Wednesday, 27 April 2016

አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል


አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል
በሰሙነ ሕማማት ጠቅለል ባለ መልኩ የምናስባቸው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት አሥራ ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል ይባላሉ፡፡ ለክርስቲያኖች እነዚህን ሕማማተ መስቀል ማወቅና ዘወትር ማሰብ ተገቢ በመሆኑ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

1.     ተኰርዖተ ርእስ (ራስና በዘንግ መመታት)፤
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን በዘንግ መመታቱንና መቀጥቀጡን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተኰርዖት›› የሚለው ቃል ኩርዐ - መታ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ርእስ ደግሞ ራስ ማለት ነው፡፡ አገረ ገዥው ጲላጦስ ‹‹እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ›› ብሎ እጁን ከታጠበ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ገርፎ ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች አሳልፎ ሰጥቶት ነበር፡፡ በአይሁድ ሕግ የተገረፈ አይሰቀልም፤ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም፡፡ እርሱ ጲላጦስ ግን ከገረፈው በኋላ፣ የበደል በደል፣ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው (ማቴ 27¸24፤ ማር 15¸15፤ ሉቃ 23¸25፤ ዮሐ 18¸39)፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ የእሾህ አክሊል ጐንጉነው ራሱ ላይ ደፍተውበታል፡፡ ራሱንም በዘንግ መትተውታል (ማር 15¸19)፡፡ የሰው ዘር ከአዳም ጀምሮ በጠላቱ በዲያብሎስ በተጐነጐነ የኃጢአት እሾህ ራሱ ተይዞ ነበርና ይህንኑ ለማስወገድ ከሰማይ የወረደ ሰማያዊ የሆነ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ ተንኮል የተጐነጐነ አክሊለ ሦክ እንደ ዘውድ ደፋ፡፡ በሲኦል ወድቆ በዲያብሎስ ተረግጦ ራሱ የሚቀጠቀጠውን የሰውን ልጅ ለማዳን መድኃኔዓለም ክርስቶስ ራሱን በመቃ ተቀጠቀጠ፡፡ ከራሱ ላይ በሚወርደው ደም ፊቱ ተሸፈነ፡፡

2.     ተፀፍዖ መልታሕት (በጥፊ መመታት)፤
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጃቸው በደም፣ ጣቶቻቸው በበደል በረከሰ በአይሁድ እጅ በጥፊ መመታቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተፀፍዖ›› የሚለው ቃል ፀፍዐ በጥፊ መታ ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ መልታሕት ደግሞ ፊት ጉንጭ ማለት ነው፡፡

ጌታችን ለሊቀ ካህናት ቀያፋ እውነትን መናገር እንደ ስድብ ተቆጥሮበት መላልሰው ፊቱን በጥፊ መትተውታል፡፡ ፊቱንም በጨርቅ ሸፍነው ‹‹ክርስቶስ ሆይ በጥፊ የመታህ ማነው? ትንቢት ተናገርልን›› እያሉ ዘብተውበታል፡፡ በጠላት ዲያብሎስ እጅ ወድቆ በነፍሱ ይቀለድበትና ይንገላታ የበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ብሎ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ ወድቆ ተጐሰመ፤ ተንገላታ፤ በጥፊም ተመታ (ማቴ 27¸27)፡፡ ጲላጦስ አሳልፎ ከሰጠው በኋላም አክሊለ ሦክ በራሱ ላይ አኑረው ቀይ ልብስ አልብሰው ‹‹የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን›› እያሉ እየተሳለቁበት በጥፊ መትተውታል (ዮሐ 19¸2-4)፡፡ አላወቁትም እንጂ እርሱ በመንግሥቱ ሽረት፣ በባሕርዩ ሞት የሌለበት የዘለዓለም አምላክ ነው፡፡

3.     ወሪቀ ምራቅ (ምራቅ መተፋት)፤
ርኩሳን አይሁድ በብርሃናዊው የክርስቶስ ፊት ላይ በሚያስጸይፍ ሁኔታ ምራቃቸውን እንደተፉበት የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ወሪቅ›› የሚለው ቃል ወረቀ ካለው ግእዛዊ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ትርጉሙም እንትፍ አለ፣ (ተፋ) ማለት ነው፡፡ በነቢዩ በኢሳይያስ መጽሐፍ (ምዕራፍ 5ዐ¸6) ‹‹ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስኩም›› ተብሎ እንደተነገረ እየዘበቱበት ምራቃቸውን ተፉበት (ማቴ 27¸29-3ዐ፤ ማር 15¸19)፡፡ በኃጢአት የቆሸሸውን የሰውን ሕይወት ለማጥራት የመጣው ንጹሐ ባሕርይ አምላክ ተተፋበት፡፡ በሥራው ከገነት ተተፍቶ፤ ተንቆ፤ ተዋርዶ የነበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ኃጢአትን ይቅር የሚል እርሱ ጌታችን ያለ ኃጢአቱ ተተፋበት፤ ተናቀ፤ ተዋረደ፡፡ እንኳን በአምላክ ፊት በሰው ፊት እንኳን መትፋት እጅግ ያስነውራል፡፡ እርሱ ግን የኃጢአታችንን ነውር ከእኛ ሊያጠፋ ነውር የሆነውን ምራቅ ተቀበለ፡፡

4.     ሰትየ ሐሞት ( መራራ ሐሞት መጠጣት)፤
ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ሳለ ተጠማሁ ባለ ጊዜ መራራ ሐሞት መጠጣቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ሰተየ›› ማለት ጠጣ ማለት ነው፡፡ ሐሞት የሚለውም አሞት ተብሎ በቁሙ ይተረጐማል፡፡ በመዝሙር 68 ቁጥር 21 ላይ ‹‹ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ፣ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ›› ብሎ ነቢዩ ዳዊትን ትንቢት ያናገረ የነቢያት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ ‹‹ተጠማሁ›› ባለ ጊዜ ሆምጣጤ ተሞልቶበት ተቀምጦ ከነበረው ዕቃ ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው ወደ አፉ አቀረቡለት፡፡ ውኃ አጠጡኝ ቢላቸው በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፡፡ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም (ማቴ 27¸34)፡፡ ጌታችንም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ ‹‹ተፈጸመ›› አለ፡፡ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ (ማቴ 27¸48፤ ማር 15¸36፤ ሉቃ 23¸36፤ ዮሐ 19¸29)፡፡

ቢጠጡት ለዘለዓለም የማያስጠማ ውኃ የሚሰጥ አምላክ፤ የተጠማችውን ነፍስ የሚያረካ ጌታ፤ ለዘለዓለም የሚፈልቅ የሕይወት ውኃ ምንጭ የሚያድል ፈጣሪ በተጠማ ጊዜ የፈጠረውን ውኃ እንኳን የሚያጠጣው የሚያቀምሰውም አላገኘም (ኢሳ 55¸1)፡፡ አርባ ዓመት ሙሉ በቃዴስ በረሃ ኳትነው ለነበሩ አባቶቻቸው ከሰማይ መና አውርዶ የመገባቸው፤ ከአለት ላይ ውኃ አመንጭቶ ያጠጣቸው ክርስቶስ በተጠማ ጊዜ ቀዝቃዛ ውኃ ነፈጉት (ዘዳ 16¸1-2ዐ፤ 1ቆሮ 1ዐ¸3)፡፡ የዝናማት፤ የባሕርና የውቅያኖስ ጌታ በውኃ ጥም ተቃጠለ፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሲኦል በረሃ ወድቀው በሕይወት ውሃ ጥም የተቃጠሉትን ነፍሳት ለማርካት ሲል እርሱ ተጠማ፡፡ በኃጢአት ወድቀው፣ በበደል ረክሰው፣ በነፍሳቸው ተጐሳቁለው፣ መራራ መከራን የሚቀበሉትንና ምረረ ገሃነም አፉን ከፍቶ ሆዱን አስፍቶ የሚጠብቃቸውን ሁሉ ለማዳን መራራ ሐሞትን ቀመሰ፤ ሆምጣጣውንም ጠጣ፡፡ የመረረውን የሰው ልጆችን ሕይወት ለማጣፈጥ የመረረውን መጠጥ ተቀበለ፡፡

5.     ተቀሥፎ ዘባን (ጀርባን መገረፍ)፤
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀርባው እስኪላጥ ያለ ርኅራኄ የመገረፉን ነገር የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተቀሥፎ›› የሚለው ቃል ቀሠፈ- ገረፈ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹‹ዘባን›› ደግሞ ጫንቃ፣ ትከሻ፣ ጀርባ ማለት ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጠው የተገረፈ አይሰቀልም፡፡ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም ነበር፡፡ ጲላጣስ ግን ኢየሱስ ክርስቶስን አስገረፈው፡፡ ከደሙ ንጹሕ ነኝ ብሎ ከታጠበ በኋላ ክርስቶስን ያለ ኃጢአቱ በመግረፍ ለአይሁድም አሳልፎ በመስጠት ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› እንዲሉ የታጠበ እጁን መልሶ አቆሸሸው (ማቴ 27¸28፤ ማር 15¸15፤ ዮሐ19¸1)፡፡

መድኃኒታችን መንፀፈ ደይን ወድቆ በእግረ አጋንንት ተጠቅጥቆ በእሳት አለንጋ የሚገረፈውን የሰው ልጅ ለማዳን ሲል ጀርባውን ለግርፋት ሰጠ፡፡ ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠር ተገረፈ፡፡ አይሁድ አገረ ገዥያቸው ጲላጣስ ላቀረበላቸው ምርጫ ይፈታላቸው ዘንድ ነፍሳትን ከሲኦል የሚያወጣውን ክርስቶስን ሳይሆን ራሱን እንኳን ከምድራዊ ወህኒ ማውጣት ያልቻለውን ወንበዴውን በርባንን መረጡ፡፡ መገረፍ ይገባው የነበረ በርባን ተለቀቀ፡፡ በነቢዩ በኢሳይያስ ‹‹ጀርባዬን ለገራፊዎች፣ ጉንጬንም ለጠጉር ነጪዎች ሰጠሁ›› (በኢሳ 5ዐ¸6) ተብሎ እንደተነገረ ጀርባውን ለገራፊዎች አሳልፎ ሰጠ፤ ጽሕሙንም ተነጨ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው የሰው ልጅ ከሚያድነው አምላክ ይልቅ የሚገርፈውንና የሚዘርፈውን ወንበዴ መርጦ ስለተገኘ ነው፡፡

6.     ተዐርቆተ ልብስ (ከልብስ መራቆት)፤
አምላካችን ኢየሱስ ክርስስቶስ ልብሱን መራቆቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተዐርቆተ›› ማለት ታረዘ፤ ተራቆተ ማለት ነው፡፡ ፀሐይና ከዋክብትን ብርሃን አልብሶ የፈጠረ አምላክ ተራቆተ፡፡ ጸጋውን ለዕሩቃን የሚያለብስ አምላክ ልብሱን ተገፍፎ ዕራቁቱን ቆመ፡፡ ጨለማን ለብሶ ጨለማን ተንተርሶ ይኖር የነበረውን ሰው መልሶ ብርሃን ያለብሰው ዘንድ የብርሃናት ጌታ፣ የጸጋ ሁሉ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገፈፈ፤ ተራቆተ፡፡

የሲኦል ወታደሮች የሆኑት አጋንንት የሰውን ልጅ ጸጋ ገፍፈውት ነበርና ጲላጦስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አሳልፎ በሰጣቸው ሰዓት ወታደሮች ልብሱን ገፍፈውታል (ማቴ 27¸27)፡፡ የሰው ልጅ ለቀረበለት ምርጫ የሰው ምላሽ ዘራፊው፤ ገራፊው ወንበዴ በርባን እንዲፈታለት ነበር፡፡ ‹‹አቅረብኩ ለከ እሳተ ወማየ፣ ደይ እዴከ ኅበ ዘፈቀድከ! እነሆ እሳትና ውኃን አቅርቤልሃለሁ፣ እጅህን ወደ ፈቀድከው ስደድ›› ሲባል የሰው ልጅ እጁን ወደ እሳት ሰደደ፡፡

7.     ርግዘተ ገቦ (ጎንን መወጋት)፤
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ጎኑን በስለታም ጦር መወጋቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ርግዘት›› የሚለው ቃል ረገዘ- ወጋ ከተሰኘ የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ ገቦ ማለት ደግሞ ጎን ማለት ነው፡፡ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አጠገብ፣ በግራና በቀኙ ሁለት ወንበዴዎች ተሰቅለው ነበር፡፡ ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ እንዳይኖር ጭናቸው ተሰብሮ እንዲወርዱ አይሁድ ጲላጦስን በለመኑት መሠረት ጭፍሮቹ የሁለቱን ወንበዴዎች ጭን ጭናቸውን ከሰበሩ በኋላ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ሲመጡ ፈጽሞ እንደሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፡፡ ነገር ግን ከጭፍሮቹ አንዱ ጎኑን በጦር ስለወጋው ወዲያው ከጎኑ ደምና ውኃ ፈሰሰ (ዮሐ 19¸33)፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደርገው ዘንድ ሞተ፤ የሰው ልጅ በዘለዓለማዊ ሞት ተይዞ ነበርና፡፡ ትልቁ ሞት በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየት ነው፡፡ በጌታችን ሞት ግን ሞት ራሱ ድል ተነሣ፡፡ የሞት መውጊያ በሆነ ኃጢአት የሞተውን ሰው ለማዳን ጎኑን በጦር ተወጋ፡፡ በሰው ልቡና ተተክሎ የነበረውን ኃጢአት ከነሥሩ ነቅሎ ስለጣለው ‹‹ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ?›› ተባለ፡፡ የሞት መውጊያው ኃጢአት ነበርና (1ቆሮ 15¸54-55፤ ኢሳ 25¸8፤ ሆሴ 13¸14)፡፡

ከተወጋው የጌታችን ጎን ደምና ውኃ መፍሰሱም የእግዚአብሔርን ልጅነትና የዘለዓለምን ሕይወት አጥቶ የነበረው ሰው ልጅነቱና ሕይወቱ እንደተመለሰለት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ ተጠምቆ ልጅነትን፣ ደሙንም ጠጥቶ የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛልና (ዮሐ 3¸5፤ ዮሐ 6¸54)፡፡

8.     ተአሮተ ድኅሪት (ወደ ኋላ መታሠር)፤
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት እጆቹን ወደኋላ የፊጥኝ መታሠሩን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተአሥሮት›› የሚለው ቃል አሠረ (ሲነበብ ይላላል) ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አሠረ ማለት ነው፡፡ ‹‹ድኅሪት›› የሚለው ቃል ደግሞ ተድኅረ- ወደኋላ አለ ከሚለው ግሥ የወጣ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጊዜው በደረሰ ሰዓት ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ በሰጠባት በዚያች ዕለትና ሰዓት ሻለቃውና ጭፍሮቹ የአይሁድም ሎሌዎች እጁን የኋሊት አሥረው መሬት ለመሬት ጎትተውታል፡፡ አፍገምግመውታል (ዮሐ 18¸12)፡፡

በኃጢአት ሰንሰለት የኋሊት ታሥሮ ጠላት ዲያብሎስ የሚያፍገመግመውን የሰው ልጅ ለማዳን፣ ሰውንም ከኃጢአት እሥራት ይፈታ ዘንድ ሲል መድኃኔዓለም ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ የኋሊት ታሠረ፡፡

9.     አምሥቱ ቅንዋተ መስቀል፤
መድኃኒታችን በመስቀል ላይ የተቸነከረባቸውን ጠንካራ የብረት ችንካሮች (ምስማሮች) የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ቅንዋት›› የሚለው ቃል ቀነወ- ቸነከረ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ መስቀል ማለት ደግሞ ዝም ብሎ የቆመ ግንድ ሳይሆን አሁን በየሥፍራው እንደምናየው ምልክት የተመሳቀለ እንጨት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቸነከረባቸው አምስቱ ችንካሮች ሳዶር፣ አላዶር፣ዳናት፣ አዴራ፤ ሮዳስ ይባላሉ፡፡ እነዚህም የአምሥቱ አዕማደ ምሥጢራት ምሳሌዎች መሆናቸውን አበው ያስተምራሉ፡፡

ሐዋርያው ቶማስ ከትንሣኤ በኋላ ወንድሞቹ ሐዋርያት ስለ ትንሣኤው በነገሩት ጊዜ ‹‹የችንካሩን ምልክት በዓይኖቼ ካላየሁ፣ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላስገሁ፣ በእጄም የተወጋውን ጎኑን ካልዳሰስኩ አላምንም›› ማለቱ በብረት ቀኖት በመቸንከሩ ነበር (ዮሐ 2ዐ¸25)፡፡ መድኃኒታችን በኃጢአት ቀኖት (ምስማር) ተይዞ የነበረውን ሰው ለማዳን በብረት ቀኖት ተቸነከረ፡፡

እንግዲህ አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል የሚባሉት እነዚህ ናቸው፡፡ ድሀ ያይደለ ጌታ፤ ፍጡር ያይደለ የፈጠረውን ሥጋ ገንዘብ ያደረገ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ብሎ ተናቀ፡፡ የሕማም ሰው፤ ደዌንም የሚያውቅ ሆነ፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፡፡ ሕማማችንንም ተሸከመ፡፡ ይህም የሰውን ልጅ ለማዳን ማለትም እኛን ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ይፈውሰንና ከሕማመ ሥጋ ከሕማመ ነፍስ ሥቃይ ያሳርፈን ዘንድ ነው፡፡ ቁስለ ኃጢአታችንን ያደርቅልን ዘንድ ስለ መተላለፋችን ቆሰለ፡፡ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን፡፡ በደላችንን ይደመስስ ዘንድ ስለ በደላችን ደቀቀ፡፡ ሊያረጋጋን ተጨነቀ፡፡ ሊያሣርፈን ተሠቃየ፡፡ አፉንም አልከፈተም፡፡

የእግዚአብሔር የመሥዋዕቱ በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ መልካምን እንጂ ግፍን አላደረገም ነበር፡፡ ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ወሰብእ ወልድ ዋህድ ኢየሱስ ክርስቶስ በጲላጦስ በተመረመረ ጊዜ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም፡፡ በፈቃዱ ነፍሱን ስለ እኛ መሥዋእት አደረገ፡፡ ፋሲካችን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሥጋውን ቆረሰልን፣ ደሙንም አፈሰሰልን (ኢሳ. 53¸1-13፤ ዮሐ. 10¸18፤ ዮሐ. 19¸30፤ 1ኛቆሮ. 5¸7)፡፡ በዚህ የተቀደሰው ሳምንት ይህንን የጌታን ውለታና የድኅነት ሥራ እናስተውል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

Monday, 25 April 2016

FEREATEWAHEDO /ፍሬ ተዋህዶ: ድንግል ማርያም የውርስ ኃጢአት ይመለከታታልን?

FEREATEWAHEDO /ፍሬ ተዋህዶ: ድንግል ማርያም የውርስ ኃጢአት ይመለከታታልን?: ክፍል 3 ካለፈው  የቀጠለ ድንግል ማርያም የውርስ ኃጢአት ይመለከታታልን ?        ባለፈው የክፍል 1 እና ክፍል 2 ዝግጅታችን  ማስነበባችን ይታወሳል በገባነው ቃል መሰረት ቀጣዩን ይዘን  ቀርበናል መልካም ንባብ...

Saturday, 23 April 2016

የዛር መንፈስ

በማለዳ መያዝ ፦ምእራፍ -አንድ 1✿የክፉ መንፈሶች ድርጊት በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን ፡፡
✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿
"የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን">>ማቴ.16÷3 የክፉ መንፈስ ድርጊት ማለት ፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ፤በሰው አማካይነት ፤ሌሎችን ለመጉዳት ተብሎ ፤ ከአጋንንት ጋር የሚመሰረትና የሚደረግ ግንኙነት ማለት ነው፡፡ ክፉ መንፈሶች በሕይወታችን ፣በኑሯችንና በዘመናችን ውስጥ ጣልቃ በመግባት ፤ጉዳት የሚያደርሱ አደገኞች ይሁኑ እንጂ ፤የእግዚአብሔር አምላክ ጥበቃ እስካለ ድረስ ፤ የጥፋት አቅምና ኃይላቸው ፍጹም ውሱን የሚሆነው የእምነትና የአምልኮት ጥንካሬ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ዛሬ የክፉ መናፍስቱ ጥቃት ከመቼውም ጌዜ በበለጠ የተስፋፋና የተመቻቸ ፤ጉዳት የማድረስ ችሎታቸው ፤የዚያኑ ያህል የተጠናከረ ከመሆኑም በላይ ፤የህብረተሰብን ማህበራዊ አኗኗርን በመለማመድና በመመሳሰል የክፉ መንፈስ ጥቃት የረቀቀ ሥልታዊ ሆኖአል፡፡ ለእነዚህ የሰው ልጆች ጠላቶች ፍጹም መጠናከር ፤ ከፍተኛ ርዳታና እገዛ ያደረጉት ደግሞ ፤በሚያስገርም ሁኔታ ፤ ራሳቸው ሰዎች ናቸው ፡፡ እንዴት ? እስቲ ሁሉንም በዝርዝር እንመልከት ፦
<<እግዚአብሔር የደሚወዱትን ሁሉ ይጠብቃል ፤>> መዝ.144(145)20 1.1 የዛር መንፈስ ፤
✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿ ዛር የሚባለው ከዘር የተወረሰ ፤ከዘር የመጣ ፤በዘር የሚሄድ ማለት ሲሆን ፤ትርጉሙም ፤ለሰው ዘር ተመሳሳይ ተፈጥሯዊ ባህርይ ያላቸው ሁሉ ፤በዘር ውስጥ ማለፋቸውን የሚያሳይ ምልክት ነው፡፡የዛር አጋንንትና ሰይጣን በቤተሰብ ውስጥ ሲመለክና ሲገበር ቆይቶ ፤ከአምላኪዎቹ የሚወለዱት ልጆች ሁሉ ፤መንፈሱ አብሯቸው ተወልዶና አድጎ ፤መጨረሻ ላይ ፤የኔ ዘር ናቸው በማለት በኃይል ያርፍባቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ዲያቢሎስ ልዩ የሆኑ በአራት የተከፈሉ ዕቅዶች አሉት ፡፡ ☞የሰውን ሕይወት ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠርና መምራት ፤የሚሔድበትን አቅጣጫ መለየት ፤
☞በከፍተኛ ፍጥነትና ግፊት ዕቅዱን ተግባራዊ ማድረግ ፤ ☞የጥቃት አድማሱን ማስፋፋትና መገምገም ፤
☞ለጊዜው በአጥቂነት የሚጠቀምባቸውን ሰዎች መሳሪያዎቹ በማድረግ ፤የኢኮኖሚ አቅም ማጎልበት ፤ክብርና ዝናን ማጎናፀፍ ፤ሌሎች ብዙዎች የሚጠፉበትን መንገድ ማመቻቸት እና በተግባር መፈጸሙን ማረጋገጥ ነው፡፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የሳጥናኤል እቅዶች ሲሆኑ በአፈጻጸም ሂደት ውስጥ ለሰብአዊ ፍጡር መረጃ እንዲያገኝ ምንም አይነት ፍንጭ አይሰጥም ፡፡ የክፉ መንፈሶች የገሐዱ ዓለም ላይ በተጨባጭ ገጽታ አለመታየታቸው ብዙዉን የሰው ልጅ የትውልድ ህልውናን ሲፈታተኑ፤ ከመኖራቸውም በላይ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠውን ተስፋ ክብር ጸጋና በረከትና ምገስን እንዳያገኝ ለመፋለም የራሳቸውን ክፋትና ጥፋት መፈጸሚያ በማድረግ ሲጠቀሙበት ኖረዋል፡፡ይህንንም በቃየን ሕይወት ማየት ይቻላል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን የዛር ምልክት ለመጀመሪያ ጊዜ የታየውና ለዘር መበላሸት ምክንያት የሆነው ሰው ፤ ቃየን ነው፡፡ ቃየን ማለት ፤ከእብራይስጥ ቋንቋ ወደ አማርኛ ሲተረጎም ፤የጦር አበጋዝ ማለት ነው፡፡
የአቤልና የቃየን መስዋዕት በእግዚአብሔር ፊት
✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿ " እግዚአብሔር ወደ አቤልና ወደ መስዋዕቱ ተመለከተ ፤ ወደ ቃየንና ወደ መስዋዕቱ አልተመለከተም ፡፡" ዘፍ .4÷4-6 ቃየን እጅግ ተናደደ ፤ፊቱም ጠቆረ ፡፡ እግዚአብሔርም ቃየንን አለው ፤"ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅህ ታደባለች ፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፡፡ ግን በእርስዋ ንገስባት፡፡" አለው፡፡በዚህ የእግዚአብሔርን ቃል ውስጥ የተገለጸት ፤ ኃጢአት ታደባለች፡፡ ፤ፈቃድዋ እና በእርስዋ ንገስባት የሚሉት ሦስት ቃላት የሚያመለክቱት ፤የሴት ጾታን ነው፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፤ቃየን የሴት ዛር አጋንንትን በጥፋት መንገድ እርሱንና ትውልዱን ትመራ ዘንድ ነገሠችበት፡፡ የቃየን መስዋዕት የስስት ፤ የንፉግነትና እግዚአብሔር ን የማይፈራና የማያመልክ መሆኑን ዲያብሎስ ስለአወቀ ፤እርሱን ለክፋት ፤ለቅናት ፤ለንዴትና ለፊት ማጥቆር እርግማን በመሳሪያነት መግለጫው በማድረግ ምድራዊ የኃጥያት አሰራርና ምት በይፋ መንገድ አገኘ፡፡ በዚህ የተነሳም ፤ ንጹህ ወንድሙን አቤልን አለምንም በደል ፤ በጥላቻና በልበ ቂመኘነት ተነሳስቶ ፤ በድንጋይ ወግሮና ደሙን አፍስሶ ገድሎታል ፡፡
ስለዚህ የቃየን መንፈስ ፤የደም አፍሳሽነት ወይም የግድያ ወንጀል ጀማሪ በመሆን ፤ ዲያብሎስን የሰው ልጅ ዘር አጥፊነትን በገሐዱ አለም ያለ እድሜ መሞትን ማሳያ በማደረግ ተጠቀመበት ፡፡ደጉ፣ ብሩኩና ቅዱሱ ሰው አቤል በአምልኮቱ ምክንያት ምተ፡፡ አሁን መስዋዕቱን እግዚአብሔር የሚቀበለው ሰው የለም፡፡ ለአምልኮት ክብር የሚሰጠው ሰው በአጠቃላይ አምላክ የወደደው ሰው ፤ አቤል የለም፡፡ለምድር የቀረው በሕይወት ያለው ቃየን ነው፡፡ ወንድሙን ያሳደደ፤ ደሙን ያፈሰሰ ፤በድንጋይ ወግሮ የገደለ፣የተረገመው ቃየን አለ፡፡ቅናት ፣ተንኮል ፣ክፋትና ምቀኝነት መሠረታዊ በመሆን ዕድሉን ያገኙት፤ለመጀመርያ ግዜ በቃየን ሕይወትና ዘመን ውስጥ ነው፡፡ አዳም ከገነት መሸሽ ፣መራቆትና መደበቅ በነበረው አስፈሪና አሳዛኝ በሆነው ሂደት ላይ የቃየን ተግባር ወንድሙን በመግደል ሲጀመር ለቀጣዩ ትውልድ የግድያ አስተማሪነቱ ለዲያብሎስ አላማ ልዩ መርሆ ሆኗል፡፡ ይህ አለም ቃየንን ይወዳል ፡፡በዚህ ምድር ስትኖር ፤ስትወጣ ፣ስትገባ ፣ስትሰራ ፣ስትማር ፣ስታገኝ ፣ስትደሰት ሁሉ በመንገድህ ላይ ፤ከግራ ፣ከቀኝ ፣ከኀላ ፣ከፊት ፣ከላይ ፣ከታች ሳይቀር ፤የቃየን መንፈስ አለ፡፡
የእግዚአብሔር ቃልና የቃየን ድምፅ ✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿ <<እግዚአብሔርም ቃየንን አለው ፤ወንድምህ አቤል ወዴት አለ? እርሱም አለ ፤ አላውቅም ፤ የወንድሜ ጠባቂ እኔ ነኝ? አለው ፦ምን አደረገህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደኔ ይጮሀል ፡፡አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፏን በከፈተች ምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ፡፡ምድርንም ባረስህ ግዜ እንግዲህ ሀይሏን አትሰጥህም፡፡በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ፡፡>> አለው ዘፍ.4÷9 <<እግዚአብሔር ተናግሮአልና ሰማያት ስሙ ፣ምድርም አድምጪ ልጆችሽን ወለድሁ ፤አሳደግሁም ፣እነሱም አመፁብኝ፡፡>> ት/ኢ.1÷2
በአዳም፣ ሔዋንና በተተኪው ትውልድ ውስጥ የዲብሎስ አስተሳሰብ ጅማሬ
✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿
ንዴት ፦የጠብ መጀመሪያ አባት እንዲሆን በቃየን ሕይወት ዲያብሎስ ከመገለጹ በላይ ፤በወንድሙ ላይ የፊት ማጥቆርና የመቀየር ገጽን የአካል ክፉ ጠባይ ጽንሰ ሀሳብ የሚታይበት ሆኖ ቃየን እንዲገለጥ አድርጎታል ፡፡ በቃየን ሕይወት የተጀመረው ቅናት ፣ ንዴት ፣ክፋት ፣ተንኮል ፣ ምቀኝነት ፣ግፍ ፣ ቁጣ ፣ብስጭት ፣ቂም እና በቀል እነዚህ ሁሉ የዲያብሎስ ሀሳቦች እስከ ዛሬ ድረስ በሰው ልጅ ልብ ውስጥ መሠረታዊ የኑሮ አካል ሆነው ከመገኘታቸው በላይ ፤ ለዘመናት የሰው ዘርና ተፈጥሮን ሲያበላሹ የቆዩ የዲያብሎስ መርሆዎች ናቸው፡፡
በቃየን የተጀመረው የፊት ማጥቆር ጠባይ ዛሬም ብዙ ሰዎች ክፉ መንፈስ በውስጣቸው ሲኖር ይሄው ችግር ሙሉ በሙሉ ይከሰታል፡፡ ፊታቸውና ቋንቋቸዉ ይለወጣል ፣ይናደዳሉ ፣ይቆጣሉ ፣ ይራገማሉ ፣ያማርራሉ ፣ መንፈሱ ከተገለጠ ደግሞ ፣ ያጓራሉ ፣ወይም በጣም ይጮኸሉ፡፡ ግልፍተኞ በሆኑ ጊዜም የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ፣ቤተሰብንና በቅርብ ያለውን ሁሉ ሊጎዱ ይችላሉ ፡፡ደም ካላዩ የማይረኩና የማይበርዱ ይሆናሉ፡፡ ቃየንም ፣ጊዜያዊ እርካታ ያገኘው ወንድሙን ከገደለ በኀላ ነበር፡፡
የደም ፍርድና የግድያ ዛር
✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿
በቃየን የተጀመረው የግድያ ውሳኔ ለዲያብሎስ የጥፋትና የሞት አሠራር ዋና ግብ አድርጎት ፣የሰው ልጅን ወደምት የመምራት ስልጣን የማግኘቱ ውጤት አንዱ መንገድ ሆኖአል፡፡ ቃየን ወንድሙን የሚያስገድል መንፈስ ያዘው ፣ ደምን የሚያፈስ ፣ደም ማየት የሚወድ ከአዳም ቀጥሎ ሁለተኛ የኃጥያት የግድያ ወንጀል ጀማሪ እንዲሆን ሰይጣን ተጠቀመበት ፡፡
ስለዚህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ደም ማየት የሚፈልጉ ዛሮች የሰውን ልጅ በመቆራኘት ፣በዓለም የህብረተሰብ ባሕል ውስጥ በተለያየ መንገድ የደም መፍሰስ ፍላጎትን አዳበሩ በእንስሶች በዶሮ ፣ በበግ የሚረጋጉ ዛሮች በአገራችን ሰፊ ቦታ ነበራቸው፡፡ ያ ሂደት ተቀይሮ በምድራችን ላይ ለዘመናት ያልተቋረጠ የጦርነት ደም ሲፈስ መኖሩ የዛሮቹ ዕድገት መሳያ አንዱ ምልክት ነው፡፡ በአሁኑ ዘመን ያሉ ዛሮች የቀድሞ ጠባያቸውን ለቀው ዘመናዊ የአጠቃቀም ሥልት በመያዝ ሲማሩ መማር ፣መሪ ሲሆኑ አብሮ መሪ መሆን ፣በሥልጣን ፣በማዕረግና በሀብት አለመርካት የመሳሰሉ ጠንቆችን ሥር የሰደደ ባሕርይዎች እንዲሆኑ በማድረግ ለክፉ ተግባራቸው መገልገያ አድርገውታል ፡፡
ከማለዳ በዓመፅ ታሪክ ውስጥ መኖር
✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿
የዓመፅ ጅማሬ ታሪክ ሲነሳ፣ የቃየን መንፈስ በአመፀኝነት የፈጸመው የግፍ ግድያ ተግባር ፣ብዙ ደም በዓለም ላይ ላፈሰሱ ፣ግጭቶች የመጀመሪያው አባትና አስተማሪ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ካለፉት ብዙ ዘመኖች ውስጥ በዓለማችን ዙሪያ የተካሄዱ ጦርነቶችና እልቂቶች የዓመፃ ግፍ የአፈጻጸሙ ማሳያ ሆነው ፣ለአሁኑ ዘመን ትውልድና ርዕዮተ -ዓለም የሞት ማገናዘቢያ የጥፋት ልጅ ሆነው፣ዛሬ የሚረግሙት ፋሽስቶችና ናዚዎች በመባል እየታወሱ የጥላቻ ታሪክ ማንጸባረቂያ ሆነዋል ፡፡ በቃየን ዘሮች ውስጥ የተከሰተው የጦረኝነትና የጦር መሣሪያ ፍልስፍና ዛሬ አድጎ ወደ አቶሚክ ደምሳሽ ቦንብና ወደ ኑክሌር የጨረር ሞት የሰው ልጅ መድረስ፣ዲያብሎስን ለጥፋት ዓላማው የላቀ እርካታ እንዲያገኝ አግዞአል፡፡ሌላው የቃየን ዘር መንፈስ ፣ወንዝን ተከትሎ መኖርንና ፣የወንዝ ውኃ መንፈስን ማምለክ ፣መጠየቅና ማማከር ፣ከወንዝ አጋንንት ጋር መዳበልና መዛመድን የጀመረ ትውልድ ነው ፡፡ይህን ሂደት ለዲያብሎስ በሰው ልጅ ልብ ውስጥ ውጣውረድና ዓመፃ እንዲመሰረት ረድቶታል ፡፡ ስለዚህ የ21ኞው ክፍለ ዘመን ትውልድ የሰይጣን የክብረ በዓል ቀንን ያከብራል ፡፡"ሐሎይ" በመባል የሚታወቀው የሰይጣን ቀን ዓለማቀፋዊ በዓል እንዲሆን አንዳንድ አገሮች ወስነዋል ፡፡ስለዚህ አሰላለፉ ፣ሰይጣን ሰው ሰይጣን ሆኖአል ማለት ነው፡፡ የቃየን የመጀመሪያ ዓመፅ በብሉይ ኪዳን ውስጥ አልፎ ፣በአዲስ ኪዳን ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል ፤ሐዋርያትን በማሳደድና በመግደል ፣ከዛም ቤተክርስቲያንን በማቃጠልና ክርስቲያኖችን በመውረር ፣ጣዖታትን በማምለክ የነበረው የከሃዲነት መንፈስ አድጎ ፤ዓለም የዓመፃ ዘመን ላይ ደረሰ፡፡
ሰው እጅ ላይና ዲያቢሎስ ላይ የወደቀ ትውልድ
✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿
አቤል ያለእድሜው በወንድሙ እጅ ላይ ወድቆና ተወግሮ ደሙ ፈሶ ሞተ፡፡ በዚህም ዘመንና ጊዜ ብዙ ሰዎች ፤ የአገር መሪዎችን ጨምሮ ፤በሰው እጅ ላይ ወድቀው መገኘት ፤የተለመደ ችግር ሆኖአል ፡፡በስራ ፣በእውቀት ፣ በሥልጣንና በመርሐ-ግብር ፣በርዕዮተ ዓለም ጫና ፣በኢኮናሚና በተመረዘ የአስተሳሰብ ተጽእኖ ሥር መያዝ ወቅታዊ ክስተት ሆኖ ይገኛል ፡፡
የችግሩ አጣብቄም የፈቃደኝነት ግዴታና የግዴታ ፈቃደኝነት ውስጥ የመግባቱ ጠባይ ከሕልውና ጋር የተያያዘ እንዲሆን ገና ከማለዳ ክፉው መንፈስ የሚያዘጋጀው ሴራና ተንኮል እንደሆነ የዘመኑ ሳይንስ አልተረዳውም ፡፡ከዚህ ገጎን የማቴሪያልና የስነ-ጥበብ አምልኮት የዘመኑን ሊሕቃን በፍልስፍና ውስጥ እንዲደበቁና የማይታየውን የክፉ መንፈስ ዓለም እንዲዘነጉት በማድረግ ዲያቢሎስ ልዩ ሚና ተጫውቷል ፡፡ ብዙ የዓለም ምሁራኖች በግሪክ ሥነ-ቃል ተዋጽዖ የሳይንሳዊ ስያሜ ላይ ዕድሜያቸውን ጨርሰ ውና እምነት አልባ በመሆን ፤ በነፍሰ ሕይወት ተዋርደዋል፡፡ በጤናና በሕክምናውም ረገድ ተመሳሳይ ብዙ ስሕተቶች በዲያብሎስ በኩል ተተግብሯል፡፡እንግዲህ በዓለም ላይ ያለዉ ችግር ከመነሻው ብቻ ሳይሆን ከመድረሻዉ ላይ የክፉ መንፈስ ውስብስብ ፈተናና በሳይንስ የማይፈታ ችግር ሆኖ ይኖራል ፡፡
በቃየንና በዘሩ ውስጥ የኃጢአትና የሞት ንግስት ዛር ✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿~
"መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚያበራ አይደለምን ? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች ፤ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፤አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት፡፡ቃየንም ወንድሙን አቤልን ፤ና! ወደ ሜዳ እንሂድ አለው፡፡ሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሳበት ገደለውም፡፡" ዘፍጥረት .4 ፥7-8 ዛሬ መላውን ዓለምና የሰው ዘር ትውልድን እያናጋው ካለዉ ክፉ መንፈሶች አንዱ ፤የሴት ዛር የአያያዝ እሽቅድድም እየተጠናከረ መምጣቱ ነው፡፡ በቃየን ልብ ውስጥ ንግሥናን ያገኘችው የኃጥያት ዛር የሴት አጋንንትና ሰይጣን፤የሴትና የወንድ ግብረ-ሰዶማውያንን (የሌዝብያንና የሆሞዎችን)መብት ሕጋዊ የጋብቻ አካል እንዲሆን በማድረግ ፤ብዙ የክርስቲያን ልጆች ፤ልብና ሕይወት አግኝታለች ፡፡
አሰላለፏን ዘመናዊ በማድረግ እንደ ትውልዱ ጠባይና አስተሳሰብ ሥልቷን በመለዋወጥ ፤ትውልዳችን በክፉ አመልና ሱስ ከእምነትና ከአባቶቹ የሃይማኖት ሥነ-ምግባር እንዲ መጣ በማድረግ፡ ከክህደት ርዕዮት ውስጥ ወደ ኃጢአት ምት በመምራት ላይ ትገኛለች ፡፡
ከማለዳ መበላሸት ✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿
ቃየን በኃጢአት ላይና ሀጢያት በቃየን ላይ ከነገሰች በሁዋላ ኮብላይና ተቅበዝባዥ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ፡፡ዛሬ የእያንዳንዱ ቤተሰብ ልጆች ፤በዚች የኃጢአት ንግስት ከማለዳው ስለሚያዙ የራሳቸው ፍላጎትና አስተሳሰብ እየመሰላቸው በክፉ መንፈስ በሚከተሉት መንገድ ይመራሉ፡፡ ለምሳሌ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ፤በሱስ መንፈስ ለመያዝ በጣም የቀረበና የሰፋ ዕድል ያላቸው ሲሆን ፤ይህንኑ ክፉ የሱስ መንፈስን የሚያስፋፋ ፣የንግድ ቤቶች በየትምህርት ቤታቸው መግቢያና መውጫ በር ላይ ገበያቸውን በማደራጀት ፤ወጣቱ በዘመናዊ የጥፋት ሥልት ውስጥ እንዲገባ አድርገዋል ፡፡
ከመነሻው አዲሱን ተተኪ ትውልድ ከትምህርት ቤት ደጃፍ እየተቀበሉ ከሚያሰናክሉና ከሚያበላሹ የጥፋት መንገዶች መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት ፤☞
♦እንሞክረው ፤እንየው ፤ለጥናት ጥሩ ነው በማለት ፤ጫት አብሮም ሲጋራ ፤በመቀጠልም ሺሻ ፣ሐሺሽ ፣መጠጥ ወዘተ...ይጀምራል ፡፡ ♦ከአደንዛዥ ዕጾች በተጓዳኝ ፣የወሲብ ፊልምችን በጋራና በተናጠል በመመልከት ፤የኃጢአት ንግሥቷ ዛር በውስጣቸው ቤትዋን ትሠራለች፤ ♦የኃጢአቷን ንግስትየሚያበረታቱ ዘፈኖች ፤ከወሲብ ቀስቃሽ አለባበስ ጋር በመታጀብ ፤ልቅ የሆነ ጠባይ እንዲወርሱ ያደርጋል ፡፡ ♦የሚያስፈሩና የሚያሰቅቁ (ሆረር) ፊልምች ውስጥ ፣ደም የሚመጡ የሰው ፍጡሮችን ፣ቤት ፣መንገድ ፣ ንብረት ፣በፈንጂና በሮኬት ፣በአውሮፕላን ድብደባ ሲወድም ፣የሰው ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ሲያልፍና አካሉ ሲጓድል በማሳየት ፤ዕድሉን ከፊልሙ ጋር እንዲያያዝ አድርገው እያደር የወደፊቱ እጣ ፈንታው በመንፈሱ ወይም በመንፈስዋ እንዲወሰን መንገድ ይጠርጋል ፡፡ከዚህ በኋላ ትውልዱ ጥፋትን አይቶና ተምሮ በመንፈሱ ተገዶ ክፋትን ቢሰራና ቢፈፀም ፤የሚያስቆጭና የሚያስገርም አይሆንም ፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ የጥፋት መንገዶችም እንደቀልድና እንደ ዋዛ ፤ከዘመናዊነት ውስጥ በመመንጨት ፣ትውልዱን ወደ ተበላሸ አቅጣጫ ሲወስዱት ብዙ ጊዜ ተስተውሏል ፡፡ይህ ሁሉ የመናፍስቱ ድርጊትና የጥቃት ሥልት መሆኑ በአንክሮ ሊታወቅ ይገባል ፡፡ ♦በኃጢአት ንግስት ዛር የተለከፉ ሰዋች ሁሉ ፤ያዩትንና የሰሙትን ፣ያደረጉትንና የፈፀሙትን ፣ወደ ማዕረግ እና ወደ ሥልጣን በማዉጣት ፤ከመልካም ነገር ይልቅ ፤ክፋትን በማበረታታት ፤ክፉዋንና ክፉውን መንፈስ የሚጠቅሙ አገልጋዮች ይሆናሉ ፡፡
♦ በዚህ ክፍለ ዘመን ያለው ትውልድ ፤ከትምህርትና ከእውቀት ጋራ በተያያዘ ሁኔታ ከሚገጥሙት ፈተናዎች መካከል ፤በኢንተርኔት ላይ ያለ ስራ ተጎልቶ በሚጨርሰው ሰፊ ጊዜ የተነሳ ፤በዓይን የሚያርፉ የሱስ መንፈሶች በላቀ ሁኔታ እየተጠቃ የመገኘቱ ሁኔታ አንዱ ነው፡፡
እነዚህ በኢንተርኔት ማለትም በምስጢራዊ የአጋንንት አምልኮት ስር የሚለቀቁ የመንፈሱ የአስተሳሰብና የክህደት ፤ዘዴዋች፤የሳይኮሎጂ ፤የስሜት ፤የወሲብ ፤የአስትሮሎጂ ፣ወዘተ....ተዋጽኦዎችን በሙሉ የ ሚያጠቃልሉ ሲሆን ፤በምንሰጣቸው ከፍተኛ አትኩሮት እና ተመስጦ የተነሳ የሚገቡ መንፈሶች ናቸው ፡፡ብዙ ጊዜ በኢንተርኔት ላይ ያለ ተጨባጭ ስራ ተጎልተው የሚያሳልፉ ሰዎች፤ልክ እንደ ካርታ ሱስ ውለው ቢያድሩበት አይሰለቹም ፡፡አንዳንዶች ውለው እንዳደሩበት ምን እንዳዩ እንኳን ሲጠየቁ ፤አስታዉሰው ለመናገር ያዳግታቸዋል ፡፡
✿በዚህ በኢንተርኔ ሱስ የተለከፉ ሰዎች ፤በሳይንሳዊ ትንታኔ ሕብረተሰቡንና ቤተሰባቸውን ግራ በማጋባትና በማስቸገር ፤ሌሎችን ከእምነት ጎዳናና አንባ ለማስወጣት፤በንቀት ቋንቋ የሚናገሩ፣የሚተቹ፣የሚቃወሙ፣የሚያፌዙና አዋቂ ሆነው ለመቅረብ የሚጥሩ፣በአጠቃላይ፤ክፉው መንፈስ የሚመላለስባቸው ማደሪያው ይሆናሉ ፡፡
ይህ የሚያመለክተን፤ክፉ መንፈሶች የዘመኑን የእውቀትና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም፤በረቀቀ ጥበብ፣ከእግዚአብሔር መንገድእንዴት እነደሚያርቁ፣የሞትና የነፍስ ጉዳት በማድረስ ላይ የሚገኙ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን፤ኢንተርኔትን ጨምሮ ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሙሉ፤ማለት ሳይሆን በዚህ ረገድ ኃጢአትን የሚያበረታታውን ፤ነዉርና ከሞራል ሥነ-ምግባር የወጣውን፣በአጠቃላይ ክፉ መንፈስ የሚመራውንና ከእግዚአብሔር ሕግ የወጣውን፤በተለይ በኢንተርኔት የሚለቀቁትን የክፉ መንፈስ መልዕክቶችን አሉታዊ ተፅእኖ ለማመልከት ነው፡፡በአጭሩ፤ኢንተርኔት የሚጠቅመንን ያህል፤በዚህ መንገድ ከተጠቀምንበት ደግሞ፤ሊጎዳን እንደሚችል የሚጠረጠር መሆን የለበትም፡፡ የሚፈውስ መድኃኒት እንዳለ ሁሉ፤የሚገድልም መድኃኒት አለ፡፡ብርሀን እንዳለ ሁሉ ጨለማም አለና !፡፡
እንዲህ አይነት ችግሮችን በዘመናዊ መንፈስ ተጽእኖ ያዳበሩ ሰዎች ባሉበት አካባቢና መንደር የሚወለዱ ልጆች፤ወላጆቻቸውን ጨምሮ፤ጭንቀት፤መረበሽ፤የልብ መደንገጥ፣እንቅልፍ መጣትና መቃተት፣ጠብና ሳያውቁት መነጫነጭ፣መበሳጨትና ግልፍተኛ መሆን፣እቃ መስበር፣መግዛትና ደግሞ መስበር፣በድርጊቱ መርካት፤የባልና ሚስት መለያየት መበጣበጥና መጯጯህ፤ሌሊት ሳያውቁት በር ከፍቶ መውጣት፣ገንዘብን ከቦርሳ አውጥቶ መጣል፣ቀንመደበትና ሌሊት መንቃት፣ሞትን መፈለግና በተቃራኒው ማማረር ወዘተ............መንፈሱና ሰዎቹ ያሉበት አካባቢ መለያ ባሕርይ ነው፡፡
በአካባቢው የሚወለዱ ልጆች ጠባይ
✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿
በአብዛኛው ቅብጥብጥ፣ትምህርት የማይወዱ፣የአመጋገብ ፍላጎታቸው የተዘበራረቀ፣አንድ ጊዜ ከአቅም በላይ የሚበሉ ሲሆን፤በሌላ ግዜ ደግሞ ምንም የማይቀምሱ፣ስማቸውንም ቤተሰባቸውን የሚረሱ፣ደንታ የሌላቸው፣መፍዘዝና ግራ መጋባት የሚታይባቸው፣እንዲሁም እሺን የማያውቁ ሁል ግዜ የአፍ መፍቻቸው እንቢ ወይም ኖ(NO)ብቻን የሚናገሩ፣የማይታዘዙ፣የማይደፈረውን የሚደፍሩና የማይናቀውን የሚንቁ፣በአንጻሩ ደግሞ፤የሚናቀዉና የሚደፈረው የሚከብዳቸው፤ተቃራኒ ጠባዮች የሚስተዋልባቸው ይሆናሉ ፡፡
ፊልም ማየት የሚወዱ፤ለብቻቸው በህልም መንፈሱ ወሲብን ሲያስተምራቸው የሚያዩ፤ገለልተኛና ብቸኝነት የሚመቻቸው ሆነዉ፤ከነበረው ትውልድ ወጣ በማለት በአካልና በአስተሳሰብ የተለዩ ሆነው ይወለዳሉ ፡፡
ቃየንና የቃየን ቤተሰብ ውጤት
✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿
የቃየን ንፉግና በረከተ-ቢስ፣ፍቅር አልባና ፣የአስተሳሰብ ክፉነት ለራሱና ለትውልዱ ብዙ መዘዞችን አስከትሏል ፡፡
♦በቃየን ሕይወት ውስጥ ትልቁ ችግር የፍቅር መንፈስ ማጣትና አለመገለጥ ነው፡፡ለጠብና ለተንኮል፣ግፍና ግድያ ወዘተ... ለመሳሰሉት የወንጀል ጀማሪዎች መከሰቻ ሆኖአል ፡፡
♦ፍቅር መልክ የሚይዘውና ውበት የሚያገኘው ሁል ግዜ ከእግዚአብሔር ንጹህ አምልኮት ጋር ሲሆን ብቻ ነው፡፡ከዚህ እውነት ከወጣ ግን ፍቅር ሚዛኑንና አቅጣጫውን በመሳት፤የመዘበራረቅ ዕድሉ እጅግ የሰፋ ነው፡፡በቃየን ሕይወት ውስጥ የታየው ፤ፍቅር፤ የጦርነት የዘፋኝነትና ከቦታ ቦታ መንከራተት፣ የወንዝ ውሀ መንፈስ የተጀመረበት ፣ የባዕድ አምልኮትና የኃይል ኑሮ ትውልድ የበቀል ሞት አስተማሪ በመሆን የአሳቹን መንፈስ አገልግለዋል ፡፡
♦በዚህም ፤አስተሳሰብ ፤ገሐዳዊውን ዓለምና የባለ አስተሳሰቡን ሕይወት ፣ኑሮና ትውልድ የሚወስን እንደሚሆን ከቃየን መገንዘብ እንደሚቻል ግልጽ ነው፡፡ ቃየን በወንድሙ ላይ በጥላቻ በመነሳት የውስጥ አስተሳሰብ ሂደት ያመጣው ውጤት ፤ ወደ ክፉ አምርቶ ፤ሽፍትነትን ፣ውንብድናን ፣ስደተኛነትን ፣ኮብላይነትና ክዳትን እንዲሁም ፤ከእግዚአብሔር እምነትና አምልኮት የራቀ ትውልድ ጠባይ እንዲሆን ዓይነተኛ ገጽታ ሆኖ እየኖረ ነው፡፡ ለክፉ ተግባር በመነሳሳት ግፊት ውሰጥ ክፉው መንፈስ በአዳም ልጅ በቃየን ላይ ዕድል በማግኘቱ ፤ጥፋትን ለመግለጥ ተጨማሪ መነሻ መንገድ እንዲያገኝ ረድቶታል ፡፡
የቃየን ገጸ ባሕርይ ለክፉው ዓለም
✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿
ዛሬ በዓለም ላይ ካለው የንፉግነት የውስጥ አስተሳሰብ በብዛት ተከስቶ የሚታየው በእግዚአብሔር ስም የሚደረጉ ክንውኖች ናቸው፡፡ እነዚህም በጎነት ማጣትና የእምነት ዋጋን ከነ ጭራሹ በመተው ፤በመርሳትና በመዘንጋት መካከል በሕልውና ውስጥ የበረከት ጅማሬ በአምላክ እንዳይመጣ ማገጃ እንቅፋት ከመሆኑም በላይ ፤የኑሮ ተስፋና የትውልድ ሰማያዊ ሥጦታ ላይ ሁለንተናዊ እጦትን እንዳመጣ በቃየን ሕይወት መማር ይቻላል ፡፡
ቃየን ለእግዚአብሄር የአምልኮና የክብር መስዋዕት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነ ፤የመጀመሪያው ንፉግ ሰው በመሆን ፤የጉልበቱ ዋጋ በእምነት መስዋዕት በኩል አልተገለጠም ፡፡ስለዚህ ቃየን በየትኛውም ትውልድ ላሉ ንፉግ ሰዎች ምሳሌ በማድረግ ፤ዲያብሎስ የመቅኖ-ቢስነትን አኗኗር በዓለም ላይ ገልጦበታል፡፡
የበረከትን ጣዕም አለማወቅ በሰው ልጅ ዘር ውሰጥ አንድ ብሎ የጀመረው በቃየን ሕይወት ውስጥ ነው ፡፡ ቃየንና ዘሩ ዕድሜያቸው ያለቀው በረከትን ለማግኘት በራሳቸው ዘዴና ጥበብ ሲፈልጉ ፤ በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ በመሆን ፤ዕድል አግኝተዋል ፡፡
በእግዚአብሔር ያልተጠበቀ በረከት ፣ፍላጎትና ተግባር ፣ያልተቀደሰ ትውልድ ምልክቱም እነደ ቃየን በመንፈሳዊ ሕይወት መቅበዝበዝ መሆኑን ለዓለም ምልክት የጥፋት አርዓያ ሆኖአል ፡፡
የካደው ትውልድ ቋንቋ
✿✿✿✿✿✿✿✿✿
"አላውቀውም ፤የወንድሜ ጠባቂ እኔ ነኝን" የሚለው የቀደመው ቋንቋ በዚህ ዘመን ይንጸባረቃል፡፡ ጾም ጸሎት አላውቅም ፤የአባቶቻችንን መንፈሳዊና ሥጋዊ ታሪካቸውን እንዲሁም ተጋድሎአቸውን አላውቅም ፤እኔ የነሱ ጠባቂ ነኝን? የሚለው የቃየን ቃል ፤ዛሬም ይሰራል ፡፡
ይህ የዛር እልህ ፣የደም እርግማን ፣የወንጀል ጩኸት ፤የአሁኑ ዘመናችንን እያሳየና በግልፅ እየመሰከረ ነው፡፡ጻድቃንና ቅዱሳንን አላውቅም የሚለው የመናፍቁ መንፈስ አንዱና ዋናው የዚህ የካደው ትውልድ ቋንቋና መግለጫ ነው፡፡
የቃየን መሸበር ፤
✿✿✿✿✿✿✿
"ቃየንም እግዚአብሔርን አለው ፦ኃጢአቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት ፡፡እነሆ ዛሬ ከምድር ፌት አሳደድኸኝ ፤ከፊትህም እሰወራለሁ ፤በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ ፤የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል ፤ "አለ፡፡
መላው ክርስቲያኖች ሁላችንም ፤ማስተዋልና መገንዘብ ያለብን ፤የዛሬ አብዛኛው ስራችንና ግብራችን ከሀጢአት ነጻ ስላልሆነ ይህ ድምፅና ኡኡታ ፤የቃየን ብቻ አለመሆኑ ነው፡፡
አሁን አቤል የለም ፤የማይራራውና "አላውቅም ፤የወንድሜ ጠባቂ እኔ ነኝ?"ያለው ቃየን ነው፡፡ ዛሬ ቃየን በሕይወት ባይኖርም መጥፎ ድርጊቱ እየተወራረሰ አሁን ድረስ በምደባር ላይ ነግሦአል፡፡ዛርን መውረስ ማለት ይህ ነው፡፡ የቃየን ዘር፤የጦርና የሙዚቃ መሳሪያዎች ጥበብ ከጦርነትና ከወንዝ አምልኮት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተበት ፤ደም አፍሣሽ ነገድ ነው፡፡የእርግማኑም ቃል ፤
"ቃየንን ሰባት እጥፍ ይቀበሉታል ላሜሕን ግን ሰባ ሰባት እጥፍ፡፡"ዘፍጥ ፤4÷24 ይህ የጦርነትና የደም ዛር ነው፡፡
"ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል ፡፡" ማቴ 16÷4
የአካባቢ ሥሞችንና የሰዎችን መጠሪያ፤የወረሱ የዛር የንግስና ሥሞች
❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀❀
በደጋና በበረሀ የወደቁት የአጋንንትና የሰይጣን የዛር መንፈሶች የሰዎችንና የአካባቢ ስሞችን እየወረሱ፤በሰዉ ዘር ላይ የተሾሙ ናቸው ፡፡
ዛሮች በተለያየ አካበቢዎች የተለያዩ ስያሜዎን የያዙ ይሁኑ እንጂ ፤በያዙት ሰዉ ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖና ጉዳት በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው፡፡
በአገራችን ከሚገኙ የዛር የንግሥና ስሞች መካከል ፤ሙጨ ዘሪጋ ፣አዳኝ ወርቁ ፣ሐጎስ ፣ጎለም እሸት ፣ጨንገር ፣ሰይፉ ጨንገር ፤የሚባሉት የዛር መንፈሶች በዋናነት የሚወዱት ግብር ፣እንሾሽላ ፣ወርቅ ሽቶ ፣በተመሳሳይ ሰከት ቡና ማፍላት ፣ጌጣጌጥ ፣በጣም የደመቀ ቀለም ያለው ልብስ መልበስ ፣ዘፈንና ከበሮ መምታት ነው፡፡
ጠቋር ፣አዳል ሞቲ ፣ወሰን አጋጅ ፣ወሰን ገፊ ፣ወሰን ራሔሎ ፣ሻንቂት ፣ሻንቆ ፣ ሃደ ሐሮ ፣ሃደ አባይ ፤አባ መጋል ፣ሼህ አንበሶ ፣ነቢ ጅላሌ ፣ብር አለንጋ ፣ገውዘ ላዝም ፣ሻንቆ አባዲና ፣አርዱላ ፣99 መሊካ ፣ሞቲ አረቢያ ፣ግራኝ አባ ጉግሳ ፣አላቲ ፣ሪሣ ፣ኦፋ አቡኮ ፣ ኦፋ ጨፌ ፣ ኦፋ ለገሰ ፣ ኦፋ ደመና ፣የታዬ ከራማ ፣የአሩሲዋ እመቤት ፣ቡሎ ገርቢ ሣማ ቀልቢ ፣ አርሜት ፣ድማሜት ፣ሙሄት ፣አብድር ቃዲር ፣ዋቅ ፣ቦዥና ጨሌ ፣የወሎ ክብሪት ፣ቤሩድ ፣ሼህ ወልይ ፣የጠረፏ ንግስት ፣አዬ ሞሚና ፣አቴቴ ዱላ ፣አውሊያ ከራማ ፣አውሊያ ሼክ ሁሴን ፣ጅላሌ አብዱል ቃድር ፣ ተኮላሽ እያሱ ፣በረኸኛ አጋንንቶች ማለትም ፤ወሰን ገፊ ፣ አዳኝ ሱማሌ ፤ ቆሌ አዳኝ የልክፍት ዛር ፣ቦረንትቻ ፣አሞር ፣ ውቃቢ ፣ወዘተ.......የንግሥና ስሞች ናቸዉ፡፡
የመናፍስቱ ሥያሜ ፣ ሥምሪትና ጥቃት ፤በዋነኛነት ሥያሜያቸውን ባገኙበት አካባቢ አይሎ የሚገኝ ቢሆንም ፤በተለያየ ምክንያቶች ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወራቸው የተነሣ ፤በሰሜን ያለው መንፈስ ፤ በደቡብ ፤በምዕራብ ያለው ፤ በሰሜን ፣ በመሐል ያለው በምስራቅ ወዘተ...ሊኖር ይችላል ፡፡
የዛር መንፈሶች ለሰዎች የሚያወርሱዋቸው አጠጠቀላይ ጠባያት
✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿✿
በየሰአቱ የሚቀያየር ጠባይና የተደበቀ ስውር ሰው መሆን ፤ውስጥ ውስጡን መሸመቅ ፤እልኸኝነት ፣ወይም ከሚገባው በላይ ግልጽ መሆን ፤ብዙውን ጊዜ በንዴት በብስጭት ጊዜውን ማሳለፍ ፣በር ዘግቶ በጨለማ መቀመጥ፣ ለብቻ ማልቀስ ፣ወሬ ማናፈስ ፣ ነገር ከያዘ አለመልቀቅ ፣ የአመል ግትርነት ፣የእግዚአብሔር ሰዉ መጥላት ፣ ማሳደድ ፣ ደምን ማፍሰስ ፣ ደም ሲፈስ ማየት ፣ ተበቃይ ፣ ቂመኛ ፣ አመፀኝነት ፣ መጋደል ፣ ሌላውን በክፉ አይን ማየት ፣ በተለይም በሌላው ኑሮና አምልኮት ፣ በእግዚአብሔር ጸጋና ሞገስ መቅናት ፣ በሌላው እድገት ፊትን ማጥቆር ፣ ስም ማጥፋት ፣ መተቸት ፣መቃወም ፣ ማፌዝ ፣ መሳደብ ፣ መራገም ፣ሐሜት ፣አሽሙር ፣መራራ ቃል መናገርና እንደሱስ መሆን ፣በገንዘብ ፣በሥልጣንና በጉልበት መሳሪያነት መተናኮል ፣ለሌላው ውድቀትና ሞት መመኘት ፣ለማጥፋትና ለማውደም መቸኮል ፣የሌሎችን ኪሳራና ውድቀት በማየት መደሰት ፣ሃይማኖት መለዋወጥና የእምነት አለመኖር ፤ ወዘተ...የመሳሰሉት ሁሉ ፤ዛር ያለባቸው ሰዎች የተለመዱ ጠባያት ናቸዉ ፡፡
የዛር መንፈሶች በአብዛኛው ተመሳሳይ ጉዳት የሚያደርሱ ቢሆንም ፤በዋነኛነት ግን ፤ ከማሕፀን ጀምሮ ለልክፍት የሚሆኑ ፣ የሰው ልጆችን ፤ ከርታታ ፣ባካኝ ፣ሰርቶ መና የሚያደርጉና የመከራ ኑሮን የሚያወርሱ ናቸው፡፡
የዛርና የውቃቢ የውርስ መንፈሶች ፤ሌሎች ወደ ሰዎች የሚላኩ የዲያብሎስ መንፈሶችን ፤በመሳብና በፍጥነት ተቀብሎ ቦታ ሰጥቶ በማስተናገድ ፤ በውስጣችን ሰይጣንን አሰባስቦ በማደራጀት ሰፊ ጠባያቸውም ፤ይታወቃሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱን አዳኝ ወርቁ የተባለውን መንፈስ ፤ በምሣሌነት እንመልከት ፡፡
አዳኝ ወርቁ
✿✿✿✿✿✿
መልካም መዓዛ ያለው ሽቶና እጣን ፤ ከጌጣጌጥ ወርቅ በብዛት የሚወድ ሲሆን ፤ መልክና ውበት ያላትን ሴት ከሌላ ወንድ አስቀድሞ ለራሱ እንደ ሚስት ስለሚይዝ ፤ የዚህ መንፈስ ሰለባ የሆኑ ብዙ ሴቶች ባል አያገቡም ፤ አይፈልጉም ፡፡
ስለዚህ የባል ፍቅርን ሳያዩ ፣ ልጅም ሳያምራቸው ፤ የቤተሰብ ኃላፊነት ሳይሰማቸው ቀርቶ ፤ ዘመናቸውን ከመንፈሱ ጋር ይጨርሳሉ ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ፤ ልጅ የመውለጃ ዕድሜያቸው ካለፈ በኋላ በተቃራኒው ፤ መንፈሱ በውስጣቸው ልጅ መውለድ እንዲያምራቸውና ፤ እንዲጓጉ በማድረግ ፤ የቁጭት ስሜት ያሳድርባቸዋል ፡፡ በዚህም የተነሣ ፤ ውስጥ ውስጡን እየተብከነከኑና ፤ በመካንነታቸው እያዘኑ ፤ ፈጣሪ አምላካቸውን እያማረሩ እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል ፡፡ የክፉው መንፈስ ዋንኛ አላማ ፤ ሰዎች በሕይወታቸው እግዚአብሔርን እንዲያማርሩ ስለሆነ ፤ በዚህ በኩል የሚያደርገው እንረቅስቃሴ የተቃና ይሆንለታል ፡፡
የአዳኝ ወርቁ ዛር ጠባይ ፤ ሴት ልጁን ያኳኩላል፣ ወርቅ በጸጉርዋ ፣ በአንገትዋና በጆሮዋ ፣በእግርዋና በእጅዋ ላይ ያበዛል ፡፡ ራሱም ልዩ ውበት የመስጠት ኃይል ያለው ሲሆን ፤በገሃዱ ዓለም ያለ ሌላ ወንድ ሲጠጋት ወይም ሲያያት ይማረክባታል ፤ የሩካቤ ፍላጎትም እንዲሰማው ያደርጋል ፡፡ ይሁን እንጂ ፤ በአብዛኛው ሴቲቱ ከወንድ ጋር ለመሆን አትፈልግም ፡፡
መንፈሱ ከብዙ ወንዶች ጋር የሚያገናኛት ቢሆንም ፤ ከሁሉም ጋር አያግባባትም ፡፡ ምክንያቱም ፤ ደም ስለሚፈልግ ፤ ከሁለቱ አንዱን ወይም ሁለቱም በማጋጨት ብሎም ለማጋደል ስለሚፈልግ ነው፡፡
ባለጸጋዎችን ፣ ሾፌሮችን እና ነጋዴዎችን ወዘተ...በመጥለፍ ገንዘባቸውን ይሰልባቸዋል ፡፡ልባቸው ላይ መልኳንና ውበቷን ያስቀምጣል ፡፡ እስኪያገኟትም ድረሰ ፣እንቅልፍ ይከለክላቸዋል ፤ ይረብሻቸዋል ፡፡ አንዳንዶቹ እስኪያብዱ ድረስ ይፈትናቸዋል፡፡
ይህ እንግዲህ መንፈሱ ሴቲቱን በሃብት ለማበልፀግ የሚሄድበት መንገድና ለኃጢአት አሰራሩ የሚጠቀምበት ዘዴ ነው፡፡
እንዲህ ዓይነትዋ ሴት አንዱን ቀን ፤ ለተማረከባት ፣ ሀብቱን ላፈሰሰባት ወንድ ስትሰጥ ፤ ሁለት ወይም ሶስት ቀን ደግሞ የመንፈሱ ተራ ይሆናል ፡፡ ይህ ፤ ከመንፈሱ ጋር የምትገናኝበት ጊዜ መሆኑ ነው ፡፡
በዚህ ወቅት ዕጣን ፣ ሉባንጃ ፣ሽቶ የመንፈሱ አልባሳት ሁሉ ሳይቀር ይዘጋጃል ፡፡ የሚጠይቃቸው የግብር ዓይነቶች ሁሉ ከተሟላ በኋላ ፤ በነጋታው ገንዘብ የሚያፈስላትን ሰው ያዘጋጅላታል ፡፡ የሰውየውን አቋም ፣ ተክለ-ሰውነት ፤ መልክና ውበቱን ፤ በሕልሟሙዋ አስቀድሞ ሊጠቁማትም ይችላል ፡፡
ሌላው ጠባዩ ፤ዓይን ለዓይን በመተያየት ፣ በድምጽ (በስልክ ውስጥ የመሚደረግ ንግግርን ይጨምራል ) ፣ሰላምታ በመጨባበጥ ፤ በልብስ በመነካካት ወዘተ...ሁሉ ሳይቀር ፤ የፍትዎት ስሜትን ያነሣሣል፡፡
በአብዛኛው ከተለመደው የተፈጥሮ ባሕርይ ወጣ ያለ የወሲብ ስሜትን ሚፈጥረው ክፉ መንፈስ መሆኑን ብዙዎች አይገነዘቡትም፡፡
ለምሳሌ ፤ አስገድዶ የመድፈር ጠባይ ፤ የዚህ የዝሙት መንፈስ አንዱ አካልና መገለጫ ነው፡፡
ለመለያየት የሚጠቀምበት ዘዴ
✿✿✿✿❀❀❀❀✿✿✿✿❀❀❀❀
ከጊዜ በኋላ ሴቲቷን የተጠጋው ፤ ሰው የማያቋርጥ ከባድ ራስምታት ፤ ሆድ መንፋት ፣መደበት ፣ ማስጨነቅ ፣በመሳሰሉት አስቸጋሪ ጠባያት፤ አማሮ ሊያባርረው ይችላል፡፡
የተለያየ አካላዊ አደጋም ያበዛበታል ፡፡ ጠቋርን የመሰለ ዛር ከሆነ የግሞ ፤ ከቅናቱ የተነሳ ፤ሕይወቱን ሊያጠፋው ሁሉ ይችላል ፡፡ ሌላው በመንፈሱ የመገለጫ ጊዜ ፤ ለእርስዋ በመኝታ ላይ ልታየውና ልትዳስሰው እንዲሁም ፤ ሌሊት ክንድዋ ልታገኘው ትችላለች፡፡
በዚህ መንገድ ብዙ ሴቶች የመንፈሱን ሩካቤ ያፈቅራሉ ፡፡ከባል ጋር ግንኙነት ባያደርጉ ፈቃዳቸው ነው፡፡በተለያየ ምክንያት ግንኙነት ቢፈጽሙ እንኳን እርካታ አይኖራቸውም ፡፡በዚህ ግንኙነት የሚፈጠሩ ልጆች ጀግም ፤ በተፈጥሮና በአስተሳሰብ የተጎዱ ሆነው ይወለዳሉ ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፤የቡዳ መንፈስ አስተላላፊዎች በመሆን ፤የሌሎችን ሕይወት ይጎዳሉ ፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ፤ ከተኙበት ሲነቁ ግን ፤ አቅፈዉ የተኙትን መንፈስ ገጽታ ፤ በዓይነ -ሕሊናቸው ሲያስታውሱት ፤ከባድ መንፈሳዊ ቀውስ ውስጥ በመግባት ፤ ከፍተኛ የሆነ ፍርሀትና ጭንቀት እንዲሁም ሽብር ውስጥ ይገባሉ ፤ ይወድቃሉ ፡፡
በተለይ ይህንን ሁኔታና ሥቃያቸውን ለሌላው ሰው ለመንገር ሥለሚያሳፍራቸው ፤ ውስጣቸው እንደቆሰለ ይኖራሉ ፡፡"ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ፤ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል ? ወይስ ሰው ስለነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል ?" ማቴ. 16÷26
ሾተላይ የዛር የመተናኮል የውርጃ መንፈስ ፤
✿✿✿❀❀❀✿✿✿❀❀❀✿✿✿❀❀
ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት ዛር ሾተላይ በመሆን ፤ እርግዝና ላይ አደጋ የመፍጠር ችሎታ የሚኖረው ሲሆን ፤ተተኪ ትውልድን በማጨንገፍ የሚረካ ፤ የሰው ደም በማፍሰስየሚደሰትና የቤተሰብን ሐዘንና ለቅሶ ፤በልጅ ማጣት መቸገራቸውን እያየ እንደ ድል የሚቆጥር ፤ ስውር እልኸኞ የዛር መንፈስ ነው፡፡
የዛር መንፈስ ከማህጸን ጀምሮ ያለው፤ ሌላ ጥቃት ፤
✿✿✿❀❀❀✿✿✿❀❀❀✿✿✿❀❀❀✿✿
ከማሕጸን የሚወረሱ የዛር መንፈሶች ፤ የእናትና የአባት የመንፈሰ ጉዳቶች በዋናነት ያስከትላሉ ፡፡
ሀ. መካን(መኻን) ማድረግ
ለ. በሚወለዱት ሕጻናት ላይ ፤ የአእምሮም ፣የጤና፣እንከንና የአካል ጉዳት መፍጠር ለምሳሌ ፤፦የዛር መንፈስ አንዳንድ ሕጻናትን የአካል ጉዳተኛ ፣ የአእምሮም ዘገምተኛ ወዘተ...ከማድረጉ በተቃራኒው ፤ ያለዕድሜ ደረጃቸው እንዲያስቡና ሥራቸው ሁሉ ፤ እንደ ትልቅ ሰው እንዲሆን ያደርጋል፡፡
ብዙ ጊዜ እንደነዚህ አይነት ሕፃናት ፤ አስተሳሰባቸው ፤ እድሜያቸው ከሚሸከመው በላይ ስለሚሆን ፤ ረዥም ዓመት በሕይወት የመቆየት ዕድላቸው የመነመነ ነው፡፡
ሐ. የሚወለዱትን ልጆች ባሕርይ ማበላሸትና መጥፎ ጠባይን ማውረስ ፤
መ. ያለዕድሜ ፤ተፈጥሯዊዉን የወር አበባ ዑደትን ማዛባት ፤ ማለትም✿ ፤ ሴት ሕፃናት ገና ለአቅመ ሔዋን ሳይደርሱና ጡት ሳያወጡ ፤ በስምንትና በዘጠኝ ዓመት ዕድሜያቸው በሚያስደነግጥ ሁኔታ የወር አበባ እንዲያዩ ያደርጋል ፤
✿ ሴት እህቶች ደግሞ ፤ ባልተለመደና በማይጠበቅ ሁኔታ ፤በአብዛኛው በሰላሣና በሰላሣ አምስት ዓመት ፤ እንዲሁም አስከ አርባ ዓመት ዕድሜ ክልል ላይ ሲደርሱ ፤ የወር አበባ ማየት እንዲያቆሙና ያለጊዜያቸው እንዲያርጡ ያደርጋል፡፡
✿ አንዳንዶቹም በዚሁ መንፈስ ጥቃት ተነሳ ፤ ከሃያ ዓመት ዕድሜያቸው ጀምሮ ፤ ለአንድ ወይም ለሁለት ዓመት ፤ወይም ከዚያም በላይ ለሚሆን ጊዜ ፤ ወር አበባቸውን ሊያጠፋው ወየይም ሳያዩ እንዲቆዩ ሊያደርግም ይችላል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በአንድ ወር ውስጥ በተደጋጋሚ የወር አበባ እንዲፈሳቸው ያደርጋል ፡፡
በሕክምናው በኩል ሐኪሞች እንደሚገልፁት " እንደዚህ ዓይነት ክስተቶች አዲስ አይደሉም ፡፡በተለያየ ምክንያት አልፎ አልፎ ሊፈጠሩ ይችላሉ ፡፡ ሆኖም ፤ በብዙ ሴቶች ላይ የመታየቱ ጉዳይ ግን ፤ ያልተለመደና ራሱን የቻለ ጥናት የሚያስፈልገው ነው፡፡" ይላሉ ፡፡
ነገር ግን ፤ በርካታ ሰዎች ከላይ የተገለፁት ችግሮችና እንከኖች በአንድ በኩል በዲያብሎስ ምሪት በክፉ መንፈሶ ተፅዕኖም ሊመጣ እንደሚችል ፤ ገና መረጃው የላቸውም ፡፡በተደጋጋሚ እንደተገለጠው ፤ ዲያብሎስ በዛር መንፈሶች በኩል ከሰዎች ጋር አብሮ እየተወለደና እየተወራረሰ ፤ ዘሬ አድርጌያቸዋለሁ እያለና መንፈሱን ከማሕፀን ጀምሮ እያስቀመጠ ፣ ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን ጉዳቶች የሚያደርስ ቢሆንም ፤ በእግዚአብሔር መንፈስ የሚሸነፍና ወደ ሲኦል ወርዶ የሚታሰር ጠላት መሆኑን ለአፍታም ያህል ፤ መጠራጠር የለብንም ፡፡
ለምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማርቆስ ወንጌል 9÷29 "ይህ ወገን በጸሎትና በጦም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም " ይላል ፡፡ ይህ ማለት ወገን ሆኖ አብሮት ስለተወለደ በአካላዊ ተፈጥሮው ላይ ደንቆሮና ዲዳ በማድረግግ የእናቱና የአባቱ ሕልውና እንደጎዳ መመልከት ይቻላል ፡፡
☞ሴት ዛር በወንድ ላይ ስትኖር ፤ የምታመጣው ጉዳት
❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀
ሴት ዛር ወንድን በምትይዝበትና አብራ ተወልዳ በምታድግበት ወቅት ፤ ሕይወቱን ትለማመድና ልክ እንደሴት ልጅ በመቀመጫው በኩል በየወሩ የወር አበባ እንዲመጣበት ታደርጋለች ፡፡
ይህ ፈፅሞ ያልለተለመደ ሁኔታ በሕክምናው በኩል፤ የአንጀት ጉዳት ወይም የኪንታሮት ችግር መስሎ እንዲታይ፤ መንፈሱ ማሳሳቻውን ያቀርባል ፡፡ምንም ይባል ምን፤የሚገርመው ግን፤በሰውየው ላይ የወር አበባ ዑደቱ ልክ እንደሴቶች ቀን እየጠበቀ ለዓመታት ያህል ያለማቋረጥ የመታየቱ ጉዳይ ነው፡፡
ይህ የተዛባ ተፈጥሮ ፤የዛር መንፈስን የሚያመልኩና የሚገበሩ ሰዎች የበዙበት አካባቢ በሚገኙ ቤተሰቦችና ማህበረሰብ ውስጥ በስፋት የሚገጥም ክስተት ነው፡፡
☞ዝብረቃ
✿❀✿❀✿❀
በማይጠበቅ ሁኔታ ድንገት አስደንጋጭ የሆነ ቃል፤በንግግር መሐል ላይ ዝብርቅ ማድረግ የተለመደ የዘመናችን ስልጡን ሕብረተሰብ ዋና ችግር ነው፡፡ይህ፤ የዛር መንፈስ ሌላው ጥቃት ነው፡፡ዝብረቃ በሁለት መልኩ ይከሰታል፡፡
ሀ.☞የተሰወረ ዝብረቃ ፤
✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀
የመንፈሱ ሚስጥራዊ አሰራር በሥራ፣ በትምህርት ፣በንግድ ሥራና ሙያ በዕቅድና በፖሊሲ ንድፈ ሐሳብ እንዲሁም በጸሎት ጊዜ ሁሉ ጣልቃ በመግባት፤ አደገኛ ነገርን የሚያመጣ የመሪዎችና የኃላፊዎች የዝብረቃት ዕዛዝን
ጨምሮ የዓለማችን ትልቁ በሕይወታችን ውስጥ የሚገኙ የመንፈስ ውጥረት ነው፡፡
ለምሳሌ ዘብረቅ ያለ ዳኛም ይሁን መሪ ቶሎ ከእስር ቤት ሃምሳ ሰዎች ይረሸኑ ብሎ ከተናገረ ፤ ሰውየው ሳያውቀው በዝብረቃ መንፈስ ሃምሳ ሰዎች ተገደሉ ማለት ነው፡፡
በሕክምናውም በመድኃኒት ምርምሩም በተለያየ ኃላፊነትና የሥልጣንና የማዕነግ እርከን ያሉ ሰዎች ላይ የጦር መሪዎችንም ጨምሮ እስካልተወሰነ ሰዓት ድረስ ፤ የዝብረቃ መንፈስ ያጠቃቸዋል ፡፡
ለ. ☞ግልጽ ዝብረቃ ፤
✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀
ከፍሬ ነገሩ ጋር የማይገናኝና የማይያያዝ ሐሳብማስገባት ፣በጨዋታ መካከል ከመልካም ሥነ-ምግባር የወጣና የወረደ ቋንቋ መጠቀም ፣ መሳደብ ፣ ማዋረድ ፣ወይም ማልቀስ ፤በተቃራኒው ፤ ከልክ በላይ መሳቅ ፤በሙሉ ሰውነት ድንገት ብድግ ብሎ መዝለልና ወዲያውኑ የመቃተት ድምፅ ማሰማት ፣በእጅና በከንፈር ለብቻ ማውራት ፣ቁጭ ብሎ መዋተት ፣ሰዎችን ያለስማቸው አጠገባቸው ባለ ሰው ስም መጥራት ፣ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን አለስማቸው መጥራት ፤ለምሳሌ ፤ እንጀራ ለማለት ፤በቆሎ ፣ውኃ ለማለት ፤ እንጨቱን አምጣና እንጠጣ ወዘተ.....ሁሉ ማለት ፤ የዚዙ ክፉ መንፈስ የሚታይና የሚሰማ የዝብረቃ አካል ነው፡፡
ያለ ዕድሜ መጃጀት
✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿
የዛር መንፈስ ከሚያስትለው ጉዳቶች መካከል ፤ ያለ ዕድሜ መጃጀት ፣ መርሳትና ሠዘንጋት አንዱ ነው፡፡ ይህ ፤ በተለይ በአሁኑ ዘሠን ትልቅ ችግር ሲሆን ፤ ጥቃቱን በብዛት የሚያሳርፍባቸው ፤ ሳይንቲስቶች ፣ፖለቲከኞች ፣ ምሁራኖችና በኃላፊነትና ስልጣንና ማዕረግ የሚገኙ ሰዎች ፣ ሴቶችን ጭምር መርሳትና መዘንጋት ከክፉው መንፈስ አንዱ መሰረታዊ ችግር ነው፡፡
በሕክምናው (ዲያሜንሺያ) ብለው ስም ስለሰጡት ፤ በሳይንሳዊ ስያሜው መንፈስነቱን መደበቂያ ምሽግ አድርጎታል ፡፡
ለጸሎት ፣ ለአምልኮትና ለእግዚአብሄር ቃል ጊዜና ቦታ የሌላቸው ሁሉ ፤ በዚህ ክፉ መንፈስ ይጠቃሉ ፡፡
☞መሰረታዊ ምልክቶቹ ፤
❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿
☞ያወጡትን ዕቅድና ፕሮግራም መርሳት፣ወይም ሐተው፤
☞ከሕሊናቸው ዕውቀታቸውና ልምዳቸው መጥፋት ወይም መሰወር ፤
☞ገንዘባቸውንና ንብረታቸውን አለመቀቆጣጠር ፤
☞ከቤታቸው ወጥተው ፤ የሚኖሩት መንደር ፣ መንገድና መኖሪያ ቤታቸው ጠፍቶአቸው ሌላውን ሰው እስከ መጠየቅ መድረስ፤
☞ምሳ ወይም እራት በልተው ፤ አልበላሁም ብለው መጣላት፣ ማኩረፍ ፣ መናደድና መጮኽ ፤
☞ሚስታቸውንና ልጆቻቸውን መርሳት ፤ አለ ዕድሜ በዚህ መንፈስ የመጠቃት ልዩ ምልክቶች ናቸው፡፡
☞አዋቂው ሰው እንደ ሕጻን መሆን
✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀
ከዚህ በተቃራኒው ፤ የዛር መንፈስ በዕድሜ ከፍ ያሉና የገፉ ሰዎችን ፤ እንደ ሕጻን እንዲያስቡና እንዲሰሩ በማድረግ ፤ መካሪና አስታራቂ በመሆኛ ዕድሜያቸው ፣ እንዲሁም ጧሪና ቀባሪ በሚያስፈልጋቸው ሰዓት ፤ እንደ ልጅ አድርጎ ቅሌትና ውርደት ውስጥ ይከታቸዋል ፡፡
☞ሾፌሮችንና ተሳፋሪዎችን በመንገዳቸው ላይ የሚያጠቁ ክፉ መንፈሶች
✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿❀✿ይቀጥላል .

ሰሙነ_ሕማማት

የሰሙነ_ሕማማት_ትርጓሜ_ና_ክንዋኔና_ሚስጢር‬
ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ከገባ ጀምሮ ያሳለፈውና ከትንሳኤው በፊት ያለው አንድ ሳምንት " የመጨረሻ ሳምንት " ተብሎ ይጠራል፡፡ በሌላ አጠራር ደግሞ " ሰሙነ ሕማማት " ይባላል፡፡ በጌታ ላይ የሞት ምክር የተመከረበትና በብዙ መከራና ሕማማት የተገደለበት ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህም ሰሙነ ሕማማት የሚለው ስያሜ ጌታ የተቀበለውን ፀዋትዎ መከራን ለማዘከር የሰጠ ስያሜ ነው፡፡ የጌታ የመስቀሉ ሕማሞች ወይም " ሕማማት መስቀል " ተብለው የሚዘከሩት አሥራ ሦስት ሲሆኑ እነዚህም፦
1. በብረት ሐብለ መጋፊያና መጋፊያው እስኪጋጠም ድረስ የኋሊት መታሰሩ
2. ከአፍንጫው ደም እስኪውጣ ድረስ 25 ጊዜ በጡጫ መመታቱ
3. 65 ጊዜ ከግንድ ማጋጨታቸው
4. 120 ጊዜ በድንጋይ ፊቱን መመታቱ
5. 365 ጊዜ በሽመል መደብደቡ
6. 80 ጊዜ ጽህሙን መነጨቱ
7. 6666 ጊዜ መገረፉ
8. አክሊለ ሦክ በራሱ ላይ መደፋቱ
9. 136 ጊዜ በምድር ላይ መውደቁ
10. ሳዶር፡ አላዶር፡ ኤዴራ፡ ዳናትና ሮዳስ በሚባሉ 5ቱ ቅንዋተ መስቀል በችንካር መቸንከሩ
11. መራራ ሐሞትን መጠጣቱ
12. መስቀሉን ተሸክሞ መንገላታቱ
13. በመስቀል መሰቀሉ ናቸው።
በዚህ ሳምንት ውስጥ ካህናትና ምዕመናን በአፀደ ቤተ ክርስትያን ተሰብስበው ከሀጥያት ርቀው ከምግብና ከመጠጥ ተቆጥቦ በጾምና በጸሎት የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ ሲያዜሙ ግብረ ሕማም የሚባለውን መጽሐፍ እያነበቡ ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ።
ከአባታችን አዳም በደል ወይንም ስሕተት በኋላ በሕማማት፣ በደዌያት፣ በመቅሰፍታት፣ ወዘተ በብዙ መከራ የሰው ልጅ ሊኖርባቸው ግድ የሆነባቸው ዘመናት ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ጥሮ ግሮ ወጥቶ ወርዶ ለፍቶ ማስኖ የዕለት ጉርስ የቀን ልብስ ማግኘት እጅግ አዳጋች ነበር፡፡ ሁልጊዜ የሰው ልጅ ቢያጠፋ ቢበድል ከሕገ እግዚአብሔር ቢወጣ እንኳ የዋህ፣ ታጋሽ፣ ቸር፣ አዛኝ የሆነ አምላክ የጠፋውን ሊፈለግ የተራበውን ሊያጠግብ የታረዘውን ሊያለብስ፣ ፍቅር ያጣውን ፍጹም ፍቅር ሊለግስ፣ ሰላም ለሌለው ፍጹም ሰላም ሊሰጥ፣ ተስፋ የሌለውን ተስፋ ሊያጐናጽፍ ከሰማይ ወረደ፤ ከድንግል ማርያም ተወለደ፤ በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀንና ሌሊት ጾመ፡፡ በጾሙም የኃጡአት ሥሮች ወይም ራሶች የተባሉትን ስስትን፣ ትዕቢትንና ፍቅረ ንዋይን ድል አደረገልን፡፡ እኛ እርሱ የጾመውን ጾም እንድናከብር እንድንጾም ምሳሌ ሆነን፡፡ ዲያብሎስን ድል አድርጐ ድል እንድንነሣው ኃይልና ምሳሌ ሆነን፡፡
‪#‎ሰሙነ_ሕማማት_ምንድን_ነው‬?
ሰመነ ስምንት /ሳምንት/ አደረገ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ከዕለተ ሆሣዕና ሰርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ ወይም ቀናት የሚያመለክት ነው፡፡ ሐመ ማለት ታመመ ማለት ሲሆን ይህም የሰውን ዘር ሁሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራዎች የሚያሳስብ ነው፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኩነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኃጢአታቸውን በቤተ ክርስቲያን አደባባይ ለካህኑ የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሳምንት ነው፡፡
በዚህ ሳምንት ብዙ አዝማደ መባልእት አይበሉም፤ ይልቁን በመራብ በመጠማት በመውጣት በመውረድ በመስገድ በመጸለይ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራዎች በማሰብ አብዝቶ ይሰገዳል፡፡ መከራውን፣ ሕማሙን፣ ድካሙን የሚያስታውሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ መዝሙረ ዳዊት ግብረ ሕማማት ወዘተ በየሰዓቱ ይነበባል፡፡
‪#‎መስቀል_መሳለም_የለም‬፡፡ ካህናትም እግዚአብሔር ይፍታህ አይሉም የሳምንቱ ሥርዓተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ ይኸውም ይህ ሳምንት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዝንበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ በመሆኑ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት መላእክት የመለከት ድምጽ በማሰማት የዳግም ምጽአትን ዕለት ለማሳሰብ ምእመናን ጥሪውን ሰምተው ለዚህም አስቀድመው ተዘጋጅተው የበዓሉ ታዳሚዎች መሆናቸውን በማጠየቅ በዚህ ሳምንት ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ በየሰዓቱ ምእመናኑን ያሳስባል፡፡
‪#‎በሰሙነ_ሕማማት_የሚገኙ_ዕለታትና_ስያሜያት‬
‪#‎ዕለተ_ሰኑይ‬ /ሰኞ/
ይህ ዕለት አንጾሖተ ቤተ መቅደስ /የቤተ መቅደስ መንጻት/ እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡ /ማር.11-11፣ ማቴ.21-18-22 ሉቃ.13-6-9/፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ «ወመሰለ ሎሙ ወይቤሎሙ አሐዱ ብእሲ በለሰ ቦቱ ውስተ አጸደ ወይኑ ወየሐውር ይንሣእ ፍሬሃ ወኢይረክብ ...»፤ ይህንም ምሳሌ አለ ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው ፍሬም ሊፈልግባት ወጥቶ ምንም አላገኘም፡፡ በማለት በበለስ ስለተመሰለ የሰው ልጅ ሕይወት በማሰብ እንዲመለስ ንስሐ እንዲገባ በሕይወትም እንዲኖር እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ማሳሰቡን ያጠይቃል፡፡ ንስሐ አልገባም አልመለስም ያለም በለሷ እንደጠወለገችና እንደተቆረጠች ሁሉ ፍሬ ባለማፍራታቸው እንደሚቆረጡ እንዲሁም ወደ እሳት እንደሚጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል፡፡ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ፍሬ የተባለ ደግሞ ሃይማኖትና ምግባርን ነው፡፡ ሁላችን ቤተ እስራኤላውያን ፍሬ ሃይማኖት ወምግባር አስተባብረን ይዘን መገኘት ይገባናል፡፡ ፍሬ አልባ እንዳንሆን ጌታ ሲመጣም እንዳናፍር የመጽሐፉን ቃል ልንጠብቅና ልንፈጽም ይገባናል፡፡ በዚህ የሕማማት የመጀመሪያ ቀን ዕለተ ሰኑይ የምናስበው የምንዘክረው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ በቸልተኝነት እንዳይደክም እንዳይጠወለግ እንዳይደርቅ ወደ እሳትም እንዳይጣል ማድረግ ይገባናል፡፡
‪#‎ዕለተ_ሠሉስ‬ /ማክሰኞ/
ይህ ቀን ጌታችን ሰኞ በተናገረውና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የጥያቄ እና የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ ጥያቄውም ጌታ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት ለጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይኸውም ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?» የሚል ነበር፡፡ /ማቴ.21-23-27/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ «ወይቤሎሙ ኢየሱስ አማን እብለክሙ ከመ መጸብሓውያን ወዘማውያት ይቀድሙክሙ ውስተ መንግሥተ እግዚአብሔር»፤ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው እውነት እላችኋለሁ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል ሲል አስተምሯል፡፡ /ማቴ.21-28/
‪#‎ዕለተ_ረቡዕ‬/እሮብ/
ይህ ዕለት ደግሞ የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ ምክር የጀመሩበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዕለቱ" የምክር ቀን" በመባል ይጠራል፡፡" መልካም መዓዛ ያለው" እና "የእንባ"ቀንም ይባላል። ምክንያቱም ማርያም ዕንተ እፍረት ዋጋው ብዙ የሆነ ሽቶ ጌታችንን በመቀባታና ስለ ሀጥያቷ ስቅስቅ ብላ በማልቀሷ ይህንን ስያሜ ተሰጠ። ማቴ 26፦3_13 ማር 14፦ 1_11 ሉቃ 22፦3_6
‪#‎ዕለተ_ሐሙስ‬/ሐሙስ/
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ለመግለጥ እና ለአርአያነት ጸሐፍት ፈሪሳውያን የአይሁድ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡ ትሕትና ፍቅር መታዘዝ እንዲሁም የአገልግሎትን ትርጉም ለማስረዳትና ለማስገንዘብ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ሕጽበተ ሐሙስ በመባልም እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም «ወሶበ ኀፀቦሙ እገሪሆሙ ነሥአ አልባሲሁ ወረፈቀ ካዕበ ወይቤሎሙ አእመርክሙኑ ዘገበርኩ ለክሙ ... ወሶበ አነ እንከ ሊቅክሙ ወእግዚእክሙ ኀፀብኩክሙ እገሪክሙ ከማሁኬ አንትሙኒ ይደልወክሙ ትኅፅቡ እግረ ቢጽክሙ፡፡»፤ «እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ እንዲህም አላቸው ያደረግሁላችሁን ታስተውሉታላችሁን?... እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል ሲል ተናግሯል፡፡ /ዮሐ.13-12-20/፡፡
ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ በማለት ምሥጢረ ቁርባንን የመሠረተበት ወይም ራሱ ምስጢረ ቁርባንን የጀመረበት ቀን በመሆኑ የምስጢር ቀን ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም የሰው ልጆች ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ከእርሱ ጋር አንድነትና ኅብረት እንዲኖረን ጥንተ ጠላት ዲለብሎስንም ፍጹም ድል ነሥተን ሰማያዊት ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ለማስቻል ነው፡፡ /ማቴ.26-26-29/፡፡
አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ በእነርሱ ጥበብና ፍላጐት ቀስ ብለው መጥተው የያዙበት ቀን ስለሆነ በዚህ ዕለት በለሆሳስ /ብዙ የድምጽ ጩኸት ሳይሰማ/ የቅዳሴ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ ስለሆነም መላው ሕዝበ ክርስቲያን በዚህ የሕጽበት፣ የምስጢር፣ የጸሎት ቀን በተባለው በዚህ ዕለት በንስሓ ታጥበው ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ቤተ ክርስቲያን በአጽንኦት ታስተምራለች፡፡
‪#‎ዕለተ_ዐርብ‬/ዓርብ/
ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ «አውቀውስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት» /1ቆሮ.1-18/፡፡ እንዳለ ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለበደል ያለጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የሆነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልእልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው፡፡ /ማቴ.27-35-75/፡፡ በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ፡፡ እነርሱ ግን እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ፡፡ ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሔደና ታንቆ ሞተ፡፡ የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ፡፡ ተማክረውም የሸክላ ሠሪ መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት፡፡ ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ፡፡ /ማቴ.27-3-9/
የሰው ልጆች በዘር ኃጢአት /ቁራኝነት/ ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት ፍጹም ድኅነት ያገኙባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ ሕማሙን ስቅለቱን ሞቱን የሚያስቡበት ጊዜ ነው፡፡ በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የሕይወት መቅጫ አርማ ሆኖ ሳለ ለእኛ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስላደረገው በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን ስለአገኘን በዚህም ምክንያት መልካሙ ዓርብ በመባል እንደሚታወቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያትታሉ፡፡
በመስቀል ላይ ሳለ 7 ነገሮችን ተናገረ/7ቱ " አጽርሐ መስቀል " በመባል ይታወቃሉ። እነሱም፦
" አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ" ማቴ 17፦46
" አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" ሉቃ 23፦34
" ዛሬ በገነት ከኔ ጋር እንድትኖር በእውነት እነግርሀለሁ" ሉቃ 23፦4
" አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ" ሉቃ 23፦ 46
" እነሆ ልጅሽ እነኋት እናትህ" ዮሐ 19፦26
" ተጠማሁ" ዮሐ 19፦28
" ሁሉ ተፈጸመ " ዮሐ 19፦ 30
ጌታ ሁሉ ተፈጸመ ብሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ስጋው በራሱፈቃድ ከለየ በኋላ አምላክነቱን ለመግለፅ የታዩ ተአምራት የሚከተሉት ናቸው፤
በሰማይ፤ /ማቴ 24፦29 እና 27፦45/
1. ፀሐይ ጨለመች
2. ጨረቃ ደም ሆነች
3. ከዋክብት ረገፉ
በምድር፤/ማቴ 27፦51_53/
1. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይእስከ ታች ተቀደደ
2. ምድር ተናወጠች
3. መቃብሮች ተከፈቱ
4. ሙታን ተነሱ
‪#‎ቀዳሜ_ስዑር‬/ቅዳሜ/
ዕለተ ቅዳሜ እግዚአብሔር የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሄዱትን እና በክንፍ የሚበሩትን በባሕር የሚዋኙትን እንስሳትን በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈበት ዕለት ነች፡፡ ይህች የመጀመሪያው ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት እግዚአብሔርን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ ስላረፈበት ሰንበት ዐባይ /ታላቋ ሰንበት/ ትባላለች ታላቋን ሰንበት እስራኤላውያን እንዲያከብሯት ታዟል፡፡ ዘፍ.1፡3፡፡
‪#‎ዕለተ_ቀዳሚት‬ /ሰንበት ዐባይ/ በዘመነ ሐዲስም የተለየ የደኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ ጥንት ሥነ ፈጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንደ ተደረገባት ሁሉ የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ የሆነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው ቸሩ አምላክ በመቃብር አርፎባታል፡፡ ማቴ.27፡61፡፡
በዚህች ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት በመሆኗ «ቀዳሜ ስዑር » ትሰኛለች፡፡ ስዑር ቀዳሜ የተባለችው በዓመት አንድ ቀን ስለ ምትጾም ነው፡፡ ምክንያቱም እናቱ ድንግል ማርያም ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንስተው ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እህል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብ ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡
ከቅዱሳን ሐዋርያት ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን በመጾምና በመጸለይ ዕለቷ እንዳከበሯት የተዋሕዶ ልጆች የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው የሚያከፍሉ /የሚጾሙ/ ለሁለት ቀን እህል ውኃ ሳይቀምሱ ያድራሉ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡
በዚህ ዕለት ከሰኞ ከሆሣዕና ማግሥት ጀምረው እስከ ስቅለተ ዓርብ ድረስ በስግደት እና በጾም ያሳለፉ ምእመናን በዕለተ ቅዳሜ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸም ካህናቱ «ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፡-በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ» የምሥራች እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡት ምእመናን ቄጠማ ይታደላል ቄጠማው የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖህ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ሆነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ዘፍ.9-1-29፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል፡፡
« ‪#‎ቄጠማ‬»፣ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነ አሁንም በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡
የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲኦል /የሲኦል ቃጠሎ/ ወደ ልምላሜ ገነት ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳሃን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡
‪#‎ሃይማኖታዊና_ትውፊታዊ_ክንዋኔዎች_በሰሙነ_ሕማማት‬
በዐቢይ ጾም ከሠርክ ሆሣዕና ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ዕለታት የሚገኙበት ሳምንታት ሰሙነ ሕማማት ይባላሉ፡፡ ዕለታቱም የዓመተ ፍዳ፣ የዓመተ ኩነኔ መታሰቢያ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዕለታት ውስጥ የተለያዩ ትውፊታዊ እና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ክንዋኔዎች ውስጥ አለ መሳሳም፣ አክፍሎት፣ ቄጤማ ማሰር፣ ጥብጣብ፣ ጉልባን እና ሕጽበተ እግር ይገኙበታል፡፡ ስለእነዚህ ክንዋኔዎች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስላለው ትውፊታዊ አፈጻጸም መዛግብት አገላብጠን እና በኢትዮጵያ ኣርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ አባል የሆኑትን ሊቀ ካህሃት ክንፈ ገብርኤል አልታዬን አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
‪#‎አለመሳሳም‬
በሰሙነ ሕማማት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፣ መሳሳምና የትከሻ ሰላምታ መለዋወጠን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት፣ አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማክሰኞ መከሩ አልሠመረላቸውም፡፡ ምክራቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡
ስለዚህ አይሁድ አያንሾካሾኩ “እንስቀለው… አንግደለው” ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ ያነን ለማስታወስ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡ መስቀልም አንሳለምም፡፡ ሳምንቱ የክፋት ምክር የተመከረበት እንጂ የፍቅርና የደስታ ሰላምታ የታየበት ባለመሆኑ ይህንን በማሰብ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡
ይሁዳ ጌታን በጠላቶቹ ለማስያዝ “እኔ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ በሰላምታው ምልክት ሰጣቸው ይህ ሰላምታ አምሐ ቅድሳት አይደለም፤ ተንኮል የተሞላበት እንጂ፡፡ የዲያቢሎስም ሰላምታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሔዋንን “ሰላም ለኪ” ብሎ ነው ያታለላት፣ የዲያቢሎስ እና የይሁዳ ሰላምታ ሰይጣናዊ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ወቅትና ሁኔታ ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ሰላምታ ልውውጥ የለም፡፡ ዛሬ እየተስተዋለ ያለው ይኸው ሰላምታ ያለመለዋወጥ ሁኔታ ሥርወ መሠረቱ ይህ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እዚህ ትውልድ ላይ ደርሷል ይቀጥላልም፡፡
‪#‎ሕጽበተ_እግር‬
ጌታ በፍጹም ትሕትና የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ሕይወት ማሕተም የሆነውን ምሥጢረ ቁርባን ያከናወነበት ዕለት ነው ጸሎተ ሐሙስ፡፡
ሕጽበተ እግር ጌታችን በዚህ ዕለት “አናንተ ለወንድማችሁ አንዲህ አድርጉ” ለማለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው “አኔ ለአናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም፣ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም፤ ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናቸሁ” /ዮሐ.13÷16-17/ በማለት ትሕትናውን አሳይቷል፡፡
ጌታ በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር ሲያጥብ “እኔ መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኳችሁ አርአያዬን ሰጥቻችኋለሁ፤ እናንተም የወንድማችሁን እግር ታጥቡ ዘንድ ይገባል፡፡ ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ለሞት አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም “ማን ይሆን?” አሉ፡፡ ጌታም “ኅብስት ቆርሼ፣ ከወጡ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ደነገጡ፡፡ ይሁዳን ማመልከቱ ደነገጡ፡፡ ይሁደን ማመልከቱ ነበር፤ ለጊዜው አልገባቸውም፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ትሕትናን ካስተማራቸው በኋላ፤ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሰጣቸው፤ የኦሪትን መሥዋዕት የሻረው እና መሥዋዕተ ሐዲስን የሠራው በዚሁ ዕለት ነው፡፡
በዚህ ሃይማኖታዊ መነሻነትም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚከናወኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- በወሎና በጎንደር ከጉልባን በተጨማሪ በተለይ በጸሎተ ሐሙስ ዕለት ብቻ የሚጋገር የተለየ ዳቦ አለ፡፡ ይህ ልዩ ዳቦ በወሎ “ትኩሴ” በጎንደር ደግሞ “ሙጌራ” ይባላል፡፡ ይህ ዳቦ ጌታ ለሐዋርያት የሰጣቸው ኅብስት አምሳያ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ከዚህ ቀን ውጪ በሌላ ጊዜ አይጋገርም፡፡ በመሆኑም ሰው ሁሉ ዳቦውን ለመብላት የሚጠባበቀው በታላቅ ጉጉት ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በሚከበርባቸው እንደ ማኅበርና ሰንበቴ በመሳሰሉት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ትውፊቶች የሚቀርብበት ጊዜ አለ፡፡
በትግራይ በዕለተ ስቅለት ከተለመደው የጾምና የስግደት ሥርዓት በተጨማሪ የሚከናወኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ በዕለቱ ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት መታሰቢያ ሲባል ወንዶች ልጆች በሙሉ ፀጉራቸውን እንዲላጩ ይደረጋል፡፡ ያን ቀን ያልተላጨ ልጅ “ኃጢአት ይሆንበታል” ስለሚባል ሳይላጭ የሚውል ልጅ የለም። ልጃገረዶች በበኩላቸው በዛፍ ላይ ገመድ በማሰር ዥዋዥዌ ይጫወታሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት የጌታን እንግልትና መስቀል ለማዘከር ነው ይባላል፡፡
እነሆ ይህንን ዕለት በማስታወስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ ቤተ ክርስቲያን ከሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ እስከ ቀሳውስት ያሉት አባቶች በያሉበት አጥቢያ /ደብር/ በመገኘት በመዓርግ የሚያንሷቸውን የካህናት፣ ዲያቆናት እና የምእመናንን እግር ያጥባሉ፤ የሚያጥቡትም የወይራ እና የወይን ቅጠል በመዘፍዘፍ ነው፡፡
‪#‎አክፍሎት‬
በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ዓርብ ከስግደት በኋላ ምእመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው እስከ እሑድ /የትንሣኤ ሰዓት/ ይሰነብታሉ፡፡ ይህ አክፍሎት ይባላል፡፡ ብዙው ምዕመን ከዓርብ ጀምሮ የሚያከፍል ሲሆን አንዳንዶች ግን ከሐሙስ ጀምረው ያከፍላሉ፡፡ ይህም እመቤታችን፣ ያዕቆብ እና ዮሐንስ የጌታን ትንሣኤ ሳናይ እህል ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሣኤ መቆየታቸውን ተከትሎ የመጣ ትውፊት ነው፡፡
ይህንን ትውፊት አስመልክቶ ሄሬኔዎስ፣ አውሳብዮስ የተባሉ ጸሐፍት፤ ሐዋርያት በሰሙነ ሕማማት ከደረቅ ዳቦ አና ከትንሽ ውኃ በቀር እንደማይመገቡ እና ከሐሙስ ጀምረው እንደሚያከፍሉ ጽፈዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሐዋርያት ሌሎቹንም እንዲያከፍሉ እንዳሳሰቡና ከሐሙስ ጀምሮ ያልተቻለው ቢያንስ ከዓርብ ጀምሮ እንዲያከፍል ማዘዛቸውን ጽፈዋል፡፡ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትም ይኸው ነው፡፡ ቅዳሜ ይበላል ማለት ግን ቅዳሴው ሌሊት ስለሆነ በልቶ ማስቀደስ ነውና በልቶ እንደመቁረብ ይቆጠራል፡፡
‪#‎ጉልባን_እና_ቄጤማ‬
ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚባላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብፅ ተሰደው በሚወጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር፤ አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያን ጊዜ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መብላት፤ ንፍሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓሉ ይታሰባል፡፡
በጸሎተ ሐሙስ ይህንን መሠረት በማድረግ የሚዘጋጀው ጉልባን አንዲህም ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ጨው ውኃ የሚያስጠማ በመሆኑ የጌታን መጠማት ያስታውሳል፡፡ ይህ ትውፊታዊ ሥርዓት ከእስራኤላውያን የመጣ ሲሆን በኢትዮጵያም አብዛኛዎቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ሥርዓቱ ዛሬም ይከበራል፡፡
‪#‎ጥብጣብ‬
በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ዓርብ የስቅለቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ምእመናኑ በሰሙነ ሕማማት የሠሩትን ይናዘዛሉ፡፡ ካህናቱም በወይራ ቅጠል ትከሻቸወን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጠባው የተግሳፅ ምሳሌ ነው፡፡ ጥብጣብ የሚደረግለት ሰው በሕማማቱ ወቅት የፈጸመው በደል ወይንም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር የስግደቱ ቁጥር ከፍ እንዲል ይደረጋል፡፡
ይህ በስቅለት ቀን የሚፈጸም ሥነ ሥርዓት ሲሆን፤ ጠብጣቤ ማለት ቸብ ቸብ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዕለተ ስቅለት ሲሰግድ ሲጸልይ፣ ሲያነብ ከዋለ በኋላ ሰርሆተ ሕዝብ /የሕዝብ መሰነባበቻ/ ከመሆኑ በፊት፤ በወይራ ቅጠል እያንዳንዱን ምእመን ጀርባ ቸብ ቸብ መደረጉ፣ የጌታን ግርፋት ያስታውሳል፡፡
‪#‎ቀጤማ‬
በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ ዓዋዲ/ እየመቱ “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ” የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር፤ ቀጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ቀጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ የደፉበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡
በዚህ ዕለት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቀጤማ ተሸክመው ቃጭል ሲያቃጭሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብስራት ነው፡፡
ያብጽሃነ ያብጽሕክሙ!
(ምንጭ፦ ስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም ዘሰሙነ ሕማማት

Friday, 22 April 2016

ክርስቶስ (ዐሰ) ተወዳጁ የኢስላም ነብይ | Part 1 | Jesus (PBUH) Beloved Prophet of Isl...

ክርስቶስ (ዐሰ) ተወዳጁ የኢስላም ነብይ | Part 1 | Jesus (PBUH) Beloved Prophet of Isl...

ክርስቶስ (ዐሰ) ተወዳጁ የኢስላም ነብይ | Part 1 | Jesus (PBUH) Beloved Prophet of Isl...

በዓለ ሆሣዕና

በዓለ ሆሣዕና
መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
(ነገረ ክርስቶስ ከሚለው መጽሐፌ ገጽ 616-617 በጥቂቱ የተወሰደ)
ሆሣዕና ማለት የዕብራይስጥ ቃል ሲኾን “ሆሻአና” ሲባል ትርጒሙም “አቤቱ አኹን አድን” ማለት ነው፤ ይኽ በዓለ ሆሣዕና ከ9ኙ ዐበይት የጌታ በዓላት ውስጥ ሲኾን ኪሩቤል ሱራፌል በፍርሀት በረዐድ ኹነው ዘፋኑን የሚሸሙት ጌታ በትሕትና በአህያና በውርንጫይቱ በትሕትና ተቀምጦ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት፣ የዘካርያስ ትንቢት የተፈጸመበት፣ ሕዝቡ ዘንባባ ይዘው የዘመሩበት፣ ሕፃናት በንጹሕ አንደበታቸው ሆሣዕና ብለው ያመሰገኑበት ታላቅ በዓል ነው፡፡
ይኽም ታሪክ በ4ቱ ወንጌላት ላይ ሲጻፍ በማቴ 21፡1 ላይ “ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ” ይላል፡፡ ቤተ ፋጌ ማለት የበለስ ቤት ማለት ሲኾን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ በሚወስደው መንገድ አቅራቢያ ያለች ትንሽ መንደር ናት፤ ኹሉን ዐዋቂ የኾነው ጌታም ጴጥሮስንና ዮሐንስን “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከርሷ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ” በማለት እንደ ማዕምረ ኅቡአትነቱ (የተሰወረውን ዐዋቂነቱ) በመንደሯ ውስጥ ስለታሰሩት አህያና ውርንጫ አስቀድሞ ይነግራቸዋል፡፡
በተናቀች ግርግም በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ ላምና አህያ ትንፋሻቸውን እንደገበሩለት፤ አኹንም በሰዎች በተናቀች አህያ በጌትነት ተቀምጦ እንዲመሰገንባት መርጧታል፡፡ ከዚያም “ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል” በማለት የኹሉ ጌታ ርሱ መኾኑን አመለከታቸው፤ በተሰጣቸው ሥልጣነ ክህነት የሕዝቡንም የአሕዛቡን ኀጢአት የማሰር የመፍታት ሰማያዊ ሥልጣነ ክህነት የተሰጣቸው ሐዋርያትን የሕዝብ ምሳሌ የኾነችውን አህያይቱንና የአሕዛብ ምሳሌ የኾነችው ውርንጫዋንም እንዲያመጡ አዟቸዋልና፤ አምጥተው “ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ”፤ በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ኮርቻ ሳይኾን ልብስ ማድረጋቸው ኮርቻ ይቈረቊራል ልብስ ግን አይቈረቊርምና የማትቈረቊር ሕግ ሠራኽልን ሲሉ፤ ዳግመኛም ልብስ በአካል ያለውን ኀፍረት እንዲሰውር አንተም በደላችንን የምትሰውርልን ይቅር ባይ ነኽ ሲሉ፡፡
ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደስ 16 ምዕራፍ ሲኾን መተርጒማነ ሐዲስ በትርጓሜ ወንጌል ላይ እንደሚገልጹት 14ቱን ጌታ በእግሩ ሲኼድ 2ቱን በአህያዋ፤ በውርንጫዋ 3 ጊዜ ቤተ መቅደሷን ዞሯል፡- 14ቱ በእግሩ መኼዱ የ10ሩ ቃላት 4ቱ የ4ቱ ኪዳናት ምሳሌ፡፡ 2ቱ በአህያዋ መጓዙ የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ፤ 3ቱን በውርንጫዋ ተቀምጦ ቤተ መቅደሱን መዞሩ የ3ትነቱ የአንድነቱ ምሳሌ ነበር፡፡ ክብር ይግባውና ጌታ ንጉሠ ነገሥት ሲኾን፤ ኪሩቤል ሱራፌል ዙፋኑን በፍርሀት በረአድ የሚሸከሙት 24ቱ ካህናተ ሰማይ ዙፋኑን በፍርሀት የሚያጥኑለት ርሱ በትሕትና የዋህ ኾኖ በተናቁት በአህያና በውርንጫይቱ ላይ ተቀመጠ፤ ይኽም የተናቁትን ሊያከብር እንደመጣና፤ በየዋሀን ምእመናን ልቡና እንደሚያድር ለማሳወቅ በነርሱ ተቀመጠ፤ በአህያ የተቀመጠ አባሮ እንደማይዝ ሸሽቶ እንደማያመልጥ ርሱም ካልፈለጉት እንደማይገኝ ከፈለጉት እንደማይታጣ በምስጢር አመለከታቸው፡፡
ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፡- ስለዚኽ ነገር በትርጓሜ ወንጌሉ ላይ “እነዚኽ እንስሳት መላውን የሰው ልጅ ይወክላሉ፡፡ ኹለቱም አህያ መኾናቸውም የሰው ልጅ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የነበረውን አኳኋን የሚያስረዳ ነው፡፡ ምክንያቱም አህያ በኦሪቱ ዘንድ ንጹሕ እንስሳ አይደለችም፤ ብዙ ክብደት ያላት የማትወደድ እንስሳ ናት፤ ዲዳ ናት፤ ደካማ ናት፡፡ ሰውም እንደተናገርን ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት እንዲኽ ነበረ፡፡” በማለት አመስጥሯል፡፡
ሊቁ ቅ. ቄርሎስ ዘእስክንድርያም፡- “ፈጣሬ ኵሉ እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ጠቢብ አድርጐ ፈጥሮት ነበር፡፡ ማሰብና ማሰላሰል የሚችል ፍጥረት አድርጐ ፈጥሮት ነበር፡፡ ሰይጣን ግን አታለለው፡፡ ምንም እንኳን ሰው በሥላሴ አምሳል ቢፈጠርም መልኩን አበላሸው፡፡ ፈጣሬ ኵሉ እግዚአብሔርን ማወቅ ተሳነው፡፡ ክፉው ሰይጣን ሰውን እንስሳ እስኪመስል ድረስ ክብሩን አዋረደው፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት፡- “ሰውስ ክብሩን አላወቀም፤ የሚጠፉ እስሳትን መሰለ” ያለውም ስለዚኹ ነው /መዝ.49፡12/፡፡ በመኾኑም አህያይቱ ክብራቸውን አጥተው ተዋርደው የነበሩትን እስራኤል ዘሥጋን ትመስላለች፡፡ እስራኤል ከሕጉ ጥቂት ነገርን ያውቃሉ፡፡ ከነቢያትና ከቅዱሳንም ትንሽ ያውቃሉ፡፡ ከኹሉም በላይ ደግሞ ወደ አሚን የሚጠራቸውን ክርስቶስን አልታዘዙትም፡፡ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ሲላቸውም እንደምን እንደ አሕያይቱ በድንቁርና ተይዘው እንደነበረ ሲገልጥላቸው ነው፡፡ ውርንጫይቱ ደግሞ አሕዛብን ትወክላለች፡፡ ውርንጫ እኽልን ለመጫን እንደማታገለግል ኹሉ አሕዛብም ማኅደረ እግዚአብሔር ከመኾን ርቀው ነበርና፡፡” በማለት ገልጽዋል፡፡
ሊቁ ጀሮምም፡- “ደቀ መዛሙርቱ አህያይቱንና ውርንጫይቱን ለመፍታት ኹለት ኾነው መላካቸው ለሕዝብም ለአሕዛብም መላካቸው ያመለክታል፡፡”
ሊቁ አምብሮስ፡- “አህያየቱን ለመፍታት ማንም አይከለክላችኁም ብሎ መላኩ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ሥልጣን ሰማያዊ መኾኑ ያመለክታል፡፡” በማለት ልዩ ምስጢርን አስተላፎበታል፡፡
ያን ጊዜ ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ ይኽንም ማድረጋቸው ስንኳን አንተ የተቀመጥኽባት አህያ መሬት መርገጥ አይገባኽም ሲሉ ነበር፤ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር፡፡
ይኽም ዘንባባ ብዙ ምሳሌ ያለው ነው፤ ይኸውም በእስራኤል ያለው ሰሌን፣ ተምር፣ ዘይት ነበርና ያነን ቈርጠው አመስግነውታል፤ ይኽም ምሳሌነት ያለው ነው፤ ይኽም ሰሌን እሾኻማ እንደኾነ ትእምርተ ኀይል ትእምርተ መዊእ አለኽ ሲሉ ነው፤ እሳት ለብልቦ ይተወዋል እንጂ እንደማያቃጥለው ባሕርይኽ አይመረመርም ሲሉ ነበር፡፡
ዳግመኛም ከሰሌን ዝንጣፊ ጋር ተመሳሳይ ተምር ይዘዋል ይኽም ተምር ልዑል ነው አንተም ልዑለ ባሕርይ ነኽ ሲሉ፤ ፍሬው አንድ እንደኾነ አንተም ዋሕደ ባሕርይ ነኽ ሲሉ፡፡ በእሾኽ የተከበበ ነው ባሕርይኽ አይመረመርም ሲሉ ነበር፡፡
የዘይት ዛፍ ነው ቢሉ ዘይት ጽኑዕ እንደኾነ ጽኑዐ ባሕርይ ነኽ ሲሉ፤ ብሩህ ነው ብሩሀ ባሕርይ ነኽ በትምህርትኽም የሰውን ልቡናን ታበራለኽ ሲሉ፤ ዘይት መሥዋዕት እንደሚኾን መሥዋዕት ትኾናለኽ ሲሉ ነበር፡፡
“የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር” በማለት በአርያም መድኀኒት እንደኾነና እግዚአብሔር አብ “የምወድደው ልጄ ይኽ ነው” ብሎ መስክሮለት የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን የሚያርቅ በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን የሚያድል መኾኑን ኹሉም መሰከሩለት፡፡
በእጅጉ የሚደንቀው የ40 ቀን የ80 ቀን ሕጻናት የፈጠራቸው ጌታ በአህያና በውርንጫ ተቀምጦ ባዩት ጊዜ በንጹሕ አንደበታቸው አንደታቸው ረቶላቸው ጌታን ዘንባባ በመያዝ ሲያመሰግኑ በእጅጉ ይደንቅ ነበር፤ ነገር ግን ጸሐፍት ፈሪሳውያን ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት፤ ኢየሱስም፦ እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? በማለት በሕጻናት እንደሚመሰገን የነርሱም ጌታ መኾኑን ከዳዊት መዝሙር በመጥቀስ ነገራቸው፡፡
ሊቁ ያዕቆብ ዘሥሩግ ሰለዚኽ ምስጢር ሲገልጸው ፡- “ፍቅርኅ ከዘባነ ኪሩብ አውርዶ በአህያ ዠርባ ላይ እንድትቀመጥ አስገደደኅ፡፡ ብዙ ዓይንና ብዙ ገጽ ካላቸው ከሠራዊተ መላክእት ይልቅ በዲዳዋ አህያ ትመሰገን ዘንድ ወደደክ፡፡ በሰማይ ሠራዊት ሠረገላ ተቀምጠኅ ክብርኅን ማሳየት አልወደድክም፤ በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጠኅ ወደ ሰማይ ሠራዊት መኼድን መረጥክ እንጂ፡፡ በአርያም እሳታውያን የሚኾኑ ኪሩቤል ያመሰግኑኻል፤ በምድርም ሕፃናት ይዘምሩልኻል፡፡ በአርያም ብርሃናውያን መላእክት በብርሃን ክንፋቸው መንገድኽን ያነጥፉልኻል፤ በምድርም ደቀ መዛሙትኽ ልብሳቸውን አንጥፈው መንገድኽን አስተካከሉ፡፡ ወዮ! አርያማዊ ሲኾን ምንም ሳይንቀን ይጐበኘን ዘንድ ከአባቱ መጣ፡፡ እርሱም በገዛ ፈቃዱ ሰው እስከ መኾን ደርሶ መጣ፡፡ በአህያ ላይ ተጭኖም ይጐበኘን ዘንድ መጣ፡፡ ነቢዩ ዘካርያስ የመንፈስ ቅዱስን እንዚራ ይዞ በደስታ ትንቢትን ለመናገር ይቻኰላል፡፡ እየደረደረም የጽዮንን ልጅ ይጠራታል፡፡” በማለት አስተምሯል፡፡
የምስጋና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ተቀምጦ ሕፃናትን ጨምሮ ዘንባባ ሰሌን በያዙት ኹሉ “ሆሣዕና በአርያም” እየተባለ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበትን ታላቁን በዓል ከኹሉም ዓለም አስበልጣ በታላቅ ክብር የምታከብርና የምታስተምረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
ይኸውም ታላቁ የምስጋና ዕለት ሊደርስ ሲቃረብ ስንዱዋ እመቤት አስቀድማ በቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ የቊርባን ምስጋና “ቦአ ኀቤሃ እግዚአ አጋዕዝት ወመናፍስት እንዘ ይጼዐን ዕዋለ አድግ ትሑት…” (የአጋዕዝትና የመናፍስት ጌታ በተዋረደ አህያ ግልገል ተቀምጦ ወደ ርሷ ገባ፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ብሩክ ነው፡፡ አንተም የአማልክት አምላክ የእስራኤልም ንጉሥ እግዚአብሔር ቡሩክ ነኽ እያሉ ለሚያመሰግኑ ሕፃናት ኹሉ ጌትነቱን አሳየ፤ የሆሳዕናን ዑደት ለነርሱ ለደቀ መዛሙርቱ አሳየ፤ ቡርክ ርሱ በታላቅ ቃል እየጮኻችኊ ሆሣዕና በአርያም በሉ አላቸው፤ ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም ሆሳዕና በአርያም፤ ከመድኀኒትነቱ የተነሣ ከዚኽ አስቀድሞ ያልተደረገ ከዚኽም በኋላ የማይደረግ ተአምራትንና መንክራትን አሳየ፤ ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም ሆሳዕና በአርያም፤ ከመድኀኒትነቱ የተነሣ ከቤቱ መሠረት ሳይናወጥ ከልዑል መንበሩ ወርዶ ጸጋንና ኀይልን አሳየ፤ ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም፤ ከመድኀኒትነቱ የተነሣ ለኃጥኣን የዕንባ ምንጭ ሰጠ፤ የበደሉትን ያጸድቃቸው ዘንድ ያደፉትን ያነጻቸው ዘንድ የሳቱትን ይመልሳቸው ዘንድ፤ ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም፤ ከመድኀኒትነቱ የተነሣ ለዕውራን ዳግመኛ የማጠፋ ዓለም ሊቀበለው የማይቻለውን ብርሃንን ሰጣቸው ከኅሊና አስቀድሞ ያውቃል ከዐሳብም በፊት አስቀድሞ ይመረምራል የሚሰወረውም የለም) በማለት መድኀኒትነቱን ስትሰብክ፤ ካህናትና ምእመናንም በአንድ ድምፅ በዚያ ዘመን የምስጋና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በተመሰገነበት በዚኽ ልዩ ምስጋና “ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም” እያሉ በመዘመር፤ ፈጣሪያቸው ክርስቶስን ያመሰግናሉ፡፡
ከዚያም በዋዜማው “በዕምርት ዕለት በዓልነ ንፉሑ ቀርነ በጽዮን ወስብኩ በደብረ መቅደስየ እስመ ይቤ ዛቲ ዕለት በዓለ እግዚአብሔር ሆሣዕና በአርያም ቡሩክ አንተ ንጉሠ እስራኤል” (በታወቀች በበዓላችን ዕለት በጽዮን መለከትን ንፉ፤ በመቅደሴ ተራራም ስበኩ ይኽቺ ዕለት የእግዚአብሔር በዓል ናት፤ በአርያም መድኀኒት የተባልኽ የእስራኤል ንጉሥ አንተ ቡሩክ (መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን የምታርቅ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን የምታድል) ነኽ) በማለት ልዩ ምስጋናዋን ዠምራ እስከ ሌሊቱ ድረስ በልዩ ምስጋና እየሰበከችው በኋላም ቤተ መቅደሱን በውርጫዋ ተቀምጦ እንደዞረ በአራቱ መኣዝን የጌትነቱ ወንጌል እየተነበበ፤ ካህናቱን ምእመናንም በእጃቸው የዘንባባ ዝንጣፊን ይዘው “ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም” እያሉ ያመሰግኑታል፡፡
ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
(ነገረ ክርስቶስ ከሚለው መጽሐፌ ገጽ 616-617 በጥቂቱ የተወሰደ)
መልካም በዓል ይኹንልን

Sunday, 3 April 2016

sibikettt

 

«ከዚህም በላይ የምታወጣውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ፤»
          ዲናር፦ የሮሜ መንግሥት የብር ምንዛሪ ሆኖ ያገለገለ ከሁሉ ያነሰ የናስ ሳንቲም ነው ፥ መጠኑም አሥራ ስድስት ሳንቲሞች ነበር። በዚያን ዘመን የአንድ ቀን የሠራተኛ ደሞዝ ሆኖ ይከፈል ነበር። ማቴ ፳፥፪። ጌታችንን በንግግር ሊያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑ ሰዎች ወደ እርሱ ተልከው መጥተው «ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ፥ ወይስ አልተፈቀደም? እንስጥን፥ ወይስ አንስጥ?» በማለት ጠይቀውት ነበር። እርሱ ግን ግብዝነታቸውን እና ተንኰላቸውን አውቆ፦ «ለምን ትፈትኑኛላችሁ? አንድ ዲናር አምጥታችሁ አሳዩኝ፤» አላቸው። ባመጡለትም ጊዜ፦ «ይህ፦ መልኩ ጽሕፈቱስ የማን ነው? » አላቸው፤ እነርሱም፦ «የቄሣር ነው፤» አሉት። እርሱም መልሶ፦ «የቄሣርን ለቄሣር ስጡ፤ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አድርጉ፤» አላቸው። ምክንያቱም፦ የንጉሥ የሆነ እንደሆነ፦ ስመ ንጉሥ ይጻፍበታል ፥ ሥእለ አንበሳ ይቀረጽበታል፤ የእግዚአብሔር ሲሆን ደግሞ፦ ስመ አምላክ ይጻፍበታል፥ ሥዕለ ኪሩብ ይቀረጽበታል።
፩፥፩፦ «የዘለዓለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?»
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፦ ደቀመዛሙርቱን ለብቻቸው አድርጎ «እናንተ የምታዩትን የሚያዩ ዓይኖች ብፁዓን ናቸው። ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ተመኙ ፥ አላዩምም፤ እናንተ የምተሰሙትንም ሊሰሙ ተመኙ ፥ አልሰሙም።» ካላቸው በኋላ እንደ ሕግ አዋቂ (ሕገ ኦሪትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው) ወደ እርሱ መጣ። ሊፈትነውም፦ «መምህር ሆይ ፥ የዘለዓለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? (የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያትን የምወርሰው ምን ሠርቼ ነው?) አለው። ጌታችንም፦ «በሕግ የተጻፈው ምንድርነው? እንዴትስ ታነባለህ?» በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መልሶለታል። ሕግ አዋቂውም ከኦሪት ዘዳግም ጠቅሶ፦ «እስራኤል ሆይ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ (አሳብህ) ፥ በፍጹም ነፍስህ (ሰውነትህ) ፥ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ። ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ፤» ይላል ፥ ሲል መለሰለት። ዘዳ ፮፥፭። በዚህን ጊዜ ጌታችን፦ «እውነት መለስህ፤ ይህን አድርግ፥ በሕይወትም ትኖራለህ፤» በማለት አዘዘው።
          ይህ ሰው የዕውቀት ባዕለጸጋ የተግባር ደሀ ነው፤ እንዲሁ በዕውቀቱ እየተመጻደቀ የሚኖር ሰው ነው፤ አመጣጡም ውዳሴ ከንቱን ሽቶ እንጂ ሕይወትን ፈልጎ አይደለም። ጌታ ሊቅነቴን ይመሰክርልኛል ብሎ ነው፤ በዚህም እርሱን በተከተለው አምስት ገበያ ሕዝብ ፊት ሞገስን ለማግኘት ነው። ዛሬም አገልግሎታቸው ሁሉ ሊቅ ለመባል ብቻ የሆነባቸው ሰዎች አሉ፤ እነዚህም መንፈሳዊ ዕውቀት እንጂ መንፈሳዊ ሕይወት ፈጽሞ የማይገኝባቸው ናቸው፤ ከዚህም የተነሣ ገንዘብ አድርገው የሚኖሩት፦ሰውን መናቅና እግዚአብሔርን መድፈር ነው። አንደበታቸው ስለ ሕይወት ይናገራል ፥ ይተረጉማል ፥ ያዜማል፥ ይቀኛል ፥ ልባቸው ግን በትዕቢት፣ በግብዝነት የተያዘ ፍጹም ሥጋዊ ነው። ይኽንን በተመለከተ፦ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፦ «አንተ ግን አይሁዳዊ ብትባል ፥በሕግም ብትደገፍ ፥ በእግዚአብሔርም ብትመካ ፥ ፈቃዱንም ብታውቅ ፥ ከሕግም ተምረህ የሚሻለውን ፈትነህ ብትወድ ፥ በሕግም የዕውቀትና የእውነት መልክ ስላለህ ፥ የዕውሮች መሪ ፥ በጨለማም ላሉ ብርሃን ፥ የሰነፎችም አስተማሪ ፥ የሕፃናትም መምህር እንደሆንህ በራስህ ብትታመን ፥ እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን? በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን? በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደ ተጻፈ።» ብሏል። ሮሜ ፪፥፲፯-፳፬።
፩፥፪፦ «ባልንጀራዬ ማነው?
          መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ዕውቀት በትህትና የሚያገለግሉበት እንጂ የሚመኩበት ፥ የሚመጻደቁበት አይደለም። እነ አርዮስ ፥ እነ ንስጥሮስ በመንፈሳዊ ዕውቀታቸው ሲፈላሰፉ ፥ ሲመጻደቁ ጠፉበት እንጂ አልዳኑበትም። ሥጋዊውም የዕውቀት ሰው ከተራ ጠመንጃ እስከ ኒዩክለር ድረስ የሠራው ፥ የፈለሰፈው ረቂቅ መሣሪያ መጥፊያው እንጂ መዳኛው አይደለም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ ፥ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ፥ ተብሎ ተጽፎአልና። ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚህችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች ፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና።» ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ቆሮ ፩፥፲፱-፳፩። 
          የሕገ ኦሪቱ ሊቅ፦ ምን ማድረግ እንዳለበት ፥ መጽድቂያውን ፥ ጌታችን በነገረው ጊዜ፦ እርሱ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ፦ «ባልንጀራዬ ማን ነው?» አለ። «የሚመስለኝ ፥ የሚተካከለኝ ማነው?» ማለቱ ነው። ራሱን ከጉልላቱ ላይ ያስቀመጠ ሰው በመሆኑ የትዕቢት ንግግር ነው። ትዕቢት ደግሞ ዲያቢሎስ የተያዘበት አሸክላ ነው ፤ ኢሳ ፲፬፥፲፪። ቅዱስ ያዕቆብ እንደተናገረው፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ያዕ ፬፥፮። ጠቢቡ ሰሎሞንም፦ «ሰውን ትዕቢቱ ያዋርደዋል፤» ብሏል። ምሳ ፳፱፥፳፫።
፩፥፫፦ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ፤
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በሊቅነቱ ብቻ ተመክቶና ተመጻድቆ፦ «ባልንጀራዬ ማነው?» ያለውን ሰው ያስተማረው በምሳሌ ነው። ምሳሌውም፦ «አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ይወርድ ነበር፤ ሽፍቶችም አገኙት፤ ደበደቡት ፥ አቈሰሉት ፥ልብሱንም ገፍፈው በሕይወትና በሞት መካከል ጥለውት ሄዱ። አንድ ካህንም በዚያች መንገድ ሲወርድ ድንገት አገኘው፤ አይቶም አልፎት ሄደ። እንዲሁም አንድ ሌዋዊ በዚያ ቦታ አገኘውና አይቶ እንደፊተኛው አልፎት ሄደ። አንድ ሳምራዊ ግን በዚያች መንገድ ሲሄድ አገኘው፤ አይቶም አዘነለት። ወደ እርሱም ቀረበ፤ ቊስሉንም አጋጥሞ አሰረለት፤ በቊስሉ ላይም ወይንና ዘይት ጨመረለት፤ በአህያውም ላይ አስቀምጦ እንዲፈውሰው የእንግዶችን ቤት ወደ ሚጠብቀው ወሰደው፤ የሚድንበትንም ዐሰበ፤ በማግስቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዳ ቤት ጠባቂው ሰጠውና፦ በዚህ አስታምልኝ፤ ከዚህ የሚበልጥ ለእርሱ የምታወጣው ቢኖር እኔ በተመለስሁ ጊዜ እከፍልሃለሁ፥ አለው። እንግዲህ ሽፍቶች ለደበደቡት ሰው ከእነዚህ ከሦስቱ ባልንጀራ የሚሆነው ማንኛው ይመስልሃል? ሲል ጠየቀው ፤ እርሱም፦ ምሕረት ያደረገለት ነዋ አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም፦ እንኪያስ አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ አለው።»የሚል ነው። ሉቃ ፲፩፥፳፱-፴፯።
          ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ መውረድ ማለት፦ ከፍ ካለ ሥፍራ ወደ ዝቅተኛው ሥፍራ መውረድ ማለት ነው። ትርጉሙም፦ ከብሮ መዋረድን ፥ተሹሞ መሻርን ፥አግኝቶ ማጣትን ያመለክታል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፦ «ገዢዎችን ከዙፋናቸው አዋርዷል፤ . . .  ባለጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል፤» ያላችው እንዲህ ዓይነቱን ነው። ሉቃ ፩፥፶፪ ፣ መዝ ፻፵፮፥፮።
፩፥፬፦ ኢያሪኮ፤
          ኢያሪኮ፦ ከጨው ባሕር በስተሰሜን አሥራ አምስት ኪ.ሜ. ፥ ከኢየሩሳሌም ደግሞ ሃያ አምስት ኪሜ ርቆ የሚገኝ ከተማ ነው። ኢያሪኮ ማለት፦ የጨረቃ ከተማ ማለት ነው፥ ይኸውም በኢያሪኮ የኖሩ የጥንት ሰዎች ጨረቃን ስላመለኩ ነው። በኢያሪኮ ዙሪያ ብዙ የውኃ ምንጮች ስላሉ ከጥንት ጀምሮ ሰዎች በዚያ መኖር ጀምረዋል። ዘዳ ፴፬፥፫። የፊተኛዋን ከተማ በታቦቱ ላይ በተገለጠ ኃይለ እግዚአብሔር ኢያሱ ወልደ  ነዌ አፍርሶታል። ኢያ ፮፥፩። አኪኤል የተባለው የቤቴል ሰው ደግሞ እንደገና ሠርቶታል። ፩ኛ ነገ ፲፮፥፴፬። በኢያሪኮ ብዙ የኦሪት ካህናት ነበሩ፤ ሉቃ ፲፥፴፩። በአዲስ ኪዳን ጌታችን የበርጤሜዎስን ዓይን ያበራው በኢያሪኮ ነው፤ ማር ፲፥፵፮። ዘኬዎስንም የጎበኘው በዚሁ ከተማ ነው። ሉቃ ፲፱፥፩። ይህንን ከተማ ሮማውያን በ67 ዓ.ም. አፍርሰውታል። ኢያሪኮ ሁለት መቶ ሃምሣ ሜትር ከባሕሩ ጠለል ዝቅ ስለሚል ከዓለም ከተሞች ሁሉ ዝቅተኛ ነው።
፩፥፭፦ ኢየሩሳሌም
          ኢየሩሳሌም፦ ማለት፦ የሰላም ከተማ ማለት ነው፤ የዮርዳኖስ ወንዝ ወደ ጨው ባሕር ከሚገባበት በምዕራብ ሠላሳ ኪ.ሜ.፥ ከታላቁ ባሕር ደግሞ ሃምሣ ኪ.ሜ. ርቃ በተራራማ ሀገር የምትገኝ ከተማ ናት። ከባሕር ወለልም ሰባት መቶ ሃምሣ ሜትር ገደማ ከፍ ትላለች። ጥንታዊ ስሟ ሳሌም ነበር፥ ቀጥሎም፦ ኢያቡስ ፣ ፆፌል ፣ ጽዮን ተብላለች፤ ዘፍ ፲፬፥፲፰ ፣ ኢያ ፲፭፥፷፫ ፤ ፲፰፥፲፮፤ ፪ኛ ዜና ፳፯፥፫፤ ፴፫፥፲፬፤ መዝ ፻፴፮፥፩። ቅድስት ከተማ ተብላም ተጠርታለች፤ ነህ ፲፩፥፩። ንጉሥ ዳዊት ኢየሩሳሌምን ከኢያቡሳውያን ከወሰዳት በኋላ የእስራኤል ሁሉ በተለይም የይሁዳ ዋና ከተማና መስገጃ አደረጋት ፤ ፪ኛ ሳሙ ፭፥፮-፲።
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። ወራት ይመጣብሻልና ፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ፥ ይከቡሻልም ፥ በየበኲሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽኝ ወደ ታች ይጥላሉ ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም ፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።» እያለ አልቅሶላታል። ሉቃ ፲፱፥፵፮። የዓለምን መጨረሻ ምልክቶች በተናገረበት አንቀጽም፦ «ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።» በማለት ተናግሯል። ሉቃ ፳፩፥፳። ሥጋውን በመቁረስ፥ ደሙን በማፍሰስ፥ ነፍሱንም አሳልፎ በመስጠት ድኅነተ ዓለምን የፈጸመው በዚያ ነው። ይኽንንም ነቢዩ ዳዊት፦ «እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ።» በማለት ተናግሯል። መዝ ፸፫፥፲፪። ነቢዩ ዳዊት ማዕከለ ምድር ያለው ኢየሩሳሌምን ነው። «ኢየሩሳሌም ሆይ ፥ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ። ባላስብሽ፥ ምላሴ በጉሮሮዬ ይጣበቅ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ።» ያለበት ጊዜም አለ። መዝ ፻፴፮፥፭።
          ኢየሩሳሌም፦ ሕገ ኦሪትም ሕገ ወንጌልም የሚሠራባት ፥ ድኅነተ ምእመናንም የሚፈጸምባት በመሆኗ ነቢያት ሁሉ ትንቢት የተናገሩት ለርሷ በርሷ ነው። ቅዱሳን ሐዋርያትም የሰበኩት ለርሷ በርሷ ነው። ኢየሩሳሌም የትንቢት መድረሻ፥የድኅነት መፈጸሚያና ፥ የስብከት መነሻ ከመሆኗም በላይ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያምና ለገነት ለመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናት።
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በወንጌል፦ ኢየሩሳሌምን፦ «የታላቁ ንጉሥ ከተማ ብሏታል።» ማቴ ፭፥፴፭። ይኸውም፥ ለጊዜው፦ ምድሪቱን ሲሆን ለፍጻሜው እመቤታችንን ፥ አንድም ገነት መንግሥተ ሰማያትን ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነፃነት የምትኖር ናት ፥ እርስዋም እናታችን ናት።» ብሏል። ገላ ፭፥፳፭። በዕብራውያን መልእክቱም ላይ፦ «ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል ፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም ፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት ፥ በሰማያትም ወደተጻፉ ወደ በኲራት ማኅበር ፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር ፥ ፍጹማንም ወደሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች ፥ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል፤» ብሏል። ዕብ ፲፪፥፳፪-፳፬። በራእይ ዮሐንስ ላይ ደግሞ፦ «ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ ፥ ወደፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬ ስምና የአምላኬ ከተማ ስም ፥ ማለት ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን ፥ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ፤» የሚል አለ። ራእ ፫፥፲፪። በተጨማሪም፦ «አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርንም አየሁ ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ፤» የሚል ተጽፏል። ራእ ፳፩፥፩-፪።   
፩፥፮፦ በወንበዴዎች እጅ መውደቅ፤
          ከፍ ብላ ከምትገኘው ከኢየሩሳሌም በጣም ዝቅተኛ ወደሆነው ሥፍራ ወደ ኢያሪኮ የወረደው ሰው የአዳም ምሳሌ ነው። ይኸውም ከልዕልና ወደ ትህትና መውረዱን፥ ከመታዘዝ ወደ አለመታዘዝ መጓዙን የሚያመለክት ነው። ወንበዴ የተባለው ደግሞ፦ ከማዕረጉ የተዋረደ ፥ ከሥልጣኑ የተሻረ ዲያቢሎስ ነው። የቀደመ ሰው አዳም፦ የነቢይነት ፥ የንጉሥነት ፥ የካህንነት ፥ የጸጋ አምላክነት(ገዢነት) መንፈሳዊ ሀብት ተስጥቶት በክብር ፣በልዕልና በገነት ይኖር ነበር። በዚህ ዓይነት በፍጹምነት ለሰባት ዓመታት ከኖረ በኋላ ወንበዴዎች የተባሉ አጋንንት አግኝተውት አስተው ልጅነቱን አስወስደውበታል። መርገመ ሥጋ ፥ መርገም ነፍስ ወድቆበት በነፍስም በሥጋም እንዲቆስል አድርገውታል። በዚህም በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ ፥ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ተጨምሮ እንዲፈረድበት ሆኗል። ልብስን እንደመገፈፍ ጸጋውን ሁሉ ተገፍፏል ፥ ከማዕረጉ ተዋርዶ፥ ከሥልጣኑ ተሽሮ ፥ ከገነት ተባርሮ ወደ ምድረ ፋይድ ተጥሏል።
፩፥፯፦ አንድ ካህን አይቶት ገለል ብሎ አለፈ፤
«መልከ ጼዴቅ፤»
          አንድ ካህን የተባለው መልከጼዲቅ ነው፤ መልከጼዴቅን ለክህነት መርጦ በማይመረመር ግብር የሾመው እግዚአብሔር ነው፤ እነ አሮን በተሾሙበት ሥርዓት፦ ተቀብቶ ፥ መሥዋዕት ተሠውቶ ፥ የከበረ ልብስ ለብሶ፥ የተሾመ አይደለም። ከሰው ወገን ከእገሌ ተቀብቶ የተሾመ ነው ፥ አይባልም፤ ከእርሱም በኋላ ሹመት ለእገሌ ተላልፏል አይባልም።
          የመልከ ጼዴቅ ክህነቱ በኖኅና በሴም ዘንድ ይታወቅ ነበር ፥ ይኸውም ምሥጢሩን እግዚአብሔር ስለገለጠላቸው ነው። ሴምም ከወገኖቹ ማንም ሳያውቅ ዓፅመ አዳምን ሊያስጠብቀው መልከ ጼዴቅን ወደ ጎልጎታ ይዞት ሄዷል። መልከ ጼዴቅም በእጁ ደም እንዳይፈስስ ተጠብቆ ፥ በንጹሕ ስንዴና ወይን በተዘጋጀ መሥዋዕት እያስታኰተ በብሕትውና ፣ በድንግልና ኖሯል። በታዘዘው መሠረት ፀጉሩን ተላጭቶ፥ ጥፍሩንም ተቆርጦ አያውቅም ፥ ኑሮውም በዓት አጽንቶ በዋሻ ነበር።
          መልአከ እግዚአብሔር እየረዳውም ከሰው ወገን ለማንም ሳይገለጥ እስከ አብርሃም ዘመን ቆይቷል። አብርሃም፦ አምላክ፦ ከእርሱ ወገን ሰው ሆኖ ከሚወለድበት ዘመን ደርሶ ለማየት ይፈልግ ነበር። እግዚአብሔር ግን «ከዚያ ዘመን አትደርስም ፥ ዮርዳኖስን ተሻግረህ ምሳሌዬን ታያለህ፤» ብሎታል። እንደተባለውም፦ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ፥ መልኬ ጼዴቅን አግኝቶ ፥ ከሁሉ አሥራት አውጥቶ ሰጥቶታል ፥ መልኬ ጼዴቅ ደግሞ ለሥጋ ወደሙ ምሳሌ የሆነውን ኅብስት በመሶበ ወርቅ ወይንኑም በጽዋ አድርጐ ሰጥቶታል። ዘፍ ፲፬፥፲፯። በዚህም ጌታን እንዳየ ተደርጎ ተቆጥሮለታል። ይኽንንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል፦ «አባታችሁ አብርሃም የእኔን ቀኔን ያይ ዘንድ ተመኘ፤ አይቶም ደስ አለው።» በማለት መስክሮለታል። ዮሐ ፰፥፶፮። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ፦ ለእግዚአብሔር ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ እንደኖረ በዝርዝር ጽፎለታል። ዕብ ፯፥፩-፫።
          እንግዲህ፦ ጌታችን በምሳሌው፦ በወንበዴዎች እጅ የቈሰለውን ሰው፦ «አንድ ካህን አይቶት ገለል ብሎ አለፈ፤» ማለቱ፦ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ የኖረው ፥ ካህኑ መልከጼዴቅ የሠዋው የስንዴና የወይን መሥዋዕት፦ ለቊስለኛው ለአዳም ምንም እንዳልጠቀመው ለመግለጥ ነው።
፩፥፰፦ አንድ ሌዋዊ አይቶት አለፈ፤
          ሌዊ፦ ከያዕቆብ አሥራ ሁለት ወንዶች ለጆች መካከል ሦስተኛው ነው። ዘፍ ፳፱፥፴፬። እኅቱን ዲናን ከአሕዘብ ወገን አንዱ ከክብር ባሳነሳት ጊዜ የሴኬምን ሰዎች ተበቅሏቸዋል፤ ይኽንንም ያደረገው ከወንድሙ ከስምዖን ጋር ነው። አባታቸው ያዕቆብ ግን፦ «በዚች ሀገር በሚኖሩ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ሰዎች የተጠላሁ ታደርጉኝ ዘንድ እኔን አስጨነቃችሁኝ፤ እኔ በቊጥር ጥቂት ነኝ፤ እነርሱ በእኔ ላይ ይሰበሰቡና ይመቱኛል። እኔም ከወገኔ ጋር እጠፋለሁ።» ብሎ አልተደሰተባቸውም። እነርሱም፦ «በጋለሞታ እንደሚደረግ በእኅታችን ያድርግባትን?» አሉ። ዘፍ ፴፬፥፩-፴፩።
          ያዕቆብ፦ በግብፅ ምድር በነበሩበት ጊዜ ፥ በኋለኛው ዘመን የሚያገኛቸውን ሁሉ ዘርዝሮ ለልጆቹ ነግሯቸዋል። ከዚህም መካከል፦ «ስምዖን እና ሌዊ ወንድማማቾች ናቸው ፤ ሰይፎቻቸው የዓመፃ መሣሪያ ናቸው። (ብዙ ደም አፍስሰዋል)። በምክራቸው ነፍሴ አትግባ፤ (ሰውነቴ በበረከት አትገናኛቸውም)፤ በቊጣቸው ሰውን ገድለዋልና፥ (ተቈጥተው የሴኬምን ሰዎች አጥፍተዋልና) ፥ በገዛ ፈቃዳቸውም የሀገርን ሥር ቈርጠዋልና። (ከአባታቸው አልተማከሩም ፥ ፈቃዱን አልጠየቁም)። ቊጣቸው ርጉም ይሁን፤ ጽኑ ነበርና፤ ኲርፍታቸውም ብርቱ ነበርና፤ በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ፤ በእስራኤልም እበትናቸዋለሁ።» የሚል አለ። ዘፍ ፵፱፥፭-፯።
          ሌዊ ከእስራኤል ነገዶች የአንዱ አባት ነው ፥ ሌዋውያን ይባላሉ፤ ዘፍ ፵፮፥፲፩። በሙሴ ዘመን የሌዊ ልጆች ፥ የሙሴን ትእዛዝ አክብረው፥ ፍቅረ ጣዖት ያደረባቸውን ሳይራሩ በማጥፋታቸው፦ «ዛሬ በረከትን እንዲያወርድላችሁ ከእናንተ እያንዳንዱ ከልጁና ፥ከወንድሙ የተነሣ እግዚአብሔርን ደስ አሰኛችሁት፤» ተብለዋል። ዘጸ ፪፥፩ ፤ ፮፥፲፮-፳፯። ክህነት የተሰጠው ለሌዊ ነገድ በመሆኑ አሮንና ልጆቹ ተቀብተው ተሹመዋል። ዘጸ ፳፰፥፩። ሌዋዊያን በጠቅላላ ለእግዚአብሔር አገልግሎት በመለየታቸውም ሥራቸውና አገልግሎታቸው በኦሪት ዘሌዋውያን ተገልጦአል። ሙሴ፦ ለመጨረሻ ጊዜ ሕዝቡን ሲባርክ ፥ ስለ ሌዊ፦ «ለሌዊ ቃሉን ፥ በመከራም ለፈተኑት ፥ በክርክር ውኃም ለሰደቡት ፥ ለእውነተኛው ሰው ጽድቁን መልስ። እናቱንና አባቱን አላየኋችሁም ላለ ፥ ወንድሞቹንም ላላወቀ ፥ ልጆቹንም ላላስተዋለ፤ ቃልህን ለጠበቀ ፥ በቃል ኪዳንህም ለተማጠነ። ፍርድህን ለያዕቆብ ፥ ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፤ በማዕጠንትህ ዕጣንን፥ በመሠዊያህም የሚቃጠል መሥዋዕትን ሁሌጊዜ ያቀርባሉ። አቤቱ ኃይሉን ባርክ፤ የእጁንም ሥራ ተቀበል፤ በሚቃወሙት ጠላቶቹ ላይ መከራን አውርድ፤ የሚጠሉትም አይነሡ፤» ብሏል። ዘዳ ፴፫፥፰-፲፩።
          ሌዋውያን በከነዓን የርስት ድርሻ ሳይሆን አርባ አምስት ከተሞች ተሰጥተዋቸዋል፤ እንደ ርስት ሆኖ የተሰጣቸው የእሥራኤል ልጆች የሚያወጡትን አሥራት ነበር። ይኽንንም ያደረገው እግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር አሮንን፦ «በምድራቸው ርስት አትወርስም፤ በመካከላቸውም ድርሻ አይሆንልህም፤ በእስራኤል ልጆች መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ፤ ለሌዊም ልጆች እነሆ፥ በምስክሩ ድንኳን አገልግሎት ስለሚያገለግሉ የእስራኤልን ልጆች ዐሥራት ርስት አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ።» ብሎታል። ዘኁ ፲፰፥፳-፳፩ ፣ ኢያ ፳፩፥፩-፵፭።
          ሌዋውያን ካህናት፦ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት አምስት ዓይነት መሥዋዕቶችን ሲያቀርቡ ኖረዋል። እነርሱም፦ የሚቃጠል መሥዋዕት ፥ የእህል ቊርባን ፥ የደኅንነት መሥዋዕት ፥ የኃጢአት መሥዋዕትና የበደል መሥዋዕት ናቸው። ዘሌዋውያን ከምዕራፍ ፩-፭። በዚህም ምክንያት፦ የአያሌ እንስሳት ደም ፈስሷል። እንግዲህ፦ «አንድ ሌዋዊ ወንበዴዎች ያቆሰሉትን ሰው አይቶት ገለል ብሎ አለፈ፤» ማለት፦ ሌዋውያን ካህናት ሲሠዉት የኖሩት መሥዋዕት ፥ የፈሰሰው ያ ሁሉ የእንስሳት ደም ወንበዴዎች የተባሉ አጋንንት በነፍስም በሥጋም ላቆሰሉት አዳም አልጠቀመውም ፥ አልረባውም ፥ አላዳነውም ፥ ማለት ነው። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፦ «የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና። . . .  መሥዋዕትንና መባን በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ስለኃጢአትም የሚሠዋ መሥዋዕትን አልወደድህም፥ በእርሱም ደስ አላለህም። . . . ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል።፤» ብሏል። ዕብ ፲፥፬-፲፩። በመሆኑም ከሊቀ ካህናቱ ከአሮን ጀምሮ እስከ ሊቀ ካህናት ሐና እና ቀያፋ ድረስ የተሠዋው መሥዋዕት ከአዳም ኃጢአት ዓለምን ማዳን አልቻለም። እነርሱ ራሳቸውም አልዳኑም።
፩፥፱፦ ደጉ ሳምራዊ፤
          ሳምራውያን፦ በሰማርያ የኖሩ ህዝብ ናቸው። ሰማርያ ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን ስድሣ አምስት ኪ.ሜ. ርቆ የሚገኝ ከተማ ነው። የእስራኤል ንጉሥ ዘንበሪ ተራራውን ገዝቶ ከተማ ሠርቶበት መናገሻም መስገጃም አድርጎታል። ፩ኛ ነገ ፲፮፥፳፬-፴፪። የሰሜኑ መንግሥት አንዳንድ ጊዜ ሰማርያ እየተባለ ይጠራ ነበር። ፩ኛ ነገ ፲፫፥፴፪ ፣ አሞ ፫፥፱። በአዲስ ኪዳን ዘመን በገሊላና በይሁዳ መካከል ያለው ሀገር ሰማርያ ይባል ነበር። ዮሐ ፬፥፬ ፣ የሐዋ ፩፥፰
          የአሦር ነገሥታት ስልምናሶርና ሳርጎን ሰማርያን ከያዙ በኋላ ዋና ዋና የተባሉ ሰዎችን ማርከው ወስደው ነበር። በእነርሱም ምትክ ብዙ ሰዎችን ከልዩ ልዩ አገር አምጥተው አስፍረዋል። እንዲህም ማድረጋቸው ለሃይማኖትና ለሀገር የሚቆረቆር ሰው እንዳይኖር ነው። ቀስ በቀስ በመጀመሪያ፦ ሥርዓታቸውን ፣ ባሕላቸውን ፣ ታሪካቸውን ፥ ቀጥሎም ሃይማኖታቸውን ለማጥፋት ነው። የመጡትም ሰዎች ከአይሁድ ጋር እየተጋቡ ተዋለዱ። በሂደትም ፈሪሃ እግዚአብሔር እየጠፋ፥ የድፍረት ኃጢአት እየሰፋ ሄደ። በዚህም ምክንያት የአንበሳ መንጋ ታዘዘባቸው ፥ እነርሱም መዓቱን በምሕረት እንዲመልስላቸው እግዚአብሔርን ማምለክ ፈለጉ፤ በዚህን ጊዜ የሙሴን ሕግ የሚያስተምራቸው ካህን ተላከላቸው። 2ኛ ነገ ፲፯፥፳፬-፴፫።
          አይሁድ ከባቢሎን ምርኮ ሲመለሱ ሳምራውያን አብረው የፈረሰውን ቤተ መቅደስ ለመሥራት ቀርበው ነበር። ዘሩባቤል ግን ጥንታውያን የእሥራኤል ዘር ባለመሆናቸው አልተቀበላቸውም። ዕዝ ፬፥፩-፬። ነህምያም ከእስራኤል አስወጥቷቸዋል። ነህ ፲፫፥፬-፱። ሳምራውያን በገሪዛን ተራራ የራሳቸውን ቤተ መቅደስ የሠሩት ከዚህ በኋላ ነው። ሳምራዊቷ ሴት ኢየሱስ ክርስቶስን፦ «አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተ ግን ይሰግዱበት ዘንድ የሚገባው ሥፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ» ያለችው ለዚህ ነው። ዮሐ ፬፥፳።
          አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይገናኙም ነበር ፥ ከእጃቸው ተቀብለው መብላትንም ሆነ መጠጣትን እንደ ርኲሰት ይቆጥሩት ነበር። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰማርያዋን ሴት፦ «ውኃ አጠጪኝ፤» ባላት ጊዜ፦ «አንተ አይሁዳዊ ስትሆን እኔም ሳምራዊት ስሆን እንዴት ከእኔ ዘንድ ውኃ ትለምናለህ? » ያለችው በዚያ ልማድ መሠረት ነው። ዮሐ ፬፥፯። ሳምራዊ መባልም እንደ ንቀት ነበር ፥ ለእርሱ ለጌታችን ክብር ምስጋና ይግባውና፦ አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስን «አንተ ሳምራዊ እንደሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ (ሎቱ ስብሐት) መናገራችን በሚገባ አይደለምን?» ያሉት ለዚህ ነው። ዮሐ ፰፥፵፰። ሳምራውያን ሕገ ኦሪትን እንጂ ትንቢተ ነቢያትን አይቀበሉም ነበር።
          ደጉ ሳምራዊ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው። ሳምራዊ ማለት ሀገር ጠባቂ ማለት ነው፥ እየሱስ ክርስቶስም እረኛችን ጠባቂያችን ነው፤ ዮሐ ፲፥፲፩ ፣፩ኛ ጴጥ ፪፥፳፬። ሀገር ጠባቂ ሀገርን የሚጠብቀው ራሱን ለሞት አሳልፎ በመስጠት ነው፥ እየሱስ ክርስቶስም እኛን በነፍስም በሥጋም የጠበቀን ራሱን ለመስቀል ሞት አሳልፎ ሰጥቶ ነው፤ የሳምራዊ ትውልዱ ከሕዝብ (ከእስራኤል) እና ከአሕዛብ ነው፥ የኢየሱስ ክርስቶስም ትውልዱ ከሕዝብም ከአሕዘብም ነው።
          ደጉ ሳምራዊ ቊስለኛውን በሩቅ አይቶ አዘነለት ፥ቀርቦም በቊስሉ ላይ ወይንና ዘይት አፈሰሰለት፤ ወይኑ፦ የቊስለኛውን ደም እንዲያቆምለት እንዲያደርቅለት ነው። ቊስል ቶሎ የሚደርቀው ከላይ ነው፥ ወዲያውም እየተሰነጣጠቀ ያሰቃያል፤ ለዚህም መከላከያ እንዲያለሰልስለት ዘይቱን አፍስሶለታል። ጌታችንም በሩቅ ማለትም በሰማይ መንበሩ ተቀምጦ ቊስለኛውን አዳም በዓይነ ምሕረቱ አየው ፥ ገጸ ምሕረቱን መለሰለት፤ ቀረበውም። (ባሕርዩን ባሕርይ አደረገ ፥ የባሕርዩ መመኪያ ከሆነች ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ፥ ያንን ተዋሕዶ ሰው ኹኖ ተወለደ)። ወይን እንደማፍሰስ ፦ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ፥ ሥጋውን ቆረሰለት ደሙን አፈሰሰለት። ጌታችን የጸሎተ ሐሙስ ዕለት ወይኑን በጽዋ አድርጎ፦ «ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤» ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፳፮፥፳፯።
          እንደ ዘይት ደግሞ የመንፈሰ ቅዱስን ጸጋ ሰጥቶታል። ይኽንን በተመለከተ ቅዱስ ዳዊት፦ «ወይን (የክርስቶስ ደሙ) የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥ ዘይትም ፊትን ያበራል ፥(መንፈስ ቅዱስ ሰውን ብሩኅ መልአክ ያስመስለዋል) ፥ እህልም (የክርስቶስ ስንዴ ሥጋው) የሰውን ጉልበት (ነፍስን) ያጠናክራል።» ብሏል። መዝ ፻፫፥፲፭። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም፦ «እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋልና ሁሉንም ታውቃላችሁ።» ያለው ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ነው።
          ደጉ ሳምራዊ ከአህያው ወረዶ ቊስለኛውን ማስቀመጡ የሚያመለክተው፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ መንበሩ መውረዱንና የአዳምን ሥጋ በዕርገት በሰማይ መንበሩ ማስቀመጡን ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «በኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያዊ ሥፍራ ከእርሱ ጋር አስቀምጠን፤» ያለው ይኽንን ምሥጢር ይዞ ነው። ኤፌ ፪፥፯። ምክንያቱም በተዋሕዶ አምላክ የሆነ ሥጋ በሰማይ የእሳት መንበር ተቀምጧልና። ቅዱስ እስጢፋኖስ በመከራው ጊዜ ሰማይ ተከፍቶለት(ምሥጢር ተገልጦለት) ፊት ለፊት አይቷል። የሐዋ ፯፥፶፭።
          ደጉ ሳምራዊ፦ ያከመውን ቊስለኛ ለእንግዶች ቤት ጠባቂ ማስረከቡ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ፈሳሽነት ያከማቸውን ምእመናን ለመምህራን የማስረከቡ ምሳሌ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስን፦ «ግልገሎቼን አሰማራ ፥ ጠቦቶቼን ጠብቅ ፥ በጎቼን አሰማራ፤» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፳፩፥፲፭። ሁለት ዲናሮች ደግሞ የሁለቱ ማለትም የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ምሳሌዎች ናቸው። የሰው ሕይወቱ የሚጠበቀው በእነዚህ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ፥ ለትምህርትና ለተግሣፅ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።» ያለው ለዚህ ነው። ፪ኛ ጢሞ ፫፥፲፮። በኤፌሶን መልእክቱም ላይ ፦ «በሐዋርያት (በአዲስ ኪዳን) እና በነቢያት (በብሉይ ኪዳን) መሠረት ላይ ታንጻችኋል ፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።» ብሏል። ኤፌ ፪፥፳።
          እግዚአብሔር፦ ነቢዩ ሕዝቅኤልን፦ «የሰው ልጅ ሆይ! ያገኘኸውን ብላ፤ ይህን መጽሐፍ ብላ፤ ሄደህም ለእስራኤል ልጆች ተናገር።» ያለው ቅዱሳት መጻሕፍትን ነው። እርሱም፦ «የሰው ልጅ ሆይ! አፍህ ይብላ፤ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ። እኔም በላሁት፤ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ፤» ብሏል። ሕዝ ፫፥፩-፬። በመሆኑም፦ በሁለት ዲናር የተመሰሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ምግበ ነፍስ ናቸው። ቅዱስ ዳዊትም፦ «ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ጣፈጠኝ።» ብሏል። መዝ ፻፲፰፥፻፫።
          ደጉ ሳምራዊ የእንግዳ ቤት ጠባቂውን፦ «ከሁለት ዲናር በላይ ብታወጣ እኔ በተመለስኩ ጊዜ እከፍልሃለሁ፤» አለው እንጂ፥ «ዋጋ የለህም፤» አላለውም። ይህም የሚያመለክተው፦ መምህራን የተሰጣቸውን፦ ሁለት ዲናር (ብሉይ ኪዳንን እና አዲስ ኪዳንን) ይዘው ፥ የምእመናንን ሕይወት ለመጠበቅ ሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍትን ቢጽፉ፥ ጌታ ሲመጣ የድካማቸውን ዋጋ እንደሚከፍላቸው ነው። ቅዱሳን ሊቃውንት፦ መጽሐፍ ቅዱስን ለማብራራት ፥ ንባቡን በመተርጐም ፥ ምሥጢሩን በማራቀቅ አያሌ መጻሕፍትን ጽፈዋል። እነዚህም አዋልድ መጻሕፍት ይባላሉ። የቅዱሳት መጻሕፍት ልጆች ማለት ነው። የገድል የድርሳን እና የተአምር መጻሕፍት ቊጥርም ከአዋልድ መጻሕፍት ነው። እነርሱም የእግዚአብሔር ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንዴት እንደፈጸሙ፥ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን የሚያሳይ ነው። መጻፍ ማጻፍም ፥ መስማት ማሰማትም ዋጋ አለው።
          እንግዲህ በተሰጡን ሁለት ዲናሮች ሥራ እንድንሠራ ፥ ሌሎችንም ቅዱሳት መጻሕፍት በመጻፍና በማጻፍ እንድንመክርና እንድንመክር ፥ የተሰጠንን አደራ እንድንጠብቅ ፥ በዚህ ዓለም ተዋርደን ምእመናን የሚከብሩትን ግብር ይዘን እንድንገኝ ፥ የሚያዝን ልቡና እንዲሰጠን ፥ የምናቆስል ሳይሆን የቆሰሉትን የምናክም እንዲያደርገን፥ የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን።

«ወዮልኝ፣»

           
         ድካማቸውን አይተው፥ ጉድለታቸውን አስተውለው፥ ራሳቸውን የሚገሥጹ፥ በራሳቸው የሚፈርዱ ሰዎች ብፁዓን (ንዑዳን፥ ክቡራን) ናቸው። ያለፈውን ዞር ብሎ በማየት፥ የቆሙበትን በማስተዋል፥ ወደፊት ሊመጣ የሚችለውንም አሻግሮ በ መመልከት፦ «ወዮልኝ፤» ብሎ ራስን ማስጠንቀቅ መንፈሳዊነት ነው። በተሰጣቸው ጸጋ ሳይኰፈሱ ፥ በአገልገሎት ብዛት ሳይጋረዱ፥ ወደ ውስጥ ማየት የአእምሮ መከ ፈት ነው። «አይገባኝም ፥ ሳይገባኝ ነው፤» ማለት የእግዚአብሔርን ቸርነት መግለጥ፥ ለጋስነቱን መመስከር ነው። በምድርም በሰማይም (በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ) ትሑት ሰብእና፥ ቅን ልቡና ይዞ መገኘት ነው። «ወዮልኝ፤» ያለ ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስ ነው። እርሱም ከዓበይት ነቢያት አንዱ ነው።

ነቢዩ ኢሳይያስ ማነው?
          ኢሳይያስ ማለት ቅቡዕ እምቅብዓ ትንቢት ማለት ነው። እንዲህ መባሉም ትንቢት የሚገልጥ መንፈስ ቅዱስ ስላደረበት ፥ ሀብተ ትንቢት ስለተሰጠው ነው። ኢያሱ ፥ ሆሴዕ ፥ ኢየሱስ መድኃኒት ማለት እንደሆነ መድኃኒት ማለትም ነው። ኢያሱ ወልደ ነዌ መድኃኒት የተባለው፡- ባጭር ታጥቆ ፥ ጋሻ ነጥቆ ፥ ዘገር ነቅንቆ ፥ አማሌቃውያንን አጥፍቶ ፥ እስራኤልን አድኖ ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ፡- «ሕማማተ (መከራ) መስቀልን ታግሦ፥ ሥጋውን ቆርሶ፥ ደሙን አፍስሶ ፥ አጋንንትን ድል አድርጐ፥ ነፍሳትን አድኖ ነው። «ኢሳይያስስ ምን ሠርቶ ነው?» እንል ይሆናል። ኢሳይያስም ወደፊት በትንቢቱ፥ በትምህርቱ እንደሚያድን ፥ እግዚአብሔር ገልጦላቸው፥ ከቤተ ግዝረት ገብተው መድኃኒት ብለውታል።
          ኢሳይያስ የነበረው፡- በይሁዳ ነገሥታት፡- በዖዝያን፥ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ነበር። ዘመኑም ከ740 - 688፡ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ነው። በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት የቤተ መንግሥቱ አማካሪ ነበር። ፪ኛ ነገ ፲፱፥፫ ኢሳ ፯፥፩። ምክንያቱም የመንፈሳውያን ምክርና ተግሣጽ ለቤተ መንግሥቱ ያስፈልጋልና ነው። (ዛሬ ዛሬ ግን የተገላቢጦሽ ነው)። የአባቱ ስም አሞጽ ይባላል። ኢሳ ፩፥፩፣ ፪ኛ ነገ ፲፱፥፩። ነቢዩ ኢሳይያስ በስድሳ ስድስት ምዕራፍ የተከፈለ የትንቢት መጽሐፍ አለው። ይልቁንም ስለ ነገረ ማርያም፡- «ናሁ ድንግል ትጸንስ፥ ወትወልድ ወልደ፥ ወትሰምዮ ስሞ አማኑኤል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወልድንም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።» በማለት ደረቅ ትንቢት (ትርጓሜ የማያሻው ትንቢት) ተናግሯል። ኢሳ ፯፥፲፬ ሰለ መከራ መስቀሉም፡- «እርሱ ግን በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፥ ሕመማችንንም ተሸከመ፥ ስለ እኛም ታመመ፤ . . . እርሱ ግን ስለ ኃጢአታችን ቈሰለ፤ ስለ በደላችንም ታመመ፥ የሰላማችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን። . . .  እርሱ ግን በመከራ ጊዜ አፉን አልከፈተም፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ የበግ ጠቦትም በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። ብሏል። ኢሳ ፶፫፥፬።
«ወዮልኝ፤» ያለው መቼ ነው?
          ነቢዩ ኢሳይያስ «ወዮልኝ፤» ያለው፦ እግዚአብሔርን በንጉሠ ነገሥት አምሳል በዙፋን ተቀምጦ ባየው ጊዜ ነው። ጊዜውም ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት ነው። «ርኢክዎ ለእግዚአብሔር ፥ እንዘ ይነብር ዲበ መንበሩ ነዋኀ ወልዑል። እግዚአብሔርን በረዥምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ (በልዑል መንበሩ) ተቀምጦ አየሁት፤ ምስጋናውም ቤቱን ሞልቶት ነበር። (ቤቱን ብርሃን ሞልቶት አየሁት)። ሱራፌልም (ሃያ አራት ካህናተ ሰማይ) በዙርያው ቆመው ነበር። (አክሊላቸውን አውርደው፥ ከጉልበታቸው ሸብረክ ብለው፥ አንገታቸውን ቀለስ አድርገው፥ የወርቅ ጽንሐ ይዘው ፥ የእሳቱን ዙፋን ዙሪያ ውን ያጥኑ ነበር)። ለእያንዳንዳቸውም ስድስት ስድስት አክናፍ ነበራቸው። ሁለት ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ዘርግተው ፊቶቻቸውን ይጋርዱ ነበር ፥ ሁለቱን ክንፎቻቸውን ወደታች ዘርግተው እግሮቻቸውን ይሸፍኑ ነበር። የተቀሩትን ሁለቱን ክንፎቻቸውን ደግሞ እንደ መስቀል ግራና ቀኝ ዘርግተው ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ይበርሩ ነበር።» ብሏል።
          ሱራፌል ሁለት ክንፎቻቸውን ወደ ላይ መዘርጋታቸው፡- «ወደላይ ቢወጡ፥ ቢወጡ አይደረስብህም ፥ (ባህርይህ አይመረመርም)፤ ማለታቸው ነው። ፊታቸውን መሸፈናቸው ደግሞ መለኮታዊ እሳት እንዳያቃጥላቸው ነው። አንድም ትእም ርተ ፍርሃት (የፍርሃት ምልክት) ነው። አንድም አንተን ማየት አይቻለንም ሲሉ ነው።  ሁለት ክንፎቻቸውን ወደታች መዘርጋታቸው፡- «ወደታች ቢወርዱ፥ ቢወርዱ አይደረስብሀም፥ ባህርይህ አይመረመርም፤» ማለታቸው ነው። እግሮቻቸውን መሸፈናቸው ደግሞ በፊትህ መገለጥ (መቆም) አይቻለንም፥ አይገባንም ማለታቸው ነው። ሁለት ክንፎቻቸውን ደግሞ በመስቀል አምሳል ግራና ቀኝ ዘርግተው ከጽንፍ እስከ ጽንፍ መብረራቸው  ትእምርተ ተልዕኮ ነው። አንድም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ብንበርር የሌለህበት ሥፍራ የለም፤ አይደረስብህም፥ ባህርይህ አይመረመርም፤ ማለታቸው ነው። በሌላ በኲል ደግሞ ከዕለተ ዓርብ በፊት በትእምርተ መስቀል አምሳል በፊቱ መታየታቸው፡- እንዲህ ባለ አርአያ ተሰቅለህ ዓለምን ታድናለህ ሲሉ ነው። በቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ፡- «የሚያቃጥል እሳት እንዳይበላቸው በመብረቅ ፊታቸውን ይሸፍናሉ፥ የኃይል ነበልባል እንዳያቃጥላቸው እግራቸውን በፍም ይሸፍናሉ፥ በአራቱ ማዕዘንና በዳርቻም ሁሉ ይወጣሉ። (ይበራሉ)።» የሚል አለ። ቁ 18
          ሱራፌል፡- «ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ፥ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች።» እያሉ፦ በታላቅ ድምፅ ፥ በአንድነት በሦስትነት ሲያመሰግኑ ነቢዩ ኢሳይያስ አይቷል ፥ ሰምቷል። ይህ ምስጋና በሰማይም በምድርም ፍጹም ነው። ሦስት ጊዜ ቅዱስ ማለታቸው ለሦስትነታቸው ፥ የቃሉ አለመለወጥ ደግሞ ለአንድነታቸው ምሳሌ ነው። ሥላሴ አንድም ሦስትም ናቸውና። ከዚህ በኋላ ጩኸው ከሚያመሰግኑት ምስጋና የተነሣ የመድረኩ መሠረት ተናወጠ፤ ቤቱንም ጢስ ሞላበት። ይህም፡- የፀውርተ መንበሩ (የእሳቱን ዙፋን የሚሸከሙ) የኪሩቤልን (የገጸ ሰብእ፥ የገጸ ላህም፥ የገጸ ንስር፥ የገጸ አንበሳ) ዕርገተ ጸሎታቸውን (የጸሎታቸውን ማረግ) ለኢሳይያስ ሲያሳየው ነው። አንድም ጢስ፦ እግዚአብሔር፦ እስራኤል ዘሥጋን ፈጽሞ እንደተጣላቸው የሚያመለክት ነው። ይኸውም በሀገራቸው ልማድ ሲገልጥለት ነው። በሀገራቸው አማላጅ የሄደ እንደሆነ፦ ጢስ አጢሰው፥ ቤት ጠርገው ይቆዩታል፤ እንዳይቀመጥ ትቢያ ይሆንበታል፥ እንዳይቆም ዓይኑን ጢስ ይወጋዋል፤ (ያቃጥለዋል)፤ በዚህን ጊዜ እንደምንም አንድ ነገር ወይም ሁለት ነገር ተናግሮ ይሄዳል። ይህም ምልጃህን ለመቀበል አልፈቀድንም ለማለት ነው። እግዚአብሔርም እስራኤል ዘሥጋን አልማለዳቸውም ሲል ጢሱን አሳይቶታል። በዚህን ጊዜ ነው ፥ ነቢዩ ኢሳይያስ፡- «እኔም ከንፈሮቼ የረከሱብኝ (በለምጽ የነደዱብኝ) ሰው በመሆኔ ፥ ከንፈሮቻቸው በረከሱባቸው ሕዝብ (ቢመክሯቸው ቢያስተምሯቸው በማይሰሙ፥ ሕገ እግዚአብሔርን በማያውቁ ወገኖች) በእስራኤል መካከል በመቀመጤ ዐይኖቼ የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን ስለአዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ፤» ያለው።
ነቢዩ ኢሳይያስ ለምን በለምጽ ተመታ?
          በኦሪቱ ለምጽ የርኲሰት ምልክት ነበር። ነቢዩ ኢሳይያስ በነበረበት በንጉሡ በዖዝያን ዘመን ሊቀ ካህናቱ አዛርያስ ይባል ነበር። ስለ ክብረ ክህነት የከበረ ልብስ ይለብስ ስለነበር ንጉሡ፡- «ምነው? ከእኔ በላይ» ቢለው፦ «ካህናቲከ ይለብሱ ጽድቀ፤ ካህናትህ ጽድቅን ይለብሳሉ፤» ተብሎ ተጽፎብሃል ሲል መለሰለት። በአደባባይ የሚቀመጠውም በቀኙ ስለነበር ፥ አሁንም «ምነው?» ቢለው፡- «ካህን ይነብር በየማነ ንጉሥ፤ ካህን በንጉሥ ቀኝ ይቀመጣል፤» ይልብሃል አለው። ሦስተኛም ንጉሡ አዛብቶ ፥ አጓድሎ ፥ የፈረደውን ፍርድ ፥ አሟልቶ አቃንቶ ፈረደ። አሁንም «ምነው?» ቢለው፡- «እምነ መንግሥት የዓቢ ክህነት፤ ከሥልጣነ መንግሥት ሥልጣነ ክህነት ይበልጣል፤» አለው።
          በዚህን ጊዜ ንጉሡ ዖዝያን፡- «እኔስ በአባቴ ወገን መንግሥት ከተሰጠው ከነገደ ይሁዳ ብወለድም በእናቴ በኲል ክህነት ከተሰጠው ከነገደ ሌዊ እወለዳለሁ፤» ብሎ ለጥፋት ልቡ ታበየ፥ አምላኩንም እግዚአብሔርን በደለ፤ ልብሰ ተክህኖውን ለብሶ፥ ማዕጠንተ ወርቁን ይዞ፥ በዕጣን መሠዊያው ላይ ያጥን ዘንድ በድፍረት ወደ መቅደስ ገባ። ካህኑም አዛርያስ፥ ከእርሱም ጋር ጽኑአን የነበሩ ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ተከትለው ገቡ። ንጉሡንም ዖዝያንን እየተቃወሙ፥ «ዖዝያን ሆይ፥ ዕጣን ማጠን ለተቀደሱት ለአሮን ልጆች ለካህናቱ ነው እንጂ ለእግዚአብሔር ታጥን ዘንድ ለአንተ አይገባህም፤ ከእግዚአብሔር ርቀሃልና ከመቅደሱ ውጣ፤ ይህም በአምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ ለአንተ ክብር አይሆንልህም፤» አሉት። ዖዝያንም ተቆጣ፤ በመቅደስም የሚያጥንበት ጥና በእጁ ነበረ፤ ካህናቱንም በተቆጣ ጊዜ በካህናቱ ፊት በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በዕጣኑ መሠዊያ አጠገብ ሳለ በግምባሩ ላይ ለምጽ ታየ። (በሻሽ ቢሸፍነው በሻሹ ላይ ወጣበት)። ታላቁ ካህን አዛርያስ ካህናቱም ፈጥነው አባረሩት። እርሱም እግዚአብሔር ቀሥፎት ነበርና ይወጣ ዘንድ ቸኰለ። እስኪሞትም ድረስ ከለምጹ አልነጻም። ፪ኛ ዜና ፳፮፥፳። ልጁ ኢዮኣታም በሱ ተተክቶ እንደ ምስለኔ ሁኖ ሲገዛ ኑሯል። ያን ጊዜ ኢሳይያስ ለዖዝያን ወዳጁ ነበር፤ ቢመክረው፥ቢያስተምረው ይመለስ ነበር፤ ነገር ግን አፍሮት ፈርቶት፥ ሳይመክረው ፥ ሳያስተምረው፥ በመቅረቱ ከከንፈሩ ለምጽ ወጥቶበት ሀብተ ትንቢት ተነሥቶታል። እግዚአብሔር፦ ንጉሡ ዖዝያን ሲሞት ጠብቆ ለኢሳይያስ የተገለጠለት፡- «የፈራኸው ንጉሥ አለፈ፤ እኔ ግን በባህርዬ ሞት፥ በመንግሥቴ ኀልፈት የለብኝም፤ በዘባነ ኪሩብ ስሠለስ፥ ስቀደስ እኖራለሁ፤» ሲለው ነበር።

ለምጽና ሥርዓቱ፤
          በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ ፲፫ እና ምዕራፍ ፲፬ ላይ ፥ እግዚአብሔር በልሙጻን ላይ የሠራውን ሥርዓት፥ ለሙሴና ለአሮን ሲነግራቸው እናገኛለን። ከዚህም ውስጥ፡- «የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው፦ ልብሱ የተቀደደ ይሁን፥ ራሱም የተገለጠ ይሁን፥ ከንፈሩንም ይሸፍን፥ ርኲስ ይባላል፤ ደዌው ባለበት ዘመን ሁሉ ርኲስ ይሆናል፤ እርሱ ርኲስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጣል፤ መኖሪያውም ከሰፈር በውጭ ይሆናል።» የሚል ይገኛል። ዘሌ ፲፫፥፵፭።
          «ልብሱ የተቀደደ ይሁን፤» ማለት፦ ስለ ኃጢአቱ ፈጽሞ ይዘን ማለት ነው። በልማድም ዕብራውያን ፈጽመው ሲያዝኑ ልብሳቸውን ለሁለት ይቀድዱታል። የዳዊት ልጅ ትዕማር የገዛ ወንድሟ ደፍሯት  ከቤት አስወጥቶ በዘጋባት ጊዜ፡- በራስዋ ላይ አመድ ነስንሳ፥ ብዙ ሕብርም ያለውን ልብሷን ተርትራ እየጮኸች አልቅሳለች። ፪ኛ ሳሙ ፲፫፥፲፱። «ራሱም የተገለጠ ይሁን፤ (አይሸፋፈን)፤» ማለት ለጊዜው ለምጹ እንዲታይ ነው። ለፍጻሜው ግን ኃጢአቱን አይሸፍን ፥ ገልጦ ለካህኑ ይናገር፥ (ይናዘዝ)፥ ማለት ነው። ጌታ በወንጌል ለምጻሙን ሰው፡- «ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤» ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፰፥፬።  
          «ከንፈሩንም (አፉን) ይሸፍን፤» ማለት፦ ለጊዜው ደዌው በትንፋሽ እንዳይተላለፍ ሲሆን ፥ ለፍጻሜው ግን «ቅዱሱን የእግዚአብሔርን ስም መጥራት አይገባኝም፤» ይበል፥ማለት ነው። ለወገቡ መታጠቂያ፥ ለእግሩም ጫማ አይኑረው፥ የሚልም አለ። ለወገቡም መታጠቂያ አይኑረው የተባለው፦ ለጊዜው የለምጻም አካሉ ልህሉህ ስለሆነ እንዳይቆስል ሲሆን ፥ ለፍጻ ሜው ግን «ንጽሕና የለኝም፤» ይበል፥ ማለት ነው። ወገብን መታጠቅ የንጽህና ምልክት ነውና። ጌታችን አምላካችን መድኃ ኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል፡- «ወገባችሁ የታጠቀ፥መብራታችሁም የበራ ይሁን፤» ያለው ለዚህ ነው። ሉቃ ፲፪፥፴፭። ትርጉሙም፡- ልቡናችሁን በንጽህና ዝናር ታጠቁ፥ የልብ ንጽሕና ይኑራችሁ፥ ማለት ነው። ይኸንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፡- «ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ኑሩ፤» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፩፥፲፫ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡- «እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት (በጽድቅ) ታጥቃችሁ ቁሙ፤» ብሏል። ኤፌ ፮፥፲፬። «ለእግሩ ጫማ አይኑረው፤» ማለትም ጫማ የምግባር ምሳሌ በመሆኑ «የምግባር ደሀ ነኝ፤» ይበል ማለት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ፦ «ወንጌልን ተጫሙ ፤ (በምግባረ ወንጌል ጸንታችሁ ቁሙ ፥ በወንጌል የታዘዘውን ፈጽሙ) ፤» ማለቱ ለዚህ ነውና። ኤፌ ፮፥፲፭።
«በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ ኃጢአትህም ተሰረየልህ፤»
          ነቢዩ ኢሳይያስ፡- «ወዮልኝ፤» በማለቱ፡- ከሱራፌል አንዱ እየበረረ ወደ እርሱ መጣ። በእጁም ከሰማይ መቅደስ ከመሠዊያው በጉጠት የወሰደው ፍም ነበረ። አፉንም ዳሰሰበትና፡- «እነሆ፥  ይህ ከንፈሮችህን ነክቷል፥ በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ኃጢአትህም ተሰረየልህ፤» ብሎታል። መሠዊያ የዓለመ ሥላሴ፥ ጉጠት የሥልጣነ እግዚአብሔር፥ ፍም የሀብተ ትንቢት ምሳሌ ነው። ከንፈሩን ማስነካቱም ሀብተ ትንቢትን መለስኩልህ ሲለው ነው። አንድም መሠዊያ የመንበር፥ ጉጠት የእርፈ መስቀል፥ መልአክ የቀሳውስት፥ ፍም የሥጋ ወደሙ፡ ምሳሌ ነው።
          ከዚህ በኋላ፡- «ማንን እልካለሁ? ማንስ ወደዚያ ሕዝብ ይሄድልናል?» የሚለውን የእግዚአብሔርን ድምፅ ሰምቷል። እርሱም፡- እነሆኝ፥ ጌታዬ፥እኔን ላከኝ፤» ሲል መልሷል። እንደ ጥንቱም፡- «ስማዕ ሰማይ፥ ወአጽምዒ ምድር፤ ሰማይ ስማ፥ ምድርም አድምጪ፤» የሚል ሆኗል። ትርጉሙም፡- «ሰማይ ሆይ፥ የእስራኤልን ነገር (ክፋታቸውን) ሰምተህ፥ ዝናም ለዘር፥ ጠል ለመከር አትስጥ፤ ምድርም ሰምተሽ የዘሩብሽን አታብቅዪ፥ የተከሉበሽን አታጽድቂ፤» ማለት ነው። አንድም በዚህ ምድር እንደ ሰማይ ከፍ ከፍ ያላችሁ ልዑላን (ባለሥልጣኖች፥ ባለጠጐች) ስሙ። እንደ መሬትም ዝቅ ዝቅ ያላችሁ ታናናሾች አድምጡ ማለት ነው። አንድም ሰማይ የተባሉ መላእክት ሲሆኑ ምድር የተባሉ የአዳም ልጆች ናቸው።
እንደ ኢሳይያስ፦ «ወዮልኝ፤» ማለት ያስፈልጋል፤
          የእግዚአብሔር ሰዎች «ወዮልኝ፤» እያሉ ራሳቸውን ገሥጸው ይኖራሉ። ጌዴዎን የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ ፊት ለፊት ስላየው ፥ ቃል በቃል ስላነጋገረው፡- «አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወዮልኝ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና፤» ብሎ ነበር። እግዚአብሔርም፡- «ሰላም ለአንተ ይሁን፥ አትፍራ፥ አትሞትም፤» ብሎታል። መሳ ፮፥፳፪። ነቢዩ ኤርምያስም፡- «በሆድ ሳልሠራ አውቄሃለሁ፥ ከማኀፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሐዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ፤» በተባለ ጊዜ፡- «ወዮ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ፥ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም፤» ብሏል። ኤር ፩፥፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ፤ » ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፱፥፲፮።
          እነዚህ «ወዮልኝ፤» ማለታቸው ለእኛ አብነት ነው። ታላላቆቹ እንዲህ ካሉ ከእኛ ከታናናሾቹ የብዙ ብዙ ይጠበቃል። ዕለት ዕለት «ወዮልኝ፤» እያልን ደረታችንን ልንደቃ፥ እንባችንን ልናፈስስ ይገባል። ሥጋችንን ደስ ከማሰኘት በስተቀር እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተን አናውቅምና። ሰውን ደስ ለማሰኘት በሰውም ዘንድ ለመወደድ (ለውዳሴ ከንቱ) እግዚአብሔርን እናሳዝናለንና። እንኳን መንፈሳዊ መሆን መምሰሉ እንኳ አቅቶናልና። ሃያ፥ሠላሳ ዓመት ቃለ እግዚአብሔር ዘር ተዘርቶብን፡- ሠላሳ፥ስድሳ፥መቶ ማፍራት የተሳነን ዘረ ቆርጥሞች ነንና። መቁረባችን ማቁረባችን ፥ መቀደሳችን ፥ ማስቀ ደሳችን፥ ማሳለማችን፥መሳለማችን፥ መናዘዛችን፥ማናዘዛችን፥ መዘመራችን፥ማዘመራችን፥ መስበካችን፥መሰበካችን ሁሉ ከንቱ ሆኖብናልና። ስለሆነም «እገሌ ሳይገባው ነው፤» የሚለውን ትተን፡- «እኔ ሳይገባኝ ነውና ወዮልኝ፤» እንበል። የእግዚአብሔር ሰዎች፡- «ወዮላችሁ፤» እስኪባሉ አይጠብቁምና።
«ወዮላችሁ፤»
          የዓለም ሰዎች፡- «ወዮላችሁ፤» እስኪባሉ ይጠብቃሉ፤ ተብለውም አይመለሱም፤ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቃሉን ትምህርት ሰምተው፥ የእጁን ተአምራት አይተው ያልተመለሱትን ጸሐፍት ፈሪሳውያንን በአንድ ምዕራፍ ላይ ብቻ ስምንት ጊዜ «ወዮላችሁ፤» ብሏቸዋል።
-      «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ።»
-      «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ ወዮላችሁ።»
-      «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ  
        ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፥ ወዮላችሁ።»
-      «ማንም በቤተመቅደስ የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በቤተመቅደስ ወርቅ የሚምል ግን በመሓላው ይያዛል 
        የምትሉ ፥ ዕውሮች መሪዎች ወዮላችሁ።»
-      «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ ከአዘሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ሰለምታወጡ፥ ፍርድንና  ምሕረ 
        ትን ፥ ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ ወዮላችሁ።»
-      «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ በውስጡ ቅሚያና ስስት፦ ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ
        ስለምታጠሩ ወዮላችሁ።»
-      «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፦ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጥ ግን የሙታን አጥንት ርኲሰትም ሁሉ
        የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ።»
-      «እናንተ ግብዞች ጻፍችና ፈሪሳውያን፦ የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ ፥ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና
        በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም በአልተባበረናቸውም ነበር ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ።»
     አይሁድ «ወዮላችሁ፤» ተብለውም አልተመለሱም፥ ጌታም እንደማይመለሱ ያውቃል። ስለሚያውቅም «እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ትመሰክራላችሁ። እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ሙሉ። እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?» ብሏቸዋል። ማቴ ፳፫፥፲፫-፴፪። ከእነርሱም በፊት የኮራዚንና የቤተ ሳይዳ ሰዎች «ወዮላችሁ»፤ ብሏቸው ነበር። ማቴ ፲፩፥፳፩።ይኸውም ንስሐ ባለመግባታቸው ነው። የሰዶምና የጐመራ ሰዎች እነርሱ ያገኙትን ዕድል አግኝተው ቢሆን ኖሮ፦ ማቅ ለብሰው ፥ ዓመድ ላይ ተኝተው ንስሐ ይገቡ እንደነበር ነግሯቸዋል። እኛም ያገኘነውን ዕድል ያላገኙ ብዙ ሕዝቦች እንዳሉ ማስተዋል አለብን። ጌታችን፦ «ወዮ ለዓለም ማሰናከያ፤ ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና ፥ ነገር ግን በእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት ለዚያ ሰው ወዮለት።» ያለበትም ጊዜ አለ። ማቴ፲፰፥፯። ያ ሰው የተባለ ለጊዜው ይሁዳ ሲሆን ለፍፃሜው የሁላችንንም ሕይወት ይመለከታል። በአንድም ይሁን በሌላ የእኛም ሕይወት ለሌላው መሰናክል እንቅፋት እየሆነ ነውና። ንጹሐ ባህርይ ኢየሱስ ክርስቶስ ፦ «ወዮላችሁ፤» ቢል የባህርይ አምላክ በመሆኑ ነው። ቅዱሳንም፦ «ወዮላችሁ፤» ቢሉ ፦ ከኃጢአት ርቀው፥ ከበደል ተለይተው፥ ሃይማኖት ይዘው ፥ ምግባር ሠርተው ነው። እኛ ግን እምነታችን ደካማ ፥ጸሎታችን የማይሰማ ፥ ምግባራችን ጐዶሎ መሆኑን እያወቅን ሌሎችን «ወዮላቸው፤» እንላለን። ከምዕመናን ፥ ከዲያቆናት፥ ከቀሳውስት፥ ከመዘምራን ፥ ከሰባክያን ፥ ከጳጳሳት ፥ የማንፈርድበት የለም። አንድም ቀን በራሳችን ፈርደን፥ «ወዮልን፤» ብለን አናውቅም። ስለዚህ ኃጢአታችን እንዲሠረይልን ፥ በደላችንም እንዲወገድልን የዘወትር ጸሎታችን «ወዮልኝ፤» የሚል ይሁን። በሌላ በኲል ግን ሃይማኖት ፥ሥርዓት ፥ ትውፊት ፥ ሲጠፋ ተመክረው ፥ ተገሥፀው የማይመለሱትን «ወዮላችሁ፤» ብሎ ማስጠንቀቅ መፍረድም ይገባል። እንግዲህ እንደ ፈሪሳዊያን ከመሆን የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት ይጠብቀን። አሜን።

« ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ ማቴ ፩÷፬ »

        ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ ፥ በአንቀጸ ብጹዓን ትምህርቱ፡- «ብፁዓን እለ ይላህዉ ይእዜ እስመ እሙንቱ ይትፌሥሑ፤ « ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው ፥ እነርሱ ደስ ይሰኛሉና፤ (መጽናናትን ያገኛሉና)፤» ብሏል።  ቅዱሳን ሐዋርያትም በዚህ ላይ ተመስርተው፦ « እናንተ ኃጥአን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት ዐሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ። እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ፥ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ ፥ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል። » እያሉ አስተምረዋል። ያዕ ፬፥፱ ኀዘን ሲባል ሁለት ዓይነት ነው። አንደኛው የማይገባ ኀዘን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሚገባ ኀዘን ነው።

፩፡- የማይገባ ኀዘን፤
          እናት አባት፥ ወንድም እኅት፥ ባል ሚስት ልጅ ሞቱብኝ፥ የዚህን ዓለም ሀብት ንብረት አጣሁ ብሎ በቀቢጸ ተስፋ ማዘን የማይገባ ኀዘን ነው። ምክንያቱም እንደ እናት አባት ሥላሴ አሉና ነው። እግዚአብሔር «አንተ አቡነ፥ ወአንተ እምነ፤» ይባላል። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ጌታችን በወንጌል፡- «እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ፡- አባታችን ሆይ፥ በሰማያት የምትኖር፥ ስምህ ይቀደስ በሉ፤» ብሎናል። ማቴ ፮፥፱። «እነኋት እናትህ።» እንዲል እመቤታችንም እናታችን ናት። ዮሐ ፲፱፥፷፯። ቅዱስ ዳዊትም፡- «እምነ ጽዮን ይብል ሰብእ፤ ሰው ሁሉ እናታችን ጽዮን አባታችን እግዚአብሔር ይላል፤» ብሏል። መዝ ፹፮፥፭። ቤተክርስቲያንም፡- ከማኅፀነ ዮርዳኖስና ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ በውስጧ ስለተወለድን (በጥምቀት የጸጋ ልጅነትን ስላገኘንባት) እናታችን ናት ዮሐ ፫፧፭፧፧ በሥርዓተ ቅዳሴ ላይ፡- «እምነ በሀ ቅድስት ቤተክርስቲያን፤ እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን ሆይ ፥ ሰላም እንልሻለን፤» የምንለው ለዚህ ነው።
እንደ ወንድም እንደ እኅትም ቅዱሳን መላእክት አሉ። ጌታችን በወንጌል፡- «ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ስንኳ እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ (ወንድም፥ እኅት፥ ሀብት ንብረት፥ ወገን የለውም ብላችሁ እንዳትንቁ ተጠበቁ)፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ሁልጊዜ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁ።» ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፲፭፥፲፩  ማንም ሰው የወንድም የእኅቱን ጥቃት እንደማይፈልግ ሁሉ መላእክትም እንደ ወንድም እንደ እኅት የሰውን ጥቃት አይፈልጉም። ሠለስቱ ደቂቅ፦ በስደት፥ በሞት ወንድም እኅታቸውን ቢያጡም በጥቃታቸው ጊዜ የደረሰላቸው አራተኛ ሆኖ አብሮአቸው ከእሳት የገባላቸው ፥ የታደጋቸውም ፥ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው። ዳን ፫፥፳፭። ዳንኤልም ወደ አናብስት ጉድጓድ በተጣለ ጊዜ አብሮት የወረደው ቅዱስ ሚካኤል ነው። ዳን ፮፥፳፪
         
          እንደ ርስት ጉልትም የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያት አለች። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- «በምድር ያለው ማደሪያ ቤታችን ቢፈርስም ፥ በሰማይ በእግዚአብሔር ዘንድ የሰው እጅ ያልሠራው ዘለዓለማዊ ቤት እንዳለን እናውቃለን። ስለ እርሱ የምንደክምለትን በሰማይ ያለውን ቤታችንን እንለብስ ዘንድ እርሱን ተስፋ እናደርጋለን።» ያለው ለዚህ ነው። ፪ኛ ቆሮ ፭፧፩ በፊልጵስዮስ መልእክቱም «አገራችን በሰማይ ነው፤» ብሏል። ፊል ፫፥፳። ቅዱስ ጴጥሮስም ደጅ የምንጠናው ሰማያዊ ርስታችንን አዲሷን ሰማይና አዲሷን ምድር ነው። ብሏል። ፪ኛ ጴጥ ፫፥፫። ከሁሉም በላይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- «ልባችሁ አይደንግጥ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያና ማረፊያ አለ፤» በማለት የሚጨበጥ የሚታመን ተስፋ ሰጥቶናል። ዮሐ ፲፬፥፩። በዚህ ያመኑ ቅዱሳን ሥጋዊው ነገር ሁሉ ሳያሳዝናቸው ሁለን ትተው ተከትለውታል። ማቴ ፲፱፥፳፯
፩፥፩ ሰው ሲሞትብን እንዴት እንዘን?
          ሞትና መቃብር የመጨረሻ አይደሉም። ከሞት አጠገብ ሕይወት፥ ከመቃብር አጠገብ ትንሣኤ አለን። እኅተ አልዓዛር ማርታ፡- «ወንድሜ፥ በመጨረሻው ቀን እንደሚነሣ አውቃለሁ፤» ብላለች። ጌታም ትንሣኤና ሕይወት እርሱ እንደሆነ ነግሯታል። ዮሐ ፲፩፥፳፬ ። ከዚህም አስቀድሞ፡- «በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ፥ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ፤» ብሎ ነበር። ዮሐ ፭፥፷፱ በሌላ በኩል ደግሞ አልዓዛርን እንደሚያስነሣው እያወቀ የፍቅሩን ያህል አልቅሶለታል። «ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህ አይሁድ እንዴት ይወደው እነደነበረ እዩ አሉ፤» ይላል። ዮሐ ፲፩፥፴፭። በመሆኑም ሰው ሲሞትብን በቀቢጸ ተስፋ ሳይሆን የፍቅራችንን ያህል ልናለቅስ ይገባል። ይኸውም፡-
፩፥፪ ነፍስ ከሥጋ ስትለይ፤
          የነፍስ ሞቷ ከእግዚአብሔር አንድነት ስትለይ በመሆኑ፡- «አንቺ ነፍስ በሞት ምክንያት ከሥጋሽ እንደተለየሽ ሁሉ በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር አንድነት ተለይተሽ ይሆን? ከእግዚአብሔርስ አንድነት አይለይሽ፤» ብሎ ስለ ነፍስ ማዘን፥ ማልቀስ ይገባል። አዳምና ሔዋንን «ሞቱ»  ያሰኛቸው ከእግዚአብሔር አንድነት መለየታቸው ነበር እንጂ የዕፀ በለስን ፍሬ እንደበሉ ወዲያው በመሞታቸው አይደለም ዘፍ ፫፥፰። አስቀድሞ የተነገራቸው «ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያሳየውና ከሚያስታውቀው ዛፍ አትበላ፤ ከእርሱ በበላህ ጊዜ ሞትን ትሞታለህና፤» የሚል ነበር። ዘፍ ፪፥፲፯። በአዲስ ኪዳንም ራሱ ባለቤቱ፡- ወደ እርሱ አንድነት ማለትም ቃለ ሕይወት ወንጌል ወደምትነገርበት ጉባኤ ያልመጡትን በቁማቸው ሙታን ብሏቸዋል። ማቴ ፰፥፳፪
፩፥፫፡- አስከሬን ከቤት ሲወጣ፤
          አስከሬን ከቤት በሚወጣበት ጊዜ፡- «አንተ ሰው፥ አንቺ ሰው በሞት ምክንያት ከምድራዊ ቤታችሁ እንደወጣችሁ ሁሉ በኃጢአት ምክንያት ከሰማይ ቤታችሁ ከመንግሥተ ሰማያት ትወጡ ይሆን? ይህንንስ አያድርግባችሁ፥ ከመንግሥተ ሰማያት አያውጣችሁ፤» ብሎ ማዘን፥ ማልቀስ ይገባል። «አምስቱ ውሾች ግን ከዚያች ሀገር ወደ ውጭ ይወጣሉ፤ እነዚህም አስማተኞች፥ ዘማውያን፥ ነፍሰ ገዳዮች፥ ጣዖት የሚያመልኩ፥ የሐሰት ሥራንም ሁሉ የሚወዱ ሁሉ ናቸው።» ይላል። ራእ ፳፪፥፲፭። ያች ሀገር መንግሥተ ሰማያት ናት። «የዚያን ጊዜም፡- ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ (እፈርድባቸዋለሁ)።» የሚልም አለ። ማቴ ፯፥፳፫።
፩፥፬፡- አስከሬን ወደ መቃብር ሲወርድ፤
          የተገነዘ አስከሬን ወደ መቃብር በሚወርድበት ጊዜ፡- «አንተ ሰው፥ አንቺ ሰው በሞት ምክንያት ወደ መቃብር እንደወረዳችሁ ሁሉ በኃጢአት ምክንያት ወደ ሲኦል ወደ ገሃነመ እሳት ትወርዱ ይሆን? ይኸንንስ አያድርግባችሁ፥ ወደ ሲኦል፥ ወደ ገሃነም አያውርዳችሁ፤» ብሎ ማዘን፥ ማለቀስ ይገባል። ምክንያቱም፡- «እናንተ የተረገማችሁ ለሰይጣንና ለመልእክተኞቹ ወደተዘጋጀው ወደ ዘለዓለም እሳት ሂዱ።» የሚል አለና ነው። ማቴ ፳፭፥፵፩ ከዚሀም አስቀድሞ «በወንድሙ ላይ በከንቱ የሚቆጣ ሁሉ እርሱ ይፈረድበታል ፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል ፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል።» ተብሎ ተነግሯል። ማቴ ፭፥፳፩። በቅዱስ ማርቆስ ወንጌል ደግሞ «እሳቱ የማይጠፉ ትሉ የማያንቀላፋ» የሚል ተጽፏል።
፪፡- የሚገባ ኀዘን፤
          ቅዱሳት መጻሕፍት በጠቅላላው የሚመክሩን የሚገባ ኀዘን እንድናዝን ነው። ጌታችንም የተናገረው ስለዚህኛው ኀዘን ነው። ነገ በነገር ሁሉ ደስ እንዲለን ዛሬ በፈቃዳችን እንድናዝን ነው። ይህም ቅዱሳንን፥ መላእክትን፥ እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኝ ነው።
          «መጀመሪያ፡- በጻፍሁት መልእክት ባሳዝናችሁም እንኳ አይጸጽተኝም፤ ብጸጸትም፥ እነሆ ያች መልእክት ለጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘነቻችሁ አያለሁ። አሁን ግን እኔ ስለ እርሷ በብዙ ደስ ይለኛል፤ ደስታዬም ስለ አዘናችሁ አይደለም፤ ንስሐ ልትገቡ ስለአዘናችሁ እንጂ፤» ፪ኛ ቆሮ ፯፥፰።
          «እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ ስለሚገባ ስለ አንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት በሰማያት ደስታ ይሆናል።» ሉቃ ፲፭፥፲።
          «እውነት እላችኋለሁ፤ ባገኘው ጊዜ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ ጠፍቶ ስለተገኘው ፈጽሞ ደስ ይለዋል። እንዲሁም ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንኳ ይጠፋ ዘንድ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት አይፈቀድም።» ይላል። ማቴ ፲፫፥፲፫። የሚገባ ኀዘንን የምናዝነው ስለ አራት ነገር ነው። እነኚህም፡-
          ፪፥፩፡- የግል ኃጢአትን እያሰቡ ማዘን፤
መቅድመ ወንጌል፡- «አልቦቱ ካልእ ኅሊና ለአዳም ላዕለ ኃጢአቱ፥ ዘእንበለ ብካይ፤ አዳም በኃጢአቱ ምክንያት በመጣበት ብድራት ከማልቀስ በስተቀር ሌላ ኅሊና (አሳብ) አልነበረውም፤» እንዲል፥ በኃጢአቱ ምክንያት አለቀሰ። «ከማዕረጌ ተዋረድኩ፥ ከሥልጣኔ ተሻርኩ» ብሎ ሳይሆን ፈጣሪዬን በደልኩ ብሎ አዘነ። ይህ እንባ፥ ይህ ኃዘን ነው፥ «ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤» የሚል ተስፋ ያሰማው፤ የአዳም ኀዘኑ ፈጣሪን ከሰማይ እንዲወርድ፥ ከድንግል ማርያም እንዲወለድ፥ በቀራንዮ በመልዕልተ መስቀል ተሰቀሎ፥ አዳምን እስከነ ልጅ ልጆቹ እንዲያድን አድርጎታል።
          ንጉሠ እስራኤል ዳዊትም ስለ ድቀቱ በነቢየ እግዚአብሔር በተገሠጸ ጊዜ፦ «እግዚአብሔርን በድያለሁ፤» ብሎ አለቀሰ። በዚህን ጊዜ ነቢዩ ናታን፦ «እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢአትህን አርቆልሃል፤ አትሞትም። ነገር ግን በዚህ ነገር ለእግዚአብሔር ጠላቶች ታላቅ የስድብ ምክንያት አድርገሃልና፤ ስለዚህ ደግሞ የተወለደልህ ልጅ ፈጽሞ ይሞታል፤» አለው። ፪ኛ ሳሙ ፲፪፥፲፫። ስምዖን ጴጥሮስም ጌታ አስቀድሞ እንደተናገረበት ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ጌታውን አላውቀውም ብሎ ነበር። ይህንንም ያለው ከልቡ ሳይሆን ከአፉ ነው፤ ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ። ስምዖን ጴጥሮስም፡- «ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤» ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ። ማቴ ፳፮፥፴፫-፸፭። ሁሉም መልካቸው ሳይለወጥ፥ ሳይሰቀቁ ዕንባቸው እንደ ሰን ውኃ ይወርድ ነበር።
፪፥፪፡- የባልንጀራን ኃጢአት እያሰቡ ማዘን፤
          ነቢዩ ሳሙኤል ስለ ንጉሥ ሳኦል ኃጢአት በመዓልትም በሌሊትም ያለቅስ ነበር። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፡- «በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከመቼ ነው?» ብሎታል። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፩። በአዲስ ኪዳን ደግሞ ከሁሉም በላይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ለኢየሩሳሌም አልቅሶላታል። «ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት። እንዲህም አላት፥አንቺስ ብታውቂ ሰላምሽ ዛሬ ነበር፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ከዐይኖችሽ ተሰወረ። ጠላቶችሽ አንቺን የሚከቡበት ቀን ይመጣል፤ ይከትሙብሻል፤ ያስጨንቁሻልም፤ በአራቱ ማዕዘንም ከብበው ይይዙሻል። አንቺን ይጥሉሻል፤ ልጆችሽንም ከአንቺ ጋር ይጥሉአቸዋል፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉልሽም፤ የይቅርታሽን ዘመን አላወቅሽምና፤» ይላል። ሉቃ ፲፱፥፵፩። በኦሪቱ የነቢያት አለቃ ሙሴ ስለ ወገኖቹ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ፡- «አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ፤» ብሏል። ዘዳ ፴፪፥፴፪። ንጉሡ ዳዊትም የእግዚአብሔር መልአክ ከሕዝቡ ሰበዐ ሺህውን በቀሠፈ ጊዜ፡- «እነሆ፥ እኔ በድያለሁ፥ ጠማማም  ሥራ እኔ አድርጌአለሁ፤ እነዚህ በጎች ግን እነርሱ ምን አደረጉ? እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ እንድትሆን እለምንሃለሁ፤» ሲል ተናግሯል። ፪ኛ ሳሙ ፳፬፥፲፯። ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፡- «ብዙ  ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለብኝ ስል በክርስቶስ ሆኜ እውነትን እናገራለሁ፤ አልዋሽምም፤ ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል። በሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና፤» ብሏል። ሮሜ ፱፥፩።
፪፥፫፡- ግፍዓ ሰማዕታትን እያሰቡ ማዘን፤
          ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን፥ የእምነት ሰዎች ታሪክ፥ ከአብርሃም ጀምሮ እየተረከ እውነቱን ቢነግራቸው አይሁድ ተበሳጩበት። ጥርሳቸውንም አፋጩበት። ቅዱስ እስጢፋኖስ ግን አድሮበት በሚኖር መንፈስ ቅዱስ ጸንቶ ወደ ሰማይ ቢመለከት ሥላሴን አየ። ያየውንም ምስጢር (ምሥጢረ ሥላሴን) ነገራቸው። እነርሱም በታላቅ ቃል ጮኸው እንዳይሰሙ ጆሮአቸውን ደፈኑ። መሬት ለመሬት እየጐተቱም ከከተማ አወጡት። በድንጋይም ቀጥቅጠው ገደሉት ፤ ደጋግ ሰዎችም አስክሬኑን አንስተው እያዘኑ እያለቀሱ ቀበሩት ይላል። የሐዋ ፰፥፪። ያሳዘናቸው፥ ያስለቀሳቸው ሞቱ ብቻ ሳይሆን የተፈጸመበት ግፍ ጭምር ነው። ስለሆነም ዓለም የግፈኞች በመሆኗ  ፍርድ ሲጓደል፥ ደሀ ሲበደል ቅዱሳን ሲገፉ ማዘን ይገባል።
፪፥፬፡- መከራ መስቀሉን እያሰቡ ማዘን፤
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን በጥቅሉ አሥራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል ተቀብሏል። ይኸንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፡- «ከኃጢአታችን ያወጣን ዘንድ፥ በጽድቁም ያድነን ዘንድ፥ እርሱ ስለ ኃጢአታችን በሥጋው በእንጨት ላይ ተሰቀለ፤ በግርፋቱም ቁስል ቁስላችሁን ተፈወሳችሁ።» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፳፬። ይህም ነቢዩ ኢሳያይስ፡- «እርሱ ግን በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፤ ስለ እኛም ታመመ፤--- እርሱ ግን ስለ ኃጢአታችን ቈሰለ፤ ስለ በደላችንም ታመመ፤--- በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን።» በማለት አስቀድሞ የተናገረው ነው። ኢሳ ፶፫፥፬። በመሆኑም ስለ እኛ ብሎ የተቀበላቸውን እነዚህን መከራዎች እያሰብን ልናዝን ይገባል። ቅዱስ ዮሐንስ የዕለተ ዓርቡን መከራ በቀራንዮ ፊት ለፊት በማየቱ ሰበዓ ዘመን ቁጽረ ገጽ (ኀዘንተኛ) ሁኖ ኑሯል። መላ ዘመኑን በፊቱ ላይ ፈገግታ አልታየም።
ለመሆኑ የእኛ ኀዘን ምን ይመስላል?
          ከደስታ በቀር ሐዘንን የምንፈልግ ሰዎች አይደለንም። ማናችንም ብንሆን ቢሳካልን ለአንድ ደቂቃ እንኳን ማዘን አንፈልግም። ቢቻለን የዓይን አምሮታችን የሥጋ ፍላጐታችን ሁሉ ተሟልቶልን በዓለም ተደስተን መኖርን እንፈልጋለን። ይልቁንም ስለ ኃጢአታችን ፈጽሞ ማዘን አንፈልግም። እንዲያውም እንደ ኃጢአት የሚያስደስተን ነገር የለም። ያመነዘሩበትን፥ ጠጥተው የሰከሩበትን፥ አጭበርብረው ብዙ ገንዘብ ያገኙበትን፥ በጭፈራ ያሳለፉበትን፥ የጠሉትን ሰው የተበቀሉበትን፥ በአጠቃላይ በተለያየ መንገድ ሰውን የጐዱበትን ዕለትና ዘመን እያስታወሱ የሚደሰቱ ፥ ሐሴትም የሚያደርጉ ሰዎች እጅግ ብዙ ፥የብዙ ብዙ ናቸው። የሰው ሕይወት በሥጋዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ሲመሰቃቀል፥ የሰው ትዳር ሲበጠበጥ ፥ ሲፈርስ ፥ በደስታ ያልተሳሉትን ስእለት ለማስገባት የሚፈልጉ ሰዎችም አይጠፉም። ሰው ሲታመም፥ ሥራም ሲፈታ አንጀታቸው ቅቤ የሚጠጣ ፈጽመው የሉም ለማለት አይቻልም። ወተቱን አጥቁረው፥ ማሩንም አምርረው ሰውን በማማት የሰውንም ስም በማጥፋት መደሰት እንደ ዘውትር ጸሎት የተያዘ የየዕለቱ ግብር ነው። የእጅ ስልካችን፥ የቤታችንም ስልክ፥ ኢ-ሜይላችንም ጭምር የሚያሳብቀው ይኸንኑ ነው። ይህ ሁሉ ከራስ ወዳድነት (ራስን ከማምለክ) የሚመነጭ ነው። «ነገር ግን በኋላ ዘመን ክፉ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፥ ገንዘብንም የሚወዱ፥ ቀባጣሪዎች፥ ትምክሀተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ ምስጋና የሌላቸው፥ ከጽድቅም የወጡ ይሆናሉ። ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ።» እንዳለ ሐዋርያ። ፪ኛ ጢሞ ፫፥፩።
          ምናልባት የምናዝነው ያሰብነውና ያቀድነው፥ ኃጢአት ሳይሳካልን ሲቀር ነው። ወይም የገፋነው ሰው ሳይወድቅ ሲቀር፥ ያዋረድነው ሰው ሲከብር፥ ያቆሰልነው ሰው ሲፈወስ፥ ያጠመድነውና ያስጠመድነው ሰው ከወጥመድ ሲያመልጥ፥ የጠላነው ያስጠላነው ሰው ሲወደድ፥ ቤት መኪና ያልነበረው ሰው እንደ እኛ ባለቤት ባለ መኪና ሲሆን ፥ በውጭው ዓለም የመኖሪያ ፈቃድ አጥቶ የተቸገረ ሰው እንደ እኛ መኖሪያ ፈቃድ ሲያገኝ፥ እንረዳው የነበረ ሰው ራሱን ሲችል ነው። የኰንትሮባንድ ነጋዴ የሚበሳጨውና የሚያዝነው ኬላ ላይ የእርሱ ተይዞ ስለተወረሰበት ሳይሆን የባልንጀሮቹ በተለያየ ምክንያት ሳይወረስ በመቅረቱ ነው። በአጠቃላይ አነጋገር በኃጢአታችንና እና በሰው ጉዳት የምንደሰት ሰዎች ነን። መመሪያችን እኔ ልደሰት ፥ ልሳቅ ፥ ይድላኝ ፤ ሌላው ግን ይዘን፥ ያልቅስ፥ ይጐስቁል ነው። እኔ ወርቅ ልልበስ ፥ ሌላው ግን አፈር ይልበስ ነው። ለአንድ አፍታ እንኳን ምድራዊው ነገር ሁሉ ሃላፊ ጠፊ መሆኑ ትዝ አይለንም። «ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ፥ ነፍሱንም ቢያጣ፥ ለሰው ምን ይረባዋል?» የሚለውን የጌታችንን ቃል የምናውቀው በጥቅስ ብቻ ነው። ማቴ ፲፯፥፳፮። ከእንግዲህ ግን እንደቃሉ ለመኖር እንጣር። እኛ ጥቂት ስንጥር እግዚአብሔር በብዙ ይረዳናል። እንደ ራሄል ወደ ሰማይ የሚወጣ እንባ ይሰጠናል። ኀዘናችን ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ ግዳጅ የሚፈጽም ይሆናል። የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን።
 

«የሚጐድለኝ ምንድር ነው»? ማቴ ፲፱ ፥ ፳።

          የጉድለት ነገር ሲነሣ ሁልጊዜ ትዝ የሚለን በኃላፊው ጠፊው ዓለም በሥጋ የሚጐድለን ብቻ ነው። ያማረ ቤት ፥ አዲስ መኪና ፥ ተርፎ በባንክ የሚቀመጥ ገንዘብ ፥ ወለል ብሎ ይታየናል። ራሰ በራው ትዝ የሚለው ጠጉር ነው። አቅሙ ካለው ጠጉር የሚያበቅል መድኃኒትና ሐኪም ያፈላልጋል። የረገፈ ጠጉሩ የተመለጠ ራሱ ሁሌ ያሳስበዋል። ትልቅ ነገር የጐደለበት ፥ ከሰው በታች የሆነ ይመስለዋል። የአፍንጫ ፥ የጥርስ ፥ የከንፈር ነገር የሚያሳስበውም አለ። የቁመቱ ማጠር ወይም መንቀዋለልም የሚያስጨንቀው ብዙ ነው። ባለማግባቱ የሚያማርር ፥ አግብቶም ልጅ ባለመውለዱ መፈጠሩን የሚረግም ብዙ ነው። ለመሆኑ እንደ ጉድለት የቆጠርነው ይህ ሁሉ ቢሟላልን እናመሰግን ይሆን? ባማረ ቤት ተቀምጠው ፥ ዘመናዊ መኪና እየነዱ ፥ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየመነዘሩ ፥ መልከ መልካም ተብለው የተደነቁ ፥ በመንፈሳዊውም በሥጋዊውም በእውቀት የመጠቁ ነገረ ግን በሐዘን ተጨብጠው ፥ በእንባ ተነክረው የሚኖሩ ብዙ ናቸው። ከዚህም አልፈው ራሳቸውን እስከ ማጥፋት የደረሱ ጥቂት አይደሉም። እግዚአብሔርን በዓለም መለወጥ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውምና። ስለሆነም ዓለም ጥላዋን ጥላብን የጠቆርን ፥ መንፈሳዊው መልካችን የጠፋብን ፥ ወደ ዓለም ዞረን የምንጸልይ ፥ ዓለምን የምናመልክ ሁሉ በሥጋ ሳይሆን በነፍስ «ምን ይጐድለናል?» ልንል ይገባናል። የነፍሳችን ከተሟላ የነፍስ በረከት ለሥጋ ይተርፋልና።
   አንድ ወጣት ባዕለጸጋ ወደ ጌታችን መጥቶ፦ «ቸር መምህር ሆይ ፥ የዘለዓለምን ሕይወት እወርስ ዘንድ ከበጎ ሥራ ወገን ምን ላድርግ?» አለው። እርሱም፦ «ለምን ቸር ትለኛለህ ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ቸር የለም፤ » አለው። « ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ። . . .  ያም ቃል ሥጋ ሆነ ፤ ( ከድንግል ማርያም የነሳውን ሥጋና ነፍስ ተዋሕዶ ሰው ሆነ ) ፤ » እንዲል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው። ዮሐ ፩ ፥ ፩። ስለሆነም ቸር ነው ፥ ቸር መባልም ይገባዋል። ታዲያ ለምንድን ነው ወጣቱን ባዕለጸጋ « ለምን ቸር ትለኛለህ ?» ያለው ፥ እንል ይሆናል። ጌታችን እንዲህ ማለቱ ስለሁለት ነገር ነው። አንደኛው ፦ « የባህርይ አምላክ መሆኔን ሳታምን ለምን ቸር ትለኛለህ? » ሲለው ነው። ሁለተኛውም ይህ ሰው ውዳሴ ከንቱ ሽቶ (ፈልጐ) በተንኰል የመጣ ሰው ነው። አመጣጡ ፦ « እኔ ቸር ስለው ፥ እርሱም አንተም ቸር ነህ ፤ » ይለኛል ብሎ ነው። ቅዱስ ዳዊት ፦ « እግዚአብሔር ልቡናን እና ኲላሊትን ይመረምራል። » እንዳለ ፥ እርሱ ልብ ያሰበውን ፥ ኲላሊት ያጤሰውን ያውቃል። መዝ ፯ ፥ ፱። ቅዱስ ዮሐንስም  ፦ ጌታችን ኢየሱስም በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ ብዙ ሰዎች ያደረገውን ተአምራት ባዩ ጊዜ አመኑ። እርሱ ጌታችን ግን አያምናቸውም ነበር ፥ ሁሉን እያንዳንዱን ያውቀዋልና ። የሰውንም ግብሩን ሊነግሩት አይሻም ፥ እርሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና።» ብሏል። ዮሐ ፪ ፥፳፫ ። ይህን ሰው « ቸር መምህር ሆይ » ፥ ሲል ላየው ፥ ለሰማው ሰው ፍጹም አማኝ ይመስላል። ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ላየን ፥ ለሰማን ሁሉ አማኝ የምንመስል በእርሱ ዘንድ ግን ከምእመናን (ከአማኞች) የማንቆጠር ብዙ ሰዎች አለን። የአምልኮት መልኩ ፥ ቅርጹ እንጂ ይዘቱ የለም። « ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚመርጡ ይሆናሉ። የአምልኮት መልክ አላቸው ፥ ኃይሉን ግን ይክዱታል ፤ » እንዳለ ።፩ኛ ጢሞ ፫ ፥ ፬።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፦ ልባቸውንም አፋቸውንም አንድ አድርገው የሚያምኑትን ምስጋና እንጂ ውስጣዊ እምነት የሌላቸውን ሰዎች መዝሙር ፥ ውዳሴ ፥ ቅዳሴ ፥ እንደማይቀበል ከተናገረ በኋላ ፦ « ወእመሰ ትፈቅድ ትባእ ውስተ ሕይወት ፥ ዕቀብ ትእዛዛተ ፤ ወደ ሕይወት ልትገባ ( የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያትን ልትወርስ ) ብትወድድስ ትእዛዛትን ጠብቅ ፤ » ብሎታል። ምክንያቱም ፦ « ሕጉ ቅዱስ ነው ፥ ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናትና » ሮሜ ፯ ፥፲፪። ቅዱስ ዳዊትም ፦ «የእግዚአብሔር ሕግ ንጹሕ ነው ፥ ነፍስንም ይፈውሳል . . . . . የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው ፥ ልብንም ደስ ያሰኛል፤የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩኅ ነው ፥ ዓይኖችንም ያበራል።» ብሏል።» መዝ ፲፰ ፥ ፰። « ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል።» ያለውም ለዚህ ነው። መዘ ፩፻፲፰ ፥ ፸፪ ።
          ወጣቱ ባዕለጸጋ ሕጉን እንዲያከብር ፥ ትዕዛዙን እንዲጠብቅ በተነገረው ጊዜ ፦ « የትኞቹን?» ሲል ጠየቀ። ጌታም ፦ አትግደል ፥ አታመንዝር ፥ አትስረቅ ፥ በሐሰትም አትመሰክር ፥ አባትህንና እናትህን አክብር ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ ።» አለው። ጐልማሳውም ፦ « ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄያለሁ ፥ እንግዲህ የሚቀረኝ (የሚጐድለኝ) ምንድነው?» በማለት በኲራት ጠየቀ።ይህ ወጣት ከትናንት እስከ ዛሬ (ከሕፃንነት እስከ ወጣትነት) ያለውን ተናገረ እንጂ ነገ ምን እንደሚሆን አያውቀውም። አብዛኛው ሰው ወጣትነት እስከሚጀምረው ድረስ ሕጉን ለማክበር ፥ ትእዛዙን ለመጠበቅ አይቸገርም። የሚቸግረው ወጣትነት ጓዙን ጠቅልሎ ሲመጣ ነው። የወጣትነት ጓዝ ደግሞ ክፉ ምኞት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ፦ «ከክፉ የጐልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል ።» ያለው ለዚህ ነው። ፪ኛ ጢሞ ፪ ፥፳፪ ።
          በተለይም የእሳትነት ዘመን (ወጣትነት) እና ገንዘብ ሲገናኙ ከባድ ነው። የሥጋ ፍላጎት በሚበዛበትና በሚያይልበት በወጣትነት ዘመን እንደልባችን የምናዝዘው ፥ ብዙ ገንዘብ ካለ ካላወቁበት በእሳት ላይ ጭድ ማለት ነው። « እድሜ ለገንዘቤ ፥» ወደ ማለት ገንዘብን ወደ ማምለክ ይኬዳል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ በገንዘብ የማይሠራ ኃጢአት ፥ ለገንዘበ ተብሎ የማይፈጸም ወንጀል የለም። ሃይማኖትንም ያስክዳል። ቅዱስ ጳውሎስ « ዳሩ ግን ባለጠጋ ሊሆኑ የሚፈልጉ ፥ በጥፋትና በመፍረስ ፥ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙም  ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ (ማምለክ) የክፋት ሁሉ ሥር ነውና ፥ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው (ሃይማኖታቸውን ለውጠው) በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ ። » እንዳለ። ፩ኛ ጢሞ ፮ ፥ ፱።
          ይህ ወጣት ባዕለጸጋ ሕጉን እያከበረ ፥ ትእዛዙን እየጠበቀ ካደገ በኋላ ፥ በልቡናውም የዘለዓለምን ሕይወት እየፈለገ በሀብት ምክንያት እንዳይጠፉ « ፍጹም ልትሆን ብትወድስ ፥ ሂድና ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድሆች ስጥ ፥ ሰማያው ሀብትንም ታገኛለህ ፥ መጥተህም ተከተለኝ። (በግብር ምሰለኝ)።» ተብሏል። እርድና (ረድእነት) ከምጽዋት ታዝዟል። ምክንያቱም ለነዳያን ፈረስ በቅሎ ፥ በሬ ላም ቢሰጧቸው ወጥቶ ወርዶ መሸጥ ስለማይሆንላቸው ባገኙት ዋጋ ይጥሉታል። ባሌቤቱ ግን የሀብቱን የከብቱን ዋጋ ስለሚያውቅ በዋጋው ይሸጠዋልና ለዚህ ነው። ወጥቶ ወርዶ መሸጥ መለወጥ ረድእነት ሲሆን ሳይነፍጉ መስጠት ደግሞ ምጽዋት ነው።
          «ወሰሚዖ ወሬዛ ዘንተ ነገረ ወሖረ እንዘ ይቴክዝ ፥ እስመ ብዙኅ ጥሪቱ ። ጐልማሳውም ይህን ነገር ሰምቶ ሀብቱ ብዙ ነበርና እያዘነ ሄደ። » እንደ ቅዱስ ዳዊት ፦ «ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል፤ » ማለት አልቻለም። እንደ ሣፋጥ ልጅ እንደ ኤልሳዕ ሀብቱን ፥ መሬቱን ፥ ንብረቱን ትቶ መከተል አልቻለም። ፩ኛ ነገ ፲፱ ፥ ፲፱ ። እንደ ሙሴ ከብዙ ገንዘብ ይልቅ ክርስቶስን መምረጥ አልሆነለትም። ዕብ ፲፩ ፥ ፳፭፦ «እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።» እንዳለ ራሱን መካድ ( ፈቃደ ሥጋውን ለፈቃደ ነፍሱ ማስገዛት) ከበደው። ማቴ ፲፮ ፥፳፭። መቼም ጥያቄው በራሱ ሰማዕትነትን የሚጠይቅ ነው። ጽድቅ፦ ሀብት፥  ንብረትን መተው ብቻ ሳይሆን ሕይወትንም ጭምር መተው (ነፍስን አሳልፎ መሰጠትን) ይጠይቃልና።
          ይህስ ሰው አቅሙን አውቆ ገና በጧቱ አዝኖ ተመልሷል። ሁለን ትቼ መከተል አይሆንልኝም ብሏል። ክርስትና ማለት ሁሉን ትቶ የክርስቶስ ተከታይ መሆን ፥ እርሱን በግብር መምሰል ማለት ነውና። ለመሆኑ ተከትለነዋል የምንል ሰዎች ፥ «ተዉ» ፥ የተባልነውን ትተን ነው የተከተልነው ወይስ ዛሬም እስከነሸክማችን ነን? አልሰማንም እንዳንል ፥ ሃያ ሠላሳ ዓመት ሰምተናል። ከመስማትም አልፈን « ጆሮ ያለው ይስማ፤» እያልን የምንጮህ ሰዎች ሆነናል። ዳሩ ግን የዕውቀት እንጂ የሕይወት ሰዎች መሆን ተስኖናል።
          የሚታየን የሰው ጉድለት እንጂ የራሳችን አይደለም። ቃሉ «እንዳይፈርድባችሁ አትፍረዱ። (ንጹሕ ሳትሆኑ አትፍረዱ)። በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋልና ፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋልና። በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ (ትንሹን ኃጢአት) ለምን ታያለህ? በአንተ ዓይን ያለውን ምሶሶ (ታላቁን ኃጢአትህን) ግን አታስተውልም? ወንድምህን በዓይንህ ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ ተወኝ እንዴት ትለዋለህ? (በኃጢአትህ ልፍረድብህ ለምን ትለዋለህ)? እነሆ ፥ በአንተ ዓይን ምሶሶ አለ። (በሰውነትህ ታላቅ ኃጢአት ተሸክመሃል)። አንተ ግብዝ አስቀድመህ በአንተ ያለውን ምሶሶ አውጣ ፥ (በመጀመሪያ ስለ ታላቁ ኃጢአትህ ፥ ስለበዛው ጉድለትህ በራስህ ላይ ፍረድ) ፥ ከዚህ በኋላ በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።» እያለን ወደ ራሳችን መመልከት ፥ ጉድለታችንን ማየት አልተቻለንም። ማቴ ፯፥፩። ጌታችን የወንድምን ኃጢአት በጉድፍ ፥ የራስን ኃጢአት በምሶሶ ፥ በሰረገላ መስሎ ያስተማረው የባልንጀራችንን ኃጢአት የምናውቀው ጥቂቱን ስለሆነ ነው። የራሳችንን ግን ከራሳችን ጠጉር ቢበዛም ሁሉንም እናውቀዋለንና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ፦ « አንተ ሰው ሆይ ፥ እውነት ለሚፈርደው ለእግዚአብሔር ምን ትመልሳለህ? በወንድምህ ላይ የምትጠላውን ያን ሥራ አንተ ራስህ ከሠራኸው በራስህ የምትፈርድ አይደለምን? አንተ ራስህ ያን ሥራ ትሠራዋለህና . . . . . አንተ ሰው ሆይ ፥ በሌላ ላይ አይተህ የምትጠላውንና የምትነቅፈውን ያን አንተ ራስህ የምትሠራው ከሆነ ፥ ከእግዚአብሔር ፍርድ እንደምታመለጥ ታስባለህን? »ብሏል። ሮሜ ፪፥፩-፫፦ እኛስ የሚጐድለን ምንድነው?
፪ ፦ እምነት ይጐድለናል፤
          የሰው እምነቱ በማግኘትም በማጣትም ፥ በደስታም በኀዘንም ይፈተናል። ጠቢቡ ሰሎሞን «ሁለትን ነገር ከአንተ እሻለሁ ፥ ሳልሞትም አትከልክለኝ ፤ ከንቱነትንና ሐሰተኝነትን ከእኔ አርቃቸው ፤ ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ ፤ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ፥ እንዳልጠግብ እንዳልክድህም ፦ እግዚአብሔርስ ማን ነው? እንዳልል፤ ድሃም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም ፥ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል።» በማለት እግዚአብሔርን የለመነው ለዚህ ነው። ምሳ ፶ ፥ ፯። ጌዴዎንን የሰባቱ ዓመት መከራ ፦ «ጌታዬ ሆይ ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው የነገሩን ተአምራቱ ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል ፥ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል፤» አሰኝቶታል።  ይህንንም ያለው፦ መልአከ እግዚአብሔር «እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤» እያለው ነው። መሳ ፮ ፥፲፫። ስምዖን ጴጥሮስ ጌታው ና እያለው ፥የነፋሱን ኃይል አይቶ በመፍራቱ ፥ መስጠምም በመጀመሩ ፦ «አንተ እምነት የጐደለህ ለምን ተጠራጠርህ? » ተብሏል። ማቴ ፲፬ ፥፴። ደቀመዛሙርቱም በታንኳ ከጌታቸው ጋር እየተጓዙ በነበረበት ሰዓት የማዕበሉ ኃይል ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ ፥ በባሕር ታላቅ መናወጥ በመሆኑ ፥ ተስፋ ቆርጠው፦ « ጌታ ሆይ ፥ አድነን ፥ ጠፋን፤ » እያሉ ጮኸው ነበር። በዚህም ምክንያት ፦ እናንተ እምነት የጐደላችሁ ፥ ስለምን ትፈራላችሁ?» ተብለዋል። ማቴ ፰፥፳፮። ከደብረ ታቦር በወረደም ጊዜ ፦« የማታምን ጠማማ (እምቢተኛ ፥ አሉተኛ) ትውልድ ሆይ ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? (ዝም እላችኋለሁ)? በማለት ገሥጿቸዋል። እነርሱም ተግሣጹን ተቀብለው፥ ብቻቸውን ወደ እርሱ ቀረቡና፦ «ጋኔኑን እኛ ልናወጣው ያልቻልነው ለምንድነው?» ብለው ጠየቁት። እርሱም፦ «ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤» አላቸው። ማቴ ፲፯ ፥፲፬-፳።
          እምነታችንን ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ፥ በገድላት ፥ በተአምራትና በድርሳናት ከተጻፉት የእምነት ታሪኮች አንፃር ስናየው ባዶ ሆኖ ነው የምናገኘው። በቅርብ ከሚገኙት የወላጆቻችን እምነት ጋር እንኳ ስናስተያየው የእኛን አምነት አለ ለማለት ያስቸግራል። ስለዚህ በደስታ ጊዜ እምነታችንን የዘነጋን ፥ በሀዘንም ጊዜ ፈጥነን ተስፋ የቆረጥን ሰዎች ፥ ስለ እምነት እውቀቱ እንጂ ሕይወቱ የሌለንም ሁሉ ፦ « አለማመኔን እርዳው ፤» ልንለው ይገባል። ማር ፱፥፳፬። የዘወትር ጸሎታችንም « እምነት ጨምርልን ፤» መሆን አለበት። ሉቃ ፲፯ ፥ ፭።
          በሌላ በኲል ደግሞ በዚህ ዓለም መናፍቃንና አሕዛብ ሲከናወንላቸው እያየን ፥ እየሰማን ውስጣችን የሚደክምብን ሰዎች አለን። ቅዱስ ዳዊት ፦ «እኔ ግን እግሮቼ ሊሰናከሉ ፥ አረማመዴም ሊወድቅ ጥቂት ቀረ። የዓመጸኞችን ሰላም አይቼ በኃጢአተኞች ላይ ቀንቼ ነበርና ፤» እንዳለ። መዝ ፸፪ ፥፪። ከዚህም በላይ «በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁአትን? እጆቼን በንጽሕና በከንቱ አጠብሁ። ሁልጊዜም የተገረፍሁ ሆንሁ ፥ መሰደቤም በማለዳ ነው። » ብሏል። በመጨረሻ ግን ፦ « በድጥ ሥፍራ አስቀመጥኻቸው ፥ ወደ ጥፋትም ጣልኻቸው። እንዴት ለጥፋት ሆኑ! በድንገት አለቁ ፥ ስለ ኃጢአታቸውም ጠፉ። ከሕልም እንደሚነቃ ፥ አቤቱ ፥ስትነቃ ምልክታቸውን ታስነውራለህ።» በማለት አድንቋል። መዝ ፸፪ ፥፲፫፥፳።
          በቤተ ክርስቲያን እየኖርን ፦ በመጸለይና ባለመጸለይ ፥ በመጾምና ባለመጾም ፥ ንስሐ በመግባትና ባለመግባት ፥ በማስቀደስና ባለማስቀደስ ፥ በመቁረብና ባለመቁረብ ፥ መስቀል በመሳለምና ባለመሳለም ፥ ጠበል በመጠጣትና ባለመጠጣት ፥ በመጠመቅና ባለመጠመቅ ፥ ቃሉን በመስማትና ባለመስማት ፥ በመዘመርና ባለመዘመር ፥ አሥራት በማውጣትና ባለማውጣት መካከል ልዩነቱ እየጠፋብን የሄደው እምነታችን እየጐደለ በመሄዱ ነው። ድሮ ድሮ ያላስቀደስን ዕለት ያመን (ይሰማን) ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን ምንም አይመስለንም። ውዳሴ ማርያሙ ፥ ዳዊቱ ያልተደገመ ዕለት ቀኑን ሙሉ መንፈሳችን ይታወክብን ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን ምንም የቀረብን አይመስለንም። እየቀረብን ፥ እየተጠጋን በመጣን ቁጥር እንደመበርታት እየደከምን መጥተናል። ድፍረቱም በዚያው ልክ ነው። የዔሊ ልጆች አፍኒን እና ፊንሐስ በእግዚአብሔር ማደሪያ በደብተራ ኦሪት እያገለገሉ እግዚአብሔርን አያውቁም ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፪፥፲፪። በቅድስናውም ስፍራ ያመነዝሩ ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፪፥፳፪። ማንኛውም ሰው እምነት ሲጐድለው እንዲህ ነው ፥ ፈሪሃ እግዚአብሔር አይኖረውም። እምነቱ ሙሉ የሆነ ዮሴፍ ግን በአሕዛብ ምድር ሆኖ እግዚአብሔርን ፈራ። የጌታው ሚስት ፦ ብእሲተ ጲጥፋር የሚያየን ሰው የለምና እንስረቅ ባለችው ጊዜ፦ «በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?» አለ። ዘፍ ፴፱ ፥ ፱። ለመሆኑ ከሰው ተሸሽገን በየጓዳው በየጐድጓዳው በእግዚአብሔር ፊት ስንት ኃጢአት ሠርተን ይሆን? «እኛን በሚቈጣጠር በእርሱ በዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው እንጂ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።» የሚለውን እናውቀዋለን። ዕብ ፬፥፲፫። ነገር ግን አልኖርንበትም። እንዲህ ሲሆን እምነት እየጐደለ ብቻ ሳይሆን እየሞተም ይሄዳል። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ፦ «ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው፤» ብሏልና። ያዕ ፩፥፲፯። በአጠቃላይ ፦
፪፥፩፦ ጸሎታችን እምነት ይጐድለዋል፤
          የምንጸልየው በመንታ ልብ በሁለት ሐሳብ ነው። «ጥበብን ያጣት ሰው ቢኖር ፥ ሳይነቅፍና ሳይነፍግ ለሁሉ በልግስና የሚሰጥ እግዚአብሔርን ይለምን ፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን አምኖ ይለምን ፥ አይጠራጠርም (ሳይጠራጠር ይለምን) ፤ የሚጠራጠር በንፋስ የሚገፋና የሚነዋወጥ የባሕር ማዕበልን ይመስላልና። ለዚያ ሰው ከእግዚአብሔር ምንም የሚያገኝ አይምሰለው። ሁለት ልብ የሆነ ሰው በመንገዱ ሁሉ ይታወካልና። » ያዕ ፩ ፥ ፭-፰።
፪፥፪ ጾማችን እምነት ይጐድለዋል፤
          የምንጾመው ቅዱስ ያሬድ ፦ «ይጹም ዓይን ፥ ይጹም ልሳን ፥ዕዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ኅሡም በተፋቅሮ ፤ » እንዳለው አልሆነም። በእምነት ልንጾማቸው የሚገባቸውን አጽዋማት የልማድ አድርገናቸዋል። ከእህል ከውኃ እንጂ ከኃጢአት ከበደል አልተከለከልንም። «ነገር ግን ጽድቅን እንደሚያደርግ የአምላኩን ፍርድ እንደማይተው ሕዝብ ዕለት ዕለት ይሹኛል ፥ መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ። አሁንም እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል ፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ። ስለምን ጾምን? አንተም አልተመለከትኸንም ፣ ሰውነታችንንስ ለምን አዋረድን? አንተም አላወቅኸንም ፥ ይላሉ። እነሆ ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ ፥ ሠራተኞቻችሁንም ታስጨንቃላችሁ። እነሆ ፥ ለጠብና ለክርክር ትጾማላችሁ።» ኢሳ ፶፰፥፪-፬።
፪፥፫፦ ምጽዋታችን እምነት ይጐድለዋል ፤
          ምጽዋት « አባታችሁ ርኅሩኅ እንደሆነ ርኅሩኆች ሁኑ፤» እንዳለ ፈጣሪያችንን የምታስመስለን ጸጋ ናት። ሉቃ ፮፥፴፮። የእኛ ግን ነገራችን ሁሉ የውዳሴ ከንቱ ነው። «ለእገሌ እንዲህ አድርጌለት ፥ ለእገሊትም እንዲህ ሠርቼላት ፥» ማለት ይቀናናል። ያየ የሰማ ፥ የተሰማማ ሁሉ « ቅዱስ ፥ ቅዱስ » እንዲለን እንፈልጋለን። የተነገረው ፦ « መልካሙን ሥራችሁን አይተው ፥ በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑት ዘንድ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።» የሚል ነበር። ማቴ ፭፥፲፮። «ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ፥ ምጽዋታችሁን በሰዎች ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው በአባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም።» ማቴ ፮፥፩
፪፥፬፦ አገልግሎታችን እምነት ይጐድለዋል፤
          በቤተ መቅደስ ፥ በቅኔ ማኅሌት ፥ በዓውደ ምሕረት ፥ (በስብከት ፥ በመዝሙር) ፥ በሰበካ ጉባኤ ፥ በሰንበት ት/ቤት ፥ በማኅበር የምናገለግል ሰዎች ሩጫችን ሁሉ የእምነት አይመስልም። ከሥጋ ጥቅም ወይም ከዝና ጋር የተቆራኘ ነው። ሰው አገልግሎ በሥጋው አይጠቀም ወይም በጸጋው አይታወቅ ማለት አይደለም። ምክንያቱም ፦ « እህልን በምታበራይበት ጊዜ በሬውን አፉን አትሰረው ፥ ለሚሠራም ደመወዙ ይገባዋል ይላልና።» ፩ኛ ጢሞ ፭፥፲፰ ፣ ዘዳ ፳፭፥፬ ፣ ማቴ ፲፥፲። በተጨማሪም «ከቶ በገዛ ገንዘቡ ወታደርነት የሚያገለግል ማነው? ወይስ መንጋ እየጠበቀ ከመንጋው ወተት የማይጠጣ ማነው? ይህን በሰው ሥልጣን ብቻ እላለሁን? ሕግስ ደግሞ ያን አይልምን? የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር ተብሎ ተጽፎአልና። እግዚአብሔርስ ስለበሬዎች ይገደዋልን? ይህን የሚለው ፈጽሞ ስለ እኛ አይደለምን?. . . . . እኛ መንፈሳዊውን ነገር የዘራንላችሁ ከሆንን የእናንተን የሥጋዊን ነገር ብናጭድ ትልቅ ነገር ነውን? ሌሎች በእናንተ ላይ ይህን መብት የሚካፈሉ ከሆነ እኛማ ይልቁን እንዴታ?» የሚል አለ። ፩ኛ ቆሮ ፱፥፯-፲፪። ነገር ግን ዓላማችን ጽድቅ ይሁን ፥ በሩን ይዘን እንቅፋት አንሁን ለማለት ነው። አለበለዚያ ጻፎችና ፈሪሳውያን በተመቱበት በትር እንመታለን። ጌታ በወንጌል ፦ « እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳዊያን መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ፥ ወዮላችሁ፤ እናንተ አትገቡም ፥ የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።» እንዳለ። ማቴ ፳፫፥፲፫።
ከዚህም ሁሉ ጋር ትኅትና ፥ ትዕግሥት ፥ ቸርነት ፥በጎነት ፥ የዋሃት ፥ ራስን መግዛት ፥ ፍቅር ፥ ደስታ ፥ ሰላም ይጐድለናል።እነዚህም ፈቃዳተ ነፍስ ናቸው። ገላ ፭፥፳፪ ። እንዲህም ማለታችን በሚበዛው መናገራችን እንጂ አራቱ ባህርያተ ሥጋ የተስማሙላቸው ፥ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ፥ ለፈቃደ ነፍስ አድልተው የሚኖሩ የሉም ማለት እይደለም። በከተማም በገጠርም ፥ በደብርም በገዳምም እግዚአብሔር የሚያውቃቸው ከዋክብት አሉ። በሰውም ዘንድ የሚታወቁ አሉ። ስለዚህ ፦ እገሌ ፥ እነ እገሌ ምን ይጐድላቸዋል ? ሳይሆን እኔን የሚጐድለኝ ምንድነው? እንበል። የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን ፥ አሜን።
 

የራሔል እንባ

          « እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የኀዘን የልቅሶና የጩኸት ድምጽ በራማ ተሰማ ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ድምጽሽን ከለቅሶ ዐይኖችሽንም ከእንባ ከልክዩ ፤ ለሥራሽ ፤ ዋጋ ይሆናልና ፥ ይላል፡፡ እግዚአብሔር ፤ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ። ለፍጻሜሽም ተስፋ አለ ፥ ይላል እግዚአብሔር ፥ ልጆችሽም ወደ ሀገራቸዎ ይመለሳሉ። » ኤር ፴፮ ፥፲፭ ፡፡
          ቅዱሳን ነቢያት የሚናገሩት ስለ ዘመናቸው ብቻ አይደለም ፤ ከዘመናቸው ጋር በማገናዘብ ስላለፈው ይናገራሉ ፥ ስለሚመጣውም ይተነብያሉ። ዓረፍተ ዘመን ሳይገታቸው ኃላፊያትንም መጻእያትንም ይተረጉማሉ። በመሆኑም ይህ ቃለ ኤርምያስ  ወደኋላም ወደፊትም የሚሠራ ነው። ለጊዜው እስራኤል ዘሥጋ በግብጽ የባርነት ዘመን የነበሩበትን ዘመን ያስታውሳል ፥ ለፍጻሜው ደግሞ በዘመነ ሥጋዌ መባቻ ማለትም መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ የተፈጸመውን ያሳያል።
      እስራኤል በባዕድ ሀገር በግብፅ በዮሴፍ ስም ተወደው ተከብረው ይኖሩ ነበር፡፡ በኋላ ግን ዮሴፍን የማያውቅ ፥ አንድም ደግነቱን ጥበቡን የማያውቅለት ንጉሥ ተነሥቶ ቀንበር አጠበቀባቸው። ይኸውም፦ የእሥራኤል ልጆች ፈጽመው በዝተዋል ፥ ከእኛ ም እነሱ ይጸናሉ ፥ ወደፊት ጠላት ቢነሣብን ከእነርሱ ወገን ተሰልፈው ይወጉናል ፥ አንድም ከበዙ ዘንድ አገራችንን ያስለቅቁናል። ብሎ ገና ለገና ፈርቶ ነው። ፈሪ ሰው ጨካኝ በመሆኑም፦ « ኑ ብልሃት እንሥራባቸው ፤ ጡብ እናስጥላቸው ፥ ኖራ እናስወቅ ጣቸው ፥ ጭቃ እናስረግጣቸው ፤ ይህን ሲያደርጉ ከዋሉ ልሙዳነ ፀብእ አይሆኑም ፥ አንድም ከድካም ብዛት ከሚስቶቻቸው አይደርሱም ፥ ካልደረሱም አይባዙም ፥ ካልበዙም አኛን አያጠፉም ፤ » አለ። ይኽንንም ብሎ አልቀረም። በብዙ ማስጨነቅ ፌቶም ፥ ራምሴንና ዖን የተባሉ ጽኑ ከተሞችን በግንብ አሠራቸው።
  
እስራኤል ዘሥጋ መከራ የሚያጸኑባቸውን ያህል እንደ መከራው ብዛት  እየበዙ ይጸኑ ነበር። ግብጻውያን ግን የእሥራኤልን ልጆች ያስመርሯቸው ፥ እየገፉ እያዳፉ በግፍዕ ይገዟቸው ነበር፡፡ በሕይወት መኖርን በሚያሰቅቅ ሥራ ሰውነታቸውን ያስጨንቋት ነበር። ከዚህም ሌላ ንጉሥ ዓቀብተ መወልዳትን ( አዋላጆችን ) ሾሞባቸዋል፡፡ እነርሱንም « ዕብራውያትን ሴቶች ስታዋልዱ ለመውለድ እንደደረሱ በአያችሁ ጊዜ ፥ ወንድ ቢሆን ግደሉት ፤ ሴት ብትሆን ግን አትግደሏት ፤ » አላቸው። እነርሱ ግን እግዚአ ብሔርን ፈርተው እንዳዘዛቸው አላደረጉም። ንጉሡም ጠርጥሮ አንድም ከነገረ ሰሪ ሰምቶ ፦ « ለምን ያዘዝኳችሁን አልፈጸ ማችሁም ? » ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ምክንያቱም ወንድ ልጅ ተወልዶ ከሦስት ወር በኋላ ሲያለቅስ ፥ ሲያነጥስ በድምጹ ይታወቃልና ነው።  ሴቶች ምክንያት አያጡምና ( ብልሆች ናቸውና )፦ « የዕብራ ውያን ሴቶች እንደ ግብፃውያን ሴቶች አይደሉም ፥ አዋላጅቱ ሳትመጣ ወልደው ይቆያሉ ፤ » ብለው መለሱለት። እነርሱ ለእስራኤል በጐ ነገር በማድረጋቸው ፥ እግዚአብሔር ለእነርሱም በጐ አደረገላቸው ፤ ንጉሡ እንዳይገድላቸው አደረገ። ( የንጉሥ ትእዛዝ መተላለፍ ያስገድላልና )። ከፍ ብሎ በእግዚአብሔር ቸርነት ፥ ዝቅ ብሎ በአዋላጆች ደግነት እሥራኤል እጅግ በዝተው በረቱ። ያንጊዜም ፈርዖን ተቆጥቶ « ከዕብራውያን የሚወለደውን ወንድ ወንዱን ከፈሳሽ ውኃ ጣሏቸው ፥ ሴት ሴቱን ግን በሕይወት ተዉአቸው ፤ » የሚል አዋጅ አናገረባቸው።
   
 
          የእንባ ሰው ራሔል የነበረችው በዚህ ዘመን ነው። ሮቤልም ስምዖንም የሚባል ባል ሞቶባት ሐዘንተኛ ነበረች። እርሱ ሲሞት ነፍሰ ጡር ብትሆንም « በእርሱ ምትክ ኖራ ውቀጪ ፥ ጭቃ ርገጪ፤ » ተባለች። መንታ ፀንሳ ኑሮ ደም ፈሰሳት ሕፃናቱም ወጥተው ፥ ወጥተው ፥ ከጭቃው ወደቁ ። ደንግጣ ብትቆም ፥ ምን ያስደነግጥሻል ? የሰው ደም ፥ የሰው ሥጋ ጭቃውን ያጸናዋል እንጂ ምን ይለዋል ብለሽ ነው? ርገጪው ፤ » አሏት ፡፡ በዚህን ጊዜ ነው ፥ « ኢሀሎኑ በዝ ሰማይ አምላከ እሥራኤል ፤ በውኑ በዚህ ሰማይ የእስራኤል አምላክ የለምን ?» ብላ እንባዋን ያፈሰሰችው። ይኽንንም እንባ በእፍኟ እየሰፈረች ወደ ላይ ረጨችው። «እንደገናም ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፤» እንዲል ፤ ኢሳ ፳፭ ፥ ፰ ፤ እንባን የሚያብስ እግዚአብሔር በሰማይ እንዳለ ታምናለችና። እንባዋ ወደ ምድር አልተመለሰም ፥ ከመንበረ ጸባዖት ደረሰ እንጂ ። « ወዐበየት ተናዝዞ ወነጊፈ ላህ ፤ ልቅሶ መተውን መጽናናትን እንቢ አለች።» ምክንያቱም ግፉ ያሳዝናልና ፥ የሕፃናቱ ሞት የፃር ነውና ፥ ሐዘን በየደጁ ኹኗልና፡፡ « እስመ ኢኮንዋ ውሉዳ ውሉደ ፤ ልጆቿ ልጆች አልሆኗትምና ፥» ሙተዋልና ፥ ባሌ ቢሞት በልጆቼ እጽናናለሁ። ያለችው ከንቱ ኹኖባታልና ። « ወኢሀለዉ በሕይወተ ሥጋ የለምና ፤» መጽናናትን እንቢ አለች፡፡ ይኽንን ነው ፥ ነቢዩ ኤርምያስ « የኀዘን የልቅሶና የጩኸት ድምፅ በራማ ተሰማ ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ፤ » ያለው።
          የራሔል እንባ እግዚአብሔር እንዲናገር ፥ በረድኤትም እንዲወርድ አድርጐታል። « ሰማዕኩ ገዓሮሙ ለሕዝብየ ፥ ወወረድኩ ከመ አድኅኖሙ ፤ የሕዝቤን ጩኸት ሰማሁ ፥ ላድናቸውም ወረድኩ ፤» አሰኝቶታል። « እግዚአብሔርም ሙሴን በግብፅ ያሉ የወገኖቼን መከራ አይቼ ፥ በሠራተኞች የተሾሙ ሹማምንት ካመጡባቸው መከራ የተነሣ ጩኸታቸውን ሰምቼ ፥ መጨነቃቸውን አውቄላቸዋለሁ። ከግብጻውያን እጅ አድናቸው ፥ ወደ ተወደደችም ሰፊ ወደምትሆን ወደ ከነዓንም እወስዳቸው ዘንድ ወረድኩ። ከግብፅም አውጥቼ ማርና ወተት ወደሚጐርፍባት ፥ ተድላ ደስታ ወደማይታጣባት አገር እወስዳቸዋለሁ ፤ » አለ። ማር ያለው ሕገ ኦሪትን ነው ፥ ማር የነካው ጨርቅ በውኃ ቢያጥቡት ፈጥኖ እንዲለቅ ሕገ ኦሪትም የሚለቅ ሕግ ነበርና። ወተት ያለው ደግሞ ሕገ ወንጌልን ነው። ወተት (ቅቤ) የነካው ጨርቅ በውኃ ቢያጥቡት እንደማይለቅ ሕገ ወንጌልም የማትለቅ ( ጸንታ የምትኖር ) ሕግ ናትና ። ዘጸ ፫ ፥ ፰ ፡፡
          በአዲስ ኪዳን ደግሞ ከላይ እንደጠቆምነው ፦ ጌታ በተወለደ ጊዜ የአይሁድ ንጉሥ የነበረ ሄሮድስን በግብር ፈርዖንን መስሎ እናገኘዋለን ፡፡ የሩቆቹ ወርቅ ዕጣንና ከርቤ ይዘው ፥ በኮከብ እየተመሩ ሁለት ዓመት ተጉዘው ሲመጡ የቅርቡ ሄሮድስ ግን ዜና ልደቱ አስደነገጠው ። ጥያቄያቸው ፦ « አይቴ ሀሎ ንጉሥ ዘተወልደ ፤ የተወለደው ንጉሥ ወዴት ነው ? » የሚል ነበርና ። ዓለም የሥልጣን ነገር ያሳስበዋል ፥ የደነገጠ አውሬም ያደርገዋል ። የደነገጠ አውሬ ማንንም እንደማይምር ዓለምም እንዲሁ ነው።
          ሄሮድስ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከሰብአ ሰገል በጥንቃቄ ከተረዳ በኋላ በልቡ ፦ «ለካ ያ ብላቴና ሁለት ዓመት ሆኖታል ፤» አለ። ካህናቱን በስውር ጠርቶ በተረዳውም መሠረት « ቤተልሔም ነው፤ » ብሎ ሰደዳቸው። ከዚህም ጋር ፦ « ሄዳችሁ የብላቴናውን  ነገር ጠይቃችሁ እርሱን ያገኛችሁት እንደሆነ እኔም እንድሰግድለት በእኔ በኲል ተመልሳችሁ ንገሩኝ፤ » አላቸው፡፡ እርሱ በሽንገላ ቢናገረውም ነገሩ ጥበበ እግዚአብሔር ነው። ሰብአ ሰገል፦ « ለካስ የሀገሩም ነገሥታት ያምኑበታልሳ ፤ » በሚል ሃይማኖታቸው እንዲጸናላቸው ነው ።
          ሰብአ ሰገል ግን ሳጥኖቻቸውን ከፍተው ወርቅ እጣን ከርቤ ለሕፃኑ ከገበሩለት በኋላ መልአኩ እንደነገራቸው በሌላ ጐዳና ፥ በሌላ ኃይለ ቃል ፥ በሌላ ሃይማኖት ተመልሰዋል ። በሌላ ጐዳና ሁለት ዓመት የተጓዙትን በአርባ ቀን ገብተዋል፡፡ በሌላ ኃይለ ቃል « ወዴት ነው?» እያሉ መጥተው ነበር ፥ « አገኘነው ፤ » እያሉ ተመልሰዋል፡፡ በሌላ ሃይማኖት « ምድራዊ ንጉሥ ፤» እያሉ መጥተው ነበር ፥ ሰማያዊ ንጉሥ ፥ የባሕርይ አምላክ » እያሉ ተመልሰዋል።
          ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደዘበቱበት  ( ባንተ በኩል እንመለሳለን ብለው በሌላ ጐዳና እንደሄዱ ) በሰማ ጊዜ ፈጽሞ ተበሳጨ። ጭፍራዎቹን ልኮ ከሰበአ ሰገል እንደተረዳው ዘመን ልክ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ፥ ከዚያም የሚያንሱትን  ፥ በቤተልሔምና በአውራጃዎችዋ ሁሉ የነበሩትን አሥራ አራት እልፍ ሕፃናት አስገደለ። ያን ጊዜ ፦ በነቢዩ በኤርምያስ ፦ « ራሔል ስለ ልጆችዋ ስታለቅስ ብዙ ልቅሶና ዋይታ ተሰማ ፤ መጽናናትንም እንቢ አለች ፤ ልጆቿ የሉምና። » የተባለው ተፈጸመ ፥ ይላል። ራሔልን አነሣ እንጂ ልያን አላነሣትም። ምክንያቱም ጌታ የተወለደው ከልያ ወገን ስለተወለደ ዕዳዋ ነው። ራሔል ግን ከእርሷ ወገን ስላልተወለደ ያለ ዕዳዋ ነው። አንድም የልያ በርኅቀተ ሀገር በብዛት ድነውላታል ፤ የራሔል ግን በማነስ በቅርበት አልቀውባታልና ነው። አንድም በራሔል የልያንም መናገር ነው። አንድም « እናታችን ራሔል ኑራልን ፥ መከራችንን አይታልን ባለቀሰችልን ፣» ብለው ስላለቀሱ ነው። አንድም እንድናለን መስሏቸው ከመቃብረ ራሔል ገብተዋል ፥ ከዚያም ተከትለው ገብተው ልጆቻቸውን ከእቅፋቸዋ ነጥቀው ፥ አንገታቸውን ጠምዘው አርደውባቸዋል። በዚህን ጊዜ አፅመ ራሔል አንብቷል።  የራሔል መቃብር ከቤተልሔም አንድ ኪ.ሜ. ይርቃል።
          በሌላ በኲል ደግሞ ከልያም ከራሔልም ወገን የተወለዱትን ሊያገናኝ የሚችለውን አባታቸውን ያዕቆብን አላነሣም። ያነሣው እናታቸውን ራሔልን ነው። ምክንያቱም፦ ወንድ ልጅ ለአቅም አዳም ፥ ሴት ልጅ ለአቅመ ሔዋን ደርሰው የሞቱ እንደሆነ ኀዘን በአባት ይጸናል። በሕፃንነት ዘመን የሞቱ እንደሆነ ግን ኀዘን በእናት ይጸናልና ለዚህ ነው ።
          ቅዱስ ማቴዎስ « ራሔል » ብሎ ትንቢተ ኤርምያስን የጠቀሰው ለዚህች ብቻ ሳይሆን በግብፅ ለነበረችውም ነው። ይኸውም ግፍን ከግፍ ሲያነፃፅር ነው።
እነዚህን ሁሉ ሕፃናት እንዴት አድርጎ ሰበሰባቸው?
          ሄሮድስ አሥራ አራት እልፍ ሕፃናት የሰበሰበው « ንጉሡ ቄሣር ፦  ሕፃናትን ሰብስበህ ፥ ልብስ ምግብ እየሰጠህ ፥ በማር በወተት አሳድገህ ፥ ለወላጆቻቸው ርስት ጉልት እየሰጠህ ጭፍራ ሥራልኝ ብሎኛል፤ » የሚል አዋጅ አናግሮ በጥበብ ነው። ያላቸው ልጆቻቸውን፥ የሌላቸው ደግሞ ልብስ ምግብ ልቀበልበት ብለው እየተዋሱ ሄደዋል። እንዲህ አድርጎ ሰብስቦ ፈጅቷቸዋል። ለሁለቱም የግፍ ታሪኮች «የኀዘን የልቅሶና የጩኸት ድምፅ በራማ ተሰማ፤» የተባለው በመላእክት ዘንድ ተሰማ ፥ ማለት ነው። ምክንያቱም ኢዮር ፥ ራማ ፥ ኤረር ዓለመ መላእክት ናቸውና። አንድም በመላእክት ፈጣሪ በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰማ ማለት ነው። ምክንያቱም መላእክት ባሉበት እግዚአብሔር አለ። አንድም ራማ የተባለች መንግሥተ ሰማያት ናት። ምሥጢራዊ ትርጉሙም ሃይማኖት ይዞ ምግባር ሠርቶ የሚገባባት አጥታ ታዝናለች ፥ ታለቅሳለች ማለት ነው።
          በዚህ ዘመን የሚያስፈልገው ሌላ ነገር ሳይሆን ይህ የራሔል እንባ ነው። ዓለም በግፍ ተከድናለችና ፥ ነፃ ሰው የለምና። «ረከሱ በበደላቸውም ጐሰቈሉ ፥ በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም። እግዚአብሔርን የሚፈልግ አስተዋይ እንዳለ ያይ ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ ሁሉ ተካክሎ በአንድነት በደለ ፤ አንድ ስንኳ በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም፡፡ ሕዝቤን እንጀራን እንደ መብላት የሚበሉ ግፍ አድራጊዎች ሁሉ አያውቁም ፥ እግዚአብሔርን አይጠሩትም።» እንዲል፡፡ መዝ ፶፪ ፥ ፩-፬ ። ስለዚህ ፦
ሀ. ለራሳችን እናልቅስ ፤
          በሕገ እግዚአብሔር ጸንተን ባለመቆማችን ( ከፍቅረ እግዚአብሔርም ከፍቅረ ቢጽም በመለየታችን ) ልናለቅስ ይገባል። «ሕግህን አልጠበቅሁምና የውኃ ፈሳሾች ከዓይኖቼ ፈሰሰ ይላልና። መዝ ፩፻፲፰ ፥ ፩፻፴፭ ፤። ቅዱስ ዳዊት ብዙ ጊዜ ለራሱና ለቤተሰቡ አልቅሷል። በኦርዮና በቤርሳቤህ ምክንያት ነቢዩ ናታን በገሠጸው ጊዜ ፦ « እግዚአብሔርን በድያለሁ ፤ » ብል አለቀሰ። ነቢዩ ናታንም፦ እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢአትህን አርቆልሃል ፥ አትሞትም። ነገር ግን በዚህ ነገር ለእግዚአብሔር ጠላቶች መነሣሣት ምክንያት አድርገሃልና ስለዚህ ደግሞ የተወሰደልህ ልጅ ፈጽሞ ይሞታል፤ » አለው። ዳግመኛም ቅጣቱ እንዲነሣለት ማቅ ለብሶ አመድ ላይ ተኛ ፥ ጾመ ፥ ለመነ ፥ ጸለየ ፥ አለቀሰ፡፡  እርሱም ራሱ « ሕፃኑ ሕያው ሳለ ፥ ምናልባት እግዚአብሔር ይምረኝ ፥ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደሆና ማን ያውቃል ብዬ ጾምሁ ፥ አለቀስሁም፤ » ብሎአል። ፪ኛ ሳሙ ፲፪፥፩-፳፫። ልጁ አቤሴሎም ባሳደደውም ጊዜ ተከናንቦ እያለቀሰ የደብረ ዘይትን አቀበት ወጥቷል፡፡ ፪ኛ ሳሙ ፲፭ ፥ ፴ ።
          ቅዱስ ዳዊት ወደ ውስጥ እየተመለከቱ ስለ ራስ በማልቀስ ያምን ነበር። ብዙ ጊዜም ውጤት አግኝቶበታል። ይኽንንም በመዝሙሩ ላይ ብዙ ቦታ ጠቅሶታል። « በጭንቀቴ ደክሜአለሁ ፥ ( ወድጄ በሰራሁት ሥራ ጠፋሁ ) ፥ ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ ፥ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ። ዐይኔ ከቁጣ የተነሣ ታወከች ፥ ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ አረጀሁ። ( ሰብአ ትካትን ፥ ሰብአ ሰዶም ፥ ሰብአ ገሞራን ባጠፋህበት መዓትህ ታጠፋኝ ይሆን ? ከማለቴ የተነሣ ዓይኔ ባከነች። ሴትና ልጅ አለንጋ ያነሡባቸው እንደሆነ ከአሁን አሁን ያሳርፉብን  ይሆን ብለው ዓይናቸው እንደሚባክን እኔ ባከንኩኝ። ከፍርድህ የተነሣ ሰውነቴ ባለ መከራ ሆነች። ከቁጡ ዕንባ የተነሣ ፊቴ ተንጣጣ ፥ ቅንድቤ ተመለጠ )። ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ አረጀሁ። ( መከራ ስላጸኑብኝ ያለ ዕድሜዬ አረጀሁ ፥ እያልሁ እንደሌለ ሰው ሆንኩኝ ፥ ሳልሞት እንደ ሞተ ሰው ተቆጠርኩኝ )፡፡ ዓመፃን የምታደርጉ ሁሉ ፥ ከእኔ ራቁ ፤ ( ጐልማሳ ገደለ ፥ የጐልማሰ ሚሰት ነሣ ፥ እያላችሁ ከፈጣሪዬ ጋር የምታጣሉኝ ሰዎች አንድም አጋንንት ከእኔ ራቁልኝ ) ፤ እግዚአብሔር የልመናዬን ቃል ሰምቶአልና። ብሏል። መዝ ፮ ፥ ፮-፰። በሌላ ምዕራፍም፦ « ልቅሶዬን መልስህ ደስ አሰኘኸኝ። ማቄን ቀድደህ ደስታን አስታጠቅኸኝ። » ብሏል፡፡ መዝ ፳፱ ፥ ፲፩።
          ቅዱስ ዳዊት የችግሩ መፍቻ ቁልፍ ምንግዜም ቢሆን እውነተኛ እንባው ነበር። ጠላቶች ሲሰድቡት ፥ ጐረቤቶቹ ሲርቁት ፥ ዘመዶቹ ሲክዱት ፥ ያዩት ሁሉ ከእርሱ ሲሸሹ ፥ ሁሉም እንደሞተ ሰው ከልብ ሲረሳው ፥ እንደጠፋ ዕቃ ሲሆን ፥ በዙሪያው የከበቡትን ሰዎች የትዕቢት ድምፅ ሲሰማ ፥ ለክፉ ነገር ተባብረው ነፍሱን ለመንጠቅ ሲማከሩ እርሱ ግን በእግዚአብሔር ታምኖ እንፋሎት ያለው እንደ ፈላ ውኃ የሚያቃጥል እንባ በጉንጮቹ ላይ ያፈስ ነበር። መዝ ፴ ፥ ፱-፲፬። ጠላቶቹ ባመጡበት መከራ ደስ ሲላቸው ልቅሶው እናት እንደሞተችበት ሰው ነበር። መዝ ፴፬፥፲፱ ።
          ቅዱስ ዳዊት ስለ ራሱ የሚያለቅሰው « ለምን ይህ መከራ መጣብኝ ፤ » በማለት ሳይሆን በተአምኖ ኃጣውዕ (ኃጢአትን በመታመን) መከራውን እንዲያርቅለት ነው። መዝ ፴፯ ፥ ፲፰። ንጉሡ እዝቅያስም፦ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ  « ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል ፤ » ባለው ጊዜ ፥ ወደ ግድግዳ ዞሮ እጅግ ታላቅ ልቅሶን በማልቀሱ ከበሽታው ተፈውሷል ፥ በዕድሜው ላይ አሥራ አምስት ዓመት ተጨምሮለታል። ሕዝ ፴፰ ፥ ፩-፭።
          ቅዱስ ጴጥሮስ ፦ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እርሱ የተናገረው ትንቢት በተፈጸመበት ጊዜ ወደ ወጭ ወጥቶ መራራ ልቅሶን አልቅሷል።
           ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈሪሳዊውን ግብዣ ተቀብሎ ከደቀመዛሙርቱ ጋር በማዕድ በተቀመጠ ጊዜ ፥ በዚያ አገር ካሉ ሰዎች ይልቅ ኃጢአተኛ የነበረች ሴት ሽቱ ይዛ መጣች። እያለቀሰች በዕንባዋ እግሩን አራሰችው ፥ በጠግሯም አበሰችው። እግሩን ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበር። እንዲህም በማድረጓ ከሰባት አጋንንት ቁራኝነት አላቀቃት ፥ « እምነ ትሽ አድኖሻልና በሰላም ሂጂ፤ » አላት። ለእኛ የሚያስፈልገን እንዲህ ዓይነት ዕንባ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ፦ « አሁን ለንስሐ ስላዘናቸሁ ደስ ብሎኛል እንጂ ስላዘናችሁ አይደለም። » ያለው ለዚህ ነውና። ፪ኛ ቆሮ ፯ ፥ ፱።
                                               ለ. ለትዳራችን እናልቅስ ፤
          ባል በሚስቱ ፥ ሚስትም በባሏ ግፍ እየፈጸሙ ነውና። « መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው ፥ ለመኝታቸውም ርኵሰት የለውም ፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። » የሚለው እንኳን ግብሩ ጥቅሱ ከጠፋብን ሰንብተናል። የሠርግ ሰሞን የጥሪ ወረቀታችንን እና ግድግዳችንን ያጨናነቀው እርሱ ነበር። ዳሩ ግን በወረቀት ላይ እንጂ በልባችን ላይ ስላልተጻፈ ፈጽሞ ተረስቷል። ዕብ ፲፫ ፥፬። ነገሩ ሁሉ፦ « ሚስት ታጫለህ ፥ ሌላም ሰው ከእርስዋ ጋር ይተኛል ፤ ቤት ትሠራለህ ፥ አትቀመጥበትም ፤ ወይን ትተክላለህ ፥ ከእርሱም አትበላም፤ » ሆኗል። ዘዳ ፳፰ ፥፴። ወንዶቹንም ቢሆን፦ « ሚስትህ ባልንጀራህን የቃል ኪዳንህ ሚስት ሆና ሳለች እርሷን አታልለሃታልና፤ » እያለን ነው ፥ እግዚአብሔር። ሚል ፪ ፥፲፬። ነገር ግን የሚያደምጥ ጠፍቶ ምድር ፍቺ በፍቺ ሆናለች። በአንድ ቤት ውስጥ እየኖርን በምንም ነገር የማንስማማ ፥ ላለመስማማት ተስማምተን ፥ ተናንቀን ፥ እጅ እጅ የሚል (የተሰለቸ) ኑሮ የምንኖር እንደተፋታን ነው  የምንቆጠረው። « ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ ፥ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል። መፋታትን እጠላለሁ ፥ ይላል የእሥራኤል አምላክ እግዚአብሔር ፤ ልብሱንም በግፍ ሥራ የሚከድነውን ሰው እጠላለሁ ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ፤ ስለዚህ እንዳታታልሉ መንፈሳችሁን ጠብቁ። » ሚል ፪ ፥፲፮።
ሐ. ለልጆቻችን እናልቅስ
          ከልጅነት እስከ እውቀት ከልጆቹ ጋር ደክሞ በልጆቹ የሚደሰት ጠፍቷል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም መስመር የለቀቁ ፥ ሰው ሰውኛውን እንዳይመለሱ ሆነው የጠፉ ፥ እንዳይነሡ ሆነው የወደቁ ልጆች ብዙዎች ናቸው። ጌታ በወንጌል፦ « እና ንተ የኢየሩሳሌም ልጆች ሆይ ፥ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔስ አታልቅሱልኝ። መካኖች ፥ ያልወለዱ ማኅፀኖችና ያላጠቡ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው ፥ የሚሉበት ወራት ይመጣልና። » ያለው በገሀድ እየታየ ነው። ሉቃ ፳፫ ፥፳፰። ንጉሥ ዳዊትን ተከታይ አብጅቶ ከዙፋኑ ያሳደደው ፥ በጦርነትም የተፋለመው የገዛ ልጁ አቤሴሎም ነው። « ዳዊትም ተከናንቦ ያለ ጫማ እያለቀሰ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ወጣ ፤ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተከናንበው እያለቀሱ ወጡ። » ይላል ። ፪ኛ ሳሙ ፲፭ ፥፴። በሃይማኖትም በኵል፦ የሊቀ ካህናቱ የዒሊ ልጆች ቤተ መቅደሱን ደፍረው ያሰደፍሩ ነበር። በዚህ የተነሣ አባታችው በእግዚአብሔር ቃል ተገሥጿል ፥ በመጨረሻም ከወንበር ወድቆ አንገቱ ተቆልምሞ ክፉ ሞት ሞቷል። ልጆቹም በጦር ሜዳ ተቀሥፈዋል። ፩ኛ ሳሙ ፪ ፥፳፪ -፳፮ ፣ ፬፥፲፪-፳፪ ።
መ. ለወገኖቻችን እናልቅስ፤
          አንድ ሕዝብ ፥ አንድ ወገን ስንሆን በዘር ተለያየተን እርስ በርስ እየተቋሰልን ነው። ከዚህ ንጹሕ የሆነ ሰው ማግኘት እጅግ ያስቸግራል። ዘረኝነትን በቃልም በጽሑፍም ፊት ለፊት የምናወግዘውም ቢሆን ከጀርባችን አዝለነው እንገኛለን። በዓለማውያን ዘንድ ብቻ አይደለም ፥ መንፈሳውያን በምንባለውም ጭምር ነው። አማርኛ ተናገሪው ሌላውን እንዳላይ እንዳልሰማ ይላል ፥ በውስጥ ግን ጐንደሬ ፥ ጐጃሜ ፥ ወሎዬ ፥ ሸዌ እያለ የተከፋፈለ ነው። እንዲህ እያለ ክፍፍሉ እስከ ጐጥ ድረስ ይወርዳል። ትግርኛ ተናጋሪውም ለጊዜው አንድ ይመስላል እንጂ፦ አድዋ ፥ ሽሬ ፥ አክሱም ፥ተምቤን ፥ አዲግራት እያለ የተከፋፈለ ነው። ኦሮምኛ ተናጋሪውም የሸዋ ፥ የወለጋ ፥ የአርሲ ፥ የሐረር ፥ የባሌ ፥ የቦረና እያለ የተከፋፈለ ነው። ለአብነት እነዚህን ጠቀስን እንጂ በሁሉም ያው ነው። ለጊዜው የምንስማማው ከእኛ ዘር ውጪ የሆነውን ለማጥቃት እንጂ በውስጣችን እሳትና ጭድ ነን። ሄሮድስና ጲላጦስ በውስጥ አይስማሙም ነበር ፥ በውጭ ግን ክርስቶስን ለመስቀል ተስማሙ። ሊቃውንቱ ክርስቶስ ፍቅር ስለሆነ በመሐል ሆኖ አስማማቸው ይላሉ። የእነርሱ መስማማት ለእርሱ ጉዳት ቢሆንም አስማማቸው ። እኛም ተጐድተንም ቢሆን ሰዎች እንዲስማሙ እናድርግ። መስሎን ነው እንጂ እንኳን ዘር ከአንድ ማኅፀን መውጣትም አያስማማም። ቃየል አቤልን ገድሎታል ፤ ዘፍ ፭ ፥ ፰። ዔሳው ያዕቆብን ሊገድለው አሳዶታል ፤ ዘፍ ፳፯ ፥ ፵፮፡፡ አቤሜሌክ የእናቱን ወገኖች አስተባብሮ በእናት የማይገናኙትን ሰበዓ የአባቱን ልጆች ( ወንድሞቹን ) ነፍሰ ገዳዮችን በገንዘብ ደልሎ አሳርዷቸዋል። መሳ ፱፥፩-፮። ሁላችንም « ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም ፤ በሕያውና በዘለዓለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ። » የሚለውን ዘንግተናል። ማስታወስም አንፈልግም ፥ ብናስታውስም ለመፈጸም አቅም አጥተናል። ፩ጴጥ ፩ ፥፳፫ ።
ሠ. ለሀገራችን እናልቅስ
          በእነ ቅዱስ ዳዊት፦ « ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ፤ . . . በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ ፤ . . . ለኢትዮጵያ ሰዎች ምግባቸውን ሰጠሃቸው፤ » የተባለላት ሀገራችን እንዴት ናት? መዝ ፷፯፥ ፴፩ ፣ ፸፩ ፥፱ ፣ ፸፫ ፥፲፬። አባቶቻችን ሀገረ እግዚአብሔር ያሰኟት ሀገራችን ምን እየመሰለች ነው? እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የበቀሉባት ፥ እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የመነኑባት ፥ ተሰዓቱ ቅዱሳን የተጠለሉባት ኢትዮጵያ ይዞታዋ እንዴት ነው? የሚለውን ለመመለስ መጻሕፍትን ማገላበጥ ሊቃውንትን መጠየቅ የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ነገራችን ሁሉ « ክምሬ ያለሽ መስሎሻል ፥ ተበልተሽ አልቀሻል ፤ ሆኗል። » በረከት ርቆናል ፥ ረድኤት ተለይቶናል። ይህም በሚበዛው መናገር እንጂ ፈጽሞ የለም ማለት አይደለም። የሃይማኖት ለዋጮች በዝተዋል ፥ በውስጥም በአፍአም አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ጠንክረዋል ፥ አሕዛብ ተበረታተዋል። « ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት » የሚለውን ለማጥፋት በሙሉ ኃይላቸው እየተረባረቡ ነው። « አቤቱ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ ፥ የቅድስናህንም መቅደስ አረከሱ ፤ » የሚለውም እየተፈጸመ ነው። መዝ ፸፰ ፥፩ ።
          ስለዚህ አገራችንን የረሳን ሁሉ ቅዱስ ዳዊትን አብነት አድርገን « ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ፤ ባላስብሽ ፥ ምላሴ ከጉሮሮዬ ትጣበቅ ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ አገሬን ባልወድድ ፤ » እንበል። መዝ ፩፻፴፮፥፭። እንደ ነህምያ በሀገር ፍቅር እንቃጠል። ነህምያ የአገሩን ጥፋት በሰማ ጊዜ አመድ ነስንሶ ከአመድ ላይ ተቀምጦ አለቀሰ ፥ ማቅ ለበሰ ፥ አያሌ ቀን አዘነ ፥ በሰማይም አምላክ ፊት ጾመ ፥ ጸለየ። ነህ ፩ ፥፬።
          ስለ ሀገር ማሰብ ማለት፦ ስለ ወንዙና ተራራው ፥ ስለ ዳር ድንበሩ ብቻ አይደለም። ከዚህ ሁሉ ጋር ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ያሰኛትን ታሪክ ፥ ሃይማኖት ፥ ሥርዓት ፥ ትውፊት ፥ ቅርስና ፥ ሕዝብ ማሰብ ማዘን ማልቀስ ያስፈልጋል ። ዋናው ነገር በሃይማኖት የሚፈስ እንባ ነው። ያን ጊዜ ጩኸታችን እስከ ራማ ድረስ ይሰማል።
ረ. ስለ ቤተ ክርስቲያናችን አንድነት እናልቅስ ፤
          የቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚመጣው « በእኔ እበልጥ፤ » መንፈስ አይደለም። « ካልተመለሳችሁ ፥ እንደዚህም ሕፃን ካል ሆናችሁ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም እነደዚህም ሕፃን ራሱን ዝቅ ያደረገ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ ይህ ነው፤ » በሚለው መንገድ ብቻ ነው። ማቴ ፲፰ ፥፫። ወንጌልም ቤተ ክርስቲያንም መንግሥተ ሰማያት ይባላሉ ።ሮሜ ፲፩ ፥፲፯። የግል ጥቅማችን እንዲጠበቅልን ቅድመ ኹኔታ በማስቀመጥም አይደለም። መቀበሉ እንደ ቀኖት ቢሰማንም ፥ እንደ ሆምጣጤ ቢመረንም « እኔ ይቅርብኝ ፥ እኔ ልጐዳ ፤» በማለት ነው። ክርስቶስ ሰውና እግዚአብሔርን  ፥ ነፍስና ሥጋን  ፥ ሰውና መላእክትን  ፥ ሕዝብንና አሕዛብን አንድ ያደረገው፣ በመስቀል ላይ ቆስሎ ነው። ስለሆነም ክርስቶስ ለቆሰለላት ቤተ ክርስቲያን ትንሽ ትንሽ እንቁሰልላት። አባቶቻችን ቅዱሳን ብዙ ቆስለውላታል ። የእነርሱ ልጆች ነን ካልን አሠረ ፍኖታቸውን እንደተሰጠን ጸጋ መጠን እንከተል። ሁላችንም ራሳችንን እንመርምር። በሌላ ዓይን ያለውን ጉድፍ ሳይሆን በእኛ ውስጥ የተተከለውን ትልቅ ምሰሶ እንመልከት። የወጭቱን ላዩን ሳይሆን ውስጡን እናጥራ፥ያን ጊዜ ውጪውም ይጠራል። ማቴ ፯ ፥፩ ፣ ፳፫ ፥ ፳፭። የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ከተፈታ የአገሪቱም ችግር ይፈታል። የትዳራችንም የልጆቻችንም ችግር ይፈታል። በመሆኑም አስቀድመን ስለ ቤተ ክርስቲያናችን እናልቅስ። የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን ።