ከሙሴ ፊት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ከበረከት ጉዲሳ
ክፍል 1
የተወደዳችሁ የዳረጎት
ዘተዋሕዶ ጦማር ተከታታዮች በመግቢያችን አንዳንድ ሃሳቦች ላይ ዉይይት አድርገን ነበር እነሆ ቀጣዩ
፩. ሙሴ
ከባርነት ያወጣቸው ህዝቦች እነማን ናቸው?
እስራኤላዊያን በግብፅ
የእስራኤላዊያን የግብፅ
የስደት ታሪክ የሚጀምረው እግዚአብሔር ስሙን ቀይሮ እስራኤል ካለው‹ ‹ነገስታትም ከጉልበትህ ይወጣሉ ለአብርሃምና ለይስሐቅ የሰጠኋትን
ምድር ላንተ እሰጣለው ከአንተም በኃላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጣለው››ዘፍ 34፡10-12 ብሎ ቃል ከገባለት ከ ያዕቆብ እና
ከልጆቹ ነው፡፡ ያዕቆብ አስራ ሀለት ልጆች ነበሩት እነሱም
ከልያ የተወለዱት ሮቤል፣ስምዖን፣ሌዊ፣ይሁዳ፣ይሳኮር እና ዛብሎን ናቸው፡፡
ከራሔል የተወለዱት ደግሞ ዮሴፍ እና ብንያም ናቸው፡፡ ከራሔል ባርያ
ከ ባላ የተወለዱት ዳን እና ንፍታሌም ናቸው፡፡ እነዲሁም ከልያ ባርያ ከዘለፋ የተወለዱት ደግሞ ጋድ እና አሴር ናቸው፡፡ ከእነሱ መካከልም ያዕቆብ በእርጅናው ወቅት የወለደው በመሆኑ አብልጦ የሚወደው
ዮሴፍን ነው፡፡ ካለው ፍቅረም የተነሳ በብዙ ኅብር ያጌጠች ቀሚስም ከሌሎቹ ወንድሞቹ ለይቶ አድርጎለታል፡፡ በዚህም ወንድሞቹ ይጠሉት
ስለነበር ከአባቱ ተልኮ ወደነሱ ዘንድ በመጣ ሰዓት ተመካክረው ለእስማኤላዊያን በ20 ብር ሸጡት እስማኤላዊያንም ወደ ግብፅ ወስደው
በግብፅ ለፈርኦን ጃንደረባ ለዘበኞቹ አለቃ ለጴጢፋራ ሸጡት ዮሴፍም በጌታው ፊት ሞገስን ስላገኘ በቤቱ ሾመው ካለውም ሁሉ ሰጠው ዮሴፍ መልከ-መልካም በመሆኑ የጌታው ሚስት ከሷ ጋር እንዲተኛ አስገደደችው
ልብሱንም ተጠምጥማ ያዘች ዮሴፍ ግን ኃጢአት ላለመስራት እነዲሁም ጌታውን ላለመበደል ሲል ልብሱን ጥሎላት ትቷት ወጣ በዚህም <ሊሳለቅብኝ ወደ እኔ ገባ>ብላ በሀሰት ከሰሰቸው ጌታውም
በቁጣ ዮሴፍን ወደ ግዞት ቤት አስገባው፡፡ በዛም ሳለ በግዞት ቤቱ አለቃ ፊት ሞገስን አገኘ በዛው ሳለ በድለው ለመጡ ለፈርኦን
የጠጅ አሳላፊ እና የእንጀራ አበዛ ህልምን ፈቶላቸዋል ይህም ህልም
ፈቺነቱ ታውቆ ለፈርኦንም ሰባቱን የጥጋብ ዘመን እነዲሁም ሰባቱን የረሀብ ዘመን የፈታውም ዮሴፍ ነው፡፡ በዚህም ፈርኦን ዮሴፍን
‹ሁሉ ነገር እግዚአብሔር ላንተ ገልጾልሃልና ካንተ በቀር ብልህ የሚሆን ዓዋቂ ሰው የለም በቤቴ ሁሉ አንተ ተሾም ሠራዊቴንም ሁሉ ለአንተ ቃል ይታዘዝ› ብሎ
በግብፅ ምድር በሙሉ ተሾመ ዮሴፍ በፈርኦን ፊት ሞገስን ከማግኘቱ
የተነሳ የጣቱን ቀለበት አደረገለት ነጭ ሀርም አለበሰው የወርቅ ዝርግፍም አሠረለት ስሙንም እስፍንቶፎኔህ አለው ‹‹ወሰየሞ ሶሞ
ፈርዖን ለዮሴፍ እስፍንቶፎኔህ›› ትርጓሜውም መዝገበ ኅቡአት ፣ ሊቀ
ማእምራን ማለትነው አማርኛ ፍቺውም የአዋቂዎች አዋቂ ማለት ሲሆን በተለምዶ አራት አይና ይባላል፡፡
የሰባቱ የድርቅ ዘመን በግብፅ አስቀድሞ ስለታወቀ በሰባቱ የጥጋብ ዘመን የተጠራቀመውን እህል
በሰባቱ የረሀብ ዘመን ይሸጡ ነበር፡፡ በዚህም ያዕቆብ በግብፅ እህል እንዳለ ሰምቶ አስሩን ልጆቹን ወደ ግበፅ ላካቸው እህልም እንዲሸምቱ
አዘዛቸው ብንያም ግን ከአባቱ ጋር ቀረ በግብፅ በደረሱ ሰዓትም ወንድማቸው ዮሴፍ አወቃቸው በመጀመሪያ
ራሱን አልገለጠላቸውም ነበር በኃላ ግን እራሱን ገለጠላቸው አትዘኑም አላቸው በደስታም አቀፋቸው ‹‹እግዚአብሔር ሕየወትን ለማዳን
ከእናንተ ፊት ሰዶኛልና›› አላቸው አባታቸውንና የቤትን ሰዎች ሁሉ ከብቶቻቸውንም ጭምር ይዘው ወደ ግብፅ እንዲመጡ ነገራቸውም በመጡም
ሰዓት በጌሴም ተቀበላቸው
አሳረፋቸውም፡፡ ጌሴም በብሉይ ኪዳን መሰረት በታችናው (ሰሜናዊ) ግብፅ በአባይ ወንዝ አፍ ሠፈር
ትገኛለች እስራኤላውያን በጌሴም 400 ዓመታትን ቆይተዋል፡፡ ጌሴም ራምሴም በመባል ትታወቃለች፡፡፡ እስራኤላዊያን ወደ ግብፅጌሴም
ሲገቡ 70 ሆነው ነበር፡፡ (ዘፍ 37 -ዘፍ 50 )
ዮሴፍ የተሸጠው በ17 አመቱ ነው በፈርኦን ሲሾም 30 ዓመቱ ነበር ያረፈው 110 ዓመቱ ነው
በሳጥን አድርገው ያኖሩትም በዛው በግብፅ ነው፡፡ በግብፅ ዮሴፍን
የሚጠላ ንጉስ ተነሳ ‹እነሆ የእስራኤል ልጆች ብዙ ጽኑ ሆኑ ይበረታቱብናል ፈፅመው በዝተዋል ከእኛም እነሱ ይፀናሉ ከጠላቶቻችን
ጋር ሆነው ዕኛን ይወጉናል ካገራችንም ያስወጡናልና ኑ ብልሃት እንስራባቸው ጡብ እናስጥላቸው ጭቃ እናስረግጣቸው ኖራ እናስወቅጣቸው›
አለ ብሎም አልቀረ መከራን ዕንዲያፀኑባቸው የሰራተኛ አለቆችን ሾመባቸው እስራአላውያን ግን መከራ ያጸኑባቸውን ያህል እንደ መከራው
ብዛት እየበዙ እየጸኑ ነበር በዚህም አልበቃ ብሎ ንጉሱ ለዕብራዊያን ሴት አዋላጆች‹ ወንድ ከተወለደ ይገደል› ብሎ ትዕዛዝ ሰጠ
ነገር ግን አዋለጆቹ እግዚአብሔርን ፈርተው የንጉሱን ትዕዛዝ ሳይፈፅሙ ቀሩ እስራኤላዊያንም ዳግም በአዋላጆች በጎነት በእግዚአብሔርም
ቸርነት በዝተው በረቱ ዳግም ንጉሱ የተወለደ ወንድ ልጅ በውሀ ይጣል ብሎ አወጅ አወጣ
በዚህ ጊዜ
ለህዝቡ ተስፋ የሚሆን ሙሴ ተወለደ
አዲስ ዘመንና ቀመሩ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዘመን የሚቆጠርበት፣ ቀመር የሚቀመርበት ትምህርት ባሕረ ሐሳብ
ይባላል። ባሕረ ሐሳብ ከሁለት የግእዝ ቃላት የተገኘ ነው። ባሕር ማለት በዘይቤ ሳይሆን በምሥጢር ወይም በምሳሌው
ዘመን ማለት ነው፤ “በመዳልው ደለወ ዓለመ በመሥፈርት ሠፈራ ለባሕር” እንዲል። ባሕርን ሰፈራት ይላል፤ ባሕር
የሚሠፈር ሳሆን ባሕርን ዘምን ለማለትና ዘመን በአዕዋዳት የሚታወድ፣ በቀመር የሚቀመር፣ የሚሠፈር መሆኑን ለማሳየት
ነው። ሐሳብ ማለት ፍችው ብዙ ቢሆንም እዚህ ላይ በአጭሩ ቁጥር ማለት ነው። “ኢትትሐሰብሙ ወርቆሙ ወብሩሮሙ
ወለጽድቅከኒ አልቦቱ ሐሳብ” (ለቸርነትህ ቁጥር ሥፍር የለውም) እንዲል አረጋዊ መንፈሳዊ፤ እንዲሁም ቅዱስ ዳዊት
“ብፁዓን እለ ተኀድገ ሎሙ ኃጢአቶሙ ወእለ ኢሐሰበ ሎሙ ኵሎ ጌጋዮሙ” (ኃጢአታቸው የተተወላቸው፣ በደላቸው
ያልተቆጠረባቸው ብፁዓን ናቸው) መዝ. 31፥1 ይላል። ስለዚህ ባሕረ ሐሳብ ማለት የዘመን አቆጣጠር ማለት ይሆናል።
ሐሳበ ባሕርም ቢል ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ነው። ኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠራቸውን፤ የበዓላትና የአጽዋማት
አከባበራችን የሚመነጨው ከባሕረ ሐሳብ ነው።የዘመን መለወጫ በመስከረም ስለመሆኑ
ሌሊቱ አልፎ ቀኑ ሲተካ ነጋ እንደምንል ክረምቱም አልፎ በጋው ሲተካ መስከረም ነጋ(ጠባ) እንላለን ይህም ከጨለማ ወደ ብርሃን ወጣን እንደማለት ነው። እንደዚሁም ሌሊቱን እንደምን አደራችሁ? ክረምቱን እንደምን ከረማችሁ? በማለትም ሰላምታ እንለዋወጣለን መልሱም እግዚአብሔር ይመስገን ብቻ ነው። ምክንያቱም ግርማ ሌሊቱን አሳልፎ ንፁህ አየርና ሰማይ ለማየት ላበቃን አምላክ ምስጋና ማቅረብ ተገቢ ስለሆነ ነው። መስከረም አሮጌው ዘመን አልፎ አዲሱ ዘመን የሚተካበት የወሮች መጀመሪያና የምድር ፍሬና የአደይ አበባ መታየት የሚጀምርበት ለፍጥረት ሁሉ አመች የሆነ የደስታ የተስፋና የበረከት ወር ነው። ስለዚህም ነቢዩ ዳዊት “በቸርነትህ ዘመን የተገኘውን እህሉን ታበዛዋለህ ተራሮች ልምላሜን አግኝተው ደስ ይሰኛሉ። የምድረ በዳ ተራሮችም በዝናብ ይረካሉ። ኮረብቶችም ደስ ብሏቸው ልምላሜውን እንደዝናር ይታጠቃሉ። የበግ አውሮች ስብን ይሰባሉ። ሸለቆዎችም እህልን ተሞልተው በደስታ ያመሰግናሉ ይዘምራሉ።” መዝ. 64፥11
መስከረም የዘመን መለወጫ ወርና ዕለት የሆነበት ምክንያት፤ ይሄውም የአዳም አስረኛ ትውልድ በሆነው በኖህ ዘመን የነበረው ማየ አይህ ከገፀ ምድር ጐድሎ ርግብ ለምለም ቅጠል ይዛ የመጣችበት እንዲሁም ኖህ ከመርከብ የወጣበት እግዚአብሔር አምላካችን በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፣ ብርድና ሙቀት፣ በጋና ክረምት፣ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም ብሎ ቃል ኪዳን የገባበት ስለሆነ ዓለም በዚህ ወር ይጀምር ነበረ (ዘፍ. 8፥8-22) ።
ሁለተኛም የኖህ ልጅ ካም ከወንድሞቹ ጋር ዕጣ በተጣጣሉ ጊዜ አፍሪካ ደረሰው ካም ወደዚህ ምድር የገባውም ልምላሜና አበባ ደምቆ አሸብርቆ በሚታይበት፣ ሌሊትና መዓልት በሚተካከሉበት በመስከረም ወር ነበር። እግዚአብሔር ለእስራኤል ነጻ የወጣችሁበት ወር የዓመት መጀመሪያ ይሁናችሁ እንዳላቸው ሁሉ (ዘጸ. 12፥2) የካም ልጆችም ይህንን ወደ ኢትዮጵያ የገቡበትን ወር የዓመት መጀመሪያ ይሁነን ብለው ርዕሰ ዓውደ ዓመት አድርገው ሰይመውታል (ኢሳ. 30፥29)።
እንቁጣጣሽ
እንጣጣሽ ልጆች ለወላጆች በአዲሱ ዓመት ዕለት የሚያቀርቡት የእንኳን አደረሳችሁ ገጸ በረከት ነው። ይኸውም ምሳሌ ዘፍ. 8፥8 በተጻፈው ታሪክ ላይ የተመሰረተ ነው። ርግብ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ ወደ ኖኅ ስለመጣች እጁን ዘርግቶ ተቀበላት ውሃም ከምድር እንደለቀቀ አወቀ ብሏል።
ሕጻናት እንደ የዋህ ርግብ ወላጆች እንደ ኖኅ ክረምት እንደ ማየ አይኅ በማድረግ ስጦታ ይሰጣሉ።
ሌላው ታሪክ ንግስተ ሳባ ለንጉሥ ሰሎሞን መቶ ሃያ መክሊተ ወርቅ እጅግም ብዙ ሽቱ የከበረ እንቈ ሰጠችው ይላል። (1ኛ ነገ 10፥10፣ 2ኛ ዜና 9፥9) ወርቅ እንቁ በፊቱ ስታቀርብለት “እንቋዕ እንቋዕ መጻእኪ ወለለ ዓመቱ ያምጽእኪ” (እንኳ እንኳ መጣሽ በየዓመቱ ያምጣሽ) ብሏት ነበርና የተከተሏት ወታደሮች በየዓመቱ እንቁጣጣሽ ይሏት ነበር።
ሁለተኛው ነጭ የወርቅ ፍልቃጭ የመሰለ ጥጥ ስለ አቀረበች እንቁ ጥጥ አመጣሽ ብሎ ነበር። ስለዚህ ነው። ሦስተኛም አበባ የመሰለ እንቁ ለጣትሽ ብሎ ነበርና በዚህ ተጠራ ይላሉ፡፡
አራተኛም በሉቃስ 1፥8 እንደ ተጻፈው ለዘካርያስ እጣ ደርሶለት ሲያገለግል መልአኩ ተገልጾለት የነገረውን ለኤልሳቤጥ ነግሯት ነበርና ስለዚህ “እንቁ እጣሽ” ተባለ።
ፍጻሜው ግን ለሔዋን ነው “እጸ በለስ መቁረጥሽ መብላትሽ ወደዚህ ዓለም መውረድሽ እንቁ ክርስቶስን ለማምጣት ነው ሲሉ እንቁጣጣሽ ተባለ ይላሉ። በግስ ዘይቤ ሲፈቱም ተንቆጠቆጠ፣ አንቆጠቆጠ በአረንጓዴ ቀጠል በነጭና በቀይ በቢጫ አደይ ወይም ጸደይ አበባ “ምድር ሆይ እግዚአብሔር አንቆጠቆጠሽ ወይም ዕንቡጥ አወጣሽ” በማለት ሊቃውንት ያብራራሉ።
ቅዱስ ዮሐንስ
ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የመሸጋገሪያው ዕለት ቅዱስ ዮሐንስ ርዕሰ ዓውደ ዓመት ተብሎ ይጠራል። የካህኑ የዘካርያስ ልጅ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ በዘመነ ሐዲስ መጀመሪያ ላይ ተነስቶ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት አስተማረ በየዓመቱ የዘመኑ መጀመሪያ ዕለት በእርሱ ስም ይጠራል።
በዚህ ዕለት ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ በአካባቢው ፀበል ወራጅ ወንዝ ይጠመቃሉ። ይኼውም ዮሐንስ “እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ክእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል” ማቴ. 3፥12 የሚለውን ለማስታወስ ነው። ሁለተኛ ጻድቁ ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከአርባ ዓመት ደዌ ስለተፈወሰ ህዝቡም ከአሮጌው ዘመን ወደ አዲሱ ሲሻገር ከእድፉና ከኃጢአት ነፅቶ ዓውደ ዓመቱን ለማክበር ይጠመቃል (ስንክሳር መስከረም 1)።
ዘመናቱ በወንጌላውያን መሰየማቸው
በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር እያንዳንዱ ዘመን በወንጌላውያን የተሰየመ የተጠራ ነው። የጌታችን የመድኃኒታችንን ቅዱስ ወንጌል የጻፉት አራት ወንጌላውያን ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ናቸው። ወንጌል ማለት የምሥራች ማለት ሲሆን በምድር ላይ ነግሦ የነበረው ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተወግዶ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ መደረጉ፣ የሰው ልጅ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገሩ፣ ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነፃ መውጣቱ የተነገረው በወንጌል ነው። ይህች ደገኛይቱ ሕግ የተባለችውን ወንጌልን አራቱ ወንጌላውያን በተለየ ቦታ በተለያየ ጊዜ ሆነው ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው በምሥጢር ሳይለያዩ ጽፈው ለእኛ አበርክተዋል። ለዚህ ውለታቸው የቀደሙት ቅዱሳን አባቶቻችን ዘመናት በስማቸው እንዲሰየሙ ደንግገዋል።
የዘመኑን ወንጌላዊ ለማወቅ 5500 ዓመተ ዓለምና ዓመተ ምሕረቱን ደምረን ለአራት ስናካፍል ቀሪው 1 ከሆነ ማቴዎስ፣ 2 ከሆነ ማርቆስ፣ 3 ከሆነ ሉቃስ፣ አልቦ (ዜሮ) ከሆነ ዮሐንስ ነው።
ከላይ እንደተመለከትነው አዲስ ዘመን የሚጀምረው መስከረም አንድ ቀን ሆኖ ይኸው በባሕረ ሐሳብ ዕለተ ቀመር ይባላል፤ ኢትዮጵያውያን ቁጥር የምንጀምርበት ስለሆነ ዕለተ ቀመር ተብሏል። ይህ ወቅት በደመና የተሸፈነው ምድር በጊሕ የሚተካበት፣ ብርሃን የሚፈነጥቅበት፣ ምድር አረንጓዴ ለብሳ ልምላሜዋ የሚታይበት የአትክልቱ መዓዛ የሚያውድበት ወቅት ነው።
በዚህም የተነሳ የሰው አእምሮ ይታደሳል ይለወጣል። በአዲስ መንፈስም ለሥራ የሚነሣሣበት ወቅት ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ በ1ኛ ጴጥ. 4፥3 ላይ “ያለፈው ዘመን ይበቃችኋል” የሚል ኃይለ ቃል አስቀምጧል። ከዚህ ኃይለ ቃል በርካታ ነገሮችን የምንማርበት ነው። አዲስ ዘመን ሲመጣ በዓል አክብሮ፣ ዘመኑን ቆጥሮ ማለፍ ብቻ ሳይሆን ካለፈው ዘመን የምንማራቸው ነገሮችን ለይተን ማስቀመጥና ጥሩ ሠርተን ያለፍነውን ማጠንከር፣ ያጐደልነውንና የደከምንበትን ጉዳይ ደግሞ የምናሻሽልበት የምንለውጥበትን መንገድ መቀየስ ይገባል። በተለይም በአዲስ ዘመን “ለዘኃለፈ ሥርየት ወለዘይመጽእ ዕቅበት” (ያለፈውን ይቅር በለን፤ በሚመጣው ይጠብቀን”) የምንልበት ሊሆን ይገባል። ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳስተማረው “የአሕዛብን ፈቃድ የፈጸማችሁበት ማለትም ዝሙትንና ምኞትን፣ ስካርንና ወድቆ ማደርን፣ ያለልክ መጠጣትንና ጣዖት ማምለክን ያደረጋችሁበት ዘመን ይበቃችኋል።” ባለው መሠረት ራሳችንን ለኃጢአት ያስገዛንበት ዘመን ከሆነ ለገቢረ ጽድቅ፤ በአምልኮተ ጣዖት የተያዝንበት ከሆነ ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር የምንመጣበትን፤ ነፍሳችንንም ሆነ ሥጋችንን አንጽተን ራሳችንን የምንለውጥበት ሊሆን ይገባል። አለበለዚያ ዘመኑ በላያችን ላይ እየተፈራረቀብን እየተቀየረ እኛ ግን በዚያ ቆመን በጠባይና ግብራችን የማንለውጥ ከሆነ ከንቱ ነው። እግዚአብሔር ይህን ዕድሜ የሰጠን ለንስሐ ነውና ዘመኑ ሲለወጥ እኛም አብረን በንስሐ እየታጠብን በሐሳብ እየጐለመስን ልንለወጥ ይገባል።
እንግዲህ የክረምቱ ደመና ተወግዶ፣ ጨለማው ተገፎ በምትኩ ጎሕ የሚቀድበት፤ ብርሃን የሚፈነጥቅበት እንደሆነ እም በአሮጌው ዘመን በሕይወታችን ውስጥ ተጋርዶ የቆየውን ጨለማ አስወግደን ብሩሕ ተስፋ የምንሰንቅበት፣ አዲስ ዕቅድ አቅደን፣ የጐደለንን መሙላትና ድካማችንን በብርታት ማረም ይገባናል። ከዘመኑ ጋር አስተሳሰባችንን አመለካከታችንን ጭምር አብሮ መለወጥ አለበት።
አዲሱ ዘመን የሰላም፣ የብልፅግና፣ አዳዲስ ነገሮችን አቅደን እነዚህንም በመፈጸም ራሳችንን፣ ቤተክርስቲያናችንንና ሀገራችንን የምናሳድግበት የምንለውጥበት እንዲሆንልን የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎትና በረከት አይለየን።
ምንጭ፡ መዝሙረ ማኅሌት ወቅዳሴ በመምህር አፈወርቅ ተክሌ (የቅኔ መምህር) 2004 ዓ.ም የ2004ዓ.ም የመስቀል ደመራን በዓል አስመልክቶ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የተዘጋጀ ልዩ ዕትም መጽሔት
http://www.sturaelmb.org/bereket.html