Sunday, 3 April 2016

sibikettt

 

«ከዚህም በላይ የምታወጣውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ፤»
          ዲናር፦ የሮሜ መንግሥት የብር ምንዛሪ ሆኖ ያገለገለ ከሁሉ ያነሰ የናስ ሳንቲም ነው ፥ መጠኑም አሥራ ስድስት ሳንቲሞች ነበር። በዚያን ዘመን የአንድ ቀን የሠራተኛ ደሞዝ ሆኖ ይከፈል ነበር። ማቴ ፳፥፪። ጌታችንን በንግግር ሊያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑ ሰዎች ወደ እርሱ ተልከው መጥተው «ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ፥ ወይስ አልተፈቀደም? እንስጥን፥ ወይስ አንስጥ?» በማለት ጠይቀውት ነበር። እርሱ ግን ግብዝነታቸውን እና ተንኰላቸውን አውቆ፦ «ለምን ትፈትኑኛላችሁ? አንድ ዲናር አምጥታችሁ አሳዩኝ፤» አላቸው። ባመጡለትም ጊዜ፦ «ይህ፦ መልኩ ጽሕፈቱስ የማን ነው? » አላቸው፤ እነርሱም፦ «የቄሣር ነው፤» አሉት። እርሱም መልሶ፦ «የቄሣርን ለቄሣር ስጡ፤ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አድርጉ፤» አላቸው። ምክንያቱም፦ የንጉሥ የሆነ እንደሆነ፦ ስመ ንጉሥ ይጻፍበታል ፥ ሥእለ አንበሳ ይቀረጽበታል፤ የእግዚአብሔር ሲሆን ደግሞ፦ ስመ አምላክ ይጻፍበታል፥ ሥዕለ ኪሩብ ይቀረጽበታል።
፩፥፩፦ «የዘለዓለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?»
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፦ ደቀመዛሙርቱን ለብቻቸው አድርጎ «እናንተ የምታዩትን የሚያዩ ዓይኖች ብፁዓን ናቸው። ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ተመኙ ፥ አላዩምም፤ እናንተ የምተሰሙትንም ሊሰሙ ተመኙ ፥ አልሰሙም።» ካላቸው በኋላ እንደ ሕግ አዋቂ (ሕገ ኦሪትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው) ወደ እርሱ መጣ። ሊፈትነውም፦ «መምህር ሆይ ፥ የዘለዓለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? (የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያትን የምወርሰው ምን ሠርቼ ነው?) አለው። ጌታችንም፦ «በሕግ የተጻፈው ምንድርነው? እንዴትስ ታነባለህ?» በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መልሶለታል። ሕግ አዋቂውም ከኦሪት ዘዳግም ጠቅሶ፦ «እስራኤል ሆይ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ (አሳብህ) ፥ በፍጹም ነፍስህ (ሰውነትህ) ፥ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ። ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ፤» ይላል ፥ ሲል መለሰለት። ዘዳ ፮፥፭። በዚህን ጊዜ ጌታችን፦ «እውነት መለስህ፤ ይህን አድርግ፥ በሕይወትም ትኖራለህ፤» በማለት አዘዘው።
          ይህ ሰው የዕውቀት ባዕለጸጋ የተግባር ደሀ ነው፤ እንዲሁ በዕውቀቱ እየተመጻደቀ የሚኖር ሰው ነው፤ አመጣጡም ውዳሴ ከንቱን ሽቶ እንጂ ሕይወትን ፈልጎ አይደለም። ጌታ ሊቅነቴን ይመሰክርልኛል ብሎ ነው፤ በዚህም እርሱን በተከተለው አምስት ገበያ ሕዝብ ፊት ሞገስን ለማግኘት ነው። ዛሬም አገልግሎታቸው ሁሉ ሊቅ ለመባል ብቻ የሆነባቸው ሰዎች አሉ፤ እነዚህም መንፈሳዊ ዕውቀት እንጂ መንፈሳዊ ሕይወት ፈጽሞ የማይገኝባቸው ናቸው፤ ከዚህም የተነሣ ገንዘብ አድርገው የሚኖሩት፦ሰውን መናቅና እግዚአብሔርን መድፈር ነው። አንደበታቸው ስለ ሕይወት ይናገራል ፥ ይተረጉማል ፥ ያዜማል፥ ይቀኛል ፥ ልባቸው ግን በትዕቢት፣ በግብዝነት የተያዘ ፍጹም ሥጋዊ ነው። ይኽንን በተመለከተ፦ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፦ «አንተ ግን አይሁዳዊ ብትባል ፥በሕግም ብትደገፍ ፥ በእግዚአብሔርም ብትመካ ፥ ፈቃዱንም ብታውቅ ፥ ከሕግም ተምረህ የሚሻለውን ፈትነህ ብትወድ ፥ በሕግም የዕውቀትና የእውነት መልክ ስላለህ ፥ የዕውሮች መሪ ፥ በጨለማም ላሉ ብርሃን ፥ የሰነፎችም አስተማሪ ፥ የሕፃናትም መምህር እንደሆንህ በራስህ ብትታመን ፥ እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን? በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን? በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደ ተጻፈ።» ብሏል። ሮሜ ፪፥፲፯-፳፬።
፩፥፪፦ «ባልንጀራዬ ማነው?
          መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ዕውቀት በትህትና የሚያገለግሉበት እንጂ የሚመኩበት ፥ የሚመጻደቁበት አይደለም። እነ አርዮስ ፥ እነ ንስጥሮስ በመንፈሳዊ ዕውቀታቸው ሲፈላሰፉ ፥ ሲመጻደቁ ጠፉበት እንጂ አልዳኑበትም። ሥጋዊውም የዕውቀት ሰው ከተራ ጠመንጃ እስከ ኒዩክለር ድረስ የሠራው ፥ የፈለሰፈው ረቂቅ መሣሪያ መጥፊያው እንጂ መዳኛው አይደለም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ ፥ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ፥ ተብሎ ተጽፎአልና። ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚህችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች ፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና።» ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ቆሮ ፩፥፲፱-፳፩። 
          የሕገ ኦሪቱ ሊቅ፦ ምን ማድረግ እንዳለበት ፥ መጽድቂያውን ፥ ጌታችን በነገረው ጊዜ፦ እርሱ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ፦ «ባልንጀራዬ ማን ነው?» አለ። «የሚመስለኝ ፥ የሚተካከለኝ ማነው?» ማለቱ ነው። ራሱን ከጉልላቱ ላይ ያስቀመጠ ሰው በመሆኑ የትዕቢት ንግግር ነው። ትዕቢት ደግሞ ዲያቢሎስ የተያዘበት አሸክላ ነው ፤ ኢሳ ፲፬፥፲፪። ቅዱስ ያዕቆብ እንደተናገረው፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ያዕ ፬፥፮። ጠቢቡ ሰሎሞንም፦ «ሰውን ትዕቢቱ ያዋርደዋል፤» ብሏል። ምሳ ፳፱፥፳፫።
፩፥፫፦ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ፤
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በሊቅነቱ ብቻ ተመክቶና ተመጻድቆ፦ «ባልንጀራዬ ማነው?» ያለውን ሰው ያስተማረው በምሳሌ ነው። ምሳሌውም፦ «አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ይወርድ ነበር፤ ሽፍቶችም አገኙት፤ ደበደቡት ፥ አቈሰሉት ፥ልብሱንም ገፍፈው በሕይወትና በሞት መካከል ጥለውት ሄዱ። አንድ ካህንም በዚያች መንገድ ሲወርድ ድንገት አገኘው፤ አይቶም አልፎት ሄደ። እንዲሁም አንድ ሌዋዊ በዚያ ቦታ አገኘውና አይቶ እንደፊተኛው አልፎት ሄደ። አንድ ሳምራዊ ግን በዚያች መንገድ ሲሄድ አገኘው፤ አይቶም አዘነለት። ወደ እርሱም ቀረበ፤ ቊስሉንም አጋጥሞ አሰረለት፤ በቊስሉ ላይም ወይንና ዘይት ጨመረለት፤ በአህያውም ላይ አስቀምጦ እንዲፈውሰው የእንግዶችን ቤት ወደ ሚጠብቀው ወሰደው፤ የሚድንበትንም ዐሰበ፤ በማግስቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዳ ቤት ጠባቂው ሰጠውና፦ በዚህ አስታምልኝ፤ ከዚህ የሚበልጥ ለእርሱ የምታወጣው ቢኖር እኔ በተመለስሁ ጊዜ እከፍልሃለሁ፥ አለው። እንግዲህ ሽፍቶች ለደበደቡት ሰው ከእነዚህ ከሦስቱ ባልንጀራ የሚሆነው ማንኛው ይመስልሃል? ሲል ጠየቀው ፤ እርሱም፦ ምሕረት ያደረገለት ነዋ አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም፦ እንኪያስ አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ አለው።»የሚል ነው። ሉቃ ፲፩፥፳፱-፴፯።
          ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ መውረድ ማለት፦ ከፍ ካለ ሥፍራ ወደ ዝቅተኛው ሥፍራ መውረድ ማለት ነው። ትርጉሙም፦ ከብሮ መዋረድን ፥ተሹሞ መሻርን ፥አግኝቶ ማጣትን ያመለክታል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፦ «ገዢዎችን ከዙፋናቸው አዋርዷል፤ . . .  ባለጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል፤» ያላችው እንዲህ ዓይነቱን ነው። ሉቃ ፩፥፶፪ ፣ መዝ ፻፵፮፥፮።
፩፥፬፦ ኢያሪኮ፤
          ኢያሪኮ፦ ከጨው ባሕር በስተሰሜን አሥራ አምስት ኪ.ሜ. ፥ ከኢየሩሳሌም ደግሞ ሃያ አምስት ኪሜ ርቆ የሚገኝ ከተማ ነው። ኢያሪኮ ማለት፦ የጨረቃ ከተማ ማለት ነው፥ ይኸውም በኢያሪኮ የኖሩ የጥንት ሰዎች ጨረቃን ስላመለኩ ነው። በኢያሪኮ ዙሪያ ብዙ የውኃ ምንጮች ስላሉ ከጥንት ጀምሮ ሰዎች በዚያ መኖር ጀምረዋል። ዘዳ ፴፬፥፫። የፊተኛዋን ከተማ በታቦቱ ላይ በተገለጠ ኃይለ እግዚአብሔር ኢያሱ ወልደ  ነዌ አፍርሶታል። ኢያ ፮፥፩። አኪኤል የተባለው የቤቴል ሰው ደግሞ እንደገና ሠርቶታል። ፩ኛ ነገ ፲፮፥፴፬። በኢያሪኮ ብዙ የኦሪት ካህናት ነበሩ፤ ሉቃ ፲፥፴፩። በአዲስ ኪዳን ጌታችን የበርጤሜዎስን ዓይን ያበራው በኢያሪኮ ነው፤ ማር ፲፥፵፮። ዘኬዎስንም የጎበኘው በዚሁ ከተማ ነው። ሉቃ ፲፱፥፩። ይህንን ከተማ ሮማውያን በ67 ዓ.ም. አፍርሰውታል። ኢያሪኮ ሁለት መቶ ሃምሣ ሜትር ከባሕሩ ጠለል ዝቅ ስለሚል ከዓለም ከተሞች ሁሉ ዝቅተኛ ነው።
፩፥፭፦ ኢየሩሳሌም
          ኢየሩሳሌም፦ ማለት፦ የሰላም ከተማ ማለት ነው፤ የዮርዳኖስ ወንዝ ወደ ጨው ባሕር ከሚገባበት በምዕራብ ሠላሳ ኪ.ሜ.፥ ከታላቁ ባሕር ደግሞ ሃምሣ ኪ.ሜ. ርቃ በተራራማ ሀገር የምትገኝ ከተማ ናት። ከባሕር ወለልም ሰባት መቶ ሃምሣ ሜትር ገደማ ከፍ ትላለች። ጥንታዊ ስሟ ሳሌም ነበር፥ ቀጥሎም፦ ኢያቡስ ፣ ፆፌል ፣ ጽዮን ተብላለች፤ ዘፍ ፲፬፥፲፰ ፣ ኢያ ፲፭፥፷፫ ፤ ፲፰፥፲፮፤ ፪ኛ ዜና ፳፯፥፫፤ ፴፫፥፲፬፤ መዝ ፻፴፮፥፩። ቅድስት ከተማ ተብላም ተጠርታለች፤ ነህ ፲፩፥፩። ንጉሥ ዳዊት ኢየሩሳሌምን ከኢያቡሳውያን ከወሰዳት በኋላ የእስራኤል ሁሉ በተለይም የይሁዳ ዋና ከተማና መስገጃ አደረጋት ፤ ፪ኛ ሳሙ ፭፥፮-፲።
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። ወራት ይመጣብሻልና ፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ፥ ይከቡሻልም ፥ በየበኲሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽኝ ወደ ታች ይጥላሉ ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም ፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።» እያለ አልቅሶላታል። ሉቃ ፲፱፥፵፮። የዓለምን መጨረሻ ምልክቶች በተናገረበት አንቀጽም፦ «ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።» በማለት ተናግሯል። ሉቃ ፳፩፥፳። ሥጋውን በመቁረስ፥ ደሙን በማፍሰስ፥ ነፍሱንም አሳልፎ በመስጠት ድኅነተ ዓለምን የፈጸመው በዚያ ነው። ይኽንንም ነቢዩ ዳዊት፦ «እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ።» በማለት ተናግሯል። መዝ ፸፫፥፲፪። ነቢዩ ዳዊት ማዕከለ ምድር ያለው ኢየሩሳሌምን ነው። «ኢየሩሳሌም ሆይ ፥ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ። ባላስብሽ፥ ምላሴ በጉሮሮዬ ይጣበቅ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ።» ያለበት ጊዜም አለ። መዝ ፻፴፮፥፭።
          ኢየሩሳሌም፦ ሕገ ኦሪትም ሕገ ወንጌልም የሚሠራባት ፥ ድኅነተ ምእመናንም የሚፈጸምባት በመሆኗ ነቢያት ሁሉ ትንቢት የተናገሩት ለርሷ በርሷ ነው። ቅዱሳን ሐዋርያትም የሰበኩት ለርሷ በርሷ ነው። ኢየሩሳሌም የትንቢት መድረሻ፥የድኅነት መፈጸሚያና ፥ የስብከት መነሻ ከመሆኗም በላይ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያምና ለገነት ለመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናት።
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በወንጌል፦ ኢየሩሳሌምን፦ «የታላቁ ንጉሥ ከተማ ብሏታል።» ማቴ ፭፥፴፭። ይኸውም፥ ለጊዜው፦ ምድሪቱን ሲሆን ለፍጻሜው እመቤታችንን ፥ አንድም ገነት መንግሥተ ሰማያትን ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነፃነት የምትኖር ናት ፥ እርስዋም እናታችን ናት።» ብሏል። ገላ ፭፥፳፭። በዕብራውያን መልእክቱም ላይ፦ «ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል ፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም ፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት ፥ በሰማያትም ወደተጻፉ ወደ በኲራት ማኅበር ፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር ፥ ፍጹማንም ወደሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች ፥ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል፤» ብሏል። ዕብ ፲፪፥፳፪-፳፬። በራእይ ዮሐንስ ላይ ደግሞ፦ «ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ ፥ ወደፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬ ስምና የአምላኬ ከተማ ስም ፥ ማለት ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን ፥ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ፤» የሚል አለ። ራእ ፫፥፲፪። በተጨማሪም፦ «አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርንም አየሁ ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ፤» የሚል ተጽፏል። ራእ ፳፩፥፩-፪።   
፩፥፮፦ በወንበዴዎች እጅ መውደቅ፤
          ከፍ ብላ ከምትገኘው ከኢየሩሳሌም በጣም ዝቅተኛ ወደሆነው ሥፍራ ወደ ኢያሪኮ የወረደው ሰው የአዳም ምሳሌ ነው። ይኸውም ከልዕልና ወደ ትህትና መውረዱን፥ ከመታዘዝ ወደ አለመታዘዝ መጓዙን የሚያመለክት ነው። ወንበዴ የተባለው ደግሞ፦ ከማዕረጉ የተዋረደ ፥ ከሥልጣኑ የተሻረ ዲያቢሎስ ነው። የቀደመ ሰው አዳም፦ የነቢይነት ፥ የንጉሥነት ፥ የካህንነት ፥ የጸጋ አምላክነት(ገዢነት) መንፈሳዊ ሀብት ተስጥቶት በክብር ፣በልዕልና በገነት ይኖር ነበር። በዚህ ዓይነት በፍጹምነት ለሰባት ዓመታት ከኖረ በኋላ ወንበዴዎች የተባሉ አጋንንት አግኝተውት አስተው ልጅነቱን አስወስደውበታል። መርገመ ሥጋ ፥ መርገም ነፍስ ወድቆበት በነፍስም በሥጋም እንዲቆስል አድርገውታል። በዚህም በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ ፥ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ተጨምሮ እንዲፈረድበት ሆኗል። ልብስን እንደመገፈፍ ጸጋውን ሁሉ ተገፍፏል ፥ ከማዕረጉ ተዋርዶ፥ ከሥልጣኑ ተሽሮ ፥ ከገነት ተባርሮ ወደ ምድረ ፋይድ ተጥሏል።
፩፥፯፦ አንድ ካህን አይቶት ገለል ብሎ አለፈ፤
«መልከ ጼዴቅ፤»
          አንድ ካህን የተባለው መልከጼዲቅ ነው፤ መልከጼዴቅን ለክህነት መርጦ በማይመረመር ግብር የሾመው እግዚአብሔር ነው፤ እነ አሮን በተሾሙበት ሥርዓት፦ ተቀብቶ ፥ መሥዋዕት ተሠውቶ ፥ የከበረ ልብስ ለብሶ፥ የተሾመ አይደለም። ከሰው ወገን ከእገሌ ተቀብቶ የተሾመ ነው ፥ አይባልም፤ ከእርሱም በኋላ ሹመት ለእገሌ ተላልፏል አይባልም።
          የመልከ ጼዴቅ ክህነቱ በኖኅና በሴም ዘንድ ይታወቅ ነበር ፥ ይኸውም ምሥጢሩን እግዚአብሔር ስለገለጠላቸው ነው። ሴምም ከወገኖቹ ማንም ሳያውቅ ዓፅመ አዳምን ሊያስጠብቀው መልከ ጼዴቅን ወደ ጎልጎታ ይዞት ሄዷል። መልከ ጼዴቅም በእጁ ደም እንዳይፈስስ ተጠብቆ ፥ በንጹሕ ስንዴና ወይን በተዘጋጀ መሥዋዕት እያስታኰተ በብሕትውና ፣ በድንግልና ኖሯል። በታዘዘው መሠረት ፀጉሩን ተላጭቶ፥ ጥፍሩንም ተቆርጦ አያውቅም ፥ ኑሮውም በዓት አጽንቶ በዋሻ ነበር።
          መልአከ እግዚአብሔር እየረዳውም ከሰው ወገን ለማንም ሳይገለጥ እስከ አብርሃም ዘመን ቆይቷል። አብርሃም፦ አምላክ፦ ከእርሱ ወገን ሰው ሆኖ ከሚወለድበት ዘመን ደርሶ ለማየት ይፈልግ ነበር። እግዚአብሔር ግን «ከዚያ ዘመን አትደርስም ፥ ዮርዳኖስን ተሻግረህ ምሳሌዬን ታያለህ፤» ብሎታል። እንደተባለውም፦ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ፥ መልኬ ጼዴቅን አግኝቶ ፥ ከሁሉ አሥራት አውጥቶ ሰጥቶታል ፥ መልኬ ጼዴቅ ደግሞ ለሥጋ ወደሙ ምሳሌ የሆነውን ኅብስት በመሶበ ወርቅ ወይንኑም በጽዋ አድርጐ ሰጥቶታል። ዘፍ ፲፬፥፲፯። በዚህም ጌታን እንዳየ ተደርጎ ተቆጥሮለታል። ይኽንንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል፦ «አባታችሁ አብርሃም የእኔን ቀኔን ያይ ዘንድ ተመኘ፤ አይቶም ደስ አለው።» በማለት መስክሮለታል። ዮሐ ፰፥፶፮። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ፦ ለእግዚአብሔር ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ እንደኖረ በዝርዝር ጽፎለታል። ዕብ ፯፥፩-፫።
          እንግዲህ፦ ጌታችን በምሳሌው፦ በወንበዴዎች እጅ የቈሰለውን ሰው፦ «አንድ ካህን አይቶት ገለል ብሎ አለፈ፤» ማለቱ፦ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ የኖረው ፥ ካህኑ መልከጼዴቅ የሠዋው የስንዴና የወይን መሥዋዕት፦ ለቊስለኛው ለአዳም ምንም እንዳልጠቀመው ለመግለጥ ነው።
፩፥፰፦ አንድ ሌዋዊ አይቶት አለፈ፤
          ሌዊ፦ ከያዕቆብ አሥራ ሁለት ወንዶች ለጆች መካከል ሦስተኛው ነው። ዘፍ ፳፱፥፴፬። እኅቱን ዲናን ከአሕዘብ ወገን አንዱ ከክብር ባሳነሳት ጊዜ የሴኬምን ሰዎች ተበቅሏቸዋል፤ ይኽንንም ያደረገው ከወንድሙ ከስምዖን ጋር ነው። አባታቸው ያዕቆብ ግን፦ «በዚች ሀገር በሚኖሩ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ሰዎች የተጠላሁ ታደርጉኝ ዘንድ እኔን አስጨነቃችሁኝ፤ እኔ በቊጥር ጥቂት ነኝ፤ እነርሱ በእኔ ላይ ይሰበሰቡና ይመቱኛል። እኔም ከወገኔ ጋር እጠፋለሁ።» ብሎ አልተደሰተባቸውም። እነርሱም፦ «በጋለሞታ እንደሚደረግ በእኅታችን ያድርግባትን?» አሉ። ዘፍ ፴፬፥፩-፴፩።
          ያዕቆብ፦ በግብፅ ምድር በነበሩበት ጊዜ ፥ በኋለኛው ዘመን የሚያገኛቸውን ሁሉ ዘርዝሮ ለልጆቹ ነግሯቸዋል። ከዚህም መካከል፦ «ስምዖን እና ሌዊ ወንድማማቾች ናቸው ፤ ሰይፎቻቸው የዓመፃ መሣሪያ ናቸው። (ብዙ ደም አፍስሰዋል)። በምክራቸው ነፍሴ አትግባ፤ (ሰውነቴ በበረከት አትገናኛቸውም)፤ በቊጣቸው ሰውን ገድለዋልና፥ (ተቈጥተው የሴኬምን ሰዎች አጥፍተዋልና) ፥ በገዛ ፈቃዳቸውም የሀገርን ሥር ቈርጠዋልና። (ከአባታቸው አልተማከሩም ፥ ፈቃዱን አልጠየቁም)። ቊጣቸው ርጉም ይሁን፤ ጽኑ ነበርና፤ ኲርፍታቸውም ብርቱ ነበርና፤ በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ፤ በእስራኤልም እበትናቸዋለሁ።» የሚል አለ። ዘፍ ፵፱፥፭-፯።
          ሌዊ ከእስራኤል ነገዶች የአንዱ አባት ነው ፥ ሌዋውያን ይባላሉ፤ ዘፍ ፵፮፥፲፩። በሙሴ ዘመን የሌዊ ልጆች ፥ የሙሴን ትእዛዝ አክብረው፥ ፍቅረ ጣዖት ያደረባቸውን ሳይራሩ በማጥፋታቸው፦ «ዛሬ በረከትን እንዲያወርድላችሁ ከእናንተ እያንዳንዱ ከልጁና ፥ከወንድሙ የተነሣ እግዚአብሔርን ደስ አሰኛችሁት፤» ተብለዋል። ዘጸ ፪፥፩ ፤ ፮፥፲፮-፳፯። ክህነት የተሰጠው ለሌዊ ነገድ በመሆኑ አሮንና ልጆቹ ተቀብተው ተሹመዋል። ዘጸ ፳፰፥፩። ሌዋዊያን በጠቅላላ ለእግዚአብሔር አገልግሎት በመለየታቸውም ሥራቸውና አገልግሎታቸው በኦሪት ዘሌዋውያን ተገልጦአል። ሙሴ፦ ለመጨረሻ ጊዜ ሕዝቡን ሲባርክ ፥ ስለ ሌዊ፦ «ለሌዊ ቃሉን ፥ በመከራም ለፈተኑት ፥ በክርክር ውኃም ለሰደቡት ፥ ለእውነተኛው ሰው ጽድቁን መልስ። እናቱንና አባቱን አላየኋችሁም ላለ ፥ ወንድሞቹንም ላላወቀ ፥ ልጆቹንም ላላስተዋለ፤ ቃልህን ለጠበቀ ፥ በቃል ኪዳንህም ለተማጠነ። ፍርድህን ለያዕቆብ ፥ ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፤ በማዕጠንትህ ዕጣንን፥ በመሠዊያህም የሚቃጠል መሥዋዕትን ሁሌጊዜ ያቀርባሉ። አቤቱ ኃይሉን ባርክ፤ የእጁንም ሥራ ተቀበል፤ በሚቃወሙት ጠላቶቹ ላይ መከራን አውርድ፤ የሚጠሉትም አይነሡ፤» ብሏል። ዘዳ ፴፫፥፰-፲፩።
          ሌዋውያን በከነዓን የርስት ድርሻ ሳይሆን አርባ አምስት ከተሞች ተሰጥተዋቸዋል፤ እንደ ርስት ሆኖ የተሰጣቸው የእሥራኤል ልጆች የሚያወጡትን አሥራት ነበር። ይኽንንም ያደረገው እግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር አሮንን፦ «በምድራቸው ርስት አትወርስም፤ በመካከላቸውም ድርሻ አይሆንልህም፤ በእስራኤል ልጆች መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ፤ ለሌዊም ልጆች እነሆ፥ በምስክሩ ድንኳን አገልግሎት ስለሚያገለግሉ የእስራኤልን ልጆች ዐሥራት ርስት አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ።» ብሎታል። ዘኁ ፲፰፥፳-፳፩ ፣ ኢያ ፳፩፥፩-፵፭።
          ሌዋውያን ካህናት፦ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት አምስት ዓይነት መሥዋዕቶችን ሲያቀርቡ ኖረዋል። እነርሱም፦ የሚቃጠል መሥዋዕት ፥ የእህል ቊርባን ፥ የደኅንነት መሥዋዕት ፥ የኃጢአት መሥዋዕትና የበደል መሥዋዕት ናቸው። ዘሌዋውያን ከምዕራፍ ፩-፭። በዚህም ምክንያት፦ የአያሌ እንስሳት ደም ፈስሷል። እንግዲህ፦ «አንድ ሌዋዊ ወንበዴዎች ያቆሰሉትን ሰው አይቶት ገለል ብሎ አለፈ፤» ማለት፦ ሌዋውያን ካህናት ሲሠዉት የኖሩት መሥዋዕት ፥ የፈሰሰው ያ ሁሉ የእንስሳት ደም ወንበዴዎች የተባሉ አጋንንት በነፍስም በሥጋም ላቆሰሉት አዳም አልጠቀመውም ፥ አልረባውም ፥ አላዳነውም ፥ ማለት ነው። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፦ «የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና። . . .  መሥዋዕትንና መባን በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ስለኃጢአትም የሚሠዋ መሥዋዕትን አልወደድህም፥ በእርሱም ደስ አላለህም። . . . ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል።፤» ብሏል። ዕብ ፲፥፬-፲፩። በመሆኑም ከሊቀ ካህናቱ ከአሮን ጀምሮ እስከ ሊቀ ካህናት ሐና እና ቀያፋ ድረስ የተሠዋው መሥዋዕት ከአዳም ኃጢአት ዓለምን ማዳን አልቻለም። እነርሱ ራሳቸውም አልዳኑም።
፩፥፱፦ ደጉ ሳምራዊ፤
          ሳምራውያን፦ በሰማርያ የኖሩ ህዝብ ናቸው። ሰማርያ ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን ስድሣ አምስት ኪ.ሜ. ርቆ የሚገኝ ከተማ ነው። የእስራኤል ንጉሥ ዘንበሪ ተራራውን ገዝቶ ከተማ ሠርቶበት መናገሻም መስገጃም አድርጎታል። ፩ኛ ነገ ፲፮፥፳፬-፴፪። የሰሜኑ መንግሥት አንዳንድ ጊዜ ሰማርያ እየተባለ ይጠራ ነበር። ፩ኛ ነገ ፲፫፥፴፪ ፣ አሞ ፫፥፱። በአዲስ ኪዳን ዘመን በገሊላና በይሁዳ መካከል ያለው ሀገር ሰማርያ ይባል ነበር። ዮሐ ፬፥፬ ፣ የሐዋ ፩፥፰
          የአሦር ነገሥታት ስልምናሶርና ሳርጎን ሰማርያን ከያዙ በኋላ ዋና ዋና የተባሉ ሰዎችን ማርከው ወስደው ነበር። በእነርሱም ምትክ ብዙ ሰዎችን ከልዩ ልዩ አገር አምጥተው አስፍረዋል። እንዲህም ማድረጋቸው ለሃይማኖትና ለሀገር የሚቆረቆር ሰው እንዳይኖር ነው። ቀስ በቀስ በመጀመሪያ፦ ሥርዓታቸውን ፣ ባሕላቸውን ፣ ታሪካቸውን ፥ ቀጥሎም ሃይማኖታቸውን ለማጥፋት ነው። የመጡትም ሰዎች ከአይሁድ ጋር እየተጋቡ ተዋለዱ። በሂደትም ፈሪሃ እግዚአብሔር እየጠፋ፥ የድፍረት ኃጢአት እየሰፋ ሄደ። በዚህም ምክንያት የአንበሳ መንጋ ታዘዘባቸው ፥ እነርሱም መዓቱን በምሕረት እንዲመልስላቸው እግዚአብሔርን ማምለክ ፈለጉ፤ በዚህን ጊዜ የሙሴን ሕግ የሚያስተምራቸው ካህን ተላከላቸው። 2ኛ ነገ ፲፯፥፳፬-፴፫።
          አይሁድ ከባቢሎን ምርኮ ሲመለሱ ሳምራውያን አብረው የፈረሰውን ቤተ መቅደስ ለመሥራት ቀርበው ነበር። ዘሩባቤል ግን ጥንታውያን የእሥራኤል ዘር ባለመሆናቸው አልተቀበላቸውም። ዕዝ ፬፥፩-፬። ነህምያም ከእስራኤል አስወጥቷቸዋል። ነህ ፲፫፥፬-፱። ሳምራውያን በገሪዛን ተራራ የራሳቸውን ቤተ መቅደስ የሠሩት ከዚህ በኋላ ነው። ሳምራዊቷ ሴት ኢየሱስ ክርስቶስን፦ «አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተ ግን ይሰግዱበት ዘንድ የሚገባው ሥፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ» ያለችው ለዚህ ነው። ዮሐ ፬፥፳።
          አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይገናኙም ነበር ፥ ከእጃቸው ተቀብለው መብላትንም ሆነ መጠጣትን እንደ ርኲሰት ይቆጥሩት ነበር። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰማርያዋን ሴት፦ «ውኃ አጠጪኝ፤» ባላት ጊዜ፦ «አንተ አይሁዳዊ ስትሆን እኔም ሳምራዊት ስሆን እንዴት ከእኔ ዘንድ ውኃ ትለምናለህ? » ያለችው በዚያ ልማድ መሠረት ነው። ዮሐ ፬፥፯። ሳምራዊ መባልም እንደ ንቀት ነበር ፥ ለእርሱ ለጌታችን ክብር ምስጋና ይግባውና፦ አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስን «አንተ ሳምራዊ እንደሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ (ሎቱ ስብሐት) መናገራችን በሚገባ አይደለምን?» ያሉት ለዚህ ነው። ዮሐ ፰፥፵፰። ሳምራውያን ሕገ ኦሪትን እንጂ ትንቢተ ነቢያትን አይቀበሉም ነበር።
          ደጉ ሳምራዊ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው። ሳምራዊ ማለት ሀገር ጠባቂ ማለት ነው፥ እየሱስ ክርስቶስም እረኛችን ጠባቂያችን ነው፤ ዮሐ ፲፥፲፩ ፣፩ኛ ጴጥ ፪፥፳፬። ሀገር ጠባቂ ሀገርን የሚጠብቀው ራሱን ለሞት አሳልፎ በመስጠት ነው፥ እየሱስ ክርስቶስም እኛን በነፍስም በሥጋም የጠበቀን ራሱን ለመስቀል ሞት አሳልፎ ሰጥቶ ነው፤ የሳምራዊ ትውልዱ ከሕዝብ (ከእስራኤል) እና ከአሕዛብ ነው፥ የኢየሱስ ክርስቶስም ትውልዱ ከሕዝብም ከአሕዘብም ነው።
          ደጉ ሳምራዊ ቊስለኛውን በሩቅ አይቶ አዘነለት ፥ቀርቦም በቊስሉ ላይ ወይንና ዘይት አፈሰሰለት፤ ወይኑ፦ የቊስለኛውን ደም እንዲያቆምለት እንዲያደርቅለት ነው። ቊስል ቶሎ የሚደርቀው ከላይ ነው፥ ወዲያውም እየተሰነጣጠቀ ያሰቃያል፤ ለዚህም መከላከያ እንዲያለሰልስለት ዘይቱን አፍስሶለታል። ጌታችንም በሩቅ ማለትም በሰማይ መንበሩ ተቀምጦ ቊስለኛውን አዳም በዓይነ ምሕረቱ አየው ፥ ገጸ ምሕረቱን መለሰለት፤ ቀረበውም። (ባሕርዩን ባሕርይ አደረገ ፥ የባሕርዩ መመኪያ ከሆነች ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ፥ ያንን ተዋሕዶ ሰው ኹኖ ተወለደ)። ወይን እንደማፍሰስ ፦ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ፥ ሥጋውን ቆረሰለት ደሙን አፈሰሰለት። ጌታችን የጸሎተ ሐሙስ ዕለት ወይኑን በጽዋ አድርጎ፦ «ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤» ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፳፮፥፳፯።
          እንደ ዘይት ደግሞ የመንፈሰ ቅዱስን ጸጋ ሰጥቶታል። ይኽንን በተመለከተ ቅዱስ ዳዊት፦ «ወይን (የክርስቶስ ደሙ) የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥ ዘይትም ፊትን ያበራል ፥(መንፈስ ቅዱስ ሰውን ብሩኅ መልአክ ያስመስለዋል) ፥ እህልም (የክርስቶስ ስንዴ ሥጋው) የሰውን ጉልበት (ነፍስን) ያጠናክራል።» ብሏል። መዝ ፻፫፥፲፭። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም፦ «እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋልና ሁሉንም ታውቃላችሁ።» ያለው ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ነው።
          ደጉ ሳምራዊ ከአህያው ወረዶ ቊስለኛውን ማስቀመጡ የሚያመለክተው፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ መንበሩ መውረዱንና የአዳምን ሥጋ በዕርገት በሰማይ መንበሩ ማስቀመጡን ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «በኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያዊ ሥፍራ ከእርሱ ጋር አስቀምጠን፤» ያለው ይኽንን ምሥጢር ይዞ ነው። ኤፌ ፪፥፯። ምክንያቱም በተዋሕዶ አምላክ የሆነ ሥጋ በሰማይ የእሳት መንበር ተቀምጧልና። ቅዱስ እስጢፋኖስ በመከራው ጊዜ ሰማይ ተከፍቶለት(ምሥጢር ተገልጦለት) ፊት ለፊት አይቷል። የሐዋ ፯፥፶፭።
          ደጉ ሳምራዊ፦ ያከመውን ቊስለኛ ለእንግዶች ቤት ጠባቂ ማስረከቡ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ፈሳሽነት ያከማቸውን ምእመናን ለመምህራን የማስረከቡ ምሳሌ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስን፦ «ግልገሎቼን አሰማራ ፥ ጠቦቶቼን ጠብቅ ፥ በጎቼን አሰማራ፤» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፳፩፥፲፭። ሁለት ዲናሮች ደግሞ የሁለቱ ማለትም የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ምሳሌዎች ናቸው። የሰው ሕይወቱ የሚጠበቀው በእነዚህ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ፥ ለትምህርትና ለተግሣፅ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።» ያለው ለዚህ ነው። ፪ኛ ጢሞ ፫፥፲፮። በኤፌሶን መልእክቱም ላይ ፦ «በሐዋርያት (በአዲስ ኪዳን) እና በነቢያት (በብሉይ ኪዳን) መሠረት ላይ ታንጻችኋል ፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።» ብሏል። ኤፌ ፪፥፳።
          እግዚአብሔር፦ ነቢዩ ሕዝቅኤልን፦ «የሰው ልጅ ሆይ! ያገኘኸውን ብላ፤ ይህን መጽሐፍ ብላ፤ ሄደህም ለእስራኤል ልጆች ተናገር።» ያለው ቅዱሳት መጻሕፍትን ነው። እርሱም፦ «የሰው ልጅ ሆይ! አፍህ ይብላ፤ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ። እኔም በላሁት፤ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ፤» ብሏል። ሕዝ ፫፥፩-፬። በመሆኑም፦ በሁለት ዲናር የተመሰሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ምግበ ነፍስ ናቸው። ቅዱስ ዳዊትም፦ «ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ጣፈጠኝ።» ብሏል። መዝ ፻፲፰፥፻፫።
          ደጉ ሳምራዊ የእንግዳ ቤት ጠባቂውን፦ «ከሁለት ዲናር በላይ ብታወጣ እኔ በተመለስኩ ጊዜ እከፍልሃለሁ፤» አለው እንጂ፥ «ዋጋ የለህም፤» አላለውም። ይህም የሚያመለክተው፦ መምህራን የተሰጣቸውን፦ ሁለት ዲናር (ብሉይ ኪዳንን እና አዲስ ኪዳንን) ይዘው ፥ የምእመናንን ሕይወት ለመጠበቅ ሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍትን ቢጽፉ፥ ጌታ ሲመጣ የድካማቸውን ዋጋ እንደሚከፍላቸው ነው። ቅዱሳን ሊቃውንት፦ መጽሐፍ ቅዱስን ለማብራራት ፥ ንባቡን በመተርጐም ፥ ምሥጢሩን በማራቀቅ አያሌ መጻሕፍትን ጽፈዋል። እነዚህም አዋልድ መጻሕፍት ይባላሉ። የቅዱሳት መጻሕፍት ልጆች ማለት ነው። የገድል የድርሳን እና የተአምር መጻሕፍት ቊጥርም ከአዋልድ መጻሕፍት ነው። እነርሱም የእግዚአብሔር ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንዴት እንደፈጸሙ፥ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን የሚያሳይ ነው። መጻፍ ማጻፍም ፥ መስማት ማሰማትም ዋጋ አለው።
          እንግዲህ በተሰጡን ሁለት ዲናሮች ሥራ እንድንሠራ ፥ ሌሎችንም ቅዱሳት መጻሕፍት በመጻፍና በማጻፍ እንድንመክርና እንድንመክር ፥ የተሰጠንን አደራ እንድንጠብቅ ፥ በዚህ ዓለም ተዋርደን ምእመናን የሚከብሩትን ግብር ይዘን እንድንገኝ ፥ የሚያዝን ልቡና እንዲሰጠን ፥ የምናቆስል ሳይሆን የቆሰሉትን የምናክም እንዲያደርገን፥ የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን።

«ወዮልኝ፣»

           
         ድካማቸውን አይተው፥ ጉድለታቸውን አስተውለው፥ ራሳቸውን የሚገሥጹ፥ በራሳቸው የሚፈርዱ ሰዎች ብፁዓን (ንዑዳን፥ ክቡራን) ናቸው። ያለፈውን ዞር ብሎ በማየት፥ የቆሙበትን በማስተዋል፥ ወደፊት ሊመጣ የሚችለውንም አሻግሮ በ መመልከት፦ «ወዮልኝ፤» ብሎ ራስን ማስጠንቀቅ መንፈሳዊነት ነው። በተሰጣቸው ጸጋ ሳይኰፈሱ ፥ በአገልገሎት ብዛት ሳይጋረዱ፥ ወደ ውስጥ ማየት የአእምሮ መከ ፈት ነው። «አይገባኝም ፥ ሳይገባኝ ነው፤» ማለት የእግዚአብሔርን ቸርነት መግለጥ፥ ለጋስነቱን መመስከር ነው። በምድርም በሰማይም (በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ) ትሑት ሰብእና፥ ቅን ልቡና ይዞ መገኘት ነው። «ወዮልኝ፤» ያለ ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስ ነው። እርሱም ከዓበይት ነቢያት አንዱ ነው።

ነቢዩ ኢሳይያስ ማነው?
          ኢሳይያስ ማለት ቅቡዕ እምቅብዓ ትንቢት ማለት ነው። እንዲህ መባሉም ትንቢት የሚገልጥ መንፈስ ቅዱስ ስላደረበት ፥ ሀብተ ትንቢት ስለተሰጠው ነው። ኢያሱ ፥ ሆሴዕ ፥ ኢየሱስ መድኃኒት ማለት እንደሆነ መድኃኒት ማለትም ነው። ኢያሱ ወልደ ነዌ መድኃኒት የተባለው፡- ባጭር ታጥቆ ፥ ጋሻ ነጥቆ ፥ ዘገር ነቅንቆ ፥ አማሌቃውያንን አጥፍቶ ፥ እስራኤልን አድኖ ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ፡- «ሕማማተ (መከራ) መስቀልን ታግሦ፥ ሥጋውን ቆርሶ፥ ደሙን አፍስሶ ፥ አጋንንትን ድል አድርጐ፥ ነፍሳትን አድኖ ነው። «ኢሳይያስስ ምን ሠርቶ ነው?» እንል ይሆናል። ኢሳይያስም ወደፊት በትንቢቱ፥ በትምህርቱ እንደሚያድን ፥ እግዚአብሔር ገልጦላቸው፥ ከቤተ ግዝረት ገብተው መድኃኒት ብለውታል።
          ኢሳይያስ የነበረው፡- በይሁዳ ነገሥታት፡- በዖዝያን፥ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ነበር። ዘመኑም ከ740 - 688፡ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ነው። በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት የቤተ መንግሥቱ አማካሪ ነበር። ፪ኛ ነገ ፲፱፥፫ ኢሳ ፯፥፩። ምክንያቱም የመንፈሳውያን ምክርና ተግሣጽ ለቤተ መንግሥቱ ያስፈልጋልና ነው። (ዛሬ ዛሬ ግን የተገላቢጦሽ ነው)። የአባቱ ስም አሞጽ ይባላል። ኢሳ ፩፥፩፣ ፪ኛ ነገ ፲፱፥፩። ነቢዩ ኢሳይያስ በስድሳ ስድስት ምዕራፍ የተከፈለ የትንቢት መጽሐፍ አለው። ይልቁንም ስለ ነገረ ማርያም፡- «ናሁ ድንግል ትጸንስ፥ ወትወልድ ወልደ፥ ወትሰምዮ ስሞ አማኑኤል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወልድንም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።» በማለት ደረቅ ትንቢት (ትርጓሜ የማያሻው ትንቢት) ተናግሯል። ኢሳ ፯፥፲፬ ሰለ መከራ መስቀሉም፡- «እርሱ ግን በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፥ ሕመማችንንም ተሸከመ፥ ስለ እኛም ታመመ፤ . . . እርሱ ግን ስለ ኃጢአታችን ቈሰለ፤ ስለ በደላችንም ታመመ፥ የሰላማችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን። . . .  እርሱ ግን በመከራ ጊዜ አፉን አልከፈተም፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ የበግ ጠቦትም በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። ብሏል። ኢሳ ፶፫፥፬።
«ወዮልኝ፤» ያለው መቼ ነው?
          ነቢዩ ኢሳይያስ «ወዮልኝ፤» ያለው፦ እግዚአብሔርን በንጉሠ ነገሥት አምሳል በዙፋን ተቀምጦ ባየው ጊዜ ነው። ጊዜውም ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት ነው። «ርኢክዎ ለእግዚአብሔር ፥ እንዘ ይነብር ዲበ መንበሩ ነዋኀ ወልዑል። እግዚአብሔርን በረዥምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ (በልዑል መንበሩ) ተቀምጦ አየሁት፤ ምስጋናውም ቤቱን ሞልቶት ነበር። (ቤቱን ብርሃን ሞልቶት አየሁት)። ሱራፌልም (ሃያ አራት ካህናተ ሰማይ) በዙርያው ቆመው ነበር። (አክሊላቸውን አውርደው፥ ከጉልበታቸው ሸብረክ ብለው፥ አንገታቸውን ቀለስ አድርገው፥ የወርቅ ጽንሐ ይዘው ፥ የእሳቱን ዙፋን ዙሪያ ውን ያጥኑ ነበር)። ለእያንዳንዳቸውም ስድስት ስድስት አክናፍ ነበራቸው። ሁለት ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ዘርግተው ፊቶቻቸውን ይጋርዱ ነበር ፥ ሁለቱን ክንፎቻቸውን ወደታች ዘርግተው እግሮቻቸውን ይሸፍኑ ነበር። የተቀሩትን ሁለቱን ክንፎቻቸውን ደግሞ እንደ መስቀል ግራና ቀኝ ዘርግተው ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ይበርሩ ነበር።» ብሏል።
          ሱራፌል ሁለት ክንፎቻቸውን ወደ ላይ መዘርጋታቸው፡- «ወደላይ ቢወጡ፥ ቢወጡ አይደረስብህም ፥ (ባህርይህ አይመረመርም)፤ ማለታቸው ነው። ፊታቸውን መሸፈናቸው ደግሞ መለኮታዊ እሳት እንዳያቃጥላቸው ነው። አንድም ትእም ርተ ፍርሃት (የፍርሃት ምልክት) ነው። አንድም አንተን ማየት አይቻለንም ሲሉ ነው።  ሁለት ክንፎቻቸውን ወደታች መዘርጋታቸው፡- «ወደታች ቢወርዱ፥ ቢወርዱ አይደረስብሀም፥ ባህርይህ አይመረመርም፤» ማለታቸው ነው። እግሮቻቸውን መሸፈናቸው ደግሞ በፊትህ መገለጥ (መቆም) አይቻለንም፥ አይገባንም ማለታቸው ነው። ሁለት ክንፎቻቸውን ደግሞ በመስቀል አምሳል ግራና ቀኝ ዘርግተው ከጽንፍ እስከ ጽንፍ መብረራቸው  ትእምርተ ተልዕኮ ነው። አንድም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ብንበርር የሌለህበት ሥፍራ የለም፤ አይደረስብህም፥ ባህርይህ አይመረመርም፤ ማለታቸው ነው። በሌላ በኲል ደግሞ ከዕለተ ዓርብ በፊት በትእምርተ መስቀል አምሳል በፊቱ መታየታቸው፡- እንዲህ ባለ አርአያ ተሰቅለህ ዓለምን ታድናለህ ሲሉ ነው። በቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ፡- «የሚያቃጥል እሳት እንዳይበላቸው በመብረቅ ፊታቸውን ይሸፍናሉ፥ የኃይል ነበልባል እንዳያቃጥላቸው እግራቸውን በፍም ይሸፍናሉ፥ በአራቱ ማዕዘንና በዳርቻም ሁሉ ይወጣሉ። (ይበራሉ)።» የሚል አለ። ቁ 18
          ሱራፌል፡- «ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ፥ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች።» እያሉ፦ በታላቅ ድምፅ ፥ በአንድነት በሦስትነት ሲያመሰግኑ ነቢዩ ኢሳይያስ አይቷል ፥ ሰምቷል። ይህ ምስጋና በሰማይም በምድርም ፍጹም ነው። ሦስት ጊዜ ቅዱስ ማለታቸው ለሦስትነታቸው ፥ የቃሉ አለመለወጥ ደግሞ ለአንድነታቸው ምሳሌ ነው። ሥላሴ አንድም ሦስትም ናቸውና። ከዚህ በኋላ ጩኸው ከሚያመሰግኑት ምስጋና የተነሣ የመድረኩ መሠረት ተናወጠ፤ ቤቱንም ጢስ ሞላበት። ይህም፡- የፀውርተ መንበሩ (የእሳቱን ዙፋን የሚሸከሙ) የኪሩቤልን (የገጸ ሰብእ፥ የገጸ ላህም፥ የገጸ ንስር፥ የገጸ አንበሳ) ዕርገተ ጸሎታቸውን (የጸሎታቸውን ማረግ) ለኢሳይያስ ሲያሳየው ነው። አንድም ጢስ፦ እግዚአብሔር፦ እስራኤል ዘሥጋን ፈጽሞ እንደተጣላቸው የሚያመለክት ነው። ይኸውም በሀገራቸው ልማድ ሲገልጥለት ነው። በሀገራቸው አማላጅ የሄደ እንደሆነ፦ ጢስ አጢሰው፥ ቤት ጠርገው ይቆዩታል፤ እንዳይቀመጥ ትቢያ ይሆንበታል፥ እንዳይቆም ዓይኑን ጢስ ይወጋዋል፤ (ያቃጥለዋል)፤ በዚህን ጊዜ እንደምንም አንድ ነገር ወይም ሁለት ነገር ተናግሮ ይሄዳል። ይህም ምልጃህን ለመቀበል አልፈቀድንም ለማለት ነው። እግዚአብሔርም እስራኤል ዘሥጋን አልማለዳቸውም ሲል ጢሱን አሳይቶታል። በዚህን ጊዜ ነው ፥ ነቢዩ ኢሳይያስ፡- «እኔም ከንፈሮቼ የረከሱብኝ (በለምጽ የነደዱብኝ) ሰው በመሆኔ ፥ ከንፈሮቻቸው በረከሱባቸው ሕዝብ (ቢመክሯቸው ቢያስተምሯቸው በማይሰሙ፥ ሕገ እግዚአብሔርን በማያውቁ ወገኖች) በእስራኤል መካከል በመቀመጤ ዐይኖቼ የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን ስለአዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ፤» ያለው።
ነቢዩ ኢሳይያስ ለምን በለምጽ ተመታ?
          በኦሪቱ ለምጽ የርኲሰት ምልክት ነበር። ነቢዩ ኢሳይያስ በነበረበት በንጉሡ በዖዝያን ዘመን ሊቀ ካህናቱ አዛርያስ ይባል ነበር። ስለ ክብረ ክህነት የከበረ ልብስ ይለብስ ስለነበር ንጉሡ፡- «ምነው? ከእኔ በላይ» ቢለው፦ «ካህናቲከ ይለብሱ ጽድቀ፤ ካህናትህ ጽድቅን ይለብሳሉ፤» ተብሎ ተጽፎብሃል ሲል መለሰለት። በአደባባይ የሚቀመጠውም በቀኙ ስለነበር ፥ አሁንም «ምነው?» ቢለው፡- «ካህን ይነብር በየማነ ንጉሥ፤ ካህን በንጉሥ ቀኝ ይቀመጣል፤» ይልብሃል አለው። ሦስተኛም ንጉሡ አዛብቶ ፥ አጓድሎ ፥ የፈረደውን ፍርድ ፥ አሟልቶ አቃንቶ ፈረደ። አሁንም «ምነው?» ቢለው፡- «እምነ መንግሥት የዓቢ ክህነት፤ ከሥልጣነ መንግሥት ሥልጣነ ክህነት ይበልጣል፤» አለው።
          በዚህን ጊዜ ንጉሡ ዖዝያን፡- «እኔስ በአባቴ ወገን መንግሥት ከተሰጠው ከነገደ ይሁዳ ብወለድም በእናቴ በኲል ክህነት ከተሰጠው ከነገደ ሌዊ እወለዳለሁ፤» ብሎ ለጥፋት ልቡ ታበየ፥ አምላኩንም እግዚአብሔርን በደለ፤ ልብሰ ተክህኖውን ለብሶ፥ ማዕጠንተ ወርቁን ይዞ፥ በዕጣን መሠዊያው ላይ ያጥን ዘንድ በድፍረት ወደ መቅደስ ገባ። ካህኑም አዛርያስ፥ ከእርሱም ጋር ጽኑአን የነበሩ ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ተከትለው ገቡ። ንጉሡንም ዖዝያንን እየተቃወሙ፥ «ዖዝያን ሆይ፥ ዕጣን ማጠን ለተቀደሱት ለአሮን ልጆች ለካህናቱ ነው እንጂ ለእግዚአብሔር ታጥን ዘንድ ለአንተ አይገባህም፤ ከእግዚአብሔር ርቀሃልና ከመቅደሱ ውጣ፤ ይህም በአምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ ለአንተ ክብር አይሆንልህም፤» አሉት። ዖዝያንም ተቆጣ፤ በመቅደስም የሚያጥንበት ጥና በእጁ ነበረ፤ ካህናቱንም በተቆጣ ጊዜ በካህናቱ ፊት በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በዕጣኑ መሠዊያ አጠገብ ሳለ በግምባሩ ላይ ለምጽ ታየ። (በሻሽ ቢሸፍነው በሻሹ ላይ ወጣበት)። ታላቁ ካህን አዛርያስ ካህናቱም ፈጥነው አባረሩት። እርሱም እግዚአብሔር ቀሥፎት ነበርና ይወጣ ዘንድ ቸኰለ። እስኪሞትም ድረስ ከለምጹ አልነጻም። ፪ኛ ዜና ፳፮፥፳። ልጁ ኢዮኣታም በሱ ተተክቶ እንደ ምስለኔ ሁኖ ሲገዛ ኑሯል። ያን ጊዜ ኢሳይያስ ለዖዝያን ወዳጁ ነበር፤ ቢመክረው፥ቢያስተምረው ይመለስ ነበር፤ ነገር ግን አፍሮት ፈርቶት፥ ሳይመክረው ፥ ሳያስተምረው፥ በመቅረቱ ከከንፈሩ ለምጽ ወጥቶበት ሀብተ ትንቢት ተነሥቶታል። እግዚአብሔር፦ ንጉሡ ዖዝያን ሲሞት ጠብቆ ለኢሳይያስ የተገለጠለት፡- «የፈራኸው ንጉሥ አለፈ፤ እኔ ግን በባህርዬ ሞት፥ በመንግሥቴ ኀልፈት የለብኝም፤ በዘባነ ኪሩብ ስሠለስ፥ ስቀደስ እኖራለሁ፤» ሲለው ነበር።

ለምጽና ሥርዓቱ፤
          በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ ፲፫ እና ምዕራፍ ፲፬ ላይ ፥ እግዚአብሔር በልሙጻን ላይ የሠራውን ሥርዓት፥ ለሙሴና ለአሮን ሲነግራቸው እናገኛለን። ከዚህም ውስጥ፡- «የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው፦ ልብሱ የተቀደደ ይሁን፥ ራሱም የተገለጠ ይሁን፥ ከንፈሩንም ይሸፍን፥ ርኲስ ይባላል፤ ደዌው ባለበት ዘመን ሁሉ ርኲስ ይሆናል፤ እርሱ ርኲስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጣል፤ መኖሪያውም ከሰፈር በውጭ ይሆናል።» የሚል ይገኛል። ዘሌ ፲፫፥፵፭።
          «ልብሱ የተቀደደ ይሁን፤» ማለት፦ ስለ ኃጢአቱ ፈጽሞ ይዘን ማለት ነው። በልማድም ዕብራውያን ፈጽመው ሲያዝኑ ልብሳቸውን ለሁለት ይቀድዱታል። የዳዊት ልጅ ትዕማር የገዛ ወንድሟ ደፍሯት  ከቤት አስወጥቶ በዘጋባት ጊዜ፡- በራስዋ ላይ አመድ ነስንሳ፥ ብዙ ሕብርም ያለውን ልብሷን ተርትራ እየጮኸች አልቅሳለች። ፪ኛ ሳሙ ፲፫፥፲፱። «ራሱም የተገለጠ ይሁን፤ (አይሸፋፈን)፤» ማለት ለጊዜው ለምጹ እንዲታይ ነው። ለፍጻሜው ግን ኃጢአቱን አይሸፍን ፥ ገልጦ ለካህኑ ይናገር፥ (ይናዘዝ)፥ ማለት ነው። ጌታ በወንጌል ለምጻሙን ሰው፡- «ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤» ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፰፥፬።  
          «ከንፈሩንም (አፉን) ይሸፍን፤» ማለት፦ ለጊዜው ደዌው በትንፋሽ እንዳይተላለፍ ሲሆን ፥ ለፍጻሜው ግን «ቅዱሱን የእግዚአብሔርን ስም መጥራት አይገባኝም፤» ይበል፥ማለት ነው። ለወገቡ መታጠቂያ፥ ለእግሩም ጫማ አይኑረው፥ የሚልም አለ። ለወገቡም መታጠቂያ አይኑረው የተባለው፦ ለጊዜው የለምጻም አካሉ ልህሉህ ስለሆነ እንዳይቆስል ሲሆን ፥ ለፍጻ ሜው ግን «ንጽሕና የለኝም፤» ይበል፥ ማለት ነው። ወገብን መታጠቅ የንጽህና ምልክት ነውና። ጌታችን አምላካችን መድኃ ኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል፡- «ወገባችሁ የታጠቀ፥መብራታችሁም የበራ ይሁን፤» ያለው ለዚህ ነው። ሉቃ ፲፪፥፴፭። ትርጉሙም፡- ልቡናችሁን በንጽህና ዝናር ታጠቁ፥ የልብ ንጽሕና ይኑራችሁ፥ ማለት ነው። ይኸንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፡- «ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ኑሩ፤» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፩፥፲፫ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡- «እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት (በጽድቅ) ታጥቃችሁ ቁሙ፤» ብሏል። ኤፌ ፮፥፲፬። «ለእግሩ ጫማ አይኑረው፤» ማለትም ጫማ የምግባር ምሳሌ በመሆኑ «የምግባር ደሀ ነኝ፤» ይበል ማለት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ፦ «ወንጌልን ተጫሙ ፤ (በምግባረ ወንጌል ጸንታችሁ ቁሙ ፥ በወንጌል የታዘዘውን ፈጽሙ) ፤» ማለቱ ለዚህ ነውና። ኤፌ ፮፥፲፭።
«በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ ኃጢአትህም ተሰረየልህ፤»
          ነቢዩ ኢሳይያስ፡- «ወዮልኝ፤» በማለቱ፡- ከሱራፌል አንዱ እየበረረ ወደ እርሱ መጣ። በእጁም ከሰማይ መቅደስ ከመሠዊያው በጉጠት የወሰደው ፍም ነበረ። አፉንም ዳሰሰበትና፡- «እነሆ፥  ይህ ከንፈሮችህን ነክቷል፥ በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ኃጢአትህም ተሰረየልህ፤» ብሎታል። መሠዊያ የዓለመ ሥላሴ፥ ጉጠት የሥልጣነ እግዚአብሔር፥ ፍም የሀብተ ትንቢት ምሳሌ ነው። ከንፈሩን ማስነካቱም ሀብተ ትንቢትን መለስኩልህ ሲለው ነው። አንድም መሠዊያ የመንበር፥ ጉጠት የእርፈ መስቀል፥ መልአክ የቀሳውስት፥ ፍም የሥጋ ወደሙ፡ ምሳሌ ነው።
          ከዚህ በኋላ፡- «ማንን እልካለሁ? ማንስ ወደዚያ ሕዝብ ይሄድልናል?» የሚለውን የእግዚአብሔርን ድምፅ ሰምቷል። እርሱም፡- እነሆኝ፥ ጌታዬ፥እኔን ላከኝ፤» ሲል መልሷል። እንደ ጥንቱም፡- «ስማዕ ሰማይ፥ ወአጽምዒ ምድር፤ ሰማይ ስማ፥ ምድርም አድምጪ፤» የሚል ሆኗል። ትርጉሙም፡- «ሰማይ ሆይ፥ የእስራኤልን ነገር (ክፋታቸውን) ሰምተህ፥ ዝናም ለዘር፥ ጠል ለመከር አትስጥ፤ ምድርም ሰምተሽ የዘሩብሽን አታብቅዪ፥ የተከሉበሽን አታጽድቂ፤» ማለት ነው። አንድም በዚህ ምድር እንደ ሰማይ ከፍ ከፍ ያላችሁ ልዑላን (ባለሥልጣኖች፥ ባለጠጐች) ስሙ። እንደ መሬትም ዝቅ ዝቅ ያላችሁ ታናናሾች አድምጡ ማለት ነው። አንድም ሰማይ የተባሉ መላእክት ሲሆኑ ምድር የተባሉ የአዳም ልጆች ናቸው።
እንደ ኢሳይያስ፦ «ወዮልኝ፤» ማለት ያስፈልጋል፤
          የእግዚአብሔር ሰዎች «ወዮልኝ፤» እያሉ ራሳቸውን ገሥጸው ይኖራሉ። ጌዴዎን የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ ፊት ለፊት ስላየው ፥ ቃል በቃል ስላነጋገረው፡- «አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወዮልኝ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና፤» ብሎ ነበር። እግዚአብሔርም፡- «ሰላም ለአንተ ይሁን፥ አትፍራ፥ አትሞትም፤» ብሎታል። መሳ ፮፥፳፪። ነቢዩ ኤርምያስም፡- «በሆድ ሳልሠራ አውቄሃለሁ፥ ከማኀፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሐዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ፤» በተባለ ጊዜ፡- «ወዮ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ፥ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም፤» ብሏል። ኤር ፩፥፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ፤ » ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፱፥፲፮።
          እነዚህ «ወዮልኝ፤» ማለታቸው ለእኛ አብነት ነው። ታላላቆቹ እንዲህ ካሉ ከእኛ ከታናናሾቹ የብዙ ብዙ ይጠበቃል። ዕለት ዕለት «ወዮልኝ፤» እያልን ደረታችንን ልንደቃ፥ እንባችንን ልናፈስስ ይገባል። ሥጋችንን ደስ ከማሰኘት በስተቀር እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተን አናውቅምና። ሰውን ደስ ለማሰኘት በሰውም ዘንድ ለመወደድ (ለውዳሴ ከንቱ) እግዚአብሔርን እናሳዝናለንና። እንኳን መንፈሳዊ መሆን መምሰሉ እንኳ አቅቶናልና። ሃያ፥ሠላሳ ዓመት ቃለ እግዚአብሔር ዘር ተዘርቶብን፡- ሠላሳ፥ስድሳ፥መቶ ማፍራት የተሳነን ዘረ ቆርጥሞች ነንና። መቁረባችን ማቁረባችን ፥ መቀደሳችን ፥ ማስቀ ደሳችን፥ ማሳለማችን፥መሳለማችን፥ መናዘዛችን፥ማናዘዛችን፥ መዘመራችን፥ማዘመራችን፥ መስበካችን፥መሰበካችን ሁሉ ከንቱ ሆኖብናልና። ስለሆነም «እገሌ ሳይገባው ነው፤» የሚለውን ትተን፡- «እኔ ሳይገባኝ ነውና ወዮልኝ፤» እንበል። የእግዚአብሔር ሰዎች፡- «ወዮላችሁ፤» እስኪባሉ አይጠብቁምና።
«ወዮላችሁ፤»
          የዓለም ሰዎች፡- «ወዮላችሁ፤» እስኪባሉ ይጠብቃሉ፤ ተብለውም አይመለሱም፤ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቃሉን ትምህርት ሰምተው፥ የእጁን ተአምራት አይተው ያልተመለሱትን ጸሐፍት ፈሪሳውያንን በአንድ ምዕራፍ ላይ ብቻ ስምንት ጊዜ «ወዮላችሁ፤» ብሏቸዋል።
-      «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ።»
-      «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ ወዮላችሁ።»
-      «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ  
        ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፥ ወዮላችሁ።»
-      «ማንም በቤተመቅደስ የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በቤተመቅደስ ወርቅ የሚምል ግን በመሓላው ይያዛል 
        የምትሉ ፥ ዕውሮች መሪዎች ወዮላችሁ።»
-      «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ ከአዘሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ሰለምታወጡ፥ ፍርድንና  ምሕረ 
        ትን ፥ ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ ወዮላችሁ።»
-      «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ በውስጡ ቅሚያና ስስት፦ ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ
        ስለምታጠሩ ወዮላችሁ።»
-      «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጥ ግን የሙታን አጥንት ርኲሰትም ሁሉ
        የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ።»
-      «እናንተ ግብዞች ጻፍችና ፈሪሳውያን፦ የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ ፥ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና
        በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም በአልተባበረናቸውም ነበር ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ።»
     አይሁድ «ወዮላችሁ፤» ተብለውም አልተመለሱም፥ ጌታም እንደማይመለሱ ያውቃል። ስለሚያውቅም «እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ትመሰክራላችሁ። እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ሙሉ። እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?» ብሏቸዋል። ማቴ ፳፫፥፲፫-፴፪። ከእነርሱም በፊት የኮራዚንና የቤተ ሳይዳ ሰዎች «ወዮላችሁ»፤ ብሏቸው ነበር። ማቴ ፲፩፥፳፩።ይኸውም ንስሐ ባለመግባታቸው ነው። የሰዶምና የጐመራ ሰዎች እነርሱ ያገኙትን ዕድል አግኝተው ቢሆን ኖሮ፦ ማቅ ለብሰው ፥ ዓመድ ላይ ተኝተው ንስሐ ይገቡ እንደነበር ነግሯቸዋል። እኛም ያገኘነውን ዕድል ያላገኙ ብዙ ሕዝቦች እንዳሉ ማስተዋል አለብን። ጌታችን፦ «ወዮ ለዓለም ማሰናከያ፤ ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና ፥ ነገር ግን በእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት ለዚያ ሰው ወዮለት።» ያለበትም ጊዜ አለ። ማቴ፲፰፥፯። ያ ሰው የተባለ ለጊዜው ይሁዳ ሲሆን ለፍፃሜው የሁላችንንም ሕይወት ይመለከታል። በአንድም ይሁን በሌላ የእኛም ሕይወት ለሌላው መሰናክል እንቅፋት እየሆነ ነውና። ንጹሐ ባህርይ ኢየሱስ ክርስቶስ ፦ «ወዮላችሁ፤» ቢል የባህርይ አምላክ በመሆኑ ነው። ቅዱሳንም፦ «ወዮላችሁ፤» ቢሉ ፦ ከኃጢአት ርቀው፥ ከበደል ተለይተው፥ ሃይማኖት ይዘው ፥ ምግባር ሠርተው ነው። እኛ ግን እምነታችን ደካማ ፥ጸሎታችን የማይሰማ ፥ ምግባራችን ጐዶሎ መሆኑን እያወቅን ሌሎችን «ወዮላቸው፤» እንላለን። ከምዕመናን ፥ ከዲያቆናት፥ ከቀሳውስት፥ ከመዘምራን ፥ ከሰባክያን ፥ ከጳጳሳት ፥ የማንፈርድበት የለም። አንድም ቀን በራሳችን ፈርደን፥ «ወዮልን፤» ብለን አናውቅም። ስለዚህ ኃጢአታችን እንዲሠረይልን ፥ በደላችንም እንዲወገድልን የዘወትር ጸሎታችን «ወዮልኝ፤» የሚል ይሁን። በሌላ በኲል ግን ሃይማኖት ፥ሥርዓት ፥ ትውፊት ፥ ሲጠፋ ተመክረው ፥ ተገሥፀው የማይመለሱትን «ወዮላችሁ፤» ብሎ ማስጠንቀቅ መፍረድም ይገባል። እንግዲህ እንደ ፈሪሳዊያን ከመሆን የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት ይጠብቀን። አሜን።

« ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ ማቴ ፩÷፬ »

        ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ ፥ በአንቀጸ ብጹዓን ትምህርቱ፡- «ብፁዓን እለ ይላህዉ ይእዜ እስመ እሙንቱ ይትፌሥሑ፤ « ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው ፥ እነርሱ ደስ ይሰኛሉና፤ (መጽናናትን ያገኛሉና)፤» ብሏል።  ቅዱሳን ሐዋርያትም በዚህ ላይ ተመስርተው፦ « እናንተ ኃጥአን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት ዐሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ። እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ፥ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ ፥ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል። » እያሉ አስተምረዋል። ያዕ ፬፥፱ ኀዘን ሲባል ሁለት ዓይነት ነው። አንደኛው የማይገባ ኀዘን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሚገባ ኀዘን ነው።

፩፡- የማይገባ ኀዘን፤
          እናት አባት፥ ወንድም እኅት፥ ባል ሚስት ልጅ ሞቱብኝ፥ የዚህን ዓለም ሀብት ንብረት አጣሁ ብሎ በቀቢጸ ተስፋ ማዘን የማይገባ ኀዘን ነው። ምክንያቱም እንደ እናት አባት ሥላሴ አሉና ነው። እግዚአብሔር «አንተ አቡነ፥ ወአንተ እምነ፤» ይባላል። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ጌታችን በወንጌል፡- «እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ፡- አባታችን ሆይ፥ በሰማያት የምትኖር፥ ስምህ ይቀደስ በሉ፤» ብሎናል። ማቴ ፮፥፱። «እነኋት እናትህ።» እንዲል እመቤታችንም እናታችን ናት። ዮሐ ፲፱፥፷፯። ቅዱስ ዳዊትም፡- «እምነ ጽዮን ይብል ሰብእ፤ ሰው ሁሉ እናታችን ጽዮን አባታችን እግዚአብሔር ይላል፤» ብሏል። መዝ ፹፮፥፭። ቤተክርስቲያንም፡- ከማኅፀነ ዮርዳኖስና ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ በውስጧ ስለተወለድን (በጥምቀት የጸጋ ልጅነትን ስላገኘንባት) እናታችን ናት ዮሐ ፫፧፭፧፧ በሥርዓተ ቅዳሴ ላይ፡- «እምነ በሀ ቅድስት ቤተክርስቲያን፤ እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን ሆይ ፥ ሰላም እንልሻለን፤» የምንለው ለዚህ ነው።
እንደ ወንድም እንደ እኅትም ቅዱሳን መላእክት አሉ። ጌታችን በወንጌል፡- «ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ስንኳ እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ (ወንድም፥ እኅት፥ ሀብት ንብረት፥ ወገን የለውም ብላችሁ እንዳትንቁ ተጠበቁ)፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ሁልጊዜ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁ።» ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፲፭፥፲፩  ማንም ሰው የወንድም የእኅቱን ጥቃት እንደማይፈልግ ሁሉ መላእክትም እንደ ወንድም እንደ እኅት የሰውን ጥቃት አይፈልጉም። ሠለስቱ ደቂቅ፦ በስደት፥ በሞት ወንድም እኅታቸውን ቢያጡም በጥቃታቸው ጊዜ የደረሰላቸው አራተኛ ሆኖ አብሮአቸው ከእሳት የገባላቸው ፥ የታደጋቸውም ፥ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው። ዳን ፫፥፳፭። ዳንኤልም ወደ አናብስት ጉድጓድ በተጣለ ጊዜ አብሮት የወረደው ቅዱስ ሚካኤል ነው። ዳን ፮፥፳፪
         
          እንደ ርስት ጉልትም የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያት አለች። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- «በምድር ያለው ማደሪያ ቤታችን ቢፈርስም ፥ በሰማይ በእግዚአብሔር ዘንድ የሰው እጅ ያልሠራው ዘለዓለማዊ ቤት እንዳለን እናውቃለን። ስለ እርሱ የምንደክምለትን በሰማይ ያለውን ቤታችንን እንለብስ ዘንድ እርሱን ተስፋ እናደርጋለን።» ያለው ለዚህ ነው። ፪ኛ ቆሮ ፭፧፩ በፊልጵስዮስ መልእክቱም «አገራችን በሰማይ ነው፤» ብሏል። ፊል ፫፥፳። ቅዱስ ጴጥሮስም ደጅ የምንጠናው ሰማያዊ ርስታችንን አዲሷን ሰማይና አዲሷን ምድር ነው። ብሏል። ፪ኛ ጴጥ ፫፥፫። ከሁሉም በላይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- «ልባችሁ አይደንግጥ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያና ማረፊያ አለ፤» በማለት የሚጨበጥ የሚታመን ተስፋ ሰጥቶናል። ዮሐ ፲፬፥፩። በዚህ ያመኑ ቅዱሳን ሥጋዊው ነገር ሁሉ ሳያሳዝናቸው ሁለን ትተው ተከትለውታል። ማቴ ፲፱፥፳፯
፩፥፩ ሰው ሲሞትብን እንዴት እንዘን?
          ሞትና መቃብር የመጨረሻ አይደሉም። ከሞት አጠገብ ሕይወት፥ ከመቃብር አጠገብ ትንሣኤ አለን። እኅተ አልዓዛር ማርታ፡- «ወንድሜ፥ በመጨረሻው ቀን እንደሚነሣ አውቃለሁ፤» ብላለች። ጌታም ትንሣኤና ሕይወት እርሱ እንደሆነ ነግሯታል። ዮሐ ፲፩፥፳፬ ። ከዚህም አስቀድሞ፡- «በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ፥ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ፤» ብሎ ነበር። ዮሐ ፭፥፷፱ በሌላ በኩል ደግሞ አልዓዛርን እንደሚያስነሣው እያወቀ የፍቅሩን ያህል አልቅሶለታል። «ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህ አይሁድ እንዴት ይወደው እነደነበረ እዩ አሉ፤» ይላል። ዮሐ ፲፩፥፴፭። በመሆኑም ሰው ሲሞትብን በቀቢጸ ተስፋ ሳይሆን የፍቅራችንን ያህል ልናለቅስ ይገባል። ይኸውም፡-
፩፥፪ ነፍስ ከሥጋ ስትለይ፤
          የነፍስ ሞቷ ከእግዚአብሔር አንድነት ስትለይ በመሆኑ፡- «አንቺ ነፍስ በሞት ምክንያት ከሥጋሽ እንደተለየሽ ሁሉ በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር አንድነት ተለይተሽ ይሆን? ከእግዚአብሔርስ አንድነት አይለይሽ፤» ብሎ ስለ ነፍስ ማዘን፥ ማልቀስ ይገባል። አዳምና ሔዋንን «ሞቱ»  ያሰኛቸው ከእግዚአብሔር አንድነት መለየታቸው ነበር እንጂ የዕፀ በለስን ፍሬ እንደበሉ ወዲያው በመሞታቸው አይደለም ዘፍ ፫፥፰። አስቀድሞ የተነገራቸው «ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያሳየውና ከሚያስታውቀው ዛፍ አትበላ፤ ከእርሱ በበላህ ጊዜ ሞትን ትሞታለህና፤» የሚል ነበር። ዘፍ ፪፥፲፯። በአዲስ ኪዳንም ራሱ ባለቤቱ፡- ወደ እርሱ አንድነት ማለትም ቃለ ሕይወት ወንጌል ወደምትነገርበት ጉባኤ ያልመጡትን በቁማቸው ሙታን ብሏቸዋል። ማቴ ፰፥፳፪
፩፥፫፡- አስከሬን ከቤት ሲወጣ፤
          አስከሬን ከቤት በሚወጣበት ጊዜ፡- «አንተ ሰው፥ አንቺ ሰው በሞት ምክንያት ከምድራዊ ቤታችሁ እንደወጣችሁ ሁሉ በኃጢአት ምክንያት ከሰማይ ቤታችሁ ከመንግሥተ ሰማያት ትወጡ ይሆን? ይህንንስ አያድርግባችሁ፥ ከመንግሥተ ሰማያት አያውጣችሁ፤» ብሎ ማዘን፥ ማልቀስ ይገባል። «አምስቱ ውሾች ግን ከዚያች ሀገር ወደ ውጭ ይወጣሉ፤ እነዚህም አስማተኞች፥ ዘማውያን፥ ነፍሰ ገዳዮች፥ ጣዖት የሚያመልኩ፥ የሐሰት ሥራንም ሁሉ የሚወዱ ሁሉ ናቸው።» ይላል። ራእ ፳፪፥፲፭። ያች ሀገር መንግሥተ ሰማያት ናት። «የዚያን ጊዜም፡- ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ (እፈርድባቸዋለሁ)።» የሚልም አለ። ማቴ ፯፥፳፫።
፩፥፬፡- አስከሬን ወደ መቃብር ሲወርድ፤
          የተገነዘ አስከሬን ወደ መቃብር በሚወርድበት ጊዜ፡- «አንተ ሰው፥ አንቺ ሰው በሞት ምክንያት ወደ መቃብር እንደወረዳችሁ ሁሉ በኃጢአት ምክንያት ወደ ሲኦል ወደ ገሃነመ እሳት ትወርዱ ይሆን? ይኸንንስ አያድርግባችሁ፥ ወደ ሲኦል፥ ወደ ገሃነም አያውርዳችሁ፤» ብሎ ማዘን፥ ማለቀስ ይገባል። ምክንያቱም፡- «እናንተ የተረገማችሁ ለሰይጣንና ለመልእክተኞቹ ወደተዘጋጀው ወደ ዘለዓለም እሳት ሂዱ።» የሚል አለና ነው። ማቴ ፳፭፥፵፩ ከዚሀም አስቀድሞ «በወንድሙ ላይ በከንቱ የሚቆጣ ሁሉ እርሱ ይፈረድበታል ፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል ፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል።» ተብሎ ተነግሯል። ማቴ ፭፥፳፩። በቅዱስ ማርቆስ ወንጌል ደግሞ «እሳቱ የማይጠፉ ትሉ የማያንቀላፋ» የሚል ተጽፏል።
፪፡- የሚገባ ኀዘን፤
          ቅዱሳት መጻሕፍት በጠቅላላው የሚመክሩን የሚገባ ኀዘን እንድናዝን ነው። ጌታችንም የተናገረው ስለዚህኛው ኀዘን ነው። ነገ በነገር ሁሉ ደስ እንዲለን ዛሬ በፈቃዳችን እንድናዝን ነው። ይህም ቅዱሳንን፥ መላእክትን፥ እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኝ ነው።
          «መጀመሪያ፡- በጻፍሁት መልእክት ባሳዝናችሁም እንኳ አይጸጽተኝም፤ ብጸጸትም፥ እነሆ ያች መልእክት ለጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘነቻችሁ አያለሁ። አሁን ግን እኔ ስለ እርሷ በብዙ ደስ ይለኛል፤ ደስታዬም ስለ አዘናችሁ አይደለም፤ ንስሐ ልትገቡ ስለአዘናችሁ እንጂ፤» ፪ኛ ቆሮ ፯፥፰።
          «እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ ስለሚገባ ስለ አንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት በሰማያት ደስታ ይሆናል።» ሉቃ ፲፭፥፲።
          «እውነት እላችኋለሁ፤ ባገኘው ጊዜ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ ጠፍቶ ስለተገኘው ፈጽሞ ደስ ይለዋል። እንዲሁም ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንኳ ይጠፋ ዘንድ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት አይፈቀድም።» ይላል። ማቴ ፲፫፥፲፫። የሚገባ ኀዘንን የምናዝነው ስለ አራት ነገር ነው። እነኚህም፡-
          ፪፥፩፡- የግል ኃጢአትን እያሰቡ ማዘን፤
መቅድመ ወንጌል፡- «አልቦቱ ካልእ ኅሊና ለአዳም ላዕለ ኃጢአቱ፥ ዘእንበለ ብካይ፤ አዳም በኃጢአቱ ምክንያት በመጣበት ብድራት ከማልቀስ በስተቀር ሌላ ኅሊና (አሳብ) አልነበረውም፤» እንዲል፥ በኃጢአቱ ምክንያት አለቀሰ። «ከማዕረጌ ተዋረድኩ፥ ከሥልጣኔ ተሻርኩ» ብሎ ሳይሆን ፈጣሪዬን በደልኩ ብሎ አዘነ። ይህ እንባ፥ ይህ ኃዘን ነው፥ «ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤» የሚል ተስፋ ያሰማው፤ የአዳም ኀዘኑ ፈጣሪን ከሰማይ እንዲወርድ፥ ከድንግል ማርያም እንዲወለድ፥ በቀራንዮ በመልዕልተ መስቀል ተሰቀሎ፥ አዳምን እስከነ ልጅ ልጆቹ እንዲያድን አድርጎታል።
          ንጉሠ እስራኤል ዳዊትም ስለ ድቀቱ በነቢየ እግዚአብሔር በተገሠጸ ጊዜ፦ «እግዚአብሔርን በድያለሁ፤» ብሎ አለቀሰ። በዚህን ጊዜ ነቢዩ ናታን፦ «እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢአትህን አርቆልሃል፤ አትሞትም። ነገር ግን በዚህ ነገር ለእግዚአብሔር ጠላቶች ታላቅ የስድብ ምክንያት አድርገሃልና፤ ስለዚህ ደግሞ የተወለደልህ ልጅ ፈጽሞ ይሞታል፤» አለው። ፪ኛ ሳሙ ፲፪፥፲፫። ስምዖን ጴጥሮስም ጌታ አስቀድሞ እንደተናገረበት ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ጌታውን አላውቀውም ብሎ ነበር። ይህንንም ያለው ከልቡ ሳይሆን ከአፉ ነው፤ ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ። ስምዖን ጴጥሮስም፡- «ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤» ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ። ማቴ ፳፮፥፴፫-፸፭። ሁሉም መልካቸው ሳይለወጥ፥ ሳይሰቀቁ ዕንባቸው እንደ ሰን ውኃ ይወርድ ነበር።
፪፥፪፡- የባልንጀራን ኃጢአት እያሰቡ ማዘን፤
          ነቢዩ ሳሙኤል ስለ ንጉሥ ሳኦል ኃጢአት በመዓልትም በሌሊትም ያለቅስ ነበር። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፡- «በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከመቼ ነው?» ብሎታል። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፩። በአዲስ ኪዳን ደግሞ ከሁሉም በላይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ለኢየሩሳሌም አልቅሶላታል። «ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት። እንዲህም አላት፥አንቺስ ብታውቂ ሰላምሽ ዛሬ ነበር፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ከዐይኖችሽ ተሰወረ። ጠላቶችሽ አንቺን የሚከቡበት ቀን ይመጣል፤ ይከትሙብሻል፤ ያስጨንቁሻልም፤ በአራቱ ማዕዘንም ከብበው ይይዙሻል። አንቺን ይጥሉሻል፤ ልጆችሽንም ከአንቺ ጋር ይጥሉአቸዋል፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉልሽም፤ የይቅርታሽን ዘመን አላወቅሽምና፤» ይላል። ሉቃ ፲፱፥፵፩። በኦሪቱ የነቢያት አለቃ ሙሴ ስለ ወገኖቹ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ፡- «አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ፤» ብሏል። ዘዳ ፴፪፥፴፪። ንጉሡ ዳዊትም የእግዚአብሔር መልአክ ከሕዝቡ ሰበዐ ሺህውን በቀሠፈ ጊዜ፡- «እነሆ፥ እኔ በድያለሁ፥ ጠማማም  ሥራ እኔ አድርጌአለሁ፤ እነዚህ በጎች ግን እነርሱ ምን አደረጉ? እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ እንድትሆን እለምንሃለሁ፤» ሲል ተናግሯል። ፪ኛ ሳሙ ፳፬፥፲፯። ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፡- «ብዙ  ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለብኝ ስል በክርስቶስ ሆኜ እውነትን እናገራለሁ፤ አልዋሽምም፤ ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል። በሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና፤» ብሏል። ሮሜ ፱፥፩።
፪፥፫፡- ግፍዓ ሰማዕታትን እያሰቡ ማዘን፤
          ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን፥ የእምነት ሰዎች ታሪክ፥ ከአብርሃም ጀምሮ እየተረከ እውነቱን ቢነግራቸው አይሁድ ተበሳጩበት። ጥርሳቸውንም አፋጩበት። ቅዱስ እስጢፋኖስ ግን አድሮበት በሚኖር መንፈስ ቅዱስ ጸንቶ ወደ ሰማይ ቢመለከት ሥላሴን አየ። ያየውንም ምስጢር (ምሥጢረ ሥላሴን) ነገራቸው። እነርሱም በታላቅ ቃል ጮኸው እንዳይሰሙ ጆሮአቸውን ደፈኑ። መሬት ለመሬት እየጐተቱም ከከተማ አወጡት። በድንጋይም ቀጥቅጠው ገደሉት ፤ ደጋግ ሰዎችም አስክሬኑን አንስተው እያዘኑ እያለቀሱ ቀበሩት ይላል። የሐዋ ፰፥፪። ያሳዘናቸው፥ ያስለቀሳቸው ሞቱ ብቻ ሳይሆን የተፈጸመበት ግፍ ጭምር ነው። ስለሆነም ዓለም የግፈኞች በመሆኗ  ፍርድ ሲጓደል፥ ደሀ ሲበደል ቅዱሳን ሲገፉ ማዘን ይገባል።
፪፥፬፡- መከራ መስቀሉን እያሰቡ ማዘን፤
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን በጥቅሉ አሥራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል ተቀብሏል። ይኸንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፡- «ከኃጢአታችን ያወጣን ዘንድ፥ በጽድቁም ያድነን ዘንድ፥ እርሱ ስለ ኃጢአታችን በሥጋው በእንጨት ላይ ተሰቀለ፤ በግርፋቱም ቁስል ቁስላችሁን ተፈወሳችሁ።» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፳፬። ይህም ነቢዩ ኢሳያይስ፡- «እርሱ ግን በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፤ ስለ እኛም ታመመ፤--- እርሱ ግን ስለ ኃጢአታችን ቈሰለ፤ ስለ በደላችንም ታመመ፤--- በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን።» በማለት አስቀድሞ የተናገረው ነው። ኢሳ ፶፫፥፬። በመሆኑም ስለ እኛ ብሎ የተቀበላቸውን እነዚህን መከራዎች እያሰብን ልናዝን ይገባል። ቅዱስ ዮሐንስ የዕለተ ዓርቡን መከራ በቀራንዮ ፊት ለፊት በማየቱ ሰበዓ ዘመን ቁጽረ ገጽ (ኀዘንተኛ) ሁኖ ኑሯል። መላ ዘመኑን በፊቱ ላይ ፈገግታ አልታየም።
ለመሆኑ የእኛ ኀዘን ምን ይመስላል?
          ከደስታ በቀር ሐዘንን የምንፈልግ ሰዎች አይደለንም። ማናችንም ብንሆን ቢሳካልን ለአንድ ደቂቃ እንኳን ማዘን አንፈልግም። ቢቻለን የዓይን አምሮታችን የሥጋ ፍላጐታችን ሁሉ ተሟልቶልን በዓለም ተደስተን መኖርን እንፈልጋለን። ይልቁንም ስለ ኃጢአታችን ፈጽሞ ማዘን አንፈልግም። እንዲያውም እንደ ኃጢአት የሚያስደስተን ነገር የለም። ያመነዘሩበትን፥ ጠጥተው የሰከሩበትን፥ አጭበርብረው ብዙ ገንዘብ ያገኙበትን፥ በጭፈራ ያሳለፉበትን፥ የጠሉትን ሰው የተበቀሉበትን፥ በአጠቃላይ በተለያየ መንገድ ሰውን የጐዱበትን ዕለትና ዘመን እያስታወሱ የሚደሰቱ ፥ ሐሴትም የሚያደርጉ ሰዎች እጅግ ብዙ ፥የብዙ ብዙ ናቸው። የሰው ሕይወት በሥጋዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ሲመሰቃቀል፥ የሰው ትዳር ሲበጠበጥ ፥ ሲፈርስ ፥ በደስታ ያልተሳሉትን ስእለት ለማስገባት የሚፈልጉ ሰዎችም አይጠፉም። ሰው ሲታመም፥ ሥራም ሲፈታ አንጀታቸው ቅቤ የሚጠጣ ፈጽመው የሉም ለማለት አይቻልም። ወተቱን አጥቁረው፥ ማሩንም አምርረው ሰውን በማማት የሰውንም ስም በማጥፋት መደሰት እንደ ዘውትር ጸሎት የተያዘ የየዕለቱ ግብር ነው። የእጅ ስልካችን፥ የቤታችንም ስልክ፥ ኢ-ሜይላችንም ጭምር የሚያሳብቀው ይኸንኑ ነው። ይህ ሁሉ ከራስ ወዳድነት (ራስን ከማምለክ) የሚመነጭ ነው። «ነገር ግን በኋላ ዘመን ክፉ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፥ ገንዘብንም የሚወዱ፥ ቀባጣሪዎች፥ ትምክሀተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ ምስጋና የሌላቸው፥ ከጽድቅም የወጡ ይሆናሉ። ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ።» እንዳለ ሐዋርያ። ፪ኛ ጢሞ ፫፥፩።
          ምናልባት የምናዝነው ያሰብነውና ያቀድነው፥ ኃጢአት ሳይሳካልን ሲቀር ነው። ወይም የገፋነው ሰው ሳይወድቅ ሲቀር፥ ያዋረድነው ሰው ሲከብር፥ ያቆሰልነው ሰው ሲፈወስ፥ ያጠመድነውና ያስጠመድነው ሰው ከወጥመድ ሲያመልጥ፥ የጠላነው ያስጠላነው ሰው ሲወደድ፥ ቤት መኪና ያልነበረው ሰው እንደ እኛ ባለቤት ባለ መኪና ሲሆን ፥ በውጭው ዓለም የመኖሪያ ፈቃድ አጥቶ የተቸገረ ሰው እንደ እኛ መኖሪያ ፈቃድ ሲያገኝ፥ እንረዳው የነበረ ሰው ራሱን ሲችል ነው። የኰንትሮባንድ ነጋዴ የሚበሳጨውና የሚያዝነው ኬላ ላይ የእርሱ ተይዞ ስለተወረሰበት ሳይሆን የባልንጀሮቹ በተለያየ ምክንያት ሳይወረስ በመቅረቱ ነው። በአጠቃላይ አነጋገር በኃጢአታችንና እና በሰው ጉዳት የምንደሰት ሰዎች ነን። መመሪያችን እኔ ልደሰት ፥ ልሳቅ ፥ ይድላኝ ፤ ሌላው ግን ይዘን፥ ያልቅስ፥ ይጐስቁል ነው። እኔ ወርቅ ልልበስ ፥ ሌላው ግን አፈር ይልበስ ነው። ለአንድ አፍታ እንኳን ምድራዊው ነገር ሁሉ ሃላፊ ጠፊ መሆኑ ትዝ አይለንም። «ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ፥ ነፍሱንም ቢያጣ፥ ለሰው ምን ይረባዋል?» የሚለውን የጌታችንን ቃል የምናውቀው በጥቅስ ብቻ ነው። ማቴ ፲፯፥፳፮። ከእንግዲህ ግን እንደቃሉ ለመኖር እንጣር። እኛ ጥቂት ስንጥር እግዚአብሔር በብዙ ይረዳናል። እንደ ራሄል ወደ ሰማይ የሚወጣ እንባ ይሰጠናል። ኀዘናችን ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ ግዳጅ የሚፈጽም ይሆናል። የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን።
 

«የሚጐድለኝ ምንድር ነው»? ማቴ ፲፱ ፥ ፳።

          የጉድለት ነገር ሲነሣ ሁልጊዜ ትዝ የሚለን በኃላፊው ጠፊው ዓለም በሥጋ የሚጐድለን ብቻ ነው። ያማረ ቤት ፥ አዲስ መኪና ፥ ተርፎ በባንክ የሚቀመጥ ገንዘብ ፥ ወለል ብሎ ይታየናል። ራሰ በራው ትዝ የሚለው ጠጉር ነው። አቅሙ ካለው ጠጉር የሚያበቅል መድኃኒትና ሐኪም ያፈላልጋል። የረገፈ ጠጉሩ የተመለጠ ራሱ ሁሌ ያሳስበዋል። ትልቅ ነገር የጐደለበት ፥ ከሰው በታች የሆነ ይመስለዋል። የአፍንጫ ፥ የጥርስ ፥ የከንፈር ነገር የሚያሳስበውም አለ። የቁመቱ ማጠር ወይም መንቀዋለልም የሚያስጨንቀው ብዙ ነው። ባለማግባቱ የሚያማርር ፥ አግብቶም ልጅ ባለመውለዱ መፈጠሩን የሚረግም ብዙ ነው። ለመሆኑ እንደ ጉድለት የቆጠርነው ይህ ሁሉ ቢሟላልን እናመሰግን ይሆን? ባማረ ቤት ተቀምጠው ፥ ዘመናዊ መኪና እየነዱ ፥ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየመነዘሩ ፥ መልከ መልካም ተብለው የተደነቁ ፥ በመንፈሳዊውም በሥጋዊውም በእውቀት የመጠቁ ነገረ ግን በሐዘን ተጨብጠው ፥ በእንባ ተነክረው የሚኖሩ ብዙ ናቸው። ከዚህም አልፈው ራሳቸውን እስከ ማጥፋት የደረሱ ጥቂት አይደሉም። እግዚአብሔርን በዓለም መለወጥ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውምና። ስለሆነም ዓለም ጥላዋን ጥላብን የጠቆርን ፥ መንፈሳዊው መልካችን የጠፋብን ፥ ወደ ዓለም ዞረን የምንጸልይ ፥ ዓለምን የምናመልክ ሁሉ በሥጋ ሳይሆን በነፍስ «ምን ይጐድለናል?» ልንል ይገባናል። የነፍሳችን ከተሟላ የነፍስ በረከት ለሥጋ ይተርፋልና።
   አንድ ወጣት ባዕለጸጋ ወደ ጌታችን መጥቶ፦ «ቸር መምህር ሆይ ፥ የዘለዓለምን ሕይወት እወርስ ዘንድ ከበጎ ሥራ ወገን ምን ላድርግ?» አለው። እርሱም፦ «ለምን ቸር ትለኛለህ ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ቸር የለም፤ » አለው። « ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ። . . .  ያም ቃል ሥጋ ሆነ ፤ ( ከድንግል ማርያም የነሳውን ሥጋና ነፍስ ተዋሕዶ ሰው ሆነ ) ፤ » እንዲል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው። ዮሐ ፩ ፥ ፩። ስለሆነም ቸር ነው ፥ ቸር መባልም ይገባዋል። ታዲያ ለምንድን ነው ወጣቱን ባዕለጸጋ « ለምን ቸር ትለኛለህ ?» ያለው ፥ እንል ይሆናል። ጌታችን እንዲህ ማለቱ ስለሁለት ነገር ነው። አንደኛው ፦ « የባህርይ አምላክ መሆኔን ሳታምን ለምን ቸር ትለኛለህ? » ሲለው ነው። ሁለተኛውም ይህ ሰው ውዳሴ ከንቱ ሽቶ (ፈልጐ) በተንኰል የመጣ ሰው ነው። አመጣጡ ፦ « እኔ ቸር ስለው ፥ እርሱም አንተም ቸር ነህ ፤ » ይለኛል ብሎ ነው። ቅዱስ ዳዊት ፦ « እግዚአብሔር ልቡናን እና ኲላሊትን ይመረምራል። » እንዳለ ፥ እርሱ ልብ ያሰበውን ፥ ኲላሊት ያጤሰውን ያውቃል። መዝ ፯ ፥ ፱። ቅዱስ ዮሐንስም  ፦ ጌታችን ኢየሱስም በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ ብዙ ሰዎች ያደረገውን ተአምራት ባዩ ጊዜ አመኑ። እርሱ ጌታችን ግን አያምናቸውም ነበር ፥ ሁሉን እያንዳንዱን ያውቀዋልና ። የሰውንም ግብሩን ሊነግሩት አይሻም ፥ እርሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና።» ብሏል። ዮሐ ፪ ፥፳፫ ። ይህን ሰው « ቸር መምህር ሆይ » ፥ ሲል ላየው ፥ ለሰማው ሰው ፍጹም አማኝ ይመስላል። ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ላየን ፥ ለሰማን ሁሉ አማኝ የምንመስል በእርሱ ዘንድ ግን ከምእመናን (ከአማኞች) የማንቆጠር ብዙ ሰዎች አለን። የአምልኮት መልኩ ፥ ቅርጹ እንጂ ይዘቱ የለም። « ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚመርጡ ይሆናሉ። የአምልኮት መልክ አላቸው ፥ ኃይሉን ግን ይክዱታል ፤ » እንዳለ ።፩ኛ ጢሞ ፫ ፥ ፬።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፦ ልባቸውንም አፋቸውንም አንድ አድርገው የሚያምኑትን ምስጋና እንጂ ውስጣዊ እምነት የሌላቸውን ሰዎች መዝሙር ፥ ውዳሴ ፥ ቅዳሴ ፥ እንደማይቀበል ከተናገረ በኋላ ፦ « ወእመሰ ትፈቅድ ትባእ ውስተ ሕይወት ፥ ዕቀብ ትእዛዛተ ፤ ወደ ሕይወት ልትገባ ( የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያትን ልትወርስ ) ብትወድድስ ትእዛዛትን ጠብቅ ፤ » ብሎታል። ምክንያቱም ፦ « ሕጉ ቅዱስ ነው ፥ ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናትና » ሮሜ ፯ ፥፲፪። ቅዱስ ዳዊትም ፦ «የእግዚአብሔር ሕግ ንጹሕ ነው ፥ ነፍስንም ይፈውሳል . . . . . የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው ፥ ልብንም ደስ ያሰኛል፤የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩኅ ነው ፥ ዓይኖችንም ያበራል።» ብሏል።» መዝ ፲፰ ፥ ፰። « ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል።» ያለውም ለዚህ ነው። መዘ ፩፻፲፰ ፥ ፸፪ ።
          ወጣቱ ባዕለጸጋ ሕጉን እንዲያከብር ፥ ትዕዛዙን እንዲጠብቅ በተነገረው ጊዜ ፦ « የትኞቹን?» ሲል ጠየቀ። ጌታም ፦ አትግደል ፥ አታመንዝር ፥ አትስረቅ ፥ በሐሰትም አትመሰክር ፥ አባትህንና እናትህን አክብር ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ ።» አለው። ጐልማሳውም ፦ « ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄያለሁ ፥ እንግዲህ የሚቀረኝ (የሚጐድለኝ) ምንድነው?» በማለት በኲራት ጠየቀ።ይህ ወጣት ከትናንት እስከ ዛሬ (ከሕፃንነት እስከ ወጣትነት) ያለውን ተናገረ እንጂ ነገ ምን እንደሚሆን አያውቀውም። አብዛኛው ሰው ወጣትነት እስከሚጀምረው ድረስ ሕጉን ለማክበር ፥ ትእዛዙን ለመጠበቅ አይቸገርም። የሚቸግረው ወጣትነት ጓዙን ጠቅልሎ ሲመጣ ነው። የወጣትነት ጓዝ ደግሞ ክፉ ምኞት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ፦ «ከክፉ የጐልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል ።» ያለው ለዚህ ነው። ፪ኛ ጢሞ ፪ ፥፳፪ ።
          በተለይም የእሳትነት ዘመን (ወጣትነት) እና ገንዘብ ሲገናኙ ከባድ ነው። የሥጋ ፍላጎት በሚበዛበትና በሚያይልበት በወጣትነት ዘመን እንደልባችን የምናዝዘው ፥ ብዙ ገንዘብ ካለ ካላወቁበት በእሳት ላይ ጭድ ማለት ነው። « እድሜ ለገንዘቤ ፥» ወደ ማለት ገንዘብን ወደ ማምለክ ይኬዳል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ በገንዘብ የማይሠራ ኃጢአት ፥ ለገንዘበ ተብሎ የማይፈጸም ወንጀል የለም። ሃይማኖትንም ያስክዳል። ቅዱስ ጳውሎስ « ዳሩ ግን ባለጠጋ ሊሆኑ የሚፈልጉ ፥ በጥፋትና በመፍረስ ፥ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙም  ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ (ማምለክ) የክፋት ሁሉ ሥር ነውና ፥ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው (ሃይማኖታቸውን ለውጠው) በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ ። » እንዳለ። ፩ኛ ጢሞ ፮ ፥ ፱።
          ይህ ወጣት ባዕለጸጋ ሕጉን እያከበረ ፥ ትእዛዙን እየጠበቀ ካደገ በኋላ ፥ በልቡናውም የዘለዓለምን ሕይወት እየፈለገ በሀብት ምክንያት እንዳይጠፉ « ፍጹም ልትሆን ብትወድስ ፥ ሂድና ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድሆች ስጥ ፥ ሰማያው ሀብትንም ታገኛለህ ፥ መጥተህም ተከተለኝ። (በግብር ምሰለኝ)።» ተብሏል። እርድና (ረድእነት) ከምጽዋት ታዝዟል። ምክንያቱም ለነዳያን ፈረስ በቅሎ ፥ በሬ ላም ቢሰጧቸው ወጥቶ ወርዶ መሸጥ ስለማይሆንላቸው ባገኙት ዋጋ ይጥሉታል። ባሌቤቱ ግን የሀብቱን የከብቱን ዋጋ ስለሚያውቅ በዋጋው ይሸጠዋልና ለዚህ ነው። ወጥቶ ወርዶ መሸጥ መለወጥ ረድእነት ሲሆን ሳይነፍጉ መስጠት ደግሞ ምጽዋት ነው።
          «ወሰሚዖ ወሬዛ ዘንተ ነገረ ወሖረ እንዘ ይቴክዝ ፥ እስመ ብዙኅ ጥሪቱ ። ጐልማሳውም ይህን ነገር ሰምቶ ሀብቱ ብዙ ነበርና እያዘነ ሄደ። » እንደ ቅዱስ ዳዊት ፦ «ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል፤ » ማለት አልቻለም። እንደ ሣፋጥ ልጅ እንደ ኤልሳዕ ሀብቱን ፥ መሬቱን ፥ ንብረቱን ትቶ መከተል አልቻለም። ፩ኛ ነገ ፲፱ ፥ ፲፱ ። እንደ ሙሴ ከብዙ ገንዘብ ይልቅ ክርስቶስን መምረጥ አልሆነለትም። ዕብ ፲፩ ፥ ፳፭፦ «እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።» እንዳለ ራሱን መካድ ( ፈቃደ ሥጋውን ለፈቃደ ነፍሱ ማስገዛት) ከበደው። ማቴ ፲፮ ፥፳፭። መቼም ጥያቄው በራሱ ሰማዕትነትን የሚጠይቅ ነው። ጽድቅ፦ ሀብት፥  ንብረትን መተው ብቻ ሳይሆን ሕይወትንም ጭምር መተው (ነፍስን አሳልፎ መሰጠትን) ይጠይቃልና።
          ይህስ ሰው አቅሙን አውቆ ገና በጧቱ አዝኖ ተመልሷል። ሁለን ትቼ መከተል አይሆንልኝም ብሏል። ክርስትና ማለት ሁሉን ትቶ የክርስቶስ ተከታይ መሆን ፥ እርሱን በግብር መምሰል ማለት ነውና። ለመሆኑ ተከትለነዋል የምንል ሰዎች ፥ «ተዉ» ፥ የተባልነውን ትተን ነው የተከተልነው ወይስ ዛሬም እስከነሸክማችን ነን? አልሰማንም እንዳንል ፥ ሃያ ሠላሳ ዓመት ሰምተናል። ከመስማትም አልፈን « ጆሮ ያለው ይስማ፤» እያልን የምንጮህ ሰዎች ሆነናል። ዳሩ ግን የዕውቀት እንጂ የሕይወት ሰዎች መሆን ተስኖናል።
          የሚታየን የሰው ጉድለት እንጂ የራሳችን አይደለም። ቃሉ «እንዳይፈርድባችሁ አትፍረዱ። (ንጹሕ ሳትሆኑ አትፍረዱ)። በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋልና ፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋልና። በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ (ትንሹን ኃጢአት) ለምን ታያለህ? በአንተ ዓይን ያለውን ምሶሶ (ታላቁን ኃጢአትህን) ግን አታስተውልም? ወንድምህን በዓይንህ ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ ተወኝ እንዴት ትለዋለህ? (በኃጢአትህ ልፍረድብህ ለምን ትለዋለህ)? እነሆ ፥ በአንተ ዓይን ምሶሶ አለ። (በሰውነትህ ታላቅ ኃጢአት ተሸክመሃል)። አንተ ግብዝ አስቀድመህ በአንተ ያለውን ምሶሶ አውጣ ፥ (በመጀመሪያ ስለ ታላቁ ኃጢአትህ ፥ ስለበዛው ጉድለትህ በራስህ ላይ ፍረድ) ፥ ከዚህ በኋላ በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።» እያለን ወደ ራሳችን መመልከት ፥ ጉድለታችንን ማየት አልተቻለንም። ማቴ ፯፥፩። ጌታችን የወንድምን ኃጢአት በጉድፍ ፥ የራስን ኃጢአት በምሶሶ ፥ በሰረገላ መስሎ ያስተማረው የባልንጀራችንን ኃጢአት የምናውቀው ጥቂቱን ስለሆነ ነው። የራሳችንን ግን ከራሳችን ጠጉር ቢበዛም ሁሉንም እናውቀዋለንና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ፦ « አንተ ሰው ሆይ ፥ እውነት ለሚፈርደው ለእግዚአብሔር ምን ትመልሳለህ? በወንድምህ ላይ የምትጠላውን ያን ሥራ አንተ ራስህ ከሠራኸው በራስህ የምትፈርድ አይደለምን? አንተ ራስህ ያን ሥራ ትሠራዋለህና . . . . . አንተ ሰው ሆይ ፥ በሌላ ላይ አይተህ የምትጠላውንና የምትነቅፈውን ያን አንተ ራስህ የምትሠራው ከሆነ ፥ ከእግዚአብሔር ፍርድ እንደምታመለጥ ታስባለህን? »ብሏል። ሮሜ ፪፥፩-፫፦ እኛስ የሚጐድለን ምንድነው?
፪ ፦ እምነት ይጐድለናል፤
          የሰው እምነቱ በማግኘትም በማጣትም ፥ በደስታም በኀዘንም ይፈተናል። ጠቢቡ ሰሎሞን «ሁለትን ነገር ከአንተ እሻለሁ ፥ ሳልሞትም አትከልክለኝ ፤ ከንቱነትንና ሐሰተኝነትን ከእኔ አርቃቸው ፤ ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ ፤ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ፥ እንዳልጠግብ እንዳልክድህም ፦ እግዚአብሔርስ ማን ነው? እንዳልል፤ ድሃም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም ፥ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል።» በማለት እግዚአብሔርን የለመነው ለዚህ ነው። ምሳ ፶ ፥ ፯። ጌዴዎንን የሰባቱ ዓመት መከራ ፦ «ጌታዬ ሆይ ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው የነገሩን ተአምራቱ ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል ፥ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል፤» አሰኝቶታል።  ይህንንም ያለው፦ መልአከ እግዚአብሔር «እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤» እያለው ነው። መሳ ፮ ፥፲፫። ስምዖን ጴጥሮስ ጌታው ና እያለው ፥የነፋሱን ኃይል አይቶ በመፍራቱ ፥ መስጠምም በመጀመሩ ፦ «አንተ እምነት የጐደለህ ለምን ተጠራጠርህ? » ተብሏል። ማቴ ፲፬ ፥፴። ደቀመዛሙርቱም በታንኳ ከጌታቸው ጋር እየተጓዙ በነበረበት ሰዓት የማዕበሉ ኃይል ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ ፥ በባሕር ታላቅ መናወጥ በመሆኑ ፥ ተስፋ ቆርጠው፦ « ጌታ ሆይ ፥ አድነን ፥ ጠፋን፤ » እያሉ ጮኸው ነበር። በዚህም ምክንያት ፦ እናንተ እምነት የጐደላችሁ ፥ ስለምን ትፈራላችሁ?» ተብለዋል። ማቴ ፰፥፳፮። ከደብረ ታቦር በወረደም ጊዜ ፦« የማታምን ጠማማ (እምቢተኛ ፥ አሉተኛ) ትውልድ ሆይ ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? (ዝም እላችኋለሁ)? በማለት ገሥጿቸዋል። እነርሱም ተግሣጹን ተቀብለው፥ ብቻቸውን ወደ እርሱ ቀረቡና፦ «ጋኔኑን እኛ ልናወጣው ያልቻልነው ለምንድነው?» ብለው ጠየቁት። እርሱም፦ «ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤» አላቸው። ማቴ ፲፯ ፥፲፬-፳።
          እምነታችንን ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ፥ በገድላት ፥ በተአምራትና በድርሳናት ከተጻፉት የእምነት ታሪኮች አንፃር ስናየው ባዶ ሆኖ ነው የምናገኘው። በቅርብ ከሚገኙት የወላጆቻችን እምነት ጋር እንኳ ስናስተያየው የእኛን አምነት አለ ለማለት ያስቸግራል። ስለዚህ በደስታ ጊዜ እምነታችንን የዘነጋን ፥ በሀዘንም ጊዜ ፈጥነን ተስፋ የቆረጥን ሰዎች ፥ ስለ እምነት እውቀቱ እንጂ ሕይወቱ የሌለንም ሁሉ ፦ « አለማመኔን እርዳው ፤» ልንለው ይገባል። ማር ፱፥፳፬። የዘወትር ጸሎታችንም « እምነት ጨምርልን ፤» መሆን አለበት። ሉቃ ፲፯ ፥ ፭።
          በሌላ በኲል ደግሞ በዚህ ዓለም መናፍቃንና አሕዛብ ሲከናወንላቸው እያየን ፥ እየሰማን ውስጣችን የሚደክምብን ሰዎች አለን። ቅዱስ ዳዊት ፦ «እኔ ግን እግሮቼ ሊሰናከሉ ፥ አረማመዴም ሊወድቅ ጥቂት ቀረ። የዓመጸኞችን ሰላም አይቼ በኃጢአተኞች ላይ ቀንቼ ነበርና ፤» እንዳለ። መዝ ፸፪ ፥፪። ከዚህም በላይ «በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁአትን? እጆቼን በንጽሕና በከንቱ አጠብሁ። ሁልጊዜም የተገረፍሁ ሆንሁ ፥ መሰደቤም በማለዳ ነው። » ብሏል። በመጨረሻ ግን ፦ « በድጥ ሥፍራ አስቀመጥኻቸው ፥ ወደ ጥፋትም ጣልኻቸው። እንዴት ለጥፋት ሆኑ! በድንገት አለቁ ፥ ስለ ኃጢአታቸውም ጠፉ። ከሕልም እንደሚነቃ ፥ አቤቱ ፥ስትነቃ ምልክታቸውን ታስነውራለህ።» በማለት አድንቋል። መዝ ፸፪ ፥፲፫፥፳።
          በቤተ ክርስቲያን እየኖርን ፦ በመጸለይና ባለመጸለይ ፥ በመጾምና ባለመጾም ፥ ንስሐ በመግባትና ባለመግባት ፥ በማስቀደስና ባለማስቀደስ ፥ በመቁረብና ባለመቁረብ ፥ መስቀል በመሳለምና ባለመሳለም ፥ ጠበል በመጠጣትና ባለመጠጣት ፥ በመጠመቅና ባለመጠመቅ ፥ ቃሉን በመስማትና ባለመስማት ፥ በመዘመርና ባለመዘመር ፥ አሥራት በማውጣትና ባለማውጣት መካከል ልዩነቱ እየጠፋብን የሄደው እምነታችን እየጐደለ በመሄዱ ነው። ድሮ ድሮ ያላስቀደስን ዕለት ያመን (ይሰማን) ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን ምንም አይመስለንም። ውዳሴ ማርያሙ ፥ ዳዊቱ ያልተደገመ ዕለት ቀኑን ሙሉ መንፈሳችን ይታወክብን ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን ምንም የቀረብን አይመስለንም። እየቀረብን ፥ እየተጠጋን በመጣን ቁጥር እንደመበርታት እየደከምን መጥተናል። ድፍረቱም በዚያው ልክ ነው። የዔሊ ልጆች አፍኒን እና ፊንሐስ በእግዚአብሔር ማደሪያ በደብተራ ኦሪት እያገለገሉ እግዚአብሔርን አያውቁም ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፪፥፲፪። በቅድስናውም ስፍራ ያመነዝሩ ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፪፥፳፪። ማንኛውም ሰው እምነት ሲጐድለው እንዲህ ነው ፥ ፈሪሃ እግዚአብሔር አይኖረውም። እምነቱ ሙሉ የሆነ ዮሴፍ ግን በአሕዛብ ምድር ሆኖ እግዚአብሔርን ፈራ። የጌታው ሚስት ፦ ብእሲተ ጲጥፋር የሚያየን ሰው የለምና እንስረቅ ባለችው ጊዜ፦ «በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?» አለ። ዘፍ ፴፱ ፥ ፱። ለመሆኑ ከሰው ተሸሽገን በየጓዳው በየጐድጓዳው በእግዚአብሔር ፊት ስንት ኃጢአት ሠርተን ይሆን? «እኛን በሚቈጣጠር በእርሱ በዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው እንጂ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።» የሚለውን እናውቀዋለን። ዕብ ፬፥፲፫። ነገር ግን አልኖርንበትም። እንዲህ ሲሆን እምነት እየጐደለ ብቻ ሳይሆን እየሞተም ይሄዳል። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ፦ «ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው፤» ብሏልና። ያዕ ፩፥፲፯። በአጠቃላይ ፦
፪፥፩፦ ጸሎታችን እምነት ይጐድለዋል፤
          የምንጸልየው በመንታ ልብ በሁለት ሐሳብ ነው። «ጥበብን ያጣት ሰው ቢኖር ፥ ሳይነቅፍና ሳይነፍግ ለሁሉ በልግስና የሚሰጥ እግዚአብሔርን ይለምን ፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን አምኖ ይለምን ፥ አይጠራጠርም (ሳይጠራጠር ይለምን) ፤ የሚጠራጠር በንፋስ የሚገፋና የሚነዋወጥ የባሕር ማዕበልን ይመስላልና። ለዚያ ሰው ከእግዚአብሔር ምንም የሚያገኝ አይምሰለው። ሁለት ልብ የሆነ ሰው በመንገዱ ሁሉ ይታወካልና። » ያዕ ፩ ፥ ፭-፰።
፪፥፪ ጾማችን እምነት ይጐድለዋል፤
          የምንጾመው ቅዱስ ያሬድ ፦ «ይጹም ዓይን ፥ ይጹም ልሳን ፥ዕዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ኅሡም በተፋቅሮ ፤ » እንዳለው አልሆነም። በእምነት ልንጾማቸው የሚገባቸውን አጽዋማት የልማድ አድርገናቸዋል። ከእህል ከውኃ እንጂ ከኃጢአት ከበደል አልተከለከልንም። «ነገር ግን ጽድቅን እንደሚያደርግ የአምላኩን ፍርድ እንደማይተው ሕዝብ ዕለት ዕለት ይሹኛል ፥ መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ። አሁንም እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል ፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ። ስለምን ጾምን? አንተም አልተመለከትኸንም ፣ ሰውነታችንንስ ለምን አዋረድን? አንተም አላወቅኸንም ፥ ይላሉ። እነሆ ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ ፥ ሠራተኞቻችሁንም ታስጨንቃላችሁ። እነሆ ፥ ለጠብና ለክርክር ትጾማላችሁ።» ኢሳ ፶፰፥፪-፬።
፪፥፫፦ ምጽዋታችን እምነት ይጐድለዋል ፤
          ምጽዋት « አባታችሁ ርኅሩኅ እንደሆነ ርኅሩኆች ሁኑ፤» እንዳለ ፈጣሪያችንን የምታስመስለን ጸጋ ናት። ሉቃ ፮፥፴፮። የእኛ ግን ነገራችን ሁሉ የውዳሴ ከንቱ ነው። «ለእገሌ እንዲህ አድርጌለት ፥ ለእገሊትም እንዲህ ሠርቼላት ፥» ማለት ይቀናናል። ያየ የሰማ ፥ የተሰማማ ሁሉ « ቅዱስ ፥ ቅዱስ » እንዲለን እንፈልጋለን። የተነገረው ፦ « መልካሙን ሥራችሁን አይተው ፥ በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑት ዘንድ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።» የሚል ነበር። ማቴ ፭፥፲፮። «ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ፥ ምጽዋታችሁን በሰዎች ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው በአባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም።» ማቴ ፮፥፩
፪፥፬፦ አገልግሎታችን እምነት ይጐድለዋል፤
          በቤተ መቅደስ ፥ በቅኔ ማኅሌት ፥ በዓውደ ምሕረት ፥ (በስብከት ፥ በመዝሙር) ፥ በሰበካ ጉባኤ ፥ በሰንበት ት/ቤት ፥ በማኅበር የምናገለግል ሰዎች ሩጫችን ሁሉ የእምነት አይመስልም። ከሥጋ ጥቅም ወይም ከዝና ጋር የተቆራኘ ነው። ሰው አገልግሎ በሥጋው አይጠቀም ወይም በጸጋው አይታወቅ ማለት አይደለም። ምክንያቱም ፦ « እህልን በምታበራይበት ጊዜ በሬውን አፉን አትሰረው ፥ ለሚሠራም ደመወዙ ይገባዋል ይላልና።» ፩ኛ ጢሞ ፭፥፲፰ ፣ ዘዳ ፳፭፥፬ ፣ ማቴ ፲፥፲። በተጨማሪም «ከቶ በገዛ ገንዘቡ ወታደርነት የሚያገለግል ማነው? ወይስ መንጋ እየጠበቀ ከመንጋው ወተት የማይጠጣ ማነው? ይህን በሰው ሥልጣን ብቻ እላለሁን? ሕግስ ደግሞ ያን አይልምን? የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር ተብሎ ተጽፎአልና። እግዚአብሔርስ ስለበሬዎች ይገደዋልን? ይህን የሚለው ፈጽሞ ስለ እኛ አይደለምን?. . . . . እኛ መንፈሳዊውን ነገር የዘራንላችሁ ከሆንን የእናንተን የሥጋዊን ነገር ብናጭድ ትልቅ ነገር ነውን? ሌሎች በእናንተ ላይ ይህን መብት የሚካፈሉ ከሆነ እኛማ ይልቁን እንዴታ?» የሚል አለ። ፩ኛ ቆሮ ፱፥፯-፲፪። ነገር ግን ዓላማችን ጽድቅ ይሁን ፥ በሩን ይዘን እንቅፋት አንሁን ለማለት ነው። አለበለዚያ ጻፎችና ፈሪሳውያን በተመቱበት በትር እንመታለን። ጌታ በወንጌል ፦ « እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳዊያን መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ፥ ወዮላችሁ፤ እናንተ አትገቡም ፥ የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።» እንዳለ። ማቴ ፳፫፥፲፫።
ከዚህም ሁሉ ጋር ትኅትና ፥ ትዕግሥት ፥ ቸርነት ፥በጎነት ፥ የዋሃት ፥ ራስን መግዛት ፥ ፍቅር ፥ ደስታ ፥ ሰላም ይጐድለናል።እነዚህም ፈቃዳተ ነፍስ ናቸው። ገላ ፭፥፳፪ ። እንዲህም ማለታችን በሚበዛው መናገራችን እንጂ አራቱ ባህርያተ ሥጋ የተስማሙላቸው ፥ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ፥ ለፈቃደ ነፍስ አድልተው የሚኖሩ የሉም ማለት እይደለም። በከተማም በገጠርም ፥ በደብርም በገዳምም እግዚአብሔር የሚያውቃቸው ከዋክብት አሉ። በሰውም ዘንድ የሚታወቁ አሉ። ስለዚህ ፦ እገሌ ፥ እነ እገሌ ምን ይጐድላቸዋል ? ሳይሆን እኔን የሚጐድለኝ ምንድነው? እንበል። የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን ፥ አሜን።
 

የራሔል እንባ

          « እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የኀዘን የልቅሶና የጩኸት ድምጽ በራማ ተሰማ ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ድምጽሽን ከለቅሶ ዐይኖችሽንም ከእንባ ከልክዩ ፤ ለሥራሽ ፤ ዋጋ ይሆናልና ፥ ይላል፡፡ እግዚአብሔር ፤ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ። ለፍጻሜሽም ተስፋ አለ ፥ ይላል እግዚአብሔር ፥ ልጆችሽም ወደ ሀገራቸዎ ይመለሳሉ። » ኤር ፴፮ ፥፲፭ ፡፡
          ቅዱሳን ነቢያት የሚናገሩት ስለ ዘመናቸው ብቻ አይደለም ፤ ከዘመናቸው ጋር በማገናዘብ ስላለፈው ይናገራሉ ፥ ስለሚመጣውም ይተነብያሉ። ዓረፍተ ዘመን ሳይገታቸው ኃላፊያትንም መጻእያትንም ይተረጉማሉ። በመሆኑም ይህ ቃለ ኤርምያስ  ወደኋላም ወደፊትም የሚሠራ ነው። ለጊዜው እስራኤል ዘሥጋ በግብጽ የባርነት ዘመን የነበሩበትን ዘመን ያስታውሳል ፥ ለፍጻሜው ደግሞ በዘመነ ሥጋዌ መባቻ ማለትም መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ የተፈጸመውን ያሳያል።
      እስራኤል በባዕድ ሀገር በግብፅ በዮሴፍ ስም ተወደው ተከብረው ይኖሩ ነበር፡፡ በኋላ ግን ዮሴፍን የማያውቅ ፥ አንድም ደግነቱን ጥበቡን የማያውቅለት ንጉሥ ተነሥቶ ቀንበር አጠበቀባቸው። ይኸውም፦ የእሥራኤል ልጆች ፈጽመው በዝተዋል ፥ ከእኛ ም እነሱ ይጸናሉ ፥ ወደፊት ጠላት ቢነሣብን ከእነርሱ ወገን ተሰልፈው ይወጉናል ፥ አንድም ከበዙ ዘንድ አገራችንን ያስለቅቁናል። ብሎ ገና ለገና ፈርቶ ነው። ፈሪ ሰው ጨካኝ በመሆኑም፦ « ኑ ብልሃት እንሥራባቸው ፤ ጡብ እናስጥላቸው ፥ ኖራ እናስወቅ ጣቸው ፥ ጭቃ እናስረግጣቸው ፤ ይህን ሲያደርጉ ከዋሉ ልሙዳነ ፀብእ አይሆኑም ፥ አንድም ከድካም ብዛት ከሚስቶቻቸው አይደርሱም ፥ ካልደረሱም አይባዙም ፥ ካልበዙም አኛን አያጠፉም ፤ » አለ። ይኽንንም ብሎ አልቀረም። በብዙ ማስጨነቅ ፌቶም ፥ ራምሴንና ዖን የተባሉ ጽኑ ከተሞችን በግንብ አሠራቸው።
  
እስራኤል ዘሥጋ መከራ የሚያጸኑባቸውን ያህል እንደ መከራው ብዛት  እየበዙ ይጸኑ ነበር። ግብጻውያን ግን የእሥራኤልን ልጆች ያስመርሯቸው ፥ እየገፉ እያዳፉ በግፍዕ ይገዟቸው ነበር፡፡ በሕይወት መኖርን በሚያሰቅቅ ሥራ ሰውነታቸውን ያስጨንቋት ነበር። ከዚህም ሌላ ንጉሥ ዓቀብተ መወልዳትን ( አዋላጆችን ) ሾሞባቸዋል፡፡ እነርሱንም « ዕብራውያትን ሴቶች ስታዋልዱ ለመውለድ እንደደረሱ በአያችሁ ጊዜ ፥ ወንድ ቢሆን ግደሉት ፤ ሴት ብትሆን ግን አትግደሏት ፤ » አላቸው። እነርሱ ግን እግዚአ ብሔርን ፈርተው እንዳዘዛቸው አላደረጉም። ንጉሡም ጠርጥሮ አንድም ከነገረ ሰሪ ሰምቶ ፦ « ለምን ያዘዝኳችሁን አልፈጸ ማችሁም ? » ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ምክንያቱም ወንድ ልጅ ተወልዶ ከሦስት ወር በኋላ ሲያለቅስ ፥ ሲያነጥስ በድምጹ ይታወቃልና ነው።  ሴቶች ምክንያት አያጡምና ( ብልሆች ናቸውና )፦ « የዕብራ ውያን ሴቶች እንደ ግብፃውያን ሴቶች አይደሉም ፥ አዋላጅቱ ሳትመጣ ወልደው ይቆያሉ ፤ » ብለው መለሱለት። እነርሱ ለእስራኤል በጐ ነገር በማድረጋቸው ፥ እግዚአብሔር ለእነርሱም በጐ አደረገላቸው ፤ ንጉሡ እንዳይገድላቸው አደረገ። ( የንጉሥ ትእዛዝ መተላለፍ ያስገድላልና )። ከፍ ብሎ በእግዚአብሔር ቸርነት ፥ ዝቅ ብሎ በአዋላጆች ደግነት እሥራኤል እጅግ በዝተው በረቱ። ያንጊዜም ፈርዖን ተቆጥቶ « ከዕብራውያን የሚወለደውን ወንድ ወንዱን ከፈሳሽ ውኃ ጣሏቸው ፥ ሴት ሴቱን ግን በሕይወት ተዉአቸው ፤ » የሚል አዋጅ አናገረባቸው።
   
 
          የእንባ ሰው ራሔል የነበረችው በዚህ ዘመን ነው። ሮቤልም ስምዖንም የሚባል ባል ሞቶባት ሐዘንተኛ ነበረች። እርሱ ሲሞት ነፍሰ ጡር ብትሆንም « በእርሱ ምትክ ኖራ ውቀጪ ፥ ጭቃ ርገጪ፤ » ተባለች። መንታ ፀንሳ ኑሮ ደም ፈሰሳት ሕፃናቱም ወጥተው ፥ ወጥተው ፥ ከጭቃው ወደቁ ። ደንግጣ ብትቆም ፥ ምን ያስደነግጥሻል ? የሰው ደም ፥ የሰው ሥጋ ጭቃውን ያጸናዋል እንጂ ምን ይለዋል ብለሽ ነው? ርገጪው ፤ » አሏት ፡፡ በዚህን ጊዜ ነው ፥ « ኢሀሎኑ በዝ ሰማይ አምላከ እሥራኤል ፤ በውኑ በዚህ ሰማይ የእስራኤል አምላክ የለምን ?» ብላ እንባዋን ያፈሰሰችው። ይኽንንም እንባ በእፍኟ እየሰፈረች ወደ ላይ ረጨችው። «እንደገናም ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፤» እንዲል ፤ ኢሳ ፳፭ ፥ ፰ ፤ እንባን የሚያብስ እግዚአብሔር በሰማይ እንዳለ ታምናለችና። እንባዋ ወደ ምድር አልተመለሰም ፥ ከመንበረ ጸባዖት ደረሰ እንጂ ። « ወዐበየት ተናዝዞ ወነጊፈ ላህ ፤ ልቅሶ መተውን መጽናናትን እንቢ አለች።» ምክንያቱም ግፉ ያሳዝናልና ፥ የሕፃናቱ ሞት የፃር ነውና ፥ ሐዘን በየደጁ ኹኗልና፡፡ « እስመ ኢኮንዋ ውሉዳ ውሉደ ፤ ልጆቿ ልጆች አልሆኗትምና ፥» ሙተዋልና ፥ ባሌ ቢሞት በልጆቼ እጽናናለሁ። ያለችው ከንቱ ኹኖባታልና ። « ወኢሀለዉ በሕይወተ ሥጋ የለምና ፤» መጽናናትን እንቢ አለች፡፡ ይኽንን ነው ፥ ነቢዩ ኤርምያስ « የኀዘን የልቅሶና የጩኸት ድምፅ በራማ ተሰማ ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ፤ » ያለው።
          የራሔል እንባ እግዚአብሔር እንዲናገር ፥ በረድኤትም እንዲወርድ አድርጐታል። « ሰማዕኩ ገዓሮሙ ለሕዝብየ ፥ ወወረድኩ ከመ አድኅኖሙ ፤ የሕዝቤን ጩኸት ሰማሁ ፥ ላድናቸውም ወረድኩ ፤» አሰኝቶታል። « እግዚአብሔርም ሙሴን በግብፅ ያሉ የወገኖቼን መከራ አይቼ ፥ በሠራተኞች የተሾሙ ሹማምንት ካመጡባቸው መከራ የተነሣ ጩኸታቸውን ሰምቼ ፥ መጨነቃቸውን አውቄላቸዋለሁ። ከግብጻውያን እጅ አድናቸው ፥ ወደ ተወደደችም ሰፊ ወደምትሆን ወደ ከነዓንም እወስዳቸው ዘንድ ወረድኩ። ከግብፅም አውጥቼ ማርና ወተት ወደሚጐርፍባት ፥ ተድላ ደስታ ወደማይታጣባት አገር እወስዳቸዋለሁ ፤ » አለ። ማር ያለው ሕገ ኦሪትን ነው ፥ ማር የነካው ጨርቅ በውኃ ቢያጥቡት ፈጥኖ እንዲለቅ ሕገ ኦሪትም የሚለቅ ሕግ ነበርና። ወተት ያለው ደግሞ ሕገ ወንጌልን ነው። ወተት (ቅቤ) የነካው ጨርቅ በውኃ ቢያጥቡት እንደማይለቅ ሕገ ወንጌልም የማትለቅ ( ጸንታ የምትኖር ) ሕግ ናትና ። ዘጸ ፫ ፥ ፰ ፡፡
          በአዲስ ኪዳን ደግሞ ከላይ እንደጠቆምነው ፦ ጌታ በተወለደ ጊዜ የአይሁድ ንጉሥ የነበረ ሄሮድስን በግብር ፈርዖንን መስሎ እናገኘዋለን ፡፡ የሩቆቹ ወርቅ ዕጣንና ከርቤ ይዘው ፥ በኮከብ እየተመሩ ሁለት ዓመት ተጉዘው ሲመጡ የቅርቡ ሄሮድስ ግን ዜና ልደቱ አስደነገጠው ። ጥያቄያቸው ፦ « አይቴ ሀሎ ንጉሥ ዘተወልደ ፤ የተወለደው ንጉሥ ወዴት ነው ? » የሚል ነበርና ። ዓለም የሥልጣን ነገር ያሳስበዋል ፥ የደነገጠ አውሬም ያደርገዋል ። የደነገጠ አውሬ ማንንም እንደማይምር ዓለምም እንዲሁ ነው።
          ሄሮድስ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከሰብአ ሰገል በጥንቃቄ ከተረዳ በኋላ በልቡ ፦ «ለካ ያ ብላቴና ሁለት ዓመት ሆኖታል ፤» አለ። ካህናቱን በስውር ጠርቶ በተረዳውም መሠረት « ቤተልሔም ነው፤ » ብሎ ሰደዳቸው። ከዚህም ጋር ፦ « ሄዳችሁ የብላቴናውን  ነገር ጠይቃችሁ እርሱን ያገኛችሁት እንደሆነ እኔም እንድሰግድለት በእኔ በኲል ተመልሳችሁ ንገሩኝ፤ » አላቸው፡፡ እርሱ በሽንገላ ቢናገረውም ነገሩ ጥበበ እግዚአብሔር ነው። ሰብአ ሰገል፦ « ለካስ የሀገሩም ነገሥታት ያምኑበታልሳ ፤ » በሚል ሃይማኖታቸው እንዲጸናላቸው ነው ።
          ሰብአ ሰገል ግን ሳጥኖቻቸውን ከፍተው ወርቅ እጣን ከርቤ ለሕፃኑ ከገበሩለት በኋላ መልአኩ እንደነገራቸው በሌላ ጐዳና ፥ በሌላ ኃይለ ቃል ፥ በሌላ ሃይማኖት ተመልሰዋል ። በሌላ ጐዳና ሁለት ዓመት የተጓዙትን በአርባ ቀን ገብተዋል፡፡ በሌላ ኃይለ ቃል « ወዴት ነው?» እያሉ መጥተው ነበር ፥ « አገኘነው ፤ » እያሉ ተመልሰዋል፡፡ በሌላ ሃይማኖት « ምድራዊ ንጉሥ ፤» እያሉ መጥተው ነበር ፥ ሰማያዊ ንጉሥ ፥ የባሕርይ አምላክ » እያሉ ተመልሰዋል።
          ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደዘበቱበት  ( ባንተ በኩል እንመለሳለን ብለው በሌላ ጐዳና እንደሄዱ ) በሰማ ጊዜ ፈጽሞ ተበሳጨ። ጭፍራዎቹን ልኮ ከሰበአ ሰገል እንደተረዳው ዘመን ልክ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ፥ ከዚያም የሚያንሱትን  ፥ በቤተልሔምና በአውራጃዎችዋ ሁሉ የነበሩትን አሥራ አራት እልፍ ሕፃናት አስገደለ። ያን ጊዜ ፦ በነቢዩ በኤርምያስ ፦ « ራሔል ስለ ልጆችዋ ስታለቅስ ብዙ ልቅሶና ዋይታ ተሰማ ፤ መጽናናትንም እንቢ አለች ፤ ልጆቿ የሉምና። » የተባለው ተፈጸመ ፥ ይላል። ራሔልን አነሣ እንጂ ልያን አላነሣትም። ምክንያቱም ጌታ የተወለደው ከልያ ወገን ስለተወለደ ዕዳዋ ነው። ራሔል ግን ከእርሷ ወገን ስላልተወለደ ያለ ዕዳዋ ነው። አንድም የልያ በርኅቀተ ሀገር በብዛት ድነውላታል ፤ የራሔል ግን በማነስ በቅርበት አልቀውባታልና ነው። አንድም በራሔል የልያንም መናገር ነው። አንድም « እናታችን ራሔል ኑራልን ፥ መከራችንን አይታልን ባለቀሰችልን ፣» ብለው ስላለቀሱ ነው። አንድም እንድናለን መስሏቸው ከመቃብረ ራሔል ገብተዋል ፥ ከዚያም ተከትለው ገብተው ልጆቻቸውን ከእቅፋቸዋ ነጥቀው ፥ አንገታቸውን ጠምዘው አርደውባቸዋል። በዚህን ጊዜ አፅመ ራሔል አንብቷል።  የራሔል መቃብር ከቤተልሔም አንድ ኪ.ሜ. ይርቃል።
          በሌላ በኲል ደግሞ ከልያም ከራሔልም ወገን የተወለዱትን ሊያገናኝ የሚችለውን አባታቸውን ያዕቆብን አላነሣም። ያነሣው እናታቸውን ራሔልን ነው። ምክንያቱም፦ ወንድ ልጅ ለአቅም አዳም ፥ ሴት ልጅ ለአቅመ ሔዋን ደርሰው የሞቱ እንደሆነ ኀዘን በአባት ይጸናል። በሕፃንነት ዘመን የሞቱ እንደሆነ ግን ኀዘን በእናት ይጸናልና ለዚህ ነው ።
          ቅዱስ ማቴዎስ « ራሔል » ብሎ ትንቢተ ኤርምያስን የጠቀሰው ለዚህች ብቻ ሳይሆን በግብፅ ለነበረችውም ነው። ይኸውም ግፍን ከግፍ ሲያነፃፅር ነው።
እነዚህን ሁሉ ሕፃናት እንዴት አድርጎ ሰበሰባቸው?
          ሄሮድስ አሥራ አራት እልፍ ሕፃናት የሰበሰበው « ንጉሡ ቄሣር ፦  ሕፃናትን ሰብስበህ ፥ ልብስ ምግብ እየሰጠህ ፥ በማር በወተት አሳድገህ ፥ ለወላጆቻቸው ርስት ጉልት እየሰጠህ ጭፍራ ሥራልኝ ብሎኛል፤ » የሚል አዋጅ አናግሮ በጥበብ ነው። ያላቸው ልጆቻቸውን፥ የሌላቸው ደግሞ ልብስ ምግብ ልቀበልበት ብለው እየተዋሱ ሄደዋል። እንዲህ አድርጎ ሰብስቦ ፈጅቷቸዋል። ለሁለቱም የግፍ ታሪኮች «የኀዘን የልቅሶና የጩኸት ድምፅ በራማ ተሰማ፤» የተባለው በመላእክት ዘንድ ተሰማ ፥ ማለት ነው። ምክንያቱም ኢዮር ፥ ራማ ፥ ኤረር ዓለመ መላእክት ናቸውና። አንድም በመላእክት ፈጣሪ በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰማ ማለት ነው። ምክንያቱም መላእክት ባሉበት እግዚአብሔር አለ። አንድም ራማ የተባለች መንግሥተ ሰማያት ናት። ምሥጢራዊ ትርጉሙም ሃይማኖት ይዞ ምግባር ሠርቶ የሚገባባት አጥታ ታዝናለች ፥ ታለቅሳለች ማለት ነው።
          በዚህ ዘመን የሚያስፈልገው ሌላ ነገር ሳይሆን ይህ የራሔል እንባ ነው። ዓለም በግፍ ተከድናለችና ፥ ነፃ ሰው የለምና። «ረከሱ በበደላቸውም ጐሰቈሉ ፥ በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም። እግዚአብሔርን የሚፈልግ አስተዋይ እንዳለ ያይ ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ ሁሉ ተካክሎ በአንድነት በደለ ፤ አንድ ስንኳ በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም፡፡ ሕዝቤን እንጀራን እንደ መብላት የሚበሉ ግፍ አድራጊዎች ሁሉ አያውቁም ፥ እግዚአብሔርን አይጠሩትም።» እንዲል፡፡ መዝ ፶፪ ፥ ፩-፬ ። ስለዚህ ፦
ሀ. ለራሳችን እናልቅስ ፤
          በሕገ እግዚአብሔር ጸንተን ባለመቆማችን ( ከፍቅረ እግዚአብሔርም ከፍቅረ ቢጽም በመለየታችን ) ልናለቅስ ይገባል። «ሕግህን አልጠበቅሁምና የውኃ ፈሳሾች ከዓይኖቼ ፈሰሰ ይላልና። መዝ ፩፻፲፰ ፥ ፩፻፴፭ ፤። ቅዱስ ዳዊት ብዙ ጊዜ ለራሱና ለቤተሰቡ አልቅሷል። በኦርዮና በቤርሳቤህ ምክንያት ነቢዩ ናታን በገሠጸው ጊዜ ፦ « እግዚአብሔርን በድያለሁ ፤ » ብል አለቀሰ። ነቢዩ ናታንም፦ እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢአትህን አርቆልሃል ፥ አትሞትም። ነገር ግን በዚህ ነገር ለእግዚአብሔር ጠላቶች መነሣሣት ምክንያት አድርገሃልና ስለዚህ ደግሞ የተወሰደልህ ልጅ ፈጽሞ ይሞታል፤ » አለው። ዳግመኛም ቅጣቱ እንዲነሣለት ማቅ ለብሶ አመድ ላይ ተኛ ፥ ጾመ ፥ ለመነ ፥ ጸለየ ፥ አለቀሰ፡፡  እርሱም ራሱ « ሕፃኑ ሕያው ሳለ ፥ ምናልባት እግዚአብሔር ይምረኝ ፥ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደሆና ማን ያውቃል ብዬ ጾምሁ ፥ አለቀስሁም፤ » ብሎአል። ፪ኛ ሳሙ ፲፪፥፩-፳፫። ልጁ አቤሴሎም ባሳደደውም ጊዜ ተከናንቦ እያለቀሰ የደብረ ዘይትን አቀበት ወጥቷል፡፡ ፪ኛ ሳሙ ፲፭ ፥ ፴ ።
          ቅዱስ ዳዊት ወደ ውስጥ እየተመለከቱ ስለ ራስ በማልቀስ ያምን ነበር። ብዙ ጊዜም ውጤት አግኝቶበታል። ይኽንንም በመዝሙሩ ላይ ብዙ ቦታ ጠቅሶታል። « በጭንቀቴ ደክሜአለሁ ፥ ( ወድጄ በሰራሁት ሥራ ጠፋሁ ) ፥ ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ ፥ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ። ዐይኔ ከቁጣ የተነሣ ታወከች ፥ ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ አረጀሁ። ( ሰብአ ትካትን ፥ ሰብአ ሰዶም ፥ ሰብአ ገሞራን ባጠፋህበት መዓትህ ታጠፋኝ ይሆን ? ከማለቴ የተነሣ ዓይኔ ባከነች። ሴትና ልጅ አለንጋ ያነሡባቸው እንደሆነ ከአሁን አሁን ያሳርፉብን  ይሆን ብለው ዓይናቸው እንደሚባክን እኔ ባከንኩኝ። ከፍርድህ የተነሣ ሰውነቴ ባለ መከራ ሆነች። ከቁጡ ዕንባ የተነሣ ፊቴ ተንጣጣ ፥ ቅንድቤ ተመለጠ )። ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ አረጀሁ። ( መከራ ስላጸኑብኝ ያለ ዕድሜዬ አረጀሁ ፥ እያልሁ እንደሌለ ሰው ሆንኩኝ ፥ ሳልሞት እንደ ሞተ ሰው ተቆጠርኩኝ )፡፡ ዓመፃን የምታደርጉ ሁሉ ፥ ከእኔ ራቁ ፤ ( ጐልማሳ ገደለ ፥ የጐልማሰ ሚሰት ነሣ ፥ እያላችሁ ከፈጣሪዬ ጋር የምታጣሉኝ ሰዎች አንድም አጋንንት ከእኔ ራቁልኝ ) ፤ እግዚአብሔር የልመናዬን ቃል ሰምቶአልና። ብሏል። መዝ ፮ ፥ ፮-፰። በሌላ ምዕራፍም፦ « ልቅሶዬን መልስህ ደስ አሰኘኸኝ። ማቄን ቀድደህ ደስታን አስታጠቅኸኝ። » ብሏል፡፡ መዝ ፳፱ ፥ ፲፩።
          ቅዱስ ዳዊት የችግሩ መፍቻ ቁልፍ ምንግዜም ቢሆን እውነተኛ እንባው ነበር። ጠላቶች ሲሰድቡት ፥ ጐረቤቶቹ ሲርቁት ፥ ዘመዶቹ ሲክዱት ፥ ያዩት ሁሉ ከእርሱ ሲሸሹ ፥ ሁሉም እንደሞተ ሰው ከልብ ሲረሳው ፥ እንደጠፋ ዕቃ ሲሆን ፥ በዙሪያው የከበቡትን ሰዎች የትዕቢት ድምፅ ሲሰማ ፥ ለክፉ ነገር ተባብረው ነፍሱን ለመንጠቅ ሲማከሩ እርሱ ግን በእግዚአብሔር ታምኖ እንፋሎት ያለው እንደ ፈላ ውኃ የሚያቃጥል እንባ በጉንጮቹ ላይ ያፈስ ነበር። መዝ ፴ ፥ ፱-፲፬። ጠላቶቹ ባመጡበት መከራ ደስ ሲላቸው ልቅሶው እናት እንደሞተችበት ሰው ነበር። መዝ ፴፬፥፲፱ ።
          ቅዱስ ዳዊት ስለ ራሱ የሚያለቅሰው « ለምን ይህ መከራ መጣብኝ ፤ » በማለት ሳይሆን በተአምኖ ኃጣውዕ (ኃጢአትን በመታመን) መከራውን እንዲያርቅለት ነው። መዝ ፴፯ ፥ ፲፰። ንጉሡ እዝቅያስም፦ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ  « ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል ፤ » ባለው ጊዜ ፥ ወደ ግድግዳ ዞሮ እጅግ ታላቅ ልቅሶን በማልቀሱ ከበሽታው ተፈውሷል ፥ በዕድሜው ላይ አሥራ አምስት ዓመት ተጨምሮለታል። ሕዝ ፴፰ ፥ ፩-፭።
          ቅዱስ ጴጥሮስ ፦ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እርሱ የተናገረው ትንቢት በተፈጸመበት ጊዜ ወደ ወጭ ወጥቶ መራራ ልቅሶን አልቅሷል።
           ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈሪሳዊውን ግብዣ ተቀብሎ ከደቀመዛሙርቱ ጋር በማዕድ በተቀመጠ ጊዜ ፥ በዚያ አገር ካሉ ሰዎች ይልቅ ኃጢአተኛ የነበረች ሴት ሽቱ ይዛ መጣች። እያለቀሰች በዕንባዋ እግሩን አራሰችው ፥ በጠግሯም አበሰችው። እግሩን ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበር። እንዲህም በማድረጓ ከሰባት አጋንንት ቁራኝነት አላቀቃት ፥ « እምነ ትሽ አድኖሻልና በሰላም ሂጂ፤ » አላት። ለእኛ የሚያስፈልገን እንዲህ ዓይነት ዕንባ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ፦ « አሁን ለንስሐ ስላዘናቸሁ ደስ ብሎኛል እንጂ ስላዘናችሁ አይደለም። » ያለው ለዚህ ነውና። ፪ኛ ቆሮ ፯ ፥ ፱።
                                               ለ. ለትዳራችን እናልቅስ ፤
          ባል በሚስቱ ፥ ሚስትም በባሏ ግፍ እየፈጸሙ ነውና። « መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው ፥ ለመኝታቸውም ርኵሰት የለውም ፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። » የሚለው እንኳን ግብሩ ጥቅሱ ከጠፋብን ሰንብተናል። የሠርግ ሰሞን የጥሪ ወረቀታችንን እና ግድግዳችንን ያጨናነቀው እርሱ ነበር። ዳሩ ግን በወረቀት ላይ እንጂ በልባችን ላይ ስላልተጻፈ ፈጽሞ ተረስቷል። ዕብ ፲፫ ፥፬። ነገሩ ሁሉ፦ « ሚስት ታጫለህ ፥ ሌላም ሰው ከእርስዋ ጋር ይተኛል ፤ ቤት ትሠራለህ ፥ አትቀመጥበትም ፤ ወይን ትተክላለህ ፥ ከእርሱም አትበላም፤ » ሆኗል። ዘዳ ፳፰ ፥፴። ወንዶቹንም ቢሆን፦ « ሚስትህ ባልንጀራህን የቃል ኪዳንህ ሚስት ሆና ሳለች እርሷን አታልለሃታልና፤ » እያለን ነው ፥ እግዚአብሔር። ሚል ፪ ፥፲፬። ነገር ግን የሚያደምጥ ጠፍቶ ምድር ፍቺ በፍቺ ሆናለች። በአንድ ቤት ውስጥ እየኖርን በምንም ነገር የማንስማማ ፥ ላለመስማማት ተስማምተን ፥ ተናንቀን ፥ እጅ እጅ የሚል (የተሰለቸ) ኑሮ የምንኖር እንደተፋታን ነው  የምንቆጠረው። « ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ ፥ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል። መፋታትን እጠላለሁ ፥ ይላል የእሥራኤል አምላክ እግዚአብሔር ፤ ልብሱንም በግፍ ሥራ የሚከድነውን ሰው እጠላለሁ ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ፤ ስለዚህ እንዳታታልሉ መንፈሳችሁን ጠብቁ። » ሚል ፪ ፥፲፮።
ሐ. ለልጆቻችን እናልቅስ
          ከልጅነት እስከ እውቀት ከልጆቹ ጋር ደክሞ በልጆቹ የሚደሰት ጠፍቷል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም መስመር የለቀቁ ፥ ሰው ሰውኛውን እንዳይመለሱ ሆነው የጠፉ ፥ እንዳይነሡ ሆነው የወደቁ ልጆች ብዙዎች ናቸው። ጌታ በወንጌል፦ « እና ንተ የኢየሩሳሌም ልጆች ሆይ ፥ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔስ አታልቅሱልኝ። መካኖች ፥ ያልወለዱ ማኅፀኖችና ያላጠቡ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው ፥ የሚሉበት ወራት ይመጣልና። » ያለው በገሀድ እየታየ ነው። ሉቃ ፳፫ ፥፳፰። ንጉሥ ዳዊትን ተከታይ አብጅቶ ከዙፋኑ ያሳደደው ፥ በጦርነትም የተፋለመው የገዛ ልጁ አቤሴሎም ነው። « ዳዊትም ተከናንቦ ያለ ጫማ እያለቀሰ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ወጣ ፤ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተከናንበው እያለቀሱ ወጡ። » ይላል ። ፪ኛ ሳሙ ፲፭ ፥፴። በሃይማኖትም በኵል፦ የሊቀ ካህናቱ የዒሊ ልጆች ቤተ መቅደሱን ደፍረው ያሰደፍሩ ነበር። በዚህ የተነሣ አባታችው በእግዚአብሔር ቃል ተገሥጿል ፥ በመጨረሻም ከወንበር ወድቆ አንገቱ ተቆልምሞ ክፉ ሞት ሞቷል። ልጆቹም በጦር ሜዳ ተቀሥፈዋል። ፩ኛ ሳሙ ፪ ፥፳፪ -፳፮ ፣ ፬፥፲፪-፳፪ ።
መ. ለወገኖቻችን እናልቅስ፤
          አንድ ሕዝብ ፥ አንድ ወገን ስንሆን በዘር ተለያየተን እርስ በርስ እየተቋሰልን ነው። ከዚህ ንጹሕ የሆነ ሰው ማግኘት እጅግ ያስቸግራል። ዘረኝነትን በቃልም በጽሑፍም ፊት ለፊት የምናወግዘውም ቢሆን ከጀርባችን አዝለነው እንገኛለን። በዓለማውያን ዘንድ ብቻ አይደለም ፥ መንፈሳውያን በምንባለውም ጭምር ነው። አማርኛ ተናገሪው ሌላውን እንዳላይ እንዳልሰማ ይላል ፥ በውስጥ ግን ጐንደሬ ፥ ጐጃሜ ፥ ወሎዬ ፥ ሸዌ እያለ የተከፋፈለ ነው። እንዲህ እያለ ክፍፍሉ እስከ ጐጥ ድረስ ይወርዳል። ትግርኛ ተናጋሪውም ለጊዜው አንድ ይመስላል እንጂ፦ አድዋ ፥ ሽሬ ፥ አክሱም ፥ተምቤን ፥ አዲግራት እያለ የተከፋፈለ ነው። ኦሮምኛ ተናጋሪውም የሸዋ ፥ የወለጋ ፥ የአርሲ ፥ የሐረር ፥ የባሌ ፥ የቦረና እያለ የተከፋፈለ ነው። ለአብነት እነዚህን ጠቀስን እንጂ በሁሉም ያው ነው። ለጊዜው የምንስማማው ከእኛ ዘር ውጪ የሆነውን ለማጥቃት እንጂ በውስጣችን እሳትና ጭድ ነን። ሄሮድስና ጲላጦስ በውስጥ አይስማሙም ነበር ፥ በውጭ ግን ክርስቶስን ለመስቀል ተስማሙ። ሊቃውንቱ ክርስቶስ ፍቅር ስለሆነ በመሐል ሆኖ አስማማቸው ይላሉ። የእነርሱ መስማማት ለእርሱ ጉዳት ቢሆንም አስማማቸው ። እኛም ተጐድተንም ቢሆን ሰዎች እንዲስማሙ እናድርግ። መስሎን ነው እንጂ እንኳን ዘር ከአንድ ማኅፀን መውጣትም አያስማማም። ቃየል አቤልን ገድሎታል ፤ ዘፍ ፭ ፥ ፰። ዔሳው ያዕቆብን ሊገድለው አሳዶታል ፤ ዘፍ ፳፯ ፥ ፵፮፡፡ አቤሜሌክ የእናቱን ወገኖች አስተባብሮ በእናት የማይገናኙትን ሰበዓ የአባቱን ልጆች ( ወንድሞቹን ) ነፍሰ ገዳዮችን በገንዘብ ደልሎ አሳርዷቸዋል። መሳ ፱፥፩-፮። ሁላችንም « ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም ፤ በሕያውና በዘለዓለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ። » የሚለውን ዘንግተናል። ማስታወስም አንፈልግም ፥ ብናስታውስም ለመፈጸም አቅም አጥተናል። ፩ጴጥ ፩ ፥፳፫ ።
ሠ. ለሀገራችን እናልቅስ
          በእነ ቅዱስ ዳዊት፦ « ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ፤ . . . በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ ፤ . . . ለኢትዮጵያ ሰዎች ምግባቸውን ሰጠሃቸው፤ » የተባለላት ሀገራችን እንዴት ናት? መዝ ፷፯፥ ፴፩ ፣ ፸፩ ፥፱ ፣ ፸፫ ፥፲፬። አባቶቻችን ሀገረ እግዚአብሔር ያሰኟት ሀገራችን ምን እየመሰለች ነው? እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የበቀሉባት ፥ እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የመነኑባት ፥ ተሰዓቱ ቅዱሳን የተጠለሉባት ኢትዮጵያ ይዞታዋ እንዴት ነው? የሚለውን ለመመለስ መጻሕፍትን ማገላበጥ ሊቃውንትን መጠየቅ የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ነገራችን ሁሉ « ክምሬ ያለሽ መስሎሻል ፥ ተበልተሽ አልቀሻል ፤ ሆኗል። » በረከት ርቆናል ፥ ረድኤት ተለይቶናል። ይህም በሚበዛው መናገር እንጂ ፈጽሞ የለም ማለት አይደለም። የሃይማኖት ለዋጮች በዝተዋል ፥ በውስጥም በአፍአም አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ጠንክረዋል ፥ አሕዛብ ተበረታተዋል። « ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት » የሚለውን ለማጥፋት በሙሉ ኃይላቸው እየተረባረቡ ነው። « አቤቱ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ ፥ የቅድስናህንም መቅደስ አረከሱ ፤ » የሚለውም እየተፈጸመ ነው። መዝ ፸፰ ፥፩ ።
          ስለዚህ አገራችንን የረሳን ሁሉ ቅዱስ ዳዊትን አብነት አድርገን « ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ፤ ባላስብሽ ፥ ምላሴ ከጉሮሮዬ ትጣበቅ ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ አገሬን ባልወድድ ፤ » እንበል። መዝ ፩፻፴፮፥፭። እንደ ነህምያ በሀገር ፍቅር እንቃጠል። ነህምያ የአገሩን ጥፋት በሰማ ጊዜ አመድ ነስንሶ ከአመድ ላይ ተቀምጦ አለቀሰ ፥ ማቅ ለበሰ ፥ አያሌ ቀን አዘነ ፥ በሰማይም አምላክ ፊት ጾመ ፥ ጸለየ። ነህ ፩ ፥፬።
          ስለ ሀገር ማሰብ ማለት፦ ስለ ወንዙና ተራራው ፥ ስለ ዳር ድንበሩ ብቻ አይደለም። ከዚህ ሁሉ ጋር ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ያሰኛትን ታሪክ ፥ ሃይማኖት ፥ ሥርዓት ፥ ትውፊት ፥ ቅርስና ፥ ሕዝብ ማሰብ ማዘን ማልቀስ ያስፈልጋል ። ዋናው ነገር በሃይማኖት የሚፈስ እንባ ነው። ያን ጊዜ ጩኸታችን እስከ ራማ ድረስ ይሰማል።
ረ. ስለ ቤተ ክርስቲያናችን አንድነት እናልቅስ ፤
          የቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚመጣው « በእኔ እበልጥ፤ » መንፈስ አይደለም። « ካልተመለሳችሁ ፥ እንደዚህም ሕፃን ካል ሆናችሁ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም እነደዚህም ሕፃን ራሱን ዝቅ ያደረገ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ ይህ ነው፤ » በሚለው መንገድ ብቻ ነው። ማቴ ፲፰ ፥፫። ወንጌልም ቤተ ክርስቲያንም መንግሥተ ሰማያት ይባላሉ ።ሮሜ ፲፩ ፥፲፯። የግል ጥቅማችን እንዲጠበቅልን ቅድመ ኹኔታ በማስቀመጥም አይደለም። መቀበሉ እንደ ቀኖት ቢሰማንም ፥ እንደ ሆምጣጤ ቢመረንም « እኔ ይቅርብኝ ፥ እኔ ልጐዳ ፤» በማለት ነው። ክርስቶስ ሰውና እግዚአብሔርን  ፥ ነፍስና ሥጋን  ፥ ሰውና መላእክትን  ፥ ሕዝብንና አሕዛብን አንድ ያደረገው፣ በመስቀል ላይ ቆስሎ ነው። ስለሆነም ክርስቶስ ለቆሰለላት ቤተ ክርስቲያን ትንሽ ትንሽ እንቁሰልላት። አባቶቻችን ቅዱሳን ብዙ ቆስለውላታል ። የእነርሱ ልጆች ነን ካልን አሠረ ፍኖታቸውን እንደተሰጠን ጸጋ መጠን እንከተል። ሁላችንም ራሳችንን እንመርምር። በሌላ ዓይን ያለውን ጉድፍ ሳይሆን በእኛ ውስጥ የተተከለውን ትልቅ ምሰሶ እንመልከት። የወጭቱን ላዩን ሳይሆን ውስጡን እናጥራ፥ያን ጊዜ ውጪውም ይጠራል። ማቴ ፯ ፥፩ ፣ ፳፫ ፥ ፳፭። የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ከተፈታ የአገሪቱም ችግር ይፈታል። የትዳራችንም የልጆቻችንም ችግር ይፈታል። በመሆኑም አስቀድመን ስለ ቤተ ክርስቲያናችን እናልቅስ። የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን ።