Thursday, 31 March 2016
‹ሀገር ማለት ሰው ነው›፤ እስኪ ሙት በለኝ!
‹ሀገር ማለት ሰው ነው›፤ እስኪ ሙት በለኝ!
D/n ዳንኤል ክብረት
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገርሙኝ ዘፈኖች አንዱ ‹ሀገር ማለት ሰው ነው› የሚለው ነው፡፡ እሥራኤላዊና ጂፕሲ ይህንን ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን? እላለሁ፡፡ አይሁድ በመላው ዓለም ለ1900 ዓመታት ያህል ተበታትነው ሲኖሩ በየአካባቢው ሰው ነበራቸው፤ያውም እንደ ብረት የጠነከረ ማኅበረሰብ፤ ሀገር ግን አልነበራቸውም፡፡ ሀገር ማለት ሰው ከሆነ አይሁድ ሀገር ፍለጋ ከሺ ዓመታት በላይ መኳተን አልነበረባቸውም፡፡ በአውሮፓ የሚኖሩት ጂፕሲዎች የታወቀ ማኅበረሰብ አላቸው፡፡ ነገር ግን ሀገር የላቸውም፡፡ ሀገር ማለት ሰው ቢሆን ኖሮ ጂፕሲ የሚባል ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ጂፕሲ የሚባል ሀገርም ይኖር ነበር፡፡ ግን የለም፡፡
በአሜሪካ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ‹በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን› የምትባል ሀገር ግን የለቺም፡፡ 1.3 ሚሊዮን የሚደረሱ ግሪኮች በአሜሪካ ይኖራሉ፡፡ ‹የአሜሪካ ግሪኮች› የምትባል ሀገር ግን የለችም፡፡ ‹ግሪክ ሲሠራ አሜሪካ ይኖራል፣ ሲያረጅ ግሪክ ይጦራል› የተባለው ሀገር ሰው ብቻ ስላልሆነ ነው፡፡
ሰዎች ተሰብስበው ሀገር ሊመሠርቱ አይችሉም፡፡ በየሀገሩ የተሰበሰቡ ማኅበረሰቦች ‹ኮሙኒቲ› ይባላሉ እንጂ ሀገር አይባሉም፡፡ ሀገር ሀገር ለመሆንና ለመባል ከሰው በተጨማሪ የምትፈልገው ብዙ ነገር አላትና፡፡ ሀገርን ሀገር ለማስባል መሬትም ያስፈልጋል፤ መሬት ሳይኖርህ ሰው ስለሰበሰብክ ብቻ ሀገር ልትሆን አትችልም፡፡ ያውም የእኔ የምትለው፣ የምትሞትለትና የምትለፋለት ታሪካዊ መሬት ያስፈልግሃል፡፡ አይሁድ በ1930 አካባቢ በኡጋንዳ ኡዋሲን ጊሹ (Uasin Gishu County) በተባለ ቦታ እንዲሠፍሩና ሀገር እንዲኖራቸው ታስቦ ነበር፡፡ እንደ ቴዎዶር ኸርዝል ያሉ ታላላቅ የጽዮናዊነት መሪዎችም ለጊዜውም ቢሆን ተስማምተውበት ነበር፡፡ ብዙኀኑ አይሁድ ግን ‹ሀገር ማለት የሆነ መሬት አይደለም፡፡ ታሪካዊ መሬት ነው› ብለው ተቃወሙት፤ሀገር ማለት የሆነ መሬት ብቻ ቢሆን ለአይሁድ ከዛሬዋ እሥራኤል ይልቅ በአየር ንብረትና በተፈጥሮ ማዕድን፣ ብሎም በአቀማመጥ ኡጋንዳ ትሻላቸው ነበር፡፡
ባድሜ ለምትባል ከጦርነቱ በፊት ብዙው ሕዝብ ሰምቷት ለማያውቅ መሬት የተደረገውን ጦርነት የረሳ ሰው ነው ‹ሀገር ማለት ሰው ነው› የሚል፡፡ ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ለባድሜ የተደረገው ጦርነት ለማን የተደረገ ነው ሊባል ነው፡፡ በሄግ ፍርድ ቤት የነበረው ክርክርስ የመሬት ክርክር እንጂ የሰው ክርክር ነበር እንዴ?
ሀገር ማለት ሰው ቢሆን ኖሮ ሰው ስለ ሀገሩ ሲያነሣ ወንዙን፣ ተራራውን፣ ሸለቆውን፣ ሜዳውን፣ ጫካውን እያነሣ ለምን ይዘፍን ነበር ፡፡
‹ያገሬ ተራራ ወንዛ ወንዙ ለምለም
እማማ ኢትዮጵያ ኑሪ ለዘላለም› ለምን ይል ነበረ፡፡
ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ይሄ የኔ ክልል፣ ጎጥና መንደር ነው የሚለው ክርክር ከየት ይመጣ ነበር? ሀገር ማለት ሰው ከሆነ የተለየና የታወቀ የሀገር ድንበርና ካርታ ለምን ያስፈልግ ነበረ? ሰውማ የትም ነው የሚኖረው፡፡ ካርታ አያሻውም፡፡ ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ለምን የአብዛኞቹ ሀገሮች ብሔራዊ መዝሙር ስለ መሬቱና ስለ ድንበሩ ያወራል? ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ለሰው ፓስፖርትና ቪዛ ለምን ያስፈልገዋል? ሰው ያለበት ቦታ ሁሉ ሀገሬ ስለሆነ ለምን እንደፈለግኩ ወጥቼ አልገባም? አንድ ሰው ወደ አንድ ሀገር ገባ የሚባለው ወደ መሬቱ ሲገባ እንጂ የሀገሩን ሰው ሲያገኝ ነው እንዴ? ምናልባትም ከአንታርክቲካ በቀር ቪዛ መጠየቅ ያለበት ሀገር አልነበረም፡፡ እርሱ ሰው የለበትምና ‹ሀገር ማለት ሰው ነው› የሚለው አይመለከተውም፡፡ ሀገር ማለት ሰው ከሆነ በሰማይ የሚሄድ አውሮፕላን ‹የአየር ክልሌን ጣሰ› ብሎ መሟገት ምን የሚሉት ሞኝነት ነው? ሰውን አልጣሰ፣ የጣሰው አየር ነው፡፡
ደግሞም አገር ማለት መሬት ብቻ አይደለም፡፡ ያማ ቢሆን ኖሮ አንታርክቲካ ሀገር ይሆን ነበር፡፡ ያማ ቢሆን ኖሮ በዓለም ላይ የሚገኙ ወደ ሃምሳ የሚጠጉ ሰው አልባ ደሴቶች(nonecumene)‹ሀገር› ተብለው በተባበሩት መንግሥታት ይመዘገቡ ነበር፡፡ ሀገር ማለት መሬት ቢሆን ኖሮ መሬት ያለው ሁሉ ሀገር ይኖረው ነበር፡፡ የአሜሪካ ሕንዶች፣ የአውስትራልያ አቦርጅኖች፣ ከጥንት ጀምሮ የሚኖሩበት መሬት አላቸው፡፡ የራሳቸው የሆነ ሀገር ግን የላቸውም፡፡ ደቡብ ሱዳናውያን የራሳቸው የሆነ የሚኖሩበት መሬት ነበራቸው፤ ሀገር ለመሆን ግን መዋጋት ነበረባቸው፡፡ ደቡብ ሱዳኖችን ያን ሁሉ ዘመን ያዋጋቸው የመሬት ጥያቄ ሳይሆን የሀገርነት ጥያቄ ነው፡፡ የራሳቸውን ፖለቲካዊ መሬት አግኝተው እንኳን ሀገር ለመሆን ገና እየተሠሩ ነው፡፡ ፍልስጤማውያን ይብዛም ይነስ የሚኖሩበት መሬት አላቸው፡፡ አገር ግን የላቸውም፡፡
አገር ከዚህ ሁሉ በላይ ነው፡፡ ሰው፣ ሰው የኖረበትና ታሪክ የሠራበት መሬት፣ ማኅበረሰብ ከማኅበረሰብ፣ ሰው ከሰው፣ ሰው ከማኅበረሰብ፣ ሰው ከመሬት፣ ሰው ከአራዊት፣ ሰው ከተፈጥሮ፣ ሰው ከወራሪ ጋር የነበረው ትግል፣ ውጊያና ወዳጅነት፤ የተረተው ተረት፣ ያወጋው ወግ፣ የፈጠረው አፈ ታሪክ፣ ያከማቸው ትዝታ፣ ሰው ለመሬቱ፣ ለወገኑና ለእምነቱ የከፈለው መሥዋዕትነት፤ የዘፈነው ዘፈን፣ ያቅራራው ቀረርቶ፣ የፎከረው ፉከራ፤ ያገኘው ድልና የተሸከመው ሽንፈት፤ ያደረሰው በደልና የደረሰበት በደል ይሄ ሁሉ ነው ሀገር፡፡
መገለጫው ቅርስ፣ መዋሐጃው ባህል፣ መታያው ልብስና መዋቢያው ጌጣጌጥ፣ መገናኛው ቋንቋ፣ መዝናኛው ጭፈራ፤ ማስተማሪያው ተረት፣ መክበሪያው ዓመት ባል፣ መጠበቢያው ምግብ፣ መቆዘሚያው እንጉርጉሮ፣ መተከዣው ልቅሶ፣ መተኪያው ልደት፣ ማሳረጊያው ቀብር፤ መገምገሚያው ምግባር፣ ማነወሪያው ነውር፤ መኩሪያ ጀግንነቱ፣ ማፈሪያ ገመናው፤ መደበቂያ ቤቱ፣ መመረሪያ ጫካው፤ ይሄ ሁሉ ነው ሀገር፡፡ ታሽቶ ተገርኝቶ ያመጣው አንድነት፣ ተጣልቶ ተባልቶ ያመጣው ልዩነት፣ እንደ ዘሐ ዘጊ የተጠላለፈው፣ እንደ እግር ሠንሠለት የተቆላለፈው፣ ሲፈተል፣ ሲገመድ፤ ሲባዘት፣ ሲዳውር፤ ሲከካ፣ ሲሰለቅ፤ ሲጣላ፣ ሲታረቅ፤ ሲያውቅና ሲማይም፤ ሲሠለጥንና ሲደኸይ፤ ሲሰፋና ሲጠብ፤ የኖረውና የኖረበት፣ የኖረለትም ነው ሀገር፡፡
ሀገር ትዝታ ነው፡፡ የትም ቦታ ስትሄድ ጠምዶ የሚያመጣህ፡፡ ምንም ሥጋ ብትቆርጥ ከብቱ ትዝ ይልሃል፤ ምንም ቢች ዳር ብትዝናና ወንዙ ትዝ ይልሃል፤ ምን በሽቱ ብትታጠን አፈሩ ይሸትሃል፤ ምን በሥጋጃ ላይ ብትሄድ ጉዝጓዙ ይመጣብሃል፡፡ በኮምፒውተር እየሠራህ ያቦካኸው ጭቃ ይናፍቅሃል፤ በጄት እየበረርክ አህያና በቅሎው ያምርሃል፤ ማንሐተን ተቀምጠህ ሰባተኛ፣ ሎንደን ተቀምጠህ ቂርቆስ፣ ኖርዌይ ሆነህ ጅግጅጋ፣ ካናዳ ሆነህ ሐረር ይወዘውዝሃል፡፡ ሀገር ማለት ትዝታ ነው፡፡
ሀገር ማለት ከምትገልጠው ብታስበው፣ ከምትኖርበት ብትሞትበት፤ ከምትስቅለት ብታለቅስለት የምትመርጥለት ነገር ነው፤ ሀገር ማለት ትተህው ብትሄድ ትቶህ የማይሄድ፣ በራቅከው ቁጥር ልብህ ውስጥ የሚቀር፣ ባወቅከው ቁጥር የምትንገበገብለት፤ በተረዳኸው ቁጥር የምትሳሳለት፣ አንተን እርሱ ውስጥ እንደምታገኘው ሁሉ እርሱንም አንተ ውስጥ የምታገኘው፤ የተሠራህበት ውሑድ፤ የተቀረጽክበት ማንነት ነው ሀገር፡፡
ሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ዘመድ የሌለው ሰው ወደ ሀገሩ ለመምጣት ባልናፈቀ ነበር፡፡ ሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ዘመዶቹ ሁሉ ከእርሱ ጋር ውጭ የሚኖሩለት ሰው ‹ሀገሬን ሀገሬን› እያለ መከራ ባላየ ነበር፡፡ ሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ሰዎች በየዘመናቱ የበደሉት ሰው ሀገሬ በደለችኝ ባለ ነበር፡፡ ሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ሰው ስለ ሀገሩ ሲያስብ ተራራውና ወንዙ፣ አዕዋፉና አራዊቱ፣ ማሳውና ቀየው ለምን ትዝ ይለው ነበር፡፡ በሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ያሸነፈ አትሌት፣ ድል ያደረገ ኳስ ተጨዋች ባንዴራው ሲሰቀል ለምን ያለቅስ ነበር?
‹አዙረሀ አዙረህ ሀገሬ መልሰኝ
በሹም ታዘዘ አፈር አታልብሰኝ› ብሎ ለምን ያንጎራጉር ነበር፡፡ ዐጽሙ በአፈሩ እንዲያርፍ ለምን ይናዘዝ ነበር፡፡ ለምን ሙሾውን፣ የሠርግ ዘፈኑን፣ ወጉን ማዕረጉን ይፈልገው ነበር፡፡
ሀገር በአርምሞ እንጂ በንግግር፣ በተግባር እንጂ በዝርዝር ሊናገሩለት የማይቻል ነገር ነው፡፡ ውጥንቅጥ ሰበዞች የሰፉት ሞሰብ፣ዓይነተ ብዙ ድርና ማጎች የሸመኑት ጋቢ፣ ልዩ ልዩ ቅመሞች የሠሩት ወጥ፣ ብዙ ገባሮች የፈጠሩት ዓባይ፣ ብዙ ትውልዶች የከመሩት ተራራ፣ ከአራቱ አቅጣጫ ተሰብስቦ በአንድ ወፍጮ የተፈጨ እህል፣ ከየአበባው ተቀስሞ በአንድ ቀፎ የተሠራ ማር፣ ከየእህሉ ወጥቶ በአንድ ማድጋ የተጠመቀ ጠላ፣ ከየ እንጨቱ ተለቅሞ በአንድ ጽንሐ የታጠነ ዕጣን ነው ሀገር፡፡
ሀገር ማለት ሰው ነው? እስኪ ሙት በለኝ
Wednesday, 30 March 2016
መጻጒዕ (ዮሐ. ፭፥፲፫)
መጻጒዕ (ዮሐ. ፭፥፲፫) |
በዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ
መጋቢት 18 ቀን 2008 ዓ.ም
የነፍሳችንን ማሠሪያ እንዲፈታና ዓለሙን ከተያዘበት የኃጢአት በሽታ እንዲያድን ለቤዛነት፤ እንዲሁም የመልካምና የበጎ ምግባራት ሁሉ አብነት ሆኖ በሥራና በቃል እንዲያስተምር ወዳለንባት ምድር በሥጋ ቅድስት ድንግል ማርያም ወረደ ተወለደ:: ቤተክርስቲያናችን በአራተኛው የዓቢይ ጾም ሳምንት እግዚአ ለሰንበት ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ"ቤተሳይዳ" የፈጸመውን ተአምራት መጻጒዕ ብላ ሰይማ ታስበዋለች። በዕለቱም በዮሐንስ ወንጌል አምስተኛው ምዕራፍ የተቀመጠው ታሪክ በልዩ ልዩ ኅብረ ምሥጢር ተገናዝቦ በሊቃውንቱ ይነገራል።
መጻጒዕ ለ፴፰ ዓመት በአልጋው ላይ ሆኖ ምሕረትን ሲጠባበቅባት የኖረባት ስፍራን "ቤተ ሳይዳ"ትባላለች።በቅዱስ መጽሐፍ የሥፍራዎችን ስያሜ ስንመረምር በይሁዳና በገሊላ ለሚገኙ ሁለት የተለያዩ ግዛቶች በተመሳሳይ አገባብ "ቤተ ሳይዳ" የሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸው እናገኛለን:: በሁለቱ አውራጃዎች (ይሁዳና ገሊላ) ሥር "ቤተ ሳይዳ" በሚል የተጠቀሱት ሥፍራዎች በትርጉም ፊደላቱ ያለአገባብ መሰደር ከወለዱት የሞክሼነት ስህተት (Metathetical Corruption) የተገኘ ክፍተት እንጂ ቦታዎቹስ በጥንታዊቷ የእስራኤል ግዛት ከመገኘታቸው ውጪ ምንም የሚያገናኛቸው መልክአ ምድራዊ ኩነት የለም "ጲላጦስ ጰንጤናዊ መልአከ ይሁዳ ወሄሮድስ ንጉሠ ገሊላ" (ሉቃ· ፫፥፩) እንዲል የግዛቶቹ አገረ ገዢዎችም እንዲሁ ለየቅል ነበሩ:: አገባቡን አካቶ ለመረዳት እንዲያመች የሁለቱንም መካናት ከተማና መንደር ለይቶ ማወቁ ተገቢ ነው::
፠ በይሁዳ ግዛት ከሚገኙና እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ገቢረ ተአምራቱን ከፈጸመባቸው ሥፍራዎች ፦ ቤተሳይዳ(Bethesda) ፣ ቢታኒያ ፣ ቤተልሔም ፣ ቤተፋጌ ፣ ኢያሪኮ ፣ ጌቴሰማኒ ፣ ሊቶስጥሮስ(ገቦታ) ፣ ኤማሁስ፣ ቀራንዮ(ጎልጎታ) ፣ ኢየሩሳሌም እና የደብረዘይት ተራራ የሚጠቀሱ ሲሆን፤
፠ በገሊላ አውራጃ ደግሞ ፦ ቤተሳይዳ(Bethsaida) ፣ ሄኖን ፣ ቃና፣ ቅፍርናሆም፣ ኮራዚ፣ ጌንሳሬጥ፣ ደብረታቦር፣ ናይን እና የገሊላ ባህር ተገልጸው እናገኛልን::
እነዚህኑ "ቤተ ሳይዳ" ዘይሁዳና "ቤተ ሳይዳ" ዘገሊላ አካባቢያዊ መገኛ ለይተው የሚያመለክቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማጣቀሻዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም በይሁዳ ኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ ያለችዋን "ወቦ ውስተ ኢየሩሳሌም ምጥማቃት ዘጵሩጳጥቄ ቅልንብትራ (ዘውእቱ ቀላየ አባግዕ ብሂል) ወይቤልዋ ስማ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ወባቲ ኃምስቱ ሕዋራት" (ዮሐ ·፭፥፪) ብሎ የገለጠበትንና በገሊላ ስለምትገኘዋ ደግሞ "ወሖሩ እሙንቱሂ ኀበ ፊልጶስ ዘቤተ ሳይዳ ዘገሊላ" (ዮሐ ፲፪፥፳፩) የሚለው ማየት ይቻላል::
በሌላ መልኩ አንዳንዶች ደግሞ በሁለቱም ሥፍራዎች ክርስቶስ አምላካችን ለፈውስ ሥራ ያገኛቸውን ሰዎች አይተው ተመሳሳይ ቦታ ሲመስላቸው ይታያል ይህም "መጻጉዕ" እና "ዕውር" የነበሩትን ማዳኑ ነው:: ይኸውም "ወቦ ውስተ ኢየሩሳሌም ምጥማቃት ዘጵሩጳጥቄ ቅልንብትራ (ዘውእቱ ቀላየ አባግዕ) ብሂል ወይቤልዋ ስማ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ወባቲ ኃምስቱ ሕዋራት …በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። (ዮሐ ·፭፥፪) የተባለውና "ወበጽሑ ቤተ ሳይዳ ወአምጽኡ ኀቤሁ ዕውረ ወአስተብቁዕዎ ይግስሶ … ወደ ቤተ ሳይዳም መጡ። ዕውርም አመጡለት፥ እንዲዳስሰውም ለመኑት።" (ማር· ፰፥፳፪) የሚለው ነው::
፨ "ቤተ ሳይዳ" ዘገሊላ (Bethsaida) በትርጉም "የማጥመጃ ቤት" የሚል ፍቺ ያለው በተለይ ከቅዱሳን ሐዋርያቱ አሳ አጥማጆቹ ወንድማማቾችና ቅዱስ ፊልጶስ የነበሩባት መንደር ናት " ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ።" (ዮሐ·፩፡፵፭) እንዲል።
፨ "ቤተ ሳይዳ" ዘይሁዳ (Bethesda or Bethchasday) የመጠመቂያ ሥፍራ ስትሆን በግሪኩ ቤተ ዛታ ( Βηθζαθά) ወይም ቅልንብትራ (κολυμβήθρα) እንዲሁም በእብራይስጡና በአረማይኩ "ቤተ`ስዳ" (Beth hesda ( בית חסד /חסדא )) በማለት "ከማጥመጃ ቤት" ለይቶ "ቤተ ሣሕል / የምሕረት ቤት" የሚል ትርጉም ያለው መጠመቂያና መላለሻ መንገድ መሆንዋን ያመለክተናል። የግእዙ መጽሐፍ ቅዱሳችንም የቦታውን ስያሜ ከእብራይስጡ "የአንድዮሽ ትርጉም" ስያሜ (ቤተ ሳይዳ) ጋር በግሪኩ ያለውንም መጠሪያ ጭምር አካቶ ቅልንብትራ ( κολυμβήθρα / kolumbethra) ሲል እናገኘዋለን::
ቤተ ሳይዳ ዘይሁዳ ባለ አምስት በር መመላለሻ አምስት ዓይነት ድውያን ፈውስን ከማየ ጥምቀቱ ሲጠባበቁ የሚኖሩባት በአምስተኛው የዮሐንስ ወንጌል ተጽፋ ያለች የጌታችን ማዳን የተገለጠባት ሥፍራ ናት። "እስመ ኦሪት መንፈቀ ፍጻሜ ወኅዳጠ መክፈልት" እንዲላት መልአከ እግዚአብሔር ለቀድሶተ ማይ ወርዶ ውኃውን ሲያናውጥ ቀድሞ የገባ የሚነጻባት በዕለቱ ከአንድ በቀር ለሌላው ፈውስ የማይደገምባት ቦታ ናት ።
ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል የድኅነት ተስፈኛ ሆኖ የኖረ መጻጉዕን በአልጋው ተኝቶ ሳለ ደዌው እንደጠናበት ፈውስ እንደዘገየበት አይቶ "መፈውስ ወማሕየዊ" ጌታችን ቀርቦ አዎን እንዲለው እያወቀ ያንን በሽተኛ "ትፈቅድኑ ትሕየው? … ባድንህ ፈቃድህ ነውን?" አለው። ብወዳችሁ አላዋቂ የሆነ የእናንተን ሥጋ ተዋሕጄ መጣሁላችሁ ሲለን ("አኮ ኢያእሚሮ ኅቡአተ አላ ከመ የሀብ መካነ ለጥንተ ትስብዕቱ ዘኢየአምር ኅቡአተ") እንዲል:: የሚገርመው ቅዱስ ጳውሎስ በእብራውያን መልእክቱ ምዕራፍ ፬ ቁጥር ፲፪ ላይ "የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።" ብሎ የመሰከረለት ጌታችን ፈውስን በመጠባበቅ ከመዳን ውጪ ሌላ ዓላማ ያልነበረውን ይህን ሰው ዓይቶ ፈቃዱን እያወቀ ግን ፍቀድልኝና ላድንህ አለው። " ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው? "(መክ ፮፥፲፪) እንዲል የሚያስፈልገንን ሳንነግረው የሚያውቅ የሚሰጠንም ከእርሱ ከፈጣሪው ውጪ በእውነት ማን አለ? መጻጒዕ ግን ኋላ የሚክድ ነውና "በሰንበት ላይ ያመጸ ፣ ራሱን ከአብ የሚያስተካክል ፣ ቤተመቅደሱን አፍርሱት ያለ መች አድነኝ ብየው ሳልፈቅድለት ያዳነኝና አልጋ ያሸከመኝ ነውኮ" ብሎ በዕለተ ዓርብ የሚከስበትን ሲያሳጣውና ለኋላ ጥፋቱ የገዛ ኅሊናው እንዲቀጣው ፈቃዱን ጠየቀው። "አልብየ ሰብእ" ሰው የሌለኝ ሆኖ እንጂ ያንንማ ማን ይጠላል በሚል ጉጉቱን ከወዳጅ አልባነቱ ጋር ድኅነትን ፈቅዶ ገለጠ። እስከ ሁከተ ማይ ሳያቆየው "ተንሥእ ንሣእ ዓራተከ ወሑር … ተንስና አልጋህን አንስተህ ሂድ" አለው ወዲያው አፈፍ ብሎ በፍጥነት ያን ሁሉ ዘመን የተሸከመች ጠንካራ አልጋ ተሸክሟት ሄደ።
ይህች "ቤተ ሳይዳ" ዘይሁዳ ምሣሌቷ ብዙ ኅብር ያለው ነው። ለአብነትም ያህል ምሳሌ፦
፩·ውኃው የቤተ አይሁድ ምሳሌ አምስት መመላለሻ የሕግጋተ ኦሪት የአምስቱ መፃሕፍተ ሙሴ በነዚያ ታጥረው ለመኖራቸው። ቀድሞ የገባባት አንዱ እንዲድን እነሱም አንድነት ቤተ እስራኤል ተሰኝተው ለመኖራቸው ምሳሌ ነው።
፪·በሌላ አገባብ
፠ በዚያ ውኀውን ለማወክ የወረደው መልአክ = ቀሳውስት(ካህናት) "ለቀድሶተ ማየ ጥምቀት" የመውረዳቸው ምሳሌ ነው።
፠ የመጠመቂያ ውኀው = የማየ ጥምቀት ምሳሌ ሲሆን
፠ በቤተ ሳይዳ ያለው አምስቱ እርከን(መመላለሻ) =የአምስቱ አእማደ ምስጢር በዚያ ሊያምኑ ያሉ ተስፈኞችና ያመኑባትም ልጅነትን ያገኙባታልና።
፠ አምስቱ ዓይነት ድውያንም የአምስቱ ጾታ ምዕመናን ከነ ፈተናቸው የተመሳጠረበት ምሳሌ ነው (አእሩግ=በፍቅረ ነዋይ፣ ወራዙት=በዝሙት፣ አንስት=በትውዝፍት በምንዝር ጌጥ፣ ካህናት=በትእቢት አእምሯችን ረቂቅ መዓረጋችን ምጡቅ እያሉ፣ መነኮሳት=በስስት ምግብን በፈለጉት ጊዜ ባያገኙት ይልቁንም አጽንኦ በአት እየፈቱ በአንሰሐስሖ ዘበከንቱ ይፈትናቸዋል) ምሳሌ ሆኖ ይነገራል።
፫·ለአዲስ ኪዳን ድኅነተ ነፍስ ምስጢራዊ ምሳሌ አገባብም አለው፤
፠ ቤተሳይዳ የበጎች በር በመባልዋ እና በኦሪቱ በጎች ወደ ቤተ መቅደስ ወጥተው ለመስዋዕት ከመቅረባቸው አስቀድሞ የሚታጠቡበት ውኀ ያለበት በመሆኑ ለአዲስ ኪዳንም የመንፈስ ቅዱስ ልጅነት የሚገኝባትን ወደ አማናዊ መስዋዕት ቅዱስ ቁርባን የምታደርስ የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ
፠ አምስቱን መመላለሻ የምታደርስ ደግሞ ወደ ፍፃሜ ሕግ ፍቅረ ቢጽና ፍቅረ እግዚአብሔር አልፎም ፍጽምት ወደሆነች ወደ ሕግጋተ ወንጌልም የምታደርስ የአምስቱ ብኄረ ኦሪት መፃሕፍተ ሙሴ ምሳሌ ያደርጋቸዋል።
፠ ለሁከተ ማይ የወረደው መልአክ የመድኃኒታችን የክርስቶስ ምሳሌ ነው
፠ ከአንድ ብቻ በቀር ሕሙም በአንድ ዕለት አለመዳኑ በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን ጥላ ሥር አምነው ያሉ ምዕመናንና ምዕመናት ብቻ ድኅነተ ነፍስ እንዳላቸው ያሳያል።
፠ የውኀው መናወጽ የሰቃልያነ ክርስቶስ "ሁከተ አይሁድ" ምሳሌ ጥንቱን "ስቅሎ ስቅሎ " የሚለው ያ ቁጣ የዕለተ ዓርብ መድኃኒት መገኛ ነውና።
እስኪ ደግሞ በማጠቃለያው ወደ መጻጒዕ ታሪክ እንመለስና ጥቂት ፍሬ ነገር ለሕይወታችን እንስማ።
ቀድሞ በ`ቤተ ሳይዳ` እያለ የነበረበትን ያንን ሁሉ ጭንቅ ኋላ በሊቶስጥሮስ የፍርድ ገቦታ ቆሞ በረሳ ጊዜ " ታዲያ ቢያድነኝ በከንቱ መች ሆነና የገዛ አልጋዬን ትቼለት የመጣሁ ለመዳኔ ዋጋ የከፈልኩበት አይደለምን?" እንኳ እንዳይል ያለ ተረፈ ደዌ አንስቶት ያለህን ይዘህ ሂድ እኔ ከአንተ አንዳች አልሻም ባሰኘ ቃል ሸኝቶታል። ግን ታዲያ ይህ ምስኪን መጻጒዕ "ሰው የለኝም" ብሎ የደረሰለትን ሰው ረሳ ማን እንደሆነ እንኳ አላወቀም። ወንጌላዊውም "ዘሐይወ ኢያእመረ ዘአሕየዎ …የዳነው ያዳነውን አላወቀውም" ( ዮሐ.፭፥፲፫) ይለዋል። ያዳነው ማን እንደሆነ ሲጠየቅ ለምሥጋና ያይደለ ለክስ ነበር ስሙን የፈለገው። "ከሚጣፍጠውም ምግቤ ሆዱን ሞላ፥ እኔንም ጣለኝ።" ተብሎ ለናቡከደነፆር በነቢዩ እንደተነገረ ያለ ነው (ኤር.፶፩፥፴፬ ) በአገራችንም ካለው ብሂለ አበው "ታሞ የተነሳ ፈጣሪውን ረሳ" የሚለው እንደነዚህ ያሉትን በሚገባ ለመግለጽ የተነገረ ነው። ሊቀ ነቢያት ሙሴን በዘዳግም ፲ ቁጥር ፳፩ ላይ እንዲህ ይላል "ዓይኖችህ ያዩትን እነዚህን ታላላቆች የሚያስፈሩትንም ነገሮች ያደረገልህ እርሱ ክብርህ ነው፥ እርሱም አምላክህ ነው።" ነገር ግን ይህን ሁሉ ያደረገውን አምላክ ብዙዎች የነበሩ "ህዝበ እስራኤል" ረስተው አሳዝነውት በምድረበዳ በከንቱ ወድቀው ቀሩ ..... ዛሬም ከደዌው :ከማጣቱ :ከችግሩ: ከሥጋ ኑሮ ጉድለቱ ዳግመኛ ለመታረቅ እንደ መጻጒዕ አምላኩን ያልረሳ ማነው? ተአምራቱን አይቶ ቃሉን ሰምቶ አምላኩን ያስታወሰስ ማነው " ቃሉን ያይና ይሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ምክር የቆመ ማን ነውና? ቃሉንስ ያደመጠ የሰማስ ማን ነው?" (ኤር. ፳፫፥፲፰) ማንም። ጌታችን ባስተማረው ማሕየዊ ቃሉ ላይ እንኳ ሳይቀር ያመጹትን አይሁድ እስኪ ተመልከቱ " ገንዘብንም የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው ያፌዙበት ነበር።" ሉቃ ፲፮፥፲፬ እኛንም ቢሆን ከአዳም እስራት ነፃ ያደረገንን አምላክ ውለታ ዘንግተን በቃሉ የምናፌዝ ሁላችንን ወደ ልባችን እንድንመለስ ነቢዩ እንዲህ ሲል ይመክረናል "እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ " እንዲል ( ኢሳ· ፳፰፥፳፪ )።
በፍፃሜ ሕይወቱ በአውደ ምኩናን የሀሰት ክስ የቀረበበትን ይህን የእውነትና የሕይወት ጌታ ቀድሞ ወደ መጠመቂያው እንኳ ለመቅረብ አቅም ያልነበረው ዛሬ ግን አልጋ ለመሸከም በበቃውና ያለ ተረፈ ደዌ በጸናው ኃይሉ የጌታውን ጉንጮች በጥፊ የመምታት ጉልበትና ድፍረት አገኘ። "ዘተሰብሐ ውስተ ገጸ ሙሴ በትስብእቱ ተጸፍአ ገጾ ወተቀስፈ ዘባኖ በእንቲአነ ከመ ይፈጽም ስምዓ ነቢይ ዘይብል መጠውኩ ዘባንየ ለመቅሰፍት ወመላትሕየ ለጽፍአት… በገጹ ነፀብራቅ የሙሴን ፊት ያበራ እርሱ በነቢዩ ጀርባዬን ለግርፋት ጉንጮቼንም ለጽፍአት ሰጠሁ ተብሎ የተነገረውን ለመፈጸም ለእኛ ሲል ፊቱን በጥፊ ተመታ ጀርባውንም ተገረፈ "እንዲል (ሰይፈ ሥላሴ) አምላከ ምሕረት የክብር ጌታ ቀድሞ "ዑቅ ኢትአብስ ዳግመ እንከ ከመ ዘየአኪ ኢይርከብከ … ከዚህ የጠናው "ስለ ደዌ ሥጋ ፈንታ ደዌ ነፍስ" እንዳያገኝህ ሁለተኛ እንዳትበድል" (ቁ ፲፬) ያለውን ዘንግቶ ደዌ ዘኃጢአትን ጠርቶ ተወዳጃት፤ በዕለተ ዓርብ የጌታውን ጉንጮች የጸፉች እጁም ደርቃ `ሰላ` ቀርታለች አንዱ ሊቅ ይህን አልሰማ ባይ መጻጒዕ እና ይቅር ባይ አምላኩን እያደነቀ በጉባዔ ቃናው ይህን ተናገረ
" ይትዐረቅ ምስለ ብእሲት ደዌሁ
ሠላሳ አዝማነ እስመ ነበረት ምስሌሁ"
(መጻጒዕ ከሚስቱ ከደዌ ጋር ይታረቅ ፤ ሠላሳ ዓመታት ከእርሱ ጋር ኑራለችና)
አብረው አያሌ ዓመታት የኖሩ ባልና ሚስት ሲፋቱ ተነፋፍቀው መለያየቱ እምቢኝ እንደሚላቸውና እንደሚታረቁ ሁሉ ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ተብሎ ሳለ ጌታውን ጸፍቶ መጻጒዕም ዳግመኛ ወደ ፴፰ ዓመት "የአልጋ ወዳጁ" ደዌ መመለሱን የቅኔው ምስጢር ያስተምረናል። እንግዲህ እኛም በኃጢአት ከሚመጣ ደዌ ተጠብቀን በአባታዊ ምሕረቱ የሚጠብቀንን ቸሩ አምላካችንን እያመሰገንን በቤቱ እንድንጸና መጻጒዕን "ተነሳ" እንዳለው እኛንም ከወደቅንበት መዘንጋት፣ ኃጢአት በንስሐእንዲያነሳንና ዳግም ከመበደልም እንዲጠብቀን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን። አሜን
|
ምኵራብ
ምኵራብ |
በቀሲስ ኃይለኢየሱስ ተመስገን
መጋቢት 10 ቀን 2008 ዓ.ም
ከሁሉ አስቀድሞ ሃይማኖትን መመስከር እንዲገባ ቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት አካል ዘእምአካል ባህርይ ዘእምባህርይ የተወለደ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አካላዊ ቃል ድህረ ዓለም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መለወጥ ሳያገኛት ዘር ምክንያት ሳይሆን ከስጋዋ ስጋ ከነፍሷነፍስ ነስቶ የተወለደ ወልደ እግዚአብሔር ወልደ ማርያም በተዋህዶ ከበረ።“ይደልዎነ ንእምን ከመ ቦቱ ለወልደ እግዚአብሔር ክልኤቱ ልደታት ቀዳማዊ ልደቱ እም እግዚአብሔር አብ እምቅድመኵሉ መዋዕል ወዳግማዊ ልደቱ እም እግእዝትነ ቅድስት ድንግል ማርያም በደኃራዊ መዋዕል”ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ ፴፬ ቁጥር ፮ ክፍል ፭ ብለን በማመን እንደ አባቶቻችን ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን ስለ ምኵራብ እንማራለን የምናነበውን ለበረከት ያድርግልን አሜን።
የእስራኤል ልጆች መቅደስ(Temple) እና ምኵራብ የሚባሉ ሁለት መንፈሳዊ መገናኛዎች ነበሩአቸው፤ ምኵራብ [በጽርዕ (Synagogue/ συναγωγή)፡ በዕብራይስጥ (Beyth Kenesset/בית כנסתይባላል። መቅደስ የሚባለው በኢየሩሳሌም ብቻ የሚገኝ ስለ ኃጢአት ስለ ምስጋና መሥዋዕት የሚቀርብበት የብሉይ ኪዳን ማዕከል ነው። ምኵራብ የቦታ ወሰን የሌለው በየአቅራቢያው የሚገኝ አጥቢያ ቤተ ጸሎት ነው።የምኵራብ መታነፅ ከባቢልን ምርኮ (exile in Babylon 538 A.D.) ጋር የተያያዘ ታሪክ አለው። በባቢሎን ምርኮ በባእድ ሀገር በዚያው ባሉበት ስርዓተ አምልኮ ለመፈፀም ዳግመኛም ይህ ሁሉ መከራ በአባቶቻችን የተደረገባቸው ቤተመቅደስን ባይሰሩ ነው እኛ ሚጠት የተደረገልን እንደሆነ ቤቱን እንሰራለን በሚል ዋናውን ቤተ መቅደስም ሆነ ብዙ ምኵራባት ሰርተዋል። 10 አባወራዎች ባሉበትም ምኵራብ እንዲሰራ ህጋቸው ያዝ ነበር። በምኵራብም የሚደረገው መንፈሳዊ አገልግልት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ማንበብ መስማትና መተርጎም ንዑሳን በዓላትንም ማክበር ነበር።ማንኛውም እስራኤላዊ በዓመት ሦስት ጊዜ ለዐበይት በዓላት በኢየሩሳሌም መቅደስ ተገኝቶ አምልኮን መፈጸም ግዴታው ነበር። በምኵራብ ግን በየዕለቱ እየተገኙ ቅዱሳት መጻሕፍትን በንባብ በትርጓሜ ይሰማሉ።
በቃል መነገሩ በልብ መታሰቡ ከፍ ከፍ ይበልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራብ ተገኝቶ እንዳስተማረ ለመግለጥ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅደስ ያሬድ ማሕሌታዊ የዓቢይ ጾም ሦስተኛውን ሰንበት ምኵራብ ብሎ ሰይሞታል። ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ፡- “ ቦኦ ኢየሱስ ምኲራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋት አበድር እመስዋዕት አነ ውእቱ እግዚአ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ትሰመይ . . .”ትርጓሜው፡- “ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ። የሃይማኖትን ቃል አስተማረ። ከመሥዋዕትም ምጽዋትን እወዳለሁ አላቸው። የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷ እኔ ነኝ አላቸው የአባቴ ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል። ምኵራብ ገብቶ ተቆጣቸው ዝም ይሉ ዘንድ ትምህርቱን የቃሉን ሞገስ፣ የነገሩን መወደድ፣ የአፉን ለዛ አደነቁ” በማለት ቅደስ ያሬድ ዘምሯል።
ቅዱስ ያሬድ በሰዓታት በወራት እና በዘመናት የተከፋፈሉ ድንቅ ምሥጢር የያዙ መዝሙራትን(ምስጋና) ከብሉያትና ከሐዲሳት ለቤተክርስቲያን እንደ ንብ ቀስሞ እንደ ሰምና ወርቅ አስማምቶ የአገልግሎት ሥርዓትን የሠራ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ነው።ለምኵራብ የሚሆነውንም ዝማሬ ከዮሐ 2፡12-25 ላይ ወስዶ አመስጥሮ እስማምቶ ጾመ ድጓ በተባለ መጽሐፉ አዘጋጅቶልናል። ይህንን የመጽሐፍ ክፍል እንደሚከተለው እናየዋለን።
ቁ.12 “ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀመዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፣ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ” ከቃና ዘገሊላው የዶኪማስ ቤት ሰርግ ውሃውን ወይን አድርጎ ታምራቱን ካሳየ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ከእናቱና ከወንድሞቹ ደቀመዛሙርት ጋር ሄደ በዚያም ጥቂት ቀን (11 ቀን ይላል በወንጌል አንድምታ) ተቀመጡ። ቁ.13 “የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።” ይህም የመጀመሪያ ፋሲካ ነው ጌታ የተሰቀለው በአራተኛው ነው።በምስጢርም ኢየሩሳሌም ወጣ መባሉ ጌታ ከሕይወት ወደመስቀል ምእመናንም ወደ ሕይወት የሚሄዱበት ዘምን በደረሰ ጊዜ ጌታ ሐገረ ሰላም ኢየሩሳሌም ወደተባለ መስቀል ሄደ ማለት ነው።ቁ.14 “በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤” ለስም አጠራሩ የክብር ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራብ በተገኘ ጊዜ በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው ከሚነበበው እና ከሚተረጎመው ከሚፀለየውም ይልቅ የሚሸጠውና የሚለውጠው በዝቶ ተመለከተ። ውንብድና ቢሉ ፈሪሳዊያን የሚያንፀባርቅ እና የሚያንሽዋሻ ልብስ ለብሰው በውጭ ከብቱን ያስደነብሩና ወደምኵራብ ያስገቡታል ከዚያም ከል የገባ አይነጣም ቤተመቅደስ የገባ አይወጣም እያሉ የህዝቡን ገንዘብ ይቀሙታል።መለወጥ ቢሉ ህዝቡ መባ ሊያስገቡ ቀይ ወርቅ ይዘው ሲመጡ እግዚአብሔርማ የሚሻው ነጭ ወርቅ እንጅ ቀይ ወርቅ ነውን ይሉታል እነርሱም በትህትና እውነት ነው ብናጣ ነው እንጅ ለእግዚአብሔርማ ንፁህ ማቅረብ ይገባል ይላሉ ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም ሁለት ቀይ ወርቅ ብታመጡ ባንድ ነጭ ወርቅ እንለውጣችኋለን እያሉ ይበዘብዟቸዋል።ከብቱን ከስቷል ጥፍሩ ዘርዝሯል ፀጉሩ አሯል ለእግዚአብሔርማ የሰባውን ማቅረብ ይገባል ይሏቸዋል እነርሱም በትህትና እውነት ነው በመንገድ ደክሞብን ከስቶብን እንጅ ለእግዚአብሔርማ የሰባውን ማቅረብ ይገባል ይላሉ ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም ሁለት የከሳ ከብት ብታመጡ ባንድ የሰባ እንለውጣችኋለን ይሏቸዋል መሸጥም ቢሉ የከሳውን ከብት አወፍረው አድልበው ይሸጡ ነበር
ቁ.15-16 “የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ። የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው፡” በቤተ ፀሎት ይህን ያልተገባ ነገር ሲፈፅሙም የገመድ ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው ይላል ይህንም ጅራፍ ሐዋርያት አዘጋጅተው ሰጥተውታል የጭፍራውን ለአለቃው መስጠት ልማድ ንውና። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ገበያውን ፈታ። ለሰውነታቸው ቤዛ የሚሆናቸው ስለሆነም የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ በትር አይችሉምና ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ አላቸው። የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው። በተአምራትም ገንዘብ ገንዘባቸውን ለይቶ ከዛፍ ላይ እንደሰፈረ ንብ ከቃ ከቃቸው ላይ አስቀምጦላቸዋል። ቁ.17 “ደቀ መዛሙርቱም የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደተጻፈ አሰቡ።”ነቢየ እግዚአብሄር ቅዱስ ዳዊት በመዝ 68፡9 በቤተ መቅደስ ስዕለ ፀሀይ አቁመውበት መስዋእተ እሪያ ሰውተውበት ገበያ አድርገውት ሲሸጡበት ሲለውጡበት በመንፈሰ ትንቢት ተመልክቶ ለቤተ እግዚአብሄር የቀናውን ቅናት እንደ እሳት አቃጠለኝ ይላል።
“እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ። ትርጉም የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና ነፍሴን በጾም አስመረርኋት። ”
ይህ ትንቢት ለጊዜው ለመቃቢስ ፍፃሜው ለጌታ የተነገረ ነው። በመቃቢስ ጊዜ አንጥያኮስ በቤተመቅደሱ አምልኮ ፀሀይ አግብቶ እሪያ ሰውቶ ነበርና፤መቃቢስ ያንን አጥፍቶ ለቤተመቅደሱ የቀናውን ቅንዓት ያመለክታል። በልዑል እግዚአብሔር ላይ በስህተትም ሆነ በድፍረት የሚቀርብ ተግዳሮት በቅዱሳንም ይደርሳል። ልዑል እግዚአብሔር ባህርዩ ደርሶ የሚገዳደር የለም እርሱ ነገሥታት የማይነሣሡበት መኳንንትም የማይበረታቱበት አምላከ አማልክት ወንጉሠ ነገሥት ነው። ነገር ግን የአምልኮቱ መገለጫ በሆኑት በቤተመቅደስ ውስጥ ባሉት ታቦታት፣ንዋያተ ቅደሳት፣በዓላትና ሥርዓቶች እንዲሁም እርሱ የላካቸውን ቅዱሳን መግፋት መገዳደር ጌታ እግዚአብሔርን መገዳደር ነው። ነቢየ እግዚአብሄር በቤተመቅደስ ገበያ አቁመው የሚገዳደሩትን ባየሁ ጊዜ ተግዳሮታቸው በእኔ ላይ ወደቀ ነፍሴንም በጾም አስመረርኋት ይላል። በደብተራ ኦሪት ሁለት እጓላተ ለህም አቁመው እንደተገዳደሩት፣መና ከደመና አውርዶ ቢመግባቸው ምንት ጣዕሙ ለዝ መና ብለው እንደተፈታተኑት ፣ በኋላም ወልደ እጓለ እምሕያው ስጋየን የበላ ደሜን የጠጣ የዘላለም ህይወት አለው ቢላቸው እፎ ይክል ዝንቱ የሀበነ ሥጋሁ ንብላዕ ብለው እንደተገዳደሩት በመንፈሰ ትንቢት ተመልክቶ ሰውነቴን በርሃብ በቀጠና አደከምኩዋት እያለ ነቢየ እግዚአብሔር የተናገረውን ደቀመዛሙርቱ አስበው እነሱም ለቤቱ ቀኑ። በዚህ ዘመን እኛም ለቤተክርስቲያን ቅናት ሊኖረን ይገባል ለክብሩ መቅናት ለገዳማቱ ለአብነት ትምህርት ቤቱ መፈታት ለሊቃውንቱ መታረዝ ልቡናችን ሊቃጠል ይገባል። “ኢየሱስም መልሶ ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው ስለዚህ አይሁድ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፣ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን አሉት። እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተመቅደስ ይል ነበር። ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ይህን እንደተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ።” ቁ.19 እና 20 በ46ቱ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት የተነገረውን ልደቱን ሞቱን በሶስተኛው ቀን መነሳቱን ሁሉ ስለ ሰውነቱ አስረዳቸው። እሠራዋለሁ አላለም አነሣዋለሁ እንጂ። በዚህም የሞቱንና የትንሣኤውን ነገር ገለጠ።
አንጽሆተ ቤተመቅደስ
ይህም ቀን የማንጻት ቀን አንጽሆተ ቤተመቅደስ ይባላል።ኦሪት ወንጌልን፣ ምኵራብ ቤተክርስቲያንን አስገኝተዋል ጌታም የበግ የፍየል መስዋእት መቅረቱን ለቤዛ ዓለም መምጣቱን አስተማሯቸዋል አስጠንቅቋቸዋል። ምኵራብ ሁሉ የማይገባባት ነበረች በመጽሐፈ ነህምያ ምዕ 13፡1 “አሞናውያንና ሞዓባውያንም ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ለዘላለም እንዳይገቡ የሚል በዚያ ተገኘ።” ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የማይመረጥባት አንተ አይሁዳዊ አንተ ሮማዊ የማትል አንዲትኵላዊት ቤተመቅደስን ሰጠን።
ምኵራብ /ቤተ መቅደስ/ የሰውልጅ ምሳሌ ነው ምኵራብ የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው። የሰው ልጅም የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው ሸቀጡም የኃጢአት ምሳሌ ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ሰውነትን ስለማንፃት እና እራስን ከሸቀጥ ስለማራገፍ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ያስተማረውን ማሰብ ያስፈልጋል እኛም የህያው አምላክ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተመቅደስ ነንና ሰውነታችን ሽያጭ የሚፀናበት እንዳይሆን ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል።
●1ኛቆሮ ምዕራፍ 3-17 “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።”
●1ኛቆሮ ምዕራፍ 6-20 ላይ “ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።”
●2ኛቆሮ ምዕራፍ 2-17 የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።
በቅዳሴ ያዕቆብ ዘስሩግ “ተንስኡ በፍርሃተ እግዚአብሔር ከመ ታፅምኡ አርኅው መሳክወ አእዛኒክሙ ወአንቅሁ ልበክሙ” እግዚአብሔርን በመፍራት ተነሱ የጆሮቻችሁን መስኮቶች ክፈቱ ልቦናችሁን አንቁት እንደተባልን ሳንፈዝ ማን አዚም አደረገባችሁ ተብለንም እንዳንወቀስ የእግዚአብሔርን ተግሳፅ የአበውን ምክር ሰምተን አሁን ሰውነታችን በንስሐ ለማንጻት እንነሳ። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም በመዝ 94፡8 “ዮም አመ ሰማዕክሙ ቃሎ ኢታፅንኡ ልበክሙ” ዛሬ የእግዚአብሔርን ቃል ስትስሙ ልባችሁን አታፅኑት እንዳለ ይህን በምኵራብ አምላካችን ያደረገውን ስንሰማ የዘረኝነት የፍቅረ ንዋይ የተንኮል የትዕቢት ሸቀጣችን ትተን ቤተመቅደስ ሰውነታችን በንስሐ አጥበን ልባችን በትህትና ሞልተን በቤቱ ለበለጠው ጸጋ ቀንተን ቅንነትንም አክለን በቤቱ ለመኖር አምላካችን ይርዳን አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
|
Tuesday, 22 March 2016
ዘወረደ
ዘወረደ |
በዲያቆን ስመኘው ጌትዬ
የካቲት 26 ቀን 2008 ዓ.ም.
እንኳን ለዓቢይ ጾም በሰላም አደረሰን። የ፳፻፰ (2008) ዓ.ም ዓቢይ ጾም የካቲት ፳፰(28) ቀንተጀምሮ ሚያዝያ ፳፫ (23) ቀን ይፈጸማል። ይህ ጾም በ 8 ታላላቅ ሳምንታት የተከፋፈለ ሲሆንእነርሱም ዘወረደ፣ ቅድስት፣ ምኲራብ፣ መጻጒዕ ፣ ደብረዘይት፣ ገብርኄር፣ ኒቆዲሞስ፣ እና ሆሳዕናይባላሉ፡፡ በዚህ ጾም ውስጥ በአጠቃላይ ጾመ እግዚእነ (የጌታችን ጾም) አርባውን ቀን ሲይዝየመጀመሪያው ሳምንት ጾመ ሕርቃል እና የመጨረሻው ሳምንት የጌታን ሕማማት የምናስብበትሰሙነ ሕማማት የቀረውን ክፍል ይይዛሉ፡፡
ዛሬ የመጀመሪያውን ሳምንት ወይም ዘወረደ የተባለውን ጾም ስያሜውን እና ምስጢሩን በታላቁሊቅ ቅዱስ ያሬድ ትምህርት እንዴት እንደተገለጠ እናያለን፡፡ የብሉያት እና የሐዲሳት መጽሐፍትሊቅ ቅዱስ ያሬድ ከጸዋትወ ዜማ መጽሐፍቱ አንዱ በሆነው የድጓ ክፍል ጾመ ድጓ (በጾምስለሚደረስ ጾመ ድጓ ተብሏል) ስለ ጾም ብዙ ጽፏል።ከዘወረደ ጀምሮ ያሉት ስምንቱም ሳምንታትስያሜያቸውን ያገኙት ከጾመ ድጓ መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ ይህ የዜማ መጽሐፍ በተለይ ዋዜማክፍሉ ላይ ያሉትን የመጀመሪያ ቀለማት በመምረጥ የየሳምንታቱን ስያሜዎች አስገኝቷል፡፡ በዘወረደድርሰቱ ቅዱስ ያሬድ በጾም ልናስባቸው እና ልናከናውናቸው የሚገቡንን ነገሮች ከሥነምግባር፣ከጸሎት፣ ከቤተክርስቲያን፣ ከመስቀሉ አንፃር እየሆነ ይነግረናል፡፡ ዛሬ በዘወረደ ድርሰቱከተገለጡት በጥቂቱ እያነበብን እንማማራለን።
ቅዱስ ያሬድ የጾሙን ድርሰት ሲጀምር “ሃሌ ሉያ “ ቅድመ ዓለም የነበረ ዓለምን አሳልፎ የሚኖርሁሉን የጀመረ ሁሉን የሚያስጀምር ሁሉን የፈጸመ ሁሉን የሚያስፈጽም ጾማችንንም እንዲሁያድርግልን እያለ ነው።ስለዚህም ቀጠለ “ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩእግዚአ ኩሉ ዘየሃዩ በቃሉ... ከላይ ከአርያም የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት ወይም ከላይመውረዱን አላወቁም ይሆን? እርሱስ በቃሉ ሁሉን የሚያድን ጌታ ነው።” የሰኞ ዋዜማውንይጀምራል።ይህንንም መነሻ አድርጋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሳምንቱን ዘወረደ ብላሰይማዋለች።
ጾሙን አሁን እንዴት እንየው? “ኩኑ እንከ ከመ ብእሲ ጠቢብ... እንግዲህ ስለ ኀጢአቱ መሰረይእንደሚጾምና እንደሚጸልይ ጥበበኛ ሰው ሁኑ።መልካም ነገርን ታገኙ ዘንድ በእውነት ሂዱሰንበትን አክብሩ መልካም ነገርን ማድረግ ተማሩ… ” ሊቁ እንደሚጾምና እንደሚጸልይ ሰው ሁኑብቻ አላለም ።ነገር ግን ጾማችንን በጥበብ ይሁን ‘ጥበበኛ’ አለን እንጂ።ዳግመኛም አስተውሉ‘እንግዲህ’ ብሎ መጀመሩን ከዚህ በፊት ምንም ሁኑ ምንም በቃ ሁሉም ይብቃ ጥበብን ወደልባችሁ ጥሯት በጥበብም ጾምን እና ጸሎትን ስለ ኃጢአታችሁ ከዚህ በኋላ ገንዘብ አድርጉ።አለፍብሎ ‘እንግዲህ’ ያለውን ቃሉን ይገልጠዋል “አከለክሙ መዋዕል ዘሃለፈ ዘተቀነይክሙ ለግእዘሥጋክሙ... ለሥጋችሁ ፈቃድ የተገዛችሁበት ያለፈው ዘመን ይብቃችሁ ከእንግዲህስ ወዲህ ጹሙጸልዩም ለእግዚአብሔር ተገዙ …” አሁን ሥጋን ከምኞቱ እና ከመሻቱ ጋር እንሰቅለዋለን።ስለዚህም ከአባቱ ከቅዱስ ጴጥሮስ የተማረውን መነገር ባለበት ጊዜ ሊቁ ነገረን።”የአሕዛብን ፈቃድያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርምባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና።” 1ጴጥ 4፡3 አሁን ጊዜውየጾም የመገዛት ነው።”ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ።” መዝ 2፡11ብሎ ቅዱስ ዳዊት የተናገረውን ቅዱስ ያሬድም በፍርሃት እንድንገዛ በአባቱ ቃል ይመክረናል።
ስለ ጾምም “ይህች የተከበረች እና ታላቅ ጾም ለሚያምኑ ሕዝበ ክርስቲያኖች የተሰጠች ናት ለእግዚአብሔር ልጆች መሪ የሆነቻቸው የዚችን ጾም ታላቅነት ተመልከቱ ።በዚህች ጾምየእሥራኤል ልጆች ባሕርን ተሻገሩባት፣ የዚችን ጾም ታላቅነት ተመልከቱ ዳንኤል ከአናብስት አፍዳነባት፣ የዚችን ጾም ታላቅነት ተመልከቱ ሶስና ከአይሁድ ረበናት ዳነችበት፣ የጾምን ክብሯንታላቅነቷን ተመልከቱ ታላቅነቷን ተመልከቱ ለሰነፎች ሀዘን ለጠቢባን ደስታቸው ናት፣ የጾምንታላቅነት ተመልከቱ የዚችን ጾም ” እያለ ልንጀምረው የምንደረደርለትን ጾም እያከበረ እያዜመአስታወቀን። በጾምስ እንዴት እንሁን እንዳይሉት ”እርሱ ልብ የሚል የሚያስተውል የሚጾምምራሱን ዝቅ የሚያደርግም ምስጉን ነው።በሕይወቱ ስለ ሠራው በጎ ሥራ ከአምላኩ ክፍያውንይወስዳል(የሚወስድ ነው) ” እያለ እያዜመ ይቀጥላል።”…እጄ ምድርን መሰረታት ቀኜም ሰማይንአጸና በሕይወት ትኖሩ ዘንድ በጾምና በጸሎት በቀናች ሃማኖት ወደ እኔ ተመለሱ።” ነፍሳችንበምትሰማው ሠማያዊ ዜማ የሚለን ነገር አለ። “እንጹም እንጸልይ በየዋሃትና በፍቅርለእግዚአብሔር እንሁን ቀደምት አባቶች ከኃጢአት እንደዳኑ በአርምሞ ከፈተና እንዳመለጡ(እንደሸሹ)”። ጾምን ከጸሎት አይለያትም ዋጋዋ ታላቅ ነውና።ጸሎት ደግሞ በልምድ ሳይሆንበተሰበረ ልብ በየውሃት መሆን አለበት ።አሁንም ቢሆን የውሃት ብቻውን አይበቃም።ሁሉንማሰሪያው ፍቅር ሊታከልበት ይገባል።ለዚህም ነው በዚህ ድርሰቱ ቅዱስ ያሬድ በየገጹ ቢያንስአንድ ጊዜ “አፍቅር ቢጸከ” “ወንድምህን ውደድ” የሚል ትእዛዝ ሳይጽፍ ያላለፈው።ፍቅር ያለውሰው ደግሞ በየትኛውም ጊዜ በምንም ሁኔታ ራሱን ለአምላኩ ያስገዛል፣አርምሞን ገንዘቡያደርጋል።ይህም እርሱን ወደ አላማው ያደርሰዋል።አላማው የእግዚአብሔር መሆን አይደለምን?የእርሱ ከሆነ ደግሞ ወጥመድን ፈተናን ሁሉ ያልፋል።ዓለም የምታዘጋጅለት ሁሉ ከአምላኩአይለየውም።ስለዚህ አባታችን በዚህ ፍቅር ኖሮ “ኦ ፍቁራንየ” እያለ ያዜምልናል ድምጹን እንስማ”የምወዳችሁ ወንድሞቼ የዚህ አለም ንብረት ምን ይጠቅመናል? ምድራዊ መዝገብ እንደሚጠፋአልሰማችሁምን?ስለዚህ በእግዚአብሄር መታመንን ያጸና በሕይወት ይኖራል” ይህን ያለን ደግሞንብረት አያስፈልግም ለማለት አይደለም ሁሉ እያለን እንደሌለን እንኑር ከአለም ከንቱ መጎምዠትእንጹም እያለን እንጂ።ይህ ይቻላልን? ትሉኝ ይሆናል።እኔ ምን እላችኋለሁ እርሱ ግን መልስአለው። “ይጹም ዓይን... ዓይን ይጹም ልሳን ይጹም ጆሮም ክፉ ከመስማት ይጹም በፍቅር ይህሁሉ ይሁን” ይህ ሁሉ ሲሆን ደግሞ እኛ በአለም እያለን ከአለም ውጪ እንሆናለን።ያኔ ደግሞሰማያዊ ሆንን፣ ጾምን ማለት ነው። “እስመ በጾም ወበጸሎት ይሰረይ ኩሉ ኃጢአት በጾም ድኅኑአበው ቀደምት ኤልያስ ዐርገ ውስተ ሰማያት” በጾምና በጸሎት ኃጢአት ሁሉ ይሰረያልና ፣የቀደሙአባቶች በጾም ዳኑ ኤልያስም ወደ ሰማያት ዐረገ።” ኤልያስን በጾም ሕያዋን ከመሬት ከፍ ብለውበጿሚው ሥጋቸው ሥጋዊውን ምድር አሸነፉ አለን።ስለዚህ ወገኖቼ በጾም ህግን መጠበቅ ብቻሣይሆን ከምድራዊ ሕግም በላይ በመሆን ከሥጋ ፈቃድ ወጥቶ ወደ ርቱዕ ሕይወት መሸጋገርእንዲቻል ሲያሳውቀን ነው።
እንዲህ ሊገስጸን ደግሞ ጀመረ። “አንተስ አስቀድመህ ራስህን መርምር” የምን ምርመራ ነው?ሥጋዊምርመራ አይደለም የነፍስ ህመምን እንጂ ።ወገኖቼ የጾምን በር ሳናንኳኳ አንከፍትም። ለመግባትግን እንድንገባ ሆነን መገኘት አለብን ።ከኃጢአታችን ጋር ከበደላችን ጋር ሆነን አንገባም። ያለፈውንትተን ንስሐ ገብተን ፣ ያቀድነውን የኃጢአት ቀጠሮ ሰርዘን ራሳችንን የተገባ ካደረግን በኋላ የበሩንደውል እንጫን። አሁን ከራሳችን ጋር ከምርመራ በኋላ ታርቀናል። ቀጣዩን እርሱ ያዚምልን “ጹምለእግዚአብሔርም ተገዛ” በእውነት ዜማው ይለያል፣ ጣዕመ ዜማው አዲስ ነው።”በምሥጋና ላይእንግዳ (ወንድም) መውደድን ጨምር” ምሥጋና ላይ መውደድ ጨምሩ ማለቱ ለምን ይሆን?በትክክል የሚጾም ጾም ምሥጋና ነው።ስለዚህ በምሥጋና ጾማችን ላይ እንግዳ (ወንድም) መውደድን ጨምሩ አለን።አሁንም እንዲሁ የተፈለጠው እንጨት(ጾምን) በልጥ ፍቅር መታሰር አለበትና ወንድማችሁን ውደዱ እያለ ሊቁ ያሳስበናል።
“ከምግብህ ላይ ስጥ የተራበን አጥግብ” ይህንን ዜማ ሰማችሁን? በጾም ያተረፍነውን (ቁርስ ወይምምሳ) ምግብ በምንበላ ሰአት በአይነት እንዳናካክሰው እንዲህ አለን። ያ ያልተበላ ምግብ በገንዘብየሥጋዊ ሕይወት ኢኮኖሚ ማድለቢያ ሳይሆን የነዚያ ተርበው ፍርፋሪ ያጡት እንግዶችነው።እንውደዳቸው ብሎን የለ?ታዲያ ሲርባቸው ቢያንስ በዚህ እናጥግባቸውና ፍቅራችንንየእውነት ጾማችንን የጽድቅ እናድርገው።የራባቸውን አብሉ ሳይሆን አጥግቡ ማለቱን ልብ እንበል።“ለድሃ አደጉም ፍረድ” ድሃ አደጉ ዛሬ በጾም ከእኛ የሚፈለገው የለምን?ለምኖ ስላልተሰጠውየእኛን ፍትህ አይሻምን? ለተራበው፣ለተጠማው፣ለታረዘው፣ለታመመው፣ የእኛን በጎነትለሚጠብቀው ሁሉ እንድረስ። እዝን ያለው በውሳጣዊ እዝን(ጆሮው) ይስማ። ጾማችን በረከትንያሰጠን ዘንድ ለችግረኞች ሁሉ መድረስ ቸል አንበል።
ራሳችንን መርምረን ፣ ብንጾም፣ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ብንገዛ፣እንደ መላእክቱ ለምሥጋናብንተጋ፣ ወንድሞቻችንን እንደ ራሳችን ብንወድ፣ካለን ለተቸገሩ ብናካፍል፣ለምስኪኑ ብንራራ በኋላበተፍጻሜቱ “ይህ ለአንተ መልካም ነው” ይለናል ።
ጌታም በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ ተብሎ በነቢዩ የተጻፈውን እንደፈጸመ ደቀ መዝሙሩም ቅዱስያሬድ የጾምን ነገር በጾሙት እየመሰለ እንዲህ አለን “ሙሴ ጾመ ዳንኤልም ጾመ ጌታም ስለ እኛጾመ ስለዚህ ጾምን ቀድሱ” ሙሴ ቢጾም ሕግን ሊቀበል ዳንኤል ቢጾም ከአናብስት አፍ ሊወጣየወገኖቹን ነፃነት ናፍቆ፣እንኪያስ ጌታ ለምን ጾመ? አርአያ ሊሆነን ፣ጾምን ሊቀድስልን እንጂ ምንጎድሎበት ምን ሊያገኝ ነው? ሁሉ በእጁ የተያዘ ነው ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስ ነግሮን የለምን?2ኛ ጴጥ 3:10 ስለዚህ እኔም ከአባቴ ጋር አልሁ ጾምን ቀድሱ ፣ተቀድሶ ተሰጥቶናልና።ጾምን ቀድሱ ያለፈውየኃጢአት አገልግሎት ይብቃ።”ጾምን ቀድሱ ሙሴ በሲና ጾሟልና ኢያሱም በጾም ዳነ በገባኦን ፀሐይን አቆመ” ።ዜማው እንዳያልቅብን ብንጓጓም ዛሬ በነገ መቀየሩ ግድ ነውና ሳይሰናበተን “በበጎሥራ ሁሉ ስትጓዙ የሰላም መንገድን ተከተሏት በእርሷም ሂዱ ጾምን ፍፁም እንጹም የሰላም እህትቅድስት ጾምን ጌታ ራሱ ጾሟታልና ” እኛም ስንሰናበት “የማይጠልቅ ፀሐይ ፣የማይጠፋብርሐን፣የማያበድሩት ባዕለ ጸጋ ፣የሐዋርያት ጌጣቸው፣የችግረኞች ሃብታቸው፣ለተገፉትመጠጊያቸው ሁልጊዜ እናመሰግንሃለን መሀሪ ንጉሥ በሥራው ቸል የማይል።የአብርሀም የይስሐቅየያዕቆብ አምላክ ምሕረትህን አሳየን በአርአያህ የሠራኸውን የፈጠርከውን ሕዝብህን አታጥፋአትተው። ” እንዳለ ቅዱስ ያሬድ።
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።ይቆየን!
|
Subscribe to:
Posts (Atom)