Saturday, 21 November 2015

 “የኢየሱስ ክብሩ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነው”
እርግጥም እንዲሁ ነው ፡ በእውኑ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሄር ነው ብላ በእግዚአብሄርነቱ ኢየሱስን የምታከብር ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን  የበለጠች ቤተክርስቲያን ማን ነች? ካቶሊክ ወይንስ ፕሮቴስታንት? ካቶሊክ አንዱን ጌታ ትከፍለዋለች ፡ ፕሮቴስታንት ደግሞ ሃያሉን አምላክ ታሳንሰዋለች ፤ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ግን ያህዌውን ኢየሱስን እናመልካለን፡፡
ነገር ግን ይገርመኛል ፤ ለኦሪታውያን ጠላታቸውን እንዲጠሉ ፡ ወዳጆቻቸውን ደግሞ እንዲወዱ ተፃፈላቸው ፤ ለክርስቲያኖች ግን ወዳጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን ጠላቶቻቸውንም እንዲወዱ ታዘዙ ፡ እንዲህም ነውና ኦርቶዶክሳውያን ይህን ሊፈፅሙ ይተጋሉ፡፡
ፕሮቴስታንቶችና ተረፈ ጴንጤ የሆኑ ተሃድሷውያን ግን ክርስቲያኖች ነን ይላሉ ወዳጆቻቸውን ግን ይጠላሉ ፡ ወዳጆቻቸውም የተባሉ ስለክርስቶስ መከራን የተቀበሉ ፡ አንዲቷን እምነት ያስተላለፉ ፡ በምልጃ የሚበረቱ ቅዱሳን ናቸው፡፡ ከቅዱሳንስ በላይ ለክርስቲያኖች ባልንጀራ ማን ሊሆን ነው? ፕሮቴስታንቶች ግን እኒህን የክርስቲያን ወዳጆች ጠልተዋል ፡ በዚህም አንድም ከክርስትና ርቀዋል ፡ ከኦሪታውያንም አንሰዋል (ኦሪት ወዳጅህን ውደድ ትላለችና)፡፡
መቼ ጠላን ይሉኝ ይሆናል ፡ ነገር ግን ስለነሱ በተወራ ጊዜ ሁሉ ከንቱ ቃል ያስቀድማሉ ፡ የንቀት ፌዝን ያሰማሉ ፡ ከክብራቸው ይልቅ ድካማቸውን በማጉላት ይጠመዳሉ ፡ ነገር ግን ክርስቶስ ያፀደቃቸውን ማን ይከሳቸዋል? እኒህ ግን እግዚአብሄር ያከበራቸው እንደዲያቢሎስ ሊከሱ ይሞክራሉ፡፡
ስለቅዱሳን ባላቸውም ጥላቻ ስለኢየሱስ አብዝተው ሲያወሩ እናያቸዋለን ፡ የኢየሱስን ስም መጥራት ህይወት ይመስላቸዋልና ይስታሉ ፡ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” የሚሉ ጌታ ኢየሱስን ግን ያላወቁ እኒህ ናቸው ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሲሆን ፍቅርን ግን አጥተው ይመላለሳሉና ፡ ስለፍቅራቸው ማነስም በክርስቶስ ከተመሰረተች ክርስትና ርቀው ከኦሪታውያንም አንሰው ይታያሉ፡፡
ስለሆነም ስለቅዱሳን በጎ መናገርን አይወዱም ፡ አንድም ስለቅዱሳን የሚናገር ሰው ሲመለከቱ ይቆጣሉ ፡ ራሳቸውን ቅዱሳን ስለማለት ግን አያፍሩም ፡ የቅዱሳንን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስንም ይጠራሉ ፡ ክርስቶስ ያከበራቸውን ደግሞ ይንቃሉ ፡ አለማውያን ማለት እኒህ ናቸው፡፡ ራሳቸውን ለማፅደቅ አንደኞች ቅዱሳንንም ለማሳነስ ፈጣኖች አለማውያን ማለት እኒህ ናቸው፡፡ ከፍቅር የተለዩ ፍቅር ክርስቶስን ግን የሚጠሩ እኒህ ናቸው፡፡ ኢየሱስ ኢየሱስ የሚልይ ኢየሱስን ግን ከአብ አሳንሰው በሁለት የሚበላለጡ አማልክት የሚያመልኩ እኒህ ናቸው፡፡
ከእነዚህ አለማውያን ተለዩ ፡ ከእነዚህ ፍቅር የራቃቸው ተለዩ ፡ ከእነዚህ አላዋቂወች ተለዩ ፡ የኢየሱስ ክብሩ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ነውና ፡ ኢየሱስን የምትወዱ ክብሩን ከሚይሰፉ ጋር ተባበሩ፡፡