Thursday, 3 December 2015

የድል ምልክት ነሽ

የድል ምልክት ነሽ
ይህ ነውጠኛ ሥጋ- መተኮሻ ቀስቱ - ነፍሴን ባቆሰለ
ከደመ ነፍሳዊ- እሳታዊ ግለት- ወላፈን የጣለ
በጦሩ አውድማ- በሕይወቴ ዓለም- በዘመቻ ስፍራ
በስጋዬ ቃታ- በ’እጅ ስጥ ድምጾች- ነፍሴ ተወጥራ
ከተሰበቀላት- ከቀስቱ ኢላማ- ቅጽበት መታደጊያ
ከአስጨናቂው ሰዓት-ባልታሰበ ቅጽበት- አንቺ ነሽ መትረፊያ
አንቺ ነሽ መመኪያ፡፡
በቁጣ ለመጣው- በትእግስት የሚቆም- የእስራኤል ጦረኛ
ቆሞ ለተረታው- ተዋግተሸ ‘ምትረቺ- አንቺ ነሽ ሠልፈኛ
በኢሎፍሊ ምድር- ዳጎል በገነነ- አምላኩን ሲረሳ
የፍልስጤም ትምክሂት- በሚያስፈራ ጊዜ- ሊያጠፋን ሲነሳ
ያንን አንገት መድፋት- ያ የልብ ስብራት- የእስራኤል እሮሮ
የህዝቡን ክፉ ውርደት- የሀገሩን ዋይታ- የሀዘን እንጉርጉሮ
የሚያቆም አንድ አባሽ- የሚያጽናና ጋሻ- ቀስቱን የሚመክት
የኑሮውን ዳጎል- በኢሎፍሊ ሰባብሮ- የሚሆን መድኃኒት
ሽተን ባጣን ጊዜ- የድል ተስፋ ጮራ- ከምድር ሲፈለግ
በምስራቅ የበቀልሽ- ጽዮን ሆይ አንቺ አለሽ- ባለ ፍሬ ሀረግ
ነሽ አንቺ ታዳጊ- በአንገት መድፋት ሀገር- ድልን አስታጣቂ
ሺ ሆነው ሲሸነፉ- አንድ ሆነሽ ብቸኛ- ጠላት አስጨናቂ
ከምርኮ በክብር- በዚያ ሠረገላ- ለነ አሚናዳብ
ለነ አቢዳራ- የቤታቸው ሞገስ- የደስታቸው ወደብ
ለነ ዳዊት ሀሴት- ለነ ኦዝያ ቅስፈት- እርግማን ለሜልኮል
ከዲያብሎስ ወጥመድ- ድል ነሺ ‘ሚሆንብሽ- መንፈሳዊ አካል
የሚገዳደሩሽ- ጽዮንን የጠሉ- ከዓላማ እንዳይደርሱ
ትዕቢት ለሞላቸው- ፍሬ አልባ እንደሆነው- ልክ እንደ በለሱ
የምስጢርሽ ንባብ- ፊደል ላልገባቸው- አንቺን ላቀለሉ
ክብርና ፍቅርሽን- ረግጠው ለሚሄዱት- ቀምሰው ላልታደሉ
ወየው ወየው ብሎ- በሚጮህ ሰባኪ- ፌዝን የታጠቁ
ከታሪክ
ከትንቢት
ጽዪንን መገዳደር-
በውርደት ሜዳ ሆነው- በቅዠት ተይዘው- ድል መጮህ መሆኑን- ምነዋ ባወቁ?
ለሽባው ምድራችን- ለዚህ ችግረኛ- ለታማማው ዓለም
ስድብ ለጎበኛት- ለቁስለኛ ሔዋን- ለተጎዳው አዳም-
ለነቢያት ጩሀት- የለቅሶአቸው ፍሬ- የእንባቸው ዋጋ
ለተሰጠው ተስፋ- ምክንያት የሚሆን- ከሚዛመድ ሥጋ
ለሥዱድ ኤርሚያስ- ለለምጻም ኢሳይያስ- እንዲሁም ዳንኤል- (ምጥው ለአንበሳ)
የሰው ልጅ እንዳይሆን - ተስፋ እንደ ሌለው- እንደ ዱር እንስሳ
ዲያብሎስ ለጣለው- በሥርቆት በዝሙት- ሕይወቱ ላደፈው
በትእቢት ፍላጻ- በፍቅር ንዋይም- ልቡን ለሰየፈው
በዚያ አስፈሪ ጊዜ- ዋስ ጠበቃ ጠፍቶ- ሲያስፈራ እሳቱ
አንቺ ነሽ መዳኛ- ጽዮን መሸሸጊያ - የድል ምልክቱ፡፡
(አክሊሉ ደበላ 2008ዓ.ም)
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን!!!

"ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ ዘምሩ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ። እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና በማስተዋል ዘምሩ።" ይላል፡፡ መዝ ፵፮፥፮-፯

ቀደም ብለው በገጸ ጦማሬ ከተለጠፉት ጽሑፎች መካከል ያልደረሳቸው ይደርሳቸው ዘንድ . . .
መዝሙር እንዴት ይደመጣል?
ዓባይነህ ካሤ - ዲን
ሰሞኑን አግሮቼ ወደ አንድ ቢሮ ይዘውኝ ገቡ፡፡ በዚያም ቢሮ ውስጥ በርካታ መንፈሳውያን እንዳሉ በሚያረጋግጥ ሁኔታ ከአንድ ኮምፒውተር ላይ አንድ መዝሙር ለስለስ ብሎ ይደመጣል፡፡ ታዲያ እኔም ለመጠየቅ ያኽል የምቀርባቸው ሰዎች ነበሩና ለመኾኑ እያዳመጣችሁት ነው ወይንስ እየሰማችሁት? የሚል ጥያቄ ሰነዘርሁላቸው፡፡ ለካ የሁሉም ጉዳይ ነበረና ሁሉም ስሜቱን መግለጥ ጀመረ፡፡ የሚገርመው መዝሙሩ የሚሰማበት ኮምፒውተር ባለቤት ከፍታው ስለወጣች ውይይቱን የተቀላቀለችው ዘግየት ብላ ነበር፡፡
ሁሉም ሰው በአንድ ነገር ተስማማ፡፡ እርሱም "ባናዳምጠውም የሚያረጋጋ መንፈስ ስለሚፈጥርልን እንዲሁ ስንከፍተው ደስ ይለናል" የሚል ነበር፡፡ እኔም በኩሌን ሀሳብ ሰንዝሬ ተስማምተን ተደማምጠን የሄድሁበትንም ሳልረሳ ወጣሁ፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ በአእምሮዬ እየተመላለሰ ከዛሬ ነገ ሀሳቤን እሰነዝራለሁ ስል የከረምሁበት አጀንዳ ነበረና የእነዚያ ወንድሞች እና እኅቶች ውይይት የበለጠ አነቃኝ፡፡ እናስ እንዴት መዝሙር ይደመጥ?
ዘመረ አመሰገነ ነው፡፡ ስለዚህም መዝሙር ማለት ምስጋና ማለት ነው፡፡ ምስጋና ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ ምስጋና በዜማ ፣ ምስጋና በጸሎት ፣ ምስጋና በጽሑፍ ፣ ምስጋና በአርምሞ ሊቀርብ የሚችል መሥዋዕት ነው፡፡ መዝሙር ስንል በልቡናችን ሰሌዳ ወለል ብሎ የሚታየን ግን በዜማ የሚደረገው ምስጋና ነው፡፡ ይኽም በዜማ የተዋዛ መዝሙር ምስጋና ብቻ ሳይኾን ጸሎትም ነው፡፡ ጸሎትም ምስጋናን ከልመና ያስተዛዘለ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ትምህርትም ነው፣ ደግሞም ምስክርነት ነው፡፡ ያመንነውን እንናገርበታለንና !
ዛሬ ዘመኑ ፈቀደልንና በድቃቂ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የፈለግነውን ያኽል ፋይሎች ይዘን በፈለግነው ቦታ ጥቅም ላይ እናውላለን፡፡ የቅጂ መብት ጉዳይ እንዳታነሡብኝ እንጂ መዝሙራትም እንዲሁ ኾነዋል፡፡
እንዲህ ከኾነ መዝሙር ስንከፍት ምን ልንጠነቀቅ ይገባል?
፩. ማዳመጥ መቻላችንን ማረጋገጥ
ቅዱስ ዳዊት "ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ ዘምሩ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ። እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና በማስተዋል ዘምሩ።" ይላል፡፡ መዝ ፵፮፥፮-፯። ከቅዱስ ቃሉ እንደተረዳነው ሲዘመር ማስተዋል ግዴታ ነው፡፡ መንፈስን ሳይሰበስቡ ምስጋና የለም፡፡ ልቡናን ሳያዘጋጁ ምስጋና የለም፡፡ መዝሙር ጸሎት ነው ብለናል፡፡ ስንጸልይ በአንቃዕዶ ልቡና በሰቂለ ኅሊና መኾን ይገባናል፡፡ "ስትጸልዩ … በከንቱ አትደገሙ" ተብለናልና፡፡ ማቴ ፮፥፯።
በሥራ ላይ እያሉ መዝሙር መክፈት የማናዳምጠው ከኾነ ምን ይረባናል? በተሰበሰበ ልቡና ኾነን ማቅረብ የሚገባንን ዝማሬ እንዴት በሜዳ ላይ? ከምንም በላይ ደግሞ እኛ የታላቁ ቅዱስና ሊቅ የቅዱስ ያሬድ ልጆች ይህ ሲጠፋን ማየት ይከብዳል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በደጉ ንጉሥ በአጼ ገብረ መስቀል ፊት ዝማሬውን ሲያቀርብ እርሱም ንጉሡም በተመስጦ ላይ ስለነበሩ በምድር ላይ እየኾነ የነበረውን እስከመርሳት ደርሰው ነበር፡፡ ንገሡ በበትረ መስቀላቸው የቅዱስ ያሬድን እግር እንደወጉት አላወቁም ነበረ፡፡ እርሱም ደግሞ ይበልጡኑ እገሩን በጦር መወጋቱ አልታወቀውም ነበር፡፡
ከምን የመጣ ነው? ከተባለ በእግዚአብሔር ፊት በልዩ ተመስጦ ኾነን ልናቀርበው የሚገባን ምስጋና ነውና ከተመስጦ የተነሣ በጦር መወጋትንም ኾነ መወጋት እስከመርሳት ደርሰዋል፡፡ ያለበለዚያ ዘጠኝ እንደጣደችው ሴት እንኾናለን፡፡
አሁን አሁን የምናየው ድርጊት ግን ከዚህ በጣም የራቀ እየኾነ ይገኛል፡፡ አንዳንዶች ክርስቲያን መኾናቸው ይታወቅላቸው ዘንድ፡፡ ሌሎች ደግሞ በእምነት የማይመስሏቸውን "ለመበቀል"፡፡ እኔም መዝሙር አለኝ ዓይነት ፉክክር፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከዘፈን ይሻላል ከማለት፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን እኛ የምንዘምረው ለአገሩ ለመንደሩ ወይ ለጋራ ሸንተረሩ ሳይኾን ለራሳችን መኾኑን አለመዘንጋት ነው፡፡
እንዲህ ከተስማማን ደግሞ መቼ እና እንዴት ማድረግ እንዳለብን ልንወሥን ይገባል፡፡ ሌላው ቀርቶ በቤታችንም ስንከፍት እያዳመጥነው መኾናችንን ማረጋገጥ ግዴታ ነው፡፡ ቤቱ የኦርቶዶክስ ነው፣ ወይንም ደግሞ እኛም መዝሙር አለን ዓይነት በቃለ እግዚአብሔር ላይ ጨዋታ አያስፈልግም፡፡
ዛሬ ዛሬ የምናየው ሁኔታ ግን እጅግም ደስ አያሰኝም፡፡ እንዲያው ስንቱን ተችተን እንዘልቀዋለን ከሚል ዝም የሚባሉ ድርጊቶች ወግ፣ ባሕል፣ ሥርዓት እስከመኾን ሲደርሱ ማየቱ ደግሞ የበለጠ ያምማል፡፡ ጥቂት ድግስ ደግሶ የቤቱ ጣሪያ እስኪገለበጥ ድረስ መዝሙር መክፈት ምን ይሉታል? የተጠራው እንዲሰማ ከኾነ በልኩ በመጠኑ ያለበለዚያ በወግ በጨዋታ በሳቅ እና በሁካታ መካካል መዝሙሩ ቢከፈት ለቃለ እግዚአብሔር የሰጠነው ቦታ ምን ላይ ነው?
፪. በእግዚአብሔር ፊት እንደቆምን ማሰብ
መዝሙር ከመዘመራችን በፊት በዓይነ ኅሊናችን በልዑል እግዚአብሔር እና በቅዱሳኑ ፊት እንደቆምን ልናስብ ይገባል፡፡ ምስጋናው ለእግዚአብሔር እና እርሱ ላከበራቸው ቅዱሳኑ ነውና እንደምናያቸው እያሰብን አኮቴት ማቅረብ ይኖርብናል፡፡ ማርያም እኅተ አልዓዛር "የማይቀሟትን በጎ ዕድልን መርጣለች" የተባለችው ልቡናዋን ሰብስባ በጌታዋ እግር ሥር ቁጭ ብላ ቃሉን በመስማቷ አይደለምን? ሉቃ ፲፥፵፪። መዝሙርም ይኽን የመንፈስ ዝግጅት ይፈልጋል፡፡
ቅድስት ልድያ ልቡናዋ ተከፍቶላት ቃለ እግዚአብሔርን ሰምታ ክርስትናን ተቀብላ ከነቤተሰብዋ የተጠመቀቸው ፣ ቅዱሳንንም በቤቷ እስከማስተናገድ የደረሰችው በአንቃዕዶ ኅሊና በማዳመጧ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት የለበሰውን የማዕረግ ልብስ ወልቆበት እንደ ተራ ሰው እስኪመስል ድረስ በታቦተ ጽዮን ፊት የዘመረው ከፊቱ የቆመውን ስላወቀ ነው፡፡ ፪ ሳሙ ፮፥፲፮።
በእኛም ዘንድ ይህ ሊለመድ ይገባል፡፡ በጥቂት በጥቂቱ ራሳችንን እያረምን መስተካከል ከእኛ ከክርስቲያኖች ይጠበቃል፡፡
፫. ሌሎች ሰዎችን አለመረበሽ
ከዚህ በላይ ያሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ካሟላን ቀጥሎ ሊያሳስበን የሚገባው በዙሪያ ገባችን ያሉት ሰዎች ናቸው፡፡ መቼም የመንዘምረው ሰውን ለማናደድ ፣ ወይም ለማብሸቅ አይደለም፡፡ ለወንድም ለወገን ሲባለ ብዙ የሚተው ነገር ይኖራል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሥጋ መብላቴ ወንድሜን የሚያሰናክል ለኾነ ለዘለዓለሙ ሥጋ አልበላም ያለው ሥጋ መብላት የሚወገዝ ኾኖ አይደለም፡፡ ፩ ቆሮ ፰፥፲፫። ነገር ግን ስለ ሌላው ኅሊና ሲባል ይተዋል፡፡ ክርስትና እንዲህ ነው፡፡ ከራስ አልፎ ለሌሎች የሚኖሩት ሕይወት!
ብዙ የዓለም ነገሮችን የምንጾመው በሕግ በሥርዓት ስለተደነገጉ ብቻ አይደለም፡፡ እንደየደረጃችን ለሰዎች ስንልም ራሳችን በራሳችን ቅር ሳይለን በደስታ የምንተዋቸው ጉዳዮችም አሉ፡፡ ስለዚህ ሁሉ ነገር ተመቻችቶልን ነገር ግን የአካባቢያችን ሁኔታ ያልተመቸ ቢኾን ከእኛ ስንፍና የተነሣ አይሁን እንጂ ብንተው በስውር የሚያይ አምላክ በግልጥ ይከፍለናል፡፡
ደግሞም ጮክ ካለው ይልቅ በለሆሳስ ያለው የበለጠ ውስጥ ድረስ ዘልቆ ይሰማል፡፡ ስለኾነም መዝሙሮቻችን ለእኛ የሚደመጡ ሌላውን የማይረብሹ መኾናቸውን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ከፍ ያለ የመንፈስ ልዕልና ያለን፣ ተቃዋሚዎች እንንቀፍ ቢሉ እንኳ ምክንያት የማይገኝብን ልንኾን ያስፈልጋል፡፡ መጽሐፍ "አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም።" ፪ ቆሮ ፮፥፫። ደግሞም ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ "ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፥ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፥ በሚጎበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን።" እንዳለው ከሕዝብም ከአሕዛብም ምክንያት ሊገኝብን አይገባም፡፡ ፩ ጴጥ ፪፥፲፪።
ቀረኝ
በእጅ ስልኮቻችን ማለትም በተንቀሳቃሽ ስልኮች የጥሪ ድምጽ ያደረግናቸው መዝሙሮችስ አያሳዝኗችሁምን? አንዳንዶች ገና የእግዚአብሔርን ስም ጠርተው ሳይጨርሱ " እግ" እንዳሉ ጉሮሯቸውን ይታነቃሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ሲጠሩ ይውላሉ እንጂ ምን እንደሚሉ የሚሰማቸው የለም፡፡ የደወለውን ሰው ማነጋገር ያልፈለጉ እንደኾን ደግሞ ድምጻቸው ይዘጋል፡፡ እንዲያው ምኑ ቅጡ፡፡ ግን ይኽ ሁሉ የሚኾነው ለእግዚአብሔር በሚቀርበው መዝሙር ላይ ነውን? ጎበዝ በጊዜ ወደ ልቡናችን እንመለስ፡፡ ጨርሶ ለተንቀሳቃሽ የስልክ መጥሪያ መዝሙራትን መጠቀም ከዓላማው ጋር አብሮ አይሄድምና እባካችሁ ስልኮቻችሁን አስተካክሉ፡፡

Yeweyin Fikir

Yeweyin Fikir
የድል ደስታ የድል ዜና
ጽዮንን ክበቧት ለምስጋና
በያሬድ ውብ ዜማ በበገና
ንሴብሆ እንበል በትህትና።
አማናዊት ጽዮን ማርያም
ኪዳንሽ ጽኑ ለዘለአለም
የተማፀነሽ ከቶ አያፍርም
አንቺን ሸልሞናል መድኀኒአለም።
በአዛጦንምድር ያሉ ነፍሳት ሁሉ
ተጨንቀው ሲጮሀኹ ወየው ወየው ሲሉ
የተዋህዶ በር ፀጋ የመስቀሉ
ቅድስተ ቅዱሳን ቤዛዊተ ኩሉ
ታላቅ ነገር ሰራች እሰይ እልል በሉ።
ድንቅ ታምር ሠርታ ያመፁ ተማረኩ
እጅ መንሽ ሰጥተው ታቦቱንም ላኩ
ለህያዋን አምላክ ፈርተው ተንበረከኩ።
ለማይናገረው ዳጎኑ ጠዖት
ምስሉን አቁመው ሲሰግዱለት
እጅና እግር አለው አይሄድበት
አፍና አፍንጫው ታይቶ ለምልክት
ከቶ አይንቀሳቀስ ቀን ከሌሊት
ደረቅ በድን ነበር የሌለው ህይወት።
ታዲያ በዚች ቀን በዙ ታምር ሆነ
የአምላክ ቸርነት ፍቅሩ ተከወነ
በህያው ምስክር ሁሉ አመነ
የከሳሽ ፉከራ ጉድጓድ ተደፈነ
የድንግል ማርያም ልጅ
ክርስቶስ ገነ።
እምዬ ኢትዮጵያ በጣም ደስ ይበልሽ
የኦሪቱን ዘመን ታቦት ተቀብለሽ
በአዲስ ኪዳኑም መስቀል ተሸልመሽ
ጠላትን ማምከኛ የፀናው እምነትሽ
ነገም እንደ ትላንት ዛሬም
ያኔን ሆነሽ
ተነሺ ለምኚ ይዘርጉ እጆችሽ።
የክህደት አርበኛ መንፈስ የባህሩ
ትውልዱን በጉርሻ ቀድሞ ማባረሩ
በሽንገላ ከንፈር መስሎ መደርደሩ
እውነት ተጋርዶበት እንዳያቅ ሚስጢሩ
የያዘውን ረስቶ ደጅ ላይ ማደሩ
በምክረ አጋንንት እርቋል ከፍቅሩ
ስቶ እያሳተ ልቦናን ማወሩ
ታይቷል ሃራጥቃ ይኽው ምስክሩ።
አማናዊት አንባ የፀሐይ እናት
የትውልድ መፅናኛ ፍሬ በረከት
ቅድስተ ቅዱሳን ኪዳነምህረት
ምልጃሽ ይታደገን ወጥቶ ከመቅረት።
የጽዮን ከተማ የዳዊት ሀገር
በኦሪቱ ዘመን መጠጊያ መንደር
በአዲስ ኪዳኑ የወንጌል ማህደር
ድንግል ማርያም ናት መሠረተ ፍቅር
አማኝ ተሰብሰቡ ኑ ና እንዘምር።
ሠይጣን ተሸነፈ እጅግ ተጨነቀ
በኤልሻዳይ ሥልጣን እነሆ ደቀቀ
ዳግም ላይነሳ ተረግጦ ወደቀ
የእርሱ ያልሆኑትን በሙሉ ለቀቀ።
ልክ እንደ አዛጦን ዘመን ዛሬም እየሳቱ
አምላክን እርቀው ጠዖት የሚያሸቱ
ሥሙን እየጠሩ ሞት የሚጎትቱ
በኑፋቄ ትምህርት እየተንገላቱ
አሉ ለምድ ለባሾች የከንቱዎች ከንቱ።
መጽሐፉ ሲገለጥ በሣሙኤል መልእክት
የታቦተ ጽዮን አስገራሚው እውነት
ፈጦ እየታየ የክርስቶስ ምህረት
ዛሬም ይክዳሉ አይልም በማለት
ይከራከራሉ በታቦት በጽላት።
ወገን እናስተውል በጥበብ እንመርምር
ገልጠን ስናነበው የአንድምታውን ሚስጢር
እርሱ ሆኖ ሳለ የዘለአለም መምህር
ኑ አድምጡኝ ብሎ አዶናይ ሲናገር
ሰመተናል አይተናል በዕምነታችን በር።
ስለዚህ አስተውል ሕዝበ እግዚአብሔር ሆይ
ከሠማይ የመጣው ኢየሱስ ኤልሻዳይ
ብርሃን ሊሆነን ነው የማይጠልቀው ፀሐይ
እንማር እንጠይቅ ስለ ሀይማኖት ገዳይ።
እንኳን አደረሰን ለዚች እለት

ጋኔንን በመዛመድ ማሳሳት

ጋኔንን በመዛመድ ማሳሳት----------ዓባይነህ ካሤ (ዲን)
"የአጥማቂዎቹ" ምስክሮች እና አዲስ "ዶግማቸው"
አንዳንድ "አጥማቂ" ነን ባዮች በያሉበት ከዚህ ቀደም በቅድስተ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ "ምስክር" እያስተዋወቁን ነው፡፡ የእነርሱን ምስክር ከማየታችን በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቅና የተሰጣቸውን ምስክሮች ቀድመን ማየት ይጠበቅብናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች ያላቸው የሚከተሉትን ነው፡፡
፩. ሥሉስ ቅዱስ
ከምስክር ሁሉ በላይ የኾነው ምስክር እግዚአብሔር ስለራሱ የሰጠው ምስክርነት ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍጹም ነውና ከእርሱ በላይ ስለእርሱ ሊነግረን የሚችል የለም፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ " እግዚአብሔርን ያየው አንድስ እንኳ የለም፡፡ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው" ሲል የደመደመው፡፡ የሐ ፩፥፲፷። አብን በወልድ ምስክርነት እንዳወቅነው ሁሉ ወልድንም በአብ ምስክርነት ዐውቀነዋል፡፡ መንፈስቅዱስንም እንዲሁ በአብ እና በወልድ ምስክርነት እንዳወቅነው ሁሉ አብና ወልድም ስለመንፈስቅዱስ መስክረዋል፡፡
ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን ስለራሱ ሲመሰክር በሙሉ ሥልጣኑ እንዲህ አለ፡፡ "ኢየሱስ መለሰ አላቸውም፦ እኔ ስለ ራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው" ዮሐ ፷፥፲፬። የባሕርዪ አባቱ የአብን ምስክርነት ደግሞ እንዲህ በማለት ይገልጠዋል፡፡ "እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፥ ይህ የማደርገው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና። የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል፡፡" እንዲል፡፡ ዮሐ ፭፥፴፮-፴፯።
እውነት ነው! በባሕረ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ጌታችን ሲጠመቅ አብ በደመና ኾኖ "በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው" ሲል ሰምተነዋል፡፡ ማቴ ፫፥፲፯። ደግሞም በደብረ ታቦር (በታቦር ተራራ) ይኸንኑ ቃል አብ እዚያው በሰማያት ኾኖ ሲደግመው ሰምተናል፡፡ "ከደመናው፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።" እንዲል ፡፡ ማቴ ፲፯፥፭።
መንፈስ ቅዱስም ስለ ወልድ የባሕርዪ አምላክነት ሲመሰክር በአምሳለ ርግብ ኾኖ በላዩ ላይ ሲያርፍ ዐይተናል፡፡ "የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ ዐየ" እንዲል፡፡ ማቴ ፫፥፲፮። ጌታችንም ከዕርገት በኋላ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ቅዱሳን ሐዋርያት እንደሚቀበሉ የተሰወረውን ምስጢር ሁሉ እንደሚገልጥላቸው ደግሞም ስለእርሱ የባሕርዪ አምላክነት ከመንፈስቅዱስ እንደሚሰሙ ሲናገር "ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል" ብሎ ነበር፡፡ ዮሐ ፲፭፥፳፮።
፪. ሥራው
ጌታችን እንደሰውነቱ ያደረጋቸው ሥራዎች እንዳሉ ሁሉ እንደ አምላክነቱ ያደረጋቸው ሥራዎችም አሉ፡፡ ነገር ግን እንዚህን ሁሉ ሰፍረን ቆጥረን ዘርዝረን አንዘልቃቸውም፡፡ ነገር ግን የባሕርዪ አምላክ የሚያደርገውን ሥራ በዘመነ ሥጋዌው እኛን በሚገባን ደረጃ ሲፈጽም ስለኖረ ከሥራው ማንነቱን ልናውቅ ችለናል፡፡ ስለዚህም የጌታችን ሥራው ለአምላክነቱ ምስክር ነው እንላለን፡፡ ለዚህም ነው "እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤ ባደርገው ግን፥ እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።" ሲል የተናገረው፡፡ ዮሐ ፲፥፴፯-፴፷። ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ አብን አኽሎ አብን መስሎ የአብን ሥራ ለማድረግ ሥላጣን ያለው ከአብ ጋር የተካካለ መኾኑን ሥራው ይመሰክራልና ሁለተኛው ምስክር ሥራው ነው፡፡
፫. ቅዱሳን
ከራሱ ከእግዚአብሔር እና ከሥራው ቀጥሎ በምስክርነት የሚጠቀሱት ቅዱሳን ናቸው፡፡ ቅዱሳን ስንል ቅዱሳን መላእክትን እና ቅዱሳን ሰዎችን ያጠቃልላል፡፡ በተለይም ቅዱሳን ሰዎች እስከሞት ድረስ ሥጋቸው እየተተለተለ፣ በሰይፍ እየተቀሉ፣ በመጋዝ እየተተረተሩ፣ በእሳት እየተቃጠሉ በብዙ መከራ ውስጥ እያለፉ የመሰከሩ ናቸውና ሰማዕታት ተብለዋል፡፡ ሰማዕታት ማለት ምስክሮች ማለት ነው፡፡
ጌታችን ደቀመዛሙርቱን "እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ።" ያላቸው ለዚህ ነው፡፡ ሉቃ ፳፬፥፵፷። ለዚህም ነው ቅዱሳን ሐዋርያት "እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት።" ሲሉ የተናገሩት፡፡ ሥራ ፲፥፴፱። ደግሞም "ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።" እንዲል፡፡ ሥራ ፩፥፷።
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ "ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ።" የተባለው ምስክርነቱ ብርሃን ለተባለ ለክርስቶስ ነበረ፡፡ ዮሐ ፩፥፯። ስለዚህ በቅዱሳኑ ምስክርነት እናምናለን፡፡
፬. ቅዱሳት መጻሕፍት
በአራተኛ ደረጃ ቅዱሳት መጻሕፍት የክርስቶስ ምስክሮች ናቸው፡፡ ይህንንም መጽሐፍ "እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው" በማለት ያረጋግጥልናል፡፡ዮሐ ፭፥፴፱። ከቅዱሳት መጻሕፍት መካከል ወንጌል ቅድምና ያላት ምስክር እንደኾነች ጌታችን እንደዚህ ሲል ነግሮናል፡፡ "ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።" ማቴ ፳፬፥፲፬።
የጠቀስናቸውን ምስክሮች ልብ ብለን እንመልከት፡፡ ጌታችን ራሱ ምስክር ብሎ የጠራቸውን እንጂ በእኛ መላምት የመረጥናቸው እንዳልኾኑ ልብ እንበል፡፡ እናም በባሕርዪው ቅዱስ ለኾነው እግዚአብሔር ምስክሮቹም ቅዱሳን ናቸው፡፡ ስለኾኑም ቅዱስ ዳዊት "ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው፤ ስለዚህ ነፍሴ ፈለገቻቸው።" ሲል ይናገራል፡፡ መዝ ፻፻፲፰፥፻፳፱። እነዚህን የመሳሰሉ ስለክርስቶስ ሲመሰክሩ እናውቃለን፡፡ አሁን አሁን ግን አንዳንድ አሳቾች "የአጋንንትን ምስክርነት" ማስረጃ እያደረጉ በተለያየ መልኩ ለገበያ በማቅረብ ኪሳቸውን እያደለቡ ይገኛሉ፡፡
የአጋንንት ምስክርነት የሚባልስ አለን?
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሌለ እንግዳ ነገር እያመጡ ሕዝብን ማደናገር ስህተት ብቻ ሳይኾን የሚያስወግዝ ድርጊት ነው፡፡ እኛ የምናውቀው ጌታ አጋንንት ስለእርሱ ለመናገር አፋቸውን ሲከፍቱ ጸጥ ያደረጋቸውን ነው፡፡ ጌታችን ወደቅፍርናሆም ሲገባ ርኩስ መንፈስ ያደረበትን አንድ ሰው አገኘ፡፡ በሰውየው ላይ ያደረው ክፉ መንፈስም ገና ምንም ሳይባል መቀባጠር ጀመረ፡፡ እንዲህ እያለ "የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ።"
ንጹሐ ባሕርዪ ጌታችን ንጹሕ ምስክርነት እንዲሁም ምስጋና ከንጹሐን ይቀበላል እንጂ ከርኩሳን መናፍስት አይቀበልምና "ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው።" ማር ፩፥፳፭። ሲያጸናውም ከዚህ ሰው ወዲያ ሌሎች አጋንንት ያደሩባቸውን ሰዎች ሲፈውስ አጋንንቱ እርሱ እግዚአብሔር መኾኑን ስላወቁ ያወቁትን እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም፡፡ "አጋንንትም ክርስቶስ መሆኑን አውቀው ነበርና ሊናገሩ አልፈቀደላቸውም።" እንዲል ማር ፩፥፴፬። ቅዱስ ሉቃስም ይኽንኑ እውነት ጽፎታል፡፡ ሉቃ ፬፥፴፭-፵፩።
ከዚህ የምንረዳው ጌታችን መቼም ቢኾን የአጋንንትን ምስክርነት እንደማይቀበል ነው፡፡ የትኛውም ጋኔን ክፉ ተናግሮ አልነበረም፡፡ ሊናገርም አይችልም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በጭራሽ የእነርሱን ምስክርነት አልፈለገውምና እንዲናገሩም አልፈቀደላቸውም፡፡ ክርስቶስ እንዳይናገሩ አፋቸውን የለጎማቸውን አጋንንት ዛሬ አንዳንዶቹ አስለፈለፍናቸው በሚል የዋኁን ምእመን ግራ ያጋቡታል፡፡ ክርስቶስ የከለከለውን የሚፈቅድ እርሱ የክርስቶስ አይደለም፡፡ ስለኾነም የቤተ ክርስቲያን አለመኾናቸውን ራሳቸው እየነገሩን እንደኾነ በማወቅ ከስሁት አሠራራቸው እንጠበቅ ዘንድ ራሳችንን እንምከር፡፡
መድረክ ለተከለከለ ጋኔን መድረክ ማመቻቸት ምን የሚሉት ሥራ ነው? እንዲህም አድርጎ ጸጋ የለምና በዚህ ክፉ ሥራቸው አንተባበርም፡፡ በተቀደሰው የእግዚአብሔር ዐውደ ምሕረት ላይ ርኩሳን መናፍስት ይናገሩበት፣ ይፈነጩበት ዘንድ መፍቀድ ኢ-ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡ እንዲያውም መድረኩን ቀስ በቀስ ለአለቃቸው ለሐሳዊ መሲህ የማመቻቸት ሥራ ይመስላል፡፡
ጌታችን እንዳይናገሩ የከለከላቸውን የአጋንንትን ምስክርነት ቅዱሳኑም አልተቀበሉም፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትን ያወደሰች ያመሰገነች እየመሰለች የማታለል ሥራ ለመሥራት እንዲመቻት ታደርግ የነበረች አንዲት ጠንቋይ ይህን ስልት ለመጠቀም ሞክራ ነበር፡፡ እንዳትነቀፍ ቅዱሳንን የተቀበለች ለመምሰል ትሞክራለች፡፡ ይህም ገበያዋ እንዳይታጎልባት የቀየሰችው መንገድ ነበረ፡፡ ቅዱሳኑን ብትቃወም ኖሮ ዘወር ብሎ የሚያያት አይኖርም ነበረና በስልት በአደባባይ የማታምንበትን ምስክርነት ልትሰጥ ትሞክራለች፡፡ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፡-
"ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን። እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፦ የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር። ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን፦ ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ።" ፲፮፥፲፮-፲፷።
ዛሬም ቅዱሳኑን የተቀበሉ የሚመስሉ የአጋንንት አገልጋዮች አሉና እናውቅባቸው ዘንድ ይገባል፡፡ ስመ ቅዱሳንን መጥራት ብቻ የእግዚአብሔር መኾንን አያመለክትም፡፡ ከዚህች ሴት የምንረዳው ይኽንኑ ሲኾን ሐዋርያትም አልፈቀዱላትም፡፡ ስለዚህ ለጋኔን ፈቃድ ሰጥተው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መድረክ የሚያስፈነጩ ሁሉ በምንም መንገድ የእና ናቸው ሊባሉ አይችሉም፡፡ ነገር ግን ከተያዙበት ቁራኝነት ተላቅቀው ዕድሜ ለፍስሐ ዘመን ለንስሐ ያገኙ ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡
አዲስ "ዶግማ"?
"አጥማቂ" ነን ባዮቹ ከሚፈጽሙት መሠረታዊ ስህተት አንዱ አዲስ ነገረ ሃይማኖት ያውም ኑፋቄ አሾልከው ለማስገባት የሚያደርጉት ጥረት ነው፡፡ በተደጋጋሚ እንደምንሰማው "በኢየሱስ ስም አልወጣም ያለው ጋኔን በማርያም ስም ወጣ" የሚል ግልብ ማደናገሪያ በማኅበረሰባችን ውስጥ ቀስ እያደረጉ እያስገቡ ነው፡፡ እንዴት? ተብለው ሲጠየቁ በኢየሱስ ስም ሲባል የማይወጣው ሐሰተኛ ኢየሱስ ስላለ ነው ይላሉ፡፡
አላወቁትም እንጂ እነርሱ እየጠሩት ያለው ሐሰተኛ ኢየሱስ መኾኑን ነው፡፡ አማናዊውን ኢየሱስ (እውነተኛውን ኢየሱስ) እንደማይጠሩት በዚህ አረጋገጡልን ማለት ነው፡፡ ጋኔኑማ አማናዊውን እንዳይጠራ ግዝት አለበት፡፡ ደግሞ እውነተኛውን ከሐሰተኛው እየለየ የሚነግራቸው ጋኔኑ እንጂ እነርሱ አለመኾናቸውን ስናውቅ ምን ያኽል በክፉ ቁራኝነት እንደተቀፈደዱ እንረዳለን፡፡ እነርሱ እንደሚሉት ከኾነ ጋኔኑ እኮ ነው ለምንድን ነው በኢየሱስ ስም ስትባል የማትወጣው ተብሎ ተጠይቆ እነርሱ የሚለፍፉትን "ማምለጫ" ያስተማራቸው፡፡ ጋኔኑማ በአማናዊው ኢየሱስ ስም ምንም ነገር እንዳያደርግ ዝምም እንዲል ስለተደረገ ምንም የማድረግ ሥልጣን የለውም፡፡ ታዲያ ተከታዮቻቸው ጋኔኑ እየሠራ ያለው በተቃራኒው እንደኾነ እንዴት ማወቅ ተሳናቸው? መልሱ አንድ እና አንድ ብቻ ነው የያዘ ቢይዛቸው የሚል፡፡
ከጋኔን ሰምቶ ጽድቅ የለም፡፡ እንዲሁም በጋኔን የማሳሳቻ ስልት ተባባሪ መኾን የእርሱ ተከታይነትን ከማረጋገጥ በቀር ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡ በእነርሱ ቤት እመቤታችንን ኦርቶዶክሳውያን ይወዳሉና እንዲህ ብንላቸው በቀላሉ ይሞኙልናል ብለው ነው፡፡ እኛ ከክርስቶስ በላይ የኾነች ድንግል ማርያም የለችንም፡፡ እኛ የምናውቃት ቅድስተ ቅዱሳን፣ የጭንቅ አማለጅ ፣ ንጽሕተ ንጹሐን፣ መትሐት ፈጣሪ መልዕልተ ፍጡራን ድንግል ማርያም ካማለደች በኋላ "የሚላችሁን አድርጉ" ብላ ወደ ክርስቶስ የምታቀርበንን ነው፡፡
እውነት ከኾነ ጋኔኑ ራሱ እነርሱ የሚሉትን የማለት ሥልጣን እንደሌለው አሳምሮ ሊነግራቸው ይችላል፡፡ ከዚህም ከዚያም ሳይኾኑ እንዳይቀሩ እንጂ ስለ ጌታችን ጋኔን ሐሰት ይናገር ዘንድ አቅም የለውም፡፡ ምናልባት እርሱ ያላሰበውን እነርሱ አስበውለት እንደኾነ እንጃ! በኢየሱስ ስም ባዮቹ እነርሱ ኾነው ሳለ ጋኔኑ ያለው የተናገረው አስመስለው ማቅረባቸው በጣም አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡ እነርሱ ከጠሩት ደግሞ ሐሰተኛው የሚለውን ምን አመጣው? ወትሮውኑም ጠሪው የጠራው ሐሰተኛውን ስለኾነ እንጂ፡፡ እነርሱ የጠሩትን ጋኔኑ "እርሱማ ሐሰተኛው ነው" ሲላቸው ካመኑት እነዚህ ሰዎች ከእግዚአብሔር ይልቅ የሚያምኑት ዲያብሎስን ለመኾኑ ሌላ ማስረጃ ፍለጋ መሄድ አያስፈልግም፡፡
ስለዚህ ከእነዚህ አስመሳዮች ራሳችንን መጠበቅ አለብን፡፡ ከመከተል በፊት ከሃይማኖታዊ፣ ከቀኖናዊ እና ትውፊታዊ ኦርቶዶክሳዊነት አንፃር እንገምግም፡፡ አጋንንት ያደሩባቸውን ሰዎች በባርነት እና በሌላም ግብረ ኃጣውእ ተብትቦ ይዞ መዞር ክርስቶሳዊነት አይደለም፡፡ ጸጋው ያደረባቸው ወዲያው ይፈውሳሉ ወዲያው ያሰናብታሉ፡፡ በዞሩበት እያዞሩ በባርነት ተብትበው የያዙ ኦርቶዶክሳዊያንንም ኾነ ቅዱሳንን አናውቅም፡፡ ይህ ብቻውን ሊያስተምረን በተገባ ነበር፡፡ ግን እንበልና ተሳሳትን፣ ዛሬ ለመመለስ ደግሞ ምክንያት አናብዛ፣ ሰዎችን ከመከተል ይልቅ የምሕረት በርን በሰፊው ከፍታ ወደምትጠብቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንመለስ፡፡ መሳሳትን ላለመቀበል አንግደርደር፡፡ እግዚአብሔር የተሳሳቱትን ሁሉ ራሳቸውን "አጥማቂ" ነን ባዮችንም ጭምር በቸርነቱ ይመልስልን፡፡

Saturday, 21 November 2015

 “የኢየሱስ ክብሩ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነው”
እርግጥም እንዲሁ ነው ፡ በእውኑ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሄር ነው ብላ በእግዚአብሄርነቱ ኢየሱስን የምታከብር ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን  የበለጠች ቤተክርስቲያን ማን ነች? ካቶሊክ ወይንስ ፕሮቴስታንት? ካቶሊክ አንዱን ጌታ ትከፍለዋለች ፡ ፕሮቴስታንት ደግሞ ሃያሉን አምላክ ታሳንሰዋለች ፤ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ግን ያህዌውን ኢየሱስን እናመልካለን፡፡
ነገር ግን ይገርመኛል ፤ ለኦሪታውያን ጠላታቸውን እንዲጠሉ ፡ ወዳጆቻቸውን ደግሞ እንዲወዱ ተፃፈላቸው ፤ ለክርስቲያኖች ግን ወዳጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን ጠላቶቻቸውንም እንዲወዱ ታዘዙ ፡ እንዲህም ነውና ኦርቶዶክሳውያን ይህን ሊፈፅሙ ይተጋሉ፡፡
ፕሮቴስታንቶችና ተረፈ ጴንጤ የሆኑ ተሃድሷውያን ግን ክርስቲያኖች ነን ይላሉ ወዳጆቻቸውን ግን ይጠላሉ ፡ ወዳጆቻቸውም የተባሉ ስለክርስቶስ መከራን የተቀበሉ ፡ አንዲቷን እምነት ያስተላለፉ ፡ በምልጃ የሚበረቱ ቅዱሳን ናቸው፡፡ ከቅዱሳንስ በላይ ለክርስቲያኖች ባልንጀራ ማን ሊሆን ነው? ፕሮቴስታንቶች ግን እኒህን የክርስቲያን ወዳጆች ጠልተዋል ፡ በዚህም አንድም ከክርስትና ርቀዋል ፡ ከኦሪታውያንም አንሰዋል (ኦሪት ወዳጅህን ውደድ ትላለችና)፡፡
መቼ ጠላን ይሉኝ ይሆናል ፡ ነገር ግን ስለነሱ በተወራ ጊዜ ሁሉ ከንቱ ቃል ያስቀድማሉ ፡ የንቀት ፌዝን ያሰማሉ ፡ ከክብራቸው ይልቅ ድካማቸውን በማጉላት ይጠመዳሉ ፡ ነገር ግን ክርስቶስ ያፀደቃቸውን ማን ይከሳቸዋል? እኒህ ግን እግዚአብሄር ያከበራቸው እንደዲያቢሎስ ሊከሱ ይሞክራሉ፡፡
ስለቅዱሳን ባላቸውም ጥላቻ ስለኢየሱስ አብዝተው ሲያወሩ እናያቸዋለን ፡ የኢየሱስን ስም መጥራት ህይወት ይመስላቸዋልና ይስታሉ ፡ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” የሚሉ ጌታ ኢየሱስን ግን ያላወቁ እኒህ ናቸው ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሲሆን ፍቅርን ግን አጥተው ይመላለሳሉና ፡ ስለፍቅራቸው ማነስም በክርስቶስ ከተመሰረተች ክርስትና ርቀው ከኦሪታውያንም አንሰው ይታያሉ፡፡
ስለሆነም ስለቅዱሳን በጎ መናገርን አይወዱም ፡ አንድም ስለቅዱሳን የሚናገር ሰው ሲመለከቱ ይቆጣሉ ፡ ራሳቸውን ቅዱሳን ስለማለት ግን አያፍሩም ፡ የቅዱሳንን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስንም ይጠራሉ ፡ ክርስቶስ ያከበራቸውን ደግሞ ይንቃሉ ፡ አለማውያን ማለት እኒህ ናቸው፡፡ ራሳቸውን ለማፅደቅ አንደኞች ቅዱሳንንም ለማሳነስ ፈጣኖች አለማውያን ማለት እኒህ ናቸው፡፡ ከፍቅር የተለዩ ፍቅር ክርስቶስን ግን የሚጠሩ እኒህ ናቸው፡፡ ኢየሱስ ኢየሱስ የሚልይ ኢየሱስን ግን ከአብ አሳንሰው በሁለት የሚበላለጡ አማልክት የሚያመልኩ እኒህ ናቸው፡፡
ከእነዚህ አለማውያን ተለዩ ፡ ከእነዚህ ፍቅር የራቃቸው ተለዩ ፡ ከእነዚህ አላዋቂወች ተለዩ ፡ የኢየሱስ ክብሩ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ነውና ፡ ኢየሱስን የምትወዱ ክብሩን ከሚይሰፉ ጋር ተባበሩ፡፡

Thursday, 12 November 2015

የተሐድሶ መረብ

የተሐድሶ መረብ አድማስና የትኩረት አቅጣጫዎች

ኅዳር 2 ቀን 2008 ዓ.ም
ክፍል ሦስት
ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጽሑፎች ተሐድሶ መናፍቃን በምን ዐይነት መንገድ ምእመናንን እየነጠቁ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ከዚህ ቀጥለን በምናወጣቸው ተከታታይ ጽሑፎች ደግሞ የተሐድሶ አድማሱ የት ድረስ እንደሆነ ለአንባቢያን ግንዛቤ የሚሰጥ መረጃ የምናቀርብ ይሆናል፡፡

የተሐድሶ እንቅስቃሴ ዓለም አቀፋዊ መልክ ያለውና በዓለም ላይ ባሉ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ላይ በፕሮቴስታንት የእምነት ተቋማት የተቃጣ ስውር ሴራ ነው፡፡ እንቅስቃሴው ከውጪ ወደ አገር ውስጥ የመጣ ስለሆነ የተሐድሶው አቀንቃኞች በአሳብ፣ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ ወዘተ ከሚያግዟቸው በልማት ስም ከተቋቋሙ ድርጅቶች ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አላቸው፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች እና ከፕሮቴስታንት ቸርቾች በሚበጀት በጀት፣ ከአገር ውስጥ እስከ ውጪ አገር በተዘረጋ መዋቅር፣ ቤተ ክርስቲያንን ከተቻለ ሙሉ በሙሉ ለመረከብ ፕሮቴስታንት ለማድረግ ካልሆነም ለሁለት ለመክፈል በሚያስችል ስልት እየሠሩ እንደሆነም ተመልክተናል፡፡

በአገር ውስጥ ያሉት ሠላሳ የሚደርሱ የተሐድሶ ማኅበራት የቤተ ክርስቲያን ምንጮች በሆኑት የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ ገዳማት፣ መንፈሳዊ ኮሌጆች፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት ላይ እንዲሁም መዋቅራዊ ድጋፍ ለማግኘት የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ ይሠራሉ፡፡ የተለያዩ መመዘኛዎችን በመጠቀም ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ መነሻቸውን አዲስ አበባ ላይ አድርገው በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ዕትም ጀምሮ በተከታታይ ጽሑፎች ከመነሻቸው ከአዲስ አበባ ጀምረን ትኩረት ሰጥተው በሚሠሩባቸው አካባቢዎች ያለውን እንቅስቃሴ እንመለከታለን፡፡

አዲስ አበባን ማእከል ያደረገው የተሐድሶ መረብ
አዲስ አበባ የተሐድሶ እንቅስቃሴው ማእከል ነው፡፡ ታሪክ የሚነግረን ተሐድሶዎች እንቅስቀሴው ሲጀመር ጀምሮ ማእከላቸውን አዲስ አበባ አድርገው ወደ ሌሎቹ የአገራችን ክፍሎች ኑፋቄያቸውን ያስፋፉት መሆኑን ነው፡፡ አዲስ አበባ ተሐድሶዎች በየአጥቢያው ተወካዮችን አስገብተው ብዙ ሥራ የሚሠሩበት፣ የተለያዩ የሥልጠና መስጫ ተቋማትን እና ኮሌጆችን ያቋቋሙበት፣ የቤት ለቤት ሥራዎችን በሰፊው የሚሠሩበት፣ የጽዋ ማኅበራትን በብዛት የፈጠሩበት፣ ከክፍለ ሀገር ለሚያመጧቸው ካህናትና ዲያቆናት ሥልጠና የሚሰጡበት ነው፡፡ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር የሚያስተላልፉት፣ አብዛኛው የተሐድሶ መናፍቃን መጻሕፍት የሚታተሙት፣ የገንዘብ ልገሳ የሚያደርጉላ ቸው የመናፍቃን ድርጅቶች የሚገኙት አዲስ አበባ ነው፡፡ ፕሮቴስታንታዊ የአምልኮ ሥርዓት የሚፈጸምባቸው የተሐድሶ አዳራሾች በስፋት የሚገኙትም እዚሁ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ የሚያስችላቸውን መዋቅራቸውን የዘረጉትና ስልታቸውን የነደፉት አዲስ አበባን ማእከል አደርገው ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከአዲስ አበባ እየተነሡ ያልደረሱበት የአገራችን ክፍል የለም ማለት ይቻላል፡፡ አዲስ አበባ ላይ ያላቸው መረብም ጠንካራና ሁሉንም አጥቢያዎች የሚያቅፍ ለማድረግ እንቅልፍ አጥተው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ መሐል አዲስ አበባ አካባቢ ካሉት አጥቢያዎች ተነቅቶባቸው ሲባረሩ በአዲስ አበባ ዙሪያ ወደሚገኙ አጥቢያዎች በመሔድ ተመሳስለው ገብተው የቅሰጣ ሥራቸውን ይሠራሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ተልእኳቸውን ተረድታ በውግዘት የለየቻቸውና አጋልጣ ምእመናን እንዲያውቋቸው ያደረገቻቸው ተሐድሶዎች ከጀርባ ሆነው በየአጥቢያው የሰገሰጓቸው ተሐድሶ መናፍቃን ተልእኳቸውን ያፋጥኑላቸዋል፡፡

እንቅስቃሴው በግልም በቡድንም እንዲሁም በድርጅት ስም የሚካሔድ ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ የተሐድሶ አቀንቃኞችን እገሌ ወእገሌ ማለቱ ባያቅትም ለአንባቢም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጠው ጥቅም ካለመኖሩና እነርሱንም የበለጠ እንዲደበቁ ዕድል መስጠት ስለሚሆን ይህንን መጠበቅ የለብንም፡፡ ነገር ግን በብዙ ቦታዎች እንደሚታየው በዓላማ እንቅስቃሴውን የሚመራው አካል አንድ ወይም ጥቂት ነው፡፡ ሌላው ግን ምን እየተሠራ እንደሆነ እንኳን ሳያውቅ ሌሎቹ ስለሔዱ ብቻ የሚከተል ነው፡፡

በተደጋጋሚ ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ካህናትን እያመጡ አዲስ አበባ ላይ ያሠለጥናሉ፡፡ በተለይ ከገጠር ለሥልጠና የሚያመጧቸው ካህናት ከጥቂቶቹ በስተቀር በየዋህነት ጉዳዩ ምን እንደሆነ ሳይረዱ የሚመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ሴራዎች ያውም የቤተ ክርስቲያን ምንጮች ያልናቸው አብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት ላይ ሓላፊነት ላላቸው ሰዎች ተሰጥቶ የፈለጉት ነገር አለመሳካቱን ስናይ የእግዚአብሔርን ጠብቆት እናደንቃለን፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ የሚሰጡት ሥልጠና ውጤት ማምጣት ያልቻለው በአንድ በኩል ከሠልጣኞች አቅም ማነስ የተነሣ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሚከተሉት ዓላማ የጥፋት በመሆኑ እግዚአብሔር እንዳይሳካላቸው ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን በረድኤት ስለሚጠብቃቸው ነው ብለን እናምናለን፡፡ ተሐድሶዎችም ምዕራባውያን ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ስውር ተልእኳቸውን ለማሳካት የበጀቱት ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንዳይቀርባቸው እንጂ ለጽድቅ ስለ ማይሠሩ ለሪፖርት ብቻ ሥልጠና ሰጥተው የሚልኳቸው ብዙዎችን ነው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መቦርቦርን እንጀራ ማብሰያ አድርገው የያዙት ብዙ የተሐድሶ ድርጅት አንቀሳቃሾች መናሃሪያቸው አዲስ አበባ ነው፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባዔ የተወገዙና ከሥልጣነ ክህነታቸው የተሻሩ ግለሰቦች ሳይቀሩ የክህነት ስማቸውን ተጠቅመው ዲያቆን፣ መሪ ጌታ እያሉ መጻሕፍት ያሳትማሉ፡፡ ሥልጠና የሚሰጡባቸው፣ ኑፋቄያቸውን የሚዘሩባቸው፣ በእነርሱ አነጋገር አምልኮት የሚፈጽሙባቸው፣ በሥውር ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ሴራ የሚጠነስሱባቸው፣ የቴቪዥን መርሐ ግብራትን የሚቀርጹባቸው፣ የግልና የኪራይ አዳራሾች አሏቸው፡፡ በእነዚህ አዳራሾች ሲያሻቸው ያስጨፍራሉ፣ ሲያሻቸው እንፈውሳለን ይላሉ፣ ሲያሻቸው ደግሞ እነርሱ ሳይማሩና የያዙት ወንጌል ሳይገባቸው ያስተምራሉ፡፡

የቤት ለቤት ቅሰጣ አልበቃ ብሏቸው በመገናኛ ብዙኀን ወደ ሕዝብ መድረስ ጀምረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ምእመናን ስለ ተሐድሶ ያላቸው ግንዛቤ እየጨመረ መምጣቱ፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ከተሐድሶዎች ጋር እያደረጉት ያለው ትንቅንቅ መጎልበቱና ለምእመናን የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብራት እየበረከቱ መምጣታቸው ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም፤ አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ ከተሐድሶዎች እጅ ነፃ ለማድረግ ግን ሰፋ ያለና የተቀናጀ ሥራ የሚጠይቅ ነው፡፡

አጥቢያቸው የሚገኘውን ሰንበት ትምህርት ቤት አፍርሰው ሌላ ሰንበት ትምህርት ቤት ለማቋቋም፣ አባላቱን ለሁለት ከፍለው አገልግሎቱ እንዳይካሔድ ለማድረግ የሚጥሩ ከተሐድሶ በሚገኝ ገንዘብ የሚደለሉ አንዳንድ አስተዳዳሪዎችና የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች መኖራቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ዓላማችንን ያስፈጽሙልናል ያሏቸውን የሰንበት ተማሪዎች ሰብስበው የተለየ ትምህርት ካስተማሩ በኋላ ተልእኮ ሰጥተው ተመልሰው ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርጉ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሌላ ተልእኮ ይዘው ተመሳስለው የገቡትን የጥፋት መልእክተኞች አካሔድ አጢነው ሲያግዷቸው ለምን ታገዱ ብለው ሰንበት ትምህርት ቤቱን ለመዝጋት የሚነሡ የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች እየበዙ መጥተዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ምን ያህል ተመሳስለው ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንደገቡ ነው፡፡ ምእመናንም ሆኑ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች እንዲህ ዓይነት የጥፋት ተልእኮ አንግበው የሚንቀሳቀሱትን ወገኖች ሲመለከቱ ማንነታቸውን የሚያሳይ መረጃ መሰብሰብ፣ ከማን ጋር እንደሚውሉ፣ ምን እንደሚሠሩ፣ አነጋገራቸው፣ አካሔዳቸው፣ ኦርቶዶክሳዊነታቸው ምን እንደሚመስል ማጣራት ይኖርባቸዋል፡፡

በአንዳንድ አጥቢያዎች ገድላትና ድርሳናት፣ ተአምረ ማርያምና ስንክሳር እንዳይነበቡ የሚከለክሉ አስተዳዳሪዎች አሉ፡፡ የጠበል ቦታ አያስፈልግም ብለው ለጋራዥ በማከራየት ገንዘብ ከመመዝበር አልፈው ምእመናንን ከድኅነት የሚለዩና የተሐድሶ አጋርነታቸውን የሚገልጡ ወገኖች አሉ፡፡ ተሐድሶዎቹ ከእንደዚህ ያሉ የጫኑዋቸውን ተሸክመው ለማስፈጸም ከሚደክሙ አካላት ጋር በመመሳጠር ዐውደ ምሕረትን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ነገር ግን በሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና በጠንካራ ምእመናን ተጋድሎ ዓላማቸው አልተሳካም፡፡ ሰባክያነ ወንጌልን የሚመድቡትና የማስተማር ሓላፊነት የተሰጣቸው አንዳንድ የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች በዐውደ ምሕረት ላይ ወጥተው ሲያስተምሩ ስለ ቅዱሳን ማስተማር የኢየሱስን ማዳን ይሸፍናል ሲሉ ይሰማሉ፡፡ የሚጋብዟቸው መምህራን ደግሞ ኢየሱስን ብቻ እንሰብካለን የሚል መፈክር አንግበው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ያልገባቸው ወይም አውቀው ለማደናገር የሚጥሩት ስለ ቅዱሳን መስበክ ስለኢየሱስ ክርስቶስ መስበክ መሆኑን ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአንዳንድ አጥቢያዎች አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ተጀምረው ሳይጠናቀቁ ገና በመቃኞ እያሉ እና አጸዱ እንኳን ቅጥር ሳይኖረው ሁሉም ቁሳቁስ የተሟላለት ዘመናዊ አዳራሽ የሚሠሩም አሉ፡፡ ለምን ተብለው ሲጠየቁ ለወንጌል ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ስለሆነ የሚል መልስ ያቀርባሉ፡፡ በእውነቱ የሰው ልጅ ድኅነት ማግኘት ገድዷቸው ይህን ቢያደርጉ መልካም ነበር፡፡ የእነሱ ዓላማ ግን ሌላ ነው፡፡ ሰዎች ከመንግሥተ ሰማያት በአፍአ እንዲቀሩ ማድረግ፡፡ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን አሳንሶ አዳራሾችን ዘመናዊ አድርጐ መገንባት የተሐድሶዎች አንድ ስልት ተደርጎ እየተሠራበት ነው፡፡ ይህንን አካሔድ የሚቃወሙትንየወንጌል ጸሮች እያሉ ይሳደባሉ፤ ምእመናን እንዲጠሏቸው ያደርጋሉ፡፡ ለአካሔዳቸው እንቅፋት ይሆናሉ ያሉዋቸውን በሓላፊነት የሚገኙ አገልጋዮች ማባረር፣ ያላጠፉትን ይህን ጥፋት ፈጸሙ በማለት የሀሰት ስም መስጠት፣ ማብልጠልና ከምእመናን ጋር ማጋጨት በአዲስ አበባ የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ በዚህ ምክንያትም በየፖሊስ ጣቢያውና በየፍርድ ቤቱ ሲጓተቱ የሚውሉ አገልጋዮች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መጥቷል፡፡

ይህ አካሔድ በቶሎ መፍትሔ ካልተሰጠው ከቅዳሴ በኋላ ዐውደ ምሕረት ላይ ተአምረ ማርያም ሳይነበብ ምእመናን ወደ አዳራሽ እንዲገቡ መደረጉ የማይቀር ነው፡፡ እነዚህ እና የመሳሰሉት አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሽፋን ተደርገው የሚሠሩ የተሐድሶ ቅሰጣዎች ናቸው፡፡

ሌላው ደግሞ በግልጽ የሚሠራው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ፍል ውኃ አካባቢ የሚገኝ ተስፋ ተሐድሶ የሚባል ድርጅት አለ፡፡ ይህ ድርጅት ላለፉት ሦስትና ዐራት ዓመታት ከተለያዩ ቦታዎች ለተውጣጡ የገዳማት አበምኔቶች፣ የአብነት ትምህርት ቤት መምህራን፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚያገለግሉ ቀሳውስትና ዲያቆናት ሥልጠና እየሰጠ በሰርተፊኬት አስመርቋል፡፡ ከ፳፻ወ፮ ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ፍኖተ ሕይወት ማኅበረ መድኀኔዓለም የተስፋ ተሐድሶ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የሚባል ተቋም ከፍቶ በዲፕሎማ ማስመረቅ ጀምሯል፡፡ ድርጅቱ ነሐሴ ፲፰ ቀን ፳፻ወ፮ ዓ.ም ደግሞ Integrated Theological Training and Skill Development for Africa ከሚባል ኮሌጅ ጋር በመተባበር የመጀመሪያ ዙር ዐሥር ተማሪዎችን በዲፕሎማ አስመርቋል፡፡

በአጠቃላይ የአዲስ አበባ እና ዙሪያውን እንቅስቃሴ ስንመለከት በገንዘብ ጥማት ልቡናቸው በታወረ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ በተሐድሶ እንቅስቀሴ መረብ ውስጥ ባሉ ስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች እና በፕሮቴስታንት ድርጅቶች ጥምረት የሚካሔድ ነው፡፡ ገንዘብ እስካገኙ ድረስ ለቤተ ክርስቲያን ዶግማና ቀኖና ደንታ የሌላቸው የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ባሉባቸው አጥቢያዎች እና ከተሐድሶዎች ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያላቸው የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች ባሉባቸው አጥቢያዎች ዐውደ ምሕረቱ የሚፈቀደው ለኦርቶዶክሳውያን ሳይሆን ለተሐድሶ መናፍቃን ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለው እንቅስቃሴ በዚህ መልክ የሚቀጥል ከሆነ ከጊዜ በኋላ የተወሰኑ አጥቢያዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አይደለንም ማለታቸው የማይቀር ነው፡፡
ሰሜኑን ማእከል ያደረገ የተሐድሶ እንቅስቃሴ
ይህ እንቅስቃሴ የክርስትና መሠረት የተጣለበትን ሰሜኑን የአገራችንን ክፍል ለማጥፋት ታቅዶ የሚካሔድ ነው፡፡ እንቅስቃሴው ጥንታውያን ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በትምህርት ስም፣ በማኅበራዊ ልማቶች ስም፣ በእርቅና ሰላም ስም፣ ማረሚያ ቤቶችን እናግዛለን በሚል ስም ምእመናን እና ሕፃናት ላይ ትኩረት አድርገው ይሠራሉ፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ ፊታውራሪዎች ከሣቴ ብርሃን የተሐድሶ ድርጅት፣ መሠረተ ክርስቶስ ቸርችና የኢትዮጵያ አዲስ ኪዳን መጥምቃዊት ቸርች ሲሆኑ በግለሰብ ደረጃ እንቅስቃሴው ውስጥ ታላቅ ሱታፌ ያላቸው ግለሰቦች አሉ፡፡

ከሣቴ ብርሃን ከመወገዙ በፊትም የትኩረት አቅጣጫው የነበረው ሰሜኑ የአገራችን ክፍል ነበር፡፡ የከሣቴ ብርሃን ቅጥረኞቹ ጽጌ ሥጦታው፣ ሠረቀ ብርሃን ዘወንጌል፣ ጌታቸው ምትኩ፣ ባዩ ታደሰና ሙሴ መንበሩ ከአዲስ አበባ ተነሥተው በጎጃም በር ወጥተው ሥልጠና ሰጥተው፣ ቅኝት አድርገውና አዳዲስ ተከታዮች አፍርተው በሸዋ በር ይመለሳሉ፡፡ በ፳፻ወ፯ ዓ.ም ብቻ ሸኖ፣ አንጾኪያ፣ ደሴ፣ ጎንደር፣ ባሕር ዳር ሁለት ጊዜ እና አዲስ አበባ ላይ ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትና አብነት ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ በአጠቃላይ ከሁለት መቶ በላይ ለሚሆኑ ካህናትና የአብነት መምህራን ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ ሥልጠናውን የሚወስዱት ሰዎች የሚመለመሉት በከሣቴ ብርሃን ቢሆንም ሥልጠናው የሚሰጠው በፕሮቴስታንት አዳራሾችና በፕሮቴስታንት ፓስተሮችም ነው፡፡

ከ፳፻ወ፭ ዓ.ም ጀምሮ ብሔራዊ ተሐድሶን አመጣለሁ እያለ ሌሎችን የተሐድሶ ድርጅቶች ሲቀሰቅስና ሲያስተባብር የነበረው ይኸው ድርጅት ባለፈው ዓመት የወንጌል አገልግሎት ማኅበራት ኅብረት የሚባለው እናት የተሐድሶ ድርጅት እንዲቋቋም አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው፡፡ ስሙን በመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ስም ሠይሞ ስለሚንቀሳቀስ የቤተ ክርስቲያን አካል መስሎ የሚታያቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ያለ ቤተ ክርስቲያን ዕውቅናና ፈቃድ ከተከፈቱት የቴሌቪዥን መርሐ ግብሮች በተጨማሪ ፳፻ወ፬ ዓ.ም ላይ የተወገዘው ከሣቴ ብርሃን የተሐድሶ ድርጅትም መጥቅዕ የተባለ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ሊጀምር ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡

ሁለተኛው የሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተሐድሶ እንቅስቃሴ ፊታውራሪ የሆነችው መሠረተ ክርስቶስ ቸርች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰሜኑን በወንጌል እንወርሳለን የሚል ፕሮጀክት ነድፋ እየሠራች ሲሆን ፕሮጀክቱ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ፈሰስ እየተደረገ የሚሠራ ነው፡፡ መሠረተ ክርስቶስ እንደሽፋን ተጠቅማ ሰሜኑ ላይ ትኩረት አድርጋ የምትሠራው ሁለት ፕሮጀክቶችን ነው፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ሰሜኑን በወንጌልና የማረሚያ ቤቶች አገልግሎት የሚባሉ ናቸው፡፡ የእነዚህ ፕሮጀክቶች ዋና የትኩረት አቅጣጫ ሰሜኑ የአገራችን ክፍል ቢሆንም በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ እንቅስቀሴዎችን ታደርጋለች፡፡

ሰሜኑን በወንጌል የሚባለው ፕሮጀክት በትግራይ፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ጎጃምና ሸዋ አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የተለያዩ አጥቢዎች፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችና ማረሚያ ቤቶች ላይ ትኩረት አድርጋ እየሠራች ነው፡፡ ለዚህ ዓላማ ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብ የምታገኘው ከተለያዩ የውጪ ድርጅቶች (የፕሮቴስታንት) ከሚላክ ገንዘብ፣ በሚያውቋቸው ሰዎች ከውጪ ከሚሰበሰብ እርዳታ እና ያሠለጠኗቸውን ሰዎች በቪሲዲ በመቅረፅና እርሱን በማሳየት ከደጋፊ ዎች በሚገኝ ገንዘብ ነው፡፡ የመሠረተ ክርስቶስ የልማት ድርጅት (Meserete Kirstos Church Relief Development) የታላቁ ተልእኮ አገልግሎት አጋር ስለሆነ ከዚህ ድርጅትም የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ይደረግላታል፡፡

የዚህ እንቅስቃሴ ዓላማ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ካህናት፣ ዲያቆናትና መሪጌቶች በገንዘብ በማታለል፣ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት፣ ማንነታቸውን መለወጣቸው እንኳን ሳይታወቃቸው የተሐድሶ እንቅስቃሴው አጋርና ቀኝ እጅ እንዲሆኑ በማድረግ በውስጥ ሆነው የተሐድሶ ሥራ እንዲሠሩ ተልእኮ መስጠት ነው፡፡ ሥልጠና የሚሰጡላቸው ደግሞ የተሐድሶውን እንቅስቃሴ ዓላማ ብለው የያዙት እነ ሠረቀ ብርሃን ዘወንጌል፣ ጽጌ ሥጦታው፣ አግዛቸው ተፈራ፣ የዕድል ፈንታ፣ ታምራት፣ ፓ/ር ሰሎሞን ከበደ፣ ወዘተ ናቸው፡፡

በ፳፻፮ ዓ.ም ብቻ ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ለመጡ ከሃምሳ በላይ ለሚሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወረዳ ቤተ ክህነት፣ ሊቃነ ካህናት፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት ሥልጠና ሰጥታለች፡፡ ሥልጠናው በተለያዩ ዙሮች መሐል ሜዳ፣ አዲስ አበባና ደብረ ዘይት ላይ የተካሔደ ነበር፡፡ ስለ እርቅና ሰላም አስተምራለሁ በሚል ሰበብ የማሠልጠኛ ሰነድ አዘጋጅታ የራሷን ዶክትሪን እያስተማረች ነው፡፡ ለዚሁ ዓላማ በ፳፻ወ፯ ዓ.ም የብርሃን ፍሬ የሚባል የበጎ አድራጎት ድርጅት አቋቁማለች፡፡ የበጎ አድራጎቱ መመሥረት ዋና ዓላማ በልማት ስም ምንፍቅናን ማስፋፋት ሲሆን “ወንጌልን ማስፋፋት ዋና ዓላማችን ቢሆንም በውስጠ ታዋቂነት የሚሠራ እንጂ ከመተዳደሪያ ደንቡ ላይ አይቀመጥም” በማለት በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የተቀመጡት የበጎ አድራጎት ማኅበሩ “የማስመሰያ” ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

1.የቂም በቀል፣ ደም የመመለስ ወይም የጥቁር ደም፣ የነፍስ ግድያ ባህልና ግጭትን እንደ ጀግንነት የመቁጠር ልማድን ለኅብረተሰቡ በማስተማር ማስወገድ፣

2.ኋላ ቀር የሥራ ባህልን፣ ከአቅም በላይ መደገስንና አባካኝነትን፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻን፣ የትዳር መፍረስንና የቤተሰብ መበተንን፣ ለዕድገትና ለሰላም ጠንቅ የሆኑ አስተሳሰብ አመለካከትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ኅብረተሰቡን በማስተማርና በማማከር ማስወገድ፣

3.በልዩ ልዩ ሱሶችና መጥፎ ልማዶች ተጠምደው ጎጂ ልማደኛ ሆነው ጎዳና ውስጥ ያሉ ወጣቶችን ካሉበት ሱስና መጥፎ ልማድ እንዲወጡ መርዳት፣

4.የአቅም ግንባታ የመልካም ሥራ ሠርቶ ማሳያ ልማቶችን መሥራት ናቸው፡፡

በማረሚያ ቤቶች ውስጥ በእርዳታ ሰበብ በመግባት በሃምሳ ስድስት (፶፮) ማረሚያ ቤቶች ላይ የእምነት ማስፋፋት ሥራ እየሠራች ሲሆን ታራሚዎቹ ሲወጡ በሚሔዱበት ቦታ የራሳቸው “ቸርች” እንዲያቋቁሙ ተልእኮ ትሰጣለች፡፡ በሃያ አንዱ (፳፩) ማረሚያ ቤቶች ደግሞ መደበኛ ሠራተኞች ተቀጥረው ይሠራሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ተቀጣሪዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዲቁናና በሰንበት ትምህርት ቤት ሲያገለግሉ የነበሩ ተሐድሶዎች ናቸው፡፡ ስውሩ የእምነት ማስፋፋት ሥራቸው እንዳይጋለጥ የተወሰኑ ማረሚያ ቤቶች ላይ የልማት ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡ የተወሰኑ ማረሚያ ቤቶች ላይ ቤተ መጻሕፍትና ካፍቴሪያ ሠርተው ሰጥተዋል፡፡ ለታራሚዎች የልብስና የሳሙና እርዳታ ያደርጋሉ፡፡

መሠረተ ክርስቶስ ከእነዚህ ሁለት ዋና ዋና ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በትምህርትና አቅም ግንባታ፣ በምግብ ዋስትና፣ በልማት፣ የተፈጥሮ አደጋን እና ኤች አይ ቪ ኤድስን በመከላከል ስም በመግባት ምእመናንን የመቀሰጥ ሥራ ትሠራለች፡፡ አዲስ አበባ፣ ናዝሬት፣ ደብረ ዘይት፣ ሆለታ፣ ማርቆስ፣ ሜታ ሮቢ፣ መሐል ሜዳ፣ ጀልዱ፣ ቀዋ ገርባ፣ ወዘተ እነዚህ ፕሮጀክቶች ተፈጻሚ የሆኑባቸውና ውጤት ያመጡባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ የልማት ሥራዎች መሠራታቸውን ማንም ኢትዮጵያዊ አይቃወምም፣ ነገር ግን በልማት ስም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናንን በመንጠቅ፣ ከማንነቱ መለየትና ከርስት መንግሥተ ሰማያት በኣፍአ እንዲቀር ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ እኛ የምንቃወመውም ርዳታውን እና ልማቱን ሳይሆን ከልማቱ በስተጀርባ ያለውንና ሰውን ከሃይማኖት መለየቱን ነው፡፡

የኢትዮጵያ አዲስ ኪዳን መጥምቃዊት ችርች ደግሞ በትምህርት ዘርፍ ላይ ተሰማርታ ሕፃናት ላይ ትኩረት አድርጋ የምትሠራ ናት፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ትምህርት ቤት በመክፈት በቅናሽ ዋጋ እና ለወላጆች በሚደረግ ድጋፍ ስም የራሷን የእምነት ማስፋፋት ሥራ እየሠራች ነው፡፡ እስካሁን የእንቅስቃሴው አድማስ በሰሜን ሸዋ ዞን ዓለም ከተማ ወረዳ ላይ ቢሆንም ከተነደፈው ፕሮጀክትና ይዘውት ከተነሡት ግብ አንጻር በዚህ እንደማያቆም ግልጽ ነው፡

ሌላው መነሣት ያለበት ጉዳይ ባለፉት ቅርብ ዓመታት ትግራይ አካባቢ እየተካሔደ ያለው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ማኅበረ ሰላማ መወገዙ የሚፈልገውን የቅሰጣ ተግባር ከመሥራት አልከለከለውም፡፡ እንዲያውም አድማሱን አስፍቶ ከምእመናን ወጥቶ በየዩኒቨርሲቲው የሚማሩ ተማሪዎችን እና የቅዱስ ፍሬምናጦስ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትን በመሰብሰብ በሥውር ማሠልጠንና ማስተማር ጀምሯል፡፡ ከማኅበረ ሰላማ በተጨማሪ ባለፈው ዓመት ትግራይ ተሐድሶ መንፈሳዊ ማኅበር (ቤተ ክርስቲያን) የሚባል የተሐድሶ ማኅበር ተመሥርቷል፡፡ ይህ ማኅበር ደንብ ቀርጾ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየን እየተካሔደ ያለው የተሐድሶ እንቅስቃሴ አድማሱ ምን ያህል ሰፊ እንደ ሆነና አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ሰሜኑን የአገራችንን ክፍል ምን ያህል ትኩረት እንዳደረጉበት ነው፡፡

የአንድ አገር ልማትና ዕድገት ወደ ላቀ ደረጃ የሚደርሰው የሃይማኖት፣ የዘር፣ የቀለም ገደብ ሳይገድበው በተባበረ ክንድ ሲሠራ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው ሁሉ የአገሩን ልማትና የኅብረተሰቡን ዕድገት የሚጠላ አይሆንም፡፡ ሆኖም የልማቱ ተባባሪዎች ነን የሚሉ አካላት ፊት ለፊት ሰውን የሚያሳሱና መልካም የሚመስሉ ነገሮችን እያሳዩ ውስጣቸው ግን በማር የተለወሱ መርዞች ይዘውና ሌላ ተልእኮ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ልማቱም ልማት፣ ዕድገቱም የተሟላ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም አንድ ሕዝብ ለአገሩ ክብር፣ ለሃይማኖቱ ፍቅር፣ ለማኅበራዊ እሴቱ ዋጋ ከሌለው ማልማትም ማደግም አይችልምና፡፡

እስካሁን ያየናቸው በልማት ስም የተሠሩት ሥራዎች ደግሞ ውስጣቸው ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ሴራ ያነገቡ የራስን አስተሳሰብና እምነት በሌ ሎች ላይ ለመጫን ዓላማ ያደረጉ ናቸው፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሔድ ግን ፍትሐዊም ሃይማኖታዊም አይደለም፡፡ ልማትን እንደ መሸፈኛ ተጠቅመው የቀረቡት ከላይ የጠቀስናቸው ተግባራትም በቤተ ክርስቲያን ላይ የተነጣጠሩ የጥፋት ተልእኮዎች እንጂ አማናዊ ልማቶች ስላልሆኑ ዝም ተብለው መታየት የለባቸውም፡፡
ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጋዜጣ፣ 23ኛ ዓመት ቁጥር 3፣ ቅጽ 23 ቁጥር 331፣ ከጥቅምት 16-30 ቀን 2008 ዓ.ም

Wednesday, 11 November 2015

መፈተን

የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ እወቁ፡፡ያዕ1፡2

እነዚህ ለማሳያነት በተጠቀሱት የማኅበሩ ተግዳሮቶች መነሻነት በአንዳንድ ግለሰቦች አማካይነት መዋቅሮችን አላግባብ በመጠቀም የግለሰቦቹን ምኞት ከግብ ለማድረስ የሚሠሩና ጥንቃቄ ያልታከለባቸው እርምጃዎች እንጂ የቤተ ክርስቲያን ወይም የመንግሥት ውሳኔ ነው ብለን አናምንም፡፡ ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አካል እንደመሆኑ ፈተና ስለማይለየው ስለሚያጋጥሙት ፈተናዎች በጸሎት፣ የሚመለከታቸው አካላት በማስረዳትና በመወያየት፣ እንዲሁም በመታገስ አልፎ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሰረተችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እግዚአብሔር እስከፈቀደበት ጊዜ ድረስ ያገለግላል፡፡

ማኅበሩ ፈተና ሲያጋጥመው መንፈሳዊ ማኅበር እንደመሆኑ መፍትሔ ለማግኘት የሚሄድባቸው መንገዶች ሁልጊዜም የታወቁ ናቸው፡፡ ችግሮች ሲመጡ ጊዜያዊና በእግዚአብሔር ኃይል በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ መሆናቸውን በመረዳት በጥበብና በትዕግስት ከሚመለከከታቸው አካላት ሁሉ ጋር እየተወያየ ይፈታል፡፡ የችግር አፈታቱ ሥርዓት መንፈሳዊነትን የተከተለ በመሆኑ ሥጋዊ አስተሳሰብን ሳይጨምር ሃይማኖታዊ ፈተና ሲመጣ ማሸነፊያው ሃይማኖታዊ ኃይል ነው ብሎ ያምናል፡፡ እርሱም እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጎ በጾምና በጸሎት በትዕግስትና በጽናት፤ እግዚአብሔርን በመጠየቅ ነው፡፡

በማርቆስ ወንጌል ላይ እንደምናገኘው፡- (ማር. 4፡37) “ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር። እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ አንቅተውም። መምህር ሆይ፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት። ነቅቶም ነፋሱን ገሠጸው ባሕሩንም። ዝም በል፥ ፀጥ በል አለው። ነፋሱም ተወ ታላቅ ፀጥታም ሆነ። እንዲህ የምትፈሩ ስለ ምን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም? አላቸው። እጅግም ፈሩና። እንግዲህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? ተባባሉ።” ይላል፡፡ በታንኳይቱ የተመሰለችው ቤተ ክርስቲያን በፈተና ልትናወጥ ትችላለች፡፡ እንዲህ ባለ ጊዜ በውስጧ ያለውን፣ ነገር ግን እኛ የድርሻችንን እስክንወጣ ድረስ የሚጠብቀውንና ዝም ያለ (የተኛ) የሚመስለውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በጸሎት መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ፈተናን ጸጥ የሚያደርግ አምላክ እንደምናመልክ ልንዘነጋ አይገባምና ፡፡

ማኅበሩ በቤተክርስቲያንም ሆነ በማኅበራችን ዙሪያ ስላሉ ነገሮች ማንኛውንም መረጃ የሚያስተላልፈው በራሱ ሚዲያና በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ሥርዓት ባለው መልኩ በሚመለከታቸው የማኅበሩ ኃላፊዎች በኩል እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በሆነ መንገድ የሚተላለፍ ልዩ ልዩ መረጃዎችንና ሀሳቦችን በመያዝ ማኅበሩን በተመለከተ የግል ሀሳብንና ተግባርን ማንጸባረቅ አግባብ አለመሆኑን ሁሉም አካላት ሊያውቀው ያስፈልጋል፡፡
ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳን ዓላማን ግብ ያለው በመሆኑ በጊዜው በሚታዩ ጥቅመኞችና አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ሁከት ሳንዘናጋ የወንጌል ተልእኳችንን በጥበብና በትዕግስት ከግብ ማድረስ ይገባናል እንላላን፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ያዕቆብ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ እወቁ፡፡ ያዕ.1፡2 እንዳለ ስለ እምነታችንና ስለቤተ ክርስተያናችን የምናደርገውን አገልግሎት ፈታኙ ዲያብሎስ ሊያደናቅፍ ሠራዊቶቹን ቢያሰማራም እግዚአብሔር አምላካችንን ትዕግስትንና ጽናትን እንዲሰጠን ፈተናውንም እንዲያሳልፍልን በጽናት እንለምነው፡፡- እርሱ በሰው ዘንድ የማይቻለውን እንድንችል ማድረግ ያውቅበታልና፡፡ ለዚህም የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን፡