Yeweyin Fikir
የድል ደስታ የድል ዜና
ጽዮንን ክበቧት ለምስጋና
በያሬድ ውብ ዜማ በበገና
ንሴብሆ እንበል በትህትና።
አማናዊት ጽዮን ማርያም
ኪዳንሽ ጽኑ ለዘለአለም
የተማፀነሽ ከቶ አያፍርም
አንቺን ሸልሞናል መድኀኒአለም።
በአዛጦንምድር ያሉ ነፍሳት ሁሉ
ተጨንቀው ሲጮሀኹ ወየው ወየው ሲሉ
የተዋህዶ በር ፀጋ የመስቀሉ
ቅድስተ ቅዱሳን ቤዛዊተ ኩሉ
ታላቅ ነገር ሰራች እሰይ እልል በሉ።
ድንቅ ታምር ሠርታ ያመፁ ተማረኩ
እጅ መንሽ ሰጥተው ታቦቱንም ላኩ
ለህያዋን አምላክ ፈርተው ተንበረከኩ።
ለማይናገረው ዳጎኑ ጠዖት
ምስሉን አቁመው ሲሰግዱለት
እጅና እግር አለው አይሄድበት
አፍና አፍንጫው ታይቶ ለምልክት
ከቶ አይንቀሳቀስ ቀን ከሌሊት
ደረቅ በድን ነበር የሌለው ህይወት።
ታዲያ በዚች ቀን በዙ ታምር ሆነ
የአምላክ ቸርነት ፍቅሩ ተከወነ
በህያው ምስክር ሁሉ አመነ
የከሳሽ ፉከራ ጉድጓድ ተደፈነ
የድንግል ማርያም ልጅ
ክርስቶስ ገነ።
እምዬ ኢትዮጵያ በጣም ደስ ይበልሽ
የኦሪቱን ዘመን ታቦት ተቀብለሽ
በአዲስ ኪዳኑም መስቀል ተሸልመሽ
ጠላትን ማምከኛ የፀናው እምነትሽ
ነገም እንደ ትላንት ዛሬም
ያኔን ሆነሽ
ተነሺ ለምኚ ይዘርጉ እጆችሽ።
የክህደት አርበኛ መንፈስ የባህሩ
ትውልዱን በጉርሻ ቀድሞ ማባረሩ
በሽንገላ ከንፈር መስሎ መደርደሩ
እውነት ተጋርዶበት እንዳያቅ ሚስጢሩ
የያዘውን ረስቶ ደጅ ላይ ማደሩ
በምክረ አጋንንት እርቋል ከፍቅሩ
ስቶ እያሳተ ልቦናን ማወሩ
ታይቷል ሃራጥቃ ይኽው ምስክሩ።
አማናዊት አንባ የፀሐይ እናት
የትውልድ መፅናኛ ፍሬ በረከት
ቅድስተ ቅዱሳን ኪዳነምህረት
ምልጃሽ ይታደገን ወጥቶ ከመቅረት።
የጽዮን ከተማ የዳዊት ሀገር
በኦሪቱ ዘመን መጠጊያ መንደር
በአዲስ ኪዳኑ የወንጌል ማህደር
ድንግል ማርያም ናት መሠረተ ፍቅር
አማኝ ተሰብሰቡ ኑ ና እንዘምር።
ሠይጣን ተሸነፈ እጅግ ተጨነቀ
በኤልሻዳይ ሥልጣን እነሆ ደቀቀ
ዳግም ላይነሳ ተረግጦ ወደቀ
የእርሱ ያልሆኑትን በሙሉ ለቀቀ።
ልክ እንደ አዛጦን ዘመን ዛሬም እየሳቱ
አምላክን እርቀው ጠዖት የሚያሸቱ
ሥሙን እየጠሩ ሞት የሚጎትቱ
በኑፋቄ ትምህርት እየተንገላቱ
አሉ ለምድ ለባሾች የከንቱዎች ከንቱ።
መጽሐፉ ሲገለጥ በሣሙኤል መልእክት
የታቦተ ጽዮን አስገራሚው እውነት
ፈጦ እየታየ የክርስቶስ ምህረት
ዛሬም ይክዳሉ አይልም በማለት
ይከራከራሉ በታቦት በጽላት።
ወገን እናስተውል በጥበብ እንመርምር
ገልጠን ስናነበው የአንድምታውን ሚስጢር
እርሱ ሆኖ ሳለ የዘለአለም መምህር
ኑ አድምጡኝ ብሎ አዶናይ ሲናገር
ሰመተናል አይተናል በዕምነታችን በር።
ስለዚህ አስተውል ሕዝበ እግዚአብሔር ሆይ
ከሠማይ የመጣው ኢየሱስ ኤልሻዳይ
ብርሃን ሊሆነን ነው የማይጠልቀው ፀሐይ
እንማር እንጠይቅ ስለ ሀይማኖት ገዳይ።
እንኳን አደረሰን ለዚች እለት
No comments:
Post a Comment