Wednesday, 30 March 2016

መጻጒዕ (ዮሐ. ፭፥፲፫)

መጻጒዕ (ዮሐ. ፭፥፲፫)

በዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ
መጋቢት 18 ቀን 2008 ዓ.ም
የነፍሳችንን ማሠሪያ እንዲፈታና ዓለሙን ከተያዘት የኃጢአት በሽታ እንዲያድን ለቤዛነት፤ እንዲሁም የመልካምና የበጎ ምግባራት ሁሉ አብነት ሆኖ በሥራና በቃል እንዲያስተምር ወዳለንባት ምድር በሥጋ ቅድስት ድንግል ማርያም ወረደ ተወለደ:: ቤተክርስቲያናችን በአራተኛው የቢይ ጾም ሳምንት እግዚአ ለሰንበት ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ"ቤተሳይዳ" የፈጸመውን ተአምራት መጻጒዕ ብላ ሰይማ ስበዋለች። በዕለቱም በዮሐንስ ወንጌል አምስተኛው ምዕራፍ የተቀመጠው ታሪክ በልዩ ልዩ ኅብረ ምሥጢር ተገናዝቦ በሊቃውንቱ ይነገራል።
መጻጒዕ ለ፴፰ ዓመት በአልጋው ላይ ሆኖ ምሕረትን ሲጠባበቅባት የኖረባት ስፍራን "ቤተ ሳይዳ"ትባላለች።በቅዱስ መጽሐፍ የሥፍራዎችን ስያሜ ስንመረምር በይሁዳና በገሊላ ለሚገኙ ሁለት የተለያዩ ግዛቶች በተመሳሳይ አገባብ "ቤተ ሳይዳ" የሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸው እናገኛለን:: በሁለቱ አውራጃዎች (ይሁዳና ገሊላ) ሥር "ቤተ ሳይዳ" በሚል የተጠቀሱት ሥፍራዎች በትርጉም ፊደላቱ ያለአገባብ መሰደር ከወለዱት የሞክሼነት ስህተት (Metathetical Corruption) የተገኘ ክፍተት እንጂ ቦታዎቹስ በጥንታዊቷ የእስራኤል ግዛት ከመገኘታቸው ውጪ ምንም የሚያገናኛቸው መልክአ ምድራዊ ኩነት የለም "ጲላጦስ ጰንጤናዊ መልአከ ይሁዳ ወሄሮድስ ንጉሠ ገሊላ" (ሉቃ· ፫፥፩) እንዲል የግዛቶቹ አገረ ገዢዎችም እንዲሁ ለየቅል ነበሩ:: አገባቡን አካቶ ለመረዳት እንዲያመች የሁለቱንም መካናት ከተማና መንደር ለይቶ ማወቁ ተገቢ ነው::
 በይሁዳ ግዛት ከሚገኙና እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ገቢረ ተአምራቱን ከፈጸመባቸው ሥፍራዎች ፦ ቤተሳይዳ(Bethesda) ፣ ቢታኒያ ፣ ቤተልሔም ፣ ቤተፋጌ ፣ ኢያሪኮ ፣ ጌቴሰማኒ ፣ ሊቶስጥሮስ(ገታ) ፣ ኤማሁስ፣ ቀራንዮ(ጎልጎታ) ፣ ኢየሩሳሌም እና የደብረዘይት ተራራ የሚጠቀሱ ሲሆን፤
 በገሊላ አውራጃ ደግሞ ፦ ቤተሳይዳ(Bethsaida) ፣ ሄኖን ፣ ቃና፣ ቅፍርናሆም፣ ኮራዚ፣ ጌንሳሬጥ፣ ደብረታቦር፣ ናይን እና የገሊላ ባህር ተገልጸው እናገኛልን::
እነዚህኑ "ቤተ ሳይዳ" ዘይሁዳና "ቤተ ሳይዳ" ዘገሊላ አካባቢያዊ መገኛ ለይተው የሚያመለክቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማጣቀሻዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም በይሁዳ ኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ ያለችዋን "ወቦ ውስተ ኢየሩሳሌም ምጥማቃት ዘጵሩጳጥቄ ቅልንብትራ (ዘውእቱ ቀላየ አባግዕ ብሂል) ወይቤልዋ ስማ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ወባቲ ኃምስቱ ሕዋራት" (ዮሐ ·፭፥፪) ብሎ የገለጠበትንና በገሊላ ስለምትገኘዋ ደግሞ "ወሖሩ እሙንቱሂ ኀበ ፊልጶስ ዘቤተ ሳይዳ ዘገሊላ" (ዮሐ ፲፪፥፳፩) የሚለው ማየት ይቻላል::
በሌላ መልኩ አንዳንዶች ደግሞ በሁለቱም ሥፍራዎች ክርስቶስ አምላካችን ለፈውስ ሥራ ያገኛቸውን ሰዎች አይተው ተመሳሳይ ቦታ ሲመስላቸው ይታያል ይህም "መጻጉዕ" እና "ዕውር" የነበሩትን ማዳኑ ነው:: ይኸውም "ወቦ ውስተ ኢየሩሳሌም ምጥማቃት ዘጵሩጳጥቄ ቅልንብትራ (ዘውእቱ ቀላየ አባግዕ) ብሂል ወይቤልዋ ስማ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ወባቲ ኃምስቱ ሕዋራት …በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። (ዮሐ ·፭፥፪) የተባለውና "ወበጽሑ ቤተ ሳይዳ ወአምጽኡ ኀቤሁ ዕውረ ወአስተብቁዕዎ ይግስሶ … ወደ ቤተ ሳይዳም መጡ። ዕውርም አመጡለት፥ እንዲዳስሰውም ለመኑት።" (ማር· ፰፥፳፪) የሚለው ነው::
፨ "ቤተ ሳይዳ" ዘገሊላ (Bethsaida) በትርጉም "የማጥመጃ ቤት" የሚል ፍቺ ያለው በተለይ ከቅዱሳን ሐዋርያቱ አሳ አጥማጆቹ ወንድማማቾችና ቅዱስ ፊልጶስ የነበሩባት መንደር ናት " ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ።" (ዮሐ·፩፡፵፭) እንዲል።
 "ቤተ ሳይዳ" ዘይሁዳ (Bethesda or Bethchasday) የመጠመቂያ ሥፍራ ስትሆን በግሪኩ ቤተ ዛታ ( Βηθζαθά) ወይም ቅልንብትራ (κολυμβήθρα) እንዲሁም በእብራይስጡና በአረማይኩ "ቤተ`ስዳ" (Beth hesda ( בית חסד /חסדא )) በማለት "ከማጥመጃ ቤት" ለይቶ "ቤተ ሣሕል / የምሕረት ቤት" የሚል ትርጉም ያለው መጠመቂያና መላለሻ መንገድ መሆንዋን ያመለክተናል። የግእዙ መጽሐፍ ቅዱሳችንም የቦታውን ስያሜ ከእብራይስጡ "የአንድዮሽ ትርጉም" ስያሜ (ቤተ ሳይዳ) ጋር በግሪኩ ያለውንም መጠሪያ ጭምር አካቶ ቅልንብትራ ( κολυμβήθρα / kolumbethra) ሲል እናገኘዋለን::
ቤተ ሳይዳ ዘይሁዳ ባለ አምስት በር መመላለሻ አምስት ዓይነት ድውያን ፈውስን ከማየ ጥምቀቱ ሲጠባበቁ የሚኖሩባት በአምስተኛው የዮሐንስ ወንጌል ተጽ ያለ የጌታችን ማዳን የተገለጠባት ሥፍራ ናት። "እስመ ኦሪት መንፈቀ ፍጻሜ ወኅዳጠ መክፈልት" እንዲላት መልአከ እግዚአብሔር ለቀድሶተ ማይ ወርዶ ውኃውን ሲያናውጥ ቀድሞ የገባ የሚነጻባት በዕለቱ ከአንድ በቀር ለሌላው ፈውስ የማይደገምባት ቦታ ናት ።
ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል የድኅነት ተስፈኛ ሆኖ የኖረ መጻጉዕን በአልጋው ተኝቶ ሳለ ደዌው እንደጠናበት ፈውስ እንደዘገየበት አይቶ "መፈውስ ወማሕየዊ" ጌታችን ቀርቦ አዎን እንዲለው እያወቀ ያንን በሽተኛ "ትፈቅድኑ ትሕየው? … ባድንህ ፈቃድህ ነውን?" አለው። ብወዳችሁ አላዋቂ የሆነ የእናንተን ሥጋ ተዋሕጄ መጣሁላችሁ ሲለን ("አኮ ኢያእሚሮ ኅቡአተ አላ ከመ የሀብ መካነ ለጥንተ ትስብዕቱ ዘኢየአምር ኅቡአተ") እንዲል:: የሚገርመው ቅዱስ ጳውሎስ በእብራውያን መልእክቱ ምዕራፍ ፬ ቁጥር ፲፪ ላይ "የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።" ብሎ የመሰከረለት ጌታችን ፈውስን በመጠባበቅ ከመዳን ውጪ ሌላ ዓላማ ያልነበረውን ይህን ሰው ዓይቶ ፈቃዱን እያወቀ ግን ፍቀድልኝና ላድንህ አለው። " ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው? "(መክ ፮፥፲፪) እንዲል የሚያስፈልገንን ሳንነግረው የሚያውቅ የሚሰጠንም ከእርሱ ከፈጣሪው ውጪ በእውነት ማን አለ? መጻጒዕ ግን ኋላ የሚክድ ነውና "በሰንበት ላይ ያመጸ ፣ ራሱን ከአብ የሚያስተካክል ፣ ቤተመቅደሱን አፍርሱት ያለ መች አድነኝ ብየው ሳልፈቅድለት ያዳነኝና አልጋ ያሸከመኝ ነውኮ" ብሎ በዕለተ ዓርብ የሚከስበትን ሲያሳጣውና ለኋላ ጥፋቱ የገዛ ኅሊናው እንዲቀጣው ፈቃዱን ጠየቀው። "አልብየ ሰብእ" ሰው የሌለኝ ሆኖ እንጂ ያንንማ ማን ይጠላል በሚል ጉጉቱን ከወዳጅ አልባነቱ ጋር ድኅነትን ፈቅዶ ገለጠ። እስከ ሁከተ ማይ ሳያቆየው "ተንሥእ ንሣእ ዓራተከ ወሑር … ተንስና አልጋህን አንስተህ ሂድ" አለው ወዲያው አፈፍ ብሎ በፍጥነት ያን ሁሉ ዘመን የተሸከመች ጠንካራ አልጋ ተሸክሟት ሄደ።
ይህች "ቤተ ሳይዳ" ዘይሁዳ ምሣሌቷ ብዙ ኅብር ያለው ነው። ለአብነትም ያህል ምሳሌ፦
፩·ውኃው የቤተ አይሁድ ምሳሌ አምስት መመላለሻ የሕግጋተ ኦሪት የአምስቱ መፃሕፍተ ሙሴ በነዚያ ታጥረው ለመኖራቸው። ቀድሞ የገባባት አንዱ እንዲድን እነሱም አንድነት ቤተ እስራኤል ተሰኝተው ለመኖራቸው ምሳሌ ነው።
፪·በሌላ አገባብ
 በዚያ ውኀውን ለማወክ የወረደው መልአክ = ቀሳውስት(ካህናት) "ለቀድሶተ ማየ ጥምቀት" የመውረዳቸው ምሳሌ ነው።
 የመጠመቂያ ውኀው = የማየ ጥምቀት ምሳሌ ሲሆን
 በቤተ ሳይዳ ያለው አምስቱ እርከን(መመላለሻ) =የአምስቱ አእማደ ምስጢር በዚያ ሊያምኑ ያሉ ተስፈኞችና ያመኑባትም ልጅነትን ያገኙባታልና።
 አምስቱ ዓይነት ድውያንም የአምስቱ ጾታ ምዕመናን ከነ ፈተናቸው የተመሳጠረበት ምሳሌ ነው (አእሩግ=በፍቅረ ነዋይ፣ ወራዙት=በዝሙት፣ አንስት=በትውዝፍት በምንዝር ጌጥ፣ ካህናት=በትእቢት አእምሯችን ረቂቅ መዓረጋችን ምጡቅ እያሉ፣ መነኮሳት=በስስት ምግብን በፈለጉት ጊዜ ባያገኙት ይልቁንም አጽንኦ በአት እየፈቱ በአንሰሐስሖ ዘበከንቱ ይፈትናቸዋል) ምሳሌ ሆኖ ይነገራል።
፫·ለአዲስ ኪዳን ድኅነተ ነፍስ ምስጢራዊ ምሳሌ አገባብም አለው፤
 ቤተሳይዳ የበጎች በር በመባልዋ እና በኦሪቱ በጎች ወደ ቤተ መቅደስ ወጥተው ለመስዋዕት ከመቅረባቸው አስቀድሞ የሚታጠቡበት ውኀ ያለበት በመሆኑ ለአዲስ ኪዳንም የመንፈስ ቅዱስ ልጅነት የሚገኝባትን ወደ አማናዊ መስዋዕት ቅዱስ ቁርባን የምታደርስ የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ
 አምስቱን መመላለሻ የምታደርስ ደግሞ ወደ ፍፃሜ ሕግ ፍቅረ ቢጽና ፍቅረ እግዚአብሔር አልፎም ፍጽምት ወደሆነች ወደ ሕግጋተ ወንጌልም የምታደርስ የአምስቱ ብኄረ ኦሪት መፃሕፍተ ሙሴ ምሳሌ ያደርጋቸዋል።
 ለሁከተ ማይ የወረደው መልአክ የመድኃኒታችን የክርስቶስ ምሳሌ ነው
 ከአንድ ብቻ በቀር ሕሙም በአንድ ዕለት አለመዳኑ በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን ጥላ ሥር አምነው ያሉ ምዕመናንና ምዕመናት ብቻ ድኅነተ ነፍስ እዳላቸው ያሳያል።
 የውኀው መናወጽ የሰቃልያነ ክርስቶስ "ሁከተ አይሁድ" ምሳሌ ጥንቱን "ስቅሎ ስቅሎ " የሚለው ያ ቁጣ የዕለተ ዓርብ መድኃኒት መገኛ ነውና።
እስኪ ደግሞ በማጠቃለያው ወደ መጻጒዕ ታሪክ እንመለስና ጥቂት ፍሬ ነገር ለሕይወታችን እንስማ።
ቀድሞ በ`ቤተ ሳይዳ` እያለ የነበረበትን ያንን ሁሉ ጭንቅ ኋላ በሊቶስጥሮስ የፍርድ ገታ ቆሞ በረሳ ጊዜ " ታዲያ ቢያድነኝ በከንቱ መች ሆነና የገዛ አልጋዬን ትቼለት የመጣሁ ለመዳኔ ዋጋ የከፈልኩበት አይደለምን?" እንኳ እንዳይል ያለ ተረፈ ደዌ አንስቶት ያለህን ይዘህ ሂድ እኔ ከአንተ አንዳች አልሻም ባሰኘ ቃል ሸኝቶታል። ግን ታዲያ ይህ ምስኪን መጻጒዕ "ሰው የለኝም" ብሎ የደረሰለትን ሰው ረሳ ማን እንደሆነ እንኳ አላወቀም። ወንጌላዊውም "ዘሐይወ ኢያእመረ ዘአሕየዎ …የዳነው ያዳነውን አላወቀውም" ( ዮሐ.፭፥፲፫) ይለዋል። ያዳነው ማን እንደሆነ ሲጠየቅ ለምሥጋና ያይደለ ለክስ ነበር ስሙን የፈለገው። "ከሚጣፍጠውም ምግቤ ሆዱን ሞላ፥ እኔንም ጣለኝ።" ተብሎ ለናቡከደነፆር በነቢዩ እንደተነገረ ያለ ነው (ኤር.፶፩፥፴፬ ) በአገራችንም ካለው ብሂለ አበው "ታሞ የተነሳ ፈጣሪውን ረሳ" የሚለው እንደነዚህ ያሉትን በሚገባ ለመግለጽ የተነገረ ነው። ሊቀ ነቢያት ሙሴን በዘዳግም ፲ ቁጥር ፳፩ ላይ እንዲህ ይላል "ዓይኖችህ ያዩትን እነዚህን ታላላቆች የሚያስፈሩትንም ነገሮች ያደረገልህ እርሱ ክብርህ ነው፥ እርሱም አምላክህ ነው።" ነገር ግን ይህን ሁሉ ያደረገውን አምላክ ብዙዎች የነበሩ "ህዝበ እስራኤል" ረስተው አሳዝነውት በምድረበዳ በከንቱ ወድቀው ቀሩ ..... ዛሬም ከደዌው :ከማጣቱ :ከችግሩ: ከሥጋ ኑሮ ጉድለቱ ዳግመኛ ለመታረቅ እንደ መጻጒዕ አምላኩን ያልረሳ ማነው? ተአምራቱን አይቶ ቃሉን ሰምቶ አምላኩን ያስታወሰስ ማነው " ቃሉን ያይና ይሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ምክር የቆመ ማን ነውና? ቃሉንስ ያደመጠ የሰማስ ማን ነው?" (ኤር. ፳፫፥፲፰) ማንም። ጌታችን ባስተማረው ማሕየዊ ቃሉ ላይ እንኳ ሳይቀር ያመጹትን አይሁድ እስኪ ተመልከቱ " ገንዘብንም የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው ያፌዙበት ነበር።" ሉቃ ፲፮፥፲፬ እኛንም ቢሆን ከአዳም እስራት ነፃ ያደረገንን አምላክ ውለታ ዘንግተን በቃሉ የምናፌዝ ሁላችንን ወደ ልባችን እንድንመለስ ነቢዩ እንዲህ ሲል ይመክረናል "እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ " እንዲል ( ኢሳ· ፳፰፥፳፪ )።
በፍፃሜ ሕይወቱ በአውደ ምኩናን የሀሰት ክስ የቀረበበትን ይህን የእውነትና የሕይወት ጌታ ቀድሞ ወደ መጠመቂያው እንኳ ለመቅረብ አቅም ያልነበረው ዛሬ ግን አልጋ ለመሸከም በበቃውና ያለ ተረፈ ደዌ በጸናው ኃይሉ የጌታውን ጉንጮች በጥፊ የመምታት ጉልበትና ድፍረት አገኘ። "ዘተሰብሐ ውስተ ገጸ ሙሴ በትስብእቱ ተጸፍአ ገጾ ወተቀስፈ ዘባኖ በእንቲአነ ከመ ይፈጽም ስምዓ ነቢይ ዘይብል መጠውኩ ዘባንየ ለመቅሰፍት ወመላትሕየ ለጽፍአት… በገጹ ነፀብራቅ የሙሴን ፊት ያበራ እርሱ በነቢዩ ጀርባዬን ለግርፋት ጉንጮቼንም ለጽፍአት ሰጠሁ ተብሎ የተነገረውን ለመፈጸም ለእኛ ሲል ፊቱን በጥፊ ተመታ ጀርባውንም ተገረፈ "እንዲል (ሰይፈ ሥላሴ) አምላከ ምሕረት የክብር ጌታ ቀድሞ "ዑቅ ኢትአብስ ዳግመ እንከ ከመ ዘየአኪ ኢይርከብከ … ከዚህ የጠናው "ስለ ደዌ ሥጋ ፈንታ ደዌ ነፍስ" እንዳያገኝህ ሁለተኛ እንዳትበድል" (ቁ ፲፬) ያለውን ዘንግቶ ደዌ ዘኃጢአትን ጠርቶ ተወዳጃት፤ በዕለተ ዓርብ የጌታውን ጉንጮች የጸፉች እጁም ደርቃ `ሰላ` ቀርታለች አንዱ ሊቅ ይህን አልሰማ ባይ መጻጒዕ እና ይቅር ባይ አምላኩን እያደነቀ በጉባዔ ቃናው ይህን ተናገረ
" ይትዐረቅ ምስለ ብእሲት ደዌሁ
ሠላሳ አዝማነ እስመ ነበረት ምስሌሁ"
(መጻጒዕ ከሚስቱ ከደዌ ጋር ይታረቅ ፤ ሠላሳ ዓመታት ከእርሱ ጋር ኑራለችና)
አብረው አያሌ ዓመታት የኖሩ ባልና ሚስት ሲፋቱ ተነፋፍቀው መለያየቱ እምቢኝ እንደሚላቸውና እንደሚታረቁ ሁሉ ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ተብሎ ሳለ ጌታውን ጸፍቶ መጻጒዕም ዳግመኛ ወደ ፴፰ ዓመት "የአልጋ ወዳጁ" ደዌ መመለሱን የቅኔው ምስጢር ያስተምረናል። እንግዲህ እኛም በኃጢአት ከሚመጣ ደዌ ተጠብቀን በአባታዊ ምሕረቱ የሚጠብቀንን ቸሩ አምላካችንን እያመሰገንን በቤቱ እንድንጸና መጻጒዕን "ተነሳ" እንዳለው እኛንም ከወደቅንበት መዘንጋት፣ ኃጢአት በንስእንዲያነሳንና ዳግም ከመበደልም እንዲጠብቀን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን። አሜን

ምኵራብ

ምኵራብ

ቀሲስ ኃይለኢየሱስ ተመስገን

መጋቢት 10 ቀን 2008 ዓ.ም
ከሁሉ አስቀድሞ ሃይማኖትን መመስከር እንዲገባ ቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት አካል ዘእምአካል ባህርይ ዘእምባህርይ የተወለደ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አካላዊ ቃል ድህረ ዓለም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መለወጥ ሳያገኛት ዘር ምክንያት ሳይሆን ከስጋዋ ስጋ ከነፍነፍስ ነስቶ የተወለደ ወልደ እግዚአብሔር ወልደ ማርያም በተዋህዶ ከበረ“ይደልዎነ ንምን ከመ ቦቱ ለወልደ እግዚአብሔር ክልኤቱ ልደታት ቀዳማዊ ልደቱ እም እግዚአብሔር አብ እምቅድመሉ መዋዕል ወዳግማዊ ልደቱ እም እግእዝትነ ቅድስት ድንግል ማርያም በደራዊ መዋዕል”ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ ፴፬ ቁጥር  ክፍል  ብለን በማመን እንደ አባቶቻችን ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን ስለ ምኵራብ እንማራለን የምናነበውን ለበረከት ያድርግልን አሜን።
የእስራኤል ልጆች መቅደስ(Temple) እና ምኵራብ የሚባሉ ሁለት መንፈሳዊ መገናኛዎች ነበሩአቸው፤ ምራብ [በጽርዕ (Synagogue/ συναγωγή)፡ በዕብራይስጥ (Beyth Kenesset/בית כנסתይባላል። መቅደስ የሚባለው በኢየሩሳሌም ብቻ የሚገኝ ስለ ኃጢአት ስለ ምስጋና መሥዋዕት የሚቀርብበት የብሉይ ኪዳን ማዕከል ነው። ምራብ የቦታ ወሰን የሌለው በየአቅራቢያው የሚገኝ አጥቢያ ቤተ ጸሎት ነው።የምኵራብ መታነፅ ከባቢልን ምርኮ (exile in Babylon 538 A.D.) ጋር የተያያዘ ታሪክ አለው። በባቢሎን ምርኮ በባእድ ሀገር በዚያው ባሉበት ስርተ አምልኮ ለመፈፀም ዳግመኛም ይህ ሁሉ መከራ በአባቶቻችን የተደረገባቸው ቤተመቅደስን ባይሰሩ ነው እኛ ሚጠት የተደረገልን እንደሆነ ቤቱን እንሰራለን በሚል ዋናውን ቤተ መቅደስም ሆነ ብዙ ምኵራባት ሰርተዋል። 10 አባወራዎች ባሉበትም ምኵራብ እንዲሰራ ህጋቸው ያዝ ነበር። በምኵራብም የሚደረገው መንፈሳዊ አገልግልት የብይ ኪዳን መጻሕፍትን ማንበብ መስማትና መተርጎም ንዑሳን በዓላትንም ማክበር ነበር።ማንኛውም እስራኤላዊ በዓመት ሦስት ጊዜ ለበይት በዓላት በኢየሩሳሌም መቅደስ ተገኝቶ አምልኮን መፈጸም ግዴታው ነበር። በምኵራብ ግን በየዕለቱ እየተገኙ ቅዱሳት መጻሕፍትን በንባብ በትርጓሜ ይሰማሉ።
በቃል መነገሩ በልብ መታሰቡ ከፍ ከፍ ይበልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራብ ተገኝቶ እንዳስተማረ ለመግለጥ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅደስ ያሬድ ማሕሌታዊ የዓቢይ ጾም ሦስተኛውን ሰንበት ምኵራብ ብሎ ሰይሞታል። ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ፡- “ ቦኦ ኢየሱስ ምኲራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋት አበድር እመስት አነ ውእቱ እግዚአ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት ኢትግበሩ ቤተ አቡ ቤተ ምስያጥ ቤትየ ቤተ ጸሎት ትሰመይ . . .”ትርጓሜው፡- “ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ። የሃይማኖትን ቃል አስተማረ። ከመሥዋዕትም ምጽዋትን እወዳለሁ አላቸው። የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷ እኔ ነኝ አላቸው የአባቴ ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል። ምኵራብ ገብቶ ተቆጣቸው ዝም ይሉ ዘንድ ትምህርቱን የቃሉን ሞገስ፣ የነገሩን መወደድ፣ የአፉን ለዛ አደነቁ” በማለት ቅደስ ያሬድ ዘምሯል።
ቅዱስ ያሬድ በሰዓታት በወራት እና በዘመናት የተከፋፈሉ ድንቅ ምሥጢር የያዙ መዝሙራትን(ምስጋና) ከብሉያትና ከሐዲሳት ለቤተክርስቲያን እንደ ንብ ቀስሞ እንደ ሰምና ወርቅ አስማምቶ የአገልግሎት ሥርዓትን የሠራ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ነው።ለምኵራብ የሚሆነውንም ዝማሬ ከዮሐ 2፡12-25 ላይ ወስዶ አመስጥሮ እስማምቶ ጾመ ድጓ በተባለ ጽሐፉ አዘጋጅቶልናል። ይህንን የመጽሐፍ ክፍል እንደሚከተለው እናየዋለን።
ቁ.12 ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀመዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፣ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ” ከቃና ዘገሊላው የዶኪማስ ቤት ሰርግ ውሃውን ወይን አድርጎ ታምራቱን ካሳየ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ከእናቱና ከወንድሞቹ ደቀመዛሙርት ጋር ሄደ በዚያም ጥቂት ቀን (11 ቀን ይላል በወንጌል አንድምታ) ተቀመጡ። ቁ.13 የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳም ወጣ።” ይህም የመጀመሪያ ፋሲካ ነው ጌታ የተሰቀለው በአራተኛው ነውበምስጢርም ኢየሩሳሌም ወጣ መባሉ ጌታ ከሕይት ወደመስቀል ምእመናንም ወደ ሕይት የሚሄዱበት ዘምን በደረሰ ጊዜ ጌታ ገረ ሰላም ኢየሩሳም ወደተባለ መስቀል ሄደ ማለት ነውቁ.14 በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤” ለስም አጠራሩ የክብር ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራብ በተገኘ ጊዜ በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው ከሚነበበው እና ከሚተረጎመው ከሚፀለየውም ይልቅ የሚሸጠውና የሚለውጠው በዝቶ ተመለከተ ውንብድና ቢሉ ፈሪሳዊያን የሚያንፀባርቅ እና የሚያንሽዋሻ ልብስ ለብሰው በውጭ ከብቱን ያስደነብሩና ወደምኵራብ ያስገቡታል ከዚያም ከል የገባ አይነጣም ቤተመቅደስ የገባ አይወጣም እያሉ የህዝቡን ገንዘብ ይቀሙታል።መለወጥ ቢሉ ህዝቡ መባ ሊያስገቡ ቀይ ወርቅ ይዘው ሲመጡ እግዚአብሔርማ የሚሻው ነጭ ወርቅ እንጅ ቀይ ወርቅ ነውን ይሉታል እነርሱም በትህትና እውነት ነው ብናጣ ነው እንጅ ለእግዚአብሔርማ ንፁህ ማቅረብ ይገባል ይላሉ ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም ሁለት ቀይ ወርቅ ብታመጡ ባንድ ነጭ ወርቅ እንለውጣችኋለን እያሉ ይበዘብዟቸዋል።ከብቱን ከስቷል ጥፍሩ ዘርዝሯል ፀጉሩ አሯል ለእግዚአብሔርማ የሰባውን ማቅረብ ይገባል ይሏቸዋል እነርሱም በትህትና እውነት ነው በመንገድ ደክሞብን ከስቶብን እንጅ ለእግዚአብሔርማ የሰባውን ማቅረብ ይገባል ይላሉ ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም ሁለት የከሳ ከብት ብታመጡ ባንድ የሰባ እንለውጣችኋለን ይሏቸዋል መሸጥም ቢሉ የከሳውን ከብት አወፍረው አድልበው ይሸጡ ነበር
ቁ.15-16 የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ። የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው፡” በቤተ ፀሎት ይህን ያልተገባ ነገር ሲፈፅሙም የገመድ ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው ይላል ይህንም ጅራፍ ሐዋርያት አዘጋጅተው ሰጥተውታል የጭፍራውን ለአለቃው መስጠት ልማድ ንውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ገበያውን ፈታ። ለሰውነታቸው ቤዛ የሚሆናቸው ስለሆነም የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ በትር አይችሉምና ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ አላቸው። የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው። በተአምራትም ገንዘብ ገንዘባቸውን ለይቶ ከዛፍ ላይ እንደሰፈረ ንብ ከቃ ከቃቸው ላይ አስቀምጦላቸዋል። ቁ.17 ደቀ መዛሙርቱም የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደተጻፈ አሰቡ።ነቢየ እግዚአብሄር ቅዱስ ዳዊት በመዝ 68፡9 በቤተ መቅደስ ስዕለ ፀሀይ አቁመውበት መስዋእተ እሪያ ሰውተውበት ገበያ አድርገውት ሲሸጡበት ሲለውጡበት በመንፈሰ ትንቢት ተመልክቶ ለቤተ እግዚአብሄር የቀናውን ቅናት እንደ እሳት አቃጠለኝ ይላል።
እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕየ ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ። ትርጉም የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና ነፍሴን በጾም አስመረርኋት። 
ይህ ትንቢት ለጊዜው ለመቃቢስ ፍፃሜው ለጌታ የተነገረ ነው። በመቃቢስ ጊዜ አንያኮስ በቤተመቅደሱ አምልኮ ፀሀይ አግብቶ እሪያ ሰውቶ ነበርና፤መቃቢስ ያንን አጥፍቶ ለቤተመቅደሱ የቀናውን ቅንዓት ያመለክታል። በልዑል እግዚአብሔር ላይ በስህተትም ሆነ በድፍረት የሚቀርብ ተግዳሮት በቅዱሳንም ይደርሳል። ልዑል እግዚአብሔር ባህርዩ ደርሶ የሚገዳደር የለም እርሱ ነገሥታት የማይነሣሡበት መኳንንትም የማይበረታቱበት አምላከ አማልክት ወንጉሠ ነገሥት ነው። ነገር ግን የአምልኮቱ መገለጫ በሆኑት በቤተመቅደስ ውስጥ ባሉት ታቦታት፣ንዋያተ ቅደሳት፣በዓላትና ሥርዓቶች እንዲሁም እርሱ የላካቸውን ቅዱሳን መግፋት መገዳደር ጌታ እግዚአብሔርን መገዳደር ነው። ነቢየ እግዚአብሄር በቤተመቅደስ ገበያ አቁመው የሚገዳደሩትን ባየሁ ጊዜ ተግዳሮታቸው በእኔ ላይ ወደቀ ነፍሴንም በጾም አስመረርኋት ይላል። በደብተራ ኦሪት ሁለት እጓላተ ለህም አቁመው እንደተገዳደሩት፣መና ከደመና አውርዶ ቢመግባቸው ምንት ጣዕሙ ለዝ መና ብለው እንደተፈታተኑት ፣ በኋላም ወልደ እጓለ እምሕያው ስጋየን የበላ ደሜን የጠጣ የዘላለም ህይወት አለው ቢላቸው እፎ ይክል ዝንቱ የሀበነ ሥጋሁ ንብላዕ ብለው እንደተገዳደሩት በመንፈሰ ትንቢት ተመልክቶ ሰውነቴን በርሃብ በቀጠና አደከምኩዋት እያለ ነቢየ እግዚአብሔር የተናገረውን ደቀመዛሙርቱ አስበው እነሱም ለቤቱ ቀኑ በዚህ ዘመን እኛም ለቤተክርስቲያን ቅናት ሊኖረን ይገባል ለክብሩ መቅናት ለገዳማቱ ለአብነት ትምህርት ቤቱ መፈታት ለሊቃውንቱ መታረዝ ልቡናችን ሊቃጠል ይገባል። ኢየሱስም መልሶ ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው ስለዚህ አይሁድ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፣ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን አሉት። እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተመቅደስ ይል ነበር። ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ይህን እንደተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ።” ቁ.19 እና 20 በ46ቱ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት የተነገረውን ልደቱን ሞቱን በሶስተኛው ቀን መነሳቱን ሁሉ ስለ ሰውነቱ አስረዳቸው። እሠራዋለሁ አላለም አነሣዋለሁ እንጂ። በዚህም የሞቱንና የትንሣኤውን ነገር ገለጠ።
አንጽሆተ ቤተመቅደስ
ይህም ቀን የማንጻት ቀን አንጽሆተ ቤተመቅደስ ይባላል።ኦሪት ወንጌልን፣ ምኵራብ ቤተክርስቲያንን አስገኝተዋል ጌም የበግ የፍየል መስዋእት መቅረቱን ለቤዛ ዓለም መምጣቱን አስተማሯቸዋል አስጠንቅቋቸዋል። ምኵራብ ሁሉ የማይገባባት ነበረች በመጽሐፈ ነህምያ ምዕ 13፡1 “አሞናውያንና ሞዓባውያንም ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ለዘላለም እንዳይገቡ የሚል በዚያ ተገኘ።” ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የማይመረጥባት አንተ አይሁዳ አንተ ሮማዊ የማትል አንዲትት ቤተመቅደስን ሰጠን
ምኵራብ /ቤተ መቅደስ/ የሰውልጅ ምሳሌ ነው ምኵራብ የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው። የሰው ልጅም የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው ሸቀጡም የኃጢአት ምሳሌ ነው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ሰውነትን ስለማንፃት እና እራስን ከሸቀጥ ስለማራገፍ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ያስተማረውን ማሰብ ያስፈልጋል እኛም የህያው አምላክ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተመቅደስ ነንና ሰውነታችን ሽያጭ የሚፀናበት እንዳይሆን ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል
1ኛቆሮ ምዕራፍ 3-17 “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።”
1ኛቆሮ ምዕራፍ 6-20 ላይ “ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።”
2ኛቆሮ ምዕራፍ 2-17 የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።
በቅዳሴ ያዕቆብ ዘስሩግ “ተንስኡ በፍርሃተ እግዚአብሔር ከመ ታፅምኡ አርኅው መሳክወ አእዛኒክሙ ወአንቅሁ ልበክሙ” እግዚአብሔርን በመፍራት ተነሱ የጆሮቻችሁን መስኮቶች ክፈቱ ልቦናችሁን አንቁት እንደተባልን ሳንዝ ማን አዚም አደረገባችሁ ተብለንም እንዳንወቀስ የእግዚአብሔርን ተግሳፅ የአበውን ምክር ሰምተን አሁን ሰውነታችን በንስ ለማንጻት እንነሳ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም በመዝ 94፡8 “ዮም አመ ሰማዕክሙ ቃሎ ኢታፅንኡ ልበክሙ ዛሬ የእግዚአብሔርን ቃል ስትስሙ ልባችሁን አታፅኑት እንዳለ ይህን በምኵራብ አምላካችን ያደረገውን ስንሰማ የዘረኝነት የፍቅረ ንዋይ የተንኮል የትዕቢት ሸቀጣችን ትተን ቤተመቅደስ ሰውነታችን በንስ አጥበን ልባችን በትህትና ሞልተን በቤቱ ለበለጠው ጸጋ ቀንተን ቅንነትንም አክለን በቤቱ ለመኖር አምላካችን ይርዳን አሜን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!