ነገረ ማርያም፡- ክፍል - ፲፯፤
ቅዱስ ዳዊት፡- የእመቤታችንን የቅድስት
ድንግል ማርያምን፡- ሥርወ ልደት ሲናገር፥ “መሠረቶቿ የተቀደሱ
ተራሮች ናቸው፤” ብሎአል። መዝ፡፹፮፥፩። እግዝአብሔር፡- አምልኰት እንዲፈጸምባቸው፥ መሥዋዕት እንዲቀርብባቸ ው፥ በረድኤትም እንዲገለጥባቸው
የመረጣቸውን ተራሮች እንደቀደሳቸው፡- ምስክሩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በሕገ ልቡና ዘመን፡- እግዚአብሔር፡- በሲና ተራራ ራስ፥ በእሳት ነበልባል አምሳል
በረድኤት ተገልጦ፥ የሲናን ሐመልማል ሳያቃጥላት ተዋሕዶ፥ ወዳጁን ሙሴን ባነጋገረው
ጊዜ፥ “ወደዚህ አትቅረብ፤ አንተ የቆምህባት ስፍራ(ተራራዋ) የተቀደሰች ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ (አውልቅ)” ብሎታል። ዘጸ፡፫፥፭። ሙሴም፡- የእግዚአብሔርን ቃል
ሰምቶ፥ የተቀደሰችውን ተራራ አክብሮ ጫማውን አውልቆአል።
የእስራኤልን ከግብፅ የባርነት ቤት መውጣት ስንመለከት፥ የነቢያት አለቃ ሙሴ፡- በእግዚአብሔር ኃይል
በብዙ ተአምራት ሕዝቡን ከግብፅ አውጥቶ እየመራ፥ በሦስተኛው ወር ሲና ምድረ በዳ አደረሳቸው፥ ይላል። እግዚአብሔርም፡- በተቀደሰችው ተራራ
ላይ ተገልጦ ሙሴን አነጋገረው። ሙሴም፡- ከእግዚአብሔር የሰማውን ለሕዝቡ ነገራቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን፡- “ከአንተ ጋር ስነጋገር
ሕዝቡ እንዲሰሙ፥ ደግሞም ለዘለዓለም እንዲያምኑብህ እነሆ በከባድ ደመና እመጣለሁ፤” አለው። በዚህም፡- ቅዱሳን በአማላጅነታቸው፥ በቃል ኪዳናቸው መታመናቸው፥
በአጸደ ሥጋ ብቻ ሳይሆን ለዘለዓለም መሆኑን መስክሮላቸዋል። በዚህን ጊዜ ሙሴ፡- ሕዝቡ ሁሉ አንድ አፍ
ሆነው (እንደ አንድ ልብ መካሪ፥ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው) “እግዚአብሔር ያለውን
ሁሉ እናደርጋለን፤” ማለታቸውን፥ ለእግዚአብሔር ነገረው። እግዚአብሔርም፡- “ወደ ሕዝቡ ሂድ፥
ዛሬና ነገ ቀድሳቸው፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፤ በሦስተኛው ቀን ሕዝቡ
ሁሉ ሲያዩ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ይወርዳልና ለሦስተኛው ቀን ይዘጋጁ። ወሰንም ለሕዝቡ በዙሪያው
አድርግላቸው፡- ወደ ተራራው እንዳትወጡ፥ ጫፉንም እንዳትነኩ ተጠንቀቁ፥ ተራራውንም የነካ ፈጽሞ
ይሞታል፤” አለው። በተባለውም ቀን በረድኤት ተገለጠ።” ነጐድጓድና መብረቅ
ከባድም ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምፅ በተራራው ላይ ሆነ፤ በሰፈሩም የነበሩት
ሕዝብ ሁሉ ተንቀጠቀጡ፤” ይላል።” ዘጸ፡፲፱፥፩-፳፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ሙሴም እጅግ እፈራለሁ፥
እንቀጠቀጥማለሁ እስኪል ድረስ፥ የሚታየው እጅግ የሚያስፈራ ነበረ፤” በማለት አድንቆ የተናገረው
ይኽንን ነው። ዕብ፡፲፪፥፳፩። እግዚአብሔር፡- ሙሴ የሚቆምበትን እና ሕዝቡ የሚቆሙበትን ስፍራ፡- ወሰን(ክልል) አበጅቶላቸው
ነበር። ከዚህም፡- የቅድስናውን ስፍራ እንዴት አድርጐ እንደ አከበረውና እንደ አስከበረው እንረዳለን። በተጨማሪም ካህናት
ብቻ የሚቆሙበትና የሚገቡበበት ስፍራ መወሰኑን እናስተውላለን። ይህም ለአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን፡- ሥርዓተ ቤተ መቅደስ
ጥሩ ምሳሌ ነው። ልዩነቱ፡- በብሉይ ኪዳን በረድዔት ሲሆን በአዲስ ኪዳን ግን በደሙ ፈሳሽነት ነው። በሕገ ኦሪት ደግሞ፥ በሙሴ እግር ለተተካ
ለኢያሱ ወልደ ነዌም፡- በኢያሪኮ አጠገብ፥ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦለት፥ “እኔ የእግዚአብሔር
ሠራዊት አለቃ ሆኜ(የሆንኩ) አሁን መጥቼአለሁ።” ባለው ጊዜ፥ ወደ ምድር ተደፍቶ ከሰገደለት በኋላ፥ “ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው
ምንድነው?” ሲል ጠይቆአል። ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልም፡-”አንተ የቆምህበት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን
አውልቅ፤” ብሎታል። ኢያሱም፡- የመልአኩን ቃል ሰምቶ፥ የተቀደሰውንም ተራራ
አክብሮ የታዘ ዘውን ፈጽሞአል። ኢያ፡፭፥፲፫። በአዲስ ኪዳን፡- በኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ደም ወደ ተቀደሰች ተራራ (ወደ ቤተክርስቲያን)
ጫማ አውልቀን ለመግባታችን መሠረቱ ይህ ነው። ከፍ ብሎ የእግዚአብሔር ቀጥሎም የመላእክት ትእዛዝ ነው። በሌላ በኵል ደግሞ
ተራሮች “የተቀደሰ፥የተቀደሰች” እየተባሉ በወንድም በሴትም አንቀጽ የተጠሩበት ምክንያት፥ ለቅዱሳን አበውም ለቅዱሳት
አንስትም ምሳሌዎች በመሆናቸው ነው።
ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ ደግሞ፥ ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- በደብረ ታቦር፡- በቅዱሳን ነቢያቱ በሙሴና በኤልያስ ፊት፥ እንዲሁም በቅዱሳን
ሐዋርያቱ በጴጥሮስ በዮሐንስና በያዕቆብ ፊት፥ ግርማ መለኰቱን፣ ክብረ መንገሥቱን አቅማቸው በሚችለው መጠን በጥቂቱ ገልጦላቸዋል። እነርሱም በመንፈስ
ቅዱስ ባልታደሰ ሰውነት ስለነበሩ ፍግም ፍግም እያሉ ወድቀዋል። ማቴ፡፲፯፥፩። ይኽንንም፡-
የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ፡-“የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት
የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ።ከገናናው ክብር
(ከባህርይ አባቱ ከአብ)፡-
በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን
ተቀብሏልና፤ (ከአብ
ጋር ትክክል የሆነ ክብሩን ራሱ አብ መስክሮለታልና)፤ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ሰማን።”
በማለት አስተምሮበታል።
፪ኛ፡ጴጥ፡፩፥፲፮።
ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ የተቀደሱ ተራራች ያላቸው
ወይም በተቀደሱ ተራሮች የመሰላቸው፥ ቅዱሳን እና ቅዱሳት የሆኑትን የእመቤታችንን የሥጋ ዘመዶች ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፡- “የድንግሊቱም
ስም ማርያም ነበረ፤“ ይለናል እንጂ፥የእናትና የአባቷን፡- እንኳን ታሪካቸውን፥ ስማቸውን እንኳ አይነግረንም። መቼም አለ እናትና
አለ አባት አልተፈጠረችም።ይኽንን የምናገኘው ከአዋልድ መጻሕፍት (የመጽሐፍ ቅዱስ ልጆች ከሚባሉ መጻሕፍት) ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ
ልጆች የተባሉበት ምክንያት፡- በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው የተጻፉ በመሆናቸውና መጽሐፍ ቅዱስንም ይበልጥ ስለሚያብራሩ ነው።
አንድም፡- አባት በልጆቹ እንደሚታውቅ መጽሐፍ ቅዱስም ይበልጥ በእነርሱ ስለሚታወቅ ነው።አዋልድ መጻሕፍት ባይኖሩ ኖሮ የመጽሐፍ
ቅዱስ መልእክት ጐዶሎ ይሆን ነበር።
የድንግል ማርያም ሥርወ ልደት፤
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም፡- በአባቷ በኵል ከንጉሡ ከቅዱስ ዳዊት ወገን ስትሆን፥ በእናቷ በኵል ደግሞ ከሊቀ ካህናቱ ከአሮን ወገን
ናት። ይህ የሚያሳየን፥ እመቤታችን፡- ከቤተ መንግሥትም ከቤተ ክህነትም ወገን መሆኗን ነው።ምክንያቱም፡- በሚደነቅ እንጂ በማይመረመር
በመንፈስ ቅዱስ ግብር፥ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ፥ በተዋህዶ ሰው ሆኖ፥ ከእርሷ የሚወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ንጉሥም
ካህንም ነውና። በባህርይ አባቱ በአብ በኵል፥ በንጉሡ በዳዊትም በኵል ንጉሥ የንጉሥ ልጅ ነው። በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደችው
ድንግል ማርያምም፡-በምድርም በሰማይም ንግሥት ናት። “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች፤” ይላል።
መዝ፡፵፬፥፱። የምድር ነገሥታት ግብር አስገባሪዎች እርሱንም፡- እንደ ሰዉ ሊያስገብሩት በመጡ ጊዜ፥ ቅዱስ ጴጥሮስ፡-“አዎን ይገብራል፤”
ብሎ ነበር። ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ኢየሱስ አስቀድሞ፡- “ስምዖን ሆይ ምን ይመ ስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥና ግብር ከማን
ይቀበላሉ? ከልጆቻቸው ነውን ወይስ ከእንግዶች?” ሲል ጠየቀው። ቅዱስ ጴጥሮስም፡- “የነገሥታት ልጆችማ ራሳቸው ነገሥታት ናቸው፥
ያስገብራሉ እንጂ አይገብሩም፥ የሚገብሩት እንግዶች ናቸው፤” አለ። በዚህን ጊዜ ጌታችን፡- “እንኪያስ ልጆቻቸው ነጻ ናቸው፤” አለ።
ይህንንም ያለው፡- ቅዱስ ጴጥሮስ ቸኵሎ፥ “አዎን ይገብራል፤” በማለቱ ነው። ነገር ግን ግብር ለመሰብሰብ የመጡ ሰዎች በዚህ ምክንያት
እንዳይሰናከሉ ሲል፥ በእርሱ ትእዛዝ፥ ቅዱስ ጴጥሮስ በአጠመደው ዓሣ ሆድ ውስጥ በተአምር የተገኘውን ሁለት እስታቴር፥ እንዱን በራሱ
ስም ሁለተኛውን ደግሞ በቅዱስ ጴጥሮስ ስም ገብሮአል።በዚህም፡- በሰውነቱ ሲገብር፥ በአምላክነቱ፣ በንጉሥነቱ ደግሞ፡- ባሕርን ዓሣ፥
ዓሣን ደግሞ እስታቴር አስገብሮአል። እዚህ ላይ በሰውነቱ፥ በአምላክነቱ ማለታችን፥ መለኰትንና ትስብእትን ነጣጥለን አይደለም፤ ሁሉም
ነገር የሆነው በተዋህዶ ነው።ኢየሱስ ክርስቶስ፡- በተዋህዶ፡- ከሁለት አካል አንድ አካል፥ ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ ሆኖአልና።
ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ፡-የጌታችንን የዘር ሐረግ
ሲጽፍ፥“የዳዊት ልጅ፥ የአብርሃም ልጅ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ መጽሐፍ፤” በማለት፡- ከአበ ብዙኃን ከአብርሃም እና ከንጉሡ
ከዳዊት ወገን መሆኑን ተናግሮአል። ማቴ፡፩፥፩።በመዋዕለ ሥጋዌውም ሁለቱ ዓይነ ስዉራን እና ከነዓናዊቱ ሴት፥ ተአምራቱን ያየ ሕዝብም፡-“የዳዊት
ልጅ፤” ብለውታል።ማቴ፡፱፥፳፯፤፲፪፥፳፫፤፲፭፥፳፪። ይኽንን ስም ያገኘው በእመቤታቸን በኵል ነው። እርሱም ራሱ ፈሪሳውያንን፡- “ስለ
ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል፥ የማንስ ልጅ ነው?” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ፥ “የዳዊት ልጅ ነው፤” ብለውት ነበር። በዚህን ጊዜ፡- “እንኪያስ
ዳዊት፡- ጌታ (እግዚአብሔር አብ)፥ ጌታዬን (እግዚአብሔር ወልድን) ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ
አለው ሲል እንዴት በመንፈስ (በመዝሙረ ትንቢት) ጌታ (ፈጣረዬ፣አምላኬ) እያለ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ (ፈጣሪ) ብሎ ከጠራው እንዴት
ልጁ ይሆናል ?” በማለት መልስ አሳጥቶአቸዋል። ማቴ፡፳፪፥፵፩።
ቅዱስ ዳዊት፡-የፈጣሪ አባት የመባል ክብር ያገኘው፥ከእርሱ
ወገን በተወለደች፥ በልጁ በድንግል ማርያም በኵል ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- ወደ ኋላ እሰከ አዳም ድረስ ያሉትን
አባቶች ያስከበረች፥ ወደፊትም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚነሡትን የምታስከብር ክብርት ልዕልት ናት። አባ ሕርያቆስ፡- “የቀደሙ
አባቶች ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገሩብሽ ድልድይ ሆይ! ከምድር እስከ ሰማይ የምትደርሽ መሰላል (አስቀድሞ ያዕቆብ በራዕይ ያየሽ
አማናዊት መወጣጫ) ሆይ! የፍጥረት ሁሉ መጀመሪያ በአንቺ ታደሰ።” በማለት ያመሰገናት ለዚህ ነው።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡-
መሥዋዕት፥ መሥዋዕት አቅራቢ እና መሥዋዕት ተቀባይ፥ማለትም፡- በአንድ ጊዜ ሦስቱንም የሆነ ሊቀ ካህናት ነው። ቅዱስ ዳዊት፡- “አንተ
እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘለዓለም ካህን ነው፤” በማለት አስቀድሞ የተናገረው ለዚህ ነው። መዝ፡፻፱፥፬፣ ዕብ፡፭፥፮። ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስም፡- “እንግዲህ ወንድሞቻችን ሆይ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ወደ መቅደስ ለመግባት ባለሟልነት አለን። በሥጋው መጋረጃ
በኵል የሕይ ወትንና የጽድቅን መንገድ ፈጽሞ አድሶልናልና። በእግዚአብር ቤት ታላቅ ካህን አለን።” ብሎአል። ዕብ፡፲፥፲፱።
ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና፤
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም፡- አባቷ ቅዱስ
ኢያቄም ከንጉሡ ከዳዊት ወገን ነው፥ እናቷ ቅድስት ሐና ደግሞ ከሊቀ ካህናቱ ከአሮን ወገን ናት። ለዚህም፡- በነገረ
ማርያም ተጽፎ፥
መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ የሚያደርገውን የእመቤታችንን ታሪክ በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ፡- ነገረ
ክርስቶስን እንኳ አሟልቶ
አይነግረንም።ይኸውም፡- ከቅዱሳን ሐዋርያት በኋላ የሚነሡ ሊቃውንት የተቀረውን ጽፈው በረከት እንዲያገኙ ነው።
ለምሳሌ፡- መጽሐፍ
ቅዱስ፡- የጌታችንን ከግብፅ ስደት መመለስ እና በናዝሬት ማደግ፥ በአሥራ ሁለት ዓመቱም በዓል ለማክበር ወደ
ኢየሩሳሌም መሄዱን
ይነግረናል እንጂ፥ እስከ አሥራ ሁለት ዓመቱ ምን እንደሠራ አይነግረንም። ከዚያም በኋላ ሠላሳ ዓመት ሞልቶት
እስኪጠመቅ ድረስ ያለውን
ታሪኩን አልመዘገበልንም። ይህም የጌታችንን የነገረ ድኅነት ታሪክ ጐደሎ ያደርግብናል። ማቴ፡፩፥፳፫፣ ሉቃ፡፪፥፵፩።
ቅዱስ ዮሐንስ
ወንጌላዊ፡- “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ
ባልበቃቸውም
ነበር ይመስለኛል።” ብሎአል። እንዲህም ማለቱ፡- እነርሱ በቃል ያስተማሩት፥ ነገር ግን በጽሑፍ ያላስቀመጡት ብዙ
ነገር መኖሩን
እና ተከታዮቻቸው፡- በአፍም በመጽሐፍም የተማሩትን አስፋፍተው እንደሚጽፉ ለመግለጥ ነው። ዮሐ፡፳፩ ፥፳፭።
ነገረ ማርያም ለነገረ ክርስቶስ መነሻ መሠረት በመሆኑ
የግድ መብራራት አለበት። ምናልባት ከክርስቶስ ከጀመርን ይበቃል፥ የሚሉ ይኖራሉ፤ በእርግጥም አሉ። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ፥ ቅዱስ
ማቴዎስ ወንጌላዊ፡- ከአብርሃም እስከ ክርስቶስ ያለውው ሠላሳ ስድስት ትውልድ ለመቍጠር አይደክምም ነበር። ማቴ፡፩፥፩-፲፮። ቅዱስ
ሉቃስም፡- ከክርስቶስ ጀምሮ ወደ ላይ እስከ አዳም ድረስ ሰባ ስምንት ትውልድ ለመቍጠር አይቸገርም ነበር። በመጨረሻም አዳምን የእግዚአብሔር
ልጅ ብሎታል። ሉቃ፡፫፥፳፫-፴፰። በመሆኑም ነገረ ማርያምን እንደሚከተለው በዝርዝር እንመለከታለን። ቴክታና በጥሪቃ የሚባሉ፥ እጅግ
ባዕለ ጸጋ የሆኑ ባልና ሚስት ነበሩ። ባዕለጸግነታቸውም የብር፥ የወርቅ ፥የወንድ እና የሴት አገልጋዮች፥የፈረስና የበቅሎ፥ የላም፣
የበግና የፍየል ነበር። በአጠቃላይ ይህ ቀራቸው የማይባሉ፥ ሁሉ የተሟላላቸው ሰዎች ነበሩ።በጥሪቃ፡- ከዕለታት በአንዱ ቀን፥ ከዕቃ
ቤቱ ገብቶ ስፍር ቍጥር የሌለውን ሀብቱን ካየ በኋላ፥ ወራሽ ልጅ ስለሌው እጅግ አዘነ። ባለቤቱን ቴክታንም፡- “ከአንቺ በቀር የምወደው
እንደሌለኝ አምላከ እስራኤል ያውቀዋል፥ ነገር ግን ልጅ የለንም፤”አላት። እርሷም፡- “ለልጅማ እኔ ምንድር ነኝ? ወደ እግዚአብሔር
እናመልክት እንጂ፤” አለችውና በጾም በጸሎት ወደ እግዚአብሔር አመለከቱ።
እግዚአብሔር የሁለቱንም ቅንንት አይቶ፥ ለቴክታ በህልም ገለጠላት። ነጭ እንቦሳ ከማኅጸንዋ
ስትወጣ ፥እንቦሳዋም እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ሲደርሱ፥ ስድስተኛይቱ እንቦሳ ጨረቃን ስትወልድ፥ ጨረቃይቱም ፀሐይን ስትወልድ
አይታ ለበጥሪቃ ነገረችውና ወደ መፈክረ ሕልም (ሕልም ወደሚፈታ ሰው) ላከችው። ሕልም ፈቺውም፡- በእንቦሳ ምሳሌ ያየችው ልጅ መሆኑን
እና ደግ ልጅ እንደሚወልዱ፥ “የጨረቃንና የፀሐይን ምሥጢር ግን፡- ጊዜ ይፍታው እንጂ ለእኔ አልተገለጠልኝም፤” አለው። ይኽንንም
ለባለቤቱ ወስዶ ነገራት። ከዚህ በኋላ ቴክታ ፀንሳ ወለደችና ስሟን ሄሜን አለቻት፥ ሄሜን ደርዲዕን ወለደች፥ ደርዲዕ ቶናህን ወለደች፥
ቶናህ ሲካርን ወለደች፥ ሲካር ሄርሜላን ወለደች፥ ሄርሜላም ቅድስት ሐናን ወለደች። ቅድስት ሐና ደግሞ ከነገደ ይሁዳ የሆነውን ቅዱስ
ኢያቄምን አግብታ ለጊዜው በመሀንነት ኖረች።ነገሥታት የሚሾሙት ከነገደ ይሁዳ ነበር፤ ምክንያቱም፡- ያዕቆብ አሥራ ሁለት ልጆቹን
በመረቀ ጊዜ፥ “ይሁዳ፥ ወንደሞችህ አንተን ያመሰግኑሃል፤ እጅህ በጠላቶችህ ደንደስ ላይ ነው፤ የአባትህ ልጆች በፊትህ ይሰግዳሉ።
ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው፤ልጄ ሆይ ከአደንህ ወጣህ፤ እንደ አንበሳ አሸመቀ፥ እንደ ሴት አንበሳም አደባ፤ ያስነሣውስ ዘንድ ማን
ይችላል? በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፥ የገዥም ዘንግ ከእግሮቹ መካከል፥ ገዥ የሆነው እስከሚመጣ ድረስ፤ የአሕዛብ መታዘዝም
ለእርሱ ይሆናል፤”ብሎ ነበር። ዘፍ፡ ፵፱፥፰።
ነገረ ማርያም፡- ክፍል - ፲፰፤
ከካህናት ወገን የምትሆን ቅድስት ሐና፥ ከነገደ ይሁዳ ከሆነ
ከቅዱስ ኢያቄም ጋር በተቀደሰ ትዳር ሲኖሩ ልጅ አልነበራቸውም። እንደ አብርሃም እና ሣራ፥ እንደ ዘካርያስ እና
ኤልሳቤጥ ከመውለድ እጅግ ዘግይተው ነበር። ሁለቱም እግዚአብሔር በሠራው ሕግ ፀንተው የሚኖሩ፥ እግዚአብሔርም የሚወዳቸው
ደጋጎች ነበሩ። ልጅ ስለ አልነበራቸው ኑሮአቸው የሐዘን እና የትካዜ ነበር። ዕለት ዕለትም ወደ
ቤተ መቅደስ እየሄዱ ልጅ እንዲሰጣቸው ልመናቸውን ከዕንባ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ያቀርቡ ነበር። ከገንዘባቸውም ከፍለው
ለድሆች እና ለጦም አዳሪዎች፥ ለቤተ እግዚአብሔርም ይሰጡ ነበር። ይኽንንም
ያደርጉ የነበረው፥
እግዚአብሔር በትክክል ልጅ እንደሚሰጣቸው ፈጽመው በማመን ነበር። “ለሚያምን ሁሉ ይቻላል፤” ማር፡፱፥፳፫።
በትዳር ሕይወት ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው።
“እግዚአብሔርን የሚፈሩት ሁሉ፥ በመንገዶቹም (በሕጉ በትእዛዙ) የሚሄዱ ምስጉኖች ናቸው። የድካምህን ፍሬ ተመገብ (ትመገባለህ)፤
ሚስትህ በቤትህ እልፍኝ ውስጥ እንደሚያፈራ ወይን ናት፤ ልጆችህ በማዕድህ ዙሪያ እንደ ወይራ ቡቃያ ናቸው። እነሆ እግዚአብሔርን
የሚፈራ ሰው እንዲህ ይባረካል።” ይላል። መዝ፡፻፳፯፥፩-፬። አበ ብዙኃን አብርሃም፡- እግዚአብሔር፡- “አብራም ሆይ፥ አትፍራ፤
እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤ ዋጋህም እጅግ ታላቅ ነው።” ባለው ጊዜ፥ “አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ ምንን ትሰጠኛለህ? እኔም ያለ ልጅ
እሄዳለሁ፤”ያለው፥ ጸጋ እግዚአብሔር የሆነ ልጅ ለምን ይቀርብኛል ብሎ ነው። እግዚአብሔርም፡- አብርሃም ልጅ እንደሚወልድ፥ ዘሩም
እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደሚበዛ ነግሮታል። ዘፍ፡፲፭፥፩-፮። በኋላም ቅድስት ሥላሴ በአብርሃም ድንኳን በእንግድነት ተገኝተው፥
“የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ወንድ ልጅ ታገኛለች፤” ብለውታል። አብርሃምና ሣራ
በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር፥ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር። ዘፍ፡፲፰፥፩-፲፭። “እግዚአብሔርም
እንደተናገረው ሣራን አሰበ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ለሣራ አደረገላት።ሣራም ፀነሰች፥ እግዚአብሔርም በተናገረው ወራት ለአብርሃም
በእርጅናው ወንድ ልጅ ወለደችለት። አብርሃምም የተወለደለትን ሣራ የወለደችለትን የልጁን ስም ይስሐቅ ብሎ ጠራው፤” ይላል። ዘፍ፡፳፩፥፩-፫።
ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደ ሆነ ስለ ቈጠረች፥ ሣራ ራስዋ ደግሞ ዕድሜዋ ካለፈ በኋላ ዘርን
ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች። ስለዚህ ደግሞ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደማይቈጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ
የነበሩት የሞተን ሰው እንኳ ከመሰለው ከአንዱ ተወለዱ።” በማለት አድንቆአል። ዕብ፡፲፩፥፲፩-፲፪።
የነቢዩ የሳሙኤል እናት ሐና መጽናናት እስከ ሚያቅታት
ድረስ ዕንባዋን ያፈሰሰችው፥ የጾመችው እና የጸለየችው ስለ ልጅ ነበር። ሐና፡- ሴሎ ወደሚገኘው ወደ እግዚአብሔር ቤት ሄደች፥ በእግዚአብሔር
ፊት ልመናዋን አበዛች፥ ድምፅዋ ሳይሰማ ከንፈሯን ታንቀሳቅስ፥ በልቧም ትናገር ነበር፤ ሊቀ ካህናቱ ዔሊም፡- የስካር መንፈስ መስሎት፥
“የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አርቂው፤” አላት። ሐናም፡- “ጌታዬ ሆይ፥ አይደለም፥ እኔስ ልብዋ ያዘነባት ሴት ነኝ፤ ጠጅና ሌላ የሚያሰክር
ነገር አልጠጣሁም፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ነፍሴን አፈሰስሁ፤ ኀዘኔ እና ጭንቀቴ ስለ በዛ እስከ አሁን ተናግሬአለሁና ባሪያህን
እንደ ምናምንቴ ሴት አትቍጠረኝ፤” ብላ መለሰችለት። ዔሊም የችግሯን ክብ ደት ተገንዝቦ፡-” በደኅና ሂጂ፥የእስራኤልም አምላክ የለመንሽውን
ልመና ይስጥሽ፤” ብሎ መረቃት። እርሷም፡- “በፊትህ ሞገስ ላግኝ፤” አለችው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በፊትዋ ላይ ኀዘን አልታየም፥
እግዚአብሔርም አሰባትና ወንድ ልጅ ወለደች። “ከእግዚአብሔር ለምኜ አገኘሁ፤” ስትል፥ ስሙን፡- “ሳሙኤል” አለችው። ሦስት ዓመት
ሲሞላውም ለእግዚአብሔር ሰጥታው በእግዚአብሔር ቤት አደገ፥ ታላቅ ነቢይም ሆነ። ፩ኛ፡ሳሙ፡፩፥፩-፳፰።
ካህኑ ዘካርያስ እና ኤልሳቤጥም ፈጽመው እስከሚያረጁ
ድረስ የጸለዩት ስለ ልጅ ነበር። “ሁለቱም በጌታ ትእዛዝ እና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ።
ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም፤ሁለቱም በዕድሜአቸው አርጅተው ነበር፤” ይላል። የመውለጃ ዘመናቸው ካለፈም በኋላ
ጸሎታቸውን አላቋረጡም ነበር።ጻድቁ ካህን ዘካርያስ በቤተ መቅደስ ሲያገለግል፥ በመሠዊያው በስተ ቀኝ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል
ተገለጠለት።ዘካርያስ፡- ልቡ ፈራ፥ ኅሊናው ደነገጠ፥ ጉልበቱ ተንቀጠቀጠ። መልአኩም፡- “ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፤
ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንደ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ፤” አለው። ለጊዜው፡- “እኔ ሽማግሌ ነኝ፥ ሚስቴም በዕድሜዋ
አርጅታለች፥ ይህን በምን አውቃለሁ? (ምልክት ስጠኝ )፤” አለ። መልአኩም፡- “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፥
እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድ ሰብክልህ ተልኬ ነበር፤ እነሆም በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚሆን
ድረስ ድዳ ትሆናለህ፥ መናገርም አትችልም፤” አለው።እንደተባለውም ሆነ፥ ከዚህም በኋላ ኤልሳቤጥ ፀነሰች። እርሷም፡- “ነቀፌታዬን
ከሰው መካከል ያስወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጎልኛል፤” ስትል ራስዋን ለአምስት ወራት ሰወረች። ጊዜው
ሲደርስም መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስን ወለደች፥ የዘካርያስም አንደበት ተፈታ። ሉቃ፡፩፥፭ -፳፭፣፶፭። በዘመነ ኦሪት ልጅ አለመውለድ
ያስነቅፍ ነበር።
ቅዱስ ኢያቄም እና ቅድስት ሐናም ትልቁ ሐዘናቸው
ልጅ ማጣታቸው ነበር። ወደ ተክል ቦታ ገብተው ሲጸልዩ፥ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ደስ ብሎአቸው ሲጫወቱ አይተው በራሳቸው አዘኑ፤ ኀዘናቸውም
ፍጹም እና ከባድ ስለ ነበር አንቀላፍቶአቸው ተኙ። በህልማቸውም ምሥጢሩ አንድ የሆነ የተለያየ ነገር አዩ። ቅዱስ ኢያቄም፡- ነጭ
ርግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ ወርዳ ከቅድስት ሐና ራስ ላይ ስታርፍ፥ በቀኝ ጆሮዋም ገብታ ከማኅፀንዋ ውስጥ ስትተኛ አየ። ቅድስት
ሐናም በበኵሏ፡- ቅዱስ ኢያቄምን ነጭ ጸምር ሲያስታጥቁት፤በትሩም
ለምልማ፣ አብባ ስታፈራ፥ ታላቅም ዛፍ ስትሆን፥ከጥላዋ ስርም ብዙዎች ሲጠለሉ እና ፍሬዋን ሲመገቡ አየች። ያዩትንም ከተጨዋወቱ በኋላ
ወደ መፈክረ ሕልም ዘንድ ሄዱ፥እርሱም ደግ ልጅ እንደሚወልዱ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን “ጊዜ ይፍታው፤”ብለው ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
ሕልሙን ያዩት ሐምሌ ሠላሳ ቀን ነው፥ከዚያን ዕለት ጀምሮ ጾም ጸሎት ያዙ፤ ከጾም ጋር የሆነ ጸሎትም ቅድመ እግዚአብሔር ይደርሳል።ነቢዩ
ዳንኤል፡- ከሥጋ እና ከቅቤ፥ ከደረቅ እንጀራም ተለይቶ ጾም ጸሎት በመያዙ ልመናው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶለታል። “በዚያም ወራት
እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ። ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፥ ሥጋ እና ጠጅም በአፌ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት
እስከ ሚፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም። . . . እርሱም (በሚያስፈራ እና በሚያስደነግጥ ግርማ የተገለጠልኝ ቅዱስ ገብርኤል)
ዳንኤል ሆይ፥ አትፍራ፤ ልብህ ያስተውል ዘንድ ካደረግህበት (ጾም ጸሎት ከጀመርክበት) ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቶአል፤
እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ፥ አለኝ፤” ብሎአል። ዳን፡፲፥፩-፲፪።
ቅዱስ ኢያቄም እና ቅድስት ሐና መኝታቸውን ለይተው
ጾም ጸሎት በያዙ በሰባተኛው ቀን፥ ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ፡- “በሕልም እንደተረዳችሁት፥ መፈክረ ሕልምም እንደተረጐመላችሁ፥ ደግ
ልጅ የምትወልዱበት ጊዜ ደርሶአልና መኝታችሁን አንድ አድርጉ፤” አላቸው። እነርሱም የታዘዙትን አደረጉ፥ ፈቃደ እግዚአብሔር በመሆኑም
ነሐሴ ሰባት ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተፀነሰች። ይኽንንም አባ ሕርያቆስ፡- “ድንግል ሆይ፥ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ
አይደለም፥ በሕግ በሆነ ሩካቤ (ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- ጋብቻ ክቡር፥ መኝታውም ንፁሕ ነው እንዳለ) ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ
እንጂ፤” በማለት በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ ተናግሮታል። ቅድስት ሐናም፡- “የሰጠኸኝን ልጅ ጊዜው ደርሶ ሲወለድ፥ መልሰን መብዓ
አድርገን ለአንተ እንሰጥሃለን፤” ብላ ተሳለች።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማኅፀን እያለች
አያሌ ተአምራትን አድርጋለች። የቅድስት ሐና ዘመድ የምትሆን አንዲት ዓይነ ስውርት ሴት ነበረች። እርስዋም የሐናን መፅነስ ሰምታ
በመደነቅ ሆድዋን ዳሰሰቻት፥ በዳሰሰችበት እጇም ዓይንዋን ብትነካ በርቶላታል። ቅድስት ሐናንም፡- “ብፅዕት መባል ይገባሻል፥ ዓለም
ከተፈጠረ ጀምሮ እንደ አንቺ በማኅፀኑ ዓይን ያበራ የለምና፤” አለቻት። ይኽንንም አብነት አድርገው ሕሙማን ሁሉ ማኅፀን ዋን እየዳሰሱ
የሚፈወሱ ሆነዋል። ዳግመኛም ሳምናስ የሚባል የአጎትዋ ልጅ ሙቶ፥ እንደ ባህሉ የአልጋውን ሸንኮር ይዛ እየዞረች ስትአለቅስ፥ የሐና
ጥላዋ ቢያርፍበት፥ አፈፍ ብሎ ተነሥቶ፥ “ሰማይ እና ምድርን ለፈጠረ እናቱ ለምትሆኚ ለአንቺ ሰላምታ ይገባሻል፤” በማለት በማኅፀን
ላለች ለድንግል ማርያም ምስጋና አቅርቦአል።
ቅድስት ሐና በማኅፀንዋ ያለች እመቤት ድንግል ማርያም በምታደርገው ተአምር የተነሣ፥ ዘመዶችዋ
ሁሉ ሰገዱላት፥ ዝናዋም በየአገሩ ተሰማ። ይኽንን ድንቅ ነገር የሰማ ሁሉ፥ “በማኅፀን ሳለ ሕሙም የፈወሰ በተወለደ ጊዜ እንደምን
ይሆን?” አለ። መቼም በማኅፀን መቀደስ መኖሩን ከቀደሙ ነቢያት ከቅዱስ ኤርምያስ ተምረናል። “የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ
ሲል መጣ፡- በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፤” ይላል። ኤር፡፩፥፬። በአዲስ ኪዳን መግቢያ ላይ ደግሞ
በቅዱስ ዮሐንስ አውቀናል። “በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ያድርበታል፤” ይላል።ሉቃ፡፩፥፲፭። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ትምህርቱ፥ “በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች (ቅዱሳን) ሆነው የሚወለዱ አሉ፤” ብሎአል። ማቴ፡፲፱፥፲፭።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ፡- ማኅደረ መለኰት፥ወላዲተ አምላክ በመሆንዋ ከእነዚህ ሁሉ ትበልጣለች። በመሆኑም በማኅፀን
ሆና ተአምር ማድረግዋ ያንስባታል እንጂ አይበዛባትም። ደግሞም ለባሪያዎቹ የተሰጠ ጸጋ፥ ምልዕተ ጸጋ ለሆነች ለእናቱ አልተሰጣትም፥
ማለት ከመንፈስ ቅዱስ አይደለም።
ነገረ ማርያም፡- ክፍል ፲፱፤
ቅዱስ ኢያቄም እና ቅድስት ሐና የተሰጣቸው ጸጋ
እጅግ ታላቅ ነበር።ታላቅነቱንም መፈክረ ሕልም እንደነገራቸው፡- በሕልማቸው እና ከቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ተረድተውታል። በመጽሐፍ ቅዱስ፡- እግዚአብሔር ፈቃዱን፡- ለአቤሜሌክ፥ ለያዕቆብ እና ለዮሴፍ
በሕልም ገልጦላቸው እንደነበር ይታወቃል። ዘፍ፡፳፥፫፤ ፳፰፥፲፪፤ ፴፯ ፥፭።የእመቤታችን ጠባቂ ለነበረ ለጻድቁ ለዮሴፍ ደግሞ፡- ነገረ ማርያም ማለትም፡- እግዚአብሔር መርጦአት፥ ቅዱሳን ነቢያት ትንቢት
ተናግረውላት፥ በመንፈስ ቅዱስ ግብር፡- በድንግልና ፀንሳ በድንግልና
የመውለዷን ነገር፥ ከዚያም በኋላ፡- ጌታን አዝላ የመሰደዷን እና ከስደት የመመለሷን ነገር፥ ቅዱሳን መላእክት በሕልም
ነግረውት ነበር። ማቴ፡፩፥፳፤ ፪፥፲፫፣፲፱። (ነገረ ማርያምን እግዚአብሔር እንዲህ ካልገለጠልን በቀር፥ ጣዕሟ በአንደበታችን
ፍቅሯም በልቡናችን ሊያድርብን አይችልም፤) ለዮሴፍ ወልደ ያዕቆብና ለነቢዩ ለዳንኤል ሕልም የመፍታት ጸጋ ተሰጥቶአቸው ስለነበረ፥ የነገሥታቱን ሕልም
እንኳ እንደፈቱላቸው መጽሐፍ ቅዱስ ቋሚ ምስክር ነው። ዘፍ፡፵፥፭፤ ፵፩፥፲፬፣ ዳን፡፪፥፳፭፤ ፬፥፬።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእናቷ ማኅፀን
እያለች አያሌ ተአምራትን በማድረጓ፥ ለቅዱስ ኢያቄምና ለቅድስት ሐና ከባድ ፈተና ሆኖባቸው ነበር።የበጎ ነገር ሁሉ ጠላት
ሰይጣን አይሁድን በምቀኝነት አስነ ሣባቸው።የምቀኝነት ምንጩ ደግሞ ክፉ ልቡና ነው፤ ማር፡፯፥፳፪። የሰው ልጅ መንፈሳዊነቱን
ትቶ ፍጹም ሥጋዊ ሲሆን ምቀኝነት ይሰለጥንበታል። ገላ፡፭፥፳፩። ፈቃደ ሥጋው ገዝቶት በክፋትና በምቀኝነት የሚኖር ሰው ደግሞ ለማንም ፍቅር ሊኖረው
አይችልም። ገላ፡፫፥፫። ሰይጣን አዳምን እና ሔዋንን ያሳሳተው በምቀኝነት ነው። ዘፍ፡፫፥፩። ቃየል
አቤልን የገደለው በምቀኝነት ነው። ፬፥፰። ዔሳው ወንድሙን ያዕቆብን ለመግደል የዛተው በምቀኝነት ነው። ዘፍ፡፳ ፯፥፵፩። የያዕቆብ ልጆች ወንድማቸውን
ዮሴፍን፡- “እንግደለውና በአንድ ጉድጓድ ውስጥ እንጣለው፤” ያሉት፥ በኋላም በሮቤል በጎ
ምክር አሳባቸውን ለውጠው ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች የሸጡት በምቀኝነት ነው። ዘፍ፡፴፯፥፳፣፳፰። ሄሮድስ፡- ሕፃኑን ኢየሱስ ክርስቶስን
ያሳደደው፥ በዚህም ምክንያት አሥራ አራት እልፍ ሕፃናትን ያሳረደው በምቀኝነት ነው። ማቴ፡፪፥፲፮። አይሁድ
ኢየሱስ ክርስቶስን እጆቹን እና እግሮቹን በቅንዋተ መስቀል ቸንክረው የገደሉት በምቀኝነት ነው። ማር፡፲፭፥፳፬።
ምቀኝነት የባህርያቸው እስከሚያስመስልባቸው የደረሱ
አይሁድ፥ በማኅፀነ ሐና ባለች ፅንስ ምክንያት የሚደረጉት ልዩ ልዩ ተአምራት አላስደሰታቸውም። ተሰብስበውም፡- “ስለዚህ ነገር ምን
እንላለን? ሐና ፀንሳ ሳለች በማኅፀንዋ ታድናለችና፥ የእስራኤልን መንግሥት አጥፍታ በእኛ ላይ ልትነግሥ አይደለምን?” ተባባሉ። ይኸውም፡- “ከአሁን ቀደም ከእነዚህ
ወገን የሆኑት ዳዊት ሰሎሞን፥ አርባ፣ አርባ ዓመት ገዝተውን ነበር፥ ከእነዚህ የሚወለደው
ደግሞ ምን ያደርገን ይሆን?” ብለው ነው። ሀገር ያወቀውን፥ ፀሐይ የሞቀውን ምቀኝነታቸውን በሃይማኖት ለመሸፈን፡- “በሙሴ ሕግ መሠረት
በድንጋይ ቀጥቅጠን እንግደላቸው፤” ብለው በሌሉበት ሞት ፈረዱባቸው። ይህ የሙሴ ሕግ የሚጠቀሰው
ለአመንዝሮች እንጂ፥ ትዳራቸውን አክብረው፥ ሕገ እግዚአብሔርን
ጠብቀው፥ በጾም በጸሎት ተወስነው በቅድስና ለሚኖሩ፥ ለቅዱስ ኢያቄምና ለቅድስት ሐና አልነበረም። ዘሌ፡፳፥፲፣ዘዳ፡፳፪፥፳፬።
መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜ፥ የመፀነሷን ነገር አስቀድሞ
በሕልም ነግሮአቸው የነበረ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፥ እያዩት ከሰማይ ወርዶ፥ “በዘመድ የከበራችሁ
ኢያቄምና ሐና ሆይ፥ ተነሡ፤” አላቸውና ወደ ሊባኖስ ተራራ ወሰዳቸው። ይህም፡- ቅዱሳን መላእክት ሎጥን
ከሰዶም አውጥተው፥ “ወደዚያ ሸሽተህ አምልጥ፤” እንደ አሉት አይነት ነው። ዘፍ፡፲፱፥፳፪። የቅዱሳን መላእክት
አማላጅነትና ተራዳኢነት ለእግዚአብሔር ሰዎች ሁልጊዜ እንዲህ እንደሚደረግላቸው አያሌ ማስረጃዎች አሉ። የእግዚአብሔር መልአክ
ቅዱስ ዮሴፍን፡- “ሄሮድስ ሕፃኑን(ኢየሱስን) ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እና እናቱንም
ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስከምነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ፤” ያለው ለዚህ ነው። ማቴ፡፪፥፲፫። የሞት ፍርድ ይጠብቀው
የነበረውን ቅዱስ ጴጥሮስንም ሰንሰለቱን ፈትቶ፥ ወኅኒ ቤቱን ከፍቶ አውጥቶታል። እርሱም በቅዱሳን መላእክት
ተራዳኢነት የሚያምን ስለሆነ፥ ወደ ልቡ ተመልሶ፡- “ጌታ መልአኩን ልኮ
ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ፤” ብሎአል። የሐዋ፡፲፪፥፩-፲፩። (የዘንድሮዎቹ ኢየሱስን
እንስብካለን ባዮች ግን ይህን አያውቁም፤ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ትክክለኛ ኢየሱሳዊ ቢሆኑ ኖሮ፥ በቅዱሳን መላእክት
ተራዳኢነት እና አማላጅነት እንደሚድኑ ያምኑ ነበር፤) ቅዱስ ጳውሎስም፡- በሥጋም በነፍስም የሚድኑትን
ሰዎች ለመራዳት ቅዱሳን መላእክት እንደሚላኩ መስክሮአል። ዕብ፡ ፩፥፲፬። (እንደ ክረምት አግቢ የፈሉ ተሀድሶዎች ግን ይህን አይመሰክሩም፤) የባህርይ ስግደት የሚሰገድለት
ጸሎት ተቀባይ ኢየሱስ ክርስቶስ፡- አብነት ሊሆነን በጌቴሴሚኒ በጸለየና በሰገደ ጊዜ፥ “ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታው
መልአክ ታየው፤” ይላል። ሉቃ፡፳፪፥፵፫። በዚህም ለሥጋ ለባሽ በጠቅላላ ተራዳኢ መልአክ እንደሚያስፈልገው አስተምሮናል። (በስሙ የሚነግዱ የዛሬዎቹ
ኢየሱሳውያን ግን ይህን ትምህርት አይተነፍሱም፤) በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ዘመን ያለ ተራዳኢ መልአክ እግዚአብሔርን ያገለገለ
ሰው ማንም የለም። ነቢዩ ኤልሳዕ፡- ቅዱሳን መላእክት የእሳት አጥር ሆነው ሲጠብቁት አይቶአል፥ የጠላትን የሠራዊት
ብዛት በማየት ፈርቶ የነበረ ሎሌውም በነቢዩ ጸሎት ተገልጦለታል። ፪ኛ፡ነገ፡፮፥፲፬-፲፯። ቅዱስ ዳዊት፡- “የእግዚአብሔር መልአክ
በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል፤”ያለው ለዚህ ነው። መዝ፡፴፫፥፯።
ቅዱስ ገብርኤል፡- ቅዱስ ኢያቄምን እና
ቅድስት ሐናን ወደ ሊባኖስ ተራራ የወሰዳቸው ያለ ምክንያት አይደለም። “ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፤ (ጥንተ አብሶ የተባለ
የአዳም ኃጢአት ያላረፈብሽ ንጽሕተ ንጹሐን ነሽ፤) ነውር የለብሽም። (የአዳም ኃጢአት የለብሽም)። እኅቴ ሙሽራ ሆይ፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር
ነዪ፤” ተብሎ ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም የተነገረው ቃለ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው። መኃ፡፬፥፯። ሊባኖስ፡- ከገሊላ በስተ ሰሜን
እና ከፊንቄ በስተ ምሥራቅ የሚገኝ ተራራማ ሀገር ነው። ዘዳ፡፩፥፯። በዝግባ ዛፍ የተሞላ ተራራ ነው፥ ንጉሡ ሰሎሞን ለቤተ
መቅደሱ ሥራ ያስፈለገውን የዝግባ እንጨት ያስመጣው ከዚያ ነበር። ፩ኛ፡ነገ፡፬፥፴፫፤ ፭፥፮። ምሳሌነቱ ጥሩ ነው፥ ከሊባኖስ የተገኘ ዝግባ
ለአግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆነ ሁሉ፥ በሊባኖስ የተወለደች ድንግል ማርያምም ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሆና ተገኝታለች። አንድም የሊባኖስ ዝግባ
ለቅዱሳን ምሳሌ ነው፤ የዚያ ፍሬው እንዲበዛለት፥ እነርሱ ደግሞ ጸጋና ክብር ይበዛላቸዋል። መዝ፡፺፩፥፲፪።
ቅድስት ሐና የፅንስዋ ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ ግንቦት አንድ ቀን፥ ከፀሐይ ይልቅ የምታበራ
ሴት ልጅ ወለደች። “እመቤታችን ማርያም መልኳ እንደ አምላክ መልክ ነው፥ የአምላክን መልክ ይመስላል፤” እንዲል፡- የመልኳ ደም ግባት
እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነበር። መዓዛዋም ከሽቱዎች ሁሉ ይበልጥ ነበር። ዘመዶቿ እና ጐረቤቶቿም
በሰሙ ጊዜ፥ ፈጽሞ ደስ አላቸውና ተሰብስበው ወደ እርሷ መጡ። ልጇንም ባዩ ጊዜ ፈጽመው
አደነቁ፥ እርስ በርሳቸውም፡- “እንደዚህ ያለች ብላቴና ከቶ አይተን አናውቅም፤” ተባባሉ። ምልዕተ ጸጋ በመሆኗ
የእግዚአብሔር ብርሃን በላይዋ ያበራ ነበር። “ከፀሐይ ይልቅ ትበሪያለሽ፤” የተባለችው ለዚህ ነው። በዚህ ምክንያት የብርሃን
ድንኳኖች በሊባኖስ ተራሮች ላይ ተተክለዋል፥ ሠራዊተ መላእክት ከሰማይ ነጕደው መጥተዋል፥ ዝማሬያቸውንም አሰምተዋል። ቅድስት ቅዱሳን ናትና
መዓዛ ቅዱሳን ተራራውን አውዶአል፥ “ዐጠንተ መንበሩ፤” እንዲል፡- የአምላክ መንበር ናትና
ዐጥነዋታል። “ኢያቄም ወሐና ወለዱ ሰማየ፤” እንዲል፡- የተወለደችው ዳግሚት
ሰማይ በመሆኗ ሰማያውያን መላእክት በእርስዋ ዘሪያ ተሰብስበዋል። ቅዱስ ያሬድ፡- “ከሰማያት በላይ ስለ አለው የአርያም የልዑል ስፍራ ምትክ በምድር ላይ ከፍተኛ አርያምን (ሰማይን) ሆነሽ የተገኘሽ
አንቺ ነሽ፤” ያለው ለዚህ ነው። እኅታቸው ስለሆነች ወደዷት፥ ማኅደረ መለኰት በመሆኗ
ደግሞ ሰገዱላት።
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም፡- ሰማያውያን
ዘመዷቿ ቅዱሳን መላእክት እና ምድራውያን ዘመዷቿ በሊባኖስ ተራራ በአንድ መሰብሰባቸው ምሳሌነት አለው።ምሳሌነቱም ለቤተክርስቲያን
ነው፤ምክንያቱም ፡-ቤተ ክርስቲያን፡-በምድር ያሉ ቅዱሳን ምእመናን እና በሰማይ የሚኖሩ ቅዱሳን አንድነት ናትና።የዚህ ሁሉ ምክ
ንያት ደግሞ እመቤታችን ናት፥ እርሷ ከዚህም በላይ ናት።አምላክ ከሰማይ ወርዶ፥ በማኅፀኗ አድሮ፥ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም
ነፍስ ነስቶ በመወለዱ፥ አምላክን እና ሰውን በተዋህዶ ያገናኘች እመቤት ናት። አሁንም በአማላጅነቷ
ሰውን እና አምላክን ታገናኛለች። የቅድስት ሐና እና የቅዱስ ኢያቄም ዘመዶች፥ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ፥ ተአምራቱ ንም እያደነቁ
በደስታ እና በሐሴት ሰባት ቀን ሰነበቱ።
ለግንቦት ልደታ የተሠራው ቀለም (ቃለ እግዚአብሔር)፥ እመቤታችንን፡- “ኦ ማርያም፡- መንክር ልደትኪ፥ ወዕፁብ
ግብርኪ፤ ማርያም ሆይ፥ ልደትሽ ድንቅ፥ ሥራሽም ዕፁብ ነው፤” ይላታል። “ይትባረክ እግዚአብሔር
ወይትአ ኰት ስሙ፤ ኪያኪ ሠናይተ ዘፈጠረ ለቤዛ ብዙኃን፤ እስመ መሠረት አንቲ ለሕይወተ ኵሉ ዓለም፤ ማርያም እምነ ወእሙ
ለእግዚእነ ሰአሊ በእንቲአነ። ለብዙዎች ድኅነት(መዳን) ምክንያት እንድትሆኚ፥ መልካሟን አንቺን የፈጠረ
እግዚአብሔር ይባረክ፤ (ይመስገን)፤ ስሙም የተመሰገነ ይሁን። ለዓለሙ ሁሉ የሕይወት
መሠረት አንቺ ነሽና፤ የጌታችን እናቱ ማርያም እናታችን ስለ እኛ ለምኚልን።” እያለ እግዚአብሔርን
ያመሰግናል፥ እመቤታችንን ደግሞ ክብሯን እያደነቀ፡- አማላጅነቷን ይማጸናል። ስለ ቅዱስ ኢያቄምና
ስለ ቅድስት ሐናም የሚናገረው አለ። “ክልኤቱ አዕሩግ እመ በከዩ ብካየ፥ ረከቡ ዘታስተሠሪ ጌጋየ፥ ለወንጌላውያን ኵልነ
ዘኮነት ምጕያየ፤ ኢያቄም ወሐና ወለዱ ሰማየ፥ ሰማዮሙኒ አሥረቀት
ፀሐየ፤ ምሥራቀ ምሥራቃት ሙፃአ ፀሐይ፥ እግዝእትነ ዘመና ሙዳይ፥ ተወልደት ዮም ዳግሚት
ሰማይ። ሁለቱ አረጋውያን (ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና) ልቅሶን ቢያለቅሱ፥ ለሁላችን ለወንጌላውያን
መሸሻ (መጠጊያ) የሆነች፥ በደልን የምታስወግድ እና ኃጢአትን የምታስተሠርይ ልጅ አገኙ፤ ኢያቄምና ሐና ሰማይን
ወለዱ፥ ሰማያቸውም ፀሐይን አወጣች፤ (ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስን ወለደች)፤ የምሥራቆች ምሥራቅ
እመቤታችን የመና ሙዳይ ናት፤ ለጽርሐ አርያም ሁለተኛ የምትሆን ዳግሚት ሰማይ ዛሬ ተወለደች፤” ይላል።
ነገረ ማርያም፡- ክፍል ፳
“በመከራዬ ጊዜ በአፌ የተናገርሁትን፥ ከንፈሮቼም ያሉትን ስእለቴን
ለአንተ እፈጽማለሁ፤ ”መዝ፡፷፭፥፲፬።
በአምላክ ኅሊና ተቀርፃ የኖረች ጽላት፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- የብጽዓት ልጅ ናት። ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና፡- “ወንድ ልጅ ብንወልድ፡- ወጥቶ ወርዶ፥ አርሶ ቆፍሮ ይርዳን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር እንሰጠዋለን። ሴት ልጅም ብንወልድ፡- እንጨት ሰብራ ውኃ ቀድታ፥ ፈጭታ ጋግራ ታገልግለን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር እንሰጣታለን።” ብለው ተስለው ነበር። በመሆኑም፡- ገና በሦስት ዓመቷ ለቤተ እግዚአብሔር ሊሰጧት ተስማሙ። ይህም፡- ሕልቃና እና ሐና፥ ነቢዩ ሳሙኤልን፡- ለቤተ እግዚአብሔር ለመስጠት እንደተስማሙት
አይነት ነው። ሐና ሕልቃናን፡- “ሕፃኑ ጡት እስኪተው ድረስ እቀመጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ዘንድ፥ በዚያም ለዘለዓለም ይሆን ዘንድ አመጣዋለሁ።” እንደ አለችው፥ ቅድስት ሐናም ቅዱስ ኢያቄምን፡- “ይህች ብላቴና ሆዷ ዘመድ ሳይወድ፥ አፏ እህል ሳይለምድ ወስደን አንሰጥምን? «የሰጠ ቢነሳ የለበትም አበሳ፤» እንደሚባለው፥ አንድ ነገር ብትሆንብን ከልጃችንም ከእግዚአብሔርም ሳንሆን እንቀራለን፤” ብለዋለች። በኦሪቱ ዘመን ሕልቃና ለሐና፡- “በዓይንሽ ደስ ያሰኘሽን አድርጊ፥ ጡትም እስኪተው ድረስ ተቀመጪ፤ ብቻ እግዚአብሔር ቃሉን ያጽና፤” እንደ አላት፥ ቅዱስ ኢያቄምም ቅድስት ሐናን፡- “ፍቅርሽ ያልቅልሽ እንደሆነ ብዬ ነው እንጂ፥ እኔማ ፈቃደኛ ነኝ፤” ብሎአታል። ምክንያቱም ከፍቅሯ ጽናት የተነሣ አንድም ቀን ከእቅፏ አውጥታት፥ ከጭኗ አውርዳት አታው ቅም። እንዲህም ማድረግዋ፡- አንድ ቀን ለብቻዋ ትታት ከደጅ ወጥታ ስትመለስ፥ መልአከ እግዚአብሔር ሰውሮባት በመከራ አግኝታት ስለነበረ ነው፤ ሁሌም እንደዚያ እየመሰላት ከላይዋ አታወርዳትም ነበር።
የነቢዩ የሳሙኤል እናት በእግዚአብሔር ቤት ቆማ፡- “ስለዚህ ሕፃን ጸለይሁ፤ እግዚአብሔርም የለመንሁትን ልመናዬን ሰጥቶኛል፤ እኔም ደግሞ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ ዕድሜውን
ሁሉ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል፤” ብላ ለሊቀ ካህናቱ ለዔሊ እንደ አስረከበችው፥ ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐናም ወደ ቤተ መቅደስ ሄደው እመቤታችንን ለሊቀ ካህናቱ ለዘካርያስ አስረክበዋታል። “በመከራዬ ጊዜ በአፌ የተናገርሁትን፥ ከንፈሮቼም ያሉትን ስእለቴን ለአንተ እፈጽማለሁ፤” ማለት እንዲህ ነው። ባያደርጉት ዕዳ እንደሚሆንባቸው ያውቃሉ።“ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ፈጽሞ ይሻዋልና፥ ኃጢአትም ይሆን ብሃልና መክፈሉን አታዘግይ። . . . ሰው በችኰላ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ (የተለየ) ነው ብሎ ቢሳል፥ ከተሳለም በኋላ ቢጸጸት ወጥመድ ነው። . . . ሰነፎች ደስ አያሰኙትምና ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ ትፈጽመው ዘንድ አትዘ ግይ፤ የተሳልኸውን ፈጽመው። ተስለህ የማትፈጽም ብትሆን ባትሳል ይሻላል፤” ይላል። ዘዳ፡፳፫፥፳፩፣ ምሳ፡፳፥፳፭፣ መክ፡፭፥፬።
“ርግቤ መደምደሚያዬም አንዲት ናት፤ለእናትዋ አንዲት ናት፥ ለወለደቻትም የተመረጠች ናት።”መኃ፡ ፮፥፱፤ እንዲል፡- ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና፡- በሐዘንና በዕንባ፥ በጾምና በጸሎት ያገኟትን አንድ ልጃቸውን፥ ለሰጣቸው ለእግዚአብሔር መልሰው ለመስጠት መወሰናቸው፥ ለእግዚአብሔር የገቡትን ቃል መጠበቃቸው፥ የሚደነቅ ሃይማኖት ነው። በመሆኑም ሃይማኖታቸውን ማድነቅ ይገባል፤ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ጽኑዕ የሆነ ሃይማኖትን እንድናደንቅ የሰጠን አብነት አለ። ይኸውም፡- የቅፍርናሆሙን መቶ አለቃ ሃይማኖት በማድነቁ ታውቆአል፤ “ለተከተሉት ሕዝብ፡- እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም አላቸው፤” ይላል። ሉቃ፡፯፥፱። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡- የአቤልን፥ የሄኖክን፥ የኖኅን፥ የአብርሃምን እና የሣራን፥ የይስ ሐቅን፥ የያዕቆብን፥ የሙሴን እና የወላጆቹን፥ ሃይማኖት አድንቆአል። ገድላቸውንም የሃይማኖት እና የምግባር ማስተማሪያ መጽሐፍ አድርጐአል። ዕብ፡፲፩፥፩-፳፰።
ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና፡- ሕፃኗን ማርያምን ይዘው ከቤተ እግዚአብሔር ሲደርሱ፥ ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ፡- ሕዝቡን ሰብስቦ እያስተማረ ነበር። እነርሱም “እነሆ ስእለት ተቀበሉን፤” አሉአቸው። “እንቀበላለን፤” ብለው ቢቀርቡ፥ ከፀሐይ ሰባት እጅ አብርታ፥ ከመብረቅ ሰባት እጅ አስፈርታ፥ የምታበራ ዕንቈ ባሕርይ መስላ ታየቻቸው። እንዲህ አይነቱ ድንቅ ተአምራት፥ እግዚአብሔር ለመረጣቸው እንደሚደረግ መጽሐፍ ቅዱስ ቋሚ ምስክር ነው። “ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ተነጋገረ የፊቱ ቍርበት አንጸባረቀ፤ (እንደ ፀሐይ አበራ)፤ . . . ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ። . . . ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ።. . . እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር።. . . በሸንጎም የተቀመጡት ትኵር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ አዩት።” ይላል፤ ዘጸ፡፴፬፥፳፱፣ ዳን፡፲፪፥፫፣ ማቴ፡፲፫፥፵፫፣ የሐዋ፡፮፥፯፤፲፭። የመልአክ ፊቱ ምን እንደሚመስል መጽሐፍ ቅዱስ ሲነግረን፡- “አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል (እንደ ብርሃን ያብለጨ ልጭ) ነበር፥ ፊቱም እንደ መብረቅ ምስያ ነበረ፥ ዓይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና (መብራት)፥ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፥ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ። . . . የጌታ መልአክ ከሰ ማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፤” ብሎናል። ዳን፡፲፥፮፣ ማቴ፡፳፰፥፪።
ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ እና ካህናቱ፡- የተሰጣትን ጸጋ አይተው፥ “ይህችን የመሰለች ልጅ ተቀብለን ምን እናደርጋታለን? ምን እናበላታለን? ምን እናጠጣታለን? ምን እናለብሳታለን? ምን እናነጥፍላታለን? ምን እንጋርድላታለን?” በማለት እንደ ሰው ተጨነቁ። በዚህ መካከል ሕፃኗ ማርያም ረኀብ ተሰምቷት አለቀሰች። በዚህን ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ፋኑኤል፡- ሰማያዊ እንጀራን በመሶበ ወርቅ፥ ሰማያዊ መጠጥን ደግሞ በብርሃን ጽዋ ይዞ፥ ወደ ታች ሳይወርድ ረቦ ታያቸው። ሕዝቡም ለአባታቸው ለካህኑ ለዘካርያስ የመጣ ጸጋ በረከት መስሎአቸው፡- “እጅ ነስተህ፥ ሰግደህ ተቀበል፤” ብለውት፥ እጅ ነስቼ ሰግጄ እቀበላለሁ ብሎ ቢቀርብ፡- ወደ ሰማይ ራቀው። ከሕዝቡም እያንዳንዳቸው እጅ ነስተን፥ ሰግደን እንቀበላለን ብለው ቢቀርቡ፡- እነርሱንም ወደ ሰማይ ራቃቸው። ከዚህ ሁሉ በኋላ ዘካርያስ ሐናን ጠርቶ፡- “ለእናንተ ለእንግዶቹ የወረደ ጸጋ በረከት ሊሆን ስለሚችል ሕፃኒቱን ይዘሽ ወደዚያ ፈቀቅ ብለሽ ተቀመጪ፤” አላት። ቅድስት ሐናም ካህኑ እንደ ነገራት ብታደርግ፥ ቀረብ ብሎ ከራሳቸው ላይ ረቦ አልወርድም አለ። ሁለተኛም ዘካርያስ ሐናን ጠርቶ፡- “አምላከ እስራኤል የሚያደርገው ነገር ስለማይታወቅ (ስለማይመረመር)፥ ሕፃኒቱን እዚያው ትተሽ አንቺ ወዲህ ነዪ፤” አላት። ቅድስት ሐና ገና ዘወር ከማለቷ፥ ቅዱስ ፋኑኤል ወርዶ፥ አንደኛውን ክንፉን አንጥፎላት፥ ሁለተኛውን ክንፉን ደግሞ ጋርዶላት እመቤታችንን መገቦአታል፥ ሰግዶላታልም። በእግዚአብሔር የታዘዙ ቅዱሳን መላእክት፡- የእግዚአብሔርን ቅዱሳን እንዲህ እንደሚመግቡ በመጽሐፍ ቅዱስ የታወቀ ነው። እመቤታችን ደግሞ ቅድስት ቅዱሳን በመሆኗ ከእነዚህ ሁሉ ትበልጣለች። “ነቢዩ ኤልያስ ከኤልዛቤል ፊት ሸሽቶ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዘ፤ መጥቶም ከክትክታ ዛፍ በታች ተቀመጠና፡- ይበቃኛል፤ አሁንም፥ አቤቱ፥ እኔ ከአባቶቼ (ከአብርሃም ከሙሴ) አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ ብሎ እንዲሞት ለመነ። በክትክታውም ዛፍ በታች ተጋ ደመ፥ እንቅልፍም አንቀላፋ፤ እነሆም መልአክ ዳሰሰውና፡-ተነሥተህ ብላ አለው።ሲመለከትም፥ እነሆ፥ በራሱ አጠገብ የተጋገረ እንጐቻና በማሰሮ ውኃ አገኘ።በላም ጠጣም፥ ተመልሶም ተኛ። የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና፡- የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነ ሥተህ ብላ አለው። ተነሥቶም በላ ጠጣም፤ በዚያም ምግብ ኃይል እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ፤” ይላል። ፩ኛ፡ነገ፡፲፱፥፩-፰።
ካህናቱና ሕዝቡም፡- “የምግቧ ነገር በቅዱሳን መላእክት እጅ ከተያዘማ ከተርታው ሰው ጋር ምን ያጋፋታል፤” ብለው፥ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አስገብተው፥ መኖሪያዋን በቤተ መቅደስ አደረጉላት። ይኸውም ነቢዩ ሳሙኤል ገና በሦስት ዓመቱ ለቤተ መቅደስ ተሰጥቶ በዚያ እንደኖረው ማለት ነው። ፩ኛ፡ሳሙ፡፩፥፳፪-፳፱። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሕንፃው ብቻ አይደለም፥ የሰው ሰውነቱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው። “የእግዚአ ብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?. . . ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።” ይላል። ፩ኛ፡ቆሮ፡፫፥፲፮፤፮፥፲፱። ከዚህ የምንማረው ትልቅ ትምህርት አለ፤ ይኸውም፡- ሰውነታችን በእውነት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከሆነ፥ እመቤታችን በልባችን ውስጥ እንድትኖር፡- የተሰጠችን የእግዚአብሔር ጸጋ እንደሆነች እናምናለን። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሆኖ ካልተገኘ ደግሞ ፈጽሞ በውስጣችን ልትኖር አትችልም። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችው ታኅሣሥ ሦስት ቀን ነው። በዚህም፡- አባቷ ቅዱስ ዳዊት ተናግሮት የነበረው ቃለ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቶአል። ከእናት ከአባቷ ቤት ወጥታ፥ ለቤተ መቅደስ ተሰጥታ፥ በዚያው እንደምትኖር አስቀድሞ ስለ ተገለጠለት፡- “ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ፥ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽንም የአባትሽንም ቤት እርሺ፤ ንጉሥ (ንጉሠ ሰማይ ወምድር እግዚአብሔር) ውበትሽን (የአዳም ኃጢአት ያልወደቀበትን ንጽሕናሽን) ወድዶአልና፤” ብሎአል። መዝ፡፵፬፥፲። ከጥንት ጀምሮ የነበሩ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፡- ከቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች በተቀመመ ምስጋናቸው፡- “አንቲ ውእቱ ንጽሕተ ንጹሐን፥ ዘነበርኪ ውስተ ቤተ መቅደስ ከመ ታቦት፥ ወመላእክት ያመጽኡ ወትረ ሲሳየኪ፥ ስቴኪኒ ስቴ ሕይወት ውእቱ፥ ወመብልዕኪኒ ኅብስት ሰማያዊ። እንደ ታቦተ እግዚአብሔር በቤተ መቅደስ ውስጥ የኖ ርሽ አንቺ፥ ከንጹሐን ይልቅ ንጽሕት ነሽ፤ ቅዱሳን መላእክት ዘወትር ምግብሽን ያመጡልሽ ነበር፥ ትጠጪው የነበረውም መጠጥ የሕይወት መጠጥ ነው፥ መብልሽም በሰው እጅ ያልተሠራ ሰማያዊ እንጀራ ነው፤” ብለዋታል።
ነገረ ማርያም፡- ክፍል-፳፩
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡-ገና በሦስት ዓመቷ ለእግዚአብሔር ተስጥታ፥ ያደገችው በቤተ መቅደስ
ውስጥ ነው። ቅዱሳን መላእክት እየመገቧት፥እየዘመሩለት እና እየሰገዱላት ዓሥራ ሁለት ዓመት በቤተ
መቅደስ ኖራለች።ቅዱስ አባ ሕርያቆስ፡- በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ፥ መንፈስ ቅዱስ ቢገልጥለት፥ አስተዳደጓ እንዴት
እንደነበረ ከሌሎቹ እያነጻጸረ ተናግሮአል። “ድንግል ሆይ! አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ (አታሞ እየመቱ፥ እስክስታ እየወረዱ
እንደሚያድጉ) እንደ ዕብራውያን ልጆች በቧልት (በቀልድ፥በፌዝ) በጨዋታ ያደግሽ አይደለም፤ በቅድስና፥ በንጽሕና
በቤተ መቅደስ ውስጥ ኖርሽ እንጂ። ድንግል ሆይ! ምድራዊ ኅብስትን የተመገብሽ አይደለሽም፥ ከሰማይ የተገኘ (በጥበብ
አምላካዊ የተሠራ) ኅብስትን ተመገብሽ እንጂ።ድንግል ሆይ! ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለሽም፥ ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ
(ከሰማይ የተገኘ) ሰማያዊ መጠጥን ነው እንጂ፤” በማለት አድንቆአል። ይኸውም ወደ ቤተ መቅደስ
በገባችበት ዕለት፥ ቅዱስ ፋኑኤል ሲመግባት በገሀድ ከታየበት ጊዜ ጀምሮ እሰከ መጨረሻው የዘለቀ ነው።
የቅዱሳት መጽሐፍትን ትርጓሜ የሚያውቅ፥ ምሥጢራቸውንም የሚያራቅቅ
ቅዱስ ያሬድም፡- በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ፡- “ከንጹሓን ሁሉ ይልቅ
ንጽሕት የሆንሽ አንቺ ነሽ፤ ከማይነቅዝ እንጨት እንደ ተሠራ በወርቅ እንደ ተጌጠ፥ ዋጋውም እጅግ ውድ
በሆነ በሚያበራ ዕንቍ እንደ ተለበጠ ታቦት በቤተ መቅደስ ውስጥ የኖርሽ፥ የተመረጥሽ ድንግል
ነሽ። እንዲህ ሆነሽ በቤተ መቅደስ ውስጥ ኖርሽ፤ ቅዱሳን መላእክትም ዘወትር ምግብሽን ያመጡልሽ ነበር፤ ቅዱሳን መላእክት እንዲህ እየጐበኙሽ
ዓሥራ ሁለት ዓመት ኖርሽ፤ መጠጥሽም የሕይወት መጠጥ ነበር፥ ምግብሽም የሰማይ ኅብስት
ነበር። አባትሽ ዳዊት በመሰንቆ አመሰገነ፤ በትንቢት መንፈስም፥ በመንፈስ ቅዱስም በገና
እየደረደረ እንዲህ ብሎ ዘመረ። ልጄ ሆይ! ስሚ፥ እዪም፥ ጆሮሽንም አዘንብዪ፥ ሕዝብሽንና የአባትሽንም
ቤት እርሺ፤ ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፥ እርሱ ጌታሽ ነውና፥ ስገጂ፥ ትሰግጂማለሽ፤” በማለት አመስግኖአታል። በማኅፀኗ ላለ፥ ጌታዋ
ለሆነ፥ ለማኅፀኗ ፍሬ መስገዷ፥ ከመነገር በላይ ነው፥ ዕፁብ ድንቅ ነው። በቤተ መቅደስ የኖረች
ታቦተ እግዚአብሔር በውስጥም በውጪም በንጹሕ ወርቅ እንደ ተለበጠች፥ እመቤታችን ቅድስት
ድንግል ማርያምም፡- በውስጥ በነፍሷ፥ በውጭ ደግሞ በሥጋዋ ንጽሕት ናት። ወርቅ የንጽሕናዋ ምሳሌ
ነው። እግዚአብሔር ታቦቷን በረድኤት እንደ ተገለጠባት፥ እመቤታችንንም፡- በተለየ አካሉ ከሰማይ በመውረድ፥ በማኅፀን ከእርሷ የነሳውን
ሥጋና ነፍስ ተዋህዶ ሰው ኹኖ በመወለድ ተገልጦባታል።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሰማይ የሆነ
ኅብስትን የተመገበች ብቻ አይደለችም፤ ሰማይ ሆና ሰማያዊ ኅብስትን ለዓለሙ የመገበች ናት። ምክንያቱም፡- የማኅፀኗ ፍሬ ኢየሱስ
ክርስቶስ ከሰማይ የወረደ፥ ከዳግሚት ሰማይ ከእርሷም የተወለደ ኅብስት ነው። “ከሰማይ የወረደ ሕያው
እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘለዓለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት
የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።” ይላል። ይህን፡- መለኰቱን አዋህዶ የሕይወት እንጀራ አድርጐ የሰጠንን ሥጋውን የነሳው ከእመቤታችን
ነው። ዮሐ፡፮፥፶፩። በመጽሐፈ ዚቅ ላይ፡- “ናሁ ተግህደ ልዕልናሃ
ለወለተ ሐና፤ ኅብስተ ሕይወት ተፀውረ በማኅፀና፤ ጽዋዓ መድኃኒት ዘአልቦ
ነውር ወኢሙስና። የሐና ልጅ የድንግል ማርያም፡- ክብሯ፥ ልዕልናዋ እነሆ ተገለጠ፤ ጥፋትና ነውር የሌለበት፡- መድኃኒት የሆነ መጠጥ
እና የሕይወት እንጀራ በማኅፀኗ አድሮአልና።” የሚል አለ። ዳግመኛም፡- “ንጽሕተ ንጹሐን ከዊና ከመ ታቦት ዘዶር ዘሲና፥ ውስተ ቤተ መቅደስ
ነበረት በቅድስና፤ ሲሳያ ኅብስተ መና ወስቴሃ ስቴ ጽሙና፤ የመለኰት እሳት እንደ
ሆነች የሲና ታቦት፡- ንጽሕተ ንጹሐን ሆና፥ በቤተ መቅደስ ውስጥ
ነበረች፤ ምግቧ የሰማይ እንጀራ፥ መጠጧም የእርጋታ መጠጥ ነበር፤” በማለት ነገረ ማርያምን
ያደንቃል። በኦሪቱ፡- እስራኤል ዘሥጋ፡- መና ከሰማይ እየወረደላቸው ተመግበው ነበር፥ዳሩ ግን ከመቅሰፍት ሞት አላዳናቸውም። ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን የዘለዓለም
ሕይወት አለው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። አባቶቻችሁ በምድረ
በዳ መና በሉ፥ ሞቱም፤ ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው።” ያለው ለዚህ ነው። ዘጸ፡ ፲፮፥፲፬፣ ዮሐ፡፮፥፵፱።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- በቤተ መቅደስ ስትኖር፥ ቅዱሳን መላእክት ያረጋጉአት
እንደነበር፥ ቅዱስ አባ ሕርያቆስ ተናግሮላታል።“ድንግል ሆይ! ተድላ ዓለም፣ ብዕለ ዓለም የሸፈጣቸው፥ አጋንንት በውዳሴ ከንቱ
የሚያታልሏቸው (ፈቃደ ሥጋ ያታለላቸው) ወራዙት(ወጣቶች) ያረጋጉሽ አይደለሽም፤ የሰማይ መላእክት ጐበኙሽ
እንጂ፤ በነገረ ማርያም እንደ ተነገረ፡- ካህናት፥ ሊቃነ ካህናት ጎበኙሽ እንጂ፤” ብሎአል። እመቤታችን፡- ከቤተ መቅደስ ሳለች፥ አይሁድ “እንጣላታለን፤”
ብለው፡ -ጦር ሠርተው ቢሄዱ፥ አጥሩ፣ ቅጥሩ እሳት ሆኖ መልሶአቸዋል። ይህንንም፡- እንደ ተአምራት ሳይሆን
እንደ ምትሐት ቆጠሩት። በዚህን ጊዜ፡- “ምትሐትን በምትሐት ነው፤” ብለው፥ “መጥቁል” የተባለ
ጠንቋይ ፈልገው አገኙ። ተጨንቀው የመጡበትን ጉዳይም ካስረዱት በኋላ፡- “እርሷን የምታጠፋልን
ከሆነ ወርቅና ብር፥ በግና ላም በብዛት እንሰጥሃለን፤” ብለው ቃል ገቡለት። ለጊዜውም እንደ እጅ
መንሻ ብዙ ወርቅና ብር ሰጡት። እርሱም፡- “የዛሬን እደሩና ነገ የምትፈልጉትን ሁሉ አደርግላችኋቸሁ፤” አላቸው። በማግሥቱም የሰጡትን
ወርቅና ብር ቢመለከት ወደ ድንጋይነት ተለውጦ አገኘው፤ እንስሳቱንም ሞተው አገኛቸው። በልቡም፡- “አይሁድ እንደ ነገሩኝ፥ ለካስ፡- የማትቻል ምትሐተኛ
ናት፤” አለ።
የተደረገውን ተአምር እንደ ምትሐት የቆጠረው መጥቁል
በሆነው ነገር እጅግ ተበሳጨ። ወደ ሦስት መቶ የሚሆኑ የአየር ላይ አጋንንትም ወደ እርሱ መጥተው፡- “ምነው አዝነሃል?
ሰማይን እንኳ ጠቅልሉት ብትለን እንጠቀልለዋለን፤” አሉት። በዚህን ጊዜ እንደ አስለመዳቸው ሰው ቢያርድላቸው፡- ሥጋውን በልተው፥ ደሙን ጠጥተው፥ እመቤታችንን
ሊያጠፉለት ቃል ገቡለት። ይህ ሁሉ ሲሆን፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- “ስድክኤል” የሚባል
የእግዚአብሔር ኅቡዕ (ስውር) ስሙ ተገልጦላት እየጸለየች ነበር፤ ቅዱሳን መላእክትም የእሳት አጥር ሆነው ይጠብቋት ነበር። በመጥቁል መሪነት የሄዱ
ሰዎችም አጋንንትም ከቤተ መቅደሱ ሳይደርሱ በአንድነት ጠፍተዋል፥ መሬትም አፏን ከፍታ ውጣቸዋለች። በዚህን ጊዜ ከአዳም
ጀምሮ እስከ እርሷ ድረስ ያሉ አበው፡- “በአማን ስብሕት፥ በአማን ውድስት አንቲ፤ በእውነት አንቺ የተመሰገንሽ
ነሽ፤” እያሉ አመስግነዋታል።
ጥንቈላ ከጥንት ጀምሮ እንደ ነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ
ይታወቃል። እግዚአብሔር ባልፈቀደው መንገድ (በሰይጣን መንገድ) መንፈሳዊ ኃይልን መፈለግ ጠንቋይነት
ነው። ጠንቋዮች የእግዚአብሔርን ሥራ ለመገዳደር የሞከሩበት ጊዜ ነበረ። ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር የላከው
ሙሴ፥ እግዚአብሔር እንደ አሳየው፥ የእግዚአብሔር በትር የተባለች በትሩን፡- በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን
ፊት እባብ ቢያደርግ፥ የግብፅ ጠንቋዮችም በትራቸውን እባብ አድርገው ነበር። ነገር ግን፡- እባብ የሆነች የሙሴ
በትር ሁሉንም እባቦች ውጣቸዋለች። ይህም የሚያሳየን፥ የእግዚአብሔር ሥራ፡- የሰይጣንን ሥራ እንዴት
እንዳጠፋው ነው። ዘጸ፡፯፥፰፣ ኢሳ፡፲፱፥፫። የአሕዛብ ነገሥታት ጠንቋዮችን በአማካሪነት በቤተ መንግሥት ያስቀምጧቸው ነበር። ዳን፡፪፥፪። እስራኤላውያንም በዚህ
መንፈስ እየተመሩ በማስቸገራቸው፡- በጠንቋዮች መንገድ እንዳይሄዱ ተከልክለው፥ጠንቋዮችንም እንዲያጠፉ ታዝዘው ነበር።ዘጸ፡፳፪፥፲፰፣ዘሌ፡፳፥፳፯። በሐዋርያት ዘመን ሲሞን የተባለ ጠንቋይ ሕዝቡን በምትሐቱ ያስቸግራቸው
ነበር፥ እንዲያውም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በቅዱሳን ሐዋርያት እጅ ሲሰጥ ባየ ጊዜ በገንዘብ ለመግዛት ፈልጐ ነበር። ቅዱስ ጴጥሮስ ግን፡- “የእግዚአብሔርን ጸጋ
በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና፥ ከዚህ ነገር ዕድል
ወይም ፈንታ የለህም። እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንስሐ ግባ፥ ምናልባትም የልብህን
አሳብ ይቅር ይልህ እንደሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን፤ በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና።” አለው። ሲሞንም ይህን
በሰማ ጊዜ፡- በአንደበቱ፡- “ካላችሁት አንዳች እንዳይደርስብኝ እናንተው ወደ ጌታ ለምኑልኝ፤” እያለ፥ ሕዝቡ ሁሉ እያዩት
በምትሐት ወደ ሰማይ ለማረግ ሞከረ። በዚህን ጊዜ፡- ቅዱስ ጴጥሮስ ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ቢያማትብበት ከሰማይ ወድቆ ተሰባብሮ ሞቶአል። የሐዋ፡፰፥፲፱-፳፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡- በርያሱስ የተባለ ጠንቋይ፥ ሀገረ ገዢውን ከማመን
እያጣመመ ስለ አስቸገረው፡- “አንተ ተንኰል ሁሉ፣ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ(ወንጌልን)
ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም፥ እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፥ ዕውርም ትሆናለህ፥ እስከ ጊዜውም ፀሐይን
አታይም።” በማለት ገሥጾታል። “ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፥ በእጁም የሚመራውን
እየዞረ ፈለገ። በዚያን ጊዜ አገረ ገዡ የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ፤” ይላል። የሐዋ፡፲፫፥፯-፲፪። እየጠነቈለች ለጌቶቿ
ብዙ ትርፍ ታመጣላቸው የነበረችውን፥ የሟርተኝነት መንፈስ የነበረባትንም ሴት፥ መንፈሱን በመገሠጽ
ከእርሷ እንዲወጣ አድሮጐአል። የሐዋ፡ ፲፮፥፲፮።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡- በቤተ መቅደስ የኖረችው፥ ስራ ፈት ሆና አይደለም፤ በአጭር ታጥቃ፣ ማድጋ
ነጥቃ ውኃ እየቀዳች፥ ሐርና ወርቅ አስማማታ እየፈተለች፥ መጋረጃ እየሠራች፥ የተቀደደውንም እየሰፋች ነው። በመጽሐፈ ዚቅ ላይ፡- “ገብርኤል መልአክ መጽአ፥ ወዜነዋ ጥዩቀ፤ በዕንቈ
ባሕርይ እንዘ ትፈትል ወርቀ፤ በዕንቈ ባሕርይ ወርቅ ስትፈትል መልአኩ
ገብርኤል መጣ፥ አስረግጦ (የተረጋገጠ ነገር) አበሠራት፤” ይላል። ከዚህም
ጋር የኦሪትን እና የነቢያትን መጻሕፍት ትመረምር ነበር። ከዕለታትም
አንድ ቀን፥ የታላቁን ነቢይ የኢሳይያስን የትንቢት
መጽሐፍ ስታነብ፡- “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወልድንም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች፤” ከሚለው አንቀጽ ደረሰች። በዚህን ጊዜ፡- “እግዚአብሔር
ዕድሜ ከጤና ሰጥቶኝ፥ አምላክን በድንግልና ፀንሳ፣ በድንግልና ከምትወልደው እመቤት ቢያደርሰኝ፥ ገረድ ኹኜ አገለግላት ነበር፤” በማለት ተመኝታ ነበር።
ነገረ ማርያም፡-ክፍል ፳፪
የተጠማ ውሻ፤
ውሻ፡- ለበጎም
ለክፉም ምሳሌ ይሆናል።በጎ ምሳሌነቱ፡- ለጌታው ታማኝ መሆኑ ነው፥ አስተማማኝ የቤት ጠባቂ
ነው። ዘጸ፡፲፩፥፯፣ ኢሳ፡፶፮፥፲። እንደሚታወቀው የሚኖረው በቤት ውስጥ ከሰው ጋር ነው። ከነዓናዊቱ ሴት፡- “የልጆችን እንጀራ
ይዞ ለውሾች (የሴምን በረከት ለከነዓን) መስጠት አይገባም፤” በተባለች ጊዜ፡- “አዎን ጌታ ሆይ፥
ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ፤ (የጻድቅ በረከት ለኃጥእ ይተርፋል፤ እንዲል፡- የሴም ልጆች በረከት፥ እርግማን ለወደቀባቸው
ለከነዓን ልጆችም ተርፎ ጾም አያድሩም)፤” ያለችው ለዚህ ነው። ማቴ: ፲፭፥፳፮። ምክንያቱም፡- ውሻ ከጌታው ጋር በቤት
እንደሚኖር፥ ጻድቁ ኖኅ የረገመው ከነዓንም እንደ ልጅ ሳይሆን፥ ለወንድሞቹ የባሪያ ባሪያ ሆኖ
በቤት እንዲኖር ተፈቅዶለታልና ነው። ዘፍ፡፱፥፳፰። ይልቁንም አሁን ባለንበት ዘመናዊ ዓለም፡- ወንጀልን ለመቆጣጠር
እና ለመከታተል፥ ከቴክኖሎጂው ይልቅ ውሻ አስተማማኝ ረዳት ሆኖ ተገኝቶአል። በክፉ ምሳሌነቱ ደግሞ፡- እንደ ርኵስ ስለ ተቆጠረ
በቅድስናው ስፍራ እንዲቆም አልተፈቀደለትም። በዚህም ለመናፍቃን እና ለአሕዛብ ምሳሌ ሆኖአል። “በእግራቸው እንዳይረግጡት
ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ የተቀደሰ ውን ለውሾች አትስጡ፤” ይላል። ማቴ፡፯፥፮። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡- “ከውሾች ተጠበቁ፤” ብሎአል። ፊል፡፫፥፪። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ
ደግሞ፡- ፈጥነው የሚክዱትን ሰዎች በውሾች መስሎ፡- “በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ
ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል። አውቀዋት ከተሰጣቸው
ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና። ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ፡- የታጠበች እርያ በጭቃ
ለመንከባለል ትመለ ሳለች እንደሚል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋለ።”በማለት ተናግሮአል።፪ኛ፡ጴጥ፡፪፥፳።ባለ ራእዩ ቅዱስ ዮሐንስም፡- ወደ መንግሥተ ሰማያት
የማይገቡትን ሰዎች በአምስት ውሾች መስሎአቸዋል።“ አምስቱ ውሾች ግን ከዚያች አገር ወጥተው ይሄዳሉ። እሊህም ሥራይን የሚያደርጉ፥ ሴሰኞች፥ ነፍሰ ገዳዮች፥ ጣዖትን የሚያመልኩና
የሐሰትን ሥራ የሚወዱ ሁሉ ናቸው፤” ይላል። ራእ፡፳፪፥፲፭። እንግዲህ ጌታችን በወንጌል፡- የእባብን መርዙን ትተን
ልባምነቱን እንድንማር በነገረን መሠረት ከውሻም ታማኝነቱን ወስደን በነገር ሁሉ ታማሽ ልንሆን ይገባል። ማቴ፡፲፥፲፮። እመቤታችን ጽዮን ድንግል
ማርያም፡- ጸወነ ሥጋ ጸወነ ነፍስ (የሥጋም የነፍስም
መጠጊያ) በመሆኗ ለሁሉም ትራራላቸዋለች።
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም፡-በቤተ መቅደስ ስትኖር፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየተመለከተች፥ ቤተ መቅደስንም እያገለገለች እንደ ነበረ ባለፈው
ተመልክተናል። በአጭር ታጥቃ፥ ማድጋ ነጥቃ፥ ተራዋን ጠብቃ የጉድጓድ ውኃ ትቀዳ ነበር። ብዙ ሴቶችም ውኃ ለመቅዳት
ወደዚያ ይመጡ ነበር። እነዚያ ሴቶች በየተራቸው ውኃ በሚቀዱበት ጊዜ ውኃ ጥም የጠናበት አንድ ውሻ እየተቅበዘበዘ
ወደ እነርሱ መጣ። እነርሱም ለተጠማው ውሻ ከሰው የሚጠበቅ ርኅራኄ ሳያደርጉለት ያባርሩታል። እመቤታችን ቅድስት
ድንግል ማርያም ግን ውሻው፡-በጽኑ ውኃ ጥም ተይዞ ከወዲያ ወዲህ፥ ከወዲህ ወዲያ ሲመላለስ
ባየች ጊዜ፡- ስለ መጠማቱ አዘነችለት። እጅግ ማዘኗን ያዩ
እነዚያ ሴቶች፡- “አንቺ ለውሻው ትራሪለታለሽን? ምናልባት ክርስቶስ የሚባለው መሲሕ የሚወለደው ካንቺ
ይሆንን?” ብለው ተሣለቁባት። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም፡-ይኸንን ነገራቸውን በሰማች ጊዜ በልብዋ ታደ
ንቅ ነበር።የእግዚአብሔር ታማኝ የምሥጢር መዝገብ እንደሆነች መጽሐፍ ቅዱስም ይመሰክራል። ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ፡- “እናቱም (በመንፈስ ቅዱስ ግብር
በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደችው እናቱ ድንግል ማርያም) ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር፤”ያለው ለዚህ ነው። ሉቃ፡፪፥፶፩።
እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም፡- ማድጋዋን አንሥታ ከሚሣለቁባት ሴቶች ራቅ ካለች በኋላ፥ በወርቅ ጫማዋ የተጠማውን
ውሻ በፍጹም ርኅራኄ ውኃ አጠጣችው። ከሴቶቹም መክከል አንዷ፡- “ሳይቸግርሽ ማድጋሽን
አጕድለሽ በምን ልትሞዪው ነው? የጉድጓድ ውኃ መቅጃው ተቋርጧል፤”አለቻት።እመቤታችን ግን፡-“ውኃ የሚገኘው ከላይ ከሰማይ (ከእግዚአብሔር) እንጂ
ከታች ከጕድጓድ አይደለም፥ ይህንን የተጠማ ውሻ ያጠጣ አምላክ ለእኔም ይሰጠኛል፤” ስትል በትህትና መለሰችላት። ይኽንን የእምነት ቃል
ተናግራ ስትጨርስ ማድጋዋ በውኃ ተሞላ፤ከቤተ መቅደስ ስትደርስ ደግሞ፡- ብሥራተ ቅዱስ ገብርኤልን
ሰምታ፡- “እንደ ቃልህ ይደረግልኝ፤” ባለች ጊዜ፥ የሕይወት ውኃ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በማኅፀኗ አደረ። መንፈስ ቅዱስ የሴቶቹን
ሳቅና ስላቅ ለውጦ እውነተኛ ትንቢት አደረገው፤ አንድም አፋቸውን ከፍቶ፥ ፊታቸውን ጸፍቶ እውነት
አናገራቸው። እመቤታችን እንደተናገረችው በረከት ሁሉ ከላይ ከሰማይ ነው።“ረዳቴ፥ ሰማይና ምድርን ከሠራ
ከእግዚአብሔር ነው፤” ይላል። መዝ፡፻፳፥፪።
ነገረ ማርያም፡- ክፍል ፳፫፤
ብሥራተ ቅዱስ ገብርኤል፤
ብሥራት፡- በቁሙ ሲተረጐም የምሥራች፥ አዲስ ነገር፥ ደስ የሚያሰኝ ወሬ፥ ስብከት፥ ትንቢት፥ ወንጌል ማለት ነው። አብሣሪው፡- “ደስ ይበልህ፥ ደስ ይበልሽ፥ ደስ ይበላችሁ፤” እያለ የተላከበትን እና
የመጣበትን የሚናገርበት ነው። ደስ የሚያሰኝ ዜና
የተነገረውም አካል፡- “ይሁንልኝ፥ ይደረግልኝ፤” እያለ ብሥራቱን በሃይማኖት
ይቀበለዋል። ጥርጥር ከገባው ግን፥ ነገሩ ከእግዚአብሔር በመሆኑ ተግሣጽ ይወድቅበታል። “አባት የሚወደውን ልጁን እንደሚገሥጽ
እግዚአብሔርም የሚወደውን ይገሥጻል።” ጻድቁ ካህን ዘካርያስ፡- የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፡- መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስን እንደሚወልድ ባበሠረው ጊዜ፥” እኔ ሽማግሌ ነኝ፥ ምስቴም አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?” በማለቱ፥ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል
ነኝ፥ እንድናገርህም ይህችንም
የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፤ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤” ብሎታል። ሕፃኑ እስከሚወለድም
ድረስ ዲዳ ሆኖአል። ሉቃ፡፩፥፲፰።
ቅዱስ ገብርኤል፡- ጥንት በዓለመ መላእክት
በሳጥናኤል ምክንያት የተነሣውን ማዕበል ጸጥ ያደረገ መልአክ ነው። ሳጥናኤል፡- ሲፈጠር የመላእክት አለቃ ሆኖ ነው፥ እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን ከፈጠረ በኋላ፥ “በሰጠኋቸው አእምሮ ተመራምረው ይወቁኝ፤” ብሎ ተሰወረባቸው። እነርሱም፡- “ከየት መጣን? ማን ፈጠረን?” ማለት ጀመሩ። ይኽንን የሰማ ሳጥናኤል፡- ከበላዩ ማንም
አለመኖሩን አይቶ፥ “እኔ ፈጠርኳችሁ፤” በማለቱ ሁከት ሆነ። በዚህን ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፡- “ንቁም በበህላዌነ
እስከ ንረክቦ ለአማላክነ፥ የፈጠረንን አምላክ እስከምናገኘው ድረስ በየህልውናችን ጸንተን እንቁም፤” በሚል ዐዋጅ አረጋግቶአቸዋል።
እግዚአብሔርም በብርሃን ጐርፍ ተገልጦላቸዋል። ቅዱስ ገብርኤል፡- አምላክ ሰው የሚሆን በትን ምሥጢር እንዲያበሥር የተመረጠው በዚህ
ምክንያት ነው። በመጀመሪያ ለቅዱሳን መላእክት የተገለጠበት ምሥጢር፥ በኋላ በተዋህዶ ሰው ሁኖ ለሰው ለሚገለጥበት ምሥጢር ምሳሌ
ነውና።
“ስድስተኛው ወር፤”
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን የተላከው በስድስተኛው ወር ነው፥ ይላል። ሉቃ፡፩፥፳፮። “ስድ ስተኛ ወር፤”
የሚለው የሚተረጐመው በሁለት ወገን ነው። የመጀመሪያው ትርጉም በስድስተኛው ሺህ ዘመን ማለት ነው። ይህም አዳም ከተፈረደበት ጊዜ
ጀምሮ ያለውን ዘመን ቆጥሮ ነው። አዳም በበደሉ ምክንያት በተፈረደበት ፍርድ ከማልቀስ በቀር ሌላ ኅሊና አልነበረውም። እግዚአብሔርም፡-
መጸጸቱን አይቶ “አምስት ቀን ተኵል (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት ) ሲፈጸም፥ ከሰማየ ሰማያት ወርጄ፥ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ
አድንሃለሁ።” የሚል ተስፋ ሰጥቶታል። በእግዚአብሔር ዘንድ ሺው ዘመን እንደ አንድ ቀን ወይም እንደ አንድ ወር እንደሚቆጠር በቅዱሳት
መጽሕፍት ተገልጧል። ነቢዩ ዳዊት፡- “ሺህ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን፥ እንደ ሌሊትም ትጋት ነውና፤” ያለው ለዚህ
ነው። መዝ፡፹፱፥፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፡- “እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ! በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ
ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ፤” ብሎአል። ፪ኛ፡ጴጥ፡፫፥፰። በመሆኑም፡-
“በስድስተኛው
ወር፤” ሲል አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ተፈጽሞ ስድስተኛው ሺህ ሲጀመር ማለት ነው። ሁለተኛው ትርጉም ደግሞ፡-
መጥምቀ መለኰት
በተፀነሰ በስድስተኛው ወር ማለት ነው።
ናዝሬት ዘገሊላ፤
ገሊላ፡- በሰሜን የምትገኝ ከሦስቱ የእስራኤል ክፍለ ሀገሮች አንዷ ናት፤ በምሥራቅ፡- ከዮርዳኖስና ከገሊላ ባሕር፥ በሰሜን፡-
ከሶርያ፥ በምዕራብ፡- ከፊንቄ ሀገር፥ በስተ ደቡብ፡- ከሰማርያ ጋር ትዋሰናለች። ከእስራኤል ምርኮ በኋላ አሕዛብ ወደ ዚህች ሀገር
በመግባታቸው የአሕዛብ ገሊላ ተብላለች። ፪ኛ፡ነገ፡፲፭፥፳፱፤ ፲፯፥፳፬፣ ማቴ፡፬፥፲፬። አሕዛብ ስለ ገቡባትም በገሊላ የሚኖሩ አይሁድ
ቋንቋቸውና ሃይማኖታቸው ትንሽ ለየት ያለ ሆነ፥ በዚህ ምክንያት ሌሎቹ አይሁድ ይንቋቸው ነበር። ማቴ፡ ፳፮፥፶፯፣ ዮሐ፡፩፥፵፯፤
፯፥፶፪።
ናዝሬት፡- በገሊላ ውስጥ የምትገኝ በተራራ ላይ የተመሠረተች ከተማ ናት፤ ከገሊላ ባሕር በስተምዕራብ ፳፭ ኪ.ሜ. ርቃ ትገኛለች።
እስራኤል ርስት በተካፈሉበት ወቅት የነገደ ዛብሎን ድርሻ ነበረች። እመቤታችን፡- ከጠባቂዋና ከዘመዷ ከጻድቁ ከዮሴፍ ጋር በዚያ ትኖር ነበር። ቅዱስ ሉቃስ በገሊላ ውስጥ የምትገኘውን
ናዝሬትን የጠቀሰው ለዚህ ነው። የናዝሬት ከተማ ወደ ጠረፍ የተጠጋች በመሆኗ በአይሁድ ዘንድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣት ከተማ አልነበረችም።እግዚአብሔር
ሁል ጊዜ የሚፈልገው ከሰውም ከቦታም የተናቀውን ነው። የነቢዩ የሳሙኤል እናት ሐና፡- እግዚአብሔር መናቋን አይቶ የልቧን መሻት
በፈጸመላት ጊዜ፡- “አትታበዩ በኵራትም አትናገሩ፤ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ
የኵራት ነገር አይውጣ፤” ያለችው ለዚህ ነው። ፩ኛ፡ሳሙ፡፪፥፫።
ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ፤
“በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ
ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፤” ይላል። (የእጮኛን ትርጉም፡- ነገረ ማርያም ክፍል ፲፪ን ተመልከት፤)
ቅዱስ ገብርኤል ወደ ድንግል ማርያም የመጣው፥ ስሟን ጠርቶ በፊቷ የተንበረከከው፥ በፍጹም ትህ ትና አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና
እንደምትወልድ ያበሠረው፥ ከእግዚአብሔር ተልኮ ነው። እግዚአብሔር ያልላ ከው፥ ወደ እመቤታችን አይመጣም፤ ስሟንም ጠርቶ አያመሰግናትም።
ወላዲተ ቃል፥ ወላዲተ አምላክ፥ እመ እግዚአብሔር ጸባዖት አይላትም። ስለዚህ ወደ እመቤታችን የመጣን፥ በቅዳሴ፣ በማኅሌትና በመዝሙር
ስሟን የምንጠራ፥ ውዳሴዋን የምንደግም ሁሉ የእግዚአብሔር መልክተኞች እንደሆንን እናምናለን።
ነገረ ማርያም፡- ክፍል ፳፬፤
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ድንግልና፡-በሦስት ወገን ነው።
በሥጋዋ፥ በነፍሷ እና በልቡናዋ ድንግል ናት፤
ይህ ድንግልና፡- የዘለዓለም ድንግልና ነው። ይህም በምሳሌ ኦሪት፥ በነቢያት ትንቢት የተረጋገጠ ነው።
ከአዳም ብቻ በቀር ከድንግል መሬት የተፈጠረ የለም፤
“እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤
በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤
ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሰው ሆነ፤” ይላል። ዘፍ፡፪፥፯። ከአንድ ከሔዋን ብቻ በቀር ከአዳም ጎን የተፈጠረ የለም፤
“እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥
አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው።
እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤
ወደ አዳምም አመጣት፤”ይላል።
ዘፍ፡፪፥፳፩
አበ ብዙኃን አብርሃም፡- ከአንድ በግ ብቻ በቀር ከዕፀ ጳጦስ አላገኘም።
“አብርሃምም ዓይኑን አነሣ፥በኋላውም እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤
አብርሃምም ሄደ፥
በጉንም ወሰደው፥
በልጁም ፈንታ መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው፤”ይላል።
ዘፍ፡፳፪፥፲፫። አብርሃም የእግዚአብሔር አብ፥ ዕፀ ሳቤቅ የድንግል ማርያም፥
በግ የኢየሱስ ክርስቶስ፥ ይስሐቅ ደግሞ የአዳም ምሳሌዎች ናቸው።
አብርሃም፡- ከዕፀ ሳቤቅ የተገኘውን አንድ ብቻ በግ በይስሐቅ ፈንታ እንደሠዋው፥ እግዚአብሔር አብም፡- ከድንግል ማርያም የተወለደውን፥ ለእርሱም ለእናቱም አንድ ብቻ የሆነውን፥
ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን፥ ስለ አዳም ልጆች ፈንታ ለሞት አሳልፎ ሰጥቶታል።
“እግዚአብሔር አንድ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወድዶአልና። . . . ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም፤” ይላል። ዮሐ፡፫፥፲፯፣ ፩ኛ፡ዮሐ፡፬፥፲።በዚህ ምሳሌ መሠረት፡- ከድንግል መሬት አንድ አዳም ብቻ እንደተፈጠረ፥ ከአዳም ጎንም አንዲት ሔዋን ብቻ እንደተፈጠረች፥
ከዕፀ ጳጦስ ደግሞ አንድ በግ ብቻ እንደተገኘ፥
ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያምም የተወለደው አንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። -ከቅዱሳን ነቢያት፥
ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስ፡- “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤እነሆ፥
ድንግል ትፀንሳለች፥
ወልድንም ትወልዳለች፥
ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች፤” ብሎአል። ኢሳ፡፯፥፲፬።ነቢዩ ሕዝቅኤልም፡- እግዚአብሔር የነገረውን ቃል በቃል በትንቢት መጽሐፉ ላይ አስቀምጦአል።“ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በስተውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ፤
ተዘግቶም ነበር።
እግዚአብሔርም፡-ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥
ሰውም አይገባበትም፤
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል፤”ብሎአል።
ሕዝ፡፵፬፥፩። የተዘጋ የመቅደስ በር የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት።“ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፤” የሚለው በድንግልና ጸንታ መኖሯን የሚያመለክት ነው።“ ሰው አይገባበትም፥ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል፤” የሚለው ኃይለ ቃል ደግሞ የሚያመለክተው፡- እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ፀንሳ፥
በድንግልና የወለደችው ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ በመሆኑ፥
ከርሷ ሰው አይወለድም፥
በድንግልና እንደጸናች ትኖራለች፥
ማለት ነው።
በመሆኑም፡- ቅድመ ፀኒስ፥ ጊዜ ፀኒስ፥ ድኅረ ፀኒስ፤
ቅድመ ወሊድ፥ጊዜ ወሊድ፥ድኅረ ወሊድ ኅትምት በድንግልና ናት።
No comments:
Post a Comment