የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ እወቁ፡፡ያዕ1፡2 |
እነዚህ ለማሳያነት በተጠቀሱት የማኅበሩ ተግዳሮቶች መነሻነት በአንዳንድ ግለሰቦች አማካይነት መዋቅሮችን አላግባብ በመጠቀም የግለሰቦቹን ምኞት ከግብ ለማድረስ የሚሠሩና ጥንቃቄ ያልታከለባቸው እርምጃዎች እንጂ የቤተ ክርስቲያን ወይም የመንግሥት ውሳኔ ነው ብለን አናምንም፡፡ ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አካል እንደመሆኑ ፈተና ስለማይለየው ስለሚያጋጥሙት ፈተናዎች በጸሎት፣ የሚመለከታቸው አካላት በማስረዳትና በመወያየት፣ እንዲሁም በመታገስ አልፎ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሰረተችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እግዚአብሔር እስከፈቀደበት ጊዜ ድረስ ያገለግላል፡፡
ማኅበሩ ፈተና ሲያጋጥመው መንፈሳዊ ማኅበር እንደመሆኑ መፍትሔ ለማግኘት የሚሄድባቸው መንገዶች ሁልጊዜም የታወቁ ናቸው፡፡ ችግሮች ሲመጡ ጊዜያዊና በእግዚአብሔር ኃይል በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ መሆናቸውን በመረዳት በጥበብና በትዕግስት ከሚመለከከታቸው አካላት ሁሉ ጋር እየተወያየ ይፈታል፡፡ የችግር አፈታቱ ሥርዓት መንፈሳዊነትን የተከተለ በመሆኑ ሥጋዊ አስተሳሰብን ሳይጨምር ሃይማኖታዊ ፈተና ሲመጣ ማሸነፊያው ሃይማኖታዊ ኃይል ነው ብሎ ያምናል፡፡ እርሱም እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጎ በጾምና በጸሎት በትዕግስትና በጽናት፤ እግዚአብሔርን በመጠየቅ ነው፡፡ በማርቆስ ወንጌል ላይ እንደምናገኘው፡- (ማር. 4፡37) “ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር። እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ አንቅተውም። መምህር ሆይ፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት። ነቅቶም ነፋሱን ገሠጸው ባሕሩንም። ዝም በል፥ ፀጥ በል አለው። ነፋሱም ተወ ታላቅ ፀጥታም ሆነ። እንዲህ የምትፈሩ ስለ ምን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም? አላቸው። እጅግም ፈሩና። እንግዲህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? ተባባሉ።” ይላል፡፡ በታንኳይቱ የተመሰለችው ቤተ ክርስቲያን በፈተና ልትናወጥ ትችላለች፡፡ እንዲህ ባለ ጊዜ በውስጧ ያለውን፣ ነገር ግን እኛ የድርሻችንን እስክንወጣ ድረስ የሚጠብቀውንና ዝም ያለ (የተኛ) የሚመስለውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በጸሎት መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ፈተናን ጸጥ የሚያደርግ አምላክ እንደምናመልክ ልንዘነጋ አይገባምና ፡፡ ማኅበሩ በቤተክርስቲያንም ሆነ በማኅበራችን ዙሪያ ስላሉ ነገሮች ማንኛውንም መረጃ የሚያስተላልፈው በራሱ ሚዲያና በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ሥርዓት ባለው መልኩ በሚመለከታቸው የማኅበሩ ኃላፊዎች በኩል እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በሆነ መንገድ የሚተላለፍ ልዩ ልዩ መረጃዎችንና ሀሳቦችን በመያዝ ማኅበሩን በተመለከተ የግል ሀሳብንና ተግባርን ማንጸባረቅ አግባብ አለመሆኑን ሁሉም አካላት ሊያውቀው ያስፈልጋል፡፡
ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳን ዓላማን ግብ ያለው በመሆኑ በጊዜው በሚታዩ ጥቅመኞችና አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ሁከት ሳንዘናጋ የወንጌል ተልእኳችንን በጥበብና በትዕግስት ከግብ ማድረስ ይገባናል እንላላን፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ያዕቆብ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ እወቁ፡፡ ያዕ.1፡2 እንዳለ ስለ እምነታችንና ስለቤተ ክርስተያናችን የምናደርገውን አገልግሎት ፈታኙ ዲያብሎስ ሊያደናቅፍ ሠራዊቶቹን ቢያሰማራም እግዚአብሔር አምላካችንን ትዕግስትንና ጽናትን እንዲሰጠን ፈተናውንም እንዲያሳልፍልን በጽናት እንለምነው፡፡- እርሱ በሰው ዘንድ የማይቻለውን እንድንችል ማድረግ ያውቅበታልና፡፡ ለዚህም የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን፡
|