Thursday, 3 December 2015

“ሰው ማለት ምን ማለት ነው?”

“ሰው ማለት ምን ማለት ነው?”
ሰው ማለት ነፋሳዊነት፣ እሳታዊነት፣ ውኃዊነት፣ መሬታዊነት
ባሕርያት ያሉት በነፍስ ተፈጥሮውም ነባቢት ለባዊትና ሕያዊት
የሆነች ነፍስ ያለችው ፍጥረት ነው፡፡ እንዲህ ብለን ግን የሰውን
ተፈጥሮ ጠቅልለን መናገር አይቻለንም፡፡ ምክንያቱም ሰውን
ከሌሎች ፍጥረታት ይልቅ እጅግ ልዩ በሆነ መልኩ
በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል ተፈጥሮአልና፡፡ ስለዚህም
ቅዱሳን አባቶች እንዲህ ብለው ሰው ለሚለው ስያሜ ትርጓሜ
ይሰጡታል፡፡
ቅዱስ ባስልዮስ ዘቄሳርያ ከትምህርቶች ሁሉ ታላቁ ትምህርት
ራሰን ማወቅ ነው፡፡ አንድ ሰው ራሱን ካወቀ እግዚአብሔርን
ያውቀዋል፡፡ እግዚአብሔርን ካወቀ ደግሞ እግዚአብሔር
አምላኩን ይመስላል፡፡ ሲል ቅዱስ ይስሐቅም አንተ በልብህ
ንጹሕ ከሆንህ ሰማይ በውስጥህ ነው፡፡ በውስጥህም
መላእክትንና የመላእክትን ጌታ ትመለከታቸዋለህ (The
Orthodox Church by Timothy Ware) ቅዱስ ይስሐቅ
እንዲህ ማለቱ ያለ ምክንያት ሆኖ አይደለም፡፡ ጌታችን
መድኃኒታችን ቃሉን በተግባር መልሰው ለሚተገብሩ
ሰዎች የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል አባቴም ይወደዋል
ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ ማደሪያ እናደርጋለን፡፡
(ዮሐ.14፡23) የሚለውን ይዞ ነው፡፡ አካላችን በሰማይ
የሚኖረው አባታችን ማደሪያ ከሆነ እኛም ሰማይ ሆንን ማለት
ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በእኛ ሰውነት ውስጥ ካለ ደግሞ
ቅዱሳን መላእክትም መገኘታቸው እርግጥ ነው፡፡
ከዚህ ጠንከር ባለ መልኩ ደግሞ የአሌክሳንደሪያው ቅዱስ
ቀሌምንጦስ ወንድምህን አስተውለህ ስትመለከተው
እግዚአብሔርን ትመለከተዋለህ ይላል፡፡ ቅዱስ
ኤፍሬምም በሰው ላይ በአመፃ የምትነሣሣ ከሆነ
በእግዚአብሔር ላይ እንደተነሣሣህ ቁጥር ነው፡፡ ለባልንጀራህ
አክብሮትን የቸርከው ከሆነ እነሆ እግዚአብሔርን አከበርኽ፡፡
ይላል፡፡
ቅዱስሄሬኔዎስ፣ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ
ዘእንዚናዙ እንዲሁም ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በአንድነት ሰው
በጸጋ አምላክ ይሆን ዘንድ ከሦስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር
ቃል ሰው ሆነ ብለው ያስተምራሉ፡፡ (The Image and
likeness of God by Vladimir Lossky) በእርግጥ ቅዱስ
ዮሐንስ አፈወርቅም የማቴዎስን ወንጌል በተረጎመበት በሁለተኛ
ድርሳኑ ገጽ 9 ላይHe suffered Himself of to be
called also the Son of David, that He might make
thee Son of God. አንተን የእግዚአብሔር ልጅ ያደርግህ
ዘንድ የዳዊት ልጅ መባልን መረጠ፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም ሙሴ
በነዝር እባብ የተነደፉት እስራኤላውያን ከፍ ተብሎ በተሰቀለው
የነሐስ እባብ እንደ ተፈወሱ አስተዋለ፡፡ በእርሱም በጥንቱ እባብ
የተነደፉትን የሚያድነውን(ክርስቶስን) ከሩቅ ተመለከተው፡፡ ሙሴ
እርሱ ብቻ ከእግዚአብሔር የጸጋው ብርሃን ተካፋይ እንደሆነ
አስተዋለ፡፡ በእርሱም እግዚአብሔር ቃል ወደ እዚህ ዓለም
በመምጣት አማልክት ዘበጸጋን በትምህርቱ እንደሚያበዛቸው
ተመለከተ፡፡ ይላል፡፡
እኚሁ አባቶች ሰው ገና ሲፈጠር በጸጋ አምላክ እንዲሆን ተደርጎ
መፈጠሩንም ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም ጌታ ሆይ
ሠዓሊ ቀለማትን አዋሕዶ ሥዕሉን እንዲሥል አንተም
አርአያህንና አምሳልህን እንዲመስሉ ሁለቱን አካላት አዋሕደህ
አንድ አካል በማድረግ በራስህ መልክ ፈጠርካቸው፡፡ ወደ ራስህ
አርአያ ተመለከትኽ የራስህን አርአያና አምሳል በእጆችህ
ሣልኸው፡፡ ጌታ ሆይ እነሆ የሣልኸውን ሥዕል አንተው ሰው
በመሆን ገለጥኸልን፡፡ሲል ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ሰው ገና
ከአፈጣጠሩ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ስለመፈጠሩ
ሲያስረዳ በአዳምና በሔዋን አስቀድሞ ያሳየን ምሳሌ ይፈጸም
ዘንድ የሙሽራው ጎን በጦር ተወጋ፤ ከጎኑም ቤተክርስቲያን
በፈሰሰው ደሙ መሠረታት(በደሙ የዋጃትን ቤተክርስቲያን
አንዲል የሐዋ.20፡28)፤ እግዚአብሔር ይህን ባወቀ አዳምንና
ሔዋንን በብቸኛ ልጁ አርዓያና አምሳል ፈጠራቸው፡፡ብሎ ጽፎልን
እናገኛለን ፡፡ (Spirituality in Syrian Tradition by
Sebastian brock) ስለዚህም ወደ ድምዳሜው ስንመጣ
ሰው ማለት በጸጋ አምላክ ሆኖ የተፈጠረ ፍጥረት መሆኑን
በእነዚህ ሁሉ ቅዱሳን አባቶች አስተምህሮ መረዳት እንችላለን፡፡
በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ተፈጠረም ስንል የጸጋ እውቀት
የተሰጠው ክፉውን ከበጎ መለየት የሚችል ፍጡር መሆኑን
ያስረዳናል፡፡ ከላይ ከሰጠናቸው ትንታኔዎች ተነሥተን ሰው
ለሚለው ስያሜ ትርጉም ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ከሦስቱ
ባሕርያተ ነፍስ ተፈጠረ ብለን ብቻ የምንቋጨው እንዳልሆነ
መረዳት እንችላለን፤ እጅግ ሰፊ ትርጉም ያለውና በውስጡም
ታላቅ የሆነ መልእክትን እንደያዘ እንገነዘባለን፡፡ ይህን እጅግ
ሰፊና ጥልቅ የሆነ ትርጉም የያዘው ሰው የሚለው ስያሜ
ለመረዳት መልክና ምሳሌ ወይም አርአያና አምሳል የሚሉትን
ቃላት አስቀድሞ መረዳት ይገባናል፡፡
መልክ (አርአያ) ማለት ምን ማለት ነው?
መልክ (አርአያ) ማለት ሰው እግዚአብሔር አምላኩን ይመስል
ዘንድ በተፈጥሮ የተሰጡት ባሕርያት ናቸው፡፡ እነዚህ ባሕርያት
ከሰው ፈጽሞ የሚወሰዱ አይደሉም፡፡ ብዙ ቅዱሳን አባቶች
መልክ (አርአያ) ለሚለው ቃል ትርጉም ሲሰጡ ሲለያዩ ይታያሉ፡፡
ለምሳሌ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዘፍጥረትን በተረጎመበት
ድርሳኑ ላይ መልክ (አርአያ) ማለት ለሰው በተፈጥሮ ፍጥረታትን
ለሚገዛበት ባሕርይው የተሰጠው ስያሜ ነው ይላል እርሱ
(ሙሴ) በእግዚአብሔር መልክ ሲል በምድር ያሉትን ሁሉ ሰው
የሚገዛቸው መሆኑን የሚያመለክተን ነው፡፡ በምድር ላይ ከሰው
በላይ የሆነ ፍጥረት የለውም ይላል፡፡ እንዲሁም ይህ ቅዱስ
ስለ ሰው ተፈጥሮ ሲያስተምር ሰው ከሚታዩት ፍጥረታት በላይ
የሆነ ፍጥረት ሲሆን ለዚህ ፍጥረት ሲባል ሁሉም ፍጥረታት
ተፈጠሩ ይላል፡፡ ያም ማለት ሰማይ፣ ምድር፣ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣
ከዋክብት፣ ተሳቢና ተራማጅ እንዲሁም በምድር ላይ ያሉ
ፍጥረታት ሁሉ ለእርሱ ተፈጠሩ
አንዳንድ ቅዱሳን ሰው በእግዚአብሔር መልክ መፈጠሩን
መንፈሳዊ ከሆነው ተፈጥሮው ጋር አገናኝተው ያስተምራሉ፡፡
ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም በእግዚአብሐር መልክ የተፈጠረችው
ነፍሳችን ናት ብሎ ሲያስተምር አንተ መንፈሳዊ ተፈጥሮ አለህ፤
ነፍስ የእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል ናት ይላል፡፡ ሰው በነፍስ
ተፈጥሮው ነጻ ፈቃድ፣ ነገሮችን የማገናዘብ ችሎታ እንዲሁም
ሓላፊነት የሚሰማው ሆኖ የተፈጠረ ፍጥረት ነው፡፡ በእነዚህ ሰው
እግዚአብሔር አምላኩን ይመስላል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ግን
ነፍሳችንም ሥጋችንም በእግዚአብሔር አርዓያ እንደተፈጠሩ
ግልጽ በሆነ መልኩ ሲያስረዳ በአዳምና በሔዋን አስቀድሞ
ያሳየን ምሳሌ ይፈጸም ዘንድ የሙሽራው ጎን በጦር ተወጋ፤
ከጎኑም (በፈሰሰው ደሙ) ቤተክርስቲያን ተመሠረተች፤
እግዚአብሔር ይህን ባወቀ አዳምንና ሔዋንን በብቸኛ ልጁ
አርአያና አምሳል ፈጠራቸው፡፡ይለናል፡፡
ሰው ሰማያዊት አካል ስላለችው ረቂቁን ዓለም የመረዳት ችሎታ
ሲኖረው ምድራዊውም አካል ስላለው ምድራዊውም እውቀት
አለው፡፡ ሰውን ከሰማያውያን መላእክትና ከምድራውያን
መላእክት ጋር ስናስተያየው ለሁለቱም ዓለማት እንግዳ
እንዳልሆነ በሁለቱም ዓለማት እኩል የመኖር ተፈጥሮአዊ
ባሕርይ እንዳለው፣ የሰማያውያንንም የምድራውያንንም እውቀት
ገንዘቡ ያደረገ ፍጥረት መሆኑን ስናስተውል በእግዚአብሔር
መልክና ምሳሌ መፈጠሩን እንገነዘባለን ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ የሰማያውያንም የምድራውያንም
ፍጥረታት እውቀት ባለቤት ነው፡፡ ሰውም በጸጋ ለሰማያውያን
መላእክት ለምድራውያን ፍጥረታት እውቀት ባይተዋር
አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታች በምድር
ከሰማይም በላይ ከሰማይም በታች ይኖራል፡፡ ሰው ሙሉ ለሙሉ
አይሁን እንጂ በታች በምድር ግዙፋን ፍጥረታትን ሲገዛ በላይ
በሰማይ ደግሞ ከሰማያውያን መላእክት ጋር እኩል በምስጋና
ይሳተፋል፡፡ ከዚህም ተነሥተን ሰው በሁለት ዓለማት እኩል
የመኖር ተፈጥሮ እንዳለው ማስተዋል እንችላለን፡፡
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ሰው በእግዚአብሔር መልክ ተፈጠረ ስንል Â
በነፍሱም በሥጋውም እንደሆነ ሲያስረዳ እንዲህ ብሎ ጽፎልን
እናገኛለን፡፡ ሰው ምድራዊና መንፈሳዊ አካል ያለው ፍጥረት
ሆኖ በመፈጠሩ ከመላእክት በተለየ በእግዚአብሔር አርዓያና
አምሳል ተፈጠረ ተባለለት፡፡ ሰው ምድራዊ ተፈጥሮ ባይኖረው
ኖሮ በእግዚአብሔር አርአያ ተፈጠረ ባላልነው ነበር፡፡ ስለዚህም
ሰው በምድራዊው ተፈጥሮውም የእግዚአብሔርን መልክ
ይዟል፡፡ ብሎ ያስተምራል፡፡
በእርግጥ ይህ እውነት ነው፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር ፍጥረትን
ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ፈጥሮአቸዋል፡፡ ወደ መኖርም
ባመጣቸው ፍጥረታትም ሌሎችንም ፍጥረታትን ፈጥሮአል፡፡
ለምሳሌ ብንወስድ የሰው ተፈጥሮ አንዱ ነው፡፡ እግዚአብሔር
አስቀድሞ ምድርን ፈጠራት፡፡ ከምድርም አፈር ሰውን አበጀው፡፡
ይህ ዓይነት ባሕርይ እንደ እግዚአብሔር አይሁን እንጂ በሰውም
ላይ ይታያል፡፡ ሰው ምንም እንኳ ነገሮችን ካለመኖር ወደ መኖር
አምጥቶ እንደ አምላኩ አይፍጠር አንጂ የተፈጠሩ ፍጥረታትን
በመጠቀም ምድራዊው አኗኗሩ ቀላልና ምቹ አንዲሆንለት ሲል
ከመላእክት በተለየ እጅግ ድንቅና ሊታመኑ የማይችሉ ተግባራትን
ሲከውን ይታያል፡፡ በዚህም አምላኩን ይመስላል፡፡
ምሳሌ(አምሳል) ማለት ምን ማለት ነው ?
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እኛ የሰው ልጆች በእግዚአብሔር
መልክ(አርአያ) የመፈጠራችን ዓለማው እግዚአብሔርን እንደ
ችሎታችን መጠን እርሱን መስለን እንመላለስ ዘንድ ነው ይላል፡፡
ከዚህ ተነሥተን ምሳሌ (አምሳል) ስንል በተፈጥሮ የተሰጠንን
ዕውቀት ተጠቅመን በተግባር እርሱን የምንመስልበት ሂደት እርሱ
ምሳሌ (አምሳል)ይባላል፡፡ እግዚአብሔር በባሕርይው ፍቅር
ነው፣ ትሑትና የዋህ ነው፣ ቅን ፈራጅ ነው፣ ጻድቅ ነው፣ ርኅሩኅ
ነው፣ መሐሪ ነው፣ ታጋሽ ነው፡፡ እነዚህ ባሕርያት ሁሉ በእኛ
ተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ባሕርያት ወደ ተግባር
መልሰን ስንፈጽማቸው እግዚአብሔርን መስለነዋል ወይም
የእግዚአብሔር ምሳሌ ወይም አምሳል በእኛ ላይ ተንጸባርቆ
ይታያል፡፡
አንዳንዶች እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር
አበጀው በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት
ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ፡፡ (ዘፍ.2፡7) የሚለውን ቃል
ይዘው መንፈስ ቅዱስ ወደ ነፍስነት ተቀይሮ ለሰው ልጅ ተሰጠው
የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይህ ግን ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡
የአሌክሳንደሪያው ቅዱስ ቄርሎስ እንዲህ ዓይነት አመለካከት
ላላቸው ወገኖች አንዲህ በማለት ይመልስላቸዋል፡-
በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት ሲል መንፈስ
ቅዱስ ለሰው ነፍስ ሆነው ብላችሁ ትተረጉማላችሁን? እንዲህ
ብሎ ማሰብ በራሱ በደል መሆኑን አትገነዘቡምን? እንዲህ
የምትሉ ከሆነ እንግዲህ ነፍስ የማትለወጥ ናት ማለት ነዋ !
ያም ማለት ለለውጥ አትገዛም፡፡ ሁል ጊዜም ባለመለወጥ
ትኖራለች ማለታችሁ ነው፡፡ ነገር ግን ነፍስ ለለውጥ የምትገዛ
ናት፡፡ ስለዚህም የማይለወጠውን መንፈስ ቅዱስን ወደ ነፍስ
ባሕርይ ተለወጠ በማለት ሳታችሁ፡፡ ስለዚህም እኛ እንዲህ
ብለን አናስተምርም፡፡ ነገር ግን ከማይለወጠው መንፈስ ቅዱስ
ነፍስ ተሰጠች እርሱዋም በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ከበረች
እንላለን፡፡
ከዚህ የምንረዳው ፍጥረት የሆነች ሕያዊት ነፍስ ከእግዚአብሔር
መሰጠቷን ነው፡፡ እቺን ነፍስ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በጸጋው
አምላኳዋን እንድትመስል ያግዛታል፡፡ አዳምና ሔዋን በበደላቸው
ምክንያት ያጡት የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ነው፡፡ ይህም ጌታችን
መድኃኒታችን በንፍሃት መንፈስ ቅዱስን በሐዋርያት ላይ
እስኪያሳድር ድረስ ቀጥሎ ነበር፡፡ (ዮሐ.21፡22)
እኛ የሰው ልጆች የመንፈስ ቅዱስን እገዛ በኃጢአት ምክንያት
ከማጣታችን የተነሣ ምንም እግዚአብሔርን በጸጋ
የምንመስልበት ተፈጥሮ ቢኖረንም አልተቻለንም ነበር፡፡ ወደዚህ
ወደ ቀደመ ክብራችን ለመመለስ ሰው ግዴታ ሊጠመቅና
ሰውነቱን የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ሊያደርገው ይገባል፡፡
እንዲህ ከሆነ በእርሱ ሰውነት ውስጥ ያደረው መንፈስ ቅዱስ
እግዚአብሔር አምላክን መስሎ የሚኖርበትን ጸጋ ያገኛል፡፡
በእርሱም በተፈጥሮ ያገኘውን እግዚአብሔርን የመምሰል አቅም
ተጠቅሞ በጸጋ እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ያድጋል፡፡
ስለዚህ አንድ ሰው በትክክለኛው ተፈጥሮ ለመኖር ከፈቀደ የግድ
ተጠምቆ ክርስቲያን በመሆን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ሊያገኝ
ይገባዋል፡፡ ያለበለዚያ ምኞት ቢኖረው እንኳ በትክክለኛው
ተፈጥሮ መኖር ይሳነዋል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ከቅድስት
ድንግል ማርያም በነሣው ሰውነቱ በኩል ሰው እንደሆነ እንዲሁ
እኛም ከመንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች በመሆን እርሱን በጸጋ ወደ
መምሰል ልንመጣ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ስለዚህ ሲያስረዳ
በሥጋዊ ልደት ካልተወለደ በቀር መንፈሳዊ የሆነውን እርሱን
ግዘፈ አካል አለው አንደማንለው ሁሉ አንዲሁ እኛም መንፈሳዊ
በሆነ ልደት ካልተወለድን በቀር መንፈሳውያን አንባልም
ይለናል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስም በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር ጽድቅን
መፈጸም እንደሚሳነን ሲያስረዳ የማደርገውን አላውቅምና
የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን
አላደርግም፡፡ በውስጥ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ
ይለኛልና፤ ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን
ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ ለዚህ ሞት
ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል ይልና በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ
ለዚህ መልስ ሲሰጥ እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን
ኩነኔ የለባቸውም፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ
ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና፡፡ ይላል
(ሮሜ 7፡15-25፣8፡1-2)
እንግዲህ እኛ ክርስቲያኖች እዳ አለብን እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን
እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብንኖር
እንሞት ዘንድ አለን፡፡ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብንገድል
በሕይወት እንኖራለን፡፡ (ሮሜ.8፡12-17) አሁን በአብ በወልድ
በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀን እግዚአብሔርን ለመምሰል
የሚያግዘንን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን አግኝተናል፡፡ ስለዚህም
ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው መልካምን ሥራ ለማድረግ
በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጥረናል፡፡ (ኤፌ.2፡10) ስለዚህ እንፍራ
ከአሁን በኋላ ለምንፈጽማቸው ኃጢአቶች ምንም ምክንያት
ማቅረብ አንችልም፡፡ ጽድቅን ከማድረግ ብንመለስ ወይም
እያወቅን ከመፈጸም ብንለግም ቅጣቱ በእኛ ላይ ይከፋል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ በውስጣችን ያደረውን መንፈስ ቅዱስን
ሰምተን ለመታዘዝና እርሱን መስለን ለመመላለስ ያብቃን፡፡
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም
ለዘለዓለሙ አሜን፡

ልጹ ደብዳቤ ለምን የአወዛጋቢነት ቁመና ይሰጠዋል? (የግል ምልከታ)

ልጹ ደብዳቤ ለምን የአወዛጋቢነት ቁመና ይሰጠዋል?
(የግል ምልከታ)
". . . በቤተ ክርስቲያኒቱ ፈቃድ ሳይሰጣቸው እና ሳያሳውቁ በየድንኳኑና አዳራሹ ጉባኤ የሚያካሂዱ መጻሕፍት፣ መጽሔት እና ጋዜጦች የመዝሙር ጋዜጦች በቤተክርስቲያኒቱ ስም የሚያሳትሙና የሚነግዱ ሁሉ ሕገ-ወጥ ተግባር እየፈጽሙ መሆኑንና በአሁኑ ጊዜ በልዩ ልዩ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የራሳቸውን ዓላማና ፍላጎት እያስተላለፉ ያሉ ተቋማት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውክልና ሳይሰጣቸው ሕገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ ግለሰቦች፣ ማኅበራትና ድርጅቶች ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማይወክሉ ስለኾነ ይኸው ሕገ-ወጥ ተግባራቸው ወደፊት እንዳይቀጥል ለኢ.ቤ.ኤስ የቴሌቪዥን ድርጅት እና የሚድያ አገልግሎት ኅትመት ለሚሰጡ ድርጅቶች እንዲሁም ለሚመለከታቸው ሚኒስቴር መ/ቤቶች በደብዳቤ እንዲገለጽ ኾኖ ከድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከኾነ ግን በሕግ የተሰጣትን መብቷን ማስከበር የግድ ስለኾነ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሕግ አገልግሎት በኩል የሕግ ክትትል እንዲደረግባቸው " ሲል የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በቁጥር ፴፭/፲፬/፳፻፰ በቀን ፳፫/፪/፳፻፰ ዓ.ም. ለጠቅላይ ቤተ ክህነት በተጻፈ ደብዳቤ ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡
ይኽንን ደብዳቤ ተከትሎ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለኢ.ቢ.ኤስ የቴሌቪዥን ድርጅት በሚል አድራሻ ". . . ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ሳይሰጣቸውና በቀጥታ ከኢ.ቢ.ኤስ የቴሌቪዥን ድርጅት ጋር ግንኙነት በመፍጠር እየተካሄደ ያለው ሕገ-ወጥ ድርጊት ሊታረም የሚገባ ድርጊት እንደመኾኑ መጠን ቤተ ክርስቲያናችን በሕገ መንግሥቱ የተሰጣትን መብት በመጋፋት በአሁኑ ጊዜ በልዩ ልዩ ሚድያዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የራሳቸውን ዓላማና ፍላጎት እያስተላለፉ ያሉ ተቋማት እና ግለሰቦች፣ ማኅበራትና ድርጅቶች ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማይወክሉ እና እውቅና ያልተሰጣቸው በመኾኑ ይኸው ሕገ-ወጥ ተግባራቸውን እንዳይቀጥሉ በጥብቅ እያሳሰብን ከአሁን በኋላ ግን ከቤተ ክርስቲያኗ ፈቃድ ሳይሰጣቸው እንደካሁን ቀደም ወደፊት እንዳይቀጥል የኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያው ፕሮግራማቸውን ተቀብሎ የሚያስተናግድ ከኾነ ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን ለማስከበር ሲባል የቴሌቪዥን ድርጅት በሕግ የምንጠይቅ መኾናችንን እየገለጽን. . ." በማለት በቁጥር ፰፻፷፭/ ፳፯፻፹፱/፳፻፷ በቀን ፯/፫/፳፻፷ ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ እገዳ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡
በእነዚህ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ደብዳቤዎች ውስጥ እገዳ የተጣለባቸው እነማን ናቸው? የሚለው አወዛጋቢ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡ "ሕገ-ወጥ" የሚለው ቃል ሊቀጸል የሚገባው ለእነማን ነው? ከእነዚህ ጋር ማኅበረ ቅዱሳን ሊደመር ይችላልን? ቀድሞውኑስ ለጊዜው የታወቁትን እና እንዲታገዱ የተፈለጉትን በስም ጠቅሶ ወደፊት ሊነሱ የሚችሉትን ደግሞ በጥቅሉ "ፈቃድ የሌላቸው" ማለት አይቻልም ነበርን?
በእርግጥ እንደ ኢ.ቢ.ኤስ. ላሉ ሦስተኛ ወገኖች የተጻፈው መልእክት ተጨማሪ ማብራሪያ ሊፈልግ እንደሚችል ማሰብ አይከብድም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እገዳው ተግባራዊ እንዲኾን ለጻፈው አካል ደግሞ ሙሉ በሙሉ ስለእነማን እንደተጻፈ ለመናገር መደናገር አይጠበቅም፡፡ ደብዳቤው እጁ የገባው የቴሌቪዥን አሠራጭ እነማንን እንደሚመለከት ለማወቅ ግርታ እንደተፈጠረበት ጠቅሶ እስኪታወቅ ድረስ ሥርጭቱን ለማቋረጥ መገደዱን አሳውቋል፡፡ በዚህ ጊዜ ወይ ሁሉንም በቤተ ክርስቲያን ስም መርሐግብር የሚያስተላልፉትን አለበለዚያም እገሌና እገሌ ብሎ መናገር መቻል ያለበት ለእኔ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ነው፡፡
ለዚህ ማብራሪያ የተጠየቀው ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግን ጉዳዩን ወደ ቋሚ ሲኖዶስ እንደመራው ታውቋል፡፡ መሠረታዊው ጥያቄ መነሣት ያለበት እዚህ ላይ ነው፡፡ የሕግ ጥያቄ ተነሥቶ ቢኾን ሕግ ተርጓሚ ወደኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ መምራቱ ምንም የማያሻማ ጉዳይ በኾነ፡፡ ነገር ግን ማንነትን የማጣራት ጥያቄ እንጂ የተነሣው የሕግ ጥያቄ አይደለም፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ በወጣው ደብዳቤ ላይ "ማኅበራት" የሚል ቃል ስላለ ብቻ ሕጋዊ እና ሕገ ወጥ ማኅበራትን በጅምላ እና በአንድ መነጽር መመልከት አይቻልም፡፡
አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ የሚባለው ብኂል ተፈጻሚ የኾነ ይመስላል፡፡ "ማኅበራት" የሚለው ቃል ስላለ ብቻ ማኅበረ ቅዱሳን እንዴት አብሮ ተጨፍልቆ ሊተረጎም ይችላል? ማኅበረ ቅዱሳን ሕገ ወጥ በሚለው ዘርፍ ፈጽሞ ሊፈረጅ የማይችል እንደኾነ ለመናገር ለእኔ ጥያቄው ከተነሣባት ቅጽበት አልፎ ሊውል ሊያድር መቻሉ አነጋጋሪ ኾኖብኛል፡፡ እንዲህ ለማለት መሠረታዊ ምክንያቶች አሉኝና፡፡
አንደኛ፡- ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ የተዋቀረ ሕጋዊ አካል ስለኾነ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በአንድ መምሪያ ወይም ሀገረ ስብከት ወይንም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ ሳይኾን የቤተ ክርስቲያን ላዕላዊ መዋቅር በኾነው በቅዱስ ሲኖዶስ ውሣኔ የተቋቋመ የአገልግሎት ማኅበር ነው፡፡ በዚህ ደረጃ የተዋቀሩት የቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ልማትና ተራድኦ ኮሚሽንን፣ የኪራይ ቤቶችን አስተዳደር፣ የሕጻናትና ቤተ ሰብ መምሪያን፣ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ከ፲፱፻፹፮ ዓ.ም. ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ተሰጥቶት በሕጋዊነት ተዋቅሮ እየሠራ ያለ ማኅበር ነው፡፡ ከዚያም በፊት ቢኾን በተለይ ከ፲፱፻፹፬ ዓ.ም. ጀምሮ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና በአበው ሊቃነ ጳጳሳት እስከ ፓትርያርኩ ድረስ ዕውቅና አግኝቶ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ መኾኑ ሊዘነጋ አይችልም፡፡
ይልቁንም ብዙ ጥናት ሲደረግበት ከቆየ በኋላ የማኅበሩ ደንብ በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ጸድቆ በሥራ ላይ የተሰየመ አንድ የእናት ቤተ ክርስቲያን ደጋፊ አካል ኾኖ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በየትኛውም መሥፈርት ይህንን አካል ሕገወጥ የሚል ያልተገባ ቃል መግለጥ አመክንዮአዊ አይኾንም፡፡ ከፍ አድርገን እንመልከተው ከተባለ ማኅበሩን በዚህ ጎራ መሰየም ቅዱስ ሲኖዶስን ከመዝለፍ ጋር ይመሳሰላል፡፡
ስለኾነም የተጻፈው ደብዳቤ በምንም ምክንያት ማኅበረ ቅዱሳንን እንደማይመለከት መናገር በልብ የታሰብን በአንደበት እስከመናገር ድረስ ካለው የጊዜ ክፍተት በላይ ሊውል ሊያድር የሚችል አልነበረም፡፡ ጅብን ሲወጉ አህያን ይጠጉ ዓይነት እንዳይኾን ስጋት አለኝ፡፡ ሕገወጥ የኾኑትን ለመቅጣት ሕጋዊውን ማስደንበር ለምን አስፈለገ?
ሁለተኛ፡- ማኅበረ ቅዱሳን ከተፈቀደለት መስመር አፈንግጦ ከኾነ በውስጥ ደብዳቤ ሊገሰጽ የሚገባው በመኾኑ
ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እጅግ በርካታ የኾኑ የደብዳቤ ልውውጦች ከፓትርያርክ ጽ/ቤት እስከ አኅጉረ ስብከት ብሎም እስከ ወረዳ ቤተ ክህነት ሲደረጉ ኖረዋል፡፡ አሁንም በዚያው መልክ ቀጥሎ ይገኛል፡፡ ሲያለማ እንደተመሰገነው ሁሉ ሲያጠፋም ሊገሠጽ ይገባዋል፡፡ ስለኾነም ጥፋት በፈጸመባቸው ጊዜያት ተግሣጽ ሲሰጠው የኖረ ማኅበር ነው፡፡ ሳያስፈቅድ የቴሌቪዥን መርሐግብር ሲያካሂድ ከተገኘም እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያን አካል በሚመለከተው ክፍል ተገቢው እርምጃ ሊወሰድበት የሚችል አካል ነው፡፡ ስለዚህ ለራስ አካል በሦስተኛ ወገን በኩል ትእዛዝ ይተላለፋል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ እናም ደብዳቤው ማኅበሩን በጭራሽ አይመለከተውም ለማለት አናመነታም፡፡
አሁንም በውስጥ ደብዳቤ ለጊዜው ማጣራት አስፈላጊ ስለኾነ ሥርጭቱን አቁም ቢባል በጸጋ ተቀብሎ ለማስተናገድ ችግር የሌለበት ማኅበር ነው፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ማኅበሩን የማይመለከት ስለኾነ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ይኽኛውን መንገድ እንዳልመረጠ መረዳት ይቻላል፡፡ ሌሎቹ ግን ምንም ዓይነት ሕጋዊ የሚባል ግንኙነት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር ስለሌላቸው የተጻፈው ደብዳቤ በቀጥታ እነርሱን እንደሚመለከት አያወላዳም፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከእነ መፈጠራቸውም ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት እንዳላገኘባቸው ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን በጉልበት ወይንም በማን አለብኝነት የቅደስት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ስም ይጠቀማሉ፡፡ እነርሱን በተመለከተ ውሣኔው ከማርፈዱ በስተቀር ምንም እንከን የለበትም፡፡
ዘገባ እያቀረበ እና እያስጸደቀ፣ ሂሳቡን እያስመረመረ፣ ትእዛዝ እና መመሪያ እየተቀበለ የእናት ቤተ ክርስቲያንን መዋቅራዊ ሰንሰለት ጠብቆ እየሠራ የሚገኝን ማኅበር አድራሻ ከሌላቸው አካላት ጋር መፈረጅ እንዳይመስልም ደጋግሞ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በየአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው በየአሕጉረ ስብከቱ ዘገባ ተካትቶ ሥራው የሚነገርለትን ማኅበር ከእነ እገሌ ጋር ጨፍልቆ ማሰብ አይመጥነውም፡፡
ሦስተኛ፡- ማኅበሩ ትምህርተ ወንጌልን በተለያዩ ዘርፎች እንዲያስተላልፍ የተፈቀደለት መኾኑ
ቀደም ሲል በጠቀስነው በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም. በጸደቀው የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደሪያ ደንብ ላይ በአንቀጽ ፬ ላይ የማኅበሩ ዓላማና ተግባር በሚለው ርእስ ሥር በቁጥር ፮ ላይ ". . . ትምህርተ ወንጌል በተለያዩ ዘዴዎች በመጽሔቶች፣ በጋዜጦች፣ በበራሪ ጽሑፎች፣ በካሴቶች፣ በኢንተርኔት፣ በኤሌክትሮኒክስ መገናኛ እና በመሳሰሉት እንዲስፋፋ ማድረግ . . ." የሚል ይገኛል፡፡
ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱም ኾነ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የወጡት ደብዳቤዎች በቀጥታ የሚመለከቱት ፈቃድ ያልተሰጣቸውን ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ስም የሚነግዱትን መኾኑ ግልጽ ሲኾን ማኅበረ ቅዱሳን ግን በማያሻማ ሁኔታ በማንኛውም የዘመኑ ጥበብ (ቴክኖሎጂ) በሚፈቅደው መንገድ ትምህርተ ወንጌልን ለማሠራጨት ፈቃድ የተሰጠው ገና በማለዳ ነው፡፡ በዚሁም መሠረት ላለፉት ፳፫ ዓመታት በተጠቀሱት መንገዶች ሁሉ ቃለ ወንጌልን ሲያሠራጭ ቆይቷል፡፡ አሁን ምንም የተለየ ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ ስለዚህ ደብዳቤው በየትኛውም መስፈርት ማኅበረ ቅዱሳንን ሊያካትት እንደማይችል እርግጠኛ መኾን ይገባል፡፡
በደንቡ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው በኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ትምህርተ ወንጌልን ለማስፋፋት ተፈቅዶለታል፡፡ ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ የሚለው ብዙ ዘርፎችን የሚያካትት ሲኾን ከእነዚህም መካከል አንደኛው የቴሌቪዥን ሥርጭት ይገኝበታል፡፡ ስለዚህ የፈቃድን ጉዳይ በማኅበሩ ላይ ማንሣት ተገቢ አይኾንም፡፡
ይሁን እንጂ ደብዳቤው የተጻፈለት አካል ጥያቄውን ማንሣቱ ስህተት አለበት ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እነዚህን ከላይ የተነሡትን መሠረታዊ ነጥቦች ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ ፈጣን ምላሽ ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ ጀምበር እስክትጠልቅ የሚያቆይ ምንም ዓይነት ብዥታ ወይንም ግርታ ሊፈጠርበት በማይችለው ጉዳይ ላይ ውሎ ማደሩ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ነውና አሁንም ሌሎች ተጨማሪ ቀናት እንዳይባክኑ ቢደረግ ሠናይ ነው፡፡
የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ በዚህች አጋጣሚ ሰርጎ ለመግባት በር የሚከፈትላቸው አካላት መኖራቸው ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ክፍተቱን እንደ በጎ አጋጣሚ በመውሰድ በቴሌቪዥን ጣቢያው ለመጠቀም በርካታ ተቃራኒ አካላት ማሰፍሰፋቸው እየተሰማ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዋነኛው የቤተ ክርስቲያን ጠላት ተብሎ የተወገዘው "የከሣቴ ብርሃን" ሐራጥቃ ተሐድሶ ይገኝበታል፡፡ ከእርሱም ባሻገር ከነባሮቹ በቤተ ክርስቲያን ነጋዴዎችም በኩል ሌላ የፍቀዱልን ውስጣዊ ግፊት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ስለኾነም፡-
፩. የማጣራቱ ጉዳይ ቶሎ እልባት አለማግኘቱ ዕድሉን ለሌሎች በሰፊው መክፈት ይኾናልና በፍጥነት ውሣኔ ቢሰጠው እና ማኅበሩ ወደጀመረው አገልግሎት እንዲቀጥል ቢደረግ፡፡
፪. ግርግሩን ምክንያት በማድረግ በደብዳቤው የታገዱት ሁለት አካላት ፈቃድ እንዲሰጣቸው አንዳንድ ሰዎች ሀሳብ እያቀረቡ እንደኾነ መሰማቱ ከፍተኛ ተቃውሞ እያስነሳ ይገኛል፡፡ ለማኅበረ ቅዱሳን በመፍቀድ ሰበብ ሌሎችም የዚህ ጽዋ ተቃማሽ እንዲኾኑ ለማድረግ ያደቡ ሰዎች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ይኽ ከተደረገ ግን ማጣፊያ የሚያጥረው ስህተት ይኾናል፡፡ ስለዚህ ደግመው ደጋግመው አባቶች እዲያስቡበት ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ከሚደረግ የማኅበረ ቅዱሳንም አገልግሎት ቢዘገይ እመርጣለሁ፡፡ ምክንያቱም ለእነዚያ ሰዎች ሙሉ ዕውቅና ከመስጠት የማይተናነስ ድርጊት ስለሚኾን፡፡ ብዙ ጊዜ አንድ ጊዜ በኾነች ሰበዝ ልክ የተሰፋችን አለላ ነጥሎ ለማውጣት ስንቸገር ዐውቃለሁና፡፡
፫. በተጻፉት ደብዳቤዎች ውስጥ "ሕገ-ወጥ" የሚለው ቃል በተደጋጋሚ ሲጠቀስ እንመለከታለን፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም ኾነ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እነዚህን ደብዳቤዎች ሲጽፉ ሕገወጥ የኾኑ አካላት መኖራቸውን ያረጋግጣል፡፡ እነዚህ ሕገወጥ እየተባሉ የተጠሩት አካላት አሁን ተመልሰው ሕጋዊ የሚኾኑበት መንገድ ሊኖር አይችልም፡፡ ጥንትም ሕገወጥ ተብለዋልና፡፡ ማኅበራት የሚለው ቃልም የተጠቀሰው ከእነርሱ መካካል ማኅበር መሥርተናል እያሉ የሚናገሩ በመኖራቸው የተጠቀሰ ቃል እንጂ ነው

የድል ምልክት ነሽ

የድል ምልክት ነሽ
ይህ ነውጠኛ ሥጋ- መተኮሻ ቀስቱ - ነፍሴን ባቆሰለ
ከደመ ነፍሳዊ- እሳታዊ ግለት- ወላፈን የጣለ
በጦሩ አውድማ- በሕይወቴ ዓለም- በዘመቻ ስፍራ
በስጋዬ ቃታ- በ’እጅ ስጥ ድምጾች- ነፍሴ ተወጥራ
ከተሰበቀላት- ከቀስቱ ኢላማ- ቅጽበት መታደጊያ
ከአስጨናቂው ሰዓት-ባልታሰበ ቅጽበት- አንቺ ነሽ መትረፊያ
አንቺ ነሽ መመኪያ፡፡
በቁጣ ለመጣው- በትእግስት የሚቆም- የእስራኤል ጦረኛ
ቆሞ ለተረታው- ተዋግተሸ ‘ምትረቺ- አንቺ ነሽ ሠልፈኛ
በኢሎፍሊ ምድር- ዳጎል በገነነ- አምላኩን ሲረሳ
የፍልስጤም ትምክሂት- በሚያስፈራ ጊዜ- ሊያጠፋን ሲነሳ
ያንን አንገት መድፋት- ያ የልብ ስብራት- የእስራኤል እሮሮ
የህዝቡን ክፉ ውርደት- የሀገሩን ዋይታ- የሀዘን እንጉርጉሮ
የሚያቆም አንድ አባሽ- የሚያጽናና ጋሻ- ቀስቱን የሚመክት
የኑሮውን ዳጎል- በኢሎፍሊ ሰባብሮ- የሚሆን መድኃኒት
ሽተን ባጣን ጊዜ- የድል ተስፋ ጮራ- ከምድር ሲፈለግ
በምስራቅ የበቀልሽ- ጽዮን ሆይ አንቺ አለሽ- ባለ ፍሬ ሀረግ
ነሽ አንቺ ታዳጊ- በአንገት መድፋት ሀገር- ድልን አስታጣቂ
ሺ ሆነው ሲሸነፉ- አንድ ሆነሽ ብቸኛ- ጠላት አስጨናቂ
ከምርኮ በክብር- በዚያ ሠረገላ- ለነ አሚናዳብ
ለነ አቢዳራ- የቤታቸው ሞገስ- የደስታቸው ወደብ
ለነ ዳዊት ሀሴት- ለነ ኦዝያ ቅስፈት- እርግማን ለሜልኮል
ከዲያብሎስ ወጥመድ- ድል ነሺ ‘ሚሆንብሽ- መንፈሳዊ አካል
የሚገዳደሩሽ- ጽዮንን የጠሉ- ከዓላማ እንዳይደርሱ
ትዕቢት ለሞላቸው- ፍሬ አልባ እንደሆነው- ልክ እንደ በለሱ
የምስጢርሽ ንባብ- ፊደል ላልገባቸው- አንቺን ላቀለሉ
ክብርና ፍቅርሽን- ረግጠው ለሚሄዱት- ቀምሰው ላልታደሉ
ወየው ወየው ብሎ- በሚጮህ ሰባኪ- ፌዝን የታጠቁ
ከታሪክ
ከትንቢት
ጽዪንን መገዳደር-
በውርደት ሜዳ ሆነው- በቅዠት ተይዘው- ድል መጮህ መሆኑን- ምነዋ ባወቁ?
ለሽባው ምድራችን- ለዚህ ችግረኛ- ለታማማው ዓለም
ስድብ ለጎበኛት- ለቁስለኛ ሔዋን- ለተጎዳው አዳም-
ለነቢያት ጩሀት- የለቅሶአቸው ፍሬ- የእንባቸው ዋጋ
ለተሰጠው ተስፋ- ምክንያት የሚሆን- ከሚዛመድ ሥጋ
ለሥዱድ ኤርሚያስ- ለለምጻም ኢሳይያስ- እንዲሁም ዳንኤል- (ምጥው ለአንበሳ)
የሰው ልጅ እንዳይሆን - ተስፋ እንደ ሌለው- እንደ ዱር እንስሳ
ዲያብሎስ ለጣለው- በሥርቆት በዝሙት- ሕይወቱ ላደፈው
በትእቢት ፍላጻ- በፍቅር ንዋይም- ልቡን ለሰየፈው
በዚያ አስፈሪ ጊዜ- ዋስ ጠበቃ ጠፍቶ- ሲያስፈራ እሳቱ
አንቺ ነሽ መዳኛ- ጽዮን መሸሸጊያ - የድል ምልክቱ፡፡
(አክሊሉ ደበላ 2008ዓ.ም)
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን!!!

"ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ ዘምሩ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ። እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና በማስተዋል ዘምሩ።" ይላል፡፡ መዝ ፵፮፥፮-፯

ቀደም ብለው በገጸ ጦማሬ ከተለጠፉት ጽሑፎች መካከል ያልደረሳቸው ይደርሳቸው ዘንድ . . .
መዝሙር እንዴት ይደመጣል?
ዓባይነህ ካሤ - ዲን
ሰሞኑን አግሮቼ ወደ አንድ ቢሮ ይዘውኝ ገቡ፡፡ በዚያም ቢሮ ውስጥ በርካታ መንፈሳውያን እንዳሉ በሚያረጋግጥ ሁኔታ ከአንድ ኮምፒውተር ላይ አንድ መዝሙር ለስለስ ብሎ ይደመጣል፡፡ ታዲያ እኔም ለመጠየቅ ያኽል የምቀርባቸው ሰዎች ነበሩና ለመኾኑ እያዳመጣችሁት ነው ወይንስ እየሰማችሁት? የሚል ጥያቄ ሰነዘርሁላቸው፡፡ ለካ የሁሉም ጉዳይ ነበረና ሁሉም ስሜቱን መግለጥ ጀመረ፡፡ የሚገርመው መዝሙሩ የሚሰማበት ኮምፒውተር ባለቤት ከፍታው ስለወጣች ውይይቱን የተቀላቀለችው ዘግየት ብላ ነበር፡፡
ሁሉም ሰው በአንድ ነገር ተስማማ፡፡ እርሱም "ባናዳምጠውም የሚያረጋጋ መንፈስ ስለሚፈጥርልን እንዲሁ ስንከፍተው ደስ ይለናል" የሚል ነበር፡፡ እኔም በኩሌን ሀሳብ ሰንዝሬ ተስማምተን ተደማምጠን የሄድሁበትንም ሳልረሳ ወጣሁ፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ በአእምሮዬ እየተመላለሰ ከዛሬ ነገ ሀሳቤን እሰነዝራለሁ ስል የከረምሁበት አጀንዳ ነበረና የእነዚያ ወንድሞች እና እኅቶች ውይይት የበለጠ አነቃኝ፡፡ እናስ እንዴት መዝሙር ይደመጥ?
ዘመረ አመሰገነ ነው፡፡ ስለዚህም መዝሙር ማለት ምስጋና ማለት ነው፡፡ ምስጋና ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ ምስጋና በዜማ ፣ ምስጋና በጸሎት ፣ ምስጋና በጽሑፍ ፣ ምስጋና በአርምሞ ሊቀርብ የሚችል መሥዋዕት ነው፡፡ መዝሙር ስንል በልቡናችን ሰሌዳ ወለል ብሎ የሚታየን ግን በዜማ የሚደረገው ምስጋና ነው፡፡ ይኽም በዜማ የተዋዛ መዝሙር ምስጋና ብቻ ሳይኾን ጸሎትም ነው፡፡ ጸሎትም ምስጋናን ከልመና ያስተዛዘለ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ትምህርትም ነው፣ ደግሞም ምስክርነት ነው፡፡ ያመንነውን እንናገርበታለንና !
ዛሬ ዘመኑ ፈቀደልንና በድቃቂ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የፈለግነውን ያኽል ፋይሎች ይዘን በፈለግነው ቦታ ጥቅም ላይ እናውላለን፡፡ የቅጂ መብት ጉዳይ እንዳታነሡብኝ እንጂ መዝሙራትም እንዲሁ ኾነዋል፡፡
እንዲህ ከኾነ መዝሙር ስንከፍት ምን ልንጠነቀቅ ይገባል?
፩. ማዳመጥ መቻላችንን ማረጋገጥ
ቅዱስ ዳዊት "ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ ዘምሩ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ። እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና በማስተዋል ዘምሩ።" ይላል፡፡ መዝ ፵፮፥፮-፯። ከቅዱስ ቃሉ እንደተረዳነው ሲዘመር ማስተዋል ግዴታ ነው፡፡ መንፈስን ሳይሰበስቡ ምስጋና የለም፡፡ ልቡናን ሳያዘጋጁ ምስጋና የለም፡፡ መዝሙር ጸሎት ነው ብለናል፡፡ ስንጸልይ በአንቃዕዶ ልቡና በሰቂለ ኅሊና መኾን ይገባናል፡፡ "ስትጸልዩ … በከንቱ አትደገሙ" ተብለናልና፡፡ ማቴ ፮፥፯።
በሥራ ላይ እያሉ መዝሙር መክፈት የማናዳምጠው ከኾነ ምን ይረባናል? በተሰበሰበ ልቡና ኾነን ማቅረብ የሚገባንን ዝማሬ እንዴት በሜዳ ላይ? ከምንም በላይ ደግሞ እኛ የታላቁ ቅዱስና ሊቅ የቅዱስ ያሬድ ልጆች ይህ ሲጠፋን ማየት ይከብዳል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በደጉ ንጉሥ በአጼ ገብረ መስቀል ፊት ዝማሬውን ሲያቀርብ እርሱም ንጉሡም በተመስጦ ላይ ስለነበሩ በምድር ላይ እየኾነ የነበረውን እስከመርሳት ደርሰው ነበር፡፡ ንገሡ በበትረ መስቀላቸው የቅዱስ ያሬድን እግር እንደወጉት አላወቁም ነበረ፡፡ እርሱም ደግሞ ይበልጡኑ እገሩን በጦር መወጋቱ አልታወቀውም ነበር፡፡
ከምን የመጣ ነው? ከተባለ በእግዚአብሔር ፊት በልዩ ተመስጦ ኾነን ልናቀርበው የሚገባን ምስጋና ነውና ከተመስጦ የተነሣ በጦር መወጋትንም ኾነ መወጋት እስከመርሳት ደርሰዋል፡፡ ያለበለዚያ ዘጠኝ እንደጣደችው ሴት እንኾናለን፡፡
አሁን አሁን የምናየው ድርጊት ግን ከዚህ በጣም የራቀ እየኾነ ይገኛል፡፡ አንዳንዶች ክርስቲያን መኾናቸው ይታወቅላቸው ዘንድ፡፡ ሌሎች ደግሞ በእምነት የማይመስሏቸውን "ለመበቀል"፡፡ እኔም መዝሙር አለኝ ዓይነት ፉክክር፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከዘፈን ይሻላል ከማለት፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን እኛ የምንዘምረው ለአገሩ ለመንደሩ ወይ ለጋራ ሸንተረሩ ሳይኾን ለራሳችን መኾኑን አለመዘንጋት ነው፡፡
እንዲህ ከተስማማን ደግሞ መቼ እና እንዴት ማድረግ እንዳለብን ልንወሥን ይገባል፡፡ ሌላው ቀርቶ በቤታችንም ስንከፍት እያዳመጥነው መኾናችንን ማረጋገጥ ግዴታ ነው፡፡ ቤቱ የኦርቶዶክስ ነው፣ ወይንም ደግሞ እኛም መዝሙር አለን ዓይነት በቃለ እግዚአብሔር ላይ ጨዋታ አያስፈልግም፡፡
ዛሬ ዛሬ የምናየው ሁኔታ ግን እጅግም ደስ አያሰኝም፡፡ እንዲያው ስንቱን ተችተን እንዘልቀዋለን ከሚል ዝም የሚባሉ ድርጊቶች ወግ፣ ባሕል፣ ሥርዓት እስከመኾን ሲደርሱ ማየቱ ደግሞ የበለጠ ያምማል፡፡ ጥቂት ድግስ ደግሶ የቤቱ ጣሪያ እስኪገለበጥ ድረስ መዝሙር መክፈት ምን ይሉታል? የተጠራው እንዲሰማ ከኾነ በልኩ በመጠኑ ያለበለዚያ በወግ በጨዋታ በሳቅ እና በሁካታ መካካል መዝሙሩ ቢከፈት ለቃለ እግዚአብሔር የሰጠነው ቦታ ምን ላይ ነው?
፪. በእግዚአብሔር ፊት እንደቆምን ማሰብ
መዝሙር ከመዘመራችን በፊት በዓይነ ኅሊናችን በልዑል እግዚአብሔር እና በቅዱሳኑ ፊት እንደቆምን ልናስብ ይገባል፡፡ ምስጋናው ለእግዚአብሔር እና እርሱ ላከበራቸው ቅዱሳኑ ነውና እንደምናያቸው እያሰብን አኮቴት ማቅረብ ይኖርብናል፡፡ ማርያም እኅተ አልዓዛር "የማይቀሟትን በጎ ዕድልን መርጣለች" የተባለችው ልቡናዋን ሰብስባ በጌታዋ እግር ሥር ቁጭ ብላ ቃሉን በመስማቷ አይደለምን? ሉቃ ፲፥፵፪። መዝሙርም ይኽን የመንፈስ ዝግጅት ይፈልጋል፡፡
ቅድስት ልድያ ልቡናዋ ተከፍቶላት ቃለ እግዚአብሔርን ሰምታ ክርስትናን ተቀብላ ከነቤተሰብዋ የተጠመቀቸው ፣ ቅዱሳንንም በቤቷ እስከማስተናገድ የደረሰችው በአንቃዕዶ ኅሊና በማዳመጧ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት የለበሰውን የማዕረግ ልብስ ወልቆበት እንደ ተራ ሰው እስኪመስል ድረስ በታቦተ ጽዮን ፊት የዘመረው ከፊቱ የቆመውን ስላወቀ ነው፡፡ ፪ ሳሙ ፮፥፲፮።
በእኛም ዘንድ ይህ ሊለመድ ይገባል፡፡ በጥቂት በጥቂቱ ራሳችንን እያረምን መስተካከል ከእኛ ከክርስቲያኖች ይጠበቃል፡፡
፫. ሌሎች ሰዎችን አለመረበሽ
ከዚህ በላይ ያሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ካሟላን ቀጥሎ ሊያሳስበን የሚገባው በዙሪያ ገባችን ያሉት ሰዎች ናቸው፡፡ መቼም የመንዘምረው ሰውን ለማናደድ ፣ ወይም ለማብሸቅ አይደለም፡፡ ለወንድም ለወገን ሲባለ ብዙ የሚተው ነገር ይኖራል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሥጋ መብላቴ ወንድሜን የሚያሰናክል ለኾነ ለዘለዓለሙ ሥጋ አልበላም ያለው ሥጋ መብላት የሚወገዝ ኾኖ አይደለም፡፡ ፩ ቆሮ ፰፥፲፫። ነገር ግን ስለ ሌላው ኅሊና ሲባል ይተዋል፡፡ ክርስትና እንዲህ ነው፡፡ ከራስ አልፎ ለሌሎች የሚኖሩት ሕይወት!
ብዙ የዓለም ነገሮችን የምንጾመው በሕግ በሥርዓት ስለተደነገጉ ብቻ አይደለም፡፡ እንደየደረጃችን ለሰዎች ስንልም ራሳችን በራሳችን ቅር ሳይለን በደስታ የምንተዋቸው ጉዳዮችም አሉ፡፡ ስለዚህ ሁሉ ነገር ተመቻችቶልን ነገር ግን የአካባቢያችን ሁኔታ ያልተመቸ ቢኾን ከእኛ ስንፍና የተነሣ አይሁን እንጂ ብንተው በስውር የሚያይ አምላክ በግልጥ ይከፍለናል፡፡
ደግሞም ጮክ ካለው ይልቅ በለሆሳስ ያለው የበለጠ ውስጥ ድረስ ዘልቆ ይሰማል፡፡ ስለኾነም መዝሙሮቻችን ለእኛ የሚደመጡ ሌላውን የማይረብሹ መኾናቸውን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ከፍ ያለ የመንፈስ ልዕልና ያለን፣ ተቃዋሚዎች እንንቀፍ ቢሉ እንኳ ምክንያት የማይገኝብን ልንኾን ያስፈልጋል፡፡ መጽሐፍ "አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም።" ፪ ቆሮ ፮፥፫። ደግሞም ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ "ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፥ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፥ በሚጎበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን።" እንዳለው ከሕዝብም ከአሕዛብም ምክንያት ሊገኝብን አይገባም፡፡ ፩ ጴጥ ፪፥፲፪።
ቀረኝ
በእጅ ስልኮቻችን ማለትም በተንቀሳቃሽ ስልኮች የጥሪ ድምጽ ያደረግናቸው መዝሙሮችስ አያሳዝኗችሁምን? አንዳንዶች ገና የእግዚአብሔርን ስም ጠርተው ሳይጨርሱ " እግ" እንዳሉ ጉሮሯቸውን ይታነቃሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ሲጠሩ ይውላሉ እንጂ ምን እንደሚሉ የሚሰማቸው የለም፡፡ የደወለውን ሰው ማነጋገር ያልፈለጉ እንደኾን ደግሞ ድምጻቸው ይዘጋል፡፡ እንዲያው ምኑ ቅጡ፡፡ ግን ይኽ ሁሉ የሚኾነው ለእግዚአብሔር በሚቀርበው መዝሙር ላይ ነውን? ጎበዝ በጊዜ ወደ ልቡናችን እንመለስ፡፡ ጨርሶ ለተንቀሳቃሽ የስልክ መጥሪያ መዝሙራትን መጠቀም ከዓላማው ጋር አብሮ አይሄድምና እባካችሁ ስልኮቻችሁን አስተካክሉ፡፡

Yeweyin Fikir

Yeweyin Fikir
የድል ደስታ የድል ዜና
ጽዮንን ክበቧት ለምስጋና
በያሬድ ውብ ዜማ በበገና
ንሴብሆ እንበል በትህትና።
አማናዊት ጽዮን ማርያም
ኪዳንሽ ጽኑ ለዘለአለም
የተማፀነሽ ከቶ አያፍርም
አንቺን ሸልሞናል መድኀኒአለም።
በአዛጦንምድር ያሉ ነፍሳት ሁሉ
ተጨንቀው ሲጮሀኹ ወየው ወየው ሲሉ
የተዋህዶ በር ፀጋ የመስቀሉ
ቅድስተ ቅዱሳን ቤዛዊተ ኩሉ
ታላቅ ነገር ሰራች እሰይ እልል በሉ።
ድንቅ ታምር ሠርታ ያመፁ ተማረኩ
እጅ መንሽ ሰጥተው ታቦቱንም ላኩ
ለህያዋን አምላክ ፈርተው ተንበረከኩ።
ለማይናገረው ዳጎኑ ጠዖት
ምስሉን አቁመው ሲሰግዱለት
እጅና እግር አለው አይሄድበት
አፍና አፍንጫው ታይቶ ለምልክት
ከቶ አይንቀሳቀስ ቀን ከሌሊት
ደረቅ በድን ነበር የሌለው ህይወት።
ታዲያ በዚች ቀን በዙ ታምር ሆነ
የአምላክ ቸርነት ፍቅሩ ተከወነ
በህያው ምስክር ሁሉ አመነ
የከሳሽ ፉከራ ጉድጓድ ተደፈነ
የድንግል ማርያም ልጅ
ክርስቶስ ገነ።
እምዬ ኢትዮጵያ በጣም ደስ ይበልሽ
የኦሪቱን ዘመን ታቦት ተቀብለሽ
በአዲስ ኪዳኑም መስቀል ተሸልመሽ
ጠላትን ማምከኛ የፀናው እምነትሽ
ነገም እንደ ትላንት ዛሬም
ያኔን ሆነሽ
ተነሺ ለምኚ ይዘርጉ እጆችሽ።
የክህደት አርበኛ መንፈስ የባህሩ
ትውልዱን በጉርሻ ቀድሞ ማባረሩ
በሽንገላ ከንፈር መስሎ መደርደሩ
እውነት ተጋርዶበት እንዳያቅ ሚስጢሩ
የያዘውን ረስቶ ደጅ ላይ ማደሩ
በምክረ አጋንንት እርቋል ከፍቅሩ
ስቶ እያሳተ ልቦናን ማወሩ
ታይቷል ሃራጥቃ ይኽው ምስክሩ።
አማናዊት አንባ የፀሐይ እናት
የትውልድ መፅናኛ ፍሬ በረከት
ቅድስተ ቅዱሳን ኪዳነምህረት
ምልጃሽ ይታደገን ወጥቶ ከመቅረት።
የጽዮን ከተማ የዳዊት ሀገር
በኦሪቱ ዘመን መጠጊያ መንደር
በአዲስ ኪዳኑ የወንጌል ማህደር
ድንግል ማርያም ናት መሠረተ ፍቅር
አማኝ ተሰብሰቡ ኑ ና እንዘምር።
ሠይጣን ተሸነፈ እጅግ ተጨነቀ
በኤልሻዳይ ሥልጣን እነሆ ደቀቀ
ዳግም ላይነሳ ተረግጦ ወደቀ
የእርሱ ያልሆኑትን በሙሉ ለቀቀ።
ልክ እንደ አዛጦን ዘመን ዛሬም እየሳቱ
አምላክን እርቀው ጠዖት የሚያሸቱ
ሥሙን እየጠሩ ሞት የሚጎትቱ
በኑፋቄ ትምህርት እየተንገላቱ
አሉ ለምድ ለባሾች የከንቱዎች ከንቱ።
መጽሐፉ ሲገለጥ በሣሙኤል መልእክት
የታቦተ ጽዮን አስገራሚው እውነት
ፈጦ እየታየ የክርስቶስ ምህረት
ዛሬም ይክዳሉ አይልም በማለት
ይከራከራሉ በታቦት በጽላት።
ወገን እናስተውል በጥበብ እንመርምር
ገልጠን ስናነበው የአንድምታውን ሚስጢር
እርሱ ሆኖ ሳለ የዘለአለም መምህር
ኑ አድምጡኝ ብሎ አዶናይ ሲናገር
ሰመተናል አይተናል በዕምነታችን በር።
ስለዚህ አስተውል ሕዝበ እግዚአብሔር ሆይ
ከሠማይ የመጣው ኢየሱስ ኤልሻዳይ
ብርሃን ሊሆነን ነው የማይጠልቀው ፀሐይ
እንማር እንጠይቅ ስለ ሀይማኖት ገዳይ።
እንኳን አደረሰን ለዚች እለት

ጋኔንን በመዛመድ ማሳሳት

ጋኔንን በመዛመድ ማሳሳት----------ዓባይነህ ካሤ (ዲን)
"የአጥማቂዎቹ" ምስክሮች እና አዲስ "ዶግማቸው"
አንዳንድ "አጥማቂ" ነን ባዮች በያሉበት ከዚህ ቀደም በቅድስተ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ "ምስክር" እያስተዋወቁን ነው፡፡ የእነርሱን ምስክር ከማየታችን በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቅና የተሰጣቸውን ምስክሮች ቀድመን ማየት ይጠበቅብናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች ያላቸው የሚከተሉትን ነው፡፡
፩. ሥሉስ ቅዱስ
ከምስክር ሁሉ በላይ የኾነው ምስክር እግዚአብሔር ስለራሱ የሰጠው ምስክርነት ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍጹም ነውና ከእርሱ በላይ ስለእርሱ ሊነግረን የሚችል የለም፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ " እግዚአብሔርን ያየው አንድስ እንኳ የለም፡፡ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው" ሲል የደመደመው፡፡ የሐ ፩፥፲፷። አብን በወልድ ምስክርነት እንዳወቅነው ሁሉ ወልድንም በአብ ምስክርነት ዐውቀነዋል፡፡ መንፈስቅዱስንም እንዲሁ በአብ እና በወልድ ምስክርነት እንዳወቅነው ሁሉ አብና ወልድም ስለመንፈስቅዱስ መስክረዋል፡፡
ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን ስለራሱ ሲመሰክር በሙሉ ሥልጣኑ እንዲህ አለ፡፡ "ኢየሱስ መለሰ አላቸውም፦ እኔ ስለ ራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው" ዮሐ ፷፥፲፬። የባሕርዪ አባቱ የአብን ምስክርነት ደግሞ እንዲህ በማለት ይገልጠዋል፡፡ "እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፥ ይህ የማደርገው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና። የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል፡፡" እንዲል፡፡ ዮሐ ፭፥፴፮-፴፯።
እውነት ነው! በባሕረ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ጌታችን ሲጠመቅ አብ በደመና ኾኖ "በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው" ሲል ሰምተነዋል፡፡ ማቴ ፫፥፲፯። ደግሞም በደብረ ታቦር (በታቦር ተራራ) ይኸንኑ ቃል አብ እዚያው በሰማያት ኾኖ ሲደግመው ሰምተናል፡፡ "ከደመናው፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።" እንዲል ፡፡ ማቴ ፲፯፥፭።
መንፈስ ቅዱስም ስለ ወልድ የባሕርዪ አምላክነት ሲመሰክር በአምሳለ ርግብ ኾኖ በላዩ ላይ ሲያርፍ ዐይተናል፡፡ "የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ ዐየ" እንዲል፡፡ ማቴ ፫፥፲፮። ጌታችንም ከዕርገት በኋላ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ቅዱሳን ሐዋርያት እንደሚቀበሉ የተሰወረውን ምስጢር ሁሉ እንደሚገልጥላቸው ደግሞም ስለእርሱ የባሕርዪ አምላክነት ከመንፈስቅዱስ እንደሚሰሙ ሲናገር "ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል" ብሎ ነበር፡፡ ዮሐ ፲፭፥፳፮።
፪. ሥራው
ጌታችን እንደሰውነቱ ያደረጋቸው ሥራዎች እንዳሉ ሁሉ እንደ አምላክነቱ ያደረጋቸው ሥራዎችም አሉ፡፡ ነገር ግን እንዚህን ሁሉ ሰፍረን ቆጥረን ዘርዝረን አንዘልቃቸውም፡፡ ነገር ግን የባሕርዪ አምላክ የሚያደርገውን ሥራ በዘመነ ሥጋዌው እኛን በሚገባን ደረጃ ሲፈጽም ስለኖረ ከሥራው ማንነቱን ልናውቅ ችለናል፡፡ ስለዚህም የጌታችን ሥራው ለአምላክነቱ ምስክር ነው እንላለን፡፡ ለዚህም ነው "እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤ ባደርገው ግን፥ እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።" ሲል የተናገረው፡፡ ዮሐ ፲፥፴፯-፴፷። ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ አብን አኽሎ አብን መስሎ የአብን ሥራ ለማድረግ ሥላጣን ያለው ከአብ ጋር የተካካለ መኾኑን ሥራው ይመሰክራልና ሁለተኛው ምስክር ሥራው ነው፡፡
፫. ቅዱሳን
ከራሱ ከእግዚአብሔር እና ከሥራው ቀጥሎ በምስክርነት የሚጠቀሱት ቅዱሳን ናቸው፡፡ ቅዱሳን ስንል ቅዱሳን መላእክትን እና ቅዱሳን ሰዎችን ያጠቃልላል፡፡ በተለይም ቅዱሳን ሰዎች እስከሞት ድረስ ሥጋቸው እየተተለተለ፣ በሰይፍ እየተቀሉ፣ በመጋዝ እየተተረተሩ፣ በእሳት እየተቃጠሉ በብዙ መከራ ውስጥ እያለፉ የመሰከሩ ናቸውና ሰማዕታት ተብለዋል፡፡ ሰማዕታት ማለት ምስክሮች ማለት ነው፡፡
ጌታችን ደቀመዛሙርቱን "እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ።" ያላቸው ለዚህ ነው፡፡ ሉቃ ፳፬፥፵፷። ለዚህም ነው ቅዱሳን ሐዋርያት "እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት።" ሲሉ የተናገሩት፡፡ ሥራ ፲፥፴፱። ደግሞም "ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።" እንዲል፡፡ ሥራ ፩፥፷።
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ "ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ።" የተባለው ምስክርነቱ ብርሃን ለተባለ ለክርስቶስ ነበረ፡፡ ዮሐ ፩፥፯። ስለዚህ በቅዱሳኑ ምስክርነት እናምናለን፡፡
፬. ቅዱሳት መጻሕፍት
በአራተኛ ደረጃ ቅዱሳት መጻሕፍት የክርስቶስ ምስክሮች ናቸው፡፡ ይህንንም መጽሐፍ "እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው" በማለት ያረጋግጥልናል፡፡ዮሐ ፭፥፴፱። ከቅዱሳት መጻሕፍት መካከል ወንጌል ቅድምና ያላት ምስክር እንደኾነች ጌታችን እንደዚህ ሲል ነግሮናል፡፡ "ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።" ማቴ ፳፬፥፲፬።
የጠቀስናቸውን ምስክሮች ልብ ብለን እንመልከት፡፡ ጌታችን ራሱ ምስክር ብሎ የጠራቸውን እንጂ በእኛ መላምት የመረጥናቸው እንዳልኾኑ ልብ እንበል፡፡ እናም በባሕርዪው ቅዱስ ለኾነው እግዚአብሔር ምስክሮቹም ቅዱሳን ናቸው፡፡ ስለኾኑም ቅዱስ ዳዊት "ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው፤ ስለዚህ ነፍሴ ፈለገቻቸው።" ሲል ይናገራል፡፡ መዝ ፻፻፲፰፥፻፳፱። እነዚህን የመሳሰሉ ስለክርስቶስ ሲመሰክሩ እናውቃለን፡፡ አሁን አሁን ግን አንዳንድ አሳቾች "የአጋንንትን ምስክርነት" ማስረጃ እያደረጉ በተለያየ መልኩ ለገበያ በማቅረብ ኪሳቸውን እያደለቡ ይገኛሉ፡፡
የአጋንንት ምስክርነት የሚባልስ አለን?
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሌለ እንግዳ ነገር እያመጡ ሕዝብን ማደናገር ስህተት ብቻ ሳይኾን የሚያስወግዝ ድርጊት ነው፡፡ እኛ የምናውቀው ጌታ አጋንንት ስለእርሱ ለመናገር አፋቸውን ሲከፍቱ ጸጥ ያደረጋቸውን ነው፡፡ ጌታችን ወደቅፍርናሆም ሲገባ ርኩስ መንፈስ ያደረበትን አንድ ሰው አገኘ፡፡ በሰውየው ላይ ያደረው ክፉ መንፈስም ገና ምንም ሳይባል መቀባጠር ጀመረ፡፡ እንዲህ እያለ "የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ።"
ንጹሐ ባሕርዪ ጌታችን ንጹሕ ምስክርነት እንዲሁም ምስጋና ከንጹሐን ይቀበላል እንጂ ከርኩሳን መናፍስት አይቀበልምና "ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው።" ማር ፩፥፳፭። ሲያጸናውም ከዚህ ሰው ወዲያ ሌሎች አጋንንት ያደሩባቸውን ሰዎች ሲፈውስ አጋንንቱ እርሱ እግዚአብሔር መኾኑን ስላወቁ ያወቁትን እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም፡፡ "አጋንንትም ክርስቶስ መሆኑን አውቀው ነበርና ሊናገሩ አልፈቀደላቸውም።" እንዲል ማር ፩፥፴፬። ቅዱስ ሉቃስም ይኽንኑ እውነት ጽፎታል፡፡ ሉቃ ፬፥፴፭-፵፩።
ከዚህ የምንረዳው ጌታችን መቼም ቢኾን የአጋንንትን ምስክርነት እንደማይቀበል ነው፡፡ የትኛውም ጋኔን ክፉ ተናግሮ አልነበረም፡፡ ሊናገርም አይችልም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በጭራሽ የእነርሱን ምስክርነት አልፈለገውምና እንዲናገሩም አልፈቀደላቸውም፡፡ ክርስቶስ እንዳይናገሩ አፋቸውን የለጎማቸውን አጋንንት ዛሬ አንዳንዶቹ አስለፈለፍናቸው በሚል የዋኁን ምእመን ግራ ያጋቡታል፡፡ ክርስቶስ የከለከለውን የሚፈቅድ እርሱ የክርስቶስ አይደለም፡፡ ስለኾነም የቤተ ክርስቲያን አለመኾናቸውን ራሳቸው እየነገሩን እንደኾነ በማወቅ ከስሁት አሠራራቸው እንጠበቅ ዘንድ ራሳችንን እንምከር፡፡
መድረክ ለተከለከለ ጋኔን መድረክ ማመቻቸት ምን የሚሉት ሥራ ነው? እንዲህም አድርጎ ጸጋ የለምና በዚህ ክፉ ሥራቸው አንተባበርም፡፡ በተቀደሰው የእግዚአብሔር ዐውደ ምሕረት ላይ ርኩሳን መናፍስት ይናገሩበት፣ ይፈነጩበት ዘንድ መፍቀድ ኢ-ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡ እንዲያውም መድረኩን ቀስ በቀስ ለአለቃቸው ለሐሳዊ መሲህ የማመቻቸት ሥራ ይመስላል፡፡
ጌታችን እንዳይናገሩ የከለከላቸውን የአጋንንትን ምስክርነት ቅዱሳኑም አልተቀበሉም፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትን ያወደሰች ያመሰገነች እየመሰለች የማታለል ሥራ ለመሥራት እንዲመቻት ታደርግ የነበረች አንዲት ጠንቋይ ይህን ስልት ለመጠቀም ሞክራ ነበር፡፡ እንዳትነቀፍ ቅዱሳንን የተቀበለች ለመምሰል ትሞክራለች፡፡ ይህም ገበያዋ እንዳይታጎልባት የቀየሰችው መንገድ ነበረ፡፡ ቅዱሳኑን ብትቃወም ኖሮ ዘወር ብሎ የሚያያት አይኖርም ነበረና በስልት በአደባባይ የማታምንበትን ምስክርነት ልትሰጥ ትሞክራለች፡፡ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፡-
"ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን። እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፦ የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር። ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን፦ ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ።" ፲፮፥፲፮-፲፷።
ዛሬም ቅዱሳኑን የተቀበሉ የሚመስሉ የአጋንንት አገልጋዮች አሉና እናውቅባቸው ዘንድ ይገባል፡፡ ስመ ቅዱሳንን መጥራት ብቻ የእግዚአብሔር መኾንን አያመለክትም፡፡ ከዚህች ሴት የምንረዳው ይኽንኑ ሲኾን ሐዋርያትም አልፈቀዱላትም፡፡ ስለዚህ ለጋኔን ፈቃድ ሰጥተው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መድረክ የሚያስፈነጩ ሁሉ በምንም መንገድ የእና ናቸው ሊባሉ አይችሉም፡፡ ነገር ግን ከተያዙበት ቁራኝነት ተላቅቀው ዕድሜ ለፍስሐ ዘመን ለንስሐ ያገኙ ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡
አዲስ "ዶግማ"?
"አጥማቂ" ነን ባዮቹ ከሚፈጽሙት መሠረታዊ ስህተት አንዱ አዲስ ነገረ ሃይማኖት ያውም ኑፋቄ አሾልከው ለማስገባት የሚያደርጉት ጥረት ነው፡፡ በተደጋጋሚ እንደምንሰማው "በኢየሱስ ስም አልወጣም ያለው ጋኔን በማርያም ስም ወጣ" የሚል ግልብ ማደናገሪያ በማኅበረሰባችን ውስጥ ቀስ እያደረጉ እያስገቡ ነው፡፡ እንዴት? ተብለው ሲጠየቁ በኢየሱስ ስም ሲባል የማይወጣው ሐሰተኛ ኢየሱስ ስላለ ነው ይላሉ፡፡
አላወቁትም እንጂ እነርሱ እየጠሩት ያለው ሐሰተኛ ኢየሱስ መኾኑን ነው፡፡ አማናዊውን ኢየሱስ (እውነተኛውን ኢየሱስ) እንደማይጠሩት በዚህ አረጋገጡልን ማለት ነው፡፡ ጋኔኑማ አማናዊውን እንዳይጠራ ግዝት አለበት፡፡ ደግሞ እውነተኛውን ከሐሰተኛው እየለየ የሚነግራቸው ጋኔኑ እንጂ እነርሱ አለመኾናቸውን ስናውቅ ምን ያኽል በክፉ ቁራኝነት እንደተቀፈደዱ እንረዳለን፡፡ እነርሱ እንደሚሉት ከኾነ ጋኔኑ እኮ ነው ለምንድን ነው በኢየሱስ ስም ስትባል የማትወጣው ተብሎ ተጠይቆ እነርሱ የሚለፍፉትን "ማምለጫ" ያስተማራቸው፡፡ ጋኔኑማ በአማናዊው ኢየሱስ ስም ምንም ነገር እንዳያደርግ ዝምም እንዲል ስለተደረገ ምንም የማድረግ ሥልጣን የለውም፡፡ ታዲያ ተከታዮቻቸው ጋኔኑ እየሠራ ያለው በተቃራኒው እንደኾነ እንዴት ማወቅ ተሳናቸው? መልሱ አንድ እና አንድ ብቻ ነው የያዘ ቢይዛቸው የሚል፡፡
ከጋኔን ሰምቶ ጽድቅ የለም፡፡ እንዲሁም በጋኔን የማሳሳቻ ስልት ተባባሪ መኾን የእርሱ ተከታይነትን ከማረጋገጥ በቀር ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡ በእነርሱ ቤት እመቤታችንን ኦርቶዶክሳውያን ይወዳሉና እንዲህ ብንላቸው በቀላሉ ይሞኙልናል ብለው ነው፡፡ እኛ ከክርስቶስ በላይ የኾነች ድንግል ማርያም የለችንም፡፡ እኛ የምናውቃት ቅድስተ ቅዱሳን፣ የጭንቅ አማለጅ ፣ ንጽሕተ ንጹሐን፣ መትሐት ፈጣሪ መልዕልተ ፍጡራን ድንግል ማርያም ካማለደች በኋላ "የሚላችሁን አድርጉ" ብላ ወደ ክርስቶስ የምታቀርበንን ነው፡፡
እውነት ከኾነ ጋኔኑ ራሱ እነርሱ የሚሉትን የማለት ሥልጣን እንደሌለው አሳምሮ ሊነግራቸው ይችላል፡፡ ከዚህም ከዚያም ሳይኾኑ እንዳይቀሩ እንጂ ስለ ጌታችን ጋኔን ሐሰት ይናገር ዘንድ አቅም የለውም፡፡ ምናልባት እርሱ ያላሰበውን እነርሱ አስበውለት እንደኾነ እንጃ! በኢየሱስ ስም ባዮቹ እነርሱ ኾነው ሳለ ጋኔኑ ያለው የተናገረው አስመስለው ማቅረባቸው በጣም አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡ እነርሱ ከጠሩት ደግሞ ሐሰተኛው የሚለውን ምን አመጣው? ወትሮውኑም ጠሪው የጠራው ሐሰተኛውን ስለኾነ እንጂ፡፡ እነርሱ የጠሩትን ጋኔኑ "እርሱማ ሐሰተኛው ነው" ሲላቸው ካመኑት እነዚህ ሰዎች ከእግዚአብሔር ይልቅ የሚያምኑት ዲያብሎስን ለመኾኑ ሌላ ማስረጃ ፍለጋ መሄድ አያስፈልግም፡፡
ስለዚህ ከእነዚህ አስመሳዮች ራሳችንን መጠበቅ አለብን፡፡ ከመከተል በፊት ከሃይማኖታዊ፣ ከቀኖናዊ እና ትውፊታዊ ኦርቶዶክሳዊነት አንፃር እንገምግም፡፡ አጋንንት ያደሩባቸውን ሰዎች በባርነት እና በሌላም ግብረ ኃጣውእ ተብትቦ ይዞ መዞር ክርስቶሳዊነት አይደለም፡፡ ጸጋው ያደረባቸው ወዲያው ይፈውሳሉ ወዲያው ያሰናብታሉ፡፡ በዞሩበት እያዞሩ በባርነት ተብትበው የያዙ ኦርቶዶክሳዊያንንም ኾነ ቅዱሳንን አናውቅም፡፡ ይህ ብቻውን ሊያስተምረን በተገባ ነበር፡፡ ግን እንበልና ተሳሳትን፣ ዛሬ ለመመለስ ደግሞ ምክንያት አናብዛ፣ ሰዎችን ከመከተል ይልቅ የምሕረት በርን በሰፊው ከፍታ ወደምትጠብቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንመለስ፡፡ መሳሳትን ላለመቀበል አንግደርደር፡፡ እግዚአብሔር የተሳሳቱትን ሁሉ ራሳቸውን "አጥማቂ" ነን ባዮችንም ጭምር በቸርነቱ ይመልስልን፡፡