Saturday, 18 June 2016

"መጥፎውን ሽሹ መልካሙን እሹ": ሎቱ ስብሐት !

"መጥፎውን ሽሹ መልካሙን እሹ": ሎቱ ስብሐት !: ©መልካሙ በየነ ግንቦት 30/2008 ዓ.ም የቅብአት እምነት ከጾም ቀናት መለያየት ውጭ ከተዋሕዶ ጋር ያለው ልዩነት ብዙ መስሎ አይታየንም ነበር አሁን ግን አምላክ የተመሰገነ ይሁን ይኼው "ወልደ አብ" ታ...

ጎጆ ቤት እና የባቄላ እሸት

ጎጆ ቤት እና የባቄላ እሸት

በአንድ አካባቢ ሁለት ጎረቤታሞች ይኖሩ ነበር፡፡ አንዱ ገንዘብ የበዛለት ይህ ቀረህ የማይባል ንብረቱ ስፍር ቁጥር የሌለው ባማረና በተዋበ ቤት በምቾትና በቅንጦት የሚኖር ተንኮለኛና ምቀኛ ባለጠጋ ሲሆን ሌላኛው ግን ከአንዲት የጎሰቆለች ጎጆ ቤት በቀር ምንም የሌለው አዛኝና ርኅሩኅ ፈሪሐ እግዚአብሔርን ገንዘቡ ያደረገ ድሃ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ያ ተንኮለኛና ምቀኛ ባለጠጋ ተንኮሉን ለመጀመር ከድኃው ጎጆ ጋር አያይዞ ጎጆ ቤት ሠራ፡፡ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ባለጠጋው ያንን መከረኛ ድሃ ጎረቤቱን “ብርዱ በጣም ስለጨመረ ጎጆዬን በእሳት አቃጥዬ ልሞቃት ስለሆነ ያንተ ጎጆ እንዳትቃጠል ከፈለግህ ራቅ አድርጋት” አለው ድሃው ጎጆውን አፍርሶ የሚሠራበት ገንዘብ እንደሌለው ስለሚያውቅ አብሮ ለማቃጠል ልቡ በተንኮል ስለተነሣሣ፡፡ ድሃውም በተንኮል እንደተነሣሣበት ስለገባው ቤቱን ለማትረፍ ገንዘብ ተበድሮ አፍርሶ ራቅ አድርጎ ለመሥራት ቢሞክርም ገንዘብ የሚያበድረው ሰው በማጣቱ ባለጠጋው የራሱን ቤት ሲያቃጥል የድሃውም ቤት አብሮ ተቃጠለ፡፡ በቀል የእግዚአብሔር መሆኑን በሚገባ የሚያውቀው ድሃ በቀሉን ለእግዚአብሔር ትቶ ቤቱ የተቃጠለበትን ቦታ አጥሮ ከቆፈረ በኋላ ባቄላ ዘርቶት ወደ ሩቅ አገር ተሰደደ፡፡ ባቄላው ለእሸት በደረሰ ጊዜ ያ ድሃ ሁኔታውን ለማየት ከስደት ተመልሶ ሳለ የባለጠጋው ልጅ እሸቱን እየቀጠፈ ሲበላ ስለደረሰበት ምስክር ለሚሆኑ ሽማግሌዎች ያሳያቸዋል፡፡ ወዲያውኑ ከዳኛ ዘንድ ሄዶ የደረሰበትን መከራና ግፍ በምሬት “በጉርብትና ሳለን ቤቴን አቃጠለብኝ እኔም ቦታዬን ባቄላ ዘርቼ ተሰደድኩለት፡፡ የባቄላውን ሁኔታ ለማየት ከስደት ስመለስ ልጁ አጥሩን ጥሶ የባቄላውን እሸት ሲቀጥፍ ደረሰኩበት፡፡ ይህንንም የአካባቢው ሽማግሌዎች ሳይቀሩ አይተዋል፡፡ ስለዚህ ለተበደልኩ ለእኔ ፍረድልኝ ፡፡”  ሲል ተናገረ  ዳኛውም ይህን የተበደለ ሰው ድምጽ እንደሰማ ያን ባለጠጋ ከነልጁ አስጠርቶ መልስ እንዲሰጥ አደረገው፡፡ የባለጠጋው መልስ ግን “የባቄለውን  ሸት እተካለታለሁ፡፡ ቤቱን ግን እኔ አላቃጠልኩበትም የራሴን ቤት እንጅ” የሚል ነበር፡፡ ልቡ በግፍ ብዛት የቆሰለው ድሃ ግን “ምትክ አልፈልግም የልጁ ሆድ ተሰንጥቆ የራሴ የሆነው ባቄላ ወጥቶ እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ፡፡በማለት በዳኛው ፊት ተናገረ፡፡ ዳኛውም ግፍህ በዝቷልና የወደድከውና የፈቀድከው ይሁን ብሎ ፈረደለት፡፡ ያ ባለጠጋ ደንግጦ ፈዘዘ ደነገዘ፡፡ ልቡ ሲመለስለት “የልጄ ሆድ ከሚሠነጠቅ ያለኝን ሀብትና ንብረት እኩል ላካፍለው”  በማለት በዳኛው ፊት ተማጸነው፡፡ ድሃውም ከብዙ ልመና በኋላ “ምን ያህል ግፍ እንደፈጸምክብኝ እንድትረዳ በመፈለጌ እንጅ የልጅህን ሞት ፈልጌ አይደለም፡፡ አሁን ግን ሥራህን ሁሉ ስላወቅኸው እንድትማርበት ትቼዋለሁ” በማለት ገንዘቡን እኩል ለመካፈል ተስማማ፡፡ ዳኛውና ሽማግሌዎች የባለጠጋውን ሀብትና ንብረት በሙሉ ለሁለት እኩል ከፍለው ሠጡት፡፡ ያ ድሃም በግፍ ከተባረረበት ቦታው ላይ ያማረ ቤት ሠርቶ በደስታ እግዚአብሔርን በማመስገን ኖረ፡፡ “በመከራህ ቀን ጥራኝ አድንህማለሁ አንተም ታከብረኛለህ፡፡”መዝ 49÷15 በማለት የተናገረ አምላክ “አቤቱ ፍረድልኝ ከጽድቅ ከራቁ ሕዝብም ክርክሬን ተከራከር ከሸንጋይና ከግፈኛ ሰው አድነኝ፡፡” መዝ 4÷21 በማለት የዳዊትን ልመና በመለመን ላይ የነበረውን ድሃ ልመና እግዚአብሔር ሰማ፡፡ መዝ33÷6  ይህ ድሃ በበቀል ተነሣስቶ በባለጠጋው ላይ አንዲትም ጉዳት አላደረሰበትም፡፡ በቀል የእግዚአብሔር መሆኑን ያውቅ ስለነበር “አቤቱ ተነሥ በቀልህንም ተበቀል፡፡” መዝ73÷22 የሚለውን የዳዊት መዝሙር እየዘመረ ቦታውን ለቅቆ ተሰደደ፡፡ “እግዚአብሔር የበቀል አምላክ ነው፡፡ የበቀል አምላክ ተገለጠ፡፡”መዝ 93÷1 በማለት ዳዊት ያመሰገነው እግዚአብሔር ለድሃው የልመናውን ዋጋ ሰጥቶታል፡፡ ስለዚህ በባለጠግነታችን ተመክተን በድሆች ላይ አንዳች ግፍ ልንፈጽም አይገባም፡፡ ምክንያቱም በገንዘባችን ብዛት መግዛት የማንችላቸው ነገሮች በርካታ ስለሆኑ፡፡ ገንዘብ እንደ በረሐ አበባ ታይቶ የሚጠፋ ከንቱ ነገር ነው፡፡ በአግባቡ ሲጠቀሙበት የሚጠቅም በአግባቡ ካልተጠቀሙበት ደግሞ የሚጎዳ ነው፡፡ ገንዘብ የምንገዛበት እንጅ የሚገዛን አይደለም፡፡ በገንዘባችን ከገዛንበት ጥቅም ላይ ዋለ ማለት ነው፤ ነገር ግን ገንዘቡ ከገዛን ትልቅ ጉዳት ይሏችኋል ይህ ነው፡፡ “ለችግረኛና ለምስኪን የሚራራ ምስጉን ነው፡፡” መዝ40÷1  ይላልና ለድሆች ራርተን የምንመጸውት ከሆነ ገንዘባችንን እንደ አብርሃም ጥቅም ላይ ማዋል ቻልን ማለት ነው፡፡ ወገኖቼ ገንዘብ በአግባቡ ካልተያዘ ጥፋቱ ይበዛልና በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ባለጠግነት ደግሞ ከአምላክ ካልተሰጠ በቀር ከየትም አይገኝም፡፡ አንዳንድ ሞኞች ስለወጡ ስለወረዱ ያገኙ ይመስላቸዋል፤ ለማግኘት መሥራት ግዴታ ነው፤ ነገር ግን አምላክም እንዲጨመርበት ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ከአምላክ ፈቃድ ውጭ የትም መሄድ አይቻልምና፡፡ ስለዚህ ለድሆች ራርተን ካለን መጽውተን በእግዚአብሔር ቤት መኖር ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡
ማጣቀሻ፡- መዝ61÷10፣ ማቴ 19÷24፣ ሉቃ12÷15፣ ሉቃ21÷1-4

ንስሓ

ንስሓ

ንስሓ ማለት መጸጸት፣ መቆርቆር፣ ኃጢአትን ስለሠሩ ማዘን፣ ማልቀስ፣ መቆጨት ነው፡፡ የበጎ ሥራ ጠላት ዲያብሎስ የሰው ልጅ መንግሥተ ሰማያትን እንዳይወርስ ክፉ መርዙን እየረጨ ከንስሓ መንገድ ያርቀናል፡፡ ኃጢአትን በኃጢአት ላይ ደርቦ ደራርቦ ያሠራህና ራስህን እንደ ሰው መቁጠር እስኪያቅትህ ድረስ ያስጨንቅሃል፡፡ ንስሓ ለመግባት ስትፈልግ “ይህን ያህል ኃጢአት እንዴት ነው ለንስሓ አባትህ የምትነግራቸው? የሚያሳፍር ኃጢአትም ሠርተሃል፡፡ ስለዚህ አሁን ተወውና ስታረጅ አንድ ጊዜ ትገላገላለህ” ይልሃል፡፡ የዕድሜ ዘመንህንም ረዘም አድርጎ ያሳይሃል፡፡ አንተም ትታለላለህ “ኃጢአቴን በሙሉ አንድ ጊዜ በሙሉ ልገላገለው” እያልህ ኃጢአትን ማጠራቀም ትጀምራለህ፡፡ እግዚአብሔር በሞት የሚጠራህ መቼ እንደሆነ ታውቃለህ? በፍጹም አታውቅም ጠላት ግን ሽህ ዘመን የምትኖር አስመስሎ ያሳይሃል፡፡ጠላት አሁንም ይቀርብና “የሠራኸው ኃጢአት በጣም ከባድ ነው፡፡ ለንስሓ አባትህ ከነገራካቸው በኋላ ለሌላ ሰው ቢነግሩብህሳ” ይልሃል፡፡ አንተ ግን አትስማው ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጠው የማሰርና የመፍታት ስልጣን ለንስሓ አባቴም ተሰጥቷቸዋል በለው፡፡ /ማቴ 17፥19/ ዲያብሎስ ግን አሁንም ሌላ ወሬ ይጀምራል፡፡ “ንስሓ አባት ምናምን እያልክ ለምን ጊዜ ትፈጃለህ? ዝም ብለህ ወደ አምላክህ ቀርበህ ይቅር በለኝ ብትለው ይቅር ይልህ የለምን?” ይልሃል፡፡ አንተ ግን ምክሩን አትቀበል በኃጢአት ማሰሪያ እንደታሰርክ ወደ ክርስቶስ ብትቀርብ “ራስህን ለካህን አሳይ” ይልሃል እንጅ አይቀበልህም፡፡ “ክርስቶስ ወደ አንዲት መንደር ሲገባ በሩቁ የቆሙ አሥር ለምጻሞች ተገናኙት እነርሱም እየጮኹ ኢየሱስ ሆይ አቤቱ ማረን አሉ፡፡ አይቶም ሂዱ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው”፡፡ /ሉቃ17፥12-14/ ስለዚህ የንስሓ አባት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ልትረዳ ያስፈልጋል፡፡ ንስሓ ሳትገባ መንግሥተ ሰማያት መግባት አትችልም፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” እያለ ይሰብክ የነበረው ለዚህ ነው፡፡ /ማቴ3፥1-2/ በንስሓ መመለስ ኃጢአትን ሁሉ እንዳይታስብ (እንዲሰረይ) ግዱፍ እነዲሆን ያደርጋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ይላል “ሕመምተኞች እንጅ ባለጤናዎች ባለመድኃኒት አያስፈልጋቸውም ነገር ግን ሄዳችሁ ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ተማሩ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሓ እንጅ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና” /ማቴ 9፥12-13/ ስለዚህ ንስሓ መግባት ተገቢ ነው ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ወደ ምድር የወረደ ኃጥአንን በንስሓ ለመጥራት እንጅ ለጻድቃን አይደለምና፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ የለበሰ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ አይደለም ኃጢአትን ላደረጉ ኃጥአን ነው እንጅ፡፡ ንስሓ ኃጢአተኛን ንጹሕና ጻድቅ የሚያደርግ ልዩ ምስጢር ነው፡፡ “በደላቸውን እምራቸዋለሁና ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና” ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ /ኤር31፥34/ ጠላት ያንተን ይቅር መባል አይወድምና ከዚህ ምሥጢር እንድትርቅለት በርካታ መሰናክሎችን ያስቀምጥብሃል፡፡ ኃጢአት ስትሠራ እነደ ማር ይጥምሃል፡፡ በኃጢአት ላይ ኃጢአት በበደል ላይ በደል ትደራርባለህ፡፡ የኃጢአት ካባ ሙቀት ይሆንሃል፤ የጽድቅ ሥራ ይቀዘቅዝሃል፡፡ ከዚህም የተነሣ ኃጢአት ባሪያው ያደርግሃል አንተም ትሆንለታለህ፡፡ የታሰርክበትን ሰንሰለት ለመፍታት ስታስብ እንቅልፍህ ይመጣል፡፡ ዕድሜህ እንደዋዛ በከንቱ ትሮጣለች፡፡ እንደ ኖኅ ዘመን ሰዎች የእግዚአብሔር ቁጣ ሳታስበው መጥቶ ንፍር ውኃ ቢዘንብብህ የት ትገባለህ? /ዘፍ6 እና ዘፍ 7 በሙሉ ተመልከት/ የሞትህ ቀን መቼ እንደሆነ አታውቅምና ንስሓ ገብተህ ተዘጋጅተህ መኖር ተገቢ ነው፡፡ ሙሽራው ሲመጣ ዘይት ፍለጋ ልትሄድ አይገባም ዘይትህን ከመብራት ጋር ይዘህ መጠበቅ እንጅ፡፡/ማቴ25፥1-ፍጻ/ የጠላትን ምክር አትቀበል እርሱ ጥሩ ምክር አይመክርህምና፡፡ እናታችን ሔዋን የጠላትን ምክር በመቀበሏ ስትጎዳ እንጅ ስትጠቀም አላየናትም፡፡ ስለዚህ ለጠላት ጆሮ ሰጥተህ አትስማው፡፡ንስሓ አትግባ እያለ የሚያስጨንቅህ ወደ ዘላለም ቅጣት ሊጥልህ እንጅ የዘላለም ሕይወትን እንድታገኝ አይደለም፡፡ የቀደመው እባብ አሁንም ንስሓ አይጠቅምም እያለ የሚጨቀጭቅህ ከሆነ የጥጦስን (ፈያታዊ ዘየማን) ታሪክ ዘርዝረህ ንገረው፡፡ ጥጦስ ቀማኛ ሽፍታ ወንበዴ ነበር፡፡ በዕለተ አርብ በኢየሱስ ክርስቶስ ቀኝ በኩል ተሰቀለ፡፡ ሰባቱን ተአምራት በዓይኑ ተመለከተ፡፡ የተሰቀለው ክርስቶስ አምላክ እንደሆነም አመነና “ጌታ ሆይ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” የሚል ታላቅ ልመና ለመነ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም በንስሓ ተቀበለውና “እውነት እልሃለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ” አለው፡፡ ይህ ወንበዴም አዳምን ተቀድሞ በክርስቶስ ደመ ማኅተም ለ5500 ዘመናት ያህል ተዘግታ የነበረችን ገነት ከፍቶ ገባ፡፡ /ሉቃ 23፥39-43/ ስለዚህ ንስሓ ቆሻሻን ሁሉ እንዲህ የሚያጠራ ሳሙና ነው እታጠብበታለሁ በለው፡፡ የኅሊናን ሸክም የሚያራግፍ ኃጢአትን ሁሉ የሚደመስስ ልዩ መድኃኒት ነውና በየሰዓቱ ውሰደው ንስሓን፡፡

ቤተ ክርስቲያንስ ሄዋን ናት

ቤተ ክርስቲያንስ ሄዋን ናት
አንድ የተሐድሶ ሰባኪ “ያረጀችው ቤተ ክርስቲያን አሮጊቷ ሣራ ወለደች፡፡ እኔን ወለደች፣ እገሌን ወለደች፣ እገሊትን ወለደች” እያለ ተሐድሶ የወለደቻቸውን ይዘረዝራል፡፡ ቤተክርስቲያን አሮጌ መባሏ ያበሳጨው የተዋሕዶ ልጅ ወደ “ሰባኪው” ተጠግቶ “መጽሐፍ ማንበብ ይቀርሃል ሣራ በእርጅናዋ ወራት የወለደችው አንድ ልጅ ይስሐቅን ብቻ እንደነበር አላወቅህም እንዴ? አሮጊቷ ሣራ እኔን፣ እገሌን፣ እገሊትን ወለደች እያልህ የምትቀባጥር፡፡ ቤተ ክርስቲያንስ አሮጊት ሣራ ሳትሆን ቀድሞ የነበረች መንታ መንታ የምትወልድ የብዙዎች እናት ሄዋን ናት፡፡፡ የግል ክብርህን ፈልገህ ደግ ይስሐቅን ነኝ ለማለት ክብርት ቤተክርስቲያንን ዝቅ ዝቅ ያደረግህበት ይህ ደፋር አንደበት በደሙ በመሠረታት በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት ስትቆም ምን ይናገር ይሆን?” በማለት ብዙ ትምህርት አስተማረው፡፡
ሥርዓቷ ሳይሆን ሕንጻዋ
አንድ መናፍቅ “ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያረጀች ያፈጀች ናትና በአዲስ ነገር መታደስ ይገባታል፡፡” እያለ በይፋ ይናገራል፡፡ ይህን የሰሙ አንድ የቤተክርስቲያን ሊቅ መናፍቁን አስጠርተው “የምትለው ሁሉ ልክ ነው፡፡ መታደስ ያለበት ግን ሥርዓቷ ሳይሆን ሕንጻዋ ስለሆነ የማሳደሻ ገንዘብ አሰባስብ” ሲሉት ያ መናፍቅ “መታደስ የሚገባው ትምህርቷ ሥርዓቷ ነው እንጅ ሕንጻዋ አይደለም”  ይላቸዋል፡፡ ሊቁም “በል እንግዲያውስ የራስህን አእምሮ በመልካም ትምህርትና ሥርዓት አድስና ከዚያ በኋላ ብንገናኝ ይሻላል” ብለው አባረሩት፡፡
እንዘምራለን ስትናፍቀን
ተሐድሶ መናፍቃን እግዚአብሔርን የሚናፍቁበትና የማይናፍቁበት ቀንና ጊዜ አላቸው፡፡ ምክንያቱም ሲፈልጉ ዘማሪ ክርስቲያን ሲፈልጉም ታዋቂ ዘፋኝ በመሆን በተደበላለቀና በተመሰቃቀለ ሕይወት ውስጥ ስለሚኖሩ ነው፡፡ በዝማሬዎቻው ውስጥ የምንሰማው
ዛሬም የአንተ ነው አዲሱ ቀን
እንዘምራለን ስትናፍቀን
የሚል ነው፡፡ በእውነት እግዚአብሔር የማይናፈቅበት ወቅት አለን? በዚያስ ወቅት መዘመር አስፈላጊ አይደለምን? ዝማሬን የናፍቆት መግለጫ ያደረጉት፡፡ ወገኖቼ ሳናውቅ በተኩላ እየተበላን ስለሆነ መንቃት ያስፈልጋል፡፡
መዶሻ ያልያዘ ሠራዊት
ተሐድሶ መናፍቃን በስብከታቸው እና በመዝሙራቸው ውስጥ “መዶሻ ያልያዘ ሠራዊት” የሚለው መሪ ቃላቸው ሆኗል፡፡ በእውነትም መዶሻ ያልያዘ ከንቱ ሠራዊት ነው፡፡ መዶሻው ቃለ እግዚአብሔር  የሚገኘው ቤተክርስቲያን ውስጥ ስለሆነ በየቦታው ሲዞሩ ይህን ማግኘት ባለመቻላቸው ቃለ እግዚአብሔርን ያልያዘ ሠራዊት ነን ሲሉ “መዶሻ ያልያዘ ሠራዊት” ነን ይላሉ፡፡ ቃለ እግዚአብሔርን ያልያዘ ሠራዊት ደግሞ የአጋንንት ስለሆነ ከተዋሕዶ ልጆች ጋር ምንም ሕብረት የለውም፡፡
ስብከት ጋዜጠኛነት አይደለም
“እገሌ ሲናገር ሲሰብክ ልዩ ተሰጥዎና ግርማ ሞገስ አለው፡፡ስለዚህም ተሐድሶ መናፍቅ ሊባል አይገባውም” የሚሉ ደጋፊዎች በዝተዋል፡፡ እነዚህ ደጋፊዎች ያልገባቸው ነገር የድምፅ ማማር ወይም የንግግር ግርማ ሞገስ መኖር የሰባኪ መመልመያ መስፈርት ማድረጋቸው ነው፡፡ ስብከት የድምፅ ግርማ ሞገስን ብቻ መሠረት ያደረገ የጋዜጠኛነት ሙያ አይደለም፡፡ ስለዚህ የንግግር ግርማ ሞገስ ያላቸው የተሐድሶ መናፍቃን ጋዜጠኛነት መወዳደር ይችላሉ እንጅ በድምጻቸው ማማር ብቻ ተዋሕዶን ሊሰብኩ አይችሉም፡፡ ስብከት በተግባር የሚኖሩት ሕይወት እንጅ እንደ ጋዜጠኛ መናገር ብቻ አይደለምና፡፡
በጣም ይመቸኛል
“እገሌ እና እገሊት ሲዘምሩ ድምጻቸው በጣም ይመቸኛል” የሚሉ በርካታ ደጋፊዎች በዝተዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች በመዝሙሩ ውስጥ ምን መልእክት እንደተላለፈ አልተረዱም፡፡ እነርሱ የተማረኩት በዘማሪዎች የድምጽ ማማር ብቻ ነው፡፡የድምጽ ማማርን የሚደግፉ ሰዎች ደግሞ ዘፋኞችንም የሚደግፉ በመሆናቸው መዝሙርና ዘፈን የተቀላቀለባቸው በመሆናቸው “ድምጻቸው ይመቸኛል” ከማለት የዘለለ ሌላ የሚደግፉበት ቃል የላቸውም፡፡ ስለዚህ መዝሙርን በዘማሪዎች ድምጽ ማማር ብቻ ሳይሆን በውስጡ ባለው መልእክትና በዜማው የቤተክርስቲያናችን መሆን አለመሆኑን ልንገነዘበው ያስፈልጋል፡፡

የመናፍቃን እውርነት!

የመናፍቃን እውርነት!


እውርነትን በ2 ከፍለን ልንመለከተው እንችላለን፡፡ ይኸውም፡- የዓይንና የልብ እውርነት በማለት ነው፡፡ በጣም አስቸጋሪውና ብዙዎችን ለጉዳት የዳረጋቸው የልብ እውርነት ነው:: “ልብ ካላየ ዓይን አያይም” እንዲሉ በልባቸው መታወር ምክንያት ዓይናቸው የሚያየውን እጃቸው የሚዳስሰውን ሁሉ ማየት መጨበጥ የተሳናቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ድንግል ማርያም አታማልድም ምክንያቱም መጽሐፍ ውስጥ ታማልዳለች የሚል ጥቅስ የለምና ብለው በድንቁርና ማስረጃ ይሞግታሉ:: ልብ ካላችሁ ስሙኝ ልጠይቃችሁ መልሱልኝ::
1. መጽሐፍ ቅዱስ የተደረገውን ሁሉ አጠቃልሎ ይዟልን? አላጠቃለለም ለዚህም ማስረጃ አለኝ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ 2ኛ ዮሐ 1፥12 ላይ “እንድጽፍላችሁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልወድም ዳሩ ግን ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ወደ እናንተ ልመጣ አፍ ለአፍም ልናገራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ” ይላል፡፡ እንዲሁም በ 3ኛ ዮሐ1÷13 ላይም “ልጽፈው የምፈልገው ብዙ ነገር ነበር ዳሩ ግን በቀለምና በብርዕ ልጽፈው አልወድም” ይላል:: ይህ ሐዋርያ ድንግልን በመስቀሉ ሥር የተቀበለ ነው:: /ዮሐ19÷27/ ስለድንግል አማላጅነት በይበልጥ የሚያውቀው ቅዱስ ዮሐንስ ነው:: ምክንያቱም እነኋት እናትህ ተብላ በእናትነት የተሰጠችው ለእርሱ ነውና፡፡ እኛም እናታችን የምንላት በዮሐንስ በኩል ለሁላችንም የተሰጠችን ስለሆነ ነው፡፡ ዮሐ 21፥25 ላይ እንዲህ ይላል “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ ኹሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” ይላል ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉንም ድርጊት በሙሉ አላሰፈረልንም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ትውፊትም ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ አንዱ ለአንዱ ማለትም አባት ለልጁ ለልጅ ልጁ በቃል ያወረሰው ትምህርት አለ፡፡ ለምሳሌ ያህል በዘፍጥረት ላይ እግዚአብሔር አዳምን በአርአያውና በአምሳሉ እንደፈጠረው ይናገራል፡፡ ከዚያም ከግራ ጎኑ ደግሞ ሔዋንን እንደፈጠረለት ይናገራል፡፡ ከዚያ በኋላ አዳም ሔዋንን አወቃትና ቃየን ተወለደ፡፡ በመቀጠልም አቤል ተወለደ፡፡ ከዚያም ቃየን አቤልን ገደለው አዳምም ሔዋንን አወቃትና ሴት ተወለደ፡፡ ከዚያ በኋላ ሴት ሄኖስ የተባለ ልጅን ወለደ፡፡ መናፍቃን እዚህ ላይ ይቆማሉ እንግዲህ ሴት ማን የምትባል ሴት አግብቶ ነው ልጅ የወለደ? እንደመጽሐፍ ቅዱስ ገለጻ ከሆነ በዚያን ወቅት ያለችው ብቸኛ ሴት እናቱ ሔዋን ብቻ ነበረች፡፡ እስከዚህ ዘመን ድረስ በሕይወት መኖር አለመኖሯ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገለጥም ማለት ነው፡፡ እስደ መጽሐፉ ግን እስከዚህ ዘመን ድረስ የተገለጠችው ሴት እሷ ብቻ ናት፡፡ ታዲያ ልጇ ሴት ከሔዋን ልጅ ወለደ ልትሉን ነውን? በፍጹም አንቀበላችሁም፡፡ እኛ ብዙ ማስረጃዎችን በትውፊትም በመጽሐፍም እናቀርባለን፡፡ ይህንን በሚገባ የሚያብራራልን የቅዱስ ጴጥሮስ ደቀመዝሙር እንደሆነ የሚናገረው ቀሌምንጦስ በጻፈው መጽሐፈ ቀሌምንጦስ ነው፡፡ ይህንን መጽሐፍ መናፍቃኑ አይቀበሉትም፡፡ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ምልጃዋንም በዮሐ2 ላይ የቃና ዘገሊላውን የመጀመሪያ ተአምር ልብ ይሏል:: መናፍቃን ይህንንም በእውርነት ያጣምሙታል እርሱን ስሙት” ብላለችናኢየሱስን ብቻ ነው የምንሰማ” ይላሉ:: ወይን ማለቁን ማን ነገራት? መናፍቃን ሆይ እንደፈረስ ላይ ላዩን ሳትጋልቡ ከፊትና ከኋላ የተጻፈውን ነገር ሁሉ ተረጋግታችሁ በማስተዋል አንብቡ:: ይህ ቃል የመስማማት ነው:: ወይን ስላለቀባቸው ወይን እንዲሰጣቸው ልጇን ጠየቀችከአንች ጋር ምን ጠብ ምን ክርክር አለኝ ጊዜየ ገና አልደረሰምና” አላት:: ይህ ስለብዙ ነገር ተነግሯል ሰፊ ሐተታ አለው፡፡ በቀላሉ ለማየት ያህል፡-
v  ጊዜየ ገና አልደረሰም ማለቱ፡-
1.  ይህን ተአምር የማደርግበት ጊዜ ገና ነው ምክንያቱም በማድጋው ያለው ወይን ሙሉ በሙሉ አላለቀም ነበርና፡፡ ሳያልቅ ተአምሩን ቢያደርግ ውሃውን ወይን አደረገ ሳይሆን ጥቂቱን ወይን አበረከተው ይባል ነበርና፣
2.  በወቅቱ ይሁዳ የለም ነበርና ውሃውን ወይን ሲያደርግ ተአምሩን ባይመለከት ኖሮ እርሱ ተአምሩን ከሌሎች ሐዋርያት ለይቶ ስለከፈለብኝ እኔም ለአይሁዳውያን አሳይዝኩት ብሎ ምክንያት ይኖረው ነበርና ምክንያ እንዳይኖረው ይሁዳ እስኪመጣ ድረስ ለመጠበቅ፤
3.  እግዚአብሔር ለሥራው ሁሉ ጊዜ እንዳለው ለማጠየቅ፣
4.  ዓለምን የማድንበት በመስቀል የምሰቀልበት ጊዜ ገና አልደረሰም ለማለት ነው፡፡
ከዚህ በሗላ ነው እንግዲህ ጊዜው ሲደርስ “እርሱን ስሙት የሚላችሁን አድርጉ” ያለቸው:: እናትና ልጅ ተስማሙ ምልጃዋ ሠራ ዶኪማስ ከማፈር ዳነ:: አንድ መናፍቅድንግል ማርያም ታማልዳለች የሚል ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ አጣሁ” አለኝ እኔምዓይን ያላቸውን ጠይቅ ያሳዩሃል” አልኩት:: ለምን እንደዚህ መለስክለት አትሉኝም መቼም ምክንያቱም የማየትና ያለማየት የማስተዋልና ያለማስተዋል ጉዳይ እንጅ ጥቅስ ጠፍቶ አይደለም፡፡ ድንግል ማርያም በሉቃስ ወንጌል ሉቃ 1:48 ላይትውልድ ሁሉ ያመሰግኑኛል” አለች:: ትውልድ የሚባለው ከ 3ቱ አይወጣም ትውልደ ሴም፣ ትውልደ ካምና ትውልደ ያፌት ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ብጽእት እያሉ በአማላጅነቷ አምነው ይማጸኗታል ያመሰግኗታል ማለት ነው:: ድንግል ማርያም በትውልደ ሴም፣ በትውልደ ካምና በትውልደ ያፌት ብጽእት ተብላ የምትመሰገን ናት ማለት ነው፡፡ ታዲያ የዛሬ መናፍቃን ትውልዳቸው ከየት ይሆን ምልጃዋን አንቀበልም ብጽእት አንላትም ያሉት? የሰው ልጅ የድንግልን እናትናትና አማላጅነት ቢክድ ኖሮ ዶኪማስ በቃናው ሠርግ ልጇን ብቻ በጠራ ነበር ግን አላደረገውም:: አያችሁ ዶኪማስ ሲያከብራት:: በሉቃስ ወንጌል እንደተጻፈው መልአኩ ገብርኤል በመፍራት አምላክን እንደምትወልድ አበሰራት:: አያችሁ የሰማይ መላእክት እንኳ ሲያከብሯት:: ኢየሱስ የተገኘው ከድንግል ማርያም ሥጋ ነው:: ኢየሱስ ክርስቶስን ያወቅነው በድንግል ማርያም ነው:: ድንግል ባትኖር ኖሮ ኢየሱስን ሥጋ ለብሶ ማየት አንችልም ነበር :: ለዓለም መዳን ምክንያት እመብርሃን ናት:: ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥሬ ቃል አሳዩን የምትሉ መናፍቃን በእርግጠኝነት ቃሉን አላጣችሁትም እውርነት ጎድቷችሁ ካልሆነ በቀር:: የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል:: መዝ111÷6 እንግዲህ ለዘላለም ማለት እስከ መቼ እንደሆነ አስቡት:: እስከ ዓለም ፍጻሜ አይደለም ከዚያም በኋላ ጭምር እንጅ:: ድንግልንም ለዘላለም እናከብራታለን አማልጅን እንላታለን:: ምክንያቱም ቅድስት ናትና መታሰቢያዋም ለዘላለም ነውና አምላክ ለእናትነት አክብሯታልና፡፡ አንድን ነገር ስታከብሩ የራሳችሁ መስፈርት ይኖራችኋል ድንግል ማርያምን ስናከብር ግን የአምላክ እናት የዓለም መዳኛ ብለን ነው:: አማላጅ ጌታ ሳይሆን ተማላጅ አምላክን አስገኝታለችና እናመሰግናታለን ከፍ ከፍም እናደርጋታለን:: ክብር ምስጋና ይግባውና ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ማርያም ቢገለጥ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ አላነሰም አልበለጠምም እኩል ነው እንጅ:: በሥጋዌው ወራት ሕዝቡን ከራሱ ጋር አስታርቋል አማለደ የምንለውም ከራሱ ጋር እንታረቅ ዘንድ ያደረገውን የቤዛነት ሥራ ነው፡፡ ያን የቤዛነት ሥራውን ያደረገልን ወድዶ ፈቅዶ ነውና እኛን ለማዳን  ወደደ ፈቀደ ብለን እንተረጉመዋለን:: አሁን ግንይማልዳል” ማለት ፍጹም ስህተት ነው:: መናፍቃን እንደ ጥያቄ የሚጠይቁ እንደመልስም የሚመልሱት እንደመከራከሪያም የሚከራከሩበት ብቸኛ ጥቅስ ሮሜ 8÷34 “ስለእኛ የሚማልደው” የሚለው ነው፡፡ በዚህ ጥቅስ መነሻነት ኢየሱስ ክርስቶስ አሁንም ይማልዳል ይላሉ:: ቃሉስለእኛ የሚፈርደው” የሚል ነው ቅርብ ጊዜ በታተሙት ላይ ግንስለእኛ የሚማልደው” ተብሎ ተቀይሮ ተጽፏል:: ለመቀየሩ ማረጋገጫ ቁጥር 33 ላይ ስንመለከት “የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው የሚኮንንስ ማን ነው?” ይላል፡፡ ይህ ማለት አንተ ገነት ግባ ብሎ የሚያጸድቅ፤አንተ ሲዖል ግባ ብሎ የሚኮንን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህን የመጨረሻ ፍርድ የሚሰጠው ደግሞ አምላክ ወይም ፈጣሪ እንጅ ፍጡር /አማላጅ/ አይደለም፡፡ ይህ አያሳምንም የሚል ካለ ደግሞ ለምን ወልድ ብቻ አማላጃችን ነው እንለዋለን አብና መንፈስ ቅዱስስ አያማልዱንምን? እስኪ ጥሬ ቃላትን እንመልከት?
v  ሮሜ 8÷26 ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናልይላል፡፡ ስለዚህ በዚህ ጥቅስ መሠረት መንፈስ ቅዱስም ይማልዳል ማለት ነው::
ኤር 7÷25 አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በየዕለቱ እየማለድሁ ባሪያዎቼን ነቢያትን ልኬባቸችሁ ነበርይላል፡፡ እዚህ ጥቅስ ላይ እግዚአብሔር የሚለው እግዚአብሔር አብን ነው፡፡ በኦሪት እንዲህ እንደአሁኑ በግልጥ ሦስትነታቸው አይታወቅም ነበርና፡፡ ሦስትነትና አንድነት በሚገባ የታወቀው ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ከተወለደ በኋላ ነውና፡፡ በዚህ ጥቅስም መሠረት እግዚአብሔር አብ ይማልዳል ማለት ነው፡፡ ታዲያ አብ አማላጅ፣ ወልድም አማላጅ፣መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ አማላጅ ከተባሉ አምላካችን ማን ሊሆን ነው? የሚማለደው ማን ነው ልንል ነው? መናፍቃን ሆይ ልብ በሉ አስተውሉ ዝም ብላችሁ ቀንጭባችሁ አትከራከሩ፡፡ በርግጥ አንዴ ልባችሁ ስለጨለመባችሁ አሁንም ትከራከሩ ይሆናል:: ነገር ግን ትክክለኛና አሳማኝ የሆነ ማስረጃ ማቅረብ የምትችሉበት ወኔ ያላችሁ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈራጅ አምላክ እንጅ አማላጅ አይደለም:: ማስረጃ ካስፈለገ ሮሜ 9÷5 “ክርስቶስ በሥጋ መጣ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነውእንዲሁም ሮሜ14÷10 ላይ  “ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና” ይላል ፈራጅነቱን ሲገልጥ፡፡