ወላዲተ አምላክ - ማርያም ..
በቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝ
ቤተክርስቲያን ድንግል ማርያም ያላትን ክብር ለመግለጥ የተለያዩ ምሳሌዎችን ትሰጣለች ።እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቅዱሳን ሁሉ ስትመሰገን የምትኖር ናት ። እመቤታችን ያላትን ክብር እንዴት እንደሚገልጹት ተጨንቀው በምን በምን እንመስልሻለን በማለት ያላትን ክብር ለመግለጽ በሰው ህሊና የሚለካ ምሳሌ ማጣታቸውን ብዙ ቅዱሳን ተናግረዋል። በተለይም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በማመስገን በቤተክርስቲያናችን ዘወትር የሚነሱት የሶርያው ቅዱስ ኤፍሬም ፤ የብህንሳው አባ ሕርያቆስ እና ኢትዮጵያዊው አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ይገኙበታል ። የእመቤታችንን ክብር ያለተረዱ ሰዎች ለምን እኛ ኦርቶዶክሳውያን እንደምናመሰግናት ዘወትር በጸሎታችን እንደምናነሳት ጥያቄ የሚያቀርቡ አሉ ። ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ከሕጻንነቱ ጀምሮ የእመቤታችንን ምስጋና ይማራል ሁልጊዜም ኣባታችን ሆይ ብሎ ጸሎት የጀመረ በመልኩ ቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እንልሻለን ብሎ ድንግል ማርያምን ሳያመሰግን የሚቀር የለም ። ቤተክርስቲያናችን ድንግል ማርያምን ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን ሁሉ በላይ በማለት ክብሯን ትገልጻለች። እኛም የእመቤታችንን ክብር ስንናገር ስለ እርሷ የተነገረውን በመረዳት መሆን ይገባል ። ድንግል ማርያምን ልዩ የሚያደርጋትና የክብሯ መገለጫ ከሆኑት የሚከተሉት ይገኙበታል።
1ኛ. ወላዲተ አምላክ መሆኗን
እመቤታችን ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ናት። አንዳንዶች የአምላክ እናት የኢየሱስ እናት በማለት ይጠራሉ በእርግጥ ይህ አጠራር በበጎ ህሊና አነጋገር ችግር ባይኖርበትም የትርጉም ፍቺ ላይ ችግረ እንዳያመጣ ወላዲተ አምላክ ብሎ መጥራት የበለጠ የተዋሕዶን ምሥጢር የሚገልጥ ይሆናልና ሁሉም ሰው ይህንን መጠሪያ ቢለምደውና ቢጠቀምበት ይመረጣል። አንዳንድ የመናፍቃን ድርጅቶች የኢየሱስ እናት ብለው እመቤታችንን የተቀበሉ ለማስመስል በራሪ ጽሑፍ የሚያሰራጩበት ጊዜ ነበር ምክንያቱም ወላዲተ አምላክ መባሏን የሚቃወሙ ነገር ግን የኢየሱስ እናት ብለው የሚጠሩ ከዚህ በፊት ነበሩና ያሳደገም እናት ተብሎ ሊጠራ ይችላልና። በተለይም ንስጥሮስ የተባለው ከሃዲ ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ልትባል አይገባም ብሎ በክህደት በመነሳቱ ዓለማቀፋዊ ጉባኤ እንዲጠራና ውግዘት እንዲተላለፍበት ሆኗል። እመቤታችን ወላዲተ አምላክ ናት የሚለው አነጋገር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው መሆኑን ስለሚገልጽ ነው ። በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሱት ውስጥ ጌታችን የተዋሐደው ሥጋ ከእመቤታችን መሆኑን አንዱን ለምሳሌ ያህል አንስተን መመልከት እንችላለን። ቅዱስ ጴጥሮስ የተናገረውን ማስተዋል ለዚህ መልስ ይሰጣል
“ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና። ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፥ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና።ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፥ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፥ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም።የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን ትሞላብኛለህ።ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው።ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደ ማለለት ስለ አወቀ፥ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ።ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን” ሐዋ 2፡25—32.
በዚህ ቃል ላይ እንደተነገረው ቅዱስ ዳዊት ሥጋዬ ብሎ የሚጠራው በእርግጥ የማንን ሥጋ ነው ? ብለን ብንጠይቅ ክርስቶስ የተዋሐደውን ሥጋ መሆኑን ምንባቡ ይናገራል ። ዳዊት ሥጋዬ ብሎ የተናገረው በእርግጥም የእርሱ ሥጋ ነው ነገር ግን ሥጋዬ አይበሰብስም ብሎ ሲናገር ደግሞ ምሥጢራዊ ትርጉም እንዳለው ያመለክታል ፤ ይህ ሊሆን የሚችለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ሲነሳ ብቻ ነውና ። ወንጌላዊ ቅዱስ ማቴዎስ እና ቅዱስ ሉቃስ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት አቆጣጠር ብለው ያስቀመጡት ጌታችን ከእመቤታችን ቅድሰት ድንግል ማርያም የተዋሐደውን ሥጋ መሠረት አድርገው ነውና፤ ይህ ባይሆን ኖሮ የትውልድ ሐረግ ለመቁጠር ባልተነሱ ነበር ። ስለዚህ እኛ ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ ወላዲተ አምላክ ብለን እናታችንን እንጠራታለን በዚህም የተዋሕዶን ምሥጢር እንመሰክራለን።
2ኛ. ዘላለማዊ ድንግል መሆኗን
እመቤታችን ድንግል ማርያም ክብሯ ከሚገለጽበት መንገድ አንዱ ዘላለማዊ ድንግልናዋን በመናገር ነው ። ድንግል ማርያም በሀሳብም በሥጋም ድንግል ናት ። የሀሳብ ድንግልና ማለት በህሊናዋ ከአንድ ሀሳብ በቀር መንታነት ያለው ሌላ ሀሳብ ፈጽሞ አለመኖሩን ለመግለጽ ነው። ከሰው ወገን የህሊና ድንግልና ያለው የለም ስለዚህ ድንግል ማርያም መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እንደተናገረው ከሴቶች ሁሉ ተለይታ የተባረከች ናት የምንለው ይህንኑ የህሊና ድንግልና ለመግለጽ ነው። እመቤታችንን ልጅ ትወልጃለሽ ብሎ ቅዱስ ገብርኤል ሲያበስራት “ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል” ብላ መናገሯ የህሊና/የሀሳብ ድንግልናዋን የሚገልጽ ነው። የሥጋ ድንግልናዋም ቢሆን ከሴቶች ሁሉ የተለየ ነው ይህንንም የድንግልናዋን ክብር ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሲገልጹ ከመፅነሷ በፊት፤ በፀነሰች ጊዜ ፤ ከፀነሰች በኋላ፤ ከመውለዷ በፊት ፤ በወለደች ጊዜ ፤ ከወለደች በኋላ ድንግል ናት በማለት በስድስት ጊዜ /ሁኔታ / ከፍለው ይናገራሉ። ይህም ሰዎች የድንግልናዋን ክብር እና ታላቅነት በመረዳት ድንግል ማርያም እንዲያከብሩና በረከትን እንዲያገኙ ነው።
ድንግል ማርያም ጌታችንን የወለደችው ማኀተመ ድንግልናዋ ሳይፈርስ ነው ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት ይህንኑ በሚያረጋግጥ መልኩ ገልጸውታል።የእመቤታችንን ዘላለማዊ ድንግልና ነብያት አስቀድመው የተናገሩ ሲሆን በተለይም ነብዩ ሕዝቅኤል እመቤታችን ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድን በማኀፀንዋ እንደምትሸከም ፤ ለመለኮት ማደሪያ እንደምትሆን እውነተኛ እና ዘላለማዊ ቤተመቅደስ በማለት ተናግሯል ። “ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር።እግዚአብሔርም፦ ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥ ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል።” ት. ሕዝ 44፡1-2 በዚህ ቦታ እንደተነገረው በተዘጋው መቅደስ የገባው የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንደሆነና ሌላም ሰው እንደማይገባበት ገልጿል። የእመቤታችንን ዘላለማዊ ድንግልና የሚጠራጠሩና በእምነት እኛን የማይመስሉ ሰዎችና መናፍቃን ቅዱስ ዮሴፍ ለእመቤታችን የተመረጠበትን ምክንያት ባለመረዳትና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወንድሞቹ ተብሎ የተቀመጠውን ቃል መነሻ በማድረግ ( ማቴ 13፡55) ሌላ ትርጉም ለመስጠት የሚነሱ እምነት የጎደላቸው ሰዎች አሉ። ቅዱስ ዮሴፍ ለእመቤታችን የተመረጠው እንዲጠብቃትና እንዲረዳት ስለነበር የተመረጠበትን ኃላፊነት በሚገባ ፈጽሟል። ይህም የእመቤታችን ረዳትና ጠባቂ መሆን ቅድስና እና የልቦና ንጽህና የሚጠይቅ ኃላፊነት ስለነበር ነው ፤ ምክንያቱም ድንግል ማርያም የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ግብር በመሆኑ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል ያለ አባት ከእመቤታችን መወለዱን ለመቀበል እግዚአብሔርን የሚፈራና በሃይማኖት መኖርን ይጠይቅ ስለነበር ነው ።ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ እንደገለጸው ፤ እመቤታችን መፅነሷን ሲረዳ እንዴት እንደፀነሰች ለማወቅ ከህሊናው በላይ ስለሆነበት የመሰለውን ነገር በጥርጣሬ ከመናገር ይልቅ እግዚአብሔር እንዲገልጽለት በመጸለይ በስውር ሊተዋት አሰበ ። “ የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች።እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ።እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ፦ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ።ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።በነቢይ ከጌታ ዘንድ።እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው።” ማቴ 1፡19—25 እዚህ ላይ እጮኛ ማለት ጠባቂ ማለት እንጂ ከጋብቻ ጋር የተገናኘ ትርጉም የለውም ።
3ኛ. የአዳም የውርስ ኀጢአት ያልደረሰባት መሆኑን (ጥንተ አብሶ የሌለባት መሆኑን)
እመቤታችን ድንግል ማርያም በአዳምና በዘሩ የነበረው የውርስ ኀጢአት ያልደረሰባት ናት። አዳም በፈጸመው ስህተት የእርሱ ልጆች በሙሉ መከራ በበዛበት በዚህ ዓለም ለመኖር ተገደዋል። የነበረው የውርስ ኀጢአት ሸክም ከባድ ስለነበር የሰው ልጆች ሕይወት በድቅድቅ ጨለማ የመኖር ያህል ነበር ። ለዚህም ነው ጌታችን ሲወለድ በድቅድቅ ጨለማ የሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ የተባለው ፡ የነበረውን ሕይወት ከባድነት ለመግለጽ ነው ( ኢሳ 9፡2 )። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን የተወለደው ፡ በመስቀል ላይ የተሰቀለው ይህንን የእዳ ደብዳቤ ሊቀድልንና ዘላለማዊ ክብር የምናገኝበትን ሕይወት ሊሰጠን ነው ። የጌታችን መምጣት አዳምንና ዘሩን ከዚህ የውርስ ኀጢአት ነጻ የሚያደርግ ስለሆነ የዓለም መድኃኒት ተብሏል።መጥምቁ ዮሐንስም ሲመሰክር የዓለሙን ሁሉ ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ያለው ከዚህ በመነሳት ነው (ዮሐ 1፡29 )። ይህ የተነገረው የውርስ ኀጢአት ግን በእመቤታችን አልነበረም ፤አልደረሰምም ። አንዳንድ ሰዎች ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም የሚለውን ቃል በመዘንጋት ድንግል ማርያም የአዳም የውርስ ኀጢአት አለባት ለማለት ሲሞክሩ እንሰማቸዋለን ። ይህ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የማትቀበለው መጻሕፍትን ያላገናዘበ በጥርጣሬ ማእበል ከተጎዳ ህሊና (ልቦና) የሚወጣ ደካማ አስተሳሰብ ነው። በዚህ ቦታ ብዙ ዝርዝር ትንታኔ ለመስጠት ባንችልም ለምስክርነት ያህል ግን እመቤታችን ጥንተ አብሶ ( የውርስ ኀጢአት) እንደሌለባት ሁለት ቦታዎችን በቀላሉ እንመለከታለን ።
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሲያበስራት የተናገረው ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ብሎ ነው የተናገራት ( ሉቃ 1፡28) መቼም የውርስ ኀጢአት ነበረባት ከተባለች ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ልትባል አትችልም ምክንያቱም የውርስ ኀጢአት ካለ ከጸጋ በታች ያደርጋልና ። አንዳንዶች እንደሚናገሩት ደግሞ ወልድ በማህፀኗ ሲያድር አነጻት ቀደሳት እንዳንል የመልአኩ ምስክርነት ጌታን ከመፅነሷ በፊት ነው ። ቅዱስ ገብርኤል ይህንን ለእመቤታችን የነገራት ሦስት ጊዜ በተለያየ ቦታና ወቅት ነው ።እመቤታችን በመልአኩ የቀረበላትን ቃል ተቀብላ እንደቃልህ ይሁንልኝ ከማለቷ በፊት ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ማለቱ ከውርስ ኀጢአት ነጻ እንደነበረች የተነገረ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ ምስክርነት ነው ። በተጨማሪም ነብዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ የተናገረው ምስክርነት ይህንን እውነታ የበለጠ የሚያረጋግጥ ነው። “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ገሞራም በመሰልነ ነበር” ኢሳ 1፡9 እዚህ ላይ ዘርን ባያስቀርልን የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመሆኗ ከሌሎች የአዳም ዘር ሁሉ የሚለያት ነገር እንዳለ ፤ በእነርሱ የደረሰ በዚህች ዘር ላይ ግን ያልደረሰ ነገር መኖሩን የሚያስረዳ ነው ። ይህም የአዳምን ዘርን በሙሉ የሚመለከተው ኀጢአት ጌታችን በሞቱ ባያጠፋልን ኖሮ ለዘላለማዊ ቅጣት ያበቃን ነበር። ከዚህ በመነሳት ነው እመቤታችን ከአዳም ዘር የተገኘች ብትሆንም አስቀድማ በአምላክ ህሊና ታስባ ትኖር ነበር በማለት ሊቃውንት የሚገልጹት።
4ኛ. የእግዚአብሔር የአካሉ ማደሪያ መሆኗን
የእመቤታችን ክብር ከፍጡራን ሁሉ በላይ ከፈጣሪ በታች ተብሎ እንዲነገር ምክንያት ከሆኑት አንዱ የእግዚአብሔር አካሉ ማደሪያ መሆኗ ነው። እግዚአብሔር በሰዎች ላይና በቅዱሳን መላእክት የሚያድረው በጸጋው ነው በእመቤታችን በቅድሰት ድንግል ማርያም ላይ ግን ጸጋ የተሞላች ብቻ ሳትሆን የእግዚአብሔር ወልድ የአካሉ ማደሪያም ሆናለች ። ሰማይና ምድር የማይችሉት አምላክ በድንግል ማርያም ማኀፀን መቀመጡ የሚደንቅ ምሥጢር ነው ። አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ እጅግ ተደንቆ የገለጸው ይህንን ምሥጢር ነው። “ ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ ሳይወሰን ፀነስሽው በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨመር በማኀፀንሽ ተወሰነ መመጠንና መመርመር የሌለበት እሳተ መለኮት በሆድሽ አደረ” በማለት እመቤታችን የወልድ ማደሪያ መሆኗን መስክሯል። ስለዚህ ነው ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ የምንላት አምላክ በማኀፀንዋ 9 ወር ከ 5 ቀን ተቀምጦ በድንግልና ወልዳዋለችና ።
5ኛ. ትንሣኤዋ እንደ ልጇ ትንሣኤ መሆኑን
የቤተክርስቲያን መሠረታዊ ትምህርት እንደሚያስረዳው ሰዎች ሁሉ በመጨረሻው ቀን ለፍርድ እንደሚነሱ እናውቃለን ፤ሰው ሞቶ እንደማይቀር ተስፋ ለመስጠትም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ እና በኩር ሆኖ አረጋግጦልናል። በዚህም መሠረት ሰዎች ሁሉ የሚነሱት በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ ዘጉባኤ መሆኑ የተረጋገጠ ነው ። በዚህ የፍርድ ቀን መንግሥተ ሰማያት ትከፈታለች መልካም ያደረጉና በሃይማኖት የጸኑ ሰዎች እርሷን ይወርሳሉ ። እስከዚህ ቀን ድረስ ግን ከሰው ወገን መንግሥተ ሰማያት የሚወርስ የለም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በቀር ። ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን በጻፈው መልእክቱ እንደገለጸው የሃይማኖት ገድል የፈጸሙ ቅዱሳንን ከገለጸ በኋላ ያለ እኛ ፍጹማን አይሆኑም በማለት የተናገረው መንግሥተ ሰማያት ተከፍታ ቅዱሳን ሁሉ እንዲወርሳት በምድር ያሉት ሁሉ ለፍርድ መቅረባቸው የሚጠበቅ መሆኑን ለመግለጽ ነው ። “እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና” ዕብ 11፡39-40. ይህ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ግን እመቤታችንን የሚመለከት አይደለም ምክንያቱም እመቤታችን ከውርስ ኀጢአት ነጻ የሆነችና ጸጋን የተሞላች በኋላም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደች ስለሆነች የፍርድ ቀን እርሷን አይመለከትም ፡ ለጥያቄ አትቀርብምና ። ለዚህ ነው የእመቤታችን ትንሣኤ ከሰው ልጆች ሁሉ ትንሣኤ የተለየ ነው የምንለው ድንግል ማርያም 64 ዓመት ከኖረች በኋላ ሞተ እረፍትን አልፋ እንደ ልጇ ተነስታለች። አሁን ደንግል ማርያም በታላቅ ክብር በመንግሥተ ሰማያት ትገኛለች። ቅዱስ ዳዊት ይህ የድንግል ማርያም ትንሣኤ አስቀድሞ እንደሚፈጸም አውቆ ትንቢት ተናገሯል። “ አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦት” መዝ 131፡8 ። እዚህ ላይ የመቅደስህ ታቦት ያለው እመቤታችን ድንግል ማርያምን ነው ፤ ታቦት ማለት የእግዚአብሔር ማደሪያ ስለሆነ እግዚአብሔር በአካሉ ያደረባት አማናዊ ታቦት እመቤታችን ናትና ። ቅዱስ ዳዊት የእመቤታችን የቅድሰት ድንግል ማርያም ሞትና ትንሣኤ ተገልጦለት እንዳመሰገናት “ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች ” መዝ 45፡9 ያለው በእግዚአብሔር መንግሥት ዘላለማዊ ንግሥት ድንግል ማርያም መሆናን ለመግለጽ ነው ።
6ኛ. በሰውም በመላእክትም የምትመሰገን መሆኗን
እግዚአብሔርን የሚያምኑ ፈቃዱ ምን እንደሆነ የሚያስተውሉ ሁሉ ድንግል ማርያምን ያመሰግኗታል።አንዳንድ ይህንን ያልተረዱ ሰዎች ለምን ድንግል ማርያም ትመሰገናለች ሲሉ ይደመጣሉ።እንኳን ደካማ የሆነው የሰው ልጆች ይቅርና በሰማይ ያሉ ቅዱሳን መላእክትም ያመሰግኗታል። ድንግል ማርያምን የምናመሰግናት የተሰጣትን ክብር በመግለጽ፤ለሰው ልጆች ሁሉ መዳን ምክንያት መሆኗን በመግለጽ እና አሁንም አማላጅ መሆኗን በመመስከር ነው ። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነገደ መላእክትን በመወከል ኤልሳቤጥ ደግሞ የሰው ልጆችን በመወከል ጸጋን ተሞላሽ በማለት ለእመቤታችን ምስጋና አቅርበዋል።እመቤታችንም በሰጠችው የሃይማኖት ምስክርነት “ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” ሉቃ 1፡49 ብላለች። ይህን የተናገረችው ለእርሷ ምስጋና ማቅረብ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ሰዎች ተረድተው ፡ በዚሁ ፈቃድ መሠረት እንዲመሩ ነው ። ድንግል ማርያም እንድትመሰገን እግዚአብሔር ከፈቀደ ሰዎቸ በተቃዉሞ ቢነሱ በመጨረሻው ቀን ተጠያቂ ያደርጋቸዋል ምክንያቱም “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።በዚያ ቀን ብዙዎች። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።የዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።” ማቴ 7 ፡21—23. ብሎ ጌታችን ተናግሯል ። እኛ ግን እንደተማርነው ድንግል ማርያምን ዘወትር እናመሰግናታለን ፤ ይህንን በማድረጋችን የበለጠ ወደ እግዚአብሔር እንቀርባለን እንጂ አንርቅም።
7ኛ. የሰው ልጆች ሁሉ አማላጅ መሆኗን
ድንግል ማርያም የዓለሙ ሁሉ መዳን ምክንያት ስለሆነች ለአማላጅነቷ ትልቅ ቦታ ይሰጣል። አማላጅነት በእግዚአብሔር ዘንድ ለተከበሩ በፈቃዱ ለሚሄዱ የሚሰጥ የክብራቸው መገለጫ የሆነ የቅድስና ደረጃ ነው ። ድንግል ማርያም አማላጃችን እንድትሆን ከሁሉ በላይ የፈቀደ እግዚአብሔር ነው ። አዳምና ልጆቹ እንደ ሰዶምና ገሞራ ከመጥፋት ምክንያተ ድህነት የሆነች እመቤታችን ናት ( ኢሳ 1፡9)። ቅዱስ ዳዊት ሲናገር ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች ያለው እመቤታችንን ሲሆን በቀኝህ ማለቱ በፈቃዱ እንዳለች የሚገልጽ ሲሆን ትቆማለች ማለቱ ደግሞ ለሰው ልጆች ምልጃ እንደምታቀርብና እግዚአብሔርም እንደሚቀበላት የሚገልጽ ነው ። እመቤታችን ድንግል ማርያም በቃና ሰርግ ቤት ተገኝታ የወይን ጠጅ የላቸውም ብላ እንዳማለደች( ዮሐ 2፡1—11) በእኛም ሕይወት የጎደለብንን ነገር እግዚአብሔር እንዲሞላልን ዘወትር ትጠይቃለች። እውነቱ ይህ ከሆነ የእመቤታችንን ክብር መቀበል ያልቻለ ሰው ፤ አማላጅነቷን የናቀ ሰው ፤ የእግዚአብሔርን ምሕረት እንዴት ሊያገኝ ይችላል ? ለቅዱሳን አባቶቻችን ምሥጢሩን ጥበቡን የገለጸ እግዚአብሔር ለእኛም የእመቤታችንን ክብር እንዲገልጽልን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
(የደብሩ ሰንበት ት/ቤት የአንደኛ ዓመት ምሥረታ በዓሉን አስመልክቶ ካዘጋጀው መጽሔት የተወሰደ)