ምዕራፍ ዐሥራ ስድስት
በ9ኙ የመንፈስ ቅዱስ ተቃዋሚዎችና መናፍቃን መልሶቻቸው ላይ የተሰጠ ግልጽ መልስ
1. ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲጽፍ፣ ሲናገር፣ ሲያስተምር ስለ መንፈስ ቅዱስ በምናስብበት፣ በምንናገርበት፣ በምንጽፍበት፣ በምናስተምርበት ጊዜ ሁሉ ጥንቃቄ እንድናደርግ ትምህርትና ምክር ይሰጣል፡፡ ቀደም ሲልም በቤተ ክርስቲያን ከተሰበሰቡት፣ ቤተ ክርስቲያን ከምታውቃቸው ታላላቅ ጉባኤያት አንዱ በ380 ዓመተ ምሕረት አካባቢ የሆነው በቁስጥንጥንያ የተሰበሰበውና መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ያንሳል የሚል የኑፋቄ የክሕደት ትምህርት በቤተ ክርስቲያን የዘራውን የቁስጥንጥንያውን ሊቀ ጳጳሳት መቅዶንዮስን ለማውገዝ የተሰበሰበው የቁስጥንጥንያ ጉባኤ ነበር፡፡ መናፍቁን አውግዞ፣ ከሹመቱ ሽሮ፣ “ሕያው ማኅየዊ ጌታ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን” የሚል የትምህርተ ሃይማኖት ውሳኔ ሰጥቶ ተነሥቶአል፡፡
2. ትምህርቱም ቀደም ብሎ በ328 ዓመተ ምሕረት በኒቅያ ጉባኤ ከተወሰነው፤ ወልድ ዋሕድ፤ ከሚለው ትምህርት ጋራ በቤተ ክርስቲያን ጸንቶ እስከ ዛሬ አለ፡፡ በኒቅያ ጉባኤ፤ ወልደ አብ ዋሕድ፤ አንድ የአብ ልጅ፤ ተብሎ ወልድ ከአብ መወለዱ እንደ ተገለጠ፤ በቁስጥንጥንያ ጉባኤም ዘሠረጸ እምአብ ከአብ የሠረጸ ተብሎ ስለ መንፈስ ቅዱስ ተነግሯል፡፡ ይህ ውሳኔ “መንፈሰ ጽድቅ ዘይወፅእ እምኀበ አብ ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ፤” ባለው በጌታ ቃል ላይ የተመሠረተ የጸና እንጂ ልብ ወለድ አነጋገር አይደለም፡፡ (ዮሐ. 15÷26)፡፡ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚለው የአብ ምስክርነት ወልድ ከአብ መወለዱን እንደሚያስረዳ (ማቴ. 17÷5)፡፡ “ከአብ የወጣ የእውነት መንፈስ፤” የሚለው የጌታ ምስክርነትም መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ መሥረጹን ለቤተ ክርስቲያን ሲያስረዳ ሲመሰክር ሲያስተምር የሚኖር ቀዋሚ ምስክር ነው፡፡ ማንም ሊቃወመው ሊያስተባብለው አይችልም፡፡
3. ይሁን እንጂ የሃይማኖት ትምህርት ውሳኔዎች በቤተ ክርስቲያን የጸኑ ቢሆኑም፣ ኑፋቄዎችን ያመነጩት መናፍቃንም የመጀመሪያዎቹ ያለፉ፣ የጠፉ ቢሆኑም የመናፍቃኑ አስተማሪ ሰይጣን የማይሞት ስለሆነ፤ እርሱ ያላማው የእነ አርዮስ፣ የእነ መቅዶንዮስ፣ የእነ ንስጥሮስ፣ የእነ ልዮን፣ የእነ ሉተር፣ የእነ ባሃኡላህ የሌሎችም መናፍቃን የኑፋቄ፣ የክሕደት ትምህርት እነርሱን መሰል በሆኑ ከአባታቸው ከሰይጣን በሚፈለፈሉት በልጆቻቸው እየተላለፈ እስከ አሁን አለ እስከ አሁን ደርሷል፡፡
በነገረ መንፈስ ቅዱስ ላይ የተነሱ መናፍቃን በነገረ ክርስቶስ ላይ እንደተነሱ መናፍቃን ቁጥራቸው ባይበዛም እውነተኛውን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በማጣመም ምእመናንን ግራ በማጋባትና ቤተ ክርስቲያንን በማናወጥ ያደረሱት ጥፋት በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ የነገረ ክርስቶስ አስተምህሮ እየዳበረና እየሰፋ ሄዶ ትልቅ የቤተ ክርስቲያን ዶግማ ለመሆን የበቃው በየጊዜው የተነሱ መናፍቃን ምላሽ ለመስጠት በተደረጉ ጥረት እንደሆነ ሁሉ ነገረ መንፈስ ቅዱስ (Pneumatology) እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰውም በዚሁ ሁኔታ እንደነበር የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል፡፡ ቀጥለን መናፍቃኑ ይዘው የተነሱትንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሊቃውንቷ የወሰደችውን እርምጃ የሰጠችውን ምላሽ አንድ በአንድ እንመለከታለን፡፡
ሀ. ሲሞን መሠርይ (Simon Magus)
ይህ ሰው ሳምራዊ ሲሆነ የሰማርያ ሰዎችን በጥንቆላው እያሳተ ብዙ ሀብት ሰብስቦ ይኖር የነበረ አደገኛ መሠርይ ነበር፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ በመጀመሪያ አስተምሯቸውና አጥምቋቸው የእግዚአብሔርን ማዳን እንደተቀበሉ ሐዋርያት ወርደው ሀብተ ልጅነት እንዲያሳድሩባቸው ነገራቸው በዚሁ መሠረት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስና ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ወርደው እጃቸውን በመጫን የመንፈስ ቅዱስን ሀብታት ሲያሳድሩባቸው አይቶ ሲሞን ይህን ሥልጣን በጥንቆላ በሰበሰበው ብር ለመግዛት ወደ ሐዋርያት ቀረብ አለ፡፡ እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔም ደግሞ ይህን ስልጣን ስጡኝ አለ፡፡ የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ መመኘት መንፈስ ቅዱስን እንደ ሥጋዊ መቁጠር ስለሆነ ትልቅ ስድብ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስን የሰደበ ኃጢአቱ እንደማይሰረይለት ሐዋርያት በሚገባ ተምረው ነበርና፡- የእግዚአብሔርን ስጦታ ገንዘብ እንድታገኝ አስበሀልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከእዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም በማለት አውግዘው ለዩት፡፡ (ማቴ. 12÷11-32፣ ዮሐዋ. 8÷18-22)፡፡ ሰማዕቱ ጁስቲን “ሲሞን መሠርይ በሚያታልል ማጂክ እየተጠቀመ በሰማርያ እንደ እግዚአብሔር ሲመለክ እንደነበር” በታሪክ ድርሳኑ መዝግቦታል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት ምስጢራትን በገንዘብ ሸጦ የተገኘ ካህን ቢኖር ያለ ምንም ማስጠንቀቂያና ይቅርታ ሥልጣኑ እንዲነሳ (እንዲያዝ) ከቤተ ክርስቲያን ከማኅበረ ካህናት እንዲለይ በቀኖና ደንግጋለች፡፡ አንድ ጳጳስ ለማይገባው ሥልጣነ ክህነት በገንዘብ ሰጥቶ ቢገኝ በቀጥታ ከሥልጣኑ እንዲሻር ሐዋርያት በቀኖናቸው ደንግገዋል፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ (ጸጋ) መስጠት የሚችለው ራሱ ባለቤቱ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ሰው መሣሪያ አስፈጻሚ ነው እንጂ የሀብቱ ባለቤት አይደለምና፡፡ እዚህ ላይ አንባቢያን ልናስተውለው የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ምሥጢረ ተክሊል፣ ቀንዲል ወዘተ ስትፈጽም ገንዘብ ልታስከፍል ትችላለች፡፡ ይህ ክፍያ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ መሸጥ ሳይሆን አገልግሎቱን ለማስፈጸሚያ የሚውል እንደሆነ ልንገነዘብ ያስፈልጋል፡፡
ለ. ቫለንቲኑ
ይህ ሰው ክርስትናን ከተቀበሉ ግብጻውያን አይሁድ መካከል ነው፡፡ በአሌክሳንድርያ የፕላቶ ፍልስፍና ትምህርት ቤት ገብቶ ብዙ ፍልስፍናን ከተማረ በኋላ ወደ ግኖስቲክ ተለወጠ፡፡ ይኸንኑ ትምህርት በ138 እ.ኤ.አ. በሮም ከተማ እየተዘዋወረ ማስተማር ጀመረ፡፡ ዓለምን ያስገኘ እግዚአብሔር በአካሉ አንድ ነው፡፡ እርሱም በብርሃን ሙላት (fullness of light) ይኖራል፡፡ ከእግዚአብሔር በክፍላት (through emanation) የተገኙ ብዙ ፍጡራን በዚህ የብርሃን ሙላት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ፍጥረት እግዚአብሔር በተሰጥሞ ብርሃን (Pleroma) ውስጥ እንደሚኖር ጠቋሚዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ፍጥረታትም አዮንስ (የመለኮት ፍንጣቂዎች) ይባላሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው በማለት የክህደት ትምህርቱን በመለዋ የሮም ከተማ አሰራጨ፡፡ ይህ መናፍቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ በፍጹም አይጠቅስም፡፡ ነገር ግን አንድ ገጽ የሚያመልኩ አይሁዳውያንን ለማሳመን አልተቸገረም ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ሮማውያን መንፈስ ቅዱስን አካላዊ መለኮት ብለው ለመቀበል ይቸገሩ ነበር፡፡ ቅዱስ አቡሊድስ ዘሮሜ “አብኒ በአካሉ ወበገጹ ወበ መልክኡ ፍጹም ውእቱ ወልድኒ በአካሉ ወበገጹ ወበመልክኡ ፍጹም ውእቱ መንፈስ ቅዱስኒ በአካሉ ወበገጹ ወበመልክኡ ፍጹም ውእቱ፡፡” እያለ በማስተማር የቫለንቲኑስን የኑፋቄ ትምህርት አስወግዷል፡፡ ትርጉሙም ለአብ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው ለወልድም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው ማለት ነው፡፡
ሐ. ሞንታኒዝም
ሞንታኒዝም በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በትንሿ ኢስያ በምትገኘው በአፍርንጊያ ብቅ ያለ የኑፋቄ ትምህርት ነው፡፡ የዚህ ኑፋቄ ትምህርት መስራች ሞንታኑስ ይባላል፡፡ ይህ ሰው ራሱን ነቢይ አድርጐ ይቆጥራል፡፡ ሲያስተምር በሚያደርገው የመድረክ ላይ የሰውነት እንቅስቃሴ ብዙዎቹን ለመማረክ ችሏል፡፡ በሚያደርገው የመድረክ ላይ ተውኔት እንግዳ ትምህርቱና ትርጉም አልባ ንግግሩ እንዳይናቅበት ለማድረግ ችሏል፡፡ አስተምሮውም፡- በታሪክ ውስጥ ሦስት መለኮታዊ መገለጦች አሉ፡፡ የመጀመሪያው በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበረው የእግዚአብሔር (ያሕዌ) መገለጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሐዲስ ኪዳን የኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ነው፡፡ ሦስተኛውን የመጨረሻው መገለጥ በእኔ በምንታኑስ አድሮ የተገለጠው መንፈስ ቅዱስ ነው የሚል ነበር፡፡ ለመንፈስ ቅዱስ መገለጥ ራሱን መሣሪያ አድርጐ ይቆጥራል፡፡ አቂላና ፕሪስካ የሚባሉ ሁለት ሴቶች የዚህ ኑፋቄ ትምህርት አቀንቃኞች ነበሩ፡፡ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳው ሰባልዮስ የኑፋቄ ትምህርቱ መነሻው የሞንታኒዝም አይዶሎጂ ነበር፡፡ ሰባልዮስ በሮም እግዚአብሔር አንድ አካል አንድ ገጽ ነው የሚል ትምህርት ተማረ፡፡ ይህን ትምርትም ያገኘው እግዚአብሔር በተለያዩ ዘመናት ራሱን በመቀያየር ዓለምን አስተዳደረ እንጂ ገጹ አንድ ነው፡፡ እያሉ ከሚያስተምሩ ሞዳሊስቲክ ሞናርኪያኒዝም ነበር፡፡ ይህንኑ ትምህርት አስፋፍቶ፡- አንዱ አካል እግዚአብሔር በዘመነ ብሉይ አብ ተብሎ ዓለምን ሲመግብ ኖረ፡፡ በዘመነ ሐዲስ ሥጋን ለብሶ ሰው በመሆን ተገለጠ በዚሁ ዘመን ይሠራ የነበረው ወልድ እየተባለ ነው፡፡ ወደ ዘለዓለም አኗኗሩ በተመለሰ በሃምሳኛው ቀን በአምሳለ እሳትና በአውሎ ነፋስ ወርዶ ለሐዋርያት ምስጢር የሚያስተረጉም ቋንቋ የሚያናግር ሀብታት በመስጠቱ መንፈስ ቅዱስ ተባለ በማለት ነገረ ቅድስት ሥላሴን (Doctrine of Holy Trinity) የሚያፋልስ ትምህርት መዝራት ጀመረ፡፡
የሰባልዮስ ከሞንታኑስ የሚለየው ሞንታኑስ የመንፈስ ቅዱስ ምግብና በእኔ ላይ አድሮ ነው ማለቱ ሲሆን ሰባልዮስ ግን በዘመነ ቤተ ክርስቲያን የሚያስተዳድረው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተብሎ ነው ይላል፡፡ የሰባልዮስም ሆነ የምንታኑስ ኑፋቄ ትምህርት ምንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ የለውም፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚጠቅሱት መረጃም የለም፡፡ እንዲሁም ምንም ዓይነት ሎጂካዊ (አመክንዮ) መከራከሪያ አያቀርቡም፡፡ ነገር ግን ሦስቱም አካላት ቅድመ ዓለም ማዕከለ ዓለም፣ ድኅረ ዓለም በአንድነት በአንዲት ሕልውና፣ በአንዲት መንግሥት ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ሦስቱም አካላት በሁሉም ዘመን በየራሳቸው ስም እንደሚኖሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል፡፡ “ወእንዘ ታጠምቅዎሙ በሉ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ” (ማቴ. 28÷19)፡፡ ወልድ በዘመነ ብሉይ ሲሠራ እንደነበረ ከነቢያት ጸሎት እንረዳለን፡፡ ነቢያት “ፈኑ እዴከ፣ ፈኑ ብርሃነከ ወዘተ” በማለት ወልድን እጅ ቀኝ ብርሃን በማለት ይጠሩት ነበር፡፡ ምንም እንኳን ወልድ እንደዘመነ ሐዲስ ወልድ ተብሎ አይጠራ እንጂ በዚህ መልክ ይታወቅ ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር መንፈስ፣ ቅዱስ መንፈስ እንዲሁም መንፈስ እየተባለ በዘመነ ብሉይ መጠራቱን በሰፊው አስቀድመን ያየነው ስለሆነ እዚህ ላይ መድገም አያስፈልግም፡፡
ተርቱሊያን ቀደም ብሎ የሞንታኒዝም ሐሳብ አራማጅ እንደነበረ ይነገራል፡፡ በኋላ ግን ሦስቱም አካላት በቅድምና በአኗኗር ዓለምን በመመገብ አንድ ናቸው፡፡ የገጽ መቀያየር የለም በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ ነገረ ሥላሴን ቀረጸ፡፡ ትሪኒቲ (Trinity) የሚለው ስያሜም የተወሰደው ከእርሱ ስም እንደሆነም ይታመናል፡፡ ትሪኒቲ ቀሹ ግሪክ ሲሆን ትርጒሙም ሥላሴ ማለት ነው፡፡ ተርቱሊያን ነገረ ቅድስት ሥላሴን (The Doctrine of Holy Trinity) ከመቀመሩም ባሻገር የቤተ ክርስቲያን ጠበቃ (Apologist) እንደነበረ ይታወቃል፡፡ የሞንታኑስ ኑፋቄ ዛሬም ራሳቸውን ጴስጠቆንጤ እያሉ በሚጠሩ ሴክቶች ይንጸባረቃል፡፡ ዘመናዊው ጴስጠቆንጤናዊ (Modern Pentecostalism) እንቅስቃሴ የመንፈስ ቅዱስን አካላዊ አምላክነት ከመካድም ባሻገር ኢየሱስ ክርስቶስን ከአምላካዊ ክብር ዝቅ የሚያደርግ ትምህርት በማሠራጨት ነገረ ድኅነት ዋጋ ቢስ እንዳደረጉ ይገኛሉ፡፡
መ. አርዮስና መንፈቀ አርዮስ (Arius and Semi – Arianism)
ብዙ ጊዜ አርዮስ ሲነሳ ትዝ የሚለን “ወልድ ፍጡር ነው” በማለት የተናገራት የኑፋቄ ትምህርት ነው፡፡ አርዮስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በታሪክ ውስጥ ከገጠማት አደገኛ መናፍቅ የመጀመሪያው ነው ማለት ይቻላል፡፡ በፕላቶም ሆነ በአርስቶትል ፍልስፍና እንዲሁም በአርጌንስ አልጐሪክ የትርጉም ስልት የበሰለ በመሆኑ ይዞ የተነሣውን የኑፋቄ ትምህርት ለማፈራረስ እጅግ ከባድ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በፍልስፍና እየታገዘ በሚፈልገው መንገድ እየተረጐመ ሊቃውንቱን ሳይቀር ግራ ያጋባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ ሊቃውንት አባቶች በአንድ መለኮት ሦስት አካላት እንዳሉ ለማስረዳት ፀሐይን ምሳሌ ተጠቅመዋል ከአርዮስ በኋላ የተነሣው አባ ሕርያቆስም ከቀደምት አበው በመውሰድ “አብ ፀሐይ ወልድ ፀሐይ መንፈስ ቅዱስ ፀሐይ አሐዱ ውእቱ ፀሐየ ጽድቅ ዘላዕለ ኲሉ” ብሏል፡፡ አባቶች ሊቃውንት አብን በክበቡ ወልድን በብርሃኑ መንፈስ ቅዱስን በሙቀቱ መስለዋል፡፡ አርዮስ በዚህ ምሳሌና ትርጉም ይስማማል፡፡ ነገር ግን አብ በክበቡ በመመሰሉ ክበቡ በሙቀትም ሆነ በብርሃን ከእርሱ ወጥተው ወደ ሕዋ ውስጥ ከሚረጩ ሙቀትና ብርሃን ይበልጣል፡፡ ሙቀትም ሆነ ብርሃን ከክበቡ እየራቀ ሲሄድ ሙቀቱም ብርሃኑም እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ በመገኘታቸው በባሕርየ መለኮት ከአብ ያንሳሉ፡፡ ከፀሐይ ክበብ እየራቅን ስንሄድ ሙቀትና ብርሃን እየቀነሰ እንደሚሄድ ሁሉ የመለኮት ይዘት እየቀነሰ በመሄዱ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ መለኮት ከአብ ቢያንስም ከአብ ጋር ይመሳሰላል በማለት መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ሳይሆን የሊቃውንቱንም ትምህርት የሚሞግት አደገኛ መናፍቅ ሆነ፡፡ በርቱዕ አንደበቱ በፍልስፍና እውቀቱ የተማረኩ ብዙ ሴቶችና ወጣቶች ትምህርቱን አሜን ብለው ተቀበሉት፡፡ አንዳንዶቹም ከእርሱ የቀሰሙትን ላልሰሙ የሚያደርሱ ሆኑ፡፡ ትምህርቱም በመላዋ እስክንድርያ እና በትውልድ ሀገሩ በሊቢያ ናኘ፡፡
ችግሩ እጅግ ያሳሰበው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ እለ እስክንድሮስ ወደ ንጉሡ ወደ ቆስጠንጢኖስ አቤት አለ፡፡ ንጉሡም ችግሩ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ተገንዝቦ በትንሿ እስያ በምትገኘው በኒቂያ ከተማ ጉባኤ እንዲደረግ ጠራ፡፡ በዚሁ መሠረት ጉባኤው ተደረገ፡፡ በተከታታይ ቀናት አርዮስ በሰላ አንደበቱ በፍልስፍና እውቀቱ ሊቃውንቱን አፋቸውን አስያዘ፡፡ እግዚአብሔር አብ ወልድን ወልዶ መንፈስ ቅዱስን አስርጾ ዓለማትን እንዲፈጥሩ አድርጓል፡፡ እግዚአብሔር አብ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ በባሕርየ መለኮት ይበልጣል አስገኝ በመሆኑም ይቀድማቸዋል አለ፡፡ ዳግመኛም አብ እነርሱንና ሰማይና ምድርን አስገኘ ሌሎቹን በሰማይና በምድር ላይ ያሉትን ፍጥረት ወልድና መንፈስ ቅዱስ አስገኙ፡፡ ዝቅተኛ ፍጡራንን ማስገኘታቸው በባሕርየ መለኮት ለማነሳቸው ማስረጃ ነው በማለት ሐሳቡን አጠናከረ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ቅዱስ አትናቴዎስ የጉባኤው ተካፋይ አልነበረም፡፡ የሄደውም የሊቀ ጳጳሱን የቅዱስ እለ እስክንድሮስን መቋሚያ ለመያዝ ነው፡፡ በማዕረጉም ገና ዲያቆን ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ በቅዱስ አትናቴዎስ ሞልቶበት ወደ ጉባኤው ዘሎ ገባ፡፡ ይህ ታሪክ ከቅዱስ ዳዊት ታሪክ ጋር ይመሳሰላል፡፡ እስራኤላውያን ከኢሎፍላውያን ጋር በተሰለፉ ጊዜ ቅዱስ ዳዊት ወደ ጦሩ ግንባር አልተጠራም ነበር፡፡ እርሱ የሄደው ለወንድሞቹ ስንቅ ለማቀበል ነበር፡፡
የፍልስጤማውያን የጦር አለቃ በሰውነቱ ቁመና በጦሩና በትጥቁ ጥንካሬ በመመካት በእስራኤላውያን በእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ የስድብ ነገር ሲናገርና ሲገዳደር የሰማ ቅዱስ ዳዊት በቁጣ ነደደ መንፈስ ቅዱስ ሞላበትና ሊሳለፈው ወረደ በትንሽ ጠጠርም ድል ነሳው፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ሊቃውንቱን ሲያስጨንቅ የነበረው አርዮስ በአንድ ብላቴና ዲያቆን አንደበቱ ተያዘ ምላሽም አጣ፡፡
ቅዱስ አትናቴዎስ አርዮስ ይዞት የተነሳውን ሐሳብ ከመረመረ በኋላ ለእያንዳንዱ ጥያቄና ሐሳብ መልስ ጥያቄ የማያስነሳ መልስ እንደሚከተለው ሰጠ፡፡ ፀሐይ እግዚአብሔር ከፈጠረው ፍጥረት መካከል እንደሆነ መጽሐፍ “ወገብረ እግዚአብሔር ብርሃናተ ዐበይተ ዘየዐቢ ብርሃን ከመ ይምልክ መዓልተ ወዘይንእስ ብርሃን ከመ ይምልክ ሌሊተ ምስለ ከዋክብት፤ እግዚአብሔር ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሰለጥን ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ” ይላል፡፡ (ዘፍ. 1÷16)፡፡ ትልቁ ብርሃን የተባለ ፀሐይ የእግዚአብሔር ሥልጣን ከአስገኛቸው ፍጥረታት መካከል ነው፡፡ የእግዚአብሔር ባሕርይ ደግሞ በፍጡር ባሕርይ በፍጹም አይመስልም እንዲያውም ተቃራኒዎች ናቸው፡፡ አባቶቻችን ሊቃውንት በፀሐይ መስለው ማስተማራቸው እግዚአብሔር የአካል ሦስትነት ሲኖረው በመለኮት ግን አንድ ነው ለማለት እንጂ ባሕርዩን ከፀሐይ ጋር ለማመሳሰል ወይም ባሕርየ መለኮቱን ለመመርመር አይደለም፡፡ ባሕርዩ እንደማይመረመር ነቢዩ የተናገረውን አስተውል፡፡ “እግዚአብሔር የዘለዓለም አምላክ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው አይደክምም አይታክትም ማስተዋሉም አይመረመርም፡፡” (ኢሳ. 40÷28) “ማስተዋሉም አይመረመርም፡፡” ማለቱ ባሕርዩ ማለቱ እንደሆነ አልተረዳህምን? ቅዱስ አትናቴዎስም በመቀጠልም አርዮስ ሆይ! ግሪካውያን ፀሐይን ሲያመልኩ በመኖራቸው በፈላስፎቻቸውም ላይ ይህ አመለካከት ተጽዕኖ ማሳደሩን እናውቃለን፡፡ ፀሐይ ፍጥረታት ከተገነቡባቸው ንጥረ ነገሮች (elements) መካከል ከእሳትና ነፋስ የተፈጠረች እንጂ ምንም የመለኮት ፍንጣቂ (Divine spark) የላትም፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ባሕርይ ጋር የምታገናኝበት መንገድ የለህም በማለት አንገቱን አስደፋው፡፡
እግዚአብሔር በምንም ሊመሰል እንደማይችል በመንፈስ ቅዱስ እየተነዳ የተናገረው የነቢዩ ኢሳይያስ የትንቢት ቃል በቂ ማስረጃ ነው፡፡ “እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ? …ሰማያትን እንደመጋረጃ የሚዘረጋቸው እንደ ድንኳንም ለመኖርያ የሚዘረጋቸው አለቆችንም እንዳልነበሩ፣ የምድርንም ፈራጆች እንደከንቱ ነገር የሚያደርጋቸው እርሱ ነው፡፡”፣ “በማን ትመስሉናላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ?” (ኢሳ. 40÷18-19፣ 46÷5)፡፡
አርዮስ፡- መንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር አብ ያንሳል አብ ታላላቅ ፍጥረታትን ሰማያትንና ምድርን ሲፈጥር መንፈስ ቅዱስ ሌሎቹ ተዋረድ ፍጥረታትን ፈጠረ ብሎ ነበርና ቅዱስ አትናቴዎስ እንዲህ በማለት ይህን አሳብ ከንቱ አደረገው፡- እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሰማያትን እንደፈጠረ በመንፈስ እየቃተተ ጻድቁ (ኢዮብ 26÷13)፡፡ በምድር ና በውኃ ላይ ሰፍፎ ምድርን ማበጃጀቱ የመፍጠር ሥራ አይደለምን? ዘፍ. 1÷2፡፡ ዘወትር እንደሚያድሳትና መዝሙረኛው ነቢይ የተናገረውን አታስተውልምን? “ትፌኑ መንፈሰከ ወይትፈጠሩ ወትሔድስ ገጻ ለምድር” መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም የምድርንም ፊት ታድሳለህ፡፡ መዝ. 103÷30 ሕዳሴ የመፍጠር ሥራ እንደሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው አሮጌው ነገር አልፏል እንሆ ሁሉም አዲስ ሆኗል” ብሏልና፡፡ (2ኛ ቆሮ. 5÷17)፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ፍጹም አምላክ ሁሉን ፈጣሪ እንደሆነ “ወዘእንበሌሁሰ አልቦ ዘኮነ ወኢምንትኒ” ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም (ዮሐ. 1÷3) በማለት ሐዋርያው መናገሩ ሰማያትንና ምድርን አያጠቃልልምን? የወልድ ባሕርይ ከአብ ባሕርይ ጋር አንድ (Homo ousios) እንደሆነ ምንም ምን ከአብ የባሕርይ ገንዘብ የጐደለው እንደሌለ ራሱ “ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፡፡” (ዮሐ. 16÷15) ብሎ የለምን? ዳግመኛም የወልድ ባሕርይ የአብን ይመስላል፡፡ አብና ወልድ በባሕርይ ይተካከላሉ እንጂ አንድ አይደሉም ትላለህ ነገር ግን አብና ወልድ በባሕርይ በክብር በምልክና አንድ እንደሆነ “እኔ እና አብ አንድ ነን” ያለውን አላነበብክምን? (ዮሐ. 10÷30)፡፡
አርዮስ፡- በግሪኩ ሆሞ ኡስዮስ (Homo ousios) የሚለውን ቃል ለውጦ ሆሞይ ኡስዮስ (Homoi – ousios) ብሎ ነበርና፡፡ አርዮስ የግሪክ ፊደል “i”ን (አዮታ) አስገባ፡፡ ሆሞ ኡስዮስ (Homo ousios) አንድ አይነት ባሕርይ (the same ousia) ማለት ሲሆን ሆሞይ ኡስዮስ (Homoi ousios) – ተመሳሳይ (የተካከለ) ባሕርይ (Similar ousia) ማለት ነው፡፡ ይህን ስርዋጽ አስቀድሞ በነበረው የቂሣርያ ቤተ ክርስቲያን አንቀጸ ሃይማኖት ውስጥ እንዲካተት አድርጐ ነበር በቅዱስ አትናቴዎስ የሚመራ አንቀጸ ሃይማኖት አርቃቂ ቡድን ሆሞ ኡስዮስ (Homo ousios) – the same ousia በማለት አስተካከሉት ወደእኛ ሲመለስ “ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ” የሚለው ነው፡፡
ይህ ኃይለ ቃል ወደ አማርኛ ሲመለስ “በመለኮቱ ከአብ ጋር የተካከለ” ተብሎ ተተርጉሞ ይገኛል፡፡ ይህ ትልቅ ስሕተት ነው፡፡ አርዮስም ሲከራከርበት የነበረው “ወልድ በመለኮቱ ከአብ ጋር ይተካከላል” (Similar ousia) በማለት ነበር፡፡ ነገር ግን መሆን ያለበት ወይም በሌላ አነጋገር “ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ” የማለው ኃይለ ቃል መተርጐም ያለበት “በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ የሆነ” ተብሎ ነው፡፡ በመተካከል (Similar) እና አንድ (the same) መካከል ትልቅ ልዩነት እንዳለ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በሒሳብ ስሌት ብናየው መተካከል (equivalent) የመጠን እንጁ የባሕርይን አንድነት አያመለክትም፡፡ ግዕዙ ችግር የለበትም ነገር ግን ወደ አማርኛ ሲመለስ ሃይማኖትን የሚያስነቅፍ ትርጉም እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ለሉቃስ ወንጌል “ቡርክት አንቲ እም አንስት” የሚለው ኃይለ ቃል ወደ አማርኛ ሲመለስ “ከሴቶች መካከል አንቺ የተባረክሽ ነሽ” ተብሎ ተተርጉሟል (ሉቃ. 1÷28-42)፡፡ ነገር ግን መተርጐም ያለበት “አንቺ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ” ተብሎ ነበር፡፡ “እምአንስት” ከሴቶች ሁሉ መባል ሲገባው ከሴቶች መካከል ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ከሴቶች መካከል ከተባለ እመቤታችንን በክብር፣ በቅድስና የሚመስሏት አሉ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እመቤታችንን ከፍጡር ወገን በክብር በቅድስና የሚመስላት እንደሌለ “መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ” በማለት ታስተምራለች “እም” የሚለው የግዕዝ አገባብ ብዙ ፍች አለው ለምሳሌ ከ…መካከል ሆና ሲፈታ ወመጽአ አሐዱ መልአክ እመላእክት ዘይረድአኒ ትርጉሙም ከመላእክት መካከል የሚረዳኝ አንድ መልአክ መጣ የሚል ነው፡፡ ከ…ሁሉ ተብሎ ሲተረጐም ደግሞ “ቡርክት አንቲ እምአንስት” አንቺ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ ይላል፡፡ ከመላእክት መካከል ሲል በክብር በሥልጣን ከሚተካከሉት (ከሚመስሉት) አንዱ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ስለዚህ “ዘ ዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ” የሚለው ኃይለ ቃል በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ የሆነ ተብሎ ቢተረጐም ከወንጌሉ ቃል (አነ ወአብ አሐዱ ንሕነ) ጋር የተስማማ ከመሆኑም በላይ “በመለኮቱ ከአብ ጋር የተካከለ” የሚለውን የአርዮስን ትምህርት የሚንድ ይሆናል፡፡
አርዮስ፡- ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ ስለተገኙ በቅድምና አብ ይበልጣቸዋል፡፡ በአብና በወልድ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ መካከል የጊዜ ልዩነት አለ ብሎ ለተከራከረበት ምላሽ ቅዱስ አትናቴዎስ መጽሐፍ ቅዱስን መነሻ በማድረግ የሚከተለውን ብሏል፡፡ የጊዜ መገኘት ከፍጥረታት መገኘት ጋር ነው፡፡ ዘመን መቆጠር የጀመረው ሰማይና ምድር በተፈጠሩበት ዕለት ነው፡፡ “ማታም ሆነ ጠዋት አንድ ቀን” የሚል ኃይለ ቃል አለና፡፡ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የሥላሴ ዘመናት ሊነገር ሊመረመር አይችልም፡፡ የወልድ መወለድ የመንፈስ ቅዱስ መስረጽ ባሕርይ ዘእምባሕርይ (ከባሕርይ የተገኘ ባሕርይ) አካል ዘእም አካል (ከአካል የተገኘ አካል) ስለሆነ በባሕርይ አይበላለጡም በአካልም አይተናነሱም ቅድምናቸውም አንድ ነው “አሐቲ ቅድምናሆሙ ለሥላሴ” በማለት ትንታኔ ሰጥቷል፡፡
የኒቂያ ጉባኤ ዋና ዓላማ በወልድ ላይ ቢሆንም ስለ ነገረ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ አትናቴዎስ የሚከተለውን ለጉባኤው አሰምቷል፡፡ መንፈስ ቅዱስ እንደ አብና ወልድ ፍጹም አካል ያለው ነው እንጂ ዝርው መንፈስ አይደለም በባሕርይ በሕልውና በቅድምና በምልክና ከሁለቱ አካላት ጋር አንድ ነው፡፡ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን አምላካዊ ክብሩ ተነግሮለታል፡፡ በቀደምት አበው አምላክ ብለው እንደጠሩት ሁሉ ሐዋርያትም አምላክ ነው በማለት አስተምረዋል፡፡ ነቢያትን በአባቶቻችን ዘመን ትንቢት እንዲናገር በዘመናችን ደግሞ ለሐዋርያት ቋንቋ አናግሯል፣ ምሥጢር አስተርጉሟል፡፡ ወልድ ከአብ ሲወለድ ምንም የባሕርይ ጉድለት የአካል ሕጸጽ እንደሌለበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስም አብን አክሎና መስሎ ሠርጿል፡፡ ሦስቱ አካላት በፈቃድ አንድ ናቸው በባሕርይ አንድ ስለሆኑ፡፡ እግዚአብሔር ሳይገደድ እንደፈቀደ ሁሉንም ነገር ያደርጋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሦስቱም አካላት ፈቃድ እንዳላቸው ይናገራል፡፡ ነገር ግን የአንዱ አካል ፈቃድ ከሁለቱ አካላት ፈቃድ የተለየ አይደለም፡፡ በአንዲት ልብ ያስባሉና፡፡
በቅዱስ አትናቴዎስ ያደረ መንፈስ ቅዱስ አንደበቱን ስለዘጋው ከዚህ በኋላ የመከራከሪያ ነጥብ አላቀረበም፡፡ አንቀጸ ሃይማኖቱም ጸሎተ ሃይማኖት ነአምን በአሐዱ አምላክ ከሚለው እስከ ወአልቦ ማኅለቅት ለመንግሥቱ እስከሚለው ተረቆ ጉባኤው ከመረመረ በኋላ በሦስት መቶ አስራ ስምንት ሊቃውንት ድምፅ ጸድቆና ተፈርሞ የሃይማኖት አንቀጽ ሆነ በንጉሡ ማኅተም በመላው ዓለም ባሉ አብያተ ቤተ ክርስቲያናት እንዲሰራጭ ተደረገ፡፡ በዚህ የተበሳጩ አርዮስና ደጋፊዎቹ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ዙሪያ የተደነገገ ድንጋጌ አለመኖሩን ተመልክተው መንፈስ ቅዱስ ሕጹጽ ነው ከአብና ከወልድ ያንሳል፡፡ የአብና የወልድ ኃይል መግለጫ ነው እንጂ አካል የለውም የሚል የኑፋቄ ትምህርት እንደገና መርጨት ጀመሩ፡፡ ሠለስቱ ምዕት ስለ አብና ወልድ አምላክነት ደንግገው የመንፈስ ቅዱስን አለማንሳታቸው ወይም አለማካተታቸው አርዮስና ተከታዮቹ እንደሚሉት የመንፈስ ቅዱስን አምላክነት ተጠራጥረው ሳይሆን ዋና አጀንዳ የነበረው የወልድ ጉዳይ ስለነበር እና ጉባኤው ብዙ የቤተ ክርስቲያን ቀኖና በማጽደቅ መጽሐፍትን መቁጠርና በቆኖና መወሰን እንዲሁም ንጉሡ ቆስጦንጢኖስ ሕዝቡን የሚመራበት ሕግ አጽድቁልኝ ብሏቸው ስለነበር ይህና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ሲያከናውኑ በነገረ መንፈስ ቅዱስ ዙሪያ በአንቀጸ ሃይማኖት ሳያስገቡ ቀርተዋል፡፡
ምንም እንኳን በአንቀጸ ሃይማኖት ውስጥ ባያካትቱም በጉባኤው የተገኙ ሊቃውንት ሁሉ እያንዳንዳቸው ለቤተ ክርስቲያን ይጠቅማል ያሉትን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ድርሳናት ደርሰዋል፡፡ በድርሳናቸውም ውስጥ ነገረ መንፈስ ቅዱስ እንዳስገቡ ከድርሳናቸው እንረዳለን፡፡ የአርዮስን ለጋሲ ሲያስቀጥሉ የነበሩ ተረፈ አርዮስ ሲመቻቸው ወልድንም በመለኮቱ ከአብ ያንሳል ሲሉ ሳይመታቸው ወልድ አምላክ ነው፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ያንሳል በዕሪና መለኮት አይኖርም በማለት የክህደት ትምህርታቸውን ከእስክንድርያ እስከ ቁስጥንጥንያ አደረሱት፡፡
አርዮሳውያን ቀስ በቀስ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ማሳደድ ጀመሩ፡፡ በ330 እ.ኤ.አ. የአንጾኪያውን ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስን ከንጉሡ ከቆስጦነጢኖስ ጋር በማጣላት ከመንበሩ ወርዶ እንዲሰደድ አደረጉት፡፡ ይህ አባት በኒቂያው ጉባኤ ላይ አንቀጸ ሃይማኖትን በማርቀቅ አርዮሳውያንን በመሟገት ትልቅ ድርሻ ነበረው ከሁለት ከሦስት ዓመት በኋላ ወደ አስር የሚጠጉ ታላላቅ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት ከመንበረ ጵጵስናቸው እንዲወርዱ ተደረገ፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ለንጉሡ እጅግ ቀራቢ በነበረው የአርዮስ ወዳጅ በኒቆምዲያ ሊቀ ጳጳስ በአውሳቢዮስ አጋዥነት ነበር፡፡ ከኒቂያ ጉባኤ በኋላ በ328 እ.ኤ.አ. በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን የተሾመው ቅዱስ አትናቴዎስን ከንጉሡ ከታላቁ ቆስጠንጢኖስ ጋር በማጣላት ለሃያ ስምንት ወራት ያህል ወደ ትሬቨርስ በረሃ አሳደዱት፡፡ የኒቆሞዲያው አውሳቢዮስ ንጉሡን በማባበል አርዮስ ከስደት ተመልሶ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲገባ የቁስጥንጥንያውን ፓትርያርክ እንዲያዝ አድርጐ ነበር፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ አልፈቀደምና አርዮስ በድንገት ሞተ፡፡ ታላቁ ቆስጠንጢኖስ ግንቦት 22 ቀን በ337 እ.ኤ.አ. አረፈ፡፡
ከእርሱ ሞት በኋላ ሦስቱ ልጆቹ ታላቋን የሮም ግዛት ለሦስት ተካፈሏት፡፡ ዳግማዊ ቆስጠንጢኖስ እየተባለ የሚጠራው እስከ ምዕራብ አልፕስ ተራራ ድረስ መላዋ አውሮፓ ደረሰችው፡፡ ቁንስጣንዲዮስ የተባለው ደግሞ ትንሿ ኢስያ፣ ግብጽ እና ምስራቅ ሶርያ ደረሱት፡፡ ሦስተኛው ልጅ ቁንስጣ ኢጣሊንና ኢለሪከምን ወሰደ፡፡ ዳግማዊ ቆስጠንጢኖስና ቁንስጣ ኦርቶዶክስን ሲደግፉ ቁንሰጣንዲዮስ የአርዮስ ደጋፊ ሆነ፡፡ ዳግማዊ ቆስጠንጢኖስ ቁንስጣንዲዮስን በማባበል አትናቴዎስን ከስደት እንዲመለስ አደረገ፡፡ አርዮሳውያን ከቁንስጣንዲዮሰ በሚደረግላቸው ድጋፍ በ339 እ.ኤ.አ. እንደገና አሳደዱት በምትኩም ቀጰዶቅያዊው ጊዮርጊስ በመንበረ ማርቆስ እንዲቀመጥ ተደረገ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ወደ ሮም ሄዶ ለሮሙ ፓፓ ጂልየስ ጉዳዩን አስረዳ፡፡ ጁልየስም አምሳ ሊቃነ ጳጳሳትን በመጥራት ጉባኤ አድርጐ አትናቴዎስ ምንም ጥፋት እንደሌለበት አረጋገጠለት ነገር ግን አትናቴዎስ ከ339-346 ለሰባት ዓመት ያህል በዚያው በስደት ኖረ፡፡ በ340 እ.ኤ.አ. በሁለት ወንድማማቾች በኦርቶዶክሳውያንና በአርዮሳውያን መካከል ያለውን ነገር ለማርገብ በ343 እ.ኤ.አ. ሳርዲካ በምትባል ከተማ ጉባኤ ጠሩ፡፡ የጉባኤው ሊቀ መንበርም የኦርቶዶክስ ተከታይ የሆነው የሆርዶቫ ሊቀ ጳጳስ ኢየሱስ ነበረ፡፡ ይህ ጉባኤም የአርዮሳውያንን የሐሰት ትምህርት በማጋለጥ የሚያቀርቧቸውን ሁሉ ክሶች ውድቅ አደረገ፡፡ የጉባኤውን ውሳኔ በመቀበልም ከጊዮርጊስ ዘቀጰዶቅያ ሞት በኋላ አትናቴዎስ ወደ መንበሩ እንዲመለስ በ350 ዓ.ም (እ.ኤ.አ.) ቁንስጣንዲዮስ ወንድሙን ገድሎ ብቸኛ የሮም ግዛት ቄሣር ሆነ፡፡ በእርሱም ድጋፍ አርዮሳውያን እየተስፋፋ በመሄድ ኦርቶዶክሳውያንን ድል ማድረግ ጀመሩ፡፡ ነገር ግን በአስተሳሰብ ለሦስት በመከፈላቸው የእርስ በርስ ጦርነት ፈጠሩ፡፡ ለሦስት የተከፈሉት አርዮሳውያን፡-
ሀ. መንፈቀ-አርዮስ (Semi-Arians)፡- እነዚህ አንጃዎች በጣም አክራሪ የሚባሉ በኒቂያው ጉባኤ ከነበሩ ከአርዮስ ተከታዮች የተገኙ ሲሆኑ የወልድን አምላክነት የሚያምኑ ናቸው፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ በመለኮት ባሕርዩ ያንሳል ይላሉ፡፡ ወልድን አምላክ ነው ብለው ቢያምኑም እንኳን በባሕርይ ይመስለዋል ይላሉ እንጂ አንድ ናቸው አይሉም ስለዚህ እነዚህ አንጃዎች የአርዮስ የቅርብ ምትኮች (Immediate successors) ተብለዋል፡፡
ለ. ዩራሲያንስ (Eurasians)፡- እነዚህ ክፍሎች ብዙም ሃይማኖታዊ እውቀት የሌላቸውን ሃይማኖቱን ለፖለቲካ ፍጆታ የሚያውሉ ናቸው፡፡ ሃይማኖትን ተገን በማድረግ የፖለቲካ ሥልጣን ማግኘት የሚሹ በመሆናቸው የሚያቀርቡት ሃይማኖታዊ ጉዳይ የሚዋዥቅ አይነት ነበር፡፡
ሐ. አኖሚያውያን (Anomians)፡- አኖሚያ (Anomia) ቃሉ የግሪክ ሲሆን ትርጉሙም የማይመሳሰል (unlike) ማለት ነው፡፡ እነዚህ ቡድኖች ወልድ በፍጹም በባሕርይ አብን አይመስልም፡፡ ወልድ የአብ ፍጹም ሕጸጽ የሌለበት (perfect being) ፍጡር ነው፡፡ ወልድ ከሌሎቹ ፍጥረታት የሚለየው በፍጹምነቱ ነው እንጂ አብን መስሎ አይደለም ይላሉ፡፡
በቀንስጣንዲዮስ ትዕዛዝ በ353 በደቡብ ፈረንሳይ በፓሪስ ከተማ በ355 በሚላን ከተማ ጉባኤ ተደረገ፡፡ ንጉሡን በመፍራት ምዕራባውያን ጳጳሳት አርዮሳውያን ሲደግፉ በጁልየስ መንበረ የተተካው የሮም ፓፕ ሊቨርየስ፣ ሂላሪ ዘጳርቴ ኡሲዮስ ዘ ሆርዶቫ ቅዱስ አትናቴዎስን ደግፈው በመቆማቸው ከየመንበረ ጵጵስናቸው ወርደው እንዲሰደዱ ተደረጉ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስም ለስድስት ዓመት ያህል ከአባ እንጦንዮስ ዘንድ ገዳም ኖረ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ባልተገኘባቸው በስርሚየም፣ በርሚኒ፣ በሰሌዩሲያ፣ በአንጋራ እና በቁስጥንጥንያ በተደረጉ ጉባኤያት ሁሉ አርዮሳውያንን የሚደግፍ ውሳኔዎች ተላለፉ፡፡ በ361 ቁንስጣንዲዮስ በጦርነት ተገደለ ጁሊያን እንደነገሠ ችግሩን ለማርገብ በማሰብ ራሱን ሃይማኖት የለሽ (pagan) እንደሆነ አወጀ፡፡ የሃይማኖት ነፃነት (Guarantee liberty to religion) በማወጁ አትናቴዎስ በ362 ወደ መንበሩ ተመለሰ፡፡ የፓጋን ፈላስፎች ክርስትናን የሚያቃልል ድርሰት እንዲዘጋጁ ንጉሡ ያበረታታ ጀመር፡፡ በዘመኑ በእስክንድርያና በጋዛ ብዙ ክርስቲያኖች ተጨፋጭፈዋል፡፡ ብዙ የፓጋን ፈላስፎች የክርስቲያንን ትምህርት የሚያንኳስስ ጽሑፍ በማዘጋጀትና በማስረጨት የክርስትናን እምነት አዳክመዋል፡፡ በ363 ከፋርሶች ጋር ጦርነት ሲያደርግ በድርጊቱ ይጠሉት የነበሩ ክርስቲያኖች እንዲሁም አርዮሳውያን በመተባበር ተቃወሙት በዚሁ ዓመት በጦርነቱ ተገደለ፡፡ በምትኩ የጦር መሪ የነበረው ጂቪያን ነገሠ፡፡ ጥሩ ክርስቲያን ስለነበር በእርሱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን እረፍት አገኘች፡፡
እንዲህ እያለች የሮም ግዛት ከታላቁ ቴዎዶስዮስ (378) ደረሰች፡፡ መፍቀሬ ሃይማኖት ነውና እያንዳንዱ አርዮሳውያን ጳጳሳት የኒቂያውን ጉባኤ ውሳኔ እንዲቀበሉና በሥራ ላይ እንዲያውሉ በ380 አዋጅ አወጀ፡፡ ጎርጐርዮስ ዘእንዚናዙ የግጉሡ የቅርብ ወዳጅ ሆነ ከ341-360 የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ የነበረው መቅዶንዮስ ከመንፈቀ አርዮስ ወገን ስለነበር በቁስጥንጥንያ ከተማ የክህደት ትምህርት አሰራጭቶ ነበር፡፡ ከዚህ ቀጥለን የመቅዶንዮሳውያንን የክህደት ትምህርትና የቤተ ክርስቲያንን የእርምጃ ውሳኔ እናያለን፡፡
ሠ. መቅዶንዮሳውያን (Mecedonianism)
የመቅደኒያኒዝም የክህደት ትምህርት መሥራች ከ341-360 ዓ.ም (እ.ኤ.አ.) የቆስጥንጥንያ ፓትርያርክ የነበረው መቅዶንዮስ ነው፡፡ ወልድ በባሕርየ መለኮቱ ከአብ ጋር አንድ ስለሆነ መንበር አለው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ግን በመለኮቱ ስለሚያንስ መንበር የለውም በማለት ያስተምር ነበር፡፡ ዘመኑ አርዮሳውያን የነገሡበት ስለነበረ ይህ ትምህርት ታላቁ ቴዎዶስዮስ እስከነገሠበት ድረስ እየተሠራጨ ኖሯል፡፡ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአርዮስ ትምህርት ጐን ለጐን ሌሎችም የምንፍቅና ትምህርት ብቅ ብቅ ብለው ስለነበር የመቅዶንዮስ የክህደት ትምህርትና እነዚህ ትምህርቶች መወገዝ ስላለባቸው በታላቁ ቴዎዶስዮስ ትእዛዝ በቁስጥንጥንያ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ (Ecumenical Council) በ381 ዓ.ም ተደረገ፡፡ የቁስጥንጥንያው ፓትርያርክ መላጥዮስ የጉባኤው ሊቀ መንበር ሆነ፡፡ በጉባኤው መካከል በድንገት ስለሞተ ከእርሱ ቀብር በኋላ ጎርጐርዮስ ዘእንዚናዙ ተተካ፡፡ በመንገድ መዘገየት የተነሳ የእስክንድርያው ፓትርያርክ ጢሞቴዎስ ጉባኤው ከተጀመረ በኋላ በመድረሱ በጎርጐርዮስ ሊቀ መንበርነት አልተስማማም ነበር፡፡ የተሰሎንቄው ሊቀ ጳጳስ አርኬላዎስም ዘግይቶ በመድረሱና ምልዓተ ጉባኤ ሳያሟላ የተደረገ ምርጫ ነው በማለት ከጢሞቴዎስ ጋር አንድ ሆኑ፡፡ ግብጾች በስልጣኔያቸው ስለሚመኩና “እኛ ያላቦካነው አይጋገርም” ባዮች ናቸውና ጎርጐርዮስን ከሥልጣኑ አወረዱት በምትኩም ኒክታሪያስን የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሲሾሙ የጉባኤው ሊቀመንበር ደግሞ ጢሞቴዎስ ዘእስክንድርያ ተሾመ፡፡ መቅዶንዮስ መንፈስ ቅዱስ መንበር የለውም ሕጹጽ ነው ላለው ምላሽ ሲሰጡም “በዓመተ ሞተ ዖዝያን ንጉሥ ርኢክዎ ለእግዚአብሔር እንዘ ይነብር ዲበ መንበሩ ልዑል ወነዊል ወሱራፌል ይጸርሑ እንዘ ይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸባዖት ምሉዕ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሐቲከ፡፡” በማለት ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገረው አንዱ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ “ዲበ መንበር ነዋኃ” ብሏልና መንፈስ ቅዱስ መንፈስ እንዳለ ያሳያል በማለት የመቅዶንዮስንና የተከታዮቹን ትምህርት ውድቅ በማድረግ አውግዘዋል መቅዶንዮስ የተወገዘ ከሞት በኋላ ነው፡፡ የሞተው በ360 ነውና (ኢሳ. 6÷1-4)፡፡
በዚህ ጉባኤ የተሰበሰቡ ጳጳሳት ቁጥር 150 እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል፡፡ በዚህ ጉባኤ ሌላው የተወገዘው የሎዶቅያ ኤጲስ የነበረው አቡሊናርዮስ ነው አቡሊናርዮስ በ360 ዓ.ም እ.ኤ.አ. ገደማ ወልድ ሥጋን ነሳ እንጂ ነፍስን አልተዋሐደም፡፡ መለኮቱ እንደነፍስ ሆነው፡፡ ወንጌልም “ቃል ሥጋ ሆነ” ነው የሚለው በማለት የክህደት ትምህርቱን አሰራጨ፡፡ ነገር ግን ወንጌል ቃል ሥጋ ሆነ ማለቱ አካላዊ ቃል በተለየ አካሉ ሥጋና ነፍስ ነስቶ ፍጹም ሰው ሆነ ለማለት ነበር፡፡ ሰውን (ሥጋና ነፍስ) ሥጋ ብሎ መጥራት ልማደ መጽሐፍ ነው፡፡ ለምሳሌ “እፌኑ መንፈስየ ዲበ ኩሉ ዘሥጋ” በሥጋ ሁሉ ላይ መንፈሴን እልካለሁ ይላል፡፡ በሰው ሁሉ ላይ በማለት እንደሆነ መገንዘብ ያሻል፡፡ (ኢዮ. 2÷28) ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ሰው ለማለት ብዙ ጊዜ የሚጠቀመው ሥጋ እንደሆነ ከመጻሕፍቶቹ መረዳት ይቻላል፡፡ (ዮሐ. 17÷1-2፣ 1ዮሐ. 4÷2)፡፡
በዚህ ጉባኤ መቅዶንዮስ፣ አቡሊናርዮስ፣ ተረፈ አርዮስ፣ በአጠቃላይ አርዮሳውያን፣ የመቅዶንዮስ ተከታዮች ተወግዘዋል፡፡ ወደ 36 የሚጠጉ መናፍቃውያን ጳጳሳትም እንደተወገዙ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸው ከተወገዙ በኋላ “ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማኅየዊ የሚለው እስከ ወንሴፎ” ትንሣኤ ሙታን እስከሚለው ድረስ ያለውን አንቀጸ ሃይማኖት አርቅቀው በኒቂያ ጉባኤ በረቀቀው ላይ ጨምረው የተሟላ አንቀጸ ሃይማኖት አድርገዋል፡፡ በዚህም የተነሣ አንቀጸ ሃይማኖታችን የኒቂያና ቁስጥንጥንያ ትብብር ጉባኤ አንቀጸ ሃይማኖት (The Neceo -Constantinople Creed) በመባል ይጠራል፡፡
ጥንታዊቷና ታሪካዊዋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታቸው በቀና ሊቃውንቶቿ አውግዛ የለየቻቸውን መናፍቃን ትምህርት ትክክል ነው ብለው ዛሬ የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ በማወክ ላይ የሚገኙ ብዙ አሳቾች ተነስተዋል፡፡ እነዚህ አሳቾች እውነተኛውን የክርስቲያን ዶግማ ስለማይቀበሉ የአምልኮት ፀባይ ያላቸው እምነት መሳይ (Cult) ይባላሉ እንጂ ክርስቲያኖች አይደሉም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የእምነታቸው መመሪያ እንደሆነ ይናገራሉ እንጂ እውነተኛ ትርጉሙን አይቀበሉም ለራሳቸው እንደሚመቻቸው ይተረጉማሉ፡፡ አንዳንዶቹም መጽሐፍ ቅዱስን አይቀበሉም፡፡ እነዚህ አሳቾች በፍጥነት እየተስፋፋ በተለይ ወጣቱንና ሴቶችን በወጥመዳቸው እያስገቡ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እጅግ ለቤተ ክርስቲያን ሥጋት እየሆኑ የመጡና ቤተ ክርስቲያን ያወገዘቻቸውን ጥንታውያን መናፍቃን ትክክል ናቸው በማለት እያወኩ ከሚገኙ መካከል ቀጥለን ጥቂቶቹን እንመለከታለን፡፡
ረ. የያህዌ ምስክሮች (Jehovah’s Witnesses)
በዘመናችን እውነተኛዋ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ለምታደርገው የድኅነት አገልግሎት የወንጌል መልዕክት ስርጭት ተፃራሪና አሳሳቢ ከሆኑት ሃይማኖት መሰል (Cult) ክፍሎች መካከል አንደኛውና አደገኛው ጄሆቫ ዊትነስ (የያህዌ ምስክሮች) የተባለው ነው፡፡ አደገኛና አሳሳቢ ያልንበት ዋነኛ ምክንያት ይህ ሀሰተኛ ሃይማኖት የሚያደርገውን ከፍተኛ እንቅስቃሴና በአጭር ጊዜ ውስጥ ያገኘውን የተፋጠነ እድገት በመመልከት ነው፡፡ የዚህ እምነት ተከታዮች እ.ኤ.አ. በ1872 ዓ.ም ከሰላሳ የማይበልጡ ነበሩ፡፡ ነገር ግን በ1981 ዓ.ም ከአራት ሚሊዮን በላይ እንደደረሱ ይታወቃል፡፡ የእምነታቸው መገለጫ የያዘውን የመጀመሪያው የጽሑፍ ስርጭታቸው “ዋች ታወር ባይብል” (Watch Tower Bible) የተባለው ሲሆን በወቅቱ ስድስት ሺህ ኮፒ ብቻ ነበር የሚያሰራጩት፡፡ ዛሬ ግን ይህ መጽሔት በወር 23 ሚሊዮን ኮፒ በ78 የተለያዩ ቋንቋዎች እየታተመ ይወጣል፡፡ በዓለም ዙሪያም በ225 አገሮች ውስጥ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችና አባላት አሏቸው፡፡
ጄሆቫ ዊትነስ በመጀመሪያ የተፀነሰው ከአንድ ጥቂት አባላት ከነበሩት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጓድ በ1872 ዓ.ም ሲሆን መስራቹም ቻርለስ ታዝ ሩሴል (Charles Taza Russell) የተባለ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ አሜሪካዊ ነው፡፡ ይህ ሰው ገና የሃያ ዓመት ወጣት እንዳለ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጓድ አቋቋመ፡፡ በዚህ ድርጅት ውስጥም መሪ በመሆን እየሠራ ጐን ለጐን የንግድ ሥራውን ያጧጡፍ ነበር፡፡ ነጋዴው ቻርለስ የመጽሐፍ ቅዱስ በቂ እውቀት ስለሌለው የክርስትናው እምነት የሚያዘውንና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነታዎች በተጣመመ መንገድ ማስተማር ጀመረ፡፡ መሠረታዊ የሆኑ የክርስትናን ዶግማዎችን ተቃወመ፡፡ እንዲያውም የአርዮስ ትምህርት ትክክል ነው በማለት በይፋ መስበክ ጀመረ፡፡
ቻርለስ ሩሴል የግል ሕይወቱ በነውርና በአሳፋሪ ድርጊት የተሞላ ነበር፡፡ በ1903 ዓ.ም (እ.ኤ.አ. 2000) ለ17 ዓመት አብራው የኖረች ሚስቱ በዝሙት ምክንያት ፈታችው ሮዝበል ከምትባል ሌላ ሴት ጋር ይማግጥ እንደነበረ ካስመሰከረች በኋላ $6,036 ዶላር የፍች አበል በፍርድ ቤት ተፈርዶበት እንዲከፍል ተደርጓል፡፡ ሩሴል የበለጠ የሚታወቀው ስለዓለም መጨረሻ በሚያውጀውና በሚናገረው የሐሰት ትንቢት ነው፡፡ ስለ አርማጌዶን የሚያስተምረው ትምህርት ብዙዎቹን ያደናገረ ነበር፡፡ ክርስቶስ ማንም ሳያየው በ1874 ዓ.ም እንደመጣ፣ የአረማውያን ዘመን በ1914 ዓ.ም እንደሚያበቃ በዚሁ ዓ.ም የአርማጌዶን ጦርነት እንደሚሆን እንዲሁም የዓለም ኃያላን መንግሥታት ወድቀው የሺ ዓመት ዘመን (ሚሊኒየም) እንደሚጀመር የሐሰት ትንቢትና ትምህርት ይረጭ ነበር፡፡ ቻርለስ ሩሴል በ1916 ከሞተ በኋላ ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ ተተክቶ ለ22 ዓመታት አገልግሏል፡፡ በዚህ ሁኔታ የተስፋፋው የጄሆቫዊትነስ እምነት (Cult) ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚቃረን የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት ፈጽሞ የሚጻረር የክህደት ትምህርት በመዝራት ቀንደኛ የቤተ ክርስቲያን ጠላት ሆነ፡፡
ጄሆቫ ዊትነስ በሥላሴ የማያምኑ ከመሆናቸውም ባሻገር ነገረ ሥላሴ (Doctrine of Trinity) ምንጩ ሰይጣን ነው በማለት ትልቅ የድፍረት ነገር ይናገራሉ፡፡ በሥላሴ ላይ ያላቸውን የክህደት እምነት የመሠረቱት በ325 ዓ.ም በኒቂያ ጉባኤ የተወገዘውን የአርዮስን ትምህርት መነሻ በማድረግ ነው፡፡ “Let God be True” (እግዚአብሔር እውነት ይሁን) በሚለው መጽሐፉ ቻርለስ ቴዝ ሩሴል “የሥላሴ እምነት ትምህርት ከኢየሱስ ወይም ከቀድሞ ቤተ ክርስቲያን የመጣ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሥላሴ የሚል ቃል የትም ሥፍራ ተጠቅሶ አይገኝም፡፡ ስለዚህ ይህ ትምህርት እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ስለ ያህዌና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳይማሩና እንዳያውቁ ለማደናገር ነው፡፡ ሥላሴ የሚል ነገር የለም” ሲል ጻፈ፡፡ በሥላሴ ምትክ ጄሆቫ ዊትነሶች የሚያስተምሩት ኢየሱስ ሁለተኛ ደረጃ ያለው እግዚአብሔር እንደሆነና ያህዌ ከፈጠራቸው ፍጥረታት መካከል ኢየሱስ ከፍተኛ ሥፍራ እንዳለው ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ይባል ነበር፡፡ በምድር በነበረበትም ዘመን ፍጹም አምላክ ሳይሆን ፍጹም ሰውነው ብለው ያምናሉ፡፡
ጄሆቫ ዊትነሶች የመጽሐፍ ቅዱስን ትርጒም ከማጣመም አልፈውም ቃሉን ለውጠውም ይጽፋሉ፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት በግልጽ የሚያስረዳውን የዮሐንስ ወንጌል (1÷1) በመጀመሪያው ቃል ነበር፡፡ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበር፡፡ የሚለውን ለውጠው “በመጀመሪያ ቃል ነበር ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ ቃልም ትንሽ እግዚአብሔር ነበረ” በማለት “አዲሱ ዓለም ዓቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም” (The New world Translation of Holy Scripture) በተባለው መጻፋቸው ጽፈውት ይገኛል፡፡ ጄሆቫ ዊትነሶች ኢየሱስ ፍጡር ነው በማለት ለመከራከሪያ የሚጠቅሱአቸው ጥቅሶች (ቈል. 1÷15 እና ራዕ. 3÷14) ናቸው፡፡ ቈላስይስ 1÷15 “እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው የሚታዩትና የማይታዩትም ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረታት ሁሉ በፊት በኩር ነው፡፡ ሁሉ በእርሱ ለእርሱ ተፈጥሯል፡፡” ጄሆቫ ዊትነሶች “የፍጥረታት ሁሉ በኩር” የሚለውን ሐረግ መዘው ኢየሱስ የመጀመሪያ ፍጡር ነው በማለት ሲሳሳቱ ይታያሉ፡፡ “ሁሉ በእርሱ ተፈጥሯል” የሚለው ኃይለ ቃል አምላክነቱን በማያሻማ መንገድ ገልጾታል፡፡ ታዲያ ፍጡር ፈጣሪ ሊሆን ይችላል? First born (በኩር) የሚለው ቃል በግሪኩ “ፓሮቶኮስ” ይላይ ትርጉሙም ከሁሉ ቅድሚያ ያለው ለመግዛት መብት ያለው ከሁሉ በላይ በሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው የበላይ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለማለት የፈለገው የሁሉ ገዥ በሥልጣን በአምላክነት ከአባቱ ጋር አንድ መሆኑን ለመናገር ነው፡፡ ጄሆቫ ዊትነሶች ኢየሱስ ፍጡር እንጂ አምላክ አይደለም በማለት የሚያቀርቡት ሌላው ጥቅስ (ራእይ 3÷14) ን ነው፡፡ ኃይለ ቃሉ እንዲህ ይላል፡፡ “… አሜን የሆነው የታመነውና እውነተኛው ምስክር እግዚአብሔር ከፈጠረው ሁሉ አስቀድሞ የነበረው እንዲህ ይላል፡፡” እግዚአብሔር ከፈጠረው ሁሉ አስቀድሞ የሚለውን ጄሆቫ ዊትነሶች የሚረዱት ኢየሱስ ቀዳሚ ፍጡር ነው በሚል ነው፡፡ ነገር ግን የዚህ ጥቅስ ትክክለኛ ትርጒሙ ኢየሱስ የዓለም ሁሉ ፈጣሪ እንደሆነ የሚያስረዳ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ጥቅሱ መነሻ ያደረገው አሜን የሆነው የታመነውና እውነተኛው ምስክር የሚሉትን ለአምላክ ብቻ የሚቀጸሉ ቃላትን ነው፡፡ ለምሳሌ “አሜን” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል የሚያገለግለው ለፈጣሪ እንጂ ለፍጡር አይደለም፡፡ “አልፋና ኦሜጋ መጀመሪያና መጨረሻ እኔ ነኝ” በማለት የሚናገረውም ቅድመ ዓለም የነበረና ዓለምን አሳልፎ የሚኖር አምላክ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በሌላ መልኩ የሁሉ መገኛ ምንጭ ገዥ መሆኑን ይገልፃል፡፡ “መጀመሪያ” የሚለው ቃል በግሪኩ አርኬ (Arche) ይላል፡፡ ትርጉሙም መነሻ ምንጭ ገዥ ማለት ነው፡፡ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት የሚመሰክሩ ጥቅሶች እንጥቀስ ብንል መጽሐፍ ቅዱስን እንደገና እንደመጻፍ ነው፡፡ ምክንያቱም አምላክነቱን የማይጠቅስ ከነቢያት ትንቢት ወይም ከኦሪት ወይም ከወንጌላት እንዲሁም ከሐዋርያት ትምህርት አናገኝምና፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
- ነቢዩ ኢሳይያስ አምላክ ብሎታል (ኢሳ. 9÷6)
- ሐዋርያትም ኢየሱስን እግዚአብሔር በማለት ጠርተውታል (ዮሐ. 1÷1-4፣ ሐዋ. 20÷28፣ ሮሜ. 9÷5፣ ቲቶ. 2÷13፣ 2ኛ ጴጥ. 1÷1፣ 1÷8)፡፡
ጄሆቫ ዊትነሶች መንፈስ ቅዱስ አካላዊ መለኮት ሳይሆን ተንቀሳቃሽ የእግዚአብሔር ኃይል ነው በማለት አምላክነቱን ይክዳሉ፡፡ “አዲሱ ዓለም ዓቀፍ ትርጉም” (The New world Translation) በሚሉት መጽሐፍ ቅዱሳቸው ውስጥ በካፒታል ሌተር “Spirit” ተብሎ ይጻፍ የነበረውን በስሞል ሌተር በመጻፍ “Holy spirit is the invisible active force of Almighty God which moves His Services to do His will” የሚል ትርጉም ሰጥተውት ይገኛሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር አገልጋዮች የእርሱን ፈቃድ እንዲፈጽሙ የሚመራ የእግዚአብሔር ቀጥተኛ የማይታይ ኃይል (ጉልበት) ነው እንጂ አካል ያለው አይደለም ይላሉ፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ አካል ያለው በባሕርይ ገንዘቡ ከአብና ከወልድ ጋር አንድ የሚሆን አምላክ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በሚገባ ዘግቦት ይገኛል፡፡
መንፈስ ቅዱስ ፍጹም አምላክ እንደሆነ (በዘፍ. 1÷2) ከመገለጹም በላይ ጻድቁ ኢዮብ “የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወትን ሰጠኝ” (ኢዮ. 33÷4) በማለት ተናግሯል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በማለት ከአብ ከወልድ ጋር ያለውን ዕሪና እግዚእና ዕሩየ ምልክና ይጠቁማል፡፡ በትንቢተ (ኢሳ. 6÷1-10) እግዚአብሔር ተብሎ የተጠራው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ቁልጭ አድርጐ ተርጉሞታል (የሐዋ. 28÷23-28) ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም እግዚአብሔር ብሎ እንደጠራው (በሐዋ. 5÷3-4) ማንበብ እንችላለን፡፡ መንፈስ ቅዱስ አካል ያለው አምላክ እንደሆነ የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብበን ልንገነዘብ እንችላለን፡፡ (የሐዋ. 13÷2፣ 1ቆሮ. 12÷11፣ ዮሐ. 15÷26፣ ዮሐ. 16÷8-11፣ ዕብ. 9÷14) ወዘተ፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ ጄሆቫ ዊትነሶች የክርስትና መሠረቶች የሆኑትን ነገረ ሥላሴ፣ ነገረ ክርስቶስ፣ ሥነ መንፈስ ቅዱስ፣ በክርስቶስ የተከፈለ ቤዛነት፣ ትንሣኤ ዳግም ምጽዓት፣ ከሞት በኋላ ያለ ሕይወት ወዘተ የሚቃወሙ ፍጹም አርዮሳውያን ስለሆኑ ከረከሰ ትምህርታቸው መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን እያጣመሙ የራሳቸውን አቋም (ትምህርት) ብቻ ለማሳመን የሚታገሉ ናቸው፡፡ በስብከታቸው ደፋሮች ታታሪዎችና የማይሰለቹ ናቸው፡፡ ታማኝነታቸው የሚለካው እምነታቸውን በትጋት ለሌሎች በሚያሰራጩት መጠን በመሆኑ ከፍተኛ ትጋትና ጥረት ያሳያሉ፡፡ ለዚህም ነው በአሁኑ ወቅት በዓለም ካሉት አሳች እምነቶች (Cults) መካከል ከፍተኛ ስለሚያምኑ ከፍርድ ለማምለጥ የወንጌል ስብከታቸውን በኃይል እያጣደፉ ይገኛሉ፡፡
ሰ. ኢየሱስ ብቻ (Only Jesus)
ባለፉት ሰማንያ ዓመታት የክህደት ትምህርታቸውን በተፋጠነ መንገድ ካስፋፉት የሦስትነትን ምስጢር (ነገረ ሥላሴ) ትምህርትና እምነት ከሚቃወሙ መካከል አንደኛውና ትልቁ በውጭ ሀገር “United Pentecostalism” በሀገራችን በኢትዮጵያ ደግሞ “የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን (Apostles’ Church)” ኢየሱስ ብቻ (Only Jesus) በመባል የሚታወቅ እምነት መሳይ የክህደት ትምህርት የሚያስፋፋ ክፍል ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ (movement) የተጀመረው በ1913 ዓ.ም እ.ኤ.አ. ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገራችንን ጨምሮ ብዙ አህጉራትን ያጥለቀለቀና በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ አህጉራት ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ አባላት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡
የ “ኢየሱስ ብቻ” (Only Jesus) ተከታዮች የእምነት አቋም “እግዚአብሔር በአካል አንድ ነው ያም አንድ አምላክ ኢየሱስ ብቻ ነው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ መገለጫዎች እንጂ አካላት አይደሉም፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስ የተለያዩ ስሞች ናቸው” የሚል ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ ሥፍራ አንድ እግዚአብሔር እንዳለ ይናገራል፡፡ “እግዚአብሔር አምላካችን አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው” (ዘዳ. 6÷4)፡፡ ሥላሴን የማይቀበሉት “የኢየሱስ ብቻ” ተከታዮች የሚጠቀሙበት ትልቁ ጥቅሳቸው ይህ ነው፡፡ አንድ እግዚአብሔር ሲል ምን ማለት ይሆን? “አንድ” የሚለው ቃል “ኢካድ” ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው፡፡ በዘዳግም 6÷4 ላይ የተገለጸው “ኢካድ” (አንድ) የሚለው ቃል የገጽ፣ የአካል አንድነትን ያሳያል ይላሉ፡፡ ነገር ግን “ኢካድ” የሚለው ዕብራይስጥ ትክክለኛ ትርጒሙ “ኅብረት” ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ እግዚአብሔር በሦስት አካላት ሦስቱ አካላት በአንድ ባሕርይ፣ በአንድ እግዚእና በአንድ ምልክና ኅብረት መኖራቸውን ለማሳየት ነው፡፡ “ኢካድ” የሚለውን ዕብራይስጥ ነቢዩ ሙሴ የአይሁድ አንቀጸ ሃይማኖት ውስጥ የተጠቀመው፡፡
የኢየሱስ ብቻ (Only Jesus) ተከታዮች መነሻቸው የሰባልዮስ የክህደት ትምህርት ነው፡፡ ሰባልዮስ “እግዚአብሔር አንድ አካል አንድ ገጽ ነው በዘመነ ብሉይ አብ ተባለ በዘመነ ሥጋዌ ወልድ ሲባል በዘመነ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ ተባለ የስም መለዋወጥ እንጂ እግዚአብሔር አንድ ገጽ ነው” የሚል የክህደት ትምህርት ከሞዳሊስቲክ ሞናኪየኒዝም ፍልስፍና ወስዶ በማስተማሩ ቤተ ክርስቲያን አውግዛ እንደለየችው ቀደም ብለን አይተናል፡፡ እነዚህ አንጃዎችም ይህን የክህደት ትምህርት መሠረት በማድረግ “ኢየሱስ አብ ነው ወልድም እርሱ ነው መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ እርሱ ነው” በማለት በኢሳይያስ 9÷6 ላይ “… ኃያል አምላክ የዘለዓለም አባት የሰላም አለቃ” ከሚለው ኃይለ ቃል “የዘለዓለም አባት” የሚለውን ሐረግ በመምዘዝ ኢየሱስ እግዚአብሔር አብ ነው የሚል ክርክር ያቀርባሉ፡፡ ነገር ግን በዕብራይስጡም ይሁን በአረብኛ እንዲሁም በግዕዝ “አብ” የሚለው ቃል ቀጥተኛ የአማርኛ ትርጉሙ አባት ማለት ስለሆነ ለተለያየ መግለጫ ሊያገለግል ይችላል ለምሳሌ “የነገድ አባቶች” (ዘጸ. 6÷24)፡፡ “የዘለዓለም አባት” (ኢሳ. 9÷6) የሚለው ኃይለ ቃል የሚያመለክተው ኢየሱስ ክርስቶስ ዘለዓለማዊ የፍጥረታት ሁሉ አባት መጋቢ ገዥ መሆኑን የሚያመለክት እንጂ በአካሉ እግዚአብሔር አብን ነው የሚል አይደለም፡፡ ሌላው የኢየሱስ ብቻ (Only Jesus) አማኞች የሚያቀርቡት መከራከሪያ “እኔና አብ አንድ ነን” (ዮሐ. 10÷30) የሚለውን ኃይለ ቃል ነው፡፡ ኢየሱስ አብን ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ አብን ቢሆን ኖሮ እኔ አብ ነኝ ይል ነበር እንጂ እኔና አብ አንድ ነን ባላለም ነበር፡፡ እኔና አብ አንድ ነን ያለበት ምክንያት በባሕርይ አንድ መሆናቸውን እንጂ አካልን የሚመለከት አይደለም፡፡
“የኢየሱስ ብቻ” ተከታዮች “አንዱ እግዚአብሔር በዘመነ ብሉይ አብ ተባለ በዘመነ ሐዲስ ሥጋ ሲለብስ ኢየሱስ ተባለ በሐዋርያት ላይ መንፈሱን ስላፈሰሰ መንፈስ ቅዱስ ተብሏል” በማለት የሰባልዮስን የክህደት ትምህርት እንደገና እንዲያገግም ያደረጉ አደገኛ መናፍቃን ናቸው፡፡ “መንፈስ ቅዱስ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው በማለት በአብና በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ የለብንም፡፡” ሐዋርያትም ያጠመቁት በኢየሱስ ስም ነው ይህ ማለት ኢየሱስ አብም መንፈስ ቅዱስ ነው በማለት የመንፈስ ቅዱስን አካላዊ አምላክነት ይክዳሉ፡፡ ለመከራከሪያ የሚጠቀሙባቸው ጥቅሶች፡-
- “በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር፡፡” (የሐዋ. 8÷16)
- “… እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፡፡” (የሐዋ. 2÷38)
- “… በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው፡፡” (የሐዋ. 10÷48)
- “ይህን በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ” (የሐዋ. 19÷5)
በማቴ. 28÷19 “… በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስም ስም እያጠመቃችኋቸው … ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፡፡” የሚለው የኢየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ካነበብናቸው ጥቅሶች ጋር አይጋጭም ወይ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ በኢየሱስ ስም የተጠመቁ ሰዎችን ማንነት ስንመለከት ከአይሁድነት ወደ ክርስትና የመጡ አይሁዶች ሳምራውያን እግዚአብሔርን ይፈሩ የነበሩ አሕዛብና የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት እንደነበሩ ከታሪኩ እንረዳለን፡፡ እነዚህ ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት እምብዛም የገባቸው አልነበሩም፡፡ የሐዋርያትም ትልቁ ተልዕኳቸው የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነትና የማዳን ሥራውን ለዓለም ማስተዋወቅ ስለነበር እንጂ በማን ስም ማጥመቅ እንደነበረባቸው የታዘዙትን ትዕዛዝ ዘንግተው አይደለም፡፡ ዳግመኛም አብና መንፈስ ቅዱስ በወልድ ሕልው መሆናቸውን ስለሚያውቁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ማጥመቃቸው በሦስቱ አካላት ስም ማጥመቅ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልድ እንጂ መንፈስ ቅዱስን እንዳልሆነና መንፈስ ቅዱስ የራሱ የሆነ አካል እንዳለው ራሱ እንዲህ በማለት መስክሯል፡፡ “እኔም አብን እለምናለሁ ለዘለዓለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፡፡” “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፡፡” “… ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ይመራችኋል፡፡” (ዮሐ. 14÷15፣ 26፣ 16÷13)፡፡
ውድ አንባቢያን የኢየሱስ ብቻ (Only Jesus) በሀገራችን በኢትዮጵያ በተለይም በመዲናችን በአዲስ አበባ የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን በሚል ስም በመንቀሳቀስ ብዙ ወጣቶችን እያሳቱ ከቀናች ሃይማኖት ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እና ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ትርጉም እንዲያፈነግጡ በማድረግ ከፍተኛ የጥፋት ዘመቻ በማፋጠን ላይ ስለሆኑ ተግተን ልንከላከላቸው ይገባል፡፡ በተለይም የሃይማኖታቸው መመሪያ መጽሐፍ ቅዱሱን የሚጠቀሙና በቅድስት ሥላሴ እምነት የሚመላለሱ የክርስትና እምነት ተከታዮች ሁሉ ይህን ችግር በጋራ መመልከት እንዳለብን ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡
ሸ. ሞርሞኒዝ (The Church of Jesus Christ latter- day Saints or Mormonism)
ይህ እምነት መሰል የአምልኮ ጠባይ ያለው ሃይማኖት (Cult) የተመሠረተው 1830 ዓ.ም እ.ኤ.አ. በኒውዮርክ ውስጥ ጆሴፍ ስሚዝ በተባለ የቬርሞንት ስቴት ተወላጅ ነው፡፡ ሞርሞኒ (Mormoni) የተባለ መልአክ ተገልጦ “አሁን ያሉት ማንኛቸውም ሃይማኖቶች ትክክል አይደሉም ተከታዮቻቸው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠሉ ናቸው በማለት በወርቅ ሳህን ላይ የተፃፈ መልዕክት ኩሞራ ከተባለ ተራራ ሥር አውጥቶ ሰጠኝ ጽሑፉንም የምተረጉምበት “ዑሪምና” ተሚም” የተባለውን ትልቅ መነጽር ሰጠኝ በማለት የሞርሞን ቅዱስ መጽሐፍ (The book of Mormonism) የተገኘ መጽሐፍ ጽፎ በ1830 ዓ.ም አሳተመ፡፡ ተገለጠልኝ ከሚለው መልአክ ስም በመውሰድ ሃይማኖቱን ሞርሞኒዝም ሲለው ተከታዮቹ ደግሞ ሞርሞኖች (Mormons) ተባሉ፡፡ ይህ እምነት የእስልምና እምነት አጀማመርን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ የእስልምና እምነት መስራች ሙሐመድ መልአክ ተገለጠልኝ እንዳለ ሁሉ ጆሴፍ ስሚዝ ሞርሞኒ የተባለ መልአክ ተገለጠልኝ ብሏል፡፡ ሙሐመድ የእስልምና ሃይማኖት መመሪያ የሆነውን ቁራንን ከመጽሐፍ ቅዱስ እየቀነጫጨበ እንደጻፈው ሁሉ The book of Mormonism የተሰኘው መጽሐፍ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቂት ጥቅሶችን በመውሰድ የተዘጋጀ ነው፡፡
ሞርሞኖች የታወቁ ሳይንቲስቶች፣ ሀብታም ነጋዴዎች፣ የፖለቲካ ሰዎችና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የታወቁ ሰዎች ስብስብ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ የራሳቸው ዩኒቨርስቲና ሴሚናሮች አሏቸው፡፡ የሥነ ጽሑፍ ስርጭታቸው በጣም የተቀላጠፈ ነው፡፡ የሞርሞን ቤተ እምነት የሚመራው እንደ አንድ ትልቅ ኮርፖሬሽን ሲሆን በዓመት ብዙ ቢሊዮን ብር የሚያስገቡ የተለያዩ የንግድ ድርጅቶች አለው፡፡ ብዙ ሰፋፊ መሬቶች፣ ሕንፃዎች አላቸው፡፡ ቦነቪል ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን፣ ቤኔፊሻል ላይፍ ኢንሹራንስ ካምፓኒ ኤልባርታ እርሻ ኮርፖሬሽን፣ ሃዋይ ካልቸራል ሴንተርና ማናጅመንት ኮርፖሬሽን ሴንተር የሞርሞን ቤተ እምነት ሀብትና ድርጅቶች ከሆኑት መካከል ናቸው፡፡ እንዲሁም በተለያዩ ኮርፖሬሽኖች ውስጥ ስቶክ (stock) ሲኖራቸው ታይም ሚረር ኮርፖሬሽን ውስጥ ብቻ የ28 ሚሊዮን ዶላር ሼር አላቸው፡፡
በተጨማሪም ማንኛውም አባል አስራት ስለሚከፍል ቤተ እምነቱ በገንዘብ የሰከረ ነው ለቤተ እምነቱ ከፍተኛ ስጦታ ከሚያበረክቱ ባለ ሀብት አባላት መካከል ቢሊየነሩ የማሪዮት ሆቴል ባለቤትና የአስሞንድ ፋምሊ ኢንተርቴነርስ (Osmond Family Entertainers) ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሞርሞኖች ሀብታቸውን በመጠቀም የአባላታቸውን ብዛት ወደ 6 ሚሊዮን አድርሰዋል በሀገራችን በኢትዮጵያም በተለይ በመዲናችን በአዲስ አበባ እየተስፋፋ እንደሆነ መረጃ አለን፡፡ በተለይም ቦሌና መገናኛ ብዙ አባላትና ጽ/ቤቶች እንዳለው ይታወቃል፡፡
ሞርሞኖች ሦስት በባሕርይ የተለያዩ አማልክት አሉ እግዚአብሔር አብ እንደሰው ሥጋና ደም አለው፡፡ መጀመሪያም ቢሆን ሰው ነው ወደ ከፍተኛ ማዕረግ የደረሰው በመለማመድ ነው፡፡ ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ቀጥሎ ያለ ጠንካራ ሰው ነው፡፡ የተወለደውም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ሳይሆን በሩካቤ ሥጋ ከእግዚአብሔር አብና ከማርያም ነው በማለት ፍጹም የወንጌሉን እውነታ ይክዳሉ፡፡ (ሉቃ. 1÷35)፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በዕድሜ እንጂ በምንም አይበልጠንም ወንዶች ኢየሱስን መሆን በመለማመድ እግዚአብሔር ይሆናል፡፡ ስለዚህ ብዙ እግዚአብሔሮች ይኖራሉ ብለው በማስተማር ነገረ መለኮትን ይቃረናሉ፡፡ የሞርሞኖች የሥነ መለኮት አቋም ከክርስትና እምነት እጅግ በጣም የራቀ ነው፡፡ ነቢያቸው ጆሴፍ ስሚዝ በመጀመሪያ የአንድ አምላክ (monotheistic) አቋም የነበረው ሲሆን ቀስ በቀስ ግን “እግዚአብሔር ከዚህ በፊት እንደኛ ሰው የነበረ ነው” የሚል እምነት ያዘ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የሞርሞን ወንድ ልጆች ወደ አምላክነት የመለወጥ እድል (mormon males have the possibility of attaining god head) አላቸው ብለው ያምናሉ፡፡ ሞርሞኖች በአንድ ጊዜ ከአንድ ሚስት በላይ ማግባትን ይፈቅዱ ነበር፡፡ ነገር ግን የአሜሪካ መንግስት ይህን ልምምዳቸውን እንዲተዉ ተጽዕኖ ስለአደረባቸው በ1890 ሰማያዊ ጋብቻ አለ በዚያ የአንድ ወንድ ብዙ ሚስት አንዲት ሴትም ብዙ ወንዶች ማግባት ይችላሉ በሚል ተክተውታል፡፡ ሞርሞኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ ጆሴፍ ስሚዝ ለፃፈው መጽሐፍ “the book of mormonism” ከፍተኛ ክብርና ሥፍራ ስለሚሰጡ እግዚአብሔር ለሰዎች የሰጠው የድኅነት መንገድ ከእነርሱ የተሠወረ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ርስት ያልታደሉ የጥፋት ልጆች ናቸውና ከእነዚህ ትምህርት መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ በተለይ ለወጣቱ ተስማሚ መስለው የሚታዩ ወጣቱን የሚያጓጓ ሐሳብ ይዘው በመቅረባቸው አደገኞች መሆናቸውን በመገንዘብ ወላጆች የልጆቻችሁን ውሎ እንድትከታተሉ አደራ እንላለን፡፡
ሞርሞኖች ስለ መንፈስ ቅዱስ ያላቸው አመለካከት ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነታ የራቀ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሰው ሁሉ ሕይወት እንጂ አካል ያለው አይደለም በማለት የመንፈስ ቅዱስን አምላክነት ይክዳሉ፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅድመ ዓለም የነበረ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር እርሱ ብቻ አንድ አምላክ እንደሆነ ይመሰክራል (ኢሳ. 43÷10) እግዚአብሔር አብ አምላክ መሆኑን (2ኛ ጴጥ. 1÷17) እግዚአብሔር ወልድ አምላክ ለመሆኑ (ዮሐ. 1÷1-14) እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አምላክ እንደሆነ (የሐዋ. 5÷3-4) ለአብነት ያህል ማየት ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የመጽሐፍ ቅዱስም ዋና ዓላማ ሦስቱ አካላት በአንድ ባሕርይ አንድ አምላክ እንደሆኑ ማሳየት ነውና ስለ እግዚአብሔር አምላክነት የሚጠራጠር ክርስቲያን እንደማይኖር እናምናለን፡፡ ስለዚህ ውድ አንባቢያን የመጽሐፍ ቅዱስን አስተምህሮ በመካድ እግዚአብሔርን ሰው ነው በማለት የሰይጣን ትምህርት የሚያስፋፉ የሞርሞኖችንና ጠቅላላ የመናፍቃን ክህደታችውን እና እንቅስቃሴው ለመግታት የሁላችንም ሃይማኖታዊ ግዴታም ስለአለብን የድርሻችንን እንወጣ በማለት ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ቀሪውን ከግብረ መንፈስ ቅዱስ መጽሐፍ ያንብቡ ይረዱ
ከአባ ሳሙኤል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ
አዲስ አበባ
Profile