Saturday, 2 April 2016

>+"+ እንኩዋን ለጻድቁ አባታችን "ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት" ዓመታዊ በዓለ-ፅንሰት በሰላም አደረሳችሁ +"+
+*" ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ "*+
=>ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ዐይን ናቸው:: ጻድቁን መንካት የቤተ ክርስቲያንን ዐይኗን መጠንቆል ነው::
+ተክለ ሃይማኖት እንደ ሊቃውንት ሊቅ: እንደ ሐዋርያት ሰባኬ ወንጌል: እንደ ሰማዕታት ብዙ ግፍ የተቀበሉ: እንደ ጻድቃን ትሩፋት የበዛላቸው: እንደ ደናግል ንጽሕናን ያዘወተሩ: እንደ ባሕታውያን ግኁስ: እንደ መላዕክትም ባለ ክንፍ አባት ነበሩ:: ለዚሕ ነው ተክለ ሃይማኖትን የኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ዐይኔ የምትላቸው::
*ልደት*
=>መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ: ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው:: እርሱ በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::
+በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል: ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በሁዋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል::
+ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የጸነሱት መጋቢት 24 ቀን በ1206 ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታሕሳስ24 ቀን በ1207 ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::
*ዕድገት*
=>የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል:: ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት: ሐዲሳትን) ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁናም ከወቅቱ ዻዻስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል::
*" መጠራት "*
=>አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑ በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ::
+የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:: "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን:: ከዚህ በሁዋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በሁዋላ ሰዓትን አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::
*" አገልግሎት "*
=>ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዻዻሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ:: ያን ጊዜ ኢትዮዽያ 2 መልክ ነበራት::
+1ኛ ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::
+2ኛው ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር::
+ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን (ጠንቁዋዮችን) አጥፍተዋል::
*" ገዳማዊ ሕይወት "*
=>ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮዽያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል:: እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ3 ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል::
+እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለ12 ዓመታት: በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለ7 ዓመታት: በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለ7 ዓመታት: በአጠቃላይ ለ26 ዓመታት አገልግለዋል::
+በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በሁዋላም ወደ ምድረ ሽዋ (ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ22 ዓመታት ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም 6 ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል::
*ስድስት ክንፍ*
=>ኢትዮዽያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮዽያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::
+የወቅቱ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በሁዋላ ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር::
+ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:-
-በቤተ መቅደስ ብስራቱን
-በቤተ ልሔም ልደቱን
-በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
-በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
-በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::
+የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ::
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ ተክልየን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው::
+በዚያም:-
*የብርሃን ዐይን ተቀብለው
*6 ክንፍ አብቅለው
*የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
*ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
*ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
*ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
*"ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::
*ተአምራት*
=>የተክልየ ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው::
*ሙት አንስተዋል
*ድውያንን ፈውሰዋል
*አጋንንትን አሳደዋል
*እሳትን ጨብጠዋል
*በክንፍ በረዋል
*ደመናን ዙፋን አድርገዋል::
+ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕጻናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና::
*ዕረፍት*
=>ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው መከራን በብዙ ተቀብለው: እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው: በተወለዱ በ99 ዓመት: ከ8 ወር: ከ1 ቀናቸው ነሐሴ 24 ቀን በ1306 ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: 10 ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::
=>አምላከ ቅዱሳን ከጻድቁ አባታችን በረከትን ይክፈለን::
=>መጋቢት 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት (ጽንሰቱ)
2.ቅዱሳን እግዚእ ኃረያና ጸጋ ዘአብ
3.ቅዱስ አባ መቃርስ ሊቀ ዻዻሳት
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ አጋቢጦስ ጻድቅ
2.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
3.ቅዱስ ሙሴ ፀሊም
4.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
5.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
6."24ቱ" ካኅናተ ሰማይ
=>+"+ በረከት በጻድቅ ሰው ራስ ላይ ነው:: የኀጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል:: የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው:: የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል:: +"+ (ምሳሌ 10:6)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

No comments:

Post a Comment