Wednesday, 9 December 2015

ኅዳር 25 የቅዱስ መርቆሬዎስ በዓለ ዕረፍት

ኅዳር 25 የቅዱስ መርቆሬዎስ በዓለ ዕረፍት
ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
የዚኽ ቅዱስ ሰማዕት ወላጆቹ ክርስቲያኖች ሲኾኑ ስሙን ፒሉፓዴር ብለውታል ትርጓሜውም “የአብ ወዳጅ” ማለት ሲኾን በመንፈሳዊ ትምህርት አጠንክረው አሳድገውታል፤ “ወተውህቦ ኀይል ዐቢይ ለቅዱስ መርቆሬዎስ ወተሰምዐ ዜናሁ በኲሉ ወተለዐለ እምሰብአ ቤተ መንግሥት” ይላል ታላቅ የድል አድራጊነት ኀይል ተሰጥቶት ዜናው በኹሉ ቦታ ሲሰማ ከቤተ መንግሥት ሰዎችን ይልቅ ከፍ ከፍ ብሏል፤ በዚኽ ምክንያት በጊዜው በነበረው ንጉሥ በዳኬዎስ ዘንድ ባለሟልነት አግኝቷል፡፡ ከዚያም በሮም ላይ የበርበር ሰዎች ተነሥተው የዳኬዎስን መንግሥት ሊወጉት መጡ፤ እጅግ ብዙዎችም ነበሩና ንጉሡ እጅግ ፈራ፤ ቅዱስ መርቆሬዎስ ግን “እግዚአብሔር ያጠፋቸው ዘንድ አለውና አትፍራ” አለው፡፡
“ወእምዝ ርእዮ ቅዱስ መርቆሬዎስ ለመልአከ እግዚአብሔር በውስተ ቀትል ወሰይፍ በሊኅ ውስተ እዴሁ” ይላል፤ የእግዚአብሔር መልአክ በውጊያው ውስጥ የተሳለ ሰይፍ በእጁ ይዞ ተገልጦለት ሰይፉን በመስጠት “ጠላቶችኽን ድል ባደረግኽ ጊዜ ፈጣሪኽ እግዚአብሔርን ዐስበው” ብሎ ሰጥቶታል፤ አንዱ ራሱ ለውጊያ የያዘው ሰይፍ ኹለተኛም ከመልአኩ የተቀበለው ሰይፍ ነበርና በዚኽ ምክንያት “አበ አስይፍት” (የሰይፎች አባት) ተብሏል፡፡
ከዚኽ በኋላ ንጉሡ ዳኬዎስ ለጣዖታት ዕጣን ሊያቀርብና በዓልን ሊያደርግ ወደዶ በዓልን ባደረገ ጊዜ ቅዱስ መርቆሬዎስ ግን ከርሱ ጋር አልወጣም፤ በዚኽ ምክንያት ንጉሡ አስጠርቶት “ለአማልክት ዕጣን ለማሳረግ ከእኔ ጋር ያልወጣኽ የእኔንስ ፍቅር ለምን ተውኽ” ብሎ ጠየቀው፤ በዚኽ ጊዜ ቅዱስ መርቆሬዎስ በንጉሡ ፊት ትጥቁንና ልብሱን ወርውሮ “እኔ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክደውም ለረከሱ ጣዖታትም አልሰግድም” በማለት መለሰለት፡፡
ንጉሡም እጅግ ተቈጥቶ ርጥብ በኾኑ የሽመል በትሮችና እንዲደበደብና ከላም ቆዳ በተሠራ ጅራፍ እንዲገረፍ አዘዘ፡፡ ቅዱስ መርቆሬዎስ ካለው ተወዳጅነት የተነሣ ሰዎች እንዳይነሡበት በመፍራት የቀጶዶቅያና የእስያ ክፍል ወደ ኾነች ወደ ቂሳርያ በብረት ማሠሪያ ታሥሮ እንዲላክ አድርጎ ብዙዎች ሥቃያትን አደረሱበት፤ ከዚያም ኅዳር ኻያ ዐምስት ክብር ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦለት ስን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ የምሕረትን ቃል ኪዳን ከገባለት በኋላ ራሱን በተሳለ ሰይፍ ቈርጠውት የሰማዕትነትን አክሊልን ተቀዳጀ፤ የሰማዕታት ዘመን ካለፈም በኋላ በመላው ዓለም አብያተ ክርስቲያናት ታንጸውለታል፤ በተለይ በእስክንድርያ እና በኢትዮጵያ በስፋት ይከበራል፡፡
ኢትዮጵያዊዉ ሊቅ አርከ ሥሉስም የቅዱስ መርቆሬዎስን ተጋድሎ በማዘከር፡-
“ሰላም ለከ መርቆሬዎስ ዘሮም
መስተጽዕነ ፈረስ ጸሊም
አመ አንደዱ ታሕቴከ ውሉደ መርገም
እምቅሡፍ አባልከ እንተ ውኅዘ ደም
አርአያ ዝናም ብዙኅ አጥፍኦ ለፍሕም”
(በጥቊር ፈረስ ላይ የተቀመጥኽ የሮም ሰው ለኾንኸው ለመርቆሬዎስ ሰላምታ ይገባኻል፤ የመርገም ልጆች ከሥርኽ እሳትን ባነደዱ ጊዜ ከተገረፈው ሰውነትኽ በብዙ ዝናብ አምሳል የፈሰሰው ደም ፍሙን አጠፋው) እያለ መስክሮለታል፡፡
ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በተአምኆ ቅዱሳን መጽሐፉ ላይ፡-
“ሰላም ለመርቆሬዎስ ሰማዕት ንጹሕ ድንግል
ፈጻሜ ቃለ ወንጌል”፡፡
(የወንጌል ቃል የፈጸመ ለኾነ ለንጹሕ ድንግል ሰማዕት መርቆሬዎስ ሰላምታ ይገባል) በማለት አመስግኖታል፡፡
ምንጭ፡- አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ የደረሰው ተአምኆ ቅዱሳን መጽሐፍ ንባቡና ትርጓሜው የሚለው መጽሐፌ
ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
የቅዱስ መርቆሬዎስ በረከት ይደርብን፡፡

No comments:

Post a Comment