ነገረ ማርያም/ክፍል አንድ/
የትንቢተ
ነቢያት ማረፊያ ፡-የስብከተ ሐዋርያት መነሻ.የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምሥጢር ነገረ ማርያም ነው፡፡ ያለ ነገረ
ማርያም ነገረ ክርስቶስን መናገር አይቻልም፡፡ በክርስትና ሃይማኖት ታሪክ የተነሡ አያሌ መናፍቃን የመጀመሪያ
ችግራቸው የነገረ ማርያምን አማናዊ ትምህርት መቀበል ነበር ፡፡ ያም ችግራቸው ክርስቶስን በትክክል እንዳያምኑት
አድርጓቸዋል፡፡ በነገረ ማርያም ላይ የተጣራ ትምህርትና እምነት ቢኖራቸው ኖሮ ለኑፋቄ አይጋለጡም ነበር ፡፡
ንስጥሮስ፡- «አምላክ ወልደ አምላክ» ብሎ በክርስቶስ ለማመን የተሳነው « ወላዲተ አምላክ . ወላዲተ ቃል. እመ
እግዚአብሔር » ብሎ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ለማመን በመቸገሩ ነበር፡፡
ነገረ ማርያምን ከነገረ ክርስቶስ መለየት አይቻልም ፡፡ የተዋሐደ ነው ፡፡ ስለ እመቤታችን የሚነገረው ክፉም ሆነ በጎ ክርስቶስን ይነካዋል፡፡ የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ በምንናገርበት ጊዜ እመቤታችንን ወደ ጎን መተው አይቻልምና፡፡ ምክንያቱም ወልዳ ያስገኘች. አዝላ የተሰደደች. በማስተማር ጊዜው ከአገር አገር አብራው የተንከራተተች ናትና ፡፡ በተሰቀለበት ዕለትም ከእግረ መስቀሉ አልተለየችም፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር ምክንያተ ድኂን አድርጓታል፡፡
ስለ ነገረ ድኅነት ስንናገር ጌታ ድኅነታችንን በመስቀል ላይ ፈጸመ የምንለው የዕለት ፅንስ ሆኖ በእመቤታችን ማኅፀን የጀመረውን ነው ፡፡ ሥጋውን ቆረሰልን .ደሙን አፈሰሰልን . ነፍሱን አሳልፎ ሰጠልን ብንል ከእርሷ የነሳውን ነው፡፡ ከእርሷ ነሥቶ በመስቀል ላይ የፈተተውን ሥጋውን እና ደሙንም የሕይወት ማዕድ አድርጎ ሰጥቶናል፡፡ መለኰታዊውን ፍህም በማኅፀን ከመሸከም ጀምሮ ይህ ታላቅ ምሥጢር የተፈጸመባት በመሆኑ መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ ሆና ትመሰገናለች ፡፡ በመዝሙራችንም ሆነ በቅዳሴአችን ከስመ ሥላሴ ቀጥሎ የምንዘምረው የእመቤታችንን ምሥጋና ነው ፡፡ ቅዱስ ዳዊት ፡- « መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው ፤ ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ . እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወድዳቸዋል፤ የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ. ስለ አንቺ የተነገረው ነገር ድንቅ ነው ፡፡» ያለው ለዚህ ነው ፡፡ መዝ 86.1-3 ፡፡ እርሷም እሳተ መለኰትን በማኅፀንዋ ተሸክማ ፡- « ሰውነቴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች ፡፡ ልቡናዬም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች ፡፡ የባርያውን ትሕትና ተመልክቷልና ፡፡ (ትንቢተ ኢሳያስን ተመልክቼ አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ከምትወልደው እመቤት ዘመን ቢያደርሰኝ ገረድ ሆኜ አገለግላታለሁ የሚለውን የልቤን አሳብ አይቷልና፡፡) እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብዕፅት ይሉኛል፡፡ ታላቅ ሥራን ሠርቶልኛልና ስሙም ቅዱስ ነው ፡፡ » ብላለች ፡፡ ሉቃ 1.46 ፡፡ ለእመቤታችን የተደረገላት ታላቅ ሥራ ፡- 1ኛ ከጥንተ አብሶ ነፃ ሆና መፈጠሯ ነው ፤ 2ኛ ፡- ከሀልዮ . ከነቢብ . ከገቢር ኃጢአት ነፃ መሆኗ ነው ፤ 3ኛ ከልማደ አንስት ነፃ መሆኗ ነው ፤ 4ኛ ሰማይና ምድር የማይችሉትን . ኪሩቤል እሳታዊ መንበሩን የሚሸከሙለትን . ሱራፌል መንበሩን የሚያጥኑለትን . መላእክት የሚንቀጠቀጡለትን በማኅፀኗ መሸከሟ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ቅዱስ ዳዊት « ሀገረ እግዚአብሔር ድንግል ማርያም ሆይ ለአንቺ የተደረገው ነገር ዕፁብ ድንቅ ነው ፤» እያልን እናመሰግናታለን ፡፡
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕት እምንጹሐን . ቅድስት እምቅዱሳን ናት ፡፡ ከተለዩ የተለየች. ከተከበሩ
የተከበረች. ከተመረጡ የጠመረጠች ማለት ነው፡፡ ይኽውም እንደሌላው መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ስላልወደቀባት ነው፡፡
ይህም ይታወቅ ዘንድ ጠቢቡ ሰሎሞን « ለስእርተ ርእስከ. ለርእስኪ. ለገጽከ=. ለቀራንብትከ=. ለአዕይንትከ=.
ለአእዛንኪ . ለመላትሕኪ ለአዕናፍኪ. ለከናፍርኪ. ለአፉከ=. ለአስናንኪ. . . . ለክሣድኪ . . .
ለአጥባትኪ፤ » እያለ መልክአ ማርያምን ማለትም የውስጥ የአፍአ ውበቷን ከማድነቅ ጋር « ወዳጄ ሆይ. ሁለንተናሽ
ውብ ነወ<. ምንም ነውር የለብሽም ፤» ብሏታል ፡፡ መኃ. 4.7 ፡፡ ነውር የተባለውም መርገመ ሥጋን መርገመ
ነፍስን ያመጣ የጥንት በደል (ጥንተ አብሶ) የሚባለው የአዳም ኃጢአት
ነው፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ጸኒስና ቅድመ ወሊድ. ጊዜ ጸኒስና ጊዜ ወሊድ. ድኅረ ፀኒስና ድኅረ ወሊድ ድንግል እንደሆነች የታመነ ነው፡፡ ኢሳ 7.04 ፤ ሕዝ #4.1-4 ፡፡ ይህም ንጽሐ ሥጋን ንጽሐ ነፍስንና ንጽሐ ልቡናን አስተባብራ. አንድ አድርጋ ይዛ መገኘቷን ያረጋግጥልናል፡፡ በመሆኑም ጠቢቡ ፡- « ምንም ነውር የለብሽም ፤ » ሲል፡- የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ፡- « ደስ ያለሽ. ጸጋንም የተመላሽ ሆይ. ደስ ይበልሽ ፤ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው ፤ ከሴቶች ተለይተሸ አንቺ የተባረክሽ ነሽ ፤ » ብሎ ከማብሠሩ በፊት. ባበሠራት ጊዘ?. ካበሠራትም በኋላ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ሉቃ 1.!6 ፡፡ ምክንያቱም ፡- መልአኩ ገብርኤል ወደ አንዲት ድንግል ተላከ ፤ ይላልና ነው ፡፡ ይህም ድንጋሌ ሥጋን ብቻ ሳይሆን ድንጋሌ ነፍስንም የሚያመለክት ነው ፡፡ ድንጋሌ ነፍስን ገንዘብ ማድረጓም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጥንተ አብሶ የተያዘችበት ጊዜ ፈጽሞ እንዳልነበረ ያሳየናል፡፡ ጠቢቡም ፡- «ወዳጄ ሆይ. ሁለንተናሽ ውብ ነው ፤» ማለቱ ለዚህ ነውና ፡፡
« ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፤ » ኢሳ1.9
ነቢየ
እግዚአብሔር ኢሳይያስ የነገረ ድኅነት ምሥጢር ተገልጦለት ያለፈውን ያለውን እና የሚመጣውን አገናዝቦ ሲናገር ፡- «
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ. እንደ ሰዶም በሆንን . እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር ፡፡
» ብሏል፡፡ ኢሳ 1.9 ፡፡ ይህም ለፍጻሜው ለእመቤታችን የተነገረ ትንቢት ነው ፡፡ ከዚህም በበለጠ ኹኔታ ትርጓሜ
የማያሻው ደረቅ ትንቢት ሲናገረም፡- « ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች. ወልድንም
ትወልዳለች. ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች ፡፡» ብሏል ኢሳ 7.04 ፡፡
እነ ኢሳይያስ በጥንተ አብሶ ምክንያት ፡- « ሁላችን እንደ ርኵስ ሰው ሆነናል ፤ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም
ጨርቅ ነው ፤ » ኢሳ %4.6፤ ቢሉም ፡- እግዚአብሔር ባወቀ ጥንተ አብሶ ፈጽሞ ባልደረሰባት በእመቤታችን ይመኩ.
ተስፋም ያደርጉ ነበር ፡፡ ለዚህም ነው፡- « እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ . . . ፤ » ያሉት ፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከጥንተ አብሶ ገና ከጧቱ ንጽሕት ሆና የተዘጋጀች ጥንተ መድኃኒት ናትና ነው፡፡
ቅዱስ ኤፍሬምም ፡- « መመኪያ አክሊላች. ጥንተ መድኃኒታችን. የንጽሕናችን መሠረት ፤» እያለ ያመሰገናት ለዚህ
ነው ፡፡
«በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር»
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር ፡፡ ይህንንም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ «
ዘእንበለ ይትፈጠር ሰማይ ወምድር. ወዘእንበለ ይሣረር ምድረ ገነƒ. ሀለወት ስብሕት ቅድስት ወቡርክት ይእቲ
ማርያም. እንተ ተሰምየት ሰንበተ ክርስቲያን ፣ ጽዮን ፣ ቅድስት፣ እሞሙ ለሰማዕት ወእኅቶሙ ለመላእክት፡፡
የመላእክት እህታቸው፣ የሰማዕታት እናታቸው፣ ጽዮን ፣ ቅድስት፣ የክርስቲያን ሰንበት የተባለች. የተመሰገነች.
በንጽሕና በድንግልና የተለየችና የተባረከች እርሷ ማርያም ሰማይና ምድር ሳይፈጠር የገነት ምድርም መሠረት ሳይጣል
ነበረች፡፡ » ብሏል ፡፡ ዳግመኛም « በቤተልሔም ተወሊዶ መድኅን ክብረ ቅዱሳን . ፍስሐ ለኵሉ ዓለም. ወሠርዐ
ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ. ወይቤላ እግዚአብሔር ለማርያም ፡- አዝማንየ አዝማንከ=. አምጣንየ አምጣንኪ. ማርያም
ሐቀፍኪዮ ወአነ ዮም ወለድኩዎ ፡፡ ለዓለሙ ኹሉ ደስታ የሚሆን የቅዱሳን ክብር መድኃኔዓለም በቤተልሔም ተወልዶ ፡-
ለሰው ልጅ ዕረፍት ሰንበትን ሠራ. እግዚአብሔር ማርያምን ፡- ዘመኖቼ ዘመኖችሽ. መጠኖቼ መጠኖችሽ ናቸው ፤ እኔ
ዛሬ ወለድኩት፡- ማርያም ሆይ አንቺ ታቀፍሺው ፡፡ » የሚል አለ ፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድጓው እንደገለጠው እግዚአብሔር
እመቤታችንን « ዘመኖቼ ዘመኖችሽ ናቸው ፤» ማለቱ ዓለም ከመፈጠሩ ዘመን ከመቆጠሩ በፊት በእርሱ ኅሊና መኖሯን
የሚያስረዳ ነው፡፡ « መጠኖቼ መጠኖችሽ ናቸው ፤» ማለቱ ደግሞ እርሱ ቅድመ ዓለም አካላዊ ቃል ወልድን ያለ እናት
ወልዶት አባት እንደሆነው እርሷም ድኅረ ዓለም አካላዊ ቃል ወልድን ያለ አባት ወልዳው እናት እንደሆነችው
የሚያመለክት ነው ፡፡ ምሥጢራዊ መልእክቱም « ወላጆች ( አባትና እናት ) ለወለዱት ልጅ እኩል እንደሆኑ ሁሉ
ወልድን በመውለድ በወላጅነት መሰልሽኝ ተስተካከልሺኝ ፤ » ሲላት ነው ፡፡ ይህም ፈጣሪን እና ፍጡርን የማነፃፀር
የማስተካከል ሳይሆን የተሰጣትን ክብርና ልዕልና የማሳየት ነው፡፡ ለምሳሌ ጌታ ደቀመዛሙርቱን ፡- « እውነት እውነት
እላችኋለሁ . በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል ፤ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፡፡»
ብሏቸዋል ፡፡ ዮሐ 14 .12 ፡፡ ይህም በማስተማርና ተአምራት በማድረግ እንደሚመስሉት ሲነግራቸው ነው ፡፡
«የሚበልጥ ያደርጋል፤» ማለቱም ፡፡ እርሱ ያስተማረው ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ነው፡፡ እነርሱ ግን ከዚህ በላይ
ሃያ ሠላሳ ዓመት የሚያስተምሩ ስለሆነ ነው፡፡ እርሱ ለአብነት ሁለት ሦስት ሙት ቢያነሣ እነርሱ ደግሞ በስሙ ከዚያ
በላይ ብዙ ስለሚያስነሡ ነው፡፡
«እመቤታችን በአዳም ባሕርይ ውስጥ»
« ማርያምሰ ተኀቱ እምትካት ውስተ ከርሱ ለአዳም. ከመ ባሕርይ ጸአዳ፤እመቤታችን ማርያም ከጥንት ጀምሮ በአዳም
ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች ፤ » ይላል ፡፡ ይህንንም በድጓው የተናገረው ቅዱስ ያሬድ ነው ፡፡
እመቤታችን በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ማብራቷ ከጥንተ አብሶ ነፃ ሆና መፈጠሯን የሚያመለክት ነው፡፡
አዳም ይኽንን ስለሚያውቅ ነው . እመቤታችንን ተስፋ ያደረገው ፡፡ ምክንያቱም በውስጡ እንደ ነጭ ዕንቁ ስታበራ
ይታወቀው ነበርና ነው ፡፡ አባ ሕርያቆስ ይህ ምሥጢር ተገልጦለት « ከገነት በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው አንቺ
ነበርሽ ፤» እያለ እመቤታችንን አመስግኗታል፡፡ ይህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትእዛዝን በመተላለፍ
በአዳም ላይ ከመጣ ጥንተ በደል በአምላካዊ ምሥጢር ተጠብቃ ከአዳም ወደ ሴት. ከሴት ወደ ኖኅ. ከኖኅ ወደ ሴም.
ከሴም ወደ አብርሃም ስትቀዳ የኖረች ንጽሕት ዘር መሆኗን ያስረዳል ፡፡ ከላይ እንደተገለጠው ነቢዩ ኢሳይያስ «
እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ » ያለው ይኽንን ነው ፡፡
« አንፂሖ ሥጋሃ ቀዲሶ ኪያሃ ኀደረ ላዕሌሃ»
ቅዱስ
ያሬድ በሌላ አንቀጽ « ሥጋዋን አንጽቶ. እርሷን ቀድሶ. በእርሷ ላይ አደረ ፤» ብሏል፡፡ ይኽንን ንባብ በመያዝ
ትርጓሜውንና ምሥጢሩን ቸል በማለት « ያነጻት የቀደሳት ከጥንተ አብሶ ነው ፤ » የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን
አይደለም፡፡ ጥንቱንም ንጽሕት ቅድስት አድርጐ በፈጠራት በእርሷ አደረ ማለት እንጂ ፡፡ « ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ፤
( ለየ ) ፤ » እንዲል ፡፡ መዝ #5.4 ፡፡ ይህም ሁሉ ከተያዘበት ከጥንተ አብሶ ለይቶ ፈጠራት ማለት ነው፡፡
ጊዜው ሲደርስ ሥላሴ፡- አብ ለማጽናƒ. ወልድ ለለቢሰ ሥÒ. መንፈስ ቅዱስ ለማንፃት በማኅጸነ ድንግል አድረዋል፡፡
እዚህ ላይ « መንፈስ ቅዱስ ለማንፃት ፤» ማለቱ ፡- የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ ማንፃት. መቀደስ መሆኑን ለመግለጥ
እንጂ እድፍ ጉድፍ ኖሮባት አይደለም ፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር የሰማይ ማደሪያውን ባለማለፍ ጸንታ የምትኖረውን
እሳታዊ ዙፋን የተዘረጋባትን . ሰባት እሳታዊ መጋረጃዎች የተጋረዱባትን . ፀዋርያነ መንበሩ ኪሩቤልና ዐጠንተ
መንበሩ ሱራፌል ያሉባትን ጽርሐ አርያምን ጥንቱኑ ንጽሕት ቅድስት አድርጐ ፈጥሯታል ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ይኽንን ምሳሌዋ
በማድረግ እመቤታችንን « ከሰማያት በላይ ያለ የአርያም የልዑል ሥፍራ ምትክ በምድር ላይ ከፍተኛ አርያምን
ሆንሽ ፤ » ብሏታል ፡፡ በመሆኑም ያቺ ጥንቱኑ ንጽሕት ቅድስት ሆና እንደተፈጠረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል
ማርያምም ጥንቱኑ ንጽሕት ቅድስት ሆና ተፈጥራለች እንጂ ኖራ ኖራ በኋላ የነፃች አይደለችም ፡፡ ለምሳሌ « ቃልህ
እጅግ የነጠረ ነው ፤» የሚል ገጸ ንባብ ይገኛል፡፡ መዝ )08.)# ፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ቃል ልክ እንደ ቅቤ .
እንደ ብረት ወይም እንደ ወርቅ ኖሮ ኖሮ የነጠረ ወይም ነጥሮ እድፍ ጉድፍ የወጣለት ነው አያሰኝም ፡፡ በመሆኑም
እመቤታችንን በአባ ሕርያቆስ ምስጋና እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሁኖ ምሥራቅንና ምዕራብን . ሰሜንና ደቡብን
ዳርቻዎችንም ሁሉ በእውነት ተመለከተ ተነፈሰ አሸተተም. እንደ አንቺ ያለ አላገኘም፡፡ የአንቺን መዓዛ ወደÅ. ደም
ግባትሽንም ወደÅ. የሚወደውንም ልጁንም ወደ አንቺ ሰደደ ፡፡ » እያልን ልናመሰግናት ይገባል፡፡ « እንደ አንቺ
ያለ አላገኘም ፤» ማለቱም ፡- « እንደ አንቺ በጥንተ አብሶ ሳይያዝ የተገኘ የለም . ከአንቺ በቀር ሁሉ ተይዟል ፤
» ማለት ነው ፡፡
« ቀዳማዊ አዳም ወዳግማዊ አዳም »
ቀዳማዊ አዳም የሚባለው ከምድር አፈር የተፈጠረው ሰው ነው ፡፡ « እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር
ፈጠረው ፤ በፊቱም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ ፡፡» እንዳለ ፡፡ ዘፍጥ
2.7 ፡፡ ዳግማዊ አዳም የተባለው ደግሞ በተለየ አካሉ ከሰማይ ወርዶ. በማኅጸነ ድንግል ማርያም አድሮ. ከሥጋዋ
ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በተዋሕዶ ሰው ሁኖ የተወለደው የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይኽንንም
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፡- « አሁንም ክርስቶስ ከሞቱ ሰዎች ሁሉ አስቀድሞ ( በኵር ሆኖ ) ተነሥቷል ፡፡
በመጀመሪያው ሰው
(
በቀዳማዊ አዳም ) ሞት መጥቷል“. በሁለተኛው ሰው ( በዳግማዊ አዳም በክርስቶስ ) ትንሣኤ ሙታን ሆነ ፡፡ ሁሉ
በአዳም እንደሚሞት እንዲሁ በክርስቶስ ሁሉ ሕያዋን ይሆናሉ፡፡ . . . መጽሐፍ እንዲህ ብሏል. የመጀመሪያው ሰው
አዳም በነፍስ ሕያው ሆኖ ተፈጠረ ፤ ሁለተኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው ፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ
ሥጋዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም ፡፡ የመጀመሪያው ሰው ከመሬት የተገኘ መሬታዊ
ነው ፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ የወረደ ሰማያዊ ነው፡፡ » በማለት ገልጦታል፡፡ 1ኛ ቆሮ 05.!-#5 ፡፡ ከዚህም
የመጀመሪያው ፍጡር ሁለተኛው ፈጣሪ. የመጀመሪያው ከምድር ሁለተኛው ከሰማይ መሆኑን እንረዳለን ፡፡ እንግዲህ
የሚያንሰው ቀዳማዊ አዳም ከመጀመሪያው ንጽሕት ከነበረች መሬት ተፈጠረ እያልን የሚበልጠውን ዳግማዊ አዳምን
ከመጀመሪያው ንጽሕት ካልነበረች. በጥንተ አብሶ አድፋ ጐድፋ ከነበረች ከድንግል ማርያም ተወለደ ማለት ክርስቶስን
ከአዳም ማሳነስ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡
«ብሥራተ ገብርኤል ወፅንሰት፡፡ »
የመላእክት
አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ ወደ እመቤታችን በመጣ ጊዜ ፡- « ደስ ያለሽ. ጸጋንም የተመላሽ ሆይ.
ደስ ይበልሽ ፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው ፤ ከሴቶች ተለይተሸ አንቺ የተባረክሽ ነሽ ፡፡» በማለት
አመስግኗታል፡፡ ሉቃ 1.!8 ፡፡ ከእርሷ በፊት ይህን በሚመስል ምስጋና የተመሰገነ ማንም አልነበረም ፡፡ ለመጀመሪያ
ጊዜ ለእመቤታችን የተሰጠ ምስጋና ነው ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጥንተ አብሶ ተይዛ ቢሆን ኖሮ
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል « ጸጋን የተመላሽ ሆይ » አይላትም ነበር፡፡ ምክንያቱም ጥንተ አብሶ ጸጋዋን ጐዶሎ
ያሰኝባት ነበርና ፡፡ ከላይ እንደገለጥነው እነ ኢሳይያስን ጽድቃቸውን የመርገም ጨርቅ ያሰኘባቸው ጥንተ አብሶ
ነው፡፡ የቅድስናን ሥራ እየሠሩ « ሁላችንም እንደ ርኵስ ሰው ሆነናል ፤ » ያሰኛቸው ይኽው ነው ፡፡ ኢሳ %4.6
እነ ኤርምያስንም ፡- « ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም፡፡ ስንዴ ዘሩ እሾህንም አጨዱ ፤ » አሰኝቷቸዋል፡፡ ኤር
02. 03፡፡ እመቤታችን ግን ከመጀመሪያው ንጽሕት ቅድስት በመሆኗ « ጸጋን የተመላሽ ሆይ ፤ » ተብላለች፡፡
አንዳንዶች፡- ለእመቤታችን ጥንተ አብሶ የጠፋላት መልአኩ ባበሠራት ጊዜ ነው ይላሉ፡፡ ይህም አባባላቸው ሁለት
ጥያቄዎችን ያስነሣል፡፡ 1ኛ ፡- ከዚህ በፊት መልአክ ያበሠራቸው ማኑሄና ሚስቱ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ለምን ጥንተ
አብሶ አልጠፋላቸውም; መሳ 03.2 ሉቃ 1.8 ፤ 2ኛ ፡- ጥንተ አብሶ የሚጠፋው በብሥራተ መልአክ ቢሆን ኖሮ
አካላዊ ቃል ከሰማይ ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰው መሆን . መከራ መቀበልና በመስቀል ላይ መሞት ለምን
አስፈለገው; በልዑል መንበሩ እንደተቀመጠ እልፍ አዕላፋት ወትእልፊተ አዕላፋት መላእክትን ልኮ በብሥራት ብቻ ጥንተ
አብሶን አያጠፋም ነበር;
አንዳንዶች ደግሞ « ጌታ በተፀነሰ ጊዜ በዚያ ቅጽበት ነው የጠፋላት ፤ » ይላሉ፡፡ ይህም ፡- «ጌታ የመጣው
ጥንተ አብሶን እንዴት አድርጐ ለማጥፋት ነው; » የሚል ጥያቄ ያስነሣል ፡፡ መልሱም « በመስቀል ላይ በሚፈጽመው
ቤዛነት በሚከፍለው መሥዋዕትነት ነው፤» የሚል ይሆናል ፡፡ እንግዲህ እመቤታችን ጥንተ አብሶ ነበረባት የሚሉ ከሆነ
«እርሷም በጥንተ አብሶ እንደተያዙ እንደማናቸውም ሰው ናት፤ » ማለታቸው ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ እንደማናቸውም
ሰው በመስቀል ላይ በሚፈጸም ቤዛነት ብቻ ከጥንተ አብሶ ትድን ነበር እንጂ ተቃዋሚዎቹ እንደሚሉት ሊሆን
አይችልም፡፡
« ሰው አይደለችም ወይ;»
ነቢዩ
ኢሳይያስ ፡- « በትር ከእሴይ ሥር ትወጣለች. አበባም ከእርሷ ይወጣል፤» በማለት ስለ እመቤታችንም ስለ ጌታም
ትንቢት ተናግሯል፡፡ ኢሳ 01.1 ፡፡ የበትር ምሳሌነት ለእመቤታችን ሲሆን የአበባ ምሳሌነት ደግሞ ለጌታ ነው፡፡
ቅዱስ ያሬድም በዚህ ትንቢት ላይ ተመሥርቶ ፡- « ትወጽእ በትር እምሥርወ ዕሴይ. ወየዐርግ ጽገ. ይእቲ በትር
አምሳለ ማርያም ቅድስት ይእቲ. ወጽጌ ዘወጽአ እምኔሃ ፤ አምሳሉ ዘወልድ ዘኀደረ ላዕሌሃ. ቃል ሥጋ ኮነ ወተወልደ
እምኔሃ፤ ከነገደ ዕሴይ በትር ትወጣለች. አበባም ከእሷ ይወጣል. ይህችውም በትር የማርያም አምሳል ናት ፤ ከእርሷ
የሚወጣውም በትር የወልድ ምሳሌ ነው፤ የአብ አካላዊ ቃል በማኅጸኗ አድሮ ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷም ነፍስን ነሥቶ
በተዋሕዶ ሰው ሁኖ ከእርሷ ተወለደ፤ » ብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ቅዱስ ማቴዎስ እንደነገረን የእመቤታችን የዘር
ሐረግ (የዘር ቅጂዋ) ከዕሴይ ወደ ዳዊት ወደ ሰሎሞን . ከዚያም ሲወርድ እስከ አልዓዛር .ከዓልዓዛር ደግሞ ሴት
ልጁ ወደምትሆን ወደ ቅሥራ. ከቅሥራም ወደ ኢያቄም የደረሰ ነው፡፡ በእናቷ በኵል ደግሞ ከሊቀ ካህናቱ ከአሮን ወገን
ናት፡፡ በመሆኑም ከሰው ወገን የተወለደች ሰው ናት፡፡
ካቶሊኮች፡-
ጥንተ አብሶን የሸሹ መስሏቸው « ሰው አይደለችም . ኃይል አርያማዊት ናት » እያሉ ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ይኽንን
የካቶሊኮች አመለካከት የሸሹ መስሏቸው «እንደማናቸውም ሰው ጥንተ አብሶ የነበረባት ሰው ናት፡፡ » ይላሉ ፡፡
የሁለቱም « ከድጡ ወደ ማጡ » ነው ፡፡ የሁለተኛዎቹ አስተሳሰብ « ከሰው ወገን የተወለደች ሰው እስከሆነች ድረስ.
የሰው ልጅ ተብላ እስከተጠራች ድረስ የግድ ጥንተ አብሶ ነበረባት ያሰኛል ፤ » የሚል ነው፡፡ ይህም አንድ
መሠረታዊ ጥያቄ ያስነሣል፡፡ ይኽውም ፡- « የሰው ወገን . የሰው ልጅ ለመባል የግድ የጥንተ አብሶ መኖር
ያስፈልጋል ወይ; » የሚል ነው ፡፡ እንዲህስ ከሆነ ቀዳማዊ አዳም ከመበደሉ በፊት ለምን ሰው ተባለ; መርገመ ሥጋን
መርገመ ነፍስን ያጠፋ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስም ለምን የሰው ልጅ ተባለ; ያሰኛል፡፡ መናፍቃኑ እነደሚሉት ቢሆን
ኖሮ፡- እነ ኢሳይያስ « እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ ፤» እያሉ አይመኩባትም ነበር፡፡ እነ ሰሎሞንም «
አልብኪ ነውር » እያሉ አያመሰግኗትም ነበር፡፡ እነ ቅዱስ ኤፍሬም « አክሊለ ምክሕነ. ወጥንተ መድኃኒት. ወመሠረተ
ንጽሕነ ፤ » እነ አባ ሕርያቆስም ፡- « ወኢረከበ ዘከማኪ፤ » አይሏትም ነበር፡፡ ስለዚህ ብርሃኑን ከጨለT.
በጐውን ከክñ. ስንዴውን ከእንክርዳድ ለይተን አባቶቻችን ባቆዩልን ልንጸና ያስፈልጋል፡፡ ነገሩ የእውቀት ብቻ
ሳይሆን የእምነት ነውና፡፡ የዕውቀት ሰዎች ሁለት ዓይነት ናቸው ፡፡ የመጀመሪያዎቹ እውቀታቸውን በትህትና ይዘው
በእምነት የሚኖሩ ሲሆኑ ሁለተኛዎቹ ግን በእውቀታቸው ሲታበዩ በጥርጥር ማዕበል የሚመቱ . በኑፋቄ የሚለዩ .
በክህደት የሚወድቁ ናቸው፡፡ ትእቢት ዲያቢሎስ የተያዘበት አሽክላ ነው፡፡ በንስሐ የማይመለሰው ለዚህ ነው፡፡
ዲያቢሎስ የትዕቢት እንጂ የእውቀትም የሥልጣንም ችግር አልነበረበትም፡፡ እነ አርዮስ. እነ ንስጥሮስ. እነ
መቅዶንዮስም የትዕቢት እንጂ የእውቀት ችግር አልነበረባቸውም፡፡ ነገር ግን እውቀታቸውን ለክፋት ተጠቀሙበት ፡፡
እስከ ዓለም ፍጻሜ ለሚነሡ መናፍቃንም መጥፎ አብነት ሆኑበት፡፡ ስለዚህ ከዚህ እንዲሠውረን ተግተን ልንጸልይ
ይገባናል፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት . የንጽሕተ ንጹሐን . የቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን የድንግል ማርያም
አማላጅነት አይለየን አሜን ፡፡
ነገረ ማርያም ክፍል ፪
እግዚአብሔር
፦ በምሳሌ ፥ በትንቢት ፥ በሕልም ፥ በራእይና በገሃድ በወዳጆቹ በኲል መልእክቱን ያስተላልፋል። ኃላፊያቱንና
መጻእያቱን ይናገራል። ኃላፊውን በመጻኢ ፥ መጻኢውን በኃላፊ አንቀጽ የሚናገርበት ጊዜም አለ። በመሆኑም ፦ ንባቡን
የሚተረጉም ፥ ትርጓሜውን የሚያመሰጥር ፥ ምስጢሩን አምልቶ አስፍቶ የሚፈትት ( የሚተነትን ) ያስፈልጋል።
- «
እከስት በምሳሌ አፉየ ፥ ወእነግር አምሳለ ዘእምትካት ፤ አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ ፥ ( ነገሬን በምሳሌ
እገልጣለሁ ፥ ወንጌልን በምሳሌ አስተምራለሁ ) ፥ ከቀድሞ ጀምሮ ያለውንም ምሳሌ እናገራለሁ፤ » ምሳ ፸፯ ፥ ፪ ፣
ማቴ ፲፫ ፥ ፴፭።
- «
ወይቤሎሙ ፥ ስምዑ ቃልየ ፥ ለእመቦ ዘኮነ ነቢየ እምኔክሙ ለእግዚአብሔር በራእይ አስተርኢ ሎቱ ፥ ወበሕልም
እትናገሮ። ነገሬን ስሙ ፥ ከእናንተ ለእግዚአብሔር ነቢይ የሆነ ሰው ቢኖር በራእይ እገለጽለታለሁ ፥ በሕልም
እነጋገረዋለሁ አላቸው። » ዘኁ ፲፪ ፥ ፮
- «
ወአኮ ከመ ቊልዔየ ሙሴ ፥ ምእመን ውእቱ ላዕለ ኲሉ ቤትየ ፤ አፈ በአፍ እትናገሮ ገሃደ ወአኮ በስውር ፥ ወርእየ
ስብሐተ እግዚአብሔር። ነገር ግን የምናገረው እንደታመነ ወዳጄ እንደ ሙሴ አይደለም ፥ እሱ በወገኖቼ በእስራኤል
ሁሉ የታመነ ነውና ፤ ተገልጬ ቃል በቃል እነጋገረዋለሁ እንጂ
በራሕይ በሕልም የምነጋገረው አይደለም ፥ የእግዚአብሔርነቴን ጌትነትም ያየ እሱ ነው። » ዘኁ ፲፪ ፥ ፯
በራሕይ በሕልም የምነጋገረው አይደለም ፥ የእግዚአብሔርነቴን ጌትነትም ያየ እሱ ነው። » ዘኁ ፲፪ ፥ ፯
-
« ይህን መጀመሪያ ዕወቁ ፥ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም። ትንቢተ ከቶ
በሰው ፈቃድ አልመጣምና ፤ ዳሩ ግን ቅዱሳን ሰዎች ከእግዚአብሔር ተልከው በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ተና ገሩ ።»
፩ኛ ጴጥ ፩ ፥፳
ቅዱስ
ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት ተግዞ ሳለ የተገለጠለትን ራእይ ሲናገር። « ወአስተርአየ ተአምር ዐቢይ በውስተ ሰማይ ፤
ታላቅ (ደገኛ የሆነ) ምልክት በሰማይ ታየ ፤ » ብሏል። ቅዱስ ዮሐንስ ይህን ምልክት ፦ ታላቅ ፥ ገናና ፥ ብርቱ ፥ ፍጹም ፥ በማለት የተናገረው ከእግዚአብሔር በመሆኑ ነው። እግዚአብሔር ታላቅ ነውና። ይኽንንም ቅዱስ ዳዊት ፦ « ዐቢየ እግዚአብሔር ፥ ወዐቢየ ኃይሉ ፤ እግዚአብሔር ታላቅ ነው ፥
( እግዚአብሔር አብ ገናና ነው ) ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው ፤ ( ኃይሉ እግዚአብሔር ወልድም ገናና ነው ) ፤
ወአልቦ ኁልቊ ለጥበቡ ። ለጥበቡም ቁጥር የለውም ። ( ጥበቡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ሀብቱ ፍጹም ነው )። »
በማለት ተናግሮታል። መዝ ፩፻፵፮ ፥ ፭ ። እግዚአብሔር ታላቅ በመሆኑ ተአምራቱም ታላላቅ ናቸው። « እግዚአብሔርን
አመስግኑት ቸር ነውና ፥ . . . የአማልክትን አምላክ አመስግኑ ፤ . . . . . የጌቶችን ጌታ አመስግኑ ፤ .
. . . . . እርሱ ብቻውን ታላላቅ ተአምራትን ያደረገ ፥ ምሕረቱ ለዘለላም ነውና ፤ » ይላል። መዝ ፩፻፴፭ ፥
፩-፬ ።
ይህ
ምልክት በሰማይ መታየቱ ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊ ፥ ሥጋዊ ያይደለ መንፈሳዊ ክብርን ፥ ልዕልናን ያሳያል። ይህ
ምልክት የታየበት ሰማይ የሚያልፈው ፥ የሚጠፋው ሰማይ አይደለም። ዛሬ የምናያቸው ሰማይና ምድር ያልፋሉ። ማቴ ፭ ፥
፲፰ ፣ ምልክቱ የታየው ጸ ንተው በሚኖሩት
ሰማያት ነው። ምክንያቱም ራሱ ቅዱስ ዮሐንስ ፦ « አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርን አየሁ ፤ የፊተኛው ሰማይና
የፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና ፤ » ብሏል። ራእ ፳፩ ፥ ፩። ቅዱስ ጴጥሮስም ፦ ሰማይና ምድር እንደሚያልፉ ፥
እንደሚጠፉም ከተናገረ በኋላ፦ « እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርባቸውን አዲሶቹን ሰማያትና አዲሲቱን ምድር ተስፋ
እናደርጋለን ። » ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፫ ፥ ፲ -፲፫ ።
፪፦ « ፀሐይን የተጐናጸፈች ፤ »
ፀሐይ ቀንን እንዲገዛ የተፈጠረ ነው። «
ለፀሐይ ቀንን ያስገዛው ምሕረቱ ለዘላለም ነውና ፤ » ይላል። መዝ ፩፻፴፭ ፥ ፰። የፀሐይ ተፈጥሮ ከእሳት ስለሆነ
ትሞቃለች ፥ ትደምቃለች። ብርሃኗም ከጨረቃ ብርሃን ሰባት እጥፍ ነው። ሄኖ ፳፩ ፥ ፶፮ ። እግዚአብሔር ማክሰኞ
ማታ ለረቡዕ አጥቢያ ፦ « ለይኩን ብርሃን ውስተ ጠፈረ ሰማይ ፤ ብርሃን በሰማይ ጠፈር ይሁን ፤» ባለ ጊዜ ጸሐይ
ጨረቃ ከዋክብት ተፈጥረዋል። ዘፍ ፮ ፥ ፲፮ ። በዚህን ጊዜ መላእክት በታላቅ ድምጽ አመስግነውታል። « ወአመ
ተፈጥሩ ከዋክብት ሰብሑኒ ኲሎሙ መላእክትየ በዓቢይ ቃል ፤ ከዋክብት በተፈጠሩ ጊዜ መላእክቴ ሁሉ በታላቅ ድምጽ
አመሰገኑኝ ፤» እንዳለ ። ኢዮ ፴፰ ፥ ፯ ።
የተፈጠሩበት
ዓላማም በዚህ ዓለም እንዲያበሩ ፥ (ጨለማን እንዲያርቁ) ፥ በመዓልትና በሌሊት መካከል ድንበር ሆነው እንዲለዩ ፥
ማለትም መለያ ምልክት እንዲሆኑ ፥ አንድም ለሰው ልጅ ምሳሌ እንዲሆኑ ነው። ፀሐይ መውጣቷ የመወለዳችን ፥ በጠፈር
ላይ ማብራቷ በዚህ ዓለም የመኖራችን ፥ መግባቷ ( በምዕራብ መጥለቋ ) የመሞታችን ፥ ተመልሳ በምሥራቅ መውጣቷ
የመነሣታችን ምሳሌ ነው። ከዚህም ሌላ ፦ ክረምት ፥ በጋ ፥ ጸደይ ፥ መጸው ብሎ አራት ክፍለ ዘመን ለመቊጠር ፥
ለሳምንት ሰባት ቀን ብሎ ለመቊጠር ፥ ሦስት መቶ ስድሳ አምስቱን ቀን ዓመት ብሎ ለመቊጠር ምልክት ይሆኑ ዘንድ
ፀሐይን ጨረቃን ከዋክብትን ፈጠረ።
፪ ፥ ፩፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ፀሐይ ነው ፤
ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፀሐይ ተመስሏል። « ወይሠርቅ ለክሙ ለእለ ትፈርሁ ስምየ ፀሐየ ጽድቅ ፤
ነገር ግን ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ይወጣላችኋል ፤ ( ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስ ይወለድላችኋል ) ፤
ይላል። ሚል ፬ ፥ ፪። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ በቅዱሱ ተራራ በደብረ ታቦር በነቢያትና በሐዋርያት ፊት ገጹ እንደ
ፀሐይ በርቷል። « ወአብርሃ ገጹ ከመ ፀሐይ ፤ ፊቱ እንደ ፀሐይ ብሩህ ሆነ ፤ ( ጌትነቱን ገለጸ ) ፤ » ይላል።
ማቴ ፲፯ ፥ ፪ ።
ፀሐይ
በጠፈረ ሰማይ ሆና እንደምታበራ ፥ በሰማይ የሚኖር እርሱ ብርሃናችን ነው። « እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ፥
የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃንን ያገኛል እንጂ በጨለማ ውስጥ አይመላለስም። ( ወደ ከህደት አይሄድም )። ብሏልና ።
ዮሐ ፰ ፥፲፪ ፣ ፱ ፥ ፭ ። ፀሐይ በመዓልትና በሌሊት መካከል እንደምትለይ ፥ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስም ፦
ጻድቃንን ከኃጥአን ፥ ኃጥአንን ከጻድቃን ይለያል። « የሰው ልጅ ( ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ ) በጌትነቱ
ቅዱሳን መላእክትን ሁሉ አስከትሎ በሚመጣበት ጊዜ ፥ ያን ጊዜ በጌትነቱ ዙፋን ይቀመጣል። አሕዘብ ሁሉ በፊቱ
ይሰበሰባሉ ፥ እረኛም በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ እየራሳቸው ይለያቸዋል። በጎችን ( ጻድቃንን ) በቀኙ ፍየሎችንም
(ኃጥአንን) በግራው ያቆማቸዋል። » ይላል ። ማቴ ፳፭ ፥ ፴፩። ፀሐይ የዕለታት ፥ የአራቱ አዝማናትና የዓመታት
መለያ እንደሆነች ፦ እነዚህን ለይቶ ባርኮ የሰጠን ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። « ወትባርክ አክሊለ ዓመተ
ምሕረትከ ፥ ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም ፥ ወይረውዩ አድባረ በድው ፤ የምሕረትህን ዓመት አክሊል ትባርካለህ ፥ ምድረ
በዳዎችም ጠልን ይጠግባሉ ፥ የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ ፤ » ያለው ለዚህ ነው። መዝ ፷፬ ፥ ፲፩ ። አክሊል
ያለው ፍሬ የሚሸከመውን የስንዴ ዛላ ነው። አክሊል የሚቀመጠው በራስ ላይ እንደሆነ ሁሉ ፍሬው ፥ ዛላው ከላይ
ነውና።
፪ ፥ ፪፦ ቅዱሳን ፀሐይ ናቸው፤
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዓለም ለይቶ የጠራቸውን ፥ ጠርቶም የመረጣቸውን ደቀመዛሙርቱን ፦ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ ፥ በተራራ ላይ የተሠራች ከተማ መሰወር አይቻላትም። » ብሏቸዋል። ማቴ ፭ ፥ ፲፬። እርሱ ፦ «
እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ፤ » ማለቱ የባህርዩ ሰለሆነ ነው ፥ የእነርሱ ግን የጸጋ ነው። በጸጋ ያከበራቸውም
እርሱ ነው። በተጨማሪም ፦ « ያንጊዜም ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ ፤ ( ከፀሐይ ሰባት እጅ
ያበራሉ ) ፤ » ብሏል። ማቴ ፲፫ ፥ ፵፫ ። በመሆኑም ቅዱሳን ባሉበት ቦታ ሁልጊዜ ብርሃን ነው። ጨለማ ይወገዳል።
ቅዱስ
ዮሐንስ « ብእሲት እንተ ትለብስ ፀሐየ፤ » ፀሐይን ተጐናጽፋ ያየው እመቤታችንን ነው። ክብሯን ፥ ልዕልናዋን ፥
ጸጋዋን እንደ ጸሐይ በሚያበራና በሚያንጸባርቅ ፥ ዓይንን በሚያጥበረብርና በሚበዘብዝ የወርቅ መጐናጸፊያ መልክ
አይቷል። ፀሐይን መልበሷ ክብሯ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ያመለክታል። በመሆኑም ክብሯን ማወቅ እርሱን
ማወቅ ነው። ለቅዱሳን ሲሆን ደግሞ ክብራቸው እርሷ መሆኗን ያሳያል። ለምሳሌ የእኔን የተርታውን ቄስ ካባ ፓትርያርኩ
ቢለብሱት ክብሩ ለእኔ እንጂ ለርሳቸው አይደለም ። እንግዲህ የእመቤታችን ክብሯ በሰማይ ከፍ ብሎ መታየቱ ክብርት
ልዕልት እንድንላት መሆኑን አውቀን ከእግዚአብሔር በታች ከፍጡራን በላይ አድርገን ልናመሰግናት ይገባል። ቅዱስ
ዳዊትም ከሁሉ አስቀድሞ ይህ ክብሯ ስለተገለጠለት ፦ « ወትቀውም ንግሥት በየማንከ ፥ በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት
ወኁብርት ፤ በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና( ወርቀ ዘቦ ግምጃ ደርባ ደራርባ ፥ ለብሳ ተጐናጽፋ ) ንግሥቲቱ
በቀኝህ ትቆማለች። ( ትገለጣለች ፥ በወርቅ ዙፋን ተቀምጣ ትታያለች ) ብሏል። መዝ ፵፬ ፥ ፱።
፫ « ጨረቃንም ከእግሯ በታች የተጫማች ፤»
ጨረቃ
የተፈጠረው ሌሊትን እንዲገዛ ነው። « ለጨረቃና ለከዋከብት ሌሊትን ያስገዛቸው ምሕረቱ ለዘላለም ነውና ፤ »
ይላል። መዝ ፩፻፴፭ ፥ ፱ ፣ ዘፍ ፩ ፦ ፲፮ ። በተጨማሪም ፦ « ወገበርከ ወርኃ በዕድሜሁ ፤ ጨረቃን በጊዜው
ፈጠርህ ፤» የሚል አለ። መዝ ፩፻፫ ፥ ፲፱።
የጨረቃ ብርሃን ከፀሐይ ብርሃን አንድ ሰባተኛ ነው። ይኽንንም የፀሐይ ፥ የጨረቃና የከዋክብት ምሥጢር የተገለጠለት
ሄኖክ ፦ « ከዚህ ሥርዓትም በኋላ ስሙ ጨረቃ የሚባል የታናሹን ብርሃን ሌላ ሥርዓት አየሁ። ክበቡም እንደ ሰማይ
ክበብ ነው ፥ የሚሄድበትንም ሠረገላ ነፋስ ይነዳዋል።
ብርሃንም በመጠን ይሰጠዋል። በወሩም ሁሉ መውጫውና መግቢያው ይለወጣል ፥ ቀኑን እንደ ፀሐይ ቀን ነው። የብርሃኑ
ሁኔታም በተስተካከለም ጊዜ የብርሃኑ መጠን ከፀሐይ ብርሃን ሰባተኛ እጅ (1/7) ይሆናል። » በማለት ነግሮናል።
ሄኖ ፳፪ ፥ ፩። ጨረቃ ብርሃኗን የምታገኘው ከፀሐይ ነው። ጨረቃ ሙሉ ሆና ትወለድና ( ትታይና ) እያጸጸች (
እየጎደለች ) ሄዳ ትጠፋለች። እንደጠፋችም አትቀርም ፥ ተመልሳ ሙሉ ሆና ትወለዳለች። ይህም መወለዷ የመወለዳችን ፥
እያጸጸች ሄዳ መጥፋቷ ኑረን ኑረን የመሞታችን ፥ እንደገና መወለዷ የመነሣታችን ምሳሌ ነው።
ቅዱስ
ዮሐንስ እመቤታችንን « ወወርኀ ታሕተ እገሪሃ ፤ » እንዲል ጨረቃን ተጫምታ አይቷል። ጨረቃ የቤተ ክርስቲያን
ምሳሌ ናት። ጨረቃ ብርሃኗን ከፀሐይ እንድታገኝ ቤተ ክርስቲያንም ብርሃኗ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
እንዲሁም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ፦ « ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ፤ » ያለላቸው ቅዱሳን
ናቸው። ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ጸጋ ያላት ፥ የመንፈስ ቅዱስ መዝገብ ቤት የሆነች ፥ በምድር ያለች የእግዚአብሔር
መንግሥት ናትና ።
ወደ
ጨረቃዋ ምሥጢር ስንመለስ ፦ ደግሞ « ጨረቃ ከእግሯ በታች የተጫማች ፤ » የሚለው ትርጉም ቤተ ክርስቲያን ተብለው
የሚጠሩ ምዕመናን ከእግሮቿ በታች ወድቀው ይሰግዱላታል ፥ ይገዙላታል ማለት ነው። ይኸውም ስለ ክርስቶስ ነው።
ምክንያቱም በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ወልደዋለችና። እንኳን የሚወዳት ይጠሏት የነበሩ እንኳ ወደ ልቡናቸው
ተመልሰው ይሰግዱላታል። ይኽንንም ነቢዩ ኢሳይያስ ፦ « የአስጨናቂዎችሽም ልጆች ወደ አንቺ ይመጣሉ ፥ የናቁሽም ሁሉ
ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ ፤ የእግዚአብሔር ከተማ ፥ የእስራኤል
ቅዱስ ይሉሻል። » በማለት ነግሮናል። ኢሳ ፷ ፥ ፲፬ ። በተጨማሪም ፦ « ነገሥታትም አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ ፥
እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ ፥ ግንባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል ፥ የእግርሽንም ትቢያ
ይልሳሉ ፤ » የሚል አለ ። ኢሳ ፵፱ ፥ ፳፫ ።
፬ ፦« በራስዋ ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት ፤ »
፬ ፥ ፩፦ አክሊል
አክሊል
፦ የክብር ምልክት የክብር መጨረሻ ነው። የሚቀዳጁትም ትልቅ ማዕረግና ታላቅ ክብር ያላቸው ሰዎች ናቸው።
እግዚአብሔር አሮንን እና ልጆቹን ለክህነት ከለያቸው ( ከመረጣቸው ) በኋላ መፈጸም የሚገባውን ሥርዓት ለሙሴ
ሲነግረው ፦ «ወታነብር አክሊለ ዲበ ርእሱ ፥ ወታነብር ቀጸላ ዘወርቅ ዲበ አክሊሉ ፤ አክሊልንም በራሱ ላይ
ታደርጋለህ ፥ የወርቁንም ቀጸላ በአክሊሉ ላይ ታኖራለህ ፤ » ብሎታል። ዘጸ ፳፱ ፥ ፮ ። ይህም ስለ ሊቀካህናቱ
ክብር ነው። ስለ ታቦቱ ክብርም ፦ « በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው ፥ በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ
አክሊል አድርግለት ፤ » ብሎታል። ዘጸ ፳፭፥፲፩።
አክሊል ( ዘውድ ) የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው። የብዕለ ሥጋ ፍጻሜው ዘውድ እንደሆነ ሁሉ የብዕለ ነፍስም ፍጻሜ አክሊል (
ዘውድ ) የምትባል መንግሥተ ሰማያት ናትና ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ « እኔ ፈጽሜ ግዳጄን ጨርሻለሁ ፥
የማርፍበት ዕድሜዬም ደርሷል። መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ ፥ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ ፥ ሃይማኖቴንም ጠብቄአለሁ።
እንግዲህ የክብር አክሊል ይቆየኛል ፤ ( መን ግሥተ ሰማያት ተዘጋጅታልኛለች )፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው
እግዚአብሔር በዚያ ቀን ለእኔ ያስረክባል ፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም። » ብሏል።
፪ኛ ጢሞ ፬ ፥ ፮ - ፰። ይህም ፦ « እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን ፥ የሕይወት አክሊልንም እሰጥሃለሁ ።»
ከሚለው ጋር አንድ ነው። ራእ ፫ ፥ ፲።
እንግዲህ
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አክሊል ተቀዳጅታ መታየቷ ከፍጥረታት ሁሉ በላይ የሆነውን ክብሯን ፥ ማዕረጓን
የሚመሰክር ነው። እርሷ መልዕልተ ፍጡራን መትህተ ፈጣሪ ናትና። በሌላ በኲል ደግሞ የነቢያት የሐዋርያት ፥ የጻድቃን
የሰማዕታት ፥ የሊቃውንት የካህናትና የምእመናን አክሊል እርሷ ናት። ቅዱስ ኤፍሬም ፦ «አክሊለ ምክሕነ ፥
ወቀዳሚተ መድኃኒትነ ፥ ወመሠረተ ንጽሕነ ፤ የመመኪያችን ዘውድ ፥ የደኅንነታችን መጀመሪያ ፥ የንጽሕናችንም መሠረት
፤» በማለት በውዳሴ ዘሠሉስ የተናገረው ለዚህ ነው።
፬ ፥ ፪ ኮከብ
ኮከብ፦
በቁሙ ሲተረጐም ፦ የብርሃን ቅንጣት ፥ የጸዳል ሠሌዳ ፥ ብርሃን የተሣለበት ፥ የሰማይ ጌጥ ፥ የጠፈር ፈርጥ ፥
ሌሊት እንደ አሸዋና እንደ ፋና በዝቶ የሚታይ ፥ የሚያበራ ፥ የፀሐይ ሠራዊት ፥ የጨረቃ ጭፍራ ማለት ነው።
የተፈጠረውም ሌሊቱን እንዲገዛ በሌሊት እንዲሰለጥን ነው። መዝ ፩፻፴፭ ፥ ፱ ። ከዋክብት በሰዎች ዘንድ የማይቆጠሩ
ናቸው። በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ቁጥራቸው ይታወቃል ፥ በየስማቸውም ይጠራቸዋል። መዝ ፩፻፵፮ ፥ ፬ ። እግዚአብሔር
አብርሃምን ወደ ሜዳ አወጣውና ፦ « ወደ ላይ ወደ ሰማይ ተመልከት ፥ ልትቆጥራቸው ትችል እንደሆነ ከዋክብትን
ቊጠራቸው ። ዘርህም እንደዚሁ ነው። » ብሎታል። ዘፍ ፲፭ ፥ ፭። በከዋክብት የተመሰሉት ከአብርሃም ወገን
የሚወለዱት ቅዱሳን ነገሥታት ፥ ቅዱሳን ነቢያት ፥ ቅዱሳን ሐዋርያት ፥ ቅዱሳን ካህናት ፥ ቅዱሳን ሊቃውንት ፥
ቅዱሳን ምእመናን ናቸው። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ነቢዩ ዳንኤል ፦ « ጥበበኞችም እንደ ሰማይ ጸዳል ፥ ከጻድቃንም
ብዙዎች እንደ ከዋክብት ለዛለዓለም ያበራሉ። » ብሏል። ዳን ፲፪ ፥ ፫። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ፦ « ኮከብ
እምኮከበ ይኄይስ ክብሩ ፤ ኮከብ ከኮከብ ክብሩ ይበልጣልና፤ » ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፲፭ ፥ ፵፩ ።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም « ወዲበ ርእሳኒ አክሊል ዘዐሠርቱ ወክልኤቱ ከዋክብት ፤ » አሥራ ሁለቱ ከዋክብት እንደ እንቊ ፈርጥ ያለበት አክሊል (
ዘውድ ) በራሷ ላይ ተቀዳጅታ ( ደፍታ ) ታይታለች። አሥራ ሁለት መሆናቸው የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ምሳሌ ነው።
አንድም ከዋክብት ሌሊትን እንዲገዙ እርሷም የጨለማን አበጋዝ ዲያቢሎስን እስከነ ሠራዊቱ እንደምትገዛቸው ያመለክታል።
በከዋክብት የተመሰሉ ሐዋርያትም ገዝተዋቸዋል። ማቴ ፲ ፥ ፩ ፣ ማር ፲፮ ፥ ፲፯።
፭ ፦ « ሴቲቱም ጸንሳ ነበረች፤ »
ይህች
ፀሐይን ተጐናጽፋ ፥ ጨረቃን ተጫምታ ፥ አሥራ ሁለት ከዋክብት እንደ እንቊ ፈርጥ ያለበት አክሊል ተቀዳጅታ
የታየችው ሴት ፀንሳ ነበር። ይህ ሁሉ ክብር የተሰጣት ፦ ከእግዚአብሔር የተላከ ቅዱስ ገብርኤልና መንፈስ ቅዱስ
ያደረባት ቅድስት ኤልሳቤጥ እንደመሰከሩት ፦ ከሴቶች ሁሉ ተለይታ የተባረከች በመሆኗ ነው። ( መርገመ ሥጋ መርገመ
ነፍስ ያልነበረባት ፥ እያማለደች በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን የምታሰጥ ናት )። ሉቃ ፩ ፥ ፳፰ ፣ ፵፪ ።
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ግብር ነው። በመሆኑም ቅድመ ፀኒስ ፥ ጊዜ ፀኒስ ፥ ድኅረ
ፀኒስ ድንግል ናት። « ናሁ ድንግል ትፀንስ ፥ ወትወልድ ወልድ ፤ እነሆ ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች ፥ ወልድንም
ትወልዳለች ፤ » እንዳለ። ኢሳ ፯ ፥ ፲፬ ። እመቤታችን፦ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፦ « ወናሁ ትፀንሲ ፥
ወትወልዲ ወልደ ፤ ወትሰምዪዮ ስሙ ኢየሱስ። እነሆ በድንግልና ትፀንሻለሽ ፥ ወልድንም ትወልጃለሽ ፤ ስሙንም
ኢየሱስ ትዪዋለሽ ። » ባላት ጊዜ ፥ «እም አይቴ ረከብከ ዘከመዝ ብሥራተ ፥ ዘእንበለ ምት
እምድንግል ፅንሰተ ፤ ወዘእንበለ ዘርዕ እምድር ዕትወተ። ምድር ያለ ዘር ታፈራ ዘንድ ፥ ሴት ያለ ወንድ ትፀንስ
ዘንድ ፥ እንዲህ ያለ የምሥራች ከማን አገኘኸው ? » ብላዋለች። እርሱም ፦ « ያንቺ ፅንስ እንደ ሌሎች ሴቶች
ፅንስ አይደለም። መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል ፥ ኃይለ ለዑል ወልድም ሥጋሽን ይለብሳል። » ብሏታል። ሉቃ ፩ ፥ ፴፩ ፣
፴፬
፮፦ « ለመውለድም ምጥ ተይዛ ትጮህ ነበር፤ »
«
ምጥ » የመጣው ከበደል በኋላ በእርግማን ነው። እግዚአብሔር ሔዋንን ፦ « አብዝኆ አበዝኆ ለኃዘንኪ ወለሥቃይኪ ፥
ወበፃዕር ለዲ ኲሎ መዋዕለ ሕይወትኪ። ኃዘንሽን ፥ ፃዕርሽን አበዛዋለሁ ፤ በምትወልጂበት ጊዜ ሁሉ በፃር በጋር
ውለጂ። » ብሏታል። ዘፍ ፫ ፥ ፲፮ ።
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም ግን የአዳምና የሔዋን መርገም ያልወደቀባት ንጽሕት ዘር ናት ። በመሆኑም ፃር ጋር
አልነበረባትም። ከሴቶች ሁሉ ተለይታ የተባረከች በመሆኗ መንፈስ ቅዱስ ከልማደ አንስት ጠብቋታል። የሚያስምጥ
የሚያስጨንቅ በዘር በሩካቤ ተፀንሶ የሚወለድ ነው። የእመቤታችን ፅንስ ግን እንበለ ዘርዕ በመንፈስ ቅዱስ በድንግልና
፥ የምትወልደውም በድንግልና በመሆኑ ምጥ ፥ ጭንቅ የለም።
ታዲያ ፦ « ለምን ? ለመውለድም ምጥ ተይዛ
ትጮህ ነበር ፤ » አለ ፥ እንል ይሆናል። ምጥ ያለው፦ ነፍሰ ጡር ሆና ለመቆጠር እስከ ዳዊት ከተማ እስከ
ቤተልሔም መጓዟን ፥ ማደሪያ አጥታ በከብቶች በረት አድራ መውለዷን ፥ በሄሮድስ ምክንያት መሰደዷን ፥ በአጠቃላይ
በአይሁድ የዘወትር ጥላቻ የደረሰባትን መከራ ነው። ምክንያቱም ጽኑዕ መከራ ምጥ ይባላልና ነው።
- «
አቤቱ በመከራዬ ጊዜ አሰብኹህ ፥ በጥቂት መከራም ገሠጽኸኝ። የጸነሰች ሴት ለመውለድ ስትቀርብ እንደምትጨነቅና
በምጥ እንደምትጮህ ፥ አቤቱ ፥ እንዲሁ በፊትህ ለወዳጅህ ሆነናል። አንተን በመፍራት አቤቱ ፥ እኛ ፀንሰናል ፥
ምጥም ይዞናል። » ኢሳ ፳፮ ፥ ፲፮።
- «
አሁንስ ለምን ክፉ መከርሽ ? እንደምትወልዽ ሴት ምጥ የደረሰብሽ ፥ ንጉሥ ስለሌለሽ ነውን? ወይስ መካሪ
ስለጠፋብሽ ነውን? የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ እንደምትወልድ ሴት አምጪ ፥ ታገሺም ፤ አሁን ከከተማ ትወጪያለሽና ፥
በሜዳም ትቀመጫለሽ ፥ ወደ ባቢሎንም ትደርሻለሽ ፥ በዚያም ያድንሻል። » ሚክ ፩ ፥ ፱።
- « ሕዝብ በሕዝብ ላይ ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ ፤ በየሀገሩም ረኃብ ፥ ቸነፈርም ፥ የምድር መናወጥም ይሆናል። እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። » ማቴ ፳፬ ፥ ፯ ።
ነገረ ማርያም ክፍል ፫
«ወአስተርአየ ካልእ ተአምር በውስተ ሰማይ፤» ቅዱስ ዮሐንስ የመጀመሪያውን ምልክት ፦ ታላቅ ፥ ገናና ፥ ደገኛ ካለ በኋላ የሁለተኛውን ግን ቀለል አድርጐ « ሌላ ምልክት በሰማይ ታየ ፤» ብሏል።
፯ ፥ ፩ ታላቅ ቀይ ዘንዶ፤
ይኸውም፦ «
አርዌ ዐቢይ ወቀይሕ ፤» እንዲል፦ እሳት የሚመስል ቀይ ዘንዶ ነው። ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶችም ነበሩት፤
በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩት። ዘንዶ (እባብ) የተባለውም ፦ የቀደመ ሰው አዳምን፦ እግዚአብሔርን ያህል
አባት ፥ ገነትን ያህል ርስት ያሳጣው ጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስ ነው። ምክንያቱም በሥጋ ከይሲ ተሰውሮ አዳምንም
ሔዋንንም አስቷቸዋልና። « እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው ከምድር አራዊት ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበር ፤ »
ይላልና። ዘፍ ፫ ፥፩። እሳት የሚመስል ቀይ መባሉም ተፈጥሮው ልክ እንደ ሌሎቹ መላእክት ከእሳትና ከነፋስ በመሆኑ
ነው። ይኽንንም ቅዱስ ዳዊት ፦ «መላእክቱን መንፈስ ፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርጋቸው።» በማለት
ገልጦታል።መዝ ፩፻፫ ፥ ፬። ይህም እሳትና ነፋስ ኃያላን ፥ ረቂቃን እንደሆኑ ሁሉ መላእ ክትም፦ ኃያላን ፥ ረቂቃን
፥ ፈጣኖች ፥ ፈጻሚያነ መፍቅድ ናቸው ፥ ለማለት ነው።
፰ ፥ ሰባት ራሶች፤
ሰባት
በዕብራዊያን ፍጹም ቁጥር ነው። ዲያቢሎስም ፍጹም ኃጢአትን ያሠራል። ሰባት ራሶች የተባሉትም ሰባቱ አርዕስተ
ኃጣውእ (ዋና ዋና ኃጢአቶች ) ናቸው። እነዚህን ዋና የተባሉትን ፥ ከእግዚአብሔር አንድነት የሚለዩትን ፥ ከክብሩም
የሚያርቁትን ኃጢአቶች በሰው አድሮ ያሠራው ሲያሠራም የሚኖረው እርሱ ነው።
፰፥፩፦ ኃጢአተ አዳም፤
«እባብም
ለሴቲቱ ፦ ሞትን አትሞቱም ፤ ከእርሷ በበላችሁ ቀን ፥ ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ ፥ እንደ እግዚአብሔርም እንደምትሆኑ
፥ መልካምንና ክፉን እንደምታውቁ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።» አላት። ዘፍ ፫፥፬። አዳምና ሔዋን በዚህ
ምክር የሰባት ዓመት ንጽሕናቸውን አቆሸሹ ፥ ቅድስናቸውን አረከሱ፤ ከማዕረጋቸው ተዋረዱ ፥ ከሥልጣናቸው ተሻሩ ፥
ከገነት ተባረሩ። ዘፍ ፫ ፥ ፲፬።
፰፥፪ ፦ ቅትለተ አቤል፤
አዳም
አቤልን «ይህ ብሩኅ ገጽ ያለው ልጄ መንግሥቴን የሚወርሰው እርሱ ነው፤» ይለው ነበር። ሁለተኛም ከቃየል ጋር
መንታ ሆና የተወለደችውን መልከ መልካም አጋባው። ሦስተኛም አቤል ከበጐቹ በኲራት ፥ ቀንዱ ያልከረከረውን ፥ ጠጉሩ
ያላረረውን ፥ጥፍሩ ያልዘረዘረውን ጠቦት መሥዋዕት እድርጐ ቢያቀርብ እግዚአብሔር ተቀበለው። በዚህ ሁሉ ምክንያት
ቃየል ተበሳጨ። ልቡ አዘነ ፥ ፊቱ ጠቆረ። በዚህን ጊዜ ሰይጣን አዛኝ መስሎ ቀርቦ ነፍስ መግደልን ለቃየል
አስተማረው። አንዱ ሰይጣን በሰው አምሳል ሁለተኛው ደግሞ በቊራ አምሳል ለቃየል ታዩት። በሰው አምሳል የታየው በቊራ
አምሳል የታየውን በደንጊያ ሲገድለውም አየ። ከዚህ በኋላ ነው ወንድሙን አቤልን የገደለው። ዘፍ ፬፥፩-፰።
፰፥፫፦ ጥቅመ ሰናዖር ፤
የዓለም
ሁሉ ቋንቋ አንድ ፥ ንግግሩም አንድ ነበር። ሰይጣን ልባቸውን አነሣሥቶት ጫፉ ሰማይ የሚደርስ ግንብ ለመሥራት
በሰናዖር ሜዳ ተሰባሰቡ። ይኸውም ስለ ሁለት ነገር ነው። አንደኛው ፦ እንደ ኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ ቢመጣ ማምለጫ
እንዲሆናቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ እግዚአብሔርን ለመውጋት ነው። በመጽሐፈ ኲፋሌ እንደ ተጻፈው አርባ ሦስት ዓመት
ፈጅቶባቸዋል። ከዚህ በኋላ ፍላፃቸውን ወደ ላይ ቢወረውሩት በአየር ላይ ያሉ አጋንንት በምትሀት ደም እየቀቡ
ይሰዱላቸው ነበር። አሁን ገና ባለቤቱን ወጋነው፥ ቀኝ አዝማቹን ፣ ግራ አዝማቹን ወጋነው ፥ አጋፋሪውን ወጋነው
ይባባሉ ጀመር። ሥላሴ ፍጥረቱ ሁሉ በከንቱ ቢጐዳ አይወዱምና ለኃጢአት እንዳይግባቡ ሰባ ሁለት ቋንቋ አመጡባቸው።
እነርሱም በምንም መግባባት ስላልቻሉ ትተውት ወረዱ። ግንቡንም ጣዖት አድርገው እንዳያመልኩት ሥላሴ ጽኑ ነፋስ
አስነሥተው በትነውታል። በዚህም ምክንያት ባቢሎን ተብሎአል። ባቢሎን ማለት ዝርው (የተበተነ) ማለት ነው። አንድም
ሕዝቡ በቋንቋ ፥ በነገር ተለያይተው በቦታ ስለተበተኑበት ባቢሎን ተብሏል። በዚህን ጊዜ ቋንቋ ከሦስት ተከፍሏል።
ሠላሳ ሁለቱ በነገደ ካም ፥ ሃያ አምስቱ በነገደ ያፌት ፥ አሥራ አምስቱ በነገደ ሴም ቀርቷል።
፰፥፬ ፦ ኃጢአተ ሰዶም፤
የሰዶማውያን
ኃጢአታቸው ወንድ ከወንድ ፥ ሴት ከሴት መጋባታቸው ነው። ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፦ «ስለዚህም
እግዚአብሔር ክፉ መቅሠፍትን አመጣባቸው ፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባቸውን ትተው ለባሕርያቸው የማይገባውን
ሠሩ። ወንዶችም እንዲሁ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን ትተው በፍትወት ተቃጠሉ፤ እርስ በራሳቸውም እየተመላለሱ ፥
ወንዶች በወንዶች ላይ የሚያዋርዳቸውን ነውር ሠሩ፤ ነገር ግን ፍጻሜአቸውን ያገኛሉ፤ ፍዳቸውን ያገኛሉ፤ ፍዳቸውም
በራሳቸው ይመለሳል።» በማለት ገልጦታል። ሮሜ ፩፥፳፮። «የአምላክህንም ስም አታርክስ ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ፤
ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ ፤ ጸያፍ ነገር ነውና።» የሚለውን አስቀድሞ በሕገ ልቡና የተሰጣቸውን
ሕግ ተላለፉ። ዘሌ ፲፰፥፳፪። እግዚአብሔርም በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን
አዘነበ፤ እነዚያም ከተሞች በዙሪያቸው ያለውንም ሁሉ ፥ በከተሞችም የሚኖሩትን ሁሉ ፥ የምድርንም ቡቃያ ሁሉ
ገለበጠ። አብርሃምም ወደ ሰዶምና ገሞራ ወደ አውራጃዎቿም ሁሉ ተመለከተ ፤ እነሆም፥ ነበልባል ከምድር እንደ ምድጃ
ጢስ ሲወጣ አየ ይላል። ዘፍ ፲፱፥፳፫።
፰፥፭፦ ኃጢአተ እሥራኤል፤
የእሥራኤል
ኃጢአት ከአምልኮተ እግዚአብሔር ወደ አምልኮተ ጣዖት ማፈግፈግ ነበር። እግዚአብሔር ከባርነት ቤት ካወጣቸው በኋላ
በሲና ምድር በዳ የወርቅ ጥጃ ሠርተው በማምለክ አሳዝነውታል። ዘጸ ፴፪፥፬። ከሞአብ ልጆች ጋር ባመነዘሩም ጊዜ
ብዔልፌጎር የተባለውን ጣዖት ተከትለው ነበር። ዘኁ ፳፭፥፩። ብዙ ጊዜ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ትተው
በዙሪያቸው ያሉ አሕዛብን አማልክት በመከተል በመስገድም እግዚአብሔርን አስቆጥተውታል። እርሱም ለጠላቶቻቸው እያሳለፈ
ይሰጣቸው ነበር። መሳ ፪፥፲፩ ፣ ፪ኛ ነገ ፲፯፥፯ ፣፳፩፥፲፩። በአጠቃላይ አነጋገር ጣዖትን ማምለክ የአጋንንት
ማኅበርተኛ መሆን ነው። ፩ኛ ቆሮ ፲፥፳ ።
፰፥፮፦ ቅትለተ ዘካርያስ፤
ካህኑ
ዘካርያስ ከሚስቱ ከኤልሳቤጥ ጋር በእግዚአብሔር ሥርዓትና በትእዛዙም ሁሉ ያለ ነውር የሚሄዱ ጻድቃን ነበሩ። ሉቃ
፩፥፮። ዘመን ከተላለፋቸው በኋላ በዕርግና ፥ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስን ወለዱ። ሉቃ
፩፥፰ ፣ ፶፯። ጌታ በወንጌል እንደተናገረ ዘካርያስን በቤተ መቅደሱና በመሠዊያው
መካከል እንዳለ ገድለውታል። ማቴ ፳፫፥፴፭። የዘካርያስም ደም ሰበዓ ዘመን ሙሉ ሲፈላ እንደ አቤል ደም ሲካሰስ
ኖሯል። ታሪኩ እንዲህ ነው። ለአንድ ዓላዊ ፦ ሲፀነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ ፥ ሲወለድ የከፈተ አንድ ሕፃን
ከካህኑ ከዘካርያስ ቤት አለልህ አሉት። እርሱም ዘካርያስን አስጠርቶ ቢጠይቀው፦ «አዎን አለ፥ምነው ጠየቅኸኝ?»
አለው። ዓላዊውም «ይኽንኑ እንድትነግረኝ ነው ፥ በል ሂድ ፤» ሲል መለሰለት። በዚህን ጊዜ ዘካርያስ «ይህ ዓላዊ
ያለ ምክንያት አልጠየቀኝም ፤ ሀብት ሳላሳድርበት ልጄን ሊያስገድለው ነው።» ብሎ ከቤተ መቅደስ አግብቶ ሲጸልይለት
ዓላዊው «ልጁን ግደሉ፤» ብሎ ጭፍራ ላከ። ከቤት ቢሄዱ አጡት። ወዲያው የእግዚአብሔር መልአክ ለኤልሳቤጥ
ተገለጠላትና ፦ ይህ ዓላዊ ልጅሽን ሊያስገድልብሽ ነውና ፥ ወደ ገዳም (በረሀ) ይዘሽው ሂጂ ፤» አላት። እርሷም
ልጁን ከዘካርያስ ተቀብላ የተባለችውን አድርጋለች። በመጨረሻም የተላኩት ጭፍሮች ወደ ቤተ መቅደስ ቢሄዱ ዘካርያስን
አግኝተው ገድለውታል።
፰፥፯ ፦ ሞተ ወልደ እግዚአብሔር፤
በአይሁድ
ልቡና አድሮ ፥ እንዳይሰሙ ፥እንዳይለሙ አዕምሮአቸውን አሳውሮ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገረፈ
ያሰቀለ ሰይጣን ነው። ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠር ድረስ ሰድስት ሺህ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ጅራፍ
ገርፈውታል። ራስ ራሱን በዘንግ ቀጥቅጠውታል። ይኽም አልበቃ ብሎ ልቡ ድረስ እስኪሰማው አክሊለ ሦክ ደፍተውበታል።
እጆቹን የኋሊት አስረውታል። በጥፊ መትተውታል ፥ አክታቸውን ተፍተውበታል ( ከብርሃናዊ ፊቱ ላይ ለጥፈውበታል )።
ከባድ መስቀል አሸክመውታል ፥ ከምድር ላይ አዳፍተውታል። ሳዶር ፥ አላዶር ፥ ዳናት ፥አዴራ ፥ ሮዳስ በተባሉ
አምስት ቀኖት ቸንክረውታል። መራራ ሐሞት አጠጥተውታል ፥ ጐኑን በጦር ወግተውታል። በመጨረሻም «ተፈጸመ፤» በማለት
በፈቃዱ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷል። ዮሐ ፲፱ ፥፴።
፱፦ አሥር ቀንዶች፤
ቀንድ በምሳሌነት፦ ኃይልን ፥ ክብርን ፥ ሥልጣንን ፥ ንግሥናን ያመለክታል።
- «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ቀንዶች ሶርያውያንን ትወጋቸዋለህ።» ፩ኛ ነገ ፳፪፥፲፩።
- «ሐናም ጸለየች፤ እንዲህም አለች፦ ልቤ በእግዚአብሔር ጸና፤ ቀንዴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ከፍ ከፍ አለ።» ፩ኛ ሳሙ ፪፥፩
- «ለንጉሦቻችንም ኃይልን ይሰጣል፤ የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል።» ፩ኛ ሳሙ ፪፥፩።
- «በዚያ ለዳዊት ቀንድን አበቅላለሁ፤» መዝ ፩፻፴፩ ፥ ፲፯።
- «በዚያ ቀን ለእሥራኤል ቤት ቀንድን አበቅላለሁ፤» ሕዝ ፳፱፥፳፩።
እነዚህ
ሁሉ ለፍጻሜው ለኢየሱስ ክርስቶስ የተነገሩ ናቸው። ይኽንንም ጻድቁ ካህን ዘካርያስ አድሮበት የሚኖር መንፈስ ቅዱስ
ምሥጢሩን ፥ ጥበቡን ቢገልጥለት፦ «ይቅር ያለን ፥ ለወገኖቹም ድኅነትን ያደረገ የእሥራኤል አምላክ እግዚአብሔር
ይመስገን ፤ ከባርያው ከዳዊት ቤት የምንድንበትን ቀንድ አስነሣልን ፤ ከጥንት ጀምሮ በነበሩ በቅዱሳን ነቢያት አፍ
እንደተናገረ። ከጠላቶቻችን እጅ ከሚጠሉንም ሁሉ እጅ ያድነን ዘንድ። ቸርነቱን ከአባቶቻችን ጋር ያደርግ ዘንድ ፥
ቅዱስ ኪዳኑንም ያስብ ዘንድ። ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሓላ ያስብ ዘንድ።» በማለት ተናግሯል። ሉቃ
፩፥፷፯።
፱ ፥ ፩፦ የሳጥናኤል ውድቀት፤
ሰይጣን
በክህደቱ አጥቶት እንጂ ክብርም ፥ ኃይልም ሥልጣንም ነበረው። በአሥሩ የመላእክት ከተሞች በተሾሙ አሥር የመላእክት
አለቆች ላይ የአለቃ አለቃ ነበር። የተፈጠረው የመላእክት አለቃ ሆኖ ነው። ይኽንንም ቀሌምንጦስ ተናግሮታል።
እግዚአብሔር መላእክትን በነገድ መቶ ፥ በከተማ አሥር አድርጐ ፈጥሮ ተሰወራቸው። ይህም ካልፈለጉኝ አልገኝም ፥
ባሕርዬም አይመረምርም ሲላቸው ነው። ወዲያው፦ «እኛ ምንድር ነን? ከየት መጣን ? ማንስ ፈጠረን? በራስ በራሳችን
ተፈጠርን ? ወይስ ከሌላ ነው?» አሉ። ዲያቢሎስ ከበታቹ እንዲህ ሲሉ ሰማ። ከበላዩ ደግሞ «ፈጠርኳችሁ፤» የሚል
አጣ። በቦታው ከሁሉ በላይ አድርጎ ፈጥሮት ነበርና «እኔ ፈጠርሁ፤» ብሎ አሰበ ፥ አስቦም አልቀረ «እኔ
ፈጠርኋችሁ፤» አለ። ይኽን ሰምተው «ሰጊድ ይገባዋል፤» ያሉ አሉ። «እኛም እንደ እርሱ ነን፤» ያሉም አሉ። «
አምላክ ነኝ ያለስ ከእርሱ በቀር ሌላ የለምና ፥ ይሆንን?» ብለው የተጠራጠሩ አሉ። ሀልዎተ እግዚአብሔርን
ሳይመረምሩ የቀሩም አሉ። እኲሌቶቹ ግን ፦ «በምን ፈጠርኋችሁ ይለናል። በቦታ ከበላይ በመሆን ፈጠርኋችሁ እንዳይለን
፥ እኛ የበታቾቻችንን መቼ ፈጠርናቸውና ነው?። በዚያውስ ላይ ምቀኞቹ አይደለንም፤ በእውነት ፈጣሪ ከሆነ ፈጥሮ ያሳየን ።» ብለው፦ «ፈጥረህ አሳየን፤» አሉት። እርሱም እፈጥራለሁ ብሎ ፥ እጁን ወደ እሳት ቢጨምር ፈጀውና «
ዋይ» አለ። በዚህን ጊዜ «በአፍአ ያለውን (የሚነገረውንና እና የሚሠራውን ብቻ የሚያውቅ) አምላክ ቢሆን ነው
እንጂ ውሳጣዊውን (ልብ ያሰበውን የሚያውቅ) አምላክ ቢሆን ኖሮ ገና ሳስበው ለምን አሰብከው ፥ «ባለኝ ነበር ፤»
አለ። ወዲያው ልቡን ተሰማውና «ዋይ» አለ። እግዚአብሔር ግን ፈወሰው። ይህንንም ማድረጉ ንስሐ ቢገባ እንደሚምረው ሲነግረው ነበር።
ከዚህ
በኋላ በመላእክት ሽብር ቢጸናባቸው፦ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል፦ «ንቁም በበህላዌነ እስከ ንረክቦ ለአምላክነ ፤
አምላካችንን እስክናገኘው ድረስ በየህልውናችን ጸንተን እንቁም ፤» በማለት አጽንቷቸዋል። ይህም በጎ አርበኛ ጦር
በተፈታ ጊዜ «አይዞህ ባለህበት ጽና፤» ብሎ እንደሚያጸናው ማለት ነው።« ወበእንተዝ ደለዎ ይፁር ዜናሃ ለማርያም ፤
በዚህ ምክንያት የድንግል ማርያምን ዜና ያደርስ ፥ ብሥራቷን ይናገር ዘንድ ተገባው ፤ » እንዲል ፥ ብሥራት ተሰጥቶታል። «በስድስተኛው ወር (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ፥ ስድስተኛው ሺህ ደግሞ ሲጀምር) መልአኩ ገብርኤል . . . ወደ አንዲት ድንግል ተላከ» ይላል። ሉቃ ፩፥፳፮።
እግዚአብሔርም
ጨርሶ ሳያስታቸው ብሎ እርሱ (ሳጥናኤል) በሌለበት በኲል በምሥራቅ ባሕረ ብርሃንን አፍስሶላቸዋል። ከዚህም ጋር
ስሙ የተጻፈበት መጽሔተ ብርሃን ቢሰጣቸው አንድነቱ ሦስትነቱ(ምሥጢረ ሥላሴ) ተገልጦላቸው « አሐዱ አብ ቅዱስ ፥
አሐዱ ወልድ ቅዱስ ፥ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤» ብለው አመስግነውታል። እርሱን ግን ባደረው ጨለማ ጠቅልሎ
በዕለተ እሑድ ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት ወደ ኢዮር
አውርዶታል።ከሰባቱ ሰማያት ሦስቱ ፦ ኢዮር ፥ራማ፥ኤረር የመላእክት ናቸው። በውስጣቸውም አስር የመላእክት ከተሞች
አሉ። በእነርሱም ላይ አስር አለቆች ተሹመዋል። እግዚአብሔር ሳጥናኤል በሌለበት በኲል ባሕረ ብርሃንን ያፈሰሰላቸው
«እኔ ፈጠርኩ » እንዳይል ነው።
ሳጥናኤል
በኢዮር ሆኖ በዕለተ ሠሉስ የተፈጠሩ ዕፅዋት፥ አዝርዕት ፥ አትክልት ፥ጽጌያትን አይቶ እንዳያደንቅ፦ «እንዲህ
አድርጐ አከናውኖ የፈጠረለት ቢኖር ነው፥ » አለ። እግዚአብሐርም «ከወደድሃት በዚያ ላኑርህ ፤» ቢለው «ደገኛይቱን
ማን ከልክሎኝ ፤» አለ። ከዚህ በኋላ ለሚካኤልና ለገብርኤል «እናንተ ኢየሩሳሌም ሰማያት ይሏችኋል ፥ ሰባቱ
ሰማያት እንኳ አያህሏትም። እኛ ከጩኸት በቀር የተጠቀምነው የለም። ገዢ ነኝ የሚለውን ወግተን እጅ እናድርግ።» ብሎ
ላከባቸው። እነርሱም የተላኩትን ከንጉሥ ከተማ እንደገባ ዕብድ ውሻ አድርገው ሰደዷቸው። ተመልሰውም አልተቀበሉንም
ቢሉት ፦ «ቀለምጺጸ እሳት (የእሳት ፍንጣሪ) የሆኑ ሚካኤል ገብርኤል በእኔ ዘንድ ምን ቁም ነገር ናቸው። ይልቁንስ
ኑ ተሸከሙኝና እንሂድ ፤» አላቸው። በዚህን ጊዜ በአርባዕቱ እንስሳ (በኪሩቤል) አምሳል አራት ሁነው ተሸክመውት
ሽቅብ እወጣለሁ ቢል ኃይል ተነሥቶታል። ወደ ታች እንጂ ወደ ላይ መውጣት የማይቻለው በመሆኑም ፦ «ጐየ እግዚእ
ምስለ አርያሙ፤ እግዚአብሔር ሰማዩን (ጽርሐ አርያምን) ጠቅልሎ ሸሸ፤» ብሎ ተመለሰ።
ቅዱሳን መላእክት ግን ፍጥረትን ሲፈጥር እያዩ ያመሰግኑ ነበር። በዕለተ ረቡዕ ፀሐይ
፥ ከዋክብት ፥ ጨረቃ ፥ ሲፈጠሩ አይተው አመስግነው አመስግን ቢሉት ፦ «አንሰ ዕድው (ውፁዕ) እምዝንቱ ኅሊና፤»
እንዲል፦ «እኔ ከዚህ ውጪ ነኝ ፥ ባይሆን አራተኛ አድርጋችሁ ብታመሰግኑኝ እወዳለሁ፤» አላቸው። እነርሱም «ይህ
ስሑት ፍጥረት እንዲህ እያለ እስከ መቼ ሲታበይ ይኖራል?» ብለው ሄደው ቢገጥሙት ድል አደረጋቸው። ሁለተኛም
ቢገጥሙት ዳግመኛ ድል አደረጋቸው። በዚህን ጊዜ፦ «እኛስ ለአምላክነትህ ቀንተን ነበረ ፥ አንተ ግን ፈቃድህ ሳይሆን
ቀረ፤» ብለው ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱ ፦ «ፈቃዳችሁ ፈቃዴ ነው ፥ ነገር ግን ድል የሚነሣበትን
(የሚሸነፍበትን) ታውቁ ዘንድ ነው፤» ብሎ ስሙ የተጻፈበትን ትእምርተ መስቀል ሰጣቸው። ያን ይዘው በዕለተ ረቡዕ
ወደዚህ ዓለም አውርደውታል። በዚህን ጊዜ የእርሱ ወገኖች ለሦስት ተከፍለዋል። ሀለዎተ እግዚአብሔርን ሳይመረምሩ
የቀሩ በአየር ቀርተዋል። ይሆን ፥ አይሆን ብለው የተጠራጠሩ በዚህ ዓለም ቀርተዋል። « አምላክ ነው ፥ ሰጊድ
ይገባዋል፤» ያሉ አብረው እንጦሮጦስ ወርደዋል።
ነገረ ማርያም ክፍል ፬
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ግብር በድንግልና የፀነሰችውን አምላክ ፥ በድንግልና በወለደችው ጊዜ ፦
ሰብአ ሰገል ፦ ዜና ልደቱን በኮከብ ተረድተው ፥ በኮከብ ተመርተው ወደ ቤተልሔም መጥተው ነበር። ቤተልሔም ለመድረስ
ሁለት ዓመት ፈጅቶባቸዋል። አመጣጣቸው፦ « የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት አለ? » እያሉ ነበር። ሠራዊቶቻቸውም
ተከትለዋቸው ስለነበር ከተማይቱ ተሸበረች። ይህ ነገር ንጉሡ ሄሮድስን አስደነገ ጠው። በስውርም የካህናት
አለቆችንና ጻፎችን አስጠርቶ ንጉሥ ክርስቶስ የተወለደው በቤተልሔም እንደሆነ አረጋገጠ። ሊቃውንቱን፦ ትንቢት ጠቅሰው
፥ ሱባዔ ቆጥረው እንዲያስረዱት በስውር የጠራቸው ፦ ሰብአ ሰገል፦ «እኛ እንኳን አውቀን ስንመጣ እርሱ የአገሩ ንጉሥ ሆኖ ሳለ እስከ አሁን አያውቅም?» ይሉኛል ብሎ ውዳሴ ከንቱን ሽቶ ነው።
ንጉሥ
ሄሮድስ እንደገና ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን በጥንቃቄ ከእነርሱ ተረዳ። በልቡም፦
«ብላቴናው ለካ ሁለት ዓመት ሆኖታል፤» አለ። ሰብአ ሰገልንም «ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ ፥ ባገኛችሁትም ጊዜ
እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ ፤» ብሎ ወደ ቤተልሔም ሰደዳቸው። እንዲህም ማለቱ እውነት ሊሰግድለት
ሳይሆን በልቡ ክፉ አስቦ ነው። ነገር ግን ፦ ልቡናንና ኲላሊትን የሚመረምር አምላክ የልቡን ሐሳብ ለመላእክት
ገለጠላቸው። አንድም መላእክቱ የሰውን ልብ የማወቅ ጸጋው አስቀድሞ ተሰጥቷቸው ስለነበር ፥ በሄሮድስ በኲል
እንዳይመለሱ፥ በሌላ ጐዳና እንዲጓዙ ለሰብአ ሰገል ነግረዋቸዋል። መንገዱም ቀንቶላቸው የሁለትን ዓመት በአርባ ቀን
ገብተዋል።
በሄሮድስ
ግን አስቀድሞ ክፉ ያሳሰበው ፥ ዘንዶ የተባለው ዲያብሎስ ሙሉ በሙሉ አደረበት። ዙፋኑ ፥ መሣሪያው አደረገው።
ሰብአ ሰገል በሌላ ጐዳና ተመልሰው ወደ አገራቸው መግባታቸው ሄሮድስን ስላበሳጨው በቤተልሔምና በአውራጃዋ የሚገኙትን
ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆኑ አሥራ አራት እልፍ ሕፃናትን አሳረደ። ይኸውም ከዚህ መካከል አይጠፋም ተብሎ
በግምት ፥ በመላ ምት የሆነ ነው። በዚህም ፦ « ድምፅ በራማ ተሰማ ፥ ልቅሶና ብዙ ዋይታ ፤ ራሔል ስለ ልጆቿ
አለቀሰች፤ መጽናናትም አልወደደችም ፥ የሉምና። » የተባለው ቃለ ኤርምያስ ነቢይ ተፈጸመ። ኤር ፴፩ ፥፲፭። ዘንዶው
በፊቷ የቆመ እመቤታችን ግን መልአከ እግዚአብሔር እንደነገራቸው ሕፃኑን ይዛ ከጠባቂዋ ከጻድቁ ከዮሴፍ ጋር ወደ
ምድረ ግብፅ ሸሸች። ይኸውም «ልጄን ከግብፅ ጠራሁት፤» የተባለው ቃለ ሆሴዕ ነቢይ እንዲፈጸም ነው። ማቴ ፪፥፩-፲፰
፣ ሆሴ ፲፩፥፩። ልጅዋን ሊበላ የተባለውም ልጅዋን ሊገድል ማለት ነው።
የብረት በትር፤
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም ፦ አሕዛብን ሁሉ በብረት ዘንግ (በትር) የሚገዛቸውን ወንድ ልጅ (ወልደ አብን)
ወለደችው። ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከአብ ተወልዶ ወልደ አብ የተባለው ፥ ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ያለ አባት
ተወልዶ ወልደ ማርያም ተባለ። ወልደ አብ ወልደ ማርያም በተዋሕዶ ከበረ። የብረት በትር የተባለው፦ ከባሕርይ አባቱ
ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ ጽኑዕ ሥልጣኑ ነው። ቅዱስ ዳዊት ፦ «በትርህና ምረኲዝህ
እነርሱ ያጸናኑኛል፤» ያለው ሥልጣኑን ነው። መዝ ፳፪፥፬። በትር ለበጐች መጠበቂያ ፥ ለተኲላት መቅጫ እንደሆነ
ሁሉ ጽኑዕ የተባለ የእግዚአብሔር ሥልጣንም ለወገኖቹ መጠበቂያ ለአሕዛብ መቅጫ ነው። ወገኖቹ የተባሉትም ወደ ግብረ
አሕዛብ በሚሳቡበት ጊዜ እነርሱንም ለትምህርት ይቀጣቸዋል። በተጨማሪም ፦ «ወትርዕዮሙ በበትረ ሐጺን ፥ ወከመ ንዋየ
ለብሐ ትቀጠቅጦሙ። ደጋጐቹን በጽኑ ሥልጣን ትጠብቃቸዋለህ ፥ ክፉዎችን ግን እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃ
ትቀጠቅጣቸዋለህ።» የሚል አለ። መዝ ፪፥፱። ሸክላ ሠሪ ፦ ሠርታ የጨረሰችውን ዕቃ ነቅዕ ያገኘችበት እንደሆነ ፥
ምን ብትደክምበት ፥ እንደገና ከስክሳ አፍርሳ ታድሰዋለች። እርሱም ከአራቱ ባህርያት የተፈጠረ ሰው በሥጋ ድካም
ኃጢአት ቢሠራ (ነቅዕ ቢገኝበት) በንሰሐ ያድሰዋል። ቅዱስ ዮሐንስም ፦ « ወይወጽእ እምነ አፉሁ ሰይፈ በሊሕ ፥
ዘቦቱ ይቀሥፎሙ ለአሕዛብ። ወውእቱ ይርዕዮሙ በበትረ ኀጺን። አሕዛብን ይመታበት ዘንድ ፥ ከአፉ የተሳለ ሰይፍ
ይወጣል፤ (አሕዛብን የሚያጠፋበት መቅሠፍት ከአፉ በሚወጣ ቃል ይታዘዛል) ፤ በጎ በጎዎቹን በተወደደ በጽኑዕ ሥልጣኑ
ይጠብቃቸዋል።» በማለት ተመሳሳይ ነገር ተናግሯል። ራእ ፲፱፥፲፭።
ሥልጣን
ከእመቤታችን
ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ፦ « የእግዚአብሔር
ልጅ (ወልደ አብ) እንደመጣ (ከሰማይ ወርዶ ፥ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ፥ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በተዋሕዶ
ሰው ሁኖ እንደተወለደ ) ፥ እውነተኛም የሆነውን እግዚአብሔርን (የባህርይ አባቱን አብን) እናውቅ ዘንድ ልቡናን
እንደሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእግዚአብሔር ልጅ (በወልደ አብ) በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንኖራለን
፤ እርሱም እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።» እንዳለ። ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳። ቅዱስ ቶማስም ቢዳሰስለት
«ጌታዬ» ቢፈጀው «አምላኬ» ብሎታል። ዮሐ ፳፥፳፰። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ መለኰታዊ ባለሥልጣን ነው።
ጌታችን
በመዋዕለ ሥጋዌው ፦ (በተዋሕዶ ሰው በሆነበት ዘመን) ፦ በሥልጣን ያስተምራቸው ስለነበር ፥ ሕዝቡ በትምህርቱ
ተደንቀዋል። ማቴ ፯፥፳፱። አጋንንትንም በሥልጣንና በኃይል ያዝዛቸው ከሰውም ልቡና ያስወጣቸው ነበር። ሉቃ ፬፥፴፮።
በዚህ ሥልጣን ኃጢአትንም ያስተሰርይ ነበር። ማር ፪፥፲። «በሕይወትና በሞት ላይ ሥልጣን አለህና ፥ ወደ ሲኦል
በሮች ታወርዳለህ ፥ ከሲኦልም ታወጣለህ ፤» እንዲል በሁሉ ላይ ባለሥልጣን ነው። ጥበብ ፲፮ ፥፲፬። እርሱም ራሱ
«በሰማይና በምድር ሥልጣን አለኝ፤» ብሏል። ማቴ ፳፰፥፲፰። ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤውም ሲናገር ፦ « እኔ በፈቃዴ
አኖራታለሁ (ነፍሴን በፈቃዴ ከሥጋዬ እለያታለሁ )
እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት (ልለያት) ሥልጣን አለኝ ፥ ደግሞም ላነሣት (ነፍሴን ከሥጋዬ አዋህጄ
ላስነሣት) ሥልጣን አለኝ፤» ብሏል። ዮሐ ፲፥፲፰። ይህ ሥልጣኑ፦ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ ነው። በሥላሴ
በሥልጣን መበላለጥ ፥ በዘመን መቀዳደም የለምና። ይህም ይታወቅ ዘንድ፦ «እኔና አብ አንድ ነን፤» ብሏል። በመሆኑም
እመቤታችን የዚህ ባለሥልጣን እናት ናት።
«ልጅዋም ወደ እግዚአብሔር ፥ ወደ ዙፋኑም ተወሰደ።»
«ልጅዋም ወደ እግዚአብሔር ፥ ወደ ዙፋኑም ተወሰደ።»
ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት እለት ወደ ሰማይ ያረገ አይደለም። ወደ ሰማይ ያረገው በዚህ
ምድር ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ቆይቶ ፥ የማዳን ሥራውንም በመልዕልተ መሰቀል ከፈጸመ በኋላ ነው። ከሙታን
ተለይቶ በተነሣ በአርባኛው ቀን በርቀት (በመርቀቅ ) ሳይሆን በርኅቀት (ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ እያለ በመራቅ)
ዐርጓል። «እስከ ቢታንያም ወደ ውጭ አወጣቸው፤ እጁንም አንሥቶ በላያቸውም ጭኖ ባረካቸው። እየባረካቸውም ራቃቸው፤
ወደ ሰማይም ዐረገ።» ይላል። ሉቃ ፳፬፥፶። ደቀመዛሙርቱ ዓይኖቻቸው ከሰማዩ ላይ ተተክለው ፥ አንጋጠው የቀሩት
ለዚህ ነበር። « ይህንም እየነገራቸው ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ተቀበለችው ፤ እነርሱም ወደ እርሱ እያዩ ወደ ሰማይ
ዐረገ፤ ከዓይናቸውም ተሰወረ። » ቅዱሳን መላእክትም ነጫጭ ለብሰው በመገለጥ ፦ «እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ ፥ ወደ
ሰማይ እያያችሁ ለምን ቆማችኋል? » አሉአቸው። የሐዋ ፩፥፱። ቅዱስ ዳዊት ፦ እግዚአብሔር በእልልታ ፥ ጌታችንም
በመለከት ድምጽ አረገ።» በማለት አስቀድሞ ትንቢት ተናግሮ ነበር። መዝ ፵፮ ፥፭።
ይህ
እንዲህ ከሆነ ፥ ለምን ሕፃኑ ፥ «ወደ እግዚአብሔር፦ ወደ ዙፋኑም ተነጠቀ ፤ (ተወሰደ)፤» ተባለ እንል ይሆናል?
አምላካችን ከሰማይ ወረደ ፥ ከድንግል ማርያም ተወለደ ፥ በምድር ላይ ተመላለሰ የምንለው ከሰማይ ዙፋኑ ሳይነቃነቅ
ነው። ሥጋንና ነፍስን የተዋሐደው ፥ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት የተገለጠው ፥ ምሉዕ በኲለሄ የሆነ አምላክ ነው።
አባ ሕርያቆስ ይህንን ምሥጢር ሲያብራራ « ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል (አካላዊ ቃል ወልድ) ወደ አንቺ መጣ ፥
ሳይወሰን ፀነስሽው ፤ በላይ ሳይጐድል ፥በታችም ሳይጨምር በማኅፀንሽ ተወሰነ፤ » ብሏል። ቅዳሴ ማርያም ቁ ፵፮ ።
ቅዱስ ዮሐንሰ አፈወርቅም፦ « ዳግመኛ የዋህድ አነዋወሩ እንደምን እንደሆነ ፥ መውረዱም እንዴት እንደሆነ ፥
መወለዱም እንዴት እንደሆነ እንናገራለን። ከአባቱ ሳይወጣ መጣ ፥ ከአነዋወሩ ሳይለይ ወረደ። ከሦስትነቱ ሳይለይ መጣ
፥ ከአንድነቱም ሳይለይ ወረደ። ከዙፋኑ ሳይለይ በድንግል ማኅፀን አደረ። ምላቱ ሳይወሰን በማኅፀን ተፀነሰ ፥
በላይ ሳይጐድል በማኅፀን ተወሰነ ፥ በታችም ሳይጨመር ተወለደ። » ብሏል። ቅዳሴ ዮሐ አፈ ቁ ፳፭። ጌታችን
በተወለደ ዕለት ቅዱሳን መላእክት ወደ ሰማይ ቢወጡ እንደ ቀድሞው ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት ቢያገኙት ፦
« ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት ፤» ብለው አመሰገኑት። ወደ ምድር ሲመለሱ ደግሞ በእመቤታችን እቅፍ ቢያገኙት ፦
« ሰላምም በምድር ፥ ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ፤ » ብለዋል። ሉቃ ፪፥፲፬። እንግዲህ ፦ « ወደ እግዚአብሔር
፥ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ ፤» ማለት እንደ ሰውነቱ የተሰደደ አምላክ በሰማይ ዙፋኑ እንዳለ መናገር ነው። ከዙፋኑ ሳይለይ
ተወለደ ፥ እንደተባለው ከዙፋኑ ሳይለይ ተሰደደ ተብሎ ይነገራል።
« እግዚአብሔር ወደ አዘጋጀላት ቦታ ወደ በረሃ ሸሸች፤»
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም ፦ በዘመኑ ሁሉ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ ትጠበቅ ዘንድ እግዚአብሔር ወደ
አዘጋጀላት ቦታ ከዘንዶው (ከሄሮድስ) ፊት ወደ በረሃ ሸሸች። ይኸውም ወደ ምድረ ግብፅ ነው። በዚህም ፦ «እነሆ ፥
እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደ ግብፅ ይመጣል፤ የግብፅም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ ፥ የግብፅም ልብ በውስጥዋ
ይቀልጣል።» የሚለው ቃለ ኢሳይያስ ነቢይ ተፈጽሟል። ኢሳ ፲፱፥፩። ፈጣን ደመና የተባለችው እመቤታችን ናት። ቅዱስ
ዮሐንስ በቁጥር ወስኖ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ስድሳ ቀን ያለው አርባ ሁለቱን ወራት ማለትም በስደት የምታሳልፈውን
ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ነው። እግዚአብሔር ያዘጋጀላት ሥፍራ የተባለችውም ደብረ ቊስቋም ናት።
« ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉት፤»
እግዚአብሔር
ዲያብሎስን ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት ወደ መላእክት ሀገር ወደ ኢዮር ያወረደው ዕለቱን ወደ እንጦሮጦስ ማውረድ አቅቶት
አይደለም። ለንሰሐ ጊዜ ሲሰጠው እንጂ። እርሱ ግን ባለፈው እንደተመለከትነው በአመጹ ገፋበት። በዚህም ምክንያት
፦በሰማይ ሰልፍ (ጦርነት) ሆነ፤ ቅዱስ ሚካኤልና ሠራዊቱ ዲያብሎስንና ሠራዊቱን ተዋጉት። እርሱም ሠራዊቱን አሰልፎ
ተዋጋቸው። ነገር ግን፦ ስሙ የተጻፈበት ትእምርተ መሰቀል ተሰጥቷቸው ስለነበር አልቻላቸውም። ከዚህም በኋላ በሰማይ
ቦታ አልተገኘላቸውም። ዓለሙን ሁሉ የሚያሰተው ዲያብሎሰና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀድሞው እባብ
(በሥጋ ከይሲ ተሰውሮ አዳምንና ሔዋንን ያሳታቸው) ወደ ምድር ተጣለ፤ ሠራዊቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። በሰማይም፦
«የአምላካችን ማዳንና ኃይል ፥ መንግሥትም ፥ የመሢሑም ሥልጣን ሆነች፤ አባቶቻችንን ፥ በእግዚአብሔር ፊት በቀንና
በሌሊት ሲያጣላቸው የነበረው ከሳሽ ወድቋልና። እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ ፥ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት
፤ ሰውነታቸውን እስከ ሞት ድረስ አልወደዱምና። (በሰማዕትነት አልፈዋልና)። ስለዚህ ሰማያትና በውሰጣቸው የምትኖሩ
(ሰማያውያን መላእክትና በሰማያዊ ግብር ጸንታችሁ የምትኖሩ ቅዱሳን) ሆይ ፥ ደስ ይበላችሁ ፤ ነገር ግን ለምድርና
(ሳይጠመቁ በአሕዛብነት ለሚኖሩና) ለባሕር (ተጠምቀው ምግባር ለሌላቸው) ወዮላቸው ! ሰይጣን ጥቂት ዘመን
እንዳለው አውቆ ከክፉ መርዙ (ከጽኑዕ ማሳቱ) ጋር ወደ እናንተ ወረዷልና፤» የሚል ድምጽ ተሰማ። ይህ ከሰማይ
የተሰማ ድምጽ፦ ጥንት በዓለመ መላእክት ፥ ስሙ የተጻፈበት የብርሃን መላእክት የተሰጣቸው ቅዱሳን ዲያብሎስን ድል
መንሳታቸውን፦ በአዲስ ኪዳን ሥጋው በተቆረሰበት፥ ደሙ በፈሰሰበት የመስቀል ኃይል ዲያብሎስን ድል እያደረጉ ለሚኖሩ
ቅዱሳን አርአያ ፥ ምሳሌ አድርጐ አቅርቧል። አንድም አነጻጽሮ ተናግሯል።
«ወንድ ልጅ የወለደችውን ያቺን ሴት አሳደዳት፤»
ዘንዶው
ወደዚህ ዓለም እንደ ወረደ ፥ አንድም ፈጽሞ ድል እንደተነሣ (እንደተሸነፈ) ባወቀ ጊዜ፦ ወንድ ልጅ (ኃያል
ወልድን) የወለደችውን ያቺን ሴት (ከሴቶች ሁሉ ተለይታ የተባረከችውን እመቤት) በሄሮድስ አድሮ አሳደዳት። ለሴቲቱም
(ለድንግል ማርያም) ከዘንዶው ፊት ርቃ ፥ አንድ ዘመን (አንድ ዓመት) ፥ ዘመናትም (ሁለት ዓመት) ፥ የዘመንም
እኲሌታ (መንፈቅ) ማለትም ሦስት ዓመት ከስድሰት ወር ወደምትጠበቅበት ወደ በረሃ (ወደ ግብፅ) እንድትበርር ፥
ሁለቱ የታላቁ ንስር ክንፎች (ንጽሐ ሥጋ እና ንጽሐ ነፍስ) ተሰጧት። ዘንዶውም እየበረረ (ለክፋት እየተፋጠነ)
ተከተላት። ጎርፉ ይወስዳትም ዘንድ (ሠራዊቱ ይገድላት ዘንድ) ፥ ከአፉ እንደ ታላቅ ወንዝ ያለ ብዙ ውኃ በዚያች
ሴት በስተኋላ አፈሰሰ። (እመቤታችን ስትሰደድ፦ ንጉሡ ሄሮድስ በአፉ ቃል የሚታዘዙ አያሌ ሠራዊት ከበስተኋላዋ
ላከባት)። ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፤ ምድሪቱ አፉዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ውኃ መጠጠችው። (የሄሮድስ
ሠራዊት የበረሃው ሐሩር እንደ እሳት ወላፈን እየገረፋቸው ፥ የአሸዋው ግለት እንደ ከሰል ፍም እየፈጃቸው ሳይመለሱ
በዚያው ቀርተዋል)። ዛፏ እንኳን ሳትቀር እንደ በር ተከፍታ በመዘጋት እመቤታችንን ሠውራታለች። ያቺ ዛፍ እስከዛሬ
ድረስ በግብፅ ትገኛለች።
እመቤታችን
በስደት ጊዜ ብዙ ተንገላታለች ፤ ተርባለች ፥ ተጠምታለች ፥ እንደ የኔቢጤም ለምናለች። ነገር ግን ሰይጣን ከፊት
ለፊት እየቀደመ የሰውን ልብ ያጸናባቸው (ያስጨክንባቸው) ነበር። ይልቁንም ኰቲባ የተባለች የቤት ሠራተኛ
እመቤታችንን ዘልፋታለች ፥ ልጇንም ከክንዶቿ ነጥቃ ከመሬት ጥላባታለች። ጻድቁ ዮሴፍም እመቤታችንን፦ « እንዳታ
ነሺው ፥ ተአምራቱን ይግለጥ ፤ » ብሏታል። በዚህን ጊዜ ሰዎቹ ወደ አራዊትነት ተለውጠው የገዛ ውሾቻቸው አሳድደዋ
ቸዋል። ይህም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ አውሬነት ተለውጦ ለሰባት ዓመት ከዱር አራዊት ጋር እንደኖረው ማለት
ነው። «ጠጉሩም እንደ አንበሳ ፥ ጥፍሩም እንደ ንስር እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች ተለይቶ ተሰድዶ ፤ እንደ በሬም
ሣር በላ፤ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ።» ይላል። ዳን ፫ ፥፴፫።
ዳክርስና
ጥጦስ የተባሉ ሽፍቶችም እመቤታችንን አስደንግጠዋታል። ዘራፊዎችም ነፍሰ ገዳዮችም ነበሩ። ለጊዜው የያዙትን
ወስደውባቸው ከፊታቸው ዘወር ቢሉም ወዲያው እርስ በርሳቸው መጨቃጨቅ ጀመሩ። ጭቅጭቁም ጥጦስ «እንመልስላቸው፤» ሲል ፥ ዳክርስ ደግሞ «አንመልስላቸውም፤» የሚል ነበረ። እመቤታችን
ግን «እንግደላቸው ፥ እንግደላቸው ፤» የሚባባሉ መስሏት ፦ «በውኑ ልጄን ከሞት ላላድነው ነው ፥ከሀገሬ
የተሰደድኩት? » ብላ አለቀሰች። ለራሷ አላሰበችም። በዚህን ጊዜ ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስ በአዋቂ ቃል፦ «እናቴ ሆይ
፥ አታልቅሺ ፥ አንዱም ለእኔ አንዱም ለሰይጣን ነው፤» አላት። በመጨረሻም ጥጦስ የራሱን ድርሻ በሙሉ ለዳክርስ
ከለቀቀለት በኋላ የእመቤታችንን መለሱላት። ጥጦስም እመቤታችንን ላግዝሽ ብሎ ሕፃኑን ተሸከመላት። በጉዞውም እንደ
በትር ይመረኰዝበት የነበረው ሰይፍ ምንም ሰይነካው ስብርብር ብሎ ስለወደቀበት አዘነ። ጌታም በአዋቂ ቃል፦ «አይዞህ
አትዘን ፤ » ካለው በኋላ በተአምር እንደቀድሞው
አደረገለት። ጌታችን ሰይፉን በኃይሉ ሰባብሮ ያሳየው በሰይፍ መመካት ከንቱ መሆኑን ሲያስተምረው ነበር። ጥጦስ
ጌታን በተሸከመው ጊዜ ከልብሱ ላይ ወዙ ስለፈሰሰበት እንደ ናርዶስ ሽቶ መዓዛው ከሩቅ ያውድ ነበር። ጌታችን
በቀራንዮ በተሰቀለ ጊዜ «አንዱም ለእኔ ፤» የተባለ ጥጦስ በቀኙ ተሰቅሏል። «አንዱም ለሰይጣን ፤» የተባለ ዳክርስ
ግን በግራው ተሰቅሏል።
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም ሦሰት ዓመት ከመንፈቅ በስደት ከተንከራተተች በኋላ፦ የእግዚአብሔር መልአክ ለአረጋዊው
ለዮሴፍ በግብፅ ሀገር በህልም ታየው። «የሕፃኑን ነፍሰ የሚሹ ሙተዋልና ፥ተነሥተህ ሕፃኑን እና እናቱን ይዘህ ወደ
እስራኤል ሀገር ሂድ አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑን እና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ምድር ገባ። አርኬላኦስም
በአባቱ በሄሮድስ ፋንታ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ ፦ «የክፉ ልጅ ክፉ» ብሎ ወደዚያ ለመሄድ ፈራ፤ በህልምም
ተገልጦለት ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ። በነቢያት ፦ «ልጄ ናዝራዊ ይባላል፤» የተባለው ይፈጸም ዘንድ ናዝሬት
ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ። ከግብፅ የተመለሱት በኢትዮጵያ በኲል ነው። ይህም ፦ «የኢትዮጵያ ድንኳንች ሲጨነቁ
አየሁ ፤» ተብሎ በነቢዩ በዕንባቆም ትንቢት የተነገረበት ነው። ዕንባ ፫፥፯። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ
ክርስቲያን ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ የእመቤታችን የስደት መታሰቢያ ነው። ማኅሌተ ጽጌ ይቆማል፥ ቅዳሴ ማርያም
ይቀደሳል። ገዳማውያንን አብነት ያደረጉ ምእመናንም በፈቃዳቸው ይጾሙታል።
«ዘንዶው በባሕር አሸዋ ላይ ቆመ፤»
ዘንዶውም
በሴቲቱ (በእመቤታችን) ላይ ተቈጥቶ ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርም
ያላቸውን የቀሩትን ልጆቿን ሊወጋቸው ሄደ። ዘንዶውም በባሕር አሸዋ ላይ ቆመ። ባሕር የተባለች ዓለም ናት፤ ባሕር
በማዕበል በሞገድ ስትናወጥ እንደምትኖር ሁሉ ዓለምም በማዕበለ ኃጢአት በማዕበለ ክህደት ፥ በሞገደ ኃጢአት በሞገደ
ክህደት ስትናወጥ ትኖራለች። አሸዋ የተባሉት ደግሞ በዚህ ዓለም እንደ አሸዋ የበዙ መናፍቃን እና አሕዛብ ናቸው።
አሸዋ ቈሪር ፥ ክቡድ እንደሆነ ሁሉ እነርሱም ቈሪራነ አእምሮ ፥ ክቡዳነ አእምሮ ናቸው፡፡ አንድም ኃጢአታቸው
ክህደታቸው እንደ አሸዋ የበዛ ነው። ኢዮብ መከራውን ከባሕር አሸዋ እንደሚከብድ ተናግሯል። ኢዮ ፮፥፫። ከአብርሃም
ወገን የሚወለዱ ጻድቃን በከዋክብት ሲመሰሉ ኃጥአኑ ደግሞ በአሸዋ ተመስለዋል። ዘፍ ፳፪፥፲፯ ፣ ሲራ ፵፬፥፳፩።
እንግዲህ ፦ «ዘንዶውም በባሕር አሸዋ ላይ ቆመ፤» ማለት፦ በመናፍቃን ፥ በአሕዛብ ልቡና አደረ ማለት ነው።
ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፭
፩፦ «ሰው እናታችን ጽዮን ይላል»
«እምነ ጽዮን ይብል ሰብእ፥ ወብእሲ ተወልደ በውስቴታ፤ ወውእቱ ልዑል ሣረራ። ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጧም ሰው ተወለደ፤ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት።» ይላል። መዝ ፹፮፥፭። ቅዱስ ዳዊት ጽዮንን እናት ብሏታል። እናት፦ ወላጅ፥ መገኛ፥የአባት ሁለተኛ ናት። እግዚአብሔር በአሠርቱ ትእዛዛት፦ «አክብር አባከ ወእመከ፤ ከመ ይኩንከ ጽድቀ፥ ወይኑኅ መዋዕሊከ በውስተ ምድር ዘይሁበከ እግዚአብሔር አምላክከ። አባትህንና እናትህን አክብር፤ መልካም እንዲሆንልህ፥ (ቸርነቱ ረድኤቱ ይደረግልህ ዘንድ) ፥ እግዚአብሔር አምላክህ በሚስጥህ ምድርም ዕድሜህ እንዲረዝም፤ » እንዳለ፦ እናት ከአባት እኲል ክብር ይገባታል። ዘጸ ፳ ፥፲፪። ጽዮን ማለት ደግሞ አምባ መጠጊያ ማለት ነው።
፩፥፩፦ የጽዮን ተራራ፤
ጽዮን
ኢየሩሳሌም ከተሠራችባቸው ተራራዎች አንዷ ናት። በመጀመሪያ ኢያቡሳውያን መሸገውባት ይኖሩ ነበር። እነዚህም
ከከነዓን የተገኙ ወገኖች ናቸው። ከነዓን የካም ልጅ ፥የኖኅ የልጅ ልጅ ነው። ዘፍ ፲፥፮ ንጉሣቸውን የገደለው ኢያሱ
ወልደ ነዌ ነበር። ኢያ ፲፥፳፫። ነገር ግን፥ ንጉሥ ዳዊት፦ እስኪያስለቅቃቸው ድረስ ጽዮን የተባለች አምባቸው
በእጃቸው ነበረች። ኢያ ፲፭፥፷፫። በጽዮን ላይ ኢያቡስ የሚባል አምባም ነበራቸው። መሳ ፲፱፥፲።
ንጉሥ
ዳዊት በኬብሮን ለሰባት ዓመታት ከነገሠ በኋላ ከኢያቡሳውያን ጋር ለመዋጋት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። እነርሱም ዳዊት
ወደዚህ ሊገባ አይችልም ብለው አስበው ነበር። ነገር ግን፥ ዳዊት፦ አምባይቱን ጽዮንን ይዞ በዚያ ተቀመጠ። የዳዊት
ከተማ ብሎ የሰየማትን ይህቺን አምባም ዙሪያዋን፦ ከሚሎ ጀምሮ ወደ ውስጥ በግንብ አጠራት፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ
ጋር ስለነበረ እየበረታ ሄደ። ዳዊትም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናው ስለ ሕዝቡ ስለ
እስራኤልም መንግሥቱን ከፍ እንዳደረገ አወቀ። ፪ኛ ሳሙ ፭፥፩-፲፪።
ጽዮን
የሚለው ስም በኋላ ላይ ለሞሪያ ተራራ ተሰጥቷል። ይኸውም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በዚያ ስለተሠራ ነው። ሞሪያ፦
አብርሃም ይስሐቅን ለመሠዋት የሄደበት ተራራ ነው። በዚያ መሠዊያ ሠርቶ ልጁን ለእግዚአብሔር አቅርቧል።
እግዚአብሔር ከላይ ከሰማይ ጠርቶ፦ «እምነትህ ታይቷልና፥ በብላቴናው ላይ እጅህን አንዳትዘረጋ፤» ባይለው ኖሮ፥
ስለቱን በአንገቱ ላይ አሳርፎ ነበር። ሊቃውንቱ በኅሊናው ሠውቶታል፦ ይላሉ። በመጨረሻም እግዚአብሔር ቀንዶቹ በዕፀ
ሳቤቅ የተያዘ ነጭ በግ አሳይቶት ስለ ይስሐቅ ፈንታ ሰውቶታል። ዘፍ ፳፪፥፩። ይህም ለነገረ ድኅነት ምሳሌ ነው።
ዕፀ ሳቤቅ የእመቤታችን፥ በግ የክርስቶስ፥ ይስሐቅ ደግሞ የአዳም ምሳሌዎች ናቸው። ንጉሥ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን
ቤተ መቅደስ የሠራው በዚህ ቦታ ላይ ነው። ይኸንን በተመለከተ በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ላይ፦ «ሰሎሞንም እግዚአብሔር
ለዳዊት በተገለጠበት በሞሪያ ተራራ ላይ ዳዊት ባዘጋጀው ስፍራ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ በኢየሩሳሌም
የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ።» የሚል ተጽፏል። ፪ኛ ዜና ፫፥፩።
ነቢዩ
ኢሳይያስም፦ «እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ለእስራኤል በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚ አብሔር
ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን።» ብሏል ኢሳ ፲፥፲፰። ምልክት የተባለው የሰናክሬም ጥፋት፦ የብልጣሶር ሞት ነው።
ሰናክ ሬም ከ705-681 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የነገሠ የአሦር ንጉሥ ነው። በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ኢየሩሳሌምን
ለማጥፋት፥ ቤተ መቅደስን ለማፍረስ ብዙ ሺህ ሠራዊት አሰልፎ ነበር። ነገር ግን ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ
ስለቀሠፋቸው፦ በአንድ ሌሊት አንድ መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ሠራዊት በድኖች ሆነው አድረዋል። እርሱም ወደ ነነዌ
ተመልሶ ለጣዖት ሲሰግድ የገዛ ልጆቹ በሰይፍ ገድለውታል። የገደሉትም፦ «ሕዝቡን አስጨርሰህ መጥተህ ፥ እኛ በማን
ላይ ልንነግሥ ነው፤ » ብለው ነው። የሥልጣን ነገ ር እንዲህ ነው። ፪ኛ ነገ ፲፰፥፴፭፣ ኢሳ ፴፮፥፴፯ ብልጣሶር
ደግሞ የናቡከደነፆር የልጅ ልጅ የናቦኒዶስ ልጅ ነው። ይህ ሰው በሺህ ለሚቆጠሩ መኳንንቱ በቤተ መንግሥት ታላቅ
ግብዣ አደረገ። በፊታቸውም የወይንጠጅ ይጠጣ ነበር። በሰከረም ጊዜ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ዘርፎ ያመጣቸውን፥
እግዚአብሔር ብቻ የሚገለገልባቸውን ቅዱሳት ንዋያት፥ (የወርቅ የብር ጽዋውን፥ ጻሕሉን)፥ መኳንንቱ፥ ሚስቶቹና
ቁባቶቹ እንዲበሉበት እንዲጠጡበት አደረገ። እነርሱም እየበሉ እየጠጡ አማልክቶቻቸውን (ጣዖቶቻቸውን) አመሰገኑ።
በዚያም ሰዓት በቤተ መንግሥቱ ግድግዳ ላይ በመቅረዙ አንጻር የሰው እጅ ጣቶች ሲጽፉ፥ ንጉሡ በገሀድ አይቶ፦ ወገቡ
እስኪላቀቅ፥ ጉልበቱን እስኪብረከረክ ድረስ ደነገጠ። የተጻፈው ጽሑፍ ምን እንደሆነ እስከነትርጉሙ እንዲነግሩትም ወደ
አስማተኞቹ ጮኸ። ነገር ግን፥ ነገሩ የመጣው ከእግዚአብሔር በመሆኑ፥ ንባቡንም ትርጉሙንም ሊነግሩት አልቻሉም
በዚህን ጊዜ ነቢዩ ዳንኤል ተጠርቶ መጣ። ንጉሡንም ከናቡከደነፆር ጥፋት ሊማር ባለመቻሉ ገሠጸው። በመጨረሻም፦
«የተጻፈው ጽሕፈት ማኔ፥ ቴቄል ፋሬስ ይላል። ማኔ ማለት፦ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቈጠረው ፈጸመውም ማለት ነው።
ቴቄል ማለት፦ በሚዛን ተመዘንህ፥ ቀልለህም ተገኘህ ማለት ነው። ፋሬስ ማለት፦ መንግሥትህ ተከፈለ፤ ለሜዶንና ላፋርስ
ሰዎች ተሰጠ ማለት ነው።» በማለት ተርጉሞታል። በዚያም ሌሊት የከለዳውያን ንጉሥ ብልጣሶር ተገድሏል። ዳን
፭፥፩-፴ ደብረ ጽዮንን የደፈሩ ሁሉ እንዲህ መጨረሻቸው አላማረም።
በሌላ
በኲል ደግሞ ነቢዩ ኢሳይያስ፦ በደብረ ጽዮን ለእግዚአብሔር ክብር የሚደረገውን ሲናገር፦ «በዚያ ዘመን ለሠራዊት
ጌታ ለእግዚአብሔር፥ ከተዋረደና ከደከመ ሕዝብ፥ ከዛሬ እስከ ዘለዓለም ታላቅ ከሆነ ወገን፥ ተስፋ ከሚያደርግና
ከሚረገጥ፥ በሀገሩ ወንዝ ዳር ከሚኖር ሕዝብ ዘንድ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ስም በተጠራበት በደብረ ጽዮን እጅ
መንሻ ይቀርባል፤» ብሏል። ኢሳ ፲፰ ፥፯። ከዚህም በተጨማሪ፦ «የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራና
በኢየሩሳሌም ላይ ይነግሣ ልና፥ በሸማግሌዎቹም ፊት ይከብራል። (በሊቃውንቱ ይመሰገናል)።» ብሏል ኢሳ ፳፩፥፳፫
ደብረ
ጽዮን እግዚአብሔር ኃይሉን በረድኤት የሚገልጥባት፥ በረከቱን የሚሰጥባት፥ ቸርነቱን የሚያሳይባት፥ ጸሎትና ምልጃ
ምስጋናም የሚቀበልባት፥ መሥዋዕት የሚያርግባት፥ ሰውና እግዚአብሔር የሚገናኙባት የሚታረቁባት ስፍራ ናት። ያከበሯትን
የምታስከብር፥ የደፈሯትን የምታሥቀስፍ የእግዚአብሔር ስፍራ ናት። እነ ናቡከደነፆር ወደ አውሬነት ተለውጠው፥
ከአራዊት ጋር ተቀላቅለው፥ ለሰባት ዓመታት እንደ ከብት ሣር እየነጩ ኖረዋል። ዳን ፬፥፴፫። በዚህም፦
፩፡፪፦ ታቦተ ጽዮን፤
የነቢያት
አለቃ ሙሴ፦ እግዚአብሔር፦ «አስቀድመህ እንዳየሃቸው ዓይነት አድርገህ ጽላት አዘጋጅ፥ ቃሎቹን እኔ
እቀርጽባቸዋለሁ።» ባለው መሠረት ሁለት ጽላት አዘጋጅቷል። ያንንም ይዞ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾሟል። እንጀራ
አልበላም ውኃም አልጠጣም። በጽላቱም ላይ አሥሩን የኪዳን ቃሎች እግዚአብሔር ፈቅዶለት ቀረጸ። ጽላቱንም ይዞ
ከደብረ ሲና በወረደ ጊዜ፥ ከእግዚአብሔር ጋር ተናጋግሮ ነበርና ፊቱ አንጸባረቀ። ዘጸ ፴፬፥፩፥፳፱። ከዚያ በፊት
ለጽላቱ ማኖሪያ ታቦት እንዲያዘጋጅ እግዚአብሔር ነግሮት ነበር። ታቦቱም በውስጥም በአፍአም በወርቅ ተለብጦ ነበር።
መክደኛውም በወርቅ የተሠራ ነበር። በላዩም ሁለት የኪሩቤል ሥዕል ተቀርጾ በወርቅ ተለብጦ ነበር። እግዚአብሔር
ባዘዘውም መሠረት ስለ ታቦቱ ክብር በታቦቱ ዙሪያ የወርቅ አክሊል አድርጐለት ነበር። በመጨረሻም፦ «በዚያም ከአንተ
ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት
ኪሩቤል መካከል ፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እናገርሃለሁ። » ሲል እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ሰጥቶታል። ዘጸ
፳፭፥፩-፳፪
የነቢያት
አለቃ ሙሴ ታቦቱን ወደ ማደሪያው ካስገባ በኋላ በመጋረጃ ሸፍኖታል። በእግዚአብሔር ማደሪያ፥ በመገናኛው ድንኳን
ሊሠራው የሚገባውን ሁሉ ከፈጸመ በኋላ ደመናው የመገናኛውን ድንኳን ከደነው። የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን
ሞላው። ደመናው በላዩ ስለነበረ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ስለሞላው ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባ ዘንድ
አልቻለም ነበር። ዘጸ ፵፥፳-፴፰
፩፡፪፥፩፦ ታቦቱና ኢያሱ፤
እሥራኤል
ዘሥጋ በጉዟቸው ሁሉ ታቦቱን ይከተሉ ነበር። በእነርሱና በታቦቱ መካከል ያለውም ርቀት በስፍር ሁለት ሺህ ክንድ
ያህል ነበር። በኢያሱ መሪነት ከዮርዳኖስ ወንዝ በደረሱ ጊዜ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ታቦቱን ያከበሩት ካህናት
እግሮቻቸው ከወንዙ መጥለቅ ሲጀምር ውኃው ተቋረጠ። ሕዝቡም በደረቅ ተሻገሩ። የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳን ታቦት
የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ጸንተው ቆመው ነበር። ሕዝቡ በጠቅላላ ከተሻገረ በኋላም
ከዮርዳኖስ ሲወጡ ውኃው እንደቀድሞው ተመለሰ። እግዚአብሔር ኃይሉን የገለጠው በታቦቱ ላይ ነው። ኢያ
፫፥፩-፲፯፤፬፥፩-፳፬። ታላቁ የኢያሪኮ ግንብም የፈረሰላቸው ሰባት ቀን ታቦቱን አክብረው በግንቡ ዙሪያ በመዞራቸው
ነው። እንዲህ እንዲያደርጉ ያዘዘቸውም እግዚአብሔር ነበር። «እግዚአብሔርም ኢያሱን፦ ተመልከት፥ ኢያሪኮንና
ንጉሥዋን፥ ኃያላንዋንም በእጅህ ሰጥቼሃለሁ። ሰልፈኞቻችሁ ሁሉ ከተማይቱን አንድ ጊዜ ይዙሯት፤ እንዲህም ስድስት ቀን
አድርጉ። ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በታቦቱ ፊት ይሸከሙ፤ በሰባተኛውም ቀን ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዙሩ፥
ካህናቱም ቀንደ መለከት ይንፉ። ቀንደ መለከቱን ባለማቋረጥ ሲነፉ ፥ የመለከቱንም ድምጽ ስትሰሙ፥ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ
ጩኸት ይጩኹ፤ የከተማይቱም ቅጥር ይወድቃል፥ አለው፤» ይላል። ኢያ ፮፥፪-፮። ኢያሱ በነገር ሁሉ ከጧት እስከ ማታ
በታቦቱ ፊት እየሰገደ እግዚአብሔርን ይማጸን ነበር። እግዚአብሔርም ቃል በቃል ያነጋግረው፥ ማድረግ የሚገባውንም
ይነግረው ነበር። ኢያ ፯፥፮-፱።
፩፡፪፥፪፦ የታቦተ ጽዮን መማረክ፤
ታቦቱ፦
ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅርብ በሆኑ ሰዎች፥ በአፍኒን እና በፊንሐስ የድፍረት ኃጢአት የተነሣ በፍልስጥኤማውያን
የተማረከበት ጊዜ ነበር። አፍኒን እና ፊንሐስ የሊቀ ካህናቱ የዔሊ ልጆች ናቸው። እግዚአብሔርን የማያውቁ
ምናምንቴዎች ነበሩ። በመገናኛው ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ያመነዝሩ ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፪፥፲፪፣፳፪። በዚህ
ምክንያት ለፈተና ጦርነት መጣ። በጦርነቱም ላይ አፍኒን እና ፊንሐስ ተቀሰፉ። ታቦቷም ተማረከች። ዔሊም ይህን
መርዶ ሰምቶ፥ ከተቀመጠበት ወንበር ወድቆ፥ አንገቱ ተቆልምሞ ሞተ። ፩ኛ ሳሙ ፬፥፩-፲፰
ፍልስጥኤማውያን
የእግዚአብሔርን ታቦት ወስደው ወደ ዳጐን ቤት (ወደ ቤተ ጣዖት) አገቡት። በዳጎንም አጠገብ አኖሩ ት። በማግሥቱ
ዳጎን የሰው እጅ ሳይነካው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ ወድቆ (ሰግዶ) ተገኘ። አንሥተውም ወደ ሥፍ ራው
መለሱት። አሁንም ዳጐን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ አገኙት። ራሱና እጆቹም ተቈራርጠው
በመድረኩ ላይ ወድቀው ነበር። በመጨረሻም፦ አዛጦን፥ ጌት፥ አስቀሎና፥ በሚባሉ የፍልስጥኤም ከተሞች ላይ
የእግዚአብሔር እጅ ከበደችባቸው። እግዚአብሔር በእባጭ ቊስል መታቸው። ሕዝቡም፦ «እኛንና ሕዝባችንን ሊገድሉ
የእስራኤልን አምላክ ታቦት አመ ጡብን፤» ብለው ጮኹ። በከተሞቹ ሁሉ የሞት ድንጋጤ ነበር። ብዙ ሰዎችም እየተቀሠፉ
ሞተው ነበር። በዚህን ጊዜ ልከው የፍል ስጥኤማውያንን አለቆች ሁሉ ሰብስበው፦ «የእስራኤልን አምላክ ታቦት ስደዱ፥
እኛንና ሕዝባችንን እንዳይገድል ወደ ስፍራው ይመ ለስ፤» አሉ። ያልሞቱትም ሰዎች በእባጭ ተመቱ፤ የከተማይቱም ዋይታ
እስከ ሰማይ ወጣ፤ ፪ኛ ሳሙ ፭፥፩፥፲፪
፩፡፪፥፫ ፦ ታቦቱና የቤትሳሚስ ሰዎች፤
ከሰባት
ወር በኋላ፥ ታቦቱን አክብረው፥ ከወርቅ እጅ መንሻ ጋር፥ በሰረገላ ላይ ጭነው መለሱ። ሰረገላውን ይስቡ የነበሩት
ሰዎች ታቦቱን እስከ ቤትሳሚስ ድረስ ሸኙ። የቤትሳሚስ ሰዎች በሸለቆው ውስጥ ስንዴ ያጭዱ ነበር። የታቦቱንም መምጣት
አይተው ደስ አላቸው። የሰረገላውንም እንጨት ፈልጠው ላሞቹን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ።
ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት፥ ከእርሱ ጋር የነበረውንም የወርቅ ዕቃ ያለበትን ሣጥን አወረዱ። በታላቁም ድንጋይ
ላይ አኖሩት። በዚህ አጋጣሚ፦ የቤትሳሚስ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ታቦት ውስጥ ተመልክተው ስለነበረ እግዚአብሔር
ከአምስት ሽህ ሰዎች መካከል ሰበዓውን መታቸው። እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ ግድያ ስለመታ ሕዝቡ አለቀሰ።
የቤትሳሚስም ሰዎች፦ «በዚህ በቅዱስ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት መቆም ማን ይችላል?» አሉ። ምክንያቱም በታቦቱ ፊት
መቆም በእግዚአብሔር ፊት መቆም ነውና። ፩ኛ ሳሙ ፮፥፩፥፳፩
፩፡፪፥፬፦ ታቦቱና ዖዛ፤
የእግዚአብሔር
ታቦት ከፍልስጥኤም ምድር ከተመለሰ በኋላ በአሚናዳብ ቤት ለሃያ ዓመታት ተቀምጧል። የእግዚአብሔርን ታቦት ለመጠበቅ
የተቀደሰው የአሚናዳብ ልጅ አልዓዛር ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፯፥፩-፪። በኋላ ግን ንጉሡ ዳዊት ከእስራኤል የተመረጡትን
ሠላሳ ሺህ ያህል ሰዎች ሰብስቦ ታቦቱን ለመቀበል ተዘጋጀ። እነርሱም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም የተጠራውን
የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጡ ዘንድ ወደ አሚናዳብ ቤት ሄዱ። በአዲስ ሰረገላም ጫኑት። የአሚናዳብ ልጆችም ዖዛና
አሒዮ አዲሱን ሰረገላ ይነዱ ነበር። ንጉሡ ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ በቅኔና በበገና፥ በመስንቆም በከበሮም፥
በነጋሪትና በጸናጽል፥ በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይዘምሩ ነበር። አሁንም በእግዚአብሔር ፊት የተባለው
በታቦቱ ፊት የፈጸሙት አገልግሎት ነው።
ወደ
ናኮንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና (እምቧ እያሉ እየዘለሉ ያመሰግኑ ነበርና) ታቦቱ ተነቃነቀ።
በዚ ህን ጊዜ ዖዛ ሳይገባው እጁን ዘርግቶ የእግዚአብሔርን ታቦተ ያዘ፤ ሳይገባው፥ ሥልጣን ሳይኖረው ነክቷልና
የእግዚአብሔር ቊጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ ስለ ድፍረቱም በዚያው ቀሠፈው። በእግዚአብሔርም ታቦት አጠገብ በዚያው ሞተ።
፪ኛ ሳሙ ፮፥፩-፲
፩፡፪-፭፦ ታቦቱና አቢዳራ፤
ንጉሡ
ዳዊት ደፋሩ ዖዛ እንደተቀሠፈ አይቶ እግዚአብሔርን ፈራ። «የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ይመጣል?» አለ።
በዚህ የተነሣ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማው ይወስድ ዘንድ አልወደደም። አለመውደዱም እግዚአብሔርን ከመፍራት
የተነሣ፥ በነዖዛ የደረሰ በእኔም ይደርስብኛል ከማለት እንጂ በሌላ አይደለም። ወደ አቢዳራ ቤትም አገባው። አቢዳራም
ልክ እንደ አሚናዳብ ቤቱን ለእግዚአብሔር ታቦት ለቀቀ። ታቦቱም በዚያ ለሦስት ወራት ያህል ተቀመጠ። እግዚአብሔርም
አቢዳራንና ቤቱን ሁሉ ባረከ። በረከት በግቢም በውጪም ተትረፈረፈ። ፪ኛ ሳሙ ፮፥፲፩።
፩፡፪፥፮፦ ዳዊትና ታቦቱ፤
ከሦስት
ወር በኋላ ንጉሥ ዳዊት፦ እግዚአብሔር የአቢዳራን ቤትና የነበረውን ሁሉ ስለ እግዚአብሔር ታቦት እንደ ባረከ ሰማ።
በዚህን ጊዜ በዖዛ መቀሠፍ የደነገጠው ኅሊናው ፥ የፈራው ልቡናው ፥ የተብረከረከው ጉልበቱ መለስ አለ። ሄዶም
የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ከተማው በደስታ አመጣው። ከእርሱም ጋር የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙ
ሰባት መሰንቆ የሚመቱ ክፍሎች ነበሩ። የእንስሳት መሥዋዕትን ይሠዉ ነበር። ዳዊትም ለዓይን የሚያንጸባርቅ ቀሚስ
ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት በገና ይደረድር ነበር። በእግዚአብሔር ፊት የተባለው በታቦቱ ፊት የተፈጸመው አገልግሎት
ነው። የእሥራኤል ቤት ሁሉ በእልልታ ቀንደ መለከት እየነፉ የእግዚአብሔርን ታቦት አመጡ።
፩፡፪፥፯፦ የሜልኮል ንቀትና የዳዊት አገልግሎት፤
ሜልኮል፦
ከሳኦል ሴቶች ልጆች ታናሽቱና የዳዊት ሚስት ናት። ታቦቱን ለመቀበል ከቤት አልወጣችም። በመስኮት ሆና ስትመለከት፦
ንጉሡ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘምር አይታ በልቧ ናቀችው። የእግዚአብሔርንም ታቦት አምጥተው ዳዊት
በተከለለት ድንኳን ውስጥ አኖሩት። ንጉሡ ዳዊትም የሚቃጠልና የሰላም መሥዋዕትን በእግዚአብሔር ፊት ካሳረገ በኋላ
ሕዝቡን በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም መረቃቻው። ቤተሰቡንም ለመመረቅ በተመለሰ ጊዜ ሜልኮል ልትቀበለው ወጣችና ፦
« ከተርታ ዘፋኞች እንዳንዱ ፦ የእስራኤል ንጉሥ በአገልጋዮቹ ሚስቶች ፊት በመገለጡ ምንኛ የተከበረ ነው ። »
በማለት አላገጠችበት። ንጉሡ ዳዊት ግን ፦ «በእግዚአብሔር ፊት እዘምራለሁ ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ
አለቃ እሆን ዘንድ ከአባትሽና ከቤቱ ሁሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር
ፊት እጫወታለሁ፤ እዘ ምራለሁም ፤ አሁንም እገለጣለሁ ፤ በዓይንሽ ፊትና እንዴት? ከበርህ ባልሽባቸው ሴቶች ልጆች
ፊት የተናቅሁ እሆናለሁ።» አላት። ሜልኮል፦ ለታቦቱም፥ ለአገልግሎቱም ፥ ለዳዊትም ክብር ባለመስጠቷ እግዚአብሔር
ማኅፀኗን ዘጋው ፥ እስከሞተችበት ቀን ድረ ስም ልጅ አልወለደችም። እግዚአብሔር አልጋ ወራሽ የሆነ ልጅ እንዳትወልድ
አደረጋት።
ንጉሡ ዳዊት ታቦቱን ወደ ጽዮን በማምጣቱ በዚህ ምክንያት ታቦተ ጽዮን ሊባል ችሏል። በዚህም ደብረ ጽዮን እንዲል፦ ታቦተ ጽዮን ተብሎ ይጠራል ማለት ነው።
፩፥፫ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን፤
ቤተ
ክርስቲያንም ጽዮን ትባላለች። ደብረ ጽዮን የሚሠዋበት መሥዋዕተ ኦሪት ነበር። በደብረ ጽዮን ዘሐዲስ ኪዳን ቤተ
ክርስቲያን ግን የሚሠዋው መሥዋዕተ ሐዲስ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። « በጽዮን መለከት ንፉ፤ በቅዱሱም ተራራ ላይ
ዓዋጅ ንገሩ፤» እንደተባለ፦ ሐዲስ ሕግ ወንጌል ይታወጅባታል። ኢዩ ፪፥፩። በተጨማሪም፦ «በጽዮን መለከትን ንፉ፤
ጾምንም ቀድሱ፤ ምሕላንም ዓውጁ፤» የሚል አለ። ኢዩ ፪ ፥፲፭። በመሆኑም ሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት ይታወጅባታል።
ጸሎተ ምሕላ ይያዝባታል። ጡት ከሚጠ ቡት ሕፃናት ጀምሮ እስከ ሽማግሌዎቹ ድረስ ሕዝቡን ሰብስቡ፤ እንደተባለ፦ ሁሉም
ለቅዳሴ፥ለማኅሌት፥ ለሰዓታት ፥ ለመዝሙር ይሰ በሰቡባታል። ሕፃናት በአርባ በሰማኒያ ቀን እየተጠመቁ አባል
ይሆኑባታል። ጌታችን በወንጌል፦ «ሕፃናትን ተዉአቸው፤ ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው፤» ያለው ለዚህ ነው።
ማቴ ፲፱ ፥፲፬። ለሐዋርያው ለቅዱስ ጴጥሮስም፦ ሕፃናቱን ፥ ወጣቶቹን እና አ ረጋውያኑን፦ በግልገሎች ፥ በጠቦቶችና
በበጎች መስሎ ጠብቃቸው ብሎታል። ዮሐ ፳፩፥፲፭።
፩፥፬፦ ጽዮን ማርያም ፤
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም «ጽዮን» ተብላ ትጠራለች። ምክንያቱም ጽዮን ማለት አምባ መጠጊያ ማለት እንደ ሆነ ሁሉ
እመቤታችንም፦ ለነፍስና ለሥጋ ፥ለኃጥአንና ለጻድቃን፥ አምባ መጠጊያ ናትና። ቅዱስ ዳዊት፦ «እስመ ኀረያ እግዚ
አብሔር ለጽዮን ፥ ወአብደራ ከመ ትኩኖ ማኅደሮ ፥ ዛቲ ይእቲ ምእራፍየ ለዓለም፤ ዝየ አኅደር እስመ ኅረይክዋ።
እግዚአብሔር ጽዮን መርጧታልና ፥ ማደሪያው ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና ፥ ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት፤
መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ።» ያለው እመቤታችንን ነው። መዝ ፩፻፴፮ ፥ ፲፫። ምክንያቱም ፦ ለእናትነት መርጦ
ያደረው በእርሷ ማኅፀን ነውና። «ለ ዘላለም መረፊያዬ ናት፤» ማለቱም፦ እርሱ የዘለዓለም አምላክ እንደሆነ ፥
እርሷም ለዘለዓለም ወላዲተ አምላክ ተብላ እንደምትኖር የሚያመለክት ነው። በሌላ ምዕራፍም፦ « ደብረ ጽዮን ዘአፍቀረ
፥ ሐነፀ መቅደሶ በአርያም ፥ወሳረረ ውስተ ምድር ዘለዓለም። የወደ ደውን የጽዮንን ተራራ ፥ መቅደሱን እንደ
አርያም ሠራ። ለዘለዓለምም በምድር ውስጥ መሠረታት።» ብሏል። መዝ ፸፯፥፷፰።
ጽርሐ
አርያም ከሰባቱ ሰማያት አንዱ ነው። በዚያ፦ ኪሩቤል የሚሸክሙት ፥ ሱራፌል የሚያጥኑት የእግዚአብሔር የእሳት ዙፋን
አለ። ዙፋኑም በሰባት የእሳት መጋረጃዎች የተጋረደ ነው። ኢሳ ፮፥፩ ፣፪ኛ ሳሙ ፬፥፬ ፣ ሕዝ ፩፥፭-፲፰ ፣ ራእ
፬፥፮-፱። ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ፦ እመቤታችንን፦ «በሰማይ ባለ ጽርሐ አርያም ፈንታ በምድር ላይ
አርያምን ሆንሽ፤» ብሏታል። ከ ዚህም፦ ቅዱስ ዳዊት «የወደደውን የጽዮንን ተራራ፥ መቅደሱን እንደ አርያም ሠራ፤»
ያለው ለእመቤታችን እንደሆነ እንረዳለን።
ድንግልናዋን
በተመለከተም፦ «ትሴብሖ ኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ፥ ወሰብሒዮ ለአምላክኪ ጸዮን ፥ እስመ አጽንዐ መናግሥተ ኆኃትኪ
፤ ኢየሩሳሌም ሆይ እግዚአብሔርን አመስግኚ ፥ ጽዮንም ሆይ አምላክሽን አመስግኚ ፤ የደጆችሽን መወርወሪያ
አጽንቶአልና፤» ብሏል። መዝ ፩፻፵፯፥፩። ይህም ፦ ለጊዜው ለከተማይቱ ሲሆን ለፍጸሜው ለእመቤታችን ነው። ይኸውም
ይታወቅ ዘንድ ኢየሩሳሌም ፥ ጽዮን ፥ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፦ በመንፈስ ቅዱስ ግብር
አምላክን በድንግልና በፀነ ሰች ጊዜ፦ «ሰውነቴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች። ልቡናዬም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት
ታደርጋለች።» በማለት አመስግናለች። ሉቃ ፩፥፵፮። የእርሷ ሰውነት፦ የሥጋን ንጽሕና ፥ የልብን ንጽሕና ፥ የነፍስን
ንጽሕና ፥ አስተባብራ አንድ አድርጋ ይዛ የተገኘች ናት። «የዶጆችሽን መወርወሪያ አጽንቷልና፤» የተባለውም
ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን ነው። እመቤታችን፦ ቅድመ ወሊድ ፥ ጊዜ ወሊድ ፥ ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና። ይኽንንም
ነቢዩ ኢሳይያስ፦ «እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ፤ ወንድ ልጅም (ወልድን) ትወልዳለች ፤ ስሙ ንም አማኑኤል ብላ
ትጠራዋለች።» በማለት ተናግሯል። ኢሳ ፯፥፲፬። ነቢዩ ሕዝቅኤልም፦ «ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስ ተውጭ ወዳለው
በር መለሰኝ፤ ተዘግቶም ነበር። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም፤
(ድንግል ማር ያም ለዘለዓለም በድንግልና ጸንታ ትኖራለች)። ሰውም አይገባባትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር
ገብቶባታልና ተዘ ግታ ትኖራለች። (አምላክ በማኅፀኗ ተፀንሶ፥ ከእርሷ ተወልዷልና በድንግልና ጸንታ ትኖራለች)።»
ብሏል። ሕዝ ፵፬፥፩-፪።
ደብረ
ጽዮንና ታቦተ ጽዮን ምሳሌዋ የሆኑላት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ዳዊት እንደተናገረላት፦ ሰው ሁሉ
እናታችን ጽዮን ይላታል። ይህም ይታወቅ ዘንድ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፥ ድኅነተ ዓለምን
በመስቀል ላይ በፈጸመ ጊዜ ፥ ወዳጁን ቅዱስ ዮሐንስን፦ «እነኋት እናትህ፤» ብሎታል። ዮሐ ፲፱፥፳፭።
፩፥፭፦ ጽዮን መንግሥተ ሰማያት፤
የምእመናን
ሁሉ ተስፋ መንግሥተ ሰማያትም ጽዮን ተብላለች። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እናንተ ግን የሕያው
እግዚአብሔር ከተማ ወደምትሆን ወደ ጽዮን ተራራ፥ በሰማያት ወዳለችው ኢየሩሳሌም ፥ ደስ ብሏቸው ወደሚኖሩ አእላፍ
መላእክት ደርሳችኋል። ስማቸው በሰማይ ወደ ተጻፈ ወደ ማኅበረ በኲርም፥ ሁሉን ወደሚገዛም ወደ እግዚአብሔር ፥ ወደ
ፍጹማን ጻድቃን ነፍሳት ፥ የአዲስ ኪዳንም መካከለኛ ወደ ሚሆን ኢየሱስ ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን
ወደሚናገር ወደ ተረጨው ደም ደርሳችኋል። » ብሏል። ዕብ ፲፪፥፳፪-፳፬። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደግሞ፦ በራእይ
መጽሐፉ ላይ ፦«እነሆ ፥ በጉን (ኢየሱስ ክርስቶስን) በጽዮን ተራራ ላይ ቆሞ አየሁ፤ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ
ስም የመንፈስ ቅዱስም ስም በግንባራቸው የተጻፈባቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። እንደ ብዙ ውኃም ድምፅና እንደ
ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅን ሰማሁ ፥ ደርዳሪዎችም እንደሚደረድሩት በገና ድምፅ ያለውን ሰማሁ።
በዙፋኑም ፊት በአራቱ እንስሶችና (በኪሩቤልና) በአለቆቹ ፊት (በሱ ራፌል ፊት) አዲስ ምስጋናን አመሰገኑ።
ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራቱ ሺህ በቀር ፦ (ሄሮድስ ካስፈጃቸው ሰማዕታተ ሕፃ ናት በቀር) ያን ምስጋና
ሊያውቅ ለማንም አልተቻለውም። ከሴቶችም ያልረከሱ እነዚህ ናቸው ፤ ደናግል ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበ ት የሚከተሉት
እነዚህ ናቸው፤ ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኲራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው። በአንደበታቸውም ሐሰት
አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውምና፤ » ብሏል። ራእ ፲፬፥፩-፭። እግዚአብሔር በቅዱስ ዳዊት አንደበት፦ «እኔ ግን
በእነርሱ ላይ ንጉሥ ሆኜ ተሾምሁ ፥ በተቀደሰ ተራራው በጽዮን ላይ።» ማለቱ ፦ ለጊዜው በዳዊት ከተማ በደብረ ጽዮን
በረድ ኤት እንደሚገለጥ ሲሆ ን ፦ ለፍጻሜው ግን ማኅፀነ ድንግል ማርያምን መናገሻ ከተማ እንደሚያደርግ
የሚያመለክት ነበር። በኋላም በምጽአት የጽዮን ተራራ በተባለች በመንግሥተ ሰማያት እንደ ባህርይ ንጉሥነቱ በእሳት
ዙፋን እንደሚገለጥ ያመለክታል። መዝ ፪፥፮። በመሆኑም የሕይወት አክሊል(የክብር መጨረሻ፥ የክብር መደምደሚያ)
የሆነች መንግሥተ ሰማያትም እናታችን ትባላለች። እናት ልጆቿን ችግር ላይ እንዳይወድቁባት ሰብስባ እንደምትይዛቸው፥
መንግሥተ ሰማያትም፦ ልጆቿ ወደገሃነመ እሳት እንዳይወድቁባት እንደ እናት ሰብስባ ትይዛቸዋለች።
ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፮
፩፦ ማኅደረ መለኰት፤
ማኅደር
የሚለው፦ በቁሙ ሲተረጐም፦ ማደሪያ ፥ሰፈር ፥ቤት፥ በኣት፥ የመኝታ ቦታ ፥ እልፍኝ ፥በታላላቅ ቤት ውስጥ የሚሠራ
ልዩ ልዩ ክፍል ፥ ደጃፍና መስኮት ያለው ፥ድንኳን ማለት ነው። ቃሉ ማደሪያነት ላለው ቦታ ኹሉ የሚነገር ነው።
መለኰት፦
ማለት ደግሞ፦ አምላክነት ፥ ፈጣሪነት ፥ አምላክ መኾን ፥ ፈጣሪ መኾን ፥ ወይም የአምላክ ባሕርይ ፥ ጠባይ፥
ኹኔታ ማለት ነው። በአጠቃላይ አነጋገር፦ አገዛዝን ፥ጌትነትን ፥ ባሕርይን ፥ አምላክነትን ፥ ክብርን ፥ ስምን
ያመለክታል።
፩፥፩፦ አገዛዝ፤
ቅዱስ
ዳዊት፦ «እግዚአብሔር በሰማይ ዙፋኑን አዘጋጀ ፥(ንጉሥ በዙፋኑ ተቀምጦ እንደሚፈርድ ይፈርዳል) ፥ በመንግሥቱም
ሁሉን ይገዛል (እንደ ጌትነቱ ሁሉን ይገዛል ) ፥ በሁሉ ይፈርዳል። ቃሉን የምትፈጽሙ ብርቱዎችና ኃያላን ፥ (ሕጉን
የምትጠብቁ ፣ ትእዛዙን የምታከብሩ ጽኑአን ኃያላንም የምትሆኑ ነቢያትና ካህናት) ፥ የቃሉንም ድምጽ የምትሰሙ
መላእክቱ ሁሉ፥ (ከምስአል ማለትም ከመለመኛ ፣ ከመማለጃ ፣ ከመማጸኛ፣ ከመጠየቂያ ቦታ ፣ ከቤተ እግዚአብሔር፣
ምሥጢር የምታውቁ)፥ እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ ሠራዊቱ ሁሉ ፥ ፈቃዱን የሚያደርጉ አገልጋዮቹ ፥ እግዚአብሔርን
ያመሰግኑታል። (እናንተ ብቻ ሳትሆኑ፦ ከሃሊነቱን ማለትም ሁሉን ቻይነቱን ፣ኃይሉን የሚገልጽባቸው ሠራዊተ መላእክት ፥
ሕጉን አምልኮቱን የሚጠብቁ ሊቃነ መላእክትም ያመሰግኑታል)።» ካለ በኋላ፦ «ውስተ ኲሉ በሐውርት መለኮቱ።
ፍጥረቶቹ ሁሉ፦ በግዛቱ ሥፍራ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል። አንድም የጌትነቱ አገዛዝ በአራቱም መዓዝን ምሉዕ
ነው።» ብሏል። መዝ ፥ ፻፪ ፥፲፱ -፳፪። በዚህ ጥቅስ ላይ ግዕዙ መለኮት ያለውን አማርኛው አገዛዝ ብሎ
ተርጉሞታል። በመሆኑም በሰማይና በምድር ለእርሱ የማይገዛ ፥ ለእርሱ የማይንበረከክ የለም።
ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስ ፦ «በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው ፥ (መለኰት የተዋሐደውን ሥጋ፦
ወልድየ ንበር በየማንየ ፣ ልጄ በቀኜ ተቀመጥ አለው) ፥ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ (መለኰት
የተዋሐደው ሥጋ፦ በተዋሕዶ፦ አምላክ ፣ ወልድ ፣ እግዚእ መባልን ገንዘብ አደረገ)፤ ይህም በሰማይና በምድር
ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ (መላእክትና ደቂቀ አዳም ይሰግዱለት ዘንድ) ፥መላስም
ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው። ( አንደበት ሁሉ ኢየሱስ
ክርስቶስ በአብ ጌትነት ያለ ፣ በክብር አንድ የሆነ ጌታ እንደሆነ ያምን ዘንድ ነው) ፤ ያለው ለዚህ ነው። ፊል
፪፥፱-፲፩።
፩፥፪፦ ጌትነት፤
ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እውነትን አውቀው በክፋታቸው በሚለውጡአት፥ በአመጸኛውና በኃጢአተኛው ሰው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር
መቅሠፍት ከሰማይ ይመጣል። እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፥ እግዚአብሔርን ማወቅ በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነው። »
በማለት በኃጥአን ላይ ስለሚመጣው መቅሠፍት ከተናገረ በኋላ ፦ « ወዘኢያስተርኢ እግዚአብሔር እምፍጥረተ ዓለም
ይትዓወቅ በፍጥረቱ ለፍጥረቱ ፥ በሐልዮ ወበአአምሮ ፥ ወከመዝ ይትአመር ኃይሉ ወመለኮቱ ዘለዓለም። የማይታየው
የእግዚአብሔር ባሕርይ እርሱም የዘለዓለም ኃይሉና ጌትነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ የፈጠረውን በማሰብና በመመርመር
ይታወቃል።» ብሏል። ሮሜ ፩፥፲፰-፳። በዚህ ጥቅስ ላይ ግዕዙ መለኮት ያለውን አማርኛው ጌትነት ብሎ ተርጉሞታል።
፩፥፫፦ ባሕርይ፤
ባሕርይ፦
በቁሙ ሲተረጐም የነገር ሁሉ ሥር ፥መሠረት ፥ምንጭ ፥መውጫ ፥መፍለቂያ ፥ መገኛ ፥ ጠባይዕ ማለት ነው። ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስ ለቈላስይስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ፦ «ዑቁ ኢይኂጠክሙ በጥበበ ነገር ዘይየውሁ ለከንቱ ፥ በሥርዓተ
ትምህርተ ሰብእ ለስሒተ ዝንቱ ዓለም ፥ በክርስቶስ ሕግ ያይደለ ፥በሰው ሠራሽ ሥርዓት ለከንቱ የሚያታልሉ ሰዎች
በነገር ማራቀቅ እንዳያታልሏችሁ ተጠንቀቁ። በእርሱ ፍጹም መለኮቱ (ባሕርዩ) በሥጋ ተገልጦ ይኖራልና። (ፍጹም
መለኮቱ በከዊን ተዋሕዷልና፥ በተዋሕዶ ከሁለት አካል አንድ አካል ፥ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆኗልና።»
ብሏል። ቈላ ፪፥፰-፱፡፡
፩፥፬፦ አምላክነት፤
አምላክ፦
በቁሙ ሲተረጐም፦ ፈጣሪ፥ ገዥ ፥ ፈራጅ ፥ዳኛ፥ሠሪ፥ቀጪ፥ፈላጭ ቆራጭ ማለት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በዳግሚት
መልእክቱ፦ «በአእምሮቱ ለአምላክነ ወኢየሱስ ክርስቶስ እግዚእነ ፥ ዘበኃይለ መለኮቱ ወሀበ ለነ ኲሎ ምግባረ ፥
ዘይወስድ ኀበ ሕይወት ወጽድቅ ፤ ውእቱ ዘጸውአነ ውስተ ስብሐቲሁ ወውስተ ሠናይቱ። በመለኮቱ ኃይል (በአምላካዊ
ሥልጣኑ) ለሕይወትና ለመልካም አምልኮ የምንሻውን ነገር ሁሉ የሰጠን ፥ (ለምጻሞችን አንጹ፣ አጋንንትን አውጡ፣ብሎ
ገቢረ ተአምራትን የሰጠን)፥ እርሱንም በማወቅ በክብሩና በበጎነቱ የጠራን እርሱ ነው። (ይኸውም፦ ወደ ጌትነቱ ፥ወደ
በጎነቱ ፥ ከሃሊነቱንና አምጻኤ ዓለማትነቱን ወደ ማወቅ ፥ አንድነቱንና ሦስትነቱን ማለትም ምሥጢረ ሥላሴን ወደ
ማወቅ ፥ ከእመቤታችን ከነፍሷ ነፍስ ከሥጋዋም ሥጋ ነስቶ በተዋሕዶ ሰው መሆኑን ማለትም ምሥጢረ ሥጋዌን ወደ ማወቅ
የጠራን የመረጠንም እርሱ ነው)።» ብሏል። ፪ኛ ጴጥ ፩፥፪-፫። በዚህም መለኮት የሚለው አምላክ ተብሎ ተተርጉሟል።
፩፥፭፦ ክብር፤
ክብር፦
በቁሙ ሲተረጐም፦ ልዕልና ፥ልቆ መገኘት፥ ብልጫ፥ሹመት፥ሽልማት፥ታላቅነት፥ኀይል ፥ ብዕል ፥ብዙ ገንዘብ ማለት ነው።
ይኽንንም በተመለከተ፦ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «ውእቱ ዘጸውዐነ ውስተ ስብሐቲሁ ወውስተ ሠናይቱ። እኛን አስቀድሞ
ወደ ጌትነቱ ፥ወደ በጎነቱ የጠራበት ነው።» ካለ በኋላ፦ «በዘቦቱ ነሐዩ ፥ ወነዐቢ፥ወንከብር፥በተስፋሁ እንተ
ጸገወነ፤ ከመ በእንተ ዝንቱ ትኲኑ ሱቱፋነ ለመለኮተ ዚአሁ። በእርሱ በማመን ጸንተን በምንኖርበት ገንዘብ ፥ እርሱ
በሰጠን ተስፋ፥ በዚህ የክብሩ ወራሾች ትሆኑ ዘንድ፤ » ብሏል። ፪ኛ ጴጥ ፩፥፬። በዚህ ጥቅስ ግዕዙ መለኮት ያለውን
አማርኛው ክብር ብሎ ተርጉሞታል።
፩፥፮፦ ስም፤
ስም፦
በቁሙ ሲተረጐም፦ ከባሕርይ ከግብር የሚወጣ፤ ቦታነትና አካልነት፥ህላዌና ሕይወት ያላቸውን ማናቸውም ኹሉ ፤
በየክፍሉና በየአካሉ፤ በየራስ ቅሉ ፤ በየአይነቱና በየመልኩ በየነገዱ፤ በየዘሩና በየአባቱ በየዘመዱ ተለይቶ
የሚጠራበት፤የሚታወቅበት ነው። እግዚአብሔርም እንደ እግዚአብሔርነቱ የሚጠራበት አምላካዊ ስም አለው። ይኽንንም
በተመለከተ፦ «መለኮትሰ ስም ዘአልቦ ብዕድና፤ መለኮት መለያየት የሌለበት ስም ነው፤» ይላል። ቅዱስ ቄርሎስ፦
መለኰት የሦስቱ መጠሪያ ስም ነው ብሏል።
፪፦ አባ ሕርያቆስ ስለ መለኰት፤
አባ
ሕርያቆስ፦ እመቤታችንን፦ ቅድስት ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ምስጋና በቅዳሴ ማርያም ላይ ስለ መለኰት በሰፊው
ተናግሯል። እመቤታችንም ማኅደረ መለኰት ሆና መመረጧን አድንቋል። «መጠንና መመርመር የሌለበት እሳተ መለኮት በሆድሽ
አደረ፤ በምድራዊ እሳት እንመስለው ዘንድ አይገባም፥ ለእሳትስ መጠን አለው ፥ ልክም አለው፤ መለኮት ግን ይህን
ያህላል ፥ ይህንንም ይመስላል ፥ ሊባል አይቻልም። ለመለኮት እንደ ፀሐይና ጨረቃ ክበብ ፥እንደ ሰውም መጠን ያለው
አይደለም ፥ ድንቅ ነው እንጂ፤ የሰው ሕሊና የመላእክትም አእምሮ በማይደርስበት በአርያሙ የሚኖር ነው እንጂ፤
ለመለኮት ወርድና ቁመት ፥ ላይና ታች ፥ ቀኝና ግራ ያለው አይደለም ፥ ግዛቱ (ጌትነቱ) በአገሩ ሁሉ ነው እንጂ፤
ለመለኮት በላይ ጠፈር በታችም መሠረት ያለው አይደለም ፥ ጠፈሩ እርሱ መሠረቱም እርሱ ነው እንጂ፤ ለመለኮት ከምድር
ከውስጧ የሆነውን ያነሣ ዘንድ ፥ ማጎንበስ ራስንም ዝቅ ማድረግ ያለበት አይደለም ፥ለጴጥሮስ እንዳሳየው ሁሉ በእጁ
የተያዘ ነው እንጂ፤» ብሏል።
ታሪክ፦
የነቢያት አለቃ ሙሴ፦ እግዚአብሔርን፦ «አትተኛምን?» ብሎ ቢጠይቀው፦ «አዎ አልተኛም፤» ብሎታል። ቅዱስ ጴጥሮስም
፦ እንደ ሙሴ ቢጠይቀው፦ በዕንቊ ጽዋ ውኃ መልቶ ሰጠው። ገና ሳይጠጣ ወዲያው እንቅልፍ እንቅልፍ ብሎት ሲያንጎላጅ
ከእጁ ወድቆ ተሰበረ፤ ሲነቃም፦ ውኃው ፈስሶ ፥ ጽዋው ተደፍቶ አገኘውና ደነገጠ። ጌታም፦ «እኔ፦ ይህን ዓለም
የያዝኩት በመካከል እጄ (በእጄ መዳፍ ) ነው ፥ በመሆኑም በእኔ እንቅልፍ ካለብኝ ፦ ዓለሙ እንዲህ ያልፍ
የለምን?» ብሎታል። ዳግመኛም « ይኽንን ዓለም እንደምን እንደያዝከው አሳየኝ፤» ቢለው፦ ዓለሙን በመሐል እጁ ይዞ ፥
እርሱን ደግሞ በመካከል አድርጐ አሳይቶታል።
አባ
ሕርያቆስ የመለኮትን ነገር ይበልጥ በማብራራት፦ «ለመለኮት በሚታይ ገንዘብ ፥ በሚወሰንም ገንዘብ ፥ ደረትና ፊት ፥
የኋላም ጀርባ ያለው አይደለም ፥ በነደ እሳት የተሸፈነ ነው እንጂ፤ ነደ እሳት ግን እርሱ ነው፥ መለኮትስ ንጹሕና
ጹሩይ ብሩህም ነው፤» ብሏል። ቁ ፵፯-፶፫።
፫፦ ጽርሐ አርያም፤
ጽርሐ
አርያም፦ የእግዚአብሔር ማደሪያ ናት። ትርጉሙም፦ በሰማይ ያለ አዳራሽ ፥ ታላቅ ቤት ፥ ማለት ነው። ጌታ በተወለደ
ጊዜ፦ ቅዱሳን መላእክት፦ «ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ፥ ሰላምም በምድር ፥ ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ ፤»
እያሉ ዘምረዋል። ሉቃ ፪፥፲፬። ይህም በሰማይ ባለ ማደሪያህ የምትመሰገን መለኮት ነህ፥ ሲሉት ነው።ጌታችንም
በምትጸልዩበት ጊዜ ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥ በሉ፤» ብሎናል። ማቴ ፮፥፰። በኦሪት ደግሞ፦ «ከቅዱስ
ማደሪያህ ከሰማይ ጐብኝ ፥ ሕዝብህንም እስራኤልን ለአባቶቻችን እንደማልህላቸው የሰጠኸንንም ወተትና ማር የምታፈሰውን
አገር ባርክ፤» የሚል ተጽፏል።ዘዳ ፳፮፥፲፭። ከዚህም ለላ በመጽሐፈ ነህምያ ላይ፦ «የሰማዮች ሰማይ፤» የተባለችው
ጽርሐ አርያም ናት። ነህ ፱፥፮። ንጉሡ ሰሎሞንም ቤተ መቅደሱን ሠርቶ ከጨረሰ ፥ ታቦቱንም ካስገባ በኋላ፦ ወደ
እግዚአብሔር የጸለየው። «በማደሪያህ በሰማይ ስማ፥ሰምተህም ይቅር በል፤» እያለ ነው። እግዚአብሔርም፦ «በሰማይ ሆኜ
እሰማለሁ፤» ብሎታል። ፪ኛ ዜና ፮፥፲፪-፵፪ ፣ ፯፥፲፩-፲፰።
ጽርሐ አርያም ከሰባቱ ሰማያት አንዷ ናት። ቅዱስ ዳዊት፦ «ወበቃለ እግዚአብሔር ጸንአ
ሰማያት ፥ በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፤ » እንዳለ፦ ባለማለፍ ጸንተው ፥ ለዘለዓለም የሚኖሩ ሰማያት ሰባት
ናቸው። መዝ ፴፪፥፮። እነዚህም፦ መንበረ መንግሥት ፣ ጽርሐ አርያም፣ ሰማይ ውዱድ ፣ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ፣ ኢዮር
፣ ራማና ኤረር ናቸው።
በሠለስቱ
ምዕት ቅዳሴ፦ ጽርሐ አርያምን በተመለከተ፦ «መንበሩ በእሳት ክሉል ፥ ወማኅደሩ በማይ ጥፉር ፥ ወዲበ ተድባበ ቤቱ
ኅንባበ ማይ ዘኢይትከዐው። ዙፋኑ በእሳት የተከበበ ነው ፥ ማደሪያውም በውኃ የተታታ ነው ፥ በቤቱም ዙሪያ ላይ
የማይፈስ የውኃ መርገፍ አለ።» የሚል ተጽፏል። በማደሪያው ውስጥ ስላለው ነገር ሲያብራራም፦ «ከዙፋኑም ብልጭልጭታ
ይወጣል ፥ ውስጡ እንደ ጋለ እሳት ነው፤ በውስጡ እንደ ክረምት ቀስተ ደመና ያለ ደገኛ ብርሃን አለ ፥ ዙሪያውም
መብረቅ ነው። ከዚያም መንበር አጠገብ አራቱ እንስሳ (ገጸ ሰብእ ፣ ገጸ ላህም ፣ ገጸ ንስር ፣ ገጸ አንበሳ)
ኅብሩ እንደ በረድ ነጭ የሆነ ሰፊ መንበር በራሳቸው እንደ ተሸከሙ ሆነው አሉ። በዚህ መንበር ዙሪያ ሃያ አራት
ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) አሉ ፥ በፊታቸውም የበጉን ሥዕል ፥ ደም የተረጨች ልብስ ፥ የታተመ መጽሐፍም ያያሉ።
ይህንንም መንበር በዞሩ ቁጥር ለዚያ ለበጉ ሥዕልና በደም ለታለለች ለዚያች ልብስ ለታተመው መጽሐፍም ሦስት ጊዜ
ይሰግዳሉ። በአዳራሹም ድንኳን የምሥጋና ጢስ ይመላል ፥ከዚያም መንበር በታች ጐዳናው ሁለት የሆነ የብርሃን እና
የነፋስ ባሕር ይፈልቃል፤ የአማልክት አምላክ በዚያ አለ ፥ የአጋዕዝትም (የጌቶች) ጌታ በዚያ አለ። በውጭ ይኖራል ፥
በውስጥም ይገኛል ፤ ያገኙት ዘንድ አይሄዱም ፥ በፈለጉት ጊዜም አይታጣም ፥ በያዙት ጊዜ አይዳሰስም ፥ ከሕሊና
ልዩ ነውና።» የሚል ተጽፏል። ቁ ፶፫-፶፰።
ቅዱስ
አትናቴዎስም በቅዳሴው፦ «እንዳንተ ዙፋኑን በእሳት የጋረደ ማነው? በልብሱ የውኃ ሥዕል ያደረገ ማነው?
ተራራዎችንስ እንዳንተ በሚዛን የመዘናቸው ፥ የባሕርንስ ውኃ በእፍኙ የሚሰፍር ማነው? እንዳንተ አዳራሹን
(ማደሪያውን) በውኃ የሚታታ ፥ ዙሪያውንስ በእሳት የሠራ ማነው? በላይ ያለው የውኃ ጠፈር በጥበብህ ወደ እሳት
ግድግዳ አይወርድም። በታች ያለው የውኃ ግድግዳም በአኗኗርህ በላይ ወዳለው ወደ ውኃው ጠፈር አይወጣም።» ብሏል። ቁ
፻፲፰። ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ደግሞ፦ «ሁሉ ከእርሱ ነው ፥ ሁሉም ስለ እርሱ ነው ፥ሁሉም የርሱ ነው ፥ ሰማይ በርሱ
ነው ፥ ከሰማያት በላይ ያለ ሰማይም የርሱ ነው ፥የአርያም ሰፋት የክብሩ ዙፋን ነው ፥ የምድርም ስፋት የእግሩ
መመላለሻ ናት። ፀሐይ የርሱ ነው ፥ ጨረቃም ከርሱ ነው ፥ ከዋክብትም የእጁ ሥራ ናቸው፤ ደመናትም መልእክተኞቹ
ነፋሳትም ሠረገላዎቹ ናቸው ፥ እሳትም የቤቱ ግድግዳ ነው። የቤቱ ጠፈር ውኃ ነው፥ የዙሪያውም ጸፍጸፍ የበረድ ሰሌዳ
ነው ፥ድንኳኖቹ ብርሃናት ናቸው። የመሠወሪያ መጋረጃውም የብርሃን መብረቅ ነው ፥ መመላለሻውም በአየር ነው»
ብሏል። ቁ ፴፮ -፴፫። ( ጠፈር ማለት በቁሙ ሰማይ ማለት ነው ፥የቤትም ክዳን ወይም ጣራ ጠፈር ይባላል። ይኽንን
በተመለከተ « እግዚአብሔርም፦ በውኃው መካከል ጠፈር ይሁን ፤ በውኃና በውኃ መካከል ማለትም፦ በሐኖስና በውቅያኖስ
መካከል ይለይ፥ አለ፤ እንዲህም ሆነ። እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፤ ከጠፈር በላይና ከጠፈር በታች ያሉትንም ውኆች
ለየ። እግዚአብሔር ያን ጠፈር ሰማይ ብሎ ጠራው።» የሚል ተጽፏል። ዘፍ ፩፥፮-፰። የቤትን ጣራ በተመለከተ ደግሞ፦
«ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ፥አኮ ዘይደልወኒ ትባእ ታሕተ ጠፈረ ቤትየ ርኲስት ፤ አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ
ክርስቶስ ሆይ ርኲስት ከሆነች ከቤቴ ጣራ በታች ትገባ ዘንድ የሚገባኝ አይደለም፤ » የሚል አለ። ሉቃ ፯፥፮።
መታታት ማለትም፦ መሥራት ፥መጐንጐን ፥ ማክረር ፥ መግመድ ፥ መሸረብ ማለት ነው።)
ነቢዩ
ሕዝቅኤል፦ ሰባቱ ሰማያት ተከፍተውለት(ምሥጢር ተገልጦለት) የእግዚአብሔርን ራእይ አይቷል። በማየቱም መንበሩን
ስለሚሸከሙ ኪሩቤል መልካቸውን ጭምር ተናግሯል። «የፊታቸው አምሳያ እንደ ሰው ፊት . . . . እንደ አንበሳ ፊት .
. . . እንደ ላም ፊት . . . .እንደ ንስር ፊት . . . . ነበራቸው፤» ብሏል። እሳታውያንና በፊትም
በጀርባም ባለ ብዙ ዓይኖች መሆናቸውን ከተናገረ በኋላ፦ «ከእንስሶች (ከኪሩቤል) ራስ በላይ የሚያስፈራ በረዶ
የሚመስል የጠፈር አምሳያ በራሳቸው ላይ ተዘርግቶ ነበር። ከጠፈሩም በታች ክንፎቻቸው እርስ በርሳቸው ተቃንተው
ነበር፤ ለእያንዳንዱም ገላውን የሚከድኑ ሁለት ሁለት ክንፎች ነበሩት። ሲሄዱም የክንፎቻቸው ድምፅ እንደ ብዙ ውኃ
ድምፅ ፥እንደ ሁሉን የሚችል አምላክ ድምፅ ፥ እንደ ታላቅም ሠራዊት ድምፅ ፥ ሆኖ ሰማሁ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ
ያደርጉ ነበር። በራሳቸውም ላይ ካለው ጠፈር በላይ ድምፅ ተሰማ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።»
በማለት የተገለጠለትን ሰማያዊ ምሥጢር በዝርዝር አስቀምጧል። በመጨረሻም፦ «በራሳቸውም በላይ ካለው ጠፈር በላይ
የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበረ፤ በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ። ከወገቡም
አምሳያ ወደ ላይ የሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ አየሁ ፥ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ። በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ
ቀስተ ደመና አምሳያ ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ።
ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ ፥ የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ፤» ብሏል። ሕዝ ፩፥፩-፳፫። ነቢዩ ኢሳይያስም
እግዚአብሔርን በታላቅ ንጉሠ ነገሥት አምሳል ፥በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ፥ ሱራፌልም ፦ «ቅዱስ ፥ቅዱስ
፥ቅዱስ » እያሉ እግዚአብሔርን በሰማይ ባለው ማደሪያው ሲያመሰግኑት አይቷል። ኢሳ ፮፥፩-፬። በሐዲስ ኪዳን
ደግሞ፦ ቅዱስ ዮሐንስ፦ ኪሩቤልንም ፥ ሱራፌልንም በራእይ አይቷል። ራእ ፬፥፮-፲፩።
፬፦ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፤
ቅዱስ
ያሬድ፦ በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ፦ እመቤታችንን፦ «ቅድስት ሆይ! ብፅዕት ነሽ ፦ የተመሰገንሽና የተባረክሽ ነሽ፥
የከበርሽና ከፍ ከፍ ያልሽ ነሽ ፥ የብርሃን መውጫ የሕይወት መሰላል ነሽ። አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ድንግል
ማርያም ሆይ! ከተለዩ የተለየሽ የመለኮት ማደሪያ ነሽ። » እያለ ካመሰገናት በኋላ ፦ «ከፍጥረት ሁሉ ይልቅ
የተከበርሽ ሆይ! አብ የወደደሽ ፥ ወልድ ያደረብሽ ፥ መንፈስ ቅዱስ ያረፈብሽ ተባልሽ። በምድር ላይ ከፍተኛ
አርያምን የሆንሽ ፥ ከሰማያት በላይ ያለ የአርያም የልዑል ሥፍራ ምትክ አንቺ ነሽ፤» ብሏታል።
በሰማይ
ባለ በእግዚአብሔር ማደሪያ ሰባት የእሳት መጋረጃዎች ያሉት የእሳት ዙፋን አለ። እግዚአብሔር ወልድ ፥ አካላዊ ቃል
ከሰማይ ወርዶ የእመቤታችንን ማኅፀን እንደ እሳት ዙፋን አድርጎ ተቀምጦባታል። ሰባቱን የሥጋና የነፍስ ባሕርያቷንም
እንደ ሰባቱ የእሳት መጋረጃ አድርጓቸዋል። አራቱ የሥጋ ባሕርያት ፦ መሬት ፥እሳት ፥ ነፋስና ውኃ ሲሆኑ፦ ሦስቱ
የነፍስ ባሕርያት ደግሞ፦ ለባዊነት (ማሰብ) ፥ነባቢነት(መናገር)፥ ሕያውነት (ዘለዓለማዊነት) ናቸው። የእግዚአብሔር
ማደሪያ የሆነችው ሰማይ፦ በተቀሩት ስድስት ሰማያት ታጥራ ተከብራ እንደምትኖር፦ እመቤታችንም ፩ኛ፦ በንጽሐ ሥጋ ፤
፪ኛ፦ በንጽሐ ነፍስ ፤ ፫ኛ፦ በንጽሐ ልቡና ፤ ፬ኛ፦ በድንጋሌ ሥጋ፤ ፭ኛ፦ በድንጋሌ ነፍስ፤ ፮ኛ፦ በድንጋሌ
ልቡና፤ ታጥራ ፥ታፍራ፥ተከብራ፥ትኖራለች።
ቅዱስ ኤፍሬም፦ በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ፦ እመቤታችንን፦ «ከቅዱሳን ክብር የማርያም ክብር ይበልጣል፤ የአብን ቃል ለመቀበል በተገባ ተገኝታለችና። መላእክት የሚፈሩትን ፥
ትጉሆች በሰማያት የሚያመሰግኑትን ድንግል ማርያም በማኅፀንዋ ተሸከመችው። ይህች ከኪሩቤል ከሱራፌልም ትበልጣለች ፥
ከሦስቱ አካል ለአንዱ ማደሪያ ሆናለችና።» ብሏል። ምክንያቱም ኪሩቤል ቢሸከሙ መንበሩን ነው ፥ ሱራፌልም ቢያጥኑ
መንበሩን ነው። እርሷ ግን በማኅፀኗ የተሸከመችው በእሳቱ መንበር ላይ የሚቀመጠውን እሳተ መለኰት ነው።
ቅዱስ
ዳዊት፦« እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታልና ፥ ማደሪያው ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና ፥ ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ
ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ አለ።» በማለት እመቤታችን ለማኅደረ መለኮትነት እንደተመረጠች አስቀድሞ
በትንቢት ተናግሮላታል። መዝ ፻፴፩ ፥፲፫። ከዚህም ሌላ፦ «የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል፤» በማለት እርሷን
ዙፋን አድርጐ እንደሚገለጥም ተናግሯል። መዝ ፹፫ ፥ ፯። በሰማይ ያለ የእግዚአብሔር ዙፋን በውስጥ በአፍአ እሳት
እንደሆነ ፦ እመቤታችንም፦ በውስጥ በአፍአ (በነፍስም ፥ በሥጋም)፦ እሳት ምሳሌው በሆነ በመንፈስ ቅዱስ የተከበበች
፥ የታጠረች ናት። «እንደ እሳት የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎችም ታዩአቸው፤ በሁሉም ላይ ተቀመጡባቸው። ሁሉም
መንፈስ ቅዱስን ተሞሉ፤» ይላል። የሐዋ ፪፥፫።
የአሥራ
አምስት ዓመት ብላቴና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅደረ መለኮት ሆና መገኘቷ ፥ ቃላት የማይገልጡት
ከመነገር በላይ ነው። ቅዱስ ኤፍሬም ፦ በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ፦ « የአብ ቃል እናቱ ንጽሕት ድንግል ሆይ!
ስለአንቺ የሚነገረውን ነገር መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው፤ ኪሩቤል ለሚሸከሙት ንጉሥ፦ ዙፋኑ (ማደሪያው)
ሆንሽ፤» ያለው ለዚህ ነው። አባ ሕርያቆስም፦ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ፦ «ድንግል ሆይ! እሳተ መለኮት በሆድሽ ባደረ
ጊዜ፦ ፊ ቱ እሳት ፥ ልብሱ እሳት ፥ቀሚሱ እሳት ነው እንደምን አላቃጠለሽም፤ ሰባት የእሳት ነበልባል መጋረጃ
በሆድሽ ውስጥ ወዴት ተጋረደ? ወዴትስ ተዘረጋ? ከጐንሽ በቀኝ ነውን? ከጐንሽ በግራ ነውን? ትንሽ አካል ስትሆኝ።
የሚያንጸባርቅ ነደ እሳት የሚከበው ኪሩቤል የተሸከሙት ዙፋን በሆድሽ ውስጥ ወዴት ተዘጋጀ? ወዴትስ ተተከለ? ታናሽ
ሙሽራ ስትሆኝ።» እያለ ከሰማያዊው ማደሪያ ጋር እያነጻጸረ አድንቋል። ምክንያቱም እርሷ የእሳቱንም ዙፋን ፥
የእሳቱንም መጋረጃዎች ሆና ተገኝታለችና።
ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፯
፩፡- ወላዲተ ቃል፤
« እግዚአብሔር ተወለደ፤»
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፡- ወንጌሉን መጻፍ የጀመረው በምሥጢረ ሥላሴ ነው። «በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ (አካላዊ ቃል፡- በአብ ህልው ሆኖ፥ ከአብ፡- በዘመንም በሥልጣንም ተካክሎ ነበረ)፤ በማለት አብን፥ «ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፤» በማለት ወልድን፥ «ይህም በመጀመሪያው በእግዚአብሔር
ዘንድ ነበረ፤ (በመንፈስ ቅዱስ ህልው ሆኖ፥ ከመንፈስ ቅዱስ በዘመንም በሥልጣንም ተካክሎ ነበረ)፤ በማለት መንፈስ
ቅዱስን አንሥቷል። ዮሐ ፩፥፩። ስለ ሦስቱ አካላትም፦ ሦስት ጊዜ እግዚአብሔር ብሏል። ይኸንን በተመለከተ ቅዱሳን
ሐዋርያትን የመሰለ፥ የተመሰገነ፥ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አትናቴዎስ፡- «የአካላዊ ቃል አባቱ እግዚአብሔር አብ በተለየ አካሉ አንድ ነው፥ የአብ ልጁ ቃሉ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ወልድም በተለየ አካሉ አንድ ነው፥ የአብ የወልድ እስትንፋሳቸው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በተለየ አካሉ አንድ ነው።» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፴፩፥፳፩) ቅዱስ ዳዊትም፡- «የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች፤» በማለት አብን፥ «የእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ አደረገችኝ፤» በማለት ወልድን፥ «የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች፤» በማለት መንፈስ ቅዱስን አንሥቷል። መዝ፡- ፻፲፯፥፲፮።
ቅዱስ
አትናቴዎስ ደግሞ፡- «አብ አምላክ ነው፥ ወልድም አምላክ ነው፥ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው፤ ነገር ግን ሦስት
አማልክት አይባሉም፥ አንድ ነው እንጂ።» ብሏል። (ሃይ አበው ፳፭፥ ፬)። ሥላሴ፡- በአካላት ፍጹም ሦስት ሆነው፦
«አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ» ተብለው በሦስት ስም ጸንተው ቢኖሩም፥ በግብርም አብ ወላዲ፥ ወልድ ተወላዲ፥ መንፈስ
ቅዱስ ሰራጺ፥ ተብለው ቢጠሩ ም ፥ በመለኮት፣ በባህርይ፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በህልውና፥ አንድ በመሆናቸው፡-
አንድ አምላክ፥ አንድ እግዚአብሔር፥አንድ ፈጣ ሪ ፥ አንድ ጌታ ተብለው ይታመናሉ። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ፡- «
እግዚአብሔርን በጌትነት ከዘመን አስቀድሞ የነበረ፥ ትክክል በሚሆኑ በሦስቱ አካላት እንዳለ እናውቀዋለን፤ ከዘመን
አስቀድመው የነበሩ፥ ዘመንን አሳልፈው የሚኖሩ ናቸውና፤ በመለኮት አንድ ናቸውና።» ብሏል። (ሃይ አበው ፺፥፲)።
የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ፊላታዎስም፡- « በስም ሦስት እንደሆኑ፥ በአካል፣ በገጽ፣ ሦስ ት ናቸው፤ በአንድ
መለኮት አንድነትም አንድ ናቸው፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፻፭፥፪)
፩፥፩፡- «ቃል»፤
ቅዱስ
ዮሐንስ፡- «ቃል»፡- ያለው ወልድን ነው፤ ምክንያቱም፦ በምሥጢረ ሥላሴ፡- አብ ልብ፥ ወልድ ቃል፥ መንፈስ ቅዱስ
እስትንፋስ ናቸውና። አብ የራሱንም ሆኖ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው፥ ወልድ የራሱንም ሆኖ የአብ የመንፈስ
ቅዱስ ቃላቸው ነው፥ መንፈስ ቅዱስም የራሱንም ሆኖ
የአብ የወልድ እስትንፋሳቸው ነው። አቡሊድስ ዘሮሜ «አብኒ ልቡናሆሙ ለወልድ ወለመንፈስ ቅዱስ፥ ወልድኒ ቃሎሙ
ለአብ ወለመንፈስ ቅዱስ፥ መንፈስ ቅዱስኒ ሕይወቶሙ ለአብ ወለወልድ፤» ብሏል። አካላዊ ቃል ሲናገር፡- አብ መንፈስ
ቅዱስ ቢሰሙት እንጂ የፍጡራን ጆሮ አይሰማውም። በእልመስጦአጊያ ላይ፡- «ወደ ሥጋዊ ጆሮ የማይገባ ነው፤ በዚህ
ዓለም ባለ፥ በምድርም በሚናገር ቃል አይደለም። ከአንተ ተገኝታ ፍጥረት ሁሉ በተፈጠረባት ቃል ነው እንጂ፥ በአንተና
በእኔ ህልውና ባለ መንፈስ ቅዱስ ህልው ሆኖ የሚናገር ይህ ቃል ነው።» የሚል ተጽፏል። ይህም ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ያመሰገነው ምስጋና ነው። «አባት ሆይ! አመሰግንሃለሁ፥
ብሎ ሥግው ቃል አመሰገነ። የማመሰግንህም በእሊህ ሥጋውያን ከናፍር አይደለም፤ እውነትና ሐሰት በሚናገሩበት በዚች
አንደበት አይደለም። በዚህ ቃል ነው እንጂ፤» ይላል። (ሃይ አበው፡- ፭፥፩፤ እልመስጦአግያ ጥምር ቃል ነው፥በቁሙ
ሲተረጐም፡- ቅድስት ሃይማኖት ማለት ነው)።
ልበ
አምላክ የተባለ ቅዱስ ዳዊት፡- በመዝሙሩ፡- «ሣህሉ ለእግዚአብሔር መልዓ ምድረ፥ ወበቃለ እግዚአብሔር ፀንዓ
ሰማያት፥ ወእምእስትንፋሰ አፉሁ ኲሉ ኃይሎሙ፤ የእግዚአብሔር ይቅርታው ምድርን ሞላ፥ በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች
ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ፤» ብሏል። መዝ ፴፪፥፭። በዚህም፡- የአብን፡- ልብነት፥
የወልድን፡-ቃልነት፥ የመንፈስ ቅዱስንም፡- እስትንፋስነት፥ መስክሯል። ምናልባት፡- «የእግዚአብሔር ይቅርታ አለ፥
እንጂ፡- መቼ ልብን አነሣ?» እንል ይሆናል። ነገር ግን፡- የይቅርታ ምንጩ፥ መገኛው፥ ልብ መሆኑን ካስተዋልን፥
መልሱን እዚያው ላይ እናገኛለን። በሌላ በኲል ደግሞ ልብ፥ ቃልና እስትንፋስ የማይለያዩ መሆናቸውን ማስተዋል
ይገባል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- ከትንቢት መጽሐፍ ጠቅሶ፡- «የጌታን ልብ ያወቀው ማነው?» ያለው አብን ነው።
ሮሜ ፲፩፥፴፬፣ ኢሳ ፵፥፲፫። እንደተባለውም፡- በአብ ልብነት የሚታሰበውን፡- በህልውና ከእርሱ ጋር አንድ ከሆኑ፥
ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ በስተቀር፥ ከፍጡር ወገን የሚያውቀው ማንም የለም። ጌታ በወንጌል፡- «ከአብ በቀር ወልድን
የሚያውቅ የለም፥ አብንም ከወልድ በቀር፡- ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር የሚያውቀው የለም፤» ያለው ለዚህ
ነው። ማቴ ፲፩፥፳፯።
አብ፡-
ልብ፥ ወልድ፡- ቃል፥ መንፈስ ቅዱስ፡- እስትንፋስ፥ ስለተባሉ፡- ወይም በልብ፥ በቃል፥ በእስትንፋስ፥
ስለተመሰሉ፡- ለአብ የተለየ ቃልና እስትንፋስ፥ ለወልድ የተለየ ልብና እስትንፋስ፥ ለመንፈስ ቅዱስም የተለየ ልብና
ቃል አላቸው ማለት አይደለም። እርስ በርሳቸው ህልዋን ናቸው፤ (በአኗኗር አንድ ናቸው)፤ አብ በልቡናነት፡- በወልድ
በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፤ (አለ)፤ ወልድ በቃልነት፡- በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፤ (አለ)፤ መንፈስ
ቅዱስም በእስትንፋስነት፡- በአብ በወልድ ህልው ነው (አለ)። ጌታ በወንጌል፡- «እኔን ያየ አብን አየ፤ እንዴት
አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ አንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁ ይህ ቃልም ከራሴ
የተናገርኩት አይደለም፤ በእኔ ያለ አብ እርሱ ይህን ሥራ ይሠራዋል፥ (በእኔ ህልው በሆነ በአብ ልብነት ይታሰባል)
እንጂ። እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤ ያለዚያም ስለ ሥራዬ እመኑኝ።» በማለት ለፊልጶስ
የመለሰለት ለዚህ ነው። ዮሐ ፲፬፥፱። ይኽንን በተመለከተም ፊላታዎስ ዘእስክንድርያ፡- «አብ፡- በወልድ በመንፈስ
ቅዱስ አለ፥ ወልድም፡- በአብ በመንፈስ ቅዱስ አለ፥ መንፈስ ቅዱስም፥ በአብና በወልድ አለ፤» ብሏል። ስለዚህ
ሥላሴ፡- እንደ አንድ ልብ አሳቢ ሆነው ያስባሉ፥ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው ይናገራሉ፥ እንደ አንድ እስትንፋስ
ሕያው ሆነው ይፈጽማሉ እንጂ መለያየት የለባቸውም። የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ኪራኮስ፡- «አብ፡- ከወልድ
ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ፡- ራሱ ብቻውን የሚሠራ አይደለም፤ እንዲሁ ወልድም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ ራሱ
ብቻውን የሚሠራ አይደለም፤ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስም፡- ከአብ ከወልድ ተለይቶ፡- ራሱ ብቻውን የሚሠራ አይደለም፤
አብ የሚሻውን፡- ወልድ መንፈስ ቅዱስ ይሠሩታል፡- እንጂ፤ ሥራቸውም እንድ ነው፥ባሕርያቸው አንድ ነውና፤» ብሏል።
(ሃይ አበው ፺፩፥፫)።
፩፥፪፦ ቃል አካላዊ ነው፤
በጽርዕ
ቋንቋ፡- አአትሪኮን፥ ብርፎሪኮን፥ አተርግዋን፥ የሚባሉ ቃላት አሉ። እነዚህም፡- አካል የሌላቸው ዝርዋን ናቸው።
የመላእክት፥ የሰው እና የእንስሳት ቃል አካል የለውም፥ ዝርው ነው። ዝርው ማለት፡- የተዘራ፥ የተበተነ፥ ብትን፥
ብትንትን፥ አንድነት የሌለው ማለት ነው። በምሳሌያዊ አነጋገር ነፋስ የበተነው አመድ ማለት ነው። የወልድ ቃልነት
ግን እንዲህ አይደለም፥ አካላዊ ነው። ይኽንን በተመለከተ፦ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘቂሣርያ፦ «ይህንንም ቃል የተባለውን
ስም፦ አተርግዋን ፥ ብርፎሪኮን ፥ አአትሪኮን ፥ ከተባሉት ከሦስቱ ዓይነት ቃላትና ከሦስቱ ግብራት ለይተን
እናውቃለን። እሊህ እግዚአብሔር የፈጠራቸው ቃላት ናቸው፤ በመጽሐፍ እንደተጻፈ በአካል ያሉ አይደሉም። አተርግዋን
(የመላእክት ቃል ነው)፤ በአካላዊነት ያለ አይደደለም፤ ብርፎሪኮንም ነቢያት ከእግዚአብሔር ዘንድ የሰሙት ቃል ነው፤
ይኸውም የትንቢት ቃል ነው፤ በአካል ተለይቶ ያለ አይደለም፤ አአትሪኮን በአየር የሚፈስሰው ቃላችን ነው፤
ከእነርሱም ድምፅ ይገኛል፤ በአካላዊነት ያለ አይደለም። ዘፍ ፲፩፥፯ ፣ ፩ኛ ቆሮ ፲፫፥፲ ፣ዕብ ፩፥፩ ፣ ፬፥፯።
የእግዚአብሔር ቃል ግን የማይለወጥ ረቂቅ ከሆነ ከአብ ባሕርይ ተገኝቶ በአካላዊነት ያለ ነው፤ ይኸውም ከአብ ጋር፦
በቅድምና የነበረ፥ ከዘመን የሚቀድም ቀዳማዊ ነው፤ ከእርሱም አይለይም፤ ልደቱ ከእርሱ አያልቅም፤ ያለመለየት በጊዜው
ሁሉ ከእርሱ ጋር ከዘመን አስቀድሞ የነበረው ነው እንጂ። ዳን ፯፥፱-፲፬ ፣ ራእ ፩፥፲፫-፲፰። ይህን ቃል፦ አካል
፥ባህርይ የላቸውም፥ ብለን እንደተናገርናቸው ቃላት፦ አካል ባሕርይ የሌለው አታስመስሉት፤ እንደ አብ እንደ መንፈስ
ቅዱስ በአካል በገጽ ፍጹም ነው እንጂ፤ ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፲፫፥፳፪)። በምሥጢረ
ሥላሴ፡- ሦስት አካላት አሉ፤ ለአብ ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ ፍጹም አካል አለው፤ ለወልድ፡- ፍጹም ገጽ ፍጹም
መልክ ፍጹም አካል አለው፤ ለመንፈስ ቅዱስም፡- ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ ፍጹም አካል አለው፤ ብለን ካመንን በኋላ፡-
ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ (ቃል) አካል የለውም፥ ማለት አንችልም። ቅዱስ ዳዊት፡- ስለ ሦስቱ አካላት፡-
«ፊትህን (ገጽህን) ፈለግሁ፤» በማለት አብን፥ «ፊትህን (ገጽህን) እሻለሁ፤» በማለት ወልድን፥ «ፊትህን(ገጽህን)
ከእኔ አትመልስ፤» በማለት መንፈስ ቅዱስን አንሥቷል። መዝ ፳፮፥፰። እንግዲህ ፊት (ገጽ) ካለ መልክም አካልም
መኖሩ ግድ ነው።
፩፥፫፦ ለምን? ቃል ብሎ ጀመረ፤
ቅዱስ
ዮሐንስ ወንጌላዊ፡- «በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤» በማለት ወንጌሉን መጻፍ የጀመረው ስለ ሦስት ነገር ነው። ፩ኛ፦
ሥላሴ በህልውና (በአኗኗር) አንድ መሆናቸውን ለመግለጥ ነው። ምክንያቱም፡- ከልብ ከእስትንፋስ ተለይቶ ለብቻው
በአፍአ (በውጭ) የሚገኝ ቃል ስለሌለ ነው። ፪ኛ፡-ሥላሴ በዘመን መቀዳዳም እንደሌለባቸው ለመግለጥ ነው።
ምክንያቱም፡- ልብ፥ እስትንፋስ ቀድመውት ወደኋላ የሚገኝ ቃል ስለሌለ ነው። ይኸንን በተመለከተ ሠለስቱ ምዕት፡-
«አብ፡- ከወልድ ተለይቶ የኖረበት ዘመን የለም፤ ወልድም ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ የኖረበት ዘመን የለም፤ መንፈስ
ቅዱስም ከአብ ከወልድ ተለይቶ የኖረበት ዘመን የለም፤ --- ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ልጅ ያለው እግዚአብሔር አብ ብቻ
ነው።--- አብ ከዘመን በኋላ አልወለደውም፥ እርሱ ቀዳማዊ ወልድ፡- ከአብ ጋር በቅድምና የነበረ ነው እንጂ።---
እንደ አብም ሁሉን የፈጠረ ነው። እንዲሁ መንፈስ ቅዱስም፡- ከአብ ከወልድ ጋር በቅድምና የነበረ ቀዳማዊ ነው፤
በሥራውም ከአብ ከወልድ ጋር አንድ ነው፤» ብለዋል። (ሃይ
አበው ፲፱፥፮)። ፫ኛ፡- የቃልን ፈጣሪነት ለመግለጥ ነው። ምክንያቱም፡- እግዚአብሔር ዓለማትን የፈጠረው በቃሉ
ነውና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- «ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠረ፥ የሚታየውም ነገር ከማይታየው እንደሆነ
በእምነት እናውቃለን።» ያለው ለዚህ ነው። ዕብ ፲፬፥፫፣ ዘፍ ፩፥፩። ቅዱስ ዳዊትም፡- «በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች
ጸኑ፤ (ባለማለፍ ጸንተው የሚኖሩ፥ ኅልፈት የሌለባቸው ሰባቱ ሰማያት ተፈጠሩ)፤» ብሏል። መዝ ፴፪፥፮። ቅዱስ
ዮሐንስም በበኵሉ፡- የቃልን ቀዳማዊነት፥ እግዚአብሔርነት፥ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በህልውና (በአኗኗር) አንድ
መሆን፥ ከተናገረ በኋላ፡- «ወኵሉ ቦቱ ኮነ፤ ወዘእንበሌሁሰ አልቦ ዘኮነ ወኢምንትኒ እምዘኮነ፤ ሁሉም በእርሱ ሆነ፤
(በእርሱ ህልውና በእርሱ አንድነት ተፈጠረ)፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም፤ (ከተፈጠረው ፍጥረት
ግን ያለ እርሱ ህልውና ማለትም እርሱ ሳይኖር ምንም ምን የተፈጠረ የለም፤» ብሏል። ዮሐ ፩፥፫።
፩፥፬፦ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤
የብሉይ
ኪዳን ዘመን የጨለማ ዘመን ነበረ። ዘመኑን ጨለማ ያሰኘው፡- በአዳም ኃጢአት ምክንያት፡- በሰው ልጅ ላይ የወደቀው
የሥጋና የነፍስ ርግማን ነው። ይህም ርግማን በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስን፥ በርደተ መቃብር (ወደ መቃብር
በመውረድ) ላይ ርደተ ገሃነምን (ወደ ገሃነመ እሳት መውረድን) ያመጣ ነው። በመሆኑም ለሰው ዘር በጠቅላላ መርገመ
ሥጋን እና መርገመ ነፍስን አስወግዶ፦ ይኸንን ጨለማ የሚገፍ ብርሃን ያስፈልገው ነበረ፤ ይህም ብርሃን ያለጥርጥር
እግዚአብሔር ነበረ። ቅዱስ ጳውሎስ፡- «ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤» ብሏል። ፩ኛ ጢሞ ፮፥፲፮።
ቅዱስ
ዮሐንስ፡- ስለ ራሱ ማንነት፡- «ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክርነት መጣ፤» ካለ በኋላ፡- «ለሰው ሁሉ
የሚያበራው (ዕውቀትን የሚገልጠው)እውነተኛው ብርሃንስ ወደ ዓለም የመጣው ነው። በዓለም ነበረ፤ (ይኸውም እንደ
እንግዳ ደራሽ፥ እንደ ውኃ ፈሳሽ፥ በዓለሙ የሌለ ሆኖ አይደለም፤ ቀዳማዊ ነው፥ ዓለሙን ያስገኘ ነው፥ (በዓለሙ
ውስጥ ከዓለሙም ውጭ ያለ ምሉዕ ነው)፤ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፤ (የሚታየውና የሚያልፈው ዓለም፥ የማይታየውና
የማያልፈውም ዓለም፥ ሁሉም በእርሱ ተፈጠረ)፤ ዓለሙ ግን አላወቀውም። (በወዲያኛው ዓለም ቅዱሳን መላእክት፡-
የባህርይ አምላክ መሆኑን አውቀው የሚያመሰግኑትን፥ በወዲህኛው ዓለም የሚኖሩ ደቂቀ አዳም ማለትም የአዳም ልጆች
አላወቁትም)። ወደ ወገኖቹ መጣ፤ (ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር ብሎ ወደፈጠራቸው ወደ ወገኖቹ መጣ፤
አንድም የበኵር ልጆቼ ወዳላቸው ወደ ወገኖቹ ወደ እስራኤል መጣ)፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። (የባህርይ
አምላክ፥ ፈጣሪ፥ እግዚአብሔር፥ ዕሩይ ምስለ አብ ወመንፈስ ቅዱስ ብለው አላመኑበትም)፥ ብሏል። ከዚህም
አያይዞ፡-ቢያምኑበት ኖሮ ምን ይጠቀሙ እንደነበረ ሲናገር፡- «ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር
ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው። (በገቢረ ኃጢአት፥ በአምልኮ ጣዖት ያሳደፉትን፤ በተፈጥሮ አግኝተውት የነበረውን
ነፃነት አደሰላቸው)። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ፡- (በጥምቀተ ክርስትና፡- ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ
ተወልደው ልጅነትን አገኙ እንጂ፡-) ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር፥ ወይም ከወንድና ከሴት ፈቃድ አልተወለዱም፤» ብሏል።
ነቢዩ
ኢሳይያስ፡- « በጨለማ የሄደ ሕዝብ (አምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን በሲኦል የኖሩ ነፍሳት) ብርሃንን አዩ፥
በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ (በሞተ ሥጋ በሞተ ነፍስ ለተያዙ ሁሉ) ብርሃን ወጣላቸው፥ በማለት ትንቢት የተናገረው
ለዚህ ነበር። ኢሳ ፱፥፪፣ ማቴ ፬፥፲፬። ጌታም ራሱ በወንጌሉ፡- «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት
ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም፤» ብሏል። ዮሐ ፰፥፲፪፣ ፱፥፭።
፪፦ ቃል ሥጋ ሆነ፤ ዮሐ ፩፥፲፬
ቅዱስ ዮሐንስ፦ «ከእግዚአብሔር
ተወለዱ፤» በማለት፦ ግዙፋኑ ከረቂቁ ከእግዚአብሔር በመንፈስ በረቂቅ ልደት እንሚወለዱ የተናገረው ያለምክንያት
አይደለም። ሰው ከእግዚአብሔር በመንፈስ መንፈሳዊ ልደት ተወልዶ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሚሆን ሁሉ፦ ረቂቁ ከግዙፉ
ማለትም፦ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ የሰው ልጅ እንደሆነ
ለመናገር ፈልጎ ነው። በመሆኑም፦ « ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤» ያላቸው፦ እንደቀድሞው ማለትም፦ እንደ ብሉይ ኪዳን
ዘመን በረድኤት ፥ በምሳሌ እንዳይመስላቸው ሲል፦ « ያ በቅድምና ነበረ ፥ በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፥
እግዚአብሔር ነው ፥ ወደ ዓለም የመጣ ብርሃን ነው፥» ያልኳችሁ አካላዊ ቃል ሥጋ ሆነ ፤ በእኛም አደረ፤ ( በኲነት
በመሆን በተዋሕዶ አደረ) ፤» ብሏቸዋል።
«ሆነ፤»
የሚለውን ይዘው ፦ «ተለወጠ፤» እንዳይሉበትም «አደረ፤» ብሏል። «አደረ፤» የሚለውንም ይዘው « ኅድረት (
መለኮት ሥጋንና ነፍስን አልተዋሃደም) ፤ » እንዳይሉበት «ሆነ፤» ብሎባቸዋል። «ኮነ፤» እና «ኀደረ፤» እንደ
አለቃና እንደ ጠበቃ ይጠባበቃሉ። «ኮነ፤» የሚለው ብቻ ተይዞ፦ «ተለወጠ፤» እንዳይባል፦ «ኀደረ፤» ይጠብቀዋል።
«ኀደረ፤» የሚለውም ተይዞ፦ «ኅድረት፤» እንዳይባል፦ «ኮነ፤» ይጠብቀዋል።
፪፥፩፦ ቃል ከእመቤታችን የነሣው ነፍስንም ጭምር ነው፤
«ቃል
ሥጋ ሆነ፤» የሚለውን፦ ንባቡን ብቻ በመያዝ፦ ነፍስን አልነሣም የሚሉ አሉ። ይህም በተዘዋዋሪ ሳይሆን ፥ ፊት
ለፊት ከእውነት ጋር መጋጨት ፣ መጣላት ነው። እውነት ደግሞ እግዚአብሔር ነው፤ የነቢዩ የሳሙኤል እናት ሐና ፦ «
ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ፤ በሰማይም ያንጐዳጉድባቸዋል፤ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል፤»
ብላለች። ፩ኛ ሳሙ ፪፥፲።
ነፍስ
ከሥጋ ጋር በተዋሕዶ ያለች በመሆኗ፦ አካላዊ ቃል በማኀጸነ ድንግል ማርያም አድሮ፦ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ሰው
በሆነ ጊዜ ፦ ከሥጋዋ ሥጋ በነሣበት ቅጽበት ፥ ከሥጋ ጋር በተዋሕዶ ያለችን ነፍስም ነሥቷል። ደግሞም ሰው ማለት
የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ነው። ሥጋ ብቻውን ወይም ነፍስ ብቻዋን ሰው አይባሉም። ስለዚህ አካላዊ ቃል ከእመቤታችን
የነሣው ሥጋን ብቻ ቢሆን ኖሮ « አምላክ ሰው ሆነ፤» አይባልም ነበር። እርሱም፦ «የሰው ልጅ፤» ተብሎ አይጠራም
ነበር። ነገር ግን ሰው የሚያሰኘውን ሥጋን ነፍስንም ከእመቤታችን ነሥቶ በተዋሕዶ ሰው በመሆኑ « የሰው ልጅ፤»
ተብሏል።
- «የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል?» ማቴ ፲፮ ፥፲፫ ።
- «የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤» ማቴ ፲፮ ፥፳፯።
- «የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ፥ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክት ይመጣሉ፤» ማቴ ፳፭ ፥ ፴፩።
- «የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደተጻፈ ይሄዳል፥ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤» ማቴ ፳፮፥፳፬።
- «ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ፤» ማቴ ፳፮ ፥፷፬።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በምድረ ግብፅ ስደት እያለች
፦ የእግዚአብሔር መልአክ፦ ለአረጋዊው ፥ለዘመዷ ፥ ለጠባቂዋ ፥ ለጻድቁ ፥ ለዮሴፍ ተገልጦ፦ «የሕፃኑን ነፍሰ
የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እሥራኤል ሀገር ሂድ፤» ብሎታል። ማቴ ፪፥፳። ቃል፦
ነፍስንም ጭምር ባይነሣ ኖሮ ፦ መልአኩ፦ የሕፃኑን(የኢየሱስን) ነፍሰ፤ » አይልም ነበር። ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጌቴሴማኒ አጸድ በጸለየ ጊዜ፦ «ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ አዘነች፤» ብሏል። ማቴ
፳፮፥፴፰። ቅዱስ አግናጥዮስ፦ ይኽንን ይዞ፦ «ነፍስን አልነሣም የሚል ፥ እንዲህም የሚክድ ሰው ፥ ነፍሴ እስከ ሞት
ድረስ አዘነች ፥ ያለውን የጌታችን የኢየሱስን ቃል ሰምቶ ፥ እንግዲህ ይፈር፤» ብሏል። (ሃይ አበው ፲፩፥፲፮)።
ጌታችን የሞቱንና የትንሣኤውን ነገር ባስተማረበትም ወቅት፦ «ነፍሴንም ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና፤» በማለት
ተናግሯል። ዮሐ ፲፥፲፯። ድኅነተ ዓለምን ፦ በመልዕልተ መስቀል በፈጸመ ጊዜ ደግሞ ፦ «ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ
ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ፤» ይላል። ማቴ ፳፯፥፶። ጌታችን፦ ስለእኛ አሳልፎ የሰጠው ይህ ነፍስ ከእመቤታችን የነሣው
ነው። ማር ፲፭፥፴፯፣ ዮሐ ፲፱፥፴። በሉቃስ ወንጌል ላይ ደግሞ፦ « አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ
አለ፥ ይህን ብሎ ነፍሱን ሰጠ።» ይላል። ሉቃ ፳፫፥፵፮። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፦ ቃል ሥጋንም ነፍስንም እንደነሣ፦
በተናገረበት አንቀጽ፦ «ነሥአ እምድንግል ሥጋ ዘቦቱ ነፍስ ነባቢት ወለባዊት፤ ከድንግል የምትናገር ፥ የምታውቅ
ነፍስ ያለችው ሥጋን ነሣ፤» ብሏል። (ሃይ አበው ፷፮፥፴)። ቅዱስ ቄርሎስ ደግሞ፦ «በኋላ ዘመንም ገብርኤል መልአክ
፥ ወደ ንጽሕት ድንግል ማርያም በተላከ ጊዜ፦ ጸጋን ክብርን የተመላሽ ድንግል ሆይ ፥ እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋን ፣
ከነፍስሽ ነፍስን ነሥቶ ሰው ይሆናልና ፥ ክብር ላንቺ ይገባል ብሎ በነገራት ጊዜ፦ ሳይወሰን በማይመረመር ግብር
ያለዘርዐ ብእሲ (ያለወንድ ዘር) በመስማት ብቻ ቃል በማኅፀኗ አደረ፤» ብሏል። (ሃይ አበው ፸፩ ፥፫)።
፪፥፪፦ የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ፤
ሰው
ማለት፦ የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ነው ብለናል። ቅዱስ ዮሐንስ፦ «ቃል ሥጋ ሆነ፤» ያለው፦ «ሥጋን ብቻ ነሣ፤»
ለማለት አይደለም ፥ የነፍስ እና የሥጋን ተዋሕዶ በሥጋ ስም ሲጠራ እንጂ። የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ በሥጋ ስም ወይም
በነፍስ ስም ሊጠራ ይችላል።
፪፥፪፥ሀ፦ በሥጋ ስም በሚጠራበት ጊዜ፤
ነቢየ
እግዚአብሔር ዳዊት፦ በመዝሙሩ፦ «ስማዕ ጸሎተ ኲሉ ዘሥጋ ዘመጽአ ኀቤከ፤ ወደ አንተ የመጣውን የሥጋን ሁሉ ጸሎት
ስማ፤» ብሏል። መዝ ፷፬ ፥ ፪። ይህም የነፍስንና የሥጋን ተዋሕዶ በሥጋ ስም ሲጠራ እንጂ፦ ነፍስ የተለየው ወይም
የሌለው ሥጋ ብቻውን ይጸልያል ፥ ማለት አይደለም። በመሆኑም፦ «የሥጋን ጸሎት፤» በማለቱ፦ «ነፍስ የሌለው ሥጋ
ብቻውን ጸለየ፤» አያሰኝበትም። ነፍስ የተለየው ሥጋማ ሙት ነው ፥ በድን ፥ሬሣ ፥አስከሬን ነው። ያዕ ፪፥፳፮።
፪፥፪ለ፦ በነፍስ ስም በሚጠራበት ጊዜ፤
ቅዱስ
ሉቃስ ወንጌላዊ፦ በግብረ ሐዋርያት መጽሐፉ ላይ፦ ስለ ዮሴፍ ወልደ ያዕቆብ ሲተርክ፦ «የአባቶችም አለቆች፦ በዮሴፍ
ቀንተው ወደ ግብጽ ሸጡት፤ እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ነበረ። ከመከራውም ሁሉ አዳነው፤ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን
ፊትም ሞገስና ጥበብን ሰጠው፤ በግብፅና በከነዓን ሀገር ረኃብና ታላቅ ጭንቅ መጣ፤ አባቶቻችንም የሚበሉት አጡ።
ያዕቆብም በግብፅ ሀገር እህል እንዳለ ሰማ፤ አባቶቻችንንም አስቀድሞ ላካቸው፤ ወደ ግብፅም እንደገና በተመለሱ ጊዜ
ወንድሞቹ ዮሴፍን አወቁት፤ ፈርዖንም የዮሴፍን ዘመዶች አወቃቸው። ዮሴፍም አባቱን ያዕቆብንና ዘመዶቹን ሁሉ
እንዲጠራቸው ላካቸው፤ ቁጥራቸውም ሰባ አምስት ነፍስ ነበረ፤» ብሏል። የሐዋ ፯፥፱-፲፬። ይህም የሥጋን እና
የነፍስን ተዋሕዶ በነፍስ ስም ሲጠራ እንጂ፦ ሥጋቸውን በከነዓን አስቀምጠው፦ በነፍስ ብቻ ወደ ግብፅ ወረዱ ፥ ማለቱ
አይደለም። ቅዱስ ዳዊትም፦ «ዐይነ ኲሉ ነፍስ ይሴፎ ኪያከ፤ የሰው ሁሉ ነፍስ አንተን ተስፋ ያደርጋል፤» በማለት
የሥጋን እና የነፍስን ተዋሕዶ በነፍስ ስም ጠርቷል። መዝ ፻፵፬፥፲፭። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም የሥጋን
እና የነፍስን ተዋሕዶ በነፍስ ስም ስትጠራ፦ «ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፤» ብላለች። ሉቃ ፩፥፵፯።
፫፦ ነፍስን ጭምር እንደነሣ የሊቃውንት ምስክርነት፤
ሊቃውንተ
ቤተ ክርስቲያን ይኽንን በተመለከተ ያስተማሩት ትምህርት ሁሉ አንድ ነው። ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ፦ «ወልድም
ኃጢአት እንደበዛ ባየ ጊዜ ፥ በማይነገርና በማይመረመር ግብር ወርዶ ፥ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም
ማኅፀን አደረ፤ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀንም በማኅፀኗ ተወሰነ። በእርሷ አድሮ ሊዋሐደው የፈጠረውን ፍጹም ሥጋን በአብ
ፈቃድ፥ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ከእርሷ ነሣ። ከፈጣሪነት እንዳናወጣው፦ አብ ፈጠረለት ፥ አንበል፤ ሊዋሐደው እርሱ
ፈጠረው እንላለን እንጂ። ከአብ ጋር በሥራው ሁሉ ( በፈጣሪነት)፦ አንድ ጌትነት ፥አንድ አገዛዝ አለውና፤ ሰው
ለመሆን በወረደ ጊዜ፥ ሥጋን ይዞ አልመጣም ፤ የሰው ዘር፦ ምክንያት ሳይሆነው፦ ከድንግል ማርያም ሥጋን ነፍስን
ነሥቶ ተዋሐደ እንጂ።» በማለት መስክሯል። (ሃይ አበው ፻፲፯፥፱)። ቅዱስ አቡሊድስም፦ «ሥጋ የሌለው እርሱ
ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን ነፍስን ነሥቶ ሰው ሆነ፤ እርሱን የምንመስል ሰማያውያን ያደርገን
ዘንድ፤ እርሱ ሰማያዊ ነውና።» በማለት አስተምሯል። (ሃይ አበው ፴፱፥፵፮)። የሮም ሊቀ ጳጳሳት፦ አዮክንድዮስም፦
«እግዚአብሔር ከሰማይ በወረደ ጊዜ፦ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀንም ባደረ ጊዜ፦ ከእርሷም ሥጋን
ነፍስን ነሥቶ ሰው በሆነ ጊዜ፦ ከሰማይ ሥጋን ይዞ አልመጣም፤ መለኮቱም ከምድር አልተገኘም።» በማለት ተናጎሯል።
(ሃይ አበው ፵፬ ፥፪) ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ደግሞ የቅዱስ ዳዊትን ትንቢት ሲተረጉም፦ «ነቢዩ ዳዊት፦ ነፍሴን በሲኦል
አትተዋትም፤ የባሕርይ ልጅህንም ሙስና መቃብርን ያይ ዘንድ አሳልፈህ አትሰጠውም፥ አለ። ይህም ጌታ በተዋሐደው አካል
ያለውን የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ያስረዳል፤ የቀና ልቡና፥ እውቀት ፥ በእርሱ ጸንቶ ይኖር ዘንድ ዳዊት የተናገረው
እውነት ሆነ። ነፍስ መለኰትን ተዋሕዳ ወደ ሲኦል ወርዳለችና፤ ሥጋም ሦስት መዓልት ፥ሦስት ሌሊት ፥ በመቃብር ሳለ፦
መለኮት፦ ከሥጋ አልተለየም። አምላክ ሰው የመሆኑን እውነትነት ያስረዳ ዘንድ፦ መለኮትና ነፍስ በሲኦል ምሥጢርን
ፈጽመዋልና፤ በሲኦልም በቁራኝነት አልተያዙምና።» ብሏል። (ሃይ አበው ፶፭፥፯)። በዚህም፦ «ቃል ሥጋን እንጂ
ነፍስን አልነሣም ፥ መለኮቱ እንደ ነፍሰ ሆነለት፤» የሚሉትን ፈጽሞ አሳፍሯቸዋል። ቅዱስ ኤራቅሊስም፦ «አምላክን
ከወለደች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው አካል፦ ሥጋ ከእርሱ ጋር አንድ ሆነ፤ ከባሕርያችን ተገኝቶ ፦
አምላክ የሆነ ሥጋ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ ሕይወቱ ሲሆን፦ የምትናገር የሥጋ ሕይወት ነፍስ አለችው፤» ብሏል። (ሃይ
አበው ፵፰፥፳፩)። ቅዱስ ቄርሎስም በበኲሉ፦ «ቅዱሳን አባቶቻችን፦ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ከአብ
ባሕርይ የተገኘ፦ አንድ ወልድ ፥ ቃል ፥ እንደሆነ ተናገሩ፤ ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ፥ ከብርሃን
የተገኘ ብርሃን ፥ ሁሉ የተፈጠረበት እርሱ፦ ነፍስን ሥጋን ነሥቶ፦ ሰው ሆነ፤ ከድንግልም በሥጋ ይወለድ ዘንድ
ወደደ፥ በእኛም ባሕርይ ተገለጠ ፥ ሰው የሆነበት ባሕርይ ይህ ነው።» በማለት የእውነት ምስክር ሆኗል። (ሃይ አበው
፸፪፥፩)
ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፰
እግዚአብሔር ተወለደ፤
ካለፈው የቀጠለ፦
፬፦ ቃል ሥጋ የሆነው ፦ ያለ ሚጠት ነው፤
ሚጠት፦
ማለት፦ መመለስ ማለት ነው። ይኽውም እንደ ማየ ግብፅ ፥ እንደ በትረ ሙሴ ነው። «ሙሴና አሮንም እግዚአብሔር
እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ አሮንም በትሩን አነሣ፤ በፈርዖንና በሹሞቹ ፊት የወንዙን ውኃ መታ፤ የወንዙም ውኃ
ሁሉ ተለወጦ ደም ሆነ።» ይላል። ዘዳ ፯፥፳። የግብፅ ወንዞች ደም የሆኑት ውኃነታቸውን ሙሉ በሙሉ ለቅቀው ነው።
በመጨረሻም ደምነታቸውን ትተው ወደ ውኃነታቸው ተመልሰዋል። ባይመለሱ ኖሮ እስከዛሬም የግብጽ ወንዞች ደም ሆነው
በቀሩ ነበር። ሚጠት ማለት እንዲህ ነው።
እግዚአብሔርም
ሙሴን፦ «ይህ በእጅህ ያለው ምንድን ነው?» አለው። እርሱም «በትር ነው፤» አለ። «ወደ መሬትም ጣለው፤ አለው፤
እባብም ሆነ፤ ሙሴም ከእርሱ ሸሸ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «እጅህን ዘርግተህ ጅራቱን ያዝ፤» አለው፤ ሙሴም እጁን
ዘርግቶ ፥ ጅራቱን ይዞ ፥ አነሣው፤ በእጁም ላይ በትር ሆነ።የሙሴ በትር እባብ የሆነችው እንጨትነቷን ለቅቃ ነው።
በዚያው አልቀረችም ፥ ተመልሳ በትር ሆናለች። ዘፀ ፫፥፪። እንግዲህ ቃል ሥጋ ሲሆን፦ አምላክነቱን ለቅቆ ሰው የሆነ
፥ ተመልሶም ሰውነቱን ለቅቆ አምላክ የሆነ አይደለም። ቅዱስ ቄርሎስ፦ «ክርስቶስን በፊት ሰው ሆኖ ኋላ ተመልሶ
አምላክ ሆነ አንለውም፤ ቃል ጥንቱን አምላክ ነበረ እንጂ፤ እርሱ አንዱ፦ ሰው የሆነ አምላክ እንደሆነ እናውቅ
ዘንድ፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፸፪፥፭)
፭፦ ቃል ሥጋ የሆነው፦ ያለ ውላጤ ነው፤
ውላጤ
ማለት መለወጥ ማለት ነው። ይህም እንደ ብእሲተ ሎጥ እና እንደ ማየ ቃና ነው። ቅዱሳን መላእክት፦ ቅዱስ ሚካኤልና
ቅዱስ ገብርኤል፦ ሎጥን፦ «ተነሣ፤ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ፤ አንተም በከተማይቱ
ሰዎች ኃጢአት እንዳትጠፋ፤» ብለውት ከከተማይቱ እያቻኮሉ አውጥተውታል። ከዚህም በኋላ፦ ራስህን አድን፤ ወደ ኋላ
አትይ ፥ በዚህም ዙሪያ ሁሉ አትቁም ፥ እንዳትጠፋም ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ።» ብለውታል። ዘፍ ፲፱
፥፲፪-፳፰። የሎጥ ሚስት ግን ቅዱሳን መላእክት የሠሩላቸውን ሥርዓት አቃልላ በዚያ ሥፍራ ቆመች ፥ ወደ ኋላዋም
አየች። በዚህም ምክንያት ሙሉ በሙሉ ተለውጣ የጨው ሐውልት ሆና ቀርታለች።
በአዲስ
ኪዳን ደግሞ፦ በቃና ዘገሊላ ሠርግ ነበረ፤ በዚህ ሠርግ ላይ፦ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና የጌታ ደቀመዛሙርት ነበሩ። እናትን ጠርቶ ልጅን ፥ ወይም ልጅን ጠርተው
እናትን፤ መምህርን ጠርተው ደቀመዛሙርትን ፥ ወይም ደቀመዛሙርትን ጠርተው መምህርን ማስቀረት ስለማይገባ ሁሉም
ተጠርተዋል። ወደ ሠርጉ የተጠሩ እድምተኞች ብዙዎች ስለነበሩ ፥ የወይን ጠጁ አልቆ ሠራተኞቹ ተጨነቁ። ከሰው ወገን
የሰው ችግር ፈጥኖ የሚገባት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሳይነግሯት አውቃላቸው አማለደቻቸው። ጌታም በስድስቱ
የድንጋይ ጋኖች ያስሞላውን ውኃ በተአምር ወደ ወይን ጠጅነት ለወጠው። ዮሐ ፪፥፩-፲፩። ውኃው ሙሉ በሙሉ ተለውጦ
የወይን ጠጅ ሆኗል። ውላጤ ማለት እንዲህ ነው። «ቃል ሥጋ ሆነ፤» ማለት ግን፦ አምላክነቱን ለቅቆ ፥ ተለውጦ፥ ሰው
ሆነ፤ ማለት አይደለም። ምክንያቱም ቃል እግዚአብሔር ነውና፤ ዮሐ ፩፥፪። እግዚአብሔር ደግሞ አይለወጥም።
ይኽንንም፦ «እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤» በማለት ነግሮናል። ሚል ፫፥፮። ደግሞም ቃል ሥጋ የሆነው በመለወጥ
ቢሆን ኖሮ፦ ጌታችን፦ ሰው ከሆነ በኋላ፦ «እኔና አብ አንድ ነን፤» አይልም ነበር። ዮሐ ፩፥፴። ሐዋርያው ቅዱስ
ጳውሎስም፦ በመስቀል ላይ የፈሰሰውን ደም፦ «የእግዚአብሔር ደም፤» አይለውም ነበር። የሐዋ ፳፥፳፰። ከዚህም ሌላ
አምላክ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን የማዳን ዓላማ መርሳት አይገባም። ለመሆኑ ጌታችን ዓለምን ለማዳን ተለወጦ ሰው
መሆን ለምን አስፈለገው? በሰማይ ዙፋን እንደተቀመጠ፦ በአንድ ነቢይ ወይም በአንድ ሐዋርያ ደም ዓለምን አያድንም
ነበር? ቅዱስ ቄርሎስ፦ «ቃል ሰው ሲሆን ከነበረበት ባህርዩ አልተለወጠም ፥ በእኛ ባሕርይ ቢገለጥም ፦ ቃል
አስቀድሞ በነበረበት ባሕርዩ ጸንቶ ኖረ፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፸፪ ፥፬) ። ዳግመኛም፦ «የማይታየው ሳይለወጥ
ሰው ሆነ፤ ከቀደሙ አበው፦ አስቀድሞ የነበረ እርሱ በሥጋ ተወለደ፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፸፪ ፥ ፲፭)።
ሦስተኛም፦ «የእግዚአብሔር ቃል ሥጋን ወደ መሆን ፥ ሥጋም መለኮትን ወደ መሆን ተለወጠ አንልም ፤ የእግዚአብሔር
ቃል አይናወጥም ፥ አይለወጥምና፤» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፸፬፥፵) ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙም፦ «ሁሉን የፈጠረ
ነው ፤ ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ ፥ ሰውም ሆኖ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከተወለደ በኋላ እግዚአብሔር ቃል ነውና፤
እርሱ መቸም መች አንድ ነው ፤ የመለኮቱ ባሕርይ አልተለወጠም፤» ብሏል። (ሃይ ፡ ፷፥፲፯)። ቅዱስ ዮሐንስ
አፈወርቅ ደግሞ፦ «ዳግመኛ ድንግልናዋ
እንዳልተለወጠ፦ ጽኑዕ መለኮቱ ከባሕርዩ አልተለወጠም፤ አምላክ ለሦስትነት እንደሚገባ ተወለደ፤» ብሏል። (ሃይ፡
አበው ፷፯ ፥፯)። ቅዱስ ኤፍሬምም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም ላይ፦ «እምድኅረ ወለደቶ ድንግልናሃ ተረክበ ፥ ወመለኮቱ
ኢተወለጠ ኮነ ወልደ ዕጓለ እመሕያው፤ «እርሱንም ከወለደችው በኋላ ማኅተመ ድንግልናዋ አልተለወጠም ፥ ሰውም ቢሆን
ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠም፤» ብሏል።
፮፦ ቃል ሥጋ የሆነው ያለ ቱሳሔ ነው፤
ቱሳሔ
ማለት፦ ቅልቅል ፥ የተቀላቀለ ማለት ነው። ይኸውም እንደ ማር እና እንደ ውኃ ፥ እንደ ወተት እና እንደ ቡና
ነው። ማር እና ውኃ ቢቀላቀሉ፦ ስም ማዕከላዊ ፥መልክ ማዕከላዊ ፥ ጣዕመ ማዕከላዊ ፥ ይገኝባቸዋል። ስም ማዕከላዊ
የሚባለው፦ የዕለቱ ብርዝ ፥ የሰነበተው ጠጅ ይባላል እንጂ ከቀደሙት ስሞች በአንዱ ወኃ ወይም ማር ተብለው አይጠሩም።
መልክ ማዕከላዊ የሚባለው፦ ብርዙ ወይም ጠጁ፦ እንደ ማር አይነጣም ፥ ወይም እንደ ውኃ አይጠቁርም ፥ ማዕከላዊ
መልክ ይይዛል። ጣዕም ማዕከላዊ የሚባለው ደግሞ፦ እንደ ማር ሳይከብድ ፥ እንደ ውኃም ሳይቀል መካከለኛ ጣዕም
ይኖረዋል። ወተት እና ቡናም ሲቀላቀሉ እንዲሁ ናቸው። እንደ ወተት ያልነጣ ፥ እንደ ቡናም ያልጠቆረ ማዕከላዊ መልክ
ያመጣሉ፤ ጣዕማቸውም ከሁለቱም ወስዶ ማዕከላዊ ይሆናል፤ ስማቸውም፦ በማዕከላዊ ስም፦ «ማኪያቶ» ቢባል እንጂ
በቀደመ ስም ቡና ወይም ወተት ተብለው አይጠሩም።
ቃል
ሥጋ የሆነው እንዲህ አይደለም፤ እንዲህ ቢሆን ኖሮ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክም ፥ የሰው ልጅም ተብሎ አይጠራም
ነበር። ነገር ግን ሰው ከሆነ በኋላ «የሰው ልጅ፤» ተብሎ ተጠርቷል። ማቴ ፲፮፥፲፫። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ
ደግሞ፦ «የእግዚአብሔር ልጅ (የአብ ልጅ ወልድ) እንደመጣ ፥ እውነተኛም የሆነውን እግዚአብሔርን እናውቅ ዘንድ
ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን፤ . . . እርሱም
እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው፤» ብሎታል። ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳። ይኽንን በተመለከተ፦ ቅዱስ ቄርሎስ፦
«መለኮትና ትስብእት እርስ በርሳቸው ሳይቀላቀሉ፦ መለየት በሌለበት ተዋሕዶ ፈጽመው አንድ ሆኑ፤» ብሏል። (ሃይ ፡
አበው ፸፫ ፥፴)።
፯፦ ቃል ሥጋ የሆነው ያለ ትድምርት ነው፤
ትድምርት
ማለት፦ መደረብ ፥ መደመር ማለት ነው። ይህም እንደ ልብስ ፥ እንደ እንጀራ ነው። ልብስ ቢደርቡት ይደረባል ፥
ቢነጥሉት ይነጠላል፤ እንጀራም ቢደርቡት ይደረባል ፥ ቢነጥሉት ይነጠላል። ቃል ሥጋ የሆነው እንዲህ፦ በመደረብ ወይም
በመደመር አይደለም። መለኮት፦ ከሥጋ ተጠግቶ ፥ ወይም ተደርቦ፥ የኖረ፦ በኋላም ተለይቶ የሄደ አይደለም። ቅዱስ
ቄርሎስ ፦ «ሥጋንም ለእርሱ ብቻ ገንዘብ አደረገ፤ ልብስ ከአካል እንዲለይ መለኮትን ከትስብእት አንለየውም፤
በተዋሕዶ ጸንቶ ይኖራል እንጂ፤ እግዚአብሔር እንደሆነ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደሆነ አውቀነዋል።» ብሏል። (ሃይ ፡
አበው ፸፪፥፴)። በተጨማሪም፦ «መለኮትና ትስብእት አንዱ ከአንዱ ጋር በኅብረት የሚኖሩ አይደለም፤ አንዱ በአንዱ
አላደረም፤ መለኮትና ትስብእት በባሕርይም በአካልም አንድ ናቸው እንጂ። ሰው የሆነ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ በዚህ
አንቀጽ ከሥጋ ጋር መዋሓዱን የምናገርለት፤ መለኮትን በመዋሓድም አምላክ የሆነው ሰው ነው፤» በማለት ተናግሯል።
(ሃይ፡ አበው ፷፩ ፥ ፳፩) ፡
፰፦ ቃል ሥጋ የሆነው ያለ ቡዓዴ ነው ፤
ቡዓዴ
ማለት፦ መለየት ፥ አለያየት ፥ ልዩነት ፥ ማለት ነው። ለምሳሌ፦ ሁለት የተለያዩ ነገሮችን ፦ (ብረትንና
እንጨትን)፦ በብሎን ማያያዝ ፥ መልሶም መለያየት ይቻላል። የቃል ሥጋ መሆን እንዲህ አይደለም። የአንጾኪያ ሊቀ
ጳጳስ አባ ዮሐንስ፦ «ይህም ወልድ ዋሕድ ፥ እግዚአብሔር ቃልን ፦ ከወለደችው ከእመቤታችን ከንጽሕት ከቅድስት
ድንግል ማርያም የተገኘ ነው፤ ግድ ሰው ሁን ፥ ያለው ሳይኖር፦ ከእርሷ በፈቃዱ ሥጋን ነሣ፤ ለመለኮት ለትስብእት
እንደሚገባ ያለመከፈል፦ (በተዋሕዶ) የአምላክነትን ፥ የሰውነትን ሥራ ሠራ፤ እንደ ሰው አነጋገር ይናገራል፤ አምላክ
እንደመሆኑ ሙት ያስነሣል፤ ድውይ ይፈውሳል፤ መከራም ይቀበላል፤ ነገር ግን፦ ከማይነገርና ከማይመረመር ተዋሕዶ
በኋላ፦ አምላካዊነት ባሕርይ ፥ ከሰብአዊት ባሕርይ ተለይታ አይደለም፤ አነጋገሩን ፥ ሥራውን ፥ መከራውን ፥ ይህ፦
ለመለኮት ይገባል፤ ይህ፦ ለትስብእት ይገባል ፥ እያልን በየራሳቸው አንለይ፤ አንድ ባሕርይ ፥ አንድ አካል ፥ አንድ
ገጽ በመሆን (በተዋሕዶ) ሠራው እንበል እንጂ፤» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፻፲፫ ፥፲፬)።
፱፦ ቃል ሥጋ የሆነው በኅድረት አይደለም፤
ከላይ
እንደገለጥነው፦ ቅዱስ ዮሐንስ፦ አስቀድሞ ፦ «ሆነ፤» ያለው፦ «አደረ፤» የሚለውን ይዘው ኅድረት እንዳይሉበት
ነው። «ኅድረት፤» ማለት፦ ማደር ማለት ነው። ይኸውም፦ እንደ ውኃና ማድጋ ፥ እንደ ዳዊትና ማኅደር ፥ እንደ
ሰይፍና ሰገባ ነው። እነዚህ አንደኛው አካል በሌለኛው አካል እንደሚቀመጡ፦ (ኀዳሪና ማኅደር) ፦ እንደሆኑ ፥
መለኰትም ፦ ሥጋን ማኅደር አድርጎ የተቀመጠ አይደለም። ይኽንን በተመለከተ፦ ቅዱስ ቄርሎስ፦ «እርሱ አንድ ወልድ
አንድ ጌታ ነው፤ ቃል በዕሩቅ ብእሲ አላደረም ፥ በክብሩም አላስተካከለውም፤ ብዙ ሰዎች በድንቊርና አስበው
እንደተናገሩት በኅድረት የልጅነትን ክብርና አምላክነትንም አልሰጠውም ፤ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ፥ ከእግዚአብሔር
የተገኘ የእግዚአብሔር ቃል፦ እርሱ ነፍስን ሥጋን ተዋሕዶ ሰው ሆነ እንጂ።» ብሏል። (ሃይ ፡አበው ፸፪ ፥ ፲፩)።
ዳግመኛም፦ «እግዚአብሔር ቃልስ ዓለምን ሳይፈጥር አስቀድሞ የነበረ ነው፤ የተዋሓደውን ሥጋም ከሰው ባሕርይ ፈጠረው፤
ከተዋሕዶ በኋላ ለክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አሉት ብሎ የተናገረ ከእነርሱ (ከአባቶቻችን) አንድ ሰው እንኳ አለን?
ወይስ በእግዚአብሔር ፈቃድ በድንግል ማኅፀን ፍጹም ሕፃን ተፈጠረ ፥ ከዚህ በኋላ ከማርያም በተገኘው በዚያ ሕፃን
እግዚአብሔር ቃል አደረበት ብሎ የተናገረ አለን? ወይስ ከተዋሕዶ በኋላ ለአንድ ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አሉት
ተብሎ ሊነገር በውኑ ይገባልን?» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፸፭ ፥፲፩)።
ተጨማሪ ማስረጃ ከሊቃውንት፤
ቅዱስ
አቡሊድስ፦ «ፈጣሪ እርሱ በሰው ያደረ አይደለም፤ በነቢያት በሐዋርያት አድሮ ሥራ የሠራ፦ ፍጹም አምላክ በሥጋ
ተገለጠ እንጂ። ሰውም ቢሆን በመለኮቱ ፍጹም ነው፤ . . . ከአብ ዘንድ ብቻውን የተወለደ ፥ ከድንግልም አንድ
ብቻውን የተወለደ እርሱ አንድ ነው እንጂ። በተዋሕዶ ሰው የሆነ የባሕርይ አምላክ ነው።» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፴፱
፥፲፩)። ዳግመኛም፦ «መቀላቀል ፥ ይህንንም የመሰለ ሌላ ነገር የለበትም እንላለን፤ ተዋሕዶው እውነተኛ ስለሆነ
ተቀላቀለ ማለት አይስማማውምና። የእግዚአብሔር ልጅ ወልድ ዋሕድ ነፍስን ሥጋን ነሥቶ ሰው ሆነ ባልን ጊዜም፦
ስለዚህም ነገር ቢሆን እነዚያ( መናፍቃን) እንደሚያምኑ መቀላቀል የለበትም፤ የቃል ባሕርይ የሥጋን ባሕርይ ወደ
መሆን ፥የሥጋ ባሕርይም የቃልን ባሕርይ ወደ መሆን አልተለወጠም፤ ሁለቱ ባሕርያት ያለመለወጥ ያለመቀላቀል ጸንተው
ይኖራሉ እንጂ።» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፵፭ ፥፭)።
ቅዱስ
ፊልክስ፦ «ክርስቶስ በሐዲስ ግብር (በኅድረት በውላጤ) አልመሰለንም፤ በማይመረመር ተዋሕዶ ባሕርያችንን ባሕርይ
አድርጎ ነው እንጂ። ብሏል። ቅዱስ ጎርጎርዮስም፦ «የእግዚአብሔር ቃል፦ ድንግል ማርያም በወለደችው ሰው እንዳደረ
የሚናገሩትን፦ እኔ ልበ ሰፊ በመሆን፦ የትስብእትና የመለኮት ሁለቱ ባሕርያት በተዋሕዶ አንድ የሆኑ አይደለምን? ብዬ
እጠይቃቸዋለሁ፤ በአካል ፍጹም የሚሆን የቃል ባሕርይ፦ የምታውቅና የምትናገር ነፍስ ያለችውም የሥጋን ባሕርይ
ተዋሕዷልና ፥ በሥጋም ከድንግል ተወልዷልና። ሰው ሆኖ የታየ እርሱም በፍጡራን ልቡና ከመመርመር የራቀ ነው፤
ከመለኮትና ከትስብእት ከሁለቱ ባሕርያት ድንቅ በሚያሰኝ ምሥጢር አንድ ክርስቶስ ሆነ፤ ቅን ልቡና ያላቸው ሰዎች ግን
አግዚአብሔር በሰው እንዳደረ አይናገሩም ፥ ተዋሕዶ አዲስ ሥራ ነውና ፥ ድንቅ ምሥጢርም ነውና። . . . እኛ
ግን እግዚአብሔር ቃልን ከነፍስ ከሥጋ አንለየውም፤ ከዓለም ሁሉ አስቀድሞ የነበረ፦ ቀዳማዊ ወልድ ዋሕድ መዋሓዱን
እናምናለን እንጂ፤ በመዋሓዱም ከሥጋው ጋር አልተቀላቀለም፤ እኛን ለማዳን ነፍስ ልቡና ያለው ሥጋን ከእኛ ባሕርይ
ነሥቶ ተዋሐደ እንጂ።» ብሏል።(ሃይ፡ አበው ፷፮፥፪ ፣፲፮)።
ቅዱስ
ዮሐንስ አፈወርቅ፦ «ነገር ግን እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅ አንድ እንደሆነ ብንናገር ፥ ወዲህም ከእኛ ባሕርይ
የተገኘ ሥጋ ያለመለየት በማይመረመር ተዋሕዶ ከቃል ጋር አንድ መሆኑን እኛ እናውቃለን፤ ሥጋ የመለኮትን ባሕርይ
እንዳልለወጠ ፥ መለኮትም እንዲሁ የሥጋን ባሕርይ አልለወጠም፤ እርሱ ወልድ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው፤»
ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፷፯ ፥፴፩)። ቅዱስ አትናቴዎስም፦ «እርሱ ሰው የሆነ አምላክ ነው፤ ስለዚህም መለኮት ሥጋን
ወደ መሆን ፥ ሥጋም መለኮትን ወደ መሆን አይለወጥም፤ እርሱ ከመለወጥ ከመለዋወጥ ሁሉ የራቀ ነው፤ ከተዋሕዶ በኋላ
ግን ፈጽሞ መለየት የለበትም፤ ሰው የሆነ ቃል፦ አንድ አካል ፥አንድ ባሕርይ መሆኑ እውነተኛ ተዋሕዶው የጸና ነው፤
እግዚአብሔር ያደረባቸው አበው እንዳስተማሩን፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፻፮፥፲፫)። ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ደግሞ፦ «አድሮ
እንደተናገረባቸው እንደ ነቢያት ሁሉ አይደለም፥ ፍጹም ሰው ሆነ እንጂ። ቃል ሥጋ ሆነ፤ አልተለወጠም ፤ መለኮቱን
ሰው ወደ መሆን አልለወጠውም ፤ ከመለኮት ጋር ጽኑዕ አንድነቱን በተዋሕዶ አደረገ እንጂ።» ብሏል። (ሃይ፡ አበው
፶፯ ፥፳፰)።
ቃል ሥጋ የሆነው በተዋሕዶ ነው፤ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፱
ካለፈው የቀጠለ፦
አካላዊ
ቃል እግዚአብሔር ሰው የሆነው በተዋሕዶ ነው። ተዋሕዶውም እንደ ነፍስና እንደ ሥጋ ተዋሕዶ ነው። ነፍስ ረቂቅ ናት
፥ ሥጋ ደግሞ ግዙፍ ነው፤ ነፍስ ረቂቅነቷን ሳትለቅ ፥ ሥጋም ግዝፈቱን ሳይተው በተዋሕዶ ጸንተው ይኖራሉ።
በመሆኑም አንድ ሰው እንጂ ሁለት አይባሉም።
ቅዱስ
ቄርሎስ፦ የተዋሕዶን ነገር በብረትና በእሳት እየመሰለ አስተምሯል። «በእግዚአብሔር ቃል፦ በረቂቅ ባሕርይ የሆነውን
ተዋሕዶ አንካድ ፤ ብረት ከእሳት በተዋሐደ ጊዜ፦ ከእሳትም በመዋሐዱ የእሳትን ባሕርይ ገንዘብ ያደርጋል፤ (ማቃጣል
መፋጀት ይጀምራል)፤ ብረት በመዶሻ በሚመታበት ጊዜ፦ ከእሳቱ ጋር በአንድነት(በተዋሕዶ) ይመታል፤ ነገር ግን
ከመዶሻው የተነሣ የእሳት ባሕርይ በምንም በምን አይጐዳም፤ ሰው የሆነ አምላክ ቃልም በመለኮቱ ሕማም ሳይኖርበት፦
በሥጋ እንደታመመ እናስተውል፤» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፸፫ ፥፲፪)።
ቅዱስ
አትናቴዎስ፦ የተዋሕዶን ምሥጢር ሲያስረዳ፦ «አሁንም በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ እንደሆነ ሰምተህ ዕወቅ፤ አምላክ
ብቻ ከሆነማ እንደምን በታመመ ነበር? ወይስ እንደምን በሰቀሉት ነበር? ወይስ እንደምን በሞተ ነበር? ይህ ሥራ፦
(ሕማምና ሞት) ከእግዚአብሔር የራቀ ነውና፤ ዘዳ ፴፪፥፵። ሰው ብቻ ከሆነ በታመመ በሞተ ጊዜ ሞትን እንደምን ድል
ይነሣው ነበር? ይህ ከሰው ኃይል በላይ ነውና። ፩ኛ ቆሮ ፭ ፥፲፫ ፣ ዕብ ፭፥፩-፬።» ብሏል። ስለ እመቤታችን ስለ
ቅድስት ድንግል ማርያም ሲናገር ደግሞ፦ «ድንግል ወንድ ሳታወቅ ሊዋሐደው በፈጠረው ሥጋ የፀነሰችውን ወለደች፤ ያለ
ኃጢአት ያለ ምጥ ወለደችው፤ የአራስነት ግብር አላገኛትም፤ ያለ ድካም ያለ መታከት አሳደገችው፤ ያለ ድካም
አጠባችው፤ ለሥጋ በሚገባ ሕግ ምን አበላዋለሁ? ምን አጠጣዋለሁ? ምን አለብሰዋለሁ? ሳትል አሳደገችው፤» ብሏል።
(ሃይ ፡ አበው ፳፯ ፥፮ ፣ ፳፰፥፲፱)። በተጨማሪም፦ «ዳግመኛም በክህደታቸው አስበው፦ ማርያም የወለደችው፦ ገዥ ፥
ፈጣሪ እንዳይደለ የሚናገሩ የመናፍቃን ልጆች ፈጽመው ምላሽ ይጡ፤ እግዚአብሔር ቃል ሥጋን ካልተዋሐደ ከእመቤታችን
ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ እንደምን አማኑኤል ተባለ? ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋ ፥
ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ ማለት ነው። ኢሳ ፯፥፲፬ ፣ ማቴ ፩፥፲፰-፳፭። እንኪያስ
ቃል ሥጋን ካልተዋሐደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ በእውነት ለዘለዓለሙ የከበረ አምላክ
ከሁሉ በላይ የሚሆን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ በሥጋ ታመመ ብሎ እንደምን ጻፈ? ሮሜ ፭፥፯-፲፪ ፣
፱፥፩-፭፤» ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፴፭፥፲፱)።
የቅዱስ
ባስልዮስ ወንድም ቅዱስ ጎርጎርዮስ፦ «ትስብእትን ከመለኮት ልዩ ነው ፥ አትበሉ፤ ከተዋሕዶ በኋላ አይለይምና፥
አይቀላቀልምና፤ መለኮትን ከተዋሐደው ከትስብእት ልዩ ነው ፥ አትበሉ፤ በርሱ ያለውን ተዋሕዶውን እመኑ እንጂ፤»
ብሏል። (ሃይ ፡ አበው ፴፭ ፥፲፱)። በተጨማሪም፦ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈውን መልእክት
በተርጐመበት አንቀጽ፦ «እግዚአብሔር አብን በመልክ የሚመስለው በባሕርይ የሚተካከለው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው
የሆነበትን ሥራ በልቡናችሁ ዕወቁ፤ ሽቶ(ፈልጎ) ቀምቶ ከእግዚአብሔር ጋር የተካከለ አይደለም፤ ራሱን አዋርዶ ሰው
ኹኖ የተገዥን ባሕርይ ተዋሕዶ ነው እንጂ። ፊል ፪፥፭-፰። ሥጋን ከመዋሐድ የበለጠ በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ድህነት
አለ? ነገር ግን እርሱ ነገሥታትን ፥ መኳንንትን ፥የሚገዛ ሲሆን፦ እኛን ወደ መምሰል በመጣ ጊዜ፥ የተገዥን
ባሕርይ በተዋሐደ ጊዜ ፥ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አላነሰም። ምድርን የፈጠረ እርሱን በትውልድ እንበልጣለን የሚሉ ሐና
ቀያፋ ዘበቱበት፤ ፍጥረትን ሁሉ የሚገዛ እርሱ የሚያርፍበት ቦታ አላገኘም፤ በሥጋ በተወለደ ጊዜ ላሞች በሚያድሩበት
በረት አስተኙት እንጂ። መዝ ፳፫፥፩፤፺፪፥፩፤፺፭፥፲፫፤ ማቴ ፰፥፳፣ ሉቃ ፪፥፩-፯። የማይለወጥ ንጹሕ ቃል
የሚለወጥ የሰውን ባሕርይ ተዋሐደ፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፴፭፥፳፱-፴፫)።
ቅዱስ
አብሊድስ፦ «ዳግመኛም ቃልን ከሥጋ አዋሕደን እንሰግድለታለን፤ . . . ፍጡር ሥጋን ፈጣሪ እንደተዋሐደው
እናምናለን፤ ፈጣሪ ከፍጡር በተዋሐደ ጊዜ ፦ አንድ አካል በመሆን የጸና አንድ ባሕርይ ሆነ፤ ሁለት አካል ሁለት
ባሕርይ አይደለም፤ የመለኮትንና የትስብእትን ተዋሕዶ እናውቃለን፤ ባሕርያችን ሁለት (ነፍስና ሥጋ) ሲሆን አንድ
ይሆናል፤ አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን ያድጋል፤ አንድ ሰውም ይባላል፤ ዘፍ ፩፥፳፮፣ ዕብ ፪፥፲፬።» ብሏል።
(ሃይ፡ አበው ፴፱፥፳፩-፳፬) ። በተጨማሪም፦ «ከአብ ጋር አንድ ነው፥ እንዳልነው ሁሉ ሥጋን በመዋሐድ ከሰው ጋር
አንድ ነው፥ እንላለን፤ መለኮትም ለሰው የሚገባ ስምን ገንዘብ ያደርጋል፤ ሥጋን በመዋሐድ ከእኛ ባሕርይ ጋር አንድ
ስለሆነ ከእርሱም ጋር አንድ ስለአደረገው። ኢሳ ፱፥፮ ፣ ማቴ ፩፥፳፪ ፣ ፊል ፪፥፭። ከተዋሐደው ከሥጋ ባሕርይ
ምንም አልተለወጠም፤ አንድ መሆንም ሰውን ወድዶ ስለ መዋሓዱ የመለኮት ባሕርይ እንዳልተለወጠ መጠን ፥ ከእርሱ ጋር
አንድ ከሚሆን ከእግዚአብሔር ጋር ገንዘቡ የሚሆን መተካከል ያለበት ስም ነው። ማቴ ፳፰፥፲፱ ፣ ሉቃ ፩፥፴፪ ፣ ዮሐ
፩፥፩ ፤ ፲፥፴ ፣ ፩ኛ ቆሮ ፰፥፮፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፵፥፲፮)።
ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ደግሞ፦ «በዘመኑ ሁሉ
የማይለያዩትን የአምላክነትን የሰውነትን ግብራት በተዋሕዶ አጸና፤ ክርስቶስ በመለኮቱ ያይደለ በሥጋ አንደታመመ
ተናገረ፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደተናገረ መለኮት ከትስብእት አልተለየም፤ መለኮትና ትስብእት አንድ ባሕርይ
በመሆን ተዋሓዱ እንጂ። ፩ኛ ጴጥ ፫፥፲፰ ፣፬-፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ፦ መለኮትንና ትስብእትን አንድ አድርጎ
እርሱን የክብር ባለቤትን ባልሰቀሉትም ነበር ብሎ ተናገረ፤ ፩ኛ ቆሮ ፪፥፰።» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፶፯ ፥ ፴፮)።
ሊቁ
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም፦ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ዕብራውያን ሰዎች የጻፈውን መልእክት በተረጎመበት እንቀጽ፦
«የተዋሐደውን ሥጋ ከመላእክት ባሕርይ የነሣው አይደለም ፥ ከአብርሃም ባሕርይ ነሣው እንጂ። ዕብ ፪ ፥ ፲፯። ለዚህ
ታላቅ ፍቅር አንክሮ ይገባል፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለሰው ወገን ለተደረገ ለማይመረመር ለዚህ ፍቅር አንክሮ
ይገባል፤ ይህ ለመላእክት ያላደረገው ነው። የተደረገውን አስተውል፤ እግዚአብሔር ከእኛ ባሕርይ የተዋሐደው ተዋሕዶ
ጥቂት ክብር አይምሰልህ፤ ይህንን ለመላእክት አላደረገውምና ፥ የመላእክት ባሕርይ አልተዋሐደችውምና ፥ የተዋሐደችው
የእኛ ባሕርይ ናት እንጂ። ባሕርያችንን ተዋሕዷል እንጂ። ከባሕርያችን ከፍሎ ተዋሐደ ለምን አላለም? ወዳጁ
እንደኮበለለ እስኪያገኘውም ድረስ እንደሄደና እንዳገኘው ሰው የእኛ ባሕርይ እንደዚህ ከእግዚአብሔር ተለይታ ነበርና፤
ከእርሱም ፈጽማ ርቃ ነበርና፤ ሥጋ በመሆን ገንዘብ እስኪያደርጋት ድረስ ፈጥኖ ፈለጋት ፤ እርሷም ተዋሐደችው፤
ይህንንም ተዋሕዶ እኛን በመውደድ እንዳደረገው የታወቀ ነው። መኃ ፫፥፬ ፣ ማቴ ፲፰፥፲፪ -፲፬፤» ብሏል። (ሃይ፡
አበው ፷፫፥፪-፭)። በተጨማሪም፦ «ተዋሕዶንም አስረዳለሁ፤ እግዚአብሔር ቃል በአካሉ ፍጹም የሚሆን ነፍስ ፣ ዕውቀት
ያለው ሥጋን ከእኛ ባሕርይ ነሥቷልና፤ እርሱንም ተዋሕዷልና፤ ስለዚህም ነፍስን ሥጋን ተዋሕዶ ሰው የሆነ
እግዚአብሔር ቃል አንድ አካል አንድ ባሕርይ እንደሆነ እንናገራለን፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፷፯፥፴)።
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም፦ ጌታን፦ በድንግልና መውለዷ በራሱ ምሥጢረ ተዋሕዶን ያስተምረናል። ይኸውም፦ በመንፈስ
ቅዱስ ግብር በድንግልና የጸነሰችውን አምላክ በድንግልና የወለደችው፦ መለኮት ከእርሷ የነሣውን ሥጋና ነፍስ በመዋሐዱ
ነው። ምክንያቱም፦ በተዋሕዶ የመለኮት ገንዘብ ለሥጋ፥ የሥጋም ገንዘብ ለመለኮት ሆኗልና። የመላእክት አለቃ ቅዱስ
ገብርኤል፦ እመቤታችንን ባበሠራት ጊዜ፦ «ከአንቺ የሚወለደው የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤ (የእግዚአብሔር አብ ልጅ፦
እግዚአብሔር ወልድ ነው፥ ከሦሥቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ነው) ፤ ማለቱም ለምሥጢረ ተዋሕዶ ምስክር ነው። ሉቃ
፩፥፴፭። ምክንያቱም መለኮት በማኅፀን ነፍስን እና ሥጋን ባይዋሐድ ኖሮ ከእመቤታችን የሚወለደው የእግዚአብሔር ልጅ፥
ከሦስቱ ቅዱስ(ከሥላሴ) አንዱ ቅዱስ ነው ፥ አይባልም ነበር።
ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፦ በመዋዕለ ሥጋዌው ያደረጋቸው ተአምራትም ምሥጢረ ተዋሕዶን የሚያሳዩ
ናቸው። ለምሳሌ፦ ሁለት ማየት የተሳናቸውን ሰዎች በእጆቹ በዳሰሳቸው ጊዜ፦ ተፈውሰዋል። ይህም ሊሆን የቻለው መለኮት
በተዋሐዶ ከሥጋ ጋር ስለነበረ ነው። ማቴ ፱፥፳፯-፴፩። ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ፦ ዓይነ ስውር የነበረውንም ብላቴና
በምራቁ አፈሩን ለውሶ በዚያ ፈውሶታል። ምራቅ የሥጋ ነው፤ ነገር ግን መለኮት ሥጋን ስለተዋሐደው ፥ ከተዋሕዶ በፊት የሥጋ ብቻ የነበረ ምራቅ የብላቴናውን ዓይን አብርቶለታል። ዮሐ ፱፥፩-፲፪።
ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው፦ መግነዝ ሳይፈታለት ፥ መቃብር ሳይከፈትለት
ነው። ሥጋ በራሱ መቃብር ሳይከፈትለት መውጣት አይችልም ። መለኮት ግን የሚያግደው የለም። በመሆኑም፦ መለኮታዊ
አካልና ባሕርይ ፥ ከሥጋ አካልና ባሕርይ ጋር ተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆኑ፦ ልዩነት ሳይኖር መቃብሩ
እንደታተመ ከመቃብር ወጥቷል። ከትንሣኤው በኋላም በሩ ሳይከፈት ደቀመዛሙርቱ ወደነበሩበት ቤት ገብቷል።
ደቀመዛሙርቱ፦ ይህ ምሥጢር ረቅቆባቸው፦ በእርሱ አምሳል ምትሐት የሚያዩ መስሏቸው ነበር። እርሱ ግን፦ « ምን
ያስደነግጣችኋል? በልባችሁስ እንዲህ ያለ ሐሳብ ለምን ይነሣሣል? እጄንና እግሬን እዩ፤ ዳስሱኝም፤ እኔ እንደሆንሁም
ዕወቁ፤ በእኔ እንደምታዩት ለምትሐት አጥንትና ሥጋ የለውምና፤» ብሎ ተዳሰሰላቸው። ይህ የዳሰሱት አካል ነው፥
መዝጊያው ሳይከፈት የገባው። ምክንያቱም መዝጊያና ግድግዳ የማያግደው መለኮት እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶታልና። ማቴ
፳፰፥፩-፲ ፣ ሉቃ ፳፬፥፲፮ ፣ ዮሐ ፳፥፲፱።
ጌታችን፦
በዝግ ቤት ለደቀመዛሙርቱ በተገለጠላቸው ጊዜ ቶማስ አልነበረም። የሆነውን ሁሉ በነገሩት ጊዜ፦ «የችንካሩን ምልክት
በእጁ ካላየሁ ፥ ጣቴንም ወደተቸነከረበት ካልጨመርሁ ፥ እጄንም ወደጎኑ ካላገባሁ አላምንም፤ አላቸው። ከስምንት
ቀን በኋላም በሩ እንደተዘጋ ፥ ቶማስ ባለበት ተገልጦላቸው፦ «ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ »አላቸው። ከዚህም በኋላ
ቶማስን ፦ ጣትህን ወዲህ አምጣና እጆቼን እይ ፤ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ
አትሁን፤» አለው። ቶማስም ፦ ከዳሰሰ በኋላ፦ «ጌታዬ አምላኬም» ብሎ መለሰ። የዳሰሰው አካል፦ እሳተ መለኮት
የተዋሐደው በመሆኑ እጁን ፈጅቶታል። በመሆኑም ቢዳሰስለት፦ «ጌታዬ» ቢፈጀው፦ «አምላኬ» ብሏል። ዮሐ ፳፥፳፰።
ቅዱስ
ዮሐንስ ወንጌላዊም፦ አይታይ አይዳሰስ የነበር መለኮት የሚታይ የሚዳሰስ ሥጋን ተዋሕዶ በሰውነት ( ነፍስንም ጭምር
በመዋሐድ) በመገለጡ፦ «ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውንና በጆሮአችን የሰማነውን ፥ በዓይኖቻችንም
ያየነውን፥ የተመለከትነውንም ፥ እጆቻችንም የዳሰሱትን እንነግራችኋለን። ሕይወት ለእኛ ተገልጻለችና አየናት ፥
ምስክርም ሆንን፤ ለእናንተም ከአብ ዘንድ ያለችውንና ለእኛ የተገለጠችውን የዘለዓለምን ሕይወት እንነግራችኋለን፤»
ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፩።
፲፩፦ አካልና ባሕርይ፤
አካልና
ባሕርይ አይነጣጠሉም፤ አካል ባለበት ባሕርይ አለ፤ ምክንያቱም የባሕርይ መገለጫው አካል ነውና። (ባሕርይ አካልን
አስገኝቶ በአካል ላይ ይገለጣል)። ለምሳሌ፦ እሳት አካልም ባሕርይም አለው፤ አካሉ፦ በእንጨት በከሰል ላይ ይገለጣል
፥ ባሕርዩ ደግሞ፦ መፋጀት ማቃጠል ነው። በመሆኑም፦ የሚፋጀውን ወይም የሚያቃጥለውን የእሳት ባሕርይ፦ ከአካሉ
መነጠል ወይም መለየት አይቻልም። ውኃም፦ እንዲሁ፦ አካልም ባሕርይም አለው። አካሉ፦ በማድጋ ተቀድቶ ፥ በቀላያት
ተዘርግቶ ቦታ በመያዙ ይታወቃል፤ ባሕርዩ ደግሞ ርጥበት ነው፤ ይህንንም ርጡብ የሆነ የውኃ ባሕርይ ከውኃ አካል
መለየት አይቻልም። አካሉ ባለበት ቦታ ሁሉ ባሕርዩ አለ።
፲፩፥፩፦ ሥጋዊ አካልና ባሕርይ፤
ከራስ
ጠጉር እስከ እግር ጥፍር ፥ በአጥንት፥ በጅማት ፥ በሥጋ ፥ በቁርበት ተያይዞና ተሸፍኖ ያለው በአንድነት አካል
ይባላል። ፍጹም ገጽ ፥ ፍጹም መለክ ያለው ነው፤ ራሱን የቻለ ፥ ለራሱ የበቃ እኔ የሚል ፥ የባሕርይ የግብር እና
የስም ባለቤት ነው። የሥጋ አካል፦ ግዙፍ ፥ ውሱን፥ የሚዳሰስና የሚጨበጥ ነው፤ የሥጋ ባሕርይ ደግሞ፦ መራብ ፥
መጠማት ፥ መድካም ፥ ማንቀላፋት ፥ መሞት ነው።
፲፩፥፪፦ መለኮታዊ አካል እና ባሕርይ፤
መለኮታዊ አካል፦ ረቂቅ፥ የማይጨበጥ ፥ የማይዳሰስ፥ እሳታዊና ምሉዕ ነው።
- «ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፤ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፥ የራሱም ጠጉር እንደ ነጭ ሱፍ ነበረ፤ ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበረ፤» ዳን ፯፥፱።
- «ራሱ ምዝምዝ ወርቅ ነው ፥ ቈንዳላው የተዝረፈረፈ ነው፤» መኃ ፭፥፲፩።
- «የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃኑ ፥ ጆሮቹም ወደ ልመናቸው ናቸውና፤» መዝ ፴፫፥፲፭።
- «ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራል፤» መዝ ፲፥፬።
- «እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም፤» መዝ ፻፲፰፥፸፫።
- «እግዚአብሔር የኖኅን የመሥዋዕቱን መዓዛ አሸተተ፤» ዘፍ ፰፥፳፩።
- «ንስር ጫጩቶቹን በክንፎቹ በታች እንደሚሰበስብ ፥ በጎኑም እንደሚያቅፍ፥ በክንፎቹ አዘላቸው፤ በደረቱም ተሸከማቸው።» ዘዳ ፴፪፥፲፩።
- «ወገቡን በጽድቅ ይታጠቃል፤ እውነትንም በጎኑ ይጎናጸፋል።» ኢሳ ፲፩፥፭።
- «የጌታችን እግሮቹ በሚቆሙበት ቦታ እንሰግዳለን፤» ፻፴፩፥፯።
- «ሰማይ የእግዚአብሔር መቀመጫ ነውና፤» ማቴ ፭፥፴፫።
- «እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮአልና ፥ ሰማይ ስማ ፤ ምድርም አድምጪ፤» ኢሳ ፩፥፪ ።
- «በእግዚአብሔር ቃል ሰማያት ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ፤» መዝ ፴፪፥፮።
መለኮታዊ
ባሕርይ ደግሞ፦ ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ፥ እስከ የሌለው ዘለዓለማዊ ነው። ፊተኛውና ኋለኛ፥ መጀመሪያና መጨረሻ ፥
እርሱ ነው ፤ ፈጣሪ ፥ ሁሉን ቻይ ነው፤ የሚሳነው ነገር የለም፤ ሕያው ነው፤ ምሉዕ በኲለሄ ነው፤ የማይለወጥ ፥
የማይታመም ፥ የማይራብ ፥ የማይጠማ ፥ የማይደክም ፥ የማይሞት ነው።
- «አልፋና ዖሜጋ ፥ ቀዳማዊና ደኃራዊ ፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ ፤» ራእ ፥፳፪፥፲፫።
- «አትፍራ ፥ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ፤ ሞቼም ነበረሁ፤ እነሆም፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ሕያው ነኝ፤» ራእ ፩፥፲፯።
- «ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የለም፤» ዮሐ ፩፥፫።
- «ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና፤ » ሉቃ ፩፥፴፯።
- «እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤» ሚል ፫፥፮።
- «አቤቱ
፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና፤ ታላቅነትና ኃይል ፥ ክብርም ፥ ድልና ጽንዕ የአንተ ነው፤. .
አቤቱ ፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ የሥልጣን ሁሉ ጌታ ነህ፤ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ ኃያል ነህ፤» ፩ኛ ዜና
፳፱፥፲፩።
- «ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ ፥ አንተ በዚያ አለህ፤ ወደ ጥልቁም ብወርድ ፥ አንተ በዚያ አለህ፤» መዝ ፻፴፰፥፯።
- «ከዘላለም እስከ ዘለዓለም ድረስ መቼም መች አንተ ነህ» መዝ ፹፱፥፪።
፲፪፦ አንድ አካል ፥ አንድ ባሕርይ፤
ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በተዋሕዶ ከሁለት አካል፦ አንድ አካል ፥ ከሁለት ባሕርይ፦ አንድ
ባሕርይ ሆኗል። ይህም ማለት፦ የሥጋ አካል እና የመለኮት አካል ተዋሕደው አንድ ሲሆኑ ፥ የሥጋ ባሕርይና የመለኮት
ባሕርይም ተዋሕደው አንድ ሆነዋል። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ አንድ አካል እና አንድ ባሕርይ ነው።
ከተዋሕዶ በኋላ ሁለትነት የለም።
ቅዱስ
አቡሊዲስ ወደ ቅዱስ ዲዮናስዮስ በላከው መልእክቱ፦ «ወንጌላዊ ዮሐንስም ቃል ሥጋ እንደሆነ በተናገረ ጊዜ፦ አንድ
ገዥ ነው አለ፤ ዮሐ ፩፥፲፬፣፩ኛ ቆሮ ፰፥፮። ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ፥ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድ
ወልድ ተብሎ ከተጠራ ፥ ሁሉ የተፈጠረበት እርሱ አንደ አካል አንድ ባሕርይ ነው፤ ወደ ሁለትነት መከፈል የለበትም።
ለሥጋውም ከመለኮቱ ወደ አንድ ወገን የተለየ ባሕርይ የለውም። ሰው፦ አንድ አካል አንድ ባሕርይ እንደሆነ ሁሉ፥
ሰው የሆነ የባሕርይ ገዥ ክርስቶስም፦ እንዲሁ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው እንጂ፤ ፊል ፪፥፭-፰። አንዱን
ክርስቶስ አንድ እንደሆነ ካላወቁትስ፦ እነሆ ፥ ዳግመኛ አንዱን ሰው ወደ ብዙ ወገን ሊከፋፍሉት ይገባቸዋል፤ ብዙ
ባሕርያትም እንዳሉት ሊናገሩ ይገባል። ምክንያቱም ከብዙ ወገን የተጠራቀመ ነውና፤ ከአጥንት ፥ ከጅማት ፥ ከአሥራው ፥
ከሥጋ ፥ ከቁርበት፥ከጥፍር ፥ ከጠጉር ፥ ከደም ፥ከነፍስ የተጠራቀመ ነውና፤ እነዚህም ሁሉ እርስ በርሳቸው ልዩ
ልዩ ናቸው። ነገር ግን በእውነት አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው፤ እንዲሁም መለኮት ከትብስእት አንድ አካል አንድ
ባሕርይ ነው፤ ወደ ሁለት አካል ፥ ወደ ሁለት ባሕርይ አይከፈልም። ዮሐ ፫፥፲፫ ፣ ሉቃ ፩፥፴፪። . . . ያለዚያ
ከሰማይ የወረደ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል እንጂ የሰው ልጅ አይባልም፤ ከድንግል ማርያም የተወለደውም የሰው ልጅ
ይባላል እንጂ የእግዚአብሔር ልጅ አይባልም። . . . ለእኛ ግን ከሰማይ በወረደ ፥ ከድንግል በተወለደ፥ በአንድ
እግዚአብሔር እናምን ዘንድ ፥ እግዚአብሔር ያጻፋቸው መጻሕፍት ያስተምሩናል። ፩ኛ ቆሮ ፰፥፮ ፣ ገላ ፬፥፬ ፣ ዮሐ
፭፥፳፯ ፣ ሉቃ ፩፥፴፪። . . . ሁለት ባሕርይ ብለው የሚያምኑ ለአንዱ እንዲሰግዱ ፥ ለአንዱ እንዳይሰግዱ፤
በመለኮት ባሕርይ እንዲጠመቁ ፥ በሥጋ ባሕርይ እንዳይጠመቁ ግድ
ይሆንባቸዋል። እምነታችን በጌታችን ሞት እንደምንከብር ከሆነ፦ የሚታመም ትስብእትና የማይታመም መለኮት አንድ
ባሕርይ ይሆናል። መክበራችን እንዲህ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ በጌታችን ሞትም ፍጹማን እንሆናለን፤» ብሏል።
(ሃይ፡ አበው ፴፱፥፮-፲፯)።
ከዚህም
በተጨማሪ፦ «እንዲሁም ከእግዚአብሔር አብ ጋር በአምላክነት ክብር አንድ ነው እንላለን፤ ሥጋም ይህን አንድ ስምን
(ክርስቶስን) ገንዘብ ያደርጋል፤ እግዚአብሔር አብን፦ በመልክ ከሚመስለው ፥ በባሕርይ ከሚተካከለው ከቃል ጋር አንድ
አካል አንድ ባሕርይ ነውና። ዮሐ ፩፥፲፬ ፣ ፲፰፤ ከአብ ጋር አንድ ነው፥ እንዳልነው፦ ሥጋን በመዋሐድ ከሰው ጋር
አንድ ነው፥ እንላለን፤ መለኮትም ለሰው የሚገባ ስምን ገንዘብ ያደርጋል፤ ሥጋን በመዋሐድ ከእኛ ባሕርይ ጋር አንድ
ስለሆነ ከእርሱም ጋር አንድ ስለአደረገው፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፵፥፲፭-፲፮)። ቅዱስ ኤራቅሊስም፦
«እግዚአብሔር ያለመለወጥ እንደምን ሰው እንደሆነ ፥ቃል ከፈጠረው ሥጋ ጋር ያለ መቀላቀል እንደምን አንድ አካል
አንድ ባሕርይ እንደ ሆነ ፥ እግዚአብሔር የሥጋን ባሕርይ፦ ያለዘር፥ ያለሩካቤ ፥ እንደምን እንደተዋሐደ መላልሰህ
በልቡናህ ብትመርምር፦ ይህ ድንቅ ምሥጢር የጎላ የተረዳ ሆኖ ታገኘዋለህ፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፵፱፥፳፭)።
የአንጾኪያው
ሊቀ ጳጳሳት የከበረ ሰማዕት አግናጥዮስም፦ ጌታ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የመሆኑን ነገር ሲናገር፦
«ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት ተወለደ፤ በእውነት አደገ ፥ በእውነት በላ ፥ ጠጣ ፥ በእውነት ተሰቀለ፥
በእውነት ታመመ ፥ ሞተ ፥ ተቀበረ ፥ ከሙታንም ተለይቶ ተነሣ። አመክ. ፮፥፲፪፣ ማቴ ፩፥፲፰-፳፭ ፣፲፩፥፲፪-፳ ፣
ሉቃ ፪፥፵-፶፪፣፩ኛ ቆሮ ፲፭፥፫። ይህንን እንዲህ ያመነ ብፁዕ ነው፤ ይህንን የካደ ግን እኛ ተስፋ ከምናደርጋት
ከተመሰገነች ሕይወት የተለየ ነው። ፩ኛ ዮሐ ፪፥፳፭። ወልድ ዋሕድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚከፍሉት፣ አንድ
አካል አንድ ባሕርይ ከሆነ በኋላ፦ ሁሉት አካል ሁለት ባሕርይ የሚያደርጉት፦ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፥ ስለ
ስድብ ፥ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለማድረግህ ነው እንጂ ብለው በአመፃቸው ከሚናገሩ አምላክን ከሰቀሉ
ከአይሁድ ጋር ይቆጠራሉ። ዮሐ ፲፥፴፪ ፣ ፩ኛ ቆሮ ፰፥፮። በወልደ እግዚአብሔር፦ ድካም ሕፀፅ አለበት የሚሉ፥
ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ የሚያደርጉትም ዕድል ፈንታቸው ከከሐድያን አይሁድ ጋር የተካከለ ነው።» ብሏል። ዮሐ
፫፥፴፮፣ (ሃይ፡ አበው ፲፪፥፪-፭)።
ኢየሱስ
ክርስቶስን ሁለት አካል ማለት ሦስት የሆኑትን የሥላሴ አካላት አራት ማድረግ ነው። ሁለት ባሕርይ ማለትም አንድ
የሆነውን የሥላሴ ባሕርይ ሁለት ማድረግ ነው። ይኽንን በተመለከተ፦ ሐዋርያዊ (እንደ ሐዋርያት የሆነ) ቅዱስ
አትናቴዎስ፦ የሃይማኖትን ነገር በተናገረበት ድርሳኑ፦ «ሰው ሆነ ፥ ስለ ማለት ፈንታም ራሳቸውን ለመጉዳት ልበ
ወለድን ነገር ፈጥረው፦ እግዚአብሔር በሰው አደረ አሉ፤ መለኮትና ትስብእት እርስ በርሳቸው ተዋሐዱ ስለ ማለት ፈንታ
ሰው ሠራሽን ነገር ፈጥረው ተናገሩ፤ የጌታችን የኢየሱስ አካል አንድ ነው ፥ ስለ ማለት ፈንታ ሁለት አካል፣ ሁለት
ባሕርያት፣ሁለት ገጽ ብለው አመኑ፤ በሦስት አካለት ስለማመን ፈንታም ሊያምኑበት ሊያስተምሩት በማይገባ ሥራ አራት
ብለው አመኑ፤» ብሏል። (ሃይ፡አበው ፳፭፥፳)።
ቅዱስ
ባስልዮስ ደግሞ፦ «ይህን አንድ ወልድን፦ ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ አንለውም፤ መለኮት ፥ በገንዘቡ አካል ፥
በገንዘቡ ባሕርይ ፣ ትስብእትም፦ በገንዘቡ አካል ፥ በገንዘቡ ባሕርይ ልዩ እንደሆኑ አንናገርም፤ አንድ አካል አንድ
ባሕርይ ነው ፥ እንላለን እንጂ። ፩ኛ ቆሮ ፰፥፮ ፣ ፪ኛ ቆሮ ፭፥፲፬። ቅዱስ ጴጥሮስም ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ
ብሎ አልተናገረም፤ አንድ አካል አንድ ባሕርይ መሆኑን አምኖ ክርስቶስ ስለ እኛ በሥጋ ታመመ አለ እንጂ። ፩ኛ ጴጥ
፪፥፳፩።» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፴፪፥፲፱)። ቅዱስ ቴዎዶጦስም፦ «ክርስቶስን የሚለየው ማነው? የአንዱን ስም
ምሥጢርስ የሚከፍል ማነው? አንዱን ስም ሁለት ሲሉት ቢገኙ ጥቅሙ ምንድር ነው? አምላክ ሰው ካልሆነ፦ ተራበ ፥
ተጠማ እንዴት ተባለ? ትስብእትን ከእግዚአብሔር ቃል የሚለዩ ፥ በባሕርይ ስም አንድ የሆነውንም የሚከፍሉ ፥ አንዱ
ክርስቶስ ሁለት እንደሆነ የሚናገሩ ፥ በነገርም ብቻ አንድ ነው የሚሉ እነዚያ እስኪ ይንገሩን። ፩ኛ ቆሮ ፲፪፥፫፤»
ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፶፫፥፴፫)።
በዚሁ
መጽሐፍ በቃለ ግዝት ላይ፦ «አንዱ ከእግዚአብሔር አብ ፥ አንዱ ከድንግል ማርያም ብሎ ሁለት ወልድ የሚል፦
ከእግዚአብሔር የተወለደው ከድንግልም የተወለደው አንድ አይደለም የሚል ቢኖር እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ከነገራቸው
ልጅነት ይለይ። እኛ ክርስቶሳውያን ግን በተዋሕዶ ሰው የኾነው አምላክ በእውነት ባሕርዩ አንድ ነው፤ አካሉ አንድ
ነው፤ ገጹ አንድ ነው፤ ነፍስም ሥጋም አለው ልንል ይገባናል፤ ሁለት ባሕርያት ፥ ሁለት አካላት ፥ ነፍስና ሥጋም
ያለው ስለሆነም፦ አንዱ ሰው ሁለት ነዋ? ለእኛስ ከዚህ ትምህርት አንድነት የለንም፤ በጎላ በተረዳ ልትናገሩት
የሚገባውስ ይህ ነው፤ ከድንግል ማርያም ነፍስን ሥጋን ነሥቶ ሰው የሆነ የእግዚአብሔር አብ ልጅ መድኃኒታችን
ክርስቶስ አንድ ነው ፥ ማለት ነው። ይህም በማይነገር በማይመረመር ድንቅ በሚሆን ተዋሕዶ ተደረገ፤ የማይታየው እርሱ
ከሚታየው ጋር ፥ ዘመን የማይቆጠርለት ዘመን ከሚቆጠርለት ጋር፥ አንድ የኾነው አንዱ ነው፤ ሁለት አይደለም፤
ሳይለወጥ ሰው የኾነ እግዚአብሔር ቃል አንድ ባሕርይ ፥ አንድ አካል ፥ አንድ ገጽ ነው እንጂ፤» ይላል። (ሃይ፡
አበው ፻፳፥፯)
ነገረ ማርያም ክፍል ፲፦
የሰው
ልጅ ባሕርይ በአዳም ኃጢአት ምክንያት አድፎ ቆሽሾ ይኖር ነበር። በዚህም ምክንያት ጽድቁ ሁሉ የመርገም ጨርቅ
ሆኖበት ፥ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ ተጨምሮበት ወደ ሲኦል ሲጋዝ ኖሯል። ይህንንም ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስ፦
«ሁላችን እንደ ርኲስ ሰው ሆነናል ፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል ፦
በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል፤ » በማለት ገልጦታል። ኢሳ ፷፬፥፮ ። እንዲህም ማለቱ፦ ነቢያት እና ካህናት
አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት የጸለዩት ጸሎት ፥ የሰዉት መሥዋዕት ፥ በዕደ እግዚአብሔር ለመያዝ አበቃቸው እንጂ፦
ለክብር ፣ ለልጅነት ፣ ለገነት ለመንግሥተ ሰማያት እንዳላበቃቸው ለመናገር ነው። እንደ «ቅጠል ረግፈናል፤»
ያለውም፦ ለጊዜው በመዓት፣ በመቅሠፍት መርገፍን ሲሆን ፥ ለፍጻሜው በአካለ ነፍስ በሲኦል መርገፍን ነው። ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስም፦ «ስለዚህም በአንድ ሰው በደል ምክንያት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባች፤ ስለዚችም ኃጢአት ሞት ገባ፤
እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስለ አደረጉ በሰው ሁሉ ላይ ሞት መጣ። . . . ነገር ግን በአዳም ኃጢአት ምክንያት
ከአዳም እስከ ሙሴ (እስከ ክርስቶስ) የበደሉትንም ያልበደሉትንም ሞት ገዛቸው፤ ሁሉ በአዳም አምሳል ተፈጥሮአልና ፥
አዳምም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ አምሳል ነውና፤» ብሏል። ሮሜ ፭፥፲፪-፲፬።
ከሰው
ወገን ባሕርይዋ ያላደፈባት ፥ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ያልወደቀባት ፥ ጥንተ አብሶ (የአዳም የጥንት በደል)
ያልነካት ፥ በሥጋም በነፍስም ፍጽምት ሆና የተፈጠረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ብቻ ናት። በዚህም
ምክንያት የአዳም ኃጢአት እንደ ቅጠል ላረገፈው የሰው ዘር በጠቅላላ የባሕርዩ መመኪያ ሆናለታለች። ነቢዩ ኢሳይያስ፦
« የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንን ፥ እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር፤»
ያለው ለፍጻሜው ስለ እርሷ ነው። ኢሳ ፩፥፱። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ የነሣውን (ነፍስንና ሥጋን ነሥቶ
የተዋሐደው) ከአብርሃም ዘር እንጂ ከመላእክት የነሣው አይደለምና። (የመላእክትን ባሕርይ ባሕርይ አላደረገም)።»
ያለው እመቤታችንን ነው። ዕብ ፪ ፥ ፲፮። ይህንን
ጠንቅቆ የሚያውቅ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም በዕለተ ሰንበት የውዳሴ ማርያም ድርሰቱ፦ «ጸጋን የተመላሽ ሆይ ፥ ከቅዱሳን
ሁሉ ይልቅ ትለምኝልን ዘንድ ለአንቺ ይገባል፤ አንቺ ከሊቃነ ጳጳሳት ትበልጫለሽ፤ ከነቢያትም ከመምህራንም
ትበልጫለሽ፤ ከሱራፌልና ከኪሩቤል ግርማ የሚበልጥ የመወደድ ግርማ አለሽ፤» ካላት በኋላ፦ «በእውነቱ የባሕርያችን
መመኪያ አንቺ ነሽ፤» ብሏታል።
አምላካችን
በሁሉ ባዕለጸጋ ነው፥ ሁሉ የእርሱ ነው ፥ የእርሱ ብልጽግና የማይጎድል ብልጽግና ነው፤ ይኽንን በተመለከተ
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «የእግዚአብሔር ባለጠግነት፥ ጥበብና ዕውቀት እንዴት ጥልቅ ነው!» ብሏል። ሮሜ ፲፩፥፴፫።
እግዚአብሔርም ከዚህ ጥልቅ ከሆነ ብልፅግናው ለሰው ልጆች ሁሉ ጸጋ አድርጎ በልግስና ሰጥቷል፥ በየጊዜውም በጸጋ
ላይ ጸጋ ይጨምራል። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፦ «እኛም ሁላችን ከሙላቱ በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀበልን። ኦሪት በሙሴ
ተስጥታ ነበርና፤ ጸጋና እውነት በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነልን፤»ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፩፥፲፮።
የባዕለጸጎች
ባዕለጸጋ የሆነ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የእኛን ባሕርይ በመንሣቱ፦ «ነገር ግን የባርያን መልክ
ይዞ ፥ በሰው ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ። እንደ ሰው ራሱን አዋረደ፤» ተብሏል። ፊል ፪፥፯። በቆሮንቶስ
መልእክትም ላይ ፦ «የጌታችን የኢየሱስ ክርሰቶስን ቸርነቱን ታውቃላችሁ፤ በእርሱ ድህነት እናንተ ባለጸጎች ትሆኑ
ዘንድ እርሱ ባለጸጋ ሲሆን፥ ስለእናንተ ራሱን ድሃ አደረገ፤» የሚል ተጽፏል። ፪ኛ ቆሮ ፰፥፱። ከሁሉም በላይ ራሱ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ሁሉ የእርሱ ሲሆን ፦ «ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መስፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ
ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም፤» ብሏል። ማቴ ፰፥፳።
ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ እንጂ፦ ከባሕርዩ ምንም
አልተለወጠም። የእኛን ባሕርይ በተዋሕዶ ገንዘብ አድርጎ ሰው ሆኗል። እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው፥
የክብር አምላክ ሲሆን በተዋሕዶ ከበረ፥ ተባለ፤ ሕይወት ሲሆን ነፍስን ነሣ፥ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፦ «ሕይወት
በእርሱ ነበረ፥ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፤» ብሏል። ዮሐ ፩፥፬። በመልእክቱም፦ «ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው
የነበረውንና በጆሮአችን የሰማነውን ፥ በዓይናችንም የተመለከትነውንም ፥ እጆቻችንም የዳሰሱትን እንነግራችኋለን።
ሕይወት ለእኛ ተገልጻለችና አየናት፤ ምስክርም ሆንን፤ ለእናንተም ከአብ ዘንድ ያለችውንና ለእኛ የተገለጠችውን
የዘለዓለምን ሕይወት እንነግራችኋለን፤» በማለት ነግሮናል። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «የሕይወትንም
ራስ ገደላችሁት ፤ » በማለት አይሁድን የወቀሳቸው እርሱ ሕይወት ስለሆነ ነው። የሐዋ ፫፥፲፭። ጌታችንም ፦ «እኔ
ሕይወት ነኝ፤» በማለት ለደቀመዛሙርቱ ነግሮአቸዋል። ዮሐ ፲፬፥፮።
አንድ
ክርስቶስ (ወልድ ዋሕድ) የሕይወት እንጀራ ሲሆን ባሕርያችንን በመንሣቱ ማለትም ረሀብ የሚስማማውን የሥጋን ባሕርይ
በመዋሐዱ ተራበ፥ ዮሐ ፮፥፴፭፤ ማቴ ፳፩፥፲፰፤ የሕይወት ውኃ ሲሆን ተጠማ፥ ዮሐ ፬፥፲፤ ፲፱፥፳፰፤ ተንገላታ፥ «
ለሞት እስከመድረስም ታዘዘ፤ ሞቱም በመስቀል የሆነው ነው።» እንዲል፦ እስከ መስቀል ሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ፤ ፊል
፪፥፰። ጌታችን ከባሕርይ አባቱ ከአብ፥ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በፈቃድ አንድ ሲሆን፦ «አባቴ ሆይ ፥
የሚቻልስ ከሆነ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን ፈቃድህ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይደለም፤ » ያለው ለዚህ
ነው። ማቴ ፳፮፥፴፱። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «ልጅም ቢሆን መከራን ስለተቀበለ መታዘዝን አወቀ፥ ከተፈጸመም
በኋላ ለሚታዘዝለት ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ የዘላለም መድኅን ሆነ፤» ብሏል። ዕብ ፭፥፰።
እርሱ
በባሕርዩ ሞት የለበትም፥ ሕያወ ባሕርይ ነው፤ ጌታችን ፦ ቅዱስ ዮሐንስን፦« አትፍራ፥ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም
እኔ ነኝ፤ ሞቼም ነበረሁ፤ እነሆም፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦል መክፈቻም በእኔ ዘንድ
አለ፤» ያለው ለዚህ ነው። ራዕ ፮፥፲፯። ጌታችን ሞት የሚስማማውን የሥጋን ባሕርይ በመዋሐዱ ሞተ፥ሞተ የተባለውም
ነፍስ ከሥጋ በመለየቷ ነው። «ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ፤» እንዲል፦ ከሥጋ የተለየች ያቺ ነፍስ የእርሱ
ናት። ዮሐ ፲፱፥፴። በሉቃስ ወንጌል ደግሞ ፦ «አባት ሆይ ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ፤» የሚል አለ። ሉቃ
፳፫፥፵፮። ጌታችን «ነፍሴ» ማለቱ በተዋሕዶ የራሱ ገንዘብ ስላደረጋት ነው። «እነሆ በጎና ጻድቅ ሰው የሸንጎ
አማካሪም የሆነ ፥ ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ ይህም በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ አርማትያስ ከምትባል
ከይሁዳ ከተማ ሆኖ እርሱ ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር። ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን
ሥጋ ለመነው። » እንዲል፦ ነፍስ የተለየችው ሥጋም በተዋሕዶ የእርሱ ገንዘብ ነው። ዮሐ ፲፱፥፴፰።
መለኮት
የእኛን ባሕርይ ተዋሐደ፥ ስንል ፦ የተዋሕዶው ምሥጢር የሰው አእምሮ ሊረዳው ከሚችለው በላይ ነው፥ ይህም፦ በሥጋ
እውቀት የሚረዱት አይደለም ማለት ነው። ለመሆኑ የነፍስን እና የሥጋን ተዋሕዶ ልንረዳ የምንችለው በምን መልክ ነው?
ነፍስ በባሕርይዋ የሥጋን ፈቃድና ምቾት ባትካፈልም፦ ፈቃዷን የምትፈጽመው በሥጋ ላይ ነው። ሥጋ የእርሱን ፈቃድ
ትቶ ለእርሷ ፈቃድ እንዲገዛ ሁልጊዜ ትፈልጋለች። ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እላችኋለሁ፤ በመንፈስ (በፈቃደ ነፍስ) ኑሩ
እንጂ የሥጋችሁን ፈቃድ አታድርጉ። ሥጋ፦ መንፈስ (ነፍስ) የማይሻውን ይሻልና፥ መንፈስም (ነፍስም) ሥጋ የማይሻውን
ይሻልና፥ የምትሹትንም እንዳታደርጉ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ፤» ያለው ለዚህ ነው፤ ገላ ፭፥፲፮። ክርስቶስም ፦
በመለኮቱ ሕማም (መከራ) የማይስማማው ሲሆን ሕማም የሚስማማትና ሁሉን አዋቂ የሆነች ነፍስ ያለውን ሥጋ ተዋሕዷል።
ጌታ
በሥጋው መከራ ሲቀበል፦ በተዋሐደው ሥጋ መከራ ተቀበለ፥ በዚህም አሥራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል ገንዘብ አደረገ።
በመሆኑም ከተዋሕዶ በኋላ ጌታን ለሁለት ከፍሎ በመለኮቱ መከራ አልተቀበለም፥ በሥጋው ብቻ መከራ ተቀበለ አይባልም።
አንድ ሰው ሥጋም ነፍስም ስላለው አንድ ሰው እንጂ ሁለት አይባልም፤ ነፍሱ ከሥጋው ጋር በተዋሕዶ አንድ ስለሆነች
አንድ ሰው መባሉ ግድ ነው። ክርስቶስም በተዋሕዶ የከበረ አምላክ ስለሆነ አንድ እንጂ ሁለት አይባልም። ከዚህ
በመቀጠል ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት፦
የጽላት ፥ የታቦት ምሳሌነት፦
የጽላት
የታቦት ምንጭ እግዚአብሔር ነው ፥ ልበ-ወለድ አይደለም። «እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን
በፈጸመ ጊዜ ሁለቱን የምስክር ጽላት ፤ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ( በግብር አምላካዊ ተጽፈው የተገኙትን)
የድንጋይ ጽላት ለሙሴ ሰጠው።» እንዲል፦ ጽላትን ቀርጾ አክብሮ ለሙሴ የሰጠው እግዚአብሔር ነው። ዘጸ ፴፩፥፲፰።
«ጽላቱም በዚህና በዚያ በሁለት ወገን ተጽፎባቸው ነበር። ጽላቱ የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ ጽሕፈቱም በጽላቱ ላይ
የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበረ፤» ይላል። ዘጸ ፴፪፥፲፭።
ጽላቱ
በተሰበሩ ጊዜም፦ እንደገና የቀደሙትን አስመስሎ እንዲቀርጽ እግዚአብሔር ለሙሴ ፈቅዶለታል። እግዚአብሔር ሙሴን፦
«የቀደሙትን ጽላት አስመስለህ ሁለት ጽላት ቀርጸህ እኔ ወደምገለጽበት ተራራ ውጣ ፥ ቀድሞ በሰበርካቸው ጽላቶች
ተጽፈው የነበሩ አሥሩ ቃላትም በእነዚህ ጽላቶች ጽፌ እሰጥሃለሁ፤ ማለዳ ወደ ደብረ ሲና ትወጣለህና ተዘጋጅተህ ንጹህ
ሁነህ እደር ፥ ማልደህም ወደ ደብረ ሲና ወጥተህ ቁም፤ ሌላ ሰው ግን ካንተ ጋር ወጥቶ ከተራራው ላይ አብሮህ
የሚቆም አይኑር፥ ላሞችም በጎችም ቢሆኑ በተራራው አቅራቢያ ሊሠማሩ አይገባም፤» አለው። ሙሴም የቀደሙትን ጽላቶች
አስመስሎ ሁለት የእብነበረድ ጽላት ቀርጾ ይዞ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ማልዶ ገሥግሦ ወደ ደብረ ሲና ወጣ።
እግዚአብሔርም
በደመና ወርዶ ፥ በደብረ ሲና ራስ ላይ ቁሞ ፥ እኔ፦ «መሓሪ ወመስተሣህል ነኝ፤ » ብሎ ተናገረ። በሙሴም ፊት
በብርሃን ሠረገላ ሁኖ የጌትነቱን ስም እየጠራ አለፈ፤ «ስሜም፦ ይቅር ባይ ፥ ከመዓት የራቀ ፥ ቸርነቱ የበዛ ፈጥሮ
የሚገዛ መባል ነው፤ የአብርሃምን መሓላ አጽንቼ ፥ ለአእላፈ እሥራኤል ቸርነትን የማደርግ ፥ አመጽን፣ በደልን ፣
ኃጢአትን የማርቅ ፥ ይቅር የምል እኔ ነኝ፤ በድሎ የማይመለሰውን ግን ከኃጢአት አላነጻውም፤ (ይቅር አልለውም) ፤»
አለ። አመጻ የድፍረት ፥ በደል የስህተት ፥ ኃጢአት የድካም ነው።
ሙሴ
የእግዚአብሔርን ቃል በሰማ ጊዜ፦ ደንግጦ ፥ አንገቱን ሰበር አድርጎ ለእግዚአብሔር የፍርሃት ስግደት ሰገደ፤
እግዚአብሔርንም፦ «በአንተ ዘንድ ሞገስን (ባለሟልነትን) ካገኘሁ ፥ አንተ ጌታዬ ከእኔ ጋር በረድኤት አብረኸኝ ሂድ
፥ እሥራኤል ክሣዳ ልቡናቸው በኃጢአት የጸና ነውና የወገኖችህን ፍጹም ኃጢአት ይቅር በል፥ ይህን ያደረግህልን
እንደሆነ ለአንተ ስንገዛ እንኖራለን፤» አለው። እግዚአብሐርም ሙሴን፦ «በወገኖችህ ዘንድ የኪዳን ምልክት ይሆን
ዘንድ ብርሃን በፊትህ እሥልብሃለሁ፥ በአራቱም መዓዝን ባሉ በአሕዛብ ዘንድ ሁሉ ተደርጎ የማያውቅ ጭጋግ ተአምራት
አደርግልሃለሁ፤ እኔም የማደርግልህ ነገር ድንቅ ነውና አንተ በመካከሉ ያለህበት ይህ ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ሥራ
ያያል፤ » አለው። ከዚህም አያይዞ አያሌ ትእዛዛትን አዝዞታል።
በመጨረሻም
እግዚአብሔር ሙሴን፦ «በእነዚህ ቃሎች ከአንተ ከእሥራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና (ሕጌን ቢጠብቁ
እጠብቃቸዋለሁና) እነዚህን ቃሎች (የነገርኩህን ሁሉ) ጻፍ፤» አለው። በዚያ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በእግዚአብሔር
ፊት ነበረ፤ እንጀራም አልበላም ፤ ውኃም አልጠጣም፤ በጽላቱም አሠሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ። ዘጸ ፴፬፥፩-፳፰።
የቀደመው
ጽላት የአዳም ምሳሌ ነው፤ ጽላቱ እምኀበ አልቦ እንደተገኘ ፥ አዳም እንበለ ዘርእ ለመገኘቱ ምሳሌ ነው፤ ጽላቱ
ሁለት ወገን መሆኑ ለነፍሱና ለሥጋው ምሳሌ ነው፤ ጽላቱ በጣዖት ምክንያት መሰበሩ ደግሞ አዳም በኃጢአት ምክንያት
ለመጎዳቱ ምሳሌ ነው፤ የመጀመሪያው ጽላት በእግዚአብሔር እጅ መሠራቱ አዳም በእግዚአብሔር እጅ ለመፈጠሩ ምሳሌ ነው።
ቅዱስ ዳዊት፦ «እጆችህ ሠሩኝ ፥ አበጃጁኝም፤» ያለው ለዚህ ነው። መዝ ፻፲፰፥፸፫። የኋለኛው ጽላት የእመቤታችን
የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ነው። ሁለት መሆኑ የነፍሷና የሥጋዋ ምሳሌ ነው። በጽላቱ ላይ ቃለ እግዚአብሔር
መቀረጹ፥ ከሦሥቱ አካላት አንዱ አካላዊ ቃል (ቃለ አብ ፥ ቃለ መንፈስ ቅዱስ) ከሰማይ ወርዶ፥ በመንፈስ ቅዱስ
ግብር በማኅፀኗ ሰው ሁኖ ለመቀረጹ ምሳሌ ነው። የኋለኛው ጽላት ከሰው ወገን በሙሴ እጅ መቀረጹ ፥ እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም ከሰው ወገን በሕግ በሆነ ሩካቤ ፥ ከቅዱስ ኢያቄምና ከቅድስት ሐና ለመወለዷ ምሳሌ ነው።
ይኽንን በተመለከተ፦ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ ፦ «ድንግል ሆይ ፥ በኃጢአት ፍትወት የተጸነስሽ
አይደለም ፥ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ፤» ብሏል። (ቅዳ፡ ማር፡ ቁጥር ፴፰)
እግዚአብሔር
ጽላቱን ለሙሴ ከመስጠቱ በፊት የጽላቱን ማደሪያ ታቦቱን እንዲያዘጋጅ ነግሮታል። ከምንና እንዴት መሥራት
እንዳለበትም አስተምሮታል። ይኽንንም ፦ «ከማይነቅዝ (ሽምሸርሰጢን ከሚባል) ዕፅ ቆርጠህ የምስክሩን ታቦት ሥራ፤ .
. . በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው፤
በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ አክሊል አድርግለት። አራት የወርቅ ቀለበቶችም አድርግለት፤ » በማለት ነግሮታል።
ዘጸ ፳፭፥፲-፲፪። ታቦት የትስብእት ፥ ወርቅ ደግሞ የመለኮት ምሳሌዎች ናቸው፤ ታቦቱ በውስጥም በውጭም በወርቅ
እንደተለበጠ፥ በወርቅ የተመሰለ መለኮትም፦ በውጭ የሚታይ ሥጋን እና በውስጥ ያለች የማትታይ ነፍስንም ተዋሕዶ ሰው
ሆኗል። ታቦቱ ከማይነቅዝ ዕፅ መሠራቱም፦ የጌታችን ሥጋው በመቃብር፦ የማይፈርስ የማይበሰብስ ለመሆኑ ምሳሌ ነው።
ይኽንን በተመለከተ ባለቤቱ ራሱ በነቢዩ በዳዊት አድሮ፦ «ነፍሴን (ሰውነቴን) በሲኦል አትተዋትምና ፥ ቅዱስህንም
መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውምና፤» ብሏል። መዝ ፲፭ ፥፲። ታቦቱ የተለበጠበት ወርቅ ንጹህ መሆኑ፦ እግዚአብሔር
በባሕርዩ ንጹሕ ለመሆኑ ምሳሌ ነው። ጌታ በተወለደ ጊዜ ሰብአ ሰገል ወርቅ መገበራቸው እርሱ ባወቀ «ንጹሐ ባሕርይ
ነህ፤ » ሲሉት ነበር ፥ አንድም ወርቅ መለኮትህ ትስብእትን ተዋሕዷል ማለትም ነው። ማቴ ፪፥፲፩። ቅዱስ ኤፍሬምም
በእሑዱ የውዳሴ ማርያም ድርሰቱ ፦ «ከማይነቅዝ እንጨት የተቀረጸ በውስጥና በውጭ በወርቅ የተለበጠ ታቦት ፥
ያለመለየትና ያለመለወጥ ሰው የሆነ ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ይመስልልናል። ይኽውም መለወጥ የሌለበት ንጹሕ መለኮት
ነው፥ ከአብ ጋር የተካከለ ነው።» ብሏል።
የሁለቱ አዕዋፍ ምሳሌነት፤
በኦሪቱ
ለምጽ የርኲሰት ምልክት ስለነበረ፥ እግዚአብሔር በልሙጻን ላይ ከመንጻታቸውና ከነጹም በኋላም ሕግ ሠርቶባቸው
ነበር። ይኽንንም፦ «ለምጽ የያዘው ሰው ሕጉ ይህ ነው፤ ከለምጽ በነጻበት ቀን ወደ ካህኑ ይወስዱታል ካህኑም ከሰፈር
ወደ ውጭ ይወጣል፤ ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም ፥ የለምጹ ደዌ ከለምጻሙ ላይ ቢጠፋ ፥ ካህኑ ስለሚነጻው ሰው ሁለት
ንጹሐን ወፎች በሕይወታቸው ፥ የዝግባም እንጨት ፥ቀይ ግምጃም ፥ ሂሶጵም ያመጣ ዘንድ ያዝዛል። ካህኑም ከሁለቱ
ወፎች አንደኛዋን በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ ያርድ ዘንድ ያዝዛል። ያልታረደችውን ወፍ ፥ የዝግባውንም
እንጨት ፥ ቀዩንም ግምጃ ፥ ሂሶጱንም ወስዶ በታረደችው ወፍ ደም ውስጥ ይነክራቸዋል። ከለምጹም በሚነጻው ሰው ላይ
ሰባት ጊዜ ይረጫል፤ ንጹሕም ይሆናል፤ ያልታረደችውንም ወፍ ወደ ሜዳ ይለቃታል።» በማለት ነግሮታል።ዘሌ ፲፬፥፩-፯።
ሁለቱ ወፎች ንጹሐን መሆናቸው፦ መለኮትም ፥
የተዋሐደው ሥጋም ንጹሐን ለመሆናቸው ምሳሌዎች ናቸው። አንዷ ወፍ ታርዳ በፈሰሰው ደም ሁለተኛዋ ወፍ ተነክራ
በሕይወት መኖሯ ፦ ጌታ በተዋሐደው ሥጋ፦ ደሙን በመስቀል ላይ አፍስሶ ነፍሱን ከሥጋው ለይቶ ቢሞትም፦ በመለኮቱ
ሕያው ለመሆኑ ምሳሌ ነው። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «ስለ እኛ ፥ ስለ ኃጢአታችን በሥጋ ሞተ፤
በመንፈስ (በመለኮት) ግን ሕያው ነው፤» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፫፥፲፰። የምንጩ ውኃ ደግሞ ለጥምቀት ውኃ ምሳሌ ነው።
ይኸውም፦ «ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤»ተብሎ የተነገረለት
ነው። ዮሐ ፫፥፭። እርሱም ራሱ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቆ፦ በጥምቀቱ የባረከው የቀደሰው ነው። ማቴ ፫፥፲፫።
የእኛን
ባሕርይ በመንሣት በተዋሕዶ ሰው የሆነ ጌታ፦ በሚበሩ አዕዋፍ የተመሰለው ከሰማይ ሰማያዊ መሆኑን ለመግለጥ ነው።
ይኽንንም፦ «ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም ፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ (ወልደ
ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) ነው።» በማለት ጌታችን ነግሮናል። ዮሐ ፫፥፲፫። እንግዲህ ለምጻሙ ሰው በወፉ ደም
ተረጭቶ ከለምጹ ፈጽሞ እንደሚነጻ ፥ የአዳም ልጆችም በመስቀል ላይ በፈሰሰ በክርስቶስ ደም፦ ከኃጢአት ፈጽመን
ነጽተናል። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ፦ «የኢየሱስ ክርሰቶስም ደም ከኃጢአታችን ሁሉ ያነጻናል፤»
ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፯። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፦ «ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይረባና ከማይጠቅም
ሥራችሁ የተቤዣችሁ በሚጠፋ በወርቅ ወይም በብር እንዳይደለ ታውቃላችሁ። ነውርና እድፍ እንደሌለው በግ በክርስቶስ
ክቡር ደም ነው እንጂ፤» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፩፥፲፰። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «እግዚአብሔር በገዛ ደሙ
የዋጃትን ቤተ ክርስቲያንን ጠብቁ፤» ብሏል። የሐዋ ፳፥፳፰።
እግዚአብሔር
ባሕርያችንን ነሥቶ ሰው ሆነ ፥ እኛን መሰለን ፥ የሥጋ ዘመድ ሆነን ፥ የምንለው የባሕርያችን መመኪያ በሆነች
እመቤት ፥ በቅድስት ድንግል ማርያም ተመክተን ነው። እርሷን ምክንያተ ድኂን አድርጎ በደሙ ፈሳሽነት ስላዳነን
እንመካባታለን ፥ ለድኅነተ ዓለም፦ በመልዕልተ መስቀል የተቆረሰ ሥጋ ፥ የፈሰሰ ደም ፥ አሳልፎ የሰጣት ነፍስ ፥
የባሕርያችን መመኪያ ከሆነች ከእርሷ የነሣው ነውና። ለዚህም ነው፥ የጌታን አዳኝነት ስንናገር እመቤታችንን መተው
የማንችለው፤ ለሚያስተውል ሰው ነገረ ማርያም ነገረ ክርስቶስ ነውና። ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፲፩
«የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ መጽሐፍ፤»
ቅዱስ
ማቴዎስ ወንጌሉን መጻፍ የጀመረው፦ «የዳዊት ልጅ፥የአብርሃም ልጅ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትወልድ መጽሐፍ፤»
በማለት ነው። እንዲህም ያለበት ምክንያት ብዙ ዓይነት ልደታት ስላሉ ከእነዚያ የተለየ መሆኑን ለመግለጥ ነው።
አምላክ በተዋሕዶ ሰው የሆነበት ምሥጢር ታላቅ በመሆኑ ተጠንቅቆ ጽፎታል። ፩ኛ ጢሞ ፫፥፲፮። ይኸውም፦ አድሮበት
በሚኖር መንፈስ ቅዱስ ወደፊት በነገረ ክርስቶስ ዙሪያ አያሌ መናፍቃን እንደሚነሡ ስለሚያውቅ አስቀድሞ የኑፋቄን
መንገድ ሲዘጋባቸው ነው።
፩፥፩፦ ልደተ አዳም፤
«ወገብሮ
እግዚአብሔር ለሰብእ እመሬተ ምድር፤ እግዚአብሔር አዳምን ከምድር መሬትን ነሥቶ ፈጠረው፤ በፊቱም የሕይወት
እስትንፋስን እፍ አለበት፤ (ሕይወት የምትሆነውን ነፍስን አሳደረበት)፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። (አዳም
ሕይወት በምትሆን ነፍስ ሕያው ባለአእምሮ ሆነ)፤» ይላል። ይህም፦ አንድ ሰው፦ ጐተራውን በፊት ሠርቶ ፥ በኋላ
እህል እንደሚያኖርበት ፥ በፊት ሥጋን ፈጥሮ ኋላ ነፍስን አምጥቶ አሳደረበት ማለት አይደለም። እግዚአብሔር፦ ሥጋን
ከአራቱ ባሕርያት (ከመሬት፣ ከነፋስ ፣ ከእሳት ፣ ከውኃ)፥ ነፍስንም እምኀበ ዐልቦ (ካለመኖር ወደ መኖር ፣
ከምንም አምጥቶ) የፈጠረው ፣ ያዋሐደው አንድ ጊዜ ነው። ዘፍ ፪፥፯።
አዳም
ማለት ከመሬት የተፈጠረ ማለት ነው፤ አንድም፦ የሚያምር ፥ ደስ የሚያሰኝ ፥ ውብ፥ ደግ፥ መልካም፥ መልከ መልካም
ማለት ነው። ከመሬት በመፈጠሩም ከድንግል መሬት ተወለደ ይባላል። በዚህም ከድንግል ማርያም ለተወለደው ዳግማዊ አዳም
ለሚባል ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኗል። ከድንግል መሬት የተወለደው አንድ አዳም እንደሆነ ሁሉ፥ ከድንግል
ማርያምም የተወለደው አንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። አዳም በዚህ ምድር የኖረው ለዘጠኝ መቶ ሠላሳ ዓመት ነው።
ዘፍ ፭፥፭።
፩፥፪፦ ልደተ ሔዋን፤
የሔዋን
ልደት ከአዳም ጎን ነው፤ «እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ላይ እንቅልፍን አመጣ፤ አንቀላፋም፤ (ማእከለ ነቂሕ
ወነዊም ሆነ፤ ይህም በእንቅልፍና በመንቃት መካከል ሆነ ማለት ነው)፤ ከጎኑም አጥንቶች አንድ አጥንትን ወስዶ
ስፍራውን በሥጋ መላው። እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ (የሴት አካል ያላት
አድርጎ ፈጠራት ፥ አንድም ስትፍት ብርህት አደረጋት)፤ ወደ አዳምም አመጣት። (መልክ ከደም ግባት አስተባብራ
የያዘች የምታምር አድርጎ ወደ አዳም አመጣት)። አዳምም፦ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፤ ሥጋዋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ
ከባልዋ ተገኝታለችና ሚስት ትሁነኝ፤ (ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል)፤ አለ።» ይላል። ዘፍ ፪፥፳፩። እናታችን
ሔዋን ኅቱም ከሆነ ከአዳም ጎን እንደተወለደች ሁሉ፥ ጌታም በድንግልና ኅትምት ከሆነች ፥ ከእመቤታችን ከቅድስት
ድንግል ማርያም ተወልዷል።
፩፥፫፦ ልደተ በግዕ፤
እግዚአብሔር
አብርሃምን ለበጎ ፈተነው፤ በሀገራቸው ልማድ፦ «አብርሃም፥አብርሃም» ብሎ በደጊመ ቃል ጠራው፤ አብርሃምም፦
«ጌታዬ፥ እነሆ አለሁ፤» አለ፤ እግዚአብሔርም፦ «የምትወደውን ልጅህን ይስሐቅን ከፍ ወደአለ ተራራ ይዘኸው ሂድ፥
ከዚያም በደረስህ ጊዜ በማሳይህ በአንድ ተራራ ላይ አውጥተህ ሠዋው፤» አለው። አብርሃምም፦ ልጁን ይስሐቅን
ይዞ፥ሁለቱንም ሎሌዎቹን አስከትሎ አህያውን ጭኖ ተነሣ። እንጨትንም ለመሠዊያ ሰነጠቀ፤ ተነሥቶም እግዚአብሔር
ወደአለው ቦታ ሄደ፤ በሦስተኛውም ቀን ደረሰ።
አብርሃም
ዓይኑን አንሥቶ ቦታውን ከሩቅ አየ። ሎሌዎቹንም፦ «አህያውን ይዛችሁ በዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ወደዚያ ተራራ ሄደን
እንሰግዳለን፤ ሰግደንም ወደ እናንተ እንመለሳለን።» አላቸው። አብርሃም፦ መሥዋዕት የሚሠዋበትን እንጨቱን አንሥቶ
ለይስሐቅ አሸከመው፤ እርሱም እሳቱንና ቢላዎውን በእጁ ያዘ፤ ሁለቱም አብረው ሄዱ። ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን፦
«አባቴ» ብሎ ጠራው፤ እርሱም፦ «ልጄ ምንድን ነው?» አለው። ይስሐቅም፦ «እሳቱና እንጨቱ እነሆ አለ፤የመሥዋዕቱ
በግ ግን ወዴት አለ?» አለው። አብርሃምም፦ «ልጄ ሆይ፥ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል፤» አለውና
ጉዞአቸውን ቀጠሉ።
እግዚአብሔር
ወዳለውም ወደዚያ ቦታ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያዉን ሠራ፤ እንጨትም ረበረበ፤ ይስሐቅም፦ እርሱ እንደሚሠዋ
አውቆ፦ «እኔን ልትሠዋኝ ይመስለኛል ፥ ስለዚህ ስወራጭ፣ ስንፈራገጥ እጅህን እንዳላስቆርጥህ እሰረኝ፤» ብሎታል።
በዚህን ጊዜ፦ እጁንና እግሩን አሥሮ ሠርጅቶ (ጠልፎ) ጣለው። ቀጥሎም የልጅ ዓይኑ ብክን ብክን ሲል ያሳዝናልና
ራርቼ ትቼው ከፈጣሪዬ ጋር እጣላለሁ ብሎ፥ አንድም ልጁ ይስሐቅ፦ ዓይኔ ብክን ብክን ሲል አይተህ ራርተህ ትተወኝና
ከፈጣሪህ ጋር ትጣላለህ ብሎት እንጨት በተረበረበበት በምሥዋዑ ላይ ደፍቶ በልቡ አስተኛው።
አብርሃምም
እጁን ዘረጋ፤ ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዎውን አነሣ። እግዚአብሔርም ከሰማይ ጠርቶ፦ «በብላቴናው ላይ እጅህን
አትዘርጋ፤ አንዳችም አታድርግበት፤ ለምትወድደው ልጅህ ከእኔ አልራራህለትምና፤ (ልጅህን ከእኔ ይልቅ
አልወደድኸውምና)፤ አንተ እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንህ አሁን አውቄአለሁ፤» አለው። አብርሃም ዓይኖቹን አቅንቶ
በተመለከተ ጊዜ፦ በኋላው እነሆ፥ አንድ በግ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ ሄዶም በጉን ወሰደውና በልጁ
በይስሐቅ ፈንታ ሠዋው። አብርሃምም፦ በዚህ ተራራ እግዚአብሔር ፈጽሞ ታየኝ ሲል ያን ቦታ፦ «ራእየ እግዚአብሔር፤»
ብሎ ጠራው።
አብርሃም
የአብ፥ ይስሐቅ ደግሞ የወልድ ምሳሌዎች ናቸው። አብርሃም ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ልጁን ይስሐቅን በሕሊናው
እንደሠዋው፥ እግዚአብሔር አብም ተቀዳሚና ተከታይ የሌለውን አንድ የባሕርይ ልጁን ፥ ስለ ሰው ልጅ ፍቅር ለሞት
አሳልፎ ሰጥቶታል። ይኽንንም ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፦ «በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ
እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶአልና።» በማለት ገልጦታል።
ዮሐ ፫፥፲፮። በመጀመሪያዪቱም መልእክቱ ላይ፦ «በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅሩ በእኛ ላይ ታወቀ፤ በእርሱ በሕይወት
እንኖር ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና።» ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፬፥፱።
ተራራው
የቀራንዮ፥ የመሠዊያው እንጨት የመስቀል ፥ እሳቱ የመንፈስ ቅዱስ፥ ሁለቱ ሎሌዎች በግራና ቀኝ ለተሰቀሉ ሰዎች ፥
ቢላዎ የሥልጣነ እግዚአብሔር ምሳሌዎች ናቸው። ቢላዎ አጥንትን ከሥጋ እንደሚለይ፥ ጌታም በገዛ ሥልጣኑ ነፍሱን
ከሥጋው ለይቷል። አብርሃም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በሰማበት በዚያ ሰዓት ወዲያው ልጁን በሕሊናው ሰውቶት ለሦስት
ቀናት ተጉዟል። ከሦስት ቀን በኋላም ይስሐቅ ድኗል። ሕሊና አብርሃም የመቃብር ምሳሌ ነው፤ ይስሐቅ በሕሊና አብርሃም
በተሠዋ በሦስተኛው ቀን መዳኑ፥ ጌታ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ለመነሣቱ ምሳሌ ነው።
አንድም በጉ የጌታ፥ ይስሐቅ ደግሞ የአዳምና የልጆቹ ምሳሌዎች ናቸው። በጉ ከሰማይ ወርዶ በኅቱም ዕፅ ተይዞ
(ከኅቱም ዕፅ ተወልዶ) መገኘቱ፥ ጌታ ከሰማይ ወርዶ ከድንግል ማርያም ለመወለዱ ምሳሌ ነው። ዕፀ ሳቤቅ የእመቤታችን
የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። በጉ ስለ ይስሐቅ ፈንታ መሠዋቱ ጌታ ለአዳምና ለልጆቹ ተላልፎ በመስቀል ላይ
ለመሠዋቱ ምሳሌ ነው። ሊቃውንቱ በጉ ከኅቱም ዕፅ ተወለደ ብለው ይተረጉሙታል። በዕፀ ሳቤቅ ቀንዶቹ ተይዞ የተገኘ
አንድ በግ ብቻ ነው ፥ ከእመቤታችንም የተወለደው አንድ የቀራንዮ በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ዘፍ ፳፪፥፩።
መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስ ኢየሱስ ክርስቶስን፦ «የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤» ያለው
ለዚህ ነው። ዮሐ ፩፥፳፱።
፬፥፩፦ ልደተ አቤል፤
አቤል
የቃኤል ታናሽ ወንድም ነው፤ ልደቱ በዘር በሩካቤ ነው፤ ከእርሱ ጋር መንታ ሆና የተወለደችው አቅሌምያ ናት፥ መልከ
ጥፉ ነበረች፤ አቤል ግን ብሩኅ ገጽ ነበረው። አባቱም፦ «ይህ ብሩኅ ገጽ ያለው ልጄ መንግሥቴን የሚወርሰው እርሱ
ነው፤» ይለው ነበር። የሚታወቀው በገርነቱ በየዋህነቱ ነው፥ ለአዳምና ለሔዋን ይታዘዛቸው ነበር፤ አዳም በሳምንት
ሦስት ጊዜ ለእግዚአብሔር ቊርባን ሲያቀርብ አይለየውም ነበር፥ ከቊርባኑም ይቀበል ነበር። ቃኤል፦ ከጸሎቱ፥ ከቊርባኑ
ብዙ ጊዜ ሲቀር አቤል ግን አንድም ቀን አያስታጉልም ነበር፤ ብዙ ጊዜ ይጾም ብዙ ጊዜም ይጸልይ ነበር። አባቱ
አዳም ባዘዘውና ባስተማረው መሠረት ንጹሕ መሥዋዕት በበጎ ኅሊና አቅርቧል፤ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ
ተመልክቷል። ዘፍ ፬፥፬። ስለየዋህ ልቡናው ፥ ስለ መሥዋዕቱም ንጹሕነት እግዚአብሔር ተደስቶበታል። አቤል፦ ልክ
እንደ አባቱ በሳምንት ሦስት ቀን መሥዋዕት ያሳርግ ነበር።
ቃኤል
አሥራ አምስት ዓመት ፥ አቤል ደግሞ አሥራ ሁለት ዓመት ሲሞላቸው፦ አባታቸው አዳም፦ ከቃኤል ጋር የተወለደችውን
ውብ ለአቤል አጋባት፤ ከአቤል ጋር የተወለደችውን መልከ ጥፉ ደግሞ ለቃኤል አጋባት። ቃኤልም ስለ ሦስት ነገር
በወንድሙ ተበሳጨበት። ፩ኛ፦ አልጋ ወራሽ በመሆኑ፤ ፪ኛ፦ መሥዋዕቱን እግዚአብሔር ስለተቀበለለት፤ ፫ኛ፦ በትዳሩ
ቀንቶበት ተቆጣ። በመጨረሻም ሰይጣን እንደአስተማረው «ና፥ወደ ሜዳ እንሂድ፤» ብሎ፥ ራሱን በድንጋይ ገምሶ
ገድሎታል። በግፍ የፈሰሰ የአቤል ደም፦ «ወንድሜ ቃኤል ገደለኝ፤» እያለ ጩኸቱን ለእግዚአብሔር አሰምቷል። ከሞተ
በኋላም በደሙ በመናገሩ ለትንሣኤ ሙታን ምሳሌ ሆኗል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ ይኽንን ይዞ፦ «አቤል ከቃኤል ይልቅ
የሚበልጥ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ በዚህም ጻድቅ እንደሆነ ተመሰከረለት፤ ምስክሩም መሥዋዕቱን በመቀበል
እግዚአብሔር ነው። በዚህም ከሞተ በኋላ ተናገረ።» በማለት ሃይማኖቱን ፥ ምግባሩን መስክሮለታል። ዕብ ፲፩፥፬።
እግዚአብሔር ቃኤልን፦ «ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?» ብሎ በጠየቀው ጊዜ፦ «አላውቅም፤ በውኑ የወንድሜ ጠባቂው እኔ
ነኝን?» በማለት ተሳልቋል። እግዚአብሔርም፦ «ምን አደረገህ? የወንድምህ የአቤል የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ
ይጮኻል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ፤»
ብሎታል። ዘፍ ፬፥፰-፲፩።
፪፦ ዳዊትና አብርሃም፤
ቅዱስ
ማቴዎስ ወንጌላዊ፦ «ወልደ ዳዊት፥ ወልደ አብርሃም፤» በማለት ከነገሥታት ዳዊትን፥ ከአበው ደግሞ አብርሃምን
አንሥቷል። ይኸውም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእነርሱ ብቻ ይወለዳል ለማለት ሳይሆን
የተለያዩ ምክንያቶች ስላሉት ነው።
፪፥፩፦ ዳዊት ሥርወ መንግሥት ስለሆነ ነው፤
ዳዊት፦
ከእሥራኤል ነገሥታት ሁሉ ይልቅ ታላቅና እጅግ ተወዳጅ ንጉሥ ነበር። የተወለደው እሴይ ከተባለ ሰው በይሁዳ
ቤተልሔም ነው። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲። እግዚአብሔር ሳይጠራው በፊት የበጎች እረኛ ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲፩
፣፲፯፥፴፬። ንጉሥ ሳኦል እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ በመመለሱ በእሥራኤል ላይ ንጉሥ እንዳይሆን እግዚአብሔር
ናቀው። «ስላነገሥሁት ተጸጸትሁ፤» በማለትም ለነቢዩ ለሳሙኤል ነገረው። ፩ኛ ሳሙ ፲፭፥፲። ንጉሥ ሳኦል በዚህና
በሌሎችም ምክንያቶች ሥርወ መንግሥት መሆን አልቻለም። «የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፤ ክፉም መንፈስ
ከእግዚአብሔር ዘንድ አስጨነቀው፤» ይላል። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲፬። በምትኩ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ዳዊት በሳሙኤል እጅ
ተቀባ። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ መጣ። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲፫። ዙፋኑን ከመውረሱ በፊት
ግን ጋሻ ጃግሬ ሆኖ ሳኦልን አገልግሎታል። በገና እየደረደረም ርኲስ መንፈስን ያርቅለት ከስቃይም ያሳርፈው ነበር።
፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲፰-፳፫። በሰይፍ ተመትቶ፥ በጦር ተወግቶ፥ በፈረስ በሠረገላ ተገፍትሮ፥ አይወድቅ የነበረውን ታላቁን
ጎልያድንም፦ በእግዚአብሔር ስምና ኃይል በወንጭፍ ድንጋይ ገድሎታል። ፩ኛ ሳሙ ፲፯፥፵፭-፶፮።
የሳኦል
ልጅ ናታን ዳዊትን እንደ ነፍሱ ስለወደደው ካባውን፥ ልብሱን፥ ሰይፉን፥ ቀስቱንና ዝናሩን ሸልሞታል። የእሥራኤል
ሴቶችም እየዘመሩና እየዘፈኑ፥ እልልም እያሉ፥ ከበሮና አታሞ ይዘው ተቀብለውታል። «ሳኦል ሺህ ገደለ፤ ዳዊትም አሥር
ሺህ ገደለ፤»እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር። በዚህም ምክንያት ሳኦል እጅግ ተቆጣ፥ ነገሩም አስከፋው፥ በዳዊትም
ላይ ቂም ያዘበት። ይሁን እንጂ ክፉ መንፈስ በየዕለቱ ሲያሰቃየው ዳዊት እየተጠራ በገና ይደረድርለት ነበር። በዚህ
አጋጣሚም ዳዊትን ከግንቡ ጋር አጣብቆ ለመግደል ከአንዴም ሁለት ጊዜ ጦር ወርውሮበት ነበር። ዳዊት ግን ከፊቱ
ዘወር ብሎ አመለጠ። እግዚአብሔር ከእርሱ ተለይቶ ከዳዊት ጋር ስለነበር ሳኦል ዳዊትን ይፈራው ነበር። ከዚህ የተነሣ
የሺ አለቃ አድርጎ (ሻለቅነት ሹሞት) በሹመት ስም ከፊቱ አራቀው። ነገር ግን በፊታቸው ይወጣና ይገባ ስለነበረ
እስራኤልና ይሁዳ ሁሉ ዳዊትን ወደዱት። ፩ኛ ሳሙ ፲፰፥፩-፲፮።
ንጉሥ
ሳኦል ዳዊትን በትዳር ሊያጠምደው ሞክሯል። ዳዊት ግን፦ «ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ሰውነቴስ
ምንድን ናት? የአባቴስ ወገን በእስራኤል ዘንድ ምንድን ነው?» በማለት የትህትናን ነገር ተናገረ። የሳኦል ልጅ
ሜሮብ ዳዊትን የምታገባበት ጊዜ ሲደርስ ለሚሆላዊው ለአድርኤል ተዳረች። ሜልኮል የተባለች ሴት ልጁ ደግሞ ዳዊትን
ወደደችው ፥ ወሬውም ለሳኦል ደርሶ ነገሩ ደስ ስለአሰኘው «እርስዋን እሰጠዋለሁ፤ እርስዋም እንቅፋት ትሆንበታለች፤»
አለ። ብላቴኖቹንም፦ «እነሆ ንጉሥ እጅግ ወድዶሃል፤ አሁንም ለንጉሥ አማች ሁን ብላችሁ በሥውር ለዳዊት ንገሩት፤»
ብሎ አዘዛቸው። ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ፦ «እኔ የተዋረድሁና ክብር የሌለኝ ሰው ስሆን ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ
ለእናንተ ትንሽ ነገር ይመስላችኋልን?» አላቸው። ንጉሡ ሳኦል፦ ይኽንን በነገሩት ጊዜ፦ «የንጉሡን ጠላቶች ይበቀል
ዘንድ ከመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት በቀር ንጉሥ ማጫ አይሻም ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት፤» አላቸው። ሳኦል እንዲህ
ማለቱ ብላቴናው ዳዊት በእነርሱ እጅ እንዲሞትለት ነው።ዳዊትና ሰዎቹም ዘምተው ሁለት መቶ ፍልስጥኤማውያንን ገደሉ።
ሳኦልም ዕድሜውን ሁሉ ለዳዊት ጠላት ሆነ። ፩ኛ ሳሙ ፲፰፥፲፯-፴።
ንጉሥ
ሳኦል፦ በፍልስጥኤማውያን ወረራ መካከል በጊልቦዓ ተራራ ላይ በገዛ እጁ ከሞተ በኋላ፦ ዳዊት አስቀድሞ በይሁዳ፥
በኋላም በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ። ፪ኛ ሳሙ ከምዕራፍ ፪ እስከ ምዕራፍ ፭። በዘመነ መንግሥቱ እግዚአብሔር
እየረዳው ታላላቅ ሥራዎችን በማከናወኑ ስመ ጥር ነበር። ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ እስራኤልን ሲያጠቁ የነበሩትን
ፍልስጥኤማውያንን አሸንፏል። ፪ኛ ሳሙ ፭፥፲፰-፳፭። አሕዛብን በማስገበር ሀገሩን አስፍቷል። ፪ኛ ሳሙ ፰፥፲፪።
ኢየሩሳሌም የተባለችውን የተመሸገች ከተማ ወርሮ ኢያቡሳዊያንን አሸንፎ መናገሻ ከተማ አድርጓታል፤ በዚህም ምክንያት
የዳዊት ከተማ ተብላለች። ፪ኛ ሳሙ ፭፥፩-፲። ታቦተ ጽዮንንም ወደዚያ በማምጣት፦ መሥዋዕት የሚሠዋባት፥ አምልኮት
የሚፈጸምባት መንፈሳዊ ሥፍራ እንድትሆን ለዚህ ክብር አብቅቷታል። የመቅደሱንም ሥርዓት አሻሻሏል። ፪ኛ ሳሙ ፮፣ ፩ኛ
ዜና ፳፰፥፫። ብዙ መዝሙራትንም ጽፏል። ዳዊት ታላቅና ገናና፥ መንፈሳዊም በመሆኑ መንግሥቱ ለክርስቶስ መንግሥት
ምሳሌ ሆኖአል። ፪ኛ ሳሙ ፯፥፰ ፣ ኢሳ ፱፥፯ ፣ ኤር ፳፫፥፭ ፣ ፴፫፥፲፬ ፣ ሕዝ ፴፬፥፳፫ ፣ ፴፯፥፳፬።
፪፥፪፦ ዳዊት ትንቢት ስለተነገረለትም ነው፤
ትንቢት
ለሌሎችም የተነገረ ቢሆንም የዳዊት ግን ይበዛል። «እግዚአብሔር ለዳዊት እንዲህ ሲል በእውነት ማለ፤ አይጸጸትምም ፥
ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁና፤ ልጆችህ ኪዳኔን፥ ይህንንም የማስተምራቸውን ምስክሬን ቢጠብቁ ፥
ልጆቻቸው በዙፋንህ ላይ ለዘለዓለም ይቀመጣሉ።» ይላል። ፻፴፩፥፲፩። ይህ ትንቢት ለጊዜው ለሰሎሞን ሲሆን ለፍጻሜው
ለጌታ ነው። ትርጉሙም ከባሕርይህ የተከፈለ ልጅህን ክርስቶስን በዙፋንህ አስቀምጥልሃለሁ ሲለው ነው። የመላእክት
አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፦ እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባበሠራት ጊዜ፦ «እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን
የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤» ያለው ለዚህ ነው። ሉቃ ፩፥፴፪። ነቢዩ ኢሳይያስም፦ «ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ
ልጅም ተሰጥቶናልና፤» ካለ በኋላ «በዳዊት ዙፋን መንግሥቱ ትጸናለች፤ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም፤» ብሏል። ኢሳ
፱፥፮። በተጨማሪም፦ «ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ አበባም ከግንዱ ይወጣል፤» ብሏል። ኢሳ ፲፩፥፩። ትርጉሙም፦
ከነገደ እሴይ (ከዳዊት ወገን) በትረ ሕይወት እመቤታችን ትወለዳለች፥ ከእርሷም አበባ ክርስቶስ ይወለዳል ማለት
ነው። ነቢዩ ኤርምያስም፦ «እነሆ ለዳዊት የጽድቅ ቊጥቋጥ አበቅልለታለሁ፤ እርሱም ፍርድንና ጽድቅን በምድር
ያደርጋል፤» የሚል አለ። ኤር ፴፫፥፲፬። ትርጉሙ ካለፈው ጋር አንድ ነው፥ አይለወጥም። በትንቢተ ሕዝቅኤል ላይ
ደግሞ፦ «በላያቸውም አንድ እረኛ አቆማለሁ፤ እርሱም ባሪያዬ ዳዊት ነው፤ እረኛም ይሆናቸዋል።» ተብሎ ተነግሯል።
በተጨማሪም፦ «ባሪያዬም ዳዊት በላያቸው ንጉሥ ይሆናል፤ ለሁሉም አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል፤ በፍርዴም ይሄዳሉ፥
ትእዛዜንም ይጠብቃሉ፤ ያደርጓትማል።» ይላል። ሕዝ ፴፯፥፳፬። ሕዝ ፴፬፥፳፫።ይህም ለፍጻሜው ለክርስቶስ የተነገረ
ቃለ ትንቢት ነው። ይኽንንም የትንቢቱ ባለቤት ራሱ ኢየሱስ ክርሰቶስ፦ «መልካም እረኛ እኔ ነኝ መልካም እረኛ
ስለበጎቹ ነፍሱን ይሰጣል። . . . . . እረኛው አንድ መንጋውም አንድ ነው፤» በማለት ነግሮናል። ዮሐ
፲፥፲፩፣፲፮።
፪፥፫፦ አብርሃም ሥርወ ሃይማኖት ስለሆነ ነው፤
አብርሃም፦
እግዚአብሔርን ያገኘው በሥነ ፍጥረት ተመራምሮ ነው። አብርሃም የኖረው የጣኦት አምልኮት በተስፋፋባት በካራን ነው።
ካራን፦ በነነዌና በኤፍራጥስ ወንዝ መካከል የነበረ ከተማ ነው። የአብርሃም አባት ታራ ጣዖት እየሠራ ይሸጥ ይለውጥ
ነበር። ይህም ልማድ ከአያቱ ከሴሩሕ ጀምሮ ተያይዞ የመጣ ነው። ሴሩሕ ናኮርን ወለደ፥ ናኮር ታራን ወለደ፥ታራ
ደግሞ አብርሃምን ወለደ። ኩፋሌ ፲፥፳፮-፴።
፪፥፫፥፩፦ አብርሃም የጣዖት አምልኮትን ተቃወመ፤
አብርሃም
ከልጅነቱ ጀምሮ፦ ጣዖታቱን በመከተልና ኃጢአትን በመሥራት እንደሚሳሳት የምድርን ስሕተት ያውቅ ነበር። አባቱም
መጽሐፍ አስተምሮታል፤ የሁለት ሱባዔ ዓመት ልጅ በነበረ ጊዜም ለጣዖት እንዳይሰግድ አባቱን ከመከተል ተለየ። ከሰዎች
ልጆች ስሕተትም ያድነው ዘንድ፥ ዕጣውም ርኲሰትንና ፌዝን በመከተል ወደ ስሕተት እንዳይሆን ሁሉን ወደ ፈጠረ ወደ
እግዚአብሔር ይጸልይ ጀመር። ኩፋሌ ፲፥፴፩-፴፫።
አብርሃም
አባቱን ታራን፦ «ምንት ተድላ ወረድኤት ለነ አባ፤ አባቴ ሆይ፥ ከእነዚህ ከጣዖታቱ ለእኛ ምን ረድኤትና ደስታ
አለን?» አለው። ታራም አብርሃምን፦ «ልጄ፥እኔም እንደማይረባንና እንደማይጠቅመን አውቃለሁ፤ ነገር ግን የዚህ ሀገር
ሰዎች በፍቅረ ጣዖት የሰከሩ ስለሆኑ እንዳያጠፉን ፈርቼ ነው፤» <እንደ ወንዙ ይሻገሩ፥ እንደ ሀገሩ
ይኖሩ፤> ብዬ ነው፤» አለው። ኩፋሌ ፲፥፵፪-፵፭።
ታራ፦
እንጨት ጠርቦ ፥ደንጊያ አለዝቦ ጣዖት ከሠራ በኋላ፥ አብርሃምን፦ «ወደ ገበያ ሒደህ ሸጠህ ና፤» አለው።
አብርሃምም በመንገድ ሳለ፦ «አፍ እያለው የማይናገር፥ እጅ እያለው የማይዳስስ፥ እግር እያለው የማይራመድ ይህ
ምንድነው?» አለ። ከገበያውም ገብቶ፦ «አፍ እያለው የማይናገር እጅ እያለው ያማይዳስስ፥ እግር እያለው የማይራመድ
ጣዖት ግዙ፤» አላቸው። «ባለቤት ያቀለለውን ገንዘብ ባለዕዳ አይቀበለውም፤» እንዲል፦ «እርሱ እንዲህ እያለ
ያራከሰው ለእኛ ምን ይረባናል?» ብለው የማይገዙት ሆኗል።
አብርሃም
ጣዖቱን ይዞ ወደ ቤቱ ሲመለስ፦ «ርቦኛል አብላኝ፥ ጠምቶኛል አጠጣኝ፤» ቢለው የማይመልስለት ሆነ። ሁለተኛም፦
«የደከመው ሰው ቢያጫውቱት ይበረታልና አጫውተኝ፤» ቢለው ዝም አለው። በመጨረሻም፦ «ይህስ ፍጡር ነው እንጂ ፈጣሪዬ
አይደለም ድዳ ነው፥ ልቡናንም የሚያስት ነው፤ ፈጣሪዬ ሌላ ነው፤» ብሎ ከትከሻው አውርዶ በደንጊያ ቀጠቀጠው።
፪፥፫፥፪፦ አብርሃም ፈጣሪውን ፈለገ፤
አብርሃም
ፈጣሪውን ለማግኘት ባደረገው ጉዞ ፍጥረታትን ይመለከት፥ ይመረምር ጀመር። ተራራውን ከፍ ብሎ ቢያየው፦ «አምላክስ
ይህ ነው፤» አለ። ይህንንም፦ አንዱ ተራራ ሌላውን ሲበልጥ አይቶ፦ «በፈጣሪ መብለጥ መበላለጥ የለበትም፥ ስለዚህ
ይህም አምላክ አይደለም፤» አለ። ሁለተኛም ነፋስ፦ ባሕር ሲገሥጽ፥ ዛፍ ሲያናውጥ አይቶ፥ «አምላክስ ይህ ነው፤»
አለ። ነፋስንም፦ ተራራ ሲገታው፥ መዝጊያ ሲመልሰው አይቶ፦ «ፈጣሪንስ የሚገታው የለም፥ ይህም አምላክ አይደለም፤»
አለ። ሦስተኛም፦ የባሕሩን ማዕበልና ሞገድ አይቶ «አምላክስ ይህ ነው፤» አለ። ባሕርም ሲሞላና ሲጐድል አይቶ፦
«በፈጣሪስ ሕፀፅ (ጉድለት) የለበትም ፥ ይህም አምላክ አይደለም፤» አለ። አራተኛም፦ እሳት፦ ደረቁን ከርጥቡ ለይቶ
ሲበላ፥ ቋያውን ሲያቃጥል አይቶ፦ «አምላክስ ይህ ነው፤» አለ። እርሱንም ውኃ ሲያጠፋው፥ መንገድ ሲከለክለው
አይቶ፦ «ይህም አምላክ አይደለም፤» አለ። አምስተኛም፦ ፀሐይ በዓለሙ መልቶ ሲያበራ አይቶ፦ «አምላክስ ይህ ነው፤»
ብሏል። እርሱም፦ በምሥራቅ ወጥቶ በምዕራብ ሲገባ አይቶ «በፈጣሪስ መውጣት መግባት የለበትም፥ ቀን ቢመግበን ማታ
ማን ይመግበናል? ለዚህም ፈጣሪ አለው፤» አለ። ከዚህ በኋላ፦ «አምላከ ፀሐይ ተናበበኒ፤ የፀሐይ አምላክ
አነጋግረኝ፤» ብሎ ጮኸ። እግዚአብሔርም ድምፁን አሰምቶታል፤ አንድም መልአከ እግዚአብሔር ተገልጦለት፦ «እነዚህ ሁሉ
ፍጡራን ናቸው ፥ የፈጠራቸው አለ፤» ብሎታል። አብርሃምን ሥርወ ሃይማኖት ያሰኘው ይህ ነው። አብርሃም ፈጣሪውን
በማግኘቱ ፥ በሌሊት ተነሥቶ፥ የጣዖታቱን ቤት በውስጡ ያለውንም ዕቃ ሁሉ አቃጠለ። እንዲህ ማድረጉንም ያወቀ ሰው
የለም፤ ወንድሙ አራን ግን ጣዖታቱን አድናለሁ ብሎ ከእሳቱ ገብቶ፥ ተቃጥሎ ሞቷል። ኩፋ ፲፩፥፩-፫።
አብርሃም፦
እግዚአብሔርን ፈልጎ ካገኘ በኋላ በጣዖት መንደር እንዲኖር አልተፈቀደለትም። «ፃእ እምድርከ ወእምአዝማዲከ
ወእምቤተ አቡከ፤ ወሑር ውስተ ምድር እንተ አርእየከ። ወእሬስየከ ሕዝበ ዐቢየ ወእባርከከ፤ ወአዐቢ ስመከ፥ ወትከውን
ቡሩከ፤ ወእባርኮሙ ለእለ ይባርኩከ፥ ወእረግሞሙ ለእለ ይረግሙከ። ከአባትህ ወገን ከዘመዶችህ ተለይተህ ከአገርህ
ውጣ፤ እኔ ወደማሳይህ ወደ ከነዓንም ሂድ። ብዙ ወገን አደርግሃለሁ፥ አከብርሃለሁ፤ ስምህንም
አከብረዋለሁ፥አገነዋለሁ፥አበ ብዙኃን እንድትባል አደርግሃለሁ። የሚመርቁህን እመርቃቸዋለሁ፥የሚረግሙህን ሰዎች
አጠፋቸዋለሁ፤» ተብሏል። አብርሃምም በፍጹም ሃይማኖት፦ ከዘመዶቹ ተለይቶ ከሀገሩ ወጥቷል፥ እግዚአብሔርን አምኖ
ወደማያውቀው ሀገር ተጉዟል። ዘፍ ፲፪፥፩-፫። እግዚአብሔር ጠርቶናል፥ እግዚአብሔርን እናገለግላለን የምንል ሰዎች
ከአብርሃም ተምረን ከመንደር ልንወጣ ማለትም ከዘረኝነት ልንላቀቅ ይገባናል፤ መንፈሳዊ ሆነናል ካልን በኋላም የሥጋ
ዝምድና ከመቊጠር ልንጠበቅ ያስፈልገናል። ለሃይማኖት ሰው ሁሉ አገሩ፥ ሁሉ ወገኑ ነውና።
አብርሃም
የመቶ ዓመት ሽማግሌ ከሆነ በኋላ ከቃል ኪዳን ሚስቱ እድሜ ከተጫናት (ዘጠና ዓመት ከሞላት) ከሣራ ይስሐቅን
የወለደው በሃይማኖት ነው። በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገኑ ሥላሴን በድንኳኑ ባስተናገደ ጊዜ፦ «ሶበ ገባእኩ
እመጽእ ኀቤከ አመ ከመ ዮም ትረክብ ሣራ ወልደ፤ እንደ ዛሬ ጊዜ ተመልሼ በረድኤት ወደ አንተ በመጣሁ ጊዜ ሣራ
ወንድ ልጅን ትወልዳለች፤» የተባለውን በሃይማኖት ተቀበለ። ተስፋውን የሰሙት ሐምሌ ሰባት ቀን ነው፤ በተነገራቸው
ተስፋ መሠረት ይስሐቅ የተፀነሰው በመስከረም ልደቱ ደግሞ በሰኔ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፦ የአብርሃምን
ሃይማኖት ሲመሰክር፦ «ስለዚህም እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሩ የሰጠው ተስፋ የታመነ ይሆን ዘንድ፥ የሚጸድቁ
በእምነት እንጂ የኦሪትን ሥራ በመፈጸም ብቻ እንዳይደለ ያውቁ ዘንድ እግዚአብሔር ጽድቅን በእምነት አደረገ።
ለብዙዎች አሕዛብ አባት አደርግሃለሁ ተብሎ እንደተጻፈ ሙታንን በሚያስነሣቸው፥ የሌሉትንም እንዳሉ በሚያደርጋቸው
በአመነበት በእግዚአብሔር ፊት አብርሃም የሁላችን አባት (የሃይማኖት አባት፥ የሃይማኖት ሥር፥ የሃይማኖት መሠረት)
ነው። አብርሃም ዘርህ እንዲህ ይሆናል ብሎ እግዚአብሔር ተስፋ እንደሰጠው ተስፋ ባልነበረ ጊዜ የብዙዎች አሕዛብ
አባት እንደሚሆን አመነ። አብርሃም የመቶ ዓመት ሽማግሌ ስለሆነ እንደ ምውት (እንደ ሬሣ) የሆነውን የራሱን ሥጋና
የሳር ማኅፀን ምውት (ሙቀት ልምላሜ የተለየው) መሆኑን እያየ በእምነት አልተጠራጠረም፤ በእምነት ጸና እንጂ፤
ለእግዚአብሔርም ክብርን ሰጠ። እግዚአብሔርም የሰጠውን ተስፋ ሊያደርግለት እንደሚችል በፍጹም ልብ አመነ።»ብሏል።ሮሜ
፬፥፲፮-፳፮።
የአብርሃም
እምነት በነገር ሁሉ ነው፤ አብርሃም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት በነበረ ጊዜ እግዚአብሔር ተገልጦለት፦ «በፊትህ የሄድሁ
ፈጣሪህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ በፊቴ መልካም አድርግ፤ ንጹሕም ሁን፤ ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል
አጸናለሁ፤ እጅግም አበዛሃለሁ፤» አለው። አብርሃምም በግንባሩ ወደቀ፤ (ሰገደ)፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን፦ አንተ
ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቃለህ፤ አንተም ከአንተም በኋላ ዘርህ በትውልዳቸው። በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም
በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቋት ቃል ኪዳኔ ይህች ናት፤ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። የሰውነታችሁን ቊልፈት
ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል። ሕፃኑንም በስምንተኛው ቀን
ትገርዙታላችሁ፤» አለው። ዘፍ ፲፯፥፩-፱። አብርሃም ይህን ሥርዓተ ግዝረት የተቀበለው በእምነት ነው። በመሆኑም
ወዲያው በቤተሰቦቹ ላይ ተግባራዊ አድርጐታል። እርሱም ራሱ በዘጠና ዘጠኝ ዓመቱ ተገዝሯል። ዘፍ ፲፯፥፳፫። ይህም
የእምነት ምልክት ሆኖ እስከ ጥምቀተ ክርስትና አድርሷል። ምክንያቱም ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነበርና ነው። ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እግዚአብሔር አብርሃምን ሳይገዘር በእምነት እንደ አጸደቀው በእርሱ ላይ ይታወቅ ዘንድ ግዝረትን
የጽድቅ ማኅተም ትሆነው ዘንድ ምልክት አድርጎ ሰጠው፤» ብሏል። ሮሜ ፬፥፲፩። በቈላስይስ መልእክቱም፦ «የኃጢአትን
ሰውነት ሸለፈት በመግፈፍ በክርስቶስ መገረዝ በሰው እጅ ያልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ። በጥምቀትም
ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል፤ በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር
ተነሥታችኋል።» በማለት ተናግሯል። ቈላ ፪፥፲፩።
አብርሃም
ልጁ ይስሐቅን በመሠዊያ ላይ አጋድሞ ሊሠዋው እጁን ያነሣው በእምነት ነው። «እኔ ለእግዚአብሔር ብዬ ስሠዋው፥
እግዚአብሔር ደግሞ ለእኔ ብሎ ከሞት አሥነስቶ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል ያለኝን ቃል ኪዳኑን ይፈጽምልኛል፤» ብሎ
አምኗል። ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «አብርሃምም እግዚአብሔር በፈተነው ጊዜ ልጁን ይስሐቅን ይሠዋው ዘንድ
በእምነት ወሰደው። በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል ብሎ ተስፋ ያናገረለትን አንድ ልጁን አቀረበው። እግዚአብሔር ከሙታን
ለይቶ ሊያስነሣው እንደሚችል አምኖአልና፤» በማለት ተናግሯል። ዕብ ፲፩፥፲፯-፲፱።
፪፥፫፥፫፦ አብርሃምም ትንቢት ተነግሮለታል፤
እግዚአብሔር፦
አብርሃምን፦ «ከሀገርህ ውጣ፥ ከዘመዶችህም ተለይ፤» ባለው ጊዜ፦ «የምድር አሕዛብ በአንተ ይባረካሉ፤ (አብርሃምን
ያከበረ ያክብርህ እያሉ በአንተ ይመራረቃሉ)፤» ብሎታል። ዘፍ ፲፪፥፫። ይህም፦ በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን
የሚያድል፥ መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን የሚያጠፋ አምላክ ኢየሱስ ክርሰቶስ ከእርሱ ወገን እንደሚወለድ የሚያመለክት
ቃለ ትንቢት ነበር። እግዚአብሔር በአንድነት በሦስትነት ለአብርሃም ተገልጦ ወደ ድንኳኑ በገባ ጊዜም፦ «የዛሬ
ዓመት እንደ ዛሬው ወደ አንተ ተመልሼ እመጣለሁ፤» ብሎታል። ይህም ለጊዜው ይስሐቅ እንደሚወለድ የሚገልጥ ቃለ
ትንቢት ሲሆን ለፍጻሜው ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ ወገን ማለትም የባሕርዩ መመኪያ ከሆነች ከእመቤታችን ከቅድስት
ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ እንደሚወለድ የሚያጠይቅ ነበር። ዘፍ ፲፰፥፲።
፫፦ «እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ፤» . . . .
ነገረማርያም ክፍል፦ ፲፪
ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ፦ በዘር በሩካቤ የተወለዱ የአበውን ልደት ሲናገር ከመጣ በኋላ፦ «የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንዲህ ነው፤» በማለት፦ ልደቱ ልዩ መሆኑን ተናግሯል። ምስጢረ ልደቱን ሲያብራራም፦
«ወሶበ ተፍኅረት እሙ ማርያም ለዮሴፍ፥ ዘእንበለ ይትቃረቡ ተረክበት ፅንስተ እንዘ ባ ውስተ ማኅፀና እመንፈስ
ቅዱስ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ፥ ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች።» ብሏል። በዚህም
የእመቤታችን ፅንሷ እንደሌሎች ሴቶች በዘር በሩካቤ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ግብር መሆኑን መስክሯል።
፩፥፩፦ የእመቤታችን እና የቅዱስ ዮሴፍ ዝምድና፤
ቅዱስ
ዮሴፍ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የቅርብ ዘመዷ ነው። ቅዱስ ማቴዎስ የአበውን ልደት እየተናገረ መጥቶ
ወደ መጨረሻው ላይ፦ «አልዓዛርም ማትያንን ወለደ፤ ማትያንም ያዕቆብን ወለደ። ያዕቆብም ክርስቶስ የተባለ ጌታ
ኢየሱስ ከእርሷ የተወለደ የማርያምን እጮኛ ዮሴፍን ወለደ።» ብሏል። ለቅዱስ ዮሴፍና ለእመቤታችን የሥጋ ዝምድና
ግንዱ አልዓዛር ነው። አልዓዛር የወለደው ማትያንን ብቻ ሳይሆን ቅስራንም ነው። ቅስራ ቅዱስ ኢያቄምን ወለደ፤ ቅዱስ
ኢያቄም ደግሞ እመቤታችንን ወለደ። ዝምድናቸው የሦስት ትውልድ ነው። ለሁለቱም ቅድመ አያታቸው አልዓዛር ነው።
አልዓዛር፤
ማትያን ፤ ቅስራ፤
ያዕቆብ፤ ኢያቄም፤
ዮሴፍ ፤ ድንግል ማርያም፤
በዕብራዊያን
ልማድ ሴትንና ወንድን ቀላቅሎ ትውልድ መቁጠር ሥርዓት አይደለም። በመሆኑም፦ ቅዱስ ማቴዎስ «ሥርዓት አፈረሰ፤»
ይሉኛል፥ ብሎ የጌታን ልደት ስለ ዝምድናቸው በዮሴፍ በኲል ቆጥሯል፥ እርሷም እንዳትቀር በቅጽል አምጥቷታል።
፪፦ እመቤታችን ለምን ለዮሴፍ ታጨች?
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም ለዮሴፍ የመታጨቷን ነገር መናፍቃን በመንፈስ ሳይሆን በሥጋ አፈታት ፈት ተው (ተርጉመው)
ስለሚያስተምሩ፦ የእንቅፋት፥ የመሰናከያ ድንጋይ ሆኖባቸዋል። ከመናፍቅነት የጸዱ ምዕመናን ደግሞ መናፍቃኑ በሚሉት
ባይስማሙም የኅሊና ጥያቄ ስለሚሆንባቸው መልስ ይፈልጋሉ። ለዚህም የማያዳግም መልስ የሚሆ ነው፥ አባቶቻችን
በአፍም በመጽሐፍም ያስተማሩት ትምህርት ነው ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከጥንተ አብሶ ነጻ ሆና
የተፈጠረችው፥ ከማኅፀን ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ የተጠበቀችው፥ አሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ የኖረ ችው፥ ሰማያዊ
ምግብ የተመገበችው፥ በቅዱሳን መላእክት የተገለገለችው፥ ለአምላክ እናትነት ነው። ይህ እንዲህ ከሆነ ለምን ለዮሴፍ
ታጨች?
፪፥፩፦ ኃይል አርያማዊት እንዳይሏት ነው፤
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም፦ ሰማይና ምድር የማይወስኑትን፥ ዓለምን በእጁ መዳፍ የያዘውን፥ መንበሩ እሳት፥ መጋረጃው
እሳት፥ አጋልጋዮቹ እሳት፥ መለኰታዊ ባሕርዩም እሳት የሆነውን አምላክ በማኅፀኗ መሸከሟ ከሰው አእምሮ በላይ ነው።
ምክንያቱም፦ እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ፥ በተዋሕዶ ሰው ሁኖ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣልና ነው።
በመሆኑም፦ «በሰው አቅም እንዴት ይቻላል? ኃያላን የሚባሉ ኪሩቤል እንኳን እሱን ሳይሆን፥ የሚሸከሙት የእሳቱን
መንበር ነው፤ ሱራፌልም የሚያጥኑት እርሱን ሳይሆን፥ የእሳቱን መንበር ነው፤ በዚህም ላይ ፊቶቻቸውንም እግሮቻቸውንም
ይሸፍናሉ፤» እያሉ፥ የእመቤታችንን ከሰው ወገን መሆን የሚጠራጠሩ፥ «ኃይል አርያማዊት (ሰማያዊት ኃይል)» የሚሉ
ሰዎች እንደሚመጡ እግዚአብሔር ያውቃል። በማወቁም፦ የሰው እጮኛ እንድትሆን ሳይሆን እንድትባል አድርጓል። ይኸውም፦
«ለሰው መታጨቷ ከሰው ወገን ብትሆን ነው፤» ለማሰኘት ነው።
፪፥፪፦ የጌታን ጽንስ ከአጋንንት ለመሰወር ነው፤
አጋንንት፦
የሰውን ጥፋቱን እንጂ ድኅነቱን አይሹም፤ ጥንትም፦ እግዚአብሔርን ያህል አባት፥ ገነትን ያህል ርስት ያሳጡት
እነርሱ ናቸው። የሰውን ልጅ ከአባቱ ለይተውት፥ ከርስቱ ነቅለውት፥ እስከ ልጅ ልጆቹ፥ በእጃቸው ጨብጠው፣ በእግራቸው
ረግጠው በሲኦል ገዝተውታል፤ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ባለ ዕዳ አድረገው አሰቃይተውታል። የጌታ ወደዚህ
ዓለም መምጣት ደግሞ ይኽንን ሁሉ ለመሰረዝ ነው፤ የሰውን ልጅ ከአጋንንት ቁራኝነት አላቅቆ ከሲኦል ለማውጣት፥ ከሞት
ወደ ሕይወት ለማሸጋገር፥ ወደ ጥንተ ርስቱ ገነት ለመመለስ ነው።
አጋንንት፦
የጌታን በመንፈስ ቅዱስ ግብር መፀነስ ሰምተውት ወይም አውቀውት ቢሆን ኖሮ፥ «ይህ ሳይሆን አይቀርም፤» እያሉ
የብዙ ሴቶችን ጽንስ ባበላሹ ነበር። ለምሳሌ፦ በልደቱ ጊዜ፥ በሄሮድስ አድረው፥ አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ
ሕጻናትን ያሳረዱት ከእነዚያ መካከል ሕፃኑ ኢየሱስ አይጠፋም በሚል ግምት ነው። ማቴ ፪፥፲፮። በመሆኑም አመቤታችን
የዮሴፍ እጮኛ እንድትባል አድርጎ፥ በመንፈስ ቅዱስ ግብር የሆነ ፅንሱን ከአጋንንት ሰውሮባቸዋል።
፪፥፫፦ ከርስት ገብቶ እንዲቆጠርላት ነው፤
በእስራኤል
ከርስት ገብቶ የሚቆጠረው ወንድ ብቻ ነው፥ ሴቶቹ ግን በወንዱ ሥር ሆነው ከርስት ገብተው ይቆጠራሉ። «በዚያም
ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሰው ሁሉ ይቈጠር ዘንድ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣ። ቄሬኔዎስ ለሶርያ መስፍን በነበረ ጊዜ
ይህ የመጀመሪያ ቈጠራ ሆነ። ሰው ሁሉ ሊቈጠር ወደየከተማው ሄደ። ዮሴፍም ከገሊላ አውራጃ ከናዝሬት ከተማ ወደ
ይሁዳ፥ ቤተልሔም ወደምትባለው ወደ ዳዊት ከተማ ወጣ፤ እርሱም ከዳዊት ሀገርና ከዘመዶቹ ወገን ነበርና። ፀንሳ ሳለች
ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይቈጠር ዘንድ ሄደ።» እንዲል፦ ከርስት ገብቶ ሊቆጠርላት እግዚአብሔር ባወቀ እጮኛዋ
ተባለ። ሉቃ ፪፥፩-፭።
፪፥፬፦ በመከራ ጊዜ እንዲከተላት ነው፤
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም፦ በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት ብዙ መከራ እንደሚያጋጥማት በእርሱ ዘንድ አስቀድሞ
የታወቀ ነው። በመሆኑም በሄሮድስ አሳዳጅነት፥ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በረሀ ለበረሀ በስደት በምትንከራተትበት ጊዜ፥
የሚከተላት፣ የሚያገለግላት ሰው ያስፈልጋታል። ይህም ሰው የሥጋ ዘመዷ የሆነ፥ እጮኛዋ የተባለ፥ አረጋዊው ዮሴፍ
ነው። «እነርሱም (ሰብአ ሰገል) ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ፥ ሄሮድስ ሕፃኑን
ሊገድለው ይሻዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ምድረ ግብጽ ሽሽ፤ እስከምነግርህም ድረስ በዚያ ኑር
አለው፤» እንዲል፦ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ እርሷን እያገለገለ አብሯት ተንከራትቷል። «እርሱም በሌሊት ተነሥቶ
ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ ግብፅ ሄደ። ከእግዚአብሔር ዘንድ፥ ልጄን ከግብፅ ጠራሁት ተብሎ በነቢይ (በነቢዩ
በሆሴዕ) የተነገረው ይፈፀም ዘንድ፤ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ።» ይሏል። ማቴ ፪፥፲፫-፲፭፣ ሆሴ
፲፩፥፩።
፪፥፭፦ በደንጊያ ከመገደል ሊያድናት ነው፤
በኦሪቱ
ሕግ ሴት ልጅ ከሕጋዊ ጋብቻ ውጪ ጸንሳ ስትገኝ፥ በአደባባይ ተፈርዶባት፥ በደንጊያ ተቀጥቅጣ ትገደላለች። ወንድም
ቢሆን፦ «አመነዘረ፤» ተብሎ ሕጉ ይፈጸምበታል። «ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ወይም ከባልንጀራው ሚስት ጋር
ቢያመነዝር አመንዝራውና አመንዝራይቱ ፈጽሞ ይገደሉ።» ይላል። ዘሌ ፳፥፲። በተጨማሪም፦ «ለወንድ የታጨች ድንግል
ልጅ ብትኖር፥ ሌላ ሰውም በከተማ ውስጥ አግኝቶ ከእርሷ ጋር ቢተኛ፥ ሁለቱን ወደዚያች ከተማ በር አውጧቸው፤
ብላቴናይቱ በከተማ ውስጥ ሳለች አልጮኸችምና፥ ሰውዬውም የባልንጀራውን ሚስት አስነውሯልና በድንጋይ ወግረው
ይግደሏቸው፤ እንዲሁ ክፉውን ነገር ከውስጥህ ታስወግዳለህ።» የሚል አለ። ዘዳ ፳፪፥፳፫።
ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ ጽንሰቱን (በመንፈስ ቅዱስ ግብር መሆኑን) ከአይሁድም
ሰውሮባቸዋል። በመሆኑም፦ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፥ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ፀንሳ በተገኘችበት ወራት፥
በስመ እጮኛ አረጋዊ ዮሴፍ በአጠገቧ ባይኖር ኖሮ፥ ሕገ ኦሪትን ለመፈጸም ብለው በደንጊያ ቀጥቅጠው ይገድሏት ነበር።
፪፥፮፦ ከስድብ ከነቀፋ ሊያድናት ነው፤
በእስራኤል
አንዲት ድንግል ሳትታጭ ከቆየች፥ ሁሉ ይሰድባታል፥ ሁሉ ይነቅፋታል፤ እንደ አገራችን ባሕል፦ «ቆማ የቀረች፥ ፈላጊ
ያጣች፤» ትባላለች። ምክንያቱም ለጋብቻ መታጨት፥ ለቁም ነገር መፈለግ፥ የጨዋነት ምልክት ነውና። በመሆኑም ያጨም፥
የታጨችም በሰው ዘንድ ክብር አላቸው። እንዲህ ካልሆነ ግን በቀጥታም ሆነ በአሽሙር የሚጐነትላቸው ይበዛል።
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም፦ ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ አድሮባት በሚኖር መንፈስ ቅዱስ ተጠብቃ፥ በእሳታውያን መላእክት
ተከብባ፥ በክንፎቻቸውም ተሸፍና የምትኖር ለእግዚአብሔር እናትነት የተመረጠች፥ የተቆለፈች፥ ተቆልፋም ለዘለዓለሙ
የምትኖር፥ እግዚአብሔር ብቻ ሳይከፍት ገብቶ ሰይከፍት የሚወጣባት፥ ሰው የማይገባባት፥ የእግዚአብሔር ቤተ መቅድስ
ናት። ቅዱስ ኤፍሬም፦ በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ ፣ በእሑዱ ክፍል፦ «በእግዚአብሔር ሥዕል የተሣሉ ኪሩቤል የሚጋርዱሽ
መቅደስ አንቺ ነሽ፤» ያለው ለዚህ ነው።
በቅዳሜውም ክፍል፦ «የማትፈርሽ መቅደስ ነሽ፤» ብሏታል። ቅዱስ ዳዊትም፦ «እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታልና፥
ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዷታልና፤ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት፤መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ።» በማለት
ትንቢቱን አስቀድሞ ተናግሯል። መዝ ፻፴፩፥፲፫። ነቢዩ ሕዝቅኤልም፦ «ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው ወደ መቅደሱ በር
መለሰኝ፤ ተዘግቶም ነበር። እግዚአብሔርም፦ ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም፤ ሰውም አይገባባትም፤
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶባታልና ተዘግታ ትኖራለች፣አለኝ፤» ብሏል።ሕዝ ፵፬፥፩-፪። በመሆኑም፦ ሰዎች
እመቤታችንን፦ በሥጋ ምኞት እንዳያስቧት ኀሊናቸውን ጠብቆላታል። ይኽንን በተመለከተ አባ ሕርያቆስ፦ መንፈስ ቅዱስ
በገለጠለት በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ፦ «ድንግል ሆይ፥ የሚያታልሉ ጎልማሶች ያረጋጉሽ አይደለሽም፥
የሰማይ መላእክት ጎበኙሽ እንጂ፤ (ተድላ ዓለም ፥ ብዕለ ዓለም ፥ ያታለላቸው ፣አንድም አጋንንት በውዳሴ ከንቱ
የሚያታልሏቸው፥ አንድም በሎሚ በቀለበት የሚያታልሉ፥ አንድም ፈቃደ ሥጋቸው ያታለላቸው ወጣቶች ያረጋጉሽ አይደለሽም፤
መላእክት ጐበኙሽ፥ አጫወቱሽ እንጂ፤» ብሏል። ቊ ፵፫። በሌላ በኩል ደግሞ፥ እንደ ሌሎች ሴቶች መስላቸው ወደ
ነቀፋና ወደ ስድብ እንዳይሄዱ፥ ዘመዷን ዮሴፍን በአጠገቧ አስቀምጦላታል። ምክንያቱም፦ «ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ
የተባረክሽ ነሽ፤» የሚለውን ስለማያውቁት ነው፥ አንድም እግዚአብሔር ባወቀ ስለተሰወረባቸው ነው። የዮሴፍ እጮኝነት፥
ምሥጢር ለተሰወረባቸው አይሁድና ለአጋንንት ሌላ ነው፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ማደሪያውን የጠበቀበት ጥበብ ነው።
ቅዱስ ዳዊት፦ እግዚአብሔርን፦ «አቤቱ ሥራህ እጅግ ታላቅ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፤» ብሎታል። መዝ
፻፫፥፳፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «የእግዚአብሔር ባለጠግነት ፥ ጥበብና ዕውቀት እንዴት ጥልቅ ነው!» ብሏል።
ሮሜ፲፩፥፴፫።
፪፥፯፦ እንዲጠብቃት እንዲያገለግላት ነው፤
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም፦ ለዮሴፍ የታጨችበት ዋናው ዓላማ እንደ አባት ሊጠብቃት፥ እንደ አሽከር ሊያገለግላት ነው።
አንድም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ድንግል ማርያምን እንዲጠብቅ እንዲያገለግል ከብዙ አረጋውያን መካከል የተመረጠ
ታማኝ አገልጋይ ነው። አባ ሕርያቆስ፥ ከላይ እንደገለጥነው፥ መንፈስ ቅዱስ ገልጦለት፥ እመቤታችንን ባመሰገነበት
ድርሰቱ፥ በቅዳሴ ማርያም ላይ፦ «ድንግልሆይ፥ ለዮሴፍ የታጨሽ ለትዳር አይደለም፥ ንጹሕ ሆኖ ሊጠብቅሽ ነው እንጂ፤»
ያለው ለዚህ ነው። ቊ ፵፬።
ኢያሱ
ወልደ ነዌ፥ ሙሴን እንዲያገለግል በመታጨቱ (በመመረጡ) እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ (ሙሴ ከዚህ ዓለም እስኪለይ) ድረስ
አገልግሎታል። በመጽሐፉ መጀመሪያ ላይ፦ «እንዲህም ሆነ፤ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ ከሞተ በኋላ፥ እግዚአብሔር
የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው፤» ይላል። ኢያ ፩፥፩። ኢያቡር የተባለው የአብርሃም
ሎሌ፥ ጌታውን አብርሃምን እስኪሸመገል፥ ዘመኑም እስኪያልፍ ድረስ ታጥቆ አገልግሎታል። ዘፍ ፳፬፥፩። ሌዋውያን
ካህኑን አሮንን እንዲያገለግሉ እግዚአብሔር መርጧቸው ነበር። «እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ የሌዊን
ነገድ አቅርበህ ያገለግሉት ዘንድ በካህኑ በአሮን ፊት አቁማቸው፤» ይላል። ዘኁ ፫፥፭።
ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረን ማገልገልን ነው፤ ይኽንንም፦ «የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ
እመሕያው ክርስቶስ) ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ ሊያገለግሉት አልመጣምና፤» በማለት ነግሮናል።
ማር ፲፥፵፭። ይኽንን በተናገረበት አንቀጽ ላይ፥ ደቀመዛሙርቱንም፦ «ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ
የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤» ብሎአቸዋል። ማር ፲፥፵፫።
ከዚህም የምንማረው፥ መልዕልተ ፍጡራን ለሆነች ለአምላክ እናት ቀርቶ፥ ለሚመስለን ወንድማችን እንኳ ባሪያ መሆን
እንደሚገባ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ፤» ብሏል።
ገላ ፭፥፲፫። ስለራሱም ሲናገር፦ «እኔ ከሁሉ ይልቅ ነጻ ስሆን ብዙዎችን ወደ ሃይማኖት እሰበስባቸው ዘንድ እንደ
ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛሁ።» ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፱፥፲፱። ሐዋርያው ራሱን ባሪያ አድርጐ ያስገዛው ከእርሱ
ለሚያንሱት እንኳ ነው።
ስምዖን
የተባለው ቁርበት ፋቂ ቅዱስ ጴጥሮስን በቤቱ ተቀብሎ አገልግሎታል፤ የሐዋ ፲፥፵፮። በብሉይ ኪዳን ዘመንም
እግዚአብሔር ያዘጋጃት መበለት፥ የሰራፕታዋ ሴት፥ ነቢዩ ኤልያስን አገልግላዋለች። «የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ
መጣ፥ እንዲህም አለው፦ ተነሥተህ በሲዶና አጠገብ ወዳለችው ወደ ሰራፕታ ሂድ፤ በዚያም ተቀመጥ፤ እነሆም፥ ትመግብህ
ዘንድ አንዲት መበለት አዝዣለሁ፤» ይላል። ፩ኛ ነገ ፲፯፥፰። ሱናማዊቷም ሴት ነቢዩ ኤልሳዕን ቤት ሠርታ
እስከመስጠት ድረስ አገልግላዋለች። ሱናማዊቷ ሴት ባሏን፦ «ይህ በእኛ ዘንድ ሁልጊዜ የሚያልፈው (ነቢዩ ኤልሳዕ)
ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው እንደሆነ አውቃለሁ። ትንሽ ቤት በሰገነቱ ላይ እንሥራ፤ በዚያም አልጋና ጠረጴዛ፥ ወንበርና
መቅረዝ እናኑርለት፤ ወደእኛም ሲመጣ ወደዚያ ይግባ አለችው፤» ይላል። ፪ኛ ነገ ፬፥፱። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦
ቅዱሳንን ማገልገል እንደሚገባ ሲናገር፦ «ለቅዱሳን ስለሚሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት መላልሰው
ማለዱን። እነርሱ አስቀድመው በፈቃዳቸው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔርም፥ ለእኛም አሳልፈው
ሰጥተዋልና እኛ እንደአሰብነው አይደለም፤ ይህንም የቸርነት ሥራ እንደጀመረ ይፈጽምላቸው ዘንድ ቲቶን ማለድነው።
በሁሉም ነገር በእምነትና በቃል፥ በዕውቀትም፥ በትጋትም በእናንተ ዘንድ በሆነው ሁሉ እኛን በመውደዳችሁ ፍጹማን
እንደሆናችሁ፥ እንዲሁም ደግሞ ይህቺን ስጦታ አብዙ።» ብሏል። ፪ኛ ቆሮ ፰፥፬።
፫፦ ዮሴፍ የተመረጠበት መንገድ፤
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም፥ ለእናት ለአባቷ የስዕለት ልጅ ናት፤ ከዚያ በፊት መሐኖች ነበሩ። በዘመነ ኦሪት፦
የሕልቃና ሚስት ሐና፦ «ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፥ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፤» ብላ
እንደተሳለች፥ ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐናም ልጅ ቢሰጣቸው መልሰው ለእግዚአብሔር እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል። ፩ኛ
ሳሙ ፩፥፲፩። ከፍጥረት ሁሉ በላይ የከበረች ልጅ እንደሚወልዱም ሁለቱም በየራሳቸው በህልም ተረድተዋል።
እግዚአብሔርም፦ ህልማቸውን እስኪፈታላቸው፥ ስእለታቸውን እስኪፈጽምላቸው ድረስ መኝታ ለይተው ጾም ጸሎት ይዘዋል፤
ሱባኤም ገብተዋል።
ጊዜው
ሲደርስ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል መኝታቸውን አንድ እንዲያደርጉ ነግሯቸው፥ ነሐሴ ሰባት ቀን እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም ተፀነሰች። ይኽንንም አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ፦ «ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ
ደነስ ዘተፀነስኪ፥ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና
ወኢያቄም ተወለድኪ። ድንግል ሆይ፥ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፥ በሕግ በሆነ በሩካቤ ከሐና ከኢያቄም
ተወለድሽ እንጂ።» በማለት ተናግሯል። ቊ ፴፰። የተወለደችውም ግንቦት አንድ ቀን ነው።
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት ሲሞላት፥ «አባ፥ እማ» ማለት ስትጀምር፥ ወስደው ለቤተ እግዚአብሔር
ሰጥተዋታል። ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ ነበር፤ እርሱም፦ ከፀሐይ ይልቅ የጠራች፥ ከጨረቃ ይልቅ የደመቀች፥ ይህችን
የመሰለች ልጅ፥ «ምን አበላታለሁ? ምን አጠጣታለሁ? ምን አለብሳታለሁ? ምን አነጥፍላታለሁ? ምንስ እጋርድላታለሁ?»
ብሎ ሰው ሰውኛውን ሲጨነቅ፥ መልአኩ ቅዱስ ፋኑኤል ከሰማይ ወርዶ፥ አንድ ክንፉን አነጠፈላት፥ በአንድ ክንፉ ደግሞ
ጋረዳት። ኅብስት ሰማያዊ፥ ጽዋ ሰማያዊም መገባት። ይኽንንም በተመለከተ አባ ሕርያቆስ፦ «ኦ ድንግል፥ አኮ ኅብስተ
ምድራዌ ዘተሴሰይኪ፥ አላ ኅብስተ ሰማያዌ እምሰማየ ሰማያት ዘበሰለ፤ ኦ ድንግል አኮ ስቴ ምድራዊ ዘሰተይኪ፥ አላ
ስቴ ሰማያዊ እምሰማየ ሰማያት ዘተቀድሐ፤ ድንገል ሆይ፥ ምድራዊ ኅብስትን የተመገብሽ አይደለሽም፥ ከሰማየ ሰማያት
የበሰለ ሰማያዊ ኅብስትን ነው እንጂ፤ ድንግል ሆይ፥ ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለሽም፥ ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ
ሰማያዊ መጠጥን ነው እንጂ፤» ብሏል። ቅዳ ማርያም ቊ ፵። ይህም በግብር አምላካዊ የተገኘ ነው። ዘካርያስም የምግቧ
ነገር ከተያዘ ብሎ ወደ ቤተመቅደስ አስገብቷታል።
በቤተ
መቅደስ፦ መላእክት እየመገቧትና እያረጋጓት አሥራ ሁለት ዓመት ተቀምጣለች። በዚያም በአጭር ታጥቃ፣ ማድጋ ነጥቃ፣
ውኃ በመቅዳት፥ ሐርና ወርቅ እያስማማች በመፍተል መጋረጃ በመሥራት፥ በአገልግሎት ኖረች እንጂ በሥራ ፈትነት
አይደለም። ይህ ነገር በጎ ኅሊና የጐደላቸውን አይሁድን አላስደሰታቸውም። «ቤተ መቅደሳችንን ታረክስብናለች፤» ብለው
በቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ላይ በጠላትነት ተነሡባት። የእነርሱ ቤተ መቅደስ የሚፈርስ ቤተ መቅደስ ነው፤
ይኽንንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ
በዚህ አይቀርም፤ (ይህ ቤተ መቅደስ እንዲህ እንዳሸበረቀ አይቀርም፥ ይፈርሳል)፤» በማለት አድንቀው ለነገሩት
ለደቀመዛሙርቱ ነግሯቸዋል። ማቴ ፳፬፥፪። እንደተናገረውም የሮም ንጉሥ ጥጦስ ኢየሩሳሌምን በወረረ ጊዜ በ70 ዓም
ፈርሷል። እመቤታችን ግን ቅዱስ ኤፍሬም በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ፥ በቅዳሜው ክፍል እንደተናገረው፥ «የማትፈርስ ቤተ
መቅደስ» ናት።
ሊቀ
ካህናቱ ዘካርያስ፥ አይሁድ፦ «እነሆ አሥራ አምስት ዓመት ሆኗታል፥ መጠነ አንስትም አድርሳለች፥ ቤተ መቅደስ
ታሳድፍብናለችና ትውጣልን፤» እያሉ አላስቆም አላስቀምጥ አሉት። እርሷ ግን፦ ጠቢቡ ሰሎሞን፦ «ወዳጄ ሆይ፥
ሁለንተናሽ ውብ ነው፥ ምንም ነውር የለብሽም።» እንዳለ፥ እድፍ ጉድፍ የሌለባት፥ ንጽሕተ ንጹሐን፥ ቅዱስተ ቅዱሳን
ናት። የረከሰውን የምትቀድስ ናት። መኃ ፬፥፯።
ዘካርያስም ወደ እርስዋ ገብቶ «ምን ይበጅሻል? እንዴት ትሆኚ?» ቢላት «ወደ እግዚአብሔር አመልክትልኝ፤»
ብላዋለች። ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት፦ «ከነገደ ይሁዳ ሚስቶቻቸው የሞቱባቸውን አስቈጥረህ፥ በትራቸውን ከቤተ
መቅደስ አግብተህ ስትጸልይበት እደርና አውጣው፤» ብሎታል። እንደተባለው ቢያደርግ ከበትረ ዮሴፍ ላይ፦ «ኦ ዮሴፍ
ወልደ ዳዊት፥ ኢትፍራህ ነሢኦታ ለማርያም ፍኅርትከ፤ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ እጮኛህን ማርያም ለመውሰድ አትፍራ፤»
የሚል ጽሑፍ ተቀርጾበት ተገኝቷል። ይኸውም፦ የነቢያት አለቃ ሙሴ፥ እግዚአብሔር እንዳዘዘው፥ በአሥራ ሁለቱ ነገደ
እስራኤል ልክ፥ አሥራ ሁለት በትሮችን ሰብስቦ፥ ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ ቢጸልይበት፥ በትረ አሮን ለምልማ፣
አብባና አፍርታ እንደተገኘችው ማለት ነው። ዘኁ ፲፯፥፩-፰። ሁለተኛም፦ ነጭ ርግብ ወርዳ ከዮሴፍ ራስ ላይ
አርፋበታለች፤ ሦስተኛም፦ ዕጣ ቢጣጣሉ ዕጣው ለዮሴፍ ወጥቶለታል። ከዚህ በኋላ ለማኅደረ መለኰትነት የተመረጠች
ድንግል ማርያምን ይጠብቃት፥ ይንከባከባትም ዘንድ ወደ ቤቱ ይዟት ሄዷል።
፬፦ እግዚአብሔር እሥራኤልን ማጨቱ፤
እግዚአብሔር
እስራኤልን በማጨቱ የእስራኤል እጮኛ ተብላለች፤ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር፥ በነቢዩ በሆሴዕ አድሮ
ሲናገር፥ «ስለዚህ እነሆ አቅበዘብዛታለሁ፤ ወደ ምድረ በዳም አወጣታለሁ፤ ለልብዋም እናገራለሁ። ከዚያም የተገኘውን
ገንዘብዋን እሰጣታለሁ። ምክርዋንም በአኮር ሸለቆ እገልጣለሁ፤ እንደ ሕፃንነትዋ ወራት፥ ከግብፅም እንደወጣችበት ቀን
ትዘምራለች። በዚያን ቀን ባሌ (እግዚአብሔር ፈጣሪዬ ነህ)፤ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እንጂ በዓሊም (ጣዖቱ እንደማያድን
እርሱም አያድንም)፤ ብለሽ አትጠሪኝም፥ ይላል እግዚአብሔር፤ የበዓሊምን (የጣዖታቱን) ስሞች ከአፍዋ
አስወግዳቸዋለሁና፥ (ጣዖታቱን እንዳታመሰግን አደርጋታለሁ)፥ ስማቸውም ከእንግዲህ ወዲህ አይታሰብም። (ቤል፣ ዳጎን
እያለች ስማቸውን አታነሣም)። በዚያም ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች (ከአሕዛብና ከኃያላን) ጋር ከመሬትም
ተንቀሳቃሾች ጋር ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ። (በጠላትነት ተነሥተው እንዳያጠፏት አደርጋለሁ)። ቀስትንና ሰይፍን፥
ጦርንም ከምድሩ እሰብራለሁ፤ (በቀስትና በሰይፍ፥ በጦርም ሊያጠፉ የሚችሉትን ሁሉ አጠፋቸዋለሁ)፤ ተዘልለሽም
ትቀመጫለሽ። (ጠላት ጠፍቶልሽ በሰላም ትኖሪያለሽ)፤» ካለ በኋላ፥ «ለዘለዓለምም ለእኔ እንድትሆኚ እጭሻለሁ፤
በጽድቅና በፍርድ በምሕረትና በይቅርታ አጭሻለሁ። (በሃይማኖት ጸንተሽ፥ ጽድቅን፣ ርትዕን፣ ጸሎትን፣ ገንዘብ
አድርገሽ ብትገኚ፥ እውነትን፣ ፍርድን፣ ምሕረትንና ይቅርታን ማጫ አድርጌ ለዘለዓለም ማደሪያዬ ልትሆኚ አጭሻለሁ)።
ለእኔም እንድትሆኚ በመታመን አጭሻለሁ፤ አንቺም እግዚአብሔርን ታውቂአለሽ። (ይቅርታን ቸርነትን አድርጌልሽ ፈጣሪሽ
እኔ እንደሆንኩ ታውቂኛለሽ)።» ብሏል። ሆሴ ፪፥፲፬-፳።
እስራኤል ዘሥጋ፥ ከግብፅ ምድር በወጡ በሦስተኛው ወር፥ እግዚአብሔር
ሙሴን፦ «በግብፃውያን ላይ ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፥ (ንስር ፈጣን እንደሆነ ፈጥኜ
እንዳወጣኋችሁ)፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ (በባለሟልነት እንዳቀርብኳችሁ) አይታችኋል። አሁንም ቃሌን በእውነት
ብትሰሙ፥ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ (የታጨ) ርስት (ወገን)
ትሆኑኛላችሁ፤ እናንተም የክህነት መንግሥት፥ የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ። (ካህናቱ ነገሥታቱ ከእናንተ ይወለዳሉ፥
ምግባር ሃይማኖት የሚጠብቁ ከእናንተ ይወለዱልኛል፥ በእኔ በእግዚአብሔር ላይ የጣዖት ውሽማ የማያበጁ ከእናንተ
ይገኙልኛል)፤ ብለህ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው።» ብሎታል። ዘፀ ፲፱፥፫-፮። በኦሪት ዘዳግም ላይ ደግሞ፦
«ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዘብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ሕዝብ
ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መርጦሃልና። እግዚአብሔር የወደዳችሁና የመረጣችሁ፥ ከአሕዛብ ሁሉ ስለበዛችሁ
አይደለም፤ እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ ጥቂቶች ነበራችሁና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አባቶቻችሁን መረጣቸው፤ ወደዳቸውም፤
ከእነርሱም በኋላ እናንተን ዘራቸውን እንደዛሬው ሁሉ ከአሕዛብ ሁሉ መረጠ።» የሚል ተጽፏል። ዘዳ ፲፥፲፭። ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስም፦ «እኒህም፦ ልጅነት፥ ክብር፥ ኪዳን፥ ሕግና አምልኮ ያላቸው፥ ተስፋም የተሰጣቸው፥ እስራኤላውያን
ናቸው። እነርሱም አባቶቻችን ናቸው፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ ተወለደ፤ እርሱም ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘለዓለም
ቡሩክ አምላክ ነው፤ አሜን።» ብሏል። ሮሜ ፱፥፬-፭።
፭፦ ምእመናን ለክርስቶስ መታጨታቸው፤
የአዲስ
ኪዳን እስራኤል፦ በሥላሴ ስም የተጠመቁ፥ በሜሮን የከበሩ፥ በሥጋ ወደሙ የታተሙ ምዕመናን ናቸው። እነርሱም
እስራኤል ዘነፍስ ይባላሉ። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «እኛ ሁሉን ትተን
ተከተልንህ፤ እንግዲህ ምን እናገኛለን?» ብሎ በጠየቀው ጊዜ፥ «እውነት እላችኋለሁ፤ የተከተላችሁኝ እናንተ በዳግም
ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ እናንተም በዐሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ፤ በዐሥራ ሁለቱም ነገደ
እስራኤል ትፈርዳላችሁ።» ብሎታል። ማቴ ፲፱፥፳፯-፳፰። «በእስራኤል ትፈርዳላችሁ፤» ማለቱም በእስራኤል ዘሥጋ
በአይሁድ ብቻ ሳይሆን እስራኤል ዘነፍስ በሚባሉ በምዕመናንም ነው።
ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስ በብሉይ ኪዳን ዘመን እስራኤል ዘሥጋ ለእግዚአብሔር እንደታጩ፥ በአዲስ ኪዳን ዘመን ደግሞ ምዕመናን
ለክርስቶስ መታጨታቸውን ሲናገር፦ «በስንፍናዬ እናገር ዘንድ (በመመካት መናገሬን) ጥቂት ልትታገሡኝ ይገባ ነበር፤
ቢሆንም በእርግጥ ታገሡኝ፤ (መመካት ሥርዓት እንደሆነ አድርጋችሁ አትያዙብኝ)፤ ለእግዚአብሔር የሚገባ ቅንዐት
እቀናላችኋለሁና፤ (መንፈሳዊ ቅንዐት እቀናላችኋለሁና)፤ ወደ እርሱ አቀርባችሁ (አዋህዳችሁ) ዘንድ ለአንዱ ንጹሕ
ድንግል ለክርስቶስ አጭቻችኋለሁና።» ብሏል። ፪ኛ ቆሮ ፲፩፥፩-፪።
ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፲፫
ጻድቁ
ዮሴፍ እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን፦ ሊጠብቃት፥ ሊያገለግላትና ሊላላካት፥ በእግዚአብሔር ፈቃድ ከካህናቱ
እጅ በአደራ ተቀብሏታል። ሰው ሰውኛውን እርሱ ይጠብቃት እንጂ ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ጠባቂዋ መንፈስ ቅዱስ ነው።
እግዚአብሔር ለተዋሕዶ አካላዊ ቃል የመረጣት ስለሆነ፥ ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ንጽሐ ጠባይዕ ሳያድፍባት፥ ከአዳም
በዘር ይተላለፍ የነበረው የውርስ ኃጢአት ሳያገኛት፥ በመንፈስ ቅዱስ ተጠብቃ ኖራለች። አምላክን በድንግልና ፀንሳ፥
በድንግልና እንደምትወልድ ያበሠራት መልአከ ቅዱስ ገብርኤል፦ «መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤» ያላት ለዚህ ነው።
ይህም፦ የምትፀንሺው፥ ከእናትሽ ማኅፀን ጀምሮ በጠበቀሽ፧ ለቅጽበተ ዓይን እንኳ ተለይቶሽ በማያውቅ በመንፈስ ቅዱስ
ግብር ነው፥ ሲላት ነው። ሉቃ ፩፥፴፰። ምክንያቱም በውስጧ ሆኖ የጠበቃት፥ በኋላም ያዋሐደ እርሱ ነውና።
የባሕርይ
አምላክ ፥ ከሰማይ ወርዶ፥ በማኅጸነ ድንግል ማርያም በተዋሕዶ ሰው የሆነበት ምሥጢር ከሰው አእምሮ በላይ ነው።
ይህ፦ አምላክ ሰው የሆነበት ጥበብ (የመንፈስ ቅዱስ ግብር) እጅግ ጥልቅና የማይመረመር ነው። ሐዋርያው ቅዱስ
ጳውሎስ፦ «የእግዚአብሔር ባለጠግነት፥ ጥበብና ዕውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ለመንገዱም ፍለጋ የለውም፤ ፍርዱንም
የሚያውቀው የለም።» ያለው ለዚህ ነው። ሮሜ ፲፩፥፴፫። ለልጁ ለጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክቱም ላይ፦ «ቤተ
ክርስቲያኒቱ የእውነት ዐምድና መሠረት የሕያው እግዚአብሔር ቤት ናት። የዚህ የመልካም አምልኮ (አምላክ ሰው
የሆነበት ምሥጢር) ታላቅ ነውና። ይኸውም በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የተረዳ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ ዘንድ
የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ ነው።» ብሏል። ፩ኛ ጢሞ ፫፥፲፮። እንኳን ይህ ታላቅ ምስጢር ቀርቶ፥
እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ሥራ ከሰው ዕውቀት በላይ በመሆኑ ከማድነቅ በስተቀር እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር (በቃላት
ለመወሰን) አስቸጋሪ ነው። ቅዱስ ዳዊት፦ «እግዚአብሔርን ሥራህ ግሩም ነው፥ በሉት፤» ያለው ለዚህ ነው።
ቅዱስ
ዮሴፍ፦ እርሱ በማያውቀው ምሥጢር እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን ፀንሳ በማግኘቱ እንደ ሰው ተቸግሯል።
ምክንያቱም፦ ምንም ዓይነት ሥጋዊ ምክንያት አያገኘባትምና ነው። በውዳሴ ማርያም ትርጓሜ፥ በዓርቡ ክፍል እንደተጻፈው
ቅዱስ ዮሴፍ ፦ ዮሐንስ የሚባል ፈላስፋ ወዳጅ ነበረውና በመልኳ መፅነሷን
አውቆ ነግሮታል። ይኽንን ይዞ ቢጠይቃት፦ «እኔስ መልአኩ አክብሮ ከነገረኝ በቀር የማውቀው የለም፤ በዚያውስ ላይ
አዕዋፍ እንዲራቡ (እንዲባዙ)፥ አዕዋም እንዲያፈሩ የሚያደርግ ማን መስሎሃል?» ብላዋለች። ከዚህም ጋር ከደጅ ቆሞ
የነበረ ደረቅ ግንድ አለምልማ አሳይታዋለች። ከዚህ በኋላ ለክብረ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም የሚወጡበት ጊዜ ደረሰ።
ቅዱስ
ዮሴፍ በአሳብ ውጣ ውረድ ኅሊናው ተወጠረ። ከቤት ትቷት እንዳይሄድም፥ ወደ በዓሉም ይዟት እንዳይወጣም ተቸገረ።
ይኸውም አይሁድን ፈርቶ ነው። ወደ በዓሉ ይዟት እንዳይወጣ፥ ቀድሞም ሊቀ ካህናቱን ዘካርያስን አስጨንቀው አሥራ
ሁለት ዓመት ከኖረችበት ቤተ መቅደስ እንድትወጣ ያስደረጉት ለምን እንደሆነ ያውቃል። «የፈራነው ደረሰ፤» ብለው፥
በሕግ ሽፋን ፅንሱን ቆራርጦ የሚያወጣና አንጀቷን የሚበጣጥስ፥ ማየ ዘለፋ እንደሚያጠጧት፥ በደንጊያ ቀጥቅጠው
እንደሚገድሏት ከእርሱ የተሠወረ አይደለም። ከቤት ትቷት እንዳይሄድ ደግሞ አፋቸውን እንደ ጦር ፈራው። ከብዙ የአሳብ
ውጣ ውረድ በኋላ ግን፥ በአይሁድ ፊት ተገልጣ ባላወቁት ምሥጢር እንዳይፈርዱባት በስውር ከቤት ትቷት ወደ በዓሉ
ለመሄድ አሰበ።
፩፥፩፦ የእግዚአብሔር መልአክ በሕልም ታየው፤
ቅዱስ
ዮሴፍ፦ ጻድቅ ሰው በመሆኑ፥ አንድም እንዲጠብቅ የተሰጠችው አደራ መትኅተ ፈጣሪ መልዕልተ ፍጡራን በመሆኗ በነገር
ሁሉ ቅዱሳን መላእክት ይራዱት ነበር። በሕልም ይነጋገሩት ነበር። ለደጋግ ሰዎች ሕልም ከእግዚአብሔር ነው። ኢዮ
፪፥፳፰፣ የሐዋ ፪፥፲፯። ያዕቆብ፦ በቤቴል ድንጋይ ተንተርሶ በተኛበት ሌሊት ጫፉ ሰማይ ደርሶ እግዚአብሔር የቆመባት
መሰላል፥ ቅዱሳን መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት (ጸሎት ሲያሳርጉባት፥ ምሕረት ሲያወርዱባት) አይቷል። ዘፍ
፳፰፥፲-፲፪። ይህች እግዚአብሔር ተገልጦ የታየባት መሰላል፥ አምላክ ሰው ኾኖ ለተገለጠባት ለእመቤታችን ለቅድስት
ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። ላባን ለመገናኘት በተጓዘ ጊዜም የእግዚአብሔርን መላእክት በዙሪያው ከትመው ሲጠብቁት
በገሀድ አይቷል። ዘፍ ፴፪፥፩-፪። በእግረ ሙሴ የተተካ ኢያሱ ወልደ ነዌም የተመዘዘ ሰይፍ የያዘውን የሠራዊት አለቃ
ቅዱስ ሚካኤልን ፊት ለፊት አይቷል። ኢያ ፭፥፲፫። ጌዴዎንንም የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ አነጋግሮታል። መሳ
፮፥፲፪። የሶምሶንን ወላጆች ማኑሄን እና ሚስቱንም አነጋግሯቸዋል። በፊታቸውም ተአምራት አድርጓል። መሳ ፲፫፥፩-፳።
ነቢዩ
ኤልያስ መፍቀሪተ ጣዖት ኤሌዛቤል ባሳደደችው ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ኅብስት በመሶብ ወርቅ
አድርጎ መግቦታል። ኅብስት የጌታ፥ መሶበ ወርቅ የእመቤታችን ምሳሌዎች ናቸው። ፩ኛ ነገ ፲፱፥ ፩-፰። ነቢዩ
ኤልሳዕ በዶታይን የሶርያው ንጉሥ በፈረሶችና በሰረገሎች ባስከበበው ጊዜ፦ ቅዱሳን መላእክት በዙሪያው ከትመው የእሳት
አጥር ሆነው ሲጠብቁት አይቷል። ሎሌውንም፦ «ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ።» በማለት
አጽናንቶታል። በነቢዩ ጸሎት ለሎሌውም ተገልጠውለታል። ፪ኛ ነገ ፮፥፲፬-፲፯። ከዓይነ ሞት የተሰወረ ሄኖክ ቅዱሳን
መላእክትን ፊት ለፊት አይቷቸዋል፥ እነ ቅዱስ ሜካኤልም ያነጋግሩት ነበር። ሄኖ ፲፮፥፩-፵፩። ዕዝራ ሱቱኤልን ቅዱስ
ዑራኤል አነጋግሮታል፥ የጥበብንም ጽዋ አጠጥቶታል። ዕዝ ፫፥፳። ቅዱስ ሩፋኤል ደግሞ ጦቢያን እያነጋገረው በመንገዱ
ሁሉ አልተለየውም ነበር። ጦቢት ፭፥፩-፳፪፣ ፮፥፩-፲፯፣፯፥፩-፲፰።
ነቢዩ
ኢሳይያስ የሱራፌልን መልካቸውን አይቷል፥ ቅዳሴአቸውንም ሰምቷል። ከሱራፌል አንዱም ከሰማይ ይዞት በመጣው እሳት
አፉን ዳስሶ ከለምጹ ፈውሶታል። ኢሳ ፮፥፩-፯። ለነቢዩ ለዳንኤል ራእዩን የሚተረጉምለት ቅዱስ ገብርኤል ነበር። ዳን
፰፥፲፭-፳፯። በጾሙ ጊዜም እየተገለጠ ይዳስሰው፥ ያነጋግረውም ነበር። ይህ ታላቅ ነቢይ፥ «ከአለቃችሁ ከሚካኤል
በቀር የሚረዳኝ ማንም የለም።» በማለት መስክሯል። ዳን ፩፥፩-፲፩። ጻድቁ ዮሴፍ፦ አባቶቹን ቅዱሳንን በዘመነ
አበው፥ በዘመነ መሳፍንት፥ በዘመነ ነገሥት፥ በዘመነ ካህናትም እየተገለጡ ያነጋገሩ ቅዱሳን መላእክት እርሱንም
አነጋግረውታል። እርሱ ሰው ሰውኛውን ሲጨነቅ መንፈሳዊውን ምሥጢር ገልጠውለታል።
፩፥፪፦ «ከእርስዋ የሚወለደው በመንፈስ ቅዱስ ነው፤»
የእግዚአብሔር
መልአክ ዮሴፍን፦ «ኦ ዮሴፍ ወልደ ዳዊት ኢትፍራህ ነሢኦታ ለማርያም ፍኅርትከ፥ እስመ ዘይትወለድ እምኔሃ እመንፈስ
ቅዱስ። የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የሚወለደው በመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ
አትፍራ።» ብሎታል። በዚህም የእመቤታችን ጽንስ በመንፈስ ቅዱስ ግብር መሆኑን አስረድቶታል። ይህንንም፦ «መንፈስ
ቅዱስ ያድርብሻል፤» ብሎ አስቀድሞ ለእመቤታችን ነግሯት ነበር። ሉቃ ፩፥፴፭። መልአኩ ዮሴፍን፦ «የዳዊት ልጅ» ብሎ
በመጥራት ንጉሡን ዳዊትን ያነሣው ያለ ምክንያት አይደለም። ይኸውም፦ «ዕድሜህም በተፈጸመ ጊዜ፤ ከአባቶችህም ጋር
ባንቀላፋህ ጊዜ፥ ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ አስነሣለሁ፤ መንግሥቱንም አዘጋጃለሁ። (በዙፋንህ
አስቀምጠዋለሁ)።» ተብሎ ለቅዱስ ዳዊት የተነገረው ትንቢት መፈጸሙን ሲያጠይቅ ነው። ፪ኛ ሳሙ ፯፥፲፪። ይህ ትንቢት
ለጊዜው ለሰሎሞን ሲሆን ለፍጻሜው ለኢየሱስ ክርስቶስ ነበረ። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን በፍጹም
ትህትና ባበሠራት ጊዜ፦ «እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል።» ያላት ለዚህ ነበር። ሉቃ
፩፥፴፪። የመጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሀንስ አባት ጻድቁ ካህን ዘካርያስም፦ አድሮበት በሚኖር መንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ፦
«ይቅር ያለን፥ ለወገኖቹም ድኅነትን ያደረገ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ከባርያው ከዳዊት ቤት
የምንድንበትን ቀንድ አስነሣልን፤» ብሏል። ሉቃ ፩፥፷፰። መልአከ አግዚአብሔር ዮሴፍን፦ «አትፍራ» ያለው፥
«ልትጠብቃት፥ ልታገለግላት ከካህናት እጅ በአደራ እንደተቀበልካት፥ ከመንፈስ ቅዱስ እጅ መቀበልንም አትፍራ፤»ሲለው
ነው። ከዚህም አያይዞ፦ «ልጅም (ወልድን) ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው (በኃጢአት ከመጣባቸው ፍዳ)
ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።» ብሎታል። በዚህም «ኢየሱስ» ብሎ ንባቡን፥ «ያድናቸዋል፤» ብሎ ትርጓሜውን
ነግሮታል። የስም ኃይሉ ትርጉሙ ነውና። ምክንያቱንም ዘርዝሮ ሲነግረው፥ «እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ልጅም
(ወልድን) ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፤ ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው። ተብሎ
ከእግዚአብሔር ዘንድ (ከእግዚአብሔር አግኝቶ) በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፤» በማለት ትንቢተ ኢሳይያስን
ጠቅሶለታል። በዚህም ላይ ነቢዩ በንባብ ብቻ ያስቀመጠውን «አማኑኤል» የሚለውን ስም ተርጉሞለታል። «ወተንሢኦ ዮሴፍ
እምንዋሙ ገብረ በከመ አዘዞ መልአከ እግዚአብሔር፤ ወነሥአ ለማርያም ፍኅርቱ። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ተነሥቶ (ነቅቶ)
የእግዚአብሔር መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውን (እንዲጠብቃት እንዲያገለግላት፥ እንዲላካት የተመረጠላትን)
ማርያምንም ወሰዳት።» የወሰዳትም ከቤቱ ወደ በዓሉ ነው።
፩፥፫፦ በዓላት፤
በመጽሐፍ
ቅዱስ እንደተመዘገበው አይሁድ ሰባት የዓዋጅ በዓላት አሉአቸው። እንደ ስምንተኛ አድርገው የሚያከብሩት አንድ ሌላ
በዓል የተጨመረው በመቃብያን ዘመን ነው። በአይሁድ ዘንድ በትእዛዝ የሚከበሩት እነዚህ በዓላት፦ ፩ኛ፦ የሰንበት
በዓል፤ ዘሌ ፳፫፥፪፤ ፪ኛ፦ የቂጣ ወይም የፋሲካ በዓል፤ ዘጸ ፲፪፥፩-፳፣ ዘሌ ፳፫፥፭-፰፤ ፫ኛ፦ ሰባት ሳምንት
ከፋሲካ በኋላ የሚከበረው የመከር በዓል፤ (በዓለ ሰዊት)፤ ዘጸ ፳፫፥፲፮፤ ፴፬፥፳፪፤ ዘኁ ፳፰፥፳፮፤ የሐዋ ፪፥፩፤
፬ኛ፦ በሰባተኛው ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን የሚከበረው የዳስ በዓል፤ ዘሌ ፳፫፥፴፱-፵፫፤ ፭ኛ፦ መለከቶች
የሚነፉበት ቀን፤ ዘሌ ፳፫፥፳፫-፳፭፣ ዘኁ ፳፱፥፩፤ ፮ኛ፦ በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን የሚከበረው የማስተስረያ
ቀን፤ ዘሌ ፳፫፥፳፮፤ ፯ኛ፦ በአስቴር ዘመን አይሁድ ከጠላቶቻቸው ዕረፍትን ያገኙባቸው ቀኖች ፉሪን፤ አሰ
፱፥፲፮-፳፰፤ ፰ኛ፦ የሶርያ ንጉሥ አውፋሬኖስ አንጥያኮስ ቤተ መቅደሱን ካረከሰ በኋላ መቃብያን እንደገና የቀደሱበት
እለት የመቅደስ መታደስ መታሰቢያ እለት ናቸው።
ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፲፬
ስለ
እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ከመናገራችን በፊት፥እርሷ የእግዚአብሔር ብቻ ቤተመቅደስ፥ የ እግዚአብሔር
ብቻ እናት፥ የእግዚአብሔር ብቻ ዙፋን፥ እንደሆነች ማመን ያስፈልጋል። ነቢዩ ሕዝቅኤል ይኸንን ታላቅ ምሥጢር በብሉይ
ኪዳን ዘመን ኾኖ፥ዐረፍተ ዘመን ሳይጋርደው ተረድቶት ነበር። ያስረዳውም እግዚአብሔር ነው። እንዴት እንዳስረዳው
ሲናገርም፦ “ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተውጭ ወደ አለው ወደ መቅደሱ በር መለሰኝ፤ተዘግቶም ነበር።
እግዚአብሔርም አንዲህ አለኝ፥ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም፤ ሰውም አይገባባትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶባታልና ተዘግታ ትኖራለች፥ አለኝ” ብሏል። ሕዝ ፵፬፥፩-፪ ይህች፦ ሕዝቅኤል በመንፈሰ ትንቢት አሻግሮ ያያት፦ የተዘጋች፥ የታተመች፥ የተቈለፈች ምሥራቃዊት ቤተ መቅደስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። እግዚአብሔር ለነቢዩ ለሕዝቅኤል እንደነገረው ሰው ከቶ ሊገባባት የማይቻለው የእግዚአብሔር ብቻ ልዩ ቤተ መቅደስ ናት። እርሱ ብቻ ሳይከፍት ገብቶ ሳይከፍት ወጥቷል። (በድንግልና እንድትጸንሰው በድንግልናም እንድትወልደው አድርጓል)። ቅዱስ ዳዊትም፦ በጾምና በጸሎት የተገለጠለትን ምሥጢር ሲናገር፦ “እግዚአብሔር ጽዮንን (ለሥጋም ለነፍስም፥ ለጻድ ቃንም ለኃጥአንም መጠጊያ የምትሆን ድንግል ማርያምን) መርጦአታልና፥ ማደሪያውም (እናቱ፥ዙፋኑ፥መቅደሱ) ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና ፥ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ አለ፤” ብሏል። መዝ ፻፴፩፥፲፫-፲፬። እግዚአብሔር ለነቢዩ ለዳዊትም እንደነገረው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ ማኅደርነት እስከምት ወልደው ድረስ ብቻ አልነበረም ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱ፦ “ይህች ለዘዓለም ማረፊያዬ ናት፤” ብሎአልና ነው። በመሆ ኑም በድንግልና እንደፀናች ለዘለዓለም ወላዲተ አምላክ ስትባል የምትኖር እንጂ ወደ ወላዲተ ሰብእነት የምትመለስ አይደለችም።
እግዚአብሔርም አንዲህ አለኝ፥ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም፤ ሰውም አይገባባትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶባታልና ተዘግታ ትኖራለች፥ አለኝ” ብሏል። ሕዝ ፵፬፥፩-፪ ይህች፦ ሕዝቅኤል በመንፈሰ ትንቢት አሻግሮ ያያት፦ የተዘጋች፥ የታተመች፥ የተቈለፈች ምሥራቃዊት ቤተ መቅደስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። እግዚአብሔር ለነቢዩ ለሕዝቅኤል እንደነገረው ሰው ከቶ ሊገባባት የማይቻለው የእግዚአብሔር ብቻ ልዩ ቤተ መቅደስ ናት። እርሱ ብቻ ሳይከፍት ገብቶ ሳይከፍት ወጥቷል። (በድንግልና እንድትጸንሰው በድንግልናም እንድትወልደው አድርጓል)። ቅዱስ ዳዊትም፦ በጾምና በጸሎት የተገለጠለትን ምሥጢር ሲናገር፦ “እግዚአብሔር ጽዮንን (ለሥጋም ለነፍስም፥ ለጻድ ቃንም ለኃጥአንም መጠጊያ የምትሆን ድንግል ማርያምን) መርጦአታልና፥ ማደሪያውም (እናቱ፥ዙፋኑ፥መቅደሱ) ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና ፥ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ አለ፤” ብሏል። መዝ ፻፴፩፥፲፫-፲፬። እግዚአብሔር ለነቢዩ ለዳዊትም እንደነገረው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ ማኅደርነት እስከምት ወልደው ድረስ ብቻ አልነበረም ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱ፦ “ይህች ለዘዓለም ማረፊያዬ ናት፤” ብሎአልና ነው። በመሆ ኑም በድንግልና እንደፀናች ለዘለዓለም ወላዲተ አምላክ ስትባል የምትኖር እንጂ ወደ ወላዲተ ሰብእነት የምትመለስ አይደለችም።
፪፦ በኲር፤
በኲር
የሚባለው በመጀመሪያ የሚወለድ ነው። ተከታይ ልጅ ኖረውም አልኖረውም፥ በመጀመሪያ የሚወለድ የሰውም ሆነ የእንስሳት
ልጅ በኲር ይባላል። ብኲርና ታላቅ በመሆኑ፥ የበኲር ልጅ ርስት (ሀብት፤ንብረት) ሲካፈል የሚደርሰው ሁለት እጥፍ
ነው። ዘዳ ፳፩፥፲፭-፲፯። በወንድሞቹም ላይ ጌታ ነው፡፡ ዔሳው ብኲርናውን አቃልሎ፥ ለወንድሙ ለያዕቆብ በምሥር
ንፍሮ ለውጦ፥ በረከትን በማጣቱ፥ “አባቴ ሆይ፥ ለእኔ በረከትን አላስቀረህልኝምን?” ብሎ ነበር። አባቱ ይስሐቅ
ግን፦“እነሆ ጌታህ አደረግሁት፤ ወንድሞቹንም ሁሉ ለእርሱ ተገዦች አደረግኋቸው፤ ወይኑንና ዘይቱንም አበዛሁ ለት፤”
ሲል መልሶለታል። ዘፍ ፳፯፥፴፮። በኦሪቱ ለሰዎችም ለእንስሳትም የበኲራት ቤዛ ልዩ ልዩ ሕግ ነበረ፤ ዘኊ
፫፥፵፪-፶፩፤፲፰፥፲፭-፲፯
ቅዱስ
ማቴዎስ ወንጌላዊ ፥ቅዱስ ዮሴፍን ፦ “የበኲር ልጇን እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም፤” ማለቱ ስለ ብዙ ነገር
ነው። በመሆኑም የመፍቻውን (የመተርጐሚያውን) ቁልፍ ማግኘት ያስፈልጋል። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን፦ “ ከእናንተም ጋራ ሳለሁ ይህን ነገርኋችሁ። ነገር ግን አብ በስሜ የሚልከው የእውነት
መንፈስ ጰራቅሊጦስ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል።” እንዳላቸው መንፈስ ቅዱስ
ምሥጢር ገላጭ ነው።አባቶቻችን ይህንን የምሥጢር ቁልፍ በማግኘታቸው በአፍም በመጽሐፍም አስተምረው አልፈዋል። ዮሐ
፲፬፥፳፭። እንግዲህ እንደ አባቶቻችን አማናዊ ትምህርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፦ “በኲር የሚሆን ልጇን
እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም፤” መባሉ፦
፪፥፩፦ የመጀመሪያ ልጇን እስከምትወልድ ድረስ ማለት ነው፤
ታላቁ
ነቢይ ኢሳይያስ፥ መተርጎምና ማመስጠር በማያስፈልገው ደረቅ የትንቢት ቃል፦ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ
ልጅንም (ወልድን) ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” ብሎ በተናገረው መሠረት ተቀዳሚና ተከታይ
የሌለውን የመጀመሪያ ልጇን ወልዳለች። ኢሳ፯፥፲፬። በድንግልና
ፀንሳ በድንግልና መውለዷም በመንፈስ ቅዱስ ግብር ነው። ይህንንም ከእግዚአብሔር የተላከ የመላእክት አለቃ ቅዱስ
ገብርኤል የእርሷ መፅነስና መውለድ እንደ አንስተ ዓለም አለመሆኑን አስቀድሞ ሲነግራት፦ “መንፈስ ቅዱስ
ያድርብሻል፤(በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነው)፤” ብሏት ነበር። ሉቃ ፩፥፴፭። በከብቶች በረት በወለደችውም ጊዜ፦ “
እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ። እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ
መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው።” የሚል የቅዱሳን መላእክት ብሥራት ለእረኞች
ተነግሯቸዋል። ሉቃ ፩፥፲።
አንዳንድ
ጊዜ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ በኲር(የመጀመሪያ) ካለ ቀጣይ ልጅ እንደአለ አያመላክትም ወይ? የሚሉ አሉ።
ለእነዚህም፥ ማለትም ባለማወቅ ለሚጠይቁትም ሆነ በክፋት ለሚጠይቁት አባቶቻችን በቅንነት መልስ ሰጥተዋል። ይህም
መልስ፦ ለእነዚህ (በቅንነት ለሚጠይቁት) ትምህርት፥ ለእነዚያ (በክፋት ለሚጠይቁት) ደግሞ ተግሳፅ ነው።
፪.፪፦ ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ የበኲር ልጅ ነው
ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የበኲር ልጅነቱ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ብቻ ሳይሆን
ለባሕርይ አባቱ ለእግዚአብሔር አብም ነው። ይህም፦ “እግዚአብሔር አለኝ አንተ ልጄ ነህ እኔም ዛሬ ወለድሁህ።”
በሚለው ቃለ እግዚአብሔር ታውቋል። መዝ ፪፥፯። እግዚአብሔር አብ፥ እግዚአብሔር ወልድን (ኢየሱስ ክርስቶስን)፥
“አንተ ልጄ ነህ፤” ማለቱ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከአብ መወለዱን፥ የአብ የበኲር ልጅ መሆኑን
ያመለ ክታል። “እኔም ዛሬ ወለድሁህ፤” የሚለው ደግሞ፤ ድኅረ ዓለም ያለ አባት፤ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል
ማርያም መወለ ዱን፤ ለእመቤታችንም የበኲር ልጅ መሆኑን የሚያመለክት ነው።ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ይዞ
የኢየሱስ ክርስቶስን የባህርይ አምላክነት፥ ፈጣሪነት፥ ከባህርይ አባቱ ከአብ ጋር ትክክል መሆኑን፥ ሲመሰክር ፦
”ከጥንት ጀምሮ እግዚአበሔር በብዙ ዐይነት እና ጎዳና (ብብዙ ኅብረ ምሳሌና በብዙ ኅብረ ትንቢት) ለአባቶቻችን
በነቢያት ተናገረ። በኋላ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገው ሁሉንም በፈጠረበት በልጁ ነገረን። እርሱም የክብሩ
መንጸባረቅና የመልኩ ምሳሌ ሆኖ፥ (እግዚአብሔር አብን በባሕርይ የሚመስለው የባሕርይ ልጁ ስለሆነ፥ በክብርም
ስለሚተካከለው)፥ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ (ከባሕርይ አባቱ ጋር በሥልጣን አንድ ስለሆነ) ኃጢአታችንን በራሱ
(በተለየ አካሉ በተዋሕዶ ሰው ሆኖ ባፈሰሰው ደሙ፥ በቆረሰው ሥጋው፥ አሳልፎ በሰጠው ነፍሱ) ካነጻ በኋላ፥ በግርማው
ቀኝ (በአብ ቀኝ፥ ከአብ ተካክሎ) ተቀመጠ። በዚህን ያህል መብለጥ (ፈጣሪ እንደመሆኑ) ከመላእክት በላይ ሆኖ
(ፈጣሪያቸው፥ ገዢያቸው በመሆኑ) ከስማቸው የሚበልጥና የሚከብር ስምን ወረሰ። (የእርሱ ስም ፍጡር የማይጠራበት
የፈጣሪ ስም ነው)። ከመላእክትስ ከሆነ ጀምሮ፥ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤ ዳግመኛም እኔ አባት
እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ያለው ከቶ ለማነው? ዳግመኛም በኲርን ወደ ዓለም በላከው ጊዜ፥ የእግዚአብሔር
መላእክት ሁሉ ይሰግዱለታል፥ አለ። ስለ መላእክቱም፥ መላእክቱን ነፋሳት፥ የሚላኩትንም የእሳት ነበልባል
የሚያደርጋቸው እርሱ ነው፥ አለ። ስለ ልጁ ግን፥ ጌታ ሆይ ዙፋንህ ለዘለዓለም ነው፤ የመንግሥትህ በትርም የጽድቅ
በትር ነው፥ አለ፤» ብሏል። ዕብ ፩፥፩-፰፣ ፪ኛ ሳሙ ፯፥፲፬፣ ፩ኛ ዜና ፲፯፥ ፲፫፣ ዘዳ ፴፪፥፵፫፣ መዝ
፩፻፫፥፬፣ መዝ ፵፬፥፮-፯። እንግዲህ ለእግዚአብሔር አብ «የበኲር ልጅ»፥ የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ተቀዳሚም
ተከታይም የሌለው የአብ የባሕርይ ልጅ እንደሆነ ሁሉ፥ ለእናቱ ለቅድስት ድንግል ማርያምም ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው
አንድ ልጅ ነው።
፪፥፫፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን በኲር ነው፤
ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቅዱሳን አምላክ ነው። ቅዱስ ቶማስ፦ በዓይኖቹ አይቶ፥ በእጆቹ ከዳሰሰ
በኋላ «ጌታዬ፥ አምላኬም» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፳፥፳፰። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም፦ «የእግዚአብሔር ልጅ
እንደመጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እግዚአብሔርን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው
በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንኖራለን፤ እርሱም እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው»።
ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «እኒህም ልጅነት፥ ክብር፥ ኪዳን፥ ሕግና አምልኮ ያላቸው፥
ተስፋም የተሰጣቸው እስራኤላውያን ናቸው። እርሱም ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ ነው፥ አሜን፤»
ብሏል። ሮሜ ፱፥፬-፭።
ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስ የባሕርይ አምላክ ብሎ የሚያምንበትን ኢየሱስ ክርስቶስን «የቅዱሳን በኲር፤» ብሎታል። ይኽንንም፦
«መንፈስ ቅዱስም ከድካማችን ይረዳናል፤ እንግዲያስ ተስፋችንን ካላወቅን ጸሎታችን ምንድነው? ነገር ግን እርሱ ራሱ
መንፈስ ቅዱስ ስለ መከራችንና ስለ ችግራችን ይፈርድልናል። እርሱም ልባችንን ይመረምራል፤ ልብ የሚያስበውንም እርሱ
ያውቃል፤ ስለ ቅዱሳንም በእግዚአብሔር ዘንድ (በሕልውና ከአብ ከወልድ ጋር አንድ ሆኖ) ይፈርዳል። እግዚአብሔር
የሚወዱትን ምርጦቹን በበጎ ምግባር ሁሉ እንደሚረዳቸው እናውቃለን። ልጁ (የአብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ)
በብዙ ወንድሞች (በቅዱሳን) መካከል በኲር ይሆን ዘንድ አስቀድሞ ያወቃቸውንና የመረጣቸውን እነርሱን ልጁን ይመስሉ
ዘንድ አዘጋጅቶአቸዋል። ያዘጋጀውን እነርሱን ጠራ፤ የጠራቸውንም እነርሱን አጸደቀ፤ የአጸደቃቸውንም እነርሱን አከበረ፤» በማለት አብሯርቷል። ሮሜ ፰፥፳፮-፴።
ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስ፥ ኢየሱስ ክርስቶስን፥ «ለቅዱሳን በኲር» ያለው ለበጎ ነገር ሁሉ ምሳሌያቸው፥ አብነታቸው እርሱ
ስለሆነ ነው። ምክንያቱም የተከተሉት የእርሱን መንገድ ነውና። የሰማዕታት አለቃ ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊገድሉት በድንጋይ
ሲቀጠቅጡት፦ «ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል፤ . . . አቤቱ፥ ይህን ኃጢአት አትቊጠርባቸው፤» ያለው
የጌታውን መንገድ ሲከተል ነበር። የሐዋ ፯፥፶፱-፷። ምክንያቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ በመስቀል
ላይ ሆኖ፥ «አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው፤. . . አባት
ሆይ፥ ነፍሴን በአንተ እጅ አደራ እሰጣለሁ፤» ብሏልና ነው። ሉቃ ፳፫፥፴፬፣ ፵፮። ይኽንን በተመለከተ፥ ሐዋርያው
ቅዱስ ጴጥሮስ ሲናገር፥ «በግፍ መከራን የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ኃዘንን ቢታገሥ ጸጋን ያገኛልና።
በድላችሁ የመጣባችሁን ብትታገሡ፥ ምስጋናችሁ ምንድርነው? ነገር ግን መልካም እየሠራችሁ፥ የደረሰባችሁን ግፍ
ብትታገሡ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ የምታስመሰግን ይህቺ ናት። ለዚህ ተጠርታችኋልና፤ ክርስቶስም እኮ ፍለጋውን ትከተሉ
ዘንድ ምሳሌውን ሊተውላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአል። እርሱ ኃጢአትን አልሠራም፤ በአንደበቱም ሐሰት
አልተገኘበትም። ሲሰድቡት አልተሳደበም፤ መከራ ሲያጸኑበትም አልተቀየመም፤» ብሎአል። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፲፱-፳፫። መምሕረ
ትኅትና፥ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ የደቀመዛሙርቱን እግር ካጠበ በኋላ፦ «ያደረግሁላችሁን ዐወቃችሁን?
እናንተ መምህራችን፦ ጌታችንም ትሉኛላችሁ፤ መልካም ትላላችሁ፤ እኔ እንዲሁ ነኝና። እኔ መምህራችሁና ጌታችሁ ስሆን
እግራችሁን ካጠብኋችሁ እናንተም እንዲሁ የባልንጀሮቻችሁን እግር ልታጥቡ ይገባችኋል። እኔ እንዳደረግሁላችሁ
እናንተም ልታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከጌታው የሚበልጥ አገልጋይ የለም፤ ከላከው
የሚበልጥ መልእክተኛም የለም። ይህንም ዐውቃችሁ ብትሠሩ ብፁዓን ናችሁ።» ያላቸው ለዚህ ነበር። ዮሐ ፲፫፥፲፪-፲፯።
ቅዱሳንም የጌታቸውን ቃል አክብረው፥ ለበጎ ምግባር ሁሉ በኲር የሆነላቸውን አምላክ መንገድ በመከተላቸው እርሱን
መስለው ተገኝተዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ « እኔ ክርስቶስን እንደምመስለው (እንደመሰልኩት) እኔን ምሰሉ፤»
ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ቆር ፲፩፥፩። «ወንድሞቻችን ሆይ፥ እኔን እንድትመስሉ እማልዳችኋለሁ፤ ስለዚህም በየስፍራው
በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዳስተማርሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የሄድሁበትን መንገድ ይገልጣላችሁ ዘንድ በእግዚአብሔር
የታመነና ልጄ ወዳጄ የሆነ ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ።» ያለበትም ጊዜ አለ። ፩ኛ ቆሮ ፬፥፲፮። በፊልጵስዩስ
መልእክቱም ላይ «ፍፁማን የሆናችሁ ሁላችሁ፥ ይህን አስቡ፤ ሌላ የምታስቡት ቢኖር፥ እርሱን እግዚአብሔር
ይገልጥላችኋል። ነገር ግን በደረስንበት ሥራ በአንድነት እንበርታ። ወንድሞቼ ሆይ፥ እኔን ምሰሉ፤ እንዲህ ባለ
መንገድ የሚሄዱትንም እኛን ታዩ እንደነበረበት ጊዜ ተጠባበቁአቸው፤» ብሏል። ፊል ፫፥፲፯፡፡
ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፲፭
አንድ
ቃል የሚፈታው፥ የሚተረጐመውና የሚመሰጠረው ከባለቤቱ ማንነት አንፃር ነው። ተናጋሪው ማነው? የተነገረውስ ለማን
ነው? የሚለው መሠረት ነው። ቋንቋው የተነገረበት ዘመን እና ባሕልም ወሳኝነት አለው። በተጨማሪም የተነገረበትን
ምክንያት እና ዓላማ ማስተዋል ያስፈልጋል። በተለይም
የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል እንደ ሥጋ አሳብ መተርጐም አደገኛ ነው። አደጋውም ስለእመ ቤታችን እና ስለቅዱሳን ባለን
እምነት ላይ ብቻ ሳይሆን፥ ስለእግዚአብሔር ማንነት ባለን እምነትም ላይ ነው። ለምሳሌ፦ «እግዚአ ብሔርም የሠራውን
ሥራ በስድስተኛው ቀን ፈጸመ፤ እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ።» የሚለውን ይዘን እግዚአብሔር
በባሕርዩ ድካም ኖሮበት ያረፈ ልናስመስለው እንችላለን። ዘፍ ፪፥፪። ነገር ግን አይደለም። ከጥቅሱ
እንደምንረዳው ሊሠራው ያሰበውን ሁሉ ማከናወኑን፥ መፈጸሙን ነው። እንዲሁም ሰባት ዕለታትን ፈጥሮ ሰባተኛዋን ቀን
ለሰው ልጅ ዕረፍት ትሆን ዘ ንድ ሕግ መሥራቱን ነው። በተጨማሪም፦ «እግዚአብሔርም የሰዎች ክፉ ሥራ በምድር ላይ
እንደበዛ፥ የልባቸው ዐሳብ ምኞትም ሁ ልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ። እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ
ተጸጸተ፤ በልቡም አዘነ ።» የሚለውን ይዘን የእግ ዚአብሔርን ጸጸት ከፍጡራን ጸጸት ጋር አመሳስለን ለእግዚአብሔር
ባሕርይ የማይስማማ ነገር ልንናገር እንችላለን። ፍጡር ቢጸጸት «እንዲህ ነገር እንደሚመጣ አውቄው ቢሆን ኖሮ
አላደርገውም ነበር፤» በሚል መንፈስ ነው። እግዚአብሔር ግን ሰውን ሳይፈጥረው በ ፊት ሰው እንደሚበድል ያውቃል።
ስለዚህ የእግዚአብሔር ጸጸት እንደ ሰው ያለ ጸጸት አይደለም። ቃሉ እንደሚያስረዳው እግዚአብ ሔር በሰው ልጅ ክፋት
ያዘነው ሐዘን እጅግ ታላቅ መሆኑን ነው። በመሆኑም ቅዱሳን አባቶቻችን ያስተማሩትን ትምህርት ማስተዋል «የበኲር
ልጅዋንም እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም፤» የሚለውን በጥልቀት እንድንገነዘብ ይረዳናል።
ፍጻሜ ያለው «እስከ»፤
በቋንቋ
አጠቃቀም ፍጸሜ ያለው «እስከ» አለ፤ ይህም የአንድን ድርጊት መጨረሻ ወይም ፍጻሜ የሚያመለክት ነው። ለምሳሌ
ነቢዩ ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ እግዚአብሔር መሥዋዕቱን በመቀበል መምለኬያነ ጣኦታትን አሳፍሮለት፥ ከሦስት ዓመት
ከመንፈቅ በኋላ ዝናብን ባዘነበለት ጊዜ፥ «ወዲያ ወዲህም እስኪመላለስ ድረስ ሰማዩ በደመናና በነፋስ ጨለመ፤ ትልቅም
ዝናብ ዘነበ፤ አክዓብም በሰረገላ ተቀምጦ እያለቀሰ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ። የእግዚአብሔርም እጅ በኤልያስ ላይ
ነበረች፤ ወገቡንም ታጥቆ ወደ ኢይዝራኤል እስከሚገባ ድረስ በአክዓብ ፊት ይሮጥ ነበር።» ይላል። ፩ኛ ነገ
፲፰፥፵፭። የነቢዩ የኤልያስ ሩጫ ፍጻሜው ኢይዝራኤል በመሆኑ «እስከ ኢይዝራኤል» ተብሏል። ከንግሥቲቱ ከኤልዛቤል
ፊት በሸሸም ጊዜ፥ የእግዚአብሔር መልአክ ያቀረበለትን ምግብ ተመግቦ፥ «በዚያው በበላው የምግብ ኃይል እስከ ኮሬብ
ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ። ይላል። ፩ኛ ነገ ፲፱፥፰። የነቢዩ የኤልያስ የአርባ ቀን እና የአርባ ሌሊት
ጉዞ መጨረሻው ፍጻሜው የኮሬብ ተራራ በመሆኑ «እስከ ኮሬብ፥» ተብሏል። ይህም ከኮሬብ አልፎ አልተጓዘም ማለት ነው።
በእግዚአብሔር ፊት በባለሟልነት የሚገለጥ፥ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፥ በቤተ መቅደስ በዕጣኑ መሠዊያ
በስተቀኝ፥ ለጻደቁ ካህን ለዘካርያስ በመገለጥ፥ መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስን እንደሚወልድ በነገረው ጊዜ፥ «ይህ
እንደሚሆን በምን አውቃ ለሁ? እነሆ፥ እኔ አርጅቻለሁ፤ የሚስቴም ዘመንዋ አልፏል፤» ብሎ ነበር። መልአኩም መልሶ፥
«እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህንም እነግርህና አበሥርህ ዘንድ ወደ አንተ ተልኬአለሁ።
አሁንም በጊዜው የሚሆነውንና የሚፈጸመውን ነገሬን አላመንኽምና ይህ እስከሚሆን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤ መናገርም
ይሳንሃል።» ብሎታል። እንዲሁም ዲዳ ሆኖ በእጁ እያመለከተ ኖሯል። ሉቃ ፩፥፲፱። ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ በኋላ ግን
አንደበቱ ተፈትቷል። «ያን ጊዜ አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱም ተናገረ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነ፤» ይላል። ሉቃ
፩፥፷፬። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ የዕለተ ምጽአትን ምልክቶች ለደቀመዛሙርቱ ከነገራቸው
በኋላ፥ «ምሳሌውንም ከበለስ ዕወቁ፤ ጫፍዋ የለሰለሰ፥ ቅጠልዋም የለመለመ እንደሆነ እነሆ መከር እንደ ደረሰ
ታውቃላችሁ። እንዲሁ እናንተ ይህን ሁሉ ባያችሁ ጊዜ፥ እንደቀረበና በደጃፍ እንዳለ ዕወቁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ
ሁሉ እስ ከሚደረግ ድረስ ይቺ ትውልደ አታልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም።» ብሎአቸዋል። ማቴ
፳፬፥፴፪። ይህም ፍጻሜ ያለው እስከ ነው። ከትንሣኤ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስን፥ በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን
ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለ ክተውም፦ «እውነት እውነት እልሃለሁ፤ አንተ ጎልማሳ ሳለህ በገዛ እጅህ ወገብህን
ታጥቀህ ወደ ወደድኸው ትሄድ ነበር፤ በሸመገልህ ጊዜ ግን እጆችህን ትዘረጋለህ፤ ወገብህንም ሌላ ያስታጥቅሃል፤
ወደማትወደውም (አትወደው ወደ ነበረ ሞት) ይወስዱሃል፤» ብሎት ነበረ። በዚህን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ፥ «ጌታ ሆይ፥
ይህስ እንዴት ይሆናል? (በምን ዓይነት አሟሟት ይሞታል)?» ብሎ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ ጠየቀ። ጌታም፦
«እስከምመጣ ይኖር ዘንድ ብወድድስ አንተን ምን አግዶህ፤ አንተ ግን ተከተለኝ፤» ብሎታል። ዮሐ ፳፮፥፲፰። የዚህም
ፍጻሜው መጨረሻው ዕለተ ምጽአት ነው፥ ያንጊዜ ግን ሃይማኖቱን መስክሮ በሰማዕትነት ያርፋል። ምክንያቱም ካልሞቱ
ትንሣኤ የለምና ነው።
ፍጻሜ የሌለው «እስከ»፤
ፍጻሜ የሌለው «እስከ» ማለት የቃሉን መጨረሻነት ወይም ፍጻሜ አልፎ ቀጣይነትን ወይም ዘለዓለማዊነትን የሚያሳይ ነው። ይኽንንም የሚያስረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። በኖኅ ዘመን ምድር በጥፋት ውኃ ተጥለቅልቃ
ነበር። በመጨረሻም፥ እግዚአብሔር ኖኅን በመርከብም ከእርሱ ጋር የነበረውን አራዊትን ሁሉ፥ እንስሳውንም ሁሉ፥
አዕዋፍንም ሁሉ፥ የሚንቀሳቀሰውንም ሁሉ ዐሰበ፤ እግዚአብሔርም በምድር ላይ ነፋስን አመጣ፤ ውኃውም ጐደለ፤ የቀላዩም
ምንጮች የሰማይ መስኮቶች ተደፈኑ፤ ዝናብም ከሰማይ ተከለከለ፤ ውኃውም ከምድር ላይ እያደር እየቀለለ ይሄድ ጀመረ፤
ከመቶ ሃምሳ ቀንም በኋላ ውኃው ጐደለ። መርከቢቱም በሰባተኛው ወር (በእኛ በጥቅምት) በወሩም በሃያሰባተኛው ቀን
በአራራት ተራራ ላይ ተቀመጠች። ውኃውም እስከ አሥረኛው ወር (በእኛ እስከ ጥር) ድረስ ይጐድል ነበር።
በአሥራአንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን (በእኛ በየካቲት መባቻ) የተራሮቹ ራስ ተገለጡ። ከአርባ ቀን በኋላም
ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ፤ ከምድርም ላይ ውኃው ጐድሎ እንደሆነ ያይ ዘንድ ቊራውን ላከው፤ እርሱም
ሄደ፤ «ነገር ግን ውኃው ከምድር ላይ እስከሚደርቅ ድረስ አልተመለሰም፤» ይላል። ዘፍ ፰፥፩-፯። ይህ፥ ፍጻሜ
የሌለው «እስከ» ይባላል፤ ምክንያቱም ቊራ ውኃው ከደረቀ በኋለም አልተመለሰምና ነው።
ታቦተ
ጽዮን ከአሚናዳብ ቤት በአዲስ ሠረገላ ተጭና ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሰች ጊዜ፥ ንጉሥ ዳዊት በክብር ይቀበላት ዘንድ
ሰባ ሺህ ሰዎችን ሰብስቦ ነበር። ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ከይሁዳ አለቆች ጋር ተነሥተው በኪሩቤል
ላይ የተቀመጠ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ስም የተጠራባትን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ያመጡ ዘንድ ሄዱ። በዜማ
መሣሪያዎች በበገናና በመሰንቆ፥ በከበሮና በነጋሪት፥ በጸናጽልና በዕንዚራ በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው
ይጫወቱ ነበር። ወደ ከተማውም አመጣት፤ የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በደረሰች ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል
በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሡም ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘምር አየችው፥ በልብዋም ናቀችው። ቤተሰቡን
ሊመርቅ በተመለሰ ጊዜም ልትቀበለው መጥታ ሰላምታ ከሰጠችው በኋላ «ከሚዘፍኑት አንዱ እንደሚገለጥ (እንደተርታ
ዘፋኝ) የእሥራኤል ንጉሥ በአገልጋዮቹ ሚስቶች ፊት በመገለጡ ምንኛ የተከበረ ነው! » ብላ አሽሟጠጠችው፥ የልቧን
ንቀት በአንደበቷ ገለጠችው። ዳዊትም ሜልኮልን፥ «በእግዚአብሔር ፊት ዘምሬአለሁ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል
ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ከአባትሽና ከቤቱ ሁሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር
ፊት እጫወታለሁ፤ እዘምራለሁም፤ አሁንም እገለጣለሁ፤ በዐይንሽ ፊትና እንዴት ከበርህ ባልሽባቸው ሴቶች ልጆች ፊት
የተናቅሁ እሆናለሁ፤» አላት። «የሳኦል ልጅ ሜልኮል እስከሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም»። ፪ኛ ሳሙ
፮፥፩-፳፫። ይህም ፈጽሞ አልወለደችም ማለት እንጂ፥ ከሞተች በኋላ በመቃብር ሳለች ወለደች ማለት አይደለም።
ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ከትንሣኤው በኋላ፥ ዐሥራ አንዱን ደቀመዛሙርት ወደ ገሊላ እንዲሄዱ
አዝዟቸው ነበር። የእግዚአብሔር መልአክ በመቃብሩ አጠገብ ለተገኙት ለመግደላዊት ማርያምና ለሁለተኛዋ ማርያም
(ለዮሐንስ እና ለያዕቆብ እናት ለማርያም ባውፍልያ) «እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ
አውቃለሁና። በዚህ የለም፤ እርሱ እንደ ተናገረው ተነሥቶአል፤ ነገር ግን ኑና ተቀብሮበት የነበረውን ቦታ እዩ።
ፈጥናችሁም ሂዱና፦ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ እነሆ፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ በዚያም ታዩታላችሁ፤ ብላችሁ ለደቀ
መዛሙርቱ ንገሩአቸው፤» ብሎ ነግሮአቸው ነበር። እነርሱም ይህንን ሰምተ ው ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር ሲፋጠኑ፥ ጌታም
አገኛቸውና፦ «ሰላም ለእናንተ ይሁን፤» አላቸው፤ ወዲያው ከእግሩ ስር ተደፍተው ሰገዱለት። እርሱም «አትፍሩ ሂዱና
ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሩአቸው፤ በዚያም ያዩኛል፤» አላቸው።
ዐሥራ
አንዱ ደቀመዛሙርት ጌታችን ኢየሱስ ወደአዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ። ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት። እኲሌቶቹ ግን
ተጠራጠሩ።(ቶማስን ለማጠየቅ ነው)። ጌታችን ኢየሱስም ቀርቦ፦ «ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። (ነፍሱና
ሥጋው ተለያይተው ስለነበር የእነርሱን መልሶ መዋሐድ ለማጠየቅ ተሰጠኝ አለ እንጂ፥ ሥጋ ሥልጣን ያገኘው፥ በተዋሕዶ
አምላክ ሰው እንደሆነ ሁሉ ሰውም አምላክ የሆነው መለኮት ሥጋንና ነፍስን በማኅፀን ተዋሕዶ የዕለት ፅንስ የሆነ
ዕለት ነው)። እንግዲህ ሂዱና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ሕዝቡን
ሁሉ አስተምሩአቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ።» ብሎአቸውል። ማቴ ፳፰፥
፩-፳። ይህም ባላችሁበት ዘመን ሁሉ አድሬባችሁ እኖራለሁ ሲላቸው እንጂ፥ ከዓለም ፍጻሜ በኋላ የሚለያቸው ሆኖ
አይደለም።
ፈሪሳውያን
ተሰብስበው ሳለ፥ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «ስለ ክርስቶስ ምን ትላላችሁ? የማን ልጅ
ነው?» ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ከማን ወገን እንደተወለደ ለማጠየቅ «የዳዊት ልጅ ነው፤» ብለውት ነበር። እርሱም መልሶ
እንግ ዲያስ ዳዊት በመንፈስ (በመዝሙረ ትንቢት) ጌታ (እግዚአብሔር አብ) ጌታዬን (እግዚአብሔር ወልድን)
ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስከ ማደርጋቸው በቀኜ ተቀመጥ እንዴት አለው? እርሱ ራሱ ዳዊት ጌታዬ ያለው፥ እንግዲህ
እንዴት ልጁ ይሆነዋል?» ብሎ ጠየቃ ቸው። ከዚህ ጥያቄ በኋላ አንድም ቃል ሊመልስለት የቻለ የለም፤ ከዚያች ቀንም
ጀምሮ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም። ማቴ ፳፪፥፵፩-፵፮፣ መዝ ፩፻፫፥፩። መዝ ፩፻፲፥፩። ከእግርህ በታች የተባለው
ከሥልጣነ መለኰት በታች ማለት ነው። ጠላት የተባሉት ለጊዜው አይሁድ፥ ለፍጻሜው አጋንንት ናቸው። ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ፥ በትንሣኤውና በዕርገቱ አይሁድንም አጋንንትንም ድል አድርጓቸዋል። በአብ ቀኝ
መቀመጡ (ከአብ ተካክሎ መኖሩ) እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም ነው እንጂ እስከ የሚገታው አይደለም። እርሱም
ራሱ፦ ሊቀ ካህናቱ፦ «አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደሆንህ ትነግረኝ ዘንድ በሕያው እግዚአብሔር
አምልሃለሁ፤» ባለው ጊዜ፥ «አንተ አልህ፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰውን ልጅ (ወልደ ዕጓለ
እመሕያው ክርስቶስን) በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ (ከአብ ጋር አንድ የሆነ ክብሩን) በሰማይ ደመና (በክብር ሲመጣ)
ታዩታላችሁ፤» ብሎታል። ማቴ ፳፮፥፷፫። ለነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ የደረሰ፥ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ እስጢፋኖስ፥ ወደ ሰማይ
ተመልክቶ፥ «እነሆ ሰማይ ተከፍቶ (ሰማያዊ ምሥጢር ምሥጢረ ሥላሴ ተገልጦ) የሰው ልጅም (ወልደ ዕጓለ እመሕያው
ክርስቶስም) በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ (በክብር ከአብ ተካክሎ) አያለሁ፤» ያለው ለዚህ ነው። የሐዋ ፯፥፶፮።
ሐዋርያውም ቅዱስ ጳውሎስም፦ «እንግዲህ እርሱ ራሱ ካጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወማቸው ማን ነው?
የሚፈርድስ ማን ነው? ይልቁንም ከሙታን ተለይቶ የተነሣው፥ በእግዚአብሔርም ቀኝ የተቀመጠው፥ (ከአብ የተካከለው)፥
ደግሞ ስለ እኛ የሚፈርደው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤» ብሏል። ሮሜ ፰፥፴፫።
«አላወቃትም፤»
ዕውቀት እጅግ ጥልቅና ረቂቅ ነገር ነው፤ ከሁሉም
በላይ የዕውቀት ባለቤት እግዚአብሔር ነው። ዕውቀቱም የባሕርይ ገንዘቡ ስለሆነ ይደነቃል እንጂ ከምንም ከማንም ጋር
የሚነጻጸር አይደለም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «የእግዚአብሔር ባለጠግነት፥ ጥበብና ዕውቀት እንዴት ጥልቅ ነው!
ለመንገዱም ፍለጋ የለውም፤ ፍርዱንም የሚያውቀው የለም። የእግዚአብሔርን ዐሳቡን ማን ያውቃል? ወይስ ማን ተማከረው?
ብድሩን ይከፍል ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ ማን አበደረው? ሁሉ ከእርሱ፥ በእርሱና ለእርሱ ነውና፤ ለእርሱም
ለዘለዓለም ክብር ምስጋና ይሁን አሜን።» ያለው ለዚህ ነው። ሮሜ ፲፫፥፴፫። ነቢዩ ዳንኤልም፦ «ጥበብና ምክር
ኃይልም ለእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይመስገን፤» ብሏል። ዳን ፪፥፳።
ዕውቀቱ
ፍጹም የሆነ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ዐዋቂ አድርጎ ፈጥሮታል። ዘፍ ፩፥፪፥፯። በየጊዜውም በተፈጥሮ በተሰጠው
ዕውቀቱ ላይ በጸጋ ዕውቀት ይጨመርለታል። ይኽንንም ነቢዩ ዳንኤል፦ «ጥበብን ለጠቢባን፥ ዕውቀትንም ለአስተዋዮች
ይሰጣል። የጠለቀውንና የተሰወረውን ይገልጣል፤ በጨለማ ያለውን (እጅግ ጥልቅና ረቂቅ የሆነውን) ያውቃል፤ ብርሃንም
(ዕውቀትም) ከእርሱ ጋር አለ። አንተ የአባቶቻችን ፈጣሪ! ዕውቀትንና ጥበብን አንተ ሰጥተኸኛልና፥ የለመንሁህንም
ነግረኸኛልና፥ የንጉሡን ሕልም፥ ትርጓሜውንም ገልጠኽልኛልና እገዛልሃለሁ፤ አመሰግንህምአለሁ።» በማለት ገልጦታል።
ዳን ፪፥፳፮። ነቢዩ ዳንኤልና ሦስቱ ወጣቶች አናንያ፥ አዛርያና ሚሳኤል ጥበብን፥ ዕውቀትንና ማስተዋልን
ከእግዚአብሔር ያገኙት በጾምና በጸሎት በመወሰናቸው ነው። ዳን ፩፥፩-፲፯።
የሰው
ልጅ ዕውቀት የጸጋ ስለሆነ ፍጹም አይደለም፤ የሚያውቀው ነገር እንዳለ ሁሉ የማያውቀው ነገር አለ፤ የሚገለጥለት
ነገር እንዳለ ሁሉ የሚሰወርበት ነገር አለ። ለምሳሌ፦ ነቢዩ ኤልሳዕ በእስራኤል ተቀምጦ በሶርያ ቤተ መንግሥት
የሚመከረውን ምክር እያወቀ ለእስራኤል ንጉሥ በመንገር ብዙ ጊዜ ሕይወቱን አድኖለታል። ፪ኛ ነገ ፮፥፩-፳፫። እርሱም
የሰማርያ ንጉሥ ሊያስገድለው በምሥጢር ባለሟሉን በላከበትም ጊዜ፥ ከቤቱ ሁኖ ስለዐወቀ አብረውት ላሉ ሽማግሌዎች፥
መልእክተኛው ገና ሳይደርስ፥ «ይህ የነፍሰ ገዳይ ልጅ ራሴን ይቆርጥ ዘንድ እንደላከ እዩ፤ መልእክተኛውም በመጣ ጊዜ
ደጁን ዘግታችሁ ከልክሉት፤ በደጅም ይቆም ዘንድ ተዉት፤ የጌታው የእግሩ ኮቴ በኋላው ነው፤» ብሏል። ከእነርሱም
ጋር ሲነጋገር እነሆ፥ መልእክተኛው ወደ እርሱ ደረሰ ይላል። ፪ኛ ነገ ፮፥፴፩-፴፫። በነቢዩ በኤልሳዕ አማላጅነት፥
ወንድ ልጅ አግኝታ የነበረችው የሱነም ሴት፥ ልጇ በሞተባት ጊዜ፥ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ገስግሳ በመምጣት፥ ከእግሩ
ስር ወድቃ ሰገደች። የነቢዩ የኤልሳዕ ሎሌ ግያዝ «እንዴት ትነካዋለች» በሚል መንፈስ ሊያርቃት መጣ። ኤልሳዕ ግን ፥
«ነፍስዋ አዝናለችና ተዋት፤ እግዚአብሔርም ያን ከእኔ ሰውሮታል፤ አልነገረኝምም፤» አለ። ፪ኛ ነገ ፬፥፰-፴፫።
ነቢዩ ኤልሳዕ በተሰጠው ጸጋ ብዙ ነገር ቢያውቅም ስለ ሱነሟ ሴት ግን ያላወቀው ነገር ነበረ። ጻድቁ ዮሴፍም ልክ
እንደዚሁ ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ያላወቀው ምሥጢር ነበረ።
መናፍቃን
ግን አስተሳሰባቸው ሥጋዊ በመሆኑ፥ «ቃየልም ሚስቱን ዐወቃት፤ ፀነሰችም፤ ሄኖሕንም ወለደች።» በሚለው መንገድ
ተጉዘው፥ የበኲር ልጅዋን እስከምትወልድ ድረስ በግብር አላወቃትም፥ ከወለደች በኋላ ግን በግብር ዐውቋታል፥ በማለት
ጆሮን ጭው የሚያደርግ ቃል ይናገራሉ። ዘፍ ፩፥፲፯። ይህም፥ ቁራ ከጥፋት ውኃ በኋላ ተመልሷል፥ ሜልኮል ከሞተች
በኋላ በመቃብር ወልዳለች፥ ጌታ ቅዱሳን ሐዋርያትን ከዓለም ፍጻሜ በኋላ ይለያቸዋል፥ ኢየሱስ በአብ ቀኝ መቀመጡ
ጠላቶቹን እስኪያዝገዛለት ድረስ ስለነበር አሁን በቀኙ የለም፥ እንደ ማለት ነው። በዚህም መንገድ ቢሆን ፈጽሞ
አላወቃትም ተብሎ ፍጻሜ በሌለው እስከ ይተረጐማል እንጂ ፍጻሜ ባለው እስከ አይተረጐምም። ለመሆኑ «ወደ ምሥራቅም
ወደሚመለከተው በስተውጭ ወደአለው ወደ መቅደሱ በር ++መለሰኝ፤ ተዘግቶም ነበር። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥
ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም፤ (በድንግልና እንደጸናች ትኖራለች)፤ ሰውም አይገባባትም፤ (ዕሩቅ
ብእሲ ከእርሷ የሚወለድ አይደለም፥ እንደሔዋን ወንዶችን ለማገልገል የተፈጠረች አይደለችም)፤ የእስራኤል አምላክ
እግዚአብሔር ገብቶባታልና ተዘግታ ትኖራለች። (አምላክ በግብረ መንፈስ ቅዱስ በተዋሕዶ ከእርሷ ሰው ሁኖ ተወልዷልና፥
በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ወልደዋለችና በድንግልና ጸንታ ትኖራለች)።» የሚለውን የነቢዩ የሕዝቅኤልን ቃለ
ትንቢት ወዴት ጥለውት ነው? ሕዝ ፵፬፥፩-፬።
«ስለ ጻድቁ ስለ ዮሴፍ የምንናገረውን እንወቅ፤»
ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፲፮
ካለፈው የቀጠለ . . .
«ስለ ጻድቁ ስለ ዮሴፍ የምንናገረውን እንወቅ፤»
የቊስጥንጥንያ
ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ ኤራቅሊስ፦ ከቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል፥ «የበኲር ልጅዋንም እስከምትወልድ ድረስ
አላወቃትም፤» የሚለውን ንባብ በተረጐመበት አንቀጽ ላይ፥ «ናእምር እንከ ዘንሔሊ በእንተ ብፁዓዊ ዮሴፍ ቅዱስ
ወምእመን፥ እስመ ውእቱ ኢያእመረ ምሥጢረ ዘይትፌጸም በእግዝእትነ ቅድስት ድንግል ማርያም። የታመነ፥ የከበረ፥
የተመሰገነ ስለሚሆን ስለዮሴፍ የምንናገረውን እንወቅ፥ እርሱ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የሚፈጸመውን
ምሥጢር አላወቀምና፤» ብሏል። ይኸውም፦ ትምህርታቸው በሊቃውንት ደረጃ የሁኑ፥ ነገር ግን ቃሉን ያለ መንገዱ
የሚተረጉሙ መናፍቃን በመነሣታቸው ለእነርሱ መልስ ይሆን ዘንድ ነው። «የምንናገረውን እንወቅ፤» ማለቱም
«እናስተውል፤» ማለቱ ነው። ምክንያቱም ምን ቢማሩ ባለማስተዋል መጥፋት፥ ማጥፋትም አለና ነው። ሊቃውንት
ዕውቀታቸውን በትህትና ካልያዙትና በጸሎት ካልጠበቁት በስተቀር መሰናክል እንደሚሆንባቸው ከጥንት ጀምሮ ከተነሡ
መናፍቃን መረዳት ይቻላል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በግሉ በጸሎት ከመትጋት ጋር ምእመናንን፦ «በምስጋና እየተጋችሁ
ለጸሎት ፅሙዳን ሁኑ። ስለ እርሱ የታሰርሁለትን የእግዚአብሔርን ምሥጢር እንድንናገር፥ እግዚአብሔር የቃሉን በር
ይከፍትልን ዘንድ ለእኛም ደግሞ ጸልዩልን፤ ለምኑልንም፤ ልናገርም እንደሚገባኝ እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ፤» ይል
የነበረው በአገልግሎቱ ችግር እንዳይፈጠር ነበር።
ቈላ ፬፥፪-፬። በመሆኑም ሐዋርያውን አብነት አድርጎ፥ በጸሎት የተጋ፥ በትህትና ያጌጠ፥ በደጋግ ምእመናን ጸሎት
የተጠበቀ ቅዱስ ኤራቅሊስ «አላወቃትም፤» የሚለውን እንደሚከተለው ተርጉሞ አስተምሯል።
ሀ፦
ጻድቁ ዮሴፍ አገልጋይ የሆነለትን ምሥጢር (በተዋሕዶ አምላክ ሰው፥ ሰውም አምላክ የሆነበትን ምሥጢር) አላወቀም፤
ለእርሱ ከታጨችለት (እንዲጠብቃት፥ እንዲያገለግላት ከተሰጠችው) ከድንግል፥ ነቢያት ስለ እርሱ፦ «ስለዚህ ጌታ ራሱ
ምልክት ይሰጣችኋል፤ (ከሥጋ መቅሠፍት የምትድኑበትን ምልክት ስላመናችሁ ከነፍስ መቅሠፍት የምትድኑበት ምልክት
ይሰጣችኋል)፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም (ወልድን) ትወልዳለች፤ (ምልክት ያልኳችሁም ድንግል
በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷን ነው)፤ ስሙንም አማኑኤል (አምላክ ወሰብእ፥ እግዚእ ወገብር) ትለዋለች። . . . ሕፃን
ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም (ወልድ) ተሰጥቶናልና፤ (ለሕማም፥ ለሞት ተሰጠልን)፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ
ይሆናል፤ (ለጌታ ሥልጣን የባሕርዩ ነው፤ አንድም መስቀል በትከሻው ላይ ነው፤ አንድም የደከመን ሰው በትከሻ
ተሸክመው እንዲያሳርፉት፥ እርሱም በሚቀበለው መከራ ነፍሳትን ያሳርፋል)፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥
የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፤» በማለት የተናገሩለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በመንፈስ ቅዱስ
ግብር ያለ ዘር አንዲወ ለድ አላወቀም፤ (ሕፃን ያለ አባት እንዲገኝ አላወቀም)። ኢሳ ፯፥፲፬፣ ፱፥፮-፯። ይኽንን
ታላቅ ምሥጢር የተረዳ ፊለጶስ ግን፦ «ሙሴ በኦሪት ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው፤»
ብሏል። እንዲህ የተባለ ናትናኤል፥ ለጊዜው ምሳሌ ኦሪትና ትንቢተ ነቢያት የተፈጸመበትን ምሥጢር ባለማወቁ፦ «በውኑ
ከናዝሬት ደግ ሰው ሊወጣ ይችላልን?» ሲል ጠይቋል። ለፍጻሜው ግን፥ ምሥጢሩን በማወቁና በመረዳቱ መምህር ሆይ፥
በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ የእስራኤልም ንጉሥ አንተ ነህ፤» በማለት እምነቱን መስክሯል። ጌታም፦
«በበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ፤ (ሄሮድስ ሕፃናትን ባስፈጀ ጊዜ፥ ወላጆችህ በንብ ቀፎ አድርገው ከበለስ በታች ሲደብቁህ
የጠበኩህ እኔ ነኝ፤ ወጣት ሳለህም ከበለስ በታች ከሰው ተሰውረህ ያፈሰስከውን ደም፥ ያሳለፍከውን ነፍስ
(የበደለህን ሰው እንደገደልከው) እኔ አውቃለሁ)፤ ስላልኩህ አመንህን? ገና ከዚህ የሚበልጥ ታያለህ፤» ብሎታል።
ዮሐ ፩፥፵፬-፶፩።
ለ፦
ጻድቁ ዮሴፍ፦ ነቢዩ ኢሳይያስ፥ «የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን (መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ያልወ ደቀባትን
ዘር ድንግል ማርያምን) ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንን፥ እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር። (ዕድል ፈንታችን
ጽዋ ተርታችን በማይጠፋ እሳት መቃጠል ይሆን ነበር)።» እንዳለ፥ ከንጹሕ ዘር የተፈጠረች ድንግል የእግዚአብሔር
ማደሪያ እንድትሆን፦ (እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ ይህች ለዘለዓለም
ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ፤ ተብሎ በቅዱስ ዳዊት አንደበት በእግዚአብሔር የተነገረላት እርሷ
መሆኗን) አላወቀም። ኢሳ ፩፥፱ ፣ መዝ ፩፻፴፩፥፲፫። ዳግመኛም፦ በጻድቁ በኖኅ አንደበት፥ «እግዚአብሔር . . .
በሴም ድንኳን ይደር፤» የተባለላት (የሴም ድንኳን ምሳሌዋ የሆነላት) እርሷ መሆኗን አላወቀም። ዘፍ ፱፥፳፯።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ሁለተኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤» ብሎ እንደተናገረለት ዳግማይ አዳም
ክርስቶስ ድንግ ልና ካላት ገነት (ጠቢቡ ሰሎሞን እኅቴ ሙሽሪት የተቈለፈች ገነት፥ የተዘጋች ገነት፥ የታተመችም
ጉድጓድ ናት ብሎ ከተናገረላት እመቤት) እንዲገኝ አላወቀም። ፩ኛ ቆሮ ፲፭፥፵፭፣ መኃ ፬፥፲፪።
ሐ፦
ጻድቁ ዮሴፍ፦ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፦ «ሁሉም በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም ያለእርሱ ምንም የሆነ የለም፤» ብሎ
የመሰከረለት፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «ይኸውም የማይታይ እግዚአብሔርን የሚመስለው (በባሕርይ የሚተካ ከለው)፥
ከፍጥረቱ ሁሉ በላይ የሆነ በኲር ነው። (የፈጠረውን ፍጥረት የሚገዛ የፍጥረታት አለቃ ነው)። በእርሱ ቃልነት
እግዚአብሔር ሁሉን ፈጥሮአልና፥ በሰማይ ያለውን በምድርም ያለውን፥ የሚታየውንና የማይታየውን፥ መናብርትም ቢሆኑ፥
አጋእዝትም ቢሆኑ፥ መኳንንትም ቢሆኑ፥ ቀደምትም ቢሆኑ፥ ሁሉን በእርሱ ቃልነት ፈጥሮአቸዋልና፤ ሁሉም በእጁ ሆነ፤
ሁሉም በእርሱ ለእርሱ ተፈጠረ፤ እርሱ ከሁሉ አስቀድሞ ነበረ፤ ሁሉም በእርሱ ጸና።» በማለት የተናገረለት፥ ፍጡራንን
ሁሉ የፈጠረ ክርስቶስ ያለዘር እንዲወለድ አላወቀም። ዮሐ ፩፥፬፣ ቈላ ፩፥፲፭-፲፰። ዳግመኛም ጠቢቡ ሰሎሞን፥
«አበባ በምድር ላይ ታየ፤ (አበባ ክርስቶስ ከምድር ከተፈጠርን ከእኛ በሥጋ ተገለጠ)፤» ብሎ እንደተናገረ፥ ነቢዩ
ዳዊትም፦ «ምድርም ፍሬዋን ትሰጣለች (ከእኛ ከምድራዊያን ወገን ከሆነች ከድንግል ፍሬ ክርስቶስ ይወለዳል)፤»
በማለት እንደተነበየ፥ «እነሆ፥ ጻድቅ ንጉሥ ይነግሣል፤ (ጻድቅ ንጉሥ ጌታ በማኅፀነ ድንግል ይነግሣል፥ አንድም
በማዕከለ ሐዋርያት ይነግሣል፥ አንድም በመስቀል ላይ ይነግሣል)፤ መሳፍንትም በፍርድ ይገዛሉ። (ቅዱሳን ሐዋርያት
በእውነት ያስተምራሉ)።» እንዳለ፥ ይህ ሁሉ የተነገረለት አምላክ ከእርሷ እንዲወለድ አላወቀም። መኃ ፪፧፲፪፣ መዝ
፹፭፥፲፪፣ ኢሳ ፴፪፥፩።
ትንቢተ
ነቢያት የሚፈጸምበት ዘመን ሲደርስ፥የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፥ ከእግዚአብሔር ተልኮ በመምጣት፥ «ማርያም
ሆይ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነት አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅንም (ወልድን)
ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ። . . . መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤ የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል፤ ከአንቺ
የሚወለደውም ቅዱስ ነው፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፤» አላት። ሉቃ ፩፥፳፮-፴፭። የድንግል ሆዷ ገፋ፥
ያለዘር የፀነሰች የድንግል የሆዷን መግፋት ባየ ጊዜ፥ የዮሴፍ ልቡ አዘነ፤ የንጽሕት እመቤታችንን ምሥጢሯን ፈጽሞ
መረመረና በማያውቀው ምሥጢር ፀንሳ ቢያገኛት በጽኑ አሳብ በማውጣት በማውረድ ተያዘ፥ ፀንሳ አገኛት፥ በዘር
የፀነሰችም መሰለው፤ ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ «የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርሷ የሚወለደው በመንፈስ ቅዱስ
ነውና፤» ብሎ እስኪነግረው ድረስ ተቸግሮ ነበር። ማቴ ፩፥፳። ዮሴፍም ይህን በሰማ ጊዜ ለድንግል ሰገደ፥
ንጽሕናዋንም አመነ፤ ነቢዩ ኢሳይያስ፦ «እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙም አማኑኤል
ይባላል፥ ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ባሕርይ ጋር አንድ ሆነ ማለት ነው፤» ብሎ የተናገረላት ድንግል እርሷ
እንደሆነች አወቀ።
ማርያም የመላኩን ንግግር በሰማች ግዜ "ይህ እንዴት ይሆናል?" ነበር ያለችው, ምክንያቱም በሰው እንደማይቻል ማርያም ታውቅ ነበረ:: መልዓኩ ገብርኤልም ቢሆን አሁን የነገራት መልዕክት በሰው እንደማይቻል ስለሚያውቅ, የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ እንደሚሆንላት ነገራት,
ReplyDelete(የሉቃስ ወንጌል ምዕ. 1)
----------
35፤ መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል
በተጨማሪም እንዲህ አላት
. . .
37፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።
ስለዚህ የሰው ስጋ አምላክን ተሸከመ ስንል በአምላክ እገዛ እንጂ, ስጋችን በራሱ አቅም እንደሌለው ሊታወቅ ይገባል::
ሙሴ አምላክን ለማየት ፈልጎ "ክብርህን (ራስህን) አሳየኝ" ባለው ግዜ, እግዚአብሔር እንዲህ በማለት መለሰለት
" ደግሞም። ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም አለ።"
(ኦሪት ዘጸአት 33:20)
በተጨማሪ የሰው ዘር ሁሉ ሐጥአተኛ ስለሆነ ከሀጥአት በሽታ መዳን ይጠበቅበታል:: ለዚህ ነው ኢየሱስ ሰውን ሊያድን ወደ ምድር የመጣው:: የሀጥአት መድሐኒት (የነፍሳችን መድሐኒት) ቢኖር ኖሮ ኢየሱስ ባልመጣልን እና ባልሞተልን ነበረ:: ማርያም መድሃኒት ብትሆን ኖሮ ኢየሱስ አያስፈልገንም ነበር::
ማርያም ራሷ የአዳም ዘር ስለሆነች, ሐጥአት አለባት, ለዚህ ነው አምላክዋን መድሃኒቴ ትለዋለች::
" ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤"
(የሉቃስ ወንጌል 1:47)
(ማርያም መድሃኒት ነሽ አልተባለችም, መድሃኒት የሆነውን ኢየሱስን እንደምትወልድ ተነገራት እንጂ)
መፅሀፍ ቅዱስ ሰው ሁሉ ሀጥያተኛ እንደሆነ, እንዲሁም በኢየሱስ ብቻ እንደሚድን ያስተምራል: :
" ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤"
(ወደ ሮሜ ሰዎች 3:23)
" ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።"
(1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1:8)
"... የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።"
(1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1:7)
(ከመጽሐፍ ቅዱስ ለመማር እፈቅዳለው, ሌሎች አስተያየቶችን አከብራለሁ, ማርያምን አከብራታለው እወዳታለው)
እና ምን?
ReplyDeleteWondime unknown, the Blessed Virgin Mary said "መድሐኒቴ" not because She Inherited Her Father Adam sin, but for Almighty God protect Her in her mother's womb. That is why Saint Gabriel called her "Full Of Grace and again God Is With You". if She is sinned that means our Lord and savior Jesus Christ incarnate the Sinned flesh. But That Could never Happened. She Protected starting from her Conception. Medicine not Always for Sick but also for protection. Thanks
ReplyDelete