፍርናሆም፣ ኮራዚ፣ ጌንሳሬጥ፣ ደብረታቦር፣ ናይን እና የገሊላ ባህር ተገልጸው እናገኛልን::
እነዚህኑ "ቤተ ሳይዳ" ዘይሁዳና "ቤተ ሳይዳ" ዘገሊላ አካባቢያዊ መገኛ ለይተው የሚያመለክቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማጣቀሻዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም በይሁዳ ኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ ያለችዋን "ወቦ ውስተ ኢየሩሳሌም ምጥማቃት ዘጵሩጳጥቄ ቅልንብትራ (ዘውእቱ ቀላየ አባግዕ ብሂል) ወይቤልዋ ስማ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ወባቲ ኃምስቱ ሕዋራት" (ዮሐ ·፭፥፪) ብሎ የገለጠበትንና በገሊላ ስለምትገኘዋ ደግሞ "ወሖሩ እሙንቱሂ ኀበ ፊልጶስ ዘቤተ ሳይዳ ዘገሊላ" (ዮሐ ፲፪፥፳፩) የሚለው ማየት ይቻላል::
በሌላ መልኩ አንዳንዶች ደግሞ በሁለቱም ሥፍራዎች ክርስቶስ አምላካችን ለፈውስ ሥራ ያገኛቸውን ሰዎች አይተው ተመሳሳይ ቦታ ሲመስላቸው ይታያል ይህም "መጻጉዕ" እና "ዕውር" የነበሩትን ማዳኑ ነው:: ይኸውም "ወቦ ውስተ ኢየሩሳሌም ምጥማቃት ዘጵሩጳጥቄ ቅልንብትራ (ዘውእቱ ቀላየ አባግዕ) ብሂል ወይቤልዋ ስማ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ወባቲ ኃምስቱ ሕዋራት …በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። (ዮሐ ·፭፥፪) የተባለውና "ወበጽሑ ቤተ ሳይዳ ወአምጽኡ ኀቤሁ ዕውረ ወአስተብቁዕዎ ይግስሶ … ወደ ቤተ ሳይዳም መጡ። ዕውርም አመጡለት፥ እንዲዳስሰውም ለመኑት።" (ማር· ፰፥፳፪) የሚለው ነው::
፨ "ቤተ ሳይዳ" ዘገሊላ (Bethsaida) በትርጉም "የማጥመጃ ቤት" የሚል ፍቺ ያለው በተለይ ከቅዱሳን ሐዋርያቱ አሳ አጥማጆቹ ወንድማማቾችና ቅዱስ ፊልጶስ የነበሩባት መንደር ናት " ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ።" (ዮሐ·፩፡፵፭) እንዲል።
 "ቤተ ሳይዳ" ዘይሁዳ (Bethesda or Bethchasday) የመጠመቂያ ሥፍራ ስትሆን በግሪኩ ቤተ ዛታ ( Βηθζαθά) ወይም ቅልንብትራ (κολυμβήθρα) እንዲሁም በእብራይስጡና በአረማይኩ "ቤተ`ስዳ" (Beth hesda ( בית חסד /חסדא )) በማለት "ከማጥመጃ ቤት" ለይቶ "ቤተ ሣሕል / የምሕረት ቤት" የሚል ትርጉም ያለው መጠመቂያና መላለሻ መንገድ መሆንዋን ያመለክተናል። የግእዙ መጽሐፍ ቅዱሳችንም የቦታውን ስያሜ ከእብራይስጡ "የአንድዮሽ ትርጉም" ስያሜ (ቤተ ሳይዳ) ጋር በግሪኩ ያለውንም መጠሪያ ጭምር አካቶ ቅልንብትራ ( κολυμβήθρα / kolumbethra) ሲል እናገኘዋለን::
ቤተ ሳይዳ ዘይሁዳ ባለ አምስት በር መመላለሻ አምስት ዓይነት ድውያን ፈውስን ከማየ ጥምቀቱ ሲጠባበቁ የሚኖሩባት በአምስተኛው የዮሐንስ ወንጌል ተጽ ያለ የጌታችን ማዳን የተገለጠባት ሥፍራ ናት። "እስመ ኦሪት መንፈቀ ፍጻሜ ወኅዳጠ መክፈልት" እንዲላት መልአከ እግዚአብሔር ለቀድሶተ ማይ ወርዶ ውኃውን ሲያናውጥ ቀድሞ የገባ የሚነጻባት በዕለቱ ከአንድ በቀር ለሌላው ፈውስ የማይደገምባት ቦታ ናት ።
ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል የድኅነት ተስፈኛ ሆኖ የኖረ መጻጉዕን በአልጋው ተኝቶ ሳለ ደዌው እንደጠናበት ፈውስ እንደዘገየበት አይቶ "መፈውስ ወማሕየዊ" ጌታችን ቀርቦ አዎን እንዲለው እያወቀ ያንን በሽተኛ "ትፈቅድኑ ትሕየው? … ባድንህ ፈቃድህ ነውን?" አለው። ብወዳችሁ አላዋቂ የሆነ የእናንተን ሥጋ ተዋሕጄ መጣሁላችሁ ሲለን ("አኮ ኢያእሚሮ ኅቡአተ አላ ከመ የሀብ መካነ ለጥንተ ትስብዕቱ ዘኢየአምር ኅቡአተ") እንዲል:: የሚገርመው ቅዱስ ጳውሎስ በእብራውያን መልእክቱ ምዕራፍ ፬ ቁጥር ፲፪ ላይ "የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።" ብሎ የመሰከረለት ጌታችን ፈውስን በመጠባበቅ ከመዳን ውጪ ሌላ ዓላማ ያልነበረውን ይህን ሰው ዓይቶ ፈቃዱን እያወቀ ግን ፍቀድልኝና ላድንህ አለው። " ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው? "(መክ ፮፥፲፪) እንዲል የሚያስፈልገንን ሳንነግረው የሚያውቅ የሚሰጠንም ከእርሱ ከፈጣሪው ውጪ በእውነት ማን አለ? መጻጒዕ ግን ኋላ የሚክድ ነውና "በሰንበት ላይ ያመጸ ፣ ራሱን ከአብ የሚያስተካክል ፣ ቤተመቅደሱን አፍርሱት ያለ መች አድነኝ ብየው ሳልፈቅድለት ያዳነኝና አልጋ ያሸከመኝ ነውኮ" ብሎ በዕለተ ዓርብ የሚከስበትን ሲያሳጣውና ለኋላ ጥፋቱ የገዛ ኅሊናው እንዲቀጣው ፈቃዱን ጠየቀው። "አልብየ ሰብእ" ሰው የሌለኝ ሆኖ እንጂ ያንንማ ማን ይጠላል በሚል ጉጉቱን ከወዳጅ አልባነቱ ጋር ድኅነትን ፈቅዶ ገለጠ። እስከ ሁከተ ማይ ሳያቆየው "ተንሥእ ንሣእ ዓራተከ ወሑር … ተንስና አልጋህን አንስተህ ሂድ" አለው ወዲያው አፈፍ ብሎ በፍጥነት ያን ሁሉ ዘመን የተሸከመች ጠንካራ አልጋ ተሸክሟት ሄደ።
ይህች "ቤተ ሳይዳ" ዘይሁዳ ምሣሌቷ ብዙ ኅብር ያለው ነው። ለአብነትም ያህል ምሳሌ፦
፩·ውኃው የቤተ አይሁድ ምሳሌ አምስት መመላለሻ የሕግጋተ ኦሪት የአምስቱ መፃሕፍተ ሙሴ በነዚያ ታጥረው ለመኖራቸው። ቀድሞ የገባባት አንዱ እንዲድን እነሱም አንድነት ቤተ እስራኤል ተሰኝተው ለመኖራቸው ምሳሌ ነው።
፪·በሌላ አገባብ
 በዚያ ውኀውን ለማወክ የወረደው መልአክ = ቀሳውስት(ካህናት) "ለቀድሶተ ማየ ጥምቀት" የመውረዳቸው ምሳሌ ነው።
 የመጠመቂያ ውኀው = የማየ ጥምቀት ምሳሌ ሲሆን
 በቤተ ሳይዳ ያለው አምስቱ እርከን(መመላለሻ) =የአምስቱ አእማደ ምስጢር በዚያ ሊያምኑ ያሉ ተስፈኞችና ያመኑባትም ልጅነትን ያገኙባታልና።
 አምስቱ ዓይነት ድውያንም የአምስቱ ጾታ ምዕመናን ከነ ፈተናቸው የተመሳጠረበት ምሳሌ ነው (አእሩግ=በፍቅረ ነዋይ፣ ወራዙት=በዝሙት፣ አንስት=በትውዝፍት በምንዝር ጌጥ፣ ካህናት=በትእቢት አእምሯችን ረቂቅ መዓረጋችን ምጡቅ እያሉ፣ መነኮሳት=በስስት ምግብን በፈለጉት ጊዜ ባያገኙት ይልቁንም አጽንኦ በአት እየፈቱ በአንሰሐስሖ ዘበከንቱ ይፈትናቸዋል) ምሳሌ ሆኖ ይነገራል።
፫·ለአዲስ ኪዳን ድኅነተ ነፍስ ምስጢራዊ ምሳሌ አገባብም አለው፤
 ቤተሳይዳ የበጎች በር በመባልዋ እና በኦሪቱ በጎች ወደ ቤተ መቅደስ ወጥተው ለመስዋዕት ከመቅረባቸው አስቀድሞ የሚታጠቡበት ውኀ ያለበት በመሆኑ ለአዲስ ኪዳንም የመንፈስ ቅዱስ ልጅነት የሚገኝባትን ወደ አማናዊ መስዋዕት ቅዱስ ቁርባን የምታደርስ የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ
 አምስቱን መመላለሻ የምታደርስ ደግሞ ወደ ፍፃሜ ሕግ ፍቅረ ቢጽና ፍቅረ እግዚአብሔር አልፎም ፍጽምት ወደሆነች ወደ ሕግጋተ ወንጌልም የምታደርስ የአምስቱ ብኄረ ኦሪት መፃሕፍተ ሙሴ ምሳሌ ያደርጋቸዋል።
 ለሁከተ ማይ የወረደው መልአክ የመድኃኒታችን የክርስቶስ ምሳሌ ነው
 ከአንድ ብቻ በቀር ሕሙም በአንድ ዕለት አለመዳኑ በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን ጥላ ሥር አምነው ያሉ ምዕመናንና ምዕመናት ብቻ ድኅነተ ነፍስ እዳላቸው ያሳያል።
 የውኀው መናወጽ የሰቃልያነ ክርስቶስ "ሁከተ አይሁድ" ምሳሌ ጥንቱን "ስቅሎ ስቅሎ " የሚለው ያ ቁጣ የዕለተ ዓርብ መድኃኒት መገኛ ነውና።
እስኪ ደግሞ በማጠቃለያው ወደ መጻጒዕ ታሪክ እንመለስና ጥቂት ፍሬ ነገር ለሕይወታችን እንስማ።
ቀድሞ በ`ቤተ ሳይዳ` እያለ የነበረበትን ያንን ሁሉ ጭንቅ ኋላ በሊቶስጥሮስ የፍርድ ገታ ቆሞ በረሳ ጊዜ " ታዲያ ቢያድነኝ በከንቱ መች ሆነና የገዛ አልጋዬን ትቼለት የመጣሁ ለመዳኔ ዋጋ የከፈልኩበት አይደለምን?" እንኳ እንዳይል ያለ ተረፈ ደዌ አንስቶት ያለህን ይዘህ ሂድ እኔ ከአንተ አንዳች አልሻም ባሰኘ ቃል ሸኝቶታል። ግን ታዲያ ይህ ምስኪን መጻጒዕ "ሰው የለኝም" ብሎ የደረሰለትን ሰው ረሳ ማን እንደሆነ እንኳ አላወቀም። ወንጌላዊውም "ዘሐይወ ኢያእመረ ዘአሕየዎ …የዳነው ያዳነውን አላወቀውም" ( ዮሐ.፭፥፲፫) ይለዋል። ያዳነው ማን እንደሆነ ሲጠየቅ ለምሥጋና ያይደለ ለክስ ነበር ስሙን የፈለገው። "ከሚጣፍጠውም ምግቤ ሆዱን ሞላ፥ እኔንም ጣለኝ።" ተብሎ ለናቡከደነፆር በነቢዩ እንደተነገረ ያለ ነው (ኤር.፶፩፥፴፬ ) በአገራችንም ካለው ብሂለ አበው "ታሞ የተነሳ ፈጣሪውን ረሳ" የሚለው እንደነዚህ ያሉትን በሚገባ ለመግለጽ የተነገረ ነው። ሊቀ ነቢያት ሙሴን በዘዳግም ፲ ቁጥር ፳፩ ላይ እንዲህ ይላል "ዓይኖችህ ያዩትን እነዚህን ታላላቆች የሚያስፈሩትንም ነገሮች ያደረገልህ እርሱ ክብርህ ነው፥ እርሱም አምላክህ ነው።" ነገር ግን ይህን ሁሉ ያደረገውን አምላክ ብዙዎች የነበሩ "ህዝበ እስራኤል" ረስተው አሳዝነውት በምድረበዳ በከንቱ ወድቀው ቀሩ ..... ዛሬም ከደዌው :ከማጣቱ :ከችግሩ: ከሥጋ ኑሮ ጉድለቱ ዳግመኛ ለመታረቅ እንደ መጻጒዕ አምላኩን ያልረሳ ማነው? ተአምራቱን አይቶ ቃሉን ሰምቶ አምላኩን ያስታወሰስ ማነው " ቃሉን ያይና ይሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ምክር የቆመ ማን ነውና? ቃሉንስ ያደመጠ የሰማስ ማን ነው?" (ኤር. ፳፫፥፲፰) ማንም። ጌታችን ባስተማረው ማሕየዊ ቃሉ ላይ እንኳ ሳይቀር ያመጹትን አይሁድ እስኪ ተመልከቱ " ገንዘብንም የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው ያፌዙበት ነበር።" ሉቃ ፲፮፥፲፬ እኛንም ቢሆን ከአዳም እስራት ነፃ ያደረገንን አምላክ ውለታ ዘንግተን በቃሉ የምናፌዝ ሁላችንን ወደ ልባችን እንድንመለስ ነቢዩ እንዲህ ሲል ይመክረናል "እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ " እንዲል ( ኢሳ· ፳፰፥፳፪ )።
በፍፃሜ ሕይወቱ በአውደ ምኩናን የሀሰት ክስ የቀረበበትን ይህን የእውነትና የሕይወት ጌታ ቀድሞ ወደ መጠመቂያው እንኳ ለመቅረብ አቅም ያልነበረው ዛሬ ግን አልጋ ለመሸከም በበቃውና ያለ ተረፈ ደዌ በጸናው ኃይሉ የጌታውን ጉንጮች በጥፊ የመምታት ጉልበትና ድፍረት አገኘ። "ዘተሰብሐ ውስተ ገጸ ሙሴ በትስብእቱ ተጸፍአ ገጾ ወተቀስፈ ዘባኖ በእንቲአነ ከመ ይፈጽም ስምዓ ነቢይ ዘይብል መጠውኩ ዘባንየ ለመቅሰፍት ወመላትሕየ ለጽፍአት… በገጹ ነፀብራቅ የሙሴን ፊት ያበራ እርሱ በነቢዩ ጀርባዬን ለግርፋት ጉንጮቼንም ለጽፍአት ሰጠሁ ተብሎ የተነገረውን ለመፈጸም ለእኛ ሲል ፊቱን በጥፊ ተመታ ጀርባውንም ተገረፈ "እንዲል (ሰይፈ ሥላሴ) አምላከ ምሕረት የክብር ጌታ ቀድሞ "ዑቅ ኢትአብስ ዳግመ እንከ ከመ ዘየአኪ ኢይርከብከ … ከዚህ የጠናው "ስለ ደዌ ሥጋ ፈንታ ደዌ ነፍስ" እንዳያገኝህ ሁለተኛ እንዳትበድል" (ቁ ፲፬) ያለውን ዘንግቶ ደዌ ዘኃጢአትን ጠርቶ ተወዳጃት፤ በዕለተ ዓርብ የጌታውን ጉንጮች የጸፉች እጁም ደርቃ `ሰላ` ቀርታለች አንዱ ሊቅ ይህን አልሰማ ባይ መጻጒዕ እና ይቅር ባይ አምላኩን እያደነቀ በጉባዔ ቃናው ይህን ተናገረ
" ይትዐረቅ ምስለ ብእሲት ደዌሁ
ሠላሳ አዝማነ እስመ ነበረት ምስሌሁ"
(መጻጒዕ ከሚስቱ ከደዌ ጋር ይታረቅ ፤ ሠላሳ ዓመታት ከእርሱ ጋር ኑራለችና)
አብረው አያሌ ዓመታት የኖሩ ባልና ሚስት ሲፋቱ ተነፋፍቀው መለያየቱ እምቢኝ እንደሚላቸውና እንደሚታረቁ ሁሉ ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ተብሎ ሳለ ጌታውን ጸፍቶ መጻጒዕም ዳግመኛ ወደ ፴፰ ዓመት "የአልጋ ወዳጁ" ደዌ መመለሱን የቅኔው ምስጢር ያስተምረናል። እንግዲህ እኛም በኃጢአት ከሚመጣ ደዌ ተጠብቀን በአባታዊ ምሕረቱ የሚጠብቀንን ቸሩ አምላካችንን እያመሰገንን በቤቱ እንድንጸና መጻጒዕን "ተነሳ" እንዳለው እኛንም ከወደቅንበት መዘንጋት፣ ኃጢአት በንስእንዲያነሳንና ዳግም ከመበደልም እንዲጠብቀን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን። አሜን

ምኵራብ

ምኵራብ

ቀሲስ ኃይለኢየሱስ ተመስገን

መጋቢት 10 ቀን 2008 ዓ.ም
ከሁሉ አስቀድሞ ሃይማኖትን መመስከር እንዲገባ ቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት አካል ዘእምአካል ባህርይ ዘእምባህርይ የተወለደ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አካላዊ ቃል ድህረ ዓለም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መለወጥ ሳያገኛት ዘር ምክንያት ሳይሆን ከስጋዋ ስጋ ከነፍነፍስ ነስቶ የተወለደ ወልደ እግዚአብሔር ወልደ ማርያም በተዋህዶ ከበረ“ይደልዎነ ንምን ከመ ቦቱ ለወልደ እግዚአብሔር ክልኤቱ ልደታት ቀዳማዊ ልደቱ እም እግዚአብሔር አብ እምቅድመሉ መዋዕል ወዳግማዊ ልደቱ እም እግእዝትነ ቅድስት ድንግል ማርያም በደራዊ መዋዕል”ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ ፴፬ ቁጥር  ክፍል  ብለን በማመን እንደ አባቶቻችን ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን ስለ ምኵራብ እንማራለን የምናነበውን ለበረከት ያድርግልን አሜን።
የእስራኤል ልጆች መቅደስ(Temple) እና ምኵራብ የሚባሉ ሁለት መንፈሳዊ መገናኛዎች ነበሩአቸው፤ ምራብ [በጽርዕ (Synagogue/ συναγωγή)፡ በዕብራይስጥ (Beyth Kenesset/בית כנסתይባላል። መቅደስ የሚባለው በኢየሩሳሌም ብቻ የሚገኝ ስለ ኃጢአት ስለ ምስጋና መሥዋዕት የሚቀርብበት የብሉይ ኪዳን ማዕከል ነው። ምራብ የቦታ ወሰን የሌለው በየአቅራቢያው የሚገኝ አጥቢያ ቤተ ጸሎት ነው።የምኵራብ መታነፅ ከባቢልን ምርኮ (exile in Babylon 538 A.D.) ጋር የተያያዘ ታሪክ አለው። በባቢሎን ምርኮ በባእድ ሀገር በዚያው ባሉበት ስርተ አምልኮ ለመፈፀም ዳግመኛም ይህ ሁሉ መከራ በአባቶቻችን የተደረገባቸው ቤተመቅደስን ባይሰሩ ነው እኛ ሚጠት የተደረገልን እንደሆነ ቤቱን እንሰራለን በሚል ዋናውን ቤተ መቅደስም ሆነ ብዙ ምኵራባት ሰርተዋል። 10 አባወራዎች ባሉበትም ምኵራብ እንዲሰራ ህጋቸው ያዝ ነበር። በምኵራብም የሚደረገው መንፈሳዊ አገልግልት የብይ ኪዳን መጻሕፍትን ማንበብ መስማትና መተርጎም ንዑሳን በዓላትንም ማክበር ነበር።ማንኛውም እስራኤላዊ በዓመት ሦስት ጊዜ ለበይት በዓላት በኢየሩሳሌም መቅደስ ተገኝቶ አምልኮን መፈጸም ግዴታው ነበር። በምኵራብ ግን በየዕለቱ እየተገኙ ቅዱሳት መጻሕፍትን በንባብ በትርጓሜ ይሰማሉ።
በቃል መነገሩ በልብ መታሰቡ ከፍ ከፍ ይበልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራብ ተገኝቶ እንዳስተማረ ለመግለጥ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅደስ ያሬድ ማሕሌታዊ የዓቢይ ጾም ሦስተኛውን ሰንበት ምኵራብ ብሎ ሰይሞታል። ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ፡- “ ቦኦ ኢየሱስ ምኲራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋት አበድር እመስት አነ ውእቱ እግዚአ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት ኢትግበሩ ቤተ አቡ ቤተ ምስያጥ ቤትየ ቤተ ጸሎት ትሰመይ . . .”ትርጓሜው፡- “ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ። የሃይማኖትን ቃል አስተማረ። ከመሥዋዕትም ምጽዋትን እወዳለሁ አላቸው። የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷ እኔ ነኝ አላቸው የአባቴ ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል። ምኵራብ ገብቶ ተቆጣቸው ዝም ይሉ ዘንድ ትምህርቱን የቃሉን ሞገስ፣ የነገሩን መወደድ፣ የአፉን ለዛ አደነቁ” በማለት ቅደስ ያሬድ ዘምሯል።
ቅዱስ ያሬድ በሰዓታት በወራት እና በዘመናት የተከፋፈሉ ድንቅ ምሥጢር የያዙ መዝሙራትን(ምስጋና) ከብሉያትና ከሐዲሳት ለቤተክርስቲያን እንደ ንብ ቀስሞ እንደ ሰምና ወርቅ አስማምቶ የአገልግሎት ሥርዓትን የሠራ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ነው።ለምኵራብ የሚሆነውንም ዝማሬ ከዮሐ 2፡12-25 ላይ ወስዶ አመስጥሮ እስማምቶ ጾመ ድጓ በተባለ ጽሐፉ አዘጋጅቶልናል። ይህንን የመጽሐፍ ክፍል እንደሚከተለው እናየዋለን።
ቁ.12 ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀመዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፣ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ” ከቃና ዘገሊላው የዶኪማስ ቤት ሰርግ ውሃውን ወይን አድርጎ ታምራቱን ካሳየ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ከእናቱና ከወንድሞቹ ደቀመዛሙርት ጋር ሄደ በዚያም ጥቂት ቀን (11 ቀን ይላል በወንጌል አንድምታ) ተቀመጡ። ቁ.13 የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳም ወጣ።” ይህም የመጀመሪያ ፋሲካ ነው ጌታ የተሰቀለው በአራተኛው ነውበምስጢርም ኢየሩሳሌም ወጣ መባሉ ጌታ ከሕይት ወደመስቀል ምእመናንም ወደ ሕይት የሚሄዱበት ዘምን በደረሰ ጊዜ ጌታ ገረ ሰላም ኢየሩሳም ወደተባለ መስቀል ሄደ ማለት ነውቁ.14 በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤” ለስም አጠራሩ የክብር ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራብ በተገኘ ጊዜ በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው ከሚነበበው እና ከሚተረጎመው ከሚፀለየውም ይልቅ የሚሸጠውና የሚለውጠው በዝቶ ተመለከተ ውንብድና ቢሉ ፈሪሳዊያን የሚያንፀባርቅ እና የሚያንሽዋሻ ልብስ ለብሰው በውጭ ከብቱን ያስደነብሩና ወደምኵራብ ያስገቡታል ከዚያም ከል የገባ አይነጣም ቤተመቅደስ የገባ አይወጣም እያሉ የህዝቡን ገንዘብ ይቀሙታል።መለወጥ ቢሉ ህዝቡ መባ ሊያስገቡ ቀይ ወርቅ ይዘው ሲመጡ እግዚአብሔርማ የሚሻው ነጭ ወርቅ እንጅ ቀይ ወርቅ ነውን ይሉታል እነርሱም በትህትና እውነት ነው ብናጣ ነው እንጅ ለእግዚአብሔርማ ንፁህ ማቅረብ ይገባል ይላሉ ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም ሁለት ቀይ ወርቅ ብታመጡ ባንድ ነጭ ወርቅ እንለውጣችኋለን እያሉ ይበዘብዟቸዋል።ከብቱን ከስቷል ጥፍሩ ዘርዝሯል ፀጉሩ አሯል ለእግዚአብሔርማ የሰባውን ማቅረብ ይገባል ይሏቸዋል እነርሱም በትህትና እውነት ነው በመንገድ ደክሞብን ከስቶብን እንጅ ለእግዚአብሔርማ የሰባውን ማቅረብ ይገባል ይላሉ ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም ሁለት የከሳ ከብት ብታመጡ ባንድ የሰባ እንለውጣችኋለን ይሏቸዋል መሸጥም ቢሉ የከሳውን ከብት አወፍረው አድልበው ይሸጡ ነበር
ቁ.15-16 የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ። የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው፡” በቤተ ፀሎት ይህን ያልተገባ ነገር ሲፈፅሙም የገመድ ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው ይላል ይህንም ጅራፍ ሐዋርያት አዘጋጅተው ሰጥተውታል የጭፍራውን ለአለቃው መስጠት ልማድ ንውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ገበያውን ፈታ። ለሰውነታቸው ቤዛ የሚሆናቸው ስለሆነም የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ በትር አይችሉምና ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ አላቸው። የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው። በተአምራትም ገንዘብ ገንዘባቸውን ለይቶ ከዛፍ ላይ እንደሰፈረ ንብ ከቃ ከቃቸው ላይ አስቀምጦላቸዋል። ቁ.17 ደቀ መዛሙርቱም የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደተጻፈ አሰቡ።ነቢየ እግዚአብሄር ቅዱስ ዳዊት በመዝ 68፡9 በቤተ መቅደስ ስዕለ ፀሀይ አቁመውበት መስዋእተ እሪያ ሰውተውበት ገበያ አድርገውት ሲሸጡበት ሲለውጡበት በመንፈሰ ትንቢት ተመልክቶ ለቤተ እግዚአብሄር የቀናውን ቅናት እንደ እሳት አቃጠለኝ ይላል።
እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕየ ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ። ትርጉም የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና ነፍሴን በጾም አስመረርኋት። 
ይህ ትንቢት ለጊዜው ለመቃቢስ ፍፃሜው ለጌታ የተነገረ ነው። በመቃቢስ ጊዜ አንያኮስ በቤተመቅደሱ አምልኮ ፀሀይ አግብቶ እሪያ ሰውቶ ነበርና፤መቃቢስ ያንን አጥፍቶ ለቤተመቅደሱ የቀናውን ቅንዓት ያመለክታል። በልዑል እግዚአብሔር ላይ በስህተትም ሆነ በድፍረት የሚቀርብ ተግዳሮት በቅዱሳንም ይደርሳል። ልዑል እግዚአብሔር ባህርዩ ደርሶ የሚገዳደር የለም እርሱ ነገሥታት የማይነሣሡበት መኳንንትም የማይበረታቱበት አምላከ አማልክት ወንጉሠ ነገሥት ነው። ነገር ግን የአምልኮቱ መገለጫ በሆኑት በቤተመቅደስ ውስጥ ባሉት ታቦታት፣ንዋያተ ቅደሳት፣በዓላትና ሥርዓቶች እንዲሁም እርሱ የላካቸውን ቅዱሳን መግፋት መገዳደር ጌታ እግዚአብሔርን መገዳደር ነው። ነቢየ እግዚአብሄር በቤተመቅደስ ገበያ አቁመው የሚገዳደሩትን ባየሁ ጊዜ ተግዳሮታቸው በእኔ ላይ ወደቀ ነፍሴንም በጾም አስመረርኋት ይላል። በደብተራ ኦሪት ሁለት እጓላተ ለህም አቁመው እንደተገዳደሩት፣መና ከደመና አውርዶ ቢመግባቸው ምንት ጣዕሙ ለዝ መና ብለው እንደተፈታተኑት ፣ በኋላም ወልደ እጓለ እምሕያው ስጋየን የበላ ደሜን የጠጣ የዘላለም ህይወት አለው ቢላቸው እፎ ይክል ዝንቱ የሀበነ ሥጋሁ ንብላዕ ብለው እንደተገዳደሩት በመንፈሰ ትንቢት ተመልክቶ ሰውነቴን በርሃብ በቀጠና አደከምኩዋት እያለ ነቢየ እግዚአብሔር የተናገረውን ደቀመዛሙርቱ አስበው እነሱም ለቤቱ ቀኑ በዚህ ዘመን እኛም ለቤተክርስቲያን ቅናት ሊኖረን ይገባል ለክብሩ መቅናት ለገዳማቱ ለአብነት ትምህርት ቤቱ መፈታት ለሊቃውንቱ መታረዝ ልቡናችን ሊቃጠል ይገባል። ኢየሱስም መልሶ ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው ስለዚህ አይሁድ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፣ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን አሉት። እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተመቅደስ ይል ነበር። ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ይህን እንደተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ።” ቁ.19 እና 20 በ46ቱ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት የተነገረውን ልደቱን ሞቱን በሶስተኛው ቀን መነሳቱን ሁሉ ስለ ሰውነቱ አስረዳቸው። እሠራዋለሁ አላለም አነሣዋለሁ እንጂ። በዚህም የሞቱንና የትንሣኤውን ነገር ገለጠ።
አንጽሆተ ቤተመቅደስ
ይህም ቀን የማንጻት ቀን አንጽሆተ ቤተመቅደስ ይባላል።ኦሪት ወንጌልን፣ ምኵራብ ቤተክርስቲያንን አስገኝተዋል ጌም የበግ የፍየል መስዋእት መቅረቱን ለቤዛ ዓለም መምጣቱን አስተማሯቸዋል አስጠንቅቋቸዋል። ምኵራብ ሁሉ የማይገባባት ነበረች በመጽሐፈ ነህምያ ምዕ 13፡1 “አሞናውያንና ሞዓባውያንም ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ለዘላለም እንዳይገቡ የሚል በዚያ ተገኘ።” ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የማይመረጥባት አንተ አይሁዳ አንተ ሮማዊ የማትል አንዲትት ቤተመቅደስን ሰጠን
ምኵራብ /ቤተ መቅደስ/ የሰውልጅ ምሳሌ ነው ምኵራብ የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው። የሰው ልጅም የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው ሸቀጡም የኃጢአት ምሳሌ ነው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ሰውነትን ስለማንፃት እና እራስን ከሸቀጥ ስለማራገፍ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ያስተማረውን ማሰብ ያስፈልጋል እኛም የህያው አምላክ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተመቅደስ ነንና ሰውነታችን ሽያጭ የሚፀናበት እንዳይሆን ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል
1ኛቆሮ ምዕራፍ 3-17 “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።”
1ኛቆሮ ምዕራፍ 6-20 ላይ “ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።”
2ኛቆሮ ምዕራፍ 2-17 የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።
በቅዳሴ ያዕቆብ ዘስሩግ “ተንስኡ በፍርሃተ እግዚአብሔር ከመ ታፅምኡ አርኅው መሳክወ አእዛኒክሙ ወአንቅሁ ልበክሙ” እግዚአብሔርን በመፍራት ተነሱ የጆሮቻችሁን መስኮቶች ክፈቱ ልቦናችሁን አንቁት እንደተባልን ሳንዝ ማን አዚም አደረገባችሁ ተብለንም እንዳንወቀስ የእግዚአብሔርን ተግሳፅ የአበውን ምክር ሰምተን አሁን ሰውነታችን በንስ ለማንጻት እንነሳ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም በመዝ 94፡8 “ዮም አመ ሰማዕክሙ ቃሎ ኢታፅንኡ ልበክሙ ዛሬ የእግዚአብሔርን ቃል ስትስሙ ልባችሁን አታፅኑት እንዳለ ይህን በምኵራብ አምላካችን ያደረገውን ስንሰማ የዘረኝነት የፍቅረ ንዋይ የተንኮል የትዕቢት ሸቀጣችን ትተን ቤተመቅደስ ሰውነታችን በንስ አጥበን ልባችን በትህትና ሞልተን በቤቱ ለበለጠው ጸጋ ቀንተን ቅንነትንም አክለን በቤቱ ለመኖር አምላካችን ይርዳን አሜን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!