Thursday, 3 December 2015

የድል ምልክት ነሽ

የድል ምልክት ነሽ
ይህ ነውጠኛ ሥጋ- መተኮሻ ቀስቱ - ነፍሴን ባቆሰለ
ከደመ ነፍሳዊ- እሳታዊ ግለት- ወላፈን የጣለ
በጦሩ አውድማ- በሕይወቴ ዓለም- በዘመቻ ስፍራ
በስጋዬ ቃታ- በ’እጅ ስጥ ድምጾች- ነፍሴ ተወጥራ
ከተሰበቀላት- ከቀስቱ ኢላማ- ቅጽበት መታደጊያ
ከአስጨናቂው ሰዓት-ባልታሰበ ቅጽበት- አንቺ ነሽ መትረፊያ
አንቺ ነሽ መመኪያ፡፡
በቁጣ ለመጣው- በትእግስት የሚቆም- የእስራኤል ጦረኛ
ቆሞ ለተረታው- ተዋግተሸ ‘ምትረቺ- አንቺ ነሽ ሠልፈኛ
በኢሎፍሊ ምድር- ዳጎል በገነነ- አምላኩን ሲረሳ
የፍልስጤም ትምክሂት- በሚያስፈራ ጊዜ- ሊያጠፋን ሲነሳ
ያንን አንገት መድፋት- ያ የልብ ስብራት- የእስራኤል እሮሮ
የህዝቡን ክፉ ውርደት- የሀገሩን ዋይታ- የሀዘን እንጉርጉሮ
የሚያቆም አንድ አባሽ- የሚያጽናና ጋሻ- ቀስቱን የሚመክት
የኑሮውን ዳጎል- በኢሎፍሊ ሰባብሮ- የሚሆን መድኃኒት
ሽተን ባጣን ጊዜ- የድል ተስፋ ጮራ- ከምድር ሲፈለግ
በምስራቅ የበቀልሽ- ጽዮን ሆይ አንቺ አለሽ- ባለ ፍሬ ሀረግ
ነሽ አንቺ ታዳጊ- በአንገት መድፋት ሀገር- ድልን አስታጣቂ
ሺ ሆነው ሲሸነፉ- አንድ ሆነሽ ብቸኛ- ጠላት አስጨናቂ
ከምርኮ በክብር- በዚያ ሠረገላ- ለነ አሚናዳብ
ለነ አቢዳራ- የቤታቸው ሞገስ- የደስታቸው ወደብ
ለነ ዳዊት ሀሴት- ለነ ኦዝያ ቅስፈት- እርግማን ለሜልኮል
ከዲያብሎስ ወጥመድ- ድል ነሺ ‘ሚሆንብሽ- መንፈሳዊ አካል
የሚገዳደሩሽ- ጽዮንን የጠሉ- ከዓላማ እንዳይደርሱ
ትዕቢት ለሞላቸው- ፍሬ አልባ እንደሆነው- ልክ እንደ በለሱ
የምስጢርሽ ንባብ- ፊደል ላልገባቸው- አንቺን ላቀለሉ
ክብርና ፍቅርሽን- ረግጠው ለሚሄዱት- ቀምሰው ላልታደሉ
ወየው ወየው ብሎ- በሚጮህ ሰባኪ- ፌዝን የታጠቁ
ከታሪክ
ከትንቢት
ጽዪንን መገዳደር-
በውርደት ሜዳ ሆነው- በቅዠት ተይዘው- ድል መጮህ መሆኑን- ምነዋ ባወቁ?
ለሽባው ምድራችን- ለዚህ ችግረኛ- ለታማማው ዓለም
ስድብ ለጎበኛት- ለቁስለኛ ሔዋን- ለተጎዳው አዳም-
ለነቢያት ጩሀት- የለቅሶአቸው ፍሬ- የእንባቸው ዋጋ
ለተሰጠው ተስፋ- ምክንያት የሚሆን- ከሚዛመድ ሥጋ
ለሥዱድ ኤርሚያስ- ለለምጻም ኢሳይያስ- እንዲሁም ዳንኤል- (ምጥው ለአንበሳ)
የሰው ልጅ እንዳይሆን - ተስፋ እንደ ሌለው- እንደ ዱር እንስሳ
ዲያብሎስ ለጣለው- በሥርቆት በዝሙት- ሕይወቱ ላደፈው
በትእቢት ፍላጻ- በፍቅር ንዋይም- ልቡን ለሰየፈው
በዚያ አስፈሪ ጊዜ- ዋስ ጠበቃ ጠፍቶ- ሲያስፈራ እሳቱ
አንቺ ነሽ መዳኛ- ጽዮን መሸሸጊያ - የድል ምልክቱ፡፡
(አክሊሉ ደበላ 2008ዓ.ም)
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን!!!

No comments:

Post a Comment