Thursday, 3 December 2015

ጋኔንን በመዛመድ ማሳሳት

ጋኔንን በመዛመድ ማሳሳት----------ዓባይነህ ካሤ (ዲን)
"የአጥማቂዎቹ" ምስክሮች እና አዲስ "ዶግማቸው"
አንዳንድ "አጥማቂ" ነን ባዮች በያሉበት ከዚህ ቀደም በቅድስተ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ "ምስክር" እያስተዋወቁን ነው፡፡ የእነርሱን ምስክር ከማየታችን በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቅና የተሰጣቸውን ምስክሮች ቀድመን ማየት ይጠበቅብናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች ያላቸው የሚከተሉትን ነው፡፡
፩. ሥሉስ ቅዱስ
ከምስክር ሁሉ በላይ የኾነው ምስክር እግዚአብሔር ስለራሱ የሰጠው ምስክርነት ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍጹም ነውና ከእርሱ በላይ ስለእርሱ ሊነግረን የሚችል የለም፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ " እግዚአብሔርን ያየው አንድስ እንኳ የለም፡፡ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው" ሲል የደመደመው፡፡ የሐ ፩፥፲፷። አብን በወልድ ምስክርነት እንዳወቅነው ሁሉ ወልድንም በአብ ምስክርነት ዐውቀነዋል፡፡ መንፈስቅዱስንም እንዲሁ በአብ እና በወልድ ምስክርነት እንዳወቅነው ሁሉ አብና ወልድም ስለመንፈስቅዱስ መስክረዋል፡፡
ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን ስለራሱ ሲመሰክር በሙሉ ሥልጣኑ እንዲህ አለ፡፡ "ኢየሱስ መለሰ አላቸውም፦ እኔ ስለ ራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው" ዮሐ ፷፥፲፬። የባሕርዪ አባቱ የአብን ምስክርነት ደግሞ እንዲህ በማለት ይገልጠዋል፡፡ "እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፥ ይህ የማደርገው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና። የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል፡፡" እንዲል፡፡ ዮሐ ፭፥፴፮-፴፯።
እውነት ነው! በባሕረ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ጌታችን ሲጠመቅ አብ በደመና ኾኖ "በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው" ሲል ሰምተነዋል፡፡ ማቴ ፫፥፲፯። ደግሞም በደብረ ታቦር (በታቦር ተራራ) ይኸንኑ ቃል አብ እዚያው በሰማያት ኾኖ ሲደግመው ሰምተናል፡፡ "ከደመናው፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።" እንዲል ፡፡ ማቴ ፲፯፥፭።
መንፈስ ቅዱስም ስለ ወልድ የባሕርዪ አምላክነት ሲመሰክር በአምሳለ ርግብ ኾኖ በላዩ ላይ ሲያርፍ ዐይተናል፡፡ "የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ ዐየ" እንዲል፡፡ ማቴ ፫፥፲፮። ጌታችንም ከዕርገት በኋላ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ቅዱሳን ሐዋርያት እንደሚቀበሉ የተሰወረውን ምስጢር ሁሉ እንደሚገልጥላቸው ደግሞም ስለእርሱ የባሕርዪ አምላክነት ከመንፈስቅዱስ እንደሚሰሙ ሲናገር "ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል" ብሎ ነበር፡፡ ዮሐ ፲፭፥፳፮።
፪. ሥራው
ጌታችን እንደሰውነቱ ያደረጋቸው ሥራዎች እንዳሉ ሁሉ እንደ አምላክነቱ ያደረጋቸው ሥራዎችም አሉ፡፡ ነገር ግን እንዚህን ሁሉ ሰፍረን ቆጥረን ዘርዝረን አንዘልቃቸውም፡፡ ነገር ግን የባሕርዪ አምላክ የሚያደርገውን ሥራ በዘመነ ሥጋዌው እኛን በሚገባን ደረጃ ሲፈጽም ስለኖረ ከሥራው ማንነቱን ልናውቅ ችለናል፡፡ ስለዚህም የጌታችን ሥራው ለአምላክነቱ ምስክር ነው እንላለን፡፡ ለዚህም ነው "እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤ ባደርገው ግን፥ እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።" ሲል የተናገረው፡፡ ዮሐ ፲፥፴፯-፴፷። ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ አብን አኽሎ አብን መስሎ የአብን ሥራ ለማድረግ ሥላጣን ያለው ከአብ ጋር የተካካለ መኾኑን ሥራው ይመሰክራልና ሁለተኛው ምስክር ሥራው ነው፡፡
፫. ቅዱሳን
ከራሱ ከእግዚአብሔር እና ከሥራው ቀጥሎ በምስክርነት የሚጠቀሱት ቅዱሳን ናቸው፡፡ ቅዱሳን ስንል ቅዱሳን መላእክትን እና ቅዱሳን ሰዎችን ያጠቃልላል፡፡ በተለይም ቅዱሳን ሰዎች እስከሞት ድረስ ሥጋቸው እየተተለተለ፣ በሰይፍ እየተቀሉ፣ በመጋዝ እየተተረተሩ፣ በእሳት እየተቃጠሉ በብዙ መከራ ውስጥ እያለፉ የመሰከሩ ናቸውና ሰማዕታት ተብለዋል፡፡ ሰማዕታት ማለት ምስክሮች ማለት ነው፡፡
ጌታችን ደቀመዛሙርቱን "እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ።" ያላቸው ለዚህ ነው፡፡ ሉቃ ፳፬፥፵፷። ለዚህም ነው ቅዱሳን ሐዋርያት "እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት።" ሲሉ የተናገሩት፡፡ ሥራ ፲፥፴፱። ደግሞም "ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።" እንዲል፡፡ ሥራ ፩፥፷።
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ "ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ።" የተባለው ምስክርነቱ ብርሃን ለተባለ ለክርስቶስ ነበረ፡፡ ዮሐ ፩፥፯። ስለዚህ በቅዱሳኑ ምስክርነት እናምናለን፡፡
፬. ቅዱሳት መጻሕፍት
በአራተኛ ደረጃ ቅዱሳት መጻሕፍት የክርስቶስ ምስክሮች ናቸው፡፡ ይህንንም መጽሐፍ "እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው" በማለት ያረጋግጥልናል፡፡ዮሐ ፭፥፴፱። ከቅዱሳት መጻሕፍት መካከል ወንጌል ቅድምና ያላት ምስክር እንደኾነች ጌታችን እንደዚህ ሲል ነግሮናል፡፡ "ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።" ማቴ ፳፬፥፲፬።
የጠቀስናቸውን ምስክሮች ልብ ብለን እንመልከት፡፡ ጌታችን ራሱ ምስክር ብሎ የጠራቸውን እንጂ በእኛ መላምት የመረጥናቸው እንዳልኾኑ ልብ እንበል፡፡ እናም በባሕርዪው ቅዱስ ለኾነው እግዚአብሔር ምስክሮቹም ቅዱሳን ናቸው፡፡ ስለኾኑም ቅዱስ ዳዊት "ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው፤ ስለዚህ ነፍሴ ፈለገቻቸው።" ሲል ይናገራል፡፡ መዝ ፻፻፲፰፥፻፳፱። እነዚህን የመሳሰሉ ስለክርስቶስ ሲመሰክሩ እናውቃለን፡፡ አሁን አሁን ግን አንዳንድ አሳቾች "የአጋንንትን ምስክርነት" ማስረጃ እያደረጉ በተለያየ መልኩ ለገበያ በማቅረብ ኪሳቸውን እያደለቡ ይገኛሉ፡፡
የአጋንንት ምስክርነት የሚባልስ አለን?
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሌለ እንግዳ ነገር እያመጡ ሕዝብን ማደናገር ስህተት ብቻ ሳይኾን የሚያስወግዝ ድርጊት ነው፡፡ እኛ የምናውቀው ጌታ አጋንንት ስለእርሱ ለመናገር አፋቸውን ሲከፍቱ ጸጥ ያደረጋቸውን ነው፡፡ ጌታችን ወደቅፍርናሆም ሲገባ ርኩስ መንፈስ ያደረበትን አንድ ሰው አገኘ፡፡ በሰውየው ላይ ያደረው ክፉ መንፈስም ገና ምንም ሳይባል መቀባጠር ጀመረ፡፡ እንዲህ እያለ "የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ።"
ንጹሐ ባሕርዪ ጌታችን ንጹሕ ምስክርነት እንዲሁም ምስጋና ከንጹሐን ይቀበላል እንጂ ከርኩሳን መናፍስት አይቀበልምና "ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው።" ማር ፩፥፳፭። ሲያጸናውም ከዚህ ሰው ወዲያ ሌሎች አጋንንት ያደሩባቸውን ሰዎች ሲፈውስ አጋንንቱ እርሱ እግዚአብሔር መኾኑን ስላወቁ ያወቁትን እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም፡፡ "አጋንንትም ክርስቶስ መሆኑን አውቀው ነበርና ሊናገሩ አልፈቀደላቸውም።" እንዲል ማር ፩፥፴፬። ቅዱስ ሉቃስም ይኽንኑ እውነት ጽፎታል፡፡ ሉቃ ፬፥፴፭-፵፩።
ከዚህ የምንረዳው ጌታችን መቼም ቢኾን የአጋንንትን ምስክርነት እንደማይቀበል ነው፡፡ የትኛውም ጋኔን ክፉ ተናግሮ አልነበረም፡፡ ሊናገርም አይችልም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በጭራሽ የእነርሱን ምስክርነት አልፈለገውምና እንዲናገሩም አልፈቀደላቸውም፡፡ ክርስቶስ እንዳይናገሩ አፋቸውን የለጎማቸውን አጋንንት ዛሬ አንዳንዶቹ አስለፈለፍናቸው በሚል የዋኁን ምእመን ግራ ያጋቡታል፡፡ ክርስቶስ የከለከለውን የሚፈቅድ እርሱ የክርስቶስ አይደለም፡፡ ስለኾነም የቤተ ክርስቲያን አለመኾናቸውን ራሳቸው እየነገሩን እንደኾነ በማወቅ ከስሁት አሠራራቸው እንጠበቅ ዘንድ ራሳችንን እንምከር፡፡
መድረክ ለተከለከለ ጋኔን መድረክ ማመቻቸት ምን የሚሉት ሥራ ነው? እንዲህም አድርጎ ጸጋ የለምና በዚህ ክፉ ሥራቸው አንተባበርም፡፡ በተቀደሰው የእግዚአብሔር ዐውደ ምሕረት ላይ ርኩሳን መናፍስት ይናገሩበት፣ ይፈነጩበት ዘንድ መፍቀድ ኢ-ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡ እንዲያውም መድረኩን ቀስ በቀስ ለአለቃቸው ለሐሳዊ መሲህ የማመቻቸት ሥራ ይመስላል፡፡
ጌታችን እንዳይናገሩ የከለከላቸውን የአጋንንትን ምስክርነት ቅዱሳኑም አልተቀበሉም፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትን ያወደሰች ያመሰገነች እየመሰለች የማታለል ሥራ ለመሥራት እንዲመቻት ታደርግ የነበረች አንዲት ጠንቋይ ይህን ስልት ለመጠቀም ሞክራ ነበር፡፡ እንዳትነቀፍ ቅዱሳንን የተቀበለች ለመምሰል ትሞክራለች፡፡ ይህም ገበያዋ እንዳይታጎልባት የቀየሰችው መንገድ ነበረ፡፡ ቅዱሳኑን ብትቃወም ኖሮ ዘወር ብሎ የሚያያት አይኖርም ነበረና በስልት በአደባባይ የማታምንበትን ምስክርነት ልትሰጥ ትሞክራለች፡፡ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፡-
"ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን። እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፦ የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር። ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን፦ ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ።" ፲፮፥፲፮-፲፷።
ዛሬም ቅዱሳኑን የተቀበሉ የሚመስሉ የአጋንንት አገልጋዮች አሉና እናውቅባቸው ዘንድ ይገባል፡፡ ስመ ቅዱሳንን መጥራት ብቻ የእግዚአብሔር መኾንን አያመለክትም፡፡ ከዚህች ሴት የምንረዳው ይኽንኑ ሲኾን ሐዋርያትም አልፈቀዱላትም፡፡ ስለዚህ ለጋኔን ፈቃድ ሰጥተው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መድረክ የሚያስፈነጩ ሁሉ በምንም መንገድ የእና ናቸው ሊባሉ አይችሉም፡፡ ነገር ግን ከተያዙበት ቁራኝነት ተላቅቀው ዕድሜ ለፍስሐ ዘመን ለንስሐ ያገኙ ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡
አዲስ "ዶግማ"?
"አጥማቂ" ነን ባዮቹ ከሚፈጽሙት መሠረታዊ ስህተት አንዱ አዲስ ነገረ ሃይማኖት ያውም ኑፋቄ አሾልከው ለማስገባት የሚያደርጉት ጥረት ነው፡፡ በተደጋጋሚ እንደምንሰማው "በኢየሱስ ስም አልወጣም ያለው ጋኔን በማርያም ስም ወጣ" የሚል ግልብ ማደናገሪያ በማኅበረሰባችን ውስጥ ቀስ እያደረጉ እያስገቡ ነው፡፡ እንዴት? ተብለው ሲጠየቁ በኢየሱስ ስም ሲባል የማይወጣው ሐሰተኛ ኢየሱስ ስላለ ነው ይላሉ፡፡
አላወቁትም እንጂ እነርሱ እየጠሩት ያለው ሐሰተኛ ኢየሱስ መኾኑን ነው፡፡ አማናዊውን ኢየሱስ (እውነተኛውን ኢየሱስ) እንደማይጠሩት በዚህ አረጋገጡልን ማለት ነው፡፡ ጋኔኑማ አማናዊውን እንዳይጠራ ግዝት አለበት፡፡ ደግሞ እውነተኛውን ከሐሰተኛው እየለየ የሚነግራቸው ጋኔኑ እንጂ እነርሱ አለመኾናቸውን ስናውቅ ምን ያኽል በክፉ ቁራኝነት እንደተቀፈደዱ እንረዳለን፡፡ እነርሱ እንደሚሉት ከኾነ ጋኔኑ እኮ ነው ለምንድን ነው በኢየሱስ ስም ስትባል የማትወጣው ተብሎ ተጠይቆ እነርሱ የሚለፍፉትን "ማምለጫ" ያስተማራቸው፡፡ ጋኔኑማ በአማናዊው ኢየሱስ ስም ምንም ነገር እንዳያደርግ ዝምም እንዲል ስለተደረገ ምንም የማድረግ ሥልጣን የለውም፡፡ ታዲያ ተከታዮቻቸው ጋኔኑ እየሠራ ያለው በተቃራኒው እንደኾነ እንዴት ማወቅ ተሳናቸው? መልሱ አንድ እና አንድ ብቻ ነው የያዘ ቢይዛቸው የሚል፡፡
ከጋኔን ሰምቶ ጽድቅ የለም፡፡ እንዲሁም በጋኔን የማሳሳቻ ስልት ተባባሪ መኾን የእርሱ ተከታይነትን ከማረጋገጥ በቀር ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡ በእነርሱ ቤት እመቤታችንን ኦርቶዶክሳውያን ይወዳሉና እንዲህ ብንላቸው በቀላሉ ይሞኙልናል ብለው ነው፡፡ እኛ ከክርስቶስ በላይ የኾነች ድንግል ማርያም የለችንም፡፡ እኛ የምናውቃት ቅድስተ ቅዱሳን፣ የጭንቅ አማለጅ ፣ ንጽሕተ ንጹሐን፣ መትሐት ፈጣሪ መልዕልተ ፍጡራን ድንግል ማርያም ካማለደች በኋላ "የሚላችሁን አድርጉ" ብላ ወደ ክርስቶስ የምታቀርበንን ነው፡፡
እውነት ከኾነ ጋኔኑ ራሱ እነርሱ የሚሉትን የማለት ሥልጣን እንደሌለው አሳምሮ ሊነግራቸው ይችላል፡፡ ከዚህም ከዚያም ሳይኾኑ እንዳይቀሩ እንጂ ስለ ጌታችን ጋኔን ሐሰት ይናገር ዘንድ አቅም የለውም፡፡ ምናልባት እርሱ ያላሰበውን እነርሱ አስበውለት እንደኾነ እንጃ! በኢየሱስ ስም ባዮቹ እነርሱ ኾነው ሳለ ጋኔኑ ያለው የተናገረው አስመስለው ማቅረባቸው በጣም አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡ እነርሱ ከጠሩት ደግሞ ሐሰተኛው የሚለውን ምን አመጣው? ወትሮውኑም ጠሪው የጠራው ሐሰተኛውን ስለኾነ እንጂ፡፡ እነርሱ የጠሩትን ጋኔኑ "እርሱማ ሐሰተኛው ነው" ሲላቸው ካመኑት እነዚህ ሰዎች ከእግዚአብሔር ይልቅ የሚያምኑት ዲያብሎስን ለመኾኑ ሌላ ማስረጃ ፍለጋ መሄድ አያስፈልግም፡፡
ስለዚህ ከእነዚህ አስመሳዮች ራሳችንን መጠበቅ አለብን፡፡ ከመከተል በፊት ከሃይማኖታዊ፣ ከቀኖናዊ እና ትውፊታዊ ኦርቶዶክሳዊነት አንፃር እንገምግም፡፡ አጋንንት ያደሩባቸውን ሰዎች በባርነት እና በሌላም ግብረ ኃጣውእ ተብትቦ ይዞ መዞር ክርስቶሳዊነት አይደለም፡፡ ጸጋው ያደረባቸው ወዲያው ይፈውሳሉ ወዲያው ያሰናብታሉ፡፡ በዞሩበት እያዞሩ በባርነት ተብትበው የያዙ ኦርቶዶክሳዊያንንም ኾነ ቅዱሳንን አናውቅም፡፡ ይህ ብቻውን ሊያስተምረን በተገባ ነበር፡፡ ግን እንበልና ተሳሳትን፣ ዛሬ ለመመለስ ደግሞ ምክንያት አናብዛ፣ ሰዎችን ከመከተል ይልቅ የምሕረት በርን በሰፊው ከፍታ ወደምትጠብቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንመለስ፡፡ መሳሳትን ላለመቀበል አንግደርደር፡፡ እግዚአብሔር የተሳሳቱትን ሁሉ ራሳቸውን "አጥማቂ" ነን ባዮችንም ጭምር በቸርነቱ ይመልስልን፡፡

No comments:

Post a Comment