Thursday, 19 May 2016

ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊው ሊቅ

 ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊው ሊቅ
መግቢያ
መላእክት ምስጋናቸው እረፍታቸው ፣ እረፍታቸው ምስጋናቸው ሆኖ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ እግዚአብሔርን ያለማቋረጥ ያመሰግናሉ፡፡ ቤተክስቲያንም አምሳለ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ናትና ይህን አብነት በማድረግ ልዑል እግዚአብሔር ሃያ አራት ሰዓት የሚመሰገንበትን የምስጋና ሥርዓት ዘርግታለች፡፡
ሕያው እግዚአብሔር የአዳም ልጆች በመላእክት ምስጋና እንዲያመሰግኑት በመውደዱ ሰማያዊውን ምጋና ይማር ዘንድ ቅዱስ ያሬድን መረጠ፡፡

• ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊው ሊቅ
ቅዱስ ያሬድ ሚያዝያ 5 ቀን 505 ዓ.ም አክሱም ከተማ ተወለደ፡፡ ያሬድ ማለት መውረድ ማለት ነው ፡፡ ሰማያዊውን ጣእመ ዜማ ወደ እኛ የሚያወርድ ነውና፡፡
‹‹ዋይ ዜማ!!! ዘሰማዕኩ እመላእክት ቅዱሳን ›› ‹‹ ከሰማይ ከቅዱሳን መላእክት የሚያስደንቅ ዜማ ሰማሁ›› በማለት እንደተናገረ በአክሱም መጻሕፍትን እያስተማረ ሳለ ከሰማያውያን መላእክት ጣእመ ዜማን ተማረ፡፡ በተመስጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ተነጠቀ፡፡ በዚያም መላእክት ልዩ ጣእም ባለው የዜማ ድምፅ ሊያመሰግኑ ሲዘምሩና ሲያሸበሽቡ አየ፡፡ ከጣዕመ ዜማውም የተነሣ ተደነቀ፡፡ የእግዚአብሔርን ስም እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስን በጠራ ጊዜ የሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ዜማ ተገለጸለት፡፡ ተመልሶም ወደ ምሥራቅ ዞሮ እጁንም ዘርግቶ ‹‹ ሃሌ ሉያ ለአብ ፣ ሃሌ ሉያ ለወልድ ፣ ሃሌሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን . . . ›› ብሎ በአክሱም ከተማ ሙራደ ቃል /የቃል መውረጃ/ በተባለችው ሥፍራ ለመጀመሪያ ጊዜ ዜማን በዐውደ ምሕረት ያሰማ የዜማ ደራሲ ነው፡፡
• የቅዱስ ያሬድ አስተዋጽኦ
ዓለም ከሚያውቃቸው የዜማ ደራስያን ከሞዛርትና ከሌሎችም አስቀድሞ ቅዱስ ያሬድ ግእዝ፣ እዝልና አራራይ በተሰኙ የዜማ ስልቶች የማይሰለችና ዘመን ተሸጋሪ ዜማን፣ የዜማ ምልክቶችንና የተለያዩ ድርሰቶችን በመድረስ ሃገራችን የዚህ ታላቅ መንፈሳዊ ሀብት ባለቤት እድትሆን አድርጓል፡፡
ቅዱስ ያሬድ በሰዓታት ፣በወራትና በዘመናት የተከፋፈሉ ድንቅ ምስጋናዎችን ከብሉያትና ከሐዲሳት ንባብና ምሥጢር ለቤተክርስቲያን እንደ ሰምና ወርቅ አስማምቶ የአገልግሎት ሥርዓትን የሠራ የቤተ ክርስቲያን አምድ ነው፡፡
የቅዱስ ያሬድ ዜማ ድንቅና ጥልቅ የነገረ ሃይማኖት አስተምህሮት ፣ የቅዱሳት መጻሕፍን ንባብ ትርጓሜ እንዲሁም የታሪክ ምስክርነትን የያዘ ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ድርሰት ነው፡፡
ቅዱስ ያሬድ ዛሬ በጉባኤ ቤት ለዜማ ትምህርት ቤተክርስቲያን የምትገለገልበትን ሥርዓተ ትምህርትና የመማሪያ መጻሕፍትን የደረሰ ሊቅ ነው፡፡ ድረሰቶቹም ምዕራፍ ፣ጾመ ድጓ፣ ዝማሬና መዋሥዕት ይባላሉ፡፡
ቅዱስ ያሬድ በአክሱም በመምህሩ በጌዴዎን ወንበር ተተክቶ መጻሕፍተ ብሉያትና ሐዲሳትን አስተምሯል፡፡ ከአቡነ አረጋዊና ከአፄ ገብረ መስቀል ጋርም በመሆን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎት በጣና ቂርቆስ ፣በዙር አባ አቡነ አረጋዊ ገዳም እንዲሁም ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ እስከ ብርብር ማርያም በመሄድ ያስተማረ ታላቅ ሐዋርያ ነው፡፡
አጠቃላይ በሥነ ጽሑፍና በቋንቋ እድገት በነገረ መለኮትና በታሪክ ትምህርት እንዲሁም በሥርዓተ ጸሎት የቤተ ክርስቲያን አንድነት በማስጠበቅ ረገድ ጽኑ መሠረትን የጣሰ ታላቅ ሊቅ ነው፡፡
• የቅዱስ ያሬድ ምናኔ
ቅዱስ ያሬድ የሕይወት ዘመኑን በጸሎትና በብሕትውና ለማሳለፍ ወደ ሰሜን ተራራ ምድረ ጸለምት በመሄድ /በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በበየዳ ወረዳ በሚገኝ ሥፍራ/ ብርድ በጸናበት በረዶ በሚፈላበት በሐዊ ተራራ በጽሙና ተቀምጧል፡፡ በዚያም ጉባኤ ዘርግቶ ትምህርት አስፋፍቶ ለሃያ ሁለት ዓመታት አስተምሯል፡፡
ቅዱስ ያሬድ ዘመኑን ሁሉ በማኅሌት እግዚአብሔርን በማገልገል በጣእመ ዜማው ዲያብስን ድል መትቶ በዚያው በሐዊ ተራራ በሚገኝ ዋሻ ውስጥ ገብቶ ግንቦት 11 ቀን በሰባ አምስት ዓመቱ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ተለይቷል፡፡ ቤተክርስቲያንም ቅድስናውንና አማላጅነቱን አምና በስሙ ጽሌ ቀርጻ፣ ቤተክርስቲያን አንጻ ፣ ድርስቶቹንም የቤተክርስቲያን መገልገያና የስርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ አድርጋ እየተጠቀመችባቸው ተገኛለች፡፡
በምናኔ በኖረበት ሥፍራም በስሙ ገዳም ተገድሞ መናንያን አሰረ ፍኖቱን ተከትለው ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው፣ በረዶውንና ውርጩን ታግሠው በስሙ እየተማጸኑ ይኖራሉ፡

የቅዱስ ያሬድ የዜማ ዓይነቶች 3ት ናቸው፡፡ እነርሱም ግእዝ፣ዕዝልና አራራይ  በመባል ይጠራሉ፡፡ ሦስቱም የዜማ ዓይነቶች ምን ጊዜም ሕያዋን ሆነው በቤተክርስቲያን ሰፊ የአገልግሎት ድርሻ አላቸው፡፡ ሦስቱም ዜማዎች መጽሓፍ ቅዱሳዊ ምሳሌና ትርጉም አላቸው የዜማዎቹ ሦስትነት የምሥጢረ ሥላሴ ምሳሌ ሲሆኑ ለአንድ አገልግሎት /ምስጋና/ መዋላቸው ደግሞ የሥላሴን አንድነት ያስረዳል፡፡

ይህም ሲተረጎም፡-
  • ግእዝ ማለት በመጀመሪያ የተገኘ ማለት ነው፡፡ የቃሉ ትርጓሜም ‹‹ገአዘ›› ነጻ ወጣ ማለት ሲሆን በዜማነቱ ሲተረጎም ስልቱ የቀና ርቱዕ ቀጥ ያለ ጠንካራ ማለት ይሆናል፡፡ ምሳሌነቱም የአብ ሲሆን ከዜማው ጠንካራነት የተነሳ ሊቃንቱ ደረቅ ዜማ ብለውታል፡፡
  • ዕዝል፡- ከግእዝ ጋር ተደርቦ ወይም ታዝሎ የሚዜም ለስላሳ ዜማ ነው ዕዝል ጽኑዕ ዜማ ማለት ሲሆን በወልድ ይመሰላል፡፡ ምክንያቱም ወልድ ጽኑዕ መከራን ተቀብሏልና፡፡
  • አራራይ፡- የሚያራራ የሚያሳዝንና ልብን የሚመስጥ ቀጠን ያለ ዜማ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ይመሰላል፡፡ ሐዋርያትን ከበዓለ ጰንጠቆስጤ /ከበዓለ ጰራቅሊጦስ/ በኋላ ያረጋጋ፣ ያጽናና እና ጥብዓት /ጽፍረት/ የሰጣቸው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡የሐዋ. 2፤1 ዮሐ.15 26 ፡፡
በቤተክስቲያን የሚቀርበው ምስጋና በሙሉ በሦስቱ የዜማ ዓይነቶች  ነው ከዚህ የሚወጣ ዜማ ያለው ዝማሬ በቤተክርስቲያን የለም ቢኖርም የቤተክርስቲያን አይደለም፡፡ ማንኛውም ሰው በቤተክርስቲያን መዝሙር የሚያቀርበው የቅዱስ ያሬድ የዜማ ምልክቶችና ዓይነቶች ተከትሎ ነው፡፡ ከሦስቱም የዜማ ዓይነቶች የወጣ ዜማ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ሦስቱም የዜማ ዓይነቶች ራሳቸውን ችለው የሚዜሙ ቢሆኑም አንዱ የዜማ ዓይነት በሌላው የዜማ ዓይነት ውስጥ የሚገኝ መሆኑን መታወቅ አለበት፡፡ ለምሳሌ ያህል በግእዝ የዜማ ዓይነት የአራራይ ዜማ ይገኛል፡፡ ይህ ሲባል ግን አንዱ ሌላውን ይተካል ማለት ሳይሆን አንዱን የዜማ ዓይነት በሌላው የዜማ ዓይነት ውስጥ በተወሰነ መጠን ተመሳስሎ ይገኛል ለማለት ነው፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት፡- የቅዳሴ፣ የኪዳን፣ የሰዓታት ጸሎት በሦስቱም የዜማ ዓይነቶች የተቀመረ ሆኖ እናገኘዋልን፡፡  አንድን ቃል ወይም ጸሎት በሦስቱም የዜማ ዓይነቶች ማዜም ይቻላል፡፡