Monday, 9 November 2015

EOTC - TV: ነገረ ድኅነት - በቅዱስ መፅሃፍ አስተምኅሮ መሰረት የትኛውን ስናደርግ ነው የምንድነው?

ለአረሙ እንድከም ወይስ ለእህሉ?

እህል ወይስ አረም ?

         በዲያቆን ዳንኤል ክብረት
አሁን ባለንበት ዘመን ያለን የኢትዮጵያ ትውልድ የሀገራችንን ታሪክ፣ የሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነትና የመሪዎቻችንን ሁኔታ ስንነጋገርና ስንጽፍ በአብዛኛው አሉታዊውን ነገር ይበልጥ ጎልቶ እንዲወጣ፣ ጥላቻ እንዲበቅል፣ ቂም እድሜ እንዲያገኝ፣ ልዩነት እንዲሰፋ፣ ጠብም ሥር እንዲሰድ በማድረግ ላይ የተመሠረተ ሆኖ ይታያል፡፡ ርግጥ ነው በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተፈጠሩ የመስተጋብር ችግሮች ሁሉ በኛም ሀገር ተፈጥረዋል፡፡ በኛ ሀገር የተፈጠሩትም በሌሎች ይገኛሉ፡፡ በዓለም ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ የኩራትም የውርደትም፣ የፍቅርም የጠብም፣ የሰላምም የጦርነትም፣ የእኩልነትም የጭቆናም፣ የመረዳዳትም የመጠፋፋትም፣ የሥልጣኔም የስይጣኔም ታሪኮች አሉ፡፡ እንኳን በአንድ ሀገር የሚኖሩ የተለያየ ዘውግ፣ ቋንቋ፣ እምነትና የኑሮ ደረጃ ያላቸው ቀርተው በተመሳሳይ ቋንቋ፣ ባሕልና የኑሮ ደረጃ የሚገኝ የአንዲት ሀገር አንድ ወጥ ሕዝብ እንኳን በውስጡ ጽጌረዳም እሾህም አለው፡፡ 

የሚገርመው ነገር ኢትዮጵያን ከዓለም የተለየች የሚያደርጋት ምን እንደሆነ አለመታወቁ ነው፡፡ ኢትዮጵያኮ ሲኦልም አልነበረችም መንግሥተ ሰማያትም አልነበረችም፡፡ ሀገር ነበረች፣ አሁንም ሀገር ነች፡፡ ሀገር የሚገጥማት ፈተና ሁሉ ገጥሟታል፤ ሀገር የሚኖራት ጸጋ ሁሉ ታድሏታል፡፡ በአንዳንድ የታሪክ ምእራፏ ለመንግሥተ ሰማያት ጠጋ፣ በሌላው ምእራፏ ደግሞ ለሲኦል ጠጋ ብላ ይሆናል እንጂ፣ ፈጽማ ሲኦልና መንግሥተ ሰማያት ሆና አታውቅም፡፡ እኛ ልጆቿ ግን ወደ መንግሥተ ሰማያት ጠጋ ማለት ብቻ ሳይሆን ምድራዊት መንግሥተ ሰማያት ብትሆንልን እንወዳለን፤ ለዚያም እንሠራለን፡፡ ወደዚያ በተጠጋችበት ታሪክም እንኮራለን፤ ወደ ሲኦል ለመውረድ አዘንብላ የነበረችበትንም ዘመን ስናስብ በልብ ስብራት እንመታለን፡፡
የታሪክ ሂደት ያመጣቸውን የትናንት ነገሮች ዛሬ አንቀይራቸውም፡፡ ሆነዋልና፡፡ ነገር ግን እንማርባቸዋለን፤ ከትናንት ወስደንም ለዛሬ እንጠቀምባቸዋለን፡፡ የዛሬ ማንነታችን መገንቢያም እናደርጋቸዋለን፡፡ በተቃራኒውም ያለፉትን ዘመናት ጠባሳዎች እየነካካን ቂምን ማመርቀዝ፣ ጥላቻን ማጎንቆል፣ ልዩነትን ማስፋት፣ ፍቅርንም ማደብዘዝ እንችላለን፡፡ ሁለቱም በእኛ ምርጫ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ምርጫው ለእህሉ ወይስ ለአረሙ ትለፋለታለህ? የሚለው ነው፡፡ 
ታሪካቸውን ለዕድገታቸውና ለሰላማዊ መስተጋብራቸው የተጠቀሙት ግን ከአረሙ ይልቅ ለእህሉ ጊዜና ጉልበታቸውን ያፈሰሱት ናቸው፡፡ ገበሬ ዓመት በሙሉ የሚለፋው አረም ለማብቀል አይደለም፡፡ አረም ለመብቀል ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ጉልጓሎ፣ አያስፈልገውም፡፡ ወንፈልና ደቦ አይሰበስብም፡፡ ጉልበትና ጊዜውን አያባክንም፣ ወዝና ላቡን አያንጠፈጥፍም፡፡ ለአረም አንድ ነገር በቂ ነው፡፡ ስንፍና ብቻ፡፡ ገበሬ ከሰነፈ ምንም ሳይደክም አረም እርሻውን ከዳር ዳር ይወርስለታል፡፡ በሬ ሳይጠምድ፣ እርሻ ሳይውል፣ ሌሊት ሳይነሣ፣ ማታ ሳይገባ፣ ዝናብ ሳይመታው፣ ፀሐይ ሳይከካው፣ ብርድ ሳይገርፈው፣ ወላፈን ሳይጠብሰው አረም እንዲሁ ይበቅልለታል፡፡ ገበሬ ለአረም አይለፋም፡፡
የገበሬን ጥበብ፣ የገበሬን ድካም፣ የገበሬን ጉልበት፣ የገበሬን ማዳበሪያ፣ የገበሬን ትዕግሥት፣ የገበሬን ሐሞት፣ የገበሬን ልምድ፣ የገበሬን  ጊዜ፣ የሚፈልገው እህሉ ነው፡፡ ወንፈልና ደቦ የሚሰበስበው ለእህሉ ሲል ነው፡፡ በሬ የሚጠምደው፣ ሞፈር የሚቆርጠው፣ ቀንበር የሚነድለው፣ ጎተራ የሚያዘጋጀው፣ አውድማ የሚለቅልቀው ለእህሉ ሲል ነው፡፡ አረም በስንፍና የሚበቅለውን ያህል እህል የሚበቅለው በጉብዝና ነው፡፡ እህል ያለ ገበሬው ጥበብ፣ ዕውቀት፣ ጉልበትና መሣሪያ ከምድር አይወለድም፡፡ አረም ግን አዋላጅ አይፈልግም፡፡ አረም በራሱ ተወልዶ በራሱ ያድጋል፡፡   
በታሪክ መስክ ላይ የተሠማራ ትውልድም ጊዜውን ማጥፋት፣ ጉልበቱን መሠዋት፣ ጥበቡን ማፍሰስ፣ ዕውቀቱን መከስከስ፣ ያለበት ለአረሙ አይደለም፡፡ ጥላቻው፣ ቂም በቀሉ፣ መቆራቆሱ፣ መናከሱ፣ መለያየቱ፣ መጠፋፋቱ፣ ይኼ የትውልድ አረም ነው፡፡ በስንፍና ብቻ ሊበቅል የሚችል፡፡ በታሪካችን ውስጥ በቅሎ የነበረው እህል ፍቅራችን ነበረ፣ አንድነታችን ነበረ፣ መዋለዳችን ነበረ፤ መዋሐዳችን ነበረ፤ ሥልጣኔያችን ነበረ፤ ጀግንነታችን ነበረ፤ ነጻነታችን ነበረ፡፡ ትኩረታችንን እህሉ ላይ ካደረግነው አረሙን እንቋቋመዋለን፡፡ መቋቋምም ብቻ ሳይሆን እናጠፋዋለን፡፡ አረሙን ማጥፋት ያለብን አረም ስላልነበረ አይደለም፣ አረምን ለመሸፋፈን ሲባልም አይደለም፡፡ አረም ስለማይጠቅመን ነው፡፡ በሀገራችን እንክርዳድ የተሰኘው አረም ሳይለቀም ቀርቶ ከስንዴ ጋር ገብቶ ጠላ የሆነ እንደሆነ ያሳብዳል፡፡ ለዚህም ነው፡-
እንክርዳድ እንክርዳድ የተንከረደደ
ስንዴ መስሎ ገብቶ ስንቱን አሳበደ
የተባለው፡፡
አሁን አሁን በሀገራችን ጉልበታችንን እየጨረስን ያለነው አረሙን ለማብቀል ይመስላል፡፡ አንዲት ጽጌረዳን ከማብቀልና ፈንድታ አበባዋ ሠፈሩን እንዲያውድ ከማድረግ ይልቅ አንድ ማሳ ሙሉ አረም ማብቀል በጣም ቀላል ነው፡፡ አረሙ ስንፍናን ብቻ ይጠይቃልና፡፡ ጽጌረዳዋን ለማብቀል ግን ከመሬቱ፣ ከሰማዩ፣ ከአየሩ፣ ከአራዊቱ፣ ከአላፊ አግዳሚው ጋር መጋደልን ይጠይቃል፡፡  
በታሪካችን ውስጥ የነበረውን እህል ዘሩን አምጥተን መዝራት፣ ዘርተን መከባከብ፣ ተከባክበንም ማሳደግ ይገባን ነበረ፡፡ ጥበባችንን፣ ዕውቀታችን፣ ገንዘባችንንና ጉልበታችንን ለእርሱ ማፍሰስ ይገባን ነበረ፡፡ አሁን ግን ድርሰቶቻችንን፣ ሚዲያዎቻችንን፣ ሐውልቶቻችንን፣ ትርክቶቻችንን፣ ዲስኩሮቻችንን፣ ንግግሮቻችንን፣ የፖለቲካ ፕሮግራሞቻችንን የምናባክነው አረሙን ለማብቀል ሆኗል፡፡ አረምኮ ይህንን ሁሉ አይፈልግም ነበር፡፡ አረምን ለማብቀል ሥርዓተ ትምህርት መቅረጽ፣ ዩኒቨርሲቲ መገንባት፣ የፖለቲካ ፓርቲ ማደራጀት፣ ሚዲያ መዘርጋት፣ ብዕርና ወረቀት ማባከን፣ ምስትርናና ዱክትርና መድረስ አያስፈልግም ነበረ፡፡ አረም እንዲሁ ይበቅላልኮ፡፡
የፖለቲከኞቻችን ብስለት፣ የምሁሮቻችን ብቃት፣ የትውልዱ ምጥቀት፣ የተቋሞቻችን ሥልጠት፣ የሐሳቦቻችን ጥልቀት፣ የሚዲያዎቻችን ፍጽመት፣ የሥልጣኔያችን ርቀት፣ የጥበበኞቻችን ልህቀት የሚታወቀው ባበቀልነው እህል እንጂ ባበቀልነው አረም ብዛት አይደለም፡፡ ለአረምማ እነዚህ ሁሉ አያስፈልጉትም፡፡ እነዚህ ያስፈለጉት ሲቻል አረሙን ቀድሞ ለመከላከል፣ ካልሆነም የበቀለውን አርሞ እህሉን አህል ለማድረግ ነበር፡፡ ለማስተማር እንጂ ለማደንቆር ምን ትምህርት ቤት ይሻል? ለማዳን እንጂ ለማሳመም ምን ሆስፒታል ያስከፍታል? ለፍትሕ እንጂ ለወንጀል ምን ዳኝነት ያስፈልጋል? ለመግባባት እንጂ ላለመግባባት ምን ቋንቋ ያስፈልጋል? ለልዕልና እንጂ ለውርደት ምን ኪነ ጥበብ ያሻል? ለዓለም ዓቀፋዊ እሴቶች እንጂ ለጎጠኝነት ምን ጥበብ መፍሰስ ያሻዋል? ለማጥገብ እንጂ ለማስራብ ምን ፖሊሲ ያስፈልጋል? ለሥልጣኔ እንጂ ለስይጣኔ ምን ፓርቲ ማቋቋም ያስፈልጋል? ለጽድቅ እንጂ ለኃጢአት ምን የእምነት ተቋም ያሻል?
የኛ ጥበብ፣ ዕውቀት፣ ገንዘብና ጉልበት አረም ላይ እየፈሰሰ ነው፡፡ የገበሬ ጉብዝና በአረም ብዛት እንደማይለካው ሁሉ የትውልድ ጉብዝናም በአረም አይለካም፡፡ ‹እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ› እንዲሉ እንኳንና የእኛ ጥበብና ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ ተጨምሮበት አረም በራሱም ሀገር ያጠፋል፡፡
እንዲህ እርሻው ሁሉ አረም እስኪወርሰው
የለም ወይ፣ የለም ወይ፣ የለም ወይ ባገር ሰው
ተብሎ የለ፡፡
አረም አያዋለዱ ሀገርን ለማሠልጠን መመኘት፣ ተኩላን እያረቡ የበግ ሥጋን እንደመመኘት ያለ ነው፡፡
በገበሬዎቻችን ታሪክ ውስጥ በ16ኛው መክዘ በሀገራችን ተከስቶ በነበረው የሃይማኖት ጦርነት ጊዜ ከ20 ዓመታት በላይ ገበሬው ተረጋግቶ በእርሻ ላይ ስላልነበር አገሩን አረም ወርሶት ነበር ይባላል፡፡ በዚያ ጊዜ ከሀገራችን ገጽ የጠፉ የእህል ዓይነቶች አሉ፡፡ ለዘር ተብሎ የተቀመጠው ወይ በቀጠና ምክንያት ተበልቶ፣ አለያም ቤቱ ሲቃጠል ተቃጥሎ፣ ካልሆነም የተቀበረበት ቦታ በዘመን ብዛት ጠፍቶ ሳይተኩ የቀሩ የእህል ዘሮች አሉ፡፡ የካሕሳይ ገብረ እግዚአብሔርን ኅብረ ብዕር ያነበበ ሰው ከሚያያቸው የእህል ዘሮች መካከል ብዙዎቹ ስማቸውን ትተው ጠፍተው የቀሩት እንዲህ ባሉ ዘመናት ነው ይባላል፡፡ አረሙ ግን አልጠፋም፡፡ እንዲያውም ተመችቶት ነበር፡፡
በታሪካችንም ውስጥ እየጠፉና እየመነመኑ የመጡ በጎ እሴቶች፣ ባሕሎች፣ ልማዶችና ወጎች አሉ፡፡ አገር ችግር ላይ ስትወድቅ እህሉን የሚያመርተው ሲያጣ፣ ዘሩ ይጠፋል፡፡ ያንን ዕድልም አረሙ ይጠቀምበታል፡፡ ምድሩም እህል ተዘርቶበት የማያውቅ ይመስላል፡፡  
አሁን ለዚህ ትውልድ ጥያቄው አንድ ነው፤ ለአረሙ እንድከም ወይስ ለእህሉ? እህሉን በማምረት ብርታትህን ታሳያለህ ወይስ አረሙን በማብቀል ስንፍናህን? የኢትዮጵያ መልክ የሚቀየረው ለዚህ ጥያቄ በምንሰጠው መልስ ነው፡

"ሉቃስ ከ12ቱ ሃዋርያት ሳይሆንቱ ከ72 አርድት ነው"

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ
ጥቅምት 24 ቀን 2008 ዓ.ም ___በዲ/ን ኃይለ ማርያም አስፋው
ሉቃስ ማለት በላቲኑ ትርጓሜ ብርሃናማ፣ ብርሃን የያዘ ማለት ነው፡፡ በትርሜ ወንጌል የተሰጠው ትርጉም ደግሞ ሉቃስ ማለት ዓቃቤ ሥራይ (ባለ መድኃኒት) ማለት ነው፣ ቀድሞ ዓቃቤ ሥራይ ዘሥጋ (ሥጋዊ ሐኪም) ነበር በኋላ ግን ዓቃቤ ሥራይ ዘነፍስ ( መንፈሳዊ ሐኪም) ሆኖአልና፡፡ አንድም ተንሣኢ (ፈጣን) ማለት ነው ለስብከተ ወንጌል ይፋጠናልና፣ አንድም መበሥር (ብሥራ ነጋሪ) ማለት ነው ብሥራተ መልአክን ይጽፋልና በማለት ይተረጉመዋል፡፡የተወለደው በሶርያ አንጾኪያ ነው፡፡ የአሕዛብ ወገን የነበረና በኋላም ወደ ክርስትና እንደተመለሰ ታሪኩን የጻፉ ይናገራሉ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ አይሁዳዊ ሳይሆን ወንጌልን የጻፈ ወንጌላዊ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ከሰባ ሁለቱ አርድዕት ነው የሚቆጠረው፡፡

ቅዱስ ሉቃስ የተወደደ ሐኪም ነበር፡፡ ለዚህም ማረጋገጫው ቅዱስ ጳውሎስ በቆላስይስ መልእክቱ ም.4፡14 የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋልበማለት ገልጦታል፡፡ በወንጌሉም አጻጻፍ ላይ ስለ ሕመማቸውና ድኅነት ስለሚያገኙበት ሁኔታ ገልጦ ጽፏል፡- ስለ ደጉ ሳሚራዊ ሉቃ 10፡30-35፣ ደም ይፈሳት ስለነበረችው ሴት ሉቃ8፡43

ቅዱስ ሉቃስ ሠዓሊ ነበር፡፡ ይህ ሞያው ወንጌሉ ሲጽፍ ሥዕላዊና ገላጭ በሆነ መልኩ ለመጻፍ ረድቶታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንደሚናገረው የቅድስት ድንግል ማርያም ምስለ ፍቁር ወልዳ ለመጀመርያ ጊዜ የሳለው እርሱ ነው፡፡እነዚህም ሥዕሎች በኢትዮጵያ ውስጥ በተድባበ ማርያም' በደብረ ዘመዳ' በዋሸራ'በጅበላ ይገኛሉ፡፡

ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታት ምስጋናው መልክአ ሥዕል ላይ ሰላም ለሥዕልኪ እንተ ሠዐላ በእዱ ሉቃስ ጠቢብ ዘእም ወንጌላውያን አሐዱ ከወንጌላውያን አንዱ የሆነው ጠቢቡ ሉቃስ ለሣላት ሥዕልሽ ሰላምታ ይገባል እያለ እመቤታችንን አመስግኖአታል፡፡

ቅዱስ ሉቃስ ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር የተገናኘው በአንጾኪያ ነው፡፡ ከዚያ በኃላ ተወዳጅ ደቀ መዝሙር ሆነ፡፡ በ2ኛ ጢሞ 4፡11 ሉቃስ ብቻ ከእኔ ጋር አለ፣ እንዲሁም ፊል 1፡24 ላይ አብረውኝም የሚሠሩ ማርቆስና አርስጥሮኮስ ዴማስም ሉቃስም ሰላምታ ያቀርቡልሃል ብሎ እንደገለጠው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሰማዕትነት እስኪቀበል ድረስ ከርሱ ጋር እንደነበር በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ ገልጧል፡፡ ከቅዱስ ጳውሎስ በፊት የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር እንደነበረ ትርጓሜ ወንጌል ላይ ለዮሐንስ ምድረ ፅርዕ ደረሰችው፣ ለሰብዓ አርድእት ግን ዕጣ የላቸውም፡፡ አንዱም ሁለቱም ሆነው አንዱን ሐዋርያ አንዱም ሁለቱም ሆነው አንዱን ሐዋርያ ተከትለው ይሄዳሉ ሉቃስም ዮሐንስን ተከትሎ ይሄዳል፡፡ መቄዶንያ የምትባል ሀገር ከፍሎ አስተምር ብሎ ሰጥቶታል፡፡

የሠለሥቱ ሐዲሳት መቅድም ደግሞ እንዲህ ይገልጠዋል ለሰብዓ አርድዕት ዕጻ የላቸውም አንዱም ሁለቱም አንዱን ሐዋርያ እየተከተሉ ይሄዳሉ ሉቃም ዮሐንስን ተከትሎ ሔዷል፣ ከሀገረ ስብከቱ ከፍሎ መቄዶንያ የምትባል ሀገር አስተምር ብሎ ሰጥቶታል፡፡ ከዚያ ገብቶ ጌታ ከፅንስ ጀምሮ ያስተማረውን ትምህርት የሠራውን ትሩፋት፣ ያደረገውን ተአምራት ቢነግራቸው ከገቢረ ኃጢያት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከአምልኮ ጣዖት ወደ አምልኮ እግዚአብሔር ተመለሱ አመኑ ተጠመቁ፡፡ ትምህርት ካልደረሰበት ለማዳረስ በሚሄድበት ጊዜ ታዖፊላ መኮንነ እስክንድርያ ይለዋል በርሱ ስብከት አምኖ ዜና ሐዋርያትን ጻፍልኝ ብሎት ጽፎለታል፡፡ አጻጻፉ አምስት ወገን ነው፤ ጌታ እንዳረገ መቶ ሃያው ቤተሰብ ባንድነት እንደ ነበሩ ይሁዳ እንደወጣ፣ በእግሩም ማትያስ እንደገባ፣ ባድነት ሳሉም መንፈስ ቅዱስ እንደ ወረደላቸው፣ በኢየሩሳሌም የነበሩ አይሁድ እስጢፋኖስን በድንጋይ ወግረው እንደገደሉት ይልቁንም መምህሩ ቅዱስ ጳውሎስ ከእምነት እስከ ሞቱ ያስተማረውን ትምህርት የሠራውን ትሩፋት ያደረገውን ተአምራት ጻፍልኝ ብሎት ጽፎለታል:: ጥቅምት 22 በሚነበበው ስንክሳር የቅዱስ ጴጥሮስም ደቀ መዝሙር እንደነበር ተገልጧል፡፡

ቅዱስ ሉቃስ ከሰማንያ አሐዱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁለት መጻሕፍት አሉት፡፡ እነሱም የሉቃስ ወንጌልና የሐዋርያት ሥራ ናቸው፡፡ቅዱስ ወንጌሉን የጻፈው በአካይያ (በሮም 62-63 ዓ.ም ጻፈው የሚሉም አሉ) 58-60 ዓ.ም ሲሆን የጻፈበት ቋንቋ ፅርዕ ነው፡፡ የአጻጻፍ ስልቱ 'የትርጉም አጠቃቀሙ' የታሪክ ሂደቱ ሲታይ ቅዱስ ሉቃስ የተማረ ሊቅ እንደነበር ያስረዳል፡፡ ሲጽፍም የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን፥ በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ፥ እኔ ደግሞ ስለ ተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ በማለት እርግጠኛ ሆኖ ነው፡፡ ይህ አገላለጡ ቅዱስ ሉቃስ የታሪክ ሰው ነበር ያሰኛል፡፡ ሁለቱንም መጻሕፍት ማለትም ወልጌሉንና የሐዋርያት ሥራ ራሱ እንደጻፈው በማያሻማ መልኩ በወንጌሉ መጨረሻና በሐዋርያት ሥራ መጀመርያ ላይ የተጠቀመው አገላለጽ በማየት መረዳት ይቻላል፡፡ ወንጌሉ በእርገት ሲጨርስ €™እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው፣ ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ። እነርሱም፤ ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ።ሉቃ 24፡50-53 በማለት ሲሆን የሐዋርያት ሥራ ሲጀምር ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ኢየሱስ የመረጣቸውን ሐዋርያትን በመንፈስ ቅዱስ ካዘዛቸው በኋላ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ፥ ያደርገውና ያስተምረው ዘንድ ስለ ጀመረው ሁሉ መጀመሪያውን ነገር ጻፍሁ፤ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው። ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም
እንዳይወጡ አዘዛቸው፥ ነገር ግን። ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ የሐ.ሥራ 1፡1-4 በማለት ነው፡፡

የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ከሦስቱ በተለየ መልኩ ታሪካዊና ስዕላዊ በሆነ መልኩ በተለይ ከአይሁድ ውጪ ያሉትና አሕዛብ ሊረዱት በሚችሉ መልኩ የተጻፈ ነው፡፡ በዘመኑ ከነበረው የአይሁድ ስለ ሴቶች ከነበራቸው አመለካከት ወጣ ባለ መልኩ ስለ ሴቶች አጉልቶ በስፋት የጻፈ ወልጌልዊ ነው ፡፡በተጨማሪም ስለ መንፈስ ቅዱስ ጸጋ፤ ስለ ጸሎት ፤ስለ ርኅራኄ ፤ስለ ሀብታምና ድሃ በሰፊው የጻፈ ወንጌላዊ ነው፡፡ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ ስለ ቤተክርስቲያን' ስለ አንድነት' የሐዋርያነት መሠረት' ዓላማ' ትጋት' ማሸነፍ' ስለ ሌላው መጨነቅ' ኃላፊነትን ስለመወጣት'ተጋድሎን'በተግባር በሚታይና በሚጨበጥ ማስረጃ የጻፈ ሐዋርያ ነው፡፡

ቅዱስ ሉቃስ የሚመሰለው በገጸ ላህም ነው፡፡ምክንያቱም አምጽኡ ላሕመ መግዝዓ ወጥብሑ ንብላእ ወንትፌሣሕ ምስሌሁ (ፍሪዳ አምጡና እረዱ ከእርሱ ጋር እየበላን ደስ ይበለን) ሉቃ.15፤23 እያለ€™ ምሳሌውን ይጽፋልና፡፡ አንድም በጤግሮስ ይመሰላል ጤግሮስ ፈለገ መዓር (የመዓር ወንዝ) ነው ርስትነቱም ጸዊረ ነገር (ምሥጢር መሸከም) የሚቻላቸው ሰዎች ርስት ነው፡፡ ሉቃስም አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዘኢየአምሩ (አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው) ይገብሩ' በትዕግሥትክሙ ታጠርይዋ ለነፍስክሙ (በመታገሳችሁ ነፍሳችሁን ገንዘብ ታደርጋላችሁ) እያለ ክቡድ ክቡድ ነገር ይጽፋልና፡፡

ቅዱስ ሉቃስ በድንግልና የኖረ ሐዋርያ ነው፡፡ በግሪክ ብዙ ሐዋርያዊ አገልግሎት ፈጽሟል፡፡ ያረፈውም በቆስጠንጢኖስ 2ኛ ዘመን በ84 ዓመቱ በሰማዕትነት ነው፡፡ ቅዱስ አጽሙ በ357 ወደ ቁስጥንጥንያ የፈለሰ ሲሆን ከቁስጥንጥንያ ወደ ጣልያን ፑዳ በ1177 ዓ.ም በድጋሚ ፈልሷል፡፡

ስለ እረፍቱም ጥቅምት 22 ቀን የሚነበበው ስንክሳር እንዲህ ይተርካል:: ቅዱሳን ጴጥሮስና ጳውሎስ ከተገደሉ በኋላ በሮም ሀገር የሚያስተምር ሆነ በቀናች ሃይማኖትም ይጸኑ ዘንድ ለምእመናን መልእክትን ይጽፍ ነበር ስለዚህም ጣዖት አምላኪዎች ከአይሁድ ጋር በመስማማት በአንድ ምክር ተስማሙ በንጉሥ ኔሮን ፊት ቆመው ስለ ሐዋርያው ሉቃስ እንዲህ ብለው ጮሁ ይህ ሉቃስ በሥራይ ብዙ ሰዎችን ወደ ትምህርቱ አስገባቸው አሉ፡፡ ንጉሥ ኔሮንም ወደ ፍርድ አደባባይ ሉቃስን እንዲያቀርቡት አዘዘ ሐዋርያው ሉቃስም ከዚህ ዓለም መውጫው እንደ ደረሰ በመንፈስ ቅዱስ አውቆ ወደ ባሕር ዳርቻ ሔደ በዚያም ዓሣ የሚያጠምድ አንድ ሽማግሌ ሰው አገኘ መጻሕፍቱንና ደብዳቤዎችን ሰጠው ወደ እግዚአብሔር መንገድ መርተው ያደርሱሀልና እሊህን መጻሕፍት ጠብቃቸው አለው፡፡ በንጉሥ ኔሮን ፊትም ቀርቦ በቆመ ጊዜ ንጉሡ በሥራይህ ሕዝቡን የምታስት እስከ መቼ ነው አለው ቅዱስ ሉቃም እኔ ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ነኝ እንጂ ሥራየኛ አይደለሁም ብሎ መለሰለት ንጉሥ ኔሮንም ሁለተኛ እንዲህ አለው እየጻፈች ሰዎችን የምታስት ይህች እጅህን እኔ እቆርጣታለሁ ይህንንም ብሎ የቀኝ እጁን እንዲቆርጡት አዘዘ፡፡ በቆረጡትም ጊዜ ንጉሥ ሆይ እኛ የዚህን ዓለም ሞት እንደማንፈራ ዕወቅ ነገር ግን የጌታዬና የፈጣሪዬን ኃይሉን ታውቅ ዘንድ አሳይሃለሁ ይህንንም ብሎ የተቆረጠች የቀኝ እጁን በግራ እጁ አንስቶ ከተቆረጠችበት ቦታዋ ላይ አገናኝቶ እንደ ቀድሞዋ ደኅነኛ አደረጋት ከዚህም በኃላ ለያት በዚያም የነበሩ አደነቁ የሠራዊቱም አለቃና ሚስቱ ብዙዎችም ሰዎች ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ቁጥራቸውም አራት መቶ ሰባ ሰባት ነፍስ ሆነ፡፡ ንጉሡም ከቅዱስ ሉቃስ ጋር ራሶቻቸውን እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጡአቸው የምስክርነት አ
ክሊልም በመንግስተ ሰማያት ተቀበሉ ከዚህም በኋላ የቅዱስ ሉቃስን ሥጋ በማቅ አይበት ውስጥ አድርገው ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ አንድ ደሴት ደረሰ ምእመናንም አግኝተው ወስደው ገነዙት በአማረ ቦታም አኖሩት ለእግዚአብሔር ምስጋነና ይሁን እኛንም በዚህ ሐዋርያ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን፡፡

ሰላም ለሉቃስ እንተ ረትዐ ልሳኑ ወንጌለ መለኮት ይጽሐፍ እምእለ ብዙኃን ወጠኑ፡፡ ከመ ያርኢ ኀይለ ቅድመ ኔሮን ወተዐይኑ አስተላጸቃ ወሌለያ የማኑ ለምትርት እስመ ላዕሌሁ ተሠውጠ ለክርስቶስ ሥልጣኑ፡፡

መስቀል ማለት ምን ማለት ነው?


መስቀል ማለት ምን ማለት ነው?
በዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ2008 ዓ.ም.
ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና በቃል መነገሩ፣ በኅሊና መዘከሩ፣ በሰው ልብ መታሰቡ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት መዘገቡ ከፍ ይበልና፣ ጌታችንንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ ልጆቹ ፈቃዱን እያደረግን እንድንኖርና እርሱም ከመልካም ምግባራችንና ከበጎ ትሩፋታችን ብቻ የተነሳ ፍጹማን እንደማንሆን ያውቃልና፣ ከማያልቅ ልግስናው ከማይጓደል ምሕረቱ ዘመናትን እየመጸወተን ደስ የሚሰኝበትን ለእኛ እያደረገ በቸርነቱ ያኖረናል:: ከእርሱና ከዓላማው ጋር ጸንተን እንድንኖርም እንዲህ ሲል በቅዱስ ወንጌል አዝዞናል:: “ዘይፈቅድ ይትልወኒ ይጽላዕ ነፍሶ ያጥብዕ ወይንሳዕ መስቀለ ሞቱ ወይትልወኒ (እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ) ወምንተ ይበቁዖ ለሰብእ ለእመ ኩሎ ዓለመ ረብሐ ወነፍሶ ኃጉለ (ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?)” (ማቴ. 16:24-26)።
ጥንቱንም ቢሆን እኛ የተፈጠርነው በሕይወት እንድንኖር ነው። ትንሳኤና ሕይወት ክርስቶስ ግን የተወለደው ስለኛ እንዲሞት ነው:: በዚህም ሁላችን ለእርሱ እንድንኖር እርሱ ስለ ሁላችን ሞተ "በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። "(1ቆሮ፣ 5:15)። ይህ ግን መስቀል የገደለው ያይደለ ይልቁንም በመስቀሉ ሞትን ገደለበት እንጂ:: "በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።" (ፊል. 2:8) እንዲል::
ሊከተለኝ የሚወድ ነፍሱን ይጥላ አለ፣ ይህም ነፍሱንና ሥጋውን የሚለይ መከራ ለመቀበል ይጨክን ሲል ነው። ሰውስ ለክርስትና ፍኖቱ ለነፍሱ ሥምረት እያደረ የሥጋውን ፈቃድ እየገፋና እየጠላ ሊኖር ይገባዋል። ለዚህም ጌታችን ተከታዩን ሃሳብ እንዲህ ሲል አስፍሮታል "ወምንተ ይበቁዖ ለሰብእ ለእመ ኩሎ ዓለመ ረብሐ ወነፍሶ ኃጉለ፤ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?" መከተሉም ቢሆን ሌጣውን ያይደለ የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይለናል::
መስቀል ምንድር ነው ?
መስቀል በቀደመው ዘመን ለኃጢአተኞች እግዚአብሔርን ለበደሉ መቅጫ የነበረ "በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና" (ዘዳ፣21:23)። ነገር ግን በአዲስ ኪዳን ለክርስቲያኖች ኃይል፣ ጽንዕ፣ ቤዛና መድኃኒተ ነፍስ ሆኖ የሚያገለግል አርማ ነው:: ወደዚህ ክብር እንዴት ሊሻገር እንደቻለ ሊያስረዱ የሚችሉ በመስቀሉ ከተፈጸሙ ድንቅ መንክራት እፁብ ተዓምራት መካከል ተከታዮቹን ሦስት ዓበይት ነጥቦች እንደእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ እንመለከታለን::
+ ጠላት የራቀበት ነው።
መስቀል የቀደመው እባብ የዲያቢሎስ ራስ የተቀጠቀጠበት እኛም ድል መንሳትን በግልጥ ያየንበት እጸ መድኃኒት ነው:: "በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ (በመስቀል) እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው።" (ቆላ፣ 2:14) እንዲል።
+ እኛ የቀረብንበት ነው።
ተመልከቱ ራሱን ወደኛ ያቀረበበት ነው አላልንም "አመ ተለአልኩ እምድር እስህብ ኩሎ ኃቤየ፤ እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።" (ዮሐ፣12:32) እንዳለ እኛን ወደራሱ አቀረበበት፣ ምክንያቱም ሰው በድሎ ራቀው እንጂ እርሱ ከሰው የተለየበት ጊዜ አልነበረምና። "እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም።" (ኤር፣23:23) እንዳለን። ይበልጡንም ለተዛምዶ ረቂቅ ቅርበቱ ያይደለ ሥጋችንን ነስቶ አማኑኤል ተሰኝቷል። "እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ።" ይህም በኩነት ታዲያ ዓላማው ወደእኛ መቅረብ ብቻ ቢሆን ይህ ልደቱ በበቃው ነበር። መስቀሉ ግን ወደኛ መምጣቱን ባንቀበል ወደራሱ ሊወስደን ወደ ሰማይ ቤታችን ሊስበን በቀራንዮ ተተከለ። ለዚህም ሊቁ ማር ኤፍሬም "አቅረበነ ኃቤሁ ዘዚአነ ሞተ ነሳ ወእንቲአሁ ሕይወተ ወኃበነ- ወደራሱ አቀረበን የእኛን ሞት ወስዶ የእርሱን ሕይወት ለእኛ ሰጠን" ሲል መነሻችንን ያስረዋል።
+ የጥል ግድግዳ የፈረሰበት
ሰው የሞትን እጽ ቆርጦ ቢበላ አምላኩን በደለ። በዚህም የጸብ ግድግዳ ተተከለ። ሰው ከአምላኩ ተለየ ልዑለ ቃል ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ "ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል።" (ኢሳ፣59:2) ሲል እንደገለጸው፣ ታዲያ ከህገ ልቡና ወደ ህገ ኦሪት መሻገሩ ፍጻሜ ያለው ድኅነት ሊያመጣ ባለመቻሉ የሚበልጥና የሚሻል አዲስ ኪዳን የሚሰጥበት አዲስ መስዋዕት የሚሰዋበት አዲስ ድንኳን አስፈለገ (ዕብ፣ 9:11)። ለዚህም የአዲስ ኪዳን ሥርዓት ክቡር ደሙ የፈሰሰበት የሕይወት ህብስት ቅዱስ ሥጋው የተቆረሰበት ዐረፍተ ማእከል የተናደበት እጸ መድኃኒት ቅዱስ መስቀሉ ተሰጠን። "እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።" (ኤፌ፣ 2:15)።
እንግዲህ በጠቅላላው መስቀል የምንለው፣ በቁሙ ከቤተክርስቲያን ጉልላት እስከ ምዕመናን ንቅሳት የሚታይ የድል ምልክት፣ በሰሌዳ ተስሎ በጣት ተመሳቅሎ የሚገኝ የድኅነት አርማ፣ ካህናት በእጃቸው ይዘው የሚፈቱበት፣ ክርስቲያኖች በአንገታቸው አስረው ማንነታቸውን የሚመሰክሩበት መገለጫ ሲሆን. በሌላ አገባብ መከራ የተጋድሎ ፍኖት ማለት ነው።
እግዚአብሔር ወልድ ክርስቶስ ስለሁላችን መዳን መከራን ተቀብሎልናል። እናስተውል፣ እያንዳንዳችን በመዳን ኑሮ ሐሳባችን፣ እቅድ ምኞታችን በመከራው ልንካፈለው፣ በሞቱ ልንመስለው ፈለጋውን ልንከተለው ይገባናል።
"ስለዚህ ኢየሱስ ደግሞ በገዛ ደሙ ሕዝቡን እንዲቀድስ ከበር ውጭ መከራን ተቀበለ። "(ዕብ፣13:12) እንደተባለ፤ ከበር ውጪ አለ በቀራንዮ ኮረብታ የራስ ቅል በተባለ ጎልጎታ ሊቀድሰን ተሰቀለ። እኛ ክርስቶስ በደረሰበት መከራ ከድቅድቁ ጨለማ ድንቁርና ወደሚደነቀው ብርሃን እውቀት የተሻገርነው፣ ስለ አዳም በደል መከሰስን ጥለን ስለራሳችን ጽድቅ መከራን በመቀበል እንድንከተለው ነው:: ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ "የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። "(1ኛ፣ጴጥ.2:21) ሲል እንዳስረዳን። በዚህም ኅሩይ ነዋይ ቅዱስ ጳውሎስ "እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ። "(ፊል.3:10-11)። ሲል ምኞቱን አስረዳን ምን ይጠቅማል? የሚል ቢኖር ልሳነ ዕፍረት እንዲህ ያስረዳዋል "ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን።" (ሮሜ. 6:5)።
ሁሉ የራሱ መስቀል አለው ሸክሙን የሚሸከምበት
"ለሁሉም እንዲህ አላቸው፦ በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ።" (ሉቃ፣9:23)
ሁሉ የራሱን ሸክም ይሸከማልና
"ወኩሉ ያመክር ምግባሮ (ሁሉ ሥራውን ይመርምር ለሌላው ሳይሆን ለራሱ የሚመካበትን) እስመ ኩሉ ፆሮ ይፀውር (እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና)" (ገላ6:5) እንዲል።ስለዚህ የምንሸከመው መስቀላችን የምንሰቀልበት ሳይሆን ሸክማችንን የምንሰቅልበት ነው::"የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ።" (ገላ፣ 5:24) እንደተባለ።
እስኪ አእምሮአችንን ከመባከን ሰብስበን ነፍሳችንን የሚያሳርፍ አንድ ታሪክ እናንብብ
"እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና። ቸር መምህር ሆይ፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው።ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አታታልል፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው።እርሱም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለው።ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና። አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፥ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መስቀሉንም ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ አለው።ነገር ግን ስለዚህ ነገር ፊቱ ጠቈረ፥ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነም ሄደ።" (ማር 10:17)። አይገርማችሁም በምድራችን ላይ ገንዘብን መውደድ የከበደ ሸክም እየሆነባቸው "ገፋኤ-ነዳይ መፍቀሬ- ነዋይ" መጠርያቸው የሆኑ ብዙዎች አሉ:: ፍቅረ ነዋይ (ገንዘብን መውደድ) ለኃጢዓት ሥርና ራስ ነው ...... ጌታችን ተርቦ ሳይሳሳ፣ ተፈትኖ ድል ሳይሆን፣ ለሁላችን አርአያ በሆነበት ገዳመ ቆሮንቶስ ጠላታችንን ድል ከነሳባቸው መንገዶች አንዱ ፍቅረ ነዋይን በጸሊዓ ነዋይ ነበር። ይህም ፍቅረ ነዋይ ርዕሰ-ኃጣውእ ከስስትና ከትዕቢት ጋር አርዕስተ ኃጥውእ እየተባለ ይጠራል። ይሁንና ግን ከአስራ ሁለቱ አንዱ በሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ ልብ ገብቶ ተሳካለት። በዚህ ሥፍራ ደግም የኃጢዓት ሥር ተብሎ ተጠራ "ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።" (1ኛ.ጢሞ.6:10) እንዲል። እንግዲህ ይህን የመሰለው ኃጢዓት ሁሉ ክቡድ ሸክም ይባላል። የምሕረት አምላክ ግን በፍቅር ልሳን እንዲህ እያለ ይጠራናል "እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።" (ማቴ.11:28-30)።
ቀሊል የሆነውን የእርሱን ሸክም እንሸከም ዘንድ እሱ የኛን ክቡድ ሸክም በመስቀል ላይ ተሸከመ:: እንግዲህ ተመልከቱ በዚህ መንገድ እኛም ሕይወታችንን እንድንሰጠው ሕይወቱን ሰጠን ለምን? የሚል ቢኖር እርሱ የብዙዎችን ኃጢዓት በእንጨት ላይ የተሸከመው ብዙዎች የእርሱን ሕይወት በዘመናቸው እንዲሸከሙ ነውና:: ነቢዩ አስቀድሞ በትንቢት እንዲህ እንዳለ "ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።" (ኢሳ 53:12) ሊቀሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም የቃሉን መፈስጸም እንዲህ ሲል እንዳስረዳ "ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤" (1ኛ.ጴጥ፣2:24)።
መከራን መቀበል (መስቀላችንን መሸከም)
+ ኃጢዓትን (አርእስተ ኃጣውእ) ያስተዋል።
"በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቶአልና።" (1ጴጥ፣ 4:2)።
+ ወደ እግዚአብሔር ያስገባል።
"ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል" (ሐዋ 14:22) እንደተባለ ለብዙዎች ዘለፋ የሆነው ይህ የቅዱሳን ሐዋርያት ምስክርነት "በጸጋ ድነናል" እያሉ ባልተገባ ፍካሬ ቃሉን እየጠቃቀሱ፤ ለመብልና መጠጥ ይህን ለመሰለው የሥጋ ፈቃድ ራሳቸውን ለሚያስገዙ ጅራፍ ይሆንባቸዋል፤ ምክንያቱም "የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና።" (ሮሜ.14:17) ይለናልና::
ማጠቃለያ
ቅዱስ አባታችን ብጹዕ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ በአንድ መጽሐፋቸው "ፈተና ያለው ትምህርት ቤት አይደለም፣ ይልቁንም ትምህርት ቤት ያለው በፈተና ውስጥ ነው" ብለዋል። እኛም እንዲህ እንላለን "ሕይወት በመከራ የተሞላ ነው ለሚል፣ የለም ለክርስቲያንስ መከራ በህይወት የተመላ ነው እንጂ"፤ ሊቁ "መከራ ኢርኅቀ እምርዕሰ ጻድቃን ወርዕሰ ጻድቃን ኢርኅቀ እምነ መከራ ግሩም." ሲል ቅኔውን ይጀምራል። የማይጠፋ ስምና የሕይወትን አክሊል ገንዘብ ሊያደርጉ ሲሹ መከራ አይርቃቸውም። ቢርቃቸውም እንኳ እነርሱ ከመከራ መች ይርቁና። መክበርያቸውን ሽተው ራሳቸው ላይ ተጋድሎ ያጸናሉ ሌላውም ሊቅ የጸናውን ሰማዕት ተመለከተና "ኦ ጊዮርጊስ ስቃየ ኮንከ ለሥቃይከ" ሲል አደነቀ እንዴት ባለ መከራ እንዲገድሉት ይጨንቃቸው የነበሩ አላውያን ቢፈጩት፣ ቢያቃጥሉት፣ አመድ አድርገው ቢበትኑት "እነሆኝ የክርስቶስ ባርያ" እያለ ሞትን ድል ቢነሳና ከመካከላቸው ቢገኝ ለስቃዩ ስቃይ ሆነበት ወይግሩም! ታዲያ የቀደሙ ምስክሮች ሕይወት ይህ ከነበረ የእኛ ተጋድሎ ወዴት ይሆን? "ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው?" (1ኛ.ጴጥ.4:18)።
እንግዲህ በሁሉ እናመስግን በፈተናችን ዋጋ በመከራችን ጸጋ እንድንቀበል እያሰብን ይህን እንጸልይ "ኦ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ አአኩተከ በእንተ ኩሉ ግብር ዘአምጻእከ ላዕሌየ እመሂ ረኃበ አው ጽጋበ እመሂ ጥኢና አው ደዌ እመሂ ፍሰሐ አው ኃዘነ...ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በእኔ ላይ ስላመጣህብኝ ነገር ሁሉ አመሰግናለሁ ረሃብ ቢሆን፣ ጥጋብ ጤንነት ቢሆን፣ ደዌ ደስታም ቢሆን ኃዘን"( ሰይፈ ሥላሴ ዘሐሙስ)።
መስቀሉን የሚሸከም ምረረ ገኃነምን ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን እየተዘከረ በመከራው ይደሰታል እንጂ አይማረርም። የጌታችን ወንድም የተሰኘ ራሱን የክርስቶስ ባርያ እያለ የጠራ ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ የመጀመርያ ምዕራፍ ቁጥር 2 እና 3 ላይ "ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት" ይለናል እኛም ከሐዋርያው ጋር እንዲህ እንላለን "ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ።" (ሮሜ፣ 8:18)።
+++ ከፍኖተ መስቀሉ ከህያው ቅዱስ ቃሉ በረከት ይክፈለን። +++